ልዩ እትም 1 1970

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ልዩ እትም፣    መስከረም 7፣ 1970

የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ

በ1969 ነሃሴ መኢሶን የትግል ስልቱን ቀይሮ በህጋዊው መድረክ ላይ የተሰማሩት አብዛኛዎቹን አባላቱን ሁቡዕ እንዲገቡ ውስኔ ያስተላልፋል። መኢሶን ህጋዊውን የትግል መድረክ ጥሎ በመውጣቱና በወሰዳቸው የፖለቲካ አቋሞች የተደናገጠው ቢሮክራሲ፣ ከቢሮክራሲው ጋር የተቃቀፈው ደርግና በአካባቢው የነበሩ አስመሳይ ተራማጆች መኢሶንን ማጥቃትና ስሙንም ማጥፋት ይጀምራሉ።

በዚህ ልዩ እትም ላይ፣ መኢሶን ህቡዕ ለመግባት የተገደደባቸውን ምክንያቶች ከዘረዘረ በኋላ መኢሶን ‘ፈረጠጠ’፣ ‘ተንሸራተተ’ የሚሉት ክሶች የመኢሶንን አቋምም ሆነ የስልት ለውጥ የማይገልጹት እንደሆነ ያብራራል። በተጨማሪም መኢሶን የሰፊው ህዝብ ጥያቄዎች የሆኑትን የዴሞክራሲያዊ መብቶችን መለቀቅ ጉዳይና ሌሎች የአብዮቱን አንገብጋቢ ጥያቄዎችን በዝርዝር ያቀርባል።

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ለሰፊው ሕዝብ ሰራተኛ ገበሬ፣ ነጋዴ፣ ወታደር፣ ምሁር መብትና ጥቅም የሚታገል ጋዜጣ

የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ይቅደም

 
ልዩ እትም                                                                    ቀን 07/01/70

 

የመኢሶን የትግል ስልት ለውጥና

የአድርባዮች አሉባልታ

ጠቅላላ ኅብረተሰባዊ ቀውስ በሰዎች ዘንድ የአእምሮ ቀውስ የሚያስከትል መሆኑን ሌኒን በየጊዜው የሜንሼኪቮሽች ምሳሌ እየተቀሰ ይናገር እንደነበር ይታወሳል። ማለትም ኀብረተሰቡ ከተለመደው ጎዳና አፈንግጦ፣ በከፍተኛ ሶሺያል፣ ፖለቲካና ኤኮኖሚ ውጥረት ሲያዝ የሰው መንፈስ ይሸበራል፣ ይጨነቃልም። የፖለቲካል ፓርቲዎችም እንደዚሁ ጥራት ያለው ፖለቲካ እስካልተከተሉ ድረስ፣ በየወቅቱ በሚፈጥሩት ውስብስብና ውጥረት በውጥረት የታከለባቸው ሁኔታዎች ግራ ይጋባሉ፣ ይጨነቃሉ፣ የሚይዙትንና የሚለቁትን ያጣሉ። ከሁኔታውም ጋር አብረው መራመድ ስለሚያቅታቸውና ከሁኔታው ጋር አብረው መራመድ ስለሚሳናቸውም፣ ስህተተኛ የፖለቲካል መስመር መከተላቸውና ከሁኔታው ጋር በማይጣጣሙ የትግል ስልቶች መጠቀማቸው የማይቀር ነው። ይህ ብቻ አይደለም። በየወቅቱ የትግል መስመራቸውንና የትግል ስልታቸውን ከሁኔታው ጋር እያገናዘቡ ለሚያራመዱት ታጋዮችና ታጋይ ድርጅቶች እንቅፋት፣ ለሕዝቡም ትግል ማነቆ ይሆናል።

ውስብስብና አስቸጋሪ የሆነ ሁኔታ ሲፈጠር፣ በዚሁ ሳንሸበር የሁኔታውን ምንነትና የሄደቱን አቅጣጫ ተረድተን ትክክለኛውን የትግል መስመርና ዘይቤ ለመቀየስ የምንችለው በሳይንሳዊ ሶሻሊዝም ቴዎሪ የተመራን ብቻ እንደሆነ ነው። ብሩህ የሆነብን የሳይንሳዊ ሶሻሊዝም ፋና እየተንቦለቦለ የምንጓዝበትን ጎዳና እያበራልን ስለምንራመድ መንገዱ ጨልሞብን ከመደናበርና አቅጣጫ ስቶ ገደል ከመግባት ያድነናል። ትክክለኛ የፖለቲካ መስመር ለመቀየስና ከጊዜ ጋር የሚሄድ የትግል ስልት ለመከተል ጠለቅ ያለ የማርክሲስት ሌኒኒስት ርእዮተዓለም እውቀት ብቻ ሳይሆን፣ አብሮትም ርእዮተ ዓለሙን የተመረኮዘ የተጨባጩ ሁኔታ ተጨባጭ ጥናት ያስፈልጋል። ማለትም ታክቲኮችንና የትግል ዘይቤዎችን መፍለቅ ያለበት ማርክሲዝምን ሌኒኒዝምን ከተመረኮዘው የሁኔታው ተጨባጭና ዳይሌክቲካዊ ጥናት መሆን አለበት።

አንድ አብዮታዊ ማርክሲስት ሌኒኒስት ድርጅት አብዮቱ የሚጠበቅበትን ለማበርከትና በየወቅቱ ከሚለዋወጠው የፖለቲካ ሁኔታ አብሮ ለመራመድ እንዲችል፣ በተለያዩ አቅጣጫዎች፣ መስኮችና የትግል ስልቶች መጠቀም መቻል አለበት። ለምሳሌ በሕጋዊና በሕገወጥ፣ በሰላማዊና በአመፃዊ፣ በፖለቲካልና በኢኮኖሚክ፣ በወታደራዊና በዲፕሎማሲያዊ፣ ወዘተ መንገዶች፣ አቅጣጫዎች መስኮችና ከሁኔታው ጋር አብረው በሚሄዱ የትግል ዘይቤዎች መጠቀምና መታገል መቻል ያስፈልገዋል። ይህ ካልሆነ ከሁኔታው ጋር ሊራመድ፣ ከፊቱ የተደቀኑትን ተግባሮች ሊያከናውን፣ የጠላትን ግፊት ሊቋቋም አይችልም።  ለአብዮት አልተዘጋጀም ማለት ነው። የአንድ ማርክሲስት ሌኒኒስት ድርጅት የተለያዩ የትግል ስልቶችን ማወቅ፣ ቦታው እንደሚጠይቀው ከአንዱ የትግል ስልት ወደሌላ እንዲሸጋገር ከማስቻሉም በላይ፣ በወቅቱም ከዳተኛ ድርጅታዊ እንቅስቃሴና ታጣፊነት እንዲኖረው ያደርጋል። ከዚሁ ቦልሼቪኮች ፓርቲ የትግል ታሪክ ዓይነተኛ ምሳሌ ነው። ለምሳሌ  ከየካቲት 1917 እስከ ጥቅምት 1917 የነበረውን የትግል ወቅት ስንመለከት፣ በቦልሼቪኮች እንደሁኔታው እያፈራረቁ በሕጋዊና በሕገወጥ፣ በግልፅና በህቡዕ፣ በሰላማዊና አመፃዊ የትግል ስልቶች ይጠቀሙ እንደነበር፣ በአጠቃላይ እነሌኒን በግልጽ ሰፊውን ሕዝብ ለመቀስቀስ ከፍተኛ ትግል ሲያካሂዱ እንደነበርና ነገር ግን በሐምሌ 1917 ጠላቶች እነሱን ለመግደልና ለማጥፋት ሲነሱ “ሸሽተው” (ሸሽተው የሚለውን ቃል ደፍሮ ለመጠቀም) ትግላቸውን በሕቡዕ እንደቀጠሉ ይታወቃል።

መኢሶን በማደግ ያለ የትግል ድርጅት ነው። ሆኖም የዚህንም ድርጅት የትግል ታሪክ እንኳን ባጭሩ ብንመለከት፣  “ሁሉም ነገር ለአብዮቱ” የሚለውን መርሆ በመከተል ለሁኔታው ተስማሚ የሆኑትን የትግል ስልቶች ከመቀየስ ወደኋላ ብሎ አያውቅም። ነገሮች አንዳንዴ ይረሳሉ። ግን ቢያንስ ቢያንስ በአሁኑ ሰአት መኢሶን ከጊዜያዊ አስተዳደር ደርግ ጋር በተለይም ከተራማጁ ክንፍ ጋር በህብረት ባለፉት አንድ ዓመት ተኩል አብሮ ለመስራት ያደረገው ጥረት ሊረሳ አይገባም። በዚያን ጊዜ “ፋሺስቱ” ደርግ እንደዚያ በአድሃሪያንና በቀኝ ክንፍ ንኡስ ከበርቴ ቡድኖች ቅስቀሳ የሰፊው ሕዝብ ወገኖች ሳይቀሩ በተወናበዱበት ጊዜ በመስመሩ ትክከለኛነት ፍጹም እምነት ስለነበረው በአድሃሪዎችና በአደርባዮች መረባረብ ሳይደናገጥ አብዮቱ እንዲገፋ ከጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ጋር በመተባበር አንዳንድ አባሎችን በሕጋዊ የትግል መስክ አሰማርቶ ሠርቷል። ያኔም ሆነ አሁን መኢሶን የትግል ስልቱን የሚቀይሰው በልወደድ ባይነትና በአደግዳጊነት በመመራት ሳይሆን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ለኢትዮጵያ አብዮት ወደፊት መግፋት የሚቻለውን ለማበርከት ነው። ከጥቂት ጊዜ ወዲህ በተፈጠረው አዲስ ሁኔታ እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ የትግል ስልቱን በመቀየር በሕጋዊ የትግል መስክ ተሰማርተው የነበሩትን አንዳንድ አባሎች መኢሶን ወደ ሕቡእ እንዲዛወሩ ማድረጉ ይታወቃል። ይህ የትግል ስልት ለውጥ ለምን እንደተደረገ ከዚህ በፊት ቢገለጽም ምክንያቶችን እንደገና እንደሚከተለው በአጭሩ በሦስት መደብ ለማቅረብ ይቻላል።

ሀ. የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ በፍጹም አደርባይነት በመዋጡ፣ ከቢሮክራሲው ጋር መተቃቀፍን በመያዙ፣ ለሰፊው ሕዝብ አብዮት ወደፊት ግፊት አስቸጋሪ የሆነ ሁኔታ ተፈጥሯል። ይህ ሀቅ የሚገልጸው አብዮታችን ከአጥቂነት ወደተከላካይነት መፈግፈግና የፀረ ሕዝብ ኃይሎች ማንሰራራትን ሲሆን በሌላም በኩል በሕጋዊ መስክ በተሰማሩት ጓዶች ላይ በሚደረገው ክትትልና የነርሱንም ሥራ ለማደናቀፍ በሚደረገው ጥረት ነው። ስለሆነም ማለትም በአጠቃለይ የሕጋዊ መስክ በመዋከቡና ከዚሁም የሚገኘው ውጤት ስለቀንሰ፣ መኢሶን ሰፊውን ሕዝብ በበለጠ ለማገልገልና የአብዮቱን ሂደት ለማፍጠን ሲል በሕጋዊ መስክ ከተሰማሩት ጥቂቶቹን ወደ ህቡዕ ለማዞር  ወሰነ።

ለ. ለሥልጣን የተስገበገቡ ኃይሎችና አድሃሪ ቢሮክራቶች በመመሳጠር ተራማጅ ግለሰቦችን፣ የመኢሶን አባላት ናቸው ብለው የሚጠሯቸውን ጓዶች ለማስገደል ፋሽስታዊ የሆኑ የነፍሰ ገዳይ ቡድኖች እንዳቋቋሙ ስለተደረሰበት፣ ይህ የጠላት በትር ሊሰነዘር የታቀደባቸውን ጓዶች ወደህቡዕ ማዛወሩ ለአባላቱ ያለበትን ግዴታ ለመጠበቅ ብቻ ሳይሆን፣ የጠላትንም ሴራንም ጭምር ለማክሸፍ ነበር። ይህንን ጥቃት ያዘጋጁ እንደነበር የሚያውቁ ምናልባትም ተባባሪ የነበሩ፣ ዛሬ “ፈርጣጮች” ከሚሉን ውስጥ ይገኙባቸዋል።

ሐ. በሐገራችን ላይ በማንዣበብ ላይ ባለው ፀረ አብዮት ሴራ እስካሁን ድረስ የተገኙትን የፖለቲካ፣ የሶሺያልና የኢኮኖሚ ድሎች እንዳይቀለበሱ፣ ስር እንዲሰዱ ማድረግና ለነርሱም አስተማማኝ መሠረት መጣሉ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፣ ከሰፊው ሕዝብ ጋር በበለጠ በመዋሃድ፣ የርሱን ንቃትና ድርጅት ክፍ ለማድረግ እንዲቻል በሰፊው ሕዝብ ዘንድ ከመቼውም በበለጠ በረከት ያሉ ታጋዮችን ማሰማራት አስፈላጊ ነበር፣ ነውም።

መኢሶን የትግል ስልቱን በመቀየሩ፣ ቢሮክራሲውና ቢሮክራሲውን ተገን ያደረጉ አስመሳይ ተራማጆችና እንደዚሁም አደርባዮች “ጊዜያቸው” የመጣላቸው መስሏቸው፣ መኢሶንን በ“በፈርጣጭነት” ና በ“መደብ መንሸራት” ለመወንጀል ሸር ጉድ ሲሉ ይታያሉ። እነዚህ አባባሎች አብዮቱን በሚጠሉ በተወሰኑ የንኡስከበርቴ አካባቢዎችና በቢሮክራሲው ዘንድ ተቀባይነት ያገኙላቸው ይሆናል።

ይኽ አባባላቸው የደስታ ነው ወይንስ የፍራቻ? አባባላቸው ከመኢሶን የትግል ስልት ለውጥ ጋር ምንም ግንኙነት የለውም። እነዚህን ቃሎች የሚሰነዝሩ “ተራማጆች” አብዮታዊ ትግል ምን እንደሆነ አልተረዱም ወይንም ደግሞ አውቀው ለማደናበር የሚፈለጉ ብቻ ናቸው።

እስቲ መኢሶንን ለማሽሟጠጥ፣ ለማንቋሸሽ የሚጠቀሙባችው ቃሎችን ባጭሩ እንመልከት፤

1. ፈረጠጠ፤- መፈርጠጥ ማለት ምን ማለት ነው? እኛ እንደሚገባን ከሆነ መፈርጠጥ ማለት ባንድ ያልተጠበቀ፣ ፊት ለፊት በተደቀነ ኃይል ተደናግጦ እግሬ አውጪኝ ብሎ ባላሳቡት አቅጣጫ ለማምለጥ መሞከር ነው። ወደሕቡዕ የገቡት ሰዎች ግን ከዚህ በፊት የጠበቋቸው ተጨባጭ የሆኑ አደጋዎችና እንቅፋቶች በኢትዮጵያ አብዮት ላይ እንደተደቀኑ አመልክተዋል። የሄዱትም እኮ፣ ግን አልገባቹ እንደሆነ ግልጽ አይደለም እንጂ ወደ ሰፊው ሕዝብ ነው። ወደ ሕዝብ የተዛወሩት ጓዶች አብዛኛዎቹ የተዋቸው በቢሮክራሲው ውስጥ ያሉ ቦታዎችን ወይም የቢሮክራሲው ተቀጥላ የሆሉ ድርጅቶችን ነው።

ግን እስቲ በነገራችን ላይ መፈርጠጥ የሚለውን ቃል ያለቦታው ደንቅሮ መናገር ከአፈቀራችሁ፣ እውነትስ ከአብዮቱ የፈረጠጠው ማነው? ከአብዮቱ የፈረጠጡት የዲሞክራሲ መብቶች ለጭቁኖች ያለገደብ በአስቸኳይ እንዲለቀቁ የሚታገሉትና ለዚሁም ለመሰዋት ዝግጁ የሆኑት እነዚህ ጓደኛ ናቸው ወይስ ይህን ለአብዮታችን ወደፊት ግፊትና እርምጃ የሕይወት እስትንፋስ ጥያቄ የሆነው የዲሞክራሲ ጥያቄ በሰበብ በአስባቡ የሚተናኮሉና አሁን መቅረብ እንደሌለበት አድርገው የሚያዩት “ተራማጆች”? ቢሮክራሲው እንዲመታ የሚታገሉት እነዚሁ ጓዶች ናቸው ፈርጣጮች ወይስ ቢሮክራሲው ተራማጆች ነው እያሉ የሚከራከሩለት አደርባዮች ከአብዮቱ የፈረጠጡት? ሰፊው ሕዝብ በጠላቶቹ ላይ ነፃና አብዮታዊ እርምጃ እንዲወስድ የሚታገሉት ናቸው ወይስ ሕዝቡን ለመቆጣጠር፣ ትግሉን ለማፈን የሚፈልጉትና አንድ ቀበሌ ተመራጭ በተገደለ ቁጥር መኢሶን የተዳከመ መስሏቸው ውስጥ ውስጡን የሚፈነድቁት? የብሄረሰቦች መብቶች በአስቸኳይ ይከበር ማለት ከአብዮት መፈርጠጥ ነው ወይ? ሌሎች ነጥቦች ለማንሳት በተቻለ ነበር።

2. መደብ መንሸራተት፣- ይህም ያለቦታው የገባ ሐረግ ነው። የመደብ መንሸራተት ማለት አንድ መደብን እወክላለሁ ብሎ የቆመ ድርጅት ወይም ደግሞ ግለሰብ አብዮቱ እየገፋ ሲሄድ ከዚያ የመደብ አቋም እያፈገፈገ የሌላን መደብ እንዲያውም የተስፋፊን መደብ አቋም ሲወስድ ነው። በዚሁ አኳኋን በአንድ በተወሰነ ወቅት በአብዮት ሰፈር የቆመ ድርጅት ወይም ግለሰብ በትግል ሂደት ከፀረ አብዮት ሰፈርም ሊቀላቀል ይችላል። ለምሳሌ በኢትዮጵያ ውስጥ ህብረቱን የመሠረቱ የኢትዮጵያ ማርክሲስት ሌኒኒስት ድርጅቶች ሌሎችም የማርክሲስት ሌኒንስት ቡድኖች የወዛደሩን መደብ ፓርቲ ለመመሥረት ብቁ ላይሆኑ ይችላሉ። አንዳንዶቹ በሕዝባዊ አብዮታዊ ግንባር ውስጥ ብቻ ሊሳተፉ ይችላሉ። ያን ጊዜ እነዚህ ድርጅቶች ወይም አባሎቻቸው የመደብ መንሸራተት አሳዩ እንላለን። ያም ሆኖ ከፀረአብዮት ሰፈር ገቡ ማለት አይደለም።

ታዲያ የመደብ መንሸራተት ሳይንሳዊ ትርጉም ይህ ሆኖ እያለ ከመኢሶን ስም ጋር ተለጥፎ በአሁኑ ወቅት የሚቀርብበት ምክንያት ምንድነው? መኢሶን የማርክሲስት-ሌኒኒስት ድርጅት አይደለም ለማለት ነው ወይንስ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ከፀረ አብዮት ሰፈር ገብቷል ለማለት ነው? “የመደብ መንሸራተትን” ክስ በመኢሶን ላይ የሚያቀርቡ ተራማጆች በምን ላይ ተመስርተው እንደሆነ ግራ የሚያጋባ ነው። ሀገር በባእድ ተወራ ሳለች እንዴት ይህን ያደርጋሉ? ይህ መቼም ስሜትን የሚቀሰቅስ ግን ትክክለኛ ያልሆነ አነጋገር ነው። የውድ እናት ሀገራችን በባእድ መወረር ከሁሉም ተራማጅና አገር ወዳድ ባላነሰ ያንገበግበናል። አብዮታችንን ብሔራዊ አንድነታችንን ለመጠበቅ በሚደረገው ትግል በፍጹም ቆራጥነት ለመታገል ቆርጠን የተነሳን ነን። የለም። ይኽን የሚያሰሙ ኃይሎች ሊያነሷቸው የማይፈልጓቸው ነጥቦች አሉ። በአሁኑ ሁኔታ የኢትዮጵያን አብዮትና አንድነት ለመጠበቅ መደረግ የሚገባቸው ነገሮች ምንድናቸው? ግን ደግሞ በዚህ አጋጣሚ አንድ አገር በውጭ ኃይል በተወረረችበት ጊዜ ስለኃይሎች አሰላለፍ (የመደብ መንሸራተትንም በዚህ ውስጥ ለማስገባት ይቻላል) አንናገር ከተበላ በብዙ አገሮች ታሪክ ውስጥ በአብዮት ወላፈን ጥቅማቸው የተነካባቸው የፊውዳሎችና የከበርቴ መደቦች አባሎች እንኳን ሳይቀሩ ከአብዮታውያን ጎን ቆመው አብረው ታግለዋል።

 
የተራማጆች ህብረትና የሰፊው ሕዝብ ጥያቄዎች

የተራማጆችን ሕብረት በሚመለከተው በኩል መኢሶን አሁንም ቢሆን የሀቀኛ ተራማጆችን ኅብረት ይፈልጋል። ግን ከዚህ በፊት እንደነበረው የወረቀት ህብረት በተግባር ሽኩቻን ለኢትዮጵያ አብዮት አይጠቅምም። እነገሌ እንዲህ ናቸው፣ እንደዚያ ያደርጋሉ ማለትን ትተን በማያስማሙንና በሚለያዩን መሠረታዊ ነጥቦች ላይ እንወያይ። ለእውነተኛ ህብረት ዲሞክራሲያዊ ውይይት ብቻ ሳይሆን ሀቅም ያስፈልገዋል። በዚህ ረገድ እስካሁን የነበረው የይስሙላ ህብረት እንደነበረ ተዳጋግሞ ተገላልጿል። ፀረ-መኢሶን ዘመቻ የያዙ ድርጅቶችም የድብብቆሽ ጨዋታውን ወደጎን ይተዉና በሀቅ እንወያይ።

የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ በዚህ ታሪካዊ ወቅት ውስጥ ትልቅ ሃላፊነት አለበት። ጥቂት የመኢሶን ጓዶች ወደ ሕቡእ መግባትን እንደትልቅ ድፍረት ቆጥሮ አሁን የተያዘውን የመኢሶን አባላት ወይም ደጋፊዎች ናቸው በሚባሉ ላይ በግልጽ ወይም በስውር እርምጃ መውሰድን ከቀጠሰ በኢትዮጵያ አብዮት ላይ ለረጅም ጊዜ የማይድን ቁስል ትቶ እንደሚሄድ ግልጽ ነው። ከዚያም በላይ አድሃርያን ተራማጅ መለዮ ለባሹንና ሰፊውን ሕዝብ ለመለያየት ባዘጋጁት ወጥመድ ውስጥ እንዳይገባ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባታል።

የሰፊውን ሕዝብ ትግል በሚመለከተው በኩል ድርጅታችን የሰፊው ሕዝብና የአብዮቱን ጥያቄዎች አያስተጋባ፣ ማናቸውንም መሰዋትነት ሳይፈራ በቆራጥነትና ያለማወላወል ይታገላል። ለአብዮቱ በወደቁት ጓዶች ደም የተነከረውን የትግል አርማ አንግቦ፣ በዚሁም የትግል አርማው የሚከተሉትን አብዮታዊ ጥያቄዎች አስፍሮ ለነርሱ ፍጻሜና ሥራ ላይ መዋል፣ በአጠቃላይ ለአብዮቱ ወደ ፊት ግፊትና ለሰፊው ሕዝብ ድል በመታገል ወደ ኋላ አይልም። የምንታገልላቸው አንገብጋቢ የአብዮቱ ጥያቄዎችን እንደሚከተለው ለመዘርዘር ይቻላል።

  1. የዲሞክራሲ መብቶች ጥያቄ፣- የሰፊውን ሕዝብ አብዮት ወደፊት ለመራመድ እንዲችል፣ ከቢሮክራሲው ቀን ተሌት ሰፊው ሕዝብ በገዛ ራሱ ታሪካዊ እርምጃዎችን ለመውሰድ እንዲችልና ለመፍጠር ችሎታው በር እንዲከፍትለት፣ ስለአብዮቱ ችግሮች መወያየትና ለነዚሁም መፍትሄዎች ለመሻት እንዲችል፣ ሕዝባዊ ድርጅቶች እንዲያብቡና የተራማጆች ሕብረት እንዲጠናከር፣ የአድሃርያንን ውስጥ ሴራና አሻጥር ለመቋቋም እንዲሁም ሰፊው ሕዝብ የዲሞክራሲያዊ የአሠራር ዘይቤያችንን አውቆ ለሥልጣን ብቁ እንዲሆን፣ መኢሶን የዲሞክራሲ መብቶች ለጭቁኖች በአስቸኳይ እንዲለቀቁ ይጠይቃል፣ ይታገላልም። በዚሁ አንፃር የዛሬ ዓመት ተኩል የታወጀው የብሔራዊ ዲሞክራቲክ አብዮት ፕሮግራም ሥራ ላይ እንዲውል፣ በየካቲት 69 በተራማጆች ሕብረት የወጣው መግለጫ በተግበር እንዲተረጉምና የጊ.ወ.አ. ደርግ እነአለማየሁ ኃይሌ እንዲተመቱ ሰሞን የገባውን ቃል እንዲጠብቅ እንጠይቃለን።

ባሁኑ ሁኔታ ይህ የዲሞክራሲ ጥያቄ የድርጅታችን ጥያቄ ብቻ ሳይሆን የሰፊው ሕዝብ ጥያቄ ነው፤ የዲሞክራሲ ጥያቄ የሰፊው ሕዝብና ለአብዮቱ ወደፊት እርምጃ አስፈላጊ ጥያቄ በመሆኑ ምንም እንኳ አንዳንድ ተራማጅ ድርጅቶች ጋር ውይይት በማካሄድ የዲሞክራሲን አስፈላጊነት ለማሳመን እየሞከርን፣ በሌላው በኩል ደግሞ የዲሞክራቲክ መብቶች እንዲከብሩ በሚደረገው ትግል ይበልጡኑ ሰፊውን ሕዝብ ለማንቃት፣ ለማደራጀትና ለማሳተፍ፣ ማለትም ሰፊ የሆነ የዲሞክራሲ ግንባር ለመፍጠር መታገል አለብን።

  1. ቢሮክራሲው እንዲመታ፣- በቢሮክራሲው ላይ እንዲዘመትበት፣ በአመራር ላይ ያሉ አድሃሪ ቢሮክራቶች ተነስተው በሀቀኛ ዲሞክራቶችና ታጋዮች እንዲተኩ፣ በአንድ በኩል የቢሮክራሲው ሚና እየመነመነ ሲሄድ በሌላው በኩል ሕዝባዊ ድርጅቶች እንዲያብቡና ተጠናክረው በየደረጃው የአስተዳደሩን ተግባር እንዲረከቡ የምናደርገውን ትግል ከመቼውም ቢሆን በበለጠ ማፋፋም አለበን።-

በቢሮክራሲው ላይ በአስቸኳይ እንዲዘመት የምንታገለው፣ ቢሮክራሲው በይዘቱ ፀረ ሕዝብ በመሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ለኢምፔሪያሊስቶችና ለአድሃሪያን የቀራቸው ዓይነተኛ መሣሪያ በመሆኑ በአብዮታችን ላይ ሊሰነዘር የሚችለውን ጥቃት ለመቅጨት እንድንችልም ነው። በቢሮክራሲው ላይ ያወጅነውን ጦርነት የተሳካ ውጤት እንዲያገኝ፣ ቢሮክራሲውን ተራማጅ ለማስመሰል ከሚሞክሩ አንዳንድ አደርባይ ድርጅቶች ጋር የርእዮተዓለም ትግል ማካሄድ እንዲኖርብን ግልጽ ነው።

  1. ሰፊው ሕዝብ እንዲታጠቅ፣- ሰፊው ሕዝብ ወታደራዊ ትምህርት እንዲቀስም፣ በበለጠና በተጠናከረ አኳኋን እንዲታጠቅ፣ በከፍተኛ ደረጃ መታገል፣ በዚህ አንፃር የሰፊውን ሕዝብ፣ የገበሬ ማህበራትን፣ የአብዮት ጥበቃ ኮሚቴዎችንና የቀበሌ ማህበራትን ትጥቅ ለማስፈታት የሚቃጡትን ማናቸውንም አድሃሪ ሙከራዎችን በጥብቅ መቃወም ያስፈልጋል።
  2. አብዮታዊ አመራር፣- የሚካሄደው ጦርነት ከቢሮክራሲው አመራር ተላቆ አብዮታዊ አመራር እንዲኖረው፣ በሠራዊቱ ውስት ሠራዊቱንም ሆነ በሚዘምትበት አካባቢ የሚገኘውን ሕዝብ የሚያነቃ አብዮታዊ ካድሬዎች እንዲሠማሩ እንታገላለን። በዚህ አኳያ ሠራዊቱ አብዮታዊ አመራር እንዳይኖረው በሚገባ እንዳይነቃ ከቢሮክራሲው በኩል የሚደረጉትን አሻጥሮች እናጋልጣለን።
  3. የነፃ ሕዝብ እርምጃ፣- አብዮታችን ከአጥቂነት ወደተከላካይነት ካፈገፈገበትና የሕዝብ ጠላቶች ባንሠራሩበት ባሁኑ ወቅት፣ አብዮታችንን ከጥቃት ለመጠበቅና የአድሃሪያንን ነጭ ሽብር ለመቅጨት ሰፊው ሕዝብ በጠላቶቹ ላይ ነፃ የሆነ እርምጃ ለመውሰድ እንዲችል፣ እንታገላለን። ይህም ትግል የተሳካ ውጤት እንዲያገኝ የሕዝቡን ትግል የሚያፍነውን ቢሮክራሲ ለመደምሰስ ከሚደረገው ትግል መቀናጀት አለበት።
  4. የብሄረሰቦች መብት እንዲከበር፣- የብሄረሰቦች መብት በወረቀት ብቻ ሳይሆን በተግባር እንዲተረጎም የእያንዳንዱ ብሄረሰብ ቋንቋ፣ ባህል ራሱን በራሱ የሚያስተዳድርበት መንገድ ከአሁኑ እንዲቀየስለት። ለኤርትራም ችግር የፖለቲካዊ መፍትሄ እንዲኖረው የምናካሂደውን ትግል መቀጠል።
  5. ብሔራዊ ነፃነት፣- አገራችን በተወረረችበት በአሁኑ ሰዓት የውጪን ጠላት ለመቋቋም በተቀዳሚ በራሳችን ኃይል እየተማመንን ከውጪ የምናገኘው ብሔራዊ ነፃነታችንን ሕልውናችንን እንዳይፃረር ከፍተኛ ቅስቀሳና ፕሮፖጋንዳ ማድረግ አለብን።

መኢሶን ከዚህ የተጠቀሱትና ሌሎችም የሕዝቡ ጥያቄዎች ሥራ ላይ ውለው የአብዮቱ ሂደት የተሳካ እንዲሆን በቆራጥነትና ያለማወላወል ይታገላል።

ድሉ የሰፊው ሕዝብ ነው
ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለጭቁኖች ባስቸኳይ
የተራማጆች ህብረት ይጠንክር
የአወናባጆች እድሜ አጭር ነው
የነቃ፣ የተደራጀና የታጠቀ የሕዝብ አመጽ ያሸንፋል
Scroll to Top