ሰሕድ ቁ. 11

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ቁጥር 11፣    ጥቅምት 19፣ 1967

የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ

መኢሶን በዚህ የሰፊው ሕዝብ ድምፅ እትሙ፣ ጥቅምት 16 ቀን በሺ የሚቆጠሩ ሥራ አጦች በኢትዮጵያ ሠራተኞች አንድነት ማኅበር (ኢሠአማ) ጽሕፈት ቤት በር ላይ በተሰበሰቡት ከርታታ ሥራ ፈላጊ ድሃ ዜጎች  ላይ ወታደራዊ ደርግ የፈጸመውን ግፍ አጥብቆ ያወግዛል። ሕዝቡን ባስቆጣው በዚህ ድርጊቱ፣ በደርግ ትዕዛዝ ቁጥራቸው በግልጽ የማይታወቀው ድሃ ዜጎች በግፍ ተገደሉ፤ ቆሰሉ ሲል ይመዘግባል። ሥራ አጥ ዜጎች በስለማዊ መንገድ የሥራ እድል እንዲያገኙ በመጠየቃቸው፣ ወታደራዊ ደርግ ፋሺስታዊ ድርጊት እንደፈጸመባቸው ያጋልጣል። “ያለምንም ደም” እያለ የሚመጻደቀው ደርግ በዚህ አይነት አስከፊ እርምጃ በታሪክ ፋሺስታዊ ሆኖ እንደሚመዘገብለት ያጋልጣል። አያይዞም፣ በሰላማዊ መንገድ የሥራ እድል እንዲያገኙ የጠየቁ ድሃ ወገኖች፣ “ሕገ ወጥነታቸው” ምኑ ላይ ነው? ሲል ይሟገታል።በደርጉ “የፌዝ ዲሞክራሲ” አንጻር፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎች፣ “መሬት ላራሹ”፣ ለሥራ አጡ የስራ ዋስትና፣ ዲሞክራሲ ለሁሉም፣ የትምሕርትና የጤና ዋስትና እና ከሲቪሉን ከወታደሩ የተውጣጣ “ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት” መቋቋም አስፈላጊ እንደሆነ በዝርዝር ያትታል።       

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ለሰፊው ሕዝብ ሰራተኛ ገበሬ፣ ነጋዴ፣ ወታደር፣ ምሁር መብትና ጥቅም የሚታገል ጋዜጣ

የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ይቅደም

 
ቁጥር 11                                                                        ቀን 19/2/67

     

የማይዘነጋ ፋሽስታዊ ድርጊት

ደም አናፈስም የሚሉት በላብአደሩ ደም ተበከሉ። የሰፊው ሕዝብ ወገነ ነን የሚሉት ሥራ ሥራ እያለ የሚጮኽውን ከርታታ በጥይት ቆሉት፣ በሰደፍ ቀጠቀጡት። ፋሽስትነታቸውን በገሃድ አስመሰከሩ። ጥቅምት 16 ቀን በሺ የሚቆጠሩ ሥራ አጦች በተሰበሰቡበት በኢሰአማ በር ላይ የሚያስቆጣ ፋሲታዊ ድርጊት ተፈጸመ፣ የብዙ ሥራ አጦች ደም ፈሰሰ፣ ብዙ ሥራ አጦች በደርጉ ቡችሎች ተደበደቡ፣ በፋሽስቶቹ ጥይት ተመትቶ ወዲያውኑ የሞተ የአንድ ከርታታ ሥራ ፈላጊ ሬሳ ብቻ እዚያው እወደቀበት ስፍራ ሲቆይ የቀሩት በሙሉ ወዲያውኑ ስለተወሰዱ ስንት እንደሞተና ስንት እንደቆሰለ እስካሁን በትክክል ማወቅ አልቻልንም። በማወናበጃ መሣሪያዎቹ ደርጉ የሰጠውን ቁጥር ግን ከእውነተኛው የራቀ መሆኑ አያጠራጥርም፣ እዚያው የነበሩት፡ ከጥይት የተረፉት የዓይን ምስክሮች፣ ግን ወዲያውኑ የሞቱት ከሦስት እንደማያንሱ ያረጋግጣሉ።

የጥቅምት 16ቱ ፋሽስታዊ ድርጊት ለምን አስፈለገ? በደርጉ የልመና መሳሪያ ጉርሻ በለመዱ ጥቂት ፀረ ሕዝብ ወታደሮች ሕይወታቸዉ የጠፋው፡ ደማቸው የፈሰሰውና በጠመንጃ ሰደፍ የተወገሩት ሥራ አጦች ኢትዮጵያ ትቅደምን የሚደግፉ ንፁሕ ኢትዮጵያውያን ነበሩ፣ በኃይለሥላሴ መንግሥትና በባእድ ከበርቴዎች አመጽ ከየሥራቸው የተባረሩ፣ የሚልሱት የሚቀምሱት ያጡ፣ ከነ ሙሉ ቤተሰባቸው በችጋር አለንጋ የሚገረፉ፣ መሰረታዊ መብቶቻቸው ተከብረው የሰፊውን ሕዝብ ኢትዮጵያ በሥራ ለመስቀደም የሚጓጉና የሚጥሩ ሰዎች ነበሩ። ታዲያ እነዚህ ሥራ አጥ ኢትዮጵያዊያን ሥራ ሥራ ስለአሉ በማንስ ላይ ቢሆን ምን የሰሩት በደል አለ? የማንንስ መብት ነክተዋል? ሥራ ይሰጠንና እንሥራ ማለቱሰ ምን ላይ ነው ‘ህገወጥነቱ’? ያለ ፈቃድ ተሰበሰቡ…. በፀጥታ አስከባሪዎች ላይ ድንጋይ ወረወሩ …ወዘተ የተባለው ፍጹም ሐሰት ማወናበጃ ነው። የስብሰባው ዓላማ ሥራ ስለማግኝት ጉዳይ ለመነጋገርና ደርጉ የሚሰጣቸውን መልስ ለመስማት ሲሆን ፍጹም ፀጥታ የተመላበት ነበር። ድንጋይ ወርውረዋል የተባለው ፍጹም ሐሰት ነው። ስብሰባ ለማድረግ አስቀድመው ጠይቀው 7/2/67 እስከ 22/2/67 ለአሥራአምስት ቀን ከኮ/በቀለ ተክሉ፡ የወንጀል መከላከል ምርመራ ረ/ዋና አዛዥ ፈቃድ ተሰጥቷቸዋል። ታዲያ ሁሉ እውቅ ሆኖ ሳለ የከርታታ ድሆችን ደም ያፈሰሰው፡ የስምንቶቹን አባት እንደወጣ ያስቀረው ‘የምርጦች’ መንግሥት እንዴት ይዋሻል?

ለጠቅላላው ሕዝብ ደህንነት የመጡ አስመስለው በወታደራዊው ደርግ ስም የሰፊውን ሕዝብ የላብና የደም ውጤት የቀሙት ጥቂት አወናባጅ መኮንኖች ስልጣንን በእጃቸው ካገቡበት ጊዜ ጀምሮ ብዙ ፋሽስታዊ ድርጊቶችን ፈጽመዋል። ኃይለሥላሴንና የብዝበዛ ጓደኞቹን አወረድንላችሁ እያሉ የሚደነፉብን ‘ምርጦች’ በሠራተኛው፣ በገበሬው፣ በሥራአጡ፣ በተራማጁ ወታደርና በጠቅላላውም በሰፊው ሕዝብ ላይ የፈጸሙት በደል ተዘርዝሮ አያልቅም። ‘ያለ ምንም ደም’ እያሉ ቢጨፍሩ፡ የመሳፍንትና የመኳንንት ደም እንዳይፈስስ ትልቅ ጥንቃቄ ቢያደርጉም በገጠርና በከተማ ብዙ የደሃ ደም አፍስሰዋል፣ የጠቅላላውን ሕዝብ መሰረታዊ መብቶች ገፍፈዋል፣ ‘መሬት ላራሹ’ ብለው የተነሱትን ጭሰኞች አስረዋል፡ በጥይት ቆልተዋል፣ የሠራተኛውን መብትና ጥቅም ለመጠበቅ መፍጨርጨር የጀመረውን የሠራተኞች አንድነት ማሕበርን አዳክመዋል፤ ወታደሮችን፣ ተማሪዎችንና ምሁራንን አስረዋል፣ አፍነዋል፣ ደብድበዋል፣ ረሽነዋል። እነዚህ ለሲአይኤ የተሸጡ አወናባጅ መኮንኖች ተራማጅ ወታደር ከመደብ ወንድሞቹ ጋር አብሮ በሕዝብ ጠላቶች ላይ የመዘዘውን ሰይፍ ወደ ሰፊው ሕዝብ እንዲያዞር በመገፋፋትና በማስገደድ ላይ ናቸው። የጥቅምት 16ቱ ደም ማፍሰስ የሚያመለክተው ይህንኑ ነው። ‘በዘመቻው’ ሳቢያ በዩንቨርስቲ ተማሪዎችና መምህራን ላይ የሚወሰደው እርምጃም ፋሺስታዊ ነው።

የእነዚህ ከርታታ ኢትዮጵያዊያን ንጹህ ደም ደመከልብ ሆኖ አይቀርም። ሰፊው ሕዝብ ፋሽስቶቹን በኃላፊነት የሚጠይቅበት ጊዜ ሩቅ አይደለም። ሰርተው እንዳይበሉ ሥራ የተነፈጉት፡ በፋሽስት ጥይት ሕይወታቸውን ያጡት ወንድሞቻችን ደም ትግላችንን ይበልጥ ያጠናክረዋል እንጂ አያዳክመውም። ጨቋኞች በሙሉ እስከተደመሰሱና [እስኪደመሰሱና- የአዘጋጆች እርማት] የሰፊው ሕዝብ ጥያቄዎች በሙሉ እስከተፈጸሙ [እስካልተፈጸሙ-የአዘጋጆች እርማት]ድረስ ትግሉ ይቀጥላል።

የሥራ አጦችና የሰፊው ሕዝብ ትግል ይቅደም
ሥራ ወደሠሪው፡ ስልጣን ወደ ሕዝቡ ይመለስ።

 

የፌዝ ዲሞክራሲ

ትርዒት 1
ሰፊው ሕዝብ መሬት ላራሹ፣ ሥራ ለሥራአጡ፣ ተገቢ ዋጋና ዋስትና ለሠራተኛው፣ ትምህርት፣ ጤና፣ የኑሮ ዋስትና፣ ዲሞክራሲ ለሁሉ፣ ከወታደርና ከሲቪል በምርጫ የተውጣጣ ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት ይቋቋም፣ ባጭር ጊዜ ውስጥ ወደመደበኛ ቀዋሚ ሕዝባዊ መንግሥት እናምራ፣ በአሁኑ ጊዜ አፋጥጠው የያዙን ችግሮች መፍትሄዎች እነዚህ ናቸው
የደርጉ ‘ምርጦች’ ቀኃስና ሲአይኤ አንድነት ሆነው ይመካከራሉ፣ የሰፊው ሕዝብ ጥያቄዎች ግራ ያጋቧቸዋል፣ ብዙ ያሳስቧቸዋል፣ አጤ ቆሪጥን አስጠርተው በእርሱ ታዛቢነት ከቀሩት ሁለት ወገኖች ጋር እንደሚከተለው ይወያያሉ።
ቀኃስ የአገር ጉዳይ፡ የሕዝብ ጉዳይ ቀላል ነገር እንዳይደለ ተገንዘባችሁት? እኔ ይህን ያህል ጊዜ እንዴት አድርጌ፡ እንዴት ያለ ዘዴ በጄ ውስጥ ጨብጬ ይዤው እንደቆየው ትንሽ ባብራራላችሁ ይርዳችሁ ይሆናል። ግን ለኔስ ምን አሰባችሁልኛል?
‘ምርጦቹ’ የእርሶ የስልጣን ጉዳይ አክትሟል፣ በዚህ እድሜ የልጅ ሥራ ለመሥራት ካልሆነ በስተቀር ለምንም አይጠቅምም። የስልጣንዎ ጉዳይ አብቅቷል፣ አልቋል፣ በዚህ በኩል ምንም ተስፋ አያደርጉ፣ ሰፊው ሕዝብ አንቅሮ ተፍቶዎታል። የዘረፉትን ወደ 15 ቢሊዮን ብር የሚሆን ገንዘብ ቢመልሱልን ግን ውጭ አገር ወይም ኢትዮጵያ ውስጥ የፈለጉበት ስፍራ ይህቺ  የቀረችዎን እድሜ በደህና እንዲጨርሱ አናደርግሎታለን፣ ይምከሩበት፣ ያስቡበት።
ሲአይኤ ጃንሆይ፡ የእርሶ ነገር አልቋል፣ ለአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም ሊሰጡ የሚችሉት ግልጋሎት በጣም ቀንሷል፣ አሁን የእርስዎ ስልጣን ላይ መቆየት ለእኛ ምንም ጥቅም አይሰጠንም። በእርስዎ መልካም ፈቃድ ደህና ደህና ቡችሎች አሳድገናል፣ በእነርሱ አመካይነት ጥቅማችንን የበለጠ ለማስጠበቅ እንችላለን። ለዉለታዎ አደጋ እንዳይደርስብዎ እናደርጋለን። ‘ከምርጦቹ’ ጋር ተግባብተው የስልጣን ላይ መቆየት መቻል ልምድዎን ቢያስረዱና ከወሰዱትም ገንዘብ ግማሹን እንኳን ቢመልሱ ወደ አሜሪካ ሄደው እንዲጦሩ ልናደርግዎ እንችል ይሆናል፡ ያስቡበት።
ቀኃስ መልካም፣ ጥሩ፣ ጉዳዩ ገብቶኛል። ገንዘብ መከጀላችሁ ከንቱ ነው፣ ምንም አልሰጣችሁም። የኔ ፍቅረነዋይ ምን ያህል እንደሆነ ሳታውቁ ቀርታችሁ ነው ይህን የምትጠይቁኝ? አስደንቆኛል። ገንዘብ፡ ብዙ ገንዘብ ለኛ ሁልጊዜ ያስፈልገናል፣ እወቁት። ስልጣን ላይ የመቆየቱ ዘዴ ማኪያቬሌን ደህና አደርጎ ማላመጥ ነው፣ አስተዋይነት፣ ብልህነት፣ ትዕግስት ወዘተ…የመሳሰሉትን ከከፋፍለህ ግዛ ጋር ማጣመርና ማዋሃድ ነው። የዜና ማሰራጫ መሳሪያዎችን በሞኖፖል ይዛችሁ በሬ ጥጃ ወለደ፣ ገደሉ ሜዳ ነው፣ ሕዝባዊ መንግሥት፣ ዲሞክራሲ ወዘተ… የሚሉት የመሳፍንትና የመኳንንት ቅሬቶች የውጭ እጅ፣ የጠላት መሣሪያ ወዘተ… ናቸው እያላችሁ የፕሮፓጋንዳ ቀልቀሏችሁን መክፈት ነው፣ በኃይል ንፉት። ይህ ብቻ ጥቂት ጊዜ ሊያስነብታችሁ ይችል ይሆናል።
ሲአይኤ ይህ ብቻ አይደለም። ጃንሆይ ያደርጉ እንደነበረው እነዚህን ሕዝባዊ መንግሥት፡ ዴሞክራሲ ወዘተ… እያሉ የሚጮሁትን ተማሪዎች፣ ሠራተኞች፣ ምሁራንና ሌሎችንም የሰፊውን ሕዝብ ክፍሎች በኃይል መምታት አለባችሁ፣ ለመሳሪያው እኛ አለን፣ ሌላም እርዳታ ይሰጣችኃል፣ ለአጤ እንሰጥ ከነበረው አስበልጠን እናቀርብላችኋለን። ምክራችንን ከተከተላችሁ፣ ትዕዛዛችንን ከፈጸማችሁ በሌላ በኩል ከቶ ሃሳብ አይግችሁ፣ እስከመጨረሻው ድረስ ከእናንተው ጋር ነን። በቬየትናምና ከልሎቹም አገሮች ያደረግነውን ታውቁ የለም? ብቻ ይህ ሚስጥር ነው፣ ሰፊው ሕዝብ እንዳያውቀው ተጠንቀቁ፣ የኛ ስም እንዳይነሳ። እኛ እንኳን ሌላ አለን፣ ይብላኝ ለእናንተ እንጂ የአጤና የፍጡሮቻቸው ዕድል ለሚጠብቃችሁ።
‘ምርጦቹ’ ሁለታችሁንም ከልባችን እናመሰግናለን ቆሪጥ ምስክራችን ነው። የገንዘቡ ጉዳይ በሰፊው ሕዝብ ዘንድ ከመሰማቱ በላይ ቀደም ብለው በደንብ የታወቀ ስለሆነ ጃንሆይ አሁን አንለቆትም፣ 4ኛ ክፍለጦር ወንደሰን ደንበኛ ቪላ ውስጥ እናስቀምጦታለን፣ ገንዘቡን አልመልስ አሉን እያልን ሰፊውን ሕዝብ ለጥቂት ጊዜ እናወናብድበታለን። ሰፊው ሕዝብ ዴሞክራሲ፣ ህዝባዊ መንግሥት፣ ከወታደር እና ከሲቪል በምርጫ የተጣጣ ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት አሁኑኑ ይቋቋም በማለት ወጥሮ ያዘን፣ ሲአይኤ፡ምን ይሻላል?ምን እናድርግ? በኃይል ተቸግረናል።
ሲአይኤ አብዳችኋል እንዴ? የምን ሕዝባዊ መንግሥት ነው? ዲሞክራሲ ለእኛ እንጂሰ ለእናንተ አይሆንም፣ እዚህ ቦታ የለውም። አሳባችንን በትክክል የተረዳችሁት አይመስለንም፣ በኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ጊዜ የሚያስፈልገው ጠንካራ መንግሥት ነው። ጠንካራ መንግሥት ደግሞ የወታደር መንግሥት ነው፣ የእኛ ቡችላ ማለት ነው። በእኛ ምርጥ ኤክስፖርቶችና በእናንተ ‘ሊቃውንት’ ተጠንቶ አልቋል። ዋናው ተግባራችሁ ይህን ሥራ ላይ መዋል ብቻ ነው። የታወቁት አባሎቻችን እነዲን ፖል፣ እነኮሪና ሌሎችም ወደዚህ መጥተው ሥራቸውን ከጀመሩ ሰንብተዋል። እነርሱ የሚሏችሁን ዝም ብላችሁ መቀበልና መከተል ነው፣ እንደምታውቁት ኢትዮጵያን ከእናንተ ይበልጥ ያውቃሉ። ለዚህ ለእናንተ ጉዳይ ከእነርሱ የተሻለ የለምና የሚሉዋችሁን አጥብቃችሁ መከተል ብቻ ነው። አለበለዚያ ምን ሊደርስባችሁ እንደሚችል ታውቁ የለም? አዎን ቀልድ የለም፣ የተዘጋጀው የወታደር መንግሥት ቶሎ ብሎ ይታወጅ። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለንን ከፍ ያለ የኢኮኖሚ ስትራቴጂ ጥቅም ለመጠበቅ የሚችል የወታደር መንግሥት ብቻ ነው። የዲሞክራሲን ጉዳይ ለጊዜው ለአሜሪካና ለአውሮፓ ማለት ለነጮች ተውት።
ትርኢት 2
‘ምርጦቹ’ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ ደስ ይበልህ! በዛሬው ቀን አጤ ኃይለሥላሴን ከስልጣን አውደን አስረናል፣ አልጋወራሹ መጥተው ዘውድ እስኪጭኑ ድረስ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት አቋቁመንልሀል ባለህበት እርጋ፣ ለጥሰጥ ብለህ ተገዛ። የሚያንገራግርና የሚበጠብጥ ይቀጣል፣ ሰዓት እላፊ ከምሽቱ አንድ ሰአት ተኩል እስከ ጠዋቱ አሥራሁለት ሰአት ነው። የጦር ኃይሎችና ፖሊሶች አዋጁን እንዲያስከብሩ ታዘዋል፣ ተባረኩ፣ አሜን።
ሰፊው ሕዝብ ጨቋኙና ግፈኛው አጤ ኃይለሥላሴ ከስልጣን መወገዳቸውን በደስታ ተቀብለነዋል፣ የሰላማዊው ሕዝብና የጦር ኃይሉ የትግል እንቅስቃሴ ውጤት ነው። ሆኖም ሦስት ተቃውሞዎች አሉን። አንደኛ፡ የኢትዮጵያ ሪፑብሊክ መታወጅ ሲገባው ዘውዱ ይቀጥላል ማለቱን በጥብቅ እንቃወማለን፣ ሁለተኛ፡ ከወታደሩና ሰላማዊው ሕዝብ በምርጫ የተውጣጣ የሕዝብ መንግሥት መቋቋም ሲገባው የወታደር መንግሥት ለብቻው መቋቋሙን በኃይል እንቃወማለን፣ ሦስተኛ፡ መሰረታዊ መብቶቻችን ተከብረውና ተጠብቀው ትልቅ የፖለቲካ ተሳትፎ ማድረግ ሲገባን መብቶቻችን በግልጽ መገፈፋቸውን አጥብቀን እንቃወማለን። እነዚህ አሁኑኑ ካልተለወጡና በጥያቄያችን መሰረት ካልተፈጸመ ትግላችን አይፈታም፣ ይቀጥላል
‘ምርጦቹ’ እኛ ስልጣን አንፈልግም፣ በአፍንጫችን ይውጣ፣ ገብርኤልን፣ ሚካኤልን፣ ማርያምን ስልጣን ብንፈልግ ኖሮ እስካሁን ድረስ ማን እጃችንን ያዘን? ይህን የሚያስወሩ አንዳንድ ተንኮለኞች ናቸው።
ሰፊው ሕዝብ ሲአይኤ የሚባለውን ጭራቅ ታውቃላችሁ? ቡችሎቹ በዙርያችሁና በውስጣችሁ ጭምር መኖራቸውን የምትክዱ ከሆነ ስለአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ያላችሁን አቋም በገሃድ ግለጡ እስቲ? ሰሞኑን ከመቶ ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ የጦር መሳሪያ ከአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም በመቀበል ላይ መሆናቸሁ አልተገለጠም? ታዲያ ምን ልታደርጉበት ነው? ለውጭ ጠላት ወይስ እኛን ለመጨፍጨፊያ? ሞኛችሁን ፈልጉ፣ እናንተ ቤት ያደረው ብልጠት እኛም ቤት አምሽቷል።
ሲአይኤ ታዲያስ ጎበዝ! ነገሩ አልቋል፣ መጋረጃው ተገልጧል፣ ምስጢራችን ታውቋል፣ እኛም እናንተም ተጋልጠናልየፕሮፓጋንዳ ወናፋችሁን ደህና አደርጋችሁ ወልውሉ፣ አጠናክሩ፣ አጫፋሪዎች መልምሉ፣ ቁጥራቸውን በርከት አድርጉ፣ ገንዘብ በትኑላቸው፣ የኢኮኖሚ ችግር ቢኖርብንም ለዚህ ያህል አይገድም፣ ወደዋሽንግተን አስቸኳይ ቴሌግራም አስተላልፈናል፣ ሁሉም ነገር ይመጣላችኃል፣ ፍጹም አታስቡ፣ ጦሩንም በደንብ አስታጥቁት። ከዚያም ‘ሕዝባዊ መንግሥት’፡ ዴሞክራሲ እያሉ የሚጮሁትን አጤ በተካኑት በከፋፍለህ ግዛ ዘዴ በመጠቀም ቶሎ ብላችሁ አድክሟቸው። እስካሁን ድረስ ደም አላፈሰስንም፣ ለውጡ ያለ ደም መጣ ያላችሁትን ለጊዜው ወደ ጎን ተውትና ሰላማዊዉን ሕዝብም ሆነ ወታደሩን ለመምታትና ደሙንም እንደጎርፍ ለማፍሰስ መዘጋጀት ይኖርባችኃል። በዚህ ትእዛዝ መሠረት አንደ ሻለቃ ጦር ከሀረር ይመጣና የምድር ጦር መሐንዲስን በድንገት ይመታዋል። 5 ሰዎች ወዲያውኑ ይሞታሉ፣ 6 ሰዎች ቆስለው ወደ ሆስፒታል ይወሰዳሉ፣ ሰፈሩ ይያዛል፣ አባሎቹ በሙሉ ይታሰራሉ። የምድር ጦር አየር ክፍል /አርሚአቬሽን/ አባሎችም ይታሰራሉ። ከክብር ዘበኛ፣ ከአየር ኃይልና ከሌሎቹም ክፍሎች የሕዝብ ወገን የሆኑት ግንባር ቀደሞች ይታሰራሉ። ተማሪዎች፣ ሰራተኞች፣ ጭሰኛና ደሃ ገበሬዎች፣ ምሁራን ተራመጆች ይደበደባሉ፣ ይታሰራሉ፣ አንዳንዶቹ ከቀድሞዎቹ ጨቋኞችና በዝባዦች  ጋር ባንድነት 4ኛ ክፍል ጦር ውስጥ ይታጉራሉ። ግን ይህ ሁሉ ትግሉን አያበርደውም፣ ይበልጡኑ እየተፋፋመና እየጠነከረ ይሄዳል
ትርዒት 3
ሰፊው ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ መብቶች አሁኑኑ ሥራ ላይ እንዲሉ ይደረግ፣ ከሲቪልና ከወታደር በምርጫ የተወጣጣ ጊዜያዊ መንግሥት ቶሎ ይቋቋም፣ ፈላጭ ቆራጭ አምባገነን መንግሥት አንፈልግም፣ ኢምፔሪያሊዝም፣ ፋሺዝምና ፊውዳሊዝም ይውደሙ፣ የንግግርና የፅሁፍ፣ የማህበርና የሰላማዊ ሰልፍ መብቶች ለዘላለም ይኑሩ።
‘ምርጦቹ’ ዲሞክራሲ፡ ዲሞክራሲ እያሉ መጮህ ምን ትርጉም አለው? ሰፊው ሕዝብ እኮ አልነቃም፣ አልተደራጀም። ተማሪና ምሁር ‘እድገት በህብረት፣ የእውቀት የሥራ ዘመቻ’ የሚባል ፕሮግራም ተዘጋጅቷልና ወደዚያ ሄዳችሁ ገጠሬውን ሕዝብ አስተምሩ፣ አይኑን ግለጡለት። ይህን የማይቀበል የሕዝብ ጠላት ነው፣ የንጉሳውያን፣ የመሳፍንት፣ የመኳንንት፣ የተያዙት ባለስልጣኖች ርዝራዥና ቅሬት ነው።
ቱልቱሎች /በአሉ ግርማ ፖውሎስ ኞኞ አጥናፍ ሰገድ አለማየሁ ሞገስ፡ ወዘተ./ አዎን አዎን፣ ዲሞክራሲ፡ ሕዝባዊ መንግሥት ለኢትዮጵያ አያስፈልጋትም፣ ይህን የሚፈልጉ  የቀድሞ መንግሥት ደጋፊዎች፡ የመሳፍንት፣ የመኳንንት፣ የተያዙት ባለልጣኖች ልጆችና ዘመዶች ናቸው። ደግሞስ ዴሞክራሲን ምኑን አውቀውት? የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችንና አስተማሪዎቻቸውን ብንወስድ ለ8000 የዩኒቨርሲቲ ሰው 4000 የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት የሚመረጡ ለዲሞክራሲ ያልደረሱ፣ ያልበሰሉ ናቸው። የቀረው ሕዝብማ ዲሞክራሲን ምኑን አውቆት? ምንስ ሊያደርግለት? ፋሽስት ወታደራዊ መንግሥት፣ ሲአይኤና ኢምፔሪያሊዝም ለዘላለም ይኑሩ! እኛንም ከገንዘቡ ከሹመቱ በሉን፡ አትርሱን፣ ሞግዚታችን፣ አለቃችን ሲአይኤ ያዘዘልንን አታስቀሩብን፣ በርትተን እንተባበር፣ የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም ጥቅም እንዲጠበቅና እንዲስፋፋ ማድረግ ዋናው ተግባራችን ነው፣ አሜን።
ሰፊው ሕዝብ ችግሮቻችን ትክክለኛ መፍትሄ ማግኘት የሚችሉት በዲሞክራሲ ነውሕዝባዊ መንግሥት ስንል ጨቋኞችና በዝበዦች የማይሳተፉበት የሰፊው ሕዝብ መንግሥት ማለታችን ነው። በጨቋችና በዝባዦች ነፃነት ላይ ገደብ ይደረግበታል፣ ቀንደኞቹ፣ በሕዝብ ላይ ግፍ የሰሩት፣ የተያዙትና ገና ያልተያዙት ሁሉ በፍጥነንት ተይዘው፡ ሁሉም ወደ ልዩ የፍርድ ሸንጎ ቀርበው ያለምንም ይግባኝ ቅጣታቸውን እንዲቀበሉ ይደረጋል። ታዲያ የኛ ጥያቄ ይህ ሲሆን ‘የቀድሞዎቹ ባለልጣኖች ርዝራዥና ቅሬት ናችሁ፣ እነርሱን ለማስፈታት ነው ሕዝባዊ መንግሥት ዴሞክራሲ እያላችሁ የምትጮሁት…’ በማለት ስማችንን የምታጠፉት ለምንድነው? የሕዝብ አንጡራ ገንዘብ የሆነውን የዜና ማሰራጫ መሳሪያ በሞኖፖል ይዛችሁ የማርከስ፣ የማቆሸሽ፣ የማጥላት የፕሮፖጋንዳ ወናፋችሁን በመልቀቅ የምታሸንፉ ይመስላችኋል? ድካማችሁ ከንቱ ነው፣ በመጨረሻ ድሉ የኛ ነው። አይናችሁን ከፍታችሁ ታሪክን ለመመልከት ብትሞክሩ ከብዙ አደጋ ለመዳን ትችሉ ይሆናል።
‘ምርጦቹ’ አዋጅ! አዋጅ! የዲሞክራሲ አዋጅ፡ ‘የመማክርት ኮሚቴ አባሎች’ በ15 ቀን ውስጥ መርጣችሁ እንድትልኩ፣ ሰዎች የሚከተሉትን ማሟላት አለባቸው፡ የኢትዮጵያ ትቅደምን/ ምርጦቹና ኢምፔሪያሊዝም ይቅደሙ/ ፍልስፍና ደህና አድርጎ የሚያውቅ፣ ችሎታ ያለው፣ የተማረ /ማን ይሆን የሚለካው/፣በሕዝብ ላይ ግፍ ያልሰራ፣ መጥፎ ጠባይና ልማድ የሌለበት/ የማይሰክር የማያመነዝር ወዘተ./። 23 ሚሊዮን የሚሆነው /አይኑን ያልከፈተ ጭሰኛና ድሃ ገበሬ አንድም ወኪል አይመርጠም። ለ15 ዓመታት ያህል ደሙን በማፍሰስ፡ ሕይወቱን በመሰዋት ጨቋኙኝንና በዝባዡን የኃይለሥላሴን መንግሥት ሲቋቋም የቆየው ተማሪም ምንም ወኪል አይኖረውም፣ በሚሊዮን የሚቆጠረውም የሥራአጥ ሠራዊት እንደዚሁ። ግማሽ ሚሊዮን የሚሆነው ሠራተኛ 3 ወኪሎች ይመርጣል። ወደ 20 የሚሆኑ መምህራን /ድጋፍ ሰጥተውናልና/ 6 ወኪሎች ይኖራቸዋል። እንዲሁም ከመስሪያ ቤቱና ከየክፍለሀገሩ ቢሮክራቾች ይመረጣሉ። ይህ አይደለም ዲሞክራሲ ማለት? የመረጣችኋቸው ወኪሎቻችሁ ሥራም ለኛ ሀሳብ ማቅረብ ነው፣ ብንፈልግ እንጠቀምበታለን፣ ካላስደሰተን ደግሞ ቀዳድደን ቆሻሻ ወረቀት መጣያ ውስጥ እንዶለዋለን።
ቱልቱሎች ታዲያስ ዴሞክራሲ ባዮች፣ አልኩባዮች፣ ይኸውላችሁ! እንግዲህ ምን ኖራችሁ! ስትጮሁለት የነበረውን አገኛችሁ አይደለም? በሸዋ ክፍለሃገር ሹማምንት ተሰብስበው ምክትል አስተዳዳሪውን መረጡ፣ ከሃረር ቀኛ/ይጥና አበበ በ74 ድምጽ ተመረጡ። የጎጃም ሕዝብ ክቡር አዲስ አለማየሁን፣ የወሎ ሕዝብ ክቡር አሰፋ ሊበንን፣ የአርሲ ሕዝብ ዶክተር ጥቀሄር ሃይሉን ወዘተ… መረጡ።
ሰፊው ሕዝብ የንግድ ሚኒስቴር ሠራተኞች ከአምስት የማያንስ ጊዜ ተሰብስበው አናምንበትም፣ አንመርጥም ብለው በመጨረሻ እፍኝ የማይሞሉ አድርባዮች ከመካከላቸው አንዱን መርጠዋል። የህዝባዊ ኑሮ እድገት ሚኒስቴርም እንደዚሁ። ይህ ዲሞክራሲ አይደለም፡ ቀልድ ነው። በዚህ አይነት መንገድ ተመርጦ የሚላከው ተላላኪ እንጂ ደንበኛ ስልጣን ያለው ወኪል አይደለም። ግሩም ዲሞክራሲ! እጡብ ድንቅ ነው። በዲሞክራሲ ከግሪኮችም ሳንበልጥ አልቀረንም። በመንግሥት ለውጥ፡በሬቮሉሽን ዓለምን ማስተማር እንደጀመረን አሁን ደግሞ ዲሞክራሲ ምን እንደሆነና እንዴት ሥራ ላይ እንደሚውል ለመላው ዓለም አብነት መሆናችን ነዋ! እኛ ግን ትግላችንን ከመቀጠል በዚህ ርካሽ ማጭበርበር አንፈታም
‘ምርጦቹ’ ‘…..የጦር ኃይል አባሎች ለኢትዮጵያ ሕዝብ ፍጹም የሆነ የሶሻል፣ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ነፃነት ለመስጠት ቃልኪዳን ገብተዋል። ይህ የማይታጠፍ ቃላችን ነው። ግን አስቀድሞ አይኑን እንዲከፍት /እውር ነውን?/ የፖለቲካ ንቃት፣ የአስተሳሰብ ለውጥ አግኝቶ የራሱ እድል ወሳኝ እንዲሆን ማድረግ ነው።’ ለዚህም የእውቀትና የሥራ ዘመቻ አዘጋጅተናል። ይህ እስኪከናወን ባለንበት መቆየት አለብን። እኛ ከላይ ፈላጭ ቁራጭ ብንሆንም እናንተ ሀሳብ አቅራቢ ተላላኪ እንድትሆኑ ይፈቀድላችኋል፣ በደሞዝና በአበል ግን አትበደሉም፣ ቢያንስ ቢያንስ ጸረዲሞክራሲ በሆነ መንገድ ይመረጡ የነበሩትን የፖርላማ አባሎች ያህል ሳታገኙ አትቀሩም። ሕዝቡ የጣለባችሁ አደራና ኃላፊነት ከባድ መሆኑን መዘንጋት የለባችሁም። ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ተመርጣችሁ የመጣችሁ የ26 ሚሊዮን ተኩል ሕዝብ ወኪሎች ናችሁእኮ! ተግባብተናል አይደለም? ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ ነው። ፍሬ ነገሩ ይህ ነው።
ቱልቱሎች የሕዝብ ሸንጎ ተሰበሰበ፣ የደርጉ ሊቀመንበር በሰፊው ሕዝብ ልዩ ልዩ ክፍሎች ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ተመርጠው የተላኩትን ከአርባ በላይ የሚሆኑ የሕዝብ እንደራሴዎች ተቀብለው አነጋገሩ፣ ስለሥራቸው መመሪያ ሰጧቸው፣ ሕዝቡ ከባድ ኃላፊነት የጣላባቸው እንደመሆኑ መጠን ባሁኑ የመሸጋገሪያ ወቅት ከደርጉ ጋር ትልቅ የሥራ ድርሻ እንደሚጠብቃቸው ገለጻ አደረጉላቸው። ከሊቀመንበሩ ንግግር በኋላ አቶ አንቶኒ በ…ክፍለሃገር ተወክለው የመጡት ‘የኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች፣ የፖሊስ ሠራዊትና የብሔራዊ ጦር ሰራዊቶች ጨቋኙን የመሳፍንትና የመኳንን መንግሥት ከህዝቡ ጫንቃ ላይ አሽቀንጥረው በመጣል ፍፁም ዲሞክራሲያዊ የአስተዳደር መስርተው እኛ የመጀመሪያን ወኪሎች ሆን እንድናገለግል በመደረጉ ታላቅ ክብር ስለተሰማኝ ክቡር ሊቀመንበሩን ከልብ አመሰግናለሁ’ በማለት ልባዊ የሆነ ደስታቸውን ገልጠው የምታሰቢያ ፎቶ ተነስተው የበዓሉ ፍጻሜ ሆነ። ይኸውላችሁ እንግዲህ ሕዝባዊ መንግሥት መቋቋሙ አይደለምን? ምን ቀረው? ታላቁ ሸንጎ ሥራውን ጀመረ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሲመኘው የነበረው ሁሉ ተሟላለት፣ እንግዲህ ሽንጥን ገትሮ መሥራት ነው፣ ዛሬም ነገም ሁልጊዜም ሽንጥን ገትሮ ወገብን ደድጐ 24 ሰዓት መሥራት ነው። የሚያዋጣው ሥራ ብቻ ነው። ከእንግዲህ ወዲያ ሕዝባዊ መንግሥት፣ ዴሞክራሲ ማለት የለም፣ ደርጋችንን ዘለአለም ያኑረው፣ ምን ጎድሎን እንግዲህ፡ ሁሉ በጃችን ሁሉ በደጃችን።
ሰፊው ሕዝብ ዲሞክራሲ ሕዝባዊ መንግሥት መሰረታዊ ሰብአዊ መብቶችና ነፃነቶች በቀልድ የሚታለፉ አይደሉም፣ አሁኑኑ ሥራ ላይ መዋል አለባቸው። መሬት ላራሹ፣ ለሥራአጡ ሥራ፣ ትምህርት ለሁሉ፣ ለሠራተኛ ተገቢ ዋጋና ዋስትና፣ ጧሪ ለሌላቸው ጡረታ፣ የጤና አገልግሎት ለሁሉ፣ በድርቅና በችጋር ለሚሰቃዩ አስቸኳይና በቂ እርዳታ ይደረግ፣ ችግራችን ባሰ እንጂ ምንም አይነት መሻሻል አላየንም። ከአር ዘሎ ቅዘን እንዳይኾን ያሰጋል። ትግላችን ድሉን እስከመታ ድረስ ይቀጥላል፣ ምንም ኃይል ሊያቆመው አይችልም

ዲሞክራሲ በአጤ ኃይለሥላሴና በምርጦቹ አይን

ቀኃሥ

‘..በነዚህም የምክር ቤቶች የሚመከሩ አማካሪዎች ሕዝቡ ተምሮና አውቆ  ለመምረጥ እስኪችል ድረስ በንጉሠ ነገስቱ ፈቃድ ከያውራጃው እየተመረጡ ይመጣሉ።’         …1923

‘..ከዚያ ወዲያ የሕዝቦችን እውቀቱ  የበቃ በሆነ ጊዜ ለዚህ ምክር ቤት የሚሆኑንን አማካሪዎች ራሱን ችሎ እየመረጠ ሊሰድልን ይችላል…’                   14/11/_4[የማይነበብ]

‘…ተወደደውን ሕዝባችንን መርተን አሳልፈን በስልጣኔ ደረጃ ተደርሶበት የማይታወቅ እርምጃ ወደ ተገኘበት ዘመን ስለአደረስነው  …24/2/48

‘ሲወርድ ሲዋረድ የቆየውን የአገራችንን የደረጀ ቅርስ መሰረት በማድረግ የሕዝባችንን የወደፊት እድል ለማሻሻል የጀመርነውን ታላቅ የስራ ትግል ከግቡ ለማድረስ እናንተም የፓርላማ አባሎች ከፍተኛ ድካም ይጠብቃችኋል። ..23/2/51

‘ምርጦች’

‘…. ሰፊው ሕዝብ አይኑን እስኪከፍትና የፖለቲካ ንቃት… አግኝቶ የራሱ እድል ወሳኝ እስኪሆን ድረስ ….’ ጠንካራ ወታደራዊ መንግሥት ያስፈልገዋል።… መስከረም 1967

  “… እውነተኛዋን ነፃነት ትርጉምና ጥቅም በጥሞናና በዘዴ ማስረዳት ተገቢ መሆኑን እናምንበታለን፣…ግቡንም ፈጸምኩ ብሎ ልቡ የሚያርፈው የሕዝቡን ሙሉ ነጻነት በተስተካከለ መንገድ ሲያስጨብጥ ብቻ ነው።”             … 25/1/67

‘በቁጥር በጣም አነስተኛ የሆነው የተደራጀውና በፖለቲካ የነቃው ክፍል ብቻ እንደጠቅላላው የኢትዮጵያ እድል ወሳኝ ተቆጥሮ መላው የአገሪቱ ሕዝብ ሳይረዳውና ሳያምንበት የጥቂቶቹን ፍላጎት ብቻ የሚያረካ እርምጃ መውሰድ ከአለፈ የተመሰቃቀለ የአስተዳደር  ፈሊጥ የማይሻል….’ ነው።

 … የሰፊው ሕዝብ ለለውጥ መዘጋጀት እጅግ አስፈላጊነት አጥብቀን ተረድተነዋል።’   ….1/1/67

ብዙ ተመሳሳይ ጥቅሶች ለማቅረብ ይቻላል፣ የበፊቱና የአሁኑ ብዙ ተመሳሳይነት አላቸው፣ አብዛኞቹ ሰዎችም /ባለልጣኖችም/ ቢሆኑ ያው አንድ ናቸው፣ የኃይለሥላሴ ፍጥሮች፣ የመሳፍንቱ፣ የመኳንንቱ ዘመድ አዝማዶች፣ የባለስልጣኖቹ ግብረአበሮችም ዛሬም እዚያው ናቸው። አንዳንዶቹማ ከባድ ስልጣን ጨብጠዋል። በእውነት ስለ እውነት ብለን እንናገርና እነዚህ ሰዎች ለሰፊው ሕዝብ የሚጠቅም ለውጥ ሊያመጡ ይችላሉ ወይ? ምርጦቹ ዙፋን ላይ ከወጡ ወዲህ የሰፊው ሕዝብ የኑሮ ሁኔታ ምን ያህል ተለወጠ?  ለውጥ ቢኖር ብዙ ሰው ከሥራ  መባረሩና የሥራአጡ ሠራዊት በእጥፍ ማደጉ፡ ተማሪው ከትምህርቱ መቋረጡ፣ አብዛኛው ገጠሬ በረሃብ ማለቁ፣ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሚባለው ተዳክሞ የነበረው ኢኮኖሚ እንኩትኩቱ መውጣቱና አገሪቷ የመጨረሻዋ ምስኪን መሆንዋ ነው። ሰፊው ሕዝብ እንጡራ ሃብት ግን የሕዝብ ወገኖችን ለማደንና ለማሰቃየት ለአሜሪካን ከርካሳ ጅፕና እንዲሁም ‘ለምርጦችና’ ለአድርባዮቹ የቀን አበል ይፈስሳል። ሰፊው ሕዝብ በደለኞቹን የሚፋረድበት ጊዜ እሩቅ አይደለም

 
እውነተኛው ዲሞክራሲ ያሸንፋል
ድሉ የሰፊ ው ሕዝብ ነው።
 
የትግል ዜናዎች
የገብረየስ ቤኛና የእሸቱ ወልደፃድቅ መለቀቅ፡-

‘ደርጉን ተቃውማችሁ ፣ ትእዛዙን  ጣሳችሁ፣ ከህግ ወጭ ተሰበሰባችሁ ወዘተ.’ በመባል ብዙ ሥራዎች ደማቸው እንደ ጎርፍ ሲፈስ፣ ተራማጆችና ተማሪዎች ሲደበደቡ፣ ሲታሰሩና ከቀድሞ ጨቋኞች ጋር በጨለማ ቤት ሲታጎሩ፣ ሁለት ቀንዳም ዘራፊዎችና አጭበርባሪዎች ባለፈው ሳምንት በነጻ ተለቀቁ።

የአማልጋሜትድ ኩባንያ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ፡ ገብረየስ ቤኛ ከቀድሞ ባለልጣኖች ጋር በመሻረክና በመመሳጠር የሰፊውን ሕዝብ አንጡራ ኃብት ሲገፍፍ ቆይቷል።ገብረየስ ቤኛ ከቀድሞ ልማት ባንክ ዋና ሥራ አስኪያጅ ከአሰፋ ደምሴና ከሌሎቹም መስሎቹ ጋር በነበረው የጥቅም መመሳጠር ባለፈው ዓመት ማዳበሪያ ለማስመጣት ካደረገው ውል ውጭ አንድ ሚሊዮን ብር ያህል የዘረፈ መሆኑ የይፋ ሚስጢር ነው። ገብረየስ ቤኛ ለጥቂት ቀናት ያህል ተይዞ ያለምንም ቅጣት የቀድሞ ሥራውን ጀምሯል። ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ?

በአሩሲ ክፍለ አገር ለብዙ ዓመታት የዴራ መዘጋጃ ቤት ሹም የነበረው ትልቁ ገበሬ እሸቱ ወልደጻድቅ የጭሰኞችና የድሃ ገበሬዎች ጠላት መሆኑ የታወቀ ነው። በዛሬው ጊዜ 46 ጋሻ መሬት ለብቻው ይዞ የሚያርሰው ባንድ በኩል የመንግሥት ሠራተኛ በሌላ በኩል ዲታ ገበሬ ሥራ ከጀመረ አንስቶ ጠቅላላ ደሞዙ ከ46 ሺ የማይበልጠው በአሁኑ ጊዜ ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ ሀብት አከማችቷል። የዚህ ዘረፋና ፀረጭሰኛ መለቀቅ የሚያስገርም ነው።

የሰፊው ሕዝብ ትግል በመስፋፋት ላይ ነው፡-

የሰፊው ሕዝብ ትግል በገጠሩ በመስፋፋትና ስር በመስደድ ላይ ነው፣ በኤርትራ፣ በትግራይ፣ በሃረር፣ በሲዳሞ፣በባሌ፣ በቤጌምድር፣ በጎጃምና በሌሎችም ክፍለ ሀገሮች በመፋፋም ላይ ነው። በከምባታ፣ በወላሞ፣ በሲዳማ፣ በደራሳ፣ በጨርጨር፣ በሃብሮ፣ በሰላሌ ወዘተ… ጭሰኞችና ድሃ ገበሬዎች ከባለ ብዙ መሬት ነፍጠኞችና ባላባቶች ጋር እየተጋጩ ናቸው።‘ምርጦቹ’ መንግሥት ወታደርና ፈጥኖ ደራሽ ልኮ ሃብታሞቹን በማገዝ ሰፊውን ሕዝብ ደብድቧል። ብዙ ጭሰኞችና ድሀ ገበሬዎች ‘ኢትዮጵያ ትቅደምን’ ተቃወማችሁ ተብለው በሃሰት ምስክር እየተመሰከረባቸው መታሰራቸው ታውቋል።

የጅማው ፋሽስታዊ ድርጊት፡-

አንድ ‘ከባድ ውሃ’ የወሰደ የንዑስ ደርግ አባል ባለፉት ቀናት ጅማ ከተማ ውስጥ አንድ ተማሪ በጥይት ገደለ። በዚህ ሕዝቡ በኃይል ከመቆጣቱም በላይ ድርጊቱ ያስቆጣቸው ተማሪዎች በማወናበጃው ዘመቻ የማይካፈሉ መሆናቸው ይነገራል።

የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ዘመቻውን ተቃወሙ፡-

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ‘የምርጦቹን’ ማስፈራራት ከምንም ሳይቆጥሩት በማወናበጃው ዘመቻ የማይሳተፉ መሆናቸውን ከፍ ባለ የድምጽ ብልጫ ወሰኑ። ተቃውሟቸዉ ዘመቻ ጨርሶ አያስፈልግም በማለት ሳይሆን ጊዜያዊ ህዝባዊ መንግሥት ሳይቋቋምና የሰፊው ሕዝብ መሰረታዊ መብቶች በሥራ ላይ ሳይውሉ ለሰፊው ሕዝብ ጠቃሚ የሆነ ዘመቻ ማድረግ አይቻልም በማለት ነው።

የጳጳሳት ፍቅረ ንዋይ፡-

በከተማው ሕዝብና በተማሪዎች በተደረገው ስብሰባ የክፍለ ሀገሩ ጳጳስ የሃይማኖት ኃላፊነታቸውን ዘንግተው በአስተዳደር ከመባለጋቸውም በላይ ከፍተኛ የብዝበዛ ተግባር በሕዝቡ ላይ በመፈጸማቸው በሕዝቡ በይፋ ተወቀሱ፣ ተገሰጹ፣ አቡኑም እንደማፈርና እንደመፍራት ብለው ከክፍለህ ሃገሩ ኮብልለው ጠፍተዋል። አቡነ ቴዎፍሎስን በተመሳሳይ ወንጀል ባለፈው ቅዳሜ እንዲነሱ ተጠይቀው ነበር።

[የአሜሪካን ዶላር ላይ ያለው ምልክትና የ ‘ኢትዮጵያ ትቅደም’ ዓርማ ሰዕል]

‘ኢትዮጵያ ትቅደም’ የሚለው ዘይቤ ‘አሜሪካ ትቅደም’ ከሚለው ፋሽስት አባባል የተቀዳ መሆኑ የታወቀ ነው። በዚህ ስዕል እንደሚታየው የኢትዮጵያን ሕዝብ ለማስፈራራት የምትሃት፣ የአስማትና የሟርት መሰል ዘዴ በመጠቀም በኢትዮጵያ ካርታ ላይ የደርግ ቆብ ደፍቶ የሚያፈጠው አይን ከአሜሪካ አንድ ብር ላይ የተቀዳ ይመስላል። የኢትዮጵያ ሰፊ የሕዝብ ይቅደም ማለቱ የበለጠ ተቀባይነት ኖሮት የእውነተኛ ኢትዮጵያዊነት ምልክት ይሆን ነበር።

Scroll to Top