ሰሕድ ቁ. 15

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ቁጥር 15፣    ህዳር 17፣ 1967 

የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ

መኢሶን በዚህ የሰፊው ሕዝብ ድምፅ እትሙ፣ ወታደራዊ መንግሥት 60 ኢትዮጵያውያንን ቅዳሜ ህዳር 14 ቀን፣ ያለፍርድ መረሸኑ ሕዝቡን እንዳስቆጣና እንዳስደነገጠ ያትታል። የቀድሞ የአጼ ኃይለ ሥላሴ ባልሥልጣናትን፣ የሕዝብ ጥያቄ ካነሱት ከጥቂት የጦር መኮንኖችና ወታደሮች ጋር አቀላቅሎ የወሰደው ይህ የግድያ እርምጃ በጽኑ የሚወገዝ መሆኑን ደጋግሞ ይገልጻል። በአፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ባለስልጣናት ላይ የፖለቲካ እርምጃ ይወሰድ ሲባል፤ አንድም ከስልጣናቸው ይሻሩ እንደሆነ እና በሌላም መልኩ በተገቢው የፍርድ ሥርዓት ቀርበው ጥፋተኞች በእስራት እንዲቀጡና ንጹሃን በነጻ እንዲሰናበቱ መሆኑን ያስገነዝባል።ሆኖም፣ ህዳር 14 ቀን ያለፍርድ በተረሽኑት 60 ግለስቦች ላይ ወታደራዊ መንግሥት የፈጸመው ድርጊት፣ አስቀድሞ በመርማሪው ኮሚሽን ሕጋዊ ምርመራና በፍርድ ችሎት ውሳኔ ያልተሰጠበት፤ “የሰውን ህሊና የሚያሸብር ፋሺስታዊ ፍጅት” ነበር ሲል ይደመድማል።         

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ለሰፊው ሕዝብ ሰራተኛ ገበሬ፣ ነጋዴ፣ ወታደር፣ ምሁር መብትና ጥቅም የሚታገል ጋዜጣ

የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ይቅደም

 
ቁጥር 15                                                                      ቀን 17/3/67

 

ታሪክን የሚያጎድፍ ፋሽስታ ድርጊት።

ቅዳሜ ህዳር 14 ቀን ማታ ወታደራዊው መንግሥት 6ዐ ሰዎችን ያለበቂ ምክንያት መረሸኑ የኢትዮጵያን ሰፊ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን የውጭ ተመልካቾችን ጭምር ግራ አጋብቷቸዋል። ምንም እንኳን እስካሁን ለደርጉ ያለቅጥ መርበትበት ምክንያት የሆነው ጉዳይ በግልጽ ባይታየንም ድርጊቱ ከመርበትበት የተነሳ የተፈፀመ መሆኑን ደርሰንበታል። ከኢትዮጵያም ሆነ ከዓለም ሕዝብ በጣም ከፍ ያለ ቁጣን አስከትሏል፣ የደርጉን ደጋፊዎች እንኳን ሳይቀር አሸብሯቸዋል። ደርጉ በቃል በሚሰብከውና በድርጊት በሚፈጽመው መካከል ትልቅ ቅራኔ መኖሩን ግልጥልጥ አድርጐታል።

የኢትዮጵያን ሰፊ ሕዝብ ከሁሉም ያስገረመውና ያስቆጣው በአቋማቸውና በሕይወት ታሪካቸው የተለያዩ፡ ሕዝቡን ሲበድሉና ሲያሰቃዩ የኖሩ አድሃሪዎችና ሲታገሉለት የነበሩትን ተራማጆች በአንድነት ጠቅልለው እንደበግ መፍጀታቸውና ያለአንዳች የቀብር ስነሥርዓት መጣላቸው ነው። በዚህች በማትረሳ ምሽት የተረሸኑትን ሰዎች በጠቅላላው እሶስት ላይ ከፍሎ ማየት ያስፈልጋል።

በአንደኛው ክፍል የቀድሞው ንጉስ አሽከሮችና ባለሟሎች ይገኛሉ። እነዚህ ሰዎች በስልጣን ላይ በነበሩበት ጊዜ ሰፊውን የኢትዮጵያ ሕዝብ የበደሉና የበዘበዙ፡ ብዙ ግፍ የፈፀሙ የፊውዳሉ ሥርዓት ምሰሶዎች ነበሩ። ስለዚህ በስልጣን ላይ ሆነው በጣም አደገኞች በነበሩበትና ደርጉን ለመገልበጥ ያሰጉ በነበሩት ጊዜ የሰፊው ሕዝብ ወገኖች የፖለቲካ እርምጃ እንዲወሰድባቸው መጠየቃቸው ይታወሳል።ሆኖም የፖለቲካ እርምጃ ሲባል የህዳር 14 ቀኑን አይነት ፋሽስታዊ ፍጅት መጠየቃቸው አልነበረም። በመሰረቱ ሰፊውን ሕዝብ በበደሉ ሰዎች ላይ የፖለቲካ እርምጃ ሲወሰድ በአስቸኳይ ጊዚያዊ ፍርድ ቤት ተቋቁሞ፡ የሰዎቹ ጉዳይ በክፍት /በግልጥ/ ችሎት ታይቶ ይፈረድባቸውና ቅጣቱም ወዲያውኑ ይፈፀማል ማለት ነው። እንደየሁኔታው በሞትም ሆነ በእሥራት የሚቀጣ ወይንም በነፃ የሚለቀቅ ይኖራል። ይህ አሰራር ሰፊው ሕዝብ ፍርዱ ለምን እንደተሰጠ በግልጽ አውቆት ትምህርት እንዲያገኝበት ይረዳዋል። በተጨማሪም በማናቸውም ሰው ላይ የሞትም ሆነ ሌላ አይነት ቅጣት ሲደርስ ተገቢ መሆኑ ለሁሉም በግልጽ ስለሚታይ የተመልካቹ ህሊና አይረበሽም።

ህዳር 14 ቀን በተረሸኑት ሰዎች ላይ የተፈፀመው ድርጊት ግን ከዚህ የተለየ፡ በዳኝነት ታይቶ ፍርድ ያልተሰጠበት፡ የሰውን ህሊና የሚያሸብር ፋሽስታዊ ፍጅት ነበር። በብዙ ምክንያቶች ሊነቀፍ ይገባል።

አንደኛ ነገር፡- ደርጉ ራሱ ‘ለሁሉም ፍትህ መስጠት አለብን’ በማለት ጉዳዩን በመርማሪ ኮሚስዩን ሲያስጠና ከቆየና ውሳኔ የሚሰጥ የጦር ፍርድ ቤት ካቋቋመ በኋላ፡ጉዳዩን በክፍት ችሎት በማስፈረድና ለሕዝቡ ተገቢውን ትምህርት በማበርከት ፈንታ እስረኞቹን ቅር በሚያሰኝ አኳኋን ያለፍርድ ረሸናቸው።

ሁለተኛ ነገር፡- የሟቾቹ አመራረጥ ጉዳይ ትክክል አይደለም። የሥርዓቱ ቁንጮ አጤ ኃይለሥላሴ በክብር ተይዘው በቤተመንግሥት ሲቀመጡ አሽከሮቻቸውን ያለፍርድ መረሸን ምን ይባላል? ደግሞስ ከታሰሩት ባለስልጣኖች መካከል እነዚህ የተረሸኑት በተለይ የተመረጡበትን ምክንያት የሚያሳይ ምንም ነገር የለም። ሦሶተኛው ነቀፌታ ደግሞ ሰብአዊ ስሜትን የሚመለከት ነው። የእነዚህ የቀድሞ ባለሥልጣኖች ጥፋት ምንም እንኳ በግልጥ ቢታወቅ በእስር ቤት ሆነው ፍርዳቸውን ሲጠባበቁ ፍርዱን ሰርዞ እንደከብት ነድቶ መረሸን ሰብአዊ ስሜትን የሚነካ የአረመኔ ተግባር ነው።

ከሞቱት ሰዎች መካከል በሁለተኛው ክፍል ሌተና ጄኔራል አማን ሚካኤል አንዶም ይገኛሉ። ደርጉ ጄኔራሉን መረሸኑን አውጆ ነበር፣ ነገር ግን ተረቱን ማንም ስላልተቀበለለት ጦርነት ከገጠሙና ብዙ ከተዋጉ በኋላ መሞታቸዉን ማመን ግድ ሆኖበታል። እንዲያውም የቀሩት 59 ሰዎች የተረሸኑት ጄኔራሉ ስለሞቱ ነው። የጄኔራውን መሞት ሕዝቡ ሲሰማ ትልቅ ተቃውሞ እንደሚነሳ በመገመት ሌሎች ሰዎችን ረሽኖ ሕዝቡን ለማወናበድና ስሜቱን ለመከፋፈል የታቀደ ይመስላል።

ሌ/ጄኔራል አማን ከዚህ በፊት ደርጉን በመወከል በወሰዱአቸው ፀረ ሕዝብ እርምጃዎች ምክንያት፣ በተለይም በአደረጓቸው ዲስኩሮች በኤርትራ የነፃነት ተዋጊዎችና በኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ላይ ደጋግመው በመዛታቸው፣ ከተራማጆች ብዙ ወቀሳና ተቃውሞ ተሰንዝሮባቸው ነበር።

ነገር ግን ወደኋላ የራሳቸውንና የደርጉን ጥፋት ስለተገነዘቡ፣ራሳቸውንም ሆነ ደርጉን ለማረም እንደሞከሩ አሁን ተረጋግጧል። ይህ ሙከራቸውም እንደጥፋት ተቆጥሮ ለሞት እንዳበቃቸው ማወቅ በጣም የሚያሳዝንና የሚያስቆጣ ነው።

በውጭ የዜና ምንጮች እንደተነገረውና ከሚታመኑ የአገር ውስጥም ምንጮች እንደታወቀው በደርጉና በጄኔራሉ መካከል ልዩነትን ካስነሱ ጉዳዩች መካከል ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው፡-

  1. ወታደራዊውን መንግሥት የሚመሩት ሰዎች የጦር እንጂ በቂ የፖለቲካ እውቀት እንደሌላቸው በማመልከት፣ ከሲቪልና ከወታደር የተውጣጣ ጊዚያዊ ሕዝባዊ መንግሥት እንዲቋቋም ጄኔራሉ ማሳሰባቸው፣
  2. የኤርትራና ሌሎችም የብሔሮች ጉዳይ ሊፈታ የሚችለው በሰላም መንገድ እንጂ በጦትነት አለመሆኑን በማመልከት፣ደርጉ ይህን ኘሮብሌም በኃይል ለመፍታት ከሚያደርገው ከንቱ ሙከራ እንዲቆጠብ ማስጠንቀቃቸው፣
  3. በቂ ዝግጅት አለመደረጉን በማመልከት፣ ‘ዕድገት በህብረት’ በሚለው ኘሮግራም ተማሪዎችን ወደ ገጠር የመላኩ ጉዳይ እንዲዘገይ ማሳሰባቸው፣

እንደምናየው እነዚህ ጥያቄዎች በሙሉ የሰፊው ሕዝብ ጥያቄዎች ናቸው። ደርጉ የጄኔራሉን አርአያ ተከትሎ በመታረም ፈንታ ጄኔራሉን አሳድኖ ማስገደሉ በጥብቅ ሊኮነን የሚገባው ፋሺስታዊ ድርጊት ነው። ደርጉ እንደትናትና የራሱና የኢትዮጵያ በሙሉ መሪ የነበሩትን ጄኔራል ከአድሀሪዎች ጋር በአንድነት በማስገደሉ፣ የኢትዮጵያንም ሆነ የዓለምን ሕዝብ አስገርሞታል። አጭበርባሪነቱን፣አወናባጅነቱንና ወስላታነቱን በይፋ አስመስክሯል። በፊት በመታለል ይደግፉት የነበሩትም የዋህ ሰዎች አሁን ድጋፋቸውን ነስተውታል።

ቅዳሜ ማታ ከተረሸኑት ሰዎች መካከል በሶስተኛው ክፍል ውስጥ ወታደራዊ አምባገነንነትን የተቃወሙና ሕዝባዊ መንግሥት እንዲቋቋም የጠየቁ የሰራዊቱ አባሎች፣ እነሻንበል ደምሴ ሽፈራው፣ ሻንበል በላይ ፀጋየ፣ ሻንበል ወ/ዩሐንስ ዘርጋው፣ምክትል የአሥር አለቃ ተክሌ ኃይሌ፣ተራ ወታደር በቀለ ወልደ ጊዩርጊስ፣ የመቶ አለቃ ተስፋየ ተክሌ፣ ጁኒየር አክማን ዩሐንስ፡ፍትዊና ኮሎኔል ይገዙ ይመኔ ይገኛሉ። እነዚህ የሰፊው ሕዝብ አርበኞች እንኳን መረሸንና ፈጽሞ መታሰርም እንዳልነበረባቸው ግልጽ ነው። እንደነዚህ ያሉትን የሰፊው ሕዝብ ወገኖች የሚረሽኑ እንደነሻለቃ መንግሥቱ ኃይለማርያም ያሉ፣ደም የጠማቸው ፋሽስታዊ ወንበዴዎች ብቻ ናቸዉ። ፋሽስታዊው ደርግ ለነዚህ የሕዝብ አርበኞች ሕይወት በቀጥታ ተጠያቂ ነው። የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ግዳጃቸውን በትክክል በመፈጸማቸው በወንበዴዎች ለተሰውት ለነዚህ ሰማዕታት ሞት የሚበቀልበት ጊዜ ሩቅ አይደለም። የሰፊው ሕዝብ ድምፅ ጋዜጣ ለነዚህ እውነተኛ የኢትዮጵያ ልጆች ቤተሰቦችና ዘመዶች ጥልቅ ኀዘኑን ይገልጻል።

ባለፈው ቅዳሜ የፈጸመውን ፋሽስታዊ ድርጊት ለሕዝብ ሲያውጅ፣ ደርጉ እግረ መንገዱን ‘በሥራ መወዘፍ’ እያመካኘ የሚጠላቸውን ንጹሕ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ከየመስሪያ ቤቱ እየጐተተ ለመረሸን እንደሚያስብ ያላንዳች ሀፍረት ገልጾ ነበር፣ በውነቱ በዚህ አኳኋን የሚዝት ምንም ሕግ የማያውቅ የወንበዴዎች ድርጅት ብቻ ነው። ‘ጀርመን ትቅደም’ በማለት የመጀመሪያውን ፋሽስታዊ መርሆ በመፍጠር ለነ ሻለቃ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ምሳሌ የሆኑት እነሂትለር እንኳን ለሰፊው ሕዝብ የነበራቸውን ንቀትና ጥላቻ ይህን ያህል ደፍረው በግልጽ አሳይተውት ይሆን?

ካለፈው ቅዳሜ፣ ኀዳር 14 ቀን የደርጉ ፋሽስታዊ ድርጊት አስፈላጊውን ትምህርት መውሰድና ተገቢውን መደምደሚያ መስጠት ያስፈልጋል። ይህ ፋሽስታዊ ድርጊት በደርጉ ውስጥ አንዳንድ ስልጣን የጠማቸው ግለሰቦች ስልጣን መያዛቸውና የዲሞክራሲ አሰራር በጭራሽ ማክተሙን፣ ደርጉ ወደፍጹም የወንበዴዎች ድርጅት መለወጡን ያመለክታል። በድርጊቱ አስቀድሞ ዲሞክራሲያዊ ውይይት ተደርጐ ከደርጉ አባሎች ብዙኃኑ ተስማምተውበት ነበር ለማለት እንዴት ይቻላል? ፍጅቱ ደርጉ ከሰፊው ሕዝብ ራሱን በመነጠሉና ድጋፍ በማጣቱ ዛሬ ከመሳሪያው በስተቀር ማንንም እንደማያምን ያሳያል። ስለዚህ ኮሽ ባለ ቁጥር በርግጋ እሾኋን በየአቅጣጫው እንደምትረጭ ጃርት፣ ትንሽ የሀሳብ ልዩነት በተነሳ ቁጥር ታንኩን በየአቅጣጫው ለማሰማራት [የማይነበብ ቃል] በሕፃኑም ላይ ሳንጃውን ለመምዘዝ አገሪቱን በደም ጐርፍ ለማጥለቅለቅ መዘጋጀቱን ያሳያል። በተጨማሪም ከዚህ በፊት በዚህ ጋዜጣ እንደተመለከተው የደርጉ ድርጊቶች አገሪቱን በሙሉ ወደ እርስበርስ ጦርነት በፍጥነት በማምራት ላይ መሆናቸውን ያረጋግጣል። ከዚህ ችግር ለመላቀቅ የሚቻለው ሰፊው ሕዝብ ድርጅቱን አጠንክሮ ትግሉን ካሰፋና ከአፋፋመ ብቻ ነው። ለዚህም ግብ ተራማጅ ኃይሎችና ድርጅቶች በሙሉ ተግባራቸውን ማስተባበር ይገባቸዋል

ከዚህ ቀደም ‘ያለምንም ደም’ እየተባለ ጆሮአችንን ሲያደነቁር የነበረው ልፈፋ ደርጉ ደም የተጠማ የፋሽስት ወንበዴዎች ድርጅት መሆኑን ለመሸፈን የታሰበ መሆኑ አሁን ለሁሉም በግልጽ ይታያል።

የደርጉ መሪ፣ የኢትዮጵያው አዶልፍ ሂትለር፣ ሻለቃ መንግሥቱ ኃይለማርያም ባለፈው ሳምንት ‘የደርጉ አባሎች በሙሉ አስተዋዩች፣ ቆራጦች፣ ፈጣኖችና ተራማጆች ናቸው። . . . . . . በተራመዱ ቁጥር የሚረግጡትን ምድር  በጥንቃቄ እያስተዋሉ ነው።’ እንቅስቃሴያችንም ‘ኢትዮጵያውያኖችን ብቻ ሳይሆን አፍሪካውያኖችንንም ያኮራና ዓለምን ያስደነቀ ነ፣ . .  . . ይህ ለውጥ . . የዓለምን ሊቃውንትን ምርምር ውድቅ አድርጐታል።’ እያለ እራሱን ሲያሻሽጥ ነበር።

እንዲህ ያለ እውቀትና ጥንቃቄ የት ይገኛል፡ የትስ ታይቶ ይታወቃል! አንድ እውነት ቢኖር የሻለቃው አሻንጉሊት የሆነው ደርግ በፋሽስታዊ ጭካኔው የዓለምን ሕዝብ አስደንቆታል። የአፍሪካ አገሮች ጋዜጦች የቅዳሜውን ምሽት ርሸና ‘የአፍሪካን ታሪክ የሚያጐድፍ ፋሽስታዊ ድርጊት’ ብለው ሲሰይሙት፣ በአረመኔነታቸው የታወቁት የነሻለቃ መንግሥቱ የምስጢር ወዳጆች፣ የአሜሪካ ኢምፔሪያሊስቶች እንኳን በድርጊቱ በጣም ስለአፈሩበት ‘ለኢትዮጵያ ስንሰጥ የነበረውን ማንኛውንም ዓይነት እርዳታ አቋርጠናል’ ብለው ለማወጅ ተገደዋል።

 
ፋሽስታዊ ወታደራዊ መንግሥት ይውደም
ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ይደራጅ
ተራማጅ ኃይሎች የትግል አንድነታቸውን ያጠንክሩ።

 

ለፋሽስታዊ ጣኦት አንንበረከክም፣

ትግሉ እየተፋፋመ ነው።

  1. የህብረተሰብ ታሪክ ተመሳሳይነት፡-

የሰውን ልጅ ታሪክ ዞር ብለን ስንመለከተው በእርግጥ በህግ የሚመራ መሆኑን እንረዳለን። ህግጋቱ ከሰው ፍጥረት፣ ከሁኔታው፣ ከፍላጎቱ፣ ለመኖር ለመሻሻል ከሚያደርገው ጥረትና ትግል የሚመነጩ ናቸው፣ የሕይወት ትግል ህግጋት ናቸው። አንድ ሰው አንድ ነገር ሲያደርግ አንድ ነገር ይከተላል፣ ትንሽም ቢሆን እንቅስቃሴ ከተደረገ ውጤት ተከታይ እንዳለው የማያከርክር እውነት ነው።

የህብረተሰብ ታሪክ በመሰረቱ ተመሳሳይና አንድም ነው ለማለት ይቻላል። ህግጋቱ፣ ሥርዓቱ እንደየስፍራው ሁኔታም ምንም እንኳን አንዳንድ ለየት ያሉ ነገሮች ቢኖራቸውም ያው በአጠቃላይ አንድ ናቸው። ከልዩነት ይልቅ ተመሳሳይነቱና አንድነቱ እጅግ በጣም ጉልህ ነው።

በየትም ሀገር ቢሆን የሕዝብ እንቅስቃሴ ይደረጋል፣ የተጨቆኑና የተበዘበዙ የህብረተሰቡ መደቦች ወይም ክፍሎች ዘወትር ይህንን ሁኔታ ደስ ብሏቸው አይቀበሉትም፣ ገዥያቻቸውን ለማስወገድና ራሳቸውን ነፃ ለማውጣት የድካማቸውን ፍሬ ለራሳቸው ጥቅም ለማድረግ ይፍጨረጨራሉ፣ ጫንቃቸውን የገሸለጠውንና ያቆሰለውን የጭቆናና የብዝበዛ ቀንበር ሰባብረው ለመጣል ዝንት ዓለም የማያቋርጥ ትግል ያደርጋሉ። እኛም አሁን ያለንበት ሁኔታ ከዚህ የተለየ አይደለም።

ጊዜ ያነሳቸው አምባገነኖች ህዝቡን አላዋቂ በማድረግ፣ እንዲያውም ምን ያውቃል ደንቆሮ ነው፣ አይኑን ገና አልከፈተም፣ ብልጣብልጦች ያወናብዱታል፣ እኛ ነን አሳቢው፣ ያለእኛ ምን አለኝታ አለው፣ እኛ ከተውነው ገደል ይገባል፣ ዘመቻ አድርገን እናስተምረዋለን፣ የታወረውን አይኑን እንከፍትለታለን፣ እስከዚያ ድረስ /ጊዜው አብዛኛውን ጊዜ አይነገርም፣ እንዲያው በደፈናው ይተዋል፣ አድርባይ ተለማማጮች 3፡5፡1ዐ አመት ወዘተ. በማለት ፍርፋሪ ይለምኑበታል/ በእኛ ሞግዚትነት ይተዳደራል፣ እኛ ሕዝቡ ነን፡ ሕዝቡ እኛ ነው፣ ይህንን የሚቃወም የሕዝብ ጠላት ነው፣ ይውደም፣ በሞት እንቀጣዋለን ወዘተ. የሚባለው ሁሉ ርካሽ ኘሮፖጋንዳ ነው።

በኢትዮጵያም ነገሩ ያው ነው፣ በፊትም የነበረው ሁኔታ ሌሎች ብዙ አገሮች ያለፉበትን ይመስላል። አጤ ኃይለሥላሴ በኢትዮጵያ ላይ ከባድ ግፍ እንደሰራ ሁሉ በሌሎችም አገሮች ቢጤዎቹ ተመሳሳይ ወንጀል ፈጽመዋል፣ በስልጣን ላይ አንሰራፍቶ ለመቆየት የመጨቆኛና የመደምሰሻ መሳሪያ-ሰላይ፡ፖሊስ፣ ወታደር፣ወዘተ.- አደራጅቶ ሰፊውን ሕዝብ ያስጨቁንና ከየካቲት 66 ጀምሮ በመካሄድ ላይ ያለውም እንቅስቃሴ በሌሎች አገሮች ከተደረጉት ጋር ብዙ ተመሳሳይነት አለው። ሰፊው ሕዝብ የትግሉ አንቀሳቃሽና ባለቤት ሆኖ ሳለ በኃይለሥላሴ ከባድ ጭቆና ምክንያት በሚገባ ባለመደራጀቱና ባለመጠናከሩ ወታደሩ ቅድሚያውን ያዘ፣ እነእንዳልካቸውን የመሳሰሉ አጭበርባሪዎች ወታደሩን በገንዘብና በሹመት በመደለል ስልጣን ኮርቻ ላይ ወጥተው ለመመቻቸት ሲጥሩ ሰፊው ሕዝብ ባለዉ የትግል መሳሪያና ዘዴ ስለተቋቋማቸው በመወገዳቸው ሌሎች የቀበሮ ባህታዊዎች መጡ፣ የድሃ ወገኖች ነን፣ ከሰፊው ሕዝብ ጉያ የወጣን ነን፣ ጨቋኞቹንና በዝባዦቹን ለማጥፋትና ሰፊውን ሕዝብ ለመበቀል ተመርጠን የመጣን ነን የሚሉ ጥቂት መኮንኖች እስልጣን ላይ ቂብ አሉ። ከሰፊው ሕዝብ ትከሻ ላይ ወጥተን እንደላደላለን ሲሉ ከሕዝብ ወገኖችና ከሰፊው ሕዝብ ተቃውሞ ገጠማቸው፣ ዛቻና ማስፈራራት ያጥለቀለቀውን የባዶ ቃላት ከበሮ በሞኖፖል በያዙት ዜና ማሰራጫ ይደልቁት ጀመር። ብዙ ጣሩ፣ ብዙ ደከሙ፣ ውጤቱ እምብዛም አልተሳካም፣ ተቃውሞው፡ማጋለጡ ቀጠለ፣ በኋላም መበሳጨት፡መቆጣት፡ ማሰር፡መግደል፡እርስበርስ መባላት መጣ። ይህ ሁሉ ‘የሊቃውንትን ምርምር’ እንደማያከሽፈው ተረዱት፣ በሌሎች አገሮች የተደረገና የሚደረግም ነውና። የትግሉ እንቅስቃሴ ከስር እየገፋ በመመጣቱ ድንጋጤ፣ ብርክ ያዛቸው፣ ህሊናቸውን በመሳት በደመነፍስ ራሳቸውን ከትግሉ እንቅስቃሴ ሞገድ ለማዳን የባጡን የቆጡን መቧጠጥ ጀመሩ።

ታዲያስ ስልጣን ያሰከራቸው ጥቂቶቹ ሴረኞች ሰሞኑን ያወጇቸው ፋሽስታዊ ህጐች የሰፊውን ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ የትግል ማእበል ምን ያህል ሊያግዱትና ሊገቱት ይችላሉ?

2. የህጐቹ ይዘት፦ 

ፋሺስታዊ ህጐቹ ይዘትና አላማ እነአዶልፍ ሂትለር፡ እነቤኑቶ ሙሶሊኒ አውጀዋቸው ከነበሩት፡ ዛሬም እነቮርስተርና እነ ኢያን ስሚዝ በደቡብ አፍሪካና በሮዴሽያ ከሚጠቀሙባቸው ጨቋኝና ፀረሕዝብ ህጐች ብዙ የሚለዩ አይደሉም። መሰረተ ሃሳባቸውና አብዛኞቹም አናቅጽ እነዚህ የፋሽዝም ቀንደኞች ይጠቀሙባቸው ከነበሩት ህጐች የተቀዱ ወይም የተገለበጡ ሳይሆኑ እንደማይቀሩ ለመገመት ይቻላል።

‘ተራማጅ’ ነን፣ ፀረአድሃሪ ነን፣ የሰፊው ሕዝብ ቤዛ ነን፣ ኢትዮጵያንና ሰፊውን ሕዝብ ለማስቀደም መስዋአት ለመሆን መጣን፣ ወዘተ. በማለት እምቢልታቸውን ሲነፉ የሰነበቱት ጥቂት ሴረኞች መኮንኖች ሰሞኑን ባወጧቸው ሶስት ህጐች እውነተኛ መልካቸውን፡ አስከፊውን ጭጐጐት ገፃቸውን ገልፀዋል። እንዲህ አድርጐም ራስን በገዛ እጅ ማጋለጥ የለም።

በልዩ ልዩ ወንጀለኛ መቅጫ ህግ አዋጅ ቁጥር 8/1967 በምእራፍ 1ና 5 የተዘረዘሩት ድንጋጌዎች ተራማጅ የሕዝብ ወገኖችንና ሰፊውን ሕዝብ ሰንገው ፀጥ ለማስደረግ የታሰቡ ናቸው። የሰፊውን ሕዝብ መሰረታዊ ሰብአዊና ብሄራዊ መብቶችና ነፃነቶች በፍፁም ይደመስሳሉ። ስልጣን ኮርቻ ላይ ፊጥ ያሉት እፍኝ የማይሞሉት ሴረኞች የሚሉትን ፍሬከርስኪ፡ የሚያቀርቡትን ምስቅልቅል ሁሉ ያለአንዳች ቅሬታና ትችት አሜን ብለን እንድንቀበል ሊያደርጉን የታቀዱ ናቸው።

‘በመንግሥትና በርእሰብሄሩ /ሴረኞቹ/ ላይ የሚሰሩ ወንጀሎች’ በሚለው ርእስ ውስጥ የተዘረዘሩት ወንጀሎች በቀጥታና በዘወርዋራ፡ በልዩ ልዩ መንገድ ወይም ዘዴ ሕዝቡን የቀሰቀሰ፡በመንግሥቱ ላይ እንዲነሳ ያደረገ፡ የአገርን ነፃነትና አንድነትና [የማይነበብ] የጐዳ፣ ርእሰብሄሩን /ሴረኞቹን/፡ ቤተሰቦቻቸውን የነካ፣ እንቅፋት የሆነባቸው፣ የተቃወማቸው፣ወዘተ. በጽኑ እሥራትና በሞት ይቀጣል ይላል። የነገሩ አስከፊነት ይህ ብቻ አይደለም፣ እነዚህ የተመለከቱት የህጉ ቃላት እንደተፈለገ ለመተርጐም የሚያስችሉ፡ አንዳች ነገር ያልሰራውን ንፁህ አገርወዳድ ሁሉ እንጦርጦስ ሊያስገቡ የሚችሉ መሆናቸው ነው። ሴረኞቹና የመረጧቸው ቱልቱላ ዳኞች የማይወዱትን፣ የማያጐነብስላቸውን፣ እንደጣኦት የማያመልካቸውን ሁሉ ሊገድሉት ይችላሉ። እንደነአለቃ ፈጠነ፣ እንደነበቀለ አናሲሞስ፣ እንደነሻምበልባሻ ገብረፃዲቅ ተወልደና እንደብዙዎቹ በኃይለሥላሴ ፋሽስታዊ መንግሥት ኢሰብአዊ ስቃይና ፍዳ እንደተቀበሉት፡ ዛሬም ይህ አሰቃቂ ሁኔታ ተመልሶ በመምጣት ላይ ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ ቀደም ብሎ ስልጣኑን በያዙት ሰዎች አካባቢ ሲወራ የነበረው ልዩ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ የተፈለገው ይበልጡኑ ለቀድሞ ባለስልጣኖች መፋረጃና መቅጫ ነው። ምእራፍ 2ና 3 የኢትዮጵያውያን ሰፊ ሕዝብ ሙልጭ አድርገው ያራቆቱትን የቀድሞ ባለስልጣኖችን ስለሚመለከቱ ወንጀለኞች ይዘረዝራል። እነዚህ ባገሪትዋና በሕዝቡ ላይ ለሃምሳ ዓመታት ያህል በአምባገነንነት ሲፈነጩበት እንደመቆየታቸው መጠን ከፍ ያለ ቅጣት የሚገባቸው ሲሆን ህጉ ይህን ያህልም ከባድ ቅጣት አላመለከተላቸውም። /በ14/3/67 የተፈመው የ6ዐ ሰዎች ግድያ ከህጉ ውጭ የተከናወነ ነው።/ በምእራፍ 3 አንቀጽ 27 በሕዝብ ላይ ከባድ ችግር /አንደ አሁኑ ድርቅ /ሲመጣ በቸልተኛነት ወይም አውቆ ዝም ያለ እንደሆነ ከ1ዐ አመት እስከእድሜ ልክ፣ ሆነ ብሎ ችግሩ እንዲስፋፋ ያደረገ እንደሆነ ቅጣቱ እስከሞት ድረስ ይሄዳል። እንግዲህ ከፍተኛው ቅጣት ይህ ነው።

ከዚህ እንደሚታየው የመንግሥቱን ስልጣን ጨብጠው ለመያዝ የሚውተረተሩት ጥቂት ‘ምርጥ’ መኮንኖች ህጉን ያወጡት በእውነት የኢትዮጵያን ሕዝብ ጠላቶች ለመቅጨትና የግፍ ዋጋቸውን ለመክፈል ሳይሆን፡ የሰፊውን ሕዝብ አለኝታዎች በመደምሰስ ያለተቃውሞና ያለተቀናቃኝ በሰፊው ሕዝብ ትከሻ ላይ አንሰራፍተው በመቀመጥ ለመዝረፍና ለማስዘረፍ ነው። የዚህ የፋሽስታዊ ህግ ዋና አላማ ሰፊውን ሕዝብ አፉን ለጉሞ፡ እጁንና እግሩን ጠፍሮ አስሮ በአገርና በውጭ አገር ከበርቴዎች ለማስበዝበዝ መሆኑ ግልጽ ነው። እንደዚህ አይነት ህግ እንዴት አድርጐ ሌላ አላማ ሊኖረው ይችላል?.

በልዩ የጦር ፍርድ ቤትም በኩል አላማው ያው ነው፣ ለይስሙላ ፍርድ ቤት አቁመናል፡ በህግና በፍርድ ቤት ነው የተቀጡት እያሉ ተራማጅ የሕዝብ ወገኖችን ለማፈንና ለመፍጀት ነው። ፍርድ ቤቱ የሰጠው ውሳኔ ይግባኝ የሌለው ብቻ አይደለም፣ እርግጥ ይግባኝ መሰረታዊ ሰብአዊ መብት ነው፣ መደፈር መገፈፍ የለበትም። እዚህም ላይ ድርጊቱ ያው ከላይ እንደተባለው ፋሽስታዊነቱን በጉልህ ያሳያል። በፍርድ ቤቱ በኩል ዋና አሳሳቢና አደገኛ ነገር የዳኞቹ ሁኔታ፡ በደርጉ /ሴረኞቹ/ የሚሾሙ የሚሻሩ፡ በትእዛዝ የሚሰሩ ወታደሮች ብቻ መሆናቸውና የህግ እውቀትና የዳኝነት ሥራ ልምድ የሌላቸዉ መሆናቸው ነው። ከእንደዚህ ያለ ሁኔታ ፍትህ ይቅርና ደህና አስተያየት እንኳን ሊገኝ ይችል ይሆን? ፍፁም አይመስልም። ከዚህ የሚጠበቀው ፍትህ ሳይሆን ተቃራኒ ነው።

አዋጁ ቁጥር 1ዐ ‘የሕዝብ ፀጥታ ደህንነትና ሰላማዊ ኑሮ ለመጠበቅ’ የሚለው የወታደራዊው መንግሥት ፍፁም ፋሽስታዊ ህግ ከደቡብ አፍሪካው የቮርስተር ፀረሕዝብ ህግ ጋር ተመሳሳይነት አለው ብለናል። ‘የዘጠና ቀን እሥራት’ ከሚለው የዘረኛው ፋሽስታዊ መንግሥት አዋጅ የተቀዳ ነው ለማለት ይቻላል፣ የአምባገነን እሥራቱ መነሾ ምክንያትና የጊዚው መጠን አንድ ከመሆናቸውም በላይ የአገር ግዛት ሚኒስትሩ እንደፈለገ ለማራዘም ይችላል። የደቡቡ አፍሪካ ጭፍራ የሆነችው የኢያን ስሚዝ ሮዴሽያም ልክ እንደዚሁ የሆነ፡ ከዚያው የተቀዳ ፋሽስታዊ ህግ እንዳላት የታወቀ ነው።

ከዚህ በላይ እንዳመለከትነው የዚህ አይነቱ ህግ በስልጣን ላይ የወጡትን ሕዝቡ ያልተቀበላቸውን፡ በሰፊው ሕዝብ ፈቃድና ምርጫ ስልጣን ያልተቀዳጁትን ፀረሕዝብ አምባገነኖች ለመጠበቅና ስልጣን ኮርቻ ላይ ለማቆየት የሚያገለግል አንድ መሳሪያ ነው። በደቡብ አፍሪካ በቮርሽተር የሚመራው የነጮች ብሄረኛ ቡድን የሶስት ሚልዮን ተኩል ነጮችን ጥቅም ለመጠበቅ ሲል ከ17 ሚልዮን በላይ የሆኑትን ጥቁሮች ለመጨቆንና ለማስበዝበዝ በተባለው ፋሽስታዊ ህግ ይጠቀማል፣ በሮዴሽያም ኢያን ስሚዝ ከግማሽ ሚልዮን የሚያንሱትን ነጮች በአምስት ሚልዩን ጥቁሮች ትከሻ ላይ አስቀምጦ ለማስቦጥቦጥ ይጠቀምበታል። የእኛዎቹ ሴረኞች ደግሞ የውጭና የአገር ከበርቴዎችን ጥቅም ለማካበትና ለመጠበቅ ከኢምፔሪያሊዝም በተቀበሉት ትእዛዝ መሰረት ስልጣን ላይ ለመቆየት የእነ ቮርሸተርን ህግ ገልብጠው አወጁት።

 ‘የዘጠና ቀኑ እሥራት ህግ’ አላማ ይህ ሲሆን ይዘቱ ደግሞ ማንንም ሰው በማንኛውም ቦታና ሰአት ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ እያፈሱ እንደከብት በረት ወህኒ ቤት ውስጥ ማጐር ነው። ይህን አስቀያሚ ፀረሕዝብ ድርጊት እንዲመራ የታደለው [የተመደበው] የአገር ግዛት ሚኒስትሩ ነው፣ ባሁኑ ጊዜ የሲአይኤው ተቀዳሚ ቡችላ ኰሎኔል በላቸው ጀማነህ ነው። ይህ የኃይለሥላሴ የመጨቆኛ መሳሪያ አንቀሳቃሽ የነበረ፡ የብዙ ንፁሃን አገርወዳዶችን ሕይወት ያጠፋ፡ በሰፊው ሕዝብ ደም የተጠመቀ፡ ባሁኑ ፋሽስታዊ ህግ ያልተደሰተውንና ያላጐበደደለትን ማናቸውም ሰው እንዳሰኘው ይዞ ለስት ወር ለማርና ጊዜውንም ለሌላ ስት ወር ለማራዘም ይችላል። ሶስት ሶስት ወር እያለ፣ ጊዜው በላቸው እስከአሰኘው ድረስ ሊራዘም ይችላል፣ ምንም ገደብ የለውም።

እኔ አንተ እርሱ ወይም እርስዎ ለአገርግዛት ሚኒስትሩ ወይም ለፀጥታው ክፍል ሹም ወይም ለፖሊሱ አዛዥ ያላስደሰትን እንደሆነ፡ የእነርሱን ኘሮፖጋንዳ እንደገደል ማሚቶ ያላስተጋባን እንደሆነ፡ እውነተኛ የአገር ፍቅር ስሜት ያሳየን እንደሆነ ተይዘን ከማጐሪያው ውስጥ ልንጣል እንችላለን። የሶስቱን ወር ስቃይ ከጨረስን በኋላ ሌላ ሶስት ወር ሊጨመርብን ይችላል፣ እንዲህ እያለም ይቀጥላል። ላመል ለቀቅ አድርጐ እንደገና እዚያው ሊመልሰን ይችላል። ይህ ብቻ አይደለም፣ ወደፍርድ ቤት ለመቅረብ አንችልም፣ ለሌላ ባለስልጣን ለማመልከት፡ አቤት ብለን ጉዳዩ እንዲታይልን ለማስደረግ ፍፁም አንችልም። የጠበቃ፣ የፍርድ ቤት መቅረብ፣ የይግባኝ፣ የአቤቱታ፣ ያለንበትን ስፍራ ወይም ሁኔታችንን ለቤተሰባችን የማሳወቅና የስንቅና የጥየቃ መብታችን ሁሉ ተደምስሷል። ሚኒስትሩና ቡችሎቹ ከሰውነት ውጭ አድርገው ሊጫወቱብን ይችላሉ።የነሂትለር የነሞሶሊኒና የነቮርሽተር ፋሽስታዊ ህግ እንደዚህ ነው። የነመንግሥቱ ኃይለማርያም /አዲሱ ኃይለሥላሴ/ የነበላቸው ጀማነህ /የጌስታፖው አለቃ ሂምለር/ የሥራ ውጤት እንደዚህ ያለ ነው።

3. በሰፊው ሕዝብ ዘንድ የፈጠረው ስሜት፡-

በአጠቃላይ ሕዝቡ በእንደዚህ አይነት ስሜት ተቀበለው ለማለት ጊዜው ገና ነው፣ ህሊና ቢስና ገለባ እንደሆኑት ጋዜጠኞቻችን ‘በፈገግታና በደስታ’ ተቀበለው አንልም። ባድርባይነታቸው፣ በጭራቆይነታቸው፣ በእስስትነታቸው የታወቁት፣ ስልጣን ላይ ለወጣ ሁሉ እንደስናር በቅሎ የሚሰገሩት ጋዜጠኞቻችን ከሚያቀርቡት ፍፁም ሃሰትና ፍሬቢስ አስተያየት የእኛው መቶ በመቶ ይለያል። ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሲታገልለት የቆየውን መብቱንና ነፃነቱን የሚገፍፈውን ፋሽስታዊ ህግ ‘እልል ብሎ ይቀበላል’ አንልም፣ እንዲያውም በሃዘንና በቁጣ እንደሚመለከተው አንጠራጠርም። እስቲ ለመሆኑ አጥናፍሰገድ የሚባለው እልም ያለ ቀጣፊ ርካሽ አድርባይ ስለፋሽስታዊው ህግ አቀባበል በ14/3/67 በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ርእሰአንቀጽ ውስጥ ያሰፈረውን እንመልከት።

‘የኢትዮጵያ ጊዚያዊ ወታደራዊ መንግሥት በቅርቡ ካከናወናቸው ብሄራዊ ተግባራት መካከል ‘ልዩ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ’ አዋጅ ከቀሩት ይልቅ ጉላት ነበረው፣ አዋጁ በሕዝብ ዘንድ የመነጋገሪያ ርእስ ሆኗል፣ ፈላጊውም በመብዛቱ አዋጁ የወጣበት ነጋሪት ጋዜጣ 55 ሳንቲም ብቻ መሸጥ ሲገባው እስከአንድ ብር አውጥቷል፣ ታትሞ የነበረው ቅጂ በሙሉ በአራት ሰአት ጊዜ ውስጥ ተሾጦ አልቋል’ ይለናል። ይህ እንኳን ማጋነን እንጂ ብዙ ክፋት ያለው አይመስልም። አዲሱን ልዩ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ በሽሚያ ገዝተው ካነበቡት መካከል እናቱን እንደተረዳ ሰው የደነገጡ እንደነበረና አብዛኛውን ሕዝብ ግን ‘ይሁን እሰይ ይሁን’ ብሎ እንደተቀበለው ጋዜጠኛ ይነግረናል። ከቢሮው ሳይወጣ አብዛኛው ሕዝብ እንዴት እንዳገኘው መጠየቅ ተገቢ ቢሆንም የአብዛኛው ሕዝብ እሰይታ ሲነግረን ደግሞ የእጥናፍሰገድን ህሊናቢስ ቀጣፊነት በደንብ እናየዋለን።

እንደነዚህ አይነት እስስቶች የሚኖሩት ለሆዳቸው ብቻ ነው። ትሞታለህ፣ ትታሰራለህ፣ ትቀጣለህ፣ ባሪያ ትሆናለህ፣ ነፃነትህንና መብትህን ትነጥቀሀል፣ ተረግጠህ ለጥሰጥ ብለህ መገዛት አለብህ፣ ወዘተ… ሲባል እሰይ ብሎ የሚቀበል ሰው ከወዴት ይገኛል? እንዴት ሊኖር ይችላል? ይህን የመሰለ እልም ያለ ውሸት ለመቀባጠርና ለመፍጠር የሚሽቀዳደሙት ለፍርፋሪ የተሸጡት ህሊናቢሶች ብቻ ናቸው።

አብዛኛው ሕዝብ በእርግጥ እንዴት እንደተቀበለው ለመናገር አንችልም፣ ፈጥረው ለፈርፋሪ መለመኛ ከሚቀባጥሩት በስተቀር ይህንን በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ለመናገር የሚችል ያለ አይመስለንም። ስለሆነም ሰፊው ሕዝብ በቁጣ፣ በድንጋጤ፣ በብስጭት፣ በመማረር፣ በትካዜ፣ በሃዘን፣ ሊቀበለው እንደሚችል ለመገመት ይቻላል። በራዲዩና በቴሌቪዥን ከተነገረ በኋላ የሰው አቀባበል እንደዚያ ነበረ። ወዳጅ መስሎ ጠላት በወረወረው ጦር ጀርባውን እንደተወጋ ሰው እንደሚሰማው አይጠረጠርም። ሌላ አይነት ስሜት ሊኖረው የሚችል ደንቆሮ ደደብ፡ የሰውነት ባህርዩ የሞተና ለገንዘብ የተሸጠ ሆድ አምላኩ ብቻ ነው ብለን እንገምታለን። አፍህን ትለጉማለህ፣ እግርና እጅህን ትታሰራለህ፣ ትገረፋለህ፣ ትገደላለህ፣ ወዘተ. ሲባል ትበላለህ፣ ትሾማለት፣ ትሸለማለህ ወዘተ… የተባለውን ያህል የሚደሰት ሰው የለምና ነው።

4. ወርቅ ላበደረ ጠጠር

ምን በበደለ ነው የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ በዚህ በፋሽስታዊ ህግ እንዲጠፈር ፣የሰራው መጥፎ ነገር፡ ወንጀሉ ምንድነው? ምን በወጣው፡ ምን በገደደ ይህ መአት ይደርስበታል? የኃይለሥላሴን የጭቆናና የብዝበዛ አልጋ አነቃንቆ መሪነቱንንና የመንግሥቱን ስልጣን ለባለመዮው ስለአስረከበ በዚህ በፋሽስታዊ ህግ መሰንከል ይገባዋል ወይ? ይህማ ባጐረስኩ ተነከስኩ መሆኑ አይደለም?

ባለፈው የካቲት የፈነዳውና አሁንም በመቀጠል ላይ ያለው ሕዝባዊው የትግል እንቅስቃሴ ለአያሌ ዘመናት ውስጥ ውስጡን ሲብላላና ብልጭ ድርግም ሲል የቆየ ነው። በመደብ በተከፋፈለ በማናቸውም ህብረተሰብ ውስጥ በጨቋኝና በተጨቋኝ በበዝባዥና በተበዝባዥ መካከል የሚካሄደው የትግል እንቅስቃሴ በኢትዮጵያም ሲካሄድ ለመቆየቱ አንድና ሁለት የለውም።

ባለፈው የካቲት ይህ ትግል ሲፈነዳና ቋያው ሃገሪቷን ከዳር እስከዳር ሲያጥለቀልቃት የሰፊው ጭቁንና ተበዝባዥ ሕዝብ ወገንና ፍላጭ ቁራጭ የሆነው ወታደርም በትግሉ ውስጥ ተሰለፈ ካንዴ ሁለቴ ወጣ ገባ ቢልም የሰፊው ተመዝባዥ ሕዝብ ትግል ሊገታ ባለመቻሉና እየገፋ በመምጣቱ ዋና ዋናዎቹ ግፈኞች ከነአለቃቸው ከስልጣን እንዲወገዱ ተደረገ። ይህ በሰፊው ሕዝብና በወታደሩ በህብረት የተካሄደ ትግል ሲሆን ዋናው አንቀሳቃሽ ሕዝቡ ነው።

ተራማጅ የሰፊው ሕዝብ ወገኖችም በግንባር ቀደምነት ከወታደሩ ጐን ሆነው፡ እጅ ለእጅ ተያይዘው አይዞህ አለንልህ፡ በዚህ በኩል በለው፣ ይህንን ለጊዜው አትንካው፣ የሚያዋጣው መንገድ ይህ ነው፣ ይህን አስቀድ፣ ያንን አስከትል ወዘተ. እየተባባሉ የትግሉን አቅጣጫ ሲያመክቱ አብረው መጡ። ከመስከረም ሁለት በኋላ አንዳንድ ሴረኞችና ስልጣን ጠማሾች ወታደራዊ መንግሥት አቋቁመው ስልጣን ቢይዙም ነገሩ እንደማያዋጣና አሁን ባለንበት የታሪክ ወቅት፡ ሕዝቡ ዴሞክራሲ በሚጠይቅበት ጊዜ ወታደራዊ መንግሥት ማቋቋሙ ትክክል አለመሆኑን፣ ሕዝቡም ለብዙ ዘመናት አፍኖ ከያዘው ልጓም ተላቅቆ በትክክል ፍላጐቱን ለመግለጥ መብቱና ነፃነቱ እንዲመለስለት፣ የተያዘውም አቅጣጫ በጣም አደገኛ፡ ምርጫውም ስህተተኛ ስለሆነ እንዲለወጥ ከመወትወትና አስተያየታቸውን ከመሰንዘር አልተቆጠቡም።

ለዚህ ጥረታቸው፡ ለዚህ ትግላቸው የተሰጠው መልስ ሌላ ነው፣ የውጭ እጅ፡ የጠላት መሳሪያ፡ የቀድሞዎቹ ባለስልጣኖች ቅሬቶች፡ የኃይለሥላሴ ርዝራዦች፡ አድሃሪዎች ወዘተ. ተባሉ። እነዚህን ማጥፋት ነው፣ ያለማወላወል ከባድ እርምጃ ልንወስድባቸው ያስፈልጋል የሚል ዛቻ፡ ማስፈራራት ማጥላላትና ስም ማጥፋት ብቻ ነበር መልሳቸዉ። ሰፊው ሕዝብ ግን በዚህ በጥቂት ሴረኞች ተንኮል አልተወናበደም፣ አልደነገጠም፣ በሚችለውና በሚመቸው መንገድ ትግሉን በመቀጠል ላይ ነው። ተራማጆችም ከሰፊው ሕዝብ ጐን በመሰለፍ ትግሉን በማንቀሳቀስ ላይ ናቸው። ይህን እስከምን ጊዜም ቢሆን ይቀጥላሉ፣ ከቶ አንዲት ስንዝር እንኳን ወደኋላ አይሉም።

ታዲያ የሚገርመው ሰፊው ሕዝብ የባላባታዊውን ሥርዓተማህበር ለብዙ ዘመናት ሲቋቋመው ቆይቶ ባለፈው የካቲት ከስሩ አነቃንቆት ስልጣኑን ከሰፊው ወታደር ጋር ለመያዝ ሲዘጋጅ ከመገለሉም በላይ ስንት ሬሳ ቀብሮ፡ አጥንቱን ከስክሶ፡ ደሙን አፍስሶ እዚህ ከደረሰ በኋላ ይህን በመሰለ ፋሽስታዊ ህግ መተብተቡ ነው። ነገሩ ወርቅ ላባደረ ጠጠር፡ እህል ላበደረ አፈር እንደመመለስ ነው። ፋሽስታዊ ህግ መታወጅ የክህደት መጨረሻ፡ይህ ነው የማይባል ስግብግብነትና ራስ ወዳድነት ነው። ስለሆነም ትግሉን ከማፋፋም በስተቀር ከቶ አያቆመውም።

5. ጭቆናንና ብዝበዛን የማስወገድ መብት፡-

ሰው የተፈጠረው ወይም ባለው መልክ ወደዚህ ዓለም የመጣው በነፃነት ነው፣ ያለአንዳች የጭቆና ሰንሰለት ሙሉ ነፃ ሆኖ ነው የተወለደው፣ ጥቂት የህብረተሰቡ ክፍሎች የሚጭኑበትን የጭቆና ቀንበር መቋቋም፡ ሰባብሮ ማስወገድ ዋና መብቱ ነው።

ይህ መሰረታዊ መብት በሰለጠኑት አገሮችና በተበባበሩት መንግሥታት የሰው ልጅ መሰረታዊያን መብቶች ውስጥ በደንብ ተመልክቷል። ማንም ሰው ወይም ሕዝብ በገዥዎቹ የሚደረግበትን ጭቆናና ብዝበዛ መቃወምና መቋቋም፡ ታግሎ አንኮታኩቶ መጣል ይችላል።

ከዚህ በላይ ከፍ ብሎ የተመለከተውን ፋሺስታዊ የህግ ቀንበር አልቀበልም፣ አልሸከምም፣ እምቢ አሻፈረኝ አልጨቆንም፣ በማለት መቋቋም የእኛ መብትና ግዴታም ጭምር ነው። ይህ የታወቀና የተረጋገጠ ሰብአዊ መብታችን እንደመሆኑ የማስከበሩና ሥራ ላይ የሚዋሉ ጉዳይ የእኛ ተግባር ነው። በጥቂቶቹ ሴረኞች የሚመራ ወታደራዊ መንግሥት የፈለገውን ሊያደርገን፣ እንደእቃ ወዲያ ወዲህ ሊያዞረን፣ እንደከብት ያሻውን ሊጭነን ወደፈለገው አቅጣጫ ሊወስደን፣ ወይም ሊመራን እንዴት ይቻለዋል? ሰብአዊ መብታችን በመግፈፍ ከሰውነት ውጭ ወደ ቁሳቁስነትና ወደ እንስሳት ደረጃ ሲለውጠን ሲነሳ በአንድነት ተነስተን መቋቋሙና ሁኔታውን መለወጡ የእኛ ቀዳማይ ግዴታ ነው።

የጭቆናንና የብዝበዛን ቀንበር የመቋቋምና የማስወገድ መብት ከሰው ልጅ ተፈጥሮ ጋር የተያያዘና በዓለም መንግሥታትም ዘንድ በደንብ ታውቆ የተከበረ ነው፣ ይህ መብት ከሰውነት ጋር የተያያዘና የማይለይ ነው። ከዚሁ ጋር የተሳሰሩትና ከእርሱ የሚመነጩ ሌሎች መሰረታዊ ሰብአዊ መብቶች እንደአሉ የታወቀ ነው። አብዛኛው የሚፈልገውን መንግሥት ማቋቋምና የመንግሥቱ በሕዝብ ቁጥጥር ስር መሆን፡ የንግግር፣ የጽሁፍ፣ የማህበር፣ ሥራ የማግኘት፣ የደህንነት፣ ወዘተ… መብቶችና ነፃነቶች እንደዚሁም ሌሎች አሉ። እነዚህን መሰረታዊ መብቶች የሚገፍፍ፣ የሚደመሰስ፣ የሚቀንስ የሚያሳጣ፣ አምባገነን ሲነሳ በኃይል መቋቋምና ማስወገድ ታላቅ ክብር ያለው ድርጊት ነው።

በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ከዚህ በላይ ከፍ ብለን እንዳመለከትነው ፋሽስታዊ የመንግሥት ሥርዓቶች በዚች አለማችን በየጊዜው ብቅ ብቅ ብለዋል። እነቤንቶ ሙሶሎኒ፣ እነአዶልፍ ሂትለር፣ እነሳላዛር፣ አሁንም ደግሞ እነቮርሸተርና እነስሚዝ ፋሺዝምን ለማንገስ፡ የሕዝቡን መብቶች ለመደምሰስና ባምባገነንነት አንሰራፍቶ ለመግዛት ተነስተው ነበር። መጨረሻቸው ግን ምን እንደሆነና ምን ሊሆንም እንደሚችል አስቀድሞ የታወቀ ነው። የሰፊው ሕዝብ ኃይል ደምስሶ ከታሪክ ቆሻሻ ስር ቀብሯዋል፣ የቀሩትንም ይቀብራቸዋል፣ ስፍራቸው እዚያ ነውና። የእኛዎቹም ፋሽስቶች ከዚያ እንደማያመልጡ ሳይታለም የተፈታ ነው። የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ይህን ታሪካዊ ግዴታውን ለማስወረድ ትግሉን በማፋፋም ላይ መሆኑ አይነተኛው የጊዜው ሁኔታ ነው።

6. የሰፊው ሕዝብ የትግል እንቅስቃሴ አግጣጫ፡-

ባለፈው ቁጥር ጋዜጣችን /14/ እንደተመለከተው የሰፊው ሕዝብ ትግል በገጠርና በከተማ በመፋፋም ላይ ነው። የትግሉ እንቅስቃሴ ወደከፍተኛ ደረጃ፡ ወደአዲስ ምዕራፍ በመሸጋገር ላይ ነው።

በገጠር ጭሰኛው ገበሬ፡ መሬት ላራሹን በመከተል ባለመሬቱን ዞር በል፡ ላንተ እርቦ ሲሶ እኩል ማፍሰስ ቀርቷል፣ መሬቱ ያራሹ ነው፣ የገበሬ ላብ ፍሬ መበዝበዝ ቀርቷል፣ኃይለሥላሴ ባላባታዊ ሥርዓት ጋር ወድሟል፣ አልቋል ደቋል ተቀብሯል፣ እርምህን አላወጣህ እንደሆነ ይኸውልህ ተረዳው፣ ሁለተኛ እዚህ እንዳትደርስ፣ ግንኙነታችን በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ይሁን እንጂ የጭሰኛና የባለመሬት፣ የበላይና የበታች ግንኙነት ከዛሬ ወዲያ እንድንቀጥል አንሻም። ወዳጄ፡ ይህን ከተቀበልክ መልካም፡ ያለበለዚያ ደማችን ይፈስሳል እንጂ አንዲት ቁና አንዲት ሳንቲም አታገኝም። ጭሰኛው ይህንንና የመሳሰሉትን በማለት የሚያርሰውን መሬት እጁ አግብቶ በብዙ ስፍራ የመሬቱ ባለቤት ሆኗል።

ባለመሬትም፡ ክንዴን ሳልንተራስ መሬቴን ማንም ሊነጥቀኝ አይችልም፣ መሬቴን አስረክቤ ነገ አፈር ገፊ፣ ተራ ገበሬ ልሆን፣ በሬ ጠምጄ ላርስ፣ ላርም ላጭድ ልውቃ ላግዝ! ይህንንስ ለጠላቴም አያድርገው! መቼ ለዚህ ተፈጠርኩና! ይህ ከመድረሱ በፊት ሞቼ መቀበሩ ይሻለኛል ወዘተ… በማለት በበኩሉ ይበሳጫል፣ ይደነፋል፣ ይፎክራል፣ ይዘጋጃል።

ጭሰኛና ባለመሬት የእርስበርስ የመደብ ጦርነት ከጀመሩ ቆይተዋል፣ ጦርነቱ እየከረረና እያደገ በመሄድ ላይ ነው። ሁለቱም ቅርሳቸውን መሳሪያ በመግዛት ያጣራሉ። መሳሪያውም በዚሁ ምክንያት ያለመጠን እየተወደደ በመሄድ ላይ ነው። ከዓመት በፊት አምስትና ስድስት መቶ ብር ያወጣ የነበረው ጓንዴ /ዴሞትፎር/ ዛሬ ከሁለት ሺ ብር በላይ ማውጣቱ በይፋ ይነገራል፣ እነኤምዋንማ አይነሱ! ነገሩ ይህ ብቻ አይደለም። ልዩ ልዩ መሳሪያዎች ዛሬ ከውጭ አገር በመግባት ላይ ናቸው። ይህም ሆኖ የሕዝቡን ፍላጐት አላረካውም፣ ገበያው በኃይል ደርቷል። ይህ ሁሉ ዝግጅት በመቀጣጠል ላይ ላለው የመደብ ጦርነት መሆኑ አንድና ሁለት ያለው አይመስለንም።

ባለፈው ሳምንት እንዳመለከትነውም የተማሪዎችና የምሁራን በሰፊው ሕዝብ ትግል ውስጥ በቀጥታ ለመሳተፍ ወደገጠር መሄድ ከዚህ በላይ የተገለጠውንም በጭሰኛና በባለብዙ መሬቶች መካከል በመካሄድ ላይ ያለውን ጦርነት ወደከፍተኛ ደረጃ በመለወጥ ላይ ነው። ይህ ዛሬ በሰሜን፣ በምሥራቅ፣ በደቡብ፣ በምእራብ በሁሉም ስፍራ በተለያዩ ደረጃዎችና መልኮች በመሄድ ላይ ነው።

በጥቂት ‘ምርጥ’ መኮንኖች የሚመራው ወታደራዊ መንግሥት የተወናበደና የተመሰቃቀለ ፋሽስታዊ ድንብርብርና በደርጉ ውስጥ ያለው የእርስበርስ መብላላት ለሁኔታው እየተባባሰና እየተፋፈመ መሄድ ዋና ምክንያት ነው ለማለት ያስደፍራል።ለዚህ ሁሉ ኃላፊና ተጠያቂዎቹ በስልጣን ኮርቻ ላይ ሆነው የሚያወናብዱት ጥቂት ዳተኛ መኮንኖችና አጫፋሪዎቻቸው ናቸው። የከተማውንም ሕዝብ በፋሽስታዊ ህጋቸውና ድብደባቸው ጭጭ ለማድረግ የሚያደርጉት ሙከራ ከምንም ሊያደርሳቸው እንደማይችል እሙን ነው። በዚህ አቅጣጫ በእጣ ምስቅልቅል ድርጊታቸው አንድ እውነት ነገር ቢኖር የገዛ መቃብራቸውን የሚቆፍሩ መሆናቸው ነው። ሠራተኛ፣ ነጋዴ፣ ባለእጅ፣ ወታደር፣ መመህር፣ ተማሪ፣ ምሁር፣ ሥራአጥ፣ እነዚህ ሁሉ ከተሜዎችም የሕዝባዊውን ትግል እንቅስቃሴ በልዩ ልዩ ዘዴና መልክ ወደፊት ከማራመድ አልቦዘኑም፣ ትግላቸውን በመጠቀልና በማፋፋም ላይ ናቸው። ሁኔታው በሚፈቅድለት መልክና ሥርዓት ትግሉ ወደፊት ከመራመድ ጋብ አላለም፣ አይልምም።

በአገሪትዋ በመላ የትግሉ ቋያ በኃይል መንደድ ጀምሯል፣ በከተማም በገጠርም የመደብ ጦርነት በመፋፋም ላይ ነው። ሰፊው ሕዝብ በቆራጥነት ትግሉን ከዚህ ላይ ሲያደርሰው፣ ትግሉም ነገድና ብሄር ሳይለይ የመደብን አንድነት አጉልቶ ሲያመለክት በድርጅት በኩል ወደኋላ የቀረ መሆኑ አያከራክርም። ሰፊው ሕዝብ አጠቃላይና ጠንካራ የትግል ድርጅት ገና አልፈጠረም። በየአቅጣጫው የሚካሄደውን የመደብ ጦርነት መልክ የሚያስይዝና የሚያቀናብር፡ ስልቱንና ዘዴውን የሚቀይስና ወደአዲሱ አይነት የሰፊው ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ መንግሥት የሚመራ ጠንካራና አጠቃላይ የትግል ድርጅት ከማናቸውም ጊዜ ይበልጥ ዛሬ አስፈላጊ ነው።

ከትግሉ ቋያ ውስጥ ገብቶ የተማገደው ሰፊ ሕዝብ ዛሬ ዋናው ጥሪው፡ ድርጅት፣ ጠንካራ ድርጅት፣ ሁሉን የሚያጠቃልል ሰፊ ዲሞክራሲያዊ ሪቮሉሽናዊ ድርጅት ነው። ይህ ጥሪ ለማን ነው? ሰፊው ሕዝብ የድርጅት ያለህ፣ የጠንካራ አጠቃላይ የትግል ድርጅት ያለህ እያለ የሚጮኸው ለማነው? ይህ ጥሪ በመጀመሪያ የሚመለከተው ቀደም ብለው የሰፊውን ሕዝብ ወገን በመምረጥ በትግሉ ሜዳ የገቡትን ተራማጆች ነው። የእነዚህ የሕዝብ ወገን ተራማጆች ታሪካዊ ተግባር ባሁኑ ወቅት ሰፊው ሕዝብ የሚጮኸለትን፡ የሚወተውትለትን ጠንካራና አጠቃላይ ሰፊ ሪቮሉሽናዊ ድርጅት መፍጠርና ትግሉን ወደድል መመራት ነው። ይህ ነው የጊዜው አቢይ ጥሪ።

አወናባጆቹና አጭበርባሪዎቹ እፍኝ የማይሞሉት ሴረኛ መኮንኖች በሰፊው ሕዝብ ጫንቃ ላይ ቀንበራቸውን የመጫንና በስልጣን ላይ ለመቆየት የሚያደርጉትንም ፋሽስታዊ ጥረት ለማክሸፍና ስልጣኑን ለባለቤቱ ለሰፊው ሕዝብ ለመመለስ የሚቻለው በመደራጀትና ትግሉን በቆራጥነት ወደፊት በመምራት ነው።

ድርጅት ኃይል ነው እየተባለ ብዙ ጊዜ መወሳቱ ብቻ በቂ አይደለም። ድርጅት ኃይል መሆኑ በብዙ አገሮች በተግባር የታየ በሥራ ላይ የዋለ ቅንጣት ያህል እንኳ የማያጠራጥር እውነት ነው። ሰፊው ሕዝብ የሚጮህለትን ጠንካራና አጠቃላይ የትግል ድርጅት ቶሎ ብሎ መፍጠር በግብር ማሳየት ያስፈልጋል። የሰፊውን ሕዝብ ጥሪ መመለሻ ሰዓት አሁን ነው። ምንም አይነት ሌላ ምርጫ ባሁኑ ጊዜ የለንም። ታሪካዊ ግዴታችንንም ቶሎ ብለን ካልተቀበልንና ካልፈፀምን፡ ከእጅ አይሻል ዶማ፡የአፍ እንጂ የተግባር ሰዎች አለመሆናችንን አስመስክረን ከታሪክ ቆሻሻዎች ጋር አብረን ከመቃጠል አናመልጥም። ይህን ጥሪ ልብ አድርገን ተገንዝበን በፍጥነት እንድንመልሰው ያስፈልጋል።

ላዲሱ ዲሞክራሲያዊ መንግሥት እንደርጅ፣
ሰፊውን ሕዝብ እናደራጅ፣ አጠቃላይና ጠንካራ
ሰፊ የትግል ድርጅት ለመመስረት ቆርጠን እንነሳ።
ድሉ የሰፊው ሕዝብ ነው።
Scroll to Top