የሰፊው ሕዝብ ድምፅ
ቁጥር 8፣ መስከረም 28፣ 1967
የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ
መኢሶን በዚህ የሰፊው ሕዝብ ድምፅ እትሙ፣ የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ በሠራተኞች፣ ጭሰኞች፣ ድሃ ገበሬዎች እና ንዑስ ከበርቴዎች ማኅበራዊ መደብ ውስጥ እንደሚጠቃለሉ ያስረዳል። ይህም ማኅበራዊ መደብ በመሠረቱ አብላጫውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ያጠቃለለ እንደሆነ ያረጋግጣል። በተጨማሪም፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ የረጅም ዘመን ብዝበዛውና ጭቆናው በቃኝ በማለት በየካቲት 1966 የጀመረው የለውጥ ትግል፣ መብቶቹን ለማስከበር ያደረገው ታሪካዊ እርምጃ እንደሆነ ያስረዳል። አያይዞም፣ በየካቲት 1966 ትግል ውስጥ ወታደሮቹም ቢሆኑ ለደረሰባቸው ግፍና በደል ለውጥ ፈላጊዎች ሆነው እንደቀረቡ የማይካድ ሃቅ እንደሆነ ይገልጻል። ሆኖም፣ ከወታደራዊ ክፍሎች ብቻ የተውጣጡ ወኪሎች፣ ብቻቸውን ተነጥለው የመንግሥት ሥልጣኑን ጨብጠው፤ ለተቀረው ሰፊ ሕዝብ ግን ሳያጋሩ በእምቢተኝነት ጠቅልለው እንደያዙ ይመዘግባል።
በዚህ ጋዜጣ አርእስት ውስጥ እንደተመለከተው የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ የሠራተኛውን፣ የጭሰኛ፣ ድሃ ገበሬውንና የንጉስ ከበርቴውን መደቦች ያጠቃልላል። ይኽውም ሲዘረዘር፡-
- ሠራተኛ፡- በፋብሪካ፣ በዘመናዊ እርሻ፣ በንግድ፣ በሕንፃ፣ በመንገድና ተመሳሳይ ኢኮኖሚ ነክ ድርጅቶች ውስጥ በመቀጠር የጉልበቱንና የአእምሮውን ኃይል እየሸጠ የሚኖረው ወዛደር መደብ ነው።
- ጭሰኛና ድሃ ገበሬ፡- ይህ ክፍል ፍጹም መሬት የሌላቸውን /60-70 በመቶ/ እርቦ፣ ሲሶ፣ እኩል አፍሳሾችና፤ ሊያኖራቸው የሚችል በቂ የሚያርሱት መሬት የሌላቸውን /20-30 በመቶ/ ሞፈር ዘማቾች ወይም ከፊል ጭሰኞችን ያጠቃልላል። ይህ ክፍል ከጠቅላላው ሕዝብ 90 በመቶ በላይ ይይዛል።
- ንዑስ ከበርቴ፡- ይህ መደብ በውስጡ ልዩ ክፍሎች አሉት። መካከለኛና ዝቅተኛ የመንግሥት ሠራተኞች ዝቅተኛ ነጋዴዎችንና ባለእጅጥበቦች፣ መምህራን፣ ምሁራን፣ ተማሪዎች፣ መካከለኛና ዝቅተኛ ወታደራዊ መኮንኖችና ወታደሮች ሌሎችም ቋሚና ኢኮኖሚ ነክ ባልሆኑ ልዩ ልዩ የዕለት ተግባራት በመሰማራት ከእጅ ወደ አፍ በሆነ የኑሮ ዘዴ የሚውተረተሩትን ሁሉ በዚህ መደቦች ለማጠቃለል ይቻላል።
የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ የምንላቸው እነዚህን ሲሆን ወታደሩም የዚህ የሰፊው ሕዝብ አካል መሆኑ ግልጽ ነው። ወታደር ወንድሙ ወይም አባቱ ከሆነው ጭሰኛና ድሃ ገበሬ፡ ሠራተኛና ነጋዴ ልጁ ወይም ወንድሙ ከሆነው ተማሪ የሚለየው የተለየ ዩኒፎርም በመልበሱና የጦር መሳሪያ በመያዙ ነው። ዋናው ልዩነት ይኽ ሲሆን ይኸውም ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ነው። በቀን ከሰባት ወይም ከስምንት ሰዓት በስተቀር የሚኖረው ያው ከቤተሰቡ፣ ከጎረቤቱ፣ ከቀበሌው ሰፊ ሕዝብ ጋር ነው። ጥቅሙም፣ ጉዳቱም፣ ሐዘኑም፣ ደስታውም ከሰፊው ሕዝብ አይለይም፤ ቁራጩ ፍላጩ ነውና። ይህን ግልጽ ነገር ለማመልከት የተገደድንበት ዋናው ምክንያት፣ ወታደሩ የሰፊው ሕዝብ አካል እንዳልሆነ፣ በመካከላቸው መሰረታዊ የጥቅም ቅራኔ እንዳለ፣ ወታደሩ ሰፊውን ሕዝብ ማመን እንደሌለበት ወዘተ…. አስመስለው በማቅረብ ለማወናበድ የሚፈልጉ አንዳንድ የሃሳብ ጨቅላዎች የሰፊውን ሕዝብ ድል ለማጨናገፍና ለግል ጥቅማቸው ለማዋል በመነሳታቸው ነው። ወታደር በሰፊው ሕዝብ ውቅያኖስ ውስጥ የሚኖር ዓሳ ማለት ነው።
የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ለአያሌ ዘመናት በነገሥታት፣ በመሳፍንት፣ በባላባቶችና በመኳንንት ሲጨቆንና ሲበዘበዝ የኖረ መሆኑ የሚያከራከር አይደለም። እስካሁን የነበረው የኢትዮጵያ ታሪክ የዚሁ የጭቆናና የብዝበዛ ታሪክ ነው። ባለፈው የካቲት የፈነዳው የትግል እሳተጎሞራ የዚህ ከመጠን ያለፈ ጭቆናና ብዝበዛ ውጤት እንደሆነ ለማንም ግልጽ ነው።
የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ብዝበዛውና ምዝበራው በዛብኝ፣ የጭቆናውን ቀንበር ለመሸከም አልቻልኩም፣ በቃኝ አንገፍግፎኛል በማለት የገዢውን መደብ የመጨቆኛና የመደምሰሻ መሳሪያዎች ተቋቋመ፣ ባንድነት ተነሳ። ምንም እንኳን በመሳርያነት ሲያገለግል ቢኖርም ወታደሩም የተጨቆነና ግፍ የተዋለበት በመሆኑ አፈሙዙን በገዥው ክፍል ላይ አዞረ፤ ከሰፊው ሕዝብ ጎን ተሰለፈ። ሰፊው ሕዝብ መሰረታዊ፣ ሰብአዊና ብሔራዊ መብቱን ከመነጠቁ የተነሳ ወደ ዲሞክራሲ የሚመራው የራሱ የሆኑ የፖለቲካ ድርጅት በማጣቱ ለጊዜው መሳሪያ ይዞና ተደራጅቶ የተገኘው ወታደር የፖለቲካ ስልጣንን ያዘ።
ታዲያ ሰፊው ሕዝብ ብኩርናውን ሸጠ ማለት ነው? አጠቃላይ የፖለቲካ ድርጅት ባይኖረውስ ሌሎች ድርጅቶች ፈፅሞ የሉትም ማለት ይቻላል? የኢትዮጵያ ሠራተኞች አንድነት ማህበር፡ የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር፣ የተማሪዎች ማሕበር፣ በየቦታው በመቋቋምና በመስፋፋት ላይ ያሉት ልዩ ልዩ የገበሬዎች ማህበራት፣ የህብረት ሥራ ድርጅቶች፣ ዕድሮች፣ የመረዳጃና የልማት ማህበሮች ወዘተ… በመጠኑም ቢሆን አሉት። በእነዚህ አማካይነት መብቱንና ጥቅሙን ለማስከበርና ለማስጠበቅ አይችልም ወይ? ከነዚህ የተወጣጡ ወኪሎች ከወታደሩ ከተወከሉ አባሎች ጋር ሆነው ጊዜያዊ የሕዝብ መንግሥት ለማቋቋም የማይችሉበት ምን በቂ ምክንያት አለ? ሰብአዊና ብሔራዊ መብቶቹና ነፃነቶቹ ባይታገዱበት በተለይ የንግግር፣ የጋዜጣ፣ የማህበር፣ የመሰብሰብ፣ መብቶች ሥራ ላይ ቢውሉና ሕዝቡ ባይታፈን እስካሁን ድረስ ሰፊውን ሕዝብ የሚወክሉ የፖለቲካ ማህበሮች /ፓርቲዎች/ ሊቋቋሙ የማይችሉበት ምን ምክንያት ይኖር ይሆን? አሁንስ ቢሆን ይህን ለማድረግ ምን የሚያስቸግር ነገር አለ?
ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ የባላባታዊውን ሥርዓትና የኢምፔሪያሊዝምን ብዝበዛና ጭቆና ለማስወገድ ታሪካዊ የትግል እንቅስቃሴ በይፋ ሲጀምር ግልጥና ተጨባጭ ጥያቄዎች ነበሩት። ከጠቅላላው ሕዝብ 90 በመቶ ገደማ የሚሆነው ጭሰኛና ደሃ ገበሬ የጠየቀው ‘መሬት ላራሹ’ የሚለውን መሪ ቃል በመከተል ራሱንና ቤተሰቡን ሊያስተዳደርበት የሚያስችለው በቂ የሚያርሰው መሬት እንዲያገኝ፣ ለባለ መሬት እርቦ፣ ሲሶ፣ እኩል ማፍሰሱ፤ እህል፣ አሻሮ፣ ብቅል፣ ማስፈጨቱና መጫኑ፤ ጌሾ መውቀጡ፣ የዓመት በዓል ሙክት መጎተቱ፣ በሆነ ባልሆነው ጉቦ መስጠቱ፣ እርሻ አርሞ፣ ውቂያ፣ ወዘተ… እየተባለ በብላሽ፣ በነፃ መሥራቱ እንዲቀርለት፣ ይህ ሁሉ ብዝበዛ እንዲወገድ የመንግሥት ባለስልጣኖች፣ ጭቃ ሹም መልከኛ፣ ባላባት፣ ዳኛ፣ ወረዳ ገዢ፣ አውራጃ ገዥ፣ እንደራሴ፣ ዳኛ፣ በጅሮንድ ጸሐፊዎች፣ ፖሊሶች፣ መታያ፣ መማለጃ፣ የዓመትበዓል፣ የአክፋይ፣ የጠረጴዛ ወዘተ…እጅ በለን በማለት መበዝበዛቸው፣ ማሰራቸው፣ መጨቆናቸው ወዘተ… እንዲቀር፣ የጤና፣ የትምህርት፣ ግብር፣ የልማት፣ የወህኒ ቤት፣ የፖሊስ ጣቢያ፣ የቤተክርስቲያን፣ የመንገድ ወዘተ…መዋጮ የጥቅም ወይም የገቢ ግብር እየተባለ በመገደድ የሚከፍለው የባለስልጣኖችን ቦርጭ ማሳበጫ መሆኑ ቀርቶ በቂ የትምህርት፣ የጤና፣ የገበያ፣ የአስተዳደር አገልግሎቶች እንዲሰጡት፣ መንገድ እንዲሰራለት፣ ለጤና ተስማሚ የሆነ ውኃና የኤሌክትሪክ መብራት እንዲያገኝ፣ ሰብአዊና ብሔራዊ መብቶቹና ነፃነቶቹ እንዲከበሩ፣ በብሔር፣ በነገድ፣ በጎሳ፣ በሃይማኖት፣ በቋንቋ፣ በጾታ በመሳሰለው ሁሉ ልዩነት መደረጉ ቀርቶ ፍጹም እኩልነት እንዲኖር ነው።
ሠራተኛው የጠየቀው ከኑሮ ሁኔታ ጋር የተመጣጠነ የሥራ ዋጋ እንዲከፈለው፣ አሠሪው የላቡን ዋጋ እንዳይዘርፈው፣ እንደፈለገውና እንደሰባራ ገል አውጥቶ እንዳይጥለው፣ ትምህርት እንዲሰጠው፣ ጤናው እንዲጠበቅለት ነው። የሥራአጡም ሰራዊት የጠየቀው ሥራ እንዲሰጠው ነው። ተማሪውም የጠየቀው ትምህርት ለሁሉም እንዲዳረስና የሰፊው ሕዝብ መብቶችና ነፃነቶች እንዲከበሩና እንዲጠበቁ፣ ጨቋኙና በዝባዡ ሥርዓት በሕዝባዊ ሥርዓት እንዲተካ ነው። ዝቅተኛው ነጋዴና ባለእጁም የጠይቀው የውጭ ካፒታሊስቶች ገበያውን በሞኖፖል እንዳይዙበት፣ እንዳያቆረቁዙት ከመንግሥት ድጋፍና እርዳታ እንዲደረግለት ነው። በወታደሩም በኩል ቢሆን የጠየቀው ደመወዝና አበል ከኑሮ ዋጋ ጋር እንዲስተካከል፣ ለመኮንኖች እንደባርያ እንደግል አሽከር ማገልገላቸው እንዲቀር ወዘተ…የሚል ሲሆን በሁሉም ዘንድ ሰብአዊና ብሔራዊ መብቶችና ነፃነቶች እንዲከበሩ፣ እነዚህንም ሊያስፈጽምና ሥራ ላይ ሊያውል የሚችል ዲሞክራሲያዊ የሕዝብ መንግሥት በፍጥነት እንዲቋቋም ነው። የጊዜው ዋና ዋና ጥያቄዎች እነዚህ ነበሩ፤ አሁንም ናቸው።
እነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች ሊሟሉ የሚችሉት ባላባታዊ ሥርዓት ተደምስሶ ከኢምፔሪያሊስት ተጽዕኖ ነጻ የሆነ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሲመሠረት ብቻ ነው። የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ የጥቂት ምርጦች ፈላጭ ቆራጭነትን አይፈልግም፣ የአንድ ነጋሲ አምባገነንነትን በጥቂት ‘ምርጦች’ አምባገነንነት ለመለወጥ ከቶ ፍላጎት የለውም። ፈላጭ ቆራጮችን፣ አምባገነኖችን የተሸከሙበት ትከሻው ተልጧል፣ ጀርባው ተገጣጥቧል። ፈላጭ ቆራጩን አምባገነን መሸከሙ አንገፍግፎታል። ሞግዚት እንሁንህ፣ እናዘጋጅህ ወዘተ… በማለት ከተመላለጠው ጫንቃው ላይ ፊጥ በማለት አዛኝ ቅቤ አንጓቾችን አጥብቆ ይቃወማቸዋል።
‘….. ኢትዮጵያ የተለየች አገር ናት፣ ሕዝቦቿም ልዩ ናቸው፣ ታሪካችን /የፈረደበት የ3ሺ አመት ታሪክ/ ከዓለም ሕዝቦች ታሪክ በምንም አይገናኝም…. የቀሩትን የዓለም ሕዝቦች የመፈንቅለ መንግሥት /ኩዴታ/ ትምህርት በማስተማር ላይ ነን፤ ዓለም አብነታችንን በአድናቆት መከተል ይኖርበታል፤ ወዘተ…’ በማለት ለሚቀባዥሩትን የስልጣን ጥም ለያዛቸው እፍኝ ለማይሞሉ ‘ምርጦች’ ልናስጠነቀቃቸው ይገባናል። አንዳንድ የሦስተኛውን ዓለም በተለይም የአፍሪካን ሃገሮች ምሳሌ ብንጠቅስ፣ ታንዛንያ ባንድ የፖለቲካ ማህበር በሚመራ መንግሥት ትተዳደራለች፤ ሶማሊያ፣ ናይጄሪያ፣ አልጄሪያ፣ ጋና፣ ወዘተ….የወታደር መንግሥት አላቸው፣ ደህና በመሥራት ላይ ናቸው፣ ሕዝቡ ተቀብሏቸዋል ወዘተ…የሚሉት ጥራዝ ነጠቅነት መክፈልት ሲሹ መቅሰፍት እንዳይኾን ጉዳዩን ጠለቅ ብለው ቢያዩት ይሻላቸዋል።
እነዚህ ሃገሮች ከኢትዮጵያ የሚላዩበት አንድ ዋና ነገር አለ። ይኸውም ለተወሰነ ጊዜ ዲሞክራሲ መኖሩ ነው። የፖለቲካ ፓርቲዎችም በነዚህ ሃገር ታሪክ ውስጥ ታይቷል። በርከት ያሉ የፖለቲካ ማህበሮች ተቋቁመዋል። ሰፊው ሕዝብ ሰብአዊና ብሔራዊ መብቶች፤ አነሰም በዛ ተከብረውለታል። ከላይ በተጠቀሱት አገሮች ውስጥ በየጊዜው የተለያዩ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች መደረጋቸውና ሕዝብም ከእነዚሁ እንቅስቃሴዎች ብዙ ትምህርት መቅሰሙ የማይካድ ነው። ከነዚህ ሃገሮች በብዙዎቹ ውስጥም ወታደራዊ መንግሥት የተቋቋመው ሰፊው ሕዝብ ሳይፈልግ በግድ ነው፤ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ቢሆኑ የሰፊው ሕዝብ ፍላጎት የማያሟሉ፣ ቅራኔ የበዛባቸው የሕዝቡን ችግሮች ለመፍታት ያልቻሉ ናቸው። ስለዚህ የነርሱን ምሳሌ ለመከተል መሞከር አለማወቅን ማሳየት ይሆናል።
‘ምርጦቹና’ አጫፋሪዎቻቸው ‘ሊቃውንት’፣ እንደዚሁም የስልጣን ፍርፋሪ ለመለቃቀም ያሰፈሰፉት ቲፎዞዎቻቸው ይህን ሀቅና እውነት አያዩም፣ በሞኖፖል በያዙዋቸው የሕዝብ ዜና ማሰራጫዎች ትክክለኛውንና የሚያዋጠውን መንገድ፤ የሰፊውን ሕዝብ እውነተኛ ፍላጎት ለማመልከት የሚቃጡትን የኢትዮጵያን የሕዝብ ወገኖች ለማጥላላትና ለማርከስ ትልቅ የማወናበድ ዘመቻ ይዘዋል። በልዩ ልዩ ተንኮልና ሴራ የዋሁን ሠራዊት በመሸንገል ለሕዝቡ ታሪካዊ ትግል እንቅፋት ሆነዋል። እውነት ብትመነምን አትሞትም የሚለውን ምሳሌ ገና ካሁኑ በመዘንጋት በተራማጅ የሕዝብ ወገኖች ላይ የውሸት ተራራ በመጫን ላይ ናቸው። የታሰሩት ባለስልጣኖች ልጆችና ወገኖች ናቸው። የውጭ መሣሪያ ናቸው፤ ሥራ የማይሰሩ ሰነፎች ናቸው ወዘተ… በማለት ለብዙ ዓመታት ትልቅ መስዋዕትነት የተቀበሉ ለሰፊው ሕዝብ መብትና ጥቅም ሲታገሉ የቆዩትን የሕዝብ ወገኖች ለማሳጣትና ከሕዝቡ ጋር ለማቃቃር በመጣር ላይ ናቸው። ይኸው ተንኮላቸው መልሶ እንደሚያጠቃቸው አንድና ሁለት የለውም። ይህንንስ ትናንት የሰው ጣኦት ከነበረውና ዛሬ ምስኪን እስረኛ ከሆነው ኃይለሥላሴ እንዴት ሊረዱት አይችሉም? ይህ ደደብነት ነው ወይስ አወናባጅነት?
የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ጥያቄዎችና ፍላጎቶችን ችላ ብለው በማለፍ ‘ምርጦቹ’ አወናባጆች የሰፊውን ሕዝብ ትርታ ተከትለን ነው የምንሄደው፣ ኃይለሥላሴንና ፍጡሮቹን ይዘን አስረንላችኋል፣ ለፍርድ እናቀርባቸዋለን፣ ሀሁ አስቆጥረን፣ ሕዝቡን አስተምረንና አዘጋጅተን የሕዝብ መንግሥት እናቋቁምለታለን፣ እኛኮ የኢትዮጵያ ድሆች ልጆች ነን የጎመን ጨማቂ ልጆች ነን፣ ወዘተ…በማለት ሰፊው ሕዝብ ሳይጠራጠር እጁን ዘርግቶ፣ ቀይ ስጋጃ አንጥፎ እንዲቀበላቸው ይፋዋጭራሉ። እውነቱ ግን ሌላ ነው።
‘ከምርጦቹ’ ውስጥ የጎመን ጭማቂ ልጅ ማን ነው? የጭሰኛና የድሃ ገበሬ ልጆችስ እነማን ናቸው? አማን አንዶም፣ በላቸው ጀማነህ፣ ብርሃኑ ባየህ፣ ወይስ እነሲሳይና ሌሎቹ ናቸው? ይህ ፍጹም ማወናበድ ነው። ሰውን የሕዝቡ ወገን የሚያደርገው ከድሃ መወለዱ ሳይሆን የሰፊውን ሕዝብ ፍላጎት ተረድቶ ከሰፊው ሕዝብ ጎን ለትግል መሰለፉ ነው። ታዲያ ለዚሁስ ቢሆን ምን ማጭበርበር ያሻዋል?
ከብዙ ጊዜ ማጥፋትና ማመንታት በኋላ አጤ ኃይለሥለሴ ከስልጣን ወርደዋል፣ መሳፍንቱና መኳንንቱ /ከሁለት መቶ የማይበልጡ/ ተይዘው 4ኛ ክፍለጦር ገብተዋል። ለምን እስካሁን ድረስ ለፍርድ አልቀረቡም? ለምንስ አልተቀጡም? ደግሞስ ሕዝቡን ሲጨቁኑትና ሲበዘብዙት የኖሩት እነዚህ ብቻ ናቸው? የኃይለሥላሴ መሳሪያ በመሆን ስንቱን አገርወዳድ በግፍ ሲቀጠቅጡ፣ ሲወግሩ፣ ሲያሰቃዩ፣ በሰው ሕይወት ሲያላግጡ፣ ሲጫወቱ የቆዩት እነኮለኔል በላቸው ጀማነህ አሁን ምን በመሥራት ላይ ናቸው? ፊትስ እነኃይለሥላሴን በጠቅላላውም በዝባዦችንና ጨቋኞችን ማን ነበር የሚጠብቃቸው? እነዚሁ አልነበሩምን? አለበለዚያማ ሰፊው ሕዝብ ድራሻቸውን ያጠፋው ነበር።
‘ምርጦቹ’ ጠንካራ መንግሥት የሚያስፈልገው መሳፍንትንና ባለስልጣኖችን ለመቅጣት፤ ሥርዓቱንም ለመለወጥ ነው ይላሉ፣ አሁን ዲሞክራሲ የተሰጠ እንደሆን እነዚያ ጨቋኞችና በዝባዦች ተመልሰው ይመጣሉ፣ ሕዝቡ ጫንቃ ላይ እንደገና ይቀመጣሉ እያሉ ያስፈራሩናል። ሕዝቡን ሞኝ ተላላ፣ ጥቅሙንና ጉዳቱን፣ ወዳጁንና ጠላቱን ለይቶ የማያውቅ ቂል አድርገው ይመለከቱታል። ይህ ሁሉ ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ ነው፣ ‘ምርጦቹ’ የሰፊውን ሕዝብ ጩኸት መቀማታቸው ነው። ‘የራሷ ሲያረባት የሰው ታማስላለች’ እንደሚባለው ነው።
‘ምርጦቹ’ አልፈው አልፈው አንዳንድ ነጠላ ድርጊቶችን በመፈጸም አላማችንን በግብር አሳይተናል እያሉ ይደነፋሉ። አላማ ብለው ያወጡት የተድበሰበሰ ነው። ራበኝ፣ ጠማኝ፣ ታረዝኩ፣ በሽታ ጨረሰኝ ለሚለው ሕዝብ ባህል፣ ታሪክ፣ ቅርስ ወዘተ…. እያሉ ማታከትና ማጭበርበር ምን ፋይዳ አለው? ስልጣን ኮርቻ ላይ ብዙ ዘመን ለመቆየት ሲባል ትግሉ ገና ነው፣ ምን ተይዞ ጉዞ፣ እኛ ዞር ያልን እንደሆን ጉድ ይፈላባቸኋል፣ እስክናሰለጥናችሁ፣ እስክናስተምራችሁ፣ ራሳችሁን በራሳችሁ ለማስተዳደር እስክትበቁና ሕዝባዊ መንግሥት እስኪቋቋም ድረስ መጠበቅ አለባችሁ፣ ጨዋ ሁኑ፣ ታገሡ፣ መብት፣ መብት፣ ዲሞክራሲ፣ ዲሞክራሲ የሚሉትን ተጠንቀቁ በማለት እየደለሉና እያስፈራሩ ሰፊውን ሕዝብ እንደፈረስ ሊጋልቡት ይፈልጋሉ።
የሕዝብ ንብረት የሆነውን ራድዮ፣ ጋዜጣና ቴሌቪዥን ጥርቅም አድርገው ይዘው ተራማጅ የሕዝብ ወገኖችን ያራክሱበታል፣ ያጥላሉበታል፣ ሕዝቡን ያወናብዱበታል፣ ያጭበረብሩበታል። ‘አልኩባዮች’ በሚል ርዕስ በእነዚሁ መሣሪያዎች ያሰራጩት ርካሽና የውሸት ዝባዝንኬ የ‘ምርጦቹን’ ምንነት ደህና አድርጎ የሚያሳይ ነው። ብልህን ማሞኘት ቂምን ማቆየት መሆኑን ማን በነገራቸው? እኛ ከሰፊው ሕዝብ ጎን የተሰለፍነው አወናባጆቹ እንደሚሉት ዝናና ታሪክ ፍለጋ አይደለም፣ የሰፊው ሕዝብ ፍላጎት እውነተኛና ትክክለኛ መሆኑን አጥብቀን የምናምን፣ከሕዝብ የወጣን የሕዝብ ወገኖች ነን። ታሪክ በቆራጥነትና በሥራ ክንውን እንጂ በምኞትና በፍላጎት የሚመጣ እንዳልሆነ አጥርተን እናውቃለን። በነገራችን ላይ ማናቸውም የኢትዮጵያ ዜጋ እኩል ነው ስንል፣ የሰፊው ሕዝብ መብቱ ይከበር፣ ፍላጎቱ ይሟላ ስንል ይህንኑ ለማስገኘት መታገልና አስፈላጊውንም መስዋዕትነት ለመቀበል ተዘጋጅተን እንጂ የአገርና የወገንን ጉዳይ ለጥቂት ‘ምርጥ መኮንኖች’ በመተው በአፍ ለማወናበድ አይደለም። እንደ ‘ምርጦቹ’ ለማወናበድ ሳይሆን በሃቅ የሰፊው ሕዝብ መብት፡ ጥቅምና ደህንነት መጠበቅ እንዳለበት እናምናለን፣ የትግሉ ባለቤት ሰፊው ሕዝብ እንደመሆኑ መጠን የርሱን ድል ማንም በማወናበድ እንዲቀማውና እንዲያበላሽበት አንፈልግም። ከሰፊው ሕዝብና ከወታደሩ በምርጫ የተውጣጣ ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት በፍጥነት ይቋቋም፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ዲሞክራሲያዊ ህገ መንግሥት ወጥቶ ደንበኛ የሕዝብ መንግሥት የሚቋቋምበት ዝግጅት ይደረግ፣ እስከዚያው ድረስ አጣዳፊ የሆኑት የመሬት ላራሹ ጉዳይ፣ የድርቁ ጉዳይ፣ ሥራ ላጣውና ከሥራ ለተባረረው ሥራ የማግኘቱ ጉዳይ፣ ለሠራተኛውም ተገቢውን የጉልበቱን ዋጋ የመክፈሉን ጉዳይ፣ ከሥራው ላይ ላለመባረር ዋስትና የማግኘቱን ጉዳይ አጥብቀን እንመልከተው፤ መፍትሄም በቶሎ ይፈለግለት ነው ያልነው። ታዲያ እነዚህ ሀሳቦች ስለቀረቡ ይህን ያህል የሚደነፉ ሰዎች በተራማጁ ክፍል ላይ ይህን ያህል ዘመቻ የሚያደርጉ ሰዎች ምን ይረቡናል? ምናቸውስ ይታመናል? የዚህ ክፍለ ሃገር፣ አውራጃ፣ ወረዳ ወዘተ …ሕዝብ ደግፎናል፤ ተቀብሎናል እያሉ በሞኖፖል በያዟቸው የዜና ማሰራጫዎች እስከመቼ ሊያወናብዱ ይችላሉ?
ትግሉ በደርጉ ውስጥም ሆነ ውጭ በመፋፋም ላይ ነው። በ‘ምርጦቹ’ ቡድንና በአብዛኛው የደርጉ አባላት መካከል በየግዜው የሚፈጠረው አለመግባባትና እነዚሁ አወናባጆች በተቀሩት የሕዝቡ ወገን በሆኑ ወታደሮች ላይ በማከታተል የወሰዱት እርምጃ፤ በተለይም የመሀንዲስ ጦርና የአርሚ አቪየሽን መወረር በቀላሉ የሚታለፍ ድርጊት አይደለም። በወታደሩ ውስጥና በጠቅላላውም ሕዝብ ዘንድ ሕዝባዊ ስሜት ያላቸውን እውነተኛ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ለማዳከምና ለማጥፋት የሚያደርጉት ዘመቻ እነዚህን አወናባጆች እንደሚያጋልጣቸው አይጠረጠርም። አማን በየመስሪያ ቤቱ እየዞረ ስለደሰኮረ፣ የሕዝብ ፍቅር፣ የአገር ፍቅር ያንገበገባቸው ወታደሮችና ሲቪሎች ስለታሰሩና ስለተገደሉ፣ ሰብአዊና ብሔራዊ መብቶች ስለታፈኑ የሰፊው ሕዝብ ትግል አይቆምም፣ ይቀጥላል እንጂ። የሲአይኤ ልኡካን እነ ኮሪና እነ ዲምፖል ከምርጦቹ ጋር በመሆን የሰፊውን ሕዝብ ትግል ለማጨናገፍ ቢዶልቱም ቅሉ ሰፊው ሕዝብ ውሎ አድሮ ድልን መቀዳጀቱ አይቀርም። የሚያሳዝነው ዛሬ ለሰፊው ሕዝብ የሚጠቅሙ ብዙ ነገሮች ሊሰሩ ሲችሉ ባንዳንድ አወናባጆች ምክንያት እንደገና በቀጠሮ መተላለፋቸው ነው።
ኢትዮጵያ ዛሬ ብዙ ታጋይ ልጆች አሏት፣ ወደፊትም በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ የአገር ፍቅር ያንገበገባቸው እውነተኛ ኢትዮጵያዊያን ይወለዳሉ፣ ያድጋሉ፣ አወናባጆችንና ከዳተኞችን፣ የአገር ሸክሞችን አሽቀንጥረው ይጥሏቸዋል። እስከዚያ ድረስ ትግሉ ይቀጥላል እንጂ አይቋረጥም። የሰፊው ሕዝብ ፍላጎት መሟላቱ አይቀርም እስከዚያ ባለን አቅም ለዴሞክራሲ እንታገላለን።
የዲሞክራሲ ትግል ያሸንፋል
ድሉ የሰፊ ሕዝብ ነው።
የወታደር አገዛዝና የዕድገት ዘመቻ
የኃይለሥላሴ ፈላጭ ቆራጭ መንግሥት በሰፊው ጭቁን ሕዝብ ረጅምና መራራ ትግል ከስልጣን ከወረደ በኋላ፡ በቦታው ተተክቶ ፈላጭ ቆራጭ ለመሆን የሚጥረው ‘የምርጥ’ መኮንኖች ቡድን ለተማሪዎች ፕሮግራም አዘጋጅቷል። ይህ ፕሮግራም ‘ዕድገት በህብረት የዕውቀትና የሥራ ዘመቻ’ ተብሎ ተሰይሟል። ይህ የዕቅድ ላይ ላዩን ማር ለብሶ በውስጡ ግን መራራ መርዝ ያዘለ ስለሆነ በዚህ ጽሁፍ ውስጥ በርእሱ ላይ በማተኮር አንዳንድ መሰረታዊ ጥያቄዎችን ለማንሳት እንሞክራለን።
በመጀመሪያ ‘የዕውቀትና የሥራ ዘመቻ’ መሰረተ ሃሳብ አዲስ አለመሆኑ ግልጽ ሊሆን ይገባዋል። ሀሳቡ ከ13 ዓመታት በፊት በዩንቨርስቲ ተማሪዎች ቀርቦ የፊውዳሉ መንግሥት ሀሳቡ ሕዝቡን በመንግሥቱ ላይ ለማሳደም የታሰበ ሴራ ነው በማለት አከሸፈው። በምትኩም ለሰፊው ሕዝብ ጠቃሚነቱ በጣም አነስ ያለ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች አገልግሎት /ሰርቪስ/ ፕሮግራም አውጆ ተማሪዎች ስለተቃወሙት ከሕዝብ ጋር ሊያጣላቸው ሞከረ። የአሁኑም ‘የምርጥ’ መኮንኖች መንግሥት ‘የዕድገት ዘመቻ’ አመጣጥ ከኃይለሥላሴ ሴራ ጋር በጣም ተመሳሳይ ነው።
የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ለኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ደህንነትና ለኑሮ መሻሻል ለብዙ ዘመናት በግንባር ቀደምትነት ተጋድሏል። ‘መሬት ላራሹ’ እንዲሰጥ የድሃው ሕዝብ መሰረታዊ መብት እንዲከበር፣ ጭቆናና ብዝበዛ እንዲቀር የኢምፔሪያሊስት ተጽእኖ ከኢትዮጵያ እንዲወገድ፣ ፈላጭ ቆራጭ የባላባታዊ አገዛዝ ወድሞ የሰፊው ሕዝብ የበላይ ገዢነት በማያወላውል አኳኋን በህግ ተረጋግጦ በሥራ ላይ እንዲውል ሲታገሉ ብዙዎች ተማሪዎች በፖሊስ ዱላና በወታደር ጥይት ሕይወታቸውን ሰውተዋል። አሁንም ቢሆን ከመላው ሰፊ ሕዝብ፣ ከመላው ሠራዊትና ከብዙሃኑ የደርጉ አባሎች ራሱን ነጥሎ የወታደር ጁንታ ለማቋቋም የሚፈልገው ‘የምርጥ’ መኮንኖች ፈላጭ ቆራጭነት በኃይለሥስላሴ ቦታ እንዲተካ አይፈልጉም።
ለመሆኑ ‘እድገት በህብረት’ የሚለው ሀሳብ በመሰረቱ ከተማሪዎች የፈለቀ ከሆነ፣ ተራማጆችም በሙሉ እስከ መስከረም 2/67 ድረስ ተማሪዎች ወደ ገጠር ተሰማርተው ሕዝቡን እንዲያስተምሩና እንዲያደረጁ ሲጠየቁ ከከረሙ በኋላ አሁን ቀኝ ኋላ ዞረው ‘የእድገት በህብረት’ን ፕሮግራም የሚቃወሙት ለምን ይሆን? የሚል ጥያቄ ከብዙ ቅን ሰዎች ይቀርባል፣ መቅረብም ይገባዋል።
መልሱ በአጭሩ እንዲህ ነው። በመሠረቱ ‘እድገት በህብረት የሥራና የእውቀት ዘመቻ’ የሚደገፍ ነው፣ ተማሪ ሆነ ሌላ ተራማጅ አይቃወመውም። ነገር ግን ፕሮግራሙ በወረቀት ላይ ብቻ ሰፍሮ እንዳይቀርና በእርግጥ በሥራ ላይ እንዲውል አስቀድሞ መፈፀም የሚገባቸው ሌሎች ጊዜያዊ ጉዳዮች አሉ ነው የሚሉት።
ባንዳንድ ተራማጅ አገሮች ለምሳሌ በሕዝባዊ ቻይናና በኩባ የሥራና የእውቀት ዘመቻ መደረጉና ለነዚህም አገሮች ጭቁንና ተበዝባዥ ሕዝቦች ከፍ ያለ ጥቅም መስጠቱ ይታወሳል። ነገር ግን በነዚህ አገሮች ዘመቻው ከመደረጉ አስቀድሞ፡-
- መሬት ከበዝባዥ ተወስዶ ላራሹ ተሰጥቶ ነበር፣ ዋና ዋና የአገሩ የኃብት ምንጮች- ፋብሪካዎች፣ ማዕድኖች፣ ታላላቅ እርሻዎች፣ የንግድ ድርጅቶች፣ ባንኮች፣ወዘተ…- የከበርቴው የብዝበዛና የጭቆና መሳሪያ ከመሆን ነፃ ወጥተው የሕዝብ ኃብት ሆነው ነበር።
- የኢምፔሪያሊስት ብዝበዛና የጥገኝነት አገዛዝ በሕዝቡ ትግል ብርታት አክትሞ ነበር።
- ሕዝባዊ መንግሥት ተቋቁሞ የሰፊው ሕዝብ ሙሉ መብቶች ተረጋግጠው ነበር። እንግዲህ የኢትዮጵያ ሁኔታ ከዚህ ምንኛ የራቀ መሆኑን ለማንም ግልጽ ሊሆን ይገባል፡-
- ምንም እንኳን ኃይለሥላሴና ግብረአበሮቹ ቢያዙም የፊውዳሉ ሥርዓት ገና አልተነካም።
- የኢምፔሪያሊዝም ብዝበዛና ተጽዕኖ እንዳለ ነው፣ እንዲያውም መልኩን በመለዋወጥ እየጠነከረ እንደሚሄድ ‘ምርጦቹ መኮንኖችና’ ሲአይኤ. በድብቅ የሚያደርጉት ግንኙነት ያመለክታል።
- የብሄሮችና የሃይማኖት እኩልነት አልተመሠረተም።
- ሕዝባዊ መንግሥት ተቋቁሞ የሰፊው ሕዝብ የበላይ ገዥነት አልተረጋገጠም፣ መሠረታዊ መብቶቹ አልተከበሩም፣ እንዲያውም በየቀኑ በመደፈር ላይ ናቸው።
ተማሪዎችና ተራማጆች በእንደዚህ ያለ ሁኔታ እድገት በህብረት የተባለው ፕሮግራም የእውቀትም ሆነ የሥራ ዘመቻ ሊሆን አይችልም ይላሉ። በአሁኑ ጊዜ ደርጉንና መንግሥቱን የሚመሩት ‘ምርጥ’ መኮንኖች ለዚህ ሁለት አይነት ትችት ይሰጣሉ። ባንድ ፊት ተማሪዎችና ተራማጆች ጥቅማቸው የተነካባቸው የታሰሩት መሳፍንት ወገን ስለሆኑ ነው፤ ፕሮግራሙን የሚቃወሙት ይላሉ። ተራማጆች ለግል ጥቅማቸው ሳይሆን ለሰፊው ሕዝብ የሚከራከሩ መሆናቸውን ደጋግመው በተግባር ስለገለጹ ይህንን ፍሬቢስና የተኮል ትችት ማንም በቀላሉ ሊቀበለው አይችልም። ስለዚህ ሁለተኛ ትችት ያቀርባሉ። ይኸውም ‘እኛ ዓለም ያደነቀን ትዕግስተኞችና ጥበበኞች ነን፣ ይህን ደንቆሮ ሰፊ ሕዝብ አንቅተን መሬት አደላድለን፣ ሕዝባዊ መንግሥትም እናመጣለን፣ ግን እንደናንተ ችኩል ስላልሆንን ቀስ ብለን እንሄዳለን’ የሚል ትችት ነው።
ምርጦቹ መኮንኖች ቅን ለመሆናቸው እርግጠኞች ብንሆን ኖሮ ጉረኝነታቸውንና ግበዝነታቸውን እንኳን ለጊዜው ናቅ አድርገን በወንድምነት ምክር ልናርማቸው በተወሰንን ነበር። ነገር ግን ደርጉና ሠራዊቱን የሸነገሉና አሁንም ሰፊውን ሕዝብ በሙሉ ለመሸንገልና ለመከፋፈል ያልተቋረጠ ጥረት የሚያደርጉት አሥር የማይሞሉ የደርጉ ምርጥ መኮንኖች ፈጽሞ ቅን አለመሆናቸውንና ስልጣን የጠማቸው ተንኮለኞች መሆናቸውን በተግባር አሳይተዋል። ፋሽስታዊ ተግባሮቻቸውን ‘በሰፊው ሕዝብ ድምጽ’ ጋዜጣ በቁጥር 7 የገለጽን ስለሆነ አሁን ወደዚያ እንመለስም። ስለዚህ አንዳንድ አስተያየቶችን ብቻ በማቅረብ እንወሰናለን።
‘ምርጦቹ’ መኮንኖች አንገልፅም እንጂ ጸረኢምፔሪያሊስት ነን፣ የሕዝብ ወገኖች ነን፣ ሕዝባዊ መንግሥትም እናቋቁማለን፣ ለዚህ ሁሉ በእውቀታችን፣ በትዕግስታችንና በጥበባችን እንተማመናለን’ ይሉናል። አንባቢ ፍረድ፤ እነዚህ ሰዎች ከሠራዊቱና ከብዙሃኑ የደርግ አባላት ተደብቀው ሌሊቱን ሌሊቱን ከምርጥ የአሜሪካ ሰላዮች ከኮሪና ከዲንፖል ጋር በመዶለት ጁንታ ለማቋቋም በመጣር ላይ ናቸው። በሕዝባዊ መንግሥት ስም በአገራችን ላይ ሊዘረጉ የሚፈልጉት በአሁኑ ቺሊ፣ በደቡብ ቬትናም፣ በደቡብ ኮሪያና በካምቦዲያ ያቋቋሙትን አይነት የአሜሪካ አሻንጉሊት የሆነ ፀረሕዝብና ፋሽስታዊ መንግሥት ነው። ይህ ነው ወይ ለኢትዮጵያችን የሚያስፈልጋት? ደግሞስ እነዚህ ሰዎች ለምን ከደርጉና ከሠራዊቱ ተደብቀው ይዶልታሉ? ደርጉንና ሠራዊቱን ያላመኑ ሰፊውን ሕዝብማ እንዴት አድርገው ሊያምኑ ነው? ሰፊውስ ሕዝብ ቅጥፈታቸውን በይፋ እያየ እንዴት ይመናቸው?
ምርጦቹ መኮንኖች የመሬት ይዞታን እናሻሽላለን ይሉናል። ግን በሌላ በኩል ደግሞ ጭሰኛውም ለባለመሬቱ እየገበረ እነደበፊቱ ይቀጥል የሚል ባለመሬቱን የሚያደፋፍር መግለጫ ሰጥተዋል። ከዚህም አልፎ ጭሰኞች ባለመሬቶቹ ላይ በተነሱባቸው ቦታዎች /ለምሳሌ በሲዳሞ ክፍለሃገር በአሬሮና በደራሳ/ ባለመሬቶችን በመደገፍ ሕዝቡን ለማስጨፍጨፍ ወታደር ልኳል። ስለዚህ እነዚህ ‘ጥበበኞችና ትዕግስተኞች ነን’ የሚሉት ‘ምርጥ’ መኮንኖች የመሬት መሻሻል እናመጣለን ሲሉ የአሜሪካ ጌቶቻቸው የሚፈልጉትን አይነት ለከበርቴነት ሥርዓት የሚስማማ ስንኩል የመሬት ድልድል ማለታቸው አይደለምን?
በመሬት መሻሻል በኩል ሰፊው ሕዝብ የሚፈልገው ላይ ላዩን መከፍከፍ ሳይሆን መሰረታዊ ለውጥ ነው። ይህም ማለት ‘መሬት ላራሹ’ ለጭሰኛውና ለድሃው ገበሬ ይሁን፣ የላቡን ፍሬ ማንም ሳይቀማው ለመንግሥት ብቻ እየገበረ ያመረተውን በሙሉ ለራሱ ጥቅም ያውል ማለት ነው። የዚህ አይነት የሰፊውን ገበሬ ፍላጎት የሚያረካ፣ በድሃው ገበሬ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ድልድል በሥራ ላይ ሊውል የሚችለው ሰፊው ደሃ ገበሬ በታዛዥነት ሳይሆን በወሳኝነት ሲሳተፍ መሆኑን ግልጽ ሊሆን ይገባዋል። ይህም እንዲሆን ሰፊው ጭቁን ሕዝብ እንዲደራጅ ያስፈልጋል። መደራጀት ደግሞ መወያየትን፣ መነጋገርን፣ መፃፍን፣ መሰብሰብንና ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግን፣ ብዝበዛንና ጭቆናን ማጋለጥን ይጠይቃል። ታዲያ ‘ምርጦቹ’ መኮንኖች እነዚህን ‘መሰረታዊና አስፈላጊ መብቶች ከሕዝብ ገፈው መሠረታዊ ለውጥ እናደርግላቸኃለን፣ ሕዝባዊ መንግሥትንም አናቋቁምላችኃለን…’ ሲሉን ዝም ብለን መሸንገል ይገባናልን? እነዚህን መሰረታዊ መብቶች እስከተከበሩ ድረስ ‘እድገት በህብረት’ ፕሮግራም የሥራም ሆነ የእውቀት ዘመቻ ሊሆን አይችልም። እውቀትን ለማሰራጨት በሰፊውና በይፋ ተወያይቶ ለሃገር እድገትና ለሰፊው ሕዝብ ደህንነት የሚሆኑ አማራጭ መንገዶችን ያለምንም ገደብ መመርመር ይጠይቃል። የሥራ ዘመቻ ከበርቴዎችንና ባላባቶችን በብላሽ አገልግሉ ካልተባለና ለሰፊው ሕዝብ የሚጠቅም ከሆነ የሰፊውን ሕዝብ መደራጀትና ከበዝባዦች ጋር መታገልን ይጠይቃል።
የደርጉን ፕሮፖጋንዳና መግለጫዎች፣ የ‘ምርጦቹን’ መኮንኖችና የሲአይኤ ጌቶቻቸውን እለታዊ ጉድጉድ ስናይ ‘እድገት በሕብረት የሥራና የእውቀት ዘመቻ’ የተባለው ፕሮግራም አሁን መታወጁ ተማሪዎችን ወደገጠር በመበታተን ትግላቸውን ለመቋቋም የተተለመ ተንኮል መሆኑ ግልጽ ይሆናል። ስለዚህ በአሁኑ ጊዜ የተማሪዎችም ሆነ የተራማጅ ተቀዳሚ ተግባር ከሰፊው ሕዝብ፣ ከመላው ሰራዊትና ከብዙሃኑ የደርጉ አባሎች ጋር መግባባትን በመፍጠር የሲአይኤ ቡችሎች የሆኑትን ‘ምርጥ’ መኮንኖች ከስልጣን ማውረድና የሰፊውን ሕዝብ መሰረታዊ መብቶች ማስከበር ነው።
እርግጥ ሕዝባዊ መንግሥት ባንድ ቀን ሊቋቋም አይችልም። ደርጉም ባንድ ቀን ጓዙን ጠቅልሎ ወደሠራዊቱ ይመለስ ማለት ማፌዝ ይሆናል። ነገር ግን በደርጉ አመራር ውስጥ ቅንና የሰፊው ሕዝብ ወገን የሆኑ ሰዎች የቡችሎቹን ቦታ ይውሰዱ፣ ደርጉም ከሰፊው ሕዝብና ከሰራዊቱ ጋር በመተባበር ወደሕዝባዊ መንግሥት የሚያመሩ እርምጃዎችን ይውሰድ እንላለን። ወደሕዝባዊ መንግሥት የሚያመሩ እርምጃ ለምሳሌ ‘መሬት ላራሹ’ የተባለውን መርሆ ያለምንም ሽፍንፍን ማወጅ፣ መሰረታዊያን መብቶችን መፍቀድና ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥትን ለመቋቋም ከሌሎች የሕዝብ ክፍሎች ጋር አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረግ ነው።
ይህ እስከሆነ [እስካልሆነ – የአዘጋጆቹ እርማት] ድረስ ተማሪዎችና ተራማጆች ወደ ገጠር ሄደው ምንም የሚያደርጉት ነገር የለም። በየካቲት የፈነዳው የሰፊው ሕዝብ ንቅናቄ መቀጠል አለበት፣ ከግቡ መድረስ አለበት። ሰፊው ሕዝብ የኃብቱ፣ የመብቱ፣ የነፃነቱ ባለቤት መሆን አለበት። ተማሪዎች ከሰፊው ሕዝብና ከሌሎች ተራማጆች ጋር ግንኙነታቸውና አንድነታቸውን ማጠናከር አለባቸው። ተማሪዎችን ከትግሉ መስክ ለማባረር የተተለመውም እቅድ መክሸፍ አለበት።