በጅምላ የተገደሉ የመኢሶን ሰማዕታት
መርካቶ የተገደሉ ጓዶች
አዲስ አበባ ከተማ፣ መርካቶ መኖሪያ ቤት ውስጥ ጥናት በማካሄድ ላይ እያሉ መስከረም 17 ቀን፣ 1969 ዓ.ም. በኢሕአፓ የነፍሰ ገዳይ ቡድን በአውቶማቲክ ጠመንጃ በጥይት እሩምታ የተገደሉት ጓዶቻችን በሙሉ ወጣቶች ነበሩ። እነዚህ ወጣቶች ኢሕአፓ ከስም ማጥፋት፣ ከዘለፋ እና ከቡጢ ተሸጋግሮ ወደ ግድያ ማምራቱን ያበሰረበት የመጀመሪያዎቹ ሰለባዎች ነበሩ።
የኢሕአፓ ነፍሰ ገዳዮች የመጀመሪያዎቹ ሰለባ የሆኑት የመኢሶን ወጣቶች የሚከተሉት ናቸው።
1) አቡበከር አብዱልመጂድ
2) ገብረ እግዚአብሄር ተስፋይ
3) ክንፈ አስፋ
ኦርማ ጋራጅ ሰፈር የተፈጸመ ግድያ
የካቲት 11፣ 1969 ዓ.ም. በመሣሪያ የተደራጀ የኢሕአፓ የግድያ ቡድን በውድቅት ሌሊት፣ የገሠሠ ታላቅ ወንድም የመስፍን በዛብህን መኖሪያ ቤት የጓሮ በር ሰብሮ ገብቶ፣ ገሠሠ በላይንና ጌታሁን ታመነን በተኙበት በጥይት እሩምታ ገደላቸው።
ገሠሠ፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሁለተኛ ዓመት የሳይንስ ተማሪ ነበር። ጌታሁን ደግሞ የሽመልስ ሐብቴ ትምህርት ቤት አሥራ አንደኛ ክፍል ተማሪ ነበር።
በዚሁ የኢሕአፓ ግድያ የእነ መስፍን ህጻን ልጅ ሞግዚትና ሴት የቤት ሠራተኛ፣ ሁለቱም በጓሮ በር አጠገብ በተኙበት ክፍል በመጀመሪያ ተገደሉ። መስፍን በዛብህና ሕጻን ሴት ልጁ በጥይት ቆስለው በሕይወት ተረፉ። መስፍን በዛብህ፣ ሰውነቱ ላይ ዐሥራ አንድ ጥይቶች ተርከፍክፈውበት፣ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በቀዶ ጥገና ከብዙ ቀናት ቆይታ በኋላ ታክሞ ወጣ። ዩሁን እንጂ፣ ምንም እንኳን በወቅቱ በሕይወት ቢተርፍም ወደ ቀደመው ሙሉ ጠንነቱ መመለስ አልቻለም። ከነገሠሠ ጋር አብሮአቸው አንድ ክፍል ውስጥ የነበረው አክሊሉ ግደይም በአጋጣሚ በሕይወት ተረፈ።
ለዚህ በበቂ ዝግጅት ኢሕአፓ ላካሄደው ግድያ ስለ ቤቱ ሁኔታና በዕለቱ በውስጡ ስለነበሩት ሰዎች መረጃውን ያቀበለው በዚያን ዕለት አብሮአቸው እቤት ውስጥ አምሽቶ የሄደው ተጠርጣሪ፣ እነገሠሠን ዩኒቨርስቲ ውስጥ በቅርብ የሚያውቅና መኢሶን ውስጥ ሰርጎ የገባ የኢሕአፓ አባል የነበረ ሰው ነው።
ገሠሠ በላይና ጌታሁን ታመነ ሲገደሉ የ21 እና የ20 ዓመት ወጣቶች ነበሩ።
በጌዴኦ አውራጃ የተገደሉ ጓዶች
መኢሶን ከደርግ ጋር የነበረውን ትብብር አቋርጦ ትግሉን በኅቡዕ ሲቀጥል፣ ጓዶቹን ለትግል ካሰማራባቸው አካባቢዎች አንዱ ጌዴኦ አውራጃ ነበር። በጌዴኦ ከተሰማሩት ጓዶች መሀል፣
1) ዘሪሁን ጋቲራ፣
2) የአሥር ዓለቃ ታደለ አበበ፣
3) ዓለምእሸት ተዘራ፣
እነዚህ ጓዶች ነሐሴ 27 ቀን 1969 ዓም በቡሌ ወረዳ ገጠር እየተዘዋወሩ ቅስቀሳ በሚያካሄዱበትና ገበሬዎችን በሚያደራጁበት ወቅት፣ ለአዳር ባረፉበት ገበሬ ቤት ውስጥ እያሉ ከዲላ ከተማ በተላከ የደርግ ጦር ተከበቡ። ይሁን እንጂ፣ የከበባቸው ጦር በወረዳ አስተዳዳሪው አስተባባሪነት ከአካባቢው ገበሬዎች ጋር ተቀላቅሎ የመጣ መሆኑን ሲያስተውሉ “በገበሬ ላይ አንተኩስም” በማለት ትጥቃቸውን ፈትተው ከነበሩበት ቤት በመውጣት በሰላም እጃቸውን ሰጡ። ነገር ግን እጃቸውን በሰላም ቢሰጡም፣ ጦሩ ያለ ፍርድ ሦስቱንም አዚያው ባሉበት በጭካኔ ረሸናቸው።
ሙሎ የተሰዉ ጓዶች
መኢሶን የትግል ስልት ለውጥ አድርጎ በኅቡዕ ለመታገል በተንቀሳቀሰበት ወቅት የድርጅቱን አመራሮች ጨምሮ በአንድነት አሥር ሰዎች የሚገኙበት ቡድን ለአዲስ አበባ ከተማ ቀረብ ያለው ሙሎ ወረዳ ውስጥ ለጊዜው እንዲጠለሉ አደረገ። ይህ ቦታ የተመረጠበት ዋናው ምክንያት የከተማውንና የገጠሩን ትግል ለማስተባበር አስተማማኝ ነው ተብሎ ስለተገመተ ብቻ ሳይሆን፣ በተጨማሪም፣ አስፈላጊ በሆነ ጊዜ ከዚህ ቦታ ተነስቶ ወደ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሊያሸጋግር የሚያስችል የተጠና መንገድም ተዘጋጅቶ ስለነበረ ነው።
ይሁንና፣ ጓዶቹ የተጠለሉበት አድራሻ ደርግ እጅ በመግባቱ፣ ገና ቡድኑ አካባቢውን እያጠና፣ ቀጣይ ተግባሮቹን እየገመገመ፣ እራሱን በማዘጋጀት ላይ እያለ፣ ነሐሴ 29 ቀን ማታ ከደርግ ጥበቃ ክፍል አንድ የመቶ ጦር ወደ ወረዳው ዘልቆ መግባቱ ተሰማ። ለደህንነት ሲባል በሶስት የተራራቁ መንደሮች ተጠልለው የነበሩት አሥሩ የቡድኑ አባላትም፣ ሌሊቱን ሙሉ ለመሰባሰብ ያደረጉዋቸው ጥረቶች ባለመሳካታቸውና በአስገዳጅ ምክንያቶች፣ ነሐሴ 30 ቀን ንጋት ላይ ቡድኑ እኩል በእኩል ተከፍሎ ተለያየ።
እሁድ ነሐሴ 30 ቀን ዶ/ር ከበደ መንገሻ፣ ዳንኤል ታደሰ፣ ምትኩ ተርፋሳ፣ ደንቢ ዲሳሳ እና ደንበል አየለ ያሉበት ንዑስ ቡድን ወንዝ ተሻግሮ ወደ ምዕራብ በማምራት ከአንድ የመኢሶን ደጋፊ ገበሬ ቤት ተጠለለ። ነገር ግን፣ እዚያም ብዙም ሳይቆይ ቡድኑ ከደርግ ጥበቃ ክፍል በመጣው ጦር ተከበበ። ሌሎቹ አምስት ጓዶች ያሉበት ንዑስ ቡድን ለጊዜው ከጦሩ ወጥመድ ውስጥ ሳይገባ አመለጠ።
ጓዶቹ የተጠለሉበት ቤት ባለቤት የነበረው ገበሬ በሕይወት ተርፎ ደርግ ከወደቀ ከሁለት ዓመት በኋላ ጓዶቹ የወደቁበትን ቦታ ለማፈላለግ ወደ አካባቢው ለተጓዙት የሟቾቹ ቤተሰቦች እና ጓዶች እንደተናገረው “መትረየስ የታጠቁ ወታደሮች ቤቱን ሲከቡ፣ ዶክተሩ እና ሚኒስቴሩ፣ ሌሎቹን ሦስት ታጋዮች፣ ‘እናንተ ወጣትና የአመራር አባላትም ያልሆናችሁ ናችሁና እጃችሁን ስጡና ሕይወታችሁን አትርፉ‘ ብለው ትዕዛዝ ሰጧቸው። እነሱ ሁለቱ ጎን ለጎን እንደተቀመጡ ተሰነባብተው በየሽጉጦቻቸው ራሳቸውን ገደሉ። ይህን ጊዜ ሦስቱ ወጣቶች መሣሪያዎቻቸውን ወድረው እየተታኮሱ በመውጣት ከባድ መትረየሶች ታጥቆ ይጠብቃቸው በነበረው ጦር የጥይት ናዳ እየተመቱ ወደቁ።”
ጓዶቹን የገደላቸው ጦር አዛዥ፣ የአምስቱም አስከሬን ወደ ሰኞ ገበያ ተወስዶ እንዲጣልና ለገበያ የሚመጣው ሰው እንዲያያቸው አዘዘ። የእነዚህን ጓዶች ማንነትና ውለታ የሚያውቁ አርሶ አደሮች፣ የአባቢውን ሹሞች ለምነውና አግባብተው አስከሬኖቹን አልብሰው፣ በአንድነት ቀበሯቸው። በመቃብራቸውም ዙሪያ ባሕር ዛፎች ተከሉ።
ከአሥራ ስድስት ዓመታት በኋላ፣ በ1985 ዓ.ም. የሟቾቹ ዘመዶችና ወዳጆች በማፈላለግ ከቦታው ሲደርሱ እነዚያ ዛፎችም አድገው በግፍ ለተገደሉት ጓዶች ጥላ ከለላ ሆነው የቆሙ ይመስሉ ነበር። የእነዚህን ሰማዕታት አጽም ከነበረበት አውጥቶ በአንድነት በዘላቂ መካነ-መቃብር ለማሳረፍ የተደረገው ተደጋጋሚ ጥረት ተጨማሪ 26 ዓመታት አስቆጥሮ በ2011 ዓ.ም. ተሳካ።
በዚህ አሰቃቂ ሽብር እራሳቸውን ያጠፉት ጓዶችና በደርግ ወታደሮች የተረሸኑት የሚከተሉት ናቸው።
1) ከበደ መንገሻ (ዶ/ር)
2) ዳንኤል ታደሰ
3) ምትኩ ተርፋሳ
4) ደምቢ ዲሣሣ
5) ደንበል አየለ
ሐረርጌ የተገደሉ ጓዶች
በ1969 ዓ.ም መጨረሻና በ1970 ዓ.ም በሐረርጌ ክፍለ አገር በርካታ የመኢሶን አባላትና ደጋፊዎች በደርግ፣ በኢሕአፓና በአካባቢው ይዘዋወሩ በነበሩ ጽንፈኛ ኃይሎች ለሞት፣ እስራትና ስቃይ ተዳርገዋል። በተለይም በ1970 አ.ም መጀመሪያ የደርግን እስራትና ግድያ ሸሽተው ወደ ገጠር የሄዱ የመኢሶን ጓዶች በአካባቢው ይዘዋወር በነበረው የኦሮሞ እስላማዊ ነጻነት ግንባር ኃይል ያለ ምንም ርኅራኄ ተረሽነዋል። በዝርዘሩ ላይ እንደሚታየው የሁሉንም ስም ማግኘት አልተቻለም። የአንዳንዶቹንም ሙሉና እውነተኛ ስም ማግኘት ስላልተቻለ የመጀመሪያ ስማቸው፣ አንዳንዴም የድርጀት ወይንም ቅጽል ስማቸው ብቻ ሰፍሯል።
እነዚህ ጓዶች የተገደሉት በምሥራቅ ሐረርጌ ልዩ ስሙ ማያ ቀሎ በተባለ ቦታ ነው።
1) ዘይዳን አህመድ
2) በላይነህ አስናቀ
3) እስክንድር ሶዳኒ
4) በቀለ (የአባቱ ስም ያልታወቀ
5) አድነው (የአባቱ ስም ያልታወቀ)
6) ጁና ትንሹ (ቅጽል ስም)
ጎንደር የተገደሉ ጓዶች
መኢሶን በጎንደር ብዙ ጓዶቹን አጥቷል። እዚህ ስር የተጠቀሰው ዝርዝር የተሟላ አይደለም። ወደፊት መረጃው እንደተገኘ የተሟላ ዝርዝር ለማቅረብ እንሞክራለን። ከ1970 ዓ.ም. ጥቅምት ወር ጀምሮ በጎንደር የተገደሉትን የመኢሶን ጓዶች በተመለከተ ከቁጥራቸው መብዛት በተጨማሪ ኅሊናችን ውስጥ ተቀርጾ የቀረው የአገዳደላቸው ሁኔታ ነው።
ከእነዚህ ውስጥ በክፍለ አገሩ አስተዳዳሪ እና የደርግ አባል በሻለቃ መላኩ ተፈራ ትዕዛዝ ደማቸው እየተቀዳ የተገደሉት ጓዶቻችንን እናስታውሳለን። በሌላኛው የደርግ አባል በገብረሕይወት ትዕዛዝ እጅ እግራቸው ታስሮ ከነሕይወታቸው ከሊማሊሞ ገደል እየተወረወሩ የተገደሉት ምንጊዜም አይረሱም። ኢዲዩ የተባለው ድርጅት ሁመራን ሲቆጣጠር ሕዝብ በተሰበሰበበት ለመቀጣጫ በሚል ጉድጓድ ቆፍሮ ከነሕይወታቸው የተቀበሩት ጓዶቻችን ምን ጊዜም ከኅሊናችን አይጠፉም።
ጎንደር ከተሰዉት የመኢሶን አባላትና ደጋፊዎች ጥቂቶቹ፣
1) ፋንቱ አበራ
2) ዳኘ አበራ
3) መንግሥቱ ይመኑ
4) ኃይሉ ብርሃኑ
5) ሰይድ አበራ
6) አየለ ቁሜ
7) አግዳጁ ገብሩ
8) ማሬ በላይ
9) ደረጀ መኮንን
10) ደጀኔ መርዕድ
11) እምሩ ኃይለ ሥላሴ
12) ደጀኔ ካሳ
13) ሸዋዬ በዛብህ
14) መለሰ መልካሙ
15) አማረ መኮንን
16) መስፍን ብሩ (ሻለቃ)
17) አሰፋ መኮንን፣
18) ብርሃኑ (ለጊዜው የአባት ስም አልተገኘም)
19) በየነ (ለጊዜው የአባት ስም አልተገኘም)
በአምቦ ዙሪያ ጥቁር እንጭኒ የተገደሉ ጓዶች
መኢሶን በነሐሴ ወር፣ 1969 ዓም ከደርግ ጋር የነበረውን ግንኙነት አቋርጦ ኅቡዕ በገባበት ወቅት ከደረሱበት ከፍተኛ ጉዳቶቸ አንዱ በአምቦ ዙሪያ ጥቁር እንጭኒ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የደረሰበት ጥቃት ነው። ደርግ ይህንን ጥቃት ሊፈጽም የቻለው የጅባትና ሜጫ አውራጃ የሕዝብ ድርጅት ጉዳይ ጸ/ቤት ካድሬ የነበሩ ሁለት ግለሰቦች በፈጸሙት ክሕደት ነው።
እነዚህ ሁለት ከሐዲዎች በድርጅቱ በተሰጣቸው የአገናኝነት ኃላፊነት ምክንያት ስለ እነ ዶር ተረፈ እንቅስቃሴ የሚያውቁትን ሁሉ ለደርግ ጽ/ቤት አሳልፈው በመስጠታቸው ከአዲስ አበባ በ1970 ዓ.ም. ታሕሳስ ወር አንድ ልዩ ኃይል ወደ ቦታው ተላከ። በከሐዲዎቹ መሪነትም እነ ዶ/ር ተረፈ ያሉበትን ቤት ያለ ምንም ችግር ለመክበብ ቻለ። ጓዶቹ በሰላም እጃቸውን ከሰጡ በኋላ የያዛቸው ጦር ከአዲስ አበባ የመጣባቸውን ተሽከርካሪዎች ወዳቆመበት በሚወስደው መንገድ በእግር ጥቂት እንደተጓዙ አሥሩንም ጓዶች አንድ ገደል አፋፍ ላይ አቁመው ረሸኗቸው።
በዚህ ጥቃት የተሰውት አሥር ጓዶች የሚከተሉት ናቸው፣
1) ተረፈ ወልደ ጻድቅ (ዶ/ር)
2) አጥናፍ-ዓለም ይማም
3) ከበደ ድሪባ
4) ኢዮብ ታደሰ
5) ለማ ፊዳ
6) ሺመልስ ኦላና
7) መርዕድ ከበደ
8) አሰፋ ነመራ
9) ዲማ ጉዲና
10) ኩመላ ካሮርሳ
ከኢሉባቡር ተወስደው የተገደሉ ጓዶች
ብዙ ግድያ በተፈጸመባቸው አስከፊ የአብዮት ዓመታት የኢሉባቡር ክፍለ አገር በአንጻራዊ ሁኔታ ለተወሰነ ጊዜ ሰላማዊ ሁኖ ቆይቶ ነበር ማለት ይቻላል። ነገር ግን፣ በ1970 ዓ.ም. መጀመሪያ ላይ በሚያሳዝን ሁኔታ ይህ የሰላማዊ ሂደት ታሪክ ጥቁር ቀለም ተቀባ። መኢሶን የትግል ስልት ለውጥ ከአደረገ በኋላ፣ በህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተወዳጅነት የነበረው፣ የመኢሶን መሥራች አባል እና የክፍለ አገሩ የሕዝብ ድርጅት ጉዳይ ጊዜያዊ ጽ/ቤት ኃላፊ የነበረው ዶ/ር ከድር መሐመድ ታሰረ። ከእርሱም ጋር አብረው በርካታ የመኢሶን ጓዶች ታሰሩ።
በ1970 ዓ.ም. ታኅሣሥ ወር፣ ዶ/ር ከድርንና ሌሎች ሦስት ጓዶችን ከእስር ቤት አውጥተው አዲስ አበባ እንደሚሄዱ አስመስለው መኪና ላይ ጫኗቸው። ነገር ግን አንዳቸውም አዲስ አበባ አልደረሱም፣ የጊቤ በረኻን እንደተሻገሩ፣ ከመኪና አውርደው ሁሉንም ያለምንም ፍርድ ረሸኗቸው።
በጊቤ በረሃ የተረሸኑት ጓዶች፤
1) ዶ/ር ከድር መሐመድ
2) ከበደ ቦረና
3) ሰንበታ ዋቅጅራ
4) ገመቹ ለሙ
የካቲት 1970 ዓ.ም. ከ4ኛ ክፍለ ጦር እስር ቤት ተወስደው የተገደሉ ጓዶች
በ1970 ዓ.ም. በታኅሣሥና ጥር ወራት በተለያዩ ቀናት ሦስት የመኢሶን አባሎች ተይዘው ደርግ ጽ/ቤት ውስጥ ያለው እስር ቤት ውስጥ ብዙ ቀናት ሲንገላቱና ሲሰቃዩ ከረሙ። ከዚያም 4ኛ ክፍለ ጦር ውስጥ ወደሚገኘው እስር ቤት ተላኩ። ለጥቂት ሳምንታት በዚያ እስር ቤት ከታሰሩ በኋላ አንድ ቀን በድንገት አድራሻው ወደ አልታወቀ ስፍራ ተወሰዱ።
በኋላ እንደተረጋገጠው፣ ሦስቱም ጓዶች ካለ ምንም ፍርድ የካቲት 1970 ዓ.ም. በደርግ ተገደሉ። ያለፈርድ ከእስር ቤት ተወሰደው የተገድሉት ወጣቶች የሚከተሉት ናቸው።
1) አስፋው ሺፈራው
2) ዮሐንስ መስፍን
3) ጀማል አባስ
ሐምሌ 1971 ዓ.ም. ከ4ኛ ክፍለ ጦር እና ከከርቸሌ እስር ቤቶች ተወስደው የተገደሉ ጓዶች
ደርግ ያለምንም ፍርድ ሁለት ዓመት ካሰራቸው በኋላ፣ ሐምሌ 1971 ዓ.ም. አምስት የመኢሶን ጓዶችን 4ኛ ክፍለ ጦር ውስጥ ከነበረው እስር ቤትና ከዋናው ወህኒ ቤት (ከርቸሌ) ወደ አልታወቀ ስፍራ ወሰዳቸው። ከዚያም ሁሉንም አሰቃቂ በሆነ መንገድ ገደላቸው።
ከደርግ መንግሥት ውድቀት በኋላ በዘመዶቻቸውና ወዳጆቻቸው ብርቱ ጥረት አጽማቸው ሊገኝ የቻለው በተራ ቁጥር 4 እና 5 የተዘረዘሩት ዶ/ር ንግሥት አዳነና ቆንጂት ከበደ ብቻ ናቸው።
ከእስር ተወስደው በደርግ የተገደሉት ጓዶች የሚከተሉት ናቸው።
1) ኃይሌ ፊዳ
2) ደስታ ታደሰ
3) ኃይሉ ገርባባ
4) ንግሥት አዳነ(ዶ/ር)
5) ቆንጂት ከበደ
መስከረም 1972 ዓ.ም. ነቀምቴ ወለጋ ከጃቶ እስር ቤት ተወስደው የተገደሉ ጓዶች
ከ1969 ነሐሴ ወር ጀምሮ በወለጋ አውራጃዎች ውስጥ የነበሩ የመኢሶን አባላትና ደጋፊዎች በሰፊው መታሰር ጀመሩ። ታስረው አዲስ አበባ ከተላኩት ሌላ፣ በሕዝብ ድርጅት ጊዜያዊ ጽ/ቤት፣ በእርሻ ሚኒስቴር፣ በመሬት ይዞታና በተለያዩ ደረጃዎች በአስተዳደር መሥሪያ ቤቶች ያገለግሉ የነበሩ በርካታ ጓዶች ወለጋ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ እስር ቤቶች ታጉረው ከፍተኛ እንግልት ይደርስባቸው ነበር።
በተለይም ነቀምቴ በሚገኘው አስከፊው የጃቶ እስር ቤት፣ እስረኞች በተለያዩ ምክንያቶች ያለምንም ፍርድ ይገደሉ ነበር። መስከረም 3፣ 1972 ዓ.ም. ከዚህ በታች ስማቸው የተዘረዘሩት ሦስት የመኢሶን አባል የሆኑ እስረኞች ጠዋት ሲነጋ ከሌሎች እስረኞች ተነጥለው ለብቻቸው በድብቅ እንዲቀመጡ ከተደረገ በኋላ ምሽት ላይ በግፍ ተረሸኑ። ከዚያም እዚያው ወህኒ ቤቱ ግቢ ተቀበሩ። እነዚህ፣ የለምንም ፍርድ፣ በድብቅ የተረሸኑት ጓዶች የሚከተሉት ናቸው።
1) እምሩ ኢብሳ
2) ብሩ ወርቁ
3) ፋሪስ ሂርጳ