ልዩ እትም 2 1968

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ልዩ እትም፣    ሚያዝያ 18፣ 1968

የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ

ይህ ልዩ እትም የኢትዮጵያ ወዛደሮች በአለም ዙርያ ካሉ ሌሎች ወዛደሮች ጋር በአንድነት ለሁለተኛ ጊዜ ማክበር መቻላቸው የትግላቸው ውጤት መሆኑን በማስታወስ ይጀምራል። በመላው ዓለም የሚገኙ ወዛደሮች ይህንን በዓል ሲያከብሩ የትግል አጋርነታቸውንና አንድነታቸውን የሚገልጹበት፣ እርስ በእርስ የሚማሩበት፣እንዲሁም መስዋዕትነት የከፈሉ ጓዶቻቸውን የሚያስታውሱበት ቀን እንደሆነ ያብራራል።

አለም አቀፋዊው የወዛደሩ ትግል ብሄራዊ ገጽታ እንዳለው አስታውሶ፣ በኢትዮጵያም ብሄራዊ ዴሞክራሲያዊ አብዮቱ ከግብ የሚደርሰው በወዛደሩ ፓርቲ ሲመራ ብቻ እንደሆነ ያስገነዝባል። ለዚህም የነቁ ወዛደሮችና አብዮታዊያን ልዩነታቸውን አስወግደው ለዚህ ፓርቲ መቋቋም እንዲታገሉ ጥሪ ያቀርባል። “የላብ አደሩ ፓርቲ ተመስርቷል” በማለት ከትግሉና ከእውነተኛው የወዛደር ፓርቲ መፈጠር ሊያዘናጉት የሚሞክሩትን ቀኝ ንዑስ ከበርቴዎችና አንዳንድ የሠራተኛው ማህበር መሪዎች ነን ከሚሉ ብልጥ ብልጦች እንዲጠንቀቅ ያሳስባል። ትግሉ እንዲገፋና በአብዮታዊያንና በነቁ ወዛደሮች ማካከል ያሉ ልዩነቶች በውይይት እንዲፈቱና አወናባጆች(ኢህአፓ) እንዲጋለጡ ለዴሞክራሲ መብቶች መታገል እንዳለባቸው፣ አሁንም ድል የሚገኘው በነቃ በተደራጀና በታጠቀ የሕዝብ ትግል ብቻ እንደሆነ አጥብቆ ያሳስባል።

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ለሰፊው ሕዝብ ሰራተኛ ገበሬ፣ ነጋዴ፣ ወታደር፣ ምሁር መብትና ጥቅም የሚታገል ጋዜጣ

የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ይቅደም

 
ልዩ እትም                                                                      ቀን 18/8/68

 

የሜይ ዴይ በዓልና የኢትዮጵያ ወዛደሮች

የዘንድሮ የሜይዴይ የዓለም ወዝአደሮች በዓል በሚያዝያ 23 ቀን ይከበራል። የኢትዮጵያ ወዛደሮች ከሰፊው ሰርቶአደር ሕዝብ ጋር ሆነው ጣምራ ጠላቶቻቸው – ፊውዳሊዝምና ኢምፔሪያሊዝምና ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝም – ለዘመናት የጫኑባቸውን የብዝበዛ የጭቆናና የግፍ ቀንበር በመሰባበር የሜይዴይ በዓላቸውን ሲያከብሩ የዘንድሮ ሁለተኛ ጊዜያቸው ነው። የኢትዮጵያ ወዛደሮች ይህን በአል ከአለም የመደብ ወንድሞቻቸው ጋር ማክበር መቻላቸው በቀላሉ የሚታይ አይደለም። የረዥም ጊዜ የትግላቸው ውጤት እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል።

ከሜይ ዴይ በዓል የኢትዮጵያ ወዛደሮች ብዙ ትምህርቶችን ይቀስማሉ። ከመላው ዓለም ወዛደሮች ወንድሞቻቸው ጋር የአንድነት ትግላቸው የደረሰበትን ከፍተኛ የእድገት ደረጃና ለወደፊቱም በመራራ ትግላቸው የሚቀዳጇቸውን ድሎች በጥንቃቄ ይመረምራሉ። የትግላቸውንም ስትራቴጂና ታክቲክ ከሀገራቸው ተጨባጭ ሁኔታ እየተነሱ ይቀይሳሉ። አስፈላጊውን ዝግጅትና ድርጅት በማሟላት፣ የሚቀሯቸውን ድሎች ለመቀዳጀት እንደገና በአፍላ ትግል ይጠመዳሉ። የራሳቸውን ትግልና የሃገራቸዉን ልዩ ሁኔታ በጥንቃቄ በመመርመርና በማገናዘብ የራሳቸውን ብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ሂደት በጥሞና ይነድፋሉ። አብዮቱን በግንባር ቀደምነት ለመምራት እንዲችሉና አብዮቱም የታለመለትን ኢላማ እንዲመታ የኢትዮጵያ ወዛደሮች አስፈላጊውን ዝግጅትና ድርጅት በማሟላት ኃይላቸውን ማስተባበርና አንድነታቸውን መጠናከር አለባቸው። ከእውነተኞቹ ተራማጅ አጋሮቻቸው ጋር በማርክሲዝም ሌኒኒዝም ርእዮተአለም እየተመሩ በቅድሚያ መደራጀት አለባቸው።

ይህ በአል የዓለም ወዛደሮች ለመብታቸው፣ ለደህንነታቸውና በሶሻሊዝም በያለበት የሚያደርጉትን ትግል የጋራ ዓላማ የሚያበስርና የትግል አንድነት የሚገልጽ አለም አቀፋዊ በአል ነው። የወዛደሮች ትግል እውነተኛ ዓለም አቀፋዊ መልኩ የሚገለጽበት ቀን ነው። የኢትዮጵያ ወዛደሮችም ይህን በዓል በማክበር ከጠቅላላው ዓለም ወዛደሮች ጋር የትግል አንድነታቸውን ይገልፃሉ። በዚህም አማካይነት ከልዩ ልዩ የወዛደሮች ትግሎች ጠቃሚ ትምህርቶችን ይቀስማሉ። ለወዛደሩና ለትግል አጋሮቹ መንግሥት፣ ከበዝባዥ መደቦች ብዝበዛና ጭቆና ነፃ ለሆነ ህብረተሰብ በተደረገው መራራ ተጋድሎ የፈሰሰውን ንጹህ የወዝአደሮች ደም በጠለቀ የሐዘን ስሜት ያስታውሳሉ። የነሱ ትግል ከአለም ወዛደሮች ትግል የተለየ ባለመሆኑ በዚህ ታላቅ ቀን የትግል አንድነታቸውን ያሰማሉ።

የወዛደሮች ትግል አለም አቀፋዊ ብቻ ሳይሆን ብሔራዊ ስለሆነ በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ተጨባጭና ልዩ ሁኔታ ላይ እንዲያተኩር ያስፈልጋል። ዛሬ በኢትዮጵያ የተለያዩና እርስ በርሳቸው የሚቃረኑ የትግል አዝማሚያዎች ስለሚታዩ ወዛደሮች ንቃታቸውን ከፍ አድርገው፣ የራሳቸው በሆነና በትክክለኛው የፖለቲካ መስመር ስር በመሰለፍ የሜይዴይ ባላቸውን ማክበር ይኖርባቸዋል።

ዛሬ በኢትዮጵያ ያለው ልዩ ሁኔታ የተፈጠረው፣ አብዮታዊ ትግሉም ከዚህ የደረሰው የሚመራው የነቃ የተደራጀና የታጠቀ የወዛደር ፓርቲ ገና ሳይፈጠር ነው። ዛሬም ቢሆን እንዲህ ያለው ፓርቲ አልተፈጠረም። ዛሬ አብዮቱ በደረሰበት ደረጃ ትግሉን ይበልጥ ለማራመድና ብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮቱን ከግቡ ለማድረስ፣ የነቁ ወዛደሮችና አብዮታዊ የፖለቲካ ድርጅቶች አወናባጀችን እያጋለጡ ወደ ድርጅታዊ አንድነት ማምራት፣ እውነተኛውን የወዛደሮች ፓርቲ ማቋቋም ይኖርባቸዋል። ስለዚህም ለእውነተኛዎቹ ተራማጆችና አብዮታውያን ወዛደሮች የመጀመሪያ ጥሪያቸው የዲሞክራሲያዊ መብቶች ለጭቁን ወገኖች ብቻ የሚለው መፈክር ይሆናል።

የለውጡ ባለቤት የሆነው ሰፊው ሕዝብ የዲሞክራሲያዊ መብቶቹን ተጎናጽፎ፣ ነቅቶ፣ ተደራጅቶና ታጥቆ የጊዜውን ዋና ጠላቶቹን-  ፊውዳሊዝምን፣ ኢምፔሪያሊዝምና ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝምን- እንዳያንበረከክ፣ የነዚህ አድሃሪ ሃይላት ርዝራዦችና ግልገሎች በዛሬው ጊዜ የተራማጅ ቃላት በማስተጋባት ተራማጅ መስለው ግራ ሲያጋቡት፣ ሲከፋፍሉትና ሲያወናብዱት ይገኛሉ። አሉባልታና ያልተጨበጠ ወሬ ሲነዙና ፀረድርጅት መርዝ ሲነሰንሱ ይገኛሉ። ዛሬማ ራሳቸውንም “እኛ ላብአደሮች” ይሉ ገብተዋል፤ የላብ አደር ፓርቲ አቋቁመናል በሚል ማወናበድ ከጸረአብዮት ሃይሎች ጋር በተግባር  የተሰለፈውን አድሃሪ ቡድናቸውን በማቅረብ ወዛደሩ እውነተኛ የትግል ድርጅቱን እንዳያቋቁም ያሻጥራሉ። የጊዜውን አንገብጋቢ ጥያቄዎች እየሸሹ ተመርጠን ጊዜያዊ መንግስት እናቋቁም ይላሉ። የጊዜውን ዋና ጠላቶች ትተው ፋሺዝምን ነገሰ በማለት ወዛደሩን ላልተዘጋጀበትና ለማያምንበት ትግል በማሰለፍ ለፀረአብዮታቸው መሳሪያ ሊያደርጉት ይጥራሉ። የራሱን አብዮት እራሱ እንዲቃወመው ይሻሉ። እንደነዚሁ ያሉ የአድሃሪ ግልገላት በኢ.ሰ.አ.ማና በየማህበሩ በመሪነትም ጭምር ይገኛሉ።

በተለይም ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ በተራማጅነት ስም በኢ.ሰ.አ.ማ ጽ/ቤት በብልጣብጥነትና በአፈጮሌነት  የተሰገሰጉት የአድሃሪ ቤተሰብ ግልገሎችና የቀኝ ክንፍ ንኡስ ከበርቴዎች ወዛደሩ ከብዝበዛ ነፃ እንዲሆን ለሚያደርገው ዝግጅት እንቅፋት ሆነውበት ቆይተዋል።

ወዛደሩ ከአጋሩ ከአርሶአደሩ ጋር ተባብሮ የስልጣኑ ባለቤት እንዲሆን መደራጀትና ይበልጥ መንቃት እንዳለበት ሲታወቅ እንዳይደራጅ እና እንዳይነቃ አፍነው ይዘውት፣ የመንግሥት ስልጣን እንዲጠይቅላቸው ይገፋፉታል። በተለይም የአድሃሪዎች ጥያቄ የሆነውን “ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግስት” ያቀርቡለታል። ጭቁን መደቦች ለዘመናት ያለቀሱት እንባ  እንዳይደርቅና መልኩን የለወጠ ብዝበዛ እንዲቀጥል ያልተደረጃውንና ያልታጠቀዉን ወዛደርና አርሶአደር ምርጫ ይደረግ በል፣ የምርጫ መንግሥት እናድናቋቁም ጠይቅ እያሉ ያወናብዱታል፣ በስሙ ይነግዱበታል። ሳይደራጅና ሳይታጠቅ ወስደው ያጋፍጡታል። ወስደው አጋፍጠውም እያባረሩና አያስገደሉ ፋሺዝም ይሉሀል ይህ ነው ይሉታል። ከፀረአብዮት ሰልፍ ውስጥ ሊከቱተት ሲጠሩ ይታያሉ።

ወዛደር ሆይ! ለመሆኑ ዛሬ የድካምህን ፍሬና የላብህን ዋጋ ለማግኘት፣ በአብዮትህ ጠላቶች በፊውዳሊዝም፣ በኢምፒሪያሊዝምና በቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝም ላይ ድልን ተቀዳጅተህ የጭቁኖችን መንግሥት ለመገንባት በመታገል ፈንታ የፖለቲካ ስልጣን ጥም ላቁነጠነጠው ምድረንኡስ ከበርቴና ፀረአብዮት ኃይሎች መሳሪያ ትሆናለህ? ስልጣን ለእነርሱ ትጠይቃለህ? ሳያደራጁህና ሳያዘጋጁህ ወደ አደገኛ አቅጣጫ ይመሩሃል። እነዚህ ኣድሀሪያንና ርዝራዦቻቸው ባንተ እና በመደብ ጓደኞችህ መነገድ ጀመረዋል። አድሀሪያንና ርዝራዞቻቸው ራሳቸውን ሕዝብ ብለው ቀርበዋል። አሁንም ላብአደሩንም ተክተው “እኛ ላብአደሮች” ማለት ከጀመሩ ሰንብተዋል። ዛሬ በኢ.ሰ.አ.ማ ጽ/ቤት ባልደረባ አለን! አለን! የሚሉትን እነዚህን አድሃሪ ንዑስ ከበርቴዎች ነቅተህባቸዉ ብልጠታችሁን ለሌላ! ማለት ይገባሃል።

የዛሬው ዋና መልእክታችን ስለዚህ አጭበርበሪዎች ምንነት ለማሳወቅ ሳይሆን ሰሞኑን በሚከበረው አለምአቀፍ የወዛደሮች ቀን /ሜይዴይ/ አከባበር አንዳንድ ነገሮችን ለማውሳት ነው።  በሚያዚያ 23 ቀን 1968 የሚከበረው ይህ የወዛደር በአል ካምናውም ይበልጥ በተጠናከረ ሁኔታ ለዲሞክራሲያዊ መብቶች መከበር የምትታገልበት ወቅት ነው።

አምና በዚህ በዓል፣ በኢትዮጵያ ምድር ለመጀመሪያ ጊዜ የወዛደሩ ምንነት በግልጽ ሲከሰት፣ በዚያውም ልክ ደግሞ እነዚሁ አድሃሪያንና ግልገሎቻቸው የአምናውንም የወዛደሮች ቀን ለራሳቸው መሳሪያና አድሃሪ ተግባር ሊጠቀሙበት ሞክረዋል። ዛሬም የሞት ሽረታቸውን የዚህን በዓል ይዘት ሊጠቀሙበት በዝግጅት ላይ ይገኛሉ። ዛሬ የራስህን በዓል ለማክበር ስትወጣ፣ የማታምንበትን የራሳቸውን መፈክር ሊያሲዙህ ይሞክራሉ። ከአንተ ጥቅምና ፍላጎት ጋር  የሚቃረን፣ አብዮትህን ሂደት የሚቀለብስ እና የሚፃረር መፈክር በተራማጅ ምሰል ቃላት ሸፍነው ይሰጡሃል። የራስህን ድርጅት ሳታጠነክር ባንተና በመደብ አጋሮችህ ስም መንግሥት ይጠይቃሉ። ሳትደራጅና ሳትታጠቀ ስልጣን አንተ እጅ ሊገባ እንደማይችል በሚገባ እያወቁ ያንተን መንቃት፣ መደራጀትና መታጠቅ ችላ ብለው በስምህ ይነግዳሉ።

ስለዚህም አንተ ይዘህ የምትወጣው ሰሌዳ፣ የምትታገልበት መፈክር በሚገባ የተረዳሀው፣ ጥቅምህን የሚጠብቅልህና አብዮቱን የሚያራምድልህ መሆን አለበት። ሃቀኛ ወዛደር ምንጊዜም ቢሆን ለመደብ ጠላቶቹ እጁን አይሰጥም። ጊዜያዊ ችግሩን ብቻ አይቶ፣ ፀረአብዮት ኃይሎች በስሙ ሲነግዱ፣ ለፀረአብዮት ትግላቸው መሣሪያ ሲያደርጉት ዝም ብሎ አያያቸውም። የመታገልና እነሱን የመደምሰስ አብዮታዊ ግዴታ አለበት።

የጊዜው መፈክሮች የጊዜውን ዋና ጠላቶች የሚመቱ፣ የወዝ አደሩን ችግር እና ብሶት የሚያሳዩ፣ የጊዜውንም ዋና የፖለቲካ ጥያቄዎች የሚያንፀባርቁ፣ ተጨባጭ ችግሮችን የሚያሳዩ መሆን አለባቸው። በተለይም ይህ ሰላማዊ ሰልፍ ወዝአደሩ ዓለምአቀፋዊ የትግል አንድነቱን የሚገልጽበት፣ የወዝአደሩ ትግል የበለጠ የምሁራን ጥንካሬ የሚያገኝበት፣ የወደፊቱም ትግል የበለጠ የሚጠናከርበት ወቅት ነው። የወዛደሩ ፓርቲ እንዲቋቋም፣ ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለጭቁን መደቦች እንዲፈቀዱ የዝቅተኛ ደመወዝ ተመን እንዲወሰን ወዘተ. የሚጠይቅበት፣ ልዩ ልዩ የሰርቶአደሩ ሕዝብ ብሶቶች የሚገለፁበትና የመደራጀት ጥያቄ፣ የፀረ ፊውዳል፣ ፀረ ኢምፔሪያሊስትና ፀረ ቢሮክራሲያዊ ከበርቴ ትግል እንዲፋፋም ወዛደሩ ያለውን ፍላጎት የሚገልጽበት ወቅት ነው።

ጊዜ አንቅሮ የተፋቸውና ገና ያልተደመሰሱት አድሃርያንና ምንነታቸው ሳይታወቅ በኢሰአማ ጽ/ቤት የተቀመጡት የመሳፍንት ሎሌዎች፣ አወናባጁ ድርጅት (ኢህአፓ) አባላት የሆኑ ቀኝ ክንፍ ንዑስ ከበርቴዎች፣ እንዲሁም በጮሌነታቸውናቸው በብልጣብልጥነታቸው ብቻ ወዛደር ነን የሚሉ አንዳንድ የማህበር መሪዎች የወዛአደሩን ትግል ለጸረ አብዮታዊ ግባቸው ለማዋል አሲረዋል። የላባደር ፓርቲ አለን በማለት እውነተኛ የወዛደሮች ፓርቲ እንዳይቋቋም የሚያሻጥሩ፣ የሰራተኛው ህጋዊ ማህበሩ ገና ከአድሃሪያን ሳይፀዳ፣ ተጨማሪ የማወናበጃ መስክ በኢ.ላ.አ.ማ በሚል ስም አቋቋምን እያሉ በሰርቶአደሩ ሕዝብ ያላግጣሉ። ኢ.ላ.አ.ማ የሚሉት የውስጥ ቡድን የነደጃች ደምስ አላምረውና የመሰሎቻቸው ልጆች አድሃሪ ቡድን መሆኑን አውቆ እነዚህኑ ግለሰቦች መታገል አለበት።

ወዛደሩን ዛሬ ቀድመውት፣ ሳይነቃ ነቅተው፣ ሳይደራጅ ተደራጅተው፣ እኛ እንምራህ፣ ተመራርጠን መንግሥት እናቋቁምልህ የሚሉህ፣ ላብ አደሩም ተራማጁም እኛው ነን የሚሉ የቀኝ ክንፍ ንዑስ ከበርቴዎች የሚያስጨብጡህን መፈክሮች አትቀበል። የሚያስይዙህን መፈክሮች ሳታምንባቸው በይሉኝታ አትቀበላቸው። ያድሃሪ ንዑስ ከበርቴ ድንፋታና ሁካታ አያሸብርህ። እነሱ የሚጠይቁት መንግሥት ለእነርሱና ለዘመዶቻቸው እንጂ ላንተ ምንህም አይደል። አንተ የራስህን የትግል መፈክሮች ይዘህ ተሰለፍ። ድሉ የነቃ የተደራጀና የታጠቀ ሰፊ ሕዝብ ነው።

ፊውዳሊዝም፣ ኢምፔሪያሊዝምና ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝም ይውደሙ።
ሰፊው ሕዝብ ያሸንፋል።
Scroll to Top