ሰሕድ ቁ. 31

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ቁጥር 31፣      ሕዳር 5፣ 1968

የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ

በዚህ ጽሁፍ መኢሶን በአብዮቱ መጀመሪያ ቀናት የተደናገጡት አድሃሪያን ለመደራጀትና ለመተባበር የሚያደርጉት ጥረት ብቻ ሳይሆን አብዮቱን ለመቀልበስ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ መስተዋሉን ያስታውቃል። የአየር መንገድ ሠራተኞች ላይ የተፈጸመው ጭፍጨፋ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መውጣትና በተራማጅ ኃይሎች ላይ የሚደርሰው ወከባ፣  አብዮቱን አሳሳቢ ሁኔታ ላይ እንደጣለው ያብራራል። በዚህ ሁኔታ በተራማጅ ኃይሎች መሃል ያሉት ውስጣዊ ቅራኔዎች በውይይት እንዲፈቱ፣ እየተስፋፋ ያለው የፖለቲካ ውዥንብር  እንዲወገድና ከሕዝባዊ ድል ጋር ተያይዞ ለሚመጣው ሕዝባዊ መንግሥት መሳካት፣ ተራማጆች ሁሉ በአንድነት በዴሞክራሲ መፈክር ስር እንዲታገሉ መኢሶን ጥሪውን ያቀርባል።

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ለሰፊው ሕዝብ ሰራተኛ ገበሬ፣ ነጋዴ፣ ወታደር፣ ምሁር መብትና ጥቅም የሚታገል ጋዜጣ

የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ይቅደም

ቁጥር 31                                                                        ቀን 5/3/68

 

ው ዠ ን ብ ር ና   ዲ ሞ ክ ራ ሲ

በየካቲት 1966 ዓ.ም. ፈንድቶ እየተጋጋለ ብዙ ድሎችን የተጐናፀፈው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለአብዮታዊ ተጋድሎ በአሁኑ ወቅት በርግጥ ባለበት ቆሞ በመርገጥ ላይ ይገኛል። በአብዮታዊ ትግል አፍላ ላይ የሚገኝ ሕዝብ ደግሞ ቆሞ ፋታ መውሰድ ከጀመረ የመቀልበሱ አደጋ ተያይዞ የሚመጣ መቅሰፍት መሆኑን የብዙ ሕዝቦች አብዮታዊ ትግል ታሪክ ደጋጋሞ ያሳየው ነው። በዚሁ በአመት ተመንፈቅ አብዮታዊ ትግላችን እንኳን ስንመለከተው የኢትዮጵያ ሕዝቦች ከዚህ ካሉበት ምእራፍ መድረስ የቻሉት እነእንዳልካቸው “ፋታ ስጡት” እያሉ ትግሉን ለመግታት ሲፍጨረጨሩ አሻፈረን ብለው በታላቅ መስዋአትነት ትግሉን ያለማቋረጥ ወደፊት መግፋትን በመምረጣቸው ነው።

ዛሬ ሰልፋቸውን እያሳመሩ ከሄዱት የመሳፍንት ርዝራዦችና አድሃሪዎች በስተቀር የኢትዮጵያን አብዮት ወደፊት ለመግፋት የሚችሉት ኃይሎች በሙሉ በውዥንብር ባህር ውስጥ የሚዋኙበት ጊዜ ነው ቢባል ከእውነት የራቀ አይሆንም። ከዚህ ውዥንብር ውስጥ ለመውጣት ተራማጆች ሁሉ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ የሃገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ ተንትነው በመረዳት ታክቲካቸውን መቀየስ አለባቸው። ይንንም ታክቲክ ለመቀየስ ሃገሪቱ የምትገኝበትን ታሪካዊ ወቅት፣ በህብረተሰቡ ውስጥ ያሉት መደቦችና የህብረተሰብ ክፍሎች በሙሉ ያላቸውን ግንኙነት፣ ዝምድናም ሆነ ቅራኔ ተንትኖ የእያንዳንዱን መደብ አሰላለፍ ሁኔታ ማጤን እንደሚያስፈልግ ታላቁ ሌኒን ያስተምረናል። ይህም ትንተና የሚደረገው ለቴዎሪ ቅንጦት ሳይሆን የጊዜውን ዋና ጠላቶች ከጊዚያዊ ወዳጆች ለመለየት፣ በጠላቶች ሰፈር ሊኖር የሚችለውን ቅራኔ በሚገባ ለማወቅና ይህንንም የግጭት ፍንጭ በማባባስና በማስፋት ጠቅላላውን የጠላት ሰፈር ለማዳከም፣ ጊዜያዊ ወዳጆች ሊሆኑ የሚችሉትን ኃይሎች ደግሞ አረጋጋቶና አሳምኖ ወደአብዮቱ የሚስብ ታክቲክ ለመከተል እንዲቻል ነው። አብዮታውያን መከተል ስላለባቸው ታክቲክ የብዙ ዘመን የቦልሼሺኮችን ፖርቲ ትግል ኤክስፒሪየንስ ጨምቆ ባቀረበበት ‘ጥራዝ ነጠቅ ኮሙኒዝም የልጅነት በሽታ’ በተባለው ታላቁ መጽሀፉ ውስጥ ስለዚህ የታክቲክ መመሪያ አንስቶ ሲጽፍ ሌኒን እንዲህ ብሏል፡-

 “ይህንን ሃቅ ያልተገነዘበ ሁሉ ስለኮሚኒዝምም ሆነ ስለዘመኑ ሳይንሳዊ ሶሻሊዝም ቅንጦት የገባው  ነገር የለም። እንደዚሁም ደግሞ ረዘም ላለ ጊዜና በተለያዩ የፖለቲካ ሁኔታዎች አማካኝነት ይህን ሃቅ ከሥራ ላይ ለማዋል መቻሉን በተግባር ያላረጋገጠ ሁሉ አብዮታዊው መደብ መላውን የሰው ዘር ከበዝባዦች ለማላቀቅ በሚያደርገው ተጋድሎ የመርዳቱን ጉዳይ ገና አላወቀበትም ማለት ነው።”

ዛሬ በኢትዮጵያ አብዮት እንደምናየው ከሆነ ተራማጁ ወገን በልዩ ልዩና በተወሳሰቡ ውስጣዊ ቅራኔዎች ተውጦ ሲዋዥቅ አድሃሪዎቹ ደግሞ የብዙ ሕዝቦችን አብዮቶች በማክሸፍ በሰለጠኑ ኢምፔሪያሊስቶች ድጋፍና ምክር ሰፈራቸውን እያጠናከሩ በተራማጁ ሰፈር ደግሞ ውዥንብርን፣ መቃቃርን፣ መለያየትን እየነዙ መሃል ሰፋሪውን መደብ ሁሉ ወደፀረአብዮቱ ሰፈር በመሳብ ላይ ይገኛሉ። ይህ ሁኔታ ባስቸኳይ ካልታረመና መላው የኢትዮጵያ ተራማጆች በታሪክ ፊት ሃላፊነታቸውን ተቀብለው የነሌኒንን ምክር ካላደመጡ አብዮታችን ባጭር ጊዜ ውስጥ ተቀልብሶ አገራችን ተመልሳ አሰቃቂ ጨለማ ውስጥ እንደምትጨመር ለመገመት አያዳግትም።

በአሁኑ ጊዜ በአድሃሪዎችና በተራማጁ መካከል ያለው የኃይል ሚዛን እንዴት ነው? ከኢትዮጵያ ሕዝቦች ዋና ጠላቶች እንጀምር። ፊውዳሊስቶቹና ኢምፔሪያሊስቶች ሳያስቡትና ልኩን ሳይረዱት ባጥለቀለቃቸው አብዮታዊ ማእበል የተደናገጡበት ወቅት አክትሟል። የፀረአብዮቱ ኃይሎች አይን በአሁኑ ጊዜ ተስፋውን በውጭ አገር፣ በአሜሪካን፣ በጀርመንና በእንግሊዝ. . .  ኢምፔሪያሊስቶች፣ እንደዚሁም በአድሃሪ አረብ አገሮች ግልጽ ድጋፍ በመደራጀት ላይ ባሉት በመሳፍንቱ ርዝራዦች ላይ ወድቋል። ታሪክና የኢትዮጵያ ጭቁን ሕዝቦች የተፏቸው ፊውዳሊስቶችና ፋሺስቶች፡ እነአስፋውወሰን ኃይለሥላሴ፣ እነመንገሻ ስዩም መቸም በመደብ ትግል ሃፍረትና ይሉኝታ የሚሉ ነገር የለምና “የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ማህበር” ብለው ቀባብተው ያቀረቡትን ንቅናቄ በማጠንከር ላይ ይገኛሉ። ይህ ፋሽስታዊ ቡድን ከላይ በጠቀስናቸው ፀረአብዮት ኃይሎች በሚቃርመው ርዳታ ራሱን ቀና ቀና ከማድረጉም በላይ በአሁኑ ጊዜ ከአገር ውስጥ አድሃሪዎች፣ ከባላባቶች፣ ከመሳፍንት ርዝራዦች፣ ከኢምፔሪያሊስት ወኪሎች፣ አንሰው አንከባክበውና ኮትኩተው ካሳደጉት የቢሮ ከበርቴዎች መደብ ጋር በመላላክ ፋሽስታዊ ሴራውን በአገራችን በማድራት ላይ ይገኛል።

    ይህ የአድሃሪዎች ሰፊር መጠናከር በሁለተኛ ደረጃ ያሉትን የብሄርና የሃይማኖት ቅራኔዎች አቻችሎ በመደብ አንድነት ላይ የተመሰረተ መሆኑን ማስገንዘብ ያስፈልጋል። ይህ ፀረአብዮት አንድነት እንኳን ኩታ- ገጠም የሆኑት አድሃሪዎች ይቅርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ውቅያኖስና ባህር አቆራርጠው ፀረሕዝብ ኃይሎች ሁሉ የተባበሩበት አንድነት ነው። የኢምፔሪያሊስት ጋዜጦች የአስፋወሰን ኃይለሥላሴና የመንገሻ ስዩም ‘የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ማህበር’ ሰራዊት ወልድያን ‘ነፃ አውጥቶአል’፣ ወይም ደግሞ የዚህ ፋሽስታዊ ቡድን መሪዎች ‘መሃል ኢትዮጵያ’ ድረስ ሄደው ‘ቋራ ላይ ተሰብስበው ነበር’ እያሉ በሬ ወለደን ለመላ ዓለም ሲያስተጋቡ ለዚህ ፋሺስታዊ ቡድን ያላቸውን ድጋፍ በይፋ መግለጫቸው መሆኑ መታወቅ አለበት።

በኢምፔሪያሊስቶቹ አስተባባሪነትና በአድሃሪው የሳውዲ አረቢያ መንግሥት አስተናጋጅነት የዚህ ‘ዲሞክራሲያዊ’ ፋሽስት ማህበር ቀንደኛ መሪዎች ጰጉሜ ሦስት ቀን 1967 ዓ.ም በጅዳ ከተማ ተሰብስበው ፀረአብዮት ሴራቸውን ለማስተባበር መሞከራቸው ያደባባይ ምስጢር ነው። በዚህ ስብሰባ ላይ ከነበሩት ውስጥ ቀንደኞቹ ነጋ ተገኝ፣ መንገሻ ስዩም፣ ኢያሱ መንገሻ፣ አሊ ሚራህና ኦስማን ሳቤህ ናቸው። ጥቅምት 2 ቀንም በቤይሩት ከተማ የኤርትራ ነፃ አውጭ ግንባር መሪዎች በሰጡት መግለጫ ‘አምባገነኑን የወታደር አገዛዝ’ ለመዋጋር በሚደረገው ጥረት ለዚህ ‘ዲሞክራሲያዊ’ የፋሽስቶች ንቅናቄ ‘የማቴሪያልና የሞራል እርዳታ’ የሚለግሱ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

በኢትዮጵያ ጭቁን ሕዝቦች አብዮታዊ ትግል ተደናግጠው አደርባዩችና አድሃሪዎች ጥቃቃን ልዩነቶቻቸውን አቻችለው አንድነታቸውን በማጠናከር ላይ ናቸው። በኛ እምነት ይህ የፀረአብዮት አንድነት የኢትዮጵያ ሕዝቦች ትግል እየገፋ በሄደ ቁጥር የሚጠነክር አንድነት ነው። በዚህም በመመራት የልዩ ልዩ ብሄሮች ተራማጆች እያደር እየጎላ ከሚሄደው የአድሃሪዎች አንድነት አስፈላጊውን ትምህርት ቀስመው እነሱም በበኩላቸው የትግል አንድነታቸውን ማጠናከር አለባቸው። አድሃሪዎች እንዲህ እንደዛር ስለተደራረቡ የኢትዮጵያ ተራማጆችና ጭቁን ሕዝቦች በምንም አይነት የሚደናገጡና የሚሸበሩ አይደለም። ሰፊው ሕዝብ እስከተባበረና የአንድነት ክንዱን እስካነሳባቸው ድረስ ተልባ ቢንጫጫ ባንድ ሙቀጫ ነውና።

የአድሃሪዎቹ ጥርቃሚ ጠቅላላውን በሰሜንም ሆነ በደቡብ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አክ እንትፍ ብለው የተፉት ቡድን ነው። በረዥም ጊዜና በተወሳሰበ ትግል ጨርሶ እንደሚደመሰስ ቅንጣት ጥርጣሬ የለንም። ይህንን እንኳን እኛ የአድሃሪዎቹ ቡድን ራሱ ጠንቅቆ ያውቀዋል። በማወናበድ ቀኑን ያራዝማል እንጂ ታግሎ አያሸንፍም። ለዚህ ነው የኢትዮጵያ ጭቁን ሕዝቦች ለዘመናት ያለቀበት የደም እንባ ገና ሳይደርቅ ሰው ያደናገረ መስሎት ‘ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ’ ነኝ ብሎ ተኳኩሎ ለመቅረብ የሞከረው። ለዚህ ነው የረዥም ጊዜ ተጋድሎ እንደሚያዋጣው አውቆ በያለበት ሁከት በመጫር፣ የፖለቲካና የኤኮኖሚ ውዥንብር በመንዛት በሚፈጠረው ግርግር ተጠቅሞ ደጋግሞ እንደሞከረውና ወደፊትም እንደሚሞክረው አድሃሪ መፈንቅለ መንግሥት ሴራ ላይ የሚያተኩረው። በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ያገሪቱ ጠቅላላ ሁኔታም ሆነ በተራማጆች መካከል ሆን ተብሎ የሚነዛው ውዥንብር ለዚህ ያድሃሪዎች ሴራ ያመቸ የሚሆነው።

በአገሪቱ በጠቅላላው ያለውን ሁኔታ እንመልከት። በገጠር የሄድን እንደሆነ በሰሜን ክፍለአገሮች በነአስፋወሰን ‘ዲሞክራቲክ ማህበር’ ቆስቋሽነት የልብ ልብ እየተሰማቸው አድሃሪዎች በተቀነባበረ የማወናበድ ዘመቻ በሰፊው ሕዝብ ጫንቃ ላይ አሰቃቂ የሆነ የርስ በርስ ጦርነት በመጫን ላይ ይገኛሉ። በደቡብ የመሬቱ አዎጅ እንደታወጀ በታላቅ አብዮታዊ መንፈስ ተነሳስቶ የነበረው ሰፊው አርሶበሌ በደርጉ እየታገዙ ባየሉት አድሃሪዎች መበርታት የተነሳ ቅስሙ በመሰበር ላይ ይገኛል። አድሃሪ ኃይሎችና የመንግሥቱ ቢሮክራሲ በሙሉ ለሰፊው ሕዝብ መጠናከር ትልቅ እንቅፋት ሆኗል። በዚህ ሁኔታ ሰፊው ሕዝብ በትግሉ ያገኛቸው አዋጆች በሥራ ላይ ለመዋልም ብዙ እንቅፋቶች አጋጥመዋቸዋል።

አዋጁ ታውጆና የገበሬ ማህበራት በያለበት ተቋቁመው በግንባር ቀደም ደረጃ የሚገኙት ማህበራት ከቀድሞ ስርዓት የመንግሥት አውታሮች ጋር በከፍተኛ ትንንቅ ላይ በነበሩበት ወቅት የሰፊው ሕዝብ ድምፅ ቁጥር 30 “ዘመቻውና አብዮቱ” በሚል ርዕስ አንድ ትንተና ማቅረቡ ይታወሳል። በዚህ ጽሁፍ ላይ የገበሬ ማህበራት መጠናከር ከቀድሞ ቢሮክራሲ ጋር ሲፋጠጡ መገንዘብ የሚገባን ትግሉ ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱን ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ አብዮት አንድ አዋሳኝ መድረክ ላይ መሆኑን አውስተን ነበር። በዚህም ትንተናችን በግንባር ቀደምነት የተጋፈጡት የገበሬ ማህበራት ታጥቀው አድሃሪዎችን መቋቋምና መደምሰስ ከቻሉ ተከታዩ ትግልና ጠቅላላው አብዮት በአዲስ እስትንፋስ ወደፊት የሚገሰግስበትና አድሃሪዎችን የሚያጥለቀልቅበት በር እንደሚከፍት፣ የኢትዮጵያ ገበሬዎች አጥብቀው የሚጠይቁት የመታጠቅ መብታቸው ከተነፈጋቸው ግን እነሱ ብቻ ሳይሆኑ ጠቅላላው አብዮት ታላቅ ውዥንብር ውስጥ ወድቆ፣ ቅስሙ ተሰብሮ የመቀልበስ አደጋ እንደሚያጋጥመው አትተን ነበር። ይህም የግንባር ቀደሞቹ የገበሬ ማህበራት ጥያቄ አብዮቱና ዲሞክራሲ በሚጠይቁት መሰረት ካልተመለሰ ዘመቻው ሆነ ጠቅላላውን የገበሬ ማህበራትን የማቋቋሙ ጉዳይ (ሄደው ሄደው የታጠቁ አድሃሪዎች መሳሪያ ላይ ለመከስከስ ከሆነ) ጨርሶ አብዮታዊ ትርጉሙን እንደሚያጣና ትልቅ ችግር እንደሚፈጠር ጠቁመን ነበር።

ዛሬ ከፊታችን ተደቅኖ የምናየው ይህንኑ ሃቅ ነው። ዲሞክራሲ ለጠየቀ ሕዝብ ፋሽስታዊ የሆነ ጊዚያዊ አዋጅ አብዮቱን በማፈን ላይ ያለው ደርግ የመታጠቅ መብቱን ለጠየቀው ገበሬ የሚሰጠው መልስ ማሰር፣ መግረፍና መረሸን ሆንዋል። እንዲያውም ከዚህ አልፎ ተርፎ በስንት ትግልና መስዋእትነት ድሃው ገበሬ ከአድሃሪዎች የቀማውን መሳሪያ መልሶ እንዲያስረክብ በማድረግ ፀረ-አብዮት ኃይሎችን ማጠናከር ሥራዬ ብሎ ይዟል። በዚህ ሁሉ የልብ ልብ የተሰማቸው አድሃሪዎች ተራማጅ የመሬት ይዞታ ሠራተኞችን፡ ዘማቶችንና ገበሬዎችን እያሳደዱ መረሸን፡ ማሰርና ማጐሳቆል ላይ ናቸው። ነገሩ እንደዚህ ሆኖ ሳለ የኢትዮጵያ ሬዲዩ ጠዋት ማታ ‘በመሬቱ አዋጅ ተደናግጠው ጫካ የገቡ ወደሰላማዊ ኑሮ ተመለሱ’ የሚለው ልፈፋው ማንንም አያታልልም። ይህ አነጋገር ሺህ ጊዜ ተቀባብቶ ቢቀርብ የአድሃሪዎች ‘ድንጋጤ’ መብረዱ የሚያመለክተው የነሱን ‘በተራማጅ ጠበል መጠመቅ’ ሳይሆን የአብዮታችንን ቀስ በቀስ እየተቀለበሰ መሄድ ነው። ከእንግዲህ ኢትዮጵያ ጭቁን ሕዝቦችዋንና አደሃሪዎችን አቻችላ ለመኖር የማትችል አገር መሆኗን የማይስቱ ተራማጆች ሁሉ ይህ አባባል ‘አድሃሪዎች አይዟችሁ፣ አብዮቱ እየተቀለበሰ ነው’ የሚል ማረጋጊያ መሆኑን ይረዱታል።

በከተማም ቢሆን በአየር መንገድ ሠራተኞች ላይ ከተፈፀመው ፋሽስታዊ ግፍ፣ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ ከሥራ ማቆሙ አድማ አለመሳካት. . . በኋላ ወዝአደሩ ለጊዜው ቅጥሙ ተሰብሮ በተስፋ መቁረጥ ባህር ውስጥ ሰምጧል። ከንዑስ ከበርቴው መደብ አብዛኛው በፀረዲሞክራቲኩ የደርግ አገዛዝ ላይ የሚያሳየው ጥላቻ ከመቸውም በማየሉ ብዙው ወደ ፀረአብዮቱ ሰፈር የመደባለቅ አደጋ ይታይበታል ለማለት ይቻላል። ለኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ መጋደል እንደወንጀል ተቆጥሮባቸው እስር ቤት እስኪጠብ ድረስ ታፍሰው በመታጐር ብዙ ታጋይ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በታላቅ ስቃይ ውስጥ ይገኛሉ። ይህ ሁሉ ሲታይ ደርጉ ፀረዲሞክራሲ ብቻ ሳይሆን ፀረሕዝብና ፀረአብዮት አቋምም ወስዷል ማለት ይቻላል።

በዚህ ሁሉ የተነሳ የተራማጅ ሰፈር ጠቅላላውን ጊዚያዊ መዳከም ስለደረሰበት በኢትዮጵያ ለፀረአብዮት ምላሽ እጅግ ያመቸ ሁኔታ በመፈጠር ላይ ነው። አደገኛ ውዥንብር አለ። የኢትዮጵያ ተራማጆች እንደምንም ተረዳድተውና ተደጋግፈው ይህንን ውዥንብር ማጣራት አለባቸው። የተራማጆች አለኝታ ከሰፊው ሕዝብ ጋር ሆነው ለዲሞክራሲ እየታገሉ አብዮቱን ከመቀልበስ ማዳን ነው። በሳይንሳዊ ትንተና ላይ የተመረኮዘ ግልጽና አብዮታዊ ታክቲክ ቀይሰው ወደፊት ለመራመድ የማይቆጠብ ጥረት ማድረግ አለባቸው። ለዚህ ደግሞ ከቆራጥና ሃቀኛ ትግላቸውና ከሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ በስተቀር ሊተማመኑበት የሚችሉበት ምንም አይነት ኃይል የለም። ይህም ከሁሉ አስቀድሞ በራሱ በተራማጁ ክፍል ውስጥ ሆን ተብሎ የሚነዛውን ውዥንብር ከምንም አይነት እወደድባይነት በራቀ ሃቀኛ ትግል እንዲወገድ መጣር ያስፈልጋል።

አንድ ቡድን ወይም ግለሰብ በርግጥ ተራማጅነቱና ለአብዮት ግንባር ቀደምነቱ የሚረጋገጠው በአንደዚህ አይነቱ የውዠንብር ጊዜ አብዩቱ ከገባበት ማጥ ሊወጣና ወደ ፊት ሊገሰግስ የሚችልበትን ዘዴ በግንባር ቀደምነት ሲጠቀምና በዚህም አላማ ፀንቶ ሲታገል ብቻ ነው። የአድሃሪዎች አመጽ ወይም የፀረዲሞክራቲኩ ደርግ የአገዛዝ ፋሽስታዊ ድርጊቶች አየተባዙ ሲሄዱ የባጥ የቆጡን ቢቀበጥሩና ቢለቀልቁ ብቻ አብዩቱ መከተል የሚገባውን ፋና ማሳየት እንደማይቻል ግልጽ ነው።

 “የሰፊው ሕዝብ ድምጽ” ለኢትዮጵያ ሕዝቦች አውነተኛ ነፃነት ከሚታገሉ ግንባር ቀደም ኃይሎች ጎን ከተሰለፈበት ወቅት አንስቶ በምንም አድርባይነትና አወደድባይነት ሳይወናበድ በታሪክ ፊት ኃላፊነቱን ሲወስድ ቆይቷል። ያገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ በመተንተን የትግሉን አቅጣጫ ለማመልከት ሲሞክር አንጂ በኃይለ ቃል ላይ ኃይለ ቃል አየደራረበ ርካሽ ተወዳጅነትን ለመሸመት ሲያሽቃበጥ የታየበት ወቅት የለም። 

አሁንም ቢሆን ፀረዲሞክራቲክ፡ ፀረሕዝብና ፀረአብዮት የሆነውን የደርግ አገዛዝ ከኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ጋር ሆኖ እየተዋጋ፣ በተራማጁም ከፍል ተሰበጣጥረው ውዥንብር የሚነዙት አንዳንድ የንኡስ ከበርቴ ጥራዝ ነጠቅ ቡድኖች በአብዮቱ ላይ የሚያስከትሉትን ክፉ መዘዝ አያየ በእወደድባይነት ብቻ ዝም ቢላቸው በታሪክ ፊት እንደሚጠየቅበት ያምናል። አሁን ካለንበት አደገኛ ሁኔታ ልንወጣ የምንችለው በሃቀኛ ትግል እነዚህን አወናባጆች አጋልጦ እውነተኛ የተራማጆች አንድነት በመመስረት ብቻ መሆኑን እናውቃለን ለዚህም አላማ ለመታገል የግንባር ቀደምነት ግዴታችን ይጠራናል።

ይህ ሃቀኛ የርእዮተዓለም ትግል አንይካሄድ የደርጉ ፀረዲሞክራቲክ አገዛዝ አፍኖታል። በዚህም ጨለማ በመጠቀምና በጠባብ የቡድን ስሜት በመካከል በተራማጆች መሃከል አንድነት አንዲላላ፣ ከሲአይኤ ሰላዮች ብቻ በሚጠበቅ ርኩስና ርካሸ ዘዴ በሃሜት᎓ በቅጥፈትና በጥቆማ ብርታት የኢትዮጵያን ተራማጆች መከፋፈልና ማዳከም ለአብዮታችን አንደማይበጅ መታወቅ አለበት እንላለን። 

የኢትዮጵያ ተራማጆች ከእንግዲህ ለሃቀኛ ትግል ተሰልፈው በሳይንሳዊ ታክቲክ ላይ የተመረኮዘ አቅጣጫ ቀይሰው በአንድነት መታገል አለባቸው። ለዚህም በአደርባይነትና በእወደድባይነት በተወሰዱ አሸብራቂ መፈክሮች ተሸፋፍነው በመሃከላቸው ውዠንብርን፣ ጥርጣሬን፣ አለመግባባትን የሚነዙትን ጥራዝነጠቅ ንኡስ ከበርቴዎችና ኤጀንት ፕርሾካተሮች በአንድ ደምጽ ማጋለጥና ተስፋ ማስቆረጥ ይኖርባቸዋለ። ይህም እንዲሆን በአሁኑ ጊዜ አጫፋሪ መፈክሮችን ትተው የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሰጡት ምርቱ ከአንክርዳዱ፡ ተራማጁ ከአወናባጁ የሚለይበትን የዲሞክራሲን ጥያቄ መሆን አለበት።

ሃቀኛ ተራማጆች አሁን ባለንበት አደገኛ ሰአት በፀረዲሞክራቲኩ የደርግ አገዛዝና በንኡስ ከበርቴ ጥራዝ ነጠቆች ማወናበድ ታፍኖ በነአስፋወሰን አድሃሪ ሴራ በመቀለበስ ላይ ሳለው የኢትዮጵያ አብዮት አዲስ የሕይወት አስትንፋስ የሚሰጠው ዲሞክራሲ ብቻ መሆኑን አይስቱትም። ስለዚህ አጫፋሪ መፈክሮችን ለጊዜው ወደጐን ትተው በዚህ የሞትና የሽረት ጥያቄ ላይ ይረባረባሉ። 

ከእንግዲህ የኢትዮጵያ ወዝአደርና ሰፊ ሕዝብ ከወደቀበት የውዥንብር አዘቅት ውስጥ ሆኖ የቀሰመውን ትምህርት ቀስሟል። ከሁሉ አብልጠው የሚጮሁ ሁሉ ከሁሉ ይበልጥ ተራማጅ መስለው የሚታዩበት ወቅት አክትሟል። ፀረዲሞክራቲኩን የደርግ አገዛዝ ተቋቁሞ፣ ከአወናባጅ ‘ተራማጆች’ ራሱን አጽድቶ ጥቅሙን መብቱንና ክብሩን ዋስትና ባለው ሁኔታ ለሚያረጋገጥበት ከሕዝባዊ ድል ጋር ተያይዞ ለሚመጣው ሕዝባዊ መንግሥት ሲሉ የኢትዮጵያ ተራማጆች በአንድ ኃይል ዲሞክራሲ በሚለው መፈክር ስር መቆም፣ መታገልና መሰዋት አለባቸው።

ለዚህም በአሁኑ ጊዜ ፋሽስታዊው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አንዲነሳ፣ በእስር ቤት ታጉረው በመሰቃየት ላይ ያሉት የኢሰአማ፣ የአስተማሪዎች ማሕበር ወገኖቻችን፣ ዘማቾችና ሌሎች አብዮታውያን ሁሉ ያለአንዳች ጊዜ ማጥፋት አንዲለቀቁ መታገል አለባቸው። 

በጠቅላላው በተራማጆች ሰፈር ያለውን ውዥንብር በሃሜት: በሲሉ ሰማሁ ሳይሆን በሰፊው ሕዝብ ፊት ትምህርት በሚሰጡ ሃቀኛ ውይይቶች ለመፍታት፣ በጠቅላላው ፀረፊውዳልና ፀረኢምፔሪያሊስት የሆኑ ኃይሎች ልዩነቶቻቸውን አውቀውና አቻችለው በአንድ አብዮታዊ ግንባር ለመተሳሰርና ለወታገል አንዲችሉ ለሰፊው ሕዝብ ወገኖች ግልጽ በሆነና በማያሻማ ሁኔታ የመደራጀትንም መብት የሚጠቀልል ፀረዲሞክራሲያዊ መብቶች አንዲታወቁ ያለአንዳች ማወላወል መታገል ያስፈልጋል። 

አሁን በተራማጁ ሰፈር ያለው ውዥንብር ያለዲሞክራሲ ሊጠፋ አይቸልም። ውዥንብሩ ሳይጣራ የምናሳልፋት እያንዳንዷ ደቂቃ ለአድሃሪዎች የቀናት ፋታ አንደምትሰጥ መዘንጋት በኢትዮጵያ ሕዝብ ትግል አንደማላገጥ ይቆጠራል።

ፋሸስታዊው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ይነሳ!
የታሰሩ ተራማጆች በሙሉ ይፈቱ!
ዲሞክራሲ ለሰፊው ሕዝብ ወገናች በሙሉ!
Scroll to Top