የሰፊው ሕዝብ ድምፅ
ቁጥር 43፣ ሐምሌ 1፣ 1968
የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ
መኢሶን በዚህ የሰፊው ሕዝብ ድምፅ እትሙ፣ “በአብዮት ሂደት ውስጥ የመደቦች መለዋወጥና መሸጋሸግ እንደማይቀር” ሌኒንን ጠቅሶ፤ በኢትዮጵያም ውስጥ ሁለት የጠላት ሰፈሮች ተፋጠው ለወሳኝ፡ፍልሚያና ድል እየተዘጋጁ እንደሆነ ያስገነዝባል።ሕዝባዊ አብዮታዊ ትግል እጅግ ረጅምና መራራ እንደመሆኑ፤ ትግሉን ከመነሻው አብረው የጀመሩት ሁሉ አብረው እንደማይቆዩና እየተንጠባጠቡ እንደሚቀሩ ይገልጻል።አንዳንዶቹም አልፈው ተርፈው አቋማቸውን ቀይረው “ኃይለ ሥሳሴ ማረን፤ የደርጉ ነገር ምንም አላማረን” እያሉ ሕዝባዊ አብዮቱን ወደ መታገል እንደዞሩና ትግሉን እንደከዱ ያብራራ።
“ማንኛውም አብዮት፣ በርግጥ አብዮት ከሆነ፣ የመደቦችን መሸጋሸግ ያስከትላል።
ስለሆነም ሰፊውን ሕዝብ ለማንቃትና በአብዮቱ እያሾፈ ሕዝቡን የሚደልሉትን ኃይሎች
ለመታገል ከተፈለገ በአብዮቱ ሂደት ቦታቸውን የለወጡትን መደቦች መርምሮ መጠቀም
ያስፈልጋል።” (ሌኒን፣ ‘ኤ ክላስ ሺፍት’፣ ሙሉ ሥራዎች ቅጽ 25፣ ገጽ 130)
የየካቲት አብዮታዊ እንቅስቃሴ ያስከተለው እንደዚህ ዓይነቱ የመደቦች መሸጋሸግ ዛሬ እየሰከነ የሚሄድበት ወቅት ነው። በዚህም የተነሳ የአብዮቱ ወዳጅና ጠላት በሚገባ እየተለየ፣ በአገራችን የተፋጠጡት ሁለት የጠላት ሰፈሮች ለወሳኙ ፍልሚያ ኃይሎቻቸውን በመሰብሰብ ላይ ናቸው።
እውነተኛ ሕዝባዊ አብዮት ረዥምና መራራ ነው። በዚህም አብዮታዊ ጉዞ መንገዱን አብሮ የጀመረ ሁሉ አብሮ አይጨርስም። ገና ከመንደርደሪያው፣ ወይም ከመሃል . . .ባጭሩ በየቦታው እየተንጠባጠቡ የሚቀሩ ብዙ አሉ። ከነዚህ መንገድ ቀሪዎችም መሃል የተወሰነው ክፍል እጁን አጥፎ ለመቀመጥ ቢችልም አብዛኞቹ አብዮቱን በመክዳት ብቻ አይወሰኑም። ቀድሞ ትንሽም መንገድ አብረዋቸው በነበሩት ላይ፣ በጠቅላላው በአብዮቱ የወደፊት ግስጋሴ ላይ አደጋ ለመጣል ያሴራሉ፣ ይፍጨረጨራሉ። ነገር ግን የታሪክ ጐማ ምንም ቢሆን ወደፊት ተጓዠ ነውና እነዚህ ከሃዲዎች በሚጥሉበት አደጋ አይገታም። እንዲያውም መንገድ ቀሪዎቹ በታሪክ ጉዞ ተጨፍልቀው ትቢያ ሆነው ይታለፋሉ።
በአብዮታዊ እንቅስቃሴ ወቅት ሃቀኛ አብዮታውያን በየጊዜውና በየትግሉ ደረጃ ከአብዮቱ የሚሰናበተውን ክፍል ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ተንትነው በጥንቃቄ መርምረው ከደረሱበት ወዳጅና ጠላትን በሚገባ ለይተው ትግሉን ወደ ፊት ማራመድ ይችላሉ። በቅድመ አብዮት ያደረጉትን፣ የአብዮቱ ማዕከል በታትኖ ከታሪክ ቤተመዘክር ሲጨምረው ልብ ያላሉትን ያረጀ ያፈጀ የመደብ ትንተናቸውን የሙጥኝ ይዘው እኝኝ ካሉ ግን፣ የትላንት የትግል ጓድ ዛሬ ከጠላት ሰፈር ተደባልቆ እነሱኑ ሊያጠፋ የሚያደርገውን ትግል ሊረዱ አይችሉም። ሕያው የሆነና የአብዮቱን የእድገት ደረጃ የተከተለ ትንተና ማድረግ ተስኗቸው ወዳጅ ከጠላት በተደበላለቀበት ትርምስ የተዝረከረከ ትግላቸው ሩቅ ሳይሄድ ወድቆ ይከሰከሳል።
በቅድመ አብዮት ኢትዮጵያችን የኃይለሥላሴን አገዛዝ የሚቃወሙ መዓት ኃይሎች ነበሩ። እስከ ተወሰነ ደረጃም ድረስ ቢሆን የነቁ መሳፍንት (ኢንላይትንድ አሪስቶክራትስ) አቀባባይ ከበርቴዎችና ትናንሽ ባላባቶች፣ ከዚያም ብሄራዊ ከበርቴው፣ ጠቅላላው ንዑስ ከበርቴ፣ ወዛደሩና ገበሬው ተጠቃለው የኃይለሥላሴን አገዛዝ በተለያየ ደረጃ ይቃወሙ ነበር። የካቲት ከፈነዳ ጀምሮ በተገኙት የሕዝብ ድሎች፣ የገጠር መሬት የሕዝብ መሆን፣ የአንዳንድ የማፍሪያና የማከፋፈያ ድርጅቶች መወረስ፣ የከተማ ቦታና ትርፍ ቤቶች የመንግሥት መሆን፣ የብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ኘሮግራም መታወጅ . . . ከላይ ከተጠቀሱት መደቦችና የሕብረተሰብ ክፍሎች አንዳንዶቹን ጠቅልለው ወደ ፀረ አብዮት ሰፈር እንዲነጉዱ አድርጓቸዋል።
“ለውጡን እኮ የተቃወመ የለም፣ እነሱ ግን አበዙት” የሚለው አነጋገር መደቦች ትግሉ ከአንድ ደረጃ ሲደርስ ከአብዮቱ ሲሰናበቱ አምባጓሮ የሚጀምሩበት አነጋገር ነው። በዚህ መልክ ከትላንት የኃይለሥላሴ ተቃዋሚዎች ውስጥ አንዳንዱ ከፀረ አብዮት ሰፈር ተደባለቆ በሕዝብ፣ ተነቅቶበትና ተተፍቶ ከታሪክ ትቢያ መጣያ ተጥሏል። አንዳንዱ ገና አልተነቃበትም። በተለይ አብዮቱን የከዳው የንዑስ ከበርቴ ክንፍ ካለፈችው የተራማጅነት ዘመኑ ባስቀራት ጥሪቱ ተሸፋፍኖ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ማወናበድ ችሎ ነበር። ይህም ክንፍ ቢሆን፣ ሰፊው ሕዝብ ከነቃ ይነቃብኛል የሚል መደባዊ ስጋት ይዞት የሰፊው ሕዝብ ወገኖች ንቃት ሕሊናቸው እንዳይዳብር ብዙ ዓይነት ማወናበድ ቢሞክርም ሳይሳካለት ስለቀረ ከጥቂት ወራት ጀምሮ እየተጋለጠ ነው። ጨርሶ ወደ መተፋትና ከታሪክ ትብያ መጣያ ውስጥ ወደመጣሉ እየተቃረበ ነው።
ይህ ከሃዲ የንዑስ ከበርቴ ክንፍ በኃይለሥላሴ ዘመን የአብዮቱ ወገን ብቻ አልነበረም። በተፈጥሮው አለሁ አለሁ፣ አትርሱኝ ማለት ስለሚያጠቃውና ከምርት መሳሪያዎች ጋር ያለው ግንኙነት የሌለ ስለሆነ ከሁሉ ‘ተወርዋሪ’ ይመስል ነበር። ከወዛደር ዲሲኘሊን ይልቅ ውካታና ድንፋታ ይወዳል። ከየካቲት በፊትም ሆነ ከየካቲት በኋላ ለተወሰነ ጊዜ በታላቅ ድንፋታ የትግሉን ፊታውራሪነት ይዞ ጥቂት የተንጐራደደ መደብ ነው። የአብዮቱ ጅራፍ ጩኸት እስካስደነገጠው ድረስ በአብዮቱ ሰፈር ከሁሉ ጽኑ ታጋይ ባይሆንም ከሁሉ ጯሂ ክፍል ነበር።
ዛሬ፣ ከየካቲት ወዲህ የተወሰዱት አብዮታዊ እርምጃዎች ይህን ክፍል አንዳንዴም ተጠናውተውታል። አንዳንዴ ለጥቂት ስተውታል። ስለሆነም አብዮቱ ከገፋ ‘ነግ በኔ’ እያለ በቁሙ የሚባንንበት ደረጃ አድርሰውታል። ተደራጅቶ ጥቅሙን ለመጠበቅ ስላልቻለ ወደፊት እድሉ ከጥልቢያኩስ ጠቁሮ ስለታየው ከትግሉ ውስጥ መላ ቅጡ ጠፍቶታል። ራሱ ተሸብሮ ሌላውንም ከማሸበር በስተቀር ምንም አይታየውም። ዛሬ የኢትዮጵያ ንዑስ ከበርቴ ቀኝ ክንፍ እንኳን የሕዝብ ድል ነጋሪት ሊጐሰምበት ይቅርና የገዛ ጥላው የሚያስደነግጠው የተሳቀቀ ክፍል ሆኗል። የትላንትናው ‘ጀብድ’ ሁሉ እንዳልነበር ተረስቶ “ኃይለሥላሴ ማረኝ የደርጉስ ነገር ምንም አላማረኝ” እያለ ቅድመ አብዮት ኢትዮጵያን መልሶ መናፈቅ ጀምሯል። መደቡ ድሮም ቢሆን ታታሪነት፣ ቆራጥነትና ትዕግስት የማይወድለት መደብ በመሆኑ ‘ከማያውቅ መለአክ የሚያውቁት ሰይጣን ይሻላል’ በሚል ፈሊጥ ከኢምፔሪያሊዝም፣ ከፊውዳሊዝምና ከአድሃሪው ቢሮክራሲ ጋር እየተመሳጠረ ይህን አጠራጣሪ የሆነበትን የአብዮት ጉዞ ለማደናቀፍ ይፈልጋል። በዚህም ታክቲክ ይቆርጥና የእርቅ እጁን ወደ ትላንት ደመኞቹ ይዘረጋላቸዋል።
ይህ ከሃዲ ክንፍ በዚህ መልክ ሰፈር ሲቀይር፣ ያንኑ አለሁ አለሁ አትርሱኝ የሚለውን ድንፋታውን ይዞ ቢሆንም በአብዮቱ ሰፈር ሆኖ ያያትን አይቷልና ዛሬ የፀረ አብዮት ኃይሎችን ፊታውራሪነት ሲይዝም ጩኸቱና ውካታው ቢጨምር እንጂ ከድሮው አይቀንስም። ከወዛደሩ ጐን ተሰልፎ ድሮ ሲታገል ዲሲኘሊን ያልተማረ፣ መጮህ ሲያሰኘው ዛሬ ከጐኑ ቆመው የሚያራግቡለት መሳፍንትና እነ ሲአይኤ የመንፈስ እርጋታ ይሰጡታል ብሎ መገመት አስቸጋሪ ነው። ስለዚህም ትላንት የተራማጁ ወገን ደንፊ ፊታውራሪ የነበረ ንዑስ ከበርቴ ዛሬ የአድሃሪው ወገን ደንፊ ፊታውራሪ ቢሆን እጅግም አያስገርምም። ይህ ወላዋዩ ንዑስ ከበርቴ የማይለየው ምልክቱ ነውና። ሌኒን እንዳለውም እንዲህ ዓይነቱ ንዑስ ከበርቴ . . “ታታሪነት፣ ድርጅት፣ ዲሲኘሊንና ጽዳት የለውም እንጂ በቀላሉ ከአንዱ ጫፍ ወደሌላው ጫፍ የሚወረወር መደብ ነው።”
ዛሬ በሃገራችን የዚህ ከሃዲ ንዑስ ከበርቴ ክንፍ ፊታውራሪነት የተያዘው ‘ኢህአፖ’ በተባለው ፀረ ወዛደር ድርጅትና ዲሞክራሲያ በተባለው ጋዜጣው ነው። ይህ ቡድን፣ በዛሬው የኢትዮጵያ ሁኔታ፣ ከደርጉ በስተቀኝ የተሰለፉትን ንዑስ ከበርቴዎችና ሌሎች አድሃሪ ኃይሎች የሚወክል የነሱም ሙሉ ድጋፍ ያለው ቡድን ነው። የዛሬ ኪሳራውን እያርገውና ይህ ቡድን እንዳሁኑ ሳይጋለጥ ብዙ ሃቀኛ ተራማጆችንም አወናብዶ ነበር። የኢትዮጵያን አብዮት በሚመለከቱ ዋና ዋና ጥያቄዎች ላይ በሙሉ የወሰዳቸው አቋሞች የመሳፍንቱና የነሲአይኤ ቢሆኑም፣ እነዚህን አቋሞችን በግራ መሳይ የነገር አጣጣሉ፣ በድንፋታውና በጩኸቱ ሸፍኖ ብዙ ወጣቶችን አወናብዶ ነበር። ነገር ግን የዲሞክራሲያ ቡድን የመደብ መሰረት የተወናበዱ ወጣቶች ብቻ አልነበሩም። ከየካቲት ወዲህ አብዮቱን ከቤተሰባቸውና ከአካባቢያቸው ጋር አብረው የከዱ አድሃሪ ወጣቶች በሙሉ፣ ከደርግ በስተቀኝ ያሉ አድሃሪ ኃይሎች በሙሉ ይህ ቡድን ደርጉን ከነሱ እኩልና ሙሉ በሙሉ ስለሚቃወምላቸው በስተጀርባው ተሰልፈው ይገኛሉ።
በነገራችን ላይ ይህ ቡድን እየተጋለጠ ሲሄድ ከፍተኛ ኪሳራ ውስጥ ይወድቃል። ደርጉ አብዮቱን የሚጠቅሙ እርምጃዎች መውሰዱን እየገፋበት ከሄደ፣ ዲሞክራሲያ የያዘውን የሙሉ ተቃውሞ ‘አቋም ይዞ መቆየት ጨርሶ መጋለጥ ይሆንበታል። ተቃውሞ ልቀንስ ካለ ደግሞ አድሃሪ ወጣቶችና ጠቅላላው ከደርጉ በስተቀኝ የሚገኘው የአድሃሪዎች ጥርቃሞ ሌላ የነቃ አድሃሪ፣ሌላ’ “ኰከብ” ይፈልጋል። ‘ቀይ ባንዲራ’ የተባለችው ቡድን ለዚህ የአድሃሪዎች “ተራማጅ ኰከብነት” ራሷን በማዘጋጀት ላይ ነች። የዲሞክራሲያ ቡድን ግን የሚቀረው ምርጫ ወይ ያለውን አቋም ይዞ ጨርሶ መጋለጥ፣ ወይ አቋሙን ቀይሮ የአድሃሪዎች ድጋፍ ማጣት ነው። በዚህ ቡድን ውስጥ ተወናብደው የተሰለፉ ሃቀኛ ተራማጆች ግልጽ የሆነ ምርጫቸውን በማሳየት ላይ ናቸው።
ለማንኛውም፣ ምንም እንኳ በመደብ ጥቅም ላይ ሃፍረት የሚሉ ነገር ባይኖርም፣ የኢትዮጵያ ንዑስ ከበርቴ ቀኝ ክንፍ በዛሬው ፀረ አብዮት አቋሙ አፍሮበታል። ስለሆነም፣ ይህ ከሃዲ ክንፍ ከላይ እንዳልነው ምንም በማያጠራጥር ሁኔታ በኢትዮጵያ አብዮት ላይ ከመሳፍንቱና ከነሲአይኤ ጋር በአንድነት ቢሰለፍም አቋሙን ተራማጅ ኩል እየቀባ ለማቅረብ ይሞክራል።
በኢትዮጵያ ሶሻሊዝም ታወጀ ሲባል እነ አስፋወሰን ኃይለሥላሴ “ኢትዮጵያውያን በቀድሞ ጊዜ ይታወቁላቸው የነበሩት ነፃነቶች ጥራት በሌለው የኢትዮጵያ ሕብረተሰባዊነት በሚል ተደመሰሱ” ብለው መግለጫ አወጡ። የኢህአፖ የውጭ ተጠሪ ሆኖ የሚሰራው ‘ዓለም ዓቀፍ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ፌዴሬሽን’ የተባለው የአድሃሪ ወጣቶች ድርጅት ‘የኢትዮጵያ ሕዝብ ዋና ጠላት የኢትዮጵያ ሕብረተሰባዊነት ነው’ ብሎ አወጀ። እነዲሞክራሲያም “በኢትዮጵያ ፋሺዝም ነገሠ” ብለው የበኩላቸውን አስተጋቡ። እነአስፋወሰን ኃይለሥላሴ ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነቅቶ፣ ተደራጅቶና ታጥቆ ሳይደቁሰን እንቅደመው በማለት “ጊዚያዊ ሕዝባዊ መንግሥት እንምረጥ” ይላሉ። የከሃዲዎች ቡድን ይህን የቀልባሾች ጥያቄ እንደማይሆን አድርጐ በነሌኒን ስም ሊያቀርብላቸው ተፍ ተፍ ይላል። እነአስፋወሰን ተራማጅ ተማሪዎች ከገበሬው ተዋሃዱብን ብለው ዘመቻውን ይቃወማሉ። እነዲሞክራሲያ አሁንም በነሌኒን ስም እየማሉ “ዘመቻውን መበተን፣ መመሪያውን መዝጋት” ያስፈልጋል እያሉ በግልጽ በጋዜጣቸዉ ይጽፋሉ። በገቢርም ዘመቻውን ለመበተን ሞክረው በንቁ ዘማቾች ከፍተኛ ትግል መክሸፋቸው ይታወሳል። እነአስፋወሰን የመሬቱን አዋጅ ይቃወማሉ። በውጭ አገር የኢህአፖ ተጠሪ ነኝ የሚለው ፌዴሬሽን አሁንም የነሌሊንን ስም እየጠቃቀሰ ይህንን አዋጅ የሚቃወመው “አድሃሪ ስለሆነ፣ አድቬንቸሪስት ስለሆነ፣ እንዲያውም (ቀደም በሎ እንደጠቀሰው) የኢትዮጵያ ጭሰኛ መሬት ካገኘ ፋሺስት ይሆናል” በሚል ሰበብ እንደሆነ በየጊዜው የሚያወጣቸው መግለጫዎች ያስረዳሉ።
ኢህአፖና መሳፍንቱ አቋማቸው ቢመሳሰል ‘የአጋጣሚ ነገር ነው’ እንዳይባል፣ በዚሁ ፊዴሬሽን በተባለው ‘አገናኝ ድርጅት’ አማካኝነት የመሳፍንቱ ‘የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ሕብረት’ እንደ አፍሪክ-አዚ አይነቶቹ የሲአይኤ ጋዜጦች፣ በገቢር በመተባበር ላይ ናቸው። ኢህአፖ ይህንን ፌዴሬሽን የተባለ የነአሰፋወሰን ግልግል ድርጅትና የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ከሃዲ ክንፍ ‘አብዮታዊ ንቅናቄ’ እያለ ያወድሰዋል። ይከራከርለታል።
ታዲያ ይህ ሁሉ ሆኖ የነዴሞክራሲያ ቡድን የዛሬን አያርገውና ለብዙ ጊዜ “ተራማጅ” ተብሎ የሚጠረጠርበት ጊዜ ነበር። ለዚህ መቸስ ይህን ቡድን የረዳቸው በአንድ በኩል ይህ ቡድን የሚወክለው የንዑስ ከበርቴ ክንፍ በአብዮቱ ታልፎና ተተፍቶ ከመሄዱ በፊት የነበረችው የተራማጅነት ቅርስ ነች ። በሌላ በኩል ደግሞ ይህ ክንፍ አደባባይ ይዞ በሚወጣው አቋሙም ሆነ አባላቱን እንኳ እየሸሸገ በሚያደርጋቸው አጠራጣሪ ግንኙነቶችና ትብብሮች ከአድሃሪዎች ጋር የተሰለፈ ቢሆንም፣ ይህንን ሁሉ ለተወሰነ ጊዜ በድንፋታ ለመሸፈን መቻሉ ነው። በተጨማሪም፣ ይህ ቡድን በደርጉ ተራማጅ እርምጃዎች ላይ ያለውን ተቃውሞ በደርጉ አድሃሪ እርምጃዎች እያሳበበ በማቅረብ ያካሄደው ቅስቀሳ፣ ደርጉ በሕዝቡ ትግል ውስጥ ስለያዘው ቦታ ግራ በተጋባው ክፍል ውስጥ “የደራ ገበያ” ማግኘቱ ነበር። በደርጉ ጥያቄ ጥራት እየተገኘ ሲሄድም፣ ደርግ ራሱም ከአድሃሪ እርምጃዎች ቀነስ፣ ከተራማጅ እርምጃዎቹ ጨመር እያደረገ ሲሄድ፣ ይህም “የደራ ገበያ” መቀዝቀዙ አልቀረም።
የዲሞክራሲያ ቡድን ይህን ክህደት ሸፍኖ አድሃሪ አቋሞቹንም ሆነ ተጠሪዎቹ በውጭ አገር ከነአስፋወሰን ድርጅት ጋር የሚያደርጉትን ትብብር የሚያስደግፉት “በኢትዮጵያ ውስጥ ያንሰራራው ፋሺስታዊ ሥርዓት ነው” በሚለው ቲዎሪ ላይ ነው። በእርግጥም ይህ ቴዎሪ ልክ ከሆነ፣ ከሃዲው ቡድን እንደሚለውም፣ እነስታሊን ፋሺስቱን ሂትለር ለመቋቋም ከአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ጋር ሳይቀር የህብረት ግንባር ፈጥረዋል። እነሆቺ ሚን የጃፖንን ፋሺዝም ለመቋቋም ከቪየትናም መሳፍንትና ከፈረንሳይ ቅኝ ገዥዎች ጋር የሕብረት ግንባር ፈጥረዋል። ስለዚህ የዚህ ከሃዲ ቡድን ‘ቲዎሪ’ የሚያመራውም ዛሬ “የደርጉን ፋሺዝም” ለመዋጋት ከኢትዮጵያ መሳፍንትና ከነሲአይኤ ጋር በህብረት መታገል ይቻላል፣ ያስፈልጋልም ለማለት ነው። በርግጥም ይህ አደገኛ ‘ቲዎሪ’ በነማርክስና በነሌኒን ስም የኢትዮጵያን ተራማጆች በመሳፍቱና በኢምፔሪያሊስቶች ጐን ለማሰለፍ ከሃዲ ምሁራን የጠነሰሱት ሴራ ነው።
የከሃዲ ምሁራኖቹ ቡድን ጠቅላላ ታክቲኩን የቀየሰው በዚህ “ደርግ ፋሺስት ነው” በሚል ተልካሻ ቲዎሪ ላይ ቢሆንም እስከዛሬ ድረስ ይህንን ቲዎሪውን ሳይንሳዊ በሆነ ትንተና ማስረዳት አልቻሉም። አንድ ጊዜ፣ በአንድ ጽሁፉ ላይ፣ “የደርግን ፋሺስታዊ ሥርዓት” ለማጋለጥ ሞክሮ ‘ፋሺዝም ጥንትም ያው አሁንም ያው ትግልም እንዲሁ’ በሚል ርእስ አቅርቦ እንደነበር ይታወሳል። በዚህ አስቂኝ ቁጥር ላይ “የደርግን ፋሺስትነት” ለማስረዳት ሞክሮ እንዳልተሳካለት እንኳን እኛና የከሃዲ ምሁራኖች ቡድን እራሱ ተገንዝቦት ነበር። ስለሆነም “የደርግን ፋሺስትነት” ለማስረዳት ‘ወደፊት በሰፊው እንመለስበታለን’ ብሎ ቃል ቢገባም “ዋናው” ጽሁፉ ሲጠበቅ መንፈቅ ሊሆነን ነው። በዚሁ አንፃር በዚሁ ተለካሻ ቲዎሪ ላይ የተመረኰዘው የከሃዲ ምሁራንና የመሳፍንቱ ትብብር ሥር እየሰደደ ስላየነው “ለመቆያ ያህል” በሰጡን ጽሁፋቸው ላይ ተመርኩዘን እኛን ከመሳፍንቱ ጐን የሚያሰልፈን ቲዎሪ ገና እንዳላቀረቡልን እናስረዳለን።
በዚህ ቁጥራቸው ላይ ገና ሲጀምሩ እንዲህ ይላሉ፡-
“ስለጊዚያዊ ወታደራዊ መንግሥት በተለይም በስልጣን መሰላል የመጨረሻው ርካብ ላይ ስለ ተቀመጡት ‘ምርጥ’ መኮንኖች በምናወራበት ጊዜ ‘ፋሺስታዊነት’ የሚለውን ቃል አዘውትረን እንጠቀማለን። ይህንን ቃል የምንጠቀመው ጭካኔንና እብሪትን በሚያመለክተው ጠባብ ትርጉም ብቻ አይደለም። ውስጣዊና ይዞታዊ ፅንሰ ሃሳቦችንም አብረን በማገናዘብ ነው። ከነዚህ ይዘቶች ለዓይነት ጥቂቶችን እንጠቅሳለን።”
ከዚህ ጥቅስ መጠርጠር እንደሚቻለው፣ “ጭካኔና እብሪት” የፋሺዝምን ላይ ላዩን የሚታይ መልክ ሲጠቁም፣ “ውስጣዊ ይዘታዊ” የሚለው አነጋገር ደግሞ የፋሺዝምን የኤኰኖሚ መሰረት ለመጠቆም የቀረበ አነጋገር ይመስለናል። ይህንን የምንለው መቸስ “ማርክሲስት” ነን ብለውናልና የፋሺዝምን ሥርዓት ኤኰኖሚያዊ መሰረት በሚገባ አሳይተውን ከዚያ ወደልባሱ (ወይም ወደ ሱፐር ስትራክቸሩ) ይሄዳሉ ከሚል ተስፋ ተነስተን ነው።
በመሰረቱ ‘ትንተናው’ መጀመር ያለበት “የኢትዮጵያ ፋሺስት ሥርዓት” የቆመበትን የኤኰኖሚ መሠረት በሚገባ በማብራራት ነበር። ከሃዲዎቹ ምሁራን ትንተናቸውን ‘በእብሪትና በጭካኔ’ ሲጀምሩ አንባቢ ትንሽ መጠርጠር ይጀምራል። ካሁን ካሁን ደረስኩበት እያለ የሚያስበው “የኢትዮጵያ ፋሽዝም የኤኰኖሚ መሰረት” ትንተና እያደር የውሃ ሽታ እየሆነበት ሲሄድ የከሃዲዎቹም ዓላማ የዚያኑ ያህል ግልጽ እየሆነለት ይሄዳል። ቀስ ብሎም ይቆርጥለታል። ይህ ጽሁፍ ከያዘው 8 ገጽ ቡትቶ ውስጥ አንባቢው እስከ ገጽ 5 ድረስ ስለፋሺዝም ‘ጭካኔና እብሪት’ ከተንቦለቦለለት በኋላ፣ በድንፋታ ብርታት ያደናገሩት የመሰላቸውን አንባቢ በተልካሻ ሰበቦች ተሰናብተውት፣ ሳይንሳዊ ትንተና ሸሽተው ወደሌላ ‘ጉዳይ’ ያልፋሉ። ስለሆነም የዲሞክራሲያ ቡድን ‘ፋሺዝም በኢትዮጵያ’ ከነአስፋወሰን ‘ፋሺዝም በኢትዮጵያ’ የሚለይበት ቅንጣት ነገር የለውም። ሁለቱም ፋሺዝም በኢትዮጵያ ሲሉ ያው በኢትዮጵያ አብዮት ጠላቶች ላይ የወረደውን ‘ጭካኔና እብሪት’ ለማመልከት ነው። ችግሩ ታድያ “የታሪክ አዋላጅ አመጽ ነው” ብሎ ‘ጭካኔና እብሪትን’ በደፈናው ሳይሆን ‘የየትኛው መደብ ጭካኔና እብሪት በየትኛው መደብ ላይ’ ብሎ ሳይጠይቅ አንድ ከመደብ አንፃር የሚመለከት ተራማጅ የአንድን ሥርዓት መልክ አይወስንም። ይቺን ይቺን ለፋሺስቶቹ የአስፋወሰን ክሊክ ይተዋል።
ማንኛውም እንቅስቃሴ መሰረታዊ የሆኑ የኤኰኖሚ ይዘቶች አሉት። ይኸ መቸስ የማርክሲዝም ሀሁ ነው። የፋሺዝም ሥርዓትም የተወሰኑ የኤኰኖሚ መሰረቶች አሉት። ዛሬ በኢትዮጵያ የሚካሄደውን አብዮታዊ እንቅስቃሴ ሕያው የሚያደርጉት የኤኰኖሚ መሰረቶችና የፋሺዝም የኤኮኖሚ መሠረቶች አንድ ናቸው ወይ? የዲሞክራሲያ ቡድን እደሚወተውተን ለነገሩ ያህል ከመሳፍንቱና ከኢምፔሪያሊስቶች ጋር ተሰልፈን ደርጉን ለመዋጋት ብንፈልግ እንኳ ይህንን መሰረታዊ አንድነት ሊያሳየን ቢችል ነበር።
ግን ይህን ሊያደርጉ አይችሉም። ፋሺዝም በመጀመሪያ አንሰራርቶ የታየባቸው አገሮች ጀርመን፣ ጣሊያን፣ ጃፖን. . . የዚህ ሥርዓት መሰረት ሞኖፖል ደረጃ የደረሰ ካፒታሊዝም ሲሆን፣ ደጋፊ ኃይሎቹ ታላላቅ ባለኢንዱስትሪዎች፣ ባለባንኮች፣ ነጋዴዎችና የመሳሰሉት ናቸው። እንዲህ ዓይነቱ ሥርዓት እንዲመሰረት የካፒታሊስቱ ሥርዓት ከፍተኛ የኢኰኖሚ ክራይስስ ውስጥ ወድቆ ኃይለኛ የወዛደር እንቅስቃሴ ወጥሮ ይዞት በዚህ የወዛደር ግፊት የተደናገጠው ታላላቁ ከበርቴ ኑሮው እያሽቆለቆለ በመውረድ ላይ ሆኖ የተበሳጨ የንዑስ ከበርቴ ድጋፍ ያስፈልጋል።
እርግጥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሶስተኛ ዓለም አገሮች በኢምፔሪያሊዝም፣ በፊውዳሊስቶችና በቢሮ ከበርቴዎች ትብብር የሚቆሙ፣ በፋሺስታዊ አመጽ የሚገዙ መንግስታት በአንዳንድ ሕዝቦች ላይ ተጭነዋል። ለነዚህ ምሳሌ ቺሊን፣ ኢራንን፣ ብራዚልን፣ ኢንዶኔዚያን . . . መጥቀስ ይቻላል። እነዚህ አገዛዞች የተወለዱበትን አካባቢ ብንመለከት አቀባባይ ከበርቴዎች፣ ቢሮክራት ካፒታሊስቶች፣ ከአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ጋር በመመሳጠርና ከሌሎች አድሃሪ ኃይሎች ጋር በመተባበር በነዚህ አገሮች ይካሄዱ የነበሩትን ተራማጅ እንቅስቃሴዎች በመቀልበስ በጭቁን ሕዝቦች ትከሻ ላይ የተጫኑ ናቸው።
የነዚህ ፋሺስታዊ አገዛዞች ኢኰኖሚያዊ መልኰች መሬትን ላራሹ ማድረግ ሳይሆን፣ እንዲያውም የቀደማቸውን ተራማጅ የመሬት ስሪቶች በመቀልበስ አርሶአደሩን እየነቀሉ መድረሻ ማሳጣት፣ የኢምፔሪያሊስቶችን በሃገሪቱ ኤኰኖሚ ፈላጭ ቆራጭነት ማጠንከር፣ የተወረሱ ፋብሪካዎችን ለቀድሞ ከበርቴዎች መልሶ ማስረከብ ወዘተ. የመሳሰሉ ናቸው።
የዛሬው የኢትዮጵያ አብዮት ኢኰኖሚያዊ ይዘት ግን ከነዚህ ፈጽሞ የተለየ ነው። የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ በአዲሱ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ጐዳና ላይ የማይናቁ ድሎችን ተጐናጽፎ ለነሱ ዋስትና ለመስጠትና ሌሎች ድሎችን ለማግኘት በትግል አፍላ ላይ ነው። የእንቅስቃሴው ይዘት መሬትን ላራሹ ያደረገውን አዋጅና ሌሎች ተራማጅ እርምጃዎችን ዋስትና ባለው ሁኔታ ከሥራ ላይ ለማዋል ነው።
የዲሞክራሲያ ቡድን መሪዎች ‘የፋሺዝም ሥርዓት በኢትዮጵያ ነገሷል’ ሲሉ፣ ይህ ዛሬ የተያዘው እንቅስቃሴ በኤኰኖሚ መሰረቱ በምን ፈሊጥ ከፋሺዝም ጋር እንደሚገናኝ ግልጽ አድርገው ማሳየት ነበረባቸው። ግን ይህን ማድረግ አይችሉምና ደፍረው አልገፉበትም። አልገፉበትም እንጂ ሰው ለማወናበድ ግን መሬት ላራሹ የሚባለው ፋሺዝምን ያመጣል ለማለት ቃጥቷቸው ነበር። በዚህ በኩል ግን ነገሩን ግልጥልጥ አድርጐ የተጋለጠው የኢህአፖ የውጭ ተጠሪ የሆነው የፌዴሬሽን ቡድን ሲሆን ይህ ድርጅት በቀጥታ የየካቲት 25/67 አዋጅ እንደወጣ መሪዎቹ ባሳለፉት ውሳኔ ይህ አዋጅ ከሥራ ላይ ከዋለ በኢትዮጵያ የፋሺዝም ሥርዓት ይነግሳል ብሎ ነበር። የዴሞክራሲያ ቡድን ይህን አቋም በአግብኦ ገረፍ አድርጐ ሲያልፍ እዚሁ ቁጥር 26 ላይ፣ ፋሺዝም፡-
“መሬት ላራሹን፣ ማምረቻዎችን መውረስ . . . የሚባሉትን መፈክሮች በወጣትነት ዘመኑ በየሃገሩ አምኖበታል፣ ያወጀባቸውም ቦታዎች አልታጡም።”
ብሏል። ባጭሩ፣ መሬት በደሃ ገበሬዎች እጅ ማስገባትን የመሰለ የአዲሱ ዲሞክራሲያዊ አብዮት እምብርት የሆነ የፖለቲካ ድርጊት ፋሺዝም ነው ሲሉን ነው። ከዚህ አባባልም ፊት ለፊት ያልተነገረን መደምደሚያ ግልጽ ነው። አርሶአደሩ መሬት አግኝቶ ፋሺስት ከሚሆን፣ ወይም ፋሺዝም በኢትዮጵያ ከሚነግስ፣ መሬቱ ለነአሰፋወሰን ይመለስና አርሶአደሩ ‘ተራማጅ’ ጭሰኛ ይሁን ነው።
ለነገሩ ያህል ግን፣ ታሪክን እንዲህ በቁሙ ካስኬዱት አይቀር እስቲ መሬትን አራሹ አርሶአደር እጅ ያስገባ ፋሺስት መንግሥት ለሞት መድሃኒት ይጥሩልን። እኛ በፋሺዝምና በመሬት ላራሹ መካከል ግንኙነት ቢታየን፣ በቪየትናምና በመጠኑም ቢሆን በቺሊ፣ በኢንዶኔዚያ፣ በብራዚል. የተቋቋሙት ፋሺስታዊ ሥርዓቶች መሬትን አራሹ እጅ ሲያስገቡ ሳይሆን መሬትን እየነጠቁ የተቋቋሙት ፋሺስታዊ ሥርዓቶች መሬትን እየነጠቁ . . . ለከበርቴዎች ሲያስረክቡና ይህንን የሚቃወም ገበሬ ሁሉ ‘ኮሙኒስት’ እያሉ ሲጨፈጭፉ ነው። እንግዲህ፣ ዛሬ በኢትዮጵያ በአብዮታዊው የመሬት አዋጅ በመመርኩዝና እርሱንም ከሥራ ላይ ለማዋል በሚሊዩን የሚቆጠሩ አርሶአደሮች በ21ሺህ የገበሬ ማህበራት ውስጥ ተደራጅተው በመታገል ላይ ናቸው። ከዚህ በኋላ አገራችን ፋሺስታዊ አገዛዝ ቢወድቅባት፣ የኢትዮጵያ ጭቁኖችና ተራማጆች በከሃዲዎቹ ምሁራን ተወናብደው ዋና ጠላት ደርጉ ነው በሚል ፈሊጥ ከመሳፈንቱና ከነሲአይኤ ጐን ተሰልፈው የነዚህን ፀረ ሕዝብ ኃይሎች ሥልጣን ላይ መመለስ ያገዙ እንደሆነ ብቻ ነው። ይህንንም የምንለው የዲሞክራሲያን ቡድን ለማጓጓት ያህል እንጂ ዲሞክራሲያ ሰፊውን ሕዝብና ተራማጆችን ከቀልባሾቹ ጎን ለማሰለፍ ያደረገው ተከታታይ ሙከራ እንደከሸፈ ለሁሉም ግልጽ ነው።
ፀረ ሕዝብ ኃይሎች አብዮታችንን ቀልብሰው ሕዝቡን ቀድመው ደርጉን ከተኩ፣ ያን ጊዜ እውነትም አዋጁን ለመቀልበስ፣ የኢትዮጵያ ጭቁን ሕዝቦች እስካሁን የተጐናፀፏቸውን ድሎች ከመዳፋቸው ፈልቅቆ ለመንጠቅና ወደጨለማው ሥርዓት መልሶ ለመጨመር፣ በመንቃት ግስጋሴ ላይ ያለውን ሰፊ ሕዝብ ለማፈን፣ የገበሬ ማህበራትን ለመበተን፣ ባለርስቱን መልሶ ለመትከል፣ ባለፋብሪካውን መልሶ ለማንገስ፣ ለአከራዩ የቤቱን ቁልፍ ለማስረከብ. . . የሚፈልግ መንግሥት ታጋዩን ሕዝብ ምንም ዓይነት ምህረትና ርኀራሄ በሌለው አመጽና ሽብር ብቻ አንበርክኰ ለመግዛት የሚሞክር፣ ከሃዲ ንዑስ ከበርቴዎች በፊታውራሪነት የሚሳተፉበት ፋሺስታዊ አገዛዝ ሊመሰረት ይችላል። ይህ በቪየትናም፣ በኢንዶኔዚያ አሁን ደግሞ በቺሊ የታየ ትምህርት እንጂ በጥቂት ምሁራን አንጐል የተፈጠረ፣ ‘ጉርዴ ሁንዴሳ’ የተባለ አድሃሪ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ እንዳለው ‘ማስበርገጊያ ቃል’ አይደለም። ተራማጆችን የሚያሳስብ ፋሺስታዊ ሥርዓት የሚያንሰራራው ያሁኑ አብዮታዊ ትግል ሲቀለበስና የዛሬ ‘ፀረ ፋሺስቶች’ ሥልጣን ሲጨብጡ ነው።
ባጭሩ፣ የዛሬው የኢትዮጵያ አብዮታዊ ትግል ተራማጅ የሆነ ኢኰኖሚያዊ መሰረት አለው። በነዚህ አዋጆች መሰረትነት እርግጥ በመሳፍንቱና በነሲአይኤ ላይ ‘ጨካኝና እብሪተኛ’ ሥርዓት ይመሰርታል። ነገር ግን ከዚህ የእንቅስቃሴው ተራማጅ የኤኰኖሚ ይዘት ተነስቶ በኢትዮጵያ ‘ፋሺዝም ነገሰ’ በማለት እነአስፋው ወሰንን ከመሰሉ ፋሺስቶች ጋር ተዳብሎ እነዚህን ተራማጅ ኢኰኖሚያዊ እርምጃዎች ለመቀልበስ ለመመቻቸት ነው። የዲሞክራሲያ ከሃዲዎች የአብዮታችንን ተራማጅ የኢኰኖሚ ይዘት ‘የፋሺዝም የኢኰኖሚ ይዘት ነው’ ለማለት ዳር ዳር አሉ እንጂ ደፍረው በግልጽ አላስቀመጡትም። ስለዚህ የመጀመሪያው ጥቅስ ውስጥ እንዳሳየነውም፣ ቅድም ‘ፋሺዝምን ጭካኔና እብሪትን’ በሚያመለክተው መልኩ ብቻ ሳይሆን ‘ውስጣዊ ይዘታዊ’ ትርጉሙን እናሳያለን ብለው ቢፎክሩም፣ ስንት ገጽ ሙሉ በሆነ ባልሆነው ድንፋታ አንባቢን ካደናገሩ በኋላ፣ ከሳይንሳዊ ትንተና እንደዋዛ ሊሰናበቱ ሲሞክሩ እንደዚህ እያሉ ያሾፋሉ።
“. . . ፋሺዝምን ሲያዩ መለየቱ ብቻ አይበቃም። ውስጣዊ ይዘታዊ መንስኤዎቹንም ማወቁ ማፍረሻውን ለማግኘት አስፈላጊ ነው። እዚህ ላይ ፋሺዝም መሰረቱ ምንድን ነው? የመደብ ይዘቱ ምንድን ነው? ፋሺዝም ሊመጣ የሚችለው ምን ዓይነት ኤኰኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ሶሺያል ሁኔታዎች ሲፈጠሩ ነው? በሃገራችን ላይ ይህ ዓይነቱ አረመኔያዊ ሥርዓት እንደምን ሊወድቅባት ቻለ? የሚሉና እነዚህን የመሳሰሉ ጥያቄዎች መቅረባቸው አይቀርም። መመለስ ይገባቸዋል። በቦታ ጥበት ምክንያት አሁን ባንወያይባቸውም ወደፊት በየተራ ማቅረባችን አይቀርም።”
እኛ ‘ሳናውቀው እንዴት አረመኔያዊ ሥርዓት ባገራችን ላይ ሊወድቅባት ቻለ በሚል የፈጠራ ጥያቄ ጭንቅላታችንን አንፈለጥም። የሚገርመን ግን የኢትዮጵያ ተራማጆች ምን ያህል ዳተኛ ብንሆን ነው እንደ ዲሞክራሲያ ያለው የከሃዲ አድሃሪያን ቡድን በአድሃሪነቱ ሳይጋለጥ፣ በኢትዮጵያ ሕዝቦች ትግል ሳይተፉ ብዙ ጊዜ ሊቆይ ቻለ የሚለው ጥያቄ ነው። እንዲያው ለነገሩ ግን የዚህን የከሃዲ ምሁራን ‘የተንዛዛ ችሎታ’ የማያውቅ ታዛቢ ዛሬ ‘ቦታ ጠበበን’ ሲሉ ለነሱው እንደሚያፍር ይሰማናል። እኛ ግን፣ ማርክሲስት ነኝ እያለ ከአንድ ዓመት ተኩል በላይ ሲያወናብድ የቆየ አድሃሪ ላወጣኸው ታክቲክ በሳይንሳዊ ትንተና ላይ የተመረኰዘ መደገፊያ አምጣ ሲባል ‘ቦታ ጠበበኝ’፣ ‘ወደፊት በየተራ’ እያለ ማቄን ጨርቄን ሲል እንዲህ ዓይነቱን እግሬ አውጭኝ እያደነቅን ከት ብለን ከመሳቅ ሌላ ምርጫ የለንም። እርግጥ ማርክሲስትም ሆኖ ሰው ቦታ ሊጠበው ይችላል። ግን በርግጥ ማርክሲስት ከሆነ የላይ የላዩን ‘ትንተና’ ፣በደርጉ ‘ጭካኔና እብሪት’ ላይ ብቻ ማተኰሩን ለነአስፋ ወሰን/ መንገሻ ሥዩም ትቶ እሱ ለሳይንሳዊ ትንተና ቦታ መስጠት ነበረበት።
ነገር ግን፣ በአብዮቱ ዋና ዋና ጥያቄዎች ላይ በሙሉ ከመሳፍንቱና ከአሜሪካን ኢምፔሪያሊስቶች ጋር የቆሙት ፣ የውጭ ክንፋቸው ነኝ የሚለው ንቅናቄ የመሬቱን አዋጅ ይቀልበስ ብሎ ሽንጡን ገትሮ ሲታገል ‘ተው’ ያላሉ ከሃዲ ምሁራን በትንተና ስልታቸው ብቻ ተንጠልጥለው ማርክሳዊ የሚሆኑበት ምንም ተአምር የላቸውም። ስለሆነም የደርጉን ፋሺስትነት እናስረዳለን ሲሉ ልክ አድሃሪዎቹ እያነሱ የሚጥሏቸውን ነጥቦች ከማስተጋባትና አመጽን በደፈናው፣ ኘሮፖጋንዳን በደፈናው፣ የዲሞክራሲን መጥፋት በደፈናው፣ የሀገር ፍቅርን ስሜት በደፈናው ከማውገዝ አልፈው ስለነዚህ ጉዳዩች ሳይንሳዊ ትንተና አያቅርቡም። ኪሳራ ማለት ይኸ ነው።
ለምሳሌ፣ የዲሞክራሲያ አድሃሪዎች ቡድን ደርጉን ፋሺስት ነው ብሎ ሲወነጅል የሚጠቅሰው አንድ ምክንያት ‘በመሰረቱ ፋሺዝም ፀረ ዲሞክራሲነት ነው’ የሚል ነው። የዓለም ፀረ ኰሙኒስቶች ሁሉ፣ ከሲአይኤ አንስቶ እስከ ጳጰሱ፣ ፊውዳሉ፣ አድሃሪው ምሁር፣ ከበርቴው ለዘብተኛው ተራማጅ፣ ከሃዲው ‘ሶሺያሊስት’ ድረስ ተረብርቦ ኰሙኒዝም ላይ ሲነሳ፣ ‘በመሰረቱ ኩሙኒዝም ፀረ ዲሞክራሲነት ነው’ እያለ ነው።
ስለዲሞክራሲያዊነትና ስለፀረ ዲሞክራሲያዊነት በደፈናው ማውራት የወዛደር ፖርቲ ልዩ ምልክት አይደለም። የርሱ ልዩ ምልክት ዲሞክራሲና ፀረ ዲሞክራሲን ባለ ቁጥር ጥያቄውን ከመደብ አንፃር መመልከቱ ነው። በአገራችንም፣ ደርጉ ሥልጣን ላይ ከወጣ ወዲህ የኢትዮጵያ አብዮት ጠላቶች የኢኮኖሚ ብዝበዛ መሰረታቸውን ተነጥቀዋል። የፖለቲካ መብታቸውን ተገፈዋል። ፀረ ዲሞክራሲ ሰፍኖባቸዋል። በሌላ በኩልም ለትግሉ እድገት የሚያስፈልገው መጠን ለሰፊው ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ መብቶች አልተከበሩለትም። በዚህን ሁኔታ፣ ሃቀኛ ተራማጆች ደርጉ በሕዝብ ጠላቶች ላይ የዘረጋውን ፀረ ዲሞክራሲያዊነት እንዲገፉበትና እንዲያጠብቀው፣ የነጠቀውን የሰፊው ሕዝብ መብት ደግሞ እንዲለቅ ይታገላሉ። በደፈናው የደርጉን ፀረ ዲሞክራሲያዊነት ማውገዝ በዚህ ፀረ ዲሞክራሲያዊነቱ ይበልጥ ከተጫናቸው የሕዝብ ጠላቶች ጐን መሰለፍ ነው። የጭቁኖችን አምባገነንነት በቅድሚያ ለመቃወም መሰናዳት ነው።
ከሃዲዎቹ ፀረ ሳይንስ ትንተናቸውን ሲቀጥሉ የፋሺዝም ሌላው መልኩ “ኃይልን እንደ ዓይነተኛ መሳርያ አድርጐ መጠቀም ነው” የሚል ፀረ አመጽ ፀረ ሳይንስ የሆነ ሃሳብ ይሰነዝራሉ። ይህም ቢሆን ሲያንስ ጨርሶ ትርጉም የሌለው የቃላት ቅጥጥል፣ ሲበዛ ደግሞ (ያውም በዛሬይቱ ኢትዮጵያ፣ ያውም ጭቁኖች ከዳር እስከዳር አስታጥቁን እያሉ በሚጮሁበት አብዮታዊ ወቅት) ጭልጥ ያለ ፀረ አብዮትና የክህደት ኘሮፖጋንዳ ነው። እናንተ ከሃዳዎች ሌኒን ‘መንግሥት ማለት የተደራጀ ዓመጽ (ኦርጋናይዝድ ቫዩለንስ) ነው’ ያለውን የት ጣላችሁት? በአሁኑ ጊዜ ኃይልን ማውገዝ አብዮቱን ማውገዝ እንደሆነ እንዴት አጣችሁት በመሰረቱ ማንኛው መንግሥት ነው፣ የትኛው ሥርዓት ነው፣ መደብ የሚባል ነገር፣ መንግሥት የሚባል ‘የተደራጀ የጭቆና መሳሪያ’ ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ ‘ኃይልን እንደ ዓይነተኛ መሳሪያ’ አድርጐ የማይጠቀም። እንደማንኛውም መንግሥት ደርግም በኃይል ይጠቀማል። ይህም በተለያዩ ጊዚያቶች የተለያዩ መልኰች ወስዷል። አንዳንድ የደርግ አድሃሪ አባሎች በየክፍላአገራቱ ሲዞሩ በተነጥላ በሰፊው ሕዝብ ወገኖች ላይ የኃይል እርምጃ አስወስደዋል። በመንግሥት ደረጃም ተራማጆች የተገደሉበት፣ የታሰሩበት ጊዜ አለ። በሌላ በኩል ደግሞ በፀረ ሕዝብ ኃይሎች ላይ ከፍተኛ የኃይል እርምጃዎች ተወስደዋል። ከስልሳ ያህሉ የኃይለሥላሴ ቀኝ እጆች አንስቶ በየጫካው ሸፍተው አብዮቱን ለመቀልበስ እስከተነሳሱት ባላባቶች ድረስ በደርግ ጡንቻ የተደቆሱ ብዙ ናቸው። እስር ቤት “የሚማቅቁት” የሕዝብ ጠላቶችም አያሌ ናቸው። አብዮታውያን ታዲያ የደርግን ኃይል መጠቀም በደፈናው አይቃወሙም። ይህንን ለአናርኪስቶችና ለከሃዲዎች ትተው መንግሥቱ በሰፊው ሕዝብ ወገኖች ላይ ክንዱን እንዳያነሳ፣ በፀረ ሕዝብ ኃይሎች ላይ ግን እንዲያውም በይበልጥ ኃይል እንዲጠቀም ይታገላሉ። ለዚህም መንግሥት ብቻ ሳይሆን ሰፊውም ሕዝብ በዚህ በፀረ ሕዝብ ኃይሎች ላይ በሚደረገው አመጽ መሰረታዊውን ቦታ እንዲይዝ ‘ሰፊው ሕዝብ ይታጠቅ’ ይላሉ። አያችሁ እናንተ ከሃዲዎች፣ ደርጉ በኃይል መጠቀሙን በደፈናው እስከተቃወማችሁ ድረስ፣ በውጭ አገር ያለው ተጠሪያችሁ ‘የፖለቲካ እስረኞች በሙሉ ይፈቱ’ የሚል አቋም እስካስተጋባላችሁ ድረስ በዛሬይቱ ኢትዮጵያ እነ ሲአይኤ እነ አስፋወሰን ሁሉ አብረዋችሁ ይሰለፋሉ። አንደኛ ግን በሰፊው ህዝብ ወገኖች ላይ የሚደረገውን አመጽ ብቻ ብትቃወሙና ተራማጅ የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ ብትሉ ኖሮ አሁን የሚያደርጉላችሁን ማንከባከብና ድጋፍ ትተው ዓይናችሁን ላፈር ይሏችሁ ነበር።
የዲሞክራሲያ ከሃዲዎች ሌላ የፋሽዝም ‘ጨካኝና እብሪተኛ’ መልክ ብለው የሚያቀርቡት “የፋሽዝም አገዛዝ የመሣሪያ ኃይል እንደበትረመንግሥት በቀኝ እጁ ጨብጦ በግራ እጁ የሚጨብጠው ፕሮፖጋንዳ ነው” የሚል ነው። እዚህም ላይ በደፈናው የቀረበው የከሃዲዎቹ አቋም ከነሲአይኤ ፀረኮሙኒስት ኘሮፖጋንዳ ጋር እንደሁለት ጠብታ ውሃ ይመሳሰላል። በመሠረቱ ማንኛውም ሥርዓት በፕሮፖጋንዳ ይጠቀማል። ነገር ግን ከማርክሲስቶች በስተቀር ሌሎች ኃይሎች በሙሉ በኃይልና በፕሮፖጋንዳ መጠቀማቸውን ዘልዓለም እንደካዱ ናቸው። ስለሆነም ፕሮፖጋንዳ ያረገ ሁሉ ፋሺስት ነው ማለት የአብዮታዊ ፕሮፓጋንዳን ተቃውሞ ፀረአብዮት ፕሮፓጋንዳ መንፋት ነው። እንዲያውም፣ ከኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ይህንን የዴሞክራሲያ አድሃሪዎች ተቃውሞ ብንመረምር አድሃሪነቱ የበለጠ ግልጽ ይሆናል። የደርጉ ፕሮፓጋንዳ በየጊዜው የተለያዩ ይዘቶች እንደ ነበርዋቸው ግልጽ ነው። ከነዚህም ይዘቶች አንዳንዶቹ አድሃሪ ነበሩ። በጠቅላላው ሲታይ ግን በዘመነ ኃይለሥላሴ ይነዛ ከነበረው አደንቋሪ ፕሮፓጋንዳ ጋር ሲወዳደር ተራማጅና ፀረ ፊውዳል ይዘቶች ነበሩት። በዚሁ የደርግ ፀረ ፊውዳል ፕሮፓጋንዳ የተሸበሩ ጳጳሳትና መሳፍንት እንደሚያደርጉት፣ የኢትዮጵያ ሃቀኛ ተራማጆች የደርጉን ፕሮፖጋንዳ በንቀትና በማጥላላት ሊመለከቱት አይችሉም። ተራማጁ ይዘቶቹን መደገፍና ማጉላት፣ አድሃሪ ይዘቶቹን መተቸትና ትክክለኛውን አስተሳሰብ ማሳየት ግዴታቸው ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የደርጉ ፕሮፓጋንዳ አድሃሪ ይዘቶች እየጠፉ፣ብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮትን የተንተራሱ ይዘቶች እየጨመሩ በመሄድ ላይ ናቸው። በአጠቃላይ ፀረ ፕሮፓጋንዳ አቋም ከመውሰድ አልፎ ዛሬ የደርግን ፕሮፓጋንዳ በደፈናው መቃወም፣ የኢትዮጵያን ሰፊ ሕዝብ ንቃት ሕሊና መጐልመስ መቃወም፣ ስለዚህም በፊውዳሊዝም ርእዩተ ዓለም ላይ የተከፈተው ጦርነት እንዲቆም መታገል ነው።
የዲሞክራሲያ አዘጋጆች የፋሺዝም ልዩ ጠባይ ብለው ካቀረቧቸውና በፀረ አብዮት ፕሮፓጋንዳ ላይ እንደተሰማሩ ከሚያስነቃባቸው ሌላኛው ነጥብ፣ ‘አክራሪ ብሄራዊ ስሜትን እንቃወማለን’ የሚለው ነው። ይህን ሲሉ የደርጉን ‘አክራሪ ብሄራዊ ስሜት’ አብዮታዊ በሆነ የሃገር ፍቅር ስሜት ለመተካት ሳይሆን ለያዙት ንግድ እንዲያመች ብቻ የተወሰደ አቋም እንደሆነ ዝቅ ብለን እናሳያለን። የካሃዲዎቹ የሃገር ፍቅር ከነአስፋወሰን የሃገር ፍቅር የተመሳሰለ ነው። የሁለቱም ፍልስፍና ‘ከሞተች ሚስቴ ምን አለኝ ካማቴ’ የሚል ስለሆነ፣ የመደብ ጥቅማቸው ስለተነካ ‘ምን አለን አገር’ ብለው ያከትማሉ። ከዚያ ወዲያ፣ ቅንጣትም ትሁን የሃገር ፍቅር ስሜት፣ ‘እናት አገር’ ‘አባት አገር’ ያለ ወዩለት! ‘ለፋሺስትነቱ ተጨባጭ መረጃ ይዞ ተጋለጠ ማለት ነው። በአገር ፍቅርና በአብዮታዊ ትግል መሃል ስላለው የተቀራረበ ግንኙነት ወደፊት በሰፊው እንመለስበት ይሆናል። አሁን ግን ሁለቱ ተደጋጋፊ እንጂ ተቃራኒ እንዳልሆኑ የነሆቺ ሚንን ስም ብቻ ጠቅሰን እንለፍ። ነገር ግን እነዚህ ከሃዲዎች ነገሩን ጠለቅ ብለው እንኳ ሳይመረምሩ ‘ሂትለር አባት አገር ሲል ምርጦቹ እናት አገር ይላሉ ሁለቱም ፋሺስቶች ናቸው’ ብለው ሲናገሩ እነሌኒን አነስታሊን ‘አባትአገር’ እያሉ ሕዝብን መቀስቀሳቸውን ከማን ለመደበቅ ነው ወይስ የኛ ‘ማርክሲስቶች’ ይህቺንም ሀቅ አያውቋት ይሆን?
የዲሞክራሲያ አዘጋጆች በዚህ ጉዳይ ላይ በአቋም ሲቸበችቡ የሚያዙት ለጭቁን ሕዝቦችዋ ሰብአዊ ክብርና ወግ ያለው ኑሮ ለማስገኘት የምትታገለውና የአካባቢው አድሃሪዎችና ኢምፔሪያሊስቶች የሚጠነስሱባትን ሴራ ለመቋቋም የምትተናነቅ ሃገራችንን እንደሂትለር ጊዜ ጀርመን አደርገው ሲያቀርቧት ነው። ደርጉ ‘የመስፋፋትና ሌሎች ጐረቤት ሕዝቦችን የመውረር ስሜት እንዳለው’ ይነግሩናል። በነሱ አባባል ደርጉ “እኛን ለማጥፋት በሚዶልቱ ታሪካዊ ጠላቶቻችን የተከበብን ስለሆንን ሳንቀደም መቅደም አልሞት ባይ ተጋዳይነት ይሆናል በማለት ሕዝብን ጦር እንዲናፍቅ፣ አይኑኑን ወደውጭ እንዲተክል” ያደርጋል ብለው ለዚህ ተጨባጭ መረጃ ‘ሂትለር ስለሩሲያውያን፣ ምርጦቹ ስለአረቦችና ስለሱማሌዎች’ ያላቸውን አስተሳሰብ እያመሳሰሉ ያቀርቡልናል።
እዚህ ላይ ብዙ ብዙ የሚያጽፈን ነገር ነበር። በደፈናው ግን አንዳንድ ነገሮችን ብቻ ጠቁመን እንለፍ። አረቦች በደፈናው፣ ሶማሌዎች በደፈናው ጠላቶቻችን ናቸው አንልም። ነገር ግን ደግሞ ያለውን አንዳንድ ሃቅ አፍረጥርጦ ለመናገር የሚያስረን፣ ምንም በአድርባይነት የሚያናግረን ሁኔታ ስለሌለ ቸብቸባና ንግድ የሌለበት ግልጽ አቋም እንግለጽ። የኢትዮጵያ አብዮት ከጐረቤት አድሃሪዎች አደጋ የለበትም ብለን ጭቁን ሕዝቦችን ለማዘናጋት አንሞክርም፣ አለበት። በሰሕድ ቁጥር 37 ላይ በሚገባ እንደገለጽነው አድሃሪ የአረብ መንግሥታት ከኢትዮጵያ ፀረ አብዮት ኃይሎች ጋርና ከዓለም ዓቀፍ ኢምፔሪያሊዝም ጋር በሃገራችንና በአብዮታችን ላይ ያሴራሉ። ለዚህም የሚገባው አፀፋ፣ ከጐረቤት አገሮች አብዮታውያን ጋር በኢንተርናሽሊዝም መንፈስ የጠበቀ አንድነት መስርቶ አድሃሪ ኃይሎችን መቋቋም ነው። አገራችንና አብዮታችን ላይ ያለውን ይህን የጐረቤት አገሮች አድሃሪዎች ሴራ መካድ ወይም መደበቅ የደርጉን ብሄርተኛነት መቃወም ወይም ከጐረቤት አገሮች ተራማጆች ጋር መተሳሰር አይደለም። ከአድሃሪዎች ጋር ተደብሎ የኢትዮጵያን ጭቁኖች አዘናግቶ በጠላት እንዲመታ ማድረግ ነው።
የዲሞክራሲያ አድሃሪዎች ዞሮ ዞሮ ደርጉን ‘በአክራሪ ብሄራዊ ስሜት’ ይከሳሉ እንጂ እነሱ የአድሃሪ ጐረቤት አገሮች መንግሥታትን ፀረ አብዮት ሴራ ለመሸፈን ሲሞክሩ ‘የአክራሪ አድርባይነት ስሜት’ አባዜ እንደያዛቸው ግልጽ ነው። ለዚህ ምሳሌ እንዲሆን ‘ሰው ሳይሰማ’ በውጭ አገር ለአንድ ‘አፍሪክ-አዚ’ ለተባለ የሲአይኤ ጋዜጣ በሰጡት ቃለ መጠይቅ (ኢንተርቪው) ላይ እንዴት እንደሚነግዱ ለማሳየት እንጥቀስ።
የዲሞክራሲያ አድሃሪዎች ከጥቂት ሳምንታት በፊት ለዚህ አፍሪክ-አዚ ለተባለ ‘የነቃ አድሃሪ’ ጋዜጣ ቃለ መጠይቅ ሰጥተው ነበር። የዚህ ቃለ መጠይቅ ዓላማ የሃገራችንን አብዮት በዓለም ተራማጆች ፊት ሆን ብሎ ለማጥላላትና ከዓለም ተራማጆች ለመነጠል ብቻ ሳይሆን ለኢህአፓ ከአረብና ከጐረቤት አገሮች ድጋፍ ለመሰብሰብ እንደሆነ ከይዘቱ ግልጽ ሆኖ ይታያል።
በዚሁ ኢንተርቪው ውስጥ፣ የኢህአፓ ቃለ አቀባይ ነኝ የሚል ሰው፣ ስለመሬት አዋጅ ጨርሶ ሥራ ላይ አለመዋልና ‘ስለመሞቱ’፣ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ውስጥ የኢምፔሪያሊስቶች ዋና ምሽግ ስለመሆንዋ፣ በዓለም ፖለቲካዋም ከኢምፔሪያሊስት ቡችሎች ከነደቡብ አፍሪካ ጋር እጅ ለእጅ ተያይዛ የቆመች መሆንዋን ጠቁሞ እንደሚከተለው ይደመድማል።
“በጂቡቲ ጉዳይ፣ በስፖኒሽ ሰሃራ ጉዳይ የኢትዮጵያ መንግሥት ከደቡብ አፍሪካ፣… ከሞቡቱና ከንጉስ ሃሰን ጋር ተሰልፏል።” ይላል።
ነገር ግን፣ ማንም ሃቀኛ ተራማጅ እንደማይስተው፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በጂቡቲም ሆነ በስፓኒሽ ሰሃራ ጉዳይ ብሄሮች የራሳቸውን እድል በራሳቸው ለመወሰን ያላቸውን መብት የሚያውቅ ነው። የዲሞክራሲያ አቋም ግን ለገበያ እንዲመች ሆኖ የተወሰደ አቋም ነው። በጂቡቲ ጉዳይ የደርጉን አቋም የሌለው ሰበብ እየሰጠ በመቃወም በዚሁ ጉዳይ ላይ አድሃሪ የመስፋፋት አቋም የወሰደችውን ሱማሊያን ይደግፋል። በስፓኒሽ ሰሃራ ጉዳይ ‘እንዳጋጣሚ’ የብሄረሰቦችን መብት ማወቁ ለገበያው የሚያዋጣ በመሆኑ እዚህ ላይ ንጉሥ ሁሴንን ተቃውሞ ከደርጉ ጋር ከስፓኒሽ ሰሃራ ሕዝብ ጐን ተሰለፈ። ግን አሁንም ለገበያው እንዲመች፣ ‘በመላ ኢትዮጵያ ያለኋችሁ እኔ ነኝ’ እያለ የሚያንቦለብለው ችብቸባና ፕሮፓጋንዳው እንዲመች፣ የደርጉን አቋም ሸፍጥ በተመላበት አድርባይነትና ጨርሶ ዓይን በላሽ ማጭበርበር አጣሞ ‘ደርጉ በንጉሱ ሀሰን ጐን ተሰልፏል’ ብሎ የሌለ አቋም ይሰጠዋል። ይኸ ታዲያ የደራ ንግድ ማካሄድ ነው? ወይስ ለኢትዮጵያና ለአፍሪካ ጭቁን ሕዝቦች ነፃነት መቆም?
ለመደምደም ያህል፣የዲሞክራሲያ መሪዎች ደፍረው እንደማይመለሱ እያወቅን፣ አንዳንድ ጥያቄዎችን አስቀምጠን ለማጠቃለል እንወዳለን።
አንደኛ። መኢሶን እስከዛሬ ድረስ የኢትዮጵያን አብዮት በሚመለከቱ ዋና ዋና ጥያቄዎች ላይ በሙሉ ግልጽ የሆነ አቋም እየወሰደ መጥቷል። አድርባይ ብትሉት፣ ወላዋይ ብትሉት፣ የፈለጋችሁን ብትሉት ከነዚህ አቋሞች አንደኛቸውም ቢሆኑ ከኢትዮጵያ ሕዝቦች ቀንደኛ ጠላቶች፣ ከነአስፋወሰን /መንገሻ ስዩም፣ ከመሳፍንቱና ከነሲአይኤ ጋር አላዳበሉትም። እንዲያውም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ድርጅቱ እየተጠናከረ ስለመጣ፣ የነመንገሻ ሥዩምና የሲአይኤ ጋዜጦች በዚህ ድርጅት ላይ ይህ ነው የማይባል የማጥላላት ዘመቻ ይዘው እናያለን። እናንተን በሚመለከተው ግን ጨርሶ የተገላቢጦሽ ነው። በመንግሥት ጥያቄ፣ በዲሞክራሲ ጥያቄ፣ በወጣቶች ዘመቻ ጥያቄ፣ በደርጉ ባህርይ. . . በጠቅላላው የኢትዮጵያን አብዮት በሚመለከቱ ዋና ዋና ጉዳዩች ላይ በሙሉ ከነዚህ የሕዝብ ጠላቶች ጋር አንድ ዓይነት አቋም እየወሰዳችሁና እየተጋለጣችሁ ይኸው እዚህ ኪሳራ ደርሳችኋል። ይህ የአቋም አንድነት ‘የአጋጣሚ’ ይመስላችኋል? መኢሶንን የሚያንቋሸሹ የኢምፔሪያሊስት ጋዜጦች እናንተን ያሞግሳሉ። ይህስ ‘የአጋጣሚ’ ይመስላችኋል? የሲአይኤ ተብለው ለታወቁ እንደ አፍሪክ-አዚ ዓይነት ጋዜጦች አርማችሁ ያለበት ኢንተርቪው ትሰጣላችሁ። እነዚህ ጋዜጦች የናንተን ሃሳብ ለማስፋፋት የሚፍጨረጨሩት ለምን ይመስላችኋል? እስቲ በኢትዮጵያ ተራማጆች ፊት፣ ተራማጅ መስላችኋቸው በሚከተሉዋችሁ ወጣቶች ፊት እነዚህን ጥያቄዎች መልሱ!!
ሁለተኛ። በሃገር ውስጥ የምታሳዩት መልክና በውጭ አገር የምታሳዩት መልክ እንደቀይና እንደነጭ የተለያየ ነው። በውጭ አገር፣ የኢህአፓ ተጠሪ ነኝ እያለ የሚያወናብደው፣ ገንዘብ የሚሰበስበው፣ ፕሮግራማችሁን የሚያሰራጨው ‘ዓለምአቀፍ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ፌዴሬሽን’ የተባለው ድርጅት ነው። ይህ ድርጅት ተራማጅ መስሎ በቃላት ድንፋታ ብቻ የኢትዮጵያን ተማሪዎች ለመከፋፈል ብዙ ጥረት ካደረገ በኋላ በሃቀኛ ተራማጆች ከፍተኛ ትግል ተጋልጧል። የናንተንና የመሳፍንቱን አቋም ሙሉ በሙሉ ይዞ፣ ‘በተጨማሪ’ እንደናንተ ዳር ዳር ማለት ሳይሆን የመሬቱን አዋጅ ተቃውሞ፣ እንዲያውም መሬት ወደግል ኃብትነት እንዲመለስ በግልጽ እየተከራከረ ነው። መረጃዎች ካላችሁ እናቀርባለን። በውጭ አገር ያሉ ተራማጅ ኢትዮጵያውያን ‘የመንገሻ ሥዩም /አሰፋ ወሰን የወጣቶች ድርጅት’ ይሉታል። እሱ ደግሞ የኢህአፓ ነኝ ይላል። እናንተ ውጭ አገር በምታትሙት ‘አብዮት’ የተባለው የእንግሊዝኛ ጋዜጣችሁ አብዮታዊ ድርጅት እያላችሁ ትክቡታላችሁ። ይህን ድርጅት ‘አብዮታዊነት’ ስትሉ እንደዲሞክራሲያ ዓይነቱን “አብዮታዊነት” ነው? ወይስ በ1968 ኢትዮጵያችን “የማንን ርስት ለማን” እያለ የሚደነፋ የመሳፍንት ርዝራዥ ሁሉ ገና ለገና ወጣት ነው፣ ገና ለገና እነሌኒንን ጠቃቅሷል ተብሎ አብዮታዊ የሚባልበት ተዓምር አለ? እስቲ በዚህ የነአስፋወሰን/መንገሻ ሥዩም የወጣቶች ድርጅትና የናንተ የዉጭ ተጠሪ ነኝ በሚል ድርጅት ላይ ያላችሁን አቋም ለኛ እንኳ ሳይሆን ለአባሎቻችሁ ስትሉ አብራሩ!
በሉ ለዛሬ ይብቃን። እናንተ ዝም ብትሉም እንመለስበታለን።