ሰሕድ ቁ. 44

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ቁጥር 44፣   ሐምሌ 20፣ 1968 

የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ

መኢሶን በዚህ የሰፊው ሕዝብ ድምፅ እትሙ፣ “ተማሪና ምሁር ከገበሬውና ከሠራተኛው ጋር ተዋሃድ፤ ከእነርሱም ተማር፤ መልሰህም አስተምራቸው፤አብረህም በመሰለፍ አዲሲቷን ኢትዮጵያ መስርት” በሚለው የተራማጆች መፈክር ዙሪያ የተደረጉት ትግሎች ፍሬ እንዳፈሩ ይጠቅሳል። ከእነዚህም የትግል ፍሬዎች መካከል የመሬት ላራሹ እና 56 ሺ ተማሪዎች “የእድገት በህብረት የእውቀትና የሥራ ዘመቻ” አማካኝነት በገጠር ተሰማርተው፤ ገበሬዎችን በማኅበራት ማደራጀታቸው በታሪክ እንደሚጠቀሱ ይጠቁማል። የተማሪዎች ሕዝባዊ መፈክሮችና የትግል ጥሪዎች እና የዘማቾች በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ስምሪት ከገበሬዎች ጥቅም ጋር የተቀናጀ መሆኑን በማስረጃ እየደገፈ ያብራራል።   

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ለሰፊው ሕዝብ ሰራተኛ ገበሬ፣ ነጋዴ፣ ወታደር፣ ምሁር መብትና ጥቅም የሚታገል ጋዜጣ

የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ይቅደም

ቁጥር 44                                                                   ቀን 20/11/68
 
 
ር እ ሰ  አ ን ቀ ጽ

ዘመቻው ያስተማረን

“ተማሪና ምሁር ከገበሬውና ከሠራተኛው ጋር ተዋሃድ፣ ከነርሱም ተማር፣ መልሰህም አስተምራቸው፣ አብረህም በመሰለፍ አዲሲቷን ኢትዮጵያ መስርት”

በሚለው መርህ ስር የኢትዮጵያ ተራማጆች ሲታገሉ ብዙ ዓመታት አልፈዋል። በኃይለሥላሴ ፋሺስታዊ አገዛዝ ሥር ይህ የተማሪና የምሁር መወሃድ ገቢር ላይ ባይውልም፣ “መሬት ላራሹ”ን የመሳሰሉት ወጣቱ ትውልድ አንግቦ የታገለላቸው መፈክሮች በጭቁኑ ሕዝብ ውስጥ ሥር ለመስደድና በየካቲት/66 በፈነዳው አብዮታዊ እንቅስቃሴ የራሱ የጭቁኑ ሕዝብ መፈክሮች ሆነው ለመቅረብ ችለዋል።

በኃይለሥላሴ የአመጽ አገዛዝ ሥር ከሠርቶ አደሩ ጭቁን ሕዝብ ጋር መዋሃድ ስላልተቻለ፣ ተራማጆችም ለየካቲት እንቅስቃሴ የግንባር ቀደምነት አመራር ለመስጠት ሳይበቁ ቀርተዋል። ይህ እንቅስቃሴ የተራማጆች ግንባር ቀደም አመራር ባያገኝም፣ የሰፊው ሕዝብ አብዮታዊ ትግል ገፍቶ ብዙ ሕዝባዊ ድሎችን ለመቀዳጀት ችሏል። የኢትዮጵያ ተራማጆች ግን፣ በኃይለሥላሴ አገዛዝ ሥር የነበራቸውን ድካም በየካቲት እቅስቃሴ አፍላ ላይም ሆነ በተከተሉት የትግል ወራቶች ለማስወገድ አልቻሉም። ማለትም ከሰፊው ሕዝብ ጋር ተዋህደው የወዛደሩን ፓርቲና ሌሎችም ታጋይ ድርጅቶችን መሥርተው ለአብዮታዊው እንቅስቃሴ አመራር ለመስጠት አልበቁም።

በዚህ ሁሉ መሃል፣ ሰፊው ሕዝብ የኃይለሥላሴን መንግሥት በትግሉ ገፍቶ ሲጥል፣ ባለመደራጀቱና ባለመጋጀቱ ሊተካው አልቻለም። በዚህም ምክንያት ወታደራዊው መንግሥት ሥልጣን ጨበጠ። ደርግም ሥልጣን እንደያዘ ከወሰዳቸው እርምጃዎች አንዱ 56ሺህ ወጣቶች የሚሳተፉበት “የእድገት በህብረት የእውቀትና የሥራ ዘመቻ” የሚለውን ፕሮግራም ማወጅ ነበር። ወታደራዊው ደርግ በዚያን ወቅት የኢትዮጵያን ሕብረተሰብ መሰረታዊ ቅራኔዎች የሚፈቱበትን መንገድ የሚያሳይ መመሪያ እንዳልነበረው ሁሉ፣ ይህ ብዙ ሺህ ወጣቶች የሚያሳትፍ ኘሮግራም በምን መንገድ እንደሚካሄድና እንዴት ከሥራ ላይ እንደሚውል የሚገልጽ መምሪያ አላቀረበም ነበር። የሆነ ሆኖ፣ ምንም ዓይነት ቀዳሚ ዝግጅት በመንግሥትም በኩል ሆነ በተራማጆች አይደረግ እንጂ፣ ይህ ዘመቻ የኢትዮጵያ ተራማጆች ከጥንትም የታገሉለትን ከሰፊው ሕዝብ ጋር የመዋሃድ መርህ በሥራ ለመተርጐም ያልተጠበቀ ቃላቅ እድል ከፈተላቸው። ይህ ከአርሶአደሩ ጋር ለመዋሃድ ከፍተኛ እድል የከፈተ ዘመቻ የሚደገፈውም ከዚሁ አንፃር ነው። አዲሱ ዲሞክራሲያዊ አብዮት በሚደረግበት አገር፣ አርሶአደሩን ከሚያክል የአብዮቱ ተሸካሚ ጋር ለማዋሃድና ከጐኑም ለመሰለፍ የሚያበቃ ኘሮግራም ለአብዮቱ ከፍተኛ ጥቅም እንደሚያስገኝ ምንም ጥርጥር የለውም። የቻይና የቪየትናም. . . ታጋዩች ከአርሶአደሩ ጋር ለመዋሃድ ባደረጉት ትግል፣ በየመንግሥቶቻቸው የደረሰባቸውን ስቃይና የተቀበሉትን መስዋእትነት ስናስታውስ፣ ይህ ዘመቻ በርግጥም ለኢትዮጵያ ተራማጅ ወጣቶች ያልተጠበቀ እድል ነው እንላለን።

እንግዲህ፣ ባንድ በኩል በቂ ዝግጅት ያልተደረገለት ኘሮግራም በመሆኑ፣ በሌላ በኩል የአብዮት ጠላቶች እንኳን ሊደመሰሱ ከሰፊው ሕዝብ የበለጠ ኃይል እያላቸው ሥራ ላይ መዋል የነበረበት ኘሮግራም በመሆኑ ብዙ ችግሮችና መሰናክሎች እንደሚኖሩት ከመጀመሪያው ግልጽ ነበር። በተለይ የመሬት አዋጅ ከወጣ በኋላ አርሶአደሩና ተራማጅ ዘማቾች በሕብረት ያካሄዱት ተጋድሎ ድል እያስገኘ ሲመጣ፣ በተራማጅ ዘማቾች ከፍተኛ ጥረት የአርሶአደሩ ንቃትና ድርጅት እየተጠናከረ ሲመጣ፣ አድሃሪ ፖሊሶችና የመሬት ከበርቴዎች፣ ቢሮክራሲው ዘመቻው ከዳር እንዳይደርስ ከፍተኛ ፀረአብዮት ተጋድሎ አድርገዋል። በዚህም ብዙ አርሶአደሮች፣ ተራማጅ ዘማቾችና አዝማቾች ተገድለዋል፣ ታስረዋል፣ ተሰቃይተዋል። የደርጉ ወላዋይነትም ብዙ ቦታዎች በገቢር እነዚህን ፀረ ሕዝብ ኃይሎች ጠቅሟል።

የዘመቻው ውጤት እየጨመረ በሄደ ቁጥር ዘመቻው እንዳይሰምር በአድሃሪ ኃይሎች የተዘረጉት መሰናክሎች እንዲሁ እየበረከቱ ሄዱ። ነገር ግን የነዚህ መሰናክሎች ፈጣሪዎች ቢሮክራሲው፣ አድሃሪ ፖሊሶችና የመሬት ከበርቴዎች እንዲሁም የደርጉ ወላዋይነት ብቻ አልነበሩም። አድሃሪ ዘማቾችና አዝማቾችም በዚህ ፀረ አብዮት ሴራ የድርሻቸውን አበርክተዋል። እነዚህም አድሃሪዎች ዘመቻውን ለመበተን ከፍተኛ ትግል አካሂደው ባንድ በኩል ቢጤዎቻቸውን የዘመቻ ጣቢያ እያስነቀሉ ወደከተማ ሲመልሱ፣ በሌላ በኩል ደግሞ በዘመቻው ችግሮች መበራከት ግራ የተጋቡ የተወሰኑ ዘማቾች ሊያሳስቱና በፀረ አብዮት ዓላማቸው ተባባሪ ሊያደርጓቸው ችለዋል። ተራማጅ ዘማቾች በከፍተኛ ቆራጥነትና መስዋእትነት ለአርሶአደሩ ትግል ያበረከቱት አስተዋጽኦ በኢትዮጵያ ሕዝቦች የትግል ታሪክ ሲታወስ የሚኖረውን ያህል፣ አድሃሪ ዘማቾችም ዘመቻውን ለመበተን ሆነ ጠቅላላ ኘሮግራሙን ለማቃወስ ባካሄዱት ፀረ አብዮት ትግል የኢትዮጵያ ጭቁን ሕዝቦች ይፋረዷቸዋል። ለየትኛውም ፀረ ሕዝብ የማይቀረው እድል ይጠብቃቸዋል።

እንግዲህ፣ የተጠቃለለው ዘመቻ፣ በተራማጅ ዘማቾች አኩሪ ትግል ከፍተኛ ድሎችን አስገኝቷል። ዛሬ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ለሚታዩት ብዙ ሺህ የገበሬ ማህበራት መፈጠር፣ ለአርሶአደሩ ንቃትና በመጠኑም ቢሆን ትጥቅ ማግኘት፣ የተራማጅ ዘማቾች አስተዋጽኦ ዓይነተኛና መሰረታዊ ነበር።

በበኩላችን፣ እነዚህ ተራማጅ ዘማቾች በብዙ መስዋእትነትና ስቃይ ከአርሶአደሩ ጋር ተባብረው ያስገኙዋቸው ድሎች እንዲጠበቁ፣ እንዲጠናከሩና ለሚቀጥሉት ድሎች መሸጋገሪያ እንዲሆኑ የዘመቻው ኘሮግራም መቀጠል አለበት እንላለን። ሰሞኑን፣ የዘመቻውን በዓል ማጠቃለያ በዓል ምክንያት በማድረግ ስለዘመቻው ቃለ መጠይቅ የሰጡ ወዛደሮችና አርሶአደሮችም ይህንኑ እንደሚፈልጉ ገልፀዋል። ነገር ግን፣ ዘመቻው ይቀጥል ሲባል፣ ባለፈው ዘመቻ የነበሩት ስህተቶች ታርመው፣ ያኔ ያልተሟሉት ዝግጅቶች አሁን ተሟልተው፣ መገኘት አለባቸው። በተጨማሪም፣ የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ በመደብ የተከፋፈለ እንደ መሆኑ ሁሉ፣ የየካቲት እንቅስቃሴና ያስገኛቸው ድሎች በአገራችን የመደቦችን አሰላለፍ የቀየረ እንደመሆኑ ሁሉ፣ የኢትዮጵያ ወጣቶች ከዚህ የመደብ ክፍፍልና የአሰላለፍ ለውጥ ነፃ ሊሆኑ እንደማይችሉ መረዳት ያስፈልጋል። የሚቀጥለው ዘመቻ ከአርሶአደሩና በጠቅላላውም ከሰፊው ሕዝብ ጐን ለመሰለፍ ፈቃደኞች የሆኑ ወጣቶች ብቻ ተሳታፊነት ሊኖረው ይገባል። በስመ ወጣትነት የሰፊው ሕዝብ ጠላቶች የዘመቻው ተሳታፊ ሆነው ቢላኩ፣ ባለፈው ዘመቻ እንዳደረጉት ሁሉ፣ የሰፊውን ሕዝብ ትግል ለማጨናገፍና የአባቶቻቸውን ፀረ አብዮት ተልእኮ ለማሟላት ይታገላሉ እንጂ ዘመቻውን ሥራ ላይ ማዋልን ያህል አብዮታዊ ተግባር አያከናውኑም። በተረፈም፣ ዛሬ የተራማጅነት መለኪያ “ተራማጅ ነን” የሚል ቅጽል ማንጠልጠል ስላልሆነ፣ ከፈቃደኝነትም ሌላ ወጣቶቹ በዛሬው አብዮታዊ እንቅስቃሴ ካላቸው አቋም ትክክለኛነት አንፃር የዘመቻ ተሳታፊዎችን መመልመል ያስፈልጋል። የተራማጅ ካባ ለብሰው የኢትዮጵያን የዛሬ ሁኔታ ለፋሺስታዊ ቅልበሳ የሚያመቻች ትግል የሚያካሄዱ ከሃዲ ወጣቶች በሚቀጥለው ዘመቻ ቦታ ሊኖራቸው አይገባም።

እንዲሁም፣ የዘማቾች ተግባር፣ የድልድይ፣ የመንገድ . . . ሥራን መጨመሩ ቢቀንስ ትክክል ይመስለናል። ተግባራቸው የፖለቲካ ንቃት በመስጠትና በማደራጀት ላይ ቢያተኩር የበለጠ ጥቅም ያስገኛልና። አርሶአደሩ ከነቃና ከተደራጀ፣ እንኳን ለራሱ ግልጋሎት የሚውሉ ድልድዮችና መንገዶች . . . መሥራት ይቅርና ጠቅላላ አገሪቷን ከከፍተኛ የብልጽግና ደረጃ የሚያደርስ ኃይል ነው። እንግዲህ፣ ዘመቻው በተሳታፊነት፣ በፈቃደኝነት፣ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ላይ በሚወሰደው አቋም ትክክለኝነት መሰረት የሚወሰን ከሆነ፣ እንዳለፈው ጊዜ ከ5ዐ ሺህ በላይ ዘማቾችን ማሰማራቱ አስፈላጊ አይሆንም። ያለፈው ዘመቻም ቢሆን የተሰማራው ወጣት ሁሉ በተግባር ላይ እንዳልተሳተፈ ግልጽ ነው። በትግል አምነው፣ ከሰፊው ሕዝብ ጐን ለመሰለፍ የቆረጡ ያነሰ ቁጥር ያላቸው ዘማቾችን የሚካፈሉበት ዘመቻ፣ አድሃሪውንና ንዝህላሉን ካግበሰበሰ የበለጠ ቁጥር ያላቸው ዘማቾች የሚካፈሉበት ዘመቻ የበለጠ ውጤት እንደሚያመጣ ግልጽ ሊሆን ይገባል።

በመጨረሻም፣ በንቃት በኩል ለመጐልመስ ተራማጅ ወጣቶች ከሠርቶ አደሩ የበለጠ እድል ቢኖራቸውም፣ የሠርቶ አደሩን ብሶትና ችግር በማወቅ ረገድ ሠርቶ አደሩ ራሱ የላቀ ነው። ሁለቱ፣ ማለትም የአብዮታዊ ቲዎሪ እውቀትና የሰፊው ሕዝብ እለታዊ ኑሮና ችግር እውቀት ሲዋሃዱ፣ ንቃትን ለማሳደግና ለማደራጀት የበለጠ ፍሬያማ ትግል ማካሄድ ይቻላል። ስለዚህም፣ የሚቀጥለው ዘመቻ ፈቃደኛ የሆኑና ትክክለኛ መስመር ያላቸውን ዘማቾች ብቻ ሳይሆን ንቁ ወዛደሮችንና አርሶአደሮችን ማቀፍ አለበት። በሌላ አነጋገር፣ ከተማሪው፣ ከወዛደሩና ከአርሶአደሩ የተውጣጡ የፖለቲካ ካድሬዎች ባለፉት 18 ወራት የተካሄደውን ዘመቻ በከፍተኛ ደረጃ መቀጠል አለባቸው። ይህ ሲሆን፣ ወዛደር-አርሶአደር ሕብረት ለመመስረት ሆነ የተያዘውን አብዮታዊ ትግል ከከፍተኛ ደረጃ ለማድረስ ካሁን የበለጠ ምቹ ሁኔታ ይፈጠራል። የቻይና አብዮታውያን፣ አብዮቱን በገጠር ስር ለማስያዝ ባደረጉት ተጋድሎ የተጠቀሙት በዚህ ዓይነቱ አብዮታዊ ዘዴ መሆኑን ማስታወስ ይጠቅማል። ለዚህም የዘማች ሠራዊት በቂ ርእዩተዓለማዊና ፖለቲካዊ ትምህርት ላጭር ጊዜ በመስጠት ባንድ በኩል ባጠቃላይ ንቃታቸውን ማሳደግ፣ በሌላ በኩል ከኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር የበለጠ ማስተዋወቅና በትግላቸው ስለሚገጥሟቸው ችግሮች ስለሚጠበቅባቸው ግዳጅ ማስረዳት ያስፈልጋል። በኛ እምነት፣ ዘመቻው ከላይ ባጭሩ ባሰፈርነው መልክ ከቀጠለ፣ ባለፈው ዘመቻ ተራማጅ ዘማቾች ያስገኛቸውን ድሎች ለማጠናከር፣ የሚቀሩትን መሰረታዊ ድሎች ለመቀዳጀት በሚደረገው ትግል የሚቀጥለው ዘመቻ ከፍተኛ ቦታ ይይዛል።

የዚህ ተከታይ ዘመቻ ተሳታፊዎችም፣ ያለባቸውን ከፍተኛ ሃላፊነት ለማሟላት በየራሳቸው ከፍተኛ ዝግጅት ማድረግ አለባቸው። የዘመቻው ተግባር መሳካት ከጠቅላላው የኢትዮጵያ አብዮት ጋር የተያያዘ እንደመሆኑ መጠን፣ ይህን አብዮት ለማሳካት በሚደረጉ ትግሎች ሁሉ መሳተፍ አለባቸው። ሃቀኛ ተራማጆችን አንድነት ለማጠናከር፣ የወዛደሩን ፓርቲ ለመፍጠር፣ ወዝአደር አርሶአደር ሕብረት ለመገንባት፣ የሰፊውን ሕዝብ የዛሬ እንቅስቃሴ የነቃ የተደራጀና የታጠቀ ሕዝባዊ ትግል ደረጃ ለማድረስ በሚደረጉት ትግሎች ሁሉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይጠበቅባቸዋል።

የኢትዮጵያ ሃቀኛ ተራማጆች፣ ተራማጅ ወጣቶች፣ ወዛደሮችና ሌሎችም ጭቁኖች እስካሁን ያካሄዷቸው ትግሎች ከፍተኛ ድሎችን አቀዳጅተዋል። በነዚህ ድሎች ላይ ተሸጋግረን ከዘላቂ ድሎቻችን የምንደርሰው ሃቀኛ ቀራማጆች ካሁን የበለጠ አንድነታችንን ስናጠናክር፣ ሰፊውን ሕዝብ ካሁን በበለጠ ስናነቃና ስናደራጅ ብቻ ነው። ይህንን ተረድተን በየተሰማራንበት የትግል መስክ ተጋድሎአችንን ማጠናከርና ማስተባበር የግንባር ቀደምትነት ግዴታችን ነው።

የተራማጅ ዘማቾች ተጋድሎ ሲታወስ ይኖራል!!
የሃቀኛ ተራማጆች አንድነት ይጠንክር!!!
ድሉ የጭቁን ሕዝቦች ነው!!

የውይይት ክበቦችና ሚናቸው

በመስከረም 68 መጀመሪያ ላይ የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከተነሳ ወዲህ በአገራችን የዲሞክራሲ ጭላንጭል እየታየ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተፈጠሩ ሁኔታዎች ሁሉ ይህንኑ የሚያረጋግጡ ናቸው። የጋዜጦችና የሌሎችም የመገናኛ ዘዴዎች ሁሉ ለማርክሳዊ ሌኒናዊ ስነጽሁፍ ክፍት መሆን፣ ከሞላ ጐደል በሳይንሳዊ የአብዮት ቲዮሪ ላይ የተመረኰዘ የብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ኘሮግራም በመንግሥት ደረጃ መውጣት፣ በሳምንት ሁለት ጊዜ በየመስሪያ ቤቶችና ድርጅቶች ውስጥ ዲሞክራሲያዊ ውይይት ማድረግ መቻሉ፣ የኤርትራን ችግር በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ድርድር ፍለጋ ጥረት መጀመሩ. . . እነዚህና ሌሎችም ለዲሞክራሲ ጭላንጭል ባገራችን እየፈካ መሄድ ቋሚ ምስክሮች ናቸው። እንደተቀሩትም ከየካቲት 66 ወዲህ የተገኙ ድሎች ሁሉ፣ እነዚህም ሰፊው ሕዝብና ተራማጅ ኃይሎች ሁሉ ( ደርጉም ውስጥ ያሉት ጭምር ) ባካሄዷቸው ትግሎች ያስገኛቸው ድሎች ናቸው።

እነዚህ የዲሞክራሲ ጭላንጭሎች ለሰፊው ሕዝብና ለጠላቶቹ ያላቸው ትርጉም ተቃራኒ ነው። ባንድ በኩል ለሰፊው ሕዝብ ትግል አመቺ የሆኑ ነገሮች ሁሉ ለሰፊው ሕዝብ ጠላቶች ጐጅ ናቸው። በሌላ በኩል ለሰፊው ሕዝብ የዲሞክራሲ ጮራ ሲፈነጠቅ ለጠላቶቹ ደግሞ እጅግ አስከፊ ቀን ይነጋላቸዋል። በዚህም ምክንያት ይህቺ የዲሞክራሲ ጮራ መልሳ እንድትዳፈን ፀረ ሕዝብ ኃይሎች በቀጥተኛና በተዘዋዋሪ መንገድ ለመታገል የተቻላቸውን ሁሉ ያደርጋሉ።

በተለይ የመሬት አዋጅ ከወጣ ወዲህ በሰፊው ሕዝብና በደርጉ መሃል የጐላው ቅራኔ በዴሞክራሲያዊ መብቶች ጥያቄ ላይ ነበር። ደርጉ ዲሞክራሲ ለጭቁኖች እየለቀቀ በሄደ ቁጥር በርሱና በሰፊው ሕዝብ መሃል ያለው ቅራኔ እየለዘበ ይሄዳል። ይህ ሲሆንም ጭቁኖች ያለጥርጥር በትግላቸው ዋና ጠላቶቻቸው ላይ ያተኩራሉ። ደርጉን እንደዋና ጠላት በማስቀመጥ እነርሱ ላይ የተሰነዘረው የትግል ጦር ደርጉ ላይ እንዲዞር ሲታገሉ የቆዩት መሳፍንትና እነሲአይኤ ይህንን በደርጉና በሰፊው ሕዝብ መሃል ያለ ቅራኔ ለዘብ ማለት በፍጹም አይፈልጉትም። ስለዚህም፣ ዲሞክራሲን በተለያዩ ደረጃዎች ለሰፊው ሕዝብ የሚለቁ የደርግ እርምጃዎች እንዲቀለበሱ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ። በሌላ በኩል ደግሞ “ፋሺዝም ነግሷል” በሚል ቲዎሪ ሰፊው ሕዝብ ደርጉን እንደዋና ጠላት እንዲታገልላቸው፣ ወይም ደግሞ “ፊውዳሊዝምንና ኢምፔሪያሊዝምን ነቅቶ መጠበቅ፣ ደርጉን መታገል” በሚል ታክቲክ ሰፊውን ሕዝብ ከጠላቶቹ ጋር አስተባብረው ደርጉን በመጣል አብዮቱን ለመቀልበስ የተነሱት የዲሞክራሲያ ከሃዲ ምሁራንም የዚህ የዲሞክራሲ ጮራ መፈንጠቅ ተፃራሪዎች ናቸው። ዋና የትግል ጓደኞቻቸው አብዮት የከዱ ንዑስ ከበርቴዎች ቢሆኑም፣ በሰፊው ሕዝብ ውስጥ ውዥንብር ለመንዛት ያመቻቸው በደርጉና በሰፊው ሕዝብ መሃል ባለው ቅራኔ ላይ ብቻ ማተኰሩ ስለሆነ፣ በደርጉና በሰፊው ሕዝብ መሃል ያለው ቅራኔ ለዘብ ካለ የውዥንብር መንዣ ገበያቸው ስለሚቀዝቀዝ የዲሞክራሲያዊ መብቶችን በማንኛውም ዓይነት ለሰፊው ሕዝብ መለቀቅ ይቃወማሉ። እንዲቀለበሱም በተዘዋዋሪ መንገድ ይታገላሉ።

እንደገናም፣ የለየላቸው የሕዝብ ጠላቶች ሆነ እነዚህ ከሃዲ ምሁራን ለሰፊው ሕዝብ ትግል አመቺ ሁኔታ መፈጠሩን ይቃወማሉ። መሳፍንትና እነሲአይኤ የሰፊው ሕዝብ ትግል በነዚህ አመቺ ሁኔታዎች ተጠቅሞ በከፍተኛ ደረጃ ከቀጠለ በነርሱ የማይበገር ኃይል እንደሚሆን ይረዳሉ። ከሃዲ ምሁራንም፣ የሰፊው ሕዝብ ትግል የበለጠ የነቃና የተደራጀ መልክ እየያዘ በሄደ ቁጥር በነርሱ ውዥንብር ሊፈታ እንደማይችል ይረዳሉ። ስለዚህ እነዚህ “ሁለት” ፀረ ሕዝብ ኃይሎች በሚደጋገፉ ዘዴዎች ለሰፊው ሕዝብ ትግል አመቺ ሁኔታ የሚፈጥር ማንኛውም እርምጃ እንዲቀለበስ ይታገላሉ።

የዛሬው አርእስታችን ወደሆነው፣ የውይይት ክበቦችን ወደፈቀደው የደርጉ ውሳኔ ስንመጣም ከላይ ባጭሩ ያነሳናቸውን ሀቆች ያረጋግጣል። የውይይት ክበቦች ጉዳይ በመጀመሪያ እንደተነሳ አድሃሪዎች ሁሉና ከሃዲ ምሁራን ሥራ ላይ እንዳይውል ከፍተኛ ተጋድሎ አደረጉ። “ሰፊው ሕዝብ ሙሉ ዲሞክራሲያዊ መብት እንጂ ቅምሻ አይፈልግም”፣ “ምርጦቹ ይህን ነገር የጀመሩት ታጋዩችን ለመልቀም እንዲያመቻቸው ነው” ወዘተ. በሚሉ ስንኩል ምክንያቶች ሠርቶ አደሩ ውይይት ክበቦቹን እንዳያቋቁም ለማድረግ ሞከሩ። ነገር ግን፣ በተራማጆች ትግልና ሰፊውም ሠርቶአደር ለመንቃት ባሳየው ከፍተኛ ፍላጐት ተሸነፈ። ሆኖም አድሃሪዎችና ከሃዲ ምሁራን ትግላቸውን በዚህ አላቆሙም። አድሃሪዎች ሁልጊዜም የሕዝብን ድል ለመቀልበስ ሳይሳካላቸው ሲቀር ታክቲካቸውን በመቀየር እነዚህን ድሎች ለራሳቸው ፀረ አብዮት ግብ መጠቀሚያ ለማድረግ ይጥራሉ። እንደዚህም ስለሆነ፣ የውይይት ክበቦችን በሚመለከተው በኩል አሁን የያዙት ታክቲክ፣ ባንድ በኩል የውይይት ክበቦች ለሰርቶአደሩ የሚኖራቸው ጥቅም እንዲኮላሽ ለማድረግ፣ በሌላ በኩል ደግሞ እነዚህን የውይይት ክበቦች የራሳቸው ፀረ አብዮት ሴራ መጠንሰሻ መሳሪያ ለማድረግ ነው።

በርከት ካሉ የውይይት ክበቦች አካባቢ እንደሚሰማው፣ ለአብዮቱ በሚጠቅሙ አርእስቶች ላይ፣ የሠርቶ አደሩን ንቃት ለማሳደግ በሚያስችሉ አርእስቶች ላይ ውይይት ከሚደረግ ይልቅ፣ በጥቃቅን ጥያቄዎች ላይ፣ በጐን ጥያቄዎች ላይ መጨቃጨቁ እንዲፋፋም አድሃሪዎችና ከሃዲ ምሁራን ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። ለምሳሌ፣ በመጀመሪያው ዙር የውይይት ክበቦች ‘ዲሞክራሲ’ በሚል አርእስት ላይ እንዲወያዩ በሚል ማሳሰቢያ ከሕዝብ ድርጅት ጉዳይ ጊዚያዊ ጽ/ቤት ቀረበ። የዲሞክራሲ ጥያቄ የሰፊው ሕዝብ ትግል አጣዳፊ ጥያቄ ነው። ከብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት መሰረታዊ ጥያቄዎች አንደኛው ነው። በዚህ አርእስት ስር፣ ስለህብረተሰብ አስተዳደግ ታሪክ፣ ዲሞክራሲ በተለያዩ የሕብረተሰብ ደረጃዎች ስለነበረው ይዘት፣ በዛሬው የኢትዮጵያ ሕዝቦች የትግል ደረጃ ዲሞክራሲያዊ መብቶች ስለሚኖራቸው ትርጉም . . . እየተወያዩ ብዙ መማርና ማስተማር ይቻላል። ይህ ሆኖ ሳለ፣ በዚህ አርእስት ላይ ተወያይቶ ለሰርቶአደሩ ንቃት ከፍተኛ እድገት መስጠት እየተቻለ፣ አድሃሪዎችና ከሃዲ ምሁራን ግን “የውይይት አርዕስት ከላይ አይወሰንብንም” የሚል የጐን ጥያቄ በማንሳት በብዙ ቦታዎች ብዙ ሳምንታት በማይረባ ንትርክ እንዲቃጠሉ አድርገዋል። በቃላት ጋጋታ ለመደበቅ ይሞክሩም እንጂ እነርሱ በመሰረቱ የተቃወሙት ‘የአርእስቱን ከላይ መወሰን’ ሳይሆን በዚህ አርእስት ላይ ውይይት ተደርጐ የሠርቶ አደሩ ንቃት ከፍ ማለቱን ነው። ለሠርቶ አደሩ፣ አርእስቱ ከየት መጣ ከየት ዋናው ነገር የአርእስቱ ጠቃሚነት ነው።  አርእስቱ ጠቃሚ እስከሆነ ድረስ፣ ‘ከላይ መጣ’ አንድ የውይይት ክበብ አባል አቀረበው ለሰርቶ አደሩ ጉዳዩ ‘የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው’ ነው። ሁለተኛም፣ እያንዳንዱ የውይይት ክበበ የየራሱን አርእስት ያጥና ቢባል ለሥርዓተ አልበኞች /ለአናርኪስቶች/ እንጂ ለሠርቶ አደሩ ጐጂ ነው። ትግላቸው አንድ ስለሆነ፣ የሚያሸንፉት ተደጋግፈው ሲታገሉ ብቻ ስለሆነ፣ ትግላቸውን ማስተባበር ያለባቸውን ያህል በአንድ አርእስት አካባቢ በመወያየት የንቃታቸውንም እድገት ቢያስተባብሩ ከፍተኛ ጥቅም እንደሚያገኙበት ግልጽ ነው።

በሌላ ቦታዎች ደግሞ ‘አብዮታዊ ኢትዮጵያ’ የተባለችው አዲስ ጋዜጣ ትነበብ አትነበብ በሚል የጐን ጥያቄ አድሃሪዎችና ከሃዲ ምሁራን ብዙ ሳምንታት እንዲባክኑ አድርገዋል። እዚህም ላይ ስለአርእስት ምርጫ ከወሰነው የሚለይ አይደለም። ባገራችን ተራማጅ የአማርኛ መጽሀፎች በጣም ጥቂት ናቸው። አብዛኛው ሠርቶ አደር ደግሞ በሌሎች የውጭ ቋንቋዎች አንብቦ የመረዳት እድል የለውም። ስለዚህም፣ ይህች ጋዜጣ ትነበብ አትነበብ የሚለውን ጥያቄ የሚወስነው የይዘቷ ሳይንሳዊነት ወይም ፀረ ሳይንሳዊነት እንጂ ከየት መምጣቷ አይደለም።

የውይይት ክበቦች የሚገባቸውንና የሚጠበቅባቸውን ተግባር እንዳያከናውኑ አድሃሪዎችና ከሃዲ ምሁራን ከሚዘረጉዋቸው መሰናክሎች ሌላኛው ሰርቶ አደሩ በጊዜያዊ ችግሮቹ ላይ ብቻ እንዲወያይ ለማድረግ የሚያካሄዱት ትግል ነው። ለዚህም፣ “የምትበላው ሳይኖርህ ምኑን ተወያየህ፣ እገሌ የተባለው ባለሥልጣን ሳይነሳልህ . . . እንዴት ከአሰሪዎችህና ከቢሮክራቶች ጋር በአንድ መድረክ ትወያያለህ . . . ወዘተ.” በሚሉ ቅስቀሳዎች በነዚህ ጥያቄዎች ላይ ክርክሩ ጦፎ የፖለቲካ ጥያቄ ለማንሳት እንዳይቻል ለማድረግ ይሞክራሉ። እርግጥ ሠርቶ አደሩ ከፍተኛ የኢኰኖሚ ችግር አለበት። የሚያጉላሉትና የሚበድሉት ባለሥልጣኖችም አሉ። ሆኖም ግን፣ በነዚህ የውይይት ክበቦች ስለነዚህ ችግሮቹ ስለተወያየ፣ እነዚህን ባለሥልጣኖች ስለተሳደበና ስላወገዘ፣ የኢኰኖሚ ችግሩ ሊቃለልለት፣ ከአድሃሪው ቢሮክራሲ ሊላቀቅ አይችልም። እንዲያውም የኢኰኖሚ ችግሩን ምንነትና መፍትሄውን ለመረዳት፣ አድሃሪው ቢሮክራሲ የሚደመሰስበትን መንገድ ለመረዳት የፖለቲካ ንቃቱን ማሳደግ እጅግ አስፈላጊው ዝግጅት ነው። ለፖለቲካ ንቃት እድገት ደግሞ የውይይት ክበቦች ዓይነተኛ መሳሪያዎች ናቸው።

ሠርቶአደሩ በቀን ተቀን ችግሮቹ ላይ ብቻ ካተኮረ፣ ወደዘላቂ ግቡ ለመድረስ የሚያስፈልገውን ንቃት አያገኝም፣ ዘላቂ ግቡ ለመድረስ ከሚያስችለው የትግል ደረጃ ላይ አይደርስም። የቀን ተቀን ችግሮቹን ችላ ሳይል፣ ዘላቂ ግቡ ለመድረስ የሚያስፈልገውን ንቃት ካገኘ ግን፣ ከዘላቂ ግቡ ለመድረስ የሚያስችለውን የትግል ደረጃ ለመያዝ ከተነሳ ግን፣ እግረ መንገዱን ለቀን ተቀን ችሮቹም መፍትሄዎች ሊያስገኝ ይችላል። አድሃሪዎችና ከሃዲ ምሁራን ይህን በሚገባ ስለሚረዱ፣ በአዛኝ ቅቤ አንጓችነት ሠርቶ አደሩ በቀን ተቀን ችግሮቹ ላይ ብቻ እንጂ በመሰረታዊ የአብዮቱ ጥያቄዎች ላይ እንዳያተኩር ለማድረግ ይፈልጋሉ።

ከላይ ያልነውን ለምሳሌ ያህል ጠቅሰን እንጂ አድሃሪዎችና ከሃዲ ምሁራን ውይይት ክበቦች የሚጠበቅባቸውን ተግባር እንዳያሟሉ የሚዘረጉትን መሰናክል ዓይነት እዚህ ላይ ዘርዝሮ መጨረስ አይቻልም። ባጭሩ ግን፣ የውይይት ክበቦች እንዳያይቋቋሙ ያደረጉት ሙከራ ከከሸፈባቸው ወዲህ፣ ለውይይት ክበቦች የሞያ ማህበር ሚና፣ ለሞያ ማህበራት የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና በመስጠት ነገሩን ሁሉ አተራምሰው ፀረ አብዮት ሴራቸውን ለማስፋፋት ሽርጉድ በማለት ላይ ናቸው። እዚህ ላይ ለሀቀኛ ተራማጆችና ለሠርቶ አደሩ ስለውይይት ክበቦች ሚና ግልጽ መሆን ያለበት ምን ድን ነው።

 መጀመሪያ ነገር፣ የውይይት ክበቦች መፈቀድ የዲሞክራሲያዊ መብቶችን ለሰፊው ሕዝብ ሙሉ በሙሉ መለቀቅ አያበስርም። ሠርቶአደሩም በዚህ “ቅምሻ” አይረካም፣ የዲሞክራሲ መብቶችን ሙሉ በሙሉ ለጭቁኖች መለቀቅ ይጠይቃል። ለዚህም ይታገላል። ነገር ግን፣ የሰፊው ጭቁን ሕዝብ አብዮታዊ የትግል ዘዴ፣ ጊዚያዊ ድሎችን፣ የመሸጋገሪያ ድሎችን ወደዘላቂው ድል፣ ዋስትና ወዳለው ድል እንዲያደርሱት አድርጐ መጠቀም ነው። “መሠረታዊ ድል ካልተገኝ እግረመንገዴን የማስገኛቸው የመሸጋገረያ ድሎች ገደል ይግቡ” የሚለው አነጋገር የጭቁኖች ሊሆን አይችልም።

እነዚህ የመሸጋገሪያ ድሎች ወደ መሰረታዊው ድል ሳያደርሱ የሚፈልጉ ከሃዲዎች ብቻ ናቸው ይህንን የሚሉት። ስለዚህ፣ ውይይት ክበቦች፣ ሙሉ በሙሉ ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለጭቁኖች እንዲለቀቁ ለሚደረገው ትግል መዘጋጃ እንዲሆኑ፣ ሠርቶ አደሩ ለዚህ ትግል ሆነ እነዚህ መብቶች ሲኖሩት በነርሱ ለመጠቀም የሚያስፈልገውን ንቃት ማግኛ ማድረክ እንዲሆኑ ለማድረግ መታገል የሃቀኛ ተራማጆች ሁሉ ተግባር ነው።

ፋሺስታዊው ኃይለሥላሴ በድንቁርናና በጭቆና ሰንሰለት ተብትቦ ከ50 ዓመታት በላይ በገዛት ኢትዮጵያ፣ ለተራማጅ አስተሳሰቦች በሩ ተዘግቶ በፊውዳላዊ ሥርዓትና አስተሳሰብ ውስጥ ስትማቅቅ በኖረች ኢትዮጵያ በሰፊው ሕዝብ ንቃተ ሕሊና ከዝቅተኛ ደረጃ ላይ መገኘት ፈጽሞ ሊያስገርም አይችልም። ከየካቲቲ/66 ወዲህ ጨቋኙ የፊውዳል ሥርዓትና አደንቋሪ ርእዩተ ዓለሙ እየተገረሰሱ ቢሄዱም በነዚህ ሁለት ዓመታት ውስጥ ይህ ለረዥም ጊዜ የኖረ ወደኋላ መቅረት እንዳልተወገደም ግልጽ ነው። በዚህ ላይ፣ በሰፊው ሕዝብ ውስጥ ስር የሰደደ፣ የወዛደሩ ፓርቲ ኖሮ ንቃተሕሊናውን ከፍ ለማድረግ ባልታገለበት ሁኔታ የሰፊው ሕዝብ ንቃተ ሕሊና በምንም ተዓምር ለአብዮቱ መሳካት የሚያስፈልገው ደረጃ አይደርስም። ስለዚህ፣ የሰፊውን ሕዝብ ንቃት ሕሊና ማሳደግን የሚበልጥ አብዮታዊ ተግባር የለም። የሰፊውን ሕዝብ ንቃት ሕሊና ለማሳደግ እድል የሚሰጥ ማንኛውም ነገር ትልቅ ቦታ ይኖረዋል። ሰፊው ሕዝብ በበቂ ሳይነቃ ሊደራጅ አይችልም። ሳይደራጅ ሊታጠቅ አይችልም። ሳይነቃ፣ ሳይደራጅና ሳይታጠቅ ደግሞ ጠላቶቹን ሊያሸንፍ አይችልም። የውይይት ክበቦች ሚና መታየት ያለበትም ከነዚህ ከተያያዙ የአብዮት ጥያቄዎች አንፃር ነው።

ከላይ፣ አናርኪስቶችና አድሃሪዎች ሁሉ ውይይት ክበቦች በጠቀስነው የተያያዙ የአብዮት ጥያቄዎች አንፃር የሚገባቸውን ሚና እንዳያሟሉ ከዘረጉት ወጥመዶች አንዱ እነዚህ የውይይት ክበቦች የሞያ ማህበር ሚና እንዲወስዱ የሚያደርጉት ጥረት መሆኑን ተናግረን ነበር። ሠርቶ አደሩ አሁን በከፍተኛ የኤኰኖሚ ችግር ውስጥ ይገኛል። ችላ የማይባልና አሳሳቢ ችግር ነው። በሰፊው ሕዝብ ድምፅ ቁጥር 41 ላይ እንደገለጽነውም፣ “የዛሬው የኢኰኖሚ ችግር የኢትዮጵያን አብዮት እድል ከሚወስኑት ከፍተኛ ጉዳዩች አንዱ ነው።” ስለዚህም ወዛደሩና ሠርቶ አደሩ ሁሉ ስለነዚህ ኢኰኖሚያዊ ችግሮች መወያየት፣ ለመፍትሄያቸውም መታገል አለባቸው። ለዚህም የሚረዷቸው፣ በትግላቸው የቆሙ የሞያ ማህበራት አሏቸው። የነዚህ ሞያ ማህበራት ዓይነተኛ ተግባር ሰርቶ አደሩ የኢኰኖሚ ችግሮች መፍትሄ ማግኘት መታገል፣ ሠርቶአደሩንም ለዚህ ትግል ማሰለፍ ነው። የውይይት ክበቦችን ወደሞያ ማህበርነት ለመለወጥ የሚደረገው አድሃሪ ሙከራ፣ ይህን የትግል መሳሪያ የሆነ የሙያ ማህበር ያዳክማል እንጂ በምንም ዓይነት ተዓምር የውይይት ክበቦችን ወደሞያ ማህበር መለወጥ አይችልም። የውይይት ክበቦች ብዙ ዝንባሌዎች የያዙ የልዩ ልዩ መደብ አባሎች የሚገኙባቸው እንደመሆናቸው መጠን የአንድ መደብ ብቸኛ መጠቀሚያ ሊሆኑ አይችሉም። ጊዚያዊ ዓላማና ተግባር ያላቸው እንደመሆናቸው መጠን፣ መደበኛ ዓላማና መሰረታዊ ተግባር ያላቸውን የሞያ ማህበራት ሊተኩ አይችሉም። እንድገመውና፣ የውይይት ክበቦች የተለያዩ መደቦች አባሎችን የያዙ፣ የፖለቲካ ንቃት ማደሪያ፣ የልዩ ልዩ የፖለቲካ መስመሮች መፋጫና መፋተጊያ መድረኰች ናቸው። የሞያ ማህበራት ለሠርቶ አደሩ የቀን ተቀን፣ ኢኰኖሚያዊና ሶሺያላዊ ችግሮች መታገያነት የቆሙ፣ በፖለቲካ ዝንባሌም ባይሆን በመደብ ተመሳሳይነት ላይ ያስተባበሩ ድርጅቶች ናቸው። ከውይይት ክበቦች የሚገኘውን ንቃት፣ የሚያሸንፈው የፖለቲካ መስመር የሞያ ማህበራትን ሊያጠናክር፣ በትግሉም ትክክለኛ አቅጣጫ ሊያስይዝ ይችላል። ይህ ግን የውይይት ክበብን የሞያ ማህበር አያደርግውም።

ከላይ እንዳልነው፣ የውይይት ክበቦች የተለያዩ መደቦች አባሎችና የተለያዩ የፖለቲካ ዝንባሌ ያላቸው ተሳታፊዎችን ያዘሉ ናቸው። የመስመር ትግል ያካሄድባቸዋል እንጂ የፖለቲካ ስምምነትና የርእዩተ ዓለም አንድነት ሊገኝባቸው አይችልም። ይህን የፖለቲካ መስመር ትግል ዴሞክራሲን በማክበርና ለጠቅላላው ሰፊ ሕዝብ ትግል በሚጠቅም መንገድ በማካሄድ የፖለቲካ ክርክሮች ለማበጣበጥ ሳይሆን ትክክለኛ መስመር ለማስያዝ እንዲጠቅሙ ማድረግ ይቻላል። ሆኖም፣ የከሃዲ ምሁራን ቀልባሽ ቡድንና ምልምሎቹ እነዚህን የውይይት ክበቦች፣ የተለያዩ የፖለቲካ መስመሮች መፋተጊያና የትክክለኛ መስመር ጥራት ማግኛ መድረክ እንዳይሆኑና የነርሱ ፀረ አብዮት መስመር መደንፊያ በመሆን እንዲወስኑ ለማድረግ ከፍተኛ ትግል ያካሄዳሉ። “ከአስተዳደር ነው፣ ከበዝባዥ ወገን ነው” በሚሉ ስሜት ነኪ የስውር ተንኰል ቅስቀሳቸው አንዳንድ ተቃዋሚያቸው የሆኑ ተሳታፊዎችን ለማስወገድ ሞክረዋል። ይህ በአስተዳደር ወይም በበዝባዥ ይሳበብም እንጂ ከነሱ የሚለይ የፖለቲካ መስመር ያላቸውን ተሳታፊዎች ለማግለል የሚጠቀሙበት ዘዴ እንደሆነ ጨርቃ ጨርቅና ልብስ ስፌት ኩባንያ በሚገኙ ወዛደሮች ላይ የደረሰው ያረጋግጣል። የፖለቲካ ክርክርን በአሉባልታ መተካት፣ ፊት ለፊት አቋምን ግልጽ አርጐ መታገልን መሸሽ መሰረታዊ የከሃዲ ምሁራን የትግል ዘዴ በመሆኑ ንቁ ሠርቶ አደሮችና ሃቀኛ ተራማጆች ሊቋቋሙት ይገባል። የውይይት ክበቦች በዲሞክራሲያዊ መንገድ የሚደረግ የፖለቲካ መስመር ትግል ማካሄጃ መድረክ ሆነው በዚህም ትግል አብዮታዊው መስመር በአሸናፊነት እንዲወጣ መታገል የግንባር ቀየምትነት ኃላፊነታቸው ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ፣ የኢትዮጵያ ወዛደር በፖርቲው ስር ሳይደራጅ አብዮቱን ሊመራ እንደማይችል የታወቀ ነገር ነው። የመንግሥት ሥልጣን ሊጨብጥ ይቅርና የመንግሥት ሥልጣን ጥያቄ እንኳን ሊያስነሳ እንደማይችል ግልጽ ነው። ቀልባሽ አናርኪስቶች “የላብአደር ፖርቲ አለላችሁ” በሚል በሬ ወለደ ይህን የእውነተኛ ወዛደር ፖርቲ በአስቸኳይ መፈጠር ለማዘግየት ሲታገሉ ቆይተዋል። ከዚህም ሌላ፣ ሥልጣን ለመያዝ ወዛደሩን በመሰላልነት ለመጠቀም በሚያደርጉት ትግል ለወዛደሩ የሞያ ማህበር የፓርቲውን ቦታ ለመስጠት ብዙ ጥረዋል። አሁን “የላብአደር ፓርቲ ፈጥረዋል” የሚለው ድንፋታ እየተጋለጠ ሄዷል። ወዛደሩም መሃል ምንም መሰረት እንደሌላቸው እየተነቃ ሄዷል። በተብለጭላጭ ድርጊቶች “የላብአደር ፓርቲ አለላቸሁ” በሚል በሬ ወለደ ይህን የእውነተኛ ወዛደር ፓርቲ በአስቸኳይ መፈጠር ለማዘግየት ሲታገሉ ቆይተዋል። ከዚህም ሌላ፣ ስልጣን ለመያዝ ወዛደሩን በመሳሪነት ለመጠቀም በሚያደርጉት ትግል ለወዛደሩ የሞያ ማህበር የፓርቲውን ቦታ ለመስጠት ብዙ ጥረዋል አሁን “የላብአደሩ ፓርቲ ፈጥረዋል” የሚለው ድንፋታ እየተጋለጠ ሄዷል። ወዘደሩም መሃል ምንም መሰረት እንደሌላቸው እየተነቃ ሄዷል። በተብለጭላጭ ድርጊቶች “የላብ አደር ፓርቲ” መሆናቸውን ለማሳየት ባደረግቸው ሙከራዎች እንኳ(ለምሳሌ በሜይ ዴይ) አይተውት የማያውቁት ወዛደር አድሃሪ መፈክራቸውን ይዘው ሊደባለቁ ሲሞክሩ ከወዛደሩ ጋር በፈጠሩት ግብ ግብ የከሃዲ ወጣቶችና የቦዘኔዎች ጥርቃሞነታቸው ታየ። በነዚህ ሁሉ መሃል፣ የወዛደር ፓርቲ ነን ከሚለው ድርቅና ይልቅ፣ የሞያ ማህበር የመንግሥት ሥልጣን ለማስጨበጥ የሚያበቃ ድርጅት አድርጐ በማቅረብ፣ የሞያ ማህበር ከጊዜያዊና ከኤኰኖሚያዊ ትግሎች አልፎ ሕብረተሰብን ነፃ ማውጣትን ለሚያህል ታላቅ ተግባር ወዛደሩን ሊመራ የሚችል ድርጅት አድርጐ በማቅረብ ለነርሱ ፀረ አብዮት ቅልበሳ ወዛደሩን መሰለል ለማድረግ፣ እውነተኛው የአብዮት መሪ የወዛደሩ ፓርቲ በአስቸኳይ እንዳይፈጠር ለማሰናከል መታገልን ይበልጥ ገፍተውበታል።

 ከላይ እንዳልነው የወዛደሩ የኢኮኖሚ ጥያቄዎች ሆኑ ትግሎች ትልቅ ቦታ ይይዛሉ። ከፖለቲካ ጥያቄዎችና ትግሎቹ ጋር ይያያዛሉ እንጂ አይቃረኑም። ስለዚህም፣ የሞያ ማህበሮች ለወዛደሩና ለሠርቶ አደሩ ትግሎች አስፈላጊ ድርጅቶች ናቸው። ሆኖም የወዛደሩ የሞያ ማህበር በምንም ዓይነት ፓርቲውን አይተካም። ማንኛውም የሞያ ማህበር የፖለቲካ ፓርቲን ቦታ ሊይዝ አይችልም። የወዛደሩን ፓርቲ አለመኖር፣ የፓርቲውን መፈጠር አስቸኳይ ያደርጋል እንጂ የሞያ ማህበርን ወደፓርቲነት አይቀይርም። የፖለቲካ ፖርቲን ሚና ለሞያ ማህበር መስጠት፣ የፓርቲውን መፈጠር፣ ስለዚህም አብዮታዊውን ትግል ወደኋላ መጐተት ነው። የኢትዮጵያ ወዛደር እንደየትኛውም ድል አድራጊ የዓለም ወዛደር ሁሉ፣ በራሱ ርእዩተ ዓለም የታነፀ ማርክሳዊ ሌኒናዊ ፓርቲ ሳይመራው አብዮት የመምራት ኃላፊነቱን፣ ታሪካዊ ተልእኰውን የማሟላት ሃላፊነቱን ሊፈጽም አይችልም። ወዛደሩን በሞያ ማህበር ትግልና አመራር ለመወሰን መሞከር የወዛደሩን ነፃነት መቃረን ነው።

 እንግዲህ፣ እነዚህን የወዛደሩን የተለያዩ ድርጅቶች የተደጋገፈ ተግባር ግን የተለያየ ሚና ተረድቶ ለወዛደሩ ንቅናቄ ጥንካሬና እድገት ለመስጠት መታገል የሃቀኛ ተራማጆችና ንቁ ወዛደሮች ተግባር ነው። የውይይት ክበቦች ወዛደሩን በራሱ ርእዩተ ዓለም ለማነጽ፣ የሠርቶ አደሩን ንቃት ለማሳደግ አመቺ እድል የከፈቱ መድረኮች ናቸው። የወዛደሩ የሞያ ማህበር፣ የሰርቶ አደሮች የሞያ ማህበራት ወዛደሩንና ሠርቶ አደሮችን ለኢኰኖሚያዊ ጥቅሞቻቸው ለማታገል፣ ፖለቲካዊ ድርጅቶች እስኪፈጠሩም ድረስ በዛሬው አብዮታዊ አንቅስቃሴ በትክክለኛ መስመር ስር ሊያሳትፉ የሚችሉ መሳሪያዎች ናቸው። የወዛደሩ ፓርቲ የኢትዮጵያን አብዮት ለመምራት፣ ወዛደሩን ለእውነተኛ ነፃነቱ ለማብቃት የሚፈጠር ተኪ የለሽ ግንባር ቀደም ድርጅት ነው። የሠርቶ አደሩ ፖለቲካዊ ድርጅቶች ብሄራዊውን ዲሞክራሲያዊ አብዮት ከግቡ ለማድረስ ባለው የጋራ ዓላማ ላይ በሚመሰረተው በወዛደሩ ፓርቲ የሚመራ አብዮታዊ ግንባር ውስጥ ሠርቶ አደሩን ተገቢ ቦታ የሚያስይዙ ድርጅቶች ናቸው።

ያለወዛደሩ ፓርቲ መሪነት፣የወዛደሩ እንቅስቃሴ ድልን ሊመታ አይችልም። ያለፖለቲካ ድርጅቶቻቸው ሠርቶአደሮች  ከጭቆና ሊላቀቁ አይችሉም። ወዛደሩን የሚያቅፍ የወዛደር ፓርቲ እስከ አሁን አልተፈጠረም።ወዛደሩ በራሱ ፓርቲ ስር ሊደራጅ ይችል ዘንድ በራሱ ርእዮተ አለም መታነጽ አለበት። በራሱ ርእዮተ አለም ለመታነጽ ከሚያስችሉት መድረኮች አንዱም የውይይት ክበብ ነው።ሠርቶአደሩም እንዲሁ በፖለቲካ ድርጅቶች ውስጥ ለመደራጀት ንቃቱ ማደግ አለበት። የውይይት ክበቦች ለዚህ ግብ ትልቅ አገልግሎት ያበርክታሉ።

እንግዲህ፣ የወዛደሩን በራሱ ርእዮተ አለም መታጠቅ ፣ የሠርቶ አደሩን ንቃት ከፍ ማለት የሕዝብ ጠላቶች ሁሉ እንደ ጦር ይፈሩታል። ንቃት ካደገ መደራጀት ይመጣልና፣ ከተደራጁ መታጠቅ ይቻላልና። ሰፊው ሕዝብ ከነቃ ከተደራጀና ከታጠቀ ደግሞ ፀረ አብዮት ሴራቸውን በማያዳግም ሁኔታ ለመደምሰስ ተፈላጊውን ኃይል ያገኛልና። በአንጻሩ፣ ሃቀኛ ተራማጆች ደግሞ ሰፊው ሕዝብ በነቃ፣ በተደራጀና በታጠቀ የሕዝብ ትግል ብቻ ሊያሸንፍ እንደሚችል ስለሚያውቁ ሰፊውን ሕዝብ ለማንቃት በማንኛውም እድል ይጠቀማሉ። የተለያዩ ቀለም ያላቸው ፀረ አብዮተኞች ኃይሎች የውይይት ክበቦች ለሠርቶ አደሩ ጠቀሜታ እንዳይሰጡ፣ የነርሱ ፀረ አብዮት መሳሪያ እንዲሆኑ የሚታገሉትን ያህል፣ ሃቀኛ ተራማጆች፣ ንቁ ወዛደሮችና ሠርቶ አደሮች ደግሞ የውይይት ክበቦቹ ለንቃት ማሳደጊያ፣ ታጋዩን ሰፊ ሕዝብ ለከፍተኛ ትግሎች ማዘጋጃ ለማድረግ መታገል አለባቸው።

ባጭሩ፣ በውይይት ክበቦች ሳቢያ የሚደረገውም ትግል በአብዮትና በፀረ አብዮት ኃይሎች መሃል የሚደረገውን ትግል ያንጸባርቃል። በአብዮትና በፀረ አብዮት ኃይሎች ማሃል የሚደረገው ትግል በከፍተኛና ዝቅተኛ ደረጃ፣ በጥቃቅንና አብይ ጉዳዮች ላይ፣ በጉልህና በውስብስብ ጥያቄዎች ላይ ሁሉ ይካሄዳል። ከነዚህም የትግል ዘርፎች አንዱም የሚናቅ ወይም ችላ የሚባል አይደለም። የውይይት ክበቦችንም በሚመለከተው በኩል የሚካሄደው ትግል ችላ ሳይባል በአብዮታዊ ኃይሎች ድል አድራጊነት ትክክለኛ አቅጣጫ መያዝ አለበት። ለዚህም፣ በአገር አቀፍ ደረጃ የሃቀኛ ተራማጆችና የንቁ ወዛደሮች አንድነት እንደሚያስፈልገው ሁሉ፣ በያንዳንዱ የውይይት ክበብ የሚገኙ ሃቀኛ ተራማጆች፣ ንቁ ወዛደሮችና ሠርቶአደሮችም ትግላቸውን ማስተባበር አለባቸው።

 
የከሃዲ ምሁራንና ሌሎችም ቀልባሾች የሚዘረጉት መሰናክል ይወድማል!
የነቃ የተደራጀና የታጠቅ ሰፊ ሕዝብ ያሸንፋል!
Scroll to Top