የሰፊው ሕዝብ ድምፅ
ልዩ እትም፣ ሐምሌ 25፣ 1970
የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ
ይህ ልዩ እትም “መኢሶን ከሞቃዲሾ ምን ይላል” በሚል ርዕስ የመኢሶን አመራር ከሆኑት ከአቶ እሸቱ ቡሊ ጋር የተደረገ ውይይት ነው ተብሎ አብዮታዊት ኢትዮጵያ መጽሔት ላይ የወጣውን ጽሁፍ ይተቻል። አቶ እሸቱ አራርሶ የሰጠውን ቃለ መጠይቅ በተመለከተ መኢሶን አቶ እሸቱን ሶማልያ እንዳላከና ቃለ መጠይቅ እንዲሰጥ ያለማዘዙን ስለሆነም የአቶ እሸቱ አስተያየት የራሱ የግለሰቡ አስተያየት እንጂ የመኢሶን እንዳልሆነ ይናገራል። በዚህም አጋጣሚ መኢሶን በሶማልያ ወረራና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ያሉት አቋሞቹ በድርጅቱ ልሳን በሆነው “በሰፊው ሕዝብ ድምጽ” ላይ የሰፈሩ መሆናቸውን ያስታውሳል።
የመላ ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራም ባንዲራ ስር ተሰልፎ የሚዋደቅ አብዮታዊ ድርጅት ነው። ይህንን ፕሮግራም ከግቡ ለማድረስ የኢትዮጵያ ጭቁን ሕዝቦች በተያያዙት እጅግ የተወሳሰበና አስቸጋሪ የሆነ ትግል ውስጥ አነስተኛም ቢሆን በብዙ ታጋይ አባሎቹና ደጋፊዎቹ መስዕዋትነት አስተዋጽኦ አድርጓል። ይህንን ፕሮግራም ከግቡ ለማድረስ አስፈላጊና ጊዜያዊ የሆኑ ተግባሮችን በየወቅቱ እየጠቆመ የትግሉን ፋና በግንባር ቀደምነት ለታጋዩ ሕዝብ በማሳየት ሲታገል ቆይቷል፣ አሁንም እየታገለ ነው። ይሄንን ደግሞ ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዳር እስከዳር ያውቀዋል።
መኢሶን በየጊዜው የሚወስዳቸው አብዮታዊ አቋሞች ሃቀኛና የሰፊው ሕዝብ አቋሞች ስለሆኑ እነዚህን ፊት ለፊት ተጋፍጦ ማጋለጥ አይቻልም። ስለሆነም ዛሬ ብቻ ሳይሆን ከኢሕአፓ “ገናናነት” ዘመን አንስቶ ፀረ ሕዝብ ኃይሎች መኢሶንን “ለመወንጀል” የጣሩት ይህ ንቅናቄ አቋሜ ብሎ በሚያስተጋባቸው ነጥቦች ላይ ሳይሆን እነሱ ራሳቸው ከሚፈጥሩለት አቋሞች እየተነሱ እንደሆነ ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ በሙሉ የሚያውቀው ሃቅ ነው።
በተለይ ከአንድ ዓመት ወዲህ ከተንሸራታች ኃይሎች ጋር አብሮ መንጎድን አሻፈረኝ ብሎ አሁንም ከሰፊው ሕዝብ ጎን በብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራም ጎዳና ላይ ፀንቶ ለመቆም የትግል ስልት ለውጥ ካደረገ ወዲህ ንቅናቄያችን ባነሳቸው የአብዮቱ አንገብጋቢ ጥያቄዎች ሳይሆን በፈጠራ “አቋሞች” መወንጀል የተለመደ ሆኗል። ይህ ራሱ ከብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራም በመንሸራተት ላይ የሚገኙ ኃይሎች በድርጅታችን አብዮታዊ አቋም ላይ ተችተው ሰፊውን ሕዝብ ለማሳመን የማይችሉ መሆናቸውን ያመኑበት ድርጊት ስለሆነ መኢሶን አይደናገጥበትም።
እንደእውነቱ ከሆነ በአብዮታችንም ሆነ በአገራችን ብሄራዊ ነፃነትና ክብር ጥያቄዎች ላይ መኢሶን የሚታገልለትንና ስፍር ቁጥር የሌላቸው አባላቱና ደጋፊዎቹ በደማቸው የፃፉትን አቋም ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠንቅቆ እንደሚያውቀው አንጠራጠርም። ነገሩ እንደዚህ ሆኖ ሳለ ፀረ ሕዝብ ኃይሎች በመኢሶን ላይ የሚያደርጉትን የሃሰትና የሸር ቅስቀሳዎች ሁሉ ለማስተባበል አንድ ዝክረ ነገር መጻፍ ያስፈልጋል። ባጭሩ በዛሬ ጊዜ በኢትዮጵያ ምድር ላይ የደርግ የተሳሳተ ፖለቲካ በሚያደርሰው የኢኮኖሚና የፖለቲካ ውድቀትና ችግር ሁሉ መኢሶንን ተጠያቂ ለማድረግ የማይነገር ነገር የለም። እህል ሲጠፋ “ቀኝ መንገደኛው” መኢሶን ይባላል። ጨው ሲጠፋ “ቀኝ መንገደኛው” መኢሶን ይባላል። ዳቦ ሰልፍ ሰራዘም “ቀኝ መንገደኛው” መኢሶን ይባላል። ትራንስፖርቱ ሲተራመስ “ቀኝ መንገደኛው” መኢሶን ይባላል። አንዲት የዲሞክራሲ ጥያቄ ስትቀርብ “ቀኝ መንገደኛው” መኢሶን ይባላል። “ካድሬው” ጠቅላላ ትርምስንና የጭፍጨፋ ስራዎቹን ሲፈፅም “ቀኝ መንገደኛው” መኢሶን ይባላል። ውሃ ሲቆም፣ መብራት ሲጠፋ፣ ቤንዚን ሲቆም፣ ቢራው ሲያልቅ፣ መረታት ሲመጣ፣ መሸነፍ ሲደርስ፣ እምነት ሲጠፋ፣ ማጣፊያው ሲያጥር. . . ሁሉኑም ነገር በመኢሶን ላይ መለጠፍ ተብሎ የተወሰነ ይመስላል። “ፈርጥጧል” “አልቆለታል” የተባለው መኢሶን “ያልተሰገሰገበት” ሕዝባዊ ድርጅት፣ የማይገኝበት የሕብረተሰብ ክፍል፣ በኢትዮጵያ ምድር ታየ የማይባልበት ሽኩቻ ጠፍቷል ማለት ይቻላል! በዚህ አይነት የዝናቡን ቧንቧ የሚዘጋውና የሚከፍተው “ቀኝ መንገደኛው” መኢሶን ነው። በሰሜንና በምስራቅ ኢትዮጵያ የተነሳውን የአንበጣ መንጋ የፈለፈለው መኢሶን ነው ቢባል ከንግዲህ ብዙም የሚገርም አለ ብለን አንገምትም።
ይህንን መግለጫ ለመስጠት ያነሳሳን በሐምሌ 15 ቀን በወጣው “አብዮታዊ ኢትዮጵያ ጋዜጣ” ላይ “መኢሶን ከሞቃዲሾ ምን ይላል?” በሚል ርዕስ ቀርቦልን ያነበብነው ጽሑፍ ነው። እንደእውነቱ ከሆነ ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ በአድሃሪው የሞቃዲሾ መንግሥት በአገራችን ላይ በተሰነዘረው ወረራ መኢሶን የወሰደውን አብዮታዊና አገር ወዳድ አቋም የሚያውቀው ስለሆነ እንዲህ አይነቱን ፍሬከርስኪ ማስተባበልን ባላስፈለገ ነበር። ነገር ግን “የአብዮታዊት ኢትዮጵያ ጋዜጣ” አዘጋጆች አቀራረብ ብዙ አገር ወዳጆቹን ከጥርጣሬ ላይ የሚጥል መስሎ ስለታየን ባጭሩም ቢሆን ለማስተባበል ተገደናል።
የ“አብዮታዊት ኢትዮጵያ” ጽሑፍ መነሻ የሆነው አንድ አቶ እሸቱ ቡሊ የተባለ ግለሰብ በሱማሊያ ሬዲዮ ጣብያ የሰጠው “ቃለ መጠይቅ” ነው። ምንም እንኳን “በቃለ መጠይቁ” ውስጥ ስለድርጅታችን የምታወሳ አንዲት ቃል እንኳን ባትገኝም የአብዮታዊት ኢትዮጵያ አዘጋጆች “አቶ እሸቱ ቡሊ የመኢሶን መሪ ከሆኑት አንድ መሆኑን” ላንባቢያን ካረጋገጡ በኋላ አቶ እሸቱ ቡሊ የሰጠውን “ቃለ መጠይቅ” የመኢሶን አቋም በማስመሰል የጽሑፋቸውን አርዕስት “መኢሶን ከሞቃዲሾ ምን ይላል?” ብለውታል።
ሃቁ ምንድነው? እሸቱ አራርሶ የመኢሶን አባል የነበረ ግለሰብ ነው። መኢሶን ግን “እሸቱ አራርሶ የመኢሶን መሪ ከሆኑት አንዱ መሆኑን” አያውቅም። ይሁንናም መኢሶን እሸቱ አራርሶ ወደ ሱማሌ እንዲሄድ ትእዛዝ አልሰጠውም። በሱማሌ ሬዲዮ በመኢሶን ስም ቃለ መጠይቅ እንዲሰጥ አላዘዘውም። እሸቱ አራርሶ ለሰጠው “ቃለመጠይቅ” በፍጹም ተጠያቂ አይደለም። መኢሶን እሸቱ አራርሶ የወሰደውን እርምጃ በአንድ ግለሰብ የተወሰደ የግለሰብ እርምጃ አድርጎ ይቆጥረዋል። ስለሆነም “መኢሶን ከሞቃድሾ ምን ይላል?” ብለው የአብዮታዊት ኢትዮጵያ አዘጋጆች ለጠየቁት መልሱ በጣም አጭር ነው። መኢሶን ከሞቃዲሾ ምንም አይልም!
“አቶ እሸቱ ቡሊ” ከሞቃዲሾ ያለውን እንተውና መኢሶን ከኢትዮጵያ ምን ይላል ለሚለው ጥያቄም መልሳችን ግልፅና ማንም የሚያውቀው ነው። መኢሶን የሚለው ሁሉ የመኢሶን ልሳን በሆነው የሰፊው ሕዝብ ድምጽ ላይ ሰፍሮ ይገኛል። ሌላው ቀርቶ በዚህ በአድሃሪው የሱማሌ ወረራ ጉዳይ መኢሶን አቋሞቹን በተደጋጋሚ አስታውቋል። አሁን በመጨረሻም በሰሕድ ቀ.66ና ለኢማሌድህ በተፃፈ ግልጽ ደብዳቤ የማያሻማ አቋሙን ገልጿል። ይህ አቋም ደግሞ እንደዚሁ ለይስሙላ የሚወረወር ላለመሆኑ በመኢሶን ባንዲራ ስር ተሰልፈው በየእለቱ የሚወድቁት ጓዶችቻን ህያው ምስክሮች ናቸው። በነዚህ ታጋይ ኢትዮጵያውያን ደም በኢትዮጵያ ምድር ላይ የሚፈፀመው የመኢሶን አቋም የሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ አቋም በመሆኑ አደርባዮቹ “የአብዮታዊት ኢትዮጵያ” አዘጋጆች ፊት ለፊት ተከራክረው ሊረቱት የሚችሉት አቋም አይደለም። ስለሆነም ይህ ሲያልቅባቸው ደግሞ ሌላ ብዙ አሳፋሪና ርካሽ “ክሶችን” ከመሰንዘር እንደማይመለሱ ሳይታለም የተፈታ ነው። ነገር ግን እንዲህ አይነቱ “የክርክር ስልት” ለኢህአፓ እንዳላዋጣው ሁሉ ለእነዚህኞቹም እንደማይበጅ አስመሳዮችና አደርባዮች ዞሮ ዞሮ መውደቂያቸው የታሪክ ትቢያ መጣያ ቅርጫት እነደሆነ ይኽም ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው።