የየካቲት 1966 የለውጥ ማዕበል ከመጣ እነሆ ግማሽ ምዕተ ዓመት ሆነው። ይህ የለውጥ ማዕበል በስኬት ይጠናቀቅ ዘንድ የመላው ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ (መኢሶን) በሙሉ ኃይሉ ተንቀሳቅሶ ነበር። መኢሶን፣ በሃያኛው ምዕተ ዓመት አጋማሽ ላይ አገራቸው ኢትዮጵያ የምትገኝበት ኋላቀርነት ያስቆጫቸው፣ ሕዝቧን ከረሃብ፣ ከበሽታና ከድንቁርና ለማላቀቅ፣ ማህበራዊ ፍትህ የሰፈነበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማነጽ ሕይወታቸውን አሳልፈው እስከ መስጠት ዝግጁ በነበሩ ሃያ አምስት ተራማጅ ኢትዮጵያውያን በነሐሴ 1960 ዓ.ም. በጀርመን አገር ሀምቡርግ ከተማ ተመሠረተ።
ድርጅቱ በተመሠረተ በ6ኛው ዓመት የየካቲት የለውጥ ማዕበል ሀገራችንን አናወጣት። የመኢሶን መስራቾች እና አባላቱም ቃል ኪዳናቸውን ጠብቀው ለውጡ ይሳካ ዘንድ የሚቻላቸውን አደረጉ።የማይደፈሩ ከሚመስሉ መንግሥታትና የፖለቲካ ኃይሎች ፊት ለእውነት በድፍረት ተሟገቱ፣ ተጋፈጡ። ዛሬ፣ አብዮቱ ይሳካ ዘንድ የመጨረሻው እሴት የሆነውን ሕይወታቸውን ከፍለው ያለፉትን ጓዶቻችንን ማስታወስ የእኛ የቀሪዎቹ ሆነ።
በእርግጥ ከግድያ ተርፈው በተፈጥሮ ሕመምና በደረሰባቸው የአካል ጉዳት ሳቢያ በሞት የተለዩን ጓዶቻችን ሆኑ፣ በሕይወት ተርፈው የወደቁት ጓዶቻቸውን ዛሬ ለመዘከር የበቁት ጓዶችም ቢሆኑ አብዮቱ ይሳካ ዘንድ ብዙ መስዋዕትነት ከፍለዋል። ብዙዎች ለረጅም እስር ተዳርገዋል፣ አብዛኛዎቹ ሰቆቃ ተፈጽሞባቸዋል፣ ጤናቸው ተጓድሏል፣ የትዳር ጓደኞቻቸውን አጥተው ልጆቻቸውን በብቸኝነት አሳድገዋል። የተቀሩትም በሚሳሱላት እና ብዙ በተመኙላት አገራቸው መኖር
ተስኗቸው ለረጅም ዓመታት የስደት ኑሮ ተዳርገዋል። ባጭሩ ለሕዝብ አልመውት ከነበረው የሕይወት ባቡር ሃዲድ እንዲወጡ ተገደዋል። እነዚህ ሁሉ፣ የኢትዮጵያ ልጆች መኢሶን ለቆመለት ዓላማ ብዙ የከፈሉ ናቸው። ዛሬ ግን ለይተን ልንዘክራቸው የተነሳነው ሕይወታቸውን የገበሩትን ብቻ ነው። እነዚህንም ቢሆን በጊዜው እርዝመት፣ በመረጃ እጦት እና በአቅም ማነስ የተነሳ በተሟላ ሁኔታ አልዘረዘርንም።
እነዚህን የመኢሶን ሰማዕታት ስንዘክር በአንድ በኩል፣ በኢሕአፓ አድፍጦ ገዳይ ቡድኖች (ገዳይ ስኳዶች) በመንገድ ላይ፣ በመሥሪያ ቤታቸው፣ በየትምህርት ቤታቸው አካባቢ እና በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥና ደጃፍ ላይ በደፈጣ ባልጠበቁትና ባላሰቡት ሁኔታ መገደላቸውን በቁጭት እያስተወስን ነው። በሌላ በኩል፣ በርካታ ጓዶቻችን በደርግ ወታደሮችና የጸጥታ ኃይሎች ታስረዋል፣ ተሰቃይተዋል፣ ተገድለዋል። በሕይወት ተይዘው፣ እዚያው በተያዙበት ስፍራ ሸዋ፣ ኢሉባቡር፣ ሐረር፣ ጎንደር፣ ወለጋና ሲዳሞ ክፍለ ሀገራት ውስጥ በቅጽበት ተረሽነዋል። አንዳንዶቹ ጓዶቻችን፣ ከመቀበራቸው በፊት በእርቃነ-ገላ አስከሬናቸው ኢሰብአዊ በሆነ ሁኔታ፣ ሙሉ ቀን ገበያ ላይ ሕዝብ እንዲያየው በደርግ ወታደሮች ተጥሏል። ሌሎቹም፣ ከነጭራሹ አስከሬናቸው እንዳይነሳና እንዳይቀበር ሆኖ፣ የጅብ እራት ሆነዋል። አንዳንድ ጓዶቻችን በነጠላና በጅምላ ተገድለው በድብቅ በመቀበራቸው የተቀበሩበትን ስፍራ እንኳን እስካሁን አጠያይቀንና አፈላልገን ማግኘት አልተቻለንም።
ሌሎች ሰማዕቶቻችን ደግሞ፣ በደርግ እስር ቤት ታስረው በግርፋት ተሰቃይተው ከወራትና ከአመታት በኋላ ከታሰሩበት ተወስደው ተረሽነዋል። በደርግ እስር ቤት ውስጥ በሕይወት እያሉ የአካል ማሰቃያ ዘዴ ዓይኖቻቸው ሳይቀሩ እየተጎጡ በጭካኔ ተገድለዋል። ጥቂቶችም ጓዶቻችን፣ ለደርግ እጃቸውን ከመስጠትና ተሰቃይቶ ከመሞት ይልቅ፣ ሕይወታቸውን በገዛ እራሳቸው ማጥፋትን መርጠዋል። ሌሎች ጥቂቶች ደግሞ፣ በአደባባይ ጎዳናዎች ላይ፣ ገሚሶቹ በግላጭ ሌሎቹም ኢሕአፓ ገደላቸው እየተባሉ በደርግ ልዩ ገዳይ ቡድን ተገድለዋል። የተሰውት የመኢሶን አባሎችና ደጋፊዎች እዚህ በዝርዝራችን የቀረቡት ብቻ አይደሉም። ሌሎች በሺዎች የሚቆጠሩ ሰማዕታት፣ በተለይ የቀበሌና የገበሬ ማኅበራት ተመራጭ መሪዎችና አባሎች፣ ወጣት ተማሪዎች፣ መምህራን፣ የፋብሪካ ሠራተኞች፣ ገበሬዎች፣ መለዮ ለባሾች እና ምሁራን በኢሕአፓ፣ በደርግ፣ በኢዲዩ፣ በኦሮሞ እስላማዊ ነጻነት ግንባርና በሶማሊያ መንግሥት ተገድለዋል። ዛሬ የእነዚህን ሁሉ ሰማዕታት አጭር ሕይወት ታሪክና ፎቶግራፍ ማቅረብ አልቻልንም። ነገር ግን፣ ዛሬ ስማቸው ባይጠቀስም፣ እንዚህ የአገር ፍቅር፣ የዓላማ ቁርጠኝነትና ጽናት ተምሳሌት የሆኑት ሰማዕታት ሁልጊዜም በልባችን ይኖራሉ።
የመኢሶን ጠላቶች ድርጅቱን ለማጠልሸት፣ አንድ በታሪክ የጨለማ ግርዶሽ ውስጥ ለመክተት ሰፊ የሐሰት ፕሮፓጋንዳ እንዳካሄዱ ይታወቃል። ሆኖም፣ ከሁሉም የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች እና ማኅበራዊ ክፍሎች የተውጣጡት እና ሕይወታቸውን የሰዉት ጓዶቻችን ይህንን የሐሰት ትርክት የሚያፈርሱ እና መና የሚያሰቀሩ ቋሚ የታሪክ ሃውልቶቻችን ናቸው። ጓዶቻችን የኢሕአፓ፣ የደርግ፣ የሶማሊያ መንግሥት፣ የብሔር ትምክሕተኞችና የጠባብ ብሔረተኞች የሽብር ሰለባ የሆኑት፣ በምንም ሌላ ምክንያት ሳይሆን በእኩልነት ላይ ለተመሠረተ፣ ዘለቄታ ላለው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አንድነት፣ መብትና ጥቅም በጽናት በመቆማቸው ነው።
ዛሬ በፖለቲካው መድረክ ተዋናይ በሆኑ ድርጅቶች እና ግለሰቦች ዘንድ ያለፈውን ትውልድ ለሁሉ ችግር መንሰኤ አድርጎ መውሰድ እና ማውገዝ፣ እንደቡራኬ እና ማሳረጊያ መጠቀም የተለመደ ፈሊጥ ሆኗል። የሰማዕቶቻችንን ዝርዝር የሚያዩ፣ የመደብ ምንጫቸው፣ የብሔረስብ፣ የጾታ እና የሃይማኖት ስብጥራቸው ምን ያህል መላ ኢትዮጵያን ያንጸባረቀ እንደነበር ይረዳሉ። የመኢሶን ጓዶቻችን ኢትዮጵያችን በሕዝባዊነቷ ደምቃ፣ በዲሞክራሲያዊነቷ ፈክታ፣ በብሔረሰቦቿ እኩልነት አሸብርቃ፣በብሔራዊ ነፃነቷ ኮርታ፣ በሕዝቦቿ ታታሪነት በልፅጋ፣ የማንም ተመጽዋች ያልሆነች፣ የተከበረች፣ የታፈረችና አንድነቷ የጠነከረ አገር እንድትሆን ለነበራቸው ምኞት ታግለዋል። ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ አብዮት በማካሄድ እኩልነት የሰፈነበት ህብረተሳባዊ ሥርዓትን ለመገንባት በጊዜው ለነበራቸው የለውጥ ራዕይ ውድ ሕይወታቸውን ሰውተዋል።
የወደቁት ጓዶቻችንን ስናስታውስ፣ በተለይም ትናንትናም ሆነ ዛሬ ሥልጣን ከጨበጡት ጋር ስናነጻጽር ብዙ ነገር ወደ ኅሊናችን ይመጣል። ጓዶቻችን እጅግ ጎልተው ይታዩናል። ከልባችን የማይጠፋው ሐዘናችን መሪር ሆኖ ይቆጠቁጠናል። የወደቁት ጓዶቻችን በአብዛኛው ውጪ ድረስ በመሄድ ሰፊ ትምህርትን የገበዩ ነበሩ። ለራሳቸው የግል ኑሮና ዝና ብቻ ቢያስቡ ሙያቸውን ተጠቅመው ብዙ ሀብት እና ሥልጣን ሊያካብቱ የሚችሉበት አመቺ ሁኔታ ነበራቸው። ይህ ግን አላጓጓቸውም። የቆሙት የግል ጥቅማቸውን በመሰዋት ለሰፊው ሕዝብ ኑሮ መሻሻል ነበር። በ መሬት ላራሹ መፈክር ስር ሲታገሉ አንዳንዶቹ ጓዶቻችን የባለመሬት ልጆች መሆናቸውን፣ ወላጆቻቸው ሲያልፉ ወራሾች የመሆን መብት እንደነበራቸው ዘንግተውት አልነበረም። የመሬት ላራሹ በስራ መተግበር ለሕዝብ ኑሮ መሻሻል፣ ለአገር እድገት ቁልፍ መሆኑን በመረዳታቸው እና በመምረጣቸው ነበር። በመሆኑም፣ ለተጎሳቆሉት የኢትዮጵያ ዜጎች የነበራቸው መቆርቆር፣ በብሔርና በሃይማኖት ሳይከፋፈሉ ለእኩልነት፣ ለነጻነት፣ ለአገር እድገት እና አንድነት ባንድ መቆምን ዛሬም ሆነ ነገ ልንወርሳቸው የሚገቡን ትሩፋቶቻቸው ናቸው እንላለን።