ሰሕድ ቁ. 29

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ቁጥር 29፣     ሐምሌ 17፣ 1967 

የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ

መኢሶን በዚህ የሰፊው ሕዝብ ድምፅ እትሙ፣ ዲሞከራሲ ለኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ የመደራጀት እርካቡ እና ዋስትናው እንደሆነ ያረጋግጣል። በአንጻሩ፣የቀድሞ ገዢ መደቦች በንጉሠ ነገሥታቱ የአገዛዝ መዋቅርና በፊውዳል ሥርዓታቸው ሥር ተደራጀተው ለዘመናት ጥቅማቸውን እንዳስጠበቁ በታሪክ እንደተረጋገጠ ይገልጻል። ስለዚህም በቀድሞ ታሪካችን ገዢ መደቦች ዲሞክራሲ ያላስፈለጋቸውን ያህል፡ አገሪቱም ዲሞክራሲ በታሪኳ እንዳላየች ያብራራል። ዲሞክራሲም ከአሥራ ስምነተኛው ክፍለ ዘመን ወዲህ የቡርዣው ሥርዓት ክስተት በመሆኑ፤ በነጉሠ ነገሥታዊ የፊውዳል ሥርዓት ውስጥ በታፈነችው አገር ውስጥ የዲሞክራሲ ጭላንጭል ይታያል ብሎ መገመት እንደማይቻል ያረጋግጣል። ባንጻሩ ግን፤ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ይበልጥ እንዲደራጁና እንዲታገሉ የዲሞክራሲ መብቶች መከበራቸው እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ ይገልጻል።     

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ለሰፊው ሕዝብ ሰራተኛ ገበሬ፣ ነጋዴ፣ ወታደር፣ ምሁር መብትና ጥቅም የሚታገል ጋዜጣ

የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ይቅደም

ቁጥር 29                                                                     ቀን 17/11/67

 

ዲሞክራሲና የመደራጀቱ ጉዳይ

ዲሞክራሲ ዛሬ የሰፊው ሕዝብ መፈክር ነው። አድሃሪ ኃይሎች ተደራጅተው ለዘመናት ሰፊውን ዋትቶ አደር ሕዝብ በገዙበት፡ የአመጽ ጫናቸውን በሰፊው በዘረጉበት አገር ውስጥ ዲሞክራሲ ልዩ ትርጉም አለው። ለሰፊው ጭቁን ሕዝብ ዴሞክራሲ የመደራጃ እርካቡ ነው፣ የኑሮ ዋስትናው ነው። ስለዚህ ዛሬ የዲሞክራሲ ጥያቄ ዋና የትግል ጥያቄ ነው።

በአገራችን ታሪክ ውስጥ መቼውንም ቢሆን ዲሞክራሲ ለኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ የደረሰበት ጊዜ አልነበረም። በባርያ ስልተምርት ላይ የቆመውንና ምን አልባትም እንደጥንት ግሪኮች ህብረተሰብ ለ‘ጨዋው’ መደብ፣ ለባለባሪያው፣ ለ‘ዜጋው’ ዲሞክራሲን ሳይሰጥ ያልቀረውን የአክሱምን ስልጣኔ፣ ከፋሽስት ኢጣሊያ ወረራ በፊት ለአንድ ሁለት ዓመት ያህል የነበረችውን የጋዜጣ ነፃነትና እንደገዳ ባሉ ባንዳንድ የቀድሞ ባህላዊ አስተዳደሮች ውስጥ የነበሩትን አንዳንድ ዴሞክራሲያዊ መልክ ነበራቸውን አሰራሮች ወደጎን ብንተው ኢትዮጵያ በፍጹም ዴሞክራሲን አላወቀችም ለማለት እንችላለን።ያገሪቷን አስተዳደግ ታሪክ ስንመለከትም ይህ ሁኔታ ፍፁም አያስደንቀንም።

ምኒሊክ የንጉሠ ነገሥቱን መንግሥት ከመፍጠራቸው በፊት በአበሻ ሀገርም ሆነ በሌሎች አሥራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን መንግሥታትና ሱልጣናት የነበረው ቢደራጅ ፊውደላዊ፡ ያለዚያም ከዚያ የሚቀድም ሥርዓት ነበር። ዲሞክራሲ ከከበርቴው ሥርዓት ጋር የሚመጣ ስለሆነ በነዚያ ባለፉት ህብረተሰቦች ውስጥ ሊታይ ይችል ነበር ተብሎ አይገመትም። የሚኒሊክ የንጉሠ ነገሥት መንግሥት በፊውዳላዊ ሥርዓት ላይ የቆመ፡ እንዲያውም ይህንን ሥርዓት ከአበሻው አገር ወደ ደቡብ ያዛመተና ያስፋፋ መንግሥት ነበር። የኢምፔሪያሊዝም በዘመኑ መግባት ይህንን የንጉሰ ነገስቱን መንግሥት መሰረታዊ ባህሪ አልለወጠውም። የኃይለሥላሴ ዘመንማ በትክክል ‘ፊውዶ-ፋሽስት’ ተብሎ ተጠርቷል። ፊውዳላዊና ፋሽስታዊ የአመጽ አገዛዝ ማለት ነው። ስለዚህም ኢትዮጵያ በታሪካዊ ውስጥ መቼውንም ቢሆን ዲሞክራሲያዊ አስተሳሰብንም ሆነ አሰራርን ለማግኘት እድል አላጋጠማትም።

ይልቁንስ ኤርትራ ለአሥር ዓመታት ያህል በእንግሊዞች ስር በነበረችበት ጊዜ ዲሞክራሲን በመጠኑም ቢሆን አይታለች። በእነዚያ አሥር ዓመታት ውስጥ በኤርትራ የንግግር፣ የጽሁፍ፣ የመደራጀት ነፃነቶች ነበሩ። ነፃ ጋዜጦች፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች፡ የሙያና ሌሎችም ህዝባዊ ድርጅቶች ነበሩ። ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በፌዴሬሽን እንድትያያዝ በተወሰነበት ወቅት፤ የራስዋ ህገ መንግሥት ዴሞክራሲያዊ ከመሆኑ የተነሳ የኃይለሥላሴም መንግሥት ቢያንስ በወረቀት ዲሞክራሲያዊ ለመምሰል እንዲችል ‘የተሻሻለውን’ ህገመንግሥቱን እንዲያወጣ ተገድዶ ነበር። ይሁንናም፡ እንደሚታወቀው ሁሉ፡ የኃይለሥላሴ መንግሥት ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን በመፍቀድ የኢትዮጵያን ወደ ኤርትራ ደረጃ ከፍ በማድረግ ፈንታ የኤርትራን ነፃ ጋዜጦች፡ የሞያ ድርጅቶችና ፓርቲዎች አንድ ባንድ ደመሰሰ፤ ኤርትራን አቆርቁዞ ወደኢትዮጵያ ደረጃ አወረዳት። ይህም በኤርትራና በኢትዮጵያ ሕዝቦች ላይ የተፈጸመ ፋሽስታዊ ወንጀል እንደነበር ግልጽ ነው።

በመጋቢት 3 ቀን 1967 ‘ኢትዮጵያ ለዜጎችዋ ሁሉ እኩል ናት’ በሚለው መግለጫው ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት በኤርትራ ያን ጊዜ ስለነበረው ዲሞክራሲ በበኩሉ የሚከተለውን ይጽፋል፡-

‘…በዚሁም /ማለት በከፋፍለህ ግዛ- ሰሕድ/ ተንኮል ምክንያት የቀበሌው ሕዝቦች በሃይማኖት ልዩነት ላይ በተመሰረተ የፖለቲካ ፓርቲ ወይም ቡድን ተከፋፍለው የእርስ በርስ ሲታገሉ ኖሩ። ቅኝ ገዢዎቹ ያነን የርስ በርስ ትግልና በዜጎቹ መካከል ያለውን ልዩነት በድርጅት መልክ ቀርጾ ኗሪ የሚያደርገውን መላ የዲሞክራሲ ሥርዓት የሚለወ አወናባጅ ስያሜ ሰጥተውት ነበር።…’

ከዚያም የመንግሥቱ መግለጫ እንዴት ይህ የእርስ በእርስ ትግል የኤርትራን ሕዝብ እንዳዳከመውና እንዴት የፖለቲካ ቡድኖች በገንዘብ እንደተሸጡ ከተናገረ በኋላ፡-

‘….ሆኖም በዚያን ጊዜም ቢሆን የሰፊው ሕዝብ ድጋፍ ከኋላው የነበረና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ስሜት በቅኝ ገዢዎች ድለላ ያልላሸቀዉ የኤርትራና የኢትዮጵያ ሕዝብ ያንድነት ማህበር የራሱን የፖለቲካ ቡድን የነፃነት ማስገኛ ግንባር አድርጎት ነበር…’ ይላል።

በዚያው ባንድ መግለጫ ውስጥ በሚገኙትና በጥቂት አረፍተ ነገሮች በሚራራቁት በነዚህ ሁለት ጥቅሶች መካከል ያሉትን አይን አውጣ ቅራኔዎች ማንም ባንዴ ሊያያቸው ስለሚችል እዚህ ላይ በዝርዝር አንመለከታቸውም። የቀሩት የዚያን ጊዜ የኤርትራ ፓርቲዎች ‘በሃይማኖት ልዩነት ላይ’ የተመሰረቱ ሲሆኑ ይህኛው መግለጫው የሚያሞግሰው ፓርቲ ግን ‘የነፃነት ማግኘት ግንባር’ ነበር! እነዚያኞቹ በገንዘብ በቅኝ ገዢዎች የተገዙ ሲሆኑ ይህኛው ግን ከኃይለሥላሴ መንግሥት ምንም ጉቦ አልተቀበልም ነበር! ቅኝ ገዢዎች የፈጠሩት ‘ዲሞክራሲ’ የሚባል መላ እነዚያኞቹ ሲጠቀሙበት እንደወንጀል፡ እንደዚህኞቹ ሲጠቀሙበት ደግሞ እንደተቀደሰ ሥርዓት ይቆጠራል።

መቼስ ይህ የመንግሥቱ መግለጫ የኤርትራን የፖለቲካ ታሪክ ፍጹም አጣምሞ እንዳቀረበ ግልጽ ነው። ባጭሩ ነገሩን ለማቅናት ያህል፡ እንግሊዞች ከኤርትራ ሊወጡ ሦስት-አራት ዓመት ሲቀራቸው በኤርትራ ቢያንስ ስድስት የታወቁ የፖለቲካ ፓርቲዎች ነበሩ።

1ኛ/ የመንግሥት መግለጫ የተጠቀሰው ‘ዩኒየኒስት ፓርቲ’ የክርስቲያኖች ሆኖ በእርግጥም ከኢትዮጵያ ጋር መዋሃድን የሚጠይቅ ነበር።

2ኛ/ የኤርትራ እስላሞች ማህበር – ‘ኤሪትሪአን ሞዝለም ሊግ’ – ቢቻል ወዲያውኑ፡ለሙሉ ነጻነት፡ ያለዚያም ለአሥር ዓመታት በኢንተርናሽናል ቁጥጥር ስር ለመኖር ይታገል ነበር።

3ኛ/ ሊበራል ፕሮግረሲቭ ፓርቲ የክርስቲያኖች ሆኖ ቀስ በቀስ በተባበሩት መንግሥታት ቁጥጥር ስር ነፃነትን እናገኝ ይል ነበር።

4ኛ/ ያዲሲቱ ኤርትራ ቡድን በጣሊያኖች ቁጥጥር ለተወሰነ ጊዜ ቆይተን ነጻነትን እናግኝ ይል ነበር።

5ኛ/ የምጽዋ የእስላሞች ብሔራዊ ቡድን ለሌሎች አሥር ዓመታት በእንግሊዞች ስር ቆይተን ከዚያ በኋላ ነፃ እንውጣ የሚል ነበር።

6ኛ/ የአርበኞች ማህበር የተባለው ድርጅት ደግሞ ‘በፖለቲካ ውስጥ ሳይገባ’ የአባሎቹን መብት ለመጠበቅ ብቻ የቆመ ነበር። ከነዚህ ፓርቲዎች ውስጥ ከመጀመሪያ በስተቀር፡ የቀሩት አብዛኞቹ ከኃይለሥላሴ ፊውዳላዊ የንጉሰ ነገስት መንግሥት ጋር መዋሃድን በጥብቅ ይቃወሙ ነበር።

ለማንኛውም ግን፡ የሃይማኖትን ባንዲራ ቢያውለበልቡም፡ ወይንም ያውለበለቡ ቢመስሉም ሁሉም የቆሙት የመደብ ጥቅምን ለመጠበቅ መሆኑን የፖለቲካ ሳይንስ ሀሁ ያስተምረናል። በማንኛውም ህብረተሰብ ታሪክ ውስጥ ከሃይማኖቶች መፈጠር ጀምሮ በሃይማኖቶች መካከል የተደረጉት ጦርነቶች የጥቅም ጦርነቶች ነበሩ። ያውሮፓውያን ክሩሴድስ ሆኑ የእስላም ሃይማኖት ታላላቅ ወረራዎች፡ በኢትዮጵያም ለሦስት መቶ መታት ያህል፡ ከአሥራሶስተኛው እስከ አሥራስድስተኛው ክፍለ ዘመን፡ በአበሻው መንግሥትና በምሥራቅ የሱልጣናት መንግሥት መካከል ተደጋግመው የተደረጉት ጦርነቶች ሀይማኖትን የመሰለፊያ ባንዲራ አደረጉት እንጂ ዋና ምክንያታቸው የጥቅም፣ የኢኮኖሚ በላይነት ፍላጎት ነበር። ከዚህ በላይ የተጠቀሱትም የኤርትራ የቀድሞ የፖለቲካ ማህበራት እንደዚሁ የመደብን ጥቅም ለመጠበቅ የቆሙ ነበሩ።

ይህ ሆኖ ሳለ ከላይ የጠቀስነው የወታደራዊዉ መንግሥት መግለጫ የሚያሳየው አንድ ዋና ነገር ቢኖር የደርጉ ‘ብሔረኛነት’- ‘የኢትዮጵያ አንድነት ፍጹምነት’ – እስከምን ድረስ አይኑን አሳውሮት የዲሞክራሲን ትርጉምና ጥቅም እንዳያይ እንዳደረገው ነው።

ወደ ዋናው አርእስታችን እንመለስና እንግዲህ ኢትዮጵያ መቼውንም ቢሆን ዲሞክራሲን ከሥራ ላይ ለማዋል እድል እንዳላገኘች አሁንም እናስታውስ። የየካቲት እንቅስቃሴ እንደፈነዳ ግን በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የዲሞክራሲ ጭላንጭል ታይቶ ነበር። የአክሊሉ መንግሥት እንደወደቀ መላው የአገሪቱ ሕዝብ፣ መላው የነቃው የህብረተሰባችን ክፍል፣ ወዝአደሩ፣ ንኡስከበርቴው፣ ገበሬውና በጠቅላላው ሰፊው ሕዝብ የዲሞክራሲን ጥያቄ አጣዳፊ በሆነ መንገድ አቅርቦ ነበር፤ ለጥቂት ጊዜና በመጠኑም ቢሆን ዲሞክራሲን በቀጥታ በሥራ ላይ ማዋል ተጀምሮ ነበር። የዛሬን አያድርገውና የካቲት 19 ቀን 1966 2ኛው ክፍለ ጦር አስመራን ይዞ ለንጉሱ ካቀረባቸው 23 ጥያቄዎች ውስጥ አንዱ የዲሞክራሲያዊ መብቶች ጥያቄ ነበር። የዛሬን አያድርገውና፡ የካቲት 21 ቀን 1966 አራተኛው ክፍለ ጦር በአዲስ አበባ ላይ ባሰራጨው የ11 ነጥቦች በራሪ ወረቀት በመጀመሪያ ደረጃ የጠየቀው የንግግርን፣ የጽሁፍን፣ የመሰብሰብን ወዘተ. ዲሞክራሲያዊ መብቶች ነበር። ባለፈው ዓመት በመጋቢት ወር በኢትዮጵያ ዲሞክራሲ ለጥቂት ሳምንታት ሰፍኖ ነበር። ያኔ ብቅ ያለችው የዲሞክራሲ ጭላንጭል እየመነመነች፣ እየተዳከመች ሄዳ መስከረም 2 ቀን 1967 ላይ ከነጭራሹ ድርግም አለች። ያ ሁሉ የየካቲት ተስፋ እንዲያ ሲቀጭ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ኃይለሥላሴን የመሰለ ፋሽስታዊ ፈላጭ ቆራጭ ከኢትዮጵያ ሕዝቦች ጫንቃ ሲወርድ፣ ሰፊው ሕዝብ ከዋይታውና ከፈንጠዝያው የትኛውን መምረጥ እንደሚገባው ማወቅ ተስኖት ነበር። እንደሚታሰበው ይህ የተቃራኒ ድርጊቶች በአንድ ላይ መምጣት በተራማጅ የህብረተሰባችን ክፍሎችም ውስጥ ታላቅ ውዥንብርን ፈጥሮ ነበር።

ፊውዳሊዝም የጨለማ ሥርዓት እንደመሆኑ መጠን በዚህ ሥርዓት ውስጥ ሰፊው ሕዝብ በምንም አይነት ስለራሱ የወደፊት እድል አንዲት ቃል እንኳን እንዳይተነፍስ፣ ስለትምህርቱም ሆነ ስለ ባህሉ፣ ስለአስተዳደሩ፣ ስለኢኮኖሚው፣ ስለፖለቲካው በአጭሩ ስለማንኛውም የህብረተሰብ ጥያቄ አሳብ እንዳይሰጥና ከላይ የተወሰነው ብቻ በግድ፡ በፋሽታዊ አመጽ እንዲፈጸመበት ተደርጎ ኖሯል።

እንደዚህ አይነቱ ፀረ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በሰፈንበት አገር፡ ሕዝቡ አሳብን የሚያገኘው ከአፍ ወደ ጆሮ በሚተላለፈው፡ አሥር ጊዜ ተለዋውጦና ተጣምሞ በሚቀርበው የመንደር ወሬ ነው። የኃይለሥላሴ መንግሥት ራሱ የመንደርን ወሬ መልቀምንና እራሱም ፈጥሮ ማሰራጨትን እንዳገዛዝ ዘይቤ ሲጠቀምበት እንደነበር ይታወሳል። የጊዜው ወታደራዊ መንግሥትም የመንግሥትን ስልጣን በተግባር ከጨበጠበት ከሰኔ 26 ቀን 1966 ጀምሮ እስከ ዛሬ ‘የሃሰት ወሬ’ የሚያሰራጩትን ለመቋቋም ብዙ ወትውቷል። ታዲያ እራሱስ በየጊዜው አውቆ ያሰራጫቸው የመንደር ወሬዎች የሉም ወይ? ራሱስ ልክ እንደኃይለሥሳሌ መንግሥት፡ የሃሰት ወሬ ከማሰራጨት መች ነፃ ሆኖ ያውቃል? ከዚህም የባሰ ግን፡ዲሞክራሲ በአገሪቷ ስለሌለ፡ ፊውዳላዊ በሆኑት የእርስ በርስ ትውውቅ፣ የወዳጅነት፣ የምልጃ፣ የመንደር ወሬ ዘዴዎች በመጠቀም ሰንቱን አድሃሪ በየስልጣን ቦታው ሹሟል።

በኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ኑሮና አሰራር ስለማይታወቁ ሌላው ቀርቶ ይህ የምንሰራበት አማርኛ ቋንቋ እንኳን ፊውዳላዊ ዘይቤዎቹን እንዳዘለ እንዲቆይ ሆኖአል። የአበሻው ፊደላዊ ሥርዓት የፈጠረው ባህል በቀጥታና በማያወላውል ቋንቋ ለማለት የሚፈልጉትን ነገር መናገርን አይፈቅድም። እንዲያውም ተቃውሞም ሆነ ሂስ በተቻለ መጠን በተሸፋፈነ ቋንቋ፣ በእንቆቅልሽ ቋንቋ እንዲቀርብ ይገደድ ነበር። ነፃ ውይይትና ክርክር መቼውንም ቢሆን አልነበሩም። አሁንም አሳብን ያለአንዳች ተጽዕኖ ባደባባይ ለማቅረብ የሚችለው ወታደራዊው መንግሥት ብቻ በሆነበት ሰአት ሰፊው አምራች ሕዝብ ተለጉሞ ከመያዙ የተነሳ ኑሮውን ለማሻሻልም ሆነ አዳዲስ ትምህርቶችን ለመቅሰም ብዙ ችግር አለበት። የሚገርመው ግን፡ ይህ በነፃ ለመናገር እርሱ ብቻ መብት ያለው መንግሥትም ቢሆን ባንዳንድ ዓብይ የአገር ጉዳዮች ላይ ግልጽና የማያወላውል አቋም አላሳየም። ለዚህ ግን ምክንያቱ የፊውዳላዊ ሥርዓት ያነጋገር ወግ ተዕእኖ ብቻ አይደለም፤ ያስተሳሰብ ውዥንብርም ነው።

 
የፖለቲካ ፓርቲው ጉዳይ፡

ያስተሳሰብ ውዥንብርን ቁልጭ አድርገው ከሚያሳዩት የአገር ጉዳዮች አንዱ የመንግሥቱ የፖለቲካ ፓርቲ ጉዳይ ነው። የፖለቲካ ፓርቲ ወይንም ፓርቲዎች ጉዳይ በእነዚያ በጥቂቶች የዲሞክራሲ ሳምንታት በመንግሥቱ ጋዜጦች በነፃ የተተቸበት ቢሆንም በመንግሥት ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ የተነሳው በታህሳስ 11 ቀን በወጣው ‘በህብረተሰባዊነት’ መመሪያ ነበር። በዚህ ‘መመሪያው’ ውስጥ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት አንድ ‘በህብረተሰባዊነት ፍልስፍና የሚመራ መደበኛ የሆነ መላውን ሕዝብ የሚስብና የሚያስተባብር ብሔራዊ የተራማጆች የፖለቲካ ህብረት መኖር አለበት’ አለ። ‘መደበኛ’ የሚለው ቃል ውዥንብርን ማስከተሉ አልቀረም። መደበኛ ከተባለ፡ ከፈለጉ ሌሎችም ሊኖሩ ይችላሉ ማለት ይሆን የሚል ጥያቄ አስነስቷል። ‘የተራማጆች የፖለቲካ ህብረት’ የተባለውንስ ምን ይሆን? ‘መመርያው’ ራሱ ከፍ ብሎ ‘የፖለቲካ ማህበር’ ያለው ነው? ታድያ እርሱ ልዩ ልዩ አስተሳሰብ ያላቸውን ተራማጅ ግለሰቦች የሚያስተባብር ‘የግለሰቦች ግንባር’ ማለት ነው? ወይንም ደግሞ ‘ማህበር’ ማለት እዚህ ላይ ፓርቲ ማለት ከሆነ፣ በፍጥረቱ ያንድን መደብ ጥቅም ብቻ ለመጠበቅ[1] በግለሰቦች ፈቃደኝነት ብቻ በነፃ የሚቋቋመው የፖለቲካ ፓርቲ እንዴት በአዋጅ ይፈጠራል? መመሪያው አዋጅ ከሆነ ማለት ነው። ‘መላውን ሕዝብ የሚስብና የሚያስተባበር’ ከተባለ ምናልባት ልዩ ልዩ ፖርቲዎችና ህዝባዊ ድርጅቶችን – ማስ ኦርጋናይዜሽንስ- የሚያቅፍ ግንባር ማለት ይሆን?

እነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች እስከ ዛሬ ሳይብራሩ ቀርተዋል። እንዲያውም ወታደራዊዉ መንግሥት ወይንም አንዳንድ የደርግ አባሎች በጊዜው ባደረጓቸው ንግግሮችና ባወጧቸው መግለጫዎች ነገሩን ከባሰ ውዥንብር ውስጥ ከተውታል።

ይህንን ሁኔታ ለማሳየት በአንድ የቅርብ ጊዜ ምሳሌ እንጀምር፡-

የደርጉ ዋና ሊቀ ሊቀመንበር ባለፈው ሰሞን በሀረርጌ ክፍለ ሀገር ለወታደሮች ባደረጉት ገለፃ ውስጥ ስለአቢዮቱ መጨረሻ ግብ ሲገልጡ “በዚህ እርምጃ (ማለትም አድሃሪዎችን በየቦታው በመያዝ- ሰሕድ) ጭቁኑ ሕዝብ ነፃነቱንና እኩልነቱን እንዲጨብጥ ከአደረግንና መብቱ ከተረጋገጠለት በኋላ የሚጠብቀን ታላቁ ኃላፊነት አንድ ራሱን የቻለ ብሄራዊ የፖለቲካ ድርጅት (ፓርቲ) ማቋቋም ነው” ብለዋል። ይህን ለማድረግ የሚያስችሉ መሰረታዊያን መብቶችን የሚያቅፍ አዋጅ በመዘጋጀት ላይ መሆኑንና ይህን አዋጅ ተዘጋጅቶ ሲወጣ አፈር ገፊውን ገበሬ፣ ወዛደሩን፣ ምሁራንና ተማሪዎችን የሚወክሉ፡ “በህብረተሰባዊት ኢትዮጵያ መመሪያዎች መሰረት የተደራጁ ማህበራት በዚህ በተባለው አንድ ብሔራዊ ፓርቲ ተጠቃልለው አገር የማስተዳደርን ከመለዮ ለባሹ ሰራዊት እንዲረከቡ ይደረጋል….” ብለዋል።

በመሰረቱ፡ ዲሞክራሲያዊ ሁኔታ እንዲፈጠርና የፈለገ ሁሉ፣ የቻለ ሁሉ፣ እንደ የመደብ ጥቅሙና ርእዮተአለሙ፣ በፓርቲዎችም ሆነ በሕዝባዊ ድርጅቶች ውስጥ እንዲሰበሰብ የሚደረገው፣ ሰፊው ሕዝብ ታግሎ ጠላቶቹን – ፊውዳሊዝምንና ኢምፔሪያሊዝምን- በአብዮታዊ ኃይል ከደመሰሰ በኋላ ‘ነፃነቱንና እኩልነቱን’ ለመጨበጥና ‘መብቱን’ ለማረጋገጥ እንዲችል ነው። ሰፊው ሕዝብ የራሱን ነፃ ድርጅቶች ሳያቋቁም አቋቁሞ ሳይታገል በምንም አይነት ተአምር ነፃነቱንና እኩልነቱን ሊያገኝ አይችልም። ነፃነቱንና እኩልነቱን የሚያስጨብጠውና መብቱን የሚያረጋግጥለት የገዛ ሃይሉ እንጂ ወታደራዊ መንግሥት አይደለም፣ ሊሆንም አይችልም። የራሱ ነፃ ድርጅቶች ከሌሉት ሰፊው ሕዝብ ምንም አያገኝም፣ ያለተጋድሎ ከላይ የሚሰጠው አንድም ነገር የለም። በሊቀመንበሩ አባባል መሰረት ግን ነፃነትንና እኩልነትን ሰጭው ወታደራዊው መንግሥት ሲሆን ‘ብሔራዊው የፖለቲካ ድርጅት’ የሚቋቋመው ግን ለንኡስ ከበርቴው ወታደራዊ መንግሥት ‘ተቀባይነት ያለው’ ሽፋን ለመስጠትና ትግሉን ለመግራት ያህል እንጂ ለአብዮቱ መግፊያ አይደለም።

‘ነፃነት፣ እኩልነትና መብት’ የመራራ ትግል ውጤቶች እንጂ በቅድሚያ ከመንግሥት የሚሰጡ ነገሮች አይደሉም። ደግሞም በኢትዮጵያ እነዚህ ቃላት ሙሉ ትርጉማቸውን የሚያገኙት ፊውዳሊዝምና ኢምፔሪያሊዝም፡ ከላይ እንዳልነው ሁሉ፡ በአብዮታዊ ኃይል ከተደመስሱ በኋላና ህዝባዊ ሥርዓት ሲቋቋም ብቻ ነው። ለዚህም የመጨረሻውን ድል በር የሚከፍተው የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ዋና ጥያቄ የሆነው የዲሞክራሲ ጥያቄ ነው። ቅደም ተከተሉ እንግዲህ መጀመሪያ ዲሞክራሲያዊ መብቶች፡ ከዚያም ካሁኑ ይበልጥ የጋለና የተደራጀ ህዝባዊ ትግል፡ ከዚያም ‘ነጻነት፣ እኩልነትና መብት’ ነው።

በጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት አስተሳሰብ ውስጥ ያለውን የቅደም – ተከተል መናጋት አልፈነው ዋናው ሊቀመንበር ቀጥለው የሚያቀርቡትን አሳብ ብንመለከት አሁንም ውዝንብር እንዳለ እንረዳለን። ሊቀመንበሩ “መሰረታውያን መብቶችን የሚያቅፍ አዋጅ በማዘጋጀት ላይ ነው” ብለዋል። ማንም እንደሚያውቀው ‘መሰረታዊያን መብቶች’ የሚባሉት የንግግር፣ የጹሁፍ፣ የመሰብሰብ፣ የማደራጀት ወዘተ. ዲሞክራሲያዊ መብቶች ናቸው። እንግዲህ  የተባለው አዋጅ እነዚህን የሚያቀፍ ከሆነ ‘አንድ ፓርቲ’ ከሚለው የመንግሥቱ ምኞት ጋር እንዴት ሊታረቅ እንደሚችል ፈጽሞ አይታየንም። የተባሉት ዲሞክራሲያዊ መብቶች የተኮላሹና እንደ ሃይለላሴ መንግሥት ህገመንግሥት ለይስሙላ የሚታወጁ የብጣሽ ወረቀት ጉዳይ ካልሆኑ በስተቀር ማለት ነው። እውነተኛ ዲሞክራሲያዊ መብቶችና አንድ ለብቻው የሆነውን የመንግሥት ፓርቲ በዚያው በአንዱ አዋጅ ለመመስረት አይቻልም።

በተረፈም እንደሊቀመንበሩ አነጋገር ይህ ፓርቲ የወዝአደሩን፣ የአፈር ገፊውን ገበሬ፣፤ የምሁራንና ተማሪዎችን’ ‘በህብረተሰባዊነት ኢትዮጵያ መመርያዎች መሰረት የተደራጁ ማህበራትን’ (ስርዝ-ሰሕድ/ ያጠቃልላል ሲባል ሻለቃ መንግሥቱ ግንቦት 3 ቀን ‘ለአፋር ሕዝብ ተወካዮች’ ካደረገው ንግግር ጋር የሚሄድ አይደለም። በዚያ ንግግር ውስጥ ሻለቃው፡-

“በፖሊቲካ ረገድ የሆነ እንደሆነ በፍልስፍናችን መሰረት ወደፊት የሚቋቋመው የሕዝብ መንግሥት በአንድ ተራማጅ የፖለቲካ ማህበር የሚመራ ነው። ይኽም ተራማጅ የፖለቲካ ማህበር በአፈር ገፊው ገበሬና በወዝአደሮች ብቻ የተገነባ ይሆናል። የመንግሥት ባለስልጣን የሚሆኑትም በዚሁ የፖለቲካ ማህበር ክልል ውስጥ ያሉት የወዛደሩና የገበሬዎች ማህበር አባሎች ይሆናሉ…” ይላል።(ስርዝ-ሰሕድ/

እዚህም ላይ ውዥንብር ተፈጥሯል ማለት ነው። በታህሳስ አሥራ አንዱ የህብረተሰባዊነት መመሪያና ሻለቃ መንግሥቱም፡ ሌሎችም የደርግ አባሎች አልፎ አልፎ በሰነዘሯቸው አንዳንድ አሳቦች የሄድን እንደሆነ የመንግሥቱ ፓርቲ ‘የተራማጆች ህብረት’፡ ‘የተራማጆች የፖለቲካ ማህበር’፡ ማለትም የተመረጡ ሰዎች የሚያቋቋሙት ‘የግለሰቦች ግንባር’ ሆኖ እናገኘዋለን። ባሁኑ የሊቀመንበሩ አባባል ይሆነ እንደሆነ ደግሞ ከሞላ ጎደል ህዝባዊ ድርጅቶችን፡ የሙያ ድርጅቶችን ሁሉ የሚያያይዝ ‘ግንባር’ ይመስላል። እንደዚያ ሆኖ እንኳን ይህኛው ግንባር አውቆም ሆነ ባለማወቅ ወደ ጎን የሚተዋቸው ሕዝባዊ ድርጅቶች- ለምሳሌ የሃይማኖቶች ተከታዮች ድርጅቶች፣ የብሄረሰቦች፣ የመረዳጃ የእድር ድርጅቶች -አሉ።

ይሁንናም፡ የታሰበው እንግዲህ ልዩ ልዩ ማህበራትን የሚያቅፍ ድርጅት ከሆነ የዚህ አይነቱ ድርጅት የመንግሥት መስሪያ ቤት እንጂ በምን ተአምር ‘አንድ ብሔራዊ ፓርቲ’ ይሆናል? ልጁን በስሙ በመጥራት ፈንታ፡ በመንግሥቱ ቋንቋ ‘አወናባጅ ስያሜ’ ለመስጠት ካልተፈለገ በስተቀር። ይህም መንግሥቱ ሊከተለው የሚፈልገውን የነታንዛንያን አይነት ‘ፓርቲዎች’ ያስታውሰናል።

እነዚህ ‘ፓርቲዎች’ በቢሮ ከበርቴውና በንኡስ ከበርቴው መደቦች አባሎች የተሞሉ ቢሮክራሲያዊ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች እንጂ የወዝአደሩና የቀሩትም ጭቁን መደቦችና የህብረተሰብ ክፍሎች ‘ፓርቲ’ አይደሉም። በተረፈም፡ ኢትዮጵያ ታንዛንያ አይደለችም። በህብረተሰባችን ውስጥ ያሉት የመደብ ትግሎች፡ ካገሪቷ ታሪክ የተነሳ፡ ሃይለኛና የለየላቸው ናቸው። ስለዚህም የራሳቸውን ጎዳና ይጠይቃሉ።

በሌላ በኩል ግን፡ የታሰበው ከተባሉት ሕዝባዊ ድርጅቶች ግለሰቦችን አስመርጦ እነዚህን ‘የፓርቲው አባላት ናችሁ’ ለማለት ከሆነ አሁንም በፍጹም የማያዋጣ መንገድ – የውዥንብር ጎዳና – ተይዞአል ማለት ነው።

1ኛ/ ወደ ‘ግለሰቦች ግንባር’፣ ወደጥቂት ሰዎች ፈላጭቆራጭ አገዛዝ፣ ወደ ቢሮ ከበርቴውና ንኡስ ከበርቴው መደቦች ዲክቴተርሽፕ ሄደን ማለት ነው።

2ኛ/ የፓርቲ አባልነት እንደሹመት የሚሰጥና የሚገፈፍ ማእረግ ሆነ ማለት ነው። አንድ ግለሰብ ባንድ ሕዝባዊ ድርጅት በሙያው በተመረጠ ቁጥር የተባለው ፓርቲ አባል ይሆናል፤ በመረጠውም ድርጅት በተሻረ ቁጥር ደግሞ አባልነቱ ይቀራል። በሌሎች አገሮች ታሪክ – ሕዝባዊ አብዮቶች ያደረጉትንም አንዳንድ አገሮች ጨምሮ- የዚህ አይነቱ የፓርቲ አባልነት ለጉቦ፣ ለግል ጥቅም መጠበቂያ፣ አባልነትን እንደፊውዳላዊ የማዕረግ ስም ከአባት ወደ ልጅ ለመውረሻ መሳሪያ ሆኗል። ሰፊው ሕዝብ እንደዚህ አይነት ‘ፓርቲዎች’ ምንም ያገኘው ጥቅም የለም።

3ኛ/ ከዚሁ ጋር አያይዞ ማንም ሊገመተው እንደሚችልና በማንኛውም አገር ታሪክ ታይቶ እንደማይታወቅ ሁሉ፡ የተለያዩ ጥቅሞችን ለማስከበር የሚቋቋሙ የሙያና ሌሎችም ህዝባዊ ድርጅቶች ‘በአንድ ፓርቲ’፡ ለአንድ መደብ ጥቅምና ርእዮተአለም መጠበቂያና ማስፋፊያ በሆነ እውነተኛ ፖርቲ ውስጥ ‘ሊጠቃለሉ’ አይችሉም። እነዚህ ድርጅቶችና ሌሎችም ፓርቲዎች በአንድ ፓርቲ ሊመሩ ይችላሉ። ይህንን ከዚህ በታች እንመለከታለን። ግን ‘አንድ ፓርቲ’ ይፈጥራሉ ማለት ፍጹም ትርጉም የለውም። ወዝአደር፣ ገበሬ፣ ምሁርና ተማሪ፣ የሃይማኖት መሪ፣ ሸማኔና ሸክላ ሰሪ፣ የባንክ ሠራተኛና ኩሊ ሁሉም በአንድ የመደብ ጥቅምና በአንድ ርእዮተአለም ላይ የተመሰረተው ‘ፓርቲ’ የፈጠሩበት ሁኔታ ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም፤ ወደፊትም የሚሆን ነገር አይደለም።

ሊቀመንበሩ እንግዲህ የዚህ አይነቱ ባህሪው በደንብ ያልታወቀ ድርጅት በአዋጅ ተቋቁሞ “የማስተዳደርን ስልጣን ከመለዩ ለባሹ ሰራዊት እንዲረከብ ይደረጋል” ይላሉ። ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት ስለመንግሥት ስልጣንና ስለ አረካከቡ ያለው አስተሳሰብ፡ በየመግለጫውና በየንግግሩ በአደባባይ የወጣውን ሁሉ፡ አንድ ራሱን የቻለ ያስተሳሰብ ውዥንብር ታሪክ ስለሆነ እዚህ ላይ አንተችበትም። ይልቁንስ የኢትዮጵያ አብዮት የግድ መከተል የሚኖርበትን ጎዳና በመጠቆም ጽሁፋችንን እንደምድም።

[1] ባንዳንድ የከበርቴ ሥርዓቶች ሰፊውን ሕዝብ ለማወናበድ ይመች ዘንድ አንዱ መደብ ሁለት-ሦስት ፓርቲዎችን ይፈጥራል። በመሰረቱ ግን ፓርቲ ያንድ መደብ የጥቅም መጠበቂያ መሳርያ ነው።

 

 

ብዮቱ የሚከተለው ጎዳና፡

ህብረተሰባዊነት መታወጁ፡ ወይንም የመንግሥት ‘መመሪያ’ ሆኖ መውጣቱ ምንም ያህል ሊለውጠው የማይችል ኢትዮጵያ የደረሰችበትና ያለችበት የታሪክ ደረጃ አለ። ይኸውም የብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት የታሪክ ደረጃ ነው።(በነገራችን ላይ፡ ‘የታሪክ ደረጃ’ ሲባል ምን ማለት እንደሆነ እዚህ ላይ ማመልከቱ ይጠቅማል። ሰዎች ፈለጉም አልፈለጉ፡ ከልባቸው ምኞች ፍጹም ነፃ በሆነ መንገድ፡ ህብረተሰቦች የግድ የሚራመዱባቸው የታሪክ ደረጃዎች አሉ። በባሪያ ስልተምርት ላይ በተመሰረተ ህብረተሰብ ሶሻሊስት፡ ወይም ከበርቴ (ቡርጇ) አብዮት ሊደረግ አይችልም ነበር፤ፊውዳላዊ አብዮት መደረግ ነበረበት። ፍጹም ፊውዳላዊ በሆነ ህብረተሰብ እንደዚሁ ሶሻሊስት አብዮት ሊደረግ ወይንም ወደ ኋላ ተቀልብሶ ወደ ባርያ ህብረተሰብ መምጣት አይቻልም ነበር። የከበርቴ አብዮት የግድ መከተል ነበረበት።በዛሬይቱ አለምም ግማሽ- ፊውዳልና ግማሽ- የጅአዙር ቅኝ አገዛዝ ሥርዓት በነገሰባቸው እንደ ኢትዮጵያ ባሉት አገሮች ሶሻሊስት አብዮት ለማድረግ አይቻልም። የዚህ አይነቱ ህብረተሰብ ኢኮኖሚያዊ፡ ፖለቲካዊና ማህበራዊ አቋም ሁሉ ይህንን አይፈቅድም። እዚህ በመጀመሪያ ደረጃ ሊከናወን የሚችለው ብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ነው። ‘የታሪክ ደረጃ’ ሲባል እንግዲህ ይህ ነው።) ይህንን የታሪክ ደረጀ ካልተረዳነውና በምኞች ወይም ባቦሰጡኝ ብቻ ከተራመድን ለህብረተሰባዊነት በር ከፋች እርምጃዎችን በመውሰድ ፈንታ እንዲያውም ለጠቅላላው አብዮት መሰናክል እንሆናለን።

ይሁንናም፡ ይህ አብዮት ለምን ‘ብሔራዊና ዴሞክራሲያዊ’ ተባለ?

አቢዮቱ ብሔራዊ የተባለበት ምክንያት ኢምፔሪያሊዝምን ስለሚቃወም ነው። ኢምፔሪያሊዝምን መቃወም ማለትም የባእድ ከበርቴዎችን ኢኮኖሚያዊ፡ ፖለቲካዊና ባህላዊ ተጽእኖዎች ማጥፋት ብቻ ሳይሆን ከነርሱ ጋር የተያያዘውን ያቀባባይ ከበርቴውንና የቢሮ ከበርቴውን መደብም መደምሰስ ማለት ነው። እነዚህ ካልተደመሰሱ ነፃ ኢኮኖሚያዊ ሥርዓት፣ ነፃ ህብረተሰብ፣ የራሱን እድል በገዛ እጁ ያስገባ ሕዝባዊ ሥርዓት ለመገንባት ፈጽሞ አይቻልም። ይህ አብዮት በዚህ ‘ብሔራዊነቱ’፡ ፀረኢምፔሪያሊስት በመሆኑ፡ የአለም ወዝአደሮች ትግል፡ የአለም ሶሻሊስት እንቅስቃሴ አንድ አካል ነው።

አብዮቱ ዲሞክራሲያዊ የተባለበት ምክንያት ፊውዳሊዝምን ስለሚቃወምና ፊውዳሊዝምንና ኢምፔሪያሊዝምን የሚቃወሙትን የህብረተሰብ መደቦችና ኃይሎች ሁሉ አስተባብሮ በአንድ ግንባር ስር ስለሚያሰልፍ ነው። እነዚህ መደቦችና የህብረተሰብ ክፍሎች ሁለቱን ጠላቶች ለመደምሰስ በሚደረገው ትግል የሚተባበሩ ከመሆናቸውም በላይ ሕዝባዊ ሥርዓት ሲቋቋምም በወዝአደሩ መሪነት ስር በመንግሥት ስልጣን ይሳተፋሉ። ማለትም፣ ይህ ስልጣን የሰፊውን ሕዝብ ዴሞክራሲ ያረጋግጣል።

አገራችንን በሚመለከተው በኩል ዋናው የጊዜው ጥያቄ የዲሞክራሲያዊ መብቶች ጥያቄ ነው። ይህንን ደጋግመን ደጋግመን ማስታወስ አለብን። እነዚህ መብቶች ከተገኙ ሰፊው ሕዝብ በነፃ ይደራጃል፣ ወዝአደሩ የራሱን መደብ ፓርቲ ያገኛል፣ ሌሎችም ጭቁን መደቦችና የህብረተሰብ ክፍሎች እንደየሁኔታቸው ይደራጃሉ። የወዝአደሩ መደብ በፓርቲው አማካይነት ታግሎ የጠቅላላውን ትግል መሪነት ቦታ በመያዝ የጭቁን መደቦችንና የህብረተሰብ ክፍሎችን ሁሉ ግንባር ይፈጥራል። ይህ ግንባር ፊውዳሊዝምንና ኢምፔሪያሊዝምን በሬቮሉሽናዊ ኃይል ደምስሶ ሕዝባዊ ሥርዓትን- የአዲሱን ዲሞክራሲ ሥርዓት- ያቋቁማል፣ ሶሻሊዝምን ለመገንባት ጽኑ መሰረት ይጥላል። ወደድንም ጠላንም፣ ብዙ መሰናክሎችና ጥምዝምዝ መንገዶች፡ አደናጋሪና ለጊዜው መውጫቸው የማይታይ መጠምዘዣዎች ቢኖሩትም የኢትዮጵያ አብዮት ጎዳና ይኸው ነው፤ ከዚህ ሌላ የለም።

ይህ ከሆነ እንግዲህ፡ ወታደራዊው መንግሥት በርግጥ ለሰፊው ሕዝብ ‘እኩልነት፡ ነፃነትና መብት’ የቆመ ከሆነ፣በሃቅ የኢትዮጵያን ሕዝብ ለማገልገል እንጂ የሕዝቡ አብዮት እንቅፋት ከመሆን ለመቆጠብ ከፈለገ፣ በአሁኑ ሰአት ላገሪትዋ ሊያበረክት የሚችለው ታሪካዊ አስተዋጽኦ እንደሚከተለው ይሆናል፡-

1ኛ/ የዚህን አብዮት እውነተኛ ወዳጆችና ጠላቶች በትክክል በመለየት፣ ሰፊው ሕዝብ በተለይም በገጠር የጀመረውን የአድሃሪ መደቦችን ድምሰሳ መደገፍ እንጂ የማይታረቁ ተፃራሪ መደቦችን ለማስታረቅ ከንቱ ሙከራ በማድረግ መሰናክል መሆኑን አሁኑኑ ማቆም አለበት። ገበሬውን በማህበሮቹ አማካይነት በደንብ ማስታጠቅ ያስፈልጋል። በዘማቾች፣ በተራማጅ፣ ያገር አስተዳደርና የመሬት ይዞታ ሠራተኞች፣ በተራማጅ አዝማቾችና፣ በገበሬ ማህበራት በየገጠሩ መሳሪያዎቻቸውን የሚቀሙትንና ተይዘው የሚታሰሩትን አድሃሪዎች መልሶ መፍታትና ማስታጠቁ መቆም አለበት።በቅርቡ በወላሞ አውራጃ እንደተደረገው ሁሉ አንዳንድ አድሃሪ የደርግ አባላት በሀሳብ ከሚስማሟቸው ያስተዳደር ሰዎች ጋር እየሆኑ ፀረሕዝብ የመሬት ከበርቴዎችንና በዝባዦችን በመደገፍ፣ ተራማጅ አስተዳዳሪዎችን በማሰር፣ የገበሬ ማህበራትንና የፍርድ ሸንጎዎችን በመበተንና የሰላማዊ ገበሬዎችን ቤት እየፈተሹ የመሳሪያ ዘረፋ በማድረግ የሚፈጽሙትን ፋሽስታዊ አመጽ ማውገዝ አለበት፣ ማቆም አለበት፣ የታሰሩትን አውራጃ አስተዳዳሪና የመሬት ይዞታ ሠራተኛ መፍታት አለበት። በልዩ ልዩ ስፍራዎች እንዳደረገውና እንደሚያደርገው ተራማጆዎችንና አድሃሪዎችን ባንድ ቁና በመስፈር፣ የፊተኞቹን መጨቆኑን፣ ማጎሳቆልና ማሰሩን ማቆም አለበት። እነዚህን የሕዝብ ወገኖች በማንኛውም ቦታና ጊዜ መደገፍ ያስፈልገዋል። በርግጥ አንዳንድ ስህተቶች ከተደረጉ የተሳሳቱት በምክርና በሂስ እንዲታረሙ ይደረጋል እንጂ የጭቆና እርምጃ ሊወሰድባቸው ፈጽሞ አይገባም። በዚህም አኳያ በየከተማው በየጊዜው በግፍ ተይዘው የታሰሩት ተራማጆች መፈታት አለባቸው። ለወደፊትም በሆነ ባልሆነው ምክንያት ተራማጅ ግለሰቦችን ይዞ ማሰር መቆም አለበት።

2ኛ/ በኢምፔሪያሊዝም ላይ አሁኑኑ እርምጃ መወሰድ አለበት። ከአሜሪካን ኢምፒሪያሊዝም ጋር ጨቋኙ የኃይለለላሴ መንግሥት የተፈራረማቸው ፀረአብዮታዊ ዉሎች መሰረዝ አለባቸው። በየመስሪያ ቤቱና በየወታደሩ ሰፈርም ውስጥ በ‘አማካሪነት’ በ‘አሰልጣኝነት’ የተሰማሩት ሰላዮች አሁኑኑ ካገር እንዲባረሩ ማደረግ ያስፈልጋል። የኢምፔሪስቶች ኤምባሲዎች በኤምባሲ ሠራተኛ ስም ወደ ኢትዮጵያውያ ያስገቧቸውን ሰላዮችና ሳቦተሮች ማስወጣት ያስፈልጋል። ወታደራዊው መንግሥት ለ‘እርዳታ’ና ለመሳሪያ ሲል ከአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም ጋር ያለውን ሽርክና ከቀጠለ ውሎ አድሮ የሕዝብ ጠላት ይሆናል። ከአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ጋር ከተቃቃረ ሰፊው ሕዝብ በሚገባ ባልተደራጀበትና ባልታጠቀበት በአሁኑ ሁኔታ ደርጉን ወይንም የደርጉን ተራማጅ ክንፍ ደምስሶ እልም ያለ ፋሽስታዊ አገዛዝን በኢትዮጵያ ሕዝቦች ላይ ይጭናል። ስለዚህ ወታደራዊው መንግሥት የኢምፔሪያሊዝምን እግር እየላሰ መኖር ካልፈለገ፣ በእርግጥ የህዝቡን ወገን ከመረጠ በኢምፔሪያሊዝም ላይ ቁርጥ ያለ እርምጃ መውሰድ ይኖርበታል፣ ሳይቀደም መቅደም ያስፈልጋል። ይህንንም ማድረግ የሚችለው ሰፊው ሕዝብ በቶሎ የራሱን የትግል ድርጅቶች እንዲያቋቁም በማድረግ ብቻ ነው።

3ኛ/ ወታደራዊው መንግሥት የራሱን የመንግሥት ቢሮክራሲያዊ ፓርቲ ጉዳይ ወደጎን ትቶ ሙሉ ዲሞክራሲያዊ መብቶችን ማወጅ አለበት። በነገራችን ላይ፣ አሁን ሰሞኑን ሊቀመንበሩ ያደረጉትንና ከላይ የተተነተነውን ያንድ ፓርቲ ጉዳይ ንግግር ኢምፔሪያሊስት አለም ማበረታቻ ባለው ድምጽ በማስተጋባት ላይ ነው። የዚህ አይነቱ ቢሮክራሲያዊ የመንግሥት ፓርቲ ለጅአዙር ቅኝ አገዛዝ መሳሪያነት በቀላሉ ለማገልገል እንደሚችል ስለሚያውቁት በርሱም ላይ ቢሆን ተስፋቸውን መጣል ይዘዋል ማለት ነው። ይህ የኢምፔሪያሊስቶች የድጋፍ ድምጽ ብቻ የእቅዱን አድሃሪነት ሊያረጋግጥ ይችላል።

የንግግር፣ የጹሁፍ፣ የመሰብሰብና የመደራጀት መብቶች ያለገደብ መፈቀድ አለባቸው። ይህም ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት በትክክል ከሥራ ላይ እንዲውል ከተፈለገ ወታደራዊው መንግሥት በማያሻማ ቋንቋና በተግባር የሰፊውን ሕዝብ አብዮታዊ ትግል መደገፍ አለበት፣ ፀረሕዝብ ድርጊቶቹን በሙሉ ማቆም አለበት፣ ተራማጅ የሰፊው ሕዝብ ወገኖችን ከአብዮታዊ ተግባራቸው ማደናቀፉ፡ ማሰሩ፣ ማንገላታቱ ቀርቶ መደገፍ ማበረታታት አለበት። ይህንን ካላደረገ ግን ውሎ ይደር እንጂ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ሳይፋረዱት አይቀሩም።

የኢትዮጵያን አብዮት ከእንግዲህ ወደኋላ የሚቀለብሰው ኃይል አይኖርም። ባገራችን ብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ይደረጋል፣ ፊውዳሊዝምና ኢምፔሪያሊዝም ይደመሰሳሉ። ትግሉ ውጣ- ውረድ የበዛበት ቢሆንም ሌሊት አልፎ ቀን መተካቱ እንደማይቀር ሁሉ

የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ያሸንፋል!
እውነተኛ ዲሞክራሲያዊ መብቶች እንታገል!
አጫጭር ዜናዎች፡-
  1. የአለም ባንክ የሚባለው የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም መሳሪያ የሆነው ድርጅት፡ የአሜሪካ ‘ኤይድ’ እና ሌሎችም የምዕራባውያን ባንኮችና የ‘እርዳታ’ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ገጠር እርዳታን ካልሰጠን ብለው ሰሞኑን ይመላለሳሉ። ለምን? የገጠሩን አብዮት ለመቀልበስ፡ የመሬት ንጉስ ከበርቴዎች እንዲፈጠሩና ገጠሩም የኢምፔሪያሊስቶች አሻንጉሊት በሆነ መንግሥት ቁጥጥር ስር እንዲገባ ለማድረግ ነው። ለምሳሌ የአለም ባንክ የእህል ጅምላ ንግድን የመንግሥት ድርጅት እንዲይዘው ለማድረግ የሚያስችል ገንዘብ ለማበደር ራሱ ጠይቋል። ሃሳቡ በተቻለ መጠን ከፍተኛ የመንግሥት እህል ቦርድ ተቋቁሞ ለኢምፔሪያሊዝም ቁጥጥር የሚያመቹ ቢሮክራቶች እንዲያካሂዱትና በዚህም አማካይነት በገበሬ ማህበሮች ላይ ተጽእኖ ለማድረግ ነው። የልማት ድርጅቶች በመንግሥት ስር መሆናቸው የሚደግፍ ቢሆንም የሕዝብ ተሳትፎ ከሌለበትና መንግሥቱ ራሱ ከሕዝብ ቁጥጥር ውጭ ከሆነ ግን አደገኛና የሚወገዝ ድርጊት ነው።
  1. ወታደራዊው መንግሥት ስልጣንን በኦፊሲዋል እጁ ያገባትን መስከረም 2 ቀን ‘የአብዮት በዓል’ ብሎ ለማክበር ብዙ ዝግጅት በማድረግ ላይ ነው፣ ብዙ ገንዘብ በማውጣት ላይ ነው። የሚገርመውና የሚያሳዝነው ግን በዚሁ በዓል ላይ እንዲካፈሉ የታዘዙት ከየገበሬው ማህበራት የሚላኩ አባላት ተፈሪ ሱሪና ጃኖ ጥለት ኩታ ለብሰው ይምጡ መባሉ ነው። የየራሳቸው አኩሪ ባህል ያላቸው ሕዝቦች፡ የሥራ ልብሳቸው ወይም የራሳቸው የወግ ልብስ ቀርቶ የግድ ባለ ጃኖዎች ይሁኑ ማለት የቀድሞው መንግሥት ያደርግ እንደነበረው የልዩ ልዩ ብሄሮችን ባህል ንቆ የሌላውን በላያቸው ላይ ከመጫን ሌላ ምንድነው?
  1. ከጉልተኞችና በጠቅላላው ከአድሃሪዎች ጋር ሕዝቡ ሰፊ የመደብ ትግል በሚያደርግበት በአሁኑ ወቅት የነዶ/እሸቱ ጮሌና የሌሎችም ተራማጆች ያለ ፍርድ በእስር ቤት መበስበስ በያንዳንዱ ተራማጅ አንጎል ውስጥ የሚጉላላት ጥያቄ ነው። አሁንም ደርጉ የመሬትን አዋጅ በትክክል በሥራ ላይ ለመዋልና ሶሻሊዝምን ለማስፋፋት የሚጥሩትን ተራማጆች ማንገላታቱን ቀጥሏል። የወላሞ አውራጃ አስተዳዳሪና የአውራጃው የመሬት ይዞታ ሠራተኛ የደርግ አባሎች አመጽ ታስረዋል። ከሥራ እስኪያጆች ማሰልጠኛ የታሰሩት ሠራተኞች ያለፍርድ በከፊል ከርቸሌ ወርደዋል። ከጭላሎ እርሻ ልማት ድርጅትም እንዲሁ በርከት ያሉ ተራማጆች ታስረው ነበር። ተራማጅ የመሬት ይዞታ ሠራተኞች፣ ተራማጅ አስተዳዳሪዎችና ዘማቾች፣ ወታደራዊዉ መንግሥት ስለማይደግፋቸውና እንዲያውም ስለሚያስፈራራቸው የአድሃሪያንና የፖሊሶች ዒላማ ሆነዋል።
  2.  ከሰኔ 27 እስከ 29 በጎንደር ከተማ የተደረገው የኢት. መምህራን ማህበር ጉባኤ ካሳለፋቸው አብዮታዊ ውሳኔዎች ጋር አያይዞ በክፍለአገሩ የደረሰውን ያስተዳደር በደል በሚገባ ገልጿል፤ በክፍለ አገሩ አስተዳዳሪ አማካይነት አድሃሪያን በሹመቱም በሽፍትነቱም እያሉ በበጌምድር በመመሸግ ላይ መሆናቸውንና አሁኑኑ ጥብቅ እርምጃ ሊወሰድባቸው እንደሚያስፈልግ አሳስቧል።
Scroll to Top