የሰፊው ሕዝብ ድምፅ
ቁጥር 32፣ ህዳር 25፣ 1968
የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ
መኢሶን በዚህ የሰፊው ሕዝብ ድምፅ እትሙ፣ አብዮቱን አጥብቀው የሚቃወሙ ኃይሎች ትግሉን ለማደናቀፍና ለመቀልበስ የሞት ሽረት ትግል እያደረጉ እንደሆነ ያስገነዝባል:: በሰሜናይቱ ኢትዮጵያ ራሱን “የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ህብረት” በሚል ድርጀት ስር፣ ራስ መንገሻ ሥዮምና ፣ ጄ/ል ነጋ ተገኝን የመሳሰሉ የቀድሞ የፊውዳል ሃይሎች፣ እንዲሁም ሌሎች በኤርትራና በትግራይ ያሉ ቀኝ ሃይሎች መሰባሰባቸውን እንደማስረጃ ያቀርባል። ከነዚህም በተተጨማሪ፣ የሕዝባዊ ትግሉ ደጋፊ ነን የሚሉ አስመሳዮችም ውዥንብር እንደሚነዙ ይጠቅሳል። በዚህም ምክንያት የአብዮቱ ሃይሎች በጭራሽ ሳይዘናጉ፤ ባንድ በኩል በትግሉ የተገኙትን ድሎች እየተንከባከቡ፤ በሌላ በኩል ደግሞ፣ ለተጨማሪ ድሎች ትግላቸውን አጠንክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ ያደርጋል። ከዚሁ ጥሪ አኳያ፣ ከዚህ በኋላ “ወዴት እንሄዳለን?” እያልን ራሳችንን መጠየቅ ተገቢ እንደሆነ ያስገነዝባል።
በማንኛውም ሕዝብ አብዮት ሙቀትና ቅዝቃዜ፡ ግለትና መብረድ መፈራረቃቸውን ታሪክ ያስተምረናል። አብዮት ትግል እንደመሆኑ አብዮተኛ ኃይሎች ገፍተው አድሃሪ ኃይሎችን ሲጥሉ አብዩቱ ይራመዳል። አድሃሪ ኃይሎች ያላቸውን ኃይል አስተባብረው የሙት ሙታቸውን ሲንፈራገጡ አብዩቱን ለጥቂት ጊዜም ቢሆን ይቀለብሳሉ። ዛሬ አብዮቱ በዚህ የአድሃሪ ኃይሎች መፈራገጥ አደጋ ላይ ጥሎት ሊቀለበስና እርምጃው ሊዘገይ በሚያሰጋበት ደረጃ ላይ ይገኛል። የጉልተኞች ተስፋ መቁረጥ በተስፋ ማግኘት ሲለወጥ፣ የኢምፔሪያሊዝም ግፊት እየጠነከረ ሲሄድ፣ የደርጉ ፀረዲሞክራሲ፡ፀረሕዝብና ፀረአብት ድርጊቶች እየበዙና እየሰመሩ ሲሄዱ፣ የተራማጅ- መሰል አድር-ባዩች ድንፋታ ትልቅ ውዥንብር ሲፈጥር፣ ቆም ብለን ‘ወዴት እንሄዳለን?’ ብለን ራሳችንን እንጠይቃለን። የዚህ ውዥንብር መፈጠር፣ የዲሞክራሲ መጥፋት፣ የፀረ አብዮት ኃይሎች መተባበር የሚያስከትለውን አደጋ በ‘ሰፊው ሕዝብ ድምጽ’ ቁጥር 31 በአጭሩ ለማመልከት ሞክረናል። ለዚህም አደጋ መኖር ዛሬ ጉልህ ማስረጃዎች አሉ።
በሰሜን ኢትዮጵያ ራሱን ‘የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ማህበር’ ብሎ የሚጠራው የነጋ ተገኝ፣ የኢያሱ መንገሻ፣ የመንገሻ ስዩም ቡድን እነ አድማሴን በቤገምድር፡ እነ ስሜነህን በጐጃም፣ እነ ብርሀነ መስቀልን በወሎ ይዞ በደርግ ላይ የጀመሩትን ትጥቃዊ ትግል ማቀነባበር ጀምሯል። ከኤርትራው ንቅናቄ ቀኝ ክንፍና ከትግራይ ንቅናቄዎች ጋር በመተባበር፣ የአፋሩን አሊ ሚራህ ጨምሮ፣ በኢምፔሪያሊዝምና በአድሃሪ የአረብ አገሮች አበረታችነትና ድጋፍ የፊውዳል ሥርዓትን ለመመለስ ይፏችራል፤ በሰፊው ሕዝብ አብዮታዊ ክንድ ከፍተኛ አደጋ የተጣለበትን ፊውዶ-ቡርጇ አገዛዝ ከማጣጣር ሊያድነውና ነፍስ ሊዘራበት ይሞክራል።
ፀረ ሕዝቡም ደርግ በዲሞክራሲ ሊፈቱ የሚችሉትን ቅራኔዎች በኃይል በመጠቀም ለማጥፋት በሕዝብ ላይ ትልቅ እልቂት ያደርጋል። የደርጉ ቀኝ ክንፍ በእሳቱ ላይ ነዳጅ እየጨመረ ሕዝቡ እንዲነሳ፣ ከአድሃሪዎች ጋር እንዲሰለፍ፣ በአፋር፣ በጐጃም፣ በቤገምድር፣ በወሎ አድሃሪዎችን በመሾም እድገት በህብረትን በማጨናገፍ አብዮቱን ጠላትና ወዳጅ በአንድ ላይ በመምታት ይረዳል። ዲሞክራሲያዊ የፖለቲካ መፍትሄ ያለውን የኤርትራን ሕዝቦች የብሄር ጥያቄ በብሄር ትምክህተኝነትና በፋሽስታዊ አመጽ በሚመራ እልቂት ሊገታው ሲሞክር ይታያል። መለስ ብሎ ደግሞ በቤገምድር፣ በሰሜን ሸዋ፣ በጐጃም፣ በትግራይ የ‘ሰላም መልእክተኞች’ ብሎ አብዩቱ እንዲቀለበስ የሚጥሩ ግለሰቦችን ‘ሽማግሌ’ እያለ ለሽፍቶች መታረቂያ የሚሆን ሃሳብ እየያዙ እንዲሄዱ ያደርጋል።
በደቡብ ኢትዮጵያ የደርጉ ፀረ ዲሞክራሲየዊ አገዛዝ ከፀረ ሕዝቡ ቢሮክራሲያዊ አስተዳደር ጋር እየተመሳጠረ አብዩቱን ለመግታት አቅጣጫውን በማስለቀቅ ላይ ይገኛል። ሕዝቡ በአዋጅ ደረጃ ያገኛቸውን አብዩቱን ሊገፉ የሚችሉ ድሎች በሥራ ላይ እንዳይውሉ ለቅንጣት ያህል እንኳን ያልተነካው የአጤ ቢሮክራሲ ከአድሃሪዎች ወንፊት እያመለጡ የሄዱትን መመሪያዎች በየዶሴው ይቀብራቸዋል፤ ወይም ተጠምዘው እንዲተረጎሙ፣ በሥራ ላይ እንዳይውሉ በተለመደው የነገር መጠምጠምና ማራዘም ዘዴው ፍሬቢስ ያደርጋቸዋል። ምሳሌ ቢያስፈልግ የመሬት ይዞታውን አዋጅ ስለ 1967 ዓ.ም. ሰብል በደርጉና በአገር አስተዳደር ሚኒስቴር የወጣው ሴርኩላር እንዴት ሊሽረው እንደሞከረ አውቆ ስለሆነ ጠቅሰን እናልፈዋለን። በየክፍለአገሩ የሚዘዋወሩት የደርግ አባሎችም በሃረርጌ፣ በሲዳሞ፣ በወለጋ ወዘተ… የገበሬዎችን ማህበራት ስብሰባዎች መበተናቸውን፣ በወላሞ የገበሬ ማህበራት መሪዎችንና የመሬት ይዞታ ሠራተኞችን ማስረሸናቸውን ማስታወሱ ይበቃል። ማህበሮች በትእዛዝ የታገዱባቸው እንዲሁ ብዙ ቦታዎች ሲሆኑ ሸፍተው የነበሩ የሕዝብ ጠላቶች በተደናበሩ የደርግ አባላት አስተናባሪነትና በቢሮክራሲው አገናኝነት ከነትጥቃቸው እንዲገቡና እንዲደራጁ መደረጉ ጐልተወ የማታዩ እውቅ ጉዳዩች ናቸው። ይህም ተግባር እየተስፋፋ ለመሄዱ አንድ ምሳሌ መጥቀስ ይበቃል።
በሲዳሞ ክፍለ አገር በመስከረምና በጥቅምት ወራት በአሬሮ አውራጃ፣ በሃገረማርያምና በቡርጂ ወረዳዎች፣ በደራሳ አውራጃ፣ በአማሮ ኬሎ ወረዳ ሻለቃ ከተማና ሃምሳ አለቃ ከበደ የተባሉት የደርግ አባሎች ባዘጋጁት ሴራ መሰረት አበራ ሞልቶትና ሻለቃ ታከለ በተባሉት ባለስልጣኖች ቀስቃሽነትና መሪነት የነጌሌ ቦረናን አንድ ሻምበል ጦርና የአዋሳን ፈጥኖ-ደራሽ ጦር በማሰለፍ በጉጂና በደራሳ ብሄረሰቦች ላይ ከፍተኛ ዘመቻ በማድረግ ትልቅ እልቂት አድርሰዋል። ‘ተወናብደው ጫካ የገቡት እጃቸውን ሰጡ፣ ወደ ህብረተሰቡ ተመለሱ’ እየተባለ የሚለፈፍላቸው የቀድሞ የመሬት ከበርቴዎች ከክፍለ አገሩ ምክትል አስተዳዳሪ ከአበራ ሞልቶትና ከሻለቃ ታከለ ጋር በመተባበር፣ ከየካቲት እንቅስቃሴ በፊት ጀምሮ ‘መሬት ላራሹ’ በሚለው መፈክር ስር ይታገል የነበረውን ጭቁን የሲዳሞ ሕዝብ አብዮታዊ እርምጃ ለማደናቀፍ ትልቅ ዘመቻ አድርገዋል፤ ብዙ ሕዝብ አስጨርሰዋል።
እነዚህ የደርግ አባላት ከላይ የተጠቀሱትን ኃይሎች አስተባብረው በግንባር ቀደምነት በዘመቻው ሲሳተፉ ‘ጉጂ ሸፍቷል’ በሚል ቢሮክራሲው በፈጠረው ሃሰተኛ ምክንያት ነበር በተደረገውም ፀረ ሕዝብ ዘመቻ ሰባት ትላልቅ ቤተሰቦች የሚገኙበትን አንድ መንደር ከህፃን እስከ አበቃ ሽማግሌ ጨፍጭፈው አውድመዋል። በሲዳሞ አብዮታዊ ትግል በመሪነታቸው የታወቁትን እነ ኤለሹ በሪዎን፣ እነ ኤሌማን፣ እነ አዱላ ጉሌሌን፣ እነ ሮባ ማናሬን፣ እነ አስፋው ጃራን በሃገረማርያም ከተማ እስር ቤት አስገብተው ረሽነዋቸዋል። ከገበሬ ማህበራትም ከያንዳንዱ 25 ሰዎች አሰልፈው አንዱን ክፍል ከሌላው ጋር እንዲዋጋ አድርገው ብዙ ተራማጅ ገበሬዎችን ጨርሰዋል።
ወታደሮቹም ከነሻምበላቸው በነፍጠኞቹ እየተጋበዙና እስከ $ 10000 (አስር ሺህ ብር) ድረስ ጥሬ ገንዘብ ከመሬት ከበርቴዎች እየተዋጣ ተሰጥቷቸው ይህን ሁሉ አርሶ አደር ሕዝብ ሲጨርሱ ስናይ በወታደሩ ልዩ ልዩ ክፍሎች፣ በመንግስቱ ቢሮክራሲ፣ በጉልተኞች፣ በመሳፍንት ርዝራዦችና እንዲሁም በአድሃሪ የደርግ አባላት መካከል አብዮቱን ለመቀልበስ የተገባው ቃልኪዳን በሰፊው ሕዝብ ላይ ከፍተኛ አደጋን ሊያስከትል እንደሚችል ከመቼውም ይበልጥ ያረጋግጥልናል።
በሃረርጌ፣ በጋምጎፋ፣ በቡታጅራ የደርግ አባሎች ያስገረፉትን፣ ያስረሸኑትን የገበሬ ማህበር መሪ፣ ወይንም ፖሊሶች የሚያሳድዷቸውን ንቁ ገበሬዎች ለመዘርዘር ይህች ጽሁፍ አትበቃንም። አደጋውን ለመጠቆም ያህል የጠቀስናቸው ምሳሌዎች ይበቃሉ ብለን እንገምታለን። ይልቅስ ራሳችንን መጠየቅ ያለብን ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ የሚለውን ጥያቄ ነው። የታሪክ ፍርጃ ሆኖ መለዩ ለባሹ የንኡስ ከበርቴ መደብ ‘አብዮቱ ግንባር ቀደም ኃይል’ እየተባለ በሚወደስበት በዛሬው አስቸጋሪ ታሪካዊ ወቅት አብዮቱ እንዴት ሊገፋ ይችላል? ተራማጅነትን ከአድሃሪነት፡ አንዳንድ ሕዝባዊ ዝንባሌዎችን ከአጠቃላይ ፀረሕዝብነት ጋር አዋህዶ የያዘው፣ ለብሄር ትምክህተኛነቱ ለከት በማጣት በስመ አንድነት የአገሪቱን መገነጣጠል፣ የሰፊውን ሕዝብ እርስ በራሱ መተላለቅ የሚያዘጋጀው የቅራኔዎች ተዋህዶ የሆነው ደርግ እስከመቼ የአብዮቱ እንቅፋት ሆኖ ይቆያል?
የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮት በየካቲት በፈነዳበት ጊዜና እንደ ሰደድ እሳት ከዳር ዳር ተቀጣጥሎ ፍርስርሱ የወጣውን፣ የበከተውን፣የተላውን፣ በአጤ ኃይለስላሴ ቁንጮነት ይመራ የነበረውን ሥርዓት በደረመሰበት ጊዜና በዛሬው ጊዜ የሚታየው የሕዝቡ ትግል ቢፋፋምም ቢገፋም ቢንርም አብዮቱ ሊራመድ፡ ዳር ሊወጣ አልቻለም። ፊውዳሊዝም ከስልጣን ኮርቻ ለጊዜው ቢፈነቀልም አልተደመሰሰም። ኢምፔሪያሊዝምም በጥቂቱ ሲፈራ ሲቸር፡ አንዳንዴ ያውም በቃላት ደረጃ ጎሽም ቢደረግም ተጽእኖው ከአገራችን ጨርሶ አልተወገደም። አሁንም በቢሮክራሲውና በደርጉ ውስጥ ተሰግስገው የሚገኙት የፊውዳሊዝምና የኢምፔሪያሊዝም ቡችሎች አብዮቱን ሊቀለብሱት ይጥራሉ። የደርጉ ወላዋይነትና ፀረዲሞክራሲነት አሁን ከሕዝቡ ጋር ተሰልፎ፣ ወዲያው የትግሉ ማእበል ሲያይል ወደ ፀረሕዝብነት፡ ወደፀረአብዮትነት አንዲቀለበስ ያደርገዋል።
ሕዝቡን እንመራለን፣ ወይም እንደአባባላቸው ‘ጠበቃህ እንጂ ነገረፈጅህ አይደለንም’ የሚሉ አድርባይ ንኡስ ከበርቴዎችም የተራማጅነት ለምድ ለብሰው፣ ያልተደራጀውን ሕዝብ ከቢሮክራሲውና ከመንግሥቱ ኃይል ጋር እያጋጩ፣ ኃይሉን እያዳከሙ ፀረአብዮት ድርጊት ይፈጽማሉ። በውጭና በውስጥ እየተደራጁ፣ በአዋጅ ደረጃ የተገኙትን ድሎች ሊቀለብሱ ከሚጥሩት ኃይሎች ጋር በመተባበር፣ ጊዜው የማይፈቅደውን መፈክር በመሰንዘር፣ ሃቀኛውን ተራማጅ ለአድሃሪዎች በመጠቆም፣ ሕዝባዊ ሥርዓት የሚመጣበትን ጊዜ በአጉል ችኩልነት የሚያርቁት የእነኝህ ተራማጅ መሰሎች መኖርና በአንዳንድ አካባቢም ተደማጭነት ማግኘት የሕዝቡ ትግል ጐዳና ምን ያህል ረዥም፡ መራራና የተወሳሰበ እንደሆነ በግልጽ ያሳያል።
የአብዮቱን ዋና ጠላቶች ፊውዳሊዝም፣፡ ኢምፔሪያሊዝምንና ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝምን በተደራጀ የሕዝብ ኃይል መምታትና መደምሰስ በሚያስፈልግበት በዛሬው ወቅት ሰፊው ሕዝብና እውነተኛው ተራማጅ የተለያዩ ጠላቶችን በአንድ ጊዜ እንዲቋቋም ተገዷል። መራራ ትግል ማድረግ ቢኖርበትም ያለማመንታት ከትግሉ እሳት ውስጥ ይገባል። የጠላትን ኃይል በመልክ በመልኩ፡ ደረጃ በደረጃ ይሰባብራል። የሰፊውን ሕዝብ ትግል በልዬ ልዩ ዘዴ፡ ከልዩ ልዩ ጐዳና ወደአሳቻ መንገድ ሊመሩት የሚሹ ክፍሎች ሁሉ ስህተታቸውን ቢያርሙና ሌላውንም ከማሳሳት ቢቆጠቡ መልካም ነው።
የአብዮቱን ፋና ከፍ አድርጐ በግንባር ቀደምነት ሕዝቡን የሚመራ ሃቀኛና አብዮታዊ ድርጅት ሕዝቡ ካላቋቋመ አብዮቱ ዳር እንደማይደርስ ዛሬ ግልጽ ነው። እንደዚህ አይነቱንም ድርጅት ሰፊው ሕዝብ የግድ ይፈጥራል። ሁኔታው ያስገድደዋል። ዛሬ የተቀለበሰውም አብዮት በተራማጆች ህብረት (በደርጉ ውስጥ ካሉት ተራማጆችም ጭምር) እንደገና ወደመስመሩ እንዲመለስ፣ ፈሩን እንዲይዝ ሕዝቡ እንዲደራጅና እንዲታጠቅ ያስፈልጋል።
ስለዚህ እውነተኛ ተራማጆች፣ በታታኝ አጋፋጮች ሳይሆኑ እውነተኛ አብዮተኞችና አብዮቱ ደጋፊዎች በሙሉ ዛሬ ፀረሕዝብ የደርግ አባሎች እየተጋለጡ ለፍርድ እንዲቀርቡ፣ ሰፊው ሕዝብ ይደራጅና ይታጠቅ ዘንድ በአዋጅ የተወሰዱት መብቶች እንዲመለሱለት፣በአብዮታውያን ኃይሎች መካከል ሰፊና ሃቀኛ ውይይት እንደዲደረግ፣ የአብዮቱ መስመር እንዲጠራና የፀረአብዮቱ ኃይሎችም ላይ ለሚደረገው ከፍተኛ ትግል ዝግጅቱ እንዲፋፋም ‘የአስቸኳይ ጊዜ’ አዋጁ እንዲነሳና የታሰሩት ተራማጆች በሙሉ እንዲፈቱ ይጠይቃል፣ ይታገላሉም።
በዋነኞቹ የሰፊው ሕዝብ ጠላቶች ላይ ሰልፉን ለማሳመር ዛሬ ለዲሞክራሲያዊ መብቶች መታገል ያስፈልጋል። ለነዚህም የሚደረገው ትግል በንኡስ ከበርቴ ምኞች በሚረኩና መስመር በለቀቁ አደርባዩች እንደሚደረገው ፀረፊውዳልና ፀረኢምፔሪያሊስት መስመሩን በተዘዋዋሪ መንገድ በመከለስ አይደለም። ይህንኑ መስመር አጥብቆ ይዞ በዚህ የትግል ጐዳና ላይ የሚያደናቅፉንን ደንቃራዎች ሁሉ በልዩ ልዩ ዘዴ በመታገል ነው።
ዛሬ ከደርግ ጋር የሚያደርገው ትግል የሚፋፋመው ዲሞክራሲ አሁን በሚለው መፈክር ስር ነው። መንግስቱና ፀረሕዝብ ኃይሎች በሙሉ በሕዝቡ ላይ የሚፈጽሙት አሰቃቂ ድርጊት ከዲሞክራሲ መጥፋት የመነጨ መሆኑን ድርጊቶቹን እያጋለጡ በማሳየት ነው። የታሰሩ ተራማጅ ምሁራን፣ ዘማቶች፣ የሰራተኛ ማህበራት መሪዎች፣ የገበሬ ማህበራት መሪዎች እንዲፈቱ በማድረግ ነው። ፀረሕዝብ ድርጊት የሚፈጽሙት ቢሮክራቶችና ወታደሮች /ከደርግ አባላትም መካከል ሆኑ ከውጭ/ ፍርዳቸውን እንዲያገኙ በመታገል ነው።
በዚህ ወደ ድርጅት፣ ከዚያም ወደሕዝባዊ ትጥቅና ከዚያም ወደሕዝባዊ መንግስት እንደርሳለን። የአብዮት ቀልባሾች መተባበር ጊዜያዊ ችግሮችን ቢፈጥርም ከዚህ አላማችን ንቅንቅ አያደርገንም። አጥብቀን እንታገላለን። የመንደር አሉባልታና ቅጥያጣ የጥቆማ ዘመቻን እናወግዛለን። ገንቢ የሆነ ሃቀኛ ሂስን እንቀበላለን። ከቀኝም ሆነ ‘ከግራ’ ሆነው፣ በስልጣን ኮርቻ ላይ ወጥተውም ሆነ ለዚያ እያሽቃበጡ የሰፊውን ሕዝብ የአብዮት ጐዳና የሚያስቱትን፣ የሚያደናቅፉትን ሁሉ እናወግዛለን፣ እንታገላላን።
የሰፊውን ሕዝብ አብዮት የሚያዳክሙ ኃይሎች በሙሉ ይውደሙ።
እውነተኛ ተራማጆች የትግል አንድነት ይፍጠሩ፣ ያጠናክሩ።
የአብዮቱ ፋና ለዘላለም ይብራ።
አቅማችን የተወሰነ በመሆኑ ብዙ ቅጂዎችን
አላሰራጨንምና በይዘቱ የምትስማሙ አንባብያን
በሙሉ አንብባችሁ ላላነበቡ ብታስተላልፉ፣
ከተቻለ ጋዜጣው የሚበራከትበትን
ዘዴ በየፊናችሁ ብትፈልጉ ለትግላችን ይበጃል።