ሰሕድ ቁ. 5

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ቁጥር 5፤    መስከረም  7፣ 1967

የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ

መኢሶን በዚህ የሰፊው ሕዝብ ድምፅ እትሙ፣ ወታደራዊ ደርግ የአጼ ኃይለ ሥላሴን መንግሥት በአዋጅ ሽሮ፤ መስከረም 2 ቀን የመንግሥት ሥልጣን እንደያዘ ያስታውሳል።ከዚህም ጊዜ ወዲህ በአንጻሩ የትግሉና የለውጡ ባለቤት የሆነው ሰፊው ሕዝብ፣ ሃሳብ የማቅረብና ምክር የመስጠት መብት ቢሰጠውም፤ የመንግሥት አስተዳደር አካባቢ እንዳይደርስ ሆኗል ሲል ሁኔታውን ይገልጻል።ወታደራዊ ደርጉ በዚህ ውሳኔው፤ ለስልጣኑ ህጋዊነት ሽፋን ለመስጠትና የሕዝብ ተቀባይነት ለማግኘት፣ ሕዝቡ ተወካዮቹን ልኮ ሕዝባዊ መንግሥት ለማቋቋም ስለማይችል ነው የሚል የማድበስበሻ ገለጻዎች በመስጠት ላይ አተኩሯል። ባንድ በኩል፣ ሕዝቡ እንዳይደራጅ መብቶቹ ተነፍገውት፤ በሌላ በኩል፤ የመደራጀት ችሎታ ወይንም አቅም የለውም ማለት፤ “አያ ጅቦ ሳታማኻኝ ብላኝ” በሚል የአበው ተረት የሚገለጽ ቅጥፈት እንደሆነ ያሰረዳል።

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ለሰፊው ሕዝብ ሰራተኛ ገበሬ፣ ነጋዴ፣ ወታደር፣ ምሁር መብትና ጥቅም የሚታገል ጋዜጣ

የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ይቅደም

ቁጥር 5                                                                         ቀን 7/1/67

 

 

አልሸሹም ዞር አሉ፤

ትግሉ ይቀጥላል ።

ነገሩ ቀደም ብሎ አልቆ ነበር፤ በሦስተኛው ዙር የተቋቋመው ወታደራዊ ደርግ አጤን ወዲያ ብሎ የመንግሥቱን ስልጣን በእጁ አግብቶ ነበር። መስከረም 2/67 የመጨረሻው መግላሊት መድፋት በተግባር ቀደም ብሎ ያለቀውን በሕግ ማወጅ ነበር። በጥቂት ‘ምርጥ’ ወታደሮች የሚመራው ወታደራዊ መንግሥት ስልጣኑን ለብቻው መያዙን በይፋ አስታወቀ።

በ5/1/67 ጨካኙና ወንጀለኛው አጤ ኃይለሥላሴም ‘መለኮታዊ’ ስልጣኑን ተገፎ እስር ቤት ገባ። [መስከረም2/67] የተሰጠው መግለጫና አዋጅ ቁጥር 2 ‘በምርጥ’ ወታደሮች የሚመራው ደርግ በያዘው ስልጣን እንዴት እንደሚሰራበት የሚያስረዳ ነው። የትግሉ እንቅስቃሴ ባለቤትና የመንግሥት ስልጣን ምንጭ ለሆነው ሰፊው ሕዝብ ግን የተጣለለት ፍርፋሪ ‘ለምርጦቹ’ ሐሳብ ማቅረብ እና ማማከር እንጂ በፍፁም ውሳኔ ውስጥ ሳይገባ ራቅ ብሎ አይኑን እንዲያቁለጨልጭ ብቻ ነበር።

ደርጉ ለሰራዊቱ ውስጥ ውስጡን ገለጻ ሲሰጥ የወታደርን አገዛዝ ያወጀው ሕዝቡ ያልተደራጀ በመሆኑ ወኪሎቹን መርጦ ለሕዝባዊ መንግሥት ሸንጎ ለመላክ ስለማይችል ነው ብሎ መናገር ጀምሯል። ይህ መሰረተቢስና ፍጹም የማወናበጃ ሃሳብ ነው። ጨቋኙና ፈላጭ ቆራጩ የኃይለሥላሴ መንግሥት መብቱን ገፎት የፖለቲካ ማህበር እንዳያቋቁም ቢደረግም ሰፊው ሕዝብ በእድር፣ በሙያና በሌላ ልዩ ልዩ አይነት መንገድ የተደራጀና ብዙ አይነት ማህበራት ያለው መሆኑ ለማንም ግልጽ ስለሆነ፤ የተሰጠው ምክንያቱ ‘አያ ጅቦ ሳታመካኝ ብላኝ’ እንደተባለው ነው። ለመሆኑ በአንድ በኩል ሕዝቡን አትደራጅ እያሉ እያስገደዱ በሌላ በኩል ደግሞ ሕዝቡ አልተደራጀም ብሎ ማማት ትልቅ ቅጥፈት አይሆንም እንዴ?

ሌላው ደግሞ ገና ባላባታዊ አገዛዝ ከስሩ አልተመነገለም። ወንጀለኞቹም ገና ለፍርድ አልቀረቡም። በዚህ ሁኔታ ከሰፊው ሕዝብና ከወታደር የተውጣጣ ጊዜያዊ መንግሥት የተቋቋመ እንደሆን ጠላት ሊያንሰራራና እንደገና ሊመለስ ይችላል የሚል ሰንካላ ምክንያት ነው። ሕዝቡን በጣም ዝቅ አድርጎ መገመት ነው። ወዳጅና ጠላቱን ሕዝብ መለየት አይችልም ተብሎ ይሆን? ይህ መቼም የማወናበጃ ፕሮፖጋንዳ ነው።

የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ሕፃን ወይም ደንቆሮ አይደለም። ወዳጅና ጠላቱን ለይቶ ያውቃል። ትናንትና ከኃይለሥላሴ ጋር በሕዝቡ ላይ በደል ይሰሩ የነበሩት የጭቆናና የብዝበዛ መሳሪያና ግብረአበሮች ሰፊው ሕዝብ በተለይም ተማሪውና ተራማጆች ከአሥር ዓመታት በላይ የተጋደሉለትን የደም ትግል ፍሬ ለመቀማት ነው ሕዝቡን ከስልጣን ለማራቅ ጥረት የሚያደርጉት፣ ሕዝቡን በስልጣን ውስጥ እንዳይሳተፍ የሚያደርጉት? በዚህ በርካሽ አስተሳሰባቸው ሕዝቡን ሊደልሉት እንደማይችሉ ማን በነገራቸው? ሁሉንም ‘ግልጥልጥ አድርገን እንናገረውና’ ደርጉን ለጊዜው በቀጥታም ሆነ በስውር መንገድ የሚመሩት ‘ምርጥ’ መኮንኖች ትናንት መስከረም 6 ቀን ተማሪዎች ሰላማዊ ሰልፍ ቢያደርጉ በኃይለሥላሴ ዘመነመንግሥት በተለመደው ፋሽታዊ ዘዴ በመጠቀም ወታደሩ እንዲበታትናቸው አዘዙ፣ ፀረሕዝብና ፀረዲሞክራሲ መልክ አሳዩ። ወታደራዊው ደርግ የኃይለሥላሴን ቦታ በመውሰድ ላይ ነው።

ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ በቆራጥነትና በህብረት በየካቲት ወር ታሪካዊውን የትግል እንቅስቃሴ በይፋ የጀመረው መብቶቹን ለመጎናፀፍና ኑሮውን ለማሻሻል ነው። ይህንን ሊያደርግ የሚችለው ከራሱ የተውጣጣ የሕዝብ ለሕዝብ የሆነ ሙሉ ዲሞክራሲያዊ መንግሥት በማቋቋም እንጅ ራሳቸውን በሾሙ ‘ምርጥ’ ወታደሮች በሚመራ የወታደር መንግሥት አይደለም። ይህንን ደህና አድርጎ መገንዘብ ከትልቅ ስህተትና ጉዳት ሊያድነን ይችላል።

ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከመካከሉና ከጠቅላላው ወታደር በምርጫ የተውጣጡ አባሎች ያሉበት አንድ ጊዜያዊ መንግሥት አሁን ራሱን በመሾም ስልጣን የጨበጠውን የወታደር መንግሥት እንዲተካው፣ ዲሞክራሲያዊ ሬፐብሊክ /የሕዝብ መንግሥት/ አሁኑኑ እንዲታወጅ፣ መሰረታዊ መብቶችና ነፃነቶች በተለይ የንግግር የጋዜጣ የማህበር የመሰብሰብ የሰላማዊ ሰልፍ ወዘተ. ነፃነቶች ከአሁኑ ጀምረው ሥራ ላይ እንዲውሉ አጥብቆ ሲጠይቅ፣ በአሁኑ ወታደራዊ መንግሥት የሚደረጉትን ፀረዲሞክራሲ ድርጊቶችን ይቃወማል።

  1. ጊዜያዊ ነው ቢባልም ወታደሩ ለብቻው የመንግሥቱን ስልጣን መያዙን
  2. የቀድሞውን የኃይለሥላሴን አርአያ በመከተል ከፍተኛና ብዙ ስልጣን /ርእሰብሄር፣ ርእሰመንግሥት፣ የመከላከያ ሚኒስቴርነት፣ ጠቅላይ ኢታማዦርነት/ በአንድ ሰው እጅ መከማቻቱን
  3. በሕዝብ የተወከሉና ብዙ ግፍ የፈጸሙ መታሰር እና ለፍርድ መቅረብ የሚገባቸው ሹመት በሹመት የሆኑ ባዲሱ መንግሥት ከፍተኛ ስልጣን ላይ መሆናቸውን
  4. ለብዙ ዓመታት ደማቸውን እያፈሰሱ የኃይለሥላሴን የግፍ አገዛዝ ሲቋቋሙ የነበሩት ተማሪዎች በወታደራዊው መንግሥት እንደዋና ጠላት ተወስደው ከመስከረም 2/67 ጀምሮ በስድስትና በአራት ኪሎ አካባቢ መሳሪያ በማስፈርና ወታደር በማሰለፍ ለማስፈራራት መቃጣቱን፣ በመስከረም 6 ቀንም የተማሪዎችን የሰልፍ መብት በመንፈግ ወታደሩ መሳሪያ ይዞ በተማሪ ላይ መዝሙቱን
  5. በተራማጆችና በሰፊው ሕዝብ ወገኖች ላይ የማሰር፣ የማስፈራራት፣ የማሳደድ፣ የማባረር ከአዲስአበባ የማስወጣት እርምጃዎች መወሰዳቸውን
  6. የሲአይኤ ቡችሎች በደርጉ ውስጥና አካባቢ መኖራቸው እየታወቀ ምንም አይነት እርምጃ ካለመወሰዱም በላይ ከፍተኛ ቦታ እንዲሰጣቸው መደረጉን
  7. የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም ከኃይለሥላሴ ባላባታዊ አገዛዝ ጋር በመሻረክ አገሪቷን የእጅአዙር ቅኝ ግዛት አድርጎአት እንደነበረ ሲታወቅ ስለዚህ ዋና ጉዳይ ምንም እርምጃ አለመወሰዱን
  8. ሰፊው ሕዝብ የንግግር፣ የጋዜጣ፣ የማህበር፣ የመሰብሰብ፣ ወዘተ. መብቱንና ነፃነቱን መገፈፉን
  9. ደንበኛና ትክክለኛ አቋምና ፕሮግራም እስካሁን ድረስ ሳይቀየስ፣ ጭሰኛውና ድሀው ገበሬ በባለመሬቶች ያለ ርህራሄ ሲጨቆንና ሲበዘበዝ፣ ሠራተኛው ከሥራ ሲባረር፣ በብዙ መቶ ሺ የሚቆጠር ሕዝብ ያለ ምንም ሥራ በረሃብና በችግር ሲኦል ውስጥ እየሰመጠ ሲሄድና የአገሪትዋም ኢኮኖሚ እየተንኮታኮተ ውልቅልቁ ሲወጣ፣ ምንም አይነት እርምጃ አለመወሰዱን አጥብቀን እንቃወማለን።      
ዲሞክራሲ ያሸንፋል
ድሉ የሰፊው ሕዝብ ነው።

ጠንካራ መንግሥት ምንድን ነው?

ባለፈው ሳምንት በዚሁ ጋዜጣ ቁጥር 4 የአገራችን ጊዜያዊ የትግል እንቅስቃሴ ሊወስዳቸው የሚችል ሁለት አቅጣጫዎችን አመልክተን ነበር። የፈሩት ይደርሳል የጠሉት ይወርሳል እንደሚባለው ከነዚህ አቅጣጫዎች የሰፊውን ሕዝብ ጥቅምና ፍላጎት የሚፃረረው አስጊ አቅጣጫ ተወስዷል። እንደተናገርነው ‘ጊዜያዊ’ መሆኑን ብናምንም ባናምንም የወታደር መንግሥት ታውጆ የመንግሥት ስልጣን በጥቂት ሰዎች እጅ ተከማችቷል።

   የትልቁ ዘንዶ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ከስልጣን መውረድ ቀደም ሲል በሕዝቡ የተጠየቀና የሚደገፍ ሲሆን፣ ደርጉ ባገሪቱ ላይ ወታደራዊ አስተዳደርን ማወጁ ለሰፊው ሕዝብ ብቻ ሳይሆን በዲሞክራሲያዊ መንገድ ደርጉ እንዲወክለው ለመረጠው ለመላ ሰራዊቱና ሕዝባዊ መንግሥት እንዲቋቋም ለሚከራከሩት የሰራዊቱ ንዑስ ደርጎች /ለምሳሌ ለአየር ኃይል፣ ለመሃንዲስ መምሪያ፣ ለአርሚ አቬሽን ወዘተ. ንኡስ ደርጎች/ እንደ ዱብ እዳ የተጣለባቸው፣ ሰፊ ምክር ያልተደረገበት፣ ፀረዲሞክራሲያዊ ድርጊት ነበር። ውሳኔው በደርጉም ውስጥ ቢሆን ጊዜ ተወስዶና ታስቦበት የተደረገ ሳይሆን፣ ጥቂቶች ሰዎች በውጭ ያዘጋጁትና በደርጉ ጠቅላላ ጉባኤ ውስጥ በሽንገላ እንዲያልፍ ያደረጉት ውሳኔ መሆኑን ብዙ ምልክቶች ያሳያሉ።

ስልጣን አልፈልግም፣ በአፍንጫዬ ይውጣ በማለት ሲምል ሲገዘት፣ ዳር ደሩን ሲሽኮረመም ሰንብቶ አሁን እስልጣኑ ኮርቻ ላይ ጉብ ያለው ደርግ ወታደራዊ አስተዳደርን ሲያውጅ የሰጠው ምክንያት ‘ጠንካራ መንግሥት ያስፈልጋል’ የሚል ነው። ጠንካራ መንግሥት ምንጊዜም ያስፈልጋል። እንዲያውም መንግሥት ሁልጊዜም ጠንካራ መሆን ይገባዋል። ግን ወታደራዊው ያስተዳደር ደርግ የመንግሥት ጥንካሬ ምንጩ ምን እንደሆነ ያውቅ ይሆን? ስለ ጠንካራ መንግሥት ሲናገር በሳንጃና በጠመንጃ ላይ የተመሰረተ ጥንካሬ ማለቱ ይሆን? ለዚያ ለዚያማ የኃይለሥላሴ መንግሥት ጠንካራ ነኝ ይል አልነበረም? ሕዝቡን በመከፋፈልና የተቃውሞ ኃይሉን በመበታተን፣ የዋሁን በስብከት በማታለል፣ አድርባዩን በጥቅም በመግዛት፣ ለመብት ታጋዩን በሳንጃ እና በጠበንጃ ፀጥ በማሰኘት ለጊዜው እውነትም ጠንካራ ይመስል ነበር፣ በነበር ቀረ እንጂ። ታዲያ የኃይለሥላሴ መንግሥት ውሎ አድሮ የብዙሃኑ ሕዝብ ጠላት መሆኑና እውነተኛ የሕዝብ ድጋፍ እንደተነፈገው በግልጽ ተረጋገጠ። ጥንካሬውም ባሸዋ ላይ እንደተገነባ ቤት እንደነበር በማያጠራጠር አኳኋን ተገለጠ። እርግጥ ነው፣ ኃይለሥላሴን ከስልጣን ለማውረድ ከሃምሳ አመት በላይ ፈጅቷል። አሁን ግን ሕዝቡ መብቱን ስላወቀ መብቱን ተገፍፎ በቀላሉ ሊገዛ እንደማይችል ደርጉ ሊያውቀው ይገባዋል።

በሳንጃ በጠመንጃና በማጭበርበር ላይ የተመሰረተ የመንግሥት ጥንካሬ የአገዳ ምርኩዝ፣ ፀረሕዝብ ጥንካሬ ነው፣ ውሎ አድሮ መሰበሩ አይቀርም። እውነተኛ አስተማማኝና ዘለቄታ ያለው የመንግሥት ጥንካሬ በሰፊው ሕዝብ ፈቃደኝነት፣ ስምምነትና ተሳታፊነት ላይ የተመሠረተ ብቻ ነው። ከዚህ ውድ ጠንካራና ዘላቂ መንግሥት ሊቋቋም ይችላል ብሎ ማመን ራስን ማታለል መሆኑን ታሪክ ደጋግሞ አሳይቷል፤ አድሃሪዎች ታሪክን አያምኑም እንጂ።

እርግጥ ጥይት ሲተኮስ፣ ሳንጃ ሲመዘዝ ለጊዜው ለማስፈራራት ያገለግል ይሆናል። የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም የጥይት ምጽዋት ለማስደንገጥና ለማስፈራራት ይበቃ ይሆናል። ነገር ግን የእውነተኛ ጥንካሬ መሠረት ሊሆን አይችልም። ሰፊው ሕዝብ ለመብቱ ለመዋጋት ክንድ ለክንድ፣ ትከሻ ለትከሻ ገጥሞ ከዘመተ ጠላቱን በገዛ መሳሪያው ሊደመስስ ስለሚችል ምንም ዓይነት መሳሪያ አይበግረውም። መትረየስ ቢተኮስ፣ ታንክ ከፊቱ ቢደገን መፍራት የለበትም።

ስለዚህ ደርጉ የመንግሥትን ጥንካሬ የሚለካው በመሳሪያ ብቻ ከሆነ በህልም አለም ውስጥ እንደሚገኝ መረዳት አለበት። ጠንካራ መንግሥት የሚገኘው ሕዝቡ ራሱ ወኪሎቹን በመምረጥ ዲሞክራሲያዊ መንግሥት ሲመሰርት ነው።

እስካሁን በደርጉ ላይ የሚቀርበው ትችት በሙሉ በሦስት ዋና ሃሳቦች አካባቢ ነው። በትግሉ እንቅስቃሴ ውስጥ የሰፊው ሕዝብ፤ በተለይ የከተሜው ሱታፌ ጎልቶ እንዳይታይ ተጽዕኖ ማድረጉ፣ ባላባታዊ አገዛዝ ከስሩ እንዳይነቀል ሲያሽሞነሙን በመክረሙና ኢምፔሪያሊዝምን ጨርሶ ባላመንካቱ ነው። እርግጥ ወታደሩ ብቻውን በተለይም ደርጉ ብቻውን ባላባታዊ ሥርዓትን ያጠፋል ብለን አንገምትም። ከአቅሙ በላይ ይሆንበታል። እዚህ ላይ ዋናው ቅሬታ ሰፊው ሕዝብ በተለይ ሠራተኛውና ገበሬው ለተግባር እንዲዘጋጅ ባለመበረታታቱና እንዲያውም በመከልከሉ ነው፣ ሕዝቡ እየተደራጀ በትግሉ ለመሳተፍና ትግሉን ለማፋፋም በሚጥርበት ጊዜ አትሰብሰቡ፣ አትሰለፉ፣ እኛው እንሥራ፣ ቁጭብላችሁ ተመልከቱን በማለቱ ነው። ታዲያ ምን ሆነ? እነኃይለሥላሴ ተያዙ፣ አንዳንድ ነገሮች ተወረሱ፣ ሥርዓቱ እንዳለ ነው፣ አልተነካም፣ የብዙ ሕዝብ መብት የገፈፉ፣ የንፁህ አገርወዳድ ደም ያፈሰሱ ባለስልጣኖች አሁንም በስልጣን ላይ አሉ። ታዲያ ይህንን ነው መሰረታዊ ለውጥ ተደረገ ብላችሁ የምትናገሩት?

በኢምፔሪያሊዝም በኩል የደርጉ አቋም ከጥርጣሬ አልፎ እየተረጋገጠ በመሄድ ላይ ነው። በኢምፔሪያሊስ ገፈፋና ተጽዕኖ በቆረቆረቆዘች አገር ለጥቂት ቀናት ሳይሆን ለሦስት ወራት ፈላጭ ቆራጭ ሆኖ የቆየው ደርግ አንዳችም ፀረኢምፔሪያሊስት መግለጫ አለመስጠቱ ጥገኛነቱን ለመሸፈን እንዳይሆን ያሰጋል።

 የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝምን እንዳያስቆጣ የሚፈራና የሚሽቆጠቆጥ መንግሥት ከርሱ ተጽእኖ ያልተላቀቀ፣ የጥገኝነትን ጉዳትና ውርደት ገና ያልተገነዘበ መንግሥት፤ አለበለዚያም እንደነኃይለሥላሴ የሌባና የአጨበርባሪ መንግሥት ብቻ ነው። እንደዚህ አይነቱ መንግሥት አገሪቱን ወደመቀመቅ ይሰዳታል እንጂ አያሻሽላትም፣ አያራምዳትም። ይህ ደህና ተደርጎ መታወቅ አለበት። የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝምን የጥገኝነትና የብዝበዛ ዣንጥላ አሽቀንጥሮ መጣል በተለይ ለዛሬይቱ ኢትዮጵያ በጣም አስፈላጊ ነው። በዚህ አቅጣጫ ባለው ትግል ላይ ብርቱ ጥረት ማድረግ የሚያስፈልገውም ለዚህ ነው። ነገሩ ፊት ወደፈራነው አቅጣጫ በመሄድ ላይ ነው። የሲአይኤ ቡችሎች በአስተዳደሩ ደርግና እርሱ በመሰረተው መንግሥት ውስጥ ጎላ ብለው መታየት ጀምረዋል። ይህ እንዳይሆን [የሚያደርግ] በኢምፔሪያሊዝም የሚደገፍ ጠንካራ መንግሥት አናውቅም፣ ታሪክ አያስተባብለንም።

 የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም በገንዘብም ሆነ በመሳሪያ መልክ ድጋፍ ሊሰጥ ይችላል። የሚሰጠው ግን እርግጠኛ ሲሆን ነው፣ አስሮ ነው። ለመበዝበዝ እንዲመቸው ሲሆንለት፤ መንግሥቱ አሜን ብሎ ሲሰግድለትና የፈለገውን ያህል ሕዝቡን እንዲዘርፍ በር ሲከፍትለት ብቻ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብስ የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝምን ከሃያ ዓመታት በላይ ያውቀው የለም እንዴ? ሕዝቡ ይህን አይደግፍም። የኢምፔሪያሊዝም ጥገኝነትን ምንጊዜም ቢሆን አይደገፍም። ዋና ጠላ ነውና።

በሌላ በኩል ደግሞ ለደርጉ ከየቦታው የተሰጠው ድጋፍ መልክ የያዘና ወሰን ያለው እንጂ ሙሉ በሙሉ በድፍኑ አይደለም። በሰፊው ሕዝብ ዘንድ ያስተዳደሩ ደርግ የተደገፈው የኃይለሥላሴንና የአንዳንድ ግብረ አበሮቹን ጉድ እና ወንጀል ዘርዝሮ ከስልጣን በማውረዱ ብቻ ነው። መንግሥታዊ ስልጣንን ደርጉ መውሰዱን፣ ባንዳንድ ሰዎች እጅ ስልጣን አለቅጥ መከማቻቱን፣ የኃይለሥላሴ መንግሥት የስለላ ድርጅት /የፀጥታ መስሪያ ቤት/ መሪ ሆኖ የሕዝብን አፍ በማሰር፣ መብት በመግፈፍና የብዙ ንጹሃን የአገር ተቆርቋሪዎችን ደም በከንቱ ያፈሰሰውን ነፍሰ ገዳይ የኮሎኔል በላቸው ጀማነህን የአገር ግዛት ሚኒስትርነትና እንደሚወራውም የደርጉ ምክትል ሊቀመንበር ሆኖ መሾሙን አይደለም። እነዚህን ሕዝቡ አይደግፍም፤ በራሱ ላይ መፍረድ ይሆናልና። ራሱ በጊዜው ፖለቲካ ትግል እንዳይሳተፍ ተከልክሎ በአጨብጫቢነት ደረጃ ብቻ ተቀምጦ እንዲመለከት መገደዱንስ ሕዝቡ እንዴት ይደግፋል?

ወታደራዊው ‘ጠንካራ መንግሥት’ ከሕዝቡ ጋር ያለውን ግንኙነት ስንመለከት፣ የሚያወራውንና የሚሰራውን ስናገናዘብ፣ የደርጉ እርምጃ ከጠቅላላው ወታደር ፍላጎት ጋር ምን ያህል እንደሚስማማና ምን ያህል እንደሚለያይ ስናመዛዝን፤ የዚህ አይነቱ መንግሥት ምን ያህል ዘላቂነት አለው ብለን እንጠይቃለን። መልሱ ከባድ አይሆንም። ዞሮ ዞሮ የአንድ መንግሥት እውነተኛ ጥንካሬ የሚመነጨው ሕዝቡ ከሚሰጠው ድጋፍ ነው። ሕዝቡን የማይወክል፣ ሕዝቡ የማይሳተፍበት፣ የሕዝቡን ፍላጎት የማያሟላ መንግሥት ለጊዜው ቢደነፋና ቢያስፈራራም እውነተኛ ጥንካሬ የለውም፣ ደካማ ነው። መንግሥት የሚጠነክረው የሕዝቡ መንግሥት ሲሆን ነው፣ በዲሞክራሲያዊ መንገድ ሲመረጥ ነው፣ የሕዝቡን፣ በተለይም የሰፊውን ሕዝብ ፍላጎትና ጥቅም ሲጠብቅ ነው፣ የሕዝቡን መሰረታዊ መብቶች ሲያምንባቸውና በሥራ ላይ እንዲውሉ ሲያደርግ ነው። ይህን የማያደርግ ሁሉ ጥንካሬው እጅግ በጣም የተወሰነ ነው። ያለሰፊው ሕዝብ ጥንካሬ የለም።

ያልተብራሩ ዓላማዎች

ሦስተኛው ዙር የጦር ኃይሎች እንቅስቃሴ ከጀመረ እነሆ ከሦስት ወር በላይ ሆነው። በዚህ ረጅም ጊዜ ውስጥ ደርጉ አንዳንድ ነጠላ ድርጊቶችን /ባለስልጣኖችን ማሰር፣ የኃይለሥላሴን ሀብት መውረስ፣ ኃይለሥላሴን ከስልጣን ማስነሳት፣ ወዘተ./ ከመፈፀም በስተቀር ጠለቅ ብሎ ሰፊው ሕዝብ ከየካቲት ጀምሮ ያነሳቸውን መሰረታዊ ጥያቄዎች ሊያሟላ የሚችል ፕሮግራም እስካሁን አላወጣም። የሕዝብ ወገን የሆኑ ተራማጆች እንደዚህ አይነቱ የተሟላ ፕሮግራም አስፈላጊ መሆኑን ደጋግሞ ከመግለጽ ካለመቆጠባቸውም ሌላ ጠቃሚነት ያላቸው በርከት ያሉ ንድፎች ማቅረባቸው የታወቀ ነው። ታድያ ደርጉ ደንበኛ ፕሮግራም ለማውጣት ምን ይሆን ችግሩ? እንዲሁም ‘ኢትዮጵያ ትቅደም’ ሲባል የርእዮተአለም ይዘቱ ምን ይሆን? ምን ይዘን ነው የምንጓዘው? ሰፊው ሕዝብስ ምን አይቶ ለወታደራዊው አስተዳደር ድጋፍ ይስጥ? ኃይለሥላሴ ተነስቶ ሌላ ኃይለሥላሴ ላለመተካቱ ዋስትናችን ምን ይሆን? የሰፊውን ሕዝብ የዕለት ኑሮ በሚመለከተው በኩል ‘አንድም ታለበ ሺህ ያው በገሌ’ ከተባለው አልፎ የባሰ አታምጣ ከማለት እንዳያደርስ ያሰጋል።

ደርጉ እስካሁን በከባድ ቃላት የተካቡ መግለጫዎች ከመስጠት በስተቀር ወደ ውስጥ ሰቅስቆ ገብቶ ችግራችንን ሊፈታ ያሰበ አይመስልም። ለምሳሌ ደርጉ እንደተቋቋመ ያወጣው ባለ13 ነጥብ ‘አላማ’ ፍፁም የተወናበደና ያልተብላላ ከመሆኑም ሌላ ወደ ሥራ ለመተርጎም የሚያስቸግር፤ በፊት ኃይለሥላሴ እና እንዳልካቸው ለኢትዮጵያ ሕዝብ ከሰጡት ድፍን ተስፋ የማይሻል ነው። ይህ ሲገርመን በመስከረም 2/67 ኃይለሥላሴን በማስወገድ ስልጣን ሲጨብጥ ደርጉ ያወጣቸው ባለ15 ነጥብ ‘ዓላማዎች’ አፍ ጭራቸው የማይያዝ፤ በተቻለ መጠን ከመሰረታዊዎቹ ሕዝባዊ ጥያቄዎች ለመሸሽ ትልቅ ትግል የተደረገባቸው፣ ደርጉ እራሱ መሰረታዊ ለውጥ ለማድረግ ያልፈለገ መሆኑን ይከስቱበታል። ዋና ዋና ጥያቄዎችን በተወናበዱ ቃላት ሸፍኖ ፍፁም አግባብ የሌላቸውን ጉዳዮች በዝርዝር ያቀርባል።

የመጀመሪያው ዓላማ ደርጉ የ‘ማንኛውም ኢትዮጵያዊ እኩልነት፤ ይኽውም የገበሬው፣ የወዝአደሩና የሌላ’ውም ጠቅላላ ሕዝብ መብትና እድገት በሚገባ እንዲጠበቅለት ያደርጋል ይላል። እዚህ ላይ ጠቅላላ ሕዝብ ሲል ምን ማለቱ ነው? በዝባዡም እንዲበዘብዝ፣ ተበዝባዥም እንዲበዘበዝ ‘መብትና እድገት’ ይጠበቅለታል ማለት ይሆን? መብትስ ሲባል የምን መብት ነው? እድገትስ የምን አይነት እድገት? እነዚህ ማብራሪያ የሌላቸው ተጨባጭ ያልሆኑ ቃላት በትናንቱ ጨቋኞችስ በየጊዜው ይወሱ አልነበረም? ደግሞም የሕዝቡ መብት የሚጠበቅ ከሆነ ሕዝቡ የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ እና የመደራጀት መብቱን ለምን ተገፈፈ? ደርጉ ለምን ድፍረት ገዝቶ ሀሳቡን ግልጽ በሆነ መንገድ አያቀርብም?

ሁለተኛው አላማ ‘በጎሳና በሃይማኖት የተመሰረተው መለያየትና የኑሮ መራራቅ ‘ኢትዮጵያ ትቅደም’ በሚለው ዓላማ መሠረት ያስወግደል ይላል። ኢትዮጵያ ትቅደም የሚለው አላማ ራሱ በብዙ በተለያዩ መንገዶች ሊተረጎም የሚችል ሲሆን እንዴት ችግርን ያስወግዳል ተብሎ ተስፋ ሊጣልበት ይቻላል? በመሰረቱ ‘ኢትዮጵያ ትቅደም’ ሲባል የሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ መብትና ጥቅም ይቅደም፣ ኑሮ ይሻሻል ወዘተ. መሆን ሲገባው፤ ደርጉ ግን እርስበርሳቸው ተፃራሪ በሆኑ አቅጣጫዎች ይተረጉመዋል። አንዳንዴ ምድሪቷን፣ አንዳንዴ ሕዝቧን በጠቅላላ፣ አንዳንዴም ሰፊውን ሕዝብ ብቻ፤በሚጠቅስ መንገድ የተረጉመዋል። እስካሁን ጥርት ያለ ትርጉም አልሰጠውም።

3ኛው፣ 5ኛው፣ 8ኛው፣ 9ኛውና 10ኛው ዓላማዎች ስለመጥፎ ባህሎችና ሞራል መጥፋት፣ ስለ ፍርድ መስተካከል፣ ስለመላዉ ህብረተሰብ እኩልነት፣ ስለመብትና ስለብሔራዊ ስሜት ያወራሉ። እነዚህ ሁሉ ያው በደነዙ ቃላት የተጻፉ ከመሆናቸውም ሌላ የእነዚህ መሰረት የሆነው የኢኮኖሚ እኩልነት ተድበስብሶ ቀርቷል። እንደሚታወቀው በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ የኑሮ መለያየት፣ የፍትህ መጓደል፣ ‘ከራስ በላይ ነፋስ’ የሚለው ዘይቤ የሚያይሉት የህብረተሰቡ አባሎች በመደብ ተከፋፍለው አንደኛው ሌላውን ሲበዘብዝና ሲጨቁን ነው። የሃብት መለያየት ካለ በዝባዥና ተበዝባዥ፣ ጨቋኝና ተጨቋኝ፣ የፍትህ መጓደልና መንዛዛት፣ የሚያደናቅፉ ‘ባሕላዊ እምነቶችና ዘይቤዎች’ ይኖራሉ። የኢኮኖሚ መደላደል ሳይኖር ሌሎቹን ችግሮች ልወጣ ቢሉ በጅ የማይል ጉዳይ ነው። ባጭሩ ‘የኢኮኖሚ ደረጃ ማስተካከልን እሹ፤ ሌላው ሁሉ ይጨመርላችኋል’ ብንል ከእውነት አንርቅም። ዓላማዎቹ ከባህልና ከሞራል ይልቅ ወደ እነዚህ መሰረታዊ ጉዳዮች ማተኮር አለባቸው።

4ኛው አላማ ስለመሬት መሻሻል ያወራል። ይህ ጉዳይ የኢትዮጵያ አርሶአደርና ወዝአደር መሰረታዊ ጥያቄ፣ የአገሪቱም ሞት ሽረት የሚለይበት ሲሆን ደርጉ በዚያው በተምታታ ዘዴ አልፎታል። ‘…ይህ እስከሆነ ድረስ ጭሰኛ የሆነው ሁሉ በሰፈረበትና በሚያርሰው መሬት ላይ የመኖርና የመጠቀም ዋስትና ይኖረዋል…’ የሚለው በትክክል ምን ማለቱ ነው? ጭሰኛው ለባለ መሬቱ ሲሶ እኩል ወዘተ. ያፈስሳል ወይስ የመንግሥት ግብር ብቻ እየከፈለ የድካሙን ዋጋ በሙሉ ይጠቀምበታል ማለት ነው? ይህ አፃፃፍ ሁኔታውን ከማባባስ በስተቀር ምንም መፍትሄ አይሰጥም። ‘መሬት ላራሹ’ በሚባልበት ጊዜ ከምርቱ እስከ 75% የሚሆነውን ለመሳፍንትና ለባላባቶች እንዲያስረክብ የሚገደደው ጭሰኛ ገበሬ ይዞታው የግሉ ሆኖ የላቡን ዋጋ ለራሱና ለቤተሰቡ ያድርግ ማለት እንደሆነ ይታወቃል፤ ታዲያ ደርጉ ‘ተራ ገበሬ’ የሚለው ይህንን ይሆን ወይንስ መሬት ከባላባቶች እየተከራየ ወይም እየገዛ በዘመናዊ መሳሪያዎች የሚያርሰው ‘ኑሮው በእርሻ የሆነው’ ከበርቴ ገበሬን ይሆን? ሕጉ ‘ባስቸኳይ’ ይወጣል ሲባልስ ምን ያህል አስቸኳይ ይሆን? ዛሬ ባለመሬት እና ጭሰኛ ተፋጧል። ዛሬ ነገ እያለ መጠበቅ ሰልችቶታል። ታዲያ እንደገና ሌላ ተስፋ መስጠት ችግሩ ፊት ላይ እስኪወድቅ መጠበቅ አይደል?

6ኛውና 7ኛው ዓላማዎች ስለጤና ጥበቃና ትምህርት መስፋፋት ይናገራሉ። ‘የጤና ዘመቻ’ ሲባል አቅም የሌለው ሁሉ የህክምና አገልግሎት በነፃ ለማግኘት መቻሉን አይገልጽም። የህክምና አዋቂዎች፣ ሆስፒታሎችና ክሊኒኮች በገጠርና በከተማ መካከል አሁን ያላቸው አድልዎ መወገድ ይገባው እንደሆነ፣ እንዴት እንደሚሻሻልና እንደሚጠፋ ምንም ዓይነት ፍንጭ አይሰጥም። በትምህርትም በኩል ቢሆን ለገጠሬውና ለወዝአደሩ ልጅ እንዴት እንደሚዳረስ አያወሳም። ትምህርት ከሥራ ጋር መያያዝ እንደሚገባውና ትምህርት ከግል ይልቅ ለህብረተሰቡ አገልግሎት እንደሚውል የሚያስችል ዘዴ አይተልምም። እንደዚያው እንደጥንቱ ‘ይስፋፋል፤ ይደረጋል’ ብቻ። ለውጡ የት ላይ ይሆን? አንቀጽ 11 ምን ለማለት እንደፈለጉ የማይገባ የቃላት ክምችት ነው ቢባል ብዙ መሳሳት አይሆንም። ‘ህብረት’ ‘እኩልነት’ ‘አስተሳሰብ’ የሚሉትን ቃላት ጣል ጣል አድርገው ተወናብደው ያውናብዳሉ። የኢትዮጵያ ዋና ችግር የመሳፍንት ታሪክና ቅርስ ዘበኝነት የሆነ ይመስላል አንቀጽ 14 ስለ ‘ባህልና የኪነጥበብ ቅርሳ ቅርሶችን’ መደራጀት ያወራል። ዳቦና ውኃ ላረረበት ሕዝብ ይሄ ምን ይበጀዋል? ለምን ደርጉ የመጀመሪያውን ተግባር በመጀመሪያ ለመሥራት እንደማይፈልግ ለማወቅ ያስቸግራል።

በውጭ ጉዳይም በኩል ገለልተኛ ነን፣ ቅኝ ግዛትን እንቃወማለን ወዘተ. ተብሏል። ግን የሚፈለገው ከኢምፔሪሊዝም በተለይ ከአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ጋር ኃይለሥላሴ የተፈራረማቸው ስምምነቶች መሰረዝና ፀረኢምፔሪያሊስት መሆንን ያለማወላወል መግለጽ ነበር። ሌላ ስፍራ እንደተመለከተው ወታደራዊው መንግሥት የበለጠ የኢምፔሪያሊዝም ጥገኛ አንዳያደርገን የሚያሰጋ ነው።

‘የደርጉ ዓላማዎች’ በመባል የወጣው ጽሑፍ በአጠቃላይ ሲታይ እንዳልካቸው ካንድ ወር በላይ ሲንደፋደፍበት ከከረመው የማጭበርበሪያ መመርያው፣ ኃይለሥላሴ የአምስት አመት ፕላን እያለ የኢትዮጵያን ሕዝብ ያወናብድበት ከነበረው ብዙ አይለይም። ነገሩ ከእጅ አይሻል ዶማ አይነት ነው ቢባል ከእውነት መራቅ አይሆንም። የሚፈለገው መሰረታዊ ለውጥ ነው ወይስ ላይ ላዩን ኪፍ ኪፍ፣ ነካ ነካ፣ አገም ጠገም? በእንደዚህ አይነት መንገድ ብዙ መሄድ ይቻል ይሆን? አይመስለንም።


(በዋናው እትም ላይ ስእል አለ)

Scroll to Top