የሰፊው ሕዝብ ድምፅ
ልዩ እትም፣ መስከረም 3፣ 1967 ዓ.ም.
የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ
ይህ የሰፊው ሕዝብ ድምፅ ልዩ እትም የወጣው ፣ የጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት (ደርግ) ስልጣን በያዘ ማግስት መስከርም 3፣ 1967 ዓ.ም. ነው፡፡ መኢሶን በዚህ ልዩ እትም፣ ደርግ የንጉሡን አገዛዝ በማውረዱ ድጋፉን ይገልጻል።
ቢሆንም ግን ደርግ ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ መንግስት ባለማወጁ፣ ዘውዱንም ሙሉ ለሙሉ ባለማስወገዱና ስልጣንን ለሕዝቡ ሳይጋራ ብቻውን መያዙን ይቃወማል።
ስለዚህ ሰፊው ሕዝብ ቀደም ሲል የጀመረውን ትግል ሳያቋርጥ እንዲቀጥል ያበረታታል። በየመስሪያ ቤቱ በየሰፈሩ ሕዝቡ እንዲደራጅ፣ ኮሚቴዎችን እንዲያቋቁምና ያሉትንም ድርጅቶች እንዲያጠናክር ጥሪ ያቀርባል። ለትግሉ መቀጠልና መሳካት፣ ከሕዝቡ ወኪሎች የተወጣጣ ጊዜያዊ መንግስት እንዲቋቋም፣ አዲስ ህገመንግሥት እንዲዘጋጅ፣ ዲሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ፣ ሕዝቡን የበደሉ ባለሥልጣኖች ተይዘው ለፍርድ እንዲቀርቡና መሬት ለአራሹ እንዲዳረስ ፣ ሕዝቡም ለነዚህ አላማዎች እንዲታገል ይቀሰቅሳል።
የግፈኛውና የወንጀለኛው የኃይለሥላሴ ከስልጣን መወገድ ባለፈው የካቲት ወር ለፈነዳው የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ የትግል እንቅስቃሴ ታላቅ ድል ነው። ሰፊው ሕዝብ በዚህ በተቀዳጀው ድል በመበረታታት ለዲሞክራሲና ለኑሮ መሻሻል የጀመረውን ትግል ከግቡ ሳያደርስ ከቶ ወደኋላ አይልም።
ደርጉ በበሰበሰው የአስተዳደር ሥርዓት ፈላጭ ቆራጭ በኃይለሥላሴና በአገልጋዮቹ ላይ የወሰደው ታሪካዊ እርምጃ የሕዝቡን ጥያቄና ፍላጎት ስለሚከተል በእርግጥ የሚደገፍ ነው።ሆኖም፡-
- የሕዝቡን የበላይነትና የሕዝቡን የስልጣን ምንጭነት በመቀበል የሕዝብ መንግስት/ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ/ አለማወጁና፡ ለአገሪቷ ውድቀት፣ ለሕዝቡ መከፋፈል ዋና ምክንያት የሆነው ዘውድ አለማስወገዱ፣
- በጊዜያዊ መልክም ቢሆን የሰፊውን ሕዝብ እውነተኛ ወኪሎች ሳይጨምር የመንግስቱን ስልጣን ለብቻው መያዙ የሕዝቡን ፍላጎትና ጥያቄ የሚፃረር መሆኑ የማያጠራጥ ነው።
የኃይለሥላሴ ባለአባታዊ መንግሥት ግብረአበርና የበላይ ጠባቂ የነበረው የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም በስለላ ድርጅቱ በሲአይኤ በኩል በደርጉ አካባቢ ጉድጉድ ሲል በመሰንበቱ የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም እጅ እንዳይኖር ያሰጋል።
እዚህ የደረሰው የሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ትግል መጨናገፍ የለበትም። ስለዚህ ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዲሞክራሲና ለኑሮ መሻሻል የጀመረውን ትግል በበለጠ ኃይል መቀጠል አለበት፣ ይገባዋልም። ትግሉ ሳይበርድ በሚከተለው አኳኋን መቀጠልና መፋፋም ይገባዋል፡-
- በየመስሪያ ቤቱ፣ በየፋብሪካው፣ በየሙያው፣ በየሰፈሩ፣ በየእድሩ፣ በየቀበሌው በሚቻልበት መንገድ ሁሉ ሰፊው ሕዝብ ኮሚቴዎች እንዲያቋቁምና እንዲደራጅ፣ ከዚህ በፊት ያሉትንም ድርጅቶች እንዲያጠናክር፣ እነዚህን በከፍተኛ ደረጃ ላይ የሚያገናኙ አጠቃላይ ኮሚቴዎች በማቋቋም ህብረቱንና አንድነቱን እንዲያጠናክር፣
- ለሙሉ ዲሞክራሲና ለኑሮ መሻሻል የትግሉ እንቅስቃሴ መነሾ የሆኑትን ጥያቄዎቹን በመልክ በመልካቸው አድርጎ እንደሚከተለው ይዞ እንዲቀርብና እንዲታገል ያስፈልጋል፡-
ሀ / ከሰፊው ሕዝብ በምርጫ የተውጣጡ ወኪሎች ያሉበት ጊዜያዊ የሕዝብ መንግሥት አሁኑኑ እንዲቋቋም፣
ለ / ሰብአዊና ብሔራዊ መብቶችና ነፃነቶች፣ በተለይ የጋዜጣ፣ የማህበር፣ የመሰብሰብ መብቶች አሁኑኑ እንዲረጋገጡና ስራ ላይ እንዲውሉ፣
ሐ/ እስከሦስት ወር ድረስ አዲስ ሕገመንግሥት ተዘጋጅቶ ሙሉ ዲሞክራሲያዊ የሕዝብ መንግሥት እንዲቋቋም፣
መ/ ኃይለሥላሴ ከነቤተሰቡና ከነግብረአበሮቹ ታስሮ ለፍርድ እንዲቀርብ፣ እርሱና ግብረአበሮዎቹ ያጋበሱት የሕዝብ ኃብት በሙሉ እንዲወረስና ለሕዝብ እንዲገባ፣
ሠ/ በመሳርያነትና በግብረአበርነት ሕዝቡን የበደሉ፣ የዘረፉና የጨቆኑ፣ አሁን በከፍተኛ ስልጣን ላይ ያሉት ብዙዎቹ ባለስልጣኖች ተይዘው ለፍርድ እንዲቀርቡና ንብረታቸውም እንዲወረስ፣
ረ/ መሬት ላራሹ፣ ለስራአጡ ስራ፣ ለሰራተኛው ሃቀኛ የጉልበት ዋጋውን፣ ለረሃብተኛውም እህልና ውኃ ወዘተ… እንዲደርሰው አስቸኳይ እርምጃ እንዲወሰድ፣
እነዚህና የመሳሰሉት ጥያቄዎች በቶሎ መልስ እስኪያገኙ ድረስ በትጋት መታገል አለብን።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ!
ብዝበዛን፣ ግፍን፣ በደልን በመቋቋም ደምህን አፍስሰህ አጥንትህን ከስክሰህ ያደረግከው ከባድ ትግል ያለፍሬ መቅረት የለበትም፣ አይገባምም። ትግሉን ማፋፋሚያ ጊዜ አሁን ነው። ለአሁኑ የኢትዮጵያ ችግር መፍትሄው ወታደራዊ መንግስት ሳይሆን የሰፊው ሕዝብ መንግስት መቋቋም ነው። ‘አባት ካለ አጊጥ፣ ጀንበር ካለ እሩጥ’ የሚለውን እውነት ምሳሌ በመከተል ትግሉን መቀጠል አሁን ሁኔታው ሳይበርድ ነው። ትጥቅህን አጥብቀህ ትግሉን ወደፊት መግፋት አለብህ። ህብረትህንና አንድነትህን በቆራጥነት ገንብተህ ትግሉን ሙሉ ዲሞክራሲያዊ መንግስት ወይም ሞት በሚል ከፍተኛ ጥሪ መምራት አለብህ።