የሰፊው ሕዝብ ድምፅ
ቁጥር 40፣ ግንቦት 11፣ 1968
የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ
መኢሶን በዚህ የሰፊው ሕዝብ ድምፅ እትሙ፣ በቅርቡ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት ያወጣው ብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራም፣ ከዚህ በፊት ከወጡት እንደ “ኢትዮጵያ ትቅደም” እና “የኢትዮጵያ ህብረተሰባዊነት” አይነት የመንግሥት መመሪያዎች በጥራቱም በይዘቱም የተሻለ እንደሆነ ይገልጻል። እንደዚህ አይነቱ መለስተኛ የፖለቲካ ፕሮግራም፣ በአገሪቱ እድገት ደረጃ ወደ ሶሻሊዝም በዝላይ በቀጥታ ለመሻገር እንደማይቻል የተገነዘበ እና በአንጻሩ፣ ጥርጊያ መንገድና ድልድይ ሆኖ የሚያገለግል እንደሆነ የተገነዘበ ፕሮግራም መሆኑን በዝርዝር ያብራራል።ሆኖም ግን፣ የደርጉ መለስተኛ ፕሮግራም በመርህ (ፕሪንሲፕል) ደረጃ የብሄረሰቦችን “የራስን በራስ የመወሰን እስከ መገንጠል መብትን” ባለማካተቱ ውሱንነት እንዳለው ያስገነዝባል።
በቅርቡ፣ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት አንድ የብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ኘሮግራም አውጥቷል። ይህ ኘሮግራም፣ ደርጉ እስካሁን እንደመንግስት መመሪያ ካወጣቸው መግለጫዎች ሁሉ፣ (“የኢዮጵያ ትቅደም” መመሪያ ሆነ “የኢትዮጵያ ሕብረተሰባዊነት” መመሪያ) በጣም የላቀ ነው። ያሁኑ በሳይንስና በአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ላይ የተመረኰዘ ነው። ዲሞክራሲያዊ አብዮት ባልተደረገባት አገር ሶሺያሊዝምን እንገነባለን የሚለውን ከተጨባጭ ሁኔታ የራቀ ሙከራ ወደ ጎን ትቶ፣ ለእውነተኛ ሶሺያሊዝም መገንቢያ ጥርጊያ መንገድ ሊከፍትና ወደዚሁ መሸጋገሪያ የሚሆን ድልድይ ሊገነባ የሚችል ኘሮግራም ነው። አብዮታዊውን ትግል ከማንኛውም ቅልበሳ ለማዳን የሚያስችለውን የሰፊውን ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ መብቶች ያለምንም ገደብ የማክበርን አስፈላጊነት የሚያውቅ ነው። ብሄራዊውን ዲሞክራሲያና አብዮት በጠነከረ መሰረት ላይ ለመጣል፣ ለማሳካትና ለዚህም ዋስትና ለመስጠት የሚያበቃውን የወዛደሩን ፖርቲ መሪነት፣ በዚሁ ፖርቲ የሚመራዉን ብሄራዊ ግንባር አስፈላኒነት፣ የሰፊውን ሕዝብ መታጠቅ አስቸኳይነትና አስፈላጊነት የሚቀበል ኘሮግራም ነው። ከነዚህ ሁሉ አንፃር ሲታይ የኘሮግራሙ ይዘት አብዮታዊና በማንኛውም ተራማጅ የሚደገፍ ነው።
ከኘሮግራሙ ይዘት እንደ አንድ ጉድለት ሊጠቀስ የሚችለው፣ ከመርህ (ከኘሪንስኘል) አንፃር ሲታይ ስለብሄረሰቦች የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት የሚያወራው ነጥብ ነው። ይህ ነጥብ፣ በኘሪንሲኘል ደረጃ፣ የብሄረሰቦች የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት አካል የሆኑትን ምርጫዎች (ለምሳሌ የመገንጠልን መብት) አይጨምርም። ይህ በመሰረቱና በአቋም ደረጃ በብሄረሰቦች መብት ላይ ገደብ እንደማበጀት ሊቆጠር ይችላል። ፍጹም ዲሞክራሲያዊ እንዲሆንና ጭቁን ብሄረሰቦች በሙሉ እምነትና ፈቃደኛነት ለጭቁኖች አንድነት ለመቀስቀስና ለመጋበዝ መብታቸውን ያለገደብ ማወቅ ያስፈልጋል።
ይህም ሆኖ ግን፣ በዚሁ የኘሮግራሙ ጉድለት ላይ እንኳ ሁለት ነገሮች ማየት ያስፈልጋል። አንደኛ ነገር ደርጉ ራሱ ቀደም ብሎ ይታይበት ከነበረው ብሄረኛነት የጭቁን ብሄረሰቦችን የእኩልነት መብት ወደማወቅ መምጣቱ አንድ እርምጃ ወደፊት መራመዱን ያሳያል። ሁለተኛ ነገር፣ የብሄረሰቦች መብት ከአቋም አንፃር ሲታይ በኘሮግራሙ ላይ ተሟልቶ ባይቀርብም፣ በአገራችን፡ ጭቁን ብሄረሰቦች ጥያቄ በሪጅናል አውቶኖሚ ሊፈታ አይችልም ማለት አይደለም። በኢትዮጵያ ያሉ ብሄረሰቦች በእኩልት ላይ በተመሰረተ አንድነት በሪጅናል አውቶኖሚ መልክ አንድ ላይ የማይኖሩበት ምክንያት የለም። ይኸ ግን ሙሉ መብታቸውን በማወቅ በሚደረግ ሰፊ ቅስቀሳና ኘሮፖጋንዳ የጭቁን ብሄረሰቦች የራሳቸው ምርጫ ሆኖ ሊመጣ ይገባል።
እንግዲህ፣ ከዚህ ከመላ የኘሮግራሙ ይዘት ጋር ሲተያይ መጠነኛ ጉድለት በስተቀር፣ የደርጉ መለስተኛ ኘሮግራም አብዮታዊ ነው። ሥራ ላይ ከዋለ የዛሬይቱን ኢትዮጵያ ቅራኔዎች ሊፈታ የሚችል ነው። እንዴት ሥራ ላይ ይውላል የሚለውን ጥያቄ ከታች እንመለስበታለን። አሁን የዚህ ኘሮግራም መታወጅ በዛሬው ተጨባጭ ሁኔታ የሚፈጥረውን ምቹና አደገኛ ሁኔታዎች ወደ ማየቱ እንለፍ።
የደርጉ መለስተኛ ኘሮግራምና የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጠላቶች
ኢምፔሪያሊዝም፣ በተለይም አማን አንዶም ከተገደለ ወዲህ፣ በደርጉ ላይ ሙሉ እምነት አጥቶ ነበር። አንዳንድ የደርጉ ተራማጅ ድርጊቶች አስደንግጠውት ነበር። ደርጉ አገሪቷን አብዮታዊ ማእበል ውስጥ የሚከቱ እንደመሬት ላራሹ ዓይነት አዋጆች እያወጣ የአገራችን አብዮት በተፋጠነ መንገድ ከቀጠለ፣ ኢምፔሪያሊዝም ያለው የበላይነት ወደ ማክተሙ እንደሚሄድ ገምቶ ነበር። ይኸ ሁሉ ሆኖ ግን ኢምፔሪያሊስቶች ደርጉን ሙሉ በሙሉ ወግድ ለማለት አልቃጡም። ከደርጉ ጋር ያላቸውን ግንኙነት አላቋረጡም። በደርጉ ላይ ለሚያምፁ ኃይሎች ምስጢራዊ እርዳታ በመስጠት ብቻ ተቆጥበው ነበር። ባጭሩ ኢምፔሪያሊስቶች ከኃይለሥላሴ መንግስት መውደቅ ወዲህ በአገራችን የተጠቀሙት ታክቲክ ባንድ በኩል ከደርጉ ጋር ያላቸውን ግንኙነት አለማቋረጥ፣ በሌላ በኩል በደርጉ ላይ የሚያሴሩ ፀረሕዝብ ኃይሎችንም መርዳት ነበር።
የደርጉ መለስተኛ ኘሮግራም ይዘት ሙሉ በሙሉ ፀረኢምፔሪያሊስት ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን ኘሮግራሙን የተደገፉ እርምጃዎች ከተከተሉ፡ በአገራችን ለሚደረገው ፀረኢምፔሪያሊስት ትግል የሚያደራጅና የሚያዘጋጅ ነው። ይህ በመሆኑ፣ ኢምፔሪያሊስቶች ይህ ኘሮግራም በሥራ ላይ እንዳይውሉና የነርሱ እድሜ እንዲራዘም ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርጉ ጥርጥር የለውም። ደርጉ የዚህን ኘሮግራም ሥራ ላይ መዋል የሚያግዙ እርምጃዎች መውሰድ ከቀጠለ፣ ኢምፔሪያሊስቶች ደርጉን ተክቶ የሚቋቋም የነርሱ አሻንጉሊት መንግስት ለማምጣት፣ ለፀረሕዝብ ኃይሎች የሚሰጡትን እርዳታ እንዲጨምሩና የብዙ አገር መፈንቅለ መንግስት ስራዎችን የመራው ሲአይኤ ለዚሁ ግብ ጥረቱን እንደሚያፋፍም ግልጽ ነው። በሌላ አነጋገር፣ የደርጉ መለስተኛ ኘሮግራም ፀረኢምፔሪያሊስት ይዘት በሥራ ላይ መዋል ሲጀምር፣ ኢምፔሪያሊስቶች “ደርጉንም እንየው” ከሚለው አቋማቸው ወደ ፍጹም ፀረደርግ አቋም እንደሚዞሩ መረዳት ያስፈልጋል።
የኢትዮጵያ ፊውዳሊስቶች ከደርጉ ጋር ከተቆራረጡ ቆይተዋል። መደባቸው ከሥልጣን ሲወርድ፣ ቀንደኛ መሪዎቻቸው ሲገደሉ፣ በመጨረሻም የብዝበዛቸው መሠረት የነበረው መሬት ሲወሰድባቸው በፀረአብዮትና በፀረደርግ ትግል ላይ ተሰማርተዋል። ጫካ ገብተው ያልተሳኩ የትጥቅ ትግሎች አካሄደዋል። አሁንም ያልተሸነፉ ፊውዳሊስቶች ከነትጥቃቸው የሚገኙባቸው ቦታዎች አሉ። በኢምፔሪያሊዝምና በአካባቢያችን አድሃሪዎች እየተረዱ ለፀረአብዮት ትግላቸው ድርጅታዊና ትጥቃዊ ዝግጅቶች እያደርጉም ነው።
የደርጉ መለስተኛ ኘሮግራም ሙሉ ለሙሉ ፀረፊውዳል ከመሆኑም በላይ ተግባራዊ ድጋፍ ከተከተለው የኢትዮጵያን ሰፊ ሕዝብ ፀረፊውዳል ትግል መስመር የሚያስይዝና ጥንካሬም የሚያስገኝለት ነው። የፀረ ፊውዳሉ ትግል መስመር መያዝና ጥንካሬ ማግኘት ደግሞ የፊውዳሎችን በማያዳግም ሁኔታ መደምሰሰ ያስከትላል። ስለዚህም፣ ፊውዳሎች ይህ ኘሮግራም ሥራ ላይ ውሎ ከታሪክ ገጽ መፋቃቸውን ለማስቀረት የጀመሩትን ፀረደርግና ፀረአብዮት ትግል ከመቸውም ይበልጥ እንደሚገፉበት ግልጽ ሊሆን ይገባል።
ከደርጉ መለስተኛ ኘሮግራም ይዘት ሌላኛው ገጽ ፀረቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝም መሆኑ ነው። የቢሮ ከበርቴው ከኢትዮጵያ ሕዝቦች ዋነኛ ጠላቶች አንደኛው ነው። ነገር ግን ከተቀሩት ሁለት ጠላቶች (ፊውዳሎችና ኢምፔያሊስቶች) ለየት ያለ ቦታ አለው። መጀመሪያ ነገር፣ ይህ መደብ እንደፊውዳሉ መደብ ከፖለቲካ ሥልጣን አልተወገደም። ደርጉ ወደደ ጠላ ሥልጣን አጋርቶታል። የደርጉ የበላይነት እርሱም ላይ ይኑር እንጂ የቢሮ ከበርቴው ዛሬም በብዙ አንጻር በሰፊው ሕዝብ ላይ የበላይነት አለው። ይህ መደብ ሥልጣን እስካለው ድረስ ደግሞ በግልጽ እንደአብዮት ጠላት የሚያስቀምጠውንና የርሱኑ መደምሰሻ የሚያዘጋጀውን መለስተኛ ኘሮግራም መቃወሙ የማይቀር ነው። የቢሮ ከበርቴው ተቃውሞ ግን እንደፊውዳሉና እንደኢምፔሪያሊስቶቹ ተቃውሞ ሁል ጊዜ ቀጥተኛ ሳይሆን የረቀቀ ይሆናል። የመሬቱን አዋጅ ሥራ ላይ ለማዋል በሚደረገው ጥረት ለማየት እንእንደተቻለው ሁሉ፣ የቢሮ ከበርቴው የተቃውሞ መንገድ በሥልጣኑ ተጠቅሞ ልዩ ልዩ አሻጥሮችን እየፈጠረ የዚህን መለስተኛ ኘሮግራም ሥራ ላይ መዋል ማደናቀፍ ይሆናል።
በሌላ አንፃር ደግሞ፣ የቢሮ ከበርቴው ኢምፔሪያሊዝም ኰትኩቶ ያሳደገው እንደመሆኑ ከዚህ ደመኛ ጠላታችን ጋር መልካም ወዳጅነትና ግንኙነት አለው። ከፊውዳሉ መደብ የበለጠ ወደኢምፔሪያሊዝም ይጠጋል። ኢምፔሪያሊስቶችም ከፊውዳሉ መደብ የበለጠ “የሰለጠነውን” ቢሮ ከበርቴ አሽከርነት ይፈልጋሉ። በብዙ አገሮች ለኢምፔሪያሊዝም ያደሩ መንግስታትን የሚመራው ይኸው የቢሮ ከበርቴ ነው። ዛሬም በአገራችን ኢምፔሪያሊስቶች ሥልጣን ሊያስለቅቁለት የሚሹት ለዚሁ አገልጋያቸው ነው። የፊውዳሉ መደብ ሳይቀር ለ“ዳግማይ ትንሳዔው” ዓይኑን የሚጥለው እዚሁ ቢሮከበርቴ ላይ ነው። ስለዚህም፣ የቢሮከበርቴው በሥልጣኑ ተጠቅሞ ከሚሰራው አሻጥር ሌላ፣ በሲአይኤ እርዳታና በተቀሩትም ፀረሕዝብ ኃይሎች ተባባሪነት ደርግን አስወግዶ ሥልጣን ሙሉ በሙሉ እጁ ውስጥ ለማስገባት ከፍተኛ ጥረት ያደርጋል። የደርጉ መለስተኛ ኘሮግራም ሥራ ላይ ከዋለ እንዲያጠፋው ስለሚያውቅም፣ በሥልጣኑ ተጠቅሞ በሚሰራው አሻጥር ለዘለቄታው ይህን ኘሮግራም ለማደናቀፍ እንደማይችል ስለሚያውቅም በተቻለ ፍቅነት ፀረ አብዮትና ፀረ ደርግ ሴራው ድል እንዲያመጣለት ይዘጋጃል።
ባጠቃላይ፣ የደርጉ መለስተኛ ኘሮግራም ፀረፊውዳል፣ ፀረኢምፔሪያሊስትና ፀረቢሮክራሲያዊ ካፒታሊስት በመሆኑ፣ ፊውዳሎች፣ ኢምፔሪያሊስቶችና የቢሮከበርቴዎች ሥራ ላይ መዋሉን ይፃረራሉ። በመፃረርም አይመለሱም፣ ሊቀለብሱት ይታገላሉ። ይህም ማለት የደርጉ መለስተኛ ኘሮግራም መውጣት የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጠላቶች አብዮታችንን ለመቀልበስ የሚያካሄዱትን ትግል እንዲያፋፍሙ፣ ድርጅታቸውንና ትጥቃቸውን በፍጥነት እንዲያሳድጉ ያደርጋቸዋል። የዚህ መለስተኛ ኘሮግራም መታወጅ በአብዩቱና በፀረ አብዮት ኃይሎች መካከል ያለውን ትግል ወደ ከፍተኛ ደረጃ ያደርሰናል። ባጭሩ አዲስ የትግል ምእራፍ መከፈቱን የማብሰሩን ያህል የፀረአብዮት አደጋ እንደሚፋፋምም ያመላክታል።
መለስተኛ ኘሮግራሙና ደርግ
ወታደራዊው ደርግ እስካሁን በርከት ያሉ ተራማጅ መመሪያዎችን አውጥቷል። ይህኛው ለየት የሚልበት ነገር ቢኖር፣ ከላይ እንዳልነው ሁሉ፣ ከዚህ በፊት ከወጡት የመንግስት መመሪያዎች ሁሉ፣ (“ኢትዮጵያ ትቅደም” ሆነ የ“ኢትዮጵያ ሶሻሊዝም”) ሳይንሳዊና ከኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ የሚነሳ መሆኑ ነው። ደርጉ እስካሁን የተጓዘውን መንገድ ስንመለከት፣ አንዱን ተራማጅ እርምጃ ሌላ አድሃሪ እርምጃ ይከተላል። እራሱ ያወጣቸውን ተራማጅ አዋጆች ሥራ ላይ መዋል ማደናቀፍ የጀመረበት ወላዋይነትም አሳይቷል። አንዳንድ አባሎቹ በየጠቅላይ ግዛቱ ሲዞሩ የመሬት ላራሹ አዋጅ ማብራሪያ በሚል ሰበብ አዋጁን ለሚቀለብሱ ኃይሎች የጠቀሙ መመሪያዎች ይሰጡ እንደነበር የአደባባይ ሚስጥር ነው።
ደርጉ በዚህ መለስተኛ ኘሮግራም ሥራ ላይ መዋልም ጉዳይ ያለፈውን ወላዋይነቱን ይቀጥልበት አይቀጥልበት ወደፊት የሚታይ ነገር ነው። የደርጉ አንዳንድ አባሎች ኘሮግራሙን ዛሬ ካለው አብዮታዊ መንፈስ ውጭ ትርጉም እየሰጡ ፀረአብዮትን የሚያግዙ መመሪያዎች ያስተላለፉ አያስተላላፉ ወደፊት የሚታይ ነገር ነው።
በማይቀረው የቢሮክራሲው አሻጥሮች ምክንያት ሰፊው ሕዝብና በቢሮክራሲው መሃል በሚነሳው ግጭት ደርጉ ከማን ጐን እንደሚሰለፍ ወደፊት የሚታይ ነገር ነው። ካሁኑ መናገር የሚቻለው፣ ደርጉ በታሪክና በኢትዮጵያ ሕዝቦች ትግል ውስጥ የማኖረውን ቦታ የሚወስነው ይህን መለስተኛ ኘሮግራም ከሥራ ላይ ለማዋል በሚደረገው ትግል የሚያሳየው ወላዋይነት ወይም ቆራጥነት መሆኑን ነው። ከላይ እንዳልነው የዚህ ኘሮግራም መውጣት የጠላት ሰፈር የሚካሄደውን ትግል እንዲያፋፍም ያደርገዋል። ዛሬ ጠላቶቻችን ከሰፊው ሕዝብ የበለጠ ድርጅታዊና ትጥቃዊ ጥንካሬ አላቸው። ይህን መለስተኛ ኘሮግራም በአስቸኳይ በተግባር ለመተርጐም ከተሞከረ፣ በአገራችን ዛሬ ያንሰራራው የፀረአብዮት አደጋ እየቀነሰ፣ ወደዘላቂው ድል እየቀረብን እንሄዳለን። ይህን ኘሮግራም ከሥራ ላይ ለማዋል በሚደረገው ትግል ደርጉ ከወላወለ፣ ለፀረአብዮት የተመቸ ሁኔታ ይፈጥራል፣ የአብዮታዊ ትግሉም መቀልበስ ሊከተል ይችላል። ደርጉ [የማይነበብ – የአዘጋጆች እርማት]
መለስተኛ ኘሮግራሙና የኢትዮጵያ ሕዝቦች ትግል
ከሁለት ዓመታት በላይ ሳያቋርጥ የተካሄደው የኢትዮጵያ ሕዝቦች ትግል ግብታዊ (ስፖንቴንየስ) ነበር። የትግሉ ግብ ምን እንደሆነ ሳይንስ ተመርኩዞ ስር የሰደደ ቅስቀሳ አልተደረገም። ይህ የደርጉ መለስተኛ ኘሮግራም፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ዛሬ ለሚያነሷቸው የትግል ጥያቄዎች መፍትሄ ሊሰጥ የሚችለውን ብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት እንደግብ አስቀምጧል። የዛሬው ትግል ማምራት ያለበት ይህንኑ አብዮት ከፍፃሜ ለማድረስ መሆን እንዳለበት ገልጿል። ይህም በቀላሉ የሚታይ ነገር ሳይሆን ለሕዝቡ ትግል አዲስ ምእራፍ መከፈቱን የሚያበስር ነው። ይህን ኘሮግራም በመመርኮዝ ሰፊው ሕዝብ ስለአብዩቱ ግብና ምንነት እንዲያውቅ ከተደረገ፣ ሰፊው ሕዝብ ብሄራዊ ዲሞክራሲያዊውን አብዮት ለማካሄድና ከግብ ለማድረስ የሚያስፈልገውን ንቃት አገኘ ማለት ነው። በቆራጥነትና በማስዋዕትነት የሚካሄደው ግብታዊ (ስፖንቴን) እንቅስቃሴ ግቡንና ዓላማውን ጠንቅቆ ወደአወቀ፣ ወደነቃ አብዮታዊ ትግል ተቀየረ ማለት ነው፡
ደርጉ ከዚህ ቀደም በብዙ ጥያቄዎች ላይ እንዳደረገው ሁሉ በመደራጀት ጥያቄም ላይ በየጊዜው የተለያዩ አቋሞች ነበሩት። ለምሳሌ፣ ፖርቲዎችና የፖለቲካ ድርጅቶች ሳይኖሩ አንድ ግንባር ይቋቋም ያለበት ጊዜ ነበር። በዚህ መለስተኛ ኘሮግራም ውስጥ ግን በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ሊሆን የሚችለውን የብዙ ፖለቲካ ድርጅቶች መቋቋም አስፈላጊነት ተቀብሏል። የወዛደሩን ፖርቲ አስፈላጊነትና አጣዳፊነት ገልጿል። የሌሎች የአብዩቱ ደጋፊዎችንም በየፈርጁ ተደራጅተው ለአንድ ዓላማ በወዛደሩ ፖርቲ መሪነት በአንድ ግንባር ስር መሰብሰብ አስፈላጊነት ጠቅሷል። ይህም በቀላሉ የሚታይ ነገር አይደለም።
እስካሁን የተካሄደው ሕዝባዊ ትግል ከነበሩት ዋነኛ ድካሞች አንዱ የሰፊው ሕዝብ አለመደራጀት ነበር። ይህ የመደራጀት ጥያቄ አጣዳፊነት የጐላው በየካቲት እንቅስቃሴ አፍላ ላይ ቢሆንም እስከዛሬም ያልተመለሰ ጥያቄ ነው። የወዛደሩ ፖርቲ አልተፈጠረም። ሌሎች የአብዩቱ ደጋፊዎች ለዚሁ ዓላማ አልተደራጁም። የድርጅት ጥያቄ እስካሁን ሳይመለስ የቆየው የመደራጀትን መብት ጨምሮ ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለሰፊው ሕዝብ ባለመከበራቸው ነው። ባገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ሰፊው ሕዝብ በሕገወጥ መንገድ ለመደራጀት ስላልቻለም ነው። የዚህ መለስተኛ ኘሮግራም የሰፊውን ሕዝብ በየፈርጁ መደራጀት አስፈላጊነት በይፋ ማወቅ ለሰፊው ሕዝብ መደራጀት አመቺ ሁኔታን ይፈጥራል። በሕጋዊ መንገድና በመንግስቱ የመገናኛ መሳሪያዎች ሳይቀር ስለወዛደሩ ፖርቲ አስፈላጊነት፣ በጠቅላላው ስለልዩ ልዩ የፖለቲካ ድርጅቶች አስፈላጊነት ማብራራት መቻሉ፣ ሰፊው ሕዝብ በፖለቲካ ድርጅቶች ውስጥ ለፖለቲካዊ ዓላማ ለመደራጀት የሚያስችለውን ንቃት ያስገኛል። ዛሬ ከራሉ ግብታዊ (ስፖንቴን) ትግል ካገኘው ንቃት ተነስቶ በየሞያ ማህበሩ እንደተደራጀው ሁሉ፣ በዚህ የፖለቲካ ድርጅቶችን አስፈላጊነት በሚገልጽ ቅስቀሳ በሚገኘው የበለጠ ንቃት ደግሞ ፖለቲካ ድርጅቶች ውስጥ ወደመደራጀቱ ይሻገራል። ይህን የመደራጀትን አስፈላጊነት በይፋ ያወቀ መለስተኛ ኘሮግራም የዲሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ከተከተለው በገቢርም ሰፊውን ሕዝብ በአፋጣኝ ማደራጀት ይቻላል።
የሰፊዉ ሕዝብ መታጠቅ ጥያቄ እንደ ድርጅቱ ጥያቄ ሁሉ አጣዳፊ ነው። አርሶአደሮች በቆራጥነት የሚያካሄዱትን ትግል ሳይታጠቁ ከግቡ ሊያደርሱ አይችሉም። እስከዛሬም ባለመታጠቃቸው ብዙ አርሶአደሮች የፊውዳሊስቶች ጥይት እራት ሆነዋል። ወዛደሩ፣ አርሶአደሩና የተቀረውም ሰፊ ሕዝብ የታጠቁ ጠላቶቻቸውን ለማሸነፍ መታጠቅ አለባቸው።
ከደርጉ መለስተኛ ኘሮግራም አብዮታዊ ይዘቶች አንዱ የሰፊውን ሕዝብ የመታጠቅ መብት ማወቁ ነዉ። እስከዛሬ ደርጉ አርሶአደሩን ለፀረፊውዳል ትግል ሊያስታጥቅ ይቅርና የመታጠቅ መብቱን ሳያውቅለት በመቆየቱ፣ አርሶአደሩ በራሱ ትግል ከፊውዳሎች የነጠቀውን መሳሪያ ለፊውዳሎች የተመለሱበት ቦታ ብዙ ነው። አርሶአደሩ የቀማውን መሳሪያ ለመንግስት እንዲያስረክብ የተደረገበትም ቦታ ብዙ ነው። የደርጉ መለስተኛ ኘሮግራም የሰፊዉን ሕዝብ የመታጠቅ መብት ማወቅ ሰፊው ሕዝብ ከደርጉም ሆነ ከደርጉ ውጭ በሚያገኘው መሳሪያ የሚታጠቅበትን ሁኔታ ይፈጥራል።
እናጠቃል። ባገራችን ሰፊው ሕዝብ ሳይሸነፍ፣ ፀረአብዮት ኃይሎችም ሳይሸነፉ ከሁለት ዓመታት በላይ ያላቋረጠ አብዮታዊ ትግል ተካሄዷል። ይህ የአብዮትና የፀረአብዮት አለመሸናነፍ ለብዙ ጊዜ ሊቆይ አይችልም። አንዱ ለሌላኛው ቦታ መልቀቀ አለበት። ወይ የሕዝብ ጠላቶች አሸንፈው ፀረአብዮት ቅልበሳ በማድረግ ብዝበዛና ጭቆናቸውን በተቀየረ መንገድ እንደገና ያሰፍሩብናል። ወይ ሰፊው ሕዝብ ብሄራዊ ዲሞክራሲያዊውን አብዮት ከግቡ በማድረስ ጠላቶቹን ይደመስሳል። የደርጉ መለስተኛ ኘሮግራም ያገራችንን የመደብ ትግል ከመቸውም ይልቅ ወደዚህ በአብዮትና በፀረአብዮት መካከል ወደሚደረግ ወሳኝ ትግል ደረጃ ያደርሰዋል። ባንድ በኩል፣ ፀረሕዝብ ኃይሎች የያዙትን ፀረ አብዮታዊ ትግል እንዲያፋፍሙ ያደርጋል። በሌላ በኩል የሰፊውን ሕዝብ ትግል የነቃ የተደራጀና የታጠቀ ጐዳና ለማስያዝ አመቺ ሁኔታ ይፈጥራል። በሌላ አነጋገር፣ የመለስተኛ ኘሮግራሙ መውጣት የተጀመረውን ትግል ወደ ወሳኝ ፍልሚያ ያቀርበዎል እንጂ የጠላቶቻችንን መደምሰሰ ወይም መዳከም አያስከትልም። የጠላቶቻችን መደምሰሰ ወይም መዳከም በመለስተኛ ኘሮግራሙ መታወጅ ምክንያት የሚመጣ ሳይሆን ይህን ኘሮግራም ሥራ ላይ ለማዋል የሚደረገው ትግል ሲሳካ ብቻ የሚመጣ ነው።
የደርጉ መለስተኛ ኘሮግራምና ሥራ ላይ የመዋሉ ጥያቄ
ከላይ እንዳልነው፣ የደርጉ መለስተኛ ኘሮግራም ይዘት አብዮታዊ ነው። ባገራችን ለተነሱ ተጨባጭ ጥያቄዎች ሁሉ (ጤና ለሁሉ፣ ትምህርት ለሁሉም፣ ሥራ ለሁሉ፣ ወዘተ. . .) የመፍትሄ ዘዴዎችን ያመለክታል። እዚህ ላይ ከመጀመሪያው ሁለት ስህተቶች መደረግ የለባቸዉም።
ባንድ በኩል “መመሪያው ወረቀት ላይ ያለ ነገር ነው”፣ “ምንም ዓይነት አዋጅ እኛን አያታልለንም” በሚሉ ግብዝ ሰበቦች ይህንን መለስተኛ ኘሮግራም ለማጥላላትና ትክክለኛ ትርጉሙን ለማሳጣት የሚጥሩ አሉ። አዋጁ በወረቀት ላይ እንዳይቀር፣ ለሰፊው ሕዝብ ችግሮች መፍትሄ አምጪ እንጂ ማታለያ እንዳይሆን የእያንዳንዱ ተራማጅ ኃላፊነት ነው። ይህን ኃላፊነት መሸከም ያልቻሉ ሰነፎች ወይም እውነተኛ ተራማጆች ይህን ኃላፊነት ለመሸከም እንዳይበቁ ለማድረግ የሚያወናብዱ ቀልባሾች የሚያደርጉትን የማጥላላት ዘመቻ መቃወምና መለስተኛ ኘሮግራሙ ትክክለኛ ግቡ ላይ እንዲደርስና ከወረቀት አልፎ በገቢር እንዲተረጐም መታገል ግዴታ ነው።
በሌላ በኩል አዋጁ ሳለ ችግር ሁሉ መፍትሄ አሰጣለሁ ስለሚል ይህን መፍትሄ ዛሬውኑ ለማየት የሚሹ፣ በመንግሥት ደረጃ የብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ኘሮግራም ስለወጣ ብቻ አብዮት ከግቡ የደረሰ የሚመስላቸው አሉ። ይህም ሌላኛው ከፍተኛ ስህተት ነው። ጠላቶቻችን በዚህ መመሪያ መውጣት ምክንያት ሊደመሰሱ ይቅርና ከላይ እንዳልነው የመመለሳቸው አደጋ ይጨምራል። የኢትዮጵያ ሕዝቦች ከነዚህ ደመኛ ጠላቶቻቸው ጋር የሚያደርጉት ትግል እንኳን ሊያከትም ወሳኝ የሆነው ትግል ከፊታችን ይጠብቀናል። እነዚህ ያገራችን ችግሮች መፍትሄዎች ደግሞ በዚህ መራራ ትግል ጠላቶቻችን ድል ሳይመቱ ሙሉ በሙሉ ሊገኙ አይችሉም። በሌላ አነጋገር መለስተኛው ኘሮግራም ብሄራዊ ዲሞክራሲያዊው አብዮት ከግቡ ከደረሰ በኋላ እንጂ ከዚህ በፊት ሙሉ በሙሉ ከሥራ ላይ ሊውል እንደማይችል ግልጽ ሊሆን ይገባል። ይህን ማለት ግን፣ አንዳንድ ጊዜያዊ ችግሮችን ለመፍታት በመሃሉ አይቻልም ማለት አይደለም። ከየካቲት እንቅስቃሴ ወዲህ የተገኙት ድሎች እንደሚያረጋግጡት ሁሉ፣ የሚካሄደው ትግል በቆራጥነት ከቀጠሉት የማይናቁ ድሎች ሊያስገኝ ይችላል። ኘሮግራሙም መፍትሄዎቹን አይሁን እንጂ ለነዚህ አይነቶች ድሎች መገኘት ዘዴውን ያመለክታል።
ስለመለስተኛ ኘሮግራሙ ይህን ካልን፣ ማን ሥራ ላይ ሊያውለው ይችላል ወደሚለው እንለፍ። በመጀመሪያ ይህ መለስተኛ ኘሮግራም በዛሬው ቢሮክራሲ አማካይነት ሥራ ላይ ሊውል አይችልም። ሌላ ቦታ እንዳልነው ሁሉ ቢሮክራሲው እንኳን ስራ ላይ ሊያውለው ከሚያደናቅፉት ዋና ዋና ኃይሎች አንዱ ነው።
ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት ራሱ ይህን ኘሮግራም ከሥራ ላይ ሊያውል አይችልም። ባንድ በኩል ገና ያልተረጋገጠው የማወላወልና ያለማወላወል ጥያቄ አለ። በሌላ በኩል ደርጉ ይህን ኘሮግራም ሥራ ላይ ሊያውል ይችላል ማለት ፊውዳሊዝም፣ ኢምፔሪያሊዝምንና ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝምን ያህል ጠላቶች ሊደመስስ ይችላል እንደማለት ነው። ይህ ደግሞ የሰፊውን ሕዝብ ታሪካዊና አብዮታዊ ድርሻ ለጥቂት ግለሰቦች መስጠት ነው። ስለዚህም ደርጉ የቀድሞ ወላዋይነቱን ካስቀረ፣ የዚህን መለስተኛ አዋጅ ሥራ ላይ መዋል የሚያግዙ እርምጃዎች በመውሰድ የሰፊውን ሕዝብ ትግል ሊያገለግል ይችላል። ሰፊውን ሕዝብ ተክቶ ግን ይህን ኘሮግራም ከሥራ ላይ ሊያውል አይችልም።
የደርጉን መለስተኛ ኘሮግራም ማን ሥራ ላይ ያውላል የሚለው ጥያቄና ብሄራዊውን ዲሞክራሲያዊ አብዮት ማን ያካሄዳል የሚሉት ጥያቄዎች አንድ ናቸው። የደርጉ መለስተኛ ኘሮግራም የብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ኘሮግራም እንደመሁኑ ሥራ ላይ ሊውል የሚችለውም በብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት አማካይነት ብቻ ነው። ብሄራዊውን ዲሞክራሲያዊ አብዮት ማካሄድ ደግሞ የሰፊው ሕዝብ ታሪካዊና አብዮታዊ ሥራ ነው። ግን ይህን ማለቱ ብቻ የተነሳውን ጥያቄ አይመልስም። ሰፊው ሕዝብ ይህን አብዮት ከግቡ ሊያደርስ የሚችለው የተወሰኑ ፖለቲካዊ፣ ድርጅታዊና ትጥቃዊ ዝግጅቶቹ ሲሟሉ ብቻ ነው።
የወዛደሩ መደብ ባገራችን ካሉት መደቦችና የሕብረተሰብ ክፍሎች ሁሉ የላቀ አብዮታዊ መደብ ነው። በዘመናችን የሚካሄደውን አብዮት ለመምራት የታሪክ ተልእኮ ያለው መደብ ነው። በዚህ መደብ ሳይመራ ብሄራዊ ዲሞክራሲያዊው አብዮት ከግቡ ሊደርስ አይችልም። ወዛደሩ ለዚህ አብዮት መሪነት እንዲበቃ ደግሞ በራሱ ፖርቲ ስር መደራጀት አለበት። በራሱ ፓርቲ ስር ሳይደራጅ ይህን ዲሞክራሲያዊ አብዮት ለመመራት አይችልም።
የኢትዮጵያን ሰፊ ሕዝብ አብዛኛውን ክፍል ያቀፈውና የፊውዳሊዝም ጭቆና ቀጥተኛ ተበዝባዥ የሆነው አርሶአደሩ ነው። የብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ተሸካሚም አርሶአደሩ ነው። አርሶአደሩ ደግሞ በተበታተነ ትግል ጠላቶቹን ሊያሸንፍ አይችልም። ብቻውን የራሱን የተበታተነ ትግል ሰብስቦ ለራሱ ትግል አመራር ሊሰጥ አይችልም። ስለዚህም በየአካባቢው የሚካሄዱት የአርሶአደሩ ትግሎች ተሰብስበው በአገር አቀፍ ደረጃ መቀነባበር አለባቸው። አርሶ አደሩም ለዚህ የትግል ደረጃ የሚያበቃው ወዛደር አርሶአደር ሕብረት ነው። የዲሞክራሲያዊው አብዮት ምሰሶም ይኸው ወዛደር አርሶአደር ሕብረት ነው።
ሌሎችም በፊውዳሊዝም፣ በኢምፔሪያሊዝምና በቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝም መደምሰስ ጥቅም የሚያገኙ ኃይሎች ትግላቸው ጥንካሬ የሚያገኘውና መስመር የሚይዘው በየፈርጁ ሲደራጅ ነው። እነዚህም ኃይሎች ተደራጅተው በወዛደሩ መሪነት፣ ወዛደር አርሶአደር ሕብረት ላይ በሚመረኮዝ የጋራ ግንባር ስር መሰብሰብ ሲችሉ በብሄራዊው ዲሞክራሲያዊው አብዮት ተገቢውን ቦታቸውን ይይዛሉ።
ከዚሁ የድርጅት ጥያቄ ጋር ተያይዞ የሰፊው ሕዝብ መታጠቅ ለዲሞክራሲያዊው አብዮት ተካሂዶ ግብ መድረስ አስፈላጊው ጥያቄ ነው። ሰፊው ሕዝብ ሳይታጠቅ ብሄራዊ ዲሞክራሲያዊው አብዮቱ ከግብ ሊደርስ አይችልም። ይህም ማለት ያልታጠቀ ሰፊ ሕዝብ የታጠቁ ጠላቶቹን ሊያሸንፍ አይችልም ማለት ነው። እንግዲህ የደርጉ መለስተኛ ፕሮግራም ሆነ ብሄራዊው ዲሞክራሲያዊ አብዮት ከግቡ ሊደርስ የሚችለው በወዛደሩ ፓርቲ በሚመራ የነቃ፣ የተደራጀና የታጠቀ የሰፊው ሕዝብ ትግል አማካይነት ብቻ ነው።
ዛሬ የወዛደሩ ፓርቲ ሳይፈጠርና እነዚህ ከላይ የጠቀስናቸው ድርጅታዊና ትጥቃዊ ዝግጅቶች ሳይሟሉ የብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራም በደርጉ ቢወጣ፣ በታሪክ የተመሰከረውን፣ በአብዮታዊ ቴዎሪ የተደገፈውን የዲሞክራሲያዊ አብዮት ጠቅላላ ሄደት ሊቀይር አይችልም። ይህም ማለት፣ የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ በወዛደሩ ፓርቲ መሪነት ነቅቶ፣ ተደራጅቶና ታጥቆ ሦስት ደመኛ ጠላቶቹን ሳይገጥም፣ ከዚህም ግጥሚያ ባሸናፊነት ወጥቶ ሥልጣን ሳይጨብጥ የደርጉ መለስተኛ ፕሮግራም ሙሉ በሙሉ ከሥራ ላይ ሊውል፣ ብሄራዊ ዲሞክራሲያዊውም አብዮት ከግብ ሊደርስ አይችልም። ይህ አብዮታዊ ሀቅ ለሰፊው ሕዝብና ለተራማጆች ሁሉ ግልጽ ሊሆን ይገባል። ተራማጆች ተግባራቸውንም ለመተለም ከዚሁ ሀቅ መነሳት ይኖርባቸዋል።
እናጠቃል። የዚህ መለስተኛ ፕሮግራም ታሪክዊ ቦታ ላገራችን ችግሮች ዛሬውኑ መፍትሄ ስለሚያስገኝ አይደለም። ሰፊው ሕዝብ ለነዚህ መፍትሄዎች እራሱ እንዲታገል ለማንቃት፣ ለማደራጀትና ለማስታጠቅ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር በመሆኑ ነው። የዚህ መለስተኛ ፕሮግራም መውጣት ለታጋዩ ሕዝብ ትግል ወደ ከፍተኛ ደረጃ መሻገር ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል ብሎ መቀመጥ አይረባንም፣ የሕዝብ ጠላቶችንም ትግል እንዲያይል እንደሚያደርግ መረዳት ያስፈልጋል። አንድገመውና፣ ለኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝቦች አስተማማኝ ድል ዋስትናው በወዛደሩ ፓርቲ የሚመራ የነቃ፣ የተደራጀና የታጠቀ አብዮታዊ ትግል ብቻ ነው።
እዚህ የትግል ደረጃ ለመድረስ፣ የሰፊውን ሕዝብ ትግል በወዛደሩ ፓርቲ ወደሚመራ የነቃ፣የተደራጀና የታጠቀ አብዮታዊ ጎዳና ለማስያዝ፣ ይህ የተፈጠረው አመቺ ሁኔታ የተራማጆችን ተግባርና ኃላፊነት እጥፍ ድርብ ያደርገዋል። በዚህ አመቺ ሁኔታ በአስቸኳይ ካልተጠቀምንበት አብዮዊው ትግል ሊቀለበስ እንደሚችል መገንዘብ አለብን። ስለዚህም ሀቀኛ ተራማጆች ሰፊውን ሕዝብ ለማንቃትና ለማደረጀት የሚያደርጉትን ጥረት ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ማፋፋም አለባቸው። ለዚህም ግብ የበለጠ ለመዘጋጀት የራሳቸውን አንድነት አጠንክረው መገኘት አለባቸው። በሳይንሳዊ ርእዮተአለምና በጠራ የፖለቲካ መስመር ላይ የእውነተኛ ተራማጆችን የጠነከረ አንድነት ገንብተው ይህን የተደራጀ ኃይላቸውን በሰፊው ሕዝብ የነፃነት ተጋድሎ ውስጥ ማሰማራት ይኖርባቸዋል። ይህ በአስቸኳይ ከተደረገ፣ እውነተኛ ተራማጆች የሰፊውን ሕዝብ ትግል የነቃ፣ የተደራጀና የታጠቀ ጎዳና ሊያሲዙ፣ ብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮቱም ከግቡ ሊደርስ ይችላል።