የሰፊው ሕዝብ ድምፅ
ቁጥር 49፣ ጥር 22፣ 1969
የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ
መኢሶን በዚህ የሰፊው ሕዝብ ድምፅ እትሙ፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮት በውጭ ከበባና በውስጥ ቡርቦራ ከፍተኛ አደጋ ላይ እንደሚገኝ ያመለክታል። በአንድ በኩል የጎረቤትና የአካባቢ አገሮች በአሜሪካን ኢምፔሪያሊስቶች እየተደገፉ የኢትዮጵያን ሕዝቦች ትግል ለመቅጨትና ብሄራዊ ህልውናዋን ለመድፈር ይጣጣራሉ። በሌላ በኩል፣ በአብዮታዊ ለውጥ ምክንያት የፖለቲካ ስልጣናቸውና የኢኮኖሚ ጥቅሞቻቸውን የተቀሙ አድሃሪ ኃይሎች ከውስጥ ቅልበሳ ለማካሄድ እንደሚታገሉ በማሳየት የአደጋውን አሳሳቢነት ያብራራል።
የኢትዮጵያ ጭቁን ሕዝቦች የአዲስ ሕይወት ተስፋቸውን ያንጠለጠሉበት፣ ለብዙ ዓመታት በትግልና በመከራ ከዚህ ከፍተኛ ደረጃ ያደረሱት አብዮታቸው ከውስጥ እየተቦረቦረ ከውጭ እየተከበበ ሊቀለበስ ከፍተኛ አደጋ ላይ ይገኛል። ዛሬ ከመቼውም የበለጠ ጭቁኖች በአብዮታቸው ላይ የሚያንዣብበውን የተቀነባበረ ሴራ ተረድተው እጅግ መራራ ለሆነው የትግል ጊዜ መሰናዳትና ከአሁኑም በትግሉ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ መሳተፍ ይኖርባቸዋል።
ዛሬ የኢትዮጵያ አብዮት ከዳር እስከዳር የተከበበ አብዮት ነው። ከሚያዋስኑን መንግሥታት አንዱም ቢሆን፣ አብዮታዊ የሆነች ኢትዮጵያ እንድትመሠረት አይፈልግም። እስካሁን ድረስ በተለያዩ ምክንያቶች የኢትዮጵያን አብዮት ከየአቅጣጫው ለማዳከም ይሞክሩ የነበሩት አድሃሪ የጎረቤት መንግሥታት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይህም ፀረ-አብዮት ሴራቸውን ከሁለት አቅጣጫ በማስተባበር ላይ ናቸው። የመጀመሪያው የውጭ ኃይሎች በዙሪያችንና በአለም አቀፍ ደረጃ የሚያደርጉት የትግል ማቀነባር ነው። 2ኛው ደግሞ እነዚህ ተቀነባብረው የከበቡንን አድሃሪ ኃይሎች አብዮታችን ከውስጥ ሆነው ከሚቦረቡሩ አድሃሪ ኢትዮጵያውያን ጋር የሚያደርጉት ትብብር ነው።
እስከዛሬ ድረስ የአካባቢው አድሀሪ ኃይሎች በአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም አስተባባሪነት ፀረ ኢትዮጵያ አብዮት ፕሮፖጋንዳ በየፊናቸው ሲያካሂዱ እንደነበረ የካርቱም፣ የሳውዲ አረቢያ፣ የሰሜን የመን ጋዜጦች በየጊዜው የሚያወጧቸውን ፅሑፎች ገለጥ አድርጎ ማየት ብቻ ይበቃል። አሁን ግን ሁኔታውን አዲስ የሚያደርገው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሃገራችንን የአካበቢውን ፀጥታ ለመንሳት በወረራ ዝግጅት ላይ ያለች ጠበኛ አገር አድርጐ ለማቅረብ የሚደረገው ሙከራ ነው። የሰሜን የመን ጋዜጦች ባለፈው ሰሞን “የኢትዮጵያ አውሮኘላኖች ግዛቴን ይሰልላሉ፣ መንደሮቼን ይደበድባሉ፣ ይህንን የመሰለ ወረራ ለመቋቋም ብቻዬን ስለማልችል የአረብ ሊግ አገሮች እንድትተባበሩኝ እየጠይቃለሁ” በማለት በይፋ ተናግረዋል። ፀረ ኰሙኒስቱ ኑሜራ በኢትዮጵያ ወሰን ላይ መጥቶ ባደረገው ንግግር “ከዚህ ወሰን ባሻገር ኢትዮጵያ፣ ሊቢያና ሌሎች ኰሙኒስት ኃይሎች ሊወሩን በመዘጋጀት ላይ ስለሆኑ ተጠንቀቁ” ብሎ ከማወጁም በላይ ይህንን “ወረራ” ለመቋቋም የአረብ ሊግን እርዳታ ጠይቋል። በኢትዮጵያ አሳቦ እራሱ የሚያዘጋጅልን ወረራ በግድ በሱዳን ወታደሮች መሆን እንደማያስፈልገውና እንደ ኢድህ፣ ኢህአፓና ኢኤልኤፍ ዓይነቶቹ “ተባባሪ ኢትዮጵያውያን” እንዳሉ ስለሚያውቀው “በሱዳን ካሉት 100.000 አስታጥቄ እልካለሁ” በማለት ዛቻውን አሰምቷል። የሳውዲ አረቢያ ነገስታት አብዮቱ ፈር ከያዘበት ጊዜ አንስተው እስካሁን ድረስ እነአሰፋ ወሰንን፣ እነመንገሻን፣ እነአሊ ሚራህን. . . በሚሊዩን የሚቆጠር ገንዘብ እያፈሰሱላቸው ሊያስተባብሩዋቸውና ሊያጠናክሯቸው ይሞክራሉ። የኤርትራ ግንባሮችን፣ በተለይ ፀረ ኰሚኒስቱን ኢኤልኤፍ በገፍ ይረዳሉ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነቅቶበት በግልጽ ከነሲአይኤ ጋር የቆመውን ኢህአፓንም “ማስተባበር” አስፈላጊ ሆኖ ስላዩት የዚህ አድሃሪ መንግሥት የስለላ ሹም ቱርኪ አቢን አብዱልአዚዝ እነዚህን የደርግ ተቃዋሚዎች “ለማስተባበር” ባለፉት ጥቂት ቀናት ብቻ ሁለት ጊዜ ካርቱም መጥቶ እንደነበረ ታውቋል። “ተራማጇ” ሱማሌ ከአባባቢው ጭቁን ሕዝቦች የተሟላ ነፃነት ይልቅ የራሷ አድሃሪ የማስፋፋት ፓሊሲ በልጦባት የኢትዮጵያ አብዮት ሲከበብ በሚፈጥረው ግርግር ለመጠቀም ሰርጐ ገቦችን እያስታጠቀች ወደ ኢትዮጵያ ትልካለች። ከቅርብ ጊዜ ወዲህም እዚህ ፀረ አብዮት ቅንብር ውስጥ በይፋ በመግባት ምክትል ኘሬዚዳንቱ ባለፈው ሳምንት “ኢትዮጵያ የአረቦችን ጥቅም ትፃረራለች” በማለት በይፋ መናገሩ በኢትዮጵያ አብዮት ላይ አድሃሪ አረብ ሀገሮችን ትብብር የሚጠራ መሆኑ ግልጽ ነው። የእንግሊዝና የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም መሳሪያ የሆነው የኬኒያ ገዥ መደብ በበኩሉ ውስጥ ውስጡን ሴራ ከሚሸረብበት ደረጃ አልፈው ዛሬ በግልፅ እንደነ ሱዳን እነ ኢዲዩ ጦር የሚያለማምዱበትና የሚያሰለጥኑበት መድረክ ሆኗል። እነዚህ ሁሉ የአካባቢው አድሃሪ ኃይሎች በአብዮታዊት ኢትዮጵያ ላይ የሚጠነስሱት ሴራ ፀረ አብዮት ስለሆነ በአገርውስጥ ያሉ ፀረ አብዮት ኃይሎች ይተባበሩበታል።
ኢዲዩ፣ ኢህአፓና ኢኤልኤፍ በእነዚህ አገሮች ሁሉ ከአድሃሪዎቹ መንግሥታት ጋር የሚያገናኟቸውና ፀረ አብዮት ሴራዎችን የሚያካሄዱባቸው ቢሮዎች አሏቸው። የኢትዮጵያን አብዮት ለመቀልበስ ከኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ የትጥቅም ሆነ የገንዘብ እርዳታ እንደማያገኙ ያውቁታል። በዚሁ አንፃር ደግሞ አገርም ተሸጦም ቢሆን ወገንም ተሸጦ ቢሆን ፀረ አብዮት ትግላቸው ይጠይቃልና የገንዘብ፣ የመሣሪያ፣ የፖለቲካና የዲፕሎማሲ እርዳታ ከእነዚህ አድሃሪ መንግሥታት እንዲሠጣቸው በእለት በእለት ታማኝነታቸውን ለማረጋገጥ ይገደዳሉ። ስለሆነም የአካባቢው አድሃሪ መንግሥታት በአገራችን ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት በቅድሚያ የኢትዮጵያን አብዮት ማንቋሸሽና ይቺን ሀገር እንደ ጠበኛ፣ እንደ ወራሪ አድርገው እንዲያቀርቡ ስለሚያዟቸው ፀረ ኢትዮጵያ ለሆነው ፕሮፖጋንዳ በባዕዳን እጅ ሲሆን የሚያጠራጥር በኢትዮጵያውያን አፍ ሲሆን ግን ይበልጥ ተቀባይነት የሚኖረው ስለሚመስላቸው በተለይ ኢዲዩና ኢሀፓ ለዚሁ ግብ ያገለግሏቸዋል። በዚህ በኩል የኢዲዩ እና የኢህአፓ አቋም ምንድነው?
ዛሬ አድሃሪ የአካባቢያችን መንግሥታት የተለቀቁበትን፣ ኢትዮጵያን የአካባቢው በጥባጭና ወራሪ አድርጎ የሚያቀርበውን ፕሮፖጋንዳ ኢዲዩ እና ኢህአፓ የጀመሩት ገና እነዚህን አገሮች ደጅ ጠኚ በነበሩበት ወቅት ነው።
“ኢዲዩ አድቮኬት” የተባለው የመሳፍንቱ ጋዜጣ ከብዙ ወራት በፊት አካባቢውን ሳልበጠብጥ በታማኝነትና በሰላም ልኖር የምችል እኔ ነኝ እንጂ አብዮታዊት ኢትዮጵያ የአካባቢውን ሰላም የምታደፈርስ ነች በሚል መንፈስ ሃገራችንን አንዱንም የጎረቤት ሀገር ሳትተው ከሁሉም ጋር ጠብ እያጫረች መሆኗን እያተተ እንደሚከተለው ፅፏል።
“በዚህ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ለብዙ ዘመናት የሰላምና የእርጋታ ኃይል የነበረችው ኢትዮጵያ ዛሬ ከጎረቤቶቿ ጋር ጠብ መጫርን ሥራዬ ብላ የያዘች ይመስላል። ልምድ የሌላቸውንና እርጋታን የማያውቋት የኢትዮጵያ ገዢዎች የአካባውን ሰላም ለማደፍረስ ከጎረቤቶቻቸው ጋር ጠብ እየጫሩ ናቸው። ለዚህም መቸስ ከሁሉ አስገራሚ የሆነው ማስረጃ በሀምሌ ወር የሱዳኑን ፕሬዝዳንት ለመገልበጥ በተደረገው ሙከራ ኢትዮጵያ የተጫወተችው ሚና ሆኖ እናገኘዋለን።. . .
በአዲስ አበባና በሞቃዲሾ መሐል ያለውን ግንኑኝነት ብንወስድ ደርጉ በሱማሌ ጠረፍ ላይ በሚያደርገው የጠብ መቆስቆሻ እንቅስቃሴና፣ ያሉትን ችግሮች ለማባባስ በሚሰነዝራቸው አጉል ደፋር የሆኑ እርምጃዎች የተነሳ እንደ ድሮው የተበላሹ ናቸው።. . .
ደርጉ በሚያደርግባቸው መሰረተ ቢስና መጠን የሳተ ፕሮፓጋንዳ የተነሳ ከቀይ ባህር ባሻገር ያላችው የሳውዲ አረቢያ ሕዝቦች እጅግ የመረረ ጥላቻ አሳድረዋል።….
በኬኒያ የሚገኘው ሌላ ወዳጅ የሆነ መንግሥትም በጠረፉ በስተሰሜን በሚካሄደው ማዕበል ቀን ተቀን ጭንቀቱ እየበዛ ሄዷል።. . .
ደርግ በጎረቤት ሀገሮች ላይ የሚፈጽመው ሁሉ የኢትዮጵያን ስም አጥቁሮታል።”
ባጭሩ፣ መሳፍንቱ ኢትዮጵያን አካባቢዋን የምትረብሽና ፀጥታ የምትነሳ ሀገር መሆኗን በአለም ፊት “እያረጋገጡ”፣ የአካባቢውን ፀጥታ ለማስከበር በኢትዮጵያ ላይ አንድ እርምጃ እንዲወሰድ እየጮሁና ለዚህም ተባባሪ እንደሚሆኑ ቃል እየገቡ በሚሊዮን የሚቆጠር ብር ይሰበስባሉ። ዘመቻው የተቀነባበረ ስለሆነ በነዚሁ ሀገሮች የፖለቲካ ፅ/ቤት የፖለቲካ ንግድ ቤቶች የከፈቱት እነ ኢህአፓን በዚህ ጥያቄ ላይ ከመሳፍንቱና ከነሲአይኤ ጋር የተመሳሰለ እንጂ ሌላ አቋም ሊወስዱ አይችሉም።
በኢህአፓ ነጋዴዎች አባባል ልክ ፋሽስቱ ሂትለር የጀርመንን ሕዝብ በአካባቢ ሕዝቦች ላይ ሲያስነሳ እንደነበረው፣ ደርግም የኢትዮጵያን ሕዝብ በአረቦችና በሱማሌዎች ላይ እንዲነሳና እንዲወራቸው ፕሮፖጋዳ ይነዛል። ከጥቂት ወራት በፊት ባወጡት ዲሞክራሲያ ቅፅ 2/ቁጥር 26፣ጊዜያዊ ወታራዊ አስተዳደር ደርግን ፋሺስት ከሚሉበት ምክንያት አንዱ “ይህ የምርጥ መኮንኖች መንግሥት በአክራሪ ብሄራዊ ስሜት ተገፋፍቶ ጎረቤት ሀገሮችን ለመውረር በሚያደርገው ዝግጅት’’ መሆኑን ተናግረው የዚህን ፕሮፖጋንዳ ይዘት ሲያቀርቡት እንደዚህ ብለዋል።
“እኛን ለማጥፋት በሚዶልቱ ታሪካዊ ጠላቶቻችን የተከበብን ስለሆነ ሳንቀደም መቅደም አልሞት ባይ ተጋዳይነት ይሆናል ማለት ሕዝቡን ጦር እንዲናፍቅ አይኑን ወደ ውጭ እንዲተክል ያደርጉታል።’’
የኢህአፓ ፍላጎት ከዚህ ደርግ ላይ ከለጠፈው አባባል ግልጽ ይሆናል። ደርግ ሊወራችሁ ነውና ሳይቀድማችሁ ቅደሙት፣ እኛ እንድናግዛችሁ ደግሞ ገንዘብ ስጡን የሚል ነው።የችብቸባ አቋም ነው።
መኢሶን የሰፊውን ሕዝብ ትግል በግንባር ቀደምነት ለመምራት የሚታገል ድርጅት እንደመሆኑ መጠን፣ ዛሬ ሳይሆን ከብዙ ወራት በፊት ኢዲዩና ኢህአፓ ለሚነዙት ፀረ ኢትዮጵያ ፕሮፓጋንዳ ሳይንሳዊ በሆነ ትንተና መልሶላቸው ነበር። ይህ አቋም ዛሬም ትክክል ስለሆነ በሰፊው እንጥቀሰው። ጋዜጣችን የሰፊው ሕዝብ ድምጽ የኢህአፓ ከሃዲዎች ይህንን አቋም የወሰዱት ለንግድ እንዲያመቻቸው እንጂ በሌላ ምንም ምክንያት እንዳይደለ ካስረዳ በኋላ አድሃሪዎችና የሰፊው ሕዝብ ወገኖች በአብዮታዊት እናት ሀገር ፍቅር አብረው እንደማይሄዱ ሲያስረዳ ዛሬ ማንም ኢትዮጵያዊ ግልጽ የሆነለትን ሃቅ እንደዚህ በማለት አስፍሮት ነበር።
“የከሀዲዎቹ የሃገር ፍቅር ከነአስፋወሰን የሀገር ፍቅር ጋር የተመሳሰለ ነው። የሁለቱም ፍልስፍና ‘ከሞተች ሚስቴ ምን አለኝ ካማቴ’ የሚል ስለሆነ የመደብ ጥቅማቸው ስለተነካ ‘ምን አገር አለን’ ብለው ያከትማሉ።’’
ስለሆነም፣ ሕጋዊ ቤታችንና መሬታችን ተወሰደብን ብለው በሃገራቸው ላይ ያኮረፉ ፀረ አብዮተኞች የፈለጉትን የችብቸባና የንግድ አቋም ቢወስዱም በዚህ ጉዳይ ላይ አብዮታዊያን መውሰድ ስላለባቸው አቋም መኢሶን እንደሚከተለው ጽፎ ነበር።
“አረቦች በደፈናው፣ ሶማሌዎች በደፈናው ጠላቶቻችን ናቸው አንልም። ነገር ግን ደግሞ ያለውን አንዳንድ ሃቅ አፍረጥርጦ ለመናገር የሚያስረን፣ ምንም በአድርባይነት የሚያናግረን ሁኔታ ስለሌለ ችብቸባና ንግድ የሌለበት ግልጽ አቋም እንናገር። የኢትዮጵያ አብዮት ከጐረቤት አድሃሪዎች አደጋ የለበትም ብለን ጭቁን ሕዝቦችን ለማዘናጋት አንሞክርም። አለበት። በሰፊው ሕዝብ ድምጽ ቁጥር 37 ላይ በሚገባ እንደገለጽነው አድሃሪ የአረብ መንግሥታት ከኢትዮጵያ ፀረ አብዮት ኃይሎች ጋርና ከዓለም አቀፍ ኢምፔሪያሊዝም ጋር በአብዮታችን ላይ ያሴራሉ። ለዚህ የሚገባው አጸፋ ከጐረቤት አገሮች ተራማጆች ጋር በኢንተርናሽናሊዝም መንፈስ የጠበቀ አንድነት መስርቶ አድሀሪ ኃይሎችን መቋቋም ነው። አገራችንና አብዮታችን ላይ ያለውን ይህን የጐረቤት አገሮች አድሀሪዎች ሴራ መካድ ወይም መደበቅ የደርጉን ብሄርተኛነት መቃወም ወይም ከጐረቤት አገሮች ተራማጆች ጋር መተሳሰር አይደለም። ከአድሀሪዎች ጋር ተዳብሎ፣ የኢትዮጵያን ጭቁኖች አዘናግቶ በጠላት እንዲመቱ ማድረግ ነው።”
ሰህድ ቁ.43 ሀምሌ 1968
የኢህአፓ አድሃሪዎች በዚህ መልክ “የኢትዮጵያን ጭቁኖች በማዘናጋት’’ ብቻ አልተወሰኑም። እንደ ኢዲዩ የኢትዮጵያን “አደገኛነት” ለጎረቤት አገሮች ብቻ ወስነው አላስቀሩትም። እንደ ፋሺስቷ ደቡብ አፍሪካ ለመላ አፍሪካና ለዓለም ጭቁን ሕዝቦች አደገኛ ሀገር መሆኗን ሲናገሩ በዓለም ጋዜጦች ተራማጅ መሳይ መርዞች ያስተላልፋሉ። አፍሪክ አዚ ለተባለ የሲአይኤ ጋዜጣ የኢህአፓ ተጠሪ ነኝ የሚል አንድ አድሃሪ ስለዚህ ጉዳይ የፃፈውን ብንመለከት እንዲህ ይላል።
“የኢትዮጵያ መንግሥት በአፍሪካ የኢምፔሪያሊስቶች ተገን ከመሆኑም በላይ የሚከተለው ፖለቲካ ከደቡብ አፍሪካ፣ ከሞቦቱና ከንጉስ ሀሰን ጋር አሰልፎታል።’’
ባጭሩ የአለም ጭቁን ሕዝቦች ለፋሽስቷ ደቡብ አፍሪካ፣ ለቡችላው ሞቡቱና ለአረመኔው ንጉስ ሀሰን የሚያሳዩትን ተገቢ ጥላቻና ተገቢ ተቃውሞ ወደ ኢትዮጵያ እንዲያዞሩት ይፋ የሆነ ጥሪ አድርጐላቸዋል ማለት ነው።
እንግዲህ ይህችን ሰፊ ሕዝቧ ከርሃብ፣ ከድንቁርናና ከበሽታ ተላቆ አዲስ ኑሮ ለመገንባት የሚፍጨረጨርባትን አገር አለም አቀፍ አድሃሪ ኃይሎች ከቀኝም “ከግራም’’ እየተነሱ እንዲያዋክቧት የኘሮፖጋንዳው ዘመቻ በዚህ መልክ ከቀጠለ በኋላ ዛሬ ለምናየው የደራና በአለም አቀፍ ደረጃ የሚቀነባበር ተቃውሞ በግልጽ ጥሪ ማድረግ አስፈላጊ ነበር። ይህንን የአለም አቀፍ አድሃሪ ኃይሎች በኢትዮጵያ ላይ እንዲነሱ የሚጋብዝ ጥሪ በቅርቡ ኢህአፓ በውጭ አገር መበተኑ ይታወቃል። ይህ የኢህአፓ የአለም አቀፍ ተቃውሞ ጥሪው፣ ባሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ላይ ከኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት የባሰ ዲሞክራሲ የጠፋበት አገዛዝ እንዳለ ከጠቆመ በኋላ፣ “ይህ ሁሉ ድርጊት በኢትዮጵያ ላይ የሚፈጸመው የተቀነባበረ አለም አቀፋዊ ተቃውሞ በመጥፋቱ ነው’’ ሲል ይፋ የሆነ የውጭ ወረራ ጥሪ አድርጓል። ይህን ጽሁፍ አብዮታዊው በአውሮፖ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማህበር ተቃውሞ አብዮታዊ የሆነ ትችት ያቀረበበት ሲሆን ኢዲዩ የተባለው የመሳፍንት ድርጅት ደግሞ ከአቋሙ ጋር እንደ ሁለት ጠብታ ውሀ ተመሳሳይ ሆኖ ስላገኘው ‘ኢዲዩ አድቮኬት’ በተሰኘው ጋዜጣው ቁጥር 4 ላይ እንዳለ አስፍሮ አስተጋብቶታል። ይህ ራሱ ከእንግዲህ ወዲያ ኢዲዩና ኢህአፓ የጠበቀ የአቋምና የተግባር አንድነት እንዳላቸዉ የሚያሳይ ድርጊት ነው።
ሲአይኤስ? ሲአይኤም ቅንብሩ ውስጥ አለበት። እንዲያውም የውስጥና የውጭ አድሃሪዎችን የሚያስተባብረው ኃይል እርሱ ነው። ስፔንስር የተባለው ሰላይ የኢትዮጵያን ሁኔታ በሚገባ ካጠና በኃላ ባለፈው ነሐሴ ወር ለአሜሪካ ምክር ቤት የኢትዮጵያን አብዮት ለመቀልበስ ስለሚቻልበት ሁኔታ ሀሳብ አቅርቦ ነበር። በዚህ ሀሳብ መነሾ የኢትዮጵያ መንግሥት በውስጥም በውጭም ብዙ ጠላቶች አለበትና እነሱን ማስተባበር ያስፈልጋል የሚል ነው።
“በብዙ ሌሎች ጉዳዮችም ሥራቸውን ሁሉ ሳየው ለኢትዮጵያ መጥፊያ የሚሆን ይመስለኛል። በሀገሪቱ ያሉትን የፖለቲካ ኃይሎች አብዛኞቹን አስቀይመዋል፣ ኢኮኖሚውንም አዳክመዋል በልዩ ልዩ ቡድኖች መሐል ያሉትን ጠቦች አክርረዋል፣ በክፍለ ሀገር የተመደበውን የፖለቲካ ስልጣን የባሰውን አዳክመውታል፣ ኢትዮጵያን ከሌሎች መንግሥታት ጋር ያላትን ግንኙነት አበላሽተውታል።’’
የሚል ሀሳብ ከሰነዘረ በኃላ አብዮቱን ለመቀልበስ ከውጭ በሚደረገው ሴራ ዛሬ ጎልቶ የምናየውን የፀረ ኮሚኒስቱን የኑሜሪን ግንባር ቀደም ሚና ሲናገር፣
“ሱዳን ስለ ኢትዮጵያ ባላት የፖለቲካና የጦር ሁኔታ እውቀት ለዚህ ተግባር /ለቅልበሳው ማለቱ ነው/ በጣም ጠቃሚ ልትሆን ትችላለች’’
በማለት የዛሬን የሱዳን የቀልባሾች ግንባር ቀደም ሚና ከብዙ ወራት በፊት ሲአይኤ አመልክቶ ነበር። በዚሁ ወረቀትና በተጨማሪም ሊቪን የተባለው ሌላው አሜሪካዊ ለምክር ቤቱ ባቀረበው ሃሳብ መሠረት ኢምፔሪያሊስቶች የኤርትራን መገንጠል ደግፈው እርዳታ እንዲለግሱና በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ችግር በማባባስ አብዮቱን ማንበርከክ እንደሚገባ ጠቅሰዋል። ስፔንሰር የተባለው አሜሪካዊ ሰላይ “ደርጉ በሀገሪቱ ያሉትን የፖለቲካ ኃይሎች አብዛኞቹን አስቀይሟል’’ ላለው መፍትሄም አፍሪካ ካንፊዴንሻል የተባለው የኢምፔሪያሊስት ጋዜጣ በጥቅምት ወር እትሙ “የኢትዮጵያ ችግሮች መፍትሄ የሚያኙት ኢህአፓ ስልጣን ከያዘ ብቻ ነው’’ ሲል ይህ እስኪሆን ድረስ ኢምፔሪያሊስቶች አሻጥራቸውንና የወረራ ሙከራቸውን እንደማያቆሙ በግልጽ ነግረውናል ማለት ነው።
እንግዲህ፣ የኢትዮጵያን ሁኔታ በምንመረምርበት ወቅት አብዮቱ ተከቧል ማለት ብቻ አይበቃም። ከውጭ የከበቡት አድሃሪ ኃይሎች አብዮታችንን ከውስጥ ከሚቦረብሩት ኢዲዩ፣ ኢህአፓ እና ኢኤልኤፍ ጋር እጅና ጓንት ሆነው እንደሚሰሩ ማወቅ ያስፈልጋል። ይህንን ሀቅ መዘንጋት ውጭ ውጭውን ሳናይ ከውስጥ ለሚወጉን ቀላል ኢላማ ሆኖ መገኘት ይሆናል። ገና ለገና የውጭ ግፊት መጣ ተብሎ በስመ ኢትዮጵያዊ ከኢዲዩና ከኢህአፓ ጋር ማለትም ከመሳፍንቱና ከልጆቻው ጋር የምንታረቅበት ምክንያት የለንም፣ አብዮታችንን እናስቀልብስ ካላልን በስተቀር።
ለዚህ አስጊና አስቸጋሪ ሁኔታ መኢሶን በምንም አይነት የማያወላውልና የማያሻማ መልስ አለው። ሴራው ከውስጥና ከውጪ በከፍተኛ ደረጃ የተቀነባበረ የአብዮት ቅልበሳ ሴራ ነው። ስለሆነም ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ተመልሶ እዚያ አስከፊ ሥርዓት ውስጥ እንዳይገባ የውስጥም የውጭም ጠላቶቹን መደምሰስ አለበት። በአገሪቱ ውስጥ ከኢዲዩ፣ ከኢህአፓና ከኢኤልኤፍ ጋር የሚደረገው የመደቦች ትግል መፋፋም አለበት። ይህንን የተቀነባረ ሴራ ተራማጁ የመለዮ ለባሹ ክፍል ብቻን ሊቋቋመው የማይችለው [የሚችለው] ስላይደለ ሕዝባዊ ሰራዊቱ በአስቸኳይ መታጠቅ አለበት። የኢትዮጵያን አብዮት ዳር ዳሩን የሚያዋክቡት ኃይሎች ከሁሉም በላይ ዓላማቸው በረዥም ጊዜ ጦርነት አብዮቱን ለመቀልበስ ሳይሆን ከየአቅጣጫው በማዋከብ በሚመጣው መዝረክረክ ከአዲስ አበባ ፋሺስታዊ በሆነ መፈንቅለ መንግሥት በኢዲዩና በኢህአፓ ተባባሪነት አንድ ፋሺስታዊ የሆነ ጊዚያዊ “ሕዝባዊ’’ መንግሥት አቋቁሞ የቺሊን ዓይነት ሁኔታ ባገራችንም ለመፍጠር ነው። ይህ እንዳይሆን፣ፀረ አብዮት ኃይሎችን በያሉበት ለመደምሰስና የተቀነባበረውን ሴራ ለማክሸፍ በከተማ ወዛደሩ፣ አብዮታዊው ወጣት፣ ጭቁን ሴቶችና የከተማ ነዋሪዎች ማህበራት የአብዮት ጥበቃ ኮሚቴዎች አቋቁመውና ታጥቀው ከውስጥ ሆኖ አብዮታቸውን የሚቦረቡረውን “የውስጥ አርበኛ’’ እየመነጠሩ በማውጣት ለአብዮቱ መከታ መሆን አለባቸው።
የአንድ አገር አብዮት በውስጥ አርበኞች በመቦርቦር ላይ እንዳለ የውጭ ኃይሎችን ግፊት በሚገባ ሊቋቋም አይችልም። ዛሬ የኢትዮጵያን አብዮት የሚቃወሙ ግለሰቦችና ድርጅቶች በዚህ የተቀነባበረ የአድሃሪዎች ሴራ ውስጥ ከፍተኛ ሚና ሊጫወቱ በሚችሉባቸው ቦታዎች ተሰግስገው ይገኛሉ። ቢሮክራሲው ከሞላ ጐደል በኢዲዩና በኢህአፓ እጅ እየወደቀ ነው። በአብዛኛው የማምረቻና የማከፋፈያ ድርጅቶች ውስጥ የተሰገሰጉት ሥራ አስኪያጆችና አስተዳዳሪዎች የታወቁና የወጣላቸው በአብዮቱ ላይ ያኮረፈው የንዑስ ከበርቴው ቀኝ ክንፍ ወኪሎች ናቸው። በውጭ አገር ኢትዮጵያን ከሚወክሉ የኤምባሲ ሠራተኞች ውስጥ ለሞት መድሃኒት እንኳ አንድ አብዮቱን የሚደግፍ ግለሰብ መገኘቱ ያጠራጥራል። እነዚህ ሁሉ ኃይሎች በኢኮኖሚና በፖለቲካ አሻጥር አብዮታችንን ለማዳከም ሌት ተቀን በመጣር ላይ ናቸዉ። ለሚያካሂዱት የቅልበሳ ዝግጅት ከመቸውም የበለጠ የትጥቅ ኃይላቸውን እያጠናከሩ ነው። ከዚያም አልፈው፣ የአብዮቱን ሰፈር ለማሸበር፣ ታጋዮችን እየገደሉ የአብዮቱን ኃይሎች ለማዳከም ከፍተኛ የግድያ ወንጀሎች እየፈጸሙ ነው።
ከዚህ ሁኔታ፣ አብዮታችን ውስጥ ውስጡን ተቦርቡሮ ያለምሰሶ ለመቆም የሚጣጣርን ቤት ለመምሰል ብዙም አልቀረውም። የውስጡ ሁኔታ በዚህ ላይ እንዳለ ነው። የጎረቤት አገሮች ‘ዘራፍ’ ማለትና ጠብ መጫር የጀመሩት። የውስጥ ሁኔታ እንዲህ ሆኖ ሳለ ወደ ውጭ ብቻ ማንጋጠጡ ኃይልን በከንቱ ማባከን ብቻ ሳይሆን መሃላችን ሆነው መቃብር ለሚቆፍሩልን ጠላቶቻችን ፋታና ጊዜ መስጠት ነው። የውስጥ አድሃሪዎችን በሚገባ ከመነጠርን፣ አብዮታችንን ከውጪ ጠላቶች ለመከላከል ብቁ እንሆናለን፣ እነሱንም አብዮታችንን ለመቀልበስ የሚጠቀሙበትን ዋና መሳሪያ እናሳጣቸዋለን። የውጭ አድሃሪዎች ላይ ብቻ አፍጠን የውስጥ ጠላቶቻችንን ለአንድ አፍታ እነኳን የዘነጋን እንደሆነ ግን፣ በባከነ ጉልበት የውጭውን ለመከላከል ስንሯሯጥ የውስጥ ጠላቶቻችን አብዮታችንን ምሰው ይቀብሩልናል፣ የውጭውንም ጠላት ላንመክት በውስጥ አድሃሪዎች እንሸነፋለን። ይህንን ሃቅ በመረዳት መኢሶን ለተራማጆች ሁሉ የሚያቀርበው ጥሪ አለው።
አብዮታችን ከውጪ ተካቧል፣ ከወስጥም ተቦርቡሯል። የውጪ ኃይሎችን በሚገባ ለመቋቋምና አብዮታችንን ከቅልበሳ ለማዳን፣ አድነንም ወደ አዲሲቷ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ለመገስገስ ዛሬ ነገ ሳንል ከማሃከላችን የሚትረመሰመሱትን የውስጥ ጠላቶች ለማጥፋት እንነሳ!!
የውስጥ አድሃሪዎች ስልጣንና መብታቸውን በውዴታ አስረክበው የማያውቁትን ያህል የጎረቤት አድሃሪ ኃይሎችም አንድ የተጨቆነች አገር ነፃነቷን ለመቀዳጀት ስትታገል በዝምታ ተመልክተው አያውቁም። አዲሲቷ ሩስያ ስትቋቋም፣ የሩስያ ገዢ መደቦች በከፍተኛ መፍጨርጨር ላይ በሚገኙበት ወቅት አሥራ አራት አድሃሪ መንግሥታት ይህችን በመራራ ትግል ከባርነት የተላቀቀች አገር ወረው ነበር። ይህ ወረራ ለነፃነትና ለእኩልነት በተነሱት የሩሲያ ጭቁኖች ድል አድራጊነት አከተመ። የኢትዮጵያ ጭቁኖች፣ አብዮታቸው ዛሬ ያለበትን ሁኔታ ተረድተው የውስጥ ጠላቶችን በመደምሰስ ከውጭ የሚመጣባቸውን ጠላት ለመቋቋም እንደ አንድ ሰው በተነሱ የሩሲያ ጭቁኖችን የመሰለ ድል የማይጎናፀፉበት ምንም ምክንያት የለም። በተራማጅ ኃይሎችና በሰፊው ሕዝብ ተገቢውን ዝግጅት ከተደረገ፣ ሺህ አድሃሪ ቢከበን በከፍተኛ መስዋዕትነት እዚህ የደረሰውን አብዮታችንን ሊቀለብስ አይችልም።