የሰፊው ሕዝብ ድምፅ
ቁጥር 54፣ ሚያዝያ 30፣ 1969
የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ
መኢሶን በዚህ እትም የሜይ ዴይን አከባበር ከአለፉት አመታት ጋር እያወዳደረ፣ ወዛደሩ በንቃተ ህሊናና በመደራጀት የደረሰበትን ደረጃ ይተነትናል። ባለፈው አመት የተያዙት መፈክሮች በአመዛኝ የኢኮኖሚ ጥያቄዎች ላይ ያተኮሩ ሲሆኑ፣ የዘንድሮዎቹ ግን ወዛደሩ ለአብዮቱ ህልውና አስፈላጊ የሚባሉ የዴሞክራሲ መብቶችን መታወጅና ለእናት አገር ህልውና መስዋዕት ለመሆን ዝግጁነትን የሚያንጸባርቁ እንደነበሩ ይጠቁምና በአንጻሩ ሰልፉ ላይ የታዪትን የዲሲፕሊ ጉድለቶችን ያነሳል። ሰልፉ ላይ ጥቂት ወዛደሮች ብቻ የድርጅቶች አርማ መያዛቸው፣ ወዛደሩ ውስጥ መሠራት የሚገባው ብዙ ስራ እንዳለ የሚያመላክት መሆኑን አስገንዝቦ፣ መኢሶን የወዛደሩ ፓርቲ እንዲቋቋም ፣ ሰፊው ሕዝብ እንዲነቃ፣ እንዲደራጅና እንዲታጠቅ፣ እንዲሁም ብሄራዊ ክብሯንና ነጻነቷን የምታስከብር አዲስ ኢትዮጵያን ለመፍጠር ከሌሎች ተራማጆች ጋር በአንድነት እስከመጨረሻው እንደሚታገል ቃል ይገባል።
ለዓለም ወዛደሮች ቀን፣ ሚያዚያ 23 ቀን 1969 በወጣው ልዩ እትሙ ውስጥ፣ የሰፊው ሕዝብ ድምጽ የሚከተሉትን ቃላት አስፍሮ ነበር፡-
“የኢትዮጵያ ወዛደር መደብ በዚህ ባንድ አመት ጊዜ ውስጥ ያገኛቸው ድሎችና በጠቅላላውም ያተረፈው የንቃተህሊና እርምጃ በጣም ከፍተኛ ነው። የኢትዮጵያ ወዛደር መደብ ባሁኑ ወቅት በነማርክስ ቋንቋ ከ“መደብ በራሱ” ወደ “መደብ ለራሱ” በመሸጋገር ላይ ይገኛል። ማለትም ከተበታተነና ቅርጽ ከሌለው አካል፣ በስሜትና በግንፍልነት በየቦታውና በየሁኔታው የተናጠል ትግልን ከሚያካሂድ መደብ፣ የቀኝ ክንፍ ንዑስ ከበርቴውና የሌሎችም አድሃሪዎችና አወናባጆች መሳሪያ ከሆነ መደብ፣ ወደተሰበሰበ፣ የራሱን ጉልበትና ታሪካዊ ሚና ወደተገነዘበ መደብ፣ ራሱን ወደቻለ የህብረተሰብ ኃይል በመሸጋገር ላይ ይገኛል።….”
እንግዲህ፣ የእሁዱን ሰልፍ አሁን ወደኃላ ዞር ብለን ስንመለከተው፣ ወዛደሩ ይህንን የሽግግር ሂደት በእርግጥም አንፀባርቋል ወይ የሚለው ጥያቄ ይቀርባል። ይህንን ጥያቄ ለመመለስ የእሁዱን ሰልፍ ጥሩ ውጤቶችና ድክመቶቹን መገምገም ያስፈልጋል።
በመጀመሪያ ደረጃ ማስተዋል የሚያስፈልገው ነገር፣ ካለፈው አመት በዓል ጋር ሲነፃፀር፣ የእሁዱ የወዛደር ሰልፍ የመደቡን ንቃትህሊና ከፍ ማለት በሚገባ ለማንፀባረቅ መቻሉን ነው። ባለፈው አመት ተይዘው ከነበሩት መፈክሮች ውስጥ ቢያንስ ሃምሳ በመቶ የኢኮኖሚ ጥያቄና የወዛደሩን የሥራ ሁኔታ የሚመለከቱ መፈክሮች ነበሩ። ያለፈው ዓመት ሰልፍ የኢትዮጵያ ወዛደር በቀኝ ክንፍ ንዑስ ከበርቴውና በሃቀኛ ተራማጆች ሰፈሮች መካከል በመምረጥ ላይ በነበረው ወቅት የተደረገ ሰልፍ ስለነበር፣ ከወጡት የፖለቲካ መፈክሮች ዋነኞቹ “ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት” እና ተቃራኒው “ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት የቀልባሾች መፈክር ነው” የሚሉት ነበሩ። ባለፈው ዓመት የወዛሮች ቀን ሰልፍ ላይ፣ እነዚህ ሁለት ሰፈሮች በኃይል ቢፋጠጡም፣ የማይናቅ የወዛደሩ ክፍል ከኢህአፖ ተጽዕኖ ገና አልተላቀቀም ነበር።
የዘንድሮውን ሰልፍ ብንመለከት፣ ከተያዙት መፈክሮች ምናልባት እስከ 80 በመቶው የፖለቲካ መፈክሮች ነበሩ። “አብዮታዊት እናት ሀገር ወይም ሞት!” ፣ የተራማጆች ህብረት ይለምልም” ፣ “ሀቀኛ የወዛደር ፓርቲ እንመስርት”፣ “ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለጭቁኖች ያለገደብ”፣ “ዲሞክራሲያዊ መብቶች አሁኑኑ”፣ “የተቋረጠው የመንጥር ዘመቻ ይቀጥል”፣ “ለአብዮታዊ የዘመቻ ጥሪ ተዘጋጅተናል!” የሚሉት በብዛት የወጡ መፈክሮች ነበሩ። ሁሉም የኢትዮጵያን አብዮት አንገብጋቢ ጥያቄዎች የሚያነሱ ናቸው። ስለሆነም፣ የኢትዮጵያ ወዛደር መደብ ካንድ የትግል አመት በኋላ በፈጣን እርምጃ ንቃተህሊናውን ከፍ እንዳደረገው ሰልፉ ግልፅ አድርጓል ለማለት ይቻላል። በተጨማሪም፣ ሌኒን ባለው መሰረት፣ በአስር “ሰላማዊ ዓመታት” ሊገኙ የማይችሉትን ትምህርቶች የኢትዮጵያ ወዛደር መደብ በአንድ የአብዮት አመት ውስጥ ለመቅሰም መቻሉን በዚያውም ለማረጋገጥ ችሏል።
መፈክሮቹን በሚመለከተው በኩል የሚያበረታታ፣ ተስፋ የሚሠጥ ሁኔታ ሲታይ፣ የሰልፉን ዝግጅት በሚመለከተው በኩል ደግሞ በርከት ያሉ ድክመቶች ታይተዋል። ባጠቃላይ፣ ሰልፉ የዲሲፕሊን ጉድለትን አሳይቷል። ለምሳሌ ብዙዎች ድርጅቶች የራሳቸውን ስነሥርዓት ጠባቂ ክፍል ከተሰላፊው ግራና ቀኝ አላሰለፉም ነበር። አንዳንድ ድርጅቶች በሩጫ ሲያልፉ፣ አንዳንዶች ከመጠን በላይ ይጎተቱ ነበር። በርከት ያሉ ቦዘኔዎች በየድርጅቱ መካከል ከመግባታቸውም በላይ፣ ቅጥ የለሽ አሰላለፍ፣ ብዙ ድንፋታና ውካታን አልፎ አልፎ አሳይተዋል።
እነዚህ የዝግጅት እና የዲሲፕሊን ጉድለቶች ሲሆኑ፣ በሌላ በኩል ግን፣ በተለይም መኢሶንን በሚመለከተው በኩል፣ አንዳንድ የድርጅታችን ደጋፊዎች የፖለቲካ ስህተቶችን ፈጽመዋል። “መኢሶን ፓርቲያችን ነው!” “መኢሶን አስታጥቆናል!” የሚሉ የቃል መፈክሮች ተደጋግመው ተሰምተዋል። እነዚህን መፈክሮች ያሳሙ የነበሩት ግለሰቦች የመኢሶን ደጋፊ ሆነው የተሳሳቱና የድርጅታችንን የፖለቲካ መስመር በቅጡ ያልተገነዘቡ ጓዶች ናቸው። አለበለዚያም ባሉበት አካባቢ በሚደረገው የመስመር ትግል ላይ ብቻ ስላተኮሩ ለጊዜው በስሜት በመገፋፋት ብቻ የተሳሳቱ ጓዶች ናቸው። መኢሶን ፓርቲም አይደለም፣ ይህንንም በፕሮግራሙ ውስጥ ጭምር ገልጾ፣ በተደጋጋሚም፣ በፅሑፎቹ ውስጥ፣ ከሌሎች ሀቀኛ ተራማጆች ጋር ህብረትንና ከዚያም ውህደትን አድርጎ የወዛደሩን ፓርቲ አብሮ ለመፍጠር እንደሚታገል ገልጿል። ትጥቅን በሚመለከተው በኩል፣ መኢሶን ከሌሎች ሀቀኛ ተራማጆች ጎን በመሠለፍ ሰፊው ሕዝብ እንዲነቃ፣ እንዲደራጅ እና እንዲታጠቅ ታግሏል። ሰፊውን ሕዝብ ያስታጠቀውና በማስታጠቅም ላይ የሚገኘው ግን ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት መሆኑ የታወቀ ነው። ሰፊው ሕዝብ አሁንም ይበልጥ እንዲነቃ፣ እንዲደራጅ እና እንዲታጠቅ መኢሶን ትግሉን ይቀጥላል። የድርጅታችንን ፕሮግራም ለሚያውቁ፣ ፅሑፎቻችንንና ድርጊቶቻችን በሃቅ ለሚከታተሉ ሁሉ ይህ ግልፅ ነው ብለን እናምናለን።
የእሁዱን ሰልፍ አይነተኛ ከሚያደርጉት ነገሮች አንዱ፣ የተራማጆች ህብረት አባል ድርጅቶች፣ ማለትም የመኢሶን፣ የማሌሪድ፣ የኢጨአት፣ የወዛደር ሊግንና የአብዮታዊ ሰደድ አርማዎች በይፋ መውጣታቸውና ወዛደሩም ለህብረት የቆመ መሆኑን ማሳየቱ ነው። እንደዚሁም፣ ካምናው ይልቅ ዘንድሮ የመኢሶንና የማሌሪድ አርማዎችና መፈክሮች በርከት ብለው በመታየታቸው ባንዳንድ የሕብረት ጓዶቻችንን ዘንድ ቅሬታ እንደተፈጠረ ሲሰማ፣ በሌላ በኩል ደግሞ በአንዳንድ የመኢሶንና የማሌሪድ ጓዶች ዘንድ በወዛደሩ ውስጥ የሰራነውን ድርጅታዊ ሥራ የማጋነን አዝማሚያ ይታያል።
ለጓዶቻችን ሁሉ የምንናገረው አንድ ነገር ቢኖር፣ የሰልፉን አንድ ጎን ብቻ ከማየት ጠቅላላውን እንዲመለከቱት ነው። ከተሰለፉት 150 ወይም 200 ሺህ ወዛደሮች ውስጥ፣ የማንም ይሁን የማንን ዓርማ ይዘው የወጡት ምናልባት 15 ወይም 20 በመቶ ያህሉ ብቻ ናቸው!! ይህም እንግዲህ ሃቀኛ ተራማጆች ገና ከወዛደሩ ጋር በሚገባ አለመዋሀዳችንን ስለሚያሳይ፣ ለወደፊቱ፣ የኢትዮጵያን አብዮታውያን የሚጠብቃቸው ተግባር በጣም ከፍተኛ ነው ማለት ነው። ነገሮች፣ ከሁሉም መአዘን ሳይሆን ካንድ ጎን ብቻ፣ የወደፊት እድገታቸውን ሳንጨመር የዛሬውን መልካቸውን ብቻ ከተመለከተለን እንስሳታለን።
የ1969 የወዛደሮች ቀን፣ በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን፣ በአስመራ፣ በቢሾፍቱ፣ በናዝሬት፣ በጂማ፣ በነቀምቴ፣ በጎንደር፣ በደሴ፣ በመቀሌና በሌሎችም ከተሞች ሲከበር፣ በየሰልፉ ላይ፣ የኢትዮጵያ ወዛደር ራሱን የቻለ የህብረተሰብ ኃይል መሆኑን አሳይቷል። ይሁንናም፣ ከላይ በተጠቀሰውና በሚያዚያ 23 በወጣው የሰፊው ሕዝብ ድምጽ ላይ እንዳልነው ሁሉ፣ ይህንን መደብ ገና ብዙ ትግሎችና መስዋዕቶች ይጠብቁታል። የኢትዮጵያ አብዮት እጅግ በጣም የተወሳሰበ፣ እንኳንስ የውጭ ተመልካችን ይቅርና በአብዮቱ በቀጥታ የሚሳተፉትን የህብረተሰባችንን ኃይሎች ሁሉ አልፎ-አልፎ የሚያደናግር ዘላቂ ወይንም ስትራቴጂያዊ አስላለፉ የማይለዋወጥና የታወቀ ቢሆንም፣ አብዮቱ በጣም ፈጣን ከመሆኑ የተነሳ፣ ታክቲካዊ የኃይሎች አሰላለፍ በየጊዜው የሚለዋወጥበት አብዮት ነው። የኢትዮጵያ ወዛደር በዚህ ውስብስብ ሁኔታ መቼውንም ቢሆን የመጨረሻ ዓላማውን እንዳፍታም ቢሆን ሳይዘነጋ፣ ማንኛውንም መሰናክልና መስዋዕትነት ሳይፈራ፣ ችግሮቹን አንድ ባንድ እያሸነፈ ወደፊት እንደሚጓዝ እና በመጨረሻም፣ በሚፈጠረው ፓርቲው አማካይነት፣ ተገቢውን ያመራሩን ቦታ ለመያዝ እንደሚበቃ መኢሶን የማያወላውል እምነት አለዉ።
ድርጅታችንን በሚመለከተው በኩል፣ መኢሶን ለተራማጆች ህብረት መጠንከር፣ ለዲሞክራሲያዊ መብቶች፣ ለወዛደሩ ፓርቲና ለአብዮታዊ ግንባሩ መፈጠር እስከመጨረሻው ድረስ ይታገላል። መኢሶን የኢትዮጵያ ወዛደር መደብ ከአድሃሪ መደቦች ተጽዕኖ ለማላቀቅ፣ ባጠቃላይም ሰፊው ሕዝብ እንዲነቃ፣ እንዲደራጅና እንዲታጠቅ ለማድረግ ባካሄደው ትግል በርከት ያሉ አብዮታዊያን ሰውቷል። በየገጠሩ በጸረአብዮት ኃይሎች ላይ በተደረጉት ዘመቻዎች በመሳተፍ፣ ብዙ ጓዶቻችን በነኢህአፓ ኢዲዮና ኢኤልኤፍ፣ በኢምፔሪያሊዝም ቅጥረኞች ጥይት ወድቀዋል። ከሌሎች አብዮታዊያን ጓዶች ጋር፣ የመኢሶንም ጓዶች “አብዮታዊት እናት ሀገር ወይም ሞት!” በሚለው መፈክር ስር ተስልፈው ተነስተዋል። ኢትዮጵያን ባጥለቀለቃት የአብዮት ማህበል ውስጥ የኢትዮጵያ ወዛደር ፓርቲ እንደሚፈጠር ፊውዳሊዝምን፣ ኢምፔሪያሊዝምንና ቢሮክራሲ ካፒታሊዝም እንደምንደመስስና ብሄራዊ ክብሯንና ነፃነቷን የምታስከብር፣ አዲስ ሕዝባዊት ኢትዮጵያ እንደምትፈጠር ስለምናውቅ እስከ መጨረሻው ድል እንታገላለን።