የመኢሶን ልሳንና ልዩ ልዩ መጣጥፎች

የመላ ኢትዮጵያ ሶሺያሊስት ንቅናቄ (መኢሶን) በምስጢር ከተቋቋመ ከስድስት አመታት በኋላ፤ከ1966 ዓ.ም ጀምሮ “የሰፊው ሕዝብ ድምፅ” በሚል ስያሜ የድርጅቱን ልሳን በህቡዕ ማውጣትና ለሕዝብ ማሰራጨት ጀመረ። ከሰፊው ሕዝብ ድምጽ ስርጭት ቀደም ሲል፣ መኢሶን ማንነቱን ሳይጠቅስ በርካታ ቀስቃሽና ትምህርታዊ የሆኑ በራሪ ወረቀቶችን በድብቅ ሲያሰራጭ ቆይቷል። በዚሁ በ1966 ዓ.ም ተራማጆችን በአንድ መድረክ ለማሰለፍ ያደርግ በነበረው ጥረት ለተወሰነ ጊዜ “የሕዝብ ድምፅ” እና “የተራማጆች ሕብረት” የተሰኙ ጋዜጦችን በተናጠልና ከሌሎች ህቡዕ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ያዘጋጅ ነበር።

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ የመጀመሪያው ቁጥር፣ “የእንቅስቃሴው ባለቤት ሰፊው ሕዝብ ነው” በሚል ርዕስ ነሐሴ 14፣ 1966 ዓ.ም. መሰራጨት ጀመረ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስከ መጋቢት 1968ዓ.ም. ድረስ የወጡት 38 ተከታታይ ቁጥሮችና ልዩ እትሞች መኢሶን እራሱን ለሕዝብ በግልፅ ሳያስተዋውቅ ያወጣቸው ሲሆኑ፤ ከዚያ በኋላ የወጡት ጽሁፎች ግን ጋዜጣው በይፋ የመኢሶን ልሳን መሆኑን ያሳወቀባቸው ናቸው።

‘የሰፊው ሕዝብ ድምፅ’ ይዘጋጅ የነበረው በድርጅቱ የመጽሔት ቦርድ ሲሆን፤ አባላቱም ወርቁ ፈረደ (ዶ/ር)፣ ከበደ መንገሻ (ዶ/ር) ፣ ፍቅሬ መርዕድና እና ዳንኤል ታደሰ ነበሩ።ይህ የመጽሄት ቦርድ ከነሐሴ 1966 ጀምሮ እስከ መጋቢት 1967 ዓ.ም. ድረስ የጋዜጣውን ዝግጅትና እትመት አካሂዷል።

በመጋቢት 1967 ዓ.ም፣ ድርጅቱ ውስጥ በነበረው የፖለቲካ መስመር ልዩነት ላይ አባላት ሰፊ ውይይት ከአካሄዱ በኋላ አዲስ የትግል ስልት ተነደፈ። የትግል ስልት ለውጡን ተከትሎ፣ መኢሶን አዲስ ድርጀታዊ አመራር መሠረተ። ‘የሰፊው ሕዝብ ድምጽ’ የመጽሔት ቦርዱ ውስጥ፤ኃይሌ ፊዳ፣ ከበደ መንገሻ (ዶ/ር)፣ ፍቅሬ መርዕድ (መስከረም 1969 ዓ.ም በኢሕአፓ እስከተገደለበት ጊዜ ድረስ)፣ አንዳርጋቸው አሰግድ እና ነገደ ጎበዜ (ዶ/ር) የጋዜጣው አዘጋጆች ሆነው እንዲሰሩ ተመደቡ። ኃይሌ ፊዳም የጋዜጣው ዋና አዘጋጅ ሆነ።

በዚህ ወቅት፣ ዮሐንስ መስፍንና ደረጀ አለማየሁ (ዶ/ር) ለሰፊው ሕዝብ ድምፅ ጽሑፎችን አልፎ አልፎ በማበርከት አገልግለዋል። በተጨማሪም፣ ሲሳይ ታከለ፣ ታደሰ በዛብህና ስማቸው በዛብህ የወረቀት ማባዣ ከውጪ አገር በማስገባት፣ በማባዛትና በማሰራጨት በድርጅቱ ውስጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ነበራቸው።

በነሐሴ 1969 ዓ.ም. መኢሶን ከደርግ ጋር የነበረውን ትብብር አቋርጦ ከህጋዊ የትግል መድረክ ራሱን አገለለ። በህጋዊ መድረክ ላይ የነበሩ አባላቱም በገጠርና በከተማ ትግሉን በህቡዕ እንዲቀጥሉ ተወሰነ።

መኢሶን የትግል ስልት ለውጥ ከአደረበት ከነሐሴ 1969 ዓ.ም. በኋላ፣ እጅግ አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ የጋዜጣውን ዝግጅት የማቀነባበር ሃላፊነት ለዮሐንስ መስፍን (ደርግ ከእስር ቤት አውጥቶ ታህሳስ 1970 ላይ እስከገደለው ጊዜ ድረስ)፣ተስፋዬ ኪዳነ ማርያም፣መዝገበ ተክለ ሃይማኖት፣አንዳርጋቸው አሰግድና ነገደ ጎበዜ (ዶ/ር) ተሰጠ።በዚህ ወቅት ለጋዜጣው ዝግጀት ሃሳብ በማቅረብ፣ በማረምና በማስተካከል፣ በሕትመት፣ የማባዥያ መሣሪያውን በመደበቅና ጋዜጣውን በማሰራጨት ይረዱ ከነበሩት በርካታ የመኢሶን አባላት መካከል ማንከልክሎት ኃይለ ሥላሴ (ዶ/ር)፣ መዝገበ ተክለ ሃይማኖትና ጴጥሮስ ቶጃ (ፕሮፌሰር) ጉልህ አስተዋጽኦ ነበራቸው።

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ የድርጅቱ ልሳን እንደመሆኑ፣ መኢሶን በተለያዩ ጊዜያት የነበሩትን የፖለቲካ አቋሞችና የትግል ስልቶች ያንጸባርቃል። ከ1966 ዓ.ም ጀምሮ የመሬት አዋጅ እስከወጣበት የካቲት 1967 ዓ.ም ገደማ ድረስ ያሉት እትሞች፣ የሕዝቡን ትግል በመደገፍና የትግሉ አቅጣጫና ትግሉ ሊጓዝ የሚችልባቸውን ጎዳናዎች በማመልከት ላይ ያተኮሩ ነበሩ። ይህ ወቅት መኢሶን ‘ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት ይቋቋም’ የሚለውን መፈክር በግንባር ቀደምትነት ያነሳበት ጊዜ እንደነበረም ይታወሳል። ትግሉ በአድሃሪያን እንዳይጠለፍና ዘላቂነት እንዲኖረው በሚል የጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግስት መቋቋም እንደ ዋና መፍትሄ አድርጎ ቀሰቀሰ። ከዚያም ደርጉ ሥልጣን ሲይዝ በመጀመሪያ ምክር አዘል ጽሁፎችን በማውጣት ከዚያም በተከታታይ የደርጉን ጸረ ህዝብ እንቅስቃሴዎች እያወገዘ፣ በተለይም ደርጉ በአሜሪካን ስለላ ድርጀት የሚመራ ቡድን ነው በማለት ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግስት እንዲቋቋም ቀሰቀሰ። ለደርጉም ‘የጥቂት ምርጥ መኮንኖች መንግስት” የሚል ስም አወጣለት። በሕዳር 1967 ደርግ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ባለስልጣኖችንና የለውጡ ተቃዋሚዎች ናቸው ያላቸውን 60 ሰዎች ሲገድል መኢሶን ተቃውሞውን አሰማ።

የየካቲት 1966ቱ አብዮታዊ ንቅናቄ በተጀመረ በአመቱ ደርግ የመሬት ላራሹን አዋጅ አወጣ። መኢሶን ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረውን የመደቦችና የኃይል አሰላለፎችን ከመረመረ በኋላ፣ ለሕዝብ የሚጠቅሙና ለውጡን የሚያራምዱ የደርግ ፖሊሲዎቹን ለመደገፍና የሕዝቡን ትግል ወደ ኋላ የሚጎትቱ እርምጃዎችን ለመቃወም የሚያስችለውን “ሂሳዊ ድጋፍ” በመባል የሚታወቀውን የትግል ስልት ማራመድ ጀመረ። ሰፊው ሕዝብ የመንግሥት ሥልጣን ባለቤት ለመሆን እንዲችል፣ እስከ አሁንም ያገኛቸውን ድሎች ውዥንብር በሚነዙ አድሃሪያን እንዳይነጠቅ ለዴሞክራሲ መብቶች መለቀቅ እስከ መጨረሻው አጥብቆ ታገለ። “ለነቃ ለተደራጀና ለታጠቀ” የሕዝብ ትግል በግንባር ቀደምትነት ቆመ።

በ1969 እና በ1970 ዓም፣ ኢትዮጵያ በሶማልያ ወረራ አደጋ ላይ በወደቀችበት ጊዜ፣ ኢትዮጵያ በቅድሚያ ከምንም ነገር በላይ በራሷ በሕዝቦችና በራሷ ምድር ሃብት ላይ መተማመን እንዳለባት በተደጋጋሚ አሳሰበ። የሌሎች አገሮች እርዳታ ድጋፍ እንጂ መሠረት ሊሆን ስለማይችል የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ማስጠበቅ የሕዝቦቿ ሃላፊነት ነው በማለት ታገለ።

መኢሶን ከደርግ ጋር የነበረውን ትብብር አቋርጦ ህጋዊውን የትግል መድረክ ጥሎ ከወጣ በኋላ ይታተሙ የነበሩ የሰፊው ሕዝብ እትሞች፣ በዴሞክራሲ መብቶች፣ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሁኔታ፣ በተቃዋሚ ድርጅቶች እንቅስቃሴ፣በተራማጆች የጋራ ግንባር፣ በአገር ሉዓላዊነትና ህልውና ላይ ያተኮሩ ነበሩ።

ከሰፊው ሕዝብ ድምጽ በተጨማሪ ከ1969 ዓ.ም ጀምሮ በመኢሶን ወጣት ክንፍ በሆነው የኢትዮጵያ አብዮታዊ ወጣቶች ንቅናቄ (ኢአወን)፣ ‘የአብዮት ፋና’ የተሰኘ ጋዜጣ ይወጣ ነበር። ጋዜጣው የመኢሶንን የፖለቲካ መስመር ከወጣቶች መንቃትና መደራጀት አንጻር ትንተናዎችንም የሚያቀርብ ነበር።

ጋዜጣው ሲጀመር ገብረ እግዚአብሔር ሃጎስ (በ1969 ጥቅምት በኢህአፓ እስከ ተገደለበት ጊዜ ድረስ)፣ ደረጀ አለማየሁ (ዶ/ር) ፣ አስተዋይ መርዕድና ተስፋዬ ኪዳነ ማርያም የጋዜጣው ቦርድ ውስጥ አገልግለዋል። መኢሶን የትግል ስልቱን ቀይሮ ትግሉን በህቡዕ ለመቀጠል ከወሰነ በኋላ ተስፋዬ ኪዳነ ማርያም፣ መኮንን ጌጡ(ዶ/ር) እና ጴጥሮስ ቶጃ (ፕሮፌሰር) የጋዜጣው አዘጋጆች ሆነው ሰርተዋል። ‘የአብዮት ፋና’ መውጣት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከመጨረሻው ድረስ ጽሁፉን ታይፕ ከማድረግ ጀምሮ በማባዛትና በማሰራጭት እንዲሁም ሃሳብ በመስጠት በርካታ የመኢሶን ወጣቶች ተሳትፈዋል።

የሴቶችን መብት በማራመድና ሴቶችን በማደራጀት ላይ የምታተኩረው ‘ታጋይ ኢትዮጵያዊት’ የምትሰኝ ጋዜጣ የመኢሶን የሴቶች ክንፍ በነበረችው በኢትዮጵያ ሴቶች አብዮታዊ ንቅናቄ (ኢሴአን) ተዘጋጅታ ትቀርብ ነበር። ‘ታጋይ ኢትዮጵያዊት’ በንግሥት አዳነ (ዶ/ር) እና ቆንጂት ከበደ ዋና አዘጋጅነት፤ ከታሕሳስ 30፣ 1968ዓ.ም ጀምሮ እስከ ነሓሴ 1969 ዓ.ም በተለይ በኢትዮጵያ ሴቶች ትግል ላይ የሚያተኩሩ በርካታ እትሞች አውጥታለች።

ከ1958 ዓ.ም ጀምሮ የመኢሶን መሪዎችና አባላት በንቃት ይሳተፉበት በነበረበት የአውሮፓ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማሕበር ውስጥ ይወጡ የነበሩ መጽሄቶች ላይ ጽሁፎችን በመጸፍ፣ በማሳተምና በማሰራጨት ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል።

ከሁሉም አንጋፋ የሆነው “ታጠቅ” በመባል የሚታወቀው መጽሔት በ1958 ዓ.ም ገደማ መጀመሪያ በእጅ ተጽፎ ተሰራጨ። በውጪ የኢትዮጵያ ተማሪ ማህበራት በህሩይ ተድላ (አውሮፓ) እና ሃጎስ ገብረየሱስ (አሜሪካ) ይመሩ በነበረ ጊዜ፣ ፍቅሬ መርዕድ የመጽሔቱ አዘጋጅ ሆኖ ተመድቦ ይሠራ ነበር።

በ1959 ዓ.ም አውሮፓ የሚገኙ ተማሪዎች ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት የጥገና ለውጥ ሳይሆን ስር ነቅል ለውጥ ነው በማለት ወደ አዲስ የትግል ምዕራፍ ተሸጋገሩ። ይህ አዲስ የትግል መስመር በማህበሩ 7ኛ ጉባኤ ላይ ጸደቀ። ‘ታጠቅ’ የቲዮሪ ጋዜጣ እንዲሆን ተወስነ።

በዚሁ ጉባኤ ላይ የቅስቀሳ፣ የማደራጃና የዜና ማሰራጫ ሆኖ የሚያገለግል ሌላ መጽሄት እንዲጀመረ ተወሰነ። በተጨማሪም ጉባኤው ይህንን መጽሄት የማዘጋጀት ሃላፊነት ለዶ/ር ወርቁ ፈረደና አንዳርጋቸው አሰግድ ሰጠ። የመጽሔቱም ስም “ትግላችን” ተባለ። ከዚያም በኋላ በቀጠሉት አመታት ኃይሌ ፊዳ፣ ነገደ ጎበዜ (ዶ/ር) ፣ መኮንን ጌጡ (ዶ/ር) ፣ ዮሐንስ መስፍን፣ ደረጀ አለማየሁ (ዶ/ር) ፣ እና ሌሎችም እዚህ ላይ ስማቸው ያልተጠቀሱ በርካታ ጓዶች የታጠቅና የትግላችን መጽሔቶቹ ዋና አዘጋጅ በመሆንና ጽሁፎችን በማበርከት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል።

በ1966 መጀመሪያ ወራት ላይ ‘ትግላችን ዜና’ የሚባል መጽሄት ተጀመረ። ዮሐንስ ኅሩይም ዋና አዘጋጅ ሆኖ ተመደበ። “ትግላችን ዜና” አጠር ያለ ትንተናና ዜና የሚያቀርብ ተወዳጅ መጽሄት ነበረ።

ዶ/ር ከበደ መንገሻ በአውሮፓ ተማሪዎች ማህበር ይወጡ የነበሩትን ከላይ የተዘረዘሩት መጽሔቶች ጥራታቸው ሳይጓደል በወቅቱ ለአንባቢያን እንዲደርሱ፣ ጠዋትና ማታ ከለ ምንም መታከት ይሰራ ነበር። ዶ/ር ከበደ መንገሻ ኮምፑተር በስፋት በማይታወቅበትና እንደ ልብ በማይገኝበት በሃምሳና በስልሳዎቹ አመታት፣ ከፊደል ለቀማ ጀምሮ፣የማተምና የማሰራጨት ሃላፊነቶችን በተለይም አድካሚ የሆነውን የአርትኦት ስራ የሙሉ ጊዜ ስራው አድርጎ ይሰራ እንደነበር ይታወሳል።

ከ1968 ዓ.ም ሐምሌ ወር ጀምሮ መኢሶን “አዲስ ፋና” በመባል የምትታወቅ ህጋዊ መጽሄት በአማረ ተግባሩ (ዶ/ር) ዋና አዘጋጅነት ማውጣት ጀመረ። መኢሶን ሕቡዕ እስከገባበት 1969 ዓ.ም. ነሐሴ ድረስ፣ አዲስ ፋና ተወዳጅ የሆኑ የፖለቲካ ትንተናዎችን በማቅረብ የታወቀች መጽሄት ነበረች።

ከ1977 ዓም ጀምሮ እስከ 1983 ዓም ድረስ የመኢሶን የውጪ አመራር፣ የኢትዮጵያን ጊዜያዊ ሁኔታና ዜናዎችንና ፖለቲካዊ አስተያየቶችን ይዛ፤ በየሁለት ወሩ የምትወጣ እና በድምሩ ሰላሳ የአማርኛ እትሞች ያበረከተች “ለአዲሲቱ ኢትዮጵያ” የተባለች ጋዜጣም እንደነበረች ይታወሳል።ከዚሁ ጋር በተመሳሳይም፣በቅድሚያ ከ1969 ዓም እስከ 1971 ዓም በፈረንሳይኛ Ethiopie Nouvelle በኋላም፤ ከ1971 ዓም እስከ 1987 ዓም በእንግሊዝኛ New Ethiopia መጽሄቶችም አውሮፖና በአሜሪካ በሚገኙ የመኢሶን የውጭ አመራር እየታተሙ ተሰራጭተዋል፡፡

በዚህ ድረ ገጽ ላይ ከዚህ በላይ የተጠቀሱት ጽሁፎችን ከየቦታው አሰባስቦ ለማቅረብ ብዙ ሙከራዎች ተደርገዋል።ምንም እንኳን ከረጅም ጊዜ በፊት የተዘጋጁትን እነዚህን ጽሁፎች ፈልጎ ማግኘት እጅግ አስቸጋሪ ቢሆንም፣ አሁንም የጎደሉትን አሟልቶ ለማቅረብ የተጀመረው ጥረት ይቀጥላል። አንባቢያን እዚህ ድረ ገጽ ላይ ያልወጡ፣ በእጃቸው የሚገኙ ጽሁፎችን ቢያጋሩን ስብስቡን የተሟላ ለማድረግ የተጀመረውን ሥራ እንደሚያግዝ አያጠራጥርም።

የሰፊው ሕዝብ ድምጽ እትሞች በቀላሉ ለመነበብ እንዲችሉ በኮምፒዩተር ታይፕ ተደርገው ቀርበዋል። ጽሁፎቹ ሲወጡ የነበራቸውን መልክ ለማየት ይረዳ ዘንድ ኦሪጂናል ጽሁፎቹ እንዲያያዙ ተደርገዋል። በተጨማሪም የያንዳንዱን እትም ዋና መልዕክት በአጭሩ መረዳት ለሚፈልጉ የተጠቃለለ “ፍሬ ሃሳብ” ቀርቧል።

በታይፕ የታተመው ጽሁፍ ላይ የማይነበቡ ወይንም የጎደሉ ቃላቶችና ፊደሎችን ከማስገባት በቀር ምንም እርማ አልተደረገም። ማብራሪያ የሚያስፈልጋቸው እርማቶች ሲደረጉ፣ አዘጋጆቹ የጨመሩት እንደሆነ በግልጽ እንዲታወቅ በቅንፍ ውስጥ [የአዘጋጆች እርማት] ተብሎ ተቀምጠዋል። ጽሁፎቹ በኮምፒዩተር ከተጻፉ በኋላ የቃላት/የሆሄያት እርማቶች ተደርገዋል። ስህተቶቹን ለማረም ብዙ ጥረት ቢደረግም፣ አንዳንድ ግድፈቶች አሁንም ሊገኙ ይችላሉ ብለን እንገምታለን። እርማቶችን ለማድረግ እንዲረዳን፣ አንባቢያን ስህተቶች ካገኙ እንዲያስታውቁን በትህትና እንጠይቃለን።

መልካም ንባብ

Scroll to Top