የሰፊው ሕዝብ ድምፅ
ቁጥር 64፣ ህዳር 7፣ 1970
የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ
በዚህ እትም መኢሶን፣ በየጊዜው በየቦታው የሚወረወሩ መፈክሮችን ብዛት አንስቶ መፈክሮች በተግባር እስካልዋሉ ድረስ በአብዮቱ ጎራ ውስጥ ያለ ብቻ ሳይሆን አድርባዩና ቢሮክራሲውም ጭምር ሊያስተጋባቸው እንደሚችል ይጠቁማል። በዚህ ረገድ አዳዲስ መፈክሮች በየጊዜው ከማውጣት ይልቅ ፣ ያሉትን መፈክሮች በስራ የማዋልን አስፈላጊነትን ጠቅሶ፣ ጥቂት ግንባር ቀደሞች ብቻቸውን ምንም የረባ ስራ መስራት ስለማይችሉ ሀቀኛ የተራማጆች ሕብረት መመስረትን አስፈላጊነት ያብራራል። ለዚህም መሠረቱ የትግል መሣሪያ የሆነው የዴሞክራሲያዊ መብቶች መለቀቅና እሱንም ተጠቅሞ የአድሃሪያንን ሴራ መቋቋም ሲቻል እንደሆነ ይተነትናል።
መግቢያ
አንዳንድ ጊዜ የሚታዘብ ሰው በእውነቱ እንደ ኢትዮጵያ አብዮት በመፈክር ብዛት የታደለ አብዮት አለ ለማለት ያስቸግረዋል። በየጊዜውና በየወቅቱ የተራማጆችን ተግባር የሚጠቁሙ መፈክሮች አይውጡ ለማለት አይደለም። መውጣት አለባቸው። ነገር ግን ብዙውን ጊዜ እንደምናየው አንዳንድ መፈክሮች ከመጠን በላይ ተደራራቢ ናቸው። ያ ቀደም ተብሎ የተነገበው መፈክር በሃቅ በስራ ላይ ቢውል ኖሮ ይህናው አዲሱና ተደራቢው መፈክር እስከዚህም ባላስፈለገ ነበር።
ለነገሩማ “ለነቃ፣ ለተደራጀና ለታጠቀ ሕዝብ አመጽ” ሲባል ይህን መፈክር የሚያስተጋባው ሁሉ ለዚህ አላማ በሀቅ ቢቆም ኖሮ እኛም ከስንት “መርሃ ግብርና” “ድርጊት ፕሮግራም” ተርፈን አብዮታችንም ስንት ወደፊት በተራመደ ነበር። ለምሳሌ በዚህ ጥያቄ ላይ ጠቅላላው የኢትዮጵያ ተራማጆች የተስማሙበት የብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራም “ሰፊው ሕዝብ በፍጥነት እንዲነቃ፣ እንዲደራጅ እና እንዲታጠቅ” “ዴሞክራሲያዊ መብቶች ያለገደብ በአጣዳፊ እንዲታወቅለት ማስፈለጉን ቁልጭ አድርጎ ይገልፃል። ይህ ከተባለ በኋላ በዚህ በዴሞክራሲ መብቶች ጥያቄ ላይ አይናችን ስንት መፈክሮች አሳየን?! ጆሯችን ስንት መፈክሮች አሰማን?
“ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለጭቁኖች ያለ ገደብ” ተባለ። ሁሉም ከሰፊው ሕዝብ መስሎ አብሮ አስተጋባ። ዝም ዝም ሲባል ጊዜ ሰፊው ሕዝብ ቀጠለና “ዴሞክራሲያዊ መብቶች ለጭቁኖች ያለገደብ ባስቸኳይ” በማለት አስተጋባ እና ይህ ጥያቄ “አጣዳፊ መሆኑን እንደገና አስታወሰ። አብዮታዊውም፣ አድርባዩም፣ ምኑም ከሰፊው ሕዝብ ተደባልቆ ደለቀ። አብዮታችን እየገፋ መጥቶ አጣዳፊ በኋላም በአስቸኳይ አጣዳፊ የተባለለት የዲሞክራሲያዊ ጥያቄ የውኃ ሽታ ሲሆንና ይህ ጥያቄ ለአብዮታዊት እናት አገራችን ህልውና የሞት ሽረት ጥያቄ እየሆነ ሲመጣ “ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለጭቁኖች ያለ ገደብ አሁኑኑ” ተባለ።ሰፊው ሕዝብና ወገኖቹ በዚህ መፈክር የአብዮቱን ሰንደቅና ለብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራም የተሰውትን ጓደኞች ሁሉ አርማ አንስተው አሁንም ወደፊት ቀጠሉ። ሳያስበው እጢው ዱብ ያለበት አስመሳዩና የቀኝ አድርባይ ሁላ ሁላ ምላሱ ይያዝበት ጀመር። መንሸራተት መጣ። አንዳንዱ ጨርሶ ያልተነሳና የማያከራከር ጉዳይ እያነሳ ከገዛ ከጥለው ጋር የመረረ ፍልምያ በመግጠም ካች አምና የተዘጋ ክርክር ፋይል እያነሳ “ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለጭቁኖች” ቢባል ይሻላል “ያለገደብ” የሚለው አሻሚ ነው በማለት ዲሞክራሲ መቼ? በሚለው ጥያቄ ላይ ከተነሳው ክርክር በተራ አፈጮሌነት ለማምለጥ ያልተሳካ የመሸሽ ሙከራ አደረገ። ሌላው አድርባይና የታሪክ አተላ በተያያዘው ክርክር ውስጥ ራሱንም ሳያጋለጥ አብዮታዊውንም አቋም ሳይዝ እንዲሁ በንዑስ ከበርቴ ብልጣ ብልጥነት ለማምለጥ “ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለጭቁኖች ያለ ገደብ በትግል” የሚል በሳይንሳዊ ጥልቀቱ ጨርሶ ወደር የማይገኝለት በብልጣብልጥነት ሙከራው ግን መደዴ የሆነ አዲስ “መፈክር” ይዞ ብቅ አለ። እኛ የኢትዮጵያ ጭቁኖችና ታጋይ ሕዝቦች ሳንሰዋ፣ ፍዳ ሳናይ እንኳን ዲሞክራሲን ያህል ቁም ነገር ቀርቶ ከጠላቶቻችን ስሙኒ አግኝተን እናውቅ ይመስል!!
የሆነ ሆኖ የዲሞክራሲ መብቶችን ጥያቄ መቃወም ማለት ዞሮ ዞሮ “የነቃ፣የተደራጀ…” የሚለውን የሰፊውን ሕዝብ የትግል አርማ መክዳት መሆኑን የተረዳው አድርባይ ሁሉ ፈስ ያለበት ዝላይ አይችልም እንዲሉ ማንም ሳይጠይቀው “አለሁ አልከዳሁም” እያለ መናዘዝ ተገደደ። መፈክር ያልተቸገረው የኢትዮጵያ አብዮት አድርባዮች በዚህ በቀውጢ ጊዜ የሚጠበቅባቸውን አስተዋጽኦ በማድረግ “ዛሬም ለነቃ ለተደራጀ….” ብለው በመፈከር በዚህ አንጋፋ መፈክር ላይ ጨርሶ ያልታሰበ ቅጥያ በመቀጣጠል ክህደታቸውን ለመሸፈን ያልተሳካ ሙከራ አደረጉ።
እንግዲህ መፈክር በመፈክር ላይ እየተደራረበ የመጣበትን ምክንያት ለመገመት አስቸጋሪ አይመስለንም። የዚህ ምክንያቱ የመፈክሮቹ በሃቅ ከሥራ ላይ አለመዋል የፈጠረው ችግር ሲሆን የዚህ ሁኔታ ደግሞ የኢትዮጵያ አብዮት አመራር በወላዋይ ንዑስ ከበርቴ እጅ በመሆኑ እንደሆነ ግልጽ ነው። አንድ መፈክር ሲወረወር ንኡስ ከበርቴው መደብ ማርክስ እንዳለው እዚያው በዚያው “ከበርቴም የሕዝብም ሰው” ስለሆነ ያን መፈክር ቀልቦ ከሕዝብ ጋር አብሮ ያስተጋባዋል። ነገር ግን እንደሰፊው ሕዝብ በዚህ መፈክር እስከመጨረሻው አይገፋም። ህብረተሰባዊ ወኔው ቶሎ ይከዳዋል። የአብዮቱንም ሂደት አመራር እስከያዘ ድረስ ይህን መፈክር ግማሽ መንገድ ላይ ለማስቀረት እንዲችል ሰፊው ሕዝብ ለነዚህ መፈክሮች ከንኡስ በርቴው ቁጥጥር ውጭ እንዲታገል አይፈልግም። በዚህም የተነሳ ንዑስ ከበርቴው የእነዚህን መፈክሮች ከሥራ ላይ መዋል አፍኖ ይይዛል ማለት ነው።
ይህ እንግዲህ አንዳንዴ እጅግ የሚያስገርም ግን ደግሞ ከንዑስ ከበርቴው የመደብ ጥቅም አንጻር ሲታይ ሙሉ በሙሉ “ሎጂክ” የተከተለ ሁኔታ ይፈጥራል። አንድን መፈክር አብዮታዊውም፣ ለመንሸራተት የሚያደባውም ንዑስ ከበርቴ፣ የሱ ተቀጢላ አድርባይም፣ ሰፊውም ሕዝብ በአንድነት ይቀበሉና ከዳር እስከዳር ያስተጋቡታል። በመፈክሩ ላይ ጠቅላላ (ስምምነት) ይገኛል። ይህ ከመሆኑ የተነሳ ለምሳሌ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ “ቢሮክራሲ ይውደም” “ዲሞክራሲ ለጭቆናዎች”… የሚሉትን መፈክሮች ኢትዮጵያ ውስጥ ማን እንደሚቃወማቸው በእርግጥ የሚታወቅ ነገር አልነበረም ለማለት ይቻላል። አብዮት አደባባይ ላይ ሁሉም ይህን መፈክር ሲያስተጋባ ከሊቀመንበሩ አንስቶ በደርግ አባሎች አልፎ እስከ ሰፊው ሕዝብ ድረስ ይህ መፈክር ተቀባይነትን ሲያገኝ ታዲያ ዴሞክራሲን የሚቃወመው ማነው? ታዲያ ቢሮክራሲን እሹሩሩ የሚለው ማነው? መፈክሩ ካላከራከረ ለምን ከሥራ ላይ አይውልም? ይባላል።
ነገሩን ልብ ላለ ሰው ግን መፈክሩ እስከዚህም አለማከራከሩ ንኡስ ከበርቴው መደብ የክርክሩን ነጥብ ከመፈክሩ ይዘት ከራሱ ዘወር አድርጎ ሥራ ላይ በሚውልበት ሁኔታ ላይ የክርክር ግንባር ለመፍጠር በመሞከሩና በዚያ ላይ በመመሸጉ መሆኑን ይረዳዋል።ንዑስ ከበርቴው መደብ ይህንን መፈክር በሰፊው ሕዝብ ተሳትፎ ሳይሆን በእኔ ቁጥጥር ስር ከሥራ ላይ አውላለሁ እያለ ለማኮላሸት ይሞክራል። ይህ የገባው ሰፊ ሕዝብ ደግሞ መፈክሮችን ከሥራ ላይ ለማዋል ያለው አንድ ቆራጥ ኃይል እሱ ብቻ መሆኑን “የነጻ ድርጊት” “የነፃ ርምጃ” ዞሮ ዞሮ ደግሞ የዲሞክራሲያዊ መብቶች ጥያቄዎችን ያቀርባል።
እንግዲህ ነገሩን ከዚህ አንፃር ከተመለከትነው የሃቀኛው የአብዮቱ ባለቤትና የአጋሮቹ ነጻ እርምጃዎችንና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ታፈነው እስከተያዙ ድረስ እንኳን ከሰፊው ሕዝብ ጀርባ ከአድሃሪው ቢሮክራሲ ጋር የሚመሳጠረው አስመሳይና አደርባይ ቀርቶ የጠነባውም ቢሮክራት ከሰፊው ሕዝብ ጋር አብዮት አደባባይ ላይ ግራ እጁን ሲያነሳ ላንቃው እስኪሰነጠቅ ድረስ “ቢሮክራው ይውደም” እያለ ቢያስተገባ ደንታ የለውም። የቢሮክራሲ መውደሚያ የሆኑትን የሕዝቡን የነጻ እርምጃና የዲሞክራሲ ጥያቄዎች አፍኖ እሰከያዘ ድረስ፣ በእነዚህ ጥያቄዎች ላይ በቀኝ አድርባዮች “ግንባር ቀደምነት” ዞሮ እስከመሸገ ድረስ አድሃሪው ቢሮክራሲ አብዮት አደባባይ ላይ የሕዝብ ወገንነቱንእያስመሰከረ ቤቱ ተመልሶ እንቅልፉን መለጠጥ ይችላል። ብቻ ዲሞክራሲና የነጻ እርምጃ ጥያቄ አይነሳ!
ከዲሞክራሲያዊ መብቶች ጥያቄ በስተቀር ዛሬ ከሰማይ በታች የሚወረወሩ መፈክሮች ሁሉ ብዙም አከራካሪ የማይሆት ለዚህ ነው እንላለን። ዛሬ ይህንን ሀቅ የተገነዘበው መፈክሮች ማስተጋባት የሰለቸዉ ሰፊ ሕዝብ የመፈክሮች መፈክር አውጥቶ “መፈክሮች በተግባር ይተርጎሙ” እያለ ማስተጋባት የጀመረበት ወቅት ነው። ስለዚህም መፈክሮችን እያነሱ መሃል መንገድ ለመበተን በሚፍጨረጨሩ አድሃሪዎችና የቀኝ አድርባዮች በአንድ በኩል ከሰፊው ሕዝብ ተዋህደው መፈክሮችን በእርግጥ በተግባር ለመተርጎም በሚታገሉ አብዮታዊያን በሌላ በኩል የዲሞክራሲ መብቶች ጥያቄ እጅግ አከራካሪ ሆኖ የሚቀርበው በዚህ የተነሳ እንደሆነ ማንም ሊረዳው ይችላል።
መኢሶንም በቅርቡ የትግል ስልት ለውጥ ያደረገው ለዘላቂው ትግል አስፈላጊውን ዝግጅት ለማድረግ የህቡዕ መዋቅሩን ለማጠናከር ብቻ ሳይሆን ዛሬ መፈክሮች በተግባር እንዲተረጎሙ ከሚሻው ከአብዮቱ ባለቤት በግንባር ቀደምነት ተዋህዶ እንጂ እንደ አድርባዮች ከሕዝብ ተደባልቆ ለማስተጋባት ብቻ ሳይሆን በተግባር ትግሉን ወደፊት ለማራመደም ነው።
ዛሬ በዚህ አላማ ተነሳስተን ለኢትዮጵያ ማርክሲስት ሌኒኒስት ድርጅቶች ለሌሎች ተራማጆችና አገር ወዳዶች ይህንን የወሬ ሳይሆን፣ የአፍ ሳይሆን፣ የወረቀት ላይ ሳይሆን፣ የትግል አንድነት ጥሪ ስናደርግ ሃሳባችን አንድ ሌላ “የድርጊት ፕሮግራም” የተባለ ተራ ዛቻ በአድርባዮቹ ላይ ሰንዝረን በኢትዮጵያ ጭቁን ሕዝቦች ትግል ለማሾፍ አይደለም። እርግጥ የምናቀርበው ምንም አዲስ መፈክር የለም። እንዲያውም ያሉትን መፈክሮች ሁሉ አናቀርባቸውም። ቁልፍ መፈክሮች ናቸው፣ለነሱ ከታገልን ሌሎችንም መፈክሮች ከሥራ ላይ ለማዋል በሩን እንከፍታለን የምንላቸው አንገባቢ መፈክሮች አሉ። አላማችን እነዚህን መፈክሮች ሰፊው ሕዝብ በሥራ ላይ እንዲያውላቸው በምን ዘዴ ተዋሐደን ልንታገል እንደምንችል አንዳንድ ተጨባጭ የትግል አቅጣጫዎችን ለመጠቆም ነው።
የምንጠቁማቸው የትግል አቅጣጫዎች ትግላችንን ወደፊት ያራምዳሉ የሚል እምነት አለን። ሌሎች ጓዶች እነዚህን የሕዝብ መፈክሮች ከሥራ ላይ ለማዋል የተሻለ አቅጣጫ አለ ካሉ ለመጠቆም፣ ይህ እኛ የምናቀርበው ደግሞ በዛ ጉድለቶች ካሏቸው እነሱን ለማሟላት በሰፊው ሕዝብ ፊት በይፋ አቋም መግለጽ አብዮታዊ ግዴታቸው ነው እንላለን። ዛሬ ይህንን የትግል አንድነት ጥሪ ስናቀርብ 1969 ዓ.ም ያወጣነው መርሐ ግብር ግሩም ነበር። ያን በሥራ ለመተርጎም ተብሎ የአጭር ጊዜ “የድርጊት ፕሮግራም” ያስፈልጋል ተብሎ የድርጊት ፕሮግራም ራሳችንን እናታልል ካላልን በስተቀር ያን የድርጊት ፕሮግራም ውሃ በልቶታል ማለት አንችልም። በድርጊት ፕሮግራማችን መሰረት “እየለየለት የመጣው የሚሊታሪ ቢሮክራሲ” እንዲመታና ተራማጅ የጦር መኮንኖች እንዲተኩ፣ በውጭ ፖለቲካ አንፃር አዳዲስ ዲፕሎማቶች እንዲተኩ…ወዘተ እያልን፣ “የተመኘነው” ሁሉ ዛሬ የት እንደደረሰ፣ ከነኢህአፓ ላይ የዛትነው ሁሉ ዛሬ ምን ያህል ከቅጥር ነፍሰ ገዳዮች ጥቃት እንደሰወረን…. በዓይናችን የምናየው ሀቅ ነው። እንዲያውም ሌሎች ቅጥር ነፍሰ ገዳዮች ተጨመሩ።
እንግዲህ ማርክሲስት ሌኒኒስት ድርጅቶችም ከጊዜ ወደጊዜ ህብረታቸውን “እያጠናከሩ” ከመርሃ ግብር ድርጊት ፕሮግራም፣ ከድርጊት ፕሮግራም ወደ “ግንባር” ሄድን ይላሉ ሰፊው ሕዝብም በሚሊዮን እየተቆጠረ አብዮታዊ መፈክሮችን ሲያስተጋባ ይታያል፣ በአጭሩ በሃገራችን ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ለአብዮቱ አመቺ ሁኔታ እያለ አብዮታችን ወደፊት መራመዱን ትቶት ለምን አድሃሪዎች አየሉ? ለምን ማርክሲስቶች የወረቀት ነበር ሆነው ይቀራሉ? ለምን የነሱ ትግል እንዲሁ በአድሃዎች ላይ በመዛት ብቻ ይወጣለታል? ይህ የሚሆንበት ምክንያት ግልጽ ነው። መፈክሮችን የሚያስተጋባ ሁሉ ለነዚህ መፈክሮች ከልብ አይታገልም። ትግሉ እንዲፋፋም ሰፊው ሕዝብ በይበልጥ እንዲሳተፍበት የዲሞክራሲን ጥያቄ በግንባር ቅድምነት የሚያነሳው ወገን አለ። በሌላ በኩል ደግሞ በንኡስ ከበርቴ የሕዝብ ፍራቻና የሕዝብ ንቀት የተነሳ የሕዝቡን ተሳትፎ ለማናናቅ እንዲያውም ገፍቶ ከመጣበት ለመቃወም የማይመለሰው ወገን አለ። በዚህ ሁኔታ የድርጊት ፕሮግራም የጥቂት ቁንጮዎች እንጂ የሰፊው ሕዝብ ስለማይሆኑ ከሥራ ላይ ሊውሉ አይችሉም። በአብዮቱ ፍላጎት ከሚነዳው ሰፊ ሕዝብ አንጻር ግንባር ቀደም ነን የሚሉት ኃይሎች ተጎታችነት፣ ማመንታት፣ ማወላወል፣ ለጊዜው ኃያል በሚመስሉ ኢምንት አድሃሪች ፊት መርበድበድና አድርባይ መሆን ያመጣሉ። የዚያን ያህል ፀረ አብዮቱ ፋታ ያገኘና ያይላል።በሀገራችን ዛሬ የምናየው ሁኔታ ይኸው ነው።
እንግዲህ ዛሬ “መፈክሮችን ወደ ተግባርም እንተርጉም” ብለን ለሀቀኛ ማርክስት ሉኒኒስት ድርጅቶችና ለሌሎች አብዮታዊያን የትግል አንድነት ጥሪ ስናቀርብ መፈክሮችን በተግባር ለመተርጎም ምን የትግል ዘዴ መከተል እንዳለብን ባጭሩ እንጠቁማለን። ከዚያም ቀጥለን ዛሬ ከሰፊው ሕዝብ ጋር ሆነው አብዮታዊያን ከሚሰነዝሯቸው ሌሎች መፈክሮች አራቱን መርጠን ለነሱ መታገል የሚያስችሉንን የትግል አቅጣጫዎች ለመጠቆም እንሞክራለን።
1. መፈክሮች በተግባር ይተርጎሙ
ይህንን የሰፊው ሕዝብ መፈክር ከሥራ ላይ ለማዋል ማርክሲስት ሌኒኒስትቶች የሚነሱበት መሰረታዊ ነጥብ የታሪክ ፈጣሪ ሰፊው ሕዝብ ነው የሚለው ነጥብ ነው። ግንባር ቀደም ኃይሎች ብቻቸውን ምን ያህል አብዮታዊ ቢሆኑ፣ ምን ያህል አገር ወዳድ ቢሆኑ፣ ምን ያህል ቆራጥ ቢሆኑ፣ ከሰፊው ሕዝብ ተገንጥለው ምንም ፋይዳ ያለው ነገር ሊሰሩ አይችሉም። መፈክሮችን በተግባር ለመተርጎም የታሪክ ፈጣሪ የሆነው ሰፊ ሕዝብ እንዲቀበላቸውና እንዲያዋህዳቸው ማድረግ፣ እንዲያምንባቸውና እንዲሞትላቸው ማዘጋጀት ወደ ድልም የሚወስዱትን ተጨባጭ እርምጃዎች በየጊዜው በየደረጃው በግንባር ቀደምነት ማሳየት ያስፈልጋል።
ይህንን ለማድረግ እንግዲህ በመጀመሪያ ማርክሲስት ሌኒኒስቶችና ሌሎች አብዮታዊያን ስለመፈክሮች ይዘት ለሰፊው ሕዝብ ግልጽ የሆነ ማብራሪያዎችን መስጠት፣ የነዚህ መፈክሮች ከሥራ ላይ መዋል ለሰፊው ሕዝብ አብዮት የሚያደርገውን አስተዋጽኦን ማሳየት አለባቸው።
ሁለተኛ ይህንን መፈክር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የሚቃወሙትን አድሃሪዎችና አድርባዮች ከደርግ ከራሱ አንስቶ እስከታች ድረስ ያለአንዳች አድርባይነት ማጋለጥና ሰፊው ሕዝብ አድሃሪዎችንና አድርባዮችን እንዲዋጋቸው መቀስቀስ አለባቸው። ለአብዮቱ መፈክሮች መዋጋት ማለት እነዚህን መፈክሮች የሚቃወሙትን አድሃሪዎች፣ በአፍ ተቀብለው በድርጊት የሚያደናቀፉትን አድርባዮችና አስመሳዮች ከመዋጋት ሌላ ትርጉም ሊኖረው አይችልምና።
ሦስተኛ እውነተኛ ማርክሲስት ሌኒኒስት ድርጅቶችና ሌሎች ሀቀኛ አብዮታዊያን በእርግጥ ግንባር ቀደም ነን ካሉ አንድ ሕዝብ የተቀበላቸውን መፈክሮች ከሥራ ላይ ለማዋል ስለሚቻልበት ሁኔታ ተጨባጭ ታክቲኮችና ርምጃዎችን በቅድሚያ እየጠቆሙ ትግሉን አለቋረጥ ወደፊት ለማራመድ መታገል አለባቸው። በዚህ ትግልም ውስጥ መፈክሩን በማብራራት ደረጃ፣ አድሃሪዎችንና አድርባዮን በማጋለጥ ደረጃና የተግባር ተጨባጭ አቅጣጫን በማሳት ደረጃ ትግል በሚካሄድበት ወቅት አድሃሪዎችና ከአድርባዮች በኩል በሰፊው ሕዝብና በወገኖቹ ሊሰነዘር የሚችል ጥቃት እንዳለ መገንዘብ ማንኛውንም ተፅእኖና ጥቃት በጋራ ለመቋቋም ዝግጁ ሆነው መጠበቅ አለባቸው ማለት ነው።
የኢትዮጵያ እውነተኛ ማርክሲስት ሌኒኒስት ድርጅቶችና ሌሎች አብዮታውያን መፈክሮችን በተግባር ለመተርጎም ከላይ በተጠቀሱ እጅግ ቀላል በሆኑ አቅጣጫዎች ከአድርባይነትና ከተጎታችነት ተቆጥበን ከታገልን በአንድነታችን ጎዳና ላይ ብዙ እርምጃዎችን ለመራመድ ከመቻላችንም በላይ ለኢትዮጵያ አብዮት የሚጠበቅብንን ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበረከትን ማለት ነው። በነዚህ ሦስት የትግል አቅጣጫዎች በመመራትም ለሚቀጥሉት አራት መፈክሮች እጅ ለእጅ ተያይዘን በሕብረት እንድንታገል መኢሶን አብዮታዊ ጥሪውን ያቀርባል።
2. የሀቀኛ ተራማጆችን ህብረት በተግባር ለመተርጎም
ይህ የሰፊው ሕዝብ መፈክር በተለይ የፀረ አብዮት ኃይሎች አንድነታቸውን አጠንክረው አብዮታችን ከቅልበሳ አፋፍ ላይ በሚገኝበት በአሁኑ ወቅት እጅግ አንገብጋቢ መፈክር ሆኖ እናገኘዋለን። በዚህም የተነሳ ዛሬ ከምንጊዜውም ይበልጥ የተራማጆች ህብረት ከወረቀት ወደ ተግባር ከወሬ ወደ ተጨባጭ ትግል እንዲተላለፍ የተቻለውን ሁሉ ማድረግ የእያንዳንዱ እውነተኛ ማርኪስስት ሌኒኒስት ድርጅት ተግባር ነው እንላለን።
መኢሶን ደግሞ ደጋግሞ እንዳስታወቀው ሀቀኛ የሆነ የተራማጆች ህብረት ይፈልጋል። ለሱም ከመታገል አቋርጦ የሚያውቅበት ወቅት የለም። ዛሬም ይህንን የትግል አንድነት መስርተን በትግል እሳት ውስጥ እየተፈተንን ለመተዋወቅና ለመቀራረብ የሚያስችለንን ጥሪ ለእውነተኛ ማርክሲስት ሌኒኒስት ድርጅቶችና ለሌሎች ሀቀኛ አብዮታዊያን በይፋ ሲያቀርብ በዚህ የቆየ ጥረቱ አንድ እርምጃ ወደፊት ለማድረግ በማሰብ ነው።
የተራማጆች ህብረት በተግባር የሚተረጎመው ጥቂት ግንባር ቀደሞች ብቻቸውን አንዱንም ሳይዙት ከፕሮግራም መርሃ ግብር፣ ከመርሃ ግብር ድርጊት ፕሮግራም እያሉ በመንቆራጠጥ ብቻ እንዳይደለ የእስካሁኑ ትግላችን ያስገነዘበን ሀቅ ነው። ይህ ሁሉ ሲያቅትና እንዲሁም አልጨበጥ ሲል፣ ማርክሲስት ሌኒኒስት ድርጅቶች በሀገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ላይ ምንም ፋይዳ ያለው ሚና መጫወት እያቃታቸው እያየ አሁንም ከስተታቸው ተምረው ወደ ሰፊው ሕዝብ ካልተዋሀዱና ከሰፊው ሕዝብ ተገንጥለው በጀመሩት “የግንባር ቀደም” ጉዞ ቢቀጥሉና ወደ ማርክሲስት ሌኒኒስቶች “ግንባር” “ቢጠናከሩ” በተጨባጭ መንገድ በድርጊት አንድነታቸውን በማጠናከር ላይ ባሉት አድሃሪዎች ላይ ሌላ ተራ ዛቻ መሰንዘር እንጂ ሌላ ምንም ትርጉም አይኖረውም።
ከብዙ ወራት ጀምሮ “የተራማጆች ህብረት ይጠንክር” እያለ ሲያስተጋባ የመጣው ሰፊ ሕዝብ መርሃ ግብር ካልነው በኋላ፣ የድርጊት ፕሮግራም ካልነው በኋላ፣ ዛሬ ደግሞ “ህብረት” ካልነው በኋላ “አልሰማ” ብሎ እንዲያውም “የተራማጆች ህብረት በተግባር ይተርጎም” ብሎ ማስተገባት መጀመሩ ከእስካሁኑ የአፍና የወረቀት እንጂ የድርጊት ህብረት አለመሆኑን በመረዳቱ እንደሆነ ግልጽ ነው! የኢትዮጵያ እውነተኛ ማርክሲስት ሌኒኒስት ድርጅቶች እንዲሁ ከተጨባጭና ከዕለታዊው የሰፊው ሕዝብ ትግል ተገንጥለው እስከተንሳፈፉ ድረስ ነገ ጠዋት ተነስተው “እንኳን ደስ ያለህ! ይኸው አሁንም እንደተለመደው ህብረታችን በመጠናከር ዛሬ ደግሞ ለሊቱን የወዛደር ፓርቲን መስርተንልህ አድረናል” ብለው ዱብ ዕዳ ሊያወርዱበት ይችላሉ። ሰፊው ሕዝብና አብዮታዊያን ግን ለዚያው በተግባር ለሚተረጎም የተራማጆች ህብረት መታገላቸውን፣ ለሀቀኛ የተራማጆች ህብረት ማስተጋባታቸውን ይቀጥላሉ።
ለምን? ምክንያቱም ሃቀኛ የተራማጆች ህብረት እንዲመሠረት፣ የተራማጆች ህብረት በተግባር እንዲተረጎም ከተፈለገ ማንም ቢሆን ዘሎ ሊያመልጣቸው የማይቻሉት ሳይንሳዊ ሁኔታዎች አሉና! ከነዚህ ዋና ዋናዎቹን ከሦስት ከፍለን እንጥቀሳቸው። አንደኛ ተራማጆች ህብረታቸው እንዲጠናከር በመሰረታዊ የአብዮት ጥያቄዎች ላይ ስምምነት ላይ መድረስ አለባቸው። ሁለተኛ እያንዳንዱ ድርጅት በእነዚህ መሰረታዊ ነጥቦች ላይ ተመርኩዞ አብዮቱ ለሚያቀርባቸው አንገብጋቢ ጥያቄዎች፣ ሰፊው ሕዝብ ግራ ለሚጋባባቸውና አመራር ለሚጠይቅባቸው ጥያቄዎች፣ ባጭሩ በየዕለቱ አብዮቱ ለሚያፈልቃቸው “ምን መደረግ አለበት” ለሚሉት ጥያቄዎች ግልጽ የሆነ የታክቲክ አቋሙን መጠቆምና በእርግጥ ለትግሉ አመራር ለመስጠት በግንባር ቀደምነት መቆም አለበት። ሦስተኛ እያንዳንዱ ድርጅት ይህንን ታክቲክ ይዞ መሰል ታክቲክ ካላቸው ጋር በጋራ ከሰፊው ሕዝብ ተዋህዶ መታገል፣ ሌላ ታክቲክ ካላቸው ጋር በይፋ ተከራክሮ በማመን ወይም በማሳመን የትግል አንድነትን ዲሞክራሲያዊ በሆነ ክርክርና መድረክ ለመመስረት መታገል ይኖርበታል።
ባጭሩ የተራማጆች ህብረት በአብዮቱ መሰረታዊ ጥያቄዎች ላይ በዲሞክራሲያዊ ውይይት ከሚፈልቅ የጋራ አቋም ይወለዳል። እንደዚሁ ከዲሞክራሲያዊ ውይይት በሚፈልቅ ተመሳሳይ ታክቲክ ተጨባጭነት ያገኛል። ይህንን የጋራ ታክቲክ ይዘው በሰፊው ሕዝብ ውስጥ በጋራ በመታገል በሚተዋወቁት፣ በሚቀራረቡት በጋራ ጠላት ፊት በጓድነትና በወንድማማችነት አብረው መቆምና መጋፈጥ የሚለምዱት ታጋይ አባሎች መራራ ትግል እየጠነከረና በተግባር እየተተረጎመ ይሄዳል። እንዲህ አይነቱ ህብረት የቁንጮች ብቻና የወረቀት ላይ ብቻ ሳይሆን በትግሉ ተጨባጭነትን የሚያገኝና የሚለመልም የየድርጅቱ ታጋዮች ከብረት የተጠነከረ ህብረት ነው። ሀሳባችን ከላይ አመራር አይኑር፣ ትንተና አይቅረብ መርሐግብር አይውጣ፣ የድርጊት ፕሮግራም አይነደፍ ለማለት እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ይኽ ሁሉ ተንጠልጥሎ እንዳይኖር፣ ከአፍና ከወረቀቱ እንዳያልፍ ተጨባጭ ታክቲክን በየጊዜው መጠቆሙ ላይና አባሎችን በዚህ ግልጽ ታክቲክ መሰረት ወደ ሰፊው ሕዝብ ማዋሃዱ ላይም እናተኩር ለማለት ነው።
እንግዲህ ለተራማጆች ህብረት በተግባር መተርጎም ከላይ የተጠቀስናቸው ሦስት ነጥቦች አስፈላጊ ናቸው ካልን ዛሬ በሀገራችን ከእነዚህ ሦስት ነጥቦች አንፃር ያሉትን የህብረት ጠሮች በአጭር ባጭሩ እንመልከት።
የመጀመሪያው የተራማጆች ህብረት እንቅፋት በማርክሲስት ሌኒኒስት ድርጅቶች ውስጥ የጦፈ የሰርጎ መግባት ፖለቲካ ሲያካሄዱ በከረሙ የሲ አይ ኤ ቡችሎችና አድሃሪ ቢሮክራቶች አማካኝነት ቀልባሽ ኃይሎች በመሰረታዊ ጥያቄዎች ላይ ያለውን ስምምነት ለማደፍረስ የሚያደርጉት ግፊት ነው። በዚህ በኩል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አብዮቱ መሰረታዊ ጥያቄዎች ላይ የሚታየው የአቋም መንሸራተትና ማወላወል ለተራማጆች ህብረት መሰረታዊ እንቅፋት ነው እንላለን። አብዮታችን ብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት በመሆኑ ከዚህ መሰረታዊ ጥያቄዎች አንዱ ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለጭቁኖች ያለአንዳች ገደብ አንዲታወቅ ለመታገል ሌላው ቀርቶ በብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራም ላይ እንኳን ከስምምነት ከተደረሰ በኋላ የወዛደር ሊግ መሪዎች “ዲሞክራሲ ያለገደብ” አይሆንም በማለት ከፍተኛ መንሸራተት በማሳየት ላይ ይገኛሉ። ማሌሪድ “ምን እንዳገኘው ወይንም ምን እንዳገኘ ሳይታወቅ” በአስቸኳይ የሚለውን ቃል የተቀበልኩት እነዚያ “ከይሲዎች” አወናብደውኝ ነው ወደሚለው አባባል አዘንብሏል። “በትግላችን” የሚል “ሳይንሳዊ” ግን ደግሞ ፍፁም ተራ የማወናበጃ ቃል አንግቦ በአብዮቱ አጣዳፊ ጥያቄዎች ላይ ውዥንብር መንዛትን መርጧል። የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ከግንድ ጋር እንዲታገልለት ካልፈለገ በስተቀር የዲሞክራሲ መብቶች ያለትግል እንደይገኙ መረዳቱን ዛሬ እንዳልደርሰበት ይታወቃል። ግን ይህ በማሌሪድ የሰሞኑ ቋንቋ “ገጽታና” ተጨማሪ “እምርታ” በዚህ አንገብጋቢ የአብዮቱ ጥያቄ ላይ ምን ያህል እንደተንሸራተቱ ያመለክታል። እዚህ ላይ በዝርዝር ባንገባበትም ዲሞክራሲን አፍኖ ይዞ የወዝአደር ፓርቲ ቀድሜ እመሰርታለው በማለት የዚያድ ባሬን አይነት የንዑስ ከበርቴና የቢሮክራሲውን ህብረት የሚያንጸባርቅ ቢሮክራሲያዊ ፓርቲ ለመመስረት መሯሯጥ፣ በጦርነቱ ሳቢያ ከፊውዳሊስቶች ፋሽስቶች የጦር መኮንኖችና ከአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ጋር መልሶ ለመታረቅ ዳር ዳር ማለት ወዘተ ለተራማጆች ህብረት መሰረታዊ እንቅፋት መፍጠር መሆኑ ግልጽ ነው።
ሁለተኛው ለተራማጆች ህብረት በተግባር መተርጐም እንቅፋት የሆነው በመሰረታዊ ጥያቄዎች ላይ የአቋም አንድነት ማግኘት ብቻውን አብዮቱን ያራመድ ይመስል አንገብጋቢ በሆኑ የታክቲክ ጥያቄዎች ላይ አድርባዎችና ጎታቾች የሚያሳዩት የማድፈጥ ፀባይና በነዚህ የታክቲክ ጥያቄዎች ላይ ሊኖሩ ስለሚችሉት ልዩነቶች ይፋና ዲሞክራሲያዊ ውይይት ይልቅ እነዚህ አድርባዮችና ጎታቾች ለፊውዳል አሉባልታ የሚያሳዩት ድክመት ነው።
በአንድ አብዮታዊ የትግል ወቅት ታክቲክ ስላለው ሚና ሌኒን ሲጽፍ “ያለ ታክቲክ ማቴሪያሊዝም በድን ነው” ብሏል። ይህ ችግር በሀገራችን እጅግ የተስፋፋ በመሆኑ አብዮታችን የግንባር ቀደም አመራር ችግር እንዳለበት ግልጽ ይመስላል። እርግጥ የዲሞክራሲ ያለመኖሩና ሀሳቦች በፍጥነት መንሸራሸር አለመቻላቸው ድርጅቶች ቶሎ ቶሎ ለሚለዋወጠው ሁኔታ የሚያቀርቡትን ታክቲክ ለሰፊው ሕዝብ ቶሎ ለማሳወቅ ችግር እንዳለባቸው ይገባናል። ነገር ግን እኮ “ህቡዕ” የሚከተው ዲሞክራሲ በሌለበት አካባቢ በይፋ ሊነገር የሚችለው በይፋ፣ በይፋ የማይቻለውን ለአብዮቱ እርምጃ የሚበጅ ነገር በነጻ ጋዜጣ አማካኝነት ለማሳተም እንዲቻል ነው!! በዚህ አቋምን በየጊዜው ባለመግለጽ በኩል የኢትዮጵያ ማርክሲስት ሌኒኒስቶች ሁሉ ከፍተኛ ድካም እንዳለብን መካድ ራስን ማታለል ብቻ ነው። በዚህም የተነሳ ለተራማጆች መተዋወቅና በጋራ ለመታገል ትልቅ እንቅፋት አለ እንላለን።
ይህንንም ስንል በየጊዜው በህቡዕ ጋዜጦች አቋም አለመውሰድ ለተራማጆች ህብረት እንቅፋት ሆኗል ስንል የወዛደር ሊግ መሪዎች እንደሚሞክሩት በተራ ብልጣብልጥነት ማምለጥም እንደማይቻል ግልጽ ነው። በተለይ በዚህ የተካኑት የወዛደር ሊግ መሪዎች አያደፍጡም። በየጊዜው “በህቡዕ” የድርጅታቸውን ህልውና የሚያረጋግጡ ወረቀቶች ይበተናሉ። ነገር ግን እነሆ ከሦስት አመት ጀምሮ ኢትዮጵያ አብዮታዊ ማእበል ውስጥ ገብታ እያንዳንዱ ሰዓት ለአብዮታዊያን የታክቲክ ጥያቄ እያቀረበች በምታፋጥጥበት ወቅት የወዝአደር ሊግ ይህንን ትቶ ስንት ወር ሙሉ ስለ አንድ ትሮትስኪ ስለተባለ የዛሬ አርባ አመት የሞተ የሩሲያ ፀረ አብዮተኛ ክፋትና “ጉድ” ለኢትዮጵያ ሕዝብ በተከታታይ “በህቡዕ” ይተርታል። ያ ሲያልቅበት ደግሞ ስለ እጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ እና ስለ ቅኝ አገዛዝ አመጣጥና አስተዳደግ በሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብም ሆነ በአብዮታዊያን አዕምሮ ምንም አይነት ውዥንብር እንዳይኖር ነገሩን ከመሰረቱ ልቅም አድርጎ ለማስረዳት እንደዚሁ “በህቡዕ” በተከታታይ ቁጥሮቹ ይተርታል። በእውነቱ ይህ ሁሉ ክፋት የለውም የሚያቀርቡትም ጽሁፎች በመሠረቱ ጠቃሚም ሊሆኑ ይችላሉ። ግን ቁም ነገሩ ላይ አይደለም መጀመርያ ነገር በእውነቱ እነዚህ ጽሁፎች ጠቃሚ ናቸውና በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ቢወጡስ? ሁለተኛ ነገር ደግሞ የወዛደር መሪዎች ልብ አላሉት እንደሆነ እንጂ ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ስንት ሰአት ነው ሲላቸው ሃያኛው ክፍለ ዘመን ውስጥ እንደምንገኝ እኮ ነው “እቅጩን” በመመለስ ላይ ያሉት!
እንዲህ አይነቱ ከአንገብጋቢ ጥያቄዎች ደፈጣና ሽሽት ራሱ የተራማጆችን ህብረት ለመመስረት አስቸጋሪ ሁኔታ እንደሚፈጥር ግልጽ ነው። ግን ደግሞ ግልጽ አቋምን ማሳየትና የሌሎችን አቋም ግልጽ በሆነ ዘዴ መተቸት በሌለበት ሁኔታ የአንድን ድርጅት አቋም እንዳንድ ምናልባት የዚያ ድርጅት አባላት ናቸው ተብሎ የሚጠራጠሩ ግለሰቦች ከሚሰነዝሩት ሹክሹክታ መገመት፣ ሌሎች ከሚያናፍሱት የፊውዳል አሉባልታ ቀልቦ ማስተጋባት ይመጣል። ይህ ደግሞ እንኳን ህብረትን ሊያጠናክረ ይቅርና በተራማጆች መካከል የባሰ ቅራኔና አለመግባባትን ብለሀል አላልኩም፣ አቋምህ ነው አቋሜ አይደለም የሚሉትን መወነጃጀሎች ይወልዳል። የተራማዶች ህብረት በተግባር መተርጎም የዚያኑ ያህል የውሃ ሽታ ይሆናል።
ሦስተኛው የተራማጆች ህብረት ጠር ስምምነት የተደረሰባቸውን ነጥቦች እንኳን ከሥራ ላይ ለመዋል ወደሚችለው አንድ ኃይል ወደ ሰፊው ሕዝብ የመሄድን ተግባር የመናቅና የመፍራት በሽታና ሕብረቱን በቁንጮችና በወረቀቶች ለመወሰን የሚታየው የንዑስ ከበርቴ አዝማሚያ ነው። በተለይ ንዑስ ከበርቴው መደብ በሚያሳየው የዲሞክራሲ ፍራቻ የሚተረጎመው ይህ በሽታ የመጣው ይህን የህብረተሰብ ክፍል አብዮት እና በጸረ አብዮት መካከል አንጠልጥሎ ይዞ እዚያው በዚያው “ከበርቴም የሕዝብ ሰው” ከሚያደርገው የመደብ ጀርባው እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል። ደጋግመን እንዳልነው የንጉስ ከበርቴው መደብ መፈክሮችን መቅለብና ከሕዝብ ጋር ግራ እጅን አብሮ ማንሳት፣ በየወንዙ መማማል ያበዛል። ነገር ግን ደግሞ በዚያው ልክ ሰፊው ሕዝብ ታሪካዊ ሚናውን እንዳይጫወት ተንደርድሮ በፀረዲሞክራቲክ አቋሙ ግንባር ቀደም ረድፍ ለመያዝ የሚቀድመው የለም። ዛሬ የኢትዮጵያ ማርክሲስት ሌኒኒስት ድርጅቶች መፈክሮችን በተግባር መተርጎምና ግንባር ቅደም ሚና መጫወት አቅቷቸው ጭራሹን ቀድሟቸው በሄደው ሰፊ ሕዝብ “መፈክራችንን በተግባር ተርጉሙ” እየተባሉ ለመወትወት የበቁት ከዚህ የንዑስ ከበርቴ መደባዊ ጠባይ ገና በማያዳግም ሁኔታ ባለመለቀቃቸው እንደሆነ ግልጽ ነው።
ከላይ በዘረዘር ነው ሁኔታ በመመራት በተግባር ለሚተርጎም ለተራማጆች ህብረት እንታገል ዘንድ መኢሶን እውነተኛ ማርክሲስት ሌኒኒስት ድርጅቶችና ለሌሎች አብዮታዊያን የሚከተሉትን የትግል አቅጣጫዎች ይጠቁማል።
ሀ/ የተራማጆች ህብረት መሰረቱ የሚጠነክረው በአብዮቱ መሰረታዊ ጥያቄዎች ላይ አንድ አይነት አቋም ሲደረስና ሁሉም ድርጅቶች በዚያ አቋም ላይ ፀንተው ሲታገሉ በመሆኑ በዛሬው ወቅት ከላይ በጠቀስናቸው በሌሎችም መሰረታዊ ጥያቄዎች ላይ የሚደረገውን መሸራተት በሰፊው ሕዝብ ፊት እያጋለጡ በጋራ ለመታገል
ለ/ የተራማጆች ህብረት በተግባር የሚተረጎመው ይፋ በሆኑ የታክቲክ አቋሞች ተመርኩዘው የድርጅቱ አባላት በጋራ ሰፊው ሕዝብ ውስጥ ገብተው ሲታገሉ በመሆኑና የሚፈለገው ህብረት መሪዎች በወረቀት ላይ የሚነድፉት ብቻ ሳይሆን ታጋዮች በሰፊው ሕዝብ ውስጥ በተግባር የሚተረጉሙት ህብረት በመሆኑ ተጎታቾችን፣ አድፋጮችን፣ የቀኝ አድርባዮችን፣ ከአንገብጋቢ የታክቲክ ጥያቄዎች ፈርጣጮችን፣ የሕዝብ ንቀትና ፍራቻ የተቆራኛቸውን ንዑስ ከበርቴዎችን በጋራ ለመታገል፣ ጥራት እንዲኖርና የፊውዳል አሉባልታ እንዲቀንስ
ሐ/ ጓዶቻችን በዚህ መልክ ተሰማርተው በግንባር በቀደምትነት በሚዋጉበት ወቅት ከአድሃሪ ኃይሎች የሚሰነዘርባቸውን ተፅዕኖና ጥቃት ከሰፊው ሕዝብ ጋር ሆነን በጋራ ለመቋቋም ቆርጠን እንድንነሳ መኢሶን የትግል አንድነት ጥሪውን ያቀርባል።
3. ቢሮክራሲ ይውደም
በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ይህ መፈክር ከየትኛውም መፈክር ገኖ የሚታይና ሰፊው ሕዝብ ከዳር እስከዳር የሚያስተጋባው መፈክር ሆኖ አናገኘዋለን። በጋዜጣና ሬዲዮ፣ በየስብሰባውና በየሰልፉ ይህንን አብዮታዊ መፈክር የማያስተጋባ የቀበሌ ተመራጭ፣ የወዛደር መሪ፣ የገበሬ ተወካይ አይገኝም። በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ይህ ነገር ፈጽሞ ሊያስገርመን አይገባም። ሰፊው ሕዝብ ይህንን ፀረ ቢሮክራሲ አቋም ከቲዮሪ ወይንም አንዳንድ ተራማጆች ስለወተወቱት አልያዘውም። ዛሬ በቢሮክራሲና በሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ መካከል እየጦፈ የመጣው ትንንቅ በስብሶ በመውደቅ ላይ ባለው የትናንቱ የስልጣን አውታር እና በአዲሱ ሕዝባዊ ስልጣን ፅንስ መካከል የሚካሄድ የሞት የሽረት ትግልና አንዱ ሌላውን ጨርሶ ሳይደመስስ በምንም አይነት የማይፈታ ተጻራሪ ቅራኔ ነው። መሰረታዊ ሀቅ ይህ ነው። ሌኒን ስለ አዲሱ ሕዝባዊ ስልጣንና ስለ አሮጌው ቢሮክራሲ ዲያሌክቲካዊ ግንኙነት ሲናገር “አዲሱ ስልጣን በአንድ ቀን ከሰማይ ዱብ አይልም” ካለፈው የስልጣን አውታር ጎን እሱን እየተቃረነ፣ ከሱ እየተዋጋና እየተናነቀ ተወልዶ ያድጋል እንጂ” ያለው ለዚህ ነው።
ዛሬ በመላ ኢትዮጵያ ፀረቢሮክራሲያዊ ትግል እጅግ አይሎ የምናገኝበት አንዱ ምክንያት 25ሺህ የገበሬ ማህበራት፣ 2000 የከተማ ነዋሪዎች ማህበራት በሺ የሚቆጠሩ የወዛደሮችና የቀበሌዎች የአብዮት ጥበቃ ኮሚቴዎች በጠቅላላው እነዚህ ሁሉ ድርጅቶች የሚወክሏቸው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ጭቁን ኢትዮጵያዊያን ራሳቸውን በራሳቸው ለማስተዳደርና እድላቸውን እጃቸው ውስጥ በማስገባት በሚያደርጉት ትንንቅ ከፊታቸው ተቀምጦ እንቅፋት የሆናቸው ቢሮክራሲው መሆኑን ስላዩት ወደፊት ለመራመድ እሱን መደምሰስ እንደሚያስፈልግ በመረዳታቸው ነው። “ቢሮክራሲ ይውደም” በሚሉበትም ጊዜ ዛሬ የኢትዮጵያ ጭቁኖች፣ እስከዚህ ድረስ በመአከላዊ ደረጃ የመንግሥት ስልጣን ጥያቄ ማቅረባቸው አይደለም። እርግጥ በሲቪልና በሚሊታሪው ውስጥ ተሰግስገው አብዮቱን ለመቀልበስ የሚያሴሩትን ኣድሃሪ ቢሮክራቶች መመንጠር የፀረቢሮክራሲ ትግል አንድ የማይነጠል አካል ነው። ነገር ግን ጥሪውን ሰፋ አድርገን ስንመለከተው የኢትዮጵያ ጭቁኖች “ቢሮክራሲ ይውደም” ሲሉ የቀድሞ ሥርዓት ለብዝበዛና ለጭቆና እንዲያመቸው ከጥቅሙ ተካፍሎ የገነባው ቢሮክራሲ፣ ጭቁኖች መርጠው የገነቧቸውን የአስተዳደርና የትግል አውታሮች አሁንም ማፈኑን አይቀጥል ማለታቸው ነው። በማዕከላዊ የመንግስት ስልጣን ደረጃ ሳይሆን ባሉበት ዝቅተኛ ደረጃ በነዚህ ሕዝባዊ ድርጅቶችና በቀድሞ ሥርዓት ቢሮክራሲ ማዕከል የስልጣን መደራረብ /ድዋል ፓወር/ ባለበት ቦታ ሁሉ የማያዳግም የበላይነት ለአዲሱ ስልጣን ጥንስሶች ይሰጥ ማለታቸው ነው። ሕዝባዊ ድርጅቶችን ለማኮላሸት የሚደረገው ጥረት ይቁም፣ ዲሞክራሲ ለሰፊው ሕዝብ ወገኖች ያለገደብ ይታወቅላቸው ማለታቸው ነው። ዞሮ ዞሮ ፀረቢሮክራሲ ትግል እንደምናየው የራስን እድል እኛ ማስገባትን የሚጠይቅ የዲሞክራሲ ጥያቄ ነውና!
ከአድሃሪው ቢሮክራሲ ከራሱ አንስቶ አድሃሪ የደርግ አባላት አልፎ እስከ ቀኝ አድርባይ ምሁራን ድረስ ያለው የፀረሕዝብ ጥርቃሞ ዛሬ ለማድበስበስ የሚፍጨረጨረው ይህንን መሰረታዊ ሀቅ ነው። የዲሞክራሲያዊ መብቶች ጥያቄ የጥቂት ሰዎች፣የመኢሶን አወናባጆች ጥያቄ እንጂ በሚሊዮን የሚቆጠረው ሰፊ ሕዝብ የቀድሞውን ሥርዓት የብዝበዛና የጭቆና ቢሮክራሲ ለማውደም የሚያነሳው ጥያቄ መሆኑን ለመሸሸግ ይሞክራል። ዲሞክራሲ በዚህ መልክ የትግል መሳሪያ መሆኑ ታውቆ እስካልታየ ድረስ ልክ አሁን በሀገራችን እንደምናየው ሁሉም ፀረቢሮክራሲ ሆኖ የሕዝብ ወዳጅ ሆኖ ሊያወናብድ ይችላል። እንደዚህም በመሆኑ በተለይ አድርባዮች “ዛሬ በቂ ዴሞክራሲ አለ” “ደርግ ከዚህ በላይ ሊሰጥ አይችልም” ጭቁኖች እንጂ ገደብ አይባልም “ዲሞክራሲ ለጭቁኖች በትግል” እያሉ በሚነዙት ውዥንብር የተነሳ ሁለቱ ጥያቄዎች በመለያየታቸው በየአደባባይና በየስብሰባው ቢሮክራሲ ራሱ ሳይቀር “ቢሮክራሲ ይውደም” እያሉ የሚያሾፉበት ደረጃ ላይ ደርሰናል።
ነገር ግን በአደባባይ ጸረ ቢሮክራሲ እየመሰሉ በዚያው እንደበታቸው ደግሞ ዲሞክራሲን የሚቃወሙት የአፍ ጸረ ቢሮክራሲ የድርጊት የቢሮክራሲያው የውስጥ አርበኞች መሆናቸውን ማወቅ ብቻ አይበቃም። ይህ ለምን እንደሆነ ማለትም ትግሉ አስቸጋሪ እንደሆነ እንድናውቀው ይረዳናል። ዛሬ የኢትዮጵያን ጭቆን ሕዝቦች ትግል ለመግታት በሚደረገው ትግል ከፍተኛ የሆነ የመደቦች አስተላለፍ ለውጥ በአይናችን ስር እየተካሄደ መሆኑን ማሳየት ያስፈልጋል። በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያን አብዮት አመራር እስካሁን ይዘው የነበረው ንዑስ ከበርቴ መደብ ድል በድል እየተቀዳጀ በሄደው ኃይሉ የኢትዮጵያ አብዮት ፊት እየተርበደበደ በአመራር ሚናው ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ መወላወልን የሚያሳይበት ታሪካዊ ወቅት ነው። በዚህ የተነሳ ወላዋዩ ንኡስ ከበርተው ከሱ በስተቀኝ ከሱ ፀረሕዝብ ኃይሎች ጋር በአድሃሪው ቢሮክራሲ አማካይነት አንድነትን ለመመስረት በመሞከር ላይ ነው። ይህንን ሀቅ ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብና የኢትዮጵያ አብዮታውያን፣ በደርግ ውስጥ የቀሩት ተራማጆችም ጭምር በሚገባ ሊያውቁት ይገባል።ከደርግ አድሃሪዎች አንስቶ፣ በፍርፋሪ ተታለው የኢትዮጵያ አብዮት እስከሸጠው አስመሳይና አድርባይ ድረስ ያለው የታሪክ አተላ የአፍ ፀረቢሮክራት የድርጊት የቢሮክራሲያዊ የውስጥ አርበኛ የሆኑበትን ይህንን በመጠንሰስ ላይ ያለውን የመደቦች አስላለፍ ለውጥ ለመረዳት ለመጪው ትግላችን እጅግ ጠቃሚ ነው እንላለን።
ከዚህ ትንተና በመነሳት መኢሶን ለኢትዮጵያ ጭቁኖች ክብር፣ ነፃነትና አንድነት ለቆሙ እውነተኛ ማርክሲስት ሌኒኒስት ድርጅቶችና ሌሎች አብዮታዊያን ፀረ-ቢሮክራሲ ትግላችንን እንድናፋፍም ጥሪ እያቀረበ በሚቀጥሉት ነጥቦች ላይ አተኩረን በጋራ ትግል ወደፊት እንራመድ ይላል።
ሀ/ “ቢሮክራሲ ይውደም ማለት ሕዝባዊ ድርጅቶች ያብቡ፣ ነጻ ርምጃዎች ይስፋፉ፣ ዲሞክራሲ ይስፈን ማለት መሆኑን በመገንዘብ የቀድሞ ስልጣን የብዝበዛና የጭቆና መሳሪያ የሆነው ቢሮክራሲ ከሕዝብ ስልጣን አውታሮች ጋር ተደርቦና ተፋጦ በሚገኝባቸው ደረጃዎች ሁሉ ስልጣን ወደ ሕዝባዊ ድርጅቶች እንዲተላለፍ በጋራ ለመታገል
ለ/ የቢሮክራሲ ማየል ከዲሞክራሲ መመንመን ጋር የተያያዘ መሆኑ ግልጽ ሆኖ ሳለ ከሰፊው ሕዝብ ጋር ሲሆኑ ፀረ ቢሮክራሲ እየመሰሉ የሰፊውን ሕዝብ የዲሞክራሲ መብቶች ያለ አንዳች ገደብ መታወጅ የሚቃወሙት አቋማቸውን በሰፊው ሕዝብ ዘንድ ለማሳወቅ
ሐ/ ከላይ እንደተባለው ዛሬ የተያዘው ፀረ ቢሮክራሲ ትግል ወላዋይ ንዑስ ከበርቴ መደብ በቢሮክራሲው አማካኝነት ከጠቅላላው ፀረ ሕዝብ ኃይሎች ጋር በመመሥረት ላይ ያለውን ሽርክና ለማፍረስ የሚደረግ የረዥም ጊዜ አስቸጋሪ ትግል መሆኑ ቢታወቅም በአጭር ጊዜ ትግል አንፃር የዚህ ርኩስ ህብረት አስተባባሪ የሆኑትን አድሃሪ የደርግ አባሎችና ቀንደኛ ቢሮክራቶች ከነፀረ ሕዝብ ድርጊታቸው እየተከታተሉ በጋራ በሰፊው ሕዝብ ፊት ለማጋለጥና እንዲታገላቸው ለማድረግ፣ አድሃሪ ቢሮክራቶች እንዲመነጠሩና በአገር ወዳድ የሲቪልና የጦር መኮንኖች እንዲተኩ ለመታገል።
መ/ በፀረ ቢሮክራሲ ትግል ሳቢያ አድሃሪ የደርግ አባሎችና ቀንደኛ ቢሮክራቶች በቀበሌ ተመራጮች፣ በወዝአደርና በገበሬ ማህበራት መሪዎች፣ በአብዮት ጥበቃ ኮሚቴዎች፣ በታጋይ መለዮ ለባሾችና ሌሎች አብዮታውያን ላይ የሚያደርሱትን ተጽዕኖዎችና ጥቃት ለማጋለጥና እነዚህን ፀረ ሕዝብ ጥቃቶች ሰፊው ሕዝብ እንዲቋቋማቸው በጋራ ለመቀስቀስ እንድንተባበር መኢሶን አብዮታዊ ጥሪውን ያቀርባል።
4.አብዮታዊ እናት አገር ወይም ሞት
በዕውነቱ እንደዚህ መፈክር ግልጽ የሆነ ግን ደግሞ በዛሬው ወቅት እንደሱ የተረገጠና የተጣለ መፈክር አለ ለማለት ያስቸግራል። አብዮታዊት እናት አገር ወይም ሞት ማለት በአብዮታዊት እናት አገራችን የመጣን ጠላት ለአብዮታችን ከመጣ ጠላት ለይተን አናየውም በዚህም የተነሳ አብዮታዊት እናት አገራችንን ለማዳን የአብዮታችንን ጠላቶችም መደምሰስ አለብን የሚል እጅግ ቀላል የሆነ አስተሳሰብ ነው። የውስጥና የውጭ ጠላቶቻችን ተቀነባብረው የሚታገሉ ስለሆነ ወረራ መጣ ብለን ይህንን ወረራ ለመቋቋም በምንም አይነት ከውስጥ አድሃሪዎች ጋር ዕርቅ መፈለግ ወይንም ደግሞ የመደባችን ትግል ለማቀዝቀዝ መሞከር ቅልበሳን መጋበዝ ነው ማለት ነው። የውጭ ጠላትን ለመቋቋምና ለመደምሰስ ከውስጥ የመደቦችን ትግል ማፋፋምና የውስጥ አድሃሪዎችን መደምሰስ ያስፈልጋል ማለት ነው። በአጭሩ አብዮታዊ እናት አገር ወይም ሞት ማለት ለነቃ ለተደራጀና ለታጠቀ ሕዝብ ትግል ብለን በተነሳንበት የትግል ጎዳና የውጭ ጦር መጣ ብለን ሳናወላውል ወደፊት እንግፋ ማለት ነው።
መኢሶንና ሌሎች አብዮታውያን ይህንን መስመር በመከተል በተደጋጋሚ “የውጭ ወረራን ለመቋቋም አብዮቱን ማፋፋም” “ቢሮክራሲው አያዝምት ይዘመትብት” “ከውስጥ አድሃሪዎች ጋር እርቅ አንፈልግም” “የውስጥ አድሃሪያንን ሴራ ነቅተን እንጠብቅ” “ለሕዝባዊው ሠራዊት አብዮታዊ አመራር” “ሁሉም ነገር ለጦሩ ግንባርና ለአብዮቱ” የሚሉ መፈክሮችን እያስተጋቡ ቆይተዋል። በዚህ በኩል የተዛባ መስመር መከተል አብዮታችንን መቀመቅ ውስጥ ሊከተው እንደሚችል ቀደም አደርጎ በመገንዘብ መኢሶን በህጋዊ ሥራ በተሠማሩ ጓዶች አማካኝነት ብዙ ተጨባጭ አሳቦችን ለጊ.ወ.መ. አቅርቦ ነበር። በአድሃሪዎች እያየሉ መምጣት የተነሳ “የዕርቅ ፖለቲካ” እየተስፋፋ በመምጣቱ አብዮታውያን ከጊ.ወ.መ. የሰነዘሩት ሃሳብ ሁሉ ተቀባይነትን እያጣ ሄደ።
የሆነ ሆኖ ከአድሃሪው ቢሮክራሲ አንስቶ እስከ ቀኝ አድርባዮች ድረስ ያለው ፀረ ሕዝብ ኃይል ይህንን መፈክር ለማድበስበስና አብዮታችንን አሁን የሚገኝበት የቅልበሳ አፋፍ ለማምጣት የቻለው ለኢትዮጵያ አብዮት የሚደረገውን ትግልን አንዱ ነገር ለአብዮታዊት ኢትዮጵያ ህልውና የሚደረገውን ትግል ሌላ ነገር አስመስሎ በማቅረብ ነው። “ሁሉን ነገር ለጦር ግንባር” የሚለውን እነሌኒን አብዮታዊ በሆነ ዘዴ የተጠቀሙበትን መፈክር የቀኝ አደርባዮችና አድሃሪው ቢሮክራሲ የተዛባ ትርጉም ሰጥተውት “አሁን ለጊዜው አብዮቱን ተወት አድርገን ይህንን የውጭ ወራሪ ዱብ እዳ እንዋጋ፣ ለጊዜው ሁሉም በዚህ ጦርነት ላይ ያተኩር፣ ከዚያ በኋላ አብዮቱን “ካቆምንበት” ተመልሰን እንቀጥልዋለን” ወደሚል ቴዎሪ ለወጡት። ስለዚህ በዚህ ጦርነት ውስጥ እያለን “አብዮቱ ይግፋ” በሚል ፈሊጥ ዲሞክራሲ እየጠየቁ ውዥንብር ለመፍጠር መሞከር፣ ለጦርነቱ ለጊዜው አስፈላጊ የሆኑትን “አዋቂ” ቢሮክራቶች ይነሱ እያሉ ፀረ ቢሮክራሲ ትግል ማካሄዱ፣ መላ ኢትዮጵያዊያን ተባብረን የውስጥ ቅራኔያችንን አቻችለን ዋናው የውጭ ጠላት እንድንቋቋም የመደቦች ትግል ይፋፋም እያሉ ማስተጋባት ተቀባይነት የሌለው ነገር ሆነ።
በዚህ ቲዎሪ መሠረት የለየላቸው አድሃሪዎች “አዋቂ” እየተባሉ በቢሮክራሲው ውስጥ ቁልፍ ቦታዎችን መልሰው ሲይዙ፣ ከየካቲቱ ወዲህ በየጊዜው ከሠራዊቱ በሲአይኤ ወኪልነትና በቀልባሽነት እየተነቃባቸው የተባረሩ መኮንኖች ከአገር ወዳድ አባት ጦረኞችና መኮንኖች ጋር ተደባልቀው ወደ ጦሩ ሲመለሱ ሲመለሱ “ሁሉም ነገር ለጦሩ ግንባር” ከሚለው አሻሚ መፈክር ጋረ የሚጋጭ ባይመስልም ይህ ድርጊት “አብዮታዊ እናት አገር ወይም ሞት” ከሚለው የሰፊው ሕዝብ መፈክር ጋር ተፃራሪ እንደሆነ አደርባዮች አልተገነዘቡ እንደሆነ፣ ይህ ድርጊት ለጊዜው የሱማሌን ጦር ከኢትዮጵያ ምድር ማስወጣት ብንችልም ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ በግርግር እየተጠናከሩ የሚመጡት ቀልባሽ ኃይሎች አሜን ብሎ ካልተንበረከከ በስተቀር እስካሁን ካየነው ይበልጥ አሰቃቂ የሆነ የለየለት የርስ በርስ ጦርነት በር ከፋች እንደሆነ አልተገነዘቡ እንደሆነ በዕውነቱ ታውረዋል ማለት ነው። ይህንን ሁሉ እየተመለከቱ ደግሞ ሰፊው ሕዝብ የሚደገስለትን ቅልበሳ፣ ሊመጣ የሚችለውን የከባድ ፈተና ወቅት፣ ከማሳየትና ለሱም እንዲዘጋጅ ከመጣደፍ ተቆጥበው ማድፈጥ ያሉት ከሆነ ከዚህ የበለጠ በአድሃሪዎች ፊት መርበድበድ፣ ከዚህ የበለጠ አደርባይነትና ከዚህ የበለጠ የታሪክ አተላነት የለም እንላለን።
በዚህ አንፃር መኢሶን ለእውነተኛ ማርክሲስት ሌኒኒስ ድርጅቶችና፣ ለሌሎች አብዮታውያን የሚያቀርበው የአፍ ሳይሆን የትግል አንድነት ጥሪ በሚቀጥሉት የትግል አቅጣጫዎች እጅ ለእጅ ተያይዘን በህብረት “አብዮታዊት እናት አገር ወይም ሞት” ለሚለው መፈክር እንድንታገልና ወደፊት እንድንገፋ ነው።
ሀ/ አብዮታዊት እናት አገር ወይም ሞት የሚለውን መፈክር በትክክል ከሥራ ላይ መዋል ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዳር እስከዳር የሚጠይቀውና የሚታገልለት በመሆኑና በዚህ በኩል በግርግር በመፈጸም ላይ ያለው መንሸራተት ለአብዮታችን ከዕለት ዕለት እጅግ አደገኛ የሆነ ሁኔታ እየፈጠረ በመሄድ ከዚህ ወሳኝ መፈክር አንፃር በየዕለቱ የሚፈጸመውን ክህደትና መንሸራተት በሰፊው ሕዝብ ፊት በጋራ በማጋለጥና በቆራጥነትም እንዲዋጋቸው በግንባር ቀደምነት አብሮ ለመሰለፍ
ለ/ የአብዮታዊት እናት አገራችንን ሕልውና ማረጋገጥ የሚቻለውና ቀልባሽ ኃይሎች በግርግር ከሚደግሱልን የለየለት የቅልበሳ የርስበርስ ጦርነት ሰፊው ሕዝብ በአሸናፊነት ሊወጣ የሚቻለው ሰፊው ሕዝብ የተጫነበትን ወረራ እየመከተ በዚያውም ነቅተን ድርጅቱንና ትጥቁን ሲያዳብር መሆኑ ግልጽ ነው። ይህ ሆኖ ሳለ በጦርነቱ ሳቢያ “ፀረ ቢሮክራሲነት ነን” “ዲሞክራሲ ነን” “የመደቦች ትግል ነን” የሚሉትን የቀኝ አደርባይ “ቴዎሪዎች” እያጋለጡ በአፍ ሳይሆን በተግባር ለነቃ፣ ለተደራጀና ለታጠቀ ሕዝብ ትግል በጋራ ለመቆም
ሐ/ ከዚህም በመነሳት “ሁሉም ነገር ለጦር ግንባር” ከሚለው ማሻማት የጀመረ መፈክር ይልቅ “ሁሉም ነገር ለጦርነቱ ግንባርና ለአብዮቱ” በሚለው አብዮታዊ ሰንደቅ ስር ተሰልፈን አንደኛ የጦሩን ግንባር በማጠናከር ሁለተኛ መሃል አገርን የግንባሩ አስተማማኝ ደጀንና የአብዮቱ አስተማማኝ ምሽግ ለማድረግ የተቀነባበረ ትግል በጋራ በሰፊው ሕዝብ ውስጥ ለማካሄድ ለዚህም
- የጦሩን ግንባር ለማጠናከር፣ ወራሪዎችን እየተጋፈጠ በመሰዋት ላይ ያለው መደባዊና ሕዝባዊ ሠራዊት ከአድሃሪው ሚሊተሪ ቢሮክራሲ ታላቅ አብዮታዊ አመራር እንዲያገኝ፣ ተራማጅ የጦር መኮንኖች አድሃሪዎችን እንዲተኩ፣ በግንባር ካሉ ክፍላተ ሃገራትና ተጨማሪ ካስፈለገ ከየድርጅቶቻችን የተውጣጡ ወጣት የፖለቲካ ካድሬዎች ከዘመቻው ጦር ጎን እንዲዋሃዱና የፖለቲካ ንቃትን እንዲያዳብሩ፣ አስፈላጊ ለሚሆነው ተጨማሪ ሕዝባዊ ሠራዊት ከሌሎች ክፍላተ ሃገራት ከማምጣት ይልቅ በነዚሁ ከግንባሩ ክፍላተ ሃገራት ገበሬዎች ጦር እንዲመለመልና እንዲሰለጥን ሰፊው ሕዝብ በገፍ ለመቀስቀስና በህብረት ለመታገል፤
- መሃል አገርን የጦር ግንባር አስተማማኝ ደጀን ለማድረግ በጦርነቱ ምክንያት ከምርት በተለየው ጉልበት የተነሳ ምርት እንዳይቀንስ፣ የተዋጊው ሠራዊት ቤተሰብ ችግር ላይ እንዳይወድቅ በስተደጀን የቀረው የዘመተውን ጉልበት እንዲተካ ለመቀስቀስ፣ የሀገሪቱን ወረራ የመመከት አቅም ለማዳበር በየገበሬው ማህበራት ሁሉ በተለይ ለጦር ግንባር ስንቅ በህብረት የሚመረቱባቸው “የጦር ግንባር ማሳዎች” እንዲቋቋሙ ሰፈውን ሕዝብ ለመቀስቀስ፣ በጦርነት ሕይወታቸውን ለሰው መለዮ ለባሽ፣ አርሶ አደር፣ ወዝአደርና ሌሎች አብዮታውያን ቤተሰቦች አስፈላጊውን የማቴሪያል የሞራል እንክብካቤ የሚደረግበትን ዘዴ በጋራ ለመፈለግና ለማስተባበር፣
- መሃል አገርን የአብዮቱ ምሽግ ለማድረግ ባስቸኳይ ሕዝባዊ ነፃ እርምጃዎችን አስፋፍቶ አሁን የናጠጡትን ቅጥር ነፍሰገዳዮች እንዲደመስስ ሰፊውን ሕዝብ በግንባር ቀደምነት መቀስቀስና አብሮት በጋራ ለመታገል፣ የሰፊው ሕዝብ የመንቃት፣ የመደራጀትና የመታጠቅ ተግባር ያላንዳች ማቋረጥ ወደፊት እንዲገሰግስና ገና ጦርነቱ ያልደረሰባቸው ክፍላተ ሃገራትን ለቀልባሽ ኃይሎች በምንም አይነት የማይመች በማድረግ፣ ለዚህም ጦርነት ላይ ነንና ዲሞክራሲ አያስፈልግም የሚል ፀረ ሕዝብ የንዑስ ከበርቴ ፈሊጥ መሆኑን አምነን የመሃል አገርን ወደ አስተማማኝ ምሽግ መለወጥ የሚቃወሙትን የቀኝ አደርባዮች ያለማወላወል ለማጋለጥና ሰፊው ሕዝብ እንዲዋጋቸው በጋራ ለመቀስቀስ ለኢትዮጵያ እውነተኛ ማርክሲስት ሊኒኒስቶች ድርጅቶችና ለተቀሩት አብዮታውያንና አገር ወዳዶች ሁሉ መኢሶን የትግል አንድነት ጥሪውን ያስተጋባል።
5. ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለጭቁኖች ያለገደብ አሁኑኑ
ከላይ እንዳልነው አደርባዮችና አድሃሪዎች በአንድ በኩል ሰፊው ሕዝብና ቆራጥ አብዮታውያን በሌላ በኩል ሆነው አብዮት አደባባይ ላይ ከፀሐይ በታች ባሉ መፈክሮቸ ሁሉ ቢስማሙ መገረም የለብንም ብለናል። በዚህ “ስምምነት ከተደረሰ” በኋላ ደግሞ ከብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት አንፃር ዋና ዋና ጥያቄዎች አንዱ በሆነው በዲሞክራሲ መብቶች ጉዳይ ክርክር ቢነሳ ለምን መገረም እንደሌለብን ገልጸናል እንዲያውም በዛሬይቱ በ1970 ኢትዮጵያ ሃቀኛው አብዮታዊ ከአወናባጅና ከአስመሳይ፣ ማርክሲስት ከንዑስ ከበርቴው ሶሻሊስት፣ ውድ እናት አገሩን ከራሱ የሚያስቀድመው ዲሞክራትና አገር ወዳድ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል ከሚለው አድርባይ ዞሮ ዞሮ ተራማጁ ከአድሃሪው የሚለይበት ጥያቄ ይህ የዲሞክራሲያዊ መብቶች ጥያቄ ሆኖ እናገኘዋለን። እንዲያውም የኢትዮጵያ ማርክሲስት ሌኒኒስት ድርጅቶች በዚህ የሕዝብና የአብዮት መሠረታዊ ጥያቄ ወደር የሌለው መንሸራተት አድርገው በሐምሌ ወር 1969 ዓ.ም. ባወጡት የድርጊት ፕሮግራም ውስጥ በድምጽ ብልጫ እስከሰረዙት ድረስ ይህ ጥያቄ ከብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራም ጀምሮ አንገብጋቢነቱና አጣዳፊነቱ ለአብዮታችን ህልውና ወሳኝነቱ ጨርሶ የሚያከራክር አልነበረም። ለሃቀኛ አብዮታውያንና ለሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ደግሞ ዛሬም የዚህ ጥያቄ ወሳኝነት የሚያከራክር አይደለም።
ዛሬ ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያስተጋባቸው መፈክሮች ሁሉ ለአድሃሪዎች የቅልበሳ ሴራ ፋታ ሳይሰጡ ከሥራ ላይ ሊውሉ የሚችሉት ዲሞክረሲያዊ መብቶች ሲታወቁ እንደሆነ ግልጽ ነው። በተግባር ለሚተረጎም የተራማጆችን ህብረት፣ የወዝአደሩ ፓርቲ ባስቸኳይ ይመስረት፣ ቢሮክራሲ ይውደም፣ አብዮታችን ከተከላካይነት ወደአጥቂነት ይሸጋገር፣ ቅጥር ነፍሰገዳዮችን ለመቋቋም ሕዝባዊ ነፃ እርምጃዎች ወዘተ የሚሉት መፈክሮች ሁሉ በተዘዋዋሪም ሆነ በቀጥታ የዲሞክራሲ ጥያቄዎች ናቸው። መፈክሮቹ በአብዮታዊ ትርጉማቸው ሲወሰዱ ያለሰፊው ሕዝብ ተሳትፎና ያለዲሞክራሲ ሙሉ በሙሉና ዋስትና ባለው ሁኔታ ከሥራ ላይ ሊውል አይችሉም ስለዚህም ይህ የዲሞክራሲ ጥያቄ ለሰፊው ሕዝብ ወገኖች እጅግ አንገብጋቢ የሆነውን ያህል ለአድሃሪዎች የመጨረሻው ምሽግ ለአስመሳዮችና ለቀኝ አደርባዮች የመጨረሻው “ተራማጅ ካባ” በመሆኑ በዚህ ጥያቄ ላይ ከባድ ትግል ቢያጋጥመን መገረም አያስፈልግም።
መኢሶን ዛሬ ለዲሞክራሲያዊ መብቶች ከሰፊው ሕዝብ ጎን ቆሞ ሲታገል የዚህ ትግል ጊዜያዊ ዓላማዎች ሁለት እንደሆኑ ተነግሯል። የመጀመሪያው ዓላማ ከላይ እንዳስረዳነው በከተማም ሆነ በገጠር የሕዝብ የሥልጣን አውታሮችና የበሰበሰው ቢሮክራሲ ተደራርበውና ተፋጠው በሚገኙባቸው ቦታዎች ሁሉ ሥልጣንን ወደሰፊው ሕዝብ ለማስገባት የሚያስችል መብት እንደሆነ ጠቁመናል። በዚህ መልክም ሲታይ ይህ የዲሞክራሲ ጥያቄ የጥቂት ግንባር ቀደም ኃይሎች ጥያቄ ብቻ ሳይሆን በሺህ በሚቆጠሩ ሕዝባዊ ድርጅቶች አማካኝነት የኢትዮጵያ ጭቁኖች ከዳር እስከዳር የሚያስታቡት አንገብጋቢ ጥያቄ እንደሆነ አሳይተናል።
ሁለተኛ መኢሶንና ሌሎች አብዮታውያን ከሰፊው ሕዝብ ጋር ሆነው “ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለጭቁኖች ያለገደብ አሁኑኑ” የሚለውን ጥያቄ የሚያስተጋቡት በነቃ በተደራጀና በታጠቀ ሕዝብ ትግል ጎዳና ላይ አብዮቱን በበለጠ ፍጥነት ለማራመድ እንዲቻል ነው። ዛሬ ምን አደርባይ ቢሆን ሰፊው ሕዝብ እንዲነቃ፣ እንዲደራጅና እንዲታጠቅ ዲሞክራሲያዊ መብቶች እንደሚያስፈልጉት ደፍሮ የሚክድ የለም። ነገሩን ለማደባበስ የሚፈለገው “አሁኑኑ” በሚለው ጥያቄ ላይ ነው። ነገር ግን ደግሞ ጠላት ከያለበት እየከበበና ከውስጥ እየቦረቦረ አብዮታችንንና እናት አገራችንን ላለማስደፈር “ዛሬ ትግላችን ከጊዜም ጋር በሆነበት ወቅት” የሰፊው ሕዝብ በአፋጣኝ መታጥቅ ለአብዮታችን ህልውና ወሳኝ ጥያቄ መሆኑን መገንዘብ አይቸገርም። ለመንቃት፣ ለመደራጀት ለመታጠቅ ዲሞክራሲያዊ መብቶች አመቺ ሁኔታን ይፈጥራሉ ከተባለ ነገሩን እንኳን ከማርክሲዝም ሌኒኒዝም አንጻር ቀርቶ ከተራ ሎጂክ አንፃር ለተመለከተ ሰው ዲሞክራሲ “ባፋጣኝ” አስፈላጊ መሆኑን ለመረዳት የሚቸግር አይመስለንም።
ሃቁ ይህ ሆኖ ሳለ፣ አፋጣኝና አጣዳፊ ጊዜ ውስጥ እያለን፣ ዲሞክራሲያዊ መብቶችን ተቃውሞ የሕዝቡን ባፋጣኝ መንቃት፣ የወዛደሩን ፓርቲና የሌሎች ዲሞክራሲያዊ ፓርቲዎችን ባፋጣኝ መመስረት፣ የሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ድርጅቶችን መፋፋትና የሕዝባዊ አብዮታዊውን ግንባር ባፋጣኝ መገንባት አፍኖ መያዝና የዚች እናት አገራችንና የአብዮታችንን ዕድል አሁንም በጥቂት ሰዎች ትከሻ ላይ ብቻ አንጠልጥሎ ለማቆየት መሞከር ቅልበሳን መጋበዝና በታሪክ ፊት ተጠያቂነትን መጥራት ነው እንላለን። በተለይም በፕሮግራም ደረጃ ከላይ የጠቀስናቸው የሰፊው ሕዝብ ወገኖች በየፈርጃቸውና በየደረጃቸው መደራጀት አግዛለሁ የሚል መንግሥት ተደራጅተው የሚታገሉትን ተራማጅ የፖለቲካ ቡድኖች የሴቶች የወጣቶች. . . ሕዝባዊ ድርጅቶች በህቡዕ ተወስነው እንዲታገሉ አፍኖ መያዝን በታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ከመሆኑም በላይ ለፀረ አብዮት ኃይሎች ይህ ነው የማይባል የውዥንብር መንዣ በአብዮታውያን ሰፈር ሰርጎ የመግቢያ ቀዳዳ እንደሰጣቸው ግልጽ ነው።
ይህንን ሁሉ በመመልከት በአፍ ሳይሆን በትግል አንድነታችንን እንድናጠናክር ለሚሹ ማርክሲስት ሌኒኒስት ለሌሎች አብዮታውያን ለዲሞክራሲ መብቶች የሚደረገውን ትግል በሚቀጥሉት አቅጣጫዎች እንድንመራ አብዮታዊ ጥሪውን ያቀርብላቸዋል።
ሀ/ ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለሰፊው ሕዝብ ወገኖች ያለአንዳች ገደብ የሚለውን መፈክር በሥራ ለመተርጎም ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት በሕዝብ ድርጅት ጉዳይ ጊዜያዊ ጽ/ቤት ረቆ መሻገት የጀመረውን የዲሞክራሲ መብቶች አዋጅ ሰፊው ሕዝብና አብዮታውያን እንዲታገሉላት በጋራ ለመቀስቀስና ለመታገል።
ለ/ ይህ ረቆ ያለው አዋጅ እንዲታወጅ ከሚደረገው ትግል ጋር ሕዝባዊ ድርጅቶች እንዲያብቡ፣ አድሃሪው ቢሮክራሲ እንዲመታ የሚካሄደውን ትግል ለማፋፋምና በአድሃሪው ቢሮክራሲ ፀረ ዲሞክራቲክ አሠራር የተነሳ በየክፍላተ ሃገሩ ታስረው የሚማቅቁት የገበሬ ማህበራት፣ የወዛደርና የቀበሌ ማህበራት የሕዝብ ድርጅት ካድሬዎች እንዲፈቱ፣ በግፍ ለተረሸኑት ኢትዮጵያን ተጠያቂ የሆኑት ቢሮክራቶች ባሉበት አካባቢ ለፍርድ እንዲቀርቡ፣
ሐ/ በከተሞችም ይህ ረቆ ያለቀው አዋጅ በተግባር እንዲተረጉም ከምናፋፍመው ትግል ጋር የቀበሌ ማህበራትን፣ የወዛደር ማህበራቱንና የአብዮት ጥበቃ ጓዶችን ነፃ ርምጃዎች ለማፋፋም፣ ለአብዮታዊ ጓዶቻችን ሕይወት ተጠያቂ ሆነው የሚገኙ አድሃሪ ቢሮክራቶችን ለሕዝባዊ ፍርድ በማቅረብ፣ በአድሃሪ ቢሮክራቶች አሻጥር የታሠሩ የአብዮት ጥበቃ ጓዶቻችና ሌሎች አብዮታውያን ሁሉ ያለአንዳች ድርድር እንዲፈቱ፣ ሰፊው ሕዝብ በጋራ እንዲታገል ለመቀስቀስ፣ በስንት መከራ እየተያዙ ከቁጥጥር ሥር የዋሉት ቅጥር ለነፍሰገዳዮችን በሰበብ አስባቡ እየለቀቀ የሰፊውን ሕዝብ ልጆች የሚያስጨርሰውና ለነጭ ሽብር ተባባሪ የሆነው አድሃሪ ቢሮክራሲ ከዚህ ፀረ ሕዝብ ሥራው እንዲቆጠብና በሕዝባዊ ድርጅቶች አማካኝነት የተያዙ ፀረ አብዮተኞች በምንም ዓይነት ያለሕዝባዊ ድርጅቶች ፈቃድ እንዳይለቀቁ ለማድረግ ሰፊው ሕዝብ እንዲታገል ለመቀስቀስ
መ/ አብዮታዊ ግዴታቸውን ሲፈጽሙ በቅጥር ነፍሰገዳዮች እጅ ከወደቁት ጓዶቻችንና በቢሮክራሲው አሻጥር ታስረው ከሚማቅቁት ወዝአደሮች፣ መለዮ ለባሾች የቀበሌ ተመራጮች የአብዮት ጥበቃ አባላትና ከሌሎች አብዮታውያን ቤተሰቦች መሃል በረሃብ አለንጋ እየተጠበሱ ከፍተኛ ችግር የሚደርሰባቸው እንዳሉ በየቀበሌያችን የምናየው ሃቅ ስለሆነ ለነዚህ ወገኖቻችን አስፈላጊ የሆነውን የማቴሪያልና የሞራል እርዳታ በጋራ ለማስተባበር ለመታገል
ሠ/ የአብዮታችንን ኃይል አስተማማኝ ፈር ለማስያዝ፣ የወዝአደሩን ፓርቲና ሌሎች ዲሞክራሲያዊ ፓርቲዎችና ድርጅቶች የሚቋቋሙበትን ሁኔታ ለማገዝ በጋራ ለመታገል፣ ሴቶች ወጣቶች ተማሪዎች በያለበት ዲሞክራሲያዊ በሆነ ዘዴ ሕዝባዊ ድርጅቶችን እንዲፈጥሩ ለመቀስቀስና በዚህ በኩል ሊመጡ የሚችሉትን ቢሮክራሲያዊ ተጽእኖዎችና እንቅፋቶች በጋራ ለመቋቋም የመደራጀት መብታቸውን ለማስከበር ከሚዋጉ ሴቶች ተማሪዎች ወጣቶች መምህራን ዲሞክራቶች አገር ወዳዶች. . . ወዘተ ጎን ተሰልፎ በጋራ ለመታገል፣ የነዚህን ድርጅቶች መፋፋት ለማፈን ወይንም ደግሞ ከንዑስ ከበርቴውና ከአድሃሪው ቢሮክራሲ ፀረ ሕዝብ ህብረት ቁጥጥር ሥር ለማምጣት የሚደረጉትን ጥረቶች በሕዝብ ፊት ያለማወላወል ለማጋለጥና በጋራ ለመዋጋት እንድንተባበር መኢሶን አብዮታዊ ጥሪውን ያቀርባል።
መደምደሚያ
መኢሶን ልክ እንደ ሰፊው ሕዝብና እንደ ሃቀኛ አብዮታውያን መፈክሮችን ማስተጋባት ብቻ ሰልችቶታል። ልክ እንደ ሰፊው ሕዝብ መፈክሮች በተግባር ይተርጎሙ ይላል። የአፍ ሳይሆን የትግል፣ የቁንጮዎች ብቻ ሳይሆን የየድርጅቶችም ታጋይ አባላት፣ የወረቀት ላይ ሳይሆን የተግባር፣ የአየር ላይ ሳይሆን ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዕለታዊ ትግሉ ከሚያፈልቃቸው አብዮታዊ መፈክሮች የሚነሳ የትግል ህብረት ይጠይቃል።
ለዚህ ዓይነቱም አንድነት በግንባር ቀደምነት ይታገላል። ሃቀኛ ህብርት ከትግል፣ ለትግል የሚመሠረት በመሆኑ እንዲህ አይነት ህብረት እንዲወለድና እንዲጠነክር ልዩነቶቻችንን አቻችለን በጋራ ልንታገልላቸው የምንችለው አቅጣጫ ይጠቁማል። በዚህ ትግል በሰፊው ሕዝብ መሃል መሆንን እየተዋወቅን እውነተኛ የታጋዮች አንድነት ወንድማማችነትና መቀራረብ ሊፈጥር ይችላል የሚል የፀና እምንት አለው። ለዚህም ይረዳል የሚለውን ሃሳብ በሹክሹክታ ሳይሆን እነሆ በማርክሲስት ሌኒኒስት ድርጅቶች አባላት፣ በተቀሩት የኢትዮጵያ ተራማጆች በሰፊው የኢትዮጵያ ተራማጆች በሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ፊት አቅርቧል። እንዲህ ዓይነቱን ጥሪ በይፋ ማቅረባችን ለአንዳንዶች ግራ ያጋባ ይሆናል። መኢሶን ግን እምነቱ በሰፊው ሕዝብ ብቻ ነው። ሰፊው ሕዝብ እንዲሳተበት ካልተደረገ ለዚህም አስፈላጊ ለሆኑት መብቶቹ ከጎኑ ሆነን ካልታገልን በመሪዎቹ መሃከል የተወሰኑ ስምምነት ምን ያህል ከሥራ ላይ እንደሚውሉ ሩቅ ሳንሄድ የአለፈው ሐምሌ የድርጊት ፕሮግራማችን ማስረጃ ነው። መኢሶንም ከላይ እንደጠቆምነው የትግል ስልት ለውጥ ያደረገው በዚህ ዕምነት ተገፋፍቶ ከታጋዩ ሕዝብ በይበልጥ ለመሳተፍ ነው።
እንደ መኢሶን አይነቱን ቆራጥ ርምጃ ለመውሰድ የሚችለው የሕዝቡን አብዮታዊ መፈክሮችን በአፍ ሳይሆን በድርጊት ለመቀበል፣ ለነሱም እስከመጨረሻው ለመጋፋት ዝግጁ በመሆን ነው። ከዚህ በተጨማሪ እንዲህ አይነቱን ቆራጥ እርምጃ ለመውሰድ አሁንም በአፍ ሳይሆን በተግባር በጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት ላይ ከቀኝ አደርባይነትና ከግራ መሳይ አድርባይነት ጨርሶ የተላቀቀ የአብዮታዊ ሂስ አቋም መያዝና እሱን ነፃ በሆነ መንገድ ከሥራ ላይ ለማዋል መታገል ያስፈልጋል። እነዚህን ሁለት ነጥቦች የሚያሟላ ድርጅት በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ከሕዝብ ትግል ከሕዝብ ጉጉትና ከሕዝብ መፈክሮች ወደኋላ የቀረ ተጎታች ድርጅት ነው። ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት ወደ ግራ ሲረገጥ ወደ ግራ ወደ ቀኝ ሲረገጥ ወደ ቀኝ የሚረግጥ አድርባይ ድርጅት ነው። ይህ ዓይነቱ ድርጅት ወደደም ጠላም ቀስ በቀስ ወደታሪክ አተላነት ይዘቅጣል።