ሰሕድ ቁ. 50

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ቁጥር 50፣    ጥር 30፣ 1969 

የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ

በዚህ እትም፣ የመኢሶን አባላት እስካሁን ከቀሰሟቸው ትምህርቶች መካካለ አንዱ፣ በማንኛቸውም ጊዜ አንደ መኢሶን አይነት ድርጅት ውስጥ ሁለት የተለያዩ የፖለቲካ መስመሮች ሊኖሩ እንደሚችሉና በአንድ ወቅት ትክክለኛው ወይንም ስህተተኛው መስመር አሸናፊ ሆኖ ሊወጣ እንደሚችል ያብራራል። መኢሶን ውስጥ የነበረውንም የሁለት መስመር ትግል ከኢትዮጵያ አብዮትና ከመኢሶን ታሪክ ጋር እያጣቀሰ፣ ለትክክለኛ ፖለቲካ መስመር አሸናፊነት ዋስትና ናቸው የሚላቸውን አብይ ሃሳቦች ይሰነዝራል። ከዚህም በመነሳት ከመኢሶን ምስረታ ጀምሮ የነበሩ የሁለት መስመር ትግሎችን በተለይም ከአብዮቱ መፈንዳት በኋላ በውስጡ ከነበሩት ሁለት መስመሮች አንዱ “የጊዜያዊ ህዝባዊ መንግስት” ና “የምርጥ መኮንኖች” የሚሉ መፈክሮችን አስቀድሞ ማራመዱ የአብዮቱ ሂደት ላይ የፈጠረውን አሉታዊ አንደምታ፣ እንዲሁም ውሎ አድሮም የግራ ቀደሙ ደንፊ ቡድን ማደናገሪያና የጸረ አብዮተኞች መጠቀሚያ እንዴት ሊሆን  እንደቻለ ይተነትናል። ከግራ ድርጀቶች ጋር የነበረውን የትብብርና የልዩነት ነጥቦችን አንስቶ የመኢሶንን የፖለቲካ መስመር ያብራራል።  

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ለሰፊው ሕዝብ ሰራተኛ ገበሬ፣ ነጋዴ፣ ወታደር፣ ምሁር መብትና ጥቅም የሚታገል ጋዜጣ

የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ይቅደም

 
ቁጥር 50                                                                    ቀን 30/05/69

 

መኢሶን በኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ እንቅስቃሴ ውስጥ

I

ከሌሎች አገሮች የአብዮታዊና የወዛደር ፓርቲዎች አነሳስና አስተዳደግ ታሪክ ጋር ሲመሳሰል፣ የመኢሶን ታሪክ በጣም የአጭር ጊዜ ታሪክ ነው። መኢሶን የረጅም ጊዜ ታሪክና ልምድ ያለው ድርጅት አይደለም። ገና ጀማሪ በመሆኑም፣ የኢትዮጵያን የወዛደር ፓርቲና ሕዝባዊ አብዮታዊ ግንባርን ለመፍጠር፣ ብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮቱን ከግብ ለማድረስና የሶሻሊስት ህብረተሰብን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ የማህበራዊ ኑሮና የባህል መሠረቶችን ለመጣል በሚደረገው የረጅም ጊዜ ትግል ውስጥ፣ አባሎቹ ሁሉ ገና ብዙ ይማራሉ።

ይሁንናም፣ ማርክሲዝም-ሌኒኒዝም ስለአንድ አብዮታዊ ድርጅት የሚያስተምረንን አንዳንድ እውነቶች፣ በዚህ በአጭር ጊዜ ታሪክ ውስጥ ድርጅቶችን በገቢር ለማረጋገጥ ችሏል። ከነዚህም ትምህርቶች ውስጥ አንዱ፣ በማንኛውም ጊዜ በአንድ ድርጅት ውስጥ ሁለት መስመሮች እንደሚኖሩ፣ በሁለቱ መካከል ትግል እንዳለና እንደ ድርጅቱ ርእዮተአለማዊና ፖለቲካዊ ብስለት፣ ባንድ በተወሰነ ወቅት፣ ትክክለኛ ወይንም ስህተተኛ መስመር፣ ከሁለት አንዱ፣ ሊያሸንፍ እንደሚችል ነው። ትክክለኛ መስመር ወደፊት ያራምዳል ውጤቶችን ያስገኛል፣ ስህተተኛ መስመር ወደኋላ ይጎትታል፣ ውድቀቶችን ያስከትላል፣ ካልታረመም ድርጅቱን ያቆረቁዝና በመጨረሻም ያጠፋዋል።

ለአንድ ማርክሲስት- ሌኒኒስት ድርጅት የፖለቲካ መስመር ትክክለኛነት ዋስትና ሊሆኑ ከሚችሉት መሃከል ሦስት ነገሮች መጥቀስ ይቻላል። እነዚህም፡- የወዛደሩን ርዮተዓለም በጥብቅ ለመከተል መቻል፣ ከሰፊው ሕዝብ ጋር መተሳሰርና በሂስና በግለሂስ በሰፊው መጠቀም ናቸው።

የወዛደሩን ርእዮተዓለም በጥብቅ መከተል ማለት መፃሐፍትን ወይንም ጥቅሶችን በቃል አጥንቶ እነዚያን በሆነ ባልሆነው ሁኔታ ሁሉ መልሶ ማስተጋባት አይደለም። ወይንም ደግሞ በቃልም ሆነ በጽሁፍ አንድን የህብረተሰብ ጥያቄ ሲገልጹ መፈክሮችን አከታትሎ ማስቀመጥ አይደለም። እንደዚሁም በሌሎች አብዮቶች ሂደት ውስጥ የደረሱትን ሁኔታዎች ወይንም የተከናወኑትን ድርጊቶች ለመገልበጥ መጣጣር አይደለም። የወዛደሩን ርዕዮተዓለም በጥብቅ መከተል ማለት ማርክሲዝም-ሌኒኒዝምንና የአብዮቶችን ታሪክ አጥንቶ፣ አዋህዶ፣ እነርሱ መሳሪያ፣ መፍቻ ቁልፍ በማድረግ የኢትዮጵያን ህብረተሰብ መደቦችና አሰላለፋቸውን አበጥሮ ማወቅና በዚህ እውቀት ላይ በመመስረት፣ ተጨባጩን ሁኔታ የሚያንፀባርቅ የድርጊት መመሪያ ማውጣት ማለት ነው። የዚህ ዓይነቱ አካሄድ ከሰብአዊነት፣ ከጥራዝ ነጠቅነትና ከግብዝነት ለመከላከል ይረዳል።

ከሰፊው ሕዝብ ጋር በጥብቅ መተሳሰር ማለት እድል ባጋጠመ ቁጥር ከገበሬው ወይንም ከወዛደሩ ሰብሳቢዎች ፊት ቀርቦ ከተጨባጭ ኑሮ የራቁ፣ ግን በአብዮታዊ ቃላት የተሞሉ፣ ስለመደቦች፣ ስለቅራኔ፣ ስለሶሻሊዝም ወዘተ. …የሚያስረዱ ከባድ ዲስኩሮችን ማድረግና ከዚያም ወደ ሌላ የግል ሥራ እና ኑሮ እየተደሰቱ መመለስ አይደለም። ከሰፊው ሕዝብ ጋር መተሳሰር ማለት በመሐሉ መኖር፣ ስሜቶቹን፣ ፍላጎቶቹን፣ ችግሮቹን በሚገባ ማጥናትና በእነዚህ ላይ ተመርኩዞ መፍትሄዎችን ለራሱ ለሰፊው ሕዝብ መልሶ በመጠቆም ለነዚህ እንዲታገል አብሮት መሰለፍ ማለት ነው። የዚህ አይነቱ መዋሓድ በባዶ ቦታና ሁኔታን በደንብ ሳይለዩ ትላልቅ “መፍትሄዎችን”፣ እቅዶችንና አሳቦችን በከንቱ ከማቅረብ ያድናል።

የወዛደሩን ርእዮተዓለም በጥብቅ ስለተከተልንና ደግሞም ከሰፊው ሕዝብ ጋር ስለተዋሃድን ዘለአለም ትክክለኞች እንሆናለንም ማለት አይደለም። ማርክሲዝም- ሌኒኒዝም የድርጊት መምሪያ ሳይንስ ነው። ነገር ግን ይህንን ሳይንስ ከተጨባጩ ሁኔታ ጋር የማገናዘቡ ነገር ቀላል ስለአይደለ፣ በግለሰብ ደረጃም ሆነ በድርጅት ስህተቶች ይፈፅማሉ። ሌኒን አንዱን ደራሲ በመጥቀስ “ወዳጄ ቲዎሪ ደረቅ ነው፣ የሕይወት ዛፍ ግን ለምለም ነው” ሲል፣ ሕይወት፣ ህብረተሰብ፣ የተወሳሰቡ ነገሮች መሆናቸውን ነው የሚገልፅው። ብዙውን ጊዜ በግለሰበኝነት /ሰብጀክቲቪዝም/ ውስጥ የሚወድቀው ነገሮችን እንደጥቁር ወይም ነጭ፣ በጣም ቀላል አድርጎ በመውሰድና ግንኙነቶቻቸውን ሁሉ በመርሳት ምክንያት ነው።  ስለሆነም፣ ስህተቶች ይፈፅማሉ። እነዚያን በጊዜውና በትክክል ለማረም ካልተቻለና ለዚህም ደግሞ ሂስና ግለሂስ በሥራ ላይ ካልዋሉ፣ ከተፈሩና ከተተው፣ የአንድ ድርጅት የፖለቲካ መስመር መዛባትና ውድቀት ያስከትላሉ።

መኢሶን በአጭር ጊዜ ታሪኩ ውስጥ እነዚህን የማርክሲዝም- ሌኒኒዝም እውነቶች በገቢር ለራሱ ለማረጋገጥ ችሏል። ለዚህም ማስረጃ አንዳንድ ምሳሌዎች በዚህ ጽሁፍ ውስጥ ይቀርባሉ። የዚህ ጽሁፍ አላማ በመኢሶን በየጊዜው የተነሱትን የመስመር ልዩነቶች በማሳየት፣ ድርጅታችን እስከዛሬ በኢትዮጵያ አብዮት እንቅስቃሴ ውስጥ የተጫወተውን ሚና በአጭሩ መገምገም ነው። ግን እንግዲህ የዚህ አይነቱ ትንተና አሁን ባለንበት ወቅት ለምን አስፈለገ? ለዚህ ልዩ ልዩ ምክንያቶች አሉ፡-

አንደኛ፣ ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ ድርጅታችን ከፍተኛ ተጋድሎን አድርጎ በተለይ በአሁኑ ወቅት ለትግሉ በጣም አመቺ ከሆነ ሁኔታ ላይ ደርሷል። የየካቲት እንቅስቃሴ ከጀመረበት አንስቶ እስከ የካቲት 67 ግድም፣ ለአንድ ዓመት ያህል፣ በደንፊው የንዑስ ከበርቴ ቡድንና በመኢሶን መስመሮች መካከል ምንም ያህል ልዩነት ሳይኖር፣ ድርጅታችን በየካቲት 67 የተለየ አቅጣጫ በያዘበት ወቅት ከደካማ ሁኔታ መነሳት ነበረበት። በ1967፣ በወዛደሩ እንቅስቃሴ፣ በመምህራን በዘማቾች እንቅስቃሴዎች ውስጥ፣ ድርጅታችን የነበረው ጉልበትና ተደማጭነት የተወሰነ ሆኖ፣ ሜዳው ከሞላ ገደል የንዑስ ከበርቴው ደንፊ ቡድን መፈንጫ እንደ ነበር ይታወሳል። ከዚያ ደካማ ሁኔታ ለመነሳት ያደረግነው ያልተቆጠበ ጥረት ብዙ ቆራጥ ታጋዮችን አፍርቶልናል። እነዚህ ከአድሃሪው “የግራ” ክንፍ ድርጅትም ጭምር ተላቀው ከእኛ ጋር የተሰለፉት ጓዶች የመኢሶንን የትግል ታሪክ ቢያውቁት የበለጠ ትምህርትና ጥንካሬን እንደሚሰጣቸው እናምናለን። ለወደፊቱም ቢሆን በድርጅታችን ውስጥ፣ ነገም ደግሞ በወዝአደሩ ፓርቲ ውስጥ፣ የመስመር ትግሎች ይኖራሉ። ጓዶቻችን ሁሉ የማርክሲዝም-ሌኒኒዝም እውቀታቸውን ካዳበሩና በዚህ ርዕዮተዓለም ከተመሩ፣ ከሰፊው ሕዝብ ጋር ከተዋሀዱና በሂስና በግለሂስ ያለ ፍርሃት ከተጠቀሙ፣ ድርጅታችን ጠንከሮ የወዛደሩን ፓርቲ ለመፍጠር በሚደረገው ትግል ውስጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያደርግ ይችላል። የድርጅቱን ታሪክ ማወቅ ለዚህም ይጠቅማል።

ሁለተኛ፣ በተለይ በ1968 በተደረገው ትግል ውስጥ፣ “ሁለት መስመሮች” የሚባለው አባባል በአገራችን በጣም ተስፋፍቶ ነበር፣ አሁንም አለ። ወደድንም ጠላንም፣ ለብዙ ሰው “ሁለት መስመሮች” የተባሉት ከመኢሶንና ከኢህአፓ ጋር ተዛምደዋል። ይሁንናም ሌሎች የኢትዮጵያ ማርክሲስት-ሌኒኒስት ድርጅቶች ኃይለኛ ፀረደንፊ ትግል ማድረጋቸው የታወቀ ነው። ከእነዚህ ድርጅቶች ጋር በመጀመሪያ ደረጃ ህብረትን፣ ከዚያም ውህደትን በመፍጠር የወዛደሩን ፓርቲ በጋራ ለመመስረትና ለመገንባት ፅኑ ፍላጎት አለን። እነዚህ የህብረት ጓዶቻችን የመኢሶንን አጭር ታሪክ ቢያውቁ የበለጠ መግባባትና መቀራረብን እንደሚፈጠር እናምናለን። የዚህ ዓይነቱ እውቀት አጉል ጥርጣሬንና አለመተማመንን ሊያስወግድ ይችላል። (በነገራችን ላይ፣ “ሁለት መስመር” የሚለው አሁንም ሆነ ወደፊት ሳይንሳዊ እውነትን ያዘለ ነው። የድርጅቶች በርከት ብሎ መታየት ይህንን ሃቅ ፈጽሞ አይሽረውም። በአንድ በተወሰነ ወቅት በአንድ አብዮታዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ሊታዩ የሚችሉት የተሰበጣጠሩ ኃይሎች ዞሮ ዞሮ ከሁለት አንደኛውን መስመር ያራመዳሉ እንደሚባለው ሁሉ፣ በዚህ አይነቱ ወቅት ሁለት ሰፈሮች፣ ሁለት ፊናዎች፣ ሁለት አዝማሚያዎች፣ ሁለት ወገኖች ብቻ ናቸው ሊኖሩ የሚችሉት። የተሰበጣጠረው አሰላለፍ የላይ ሽፋን ነው፤ ጊዜያዊ ነው፤ ስለሆነም ሊያሳስት ይችላል።)

ሦስተኛ፣ በልዩ ልዩ የፖለቲካ ጥያቄዎች ላይ በተለያዩ ጊዜያት መኢሶን አቋሞችን ወስዷል። በተለይም በየካቲት 67 የድርጅቱ ጠቅላላ መስመር ከተለወጠና፣ መኢሶን “አብዮታዊ ሂስ” የሚባለውን መመሪያ ወስዶ፣ በጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት ላይ ሊኖረው የሚገባውን አቀራረብ ከቀየሰ በኋላ፣ በልዩ ልዩ ነጥቦች ላይ የወሰዳቸው አቋሞች ይታወቃሉ። አንዳንድ ሰዎች እነዚህ አቋሞች ድንገት ከሰማይ ዱብ እንዳሉ አድርገው ይመለከቷቸዋል። በነርሱ ላይ በድርጅቱ ውስጥ ትልቅ ትግል እንደተደረገ ስለማያውቁ፣ ወይንም ደግሞ ጠቅላላ የድርጅታችንን አቋሞችና ድርጊቶች በሚገባ ስላልተከታተሉ፣ በተወሰኑ ጥያቄዎች ላይ የተወሰዱት አቋሞች ባቦ ሰጡኘ የተወሰዱ ሳይመስሏቸው አልቀሩም። በአሁኑ ሰዓት የዚህ አይነቱ ጽሁፍ መውጣት እነዚህ ሰዎች ድርጅታችንን ይበልጥ እንዲረዱት ያደርጋል የሚል እምነት አለን።

አዎን፣ መኢሶን በኢትዮጵያ አብዮታዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ከታየበት ጊዜ አንስቶ በልዩ ልዩ ጥያቄዎች ላይ አቋሞችን ወስዷል። ከነዚህ ውስጥ አንዳንዶቹ ከተወሰዱበት ወቅት ትክክል ሆነው፣ ዛሬ ግን ወደኋላ ተመልሶ ለተመለከታቸው ስህተተኛ ሊመስሉ ይችላሉ። ወይንም እርስ በርሳቸው የሚቃረኑ ይመስላሉ። እነዚህ የተወሰዱበትን ሁኔታና አካባቢ ለማስታወስ ካልተቻለ፣ ተመልካቹ እራሱ ይሳሳታል። እንደዚሁም የተወሰዱበትን ትክክለኛ አቋሞች በሁኔታቸውና ካካባቢያቸው ውስጥ መልሶ አስቀምጦ ማየት እንደሚያስፈልግ ግልጽ ነው።

II

ድርጅታችን መጀመርያ ሲቋቋም በትግል ውስጥ ነበር የተፈጠረው። እንደሚታወቀው ሁሉ፣ መኢሶን ከኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ የፈለቀ ድርጅት ነው። በፕሮግራሙ ውስጥ እነደተጠቀሰው፣ ወቅቱ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ትግል፣ የወዛደሩ፣ የአርሶአደሩ፣ የብሄረሰቦችና የተማሪዎች ትግል የተፋፋመበትና በአንጻሩ የኃይለሥላሴ ፊውዶፋሽስት መንግሥት ጭቆናውን ያባባሰበት ወቅት ነበር። ስለሆነም፣ የአንድ አብዮታዊ ድርጅት አስፈላጊነት ግልፅ ነበር።

በዚህ አይነቱ ሁኔታ፣ ድርጅቱን የመፍጠሩ ጥያቄ ሲነሳ፣ አብረውን ተሰልፈው ከነበሩት አብዮታዊ ምሁራንና ተማሪዎች ውስጥ በድርጅት አፈጣጠር ጥያቄ ላይ የቀኝና “የግራ” አስተሳሰቦች የነበሯቸው ይገኙ ነበር። የቀኝ አድርባይነትን ያሳዩ የነበሩት፣ መፍጠር የሚያስፈልገው “ሰፊ መሠረት” ያለውና በጥብቅ ዲሲፕሊን ያልተሳሰረ የዲሞክራቶች ድርጅትን እንጂ ማርክሲስት-ሌኒኒስት የሆነና በዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት የሚመራን ድርጅት አይደለም ይሉ ነበር። እነርሱ የፈለጉት መዋቅር እያንዳንዱ የድርጅቱ አባል “ነፃ” /ኦቶኖመስ/ ሆኖ የሚንቀሳቀስበትን መዋቅር ነበር። ለዚህም “የኦቶኖሚ” ጥያቄ የሰጡት ምክንያት፣ ሁላችንም ብንሆን ለማርክሲዝም-ሌኒኒዝም አዲሶች ስለሆንንና አንዱ ሌላውን ሊመራ ይችላል የሚባልበት ሁኔታ ስለሌለ ነው የሚል ሲሆን፣ ይህ አባባል የከበርቴ ምሁራንን የዲሲፕሊን ፍርሃት፣ ግለሰብኝነትና “ከማን አንሼን” ከማንፀባረቅ በስተቀር ምንም ሳይንሳዊ መሰረት የሌለው ምክንያት ነበር። በተጨማሪም፣ ለነርሱ የኢትዮጵያ አብዮት ገና እጅግ በጣም ሩቅ ሆኖ ይታያቸው ነበር። ከእነዚህ የቀኝ አድርባይነትን ያሳዩ ከነበሩት ምሁራን ውስጥ ብዙሃኑ ለጥቂት ጊዜያት በጠባብ “የጥናት ቡድን” ውስጥ ቆይተው፣ የየካቲት እንቅስቃሴም ሲመጣ ፍጹም ግራ ተጋብተው ወደመኮላሸትና ትግሉን ወደመተው ገብተዋል። አንዳንዶቹም ከ“ግራ”  አድርባዮች ጋር ከፀረአብዮቱ ሰፈር ተደባልቀዋል። ከየካቲት እንቅስቃሴ ወዲህም መኢሶን ሊመልሳቸው ያደረገው ጥረት ፍሬን አልሰጠም።

በሌላ በኩል ደግሞ፣ “የግራ” አድርባይነትን ያራመዱ የነበሩት፣ የኢትዮጵያ አብዮት “ከመብሰልም አልፎ ስለ በሰበሰ”፣ የሚፈጠረው ድርጅት ጠንካራ እስኪሆን ሳንጠብቅ፣ መቶ ያህል ሰዎችን ይዘንና ከኤርትራ ግንባሮች፣ ኢ.ኤል.ኤፍ/ እና በኋላም ከፒ.ኤል.ኤፍ/ ጋር ተጠግተን ወዲያውኑ የገሪላ ውጊያን መጀመር አለብን ያሉ ነበሩ። ለነዚህ ወገኖች፣ የኢትዮጵያ አብዮት በአንድ ዕለት ደርሶ-መልስ የሚከናወን መስሎ ስለታየ፣ ጠንካራ ድርጅትን ለመፍጠር፣ ድርጅቱም በሰፊው ሕዝብ ውስጥ ቅስቀሳና ፕሮፖጋንዳን አካሂዶ ከዚያም ደረጃ በደረጃ ወደሕዝባዊ ጦርነት እንዲያመራ ማቀድ “በኢትዮጵያ አብዮት ላይ ወንጀል መፈፀም” ነበር። የ“ግራ” አድርባዮቹ ዛሬ ኢህአፓ በሚል ስም የታወቀውን ድርጅት ፈጥረው እንዳቀዱት ሁሉ አምሳ የማይሞሉ ተዋጊዎችን በኤርትራ በረሃ አሰማሩ። ከእነዚያ ውስጥ ብዙዎቹ በእርግጥ በቆራጥነት ለኢትዮጵያ ሕይወታቸውን አሳልፎ ለመስጠት ዝግጁ የሆኑ ሃቀኛ፣ ግን የተሳሳቱ ጓዶች ነበሩ። የታሪክ ፍርድ ሆኖ፣ የየካቲት እንቅስቃሴ በፈነዳና የኢትዮጵያ ሕዝቦች ትግል አንዳንድ ድሎችን በተቀዳጀበት ወቅት፣ ከእነዚህ ጓዶች ውስጥ አንዳንዶቹ ሁኔታውን በትክክል በመገምገም ሰልፋቸውን ለማስተካከል ሲችሉ አንዳንድ ደግሞ እንሰዋለታለን ባሉት አርሶአደር እጅ እንዲወድቁ ሆነዋል።

መኢሶን አንድአንድ ማርክሲስት-ሌኒኒስት ድርጅት ሊቋቋምና እስከዛሬ እየወደቀ የተነሳ አንድነቱን ጠብቆ ወደፊት ለመራመድ የቻለው፣ በትግል ውስጥ ስለተፈጠረ ነው። በመጀመሪያ ደረጃም እነዚያን የቀኝና “የግራ” አስተሳሰቦችን ለማሸነፍ ስለቻለ ነው። መኢሶን፣ የቅኝ አድርባዮችና “የግራ” አድርባዮች ድርጅቶችና ቡድኖች የተፈጠሩት በተማሪ ማህበራት አካባቢ ስለሆነ ትግላቸውንም ያስፋፉት በተማሪ ማህበራት ውስጥ ነበር። በአገር ውስጥ ከነዚህ መስመሮች በስውር ትግሉ አንዳንዴም ሲተባበሩ በውጭ አገር ግን በገሃድ ሲታገሉ እስከ 1966 ድረስ ቆዩ።

ላለፉት ስድስት ዓመታት በውጭ አገር የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማህበራት ውስጥ የተካሄዱትና አሁንም በመካሄድ ላይ ያሉት ሃይለኛ ፖለቲካዊና ርእዮተአለማዊ ትግሎች ዞሮ ዞሮ በመኢሶንና በኢህአፓ መካከል የተካሄዱ ትግሎች ናቸው ለማለት ይቻላል። የታህሳስ 53ን የኮዴታ ሙከራ፣ የተማሪ ማህበራትን ታሪካዊ ሚናና አደረጃጀታቸውን፣ የብሄር ጥያቄዎችን፣ በኢትዮጵያ ያሉትን ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች በሚመለከቱና በሌሎችም ጥያቄዎች ላይ ሁለቱ ወገኖች ሲፋጩ ቆይተዋል። አንባቢው ዝርዝሩን በተለይ ከአውሮፓ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማህበር ጽሑፎች ሊያገኘው ይችላል። በተለይ ግን የየካቲት እንቅስቃሴ ከፈነዳ በኋላ፣ ይህንን እንቅስቃሴ ማን መራው (ማለትም ባህሪው ምንድነው) በሚለው ጥያቄ ላይ፣ በመሬት ላራሹ መፈክር ላይ፣ በፓርቲዎች የመመስረት ጉዳይ ላይ፣ በጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥትና በሌሎችም የኢትዮጵያ አብዮት ጥያቄዎች ላይ የነበሩት ትግሎች፣ ሁለቱ ድርጅቶች እየተራራቁ እንዲሄዱ አድርገዋል። ከመኢሶን የዚያን ጊዜ ዳተኝነት የተነሳ ከኢህአፓ ጋር ተሰልፈው ከነበሩት ሃቀኛና ከሁሉም የበሰሉ አብዮታዊያን ውስጥ ብዙሃኑ ወደ ድርጅታችን ሊመለሱ የቻሉት በዚህ በከረረ ትግል ውስጥ ነበር።

ይህም ሆኖ ሳለ፣ በተለይ ከመስከረም እስከ የካቲት 67 በነበረው ጊዜ ውስጥ የሁለቱ ድርጅቶች አንድ አይነት መፈክሮች ይዘው መውጣት ከድርጅታችን ያመራር ጉድለት የመነጨ እንጂ በሁለቱ ያስተዳደግ ህግ ላይ የተመሰረተ አንድነት አልነበረም።

ይሁንናም፣ ከጥር – የካቲት 1967፣ መኢሶን የተራማጆችን ህብረት አስፈላጊነት በመገንዘብ፣ በድርጅታችንና በኢህአፓ፣ እንደዚሁም በሌሎች ቡድኖች መካከል በከፍተኛ ደረጃ ውይይት እንዲከፈት አደረገ። የተራማጆችን የተግባር አንድነት ለመፍጠር፣ በአስተሳሰብም ለመቀራረብና ከዚያም ተዋህዶ የወዛደሩን ፓርቲ ለመመስረት፣ መጀመርያ በኢትዮጵያ ሁኔታ ትንተና ላይ፣ በወዳጅና በጠላት መደቦች አሰላለፍ፣ በደርጉ ባህሪና በጊዜው አጣዳፊ ተግባሮች ላይ፣ ከስምምነት ላይ መድረስ ያስፈልግ ነበር። በዚያን ጊዜ ከነበረው ሁኔታ ለመገመት ይቻል እንደነበር ሁሉና ባለፉት ሁለት አመታት ከተፈጠሩት ሁኔታዎች ለማረጋገጥ እንደሚቻል ሁሉ፣ በምንም ነጥብ ላይ ስምምነት ለማግኘት አልተቻለም። የኢህአፓ ምኞት ፀረ-ደርግ ግንባርን ፈጥሮ በተቻለ ፍጥነት የመንግሥትን ስልጣን ለመያዝ ሲሆን፣ መኢሶን ግን ይሄንን ስልጣን ሕዝብ እንዲይዝ ለማድረግ መታገል ነበር። እነዚህ ሁለት የተራራቁ ዓላማዎች በምንም መንገድ ሊቀራረቡ ካለመቻላቸውም በላይ፣ ሌላው ቆርቶ ኢህአፓ በጋዜጣችን በሰፊው ሕዝብ ድምጽ ላይ ቀደም ብሎ ጀምሮት የነበረውን የስም ማጥፋት ዘመቻ እንዲያቆምና በፕሪንስፕል ጥያቄዎች ላይ እንዲያተኩር የተጠየቀውን ማሟላት አልቻለም። ስለሆነም፣ ከረጅም ጊዜ ከንቱ ክርክር በኋላ ውይይቱ ያላንዳች መደምደሚያ እንዲቋረጥ ተደርጓል።

ኢህአፓን በሚመለከተው በኩል በድርጅታችን ውስጥ ሁለት መስመሮች ነበሩ። አንደኛው መስመር የኢህአፓ ሰዎች የተሳሳቱ አብዮታዊያን ናቸው፣ በጥንቃቄ ከተያዙና ከተመከሩ ሊታረሙ ይችላሉ፣ ቀስ በቀስም አብረን የወዛደር ፓርቲን ለመፍጠር እንችላለን የሚል ነበር። ሁለተኛው ደግሞ ሰዎቹ የንኡስ ከበርቴው ሪቮሉሽኒዝም[1] ያጠቃቸው፣ ጥራዝ ነጠቆች፣ በሳይንሳዊ ትንተና ፋንታ በአሉባልታ፣ በመንደር ወሬና በስሜት የሚመሩና ስለዚህም ተጨባጩን ያገሪቱዋን ሁኔታ በትክክል ለማየት የማይችሉ ስለሆኑ፣ የሂስ ተኩስ ተከፍቶባቸው ይጋለጡ የሚል ነበር። እንደዚያም ሆኖ ግን፣ ድርጅታችን በጥር 67 ውይይትን ለማድረግ መሞከሩ ትክክለኛ እርምጃ እንደነበር ግልጽ ነው። ኢህአፓን ለመመለስ እስከመጨረሻው መታገል ተገቢ ነገር ከመሆኑም በላይ፣ በጊዜው የነበረውና ዛሬም ያለው የኢትዮጵያ ሁኔታ ባንድነት ሊሰበሰብ የሚችለውን ኃይል የማስተባበርን ግዴታ ከሃቀኛ ተራማጆች ይጠይቃልና።

መደብ ከገመድ ይጎትታል እንደሚባለው ሁሉ፣ ኢሕአፓ የመደብ ባህሪውን ሊለወጥ አልቻለም። ከግንቦት 67 ጀምሮ በክረምቱ የኢሰአማንና የመምህራን ማህበርን አመራሮች አወናብዶ በቁጥጥሩ ስር ካደረገ በኋላ፣ በአንድ በኩል በእነዚህ “ውጤቶቹ” ስለሰከረ፣ በሌላ በኩል ደግሞ በመስከረም 2/68 ደርጉ አንድ እራሱን የቻለ የወታደር ፓርቲ ያውጃል የሚል ወሬ ስለነበር፣ ደርጉን ለመቅደም ሲል፣ ፕሮግራሙን አወጀ። መጀመርያ የመምህራን ማህበር፣ ከዚያም ኢሰአማ በጀብደኘነትና በድንፋታ የተሞሉ ውሳኔዎችን እንዲያሳልፉ በማድረግ አጋፈጣቸው። በመስከረም ወር 68፣ ጠቅላላ የሥራ ማቆም እርምጃዎችን አስወስዳለሁ ብሎ በመደንፋት፣ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ሠራተኞች ላይ እንዲተኮስና ሰባት ሰዎች እንዲሞቱ፣ በርከት ያሉት እንዲቆስሉ፣ በአዲስ አበባና በአካባቢዋ ያስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅና ብዙ የኢሰአማ የመምህራን አባሎች እንዲታፈሱ ለማድረግ በቃ። በነዚህ ድርጊቶች የደርግን “ፋሽዝም”  ለማስመስከር የቻለ መሰለው። በዚህ ሁኔታ፣ ድርጅታችን ከግንቦት 67 ጀምሮ ሂሶችን በኢህአፓ ላይ ሲሰነዝር ከቆየ በኋላ፣ በመስከረም 68 የድርጅቱን ፍጹም ፀረአብዮታዊነት ማጋለጥ ጀመረ።

ኢህአፓ በ1967 መጨረሻና 1968 የወዛደሩን፣ በተለይም የመምህራንን እና የወጣቶችን እንቅስቃሴዎች በሙሉ በክሏቸዋል። የመሬት ላራሹና የከተማ ቦታና ትርፍ ቤቶች አዋጆች ከወጡ በኋላ በተለይ፣ ከንዑስ ከበርቴው ክፍል ብዙ ደጋፊዎችን ለማግኘት ችሏል። በተረፈም፣ የአብዮቱ እርምጃ የመታቸውና ያስደነበራቸው የህብረተሰባችን መደቦች ሁሉ- የመሬት ከበርቴ፣ የቢሮ ከበርቴውና የቀኝ ክንፍ ንዑስ ከበርቴው-በኢህአፓ “ጠበቃቸውን” ወይንም “ነገረፈጃቸውን”  ለማግኘት ችለዋል። የኢህአፓ መፈክሮችና እንቅስቀሳዎች የወደቁት መደቦች ሁሉ የሚያሰለፉ፣ የኢምፔሪያሊዝምና ሌሎችም ቀልባሽ ኃይሎችን ሁሉ የሚስቡ ስለሆኑ ይህ ፀረ አብዮታዊ ድርጅት ባጭር ጊዜ ውስጥ ሊጠናከር ችሎ ነበር።

“የመደቦች ትግል በፈረንሳይ” በሚለው ጽሁፋ ውስጥ፣ ካርል ማርክስ “……ንዑስ ከበርቴው በከበርቴው ላይ ያለውን አብዮታዊ አመለካከት ይዞ የሚቆየው ወዛደሩ ከኋላ እስከ ተሰለፈ ድረስ ብቻ ነው” ብሏል። ወዛደሩ ለራሱ የመደብ ጥቅም ነቅቶ፣ ከንኡስ ከበርቴው ኃላ ሳይሆን ከፊቱ የተሰለፈ እለት የንዑስ ከበርቴው ፀረ ከበርቴነት ያከትማል። ንዑስ ከበርቴው መክዳት ይጀምራል። 1967 እና 68 የኢትዮጵያ አብዮት ያገኛቸው አንዳንድ ድሎች ሰርቶ አደሩን ሕዝብ ወደፊት መድረክ የሚያጡት መሆናቸው ሲሰማው፣ በኃይለሥላሴ ፊውዳሊስት ሥርዓት ላይ “አብዮታዊ አመለካከት” የነበረው የቀኝ ክንፍ ንኡስ ከበርቴ ተደናግጦ ወደ ፀረ አብዮቱ ሰፈር መገስገስን የግድ መምረጥ ነበረበት። የኢህአፓ የጭድ እሳት መንቦግቦግ የሚገልፀው ይህ እውነት ነው።

አሁን ባለንበት ወቅት፣ ከአንድ አመት በላይ ከፈጀ የከረረ የፖለቲካ ትግል በኋላ፣ ድርጅታችንና ሌሎችም ማርክሲስት -ሌኒኒስት ቡድኖች የንዑስ ከበርቴውን ደንፊ ቡድን በፖለቲካ ደረጃ ሊደመስሱት ችለዋል። ስለዚህም ነው፣ ይህ ፀረ አብዮታዊ ድርጅት እውነተኛ መልኩን በማሳየት፣ አብዮታዊያን ቀደም ብለው እንደተነበዩት ሁሉ፣ ወደ ነፍሰገዳይነት የተዛወረው። የቀድሞ ሥራውን ሁሉ የኢትዮጵያን ሁኔታ ለቅልበሳ ማመቻቸት እንደነበር የሚመሰክረው ዛሬ ኢምፔሪያዝም፣ ከኢ.ዲ.ዮና ከሌሎችም አድሃሪ ኃይሎች የሞራልና የማቴሪያል ድጋፍ ማግኘቱ ነው። ይህ ሁሉ ግን ከጠቅላላ ፖለቲካዊና ድርጅታዊ ክስረት አያድነውም። ኢህአፓ በጓዶቻችን ላይ የፈፀመውንና የሚፈጽመውን ግድያ እንበቀላለን። የኢትዮጵያ ሕዝቦች ከፊውዳሊዝም እና ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝም ጋር በሚያደርጉት ትግል ውስጥ፣ እነርሱን መስሎ የተደባለቀውን ይህንን ያድሃሪያን የውስጥ አርበኛ ያጋልጡታል፣ ይደመስሱታል።

[1] ሪቮሉሽኒዝም የቀኝ ክንፍ ንዑስ ከበርቴ ርእዮተአለም ሲሆን፣ እርሱም ጊዜና ሁኔታን ከሳይንሳዊ ሶሻሊዝም አንጻር ሳይመረምሩ፣ አብዮት-አብዮት እያሉ አይን ጨፍኖ መሯሯጥን ያመለክታል። የንጉስ ከበርቴውን የቅብዝብ

ዝነት ባህርይ ያንጸባርቃል። የሪቮሉሽኒዝም ነባራዊ አላማ የወደዛሩን እንቅስቃሴ በማጋፈጥ ማስመታትና ወዛደሩን በመበታተን ተስፋ ማስቆረጥ ነው።

III

በየካቲት 66 የፈነዳው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ እንቅስቃሴ በአገሪቷ ታሪክ ውስጥ ወደር ያልነበረው እንቅስቃሴ ነው። የኢትዮጵያን ህብረተሰብ መደቦች ሁሉ ከዳር እሰከ ዳር የቀሳቀሰና በትግል አፍላ ውስጥ የጨመረ እንቅስቃሴ ስለነበር፣ ከቀደሙት እንቅስቃሴዎች ሁሉ በጥልቀቱና በስፋቱ እጅግ የተለየ ነበር። ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ፣ ይህ እንቅስቃሴ ፈጽሞ ያልታለሙ ድሎችን ያስገኘ ከመሆኑም በላይ፣ አሁንም እየወደቀ- እየተነሳ፣ አያሌ መሰናክሎችን እያከሸፈ፣ ወደፊት በመገስገስ ላይ ይገኛል። በእርግጥ ይህ አብዮት አሁንም ገና ከቅልበሳ ሊድን ይችላል ከሚባልበት ደረጃ ላይ አልደረሰም፤ ሰፊው ሕዝብ የአብዮቱን ጠላቶች ደምስሶ የመንግሥትን ስልጣን ገና አልያዘምና።

በብዙ የድርጅታችን ጽሁፎች ተደጋግሞ እንደተነገረው፣ የኢትዮጵያ ጭቁን ሕዝቦች የየካቲት እንቅስቃሴ በፈነዳበት ወቅት የመንግሥትን ስልጣን ለመያዝ አልተዘጋጁም ነበር። እንቅስቃሴው ግብታዊ ከመሆኑም ሌላ፣ ይህንን ግብታዊነት ወደ ተቀናበረ ትግል ለመለወጥ የሚችል፣ ሰፊው ሕዝብ በመሪነት የተቀበለው አብዮታዊ ድርጅት አልነበረም። በሌላ በኩል ደግሞ፣ ገዥ መደቦችም፣ ማለትም ፊውዳላዊው መደብና የቢሮ ከበርቴው፣ እንቅስቃሴው ይህንን ያህልም ርቆ የሚሄድ አልመሰላቸውም ነበር። በተለየም የተማሩ መሳፍንትንና የዘመናዊ ቢሮክራሲያዊ ከበርቴዎችን ስልጣን ለማደላደል ተቋቁሞ የነበረው የእንዳልካቸው መንግሥትና የእርሱ ሙሉ ደጋፊ የነበረውም የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም፣ በእንቅስቃሴው ባህርይ ላይ ያልነቃበት ስለነበረ የእንዳልካቸው መንግሥት፣ እንደ አክሊሉ መንግሥት ሁሉ ወዲያውኑ ሊወገድ ችሏል። እንደዚያም ሆኖ ግን ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ የመንግሥትን ስልጣን ከጁ ከሚያስገባበት ሁኔታ ላይ አልነበረም። ይህንን ለማድረግ የሚያስችለው፣ ለመንግሥት ስልጣን ያዘጋጀው፣ ትግሉን አቀነባብሮ የሚመራ ድርጅት አልነበረውም።

የማንኛውም አብዮታዊ እንቅስቃሴ ዋና ጥያቄ የመንግሥት ስልጣን ጥያቄ መሆኑና ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ የመንግሥትን ስልጣን ከሚይዝበት ሁኔታ ላይ እንዳልነበረ ግልፅ ሆኖ ሳለ፣ በሚያዝያ 1966፣ ለመጀመሪያ ጊዜ “ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት” የሚለውን መፈክር አውጥቶ አሰራጨ። በዚህ መፈክር ላይ በቅድሚያ በድርጅቱ ውስጥ ሰፊ ውይይት አልተካሄደበትም ነበር። “ለጥቂት ቀናት የመንግሥት ሥልጣን በአየር ላይ የተንጠለጠለችና የሚቀልባት ያጣች ኳስ ስለነበረች” በማለት፣ ደግሞም በሚያዚያ ወር እንዳልካቸው መንግሥት የያዘው አዝማሚያ ቢቀጥልና ሥልጣኑን ቢያደላድል ኖሮ አብዮታዊ እንቅስቃሴ ባጭሩ የሚቀጭ ስለነበር የጊዜውን አጣዳፊነት በመመልከት፣ የድርጅታችን ማዕከላዊ አመራር በገዛ ስልጣኑ መፈክሩን አወጣው።

ወዲያውኑ በድርጅቱ ውስጥ፣ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር፣ ተቃዋሚ ድምፆች መሰማት ጀመሩ። በነሐሴ ወር 66 በአውሮፓ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ጉባኤ ላይ የኢህአፓ ደጋፊዎች የመኢሶንን መፈክር ይዘው ሲከራከሩ፣ የመኢሶን ደጋፊዎች ደግሞ መፈክሩን ተቃውመው እስከመከራከርና እስከማሸነፍ ደርሰዋል።

የየካቲትን እንቅስቃሴ ባህርይ የድርጅታችን አንዱ ክፍልም ሆነ የንዑስ ከበርቴው ደንፊ ቡድን፣ ገዥ መደቦችም ሆኑ ኢምፔሪያሊዝም በጊዜው በትክክል ያልተረዱት፣ በትግሉ ውስጥ የመደቦች አሰላለፍ ለጥቂት ወራት ተዘበራርቆ ስለነበር ነው። በድርጅታችን ውስጥ “የጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት” ተቃዋሚ ክፍል፣ ይህንን ዝብርቅርቅ ሁኔታ ዘልቆ በመመልከት እንቅስቃሴው ከመጀመሪያው የቡርዧ ዲሞክራቲክ አብዮትን መልክ የያዘና በንጉስ ከበርቴው የተመራ መሆኑን በማመን ሲከራከር፣ ደንፊዎች ግን እንቅስቃሴውን የጀመረውና የመራውን “ከፍተኛ ዴሞክራሲያዊ የሆነው የኢትዮጵያዊ ወዛደር መደብ ነው” እስከማለት ደርሰው ነበር። አድሃሪ መደቦችና ኢምፔሪያሊዝም በበኩላቸው በተለመደው አሳባዊ አመለከታቸው የእንቅስቃሴውን ምንጭ ይፈልግ የነበረው በጥቂት “ቀንደኛ መሪዎች”፣ በግለሰቦች ዘንድ ስለነበር፣ ሊረዱትና ከቁጥጥራቸው ስር ሊያውሉት ፈጽሞ አልቻሉም።

የጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት መፈክር ሊወረወር የቻለው የየካቲትን እንቅስቃሴ ባህርይም ካለመረዳት የተነሳ ሲሆን፣ በመሠረቱ፣ እስከ የካቲት 67 ድረስ፣ መኢሶን ይህንን መፈክር ሲያራምደው ቆይቷል። በየካቲት 67 በአመራሩ ውስጥ የነበረው ክርክር ለድርጅቱ አንድነት የሚያሰጋ በሆነበት ወቅት፣ ለጊዜው ድርጅቱ መፈክሩን ማራመዱን እንዲያቆምና በድርጅቱ ውስጥ ሰፊ ውይይት እንዲደረግበት ተወሰነ። ውይይቱ ተካሂዶ መፈክሩ ውድቅ ሲሆን፣ በግንቦት 67 መኢሶን በይፋ መፈክሩን መጋለጥ ጀመረ። እራሱ ያወጣውንና ለደንፊው ቡድን ያስጨበጠውን መፈክር ተዋግቶ ለማሸነፍ ከዓመት በላይ ጊዜና ብዙ ጉልበትን ጠይቆታል። (በነገራችን ላይ፣ የንኡስ ከበርቴው ደንፊ ቡድን እኝኝ ብሎ ይዞት የቆየው “የምርጥ መኮንኖች መንግሥት” የሚለውን አጠራር ያስታቀፈው ይኸው የመኢሶን ክፍል ነበር!)

የየካቲት 66 የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ እንቅስቃሴ በፈነዳበት ወቅት፣ ምንም እንኳን ሰሙን በይፋ ባይገልጥም፣ ድርጅታችን ከነበሩት ቡድኖች ሁሉ የበለጠ ጥንካሬና ተሰሚነት የነበረው ከመሆኑም በላይ፣ የቀሩት ሁሉ፣ ኢህአፓንም ጨምሮ፣ ከርሱ ጋር የተያያዙ ነበሩ። እርሱ ነበር የሚመራቸው ለማለት ይቻላል። ስለሆነም፣ “ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት” የሚለውን መፈክር ሲያወጣ ሁሉም ከሞላ ጎደል ተቀብለውታል። በጊዜው ተቃውሞውን አሰምቶ የነበረው የአብዮት ቡድን ሲሆን፣ እርሱም መፈክሩን የተቃወመው መፈክሩ የሚያስከትላቸውን ቲዎሪያዊና የተግባር ትርጉሞችን በመገምገም ሳይሆን፣ ቡድኑ “ጊዜው የመሳሪያ ትግል ነው” በሚል ሰበብ ወደ ቴሮሪዝም ለመሻገር አቅዶ ስለነበር ነው። የአብዮት ቡድን ብዙም ሳይቆይ ከኢሕአፓ ጋር መዋሃድና የሁለቱ ቡድኖች በ1969 በግድያ መሰማራት ከመጀመሪያውም የነበራቸውን የመደብ ጠባይ -የንኡስ ከበርቴ ፖፑሊስትነታቸውን- በሚገባ አረጋግጧል።

በሌላ በኩል ደግሞ፣ ከ1966 በፊት፣ በስልጣን ጥያቄ፣ በብሔር ጥያቄ ግልፅ ያልነበረ አቋም የነበራቸው አንዳንድ ምሁራንና ንዑስ ቡድኖች ማርክሲዝምን ለማስፋፋት ከመኢሶን አባላት ጋር ተባብረው፣ በስውርና በግልፅ በሚሰሩ የጥናት ክበቦችና የሙያ ማህበሮች ውስጥ ሲሰሩ ቆይተው ነበር። አንዱ አከራካሪ አቋማቸው ጥቂት ወታደሮችን ይዘው ኩዴታ ለማድረግ የሚመኙ መሆናቸው፣ ሌላው ኤርትራ ጥያቄ ላይ ፍፁም ትምክህተኝነትን ማሳየታቸው ነበር። እንደዚሁም ደግሞ ሌሎች የነዚህ ተቃራኒ የሆኑ፣ የኢትዮጵያን ሕዝቦች ትግል ከብሄረሰብ አንጻር ብቻ የሚመለከቱት፣ ጠባብ ብሄረተኞች ነበሩ። እነዚህ ወገኖች፣ አንዳንድም የመኢሶን አባላትና ደጋፊዎች ተጨምረው፣ ከመኢሶን ርቀው 1967 እና 68 ውስጥ አዳዲስ ቡድኖችን እስከመፍጠር ደርሰዋል።

“ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት” የሚለው መፈክር ድርጅታችንን ከነበረው የመሪነትና የጥንካሬ ቦታ ወደታች እንዳቆረቆዘው ባለፉት የሁለት ዓመታት የተደረጉት ትግሎች በሚገባ አሳይተዋል። አንዳንድ ሰዎች ይህ መፈክር ስህተተኛ ቢሆንም በጊዜው የመለዮ ለባሹና በጠቅላላውም የሰፊውን ሕዝብ ትግል በማፋፋም የኃይለሥላሴን መውደቅ እስከ ማስከተል ደርሷል ይላሉ። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን፣ የሰፊውን ሕዝብ እና የመለዮ ለባሹን ትግል ያፋፋመው መፈክሩ ራሱ ሳይሆን፣ በጠቅላላቸው በእንዳልካቸው መንግሥትና በሚካኤል እምሩ መንግሥቶች ላይ፣ ከዚያም በኃይለሥላሴን በራሱ ላይ የነበረው ተቃውሞ ነበር። ኃይለሥላሴን በማጋለጥ በኩል በተለይ ድርጅታችን ከፍተኛ ሚናን ተጫውቷል።

እንዳልካቸው ስልጣን ላይ ሲወጣ የተሰነዘረው “የእንዳልካቸው መንግሥት ይውደቅ” የሚለው መፈክር ትክክለኛ እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም። እንደዚሁም እንዳልካቸው ወድቆ በሚካኤል እምሩ ሲተካ፣ “ጉልቻ ቢለዋወጥ ወጥ  አያጠፈጥም” በማለት የእርሱንም መንግሥት መውደቅ መጠየቅ ትክክለኛ ነበር። ነገር ግን እነዚህን መፈክሮች ሊከተሉ የሚገቡ ሌሎች መፈክሮች “ዴሞክራሲያዊ መብቶች ይታወቁ! ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ይቋቋም!” የሚሉት ነበሩ።በተለይም በመጋቢት እና በሚያዚያ 66 በየቦታው ሕዝባዊ ኮሚቴዎች መቋቋም በያዙበት እና በመኢሶን እንቅስቃሴ አንቀሳቃሽነት የመንግሥት መስሪያ ቤቶችን አጠቃላይ ኮሚቴ ለማቋቋም በቻሉበት ወቅት፣ ዋናው ትግል ማተኮር የነበረበት ወዲያውኑ የመንግሥትን ስልጣን ለመያዝ በመሞከር ላይ ሳይሆን በሰፊው ሕዝብ ነፃ የመደራጀት ጥረት ላይ እንደነበር፣ ዛሬም እንኳን ያለንበት የትግል ደረጃ ራሱ የመሰክራል። አሁንም ገና ሰፊ ሕዝብ ይበልጥ መደራጀት አለበትና።

በ“ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት” ላይ የተደረገው የመስመር ትግል፣ በተለይም ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት ከተቋቋመ በኋላ፣ ከደርጉ የመደብ ባህሪ ጥያቄም ጋር የተያዘ ነበር። ይህንን ጥያቄ በሚመለከተው በኩል፣ ዋናው ጥያቄ “ደርጉ በሲአይኤ የሚመራ የምርጥ መኮንኖች ቡድን ነው ወይንስ የአገር ወዳድ እና የለውጥ ፈላጊ ንዑስ ከበርቴዎች ሸንጎ ነው” የሚለው ነበር። በፊተኛው አስተሳሰብ ከተሄደ፣ ደርጉ፣ 1968 ኢሕአፓ እንዳለው ሁሉ፣ የኢምፔሪያልዝም የቢሮና የአቀባባይ ከበርቴውን መደቦች ጥቅም የሚጠብቅ ቡድን ስለሆነ እስከ መጨረሻው ልንዋጋው ይገባል ማለት ነው። ሁለተኛው ከሆነ፣ ደርጉ የንጉስ ከበርቴውን መደብ የግራ ክንፍ የሚወክልና ቢያንስ ለዴሞክራሲያዊ ለውጦች የሚታገል ኃይል ይሆናል። ስለሆነም፣ ከእርሱ ጋር ጊዜያዊ ወዳጅነትን ለመፍጠር ይቻላል ማለት ነበር።

ደርጉ በሲ.አይ.ኤ. የሚመራ የምርጥ መኮንኖች ቡድን ነው የሚለውን አስተሳሰብ ካስከተሉት ነገሮች አንዱ የኢትዮጵያን ሠራዊት ያሰለጠኑና ያስታጠቁ፣ የሚቆጣጠሩት አሜሪካኖች መሆናቸውና በደርግ ውስጥ ካሉት መኮንኖች ብዙዎቹ በአሜሪካ አገር የሰለጠኑ መሆናቸው ነበር። በተጨማሪም የጥቂት የደርጉ አባላት መኮንኖች በሚስጢር ካንዳንድ አሜሪካኖች ጋር መገናኘነትና የደርጉ በኢምፔሪያሊዝም ላይ ወላዋይ አቋም ይዞ መቆየት ጥርጣሬውን አጠናክሮታል። በእርግጥ ከያንኪዎች ጋር የቅርብ ግንኙነትና መመሳጠር የነበራቸው እንደነሲሳይ ሀብቴ ያሉ ፀረ ኮሚኒስት የደርጉ አባሎችና ሌሎችም ከፍተኛ መኮንኖች መኖራቸው ባይቀርም፣ በጠቅላላው የመለዮ ለባሹ እንቅስቃሴና የደርጉም አመጣጥ፣ ደርጉም  ሂስ ሲሰነዘርበት አልፎ አልፎ መቀበሉ፣ በተራማዶች በኩል በደርጉ ላይ የነበረውን ጥርጣሬ ሊቀንስ የተገባው ነበር።

ደርግ ከተቋቋመበት ከሰኔ 1966 – የየካቲት 67 ድረስ የነበረው የድርጅታችን መሪ አስተሳሰብ ከሞላ ጎደል በጥርጣሬ ላይ የተመሰረተ ስለነበር፣ በዚህ ጊዜ ውስጥ በርከት ያሉ የፖለቲካ ስሕተቶች ተፈጽመዋል። በሰኔና በሐምሌ ወሮች ደርጉ ከተራማጆች የፖለቲካ አስተሳሰብ ድጋፍን ይጠብቅ በነበረበት ወቅት፣ አስተያየቶችን ፖስታ እስከ መጠየቅ በደረሰበት ወቅት፣ መኢሶን ይህንን ድጋፍ ሊያቀርብ ሲችል፣ ደርጉን በጥርጣሬ በመመልከት ስለሸሸውና ከ“ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት” ሌላ ሊያቀርብለት ያዘጋጀው ተግባራዊ አሳብ ስላልነበረው አንዳንድ ሪፎርሚስቶችና አድሃሪዎች የበለጠ ተደማጭነትን ለማግኘት ችለው ነበር። መኢሶን የዕድገት በህብረት ዘመቻን አሳብ መሉ በሙሉ ደግፎ በመውጣት አመራሩን በመያዝና አብዮታዊ አስተሳሰቡን በዚያ አማካኝነት ለመላ ኢትዮጵያ ለማድረስ ሲችል፣ ለሀሳቡ ሙሉ ድጋፍን ነፍጎ አመራሩን ለሌሎች ትቷል። እነዚህና ሌሎችንም የተሳሳቱ የፖለቲካ እርምጃዎች የፈለቁት ከተሳሳተ የደርግ ባህሪ ትንተና ሲሆን፣ እነዚህ እርምጃዎች ድርጅታችንን ጎድተው፣ ለደንፊዎቹ መስፋፋትና ለሌሎችም አድሃሪዎች አመቺ ሁኔታን ፈጥረውላቸዋል።

በታህሳስ 1967፣ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት የታወቀውን የሶሻሊዝም መመሪያውን ያወጣው በሃቀኛ ተራማጆች ተዕእኖ ሳይሆን፣ በሪፎርሚስቶች ተፅዕኖ ስር ሆኖ ነበር። የመምሪያው መውጣት እራሱ ትልቅ እርምጃ ሆኖ ሳለ፣ በተለይ ዲሞክራሲያዊ መብቶችንና የፖርቲን ጉዳይ በሚመለከተው በኩል፣ መመሪያው ፍጹም ስህተተኛው ነጥቦችን ይዞ ነበር። ይሁንናም፣ በጥር 1967፣ ከደርጉ አካባቢ የተባለውን አንድ ፓርቲ ስለመፍጠር ጉዳይ እንዳጋጣሚ የድርጅታችን አንዳንድ ጓዶች ተጠርተው አሳብ ተጠየቀው ነበር።አዝማሚያው እነዚህ ጓዶችና ሌሎችም ተራማጆች በደርጉ ዙሪያ ተሰብስበው የተባለውን ፓርቲ እንዲፈጥሩ ወደ መጠየቅ ነበር። ይህ አጋጣሚ በድርጅቱ አመራር ውስጥ በደርጉ ባህርይ ለይ የነበረውን ክርክር ከማፋፋሙም በላይ፣ በእኛ እና በደርጉ መካከል መኖር ስለሚገባው ግንኙነት፣ ደርጉን እንዴት መመልከት አለብን በሚለው ጥያቄ ላይ ትግልን አስከተለ። ስለሆነም፣ ከብዙ ክርክር በኋላ፣ በአንድ በኩል ለደርጉ የፖለቲካ አስተሳሰብና ድርጊቶች በተቻለ መንገድ ሁሉ አብዮተዊ አዝማሚያ እንዲይዝ ትግል ማድረግ እንዳለብን ሲታመን፣ በሌላ በኩል ደግሞ፣ከዚሁ ጋር ተያይዞ፣ የደርጉን ፀረዲሞክራሲያዊ “ያንድ ፓርቲ” አሳብ ለማስወገድና ለዲሞክራሲወ መብቶች በሰፊው ቅስቀሳ ለማድረግ ተወሰነ።

እንደሚታወሰው በጥር 1967፣ በኤርትራ፣ በተዋጊ ግንባሮችና በኢትዮጵያ ሰራዊት መካከል ኃይለኛ ግጭት ተደርጎ ነበር። ድርጅታችን ከተፈጠረበት ወቅት ጀምሮ የኤርትራን ሕዝብ ትግል ደግፏል። ይህንን ለዴሞክራሲና ለእኩልነት የተደረገውን ትግል ይደገፍ እንጂ የማንኛውንም የኢትዮጵያን ብሄረሰብ ከንጉሠ ነገስቱ መንግሥትም ሆነ ለሌላ መንግሥት እስከ መገንጠል ያላቸውን መብት ይወቅ እንጂ፣ መኢሶን የኢሀፓን አድርባይነት በመከተል የግንባሮቹን የበላይ ተጠባባቂነት ፈጽሞ አልተቀበለውም። በጥር 67፣ በኢትዮጵያ ውስጥ እና በአካባቢዋም የኃይሎች አሰላለፍ በኃይለሥላሴ ዘመን ከነበረው አሰላለፍ ፍጹም ተለውጦ ነበር። በጥር 67ና ዛሬም የኤርትራ ግንባሮች በድርጊታቸው ከኢትዮጵያ አብዮት ጠላቶች ጋር መሰለፋቸውን ማሳየት ባስፈለገበት ወቅት፣ የድርጅታችን አመራር በግንባሮቹ ላይ ምንም አይነት ሂስ ማቅረብ አያስፈልግም የሚል አቋም ነበረው። በኤርትራ ጉዳይ ሰፋ ያለ ክርክር ከተደረገ በኋላ፣ በየካቲት 67፣ ድርጅታችን፣ በአንድ በኩል የደርጉ “የኢትዮጵያ አንድነት ፍፁምነት” የጉልበተኛና የትምክተኛ አስተሳሰብ በመቃወም፣ በሌላ በኩል ደግሞ የግንባሮቹ “የኢትዮጵያን መበታተን ቲዎሪ” በማጋለጥ፣ ለኤርትራ ችግር የሰላማዊ መፍትሄን አሳብ አቀረበ። የመኢሶን አሳብ መጀመሪያ የተኩስ ማቆም ስምምነት በውይይት እንዲገኝ፣ ከዚያም የሦስት-አራት ዓመታት ሰላማዊ ሁኔታ ተፈጥሮ የኢትዮጵያና የኤርትራም ሕዝቦች በመገንጠል ጥያቄ ላይ ሰፊ ዴሞክራሲያዊ ውይይትን እንዲያደርጉና ከዚያ በኋላ የኤርትራ ሕዝብ የገዛ እድሉን እንዲወስን ነበር። ለመገምት እንደሚቻለው ሁሉ፣ ደርግም ሆነ ግንባሮቹ በዚያን ጊዜ የዚህ አይነቱን አስተሳሰብ ለመከተል ስላልቻሉ የኤርትራ ችግር ወደ መፍትሄው ባይቀርብም፣ ከዚያ ወዲህም ቢሆን ድርጅታችን ለሰላማዊ መፍትሄ እንደታገለ ነው።

ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት ከተቋቋመበት ወቅት አንስቶ እስከ የካቲት 67 ድረስ፣ ይህንን መንግሥት በሚመለከተው በኩል የመኢሶን መመሪያ፣ እንደደንፊዎቹ መመሪያ ሁሉ፣ “የማያቋርጥ ተቃውሞ” ነበር። ከደንፊዎቹ በዚህ በኩል የሚለየውም ደርጉ የሚወስዳቸውን አንዳንድ ተራማጅ እርምጃች በጽሁፎቹ መደገፍ ነበር። በመንግሥት ጥያቄ ላይ ግን፣ ከተማሪ ማህበራት ልምድ የተወረሰውና “ሕጋዊ ትግል”ን ፈጽሞ የማያውቀውን ጭፍን መመሪያ የመለወጫው ወቅት እንደመጣ ድርጅታችን፣ በተለይም አመራሩ፣ አልታየውም ነበር። በሌላ በኩል፣ በዚሁ ጊዜ ውስጥ፣ የ“ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት” ተቃዋሚ የድርጅታችን ክፍሎች ሰንዝረው የነበረው “የሂስ ድጋፍ” ወይንም “የአብዮታዊ ሂስ” መመሪያ በድርጅቱ ውስጥ መስፋትን ይዞ ነበር። ይሄኛው መመርያ የተመሰረተው የደርጉን አመጣጥ የወሰዳቸውን እርምጃዎችና ወደፊትም ሊኖረው በሚችለው የአብዮታዊ ሚና ግምገማ ላይ ሆኖ፣ በአንድ በኩል የደርጉን ፀረ ፊውዳልና- ፀረኢምፔሪያሊስት አዝማሚያዎችና በሌላ በኩል ደግም በደርጉና በሰፊው ሕዝብ መካከል ያለውን ቅራኔ በመመልከት ፣ይህኛው ለጊዜው የሁለተኛ ደረጃን ለመያዝ የሚችል መሆኑን በማመን ላይ ነበር። በየካቲት 67 ይህኛው መስመር በድርጅታችን ውስጥ ያሸናፊነቱን ቦታ ለመያዝ ችሏል።

“የአብዮታዊ ሂስ” መመሪያ የመሬት አዋጁ ከሥራ ላይ ለማዋልና በእድገት በህብረት ዘመቻ ጭምር መኢሶን ልባዊ ተሳትፎውን እንዲያደርግ ሰፊ በር ከፍቷል። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ የደርጉ “የአንድ ፓርቲ” አሳብ ቀስ በቀለ ተለውጦ አንድ የሕዝብን መደረጀት የሚያግዝና የሶሻሊዝምን ፍልስፍና የሚያስፋፋ ተቋም እንዲፈጠር እና መኢሶንም ሕጋዊ ትግሉን እንዲያፋፍመው ለማድረግ የተቻለው፣ በድርጅታችን ውስጥ ይህ የመስመር ለውጥ ከተደረገ በኋላ ነበር። ዛሬ የኢትዮጵያ አብዮት የያዘውን አቅጣጫና የደረሰበትን ደረጃ ስንመለከት፣ ይህ የመስመር ለውጥ ለአብዮቱና ለድርጅታችን ያመጣውን ጥቅም በግልጽ ለማየት ይቻላል።

ከዚህ በላይ እንደተጠቀሰው፣ ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ በካቲት 66ም ሆነ በመስከረም 67 የመንግሥትን ስልጣን ለመያዝ ያልቻለው ትግሎቹን አቀናብሮ የሚመራ ጠንካራ ድርጅት ስላልነበረ ነው። በእርግጥ መኢሶንና ሌሎችም የግራ ቡድኖች ነበሩ። ነገር ግን ሁሉም ገና ለጋ የሆኑ፣ በሰፊው ሕዝብ ውስጥ ያልተተከሉ የምሁራን በድኖች እንጂ አንዱም የወዛደን ፓርቲ ከሩቁም የሚመስል ድርጅት አልነበረም። ስለሆነም፣ የወዛደሩን ፓርቲ በመፍጠር ጥያቄም በመኢሶን ውስጥ የመስመር ልዩነት ነበር። የመጀመሪያው መስመር መኢሶንና ሌሎቹም የተራማጆች ቡድኖች በአንድ ላይ ሆነው አንድ ሰፊ ዴሞክራሲያዊ ድርጅትን ካቋቋሙ በኋላ፣ ከዚህ ድርጅቶች ውስጥ የወዛደሩ ፓርቲ ይወጣል ሲል ሁለተኛ ደግሞ መጀመሪያ በተራማጅ ቡድኖች መካከል ህብረት እና መቀራረብ እንዲፈጠርና ከዚያም ወደ ውህደት በመድረስ የወዛደሩን ፓርቲ ለመፍጠር ይቻላል የሚል ነበር። ከህዳር 67 እስከ የካቲት67 ድረስ በዚህ ነጥብ ላይ ሰፊ ውይይት ከተደረገ በኋ፣ ይህኛው መስመር ሊፀድቅ ችሎ፣ በጊዜው በነበረው “የተራማጆች ህብረት” በተባለው ጋዜጣ ላይ በግልጽ ሊወጣ በቅቷል።

የየካቲትን እንቅስቃሴ ባህርይ፣ የመንግሥትን ስልጣን ጥያቄ፣ በደርጉ ላይ ሊኖረን ስለሚገባን አቋም፣ ከግራ ድርጅቶች ጋር ሊኖረን ስለሚገባው ግንኙነትና ስለወዛደር ፓርቲ አፈጣጠር፣ እንደዚሁም በሌሎች የአብዮቱና የጊዜው ጥያቄዎች ላይ በመኢሶን ውስጥ የከረረረ የመስመር ትግል ነበር። ከየካቲት 66 ወዲህ በተደረገው ትግል ውስጥ፣ መኢሶን አንድ ትልቅ የወደፊት እርምጃን ያደረገው፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ እንቅስቃሴ ተጀምሮ በአመቱ፣ በየካቲት 67 የያዘው አዲስ መስመር ነበር። ከየካቲት 66 እስከ መስከረም 2/67 ድረስ፣ ድርጅታችን በነበረው አቅም፣እንደ ሌሎቹ ድርጅቶች ሁሉ፣ ለኃይለሥላሴ መንግሥት መውደቅ የማይናቅ አስተዋጽኦን አድርጓል። ከመስከረም እስከ የካቲት 67 ድረስ ግን፣ የእንቅስቃሴውንና የደርጉን ባህሪዎች፣ የወዳጅንና የጠላትን መደቦች ኃይሎች በመገምገም በኩል፣ የጊዜውን አንገብጋቢ ጥያቄዎች በመረዳትና ትክክለኛ መፈክሮችን በማንሳት በኩል፣ እንደዚሁም በሌሎች መሰረታዊ ጥያቄዎች ላይ ድርጅታችን ስህተተኛ መስመር እንደነበረው በሥራው አሳይቷል። ስለሆነም፣ በየካቲት 67 የመስመር ለውጥ ሲደረግ፣ ከእርሱም ጋር የማዕከላዊ አመራሩ ለውጥ እንዲደረግ የግድ ነበር። እነዚህ ለውጦች በመደረጋቸው መኢሶን ተጠናክሮ ለኢትዮጵያ አብዮት የተሻለ አስተዋፅን ለማድረግ ችሏል።

መሰረታዊ በሆኑ የኢትዮጵያ አብዮት ጥያቄዎች ላይ የመስመር ለውጥ ሲደረግ፣ መኢሶን ድርጅታዊ አንድነቱን ሊጠበቅ ችሏል። ይህ ሊሆን የቻለበት ምክንያት (ከ66 በፊትም ሆነ በኋላ ከድርጅቱ በየጊዜው ከለቀቁትና ከተወገዱት አባሎች በስተቀር) የጓዶቹ ፍፁም ለአብየቱ መሰለፍና አብዮቱን ከራሳቸው በማስቀደም ለመታረም ዝግጁ መሆን ነበር። ወደፊትም ቢሆን፣ እያንዳንዱ ጓድ ለአብዮቱ እስከ ቆመ ድረስ ህይወቱን ጭምር አሳልፎ ለመስጠት ዝግጁ እስከሆነ ድረስ፣ ድርጅቱም ራሱን ከክለሳ እስከ ጠበቀ ድረስ፣ የመስመር ትግል፣ ሂስና ግለሂስ የሚያስፈሩ ነገሮች አይሆኑም። ከድርጅታችን አጭር የሕይወት ታሪክ በግልፅ ለማየት እንደሚቻለው ሁሉ፣ እነዚህ አጠነከሩን፣ ወደፊት እንድንራመድ አደረጉን እንጂ፣ አላዳካሙንም፣ አልበታተኑንም። ስለሆነም፣ ድርጅታችን መጠናከሩንና የበለጠ አስተዋጽኦን ማድረጉን ይቀጥላል።

ከግንቦት 67 እስከ ህዳር 68 የነበረ ጊዜ በኢትዮጵያ አብዮት የሦስት ዓመታት ታሪክ ውስጥ በጣም አስቸጋሪ ወቅት ነበር። ባንድ በኩል፣ ደርጉ የማወላወል ጠባዩን በማሳየት፣ የሠራተኛ ማህበር ላይ፣ በዘማቾች፣ በተራማጅ የመሬት ይዞታ ሠራተኞችና አስተዳዳሪዎች ላይ፣ በተማሪዎችም ላይ በርከት ያሉ የጭቆና እርምጃዎችን ወስዷል። ዘማቾች ትጥቅ ያስፈቱትን የመሬት ከበርቴ መልሶ በማስታጠቅ፣ የሸፈተውን ምህረት ተደርጎልሃል እያለ በመመለስና እንደገና ፀረ ሕዝብ ድርጊቶችን እንዲፈጽም እድል በመስጠት፣ በብዙ ቦታዎች ከአድሃሪዎች ጋር ተሰልፏል። በመስከረም ወር 68 በኢትዮጵያ አየር መንገድ ሠራተኞች ላይ ደርጉ ተደናብሮ የወሰደው እርምጃና ያስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ፍጹም ፀረ ሕዝብ ነበሩ። በጠቅላላው በደርጉ ውስጥ የቀኝ አዝማሚያዎች የአሸነፉበት ወቅት ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ የደንፊው ቡድን የአጉል ጀብደኝነት ድርጊቶች፣ በሠራተኛና በወጣቱ ውስጥ የነዛው ውዥንብርና የድንፋታ መንፈስ ለደርጉ የቀኝ ክንፍ አምቺ ሁኔታን ፈጥሮ ነበር። በዚህ ሁሉ ላይ ደግሞ የተለመደው የክረምት የእህል እጥረትና የዋጋ መናር ሲጨመር በጠቅላው አብዮቱ እንዳይቀለበስ ከሚያሰጋበት ሁኔታ ላይ ደርሶ ነበር። “የአብዮታዊ ሂስ” መመሪያችን ከፈተና ላይ የወደቀበት ወቅት ነበር። ይሁንናም፣ ያ ወቅት ለጊዜው አስቸጋሪ ቢሆንም ዘላቂነት ሊኖረው እንደማይችል በመገንዘብ፣ ድርጅታችን በመስመሩ ጸንቶ ትግሉን ለማፋፋም ችሏል። የደርጉን ወላዋይነትና የደንፊውን ቡድን የአጉል ጅብደኝነት ድርጊቶችን ማጋለጥና የአብዮቱን አቅጣጫ ለሰፊው ሕዝብ መጠቆም የወቅቱ ትክክለኛ ታክቲክ ነበር።

ይህ ታክቲክ ዛሬም ትክክል መሆኑን እናውቃለን። ዛሬም በደርግ ውስጥ የቀኝ አዝማሚያዎች አሉ። ዛሬም የደርጉ ቀኝ ክንፍና ደንፊው ቡድን እንዲሁም የመሳፍንት ተስፋ ለዘውድ ቡድን በተግባር ሊተባበሩና ቅልበሳን ሊያመጡ እንደሚችሉ እናውቃለን። ነገር ግን ዛሬም እንደትናንት የሰፊው ሕዝብ መንቃት፣ መደራጀትና መታጠቅ አማራጭ የሌለው የአብዮቱ ጎዳና ስለሆነ በ“አብዮታዊ ሂስ መመሪያ ለሰፊው ሕዝብ ያለአንዳች አድርባይነት ትክክለኛውን የአብዮቱን አቅጣጫ እንጠቁማለን።

የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ እንቅስቃሴ በታሪክ አይን ሲታይ በጣም አጭር በሆነ ጊዜ ውስጥ ፈጽሞ ሊናቁ የማይችሉ ድሎችን አግኝቷል። ከነዚህ ውስጥ አንዳንዶቹን ለመጥቀስ ያህል፣ የዘውድ አገዛዝ መገርሰስ፣ የገጠር መሬት፣ የከተማ ቦታ ትርፍ ቤቶች፣ በርከት ያሉ የማምረቻና የማከፋፈያ ድርጅቶች፣ የሕዝብ ንብረት ተደርገዋል። በኃይለሥላሴ ዘመን ስሙን እንኳ ማንሳት እንደወንጀል ይቆጠር የነበረው እና መጽሐፍቱ እየተሰበሰቡ ይቃጠሉ የነበረው ሶሻሊዝም በሰፊው በመስፋፋት ላይ ይገኛል። ዛሬ በኢትዮጵያ ግልፅ የሆነ የብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራም ወጥቶ በዚያ ውስጥ የብሄረሰቦች የራስን እድል የመወሰን በይፋ ታውቋል። …… እነዚህንና ሌሎችም ትላልቅ እድሎች በዚህ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊገኙ የቻሉበት ምክንያት ምንድነው? የተገኙትሰ ድሎች ቃል ብቻ ናቸው ወይስ በግብርም ይታያሉ?

የኢትዮጵያ አብዮት እንቅስቃሴ ያስገኛቸውን ድሎች የሚመለከተው በኩል፣ ኢምፔሪያሊዝምና አድሃሪዎች ሁሉ፣ የኢሃአፓንም ደንፊዎች ጨምሮ፣ ያላቸው አቋም አንድ ነው። በኢትዮጵያ ምንም ያለው ለውጥ አልተደረገም የሚሉ አሉ። ወይንም ደግሞ የተደረጉት ለውጦች አገሪቷን ከጨለማ የፋሽስታዊ አገዛዝ ስር አስገባት፣ ስለዚም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ከሁሉ አስቀድሞ ይህንን “የደርግ ፋሺዝም” ተዋግተው ማስወገድ አለባቸው ይላሉ። ወይንም ደግሞ፣ የተደረጉት ለውጦች በቃል፣ በአዋጅ ደረጃ ብቻ እንደቀሩ ግን ለጊዜው ሰፊውን ሕዝብ ለመደለል እንዲያገለግሉ የታቀዱ ናቸው ይላሉ። ይህ ሁሉ መቼስ ኢምፔሪያዝምንና እና የወደቁት መደቦች የራሳቸውን የመመለሻ መንገድ የሚያዘጋጁበት፣ የአለም ሕዝቦችን አስተያየት የሚያወናብዱበት ስልት እንጂ ከተጨባጩ የኢትዮጵያ ሁኔታ ጋር በሩቅም እንኳን የማይመሳሰል ነገር ነው።

የኢትዮጵያ ሕዝቦች በእርግጥም የማይናቁ ድሎችን አግኝተዋል። የሰፊውን ሕዝብ ትግሎች አቀነባብሮ የሚመራ ጠንካራ አብዮታዊ ድርጅት በሌለበት ሁኔታ፣ የኢትዮጵያ አብዮት እስካሁን እነዚህን ድሎች ማግኘቱና ሳይቀለበስም መቆየቱ ብዙውን የውጭ ተመልከች ሳያስደንቅ አይቀርም። ድሎቹ የተገኙበትን ምክንያት እንደሚከተለው ለማቅረብ ይቻላል፡-

አንደኛ፣ የኢትዮጵያ ውስጥና የውጭ ሁኔታዎች ለለውጥ አመቺ ነበሩ። በአንድ በኩል የቀድሞ ሥርአት ፍጹም የበሰብሰብ ከመሆኑ የተነሳ፣ የኢትዮጵያን ሕዝቦች የተፋፈመ ትግል- የገበሬዎችን አመጾች፣ የወዛደሩን እንቅስቃሴ፣ የተማሪዎችን አብዮታዊ ትግሎች የብሄረሰቦችን የመብት ተጋድሎ- ከቁጥጥር ስር ለማድረግ አልቻለም። ከዚህም የተነሳ በገዢ መደቦች በራሳቸው ውስጥ፣ ማለትም በፊውደላዊው መደብ እና በቢሮ ከበርቴው መደብ መካከልና በያንዳንዱም መደብ ውስጥ በተለያዩ ቡድኖች መካከል፣ኃይለኛ የስልጣን ሽሚያ ነበር። ገዢ መደቦች እንደቀድሞ በጸጥታ ለመግዛት አልቻሉም። በሌላ በኩል ደግሞ፣ የቀድሞን ሥርአት አቅፎና ደግፎ ይዞት የነበረው የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም እራሱ ኢንዶ ቻይና ሕዝቦች ትግል ተሸፍኖ ሀፍረትን ከተከናነበ በኋላ፣ በብዙ የውስጥና የውጭ ችግሮች ተወጥሮ ተይዞ በኢትዮጵያ ሁኔታ ላይ የቀድሞዎቹን ገዥ መደቦች ከውድቀት ሊያድናቸው ከማይችልበት ሁኔታ ላይ ነበር ስለዚህም፣ የየካቲት እንቅስቃሴ ፈንድቶ በጥቂት ወራት ውስጥ ከሁለቱም ኃይሎች ቁጥጥር ውጭ ሊሆን ችሏል።

ሁለተኛ፣ የንጉሰ ነገስቱ የመጨቆኛ መሳሪያዎች የነበሩት የጦር ኃይሎች በሥርዓቱን ላይ አፈሙዛቸውን ማዞራቸው ለለውጡ ወሳኝ ነገር ነበር። የኢትዮጵያ መለዩ ለባሽ ራሱን ጭቁን ሆኖ ሰፊውን ሕዝብ የሚጨቁን ከመሆኑም በላይ፣እርስ በእርሱ የተከፋፈልና በተለይም ለንጉሰ ነገስቱ “ፍጹም ታማኝ” የሆነ ኃይል ነበር። ንቅናቄው ከደሞዝ ጭማሪ ጥያቄ አልፎ ወደ ፖለቲካ ጥያቄ ሊዛወር የቻለው በውስጡ የነቁ ወጣት መኮንኖችና ባለሌላ ማዕረጎችም ስለነበሩና እነዚህም የሥርዓቱን መበስበስ በመገንዘብ፣በቆራጥነት በመነሳሳት መላ ሰራዊቱን ለማስከተል በመቻላቸው ነው።ያለነዚህ ቆራጥ ታጋዮችና ያለመለዮ ለባሹ ምንም ያህል ለውጥ ሊመጣ ባልቻለ ነበር።

ሦስተኛ በሰኔ 66 የጦር ኃይሎች አስተባባሪ ደርግ በቆመበት ወቅት ጥቂትና ተራማቾችና አገርወዳድ ግለሰቦች ደርገን በአሳብ ሊረዱት እንደቻሉ ይታወቃል። በተለይ ግን ከታሳህሳስ-ጥረ1967 ጀምሮ በሃቀኛ የኢትዮጵያ ተራማጆች እና በደርጉ የግራ ክንፍ መካከል የገቢር ህብረት ተፈጥሮ ነበር። ስለሆነም፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ እንቅስቃሴ የተባሉትን ደሎች እንዲያገኝ ካደረጉት ነገሮች ውስጥ አንዱ የሃቀኛ ተራማጆች ከደርጉ ጋር መሰለፍ ነበር። የኢትዮጵያ  አብዮታዊያን ይህንን ቆራጥ እርምጃ ባይወስዱና እንደ ኢህአፓ ጀብደኞች “በማያቋርጥ ተቃውሞ” ቢፀኑ ኖሮ፣ አብዮቱ በርግጥ ይቀለበስ ነበር ለማለት ይቻላል።

የኢትዮጵያ አብዮት የማይናቁ ድሎችን ተቀዳጅቷል፤ ግን እነዚህ ድሎች በቀላሉ የተገኙ አልነበሩም። የመሬት ላራሹ አዋጅ በየቦታው ውጊያዎንች በመፍጠሩ ብዙ ጭቁን መለዮ ለባሾች፣ አዝማቾች፣ ዘማቾች፣ የመሬት ይዞታ ሠራተኞችና አርሶ አደሮች ሕይወታቸውን መስዋእት አድርገዋል። ይህንን አዋጅና ሌሎችን በመቃወም የተነሳሱት አድሃሪዎች በየቦታው በመጠኑም ቢሆን ተደምሰዋል። በአንድ ጊዜና አገር አቀፍ በሆነ የእርስበርስ ጦርነት አይሁን እንጂ በየቦታውና በየጊዜው በአብዮትና በፀረአብዮት ኃይሎች መካከል ትላልቅ ግጭቶች ተደርገው ሰፊው ሕዝብ ብዙ መስዋዕቶችን ተቀብሏል። መኢሶንም በትግሉ ሜዳ ካሰማራቸው ቆራጥ ታጋዮች ውስጥ በርከት ያሉ ጓዶችን አጥቷል። ይሁንም፣ ለተገኙት ድሎች ሰፊው ሕዝብ ብዙ መስዋእትነትን የደረገ ቢሆንም፣ እነዚህ ድሎች አሁንም ገና ስር አልሰደዱም። የኢትዮጵያ ሕዝቦች ነቅተው፣ ተደራጅተውና ታጥቀው ያገኟቸውን ድሎች እስከመጨረሻው ለመጠበቅና አዳዲስ ድሎችንም ለመቀዳጀት ገና ብዙ መንገድ ይቀራቸዋል። የወዛደሩን ፓርቲና በዚህም ፓርቲ የሚመራ አብዮታዊ ግንባርን ፈጥረው፣ ፊውዳሊዝምን፣ኢምፔሪያሊዝምንና ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝምን ደምስሰው የመንግሥትን ስልጣን በእጃቸው እስካላስገቡ ድረስ፣ ያገኟቸው ድሎች ዘላቂ ሊሆኑ እንደማይችሉ ግልጽ ነው።

ይህንን ስለሚያውቁ፣ የኢትዮጵያ አብዮት ጠላቶች በአሁኑ ወቅት አብዮቱን ለመቀልበሰ በመሯሯጥ ላይ ይገኛሉ። እነ መንገሻ ስዩም- ነጋ ተገኝ-አሊሚራህ (የኢድዩ መሳፍንት) በኢምፔሪያሊሰትና በአንዳንድ አድሃሪ የአረብ መንግሥታት ታግዘው፣ ኢ.ኤል.ኤፍ. ጋር ግንባር ፈጥረው፣ አብዮቱን በመክበብ ላይ ይገኛሉ። ከእነርሱ ጋር ተሰልፏል። እነዚህ ኃይሎች የቢሮክራሲያዊ ከበርቴውንና የመሬት ከበርቴውን ፀረ አብዮታዊ ሴራዎችና ድርጊቶች ያቀነባበራሉ። በጎረቤት አገሮች ድጋፍን አግኝተዋል። የፀረ አብዮቱ ካምፕ አላማ በኢትዮጵያ የተጀመረውን እውነተኛ የሕዝቦች ነፃነት እንቅስቃሴ ርቆ ሳይሄድ ለመቅጨትና ኢትዮጵያ ተመለሳ በጨለማው ሥርዓት ሥር ወድቃ፣ ደካማና ወደኋላ የቀረች ሃገር ሆና እንድትኖር ለማድረግ ነው።

ይህንን የፀረአብዮት ኃይሎች ሴራ ሊያከሽፍ ከሚችለው የነቃ፣ ተደራጀትና የታጠቀ የሕዝብ ኃይል ብቻ ነው። መኢሶን በአሁኑ ሰዓት የሚታገለው የዚህ ዓይነቱ ኃይል በተቻለ ፍጥነት እንዲፈጠርና እንዲጠናከር ሲሆን፣ የኢትዮጵያን አብዮት የዓለም ፀረኢምፔሪያሊስትና ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ሁሉ ከመደገፍ እንደማይቆጠቡ ያምናል።

የነቃ፣ የተደራጀና የታጠቀ የሕዝብ ኃይል እንደሚያስፈልግ ለማሳወቅ ድርጅታችን በየእለቱ ሰፊ ቅስቀሳን እንደሚያደርግ በግልጽ እየታየ፣ አንዳንድ ሰዎች እና ቡድኖች “የመንግሥትን ስልጣን አያያዝ በሚመለከተው በኩል መኢሶን ቁልጭ ያለ አቋም የለውም” እስከማለት ይደርሳሉ! የኢትዮጵያ መለዮ ለባሽ ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ለአብዮቱ እስካሁን ያደረጉት አስተዋጽኦ በጣም ከፍተኛ መሆኑንና ወደፊትም ብዙ ሊያበረከቱ እንደሚችሉ ቢያምንም እነዚህ ኃይሎች እንዳሉ እስከመጨረሻው ለአብዮቱ ይቆማሉ በሚለው የህልም እንጀራ ድርጅታችን ፈጽሞ አያምንበትም። በደርጉ ውስጥም ሆነ በመለዮ ለባሹ ውስጥ ያሉት አብዮታዊና ፀረአብዮት ሰልፋቸውን ለይተው የሚፋጠጡበት ወቅት በርግጥ ይመጣል። ለዚህም ነው የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ በየእለቱ ይበልጥ መንቃት፣ መደራጀት እና መታጠቅ ያለበት።

በአጭር ጊዜ ሲታይ፣ ጅርጅታችን የሚታገለው ለዲሞክራሲያዊ መብቶች መታወቅ፣ ለቢሮክራሲው መሻሻል፣ ለተራማጆች ህብረትና ለወዛደሩ ፓርቲ መፈጠር ነው። የድርጅታችን ባስተሳሰብም ሆነ በሰው ጉልበት እና በድርጊት መጠናከር ለወዛደሩ ፓርቲ መፈጠር ዋስትና ነው። የተራማጆችን ህብረትና የወዛደሩን ፓርቲ እንፈጥራለን። ድርጅታችን በያዘው ትክክለኛ መስመር ቆርጦ ከገፋ፣ ማንኛውም መስዋዕትነት ሳይፈራ መሰናክሎችን ሁሉ ካሸነፈ፣ ከሰፊው ሕዝብ ጋር በጥብቅ ከተሳሰረና ማርክሲዝም-ሌኒኒዝምን የድርጊቶቹ ሁሉ መመሪያ ካደረገ ለኢትዮጵያ አብዮት የሚጠበቅበትን ድርሻ በርግጥ ያበረክታል።

[የማይነበብ መፈክር – አዘጋጆቹ]
የተራማጅ ኃይሎች ህብረት ይመሰረታል!
ፀረ አብዮታውያንን ይደመስሳሉ!
ሰፊው ሕዝብ ያሸንፋል!
Scroll to Top