ልዩ እትም 3 1967

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ልዩ እትም፣      ግንቦት 28፣ 1967

የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ

“መሬት ላራሹ” ከታወጀና ተማሪዎች “በእድገት በኅብረት” ዘመቻ በየገጠሩ ከተሰማሩ በኋላ፣ በገጠርም በከተማም ለዴሞክራሲ የሚደረገው ትግል ተፋፋመ። በዚህን ጊዜ ደርጉ ይህንን የሕዝብ መነሳሳት ከማገዝ ይልቅ ከአድሃሪያን ኃይሎች ጋር በመሆን ትግሉን ማፈን ጀመረ። የደርግ አባላት በየመስሪያ ቤቱና በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች እየተዘዋወሩ ተራማጆችና ተማሪዎችን “አድሃሪ” በማለት ኮነኑ። ከዚያም አልፈው በርካታ ተማሪዎች አሰሩ። በየክፍለ ሃገሩ ያሉ ተራማጅ አስተዳዳሪዎችና የመሬት ይዞታ ሠራተኞች ከስራ ገበታቸው ተባረሩ። መኢሶን በዚህ ልዩ እትሙ አገሪቱ ያለችበትን ሁኔታ ከዘረዘረ በኋላ አብዮቱን ከመቀልበስ አደጋ ለማዳን፣ለዴሞክራሲ የሚደረገው ትግል መፋፋም እንዳለበት አጥብቆ ያሳስባል።

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ለሰፊው ሕዝብ ሰራተኛ ገበሬ፣ ነጋዴ፣ ወታደር፣ ምሁር መብትና ጥቅም የሚታገል ጋዜጣ

የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ይቅደም

 
ልዩ እትም                                                                    ቀን 28/9/67

 

ለዴሞክራሲያዊ መብቶች የሚደረገው ትግል በመፋፋም ላይ ነው።

እንግፋበት!

እነዚህ ቃላት በሚፃፉበት ወቅት ቁጥራቸው ከአምስት ሺህ በላይ የሚሆን ወጣት ተማሪዎችንና ዘማች የሰፊው ሕዝብ ልጆች በጊዜያዊው ወታደራዊ መንግሥት እስር ቤቶች በመሰቃየት ላይ ናቸው። ከሁሉ አስቀድመን ለመግለጽ የምንፈልገው አንድ ሃቅ አለ። በአሁኑ ጊዜ ‘ተራማጅ ነኝ’ የሚለው ደርግ ትእዛዝ ከታሰሩት የሕዝብ ደም መጣጮችና አድሃሪዎች ይልቅ በየጦር ሰፈሩና በየፖሊስ ጣቢያው የሚማቅቁት ተራማጅ የሕዝብ ልጆች ቁጥር እጥፍ ድርብ መሆኑን ነው።

በአድሃሪዎች ሙሉ ቁጥጥር ስር እየገባ በመሄድ ላይ ያለው ደርግ የስመ ጥፉውን የኃይለሥላሴን ዘመን አፈሳ መጀመሩ ከአስራ አምስት ቀን ወዲህ በከፍተኛ ተቃውሞ እየተፋፋመ የሄደው የሕዝብ ትግል አስጨንቆ እንደያዘው ያሳያል። ይህንን ትግል ለማፈን መጀመሪያ በአፈጻድቅ ፕሮፖጋንዳ ሞከረ። አልሰራም። በየድርጅቱና በየፋብሪካው ‘ገለጣ’ እያለ ቢዞር መጋለጥ ብቻ እየሆነ አስቸገረው። ከዚያም ማስፈራራት ጀመረ፣ ግራም ቀኝም ሳይለይ ሁሉን ‘አድሃሪ’ ሁሉን ‘አታውቅም ዝም በል’ ሁሉን ‘ኢትዮጵያ ትቅደም ሰይፍ ይመዘዝብሃል’ ሁሉን ‘ተኩላ ባህታዊ’ እያለ የሰፊውን ሕዝብ ወገን ለመከፋፈል፣ ጥርጣሬ ለመንዛት፣ ለማስፈራራት ሞከረ። በዚህ በኩል በያለበት የደረሰበትን ኪሳራ ሁላችንም እናውቀዋለን። አሁን የሕዝቡን ትግል ማወናበድና ማስፈራራት አላግደው ስላለ ተማሪዎችን እያፈሰ ማጎር ጀመረ። አንድ መንግሥት አፈጻድቅ ፕሮፖጋንዳናቱ አላዋጣህ ብሎት ይህንን የመሰለ ፋሽስታዊ ድርጊት ለመውሰድ ሲገደድ የሕዝብ ትግል አይሎበት መቋቋም እንዳቃተው እንጂ በምንም አይነት ኃይለኝነቱን አያሳይም።

ዛሬ በእስር ቤት የሚማቅቁት እህቶቻችንና ወንድሞቻችን ያቀረቧቸው ጥያቄዎች ከሰፊው ሕዝብ ጥያቄዎች ተለይተው አይታዩም። ስመ ጥፉው ኃይለሥላሴ እጅ እጅ እስኪለን ድረስ ባሰለቸን አነጋገር ዛሬ በአድሃሪዎች በመጥለቅለቅ ላይ ያለው የአድሃሪዎች ደርግ ‘ጥቂት ተማሪዎች’ እያለ የሰፊውን ተማሪ ትግል ለማንቋሸሽ ቢሞክር ከራሱ በቀር የሚያታልለው ማንም የለም። የለመድነው፣ የምናውቀው፣ የሰለቸን፣ ቋቅ ያለን አነጋገር ነውና።

በመሠረቱ ታጋዮች ተማሪዎች ያነሷቸው ጥያቄዎች የዲሞክራሲ መብቶች ጥያቄዎች ናቸው። በእነዚህ ጥያቄዎች ደግሞ ዛሬ ያልተሰለፈ የሰፊው ሕዝብ ወገን ስለሌለ 90 በመቶ የኢትዮጵያ ሕዝብ አብሯቸው ነው። ግንቦት 2 ቀን ጠቅላላ ጉባኤውን የፈጸመው የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር የደርጉን ፀረ ዴሞክራሲያዊ ድርጊቶች በጥብቅ አውግዞ ለሰፊው ሕዝብ ወገኖች እነዚህ መብቶች ያለአንዳች ገደብ እንዲታወጁ ጠይቋል። ይህ ካልሆነ ደግሞ ያላንዳች ማወላወል በትግሉ እንደሚገፋ አስታውቋል። በኢትዮጵያ ገጠር ተሰማርተው የሁላችንንም አድናቆት ባተረፈ ቀልጣፋነት ከሕዝቡ ጋር በመወሃድ ላይ ያሉት ዘማቾች በሙሉ እነዚህ መብቶች ከስራ ላይ እንዲውሉ ጠይቀዋል።  ለዚህም በመታገል ላይ ናቸው። ባለፈው የወዛደሮች ቀን ወዛደሩና ጠቅላላው ተራማጅ የተሰለፉባቸው መፈክሮች እነዚህ ሲሆኑ አንዳንዶቹን ለመጥቀስ ያህል፡- ‘የጽሁፍ፣ የመናገር፣ የመስብሰብ መብቶች ይሰጡን’ ‘የሕዝብ ተሳትፎ የሌለበት ሶሻሊዝም የለም’ ‘ፀረ-ዲሞክራሲያዊ እርምጃዎች ይወገዙ’ ‘የሰፊው ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ መብቶች ይከበሩ’ የሚሉ ነበሩ።  ከዚያም ትግሉ ተፋፍሞ ባለፈው ሳምንት ውስጥ የደርጉ አባሎች ‘ገለጣ’ እያሉ በየመስሪያ ቤቱ ሲዞሩ የተፋጠጡበትና የተጋለጡበት ይኸው የዲሞክራሲያዊ ጥያቄ ነበር። እግራቸው በረገጠበት መስሪያ ቤት፣ ፋብሪካ፣ ድርጅት በሙሉ ወዛደሩና ሌሎችም ተራማጆች (የአየር መንገድ ሰራተኞች፣ የምድር ባቡር፣ የኮካኮላ ፋብሪካ፣ የፍርድ ሚኒስቴር፣ የሥራና የመገናኛ፣ የብሔራዊ ኃብት ልማት፣ የቴሌኮሙኒኬሽን፣ የመሬት ይዞታ፣ የጥጥ ፋብሪካ…. ሰራተኞች) በያሉበት የታገሉት ለእነዚህ ጥያቄዎች ነበር ።

በአጭሩ ዛሬ ዲሞክራሲ የሰፊ ሕዝብ እንጂ ‘የጥቂት ተማሪዎች’ ጥያቄ አይደለም። ስለዚህ ትላንት እነኃይለሥላሴ ‘መሬት ላራሹን’ የጥቂት ተማሪዎች ሴራ ይሉ እንደነበረው ዛሬ ይህን የዲሞክራሲ ጥያቄ ‘የጥቂት ተማሪዎች’ ጥያቄ ለማስመሰል መሞከር ጨርሶ ማወናበድ ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ ደርጉ እንደሚሞክረው የሰፊውን የኢትዮጵያ ተማሪ ትግል ‘አድሃሪ’ ብሎ ማሰናበትም ከንቱ ሙከራ ነው። ለ15 ዓመታት ሙሉ የኃይለሥላሴን የፕሮፓጋንዳ፡ የጦርና የፖሊስ ጥይት- ዝናብ ተጋፍጦ፡ የእስራትና የግርፋት መከራ ተቀብሎ በግንባር ቀደምትነት የተሰለፈውንና በመላ አፍሪካ ወደር የሌለውን ስመ ጥሩን የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ በጥቂት አድሃሪዎች ይመራል ማለት እንደታላቅ ስድብ የምንቆጥረው አነጋገር ነው። እርግጥ ተማሪው ንቅናቄ ውስጥ አንዳንድ ሰርጎ ገብ አድሃሪዎች መኖራቸው አይካድም። ነገሩ ከመስመር የሚወጣው ራሱ በአድሃሪዎች ባህር እየተጥለቀለቀ በማዋኘት ላይ ያለው ደርግ በተራማጁ የተማሪ ንቅናቄ ባህር ውስጥ ከጠብታ የማያልፉትን አድሃሪ ግለሰቦች የሰፊው ተማሪ ንቅናቄ መልክ ወሳኞች አድርጎ ሲወስዳቸው ነው። ደግሞስ በአሁኑ ጊዜ ከደርጉ ከራሱ አንስቶ አድሃሪዎች የሌሉበት ማን አለ? እንዲያውስ ተማሪውም ሆነ ሰፊው ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ መብቶቹን የሚጠይቀው በየመስሪያ ቤቱ አድሃሪ ቢሮክራቶችን ለመፈንቀል፣ በያለበት አድሃሪዎችን እያጋለጠ ከትግሉ በመነጠል አይደለም እንዴ! የደርጉስ አድሃሪዎች ዛሬ ዲሞክራሲን ከጦር የሚፈሩት ዴሞክራሲ ከታወጀ ተሸፋፍነን ማወናበድ ይቸግርና እንጋለጣለን ብለው በመፍራት አይደለም እንዴ! ሰፊው ተማሪና ሰፊው ሕዝብ በአንድ በኩል፡ አድሃሪ ኃይሎችና ደርጉ በሌላ በኩል ሆነው እየተሰለፉ የሄዱበት ይህ የዲሞክራሲ ጥያቄ ዛሬ ከመጠን በላይ እየከረረና እየተፋፋመ የሚሄድ ለሁለቱም ወገን ግን የሞት ወይም የሽረት ትግል ሆኗል።

በባላገሩ ይህ ጥያቄ ተፋፍሟል። በዘማቹ፡ በተራማጅ አስተዳዳሪዎችንና በአርሶበለው የህብረት ተጋድሎ የተነሳ ከደርጉ ቁጥጥር ውጭ አንዳንድ ዴሞክራሲያዊ መብቶች ከሥራ ላይ በመዋል ላይ ናቸው። በሕዝቡ ትግል ታልፎ ከሄደ በኋላ ቱስ ቱስ ማለት የጀመረው ደርግ ግን ከአድሃሪዎች ጋር በመተባበር ዲሞክራሲን ለማፈን በመፍጨርጨር ላይ ነው። ትግሉ በከረረበት ቦታ ሁሉ ለአድሃሪዎች እያገዘ ተራማጅ አስተዳዳሪዎችን ከሥራ ያባርራል። በከፋ፣ በሃይቆችና ቡታጅራ የምናየው ይህንን ነው። የዘመቻ ጣቢያዎችን እንዳሉ ይዘጋል። በሃረርጌ፣ በባሌ፣ በትግራይ፣ በከፋ የምናየው ይህንን ነው።

በከተማ የሄደን እንደሆነ አስተማሪው፣ ተማሪው፣ ወዛደሩ፣ የመንግሥት ሠራተኛው፣ በጠቅላላው ተራማጁ ‘ዲሞክራሲያዊ መብቶች’ እያለ ትግሉን አፋፍሟል። በባላገር እንደሚሆነው ሁሉ በከተማም ደርጉ ፀረ-ዲሞክራሲያዊውን ወገን እየመረጠ በመጋለጥ ላይ ነው። የ5000 ወንድሞቻችንና እህቶቻችን መታፈስ ለዚህ መጋለጥ ቋሚ ምስክር ነው። ኢሰአማን አፍርሶ፡ የራሱን ሰዎች በየቦታው ከሰካካ በኋላ ‘ምርጫ አስደረግሁ’ ብሎ በቅምጦቹ የሚመራ ማህበር ለማቋቋም የጠነሰሰው አድሃሪ ሴራ ከሞላ ጎደል ከሽፏል። ተራማጁ ወገን ነቅቶ በአንድነት ተነሳስቶ ፋታ ስለነሳው የፈለገውን ‘ምርጫ’ ለማስደረግ አልቻለም። ተራማጅ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ባለማወላወል ባደረጉት ትግል የሠራተኛው ማህበር እንደገና ተከፍቷል። አድሃሪዎቹ ዲሞክራሲን ለማፈን የሚያደርጉት ሙከራ ግን አላቋረጠም። ትግሉም በዚሁ አንፃር በመቀጠሉ ደርጉ ከእንግዲህ ያለው ምርጫ ከተማውን በማጥለቅለቅ ላይ ያለውን ይህንን የዲሞክራሲ ጥያቄ እንደጀመረው በኃይል ለማፈን ሞክሮ ከሰፊው ሕዝብ ወገኖች ጨርሶ መቆራረጥና በአድሃሪዎች እጅ ተጠቃልሎ መግባት ነው። በዚህም እንደ ስመጥፉ ‘የፀጥታ ኮሚሽን’ ተዋርዶ ከታሪክ መድረክ መውረድ፣ ወይም ደግሞ ለዴሞክራሲ ከሚታገሉት ኃይሎች ጎን ተሰልፎ ትግሉን ወደፊት መግፋት ብቻ ነው።መሃል መቆምና በተፋፋመው የመደቦች ትግል በአስታራቂነት መቅረብ የማይቻል ጉዳይ ነው።

ደርጉ በአፍ ብቻ ‘የሰፊው ሕዝብ ወገን ነኝ’ እያለ ሲያላዝን አድሃሪ ኃይሎች በከተማም በገጠርም እየተጠናከሩ በመሄድ ላይ ናቸው። ለውጡን በመቃወም ከሸፈቱት አድሃሪዎች ጎን ዛሬ አሊ ሚራህም ተሰልፏል። የአፋር ሕዝብ ጨቋኝ ገዥ የነበረው ቢትወደድ አሊ ሚራህ ዛሬ ሙሉ በሙሉ ሸፍቶ ከመደብ ወንድሞቹ ተቀላቅሏል። የነዚህ  አድሃሪ ኃይሎች መጠናከር የርስ በርስ ጦርነትን መከፈት በግልፅ ያሳያል። በደርጉ ወላዋይነትና ፀረ-ዲሞክራሲያዊነት ብቻ ሰፊው ሕዝብ ሳይደረጅና ሳይዘጋጅ በዚህ ጦርነት ውስጥ መግባቱ በጣም የሚያሳዝን ነው። የደርጉ ምርጫ ይህ መሆኑ እጅግ አሳፋሪ ነው።

ደርጉ የመረጠውን ቢመርጥ የኢትዮጵያ ተማሪዎችና የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ትግላቸውን ለመጀመር እሱን እንዳልጠበቁ ሁሉ አሁንም ከሱ ጋር ትግላቸው አያከትምም። ለዴሞክራሲ የሚደረገው ትግል ይፋፋማል እንጂ አያቆምም። ዲሞክራሲ አድሃሪና ተራማጅ መሳይ ሁሉ በሰፊው ሕዝብ ፊት የሚገለጥበት፣ ሕዝቡ የሚማርበትና የሚደራጅበት የትግል መሣሪያ ነው። ይህንን እኛም እናውቀዋለን፣ አድሃሪዎችም፣ አወናባጆችም፣ የአዋጅ ሶሻሊስቶችም ያውቁታል። ሰፊው ሕዝብ ይህንን ጥያቄ የሙጥኝ ብሎ የያዘው፣ ጠላቶቹ ደግሞ ከጦር የሚፈሩት በዚሁ የተነሳ  ነው። በሁለታችንም በኩል የሞት ወይም የሽረት ጥያቄ ነው፣ የመደቦች ችግል ነው እንግፋበት!

ካለፉት ከአስራአምስት ቀናት ወዲህ በጠቅላላው በገጠሩ፣ በየመስሪያ ቤቱ፣ በየፋብሪካው፣ በየት/ቤቱና በልዩ ልዩ ማህበራት እየተቀጣጠለ በመፋፋም ላይ ያለው ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የሚደረገው ትግል ያለማቋረጥ መግፋት አለበት። በየመስኩ የምንገኝ ተራማጆች በአንድነት ተጋግዘን ካልታገልን ይህንን መብት አዝኖ የሚወረውርልን የለም። አሁኑኑ ትግላችንን አፋፍመን የአድሃሪዎቹን ሴራ በጊዜው ካላከሸፍነው ሪቮሉሽኑ ወደኋላ የሚወረወርበት ታላቅ አደጋ አለ። ከያለበት፣ከመስሪያ ቤት መስሪያ ቤት፣ ከፋብሪካ ፋብሪካ፣ ከድርጅት ድርጅት፣ ኃይላችንን እናስተባብር። አድሀሪዎች እንዳይቀድሙን። ፋታ አንስጣቸው!

በያለንበት ተማሪዎች እንዲፈቱ እንጠይቅ
በያለንበት ተራማጆች እንዲፈቱ እንጠይቅ
ለዴሞክራሲያዊ መብቶች ትግሉ ይፋፋም
የኢትዮጵያ ሕዝብ ያሸንፋል።
Scroll to Top