የሰፊው ሕዝብ ድምፅ
ልዩ እትም፣ ታህሣሥ 10፣ 1972
የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ
ይህ ልዩ እትም፣ “የሠርቶ አደሩ ፓርቲ አደራጅ ኮሚሺን” በማለት የተመሠረተው ተቋም፣ ደርግ ስሙን ቀይሮ የወዛደሩ ፓርቲ ነኝ ለማለት የፈጠረው ማጭበርበሪያ ሂደት አካል እንደሆነ ያጋልጣል። መኢሶን ይህ ብዙ ሠራተኞችን ያሰረ፣ በሕዝቡ ላይ ከፍተኛ በደል የፈጸመ፣ በጭቁን ብሄረሰቦች ላይ ጭፍጨፋ ያካሄደ ድርጅት የኢትዮጵያ ሕዝቦች ተባብረው የሚፈጥሩትን አብዮታዊ ድርጀት እንደማይተካ ያስገነዝባል። እንዲያውም ይህ ኮሚሺን ራሱ ለዴሞክራሲ፣ ለብሄራዊ ነጻነትና ለብሄረሰቦች እኩልነት የሚታገሉ ኃይሎች ጠላት ስለሆነ የኢትዮጵያ ህዝቦች በአንድነት እንዲታገሉት ጥሪ ያቀርባል።ከዚያም አክሎ፣በየፋብሪካው በየማሳውና በየቦታው የሚቋቋመው እውነተኛውን የወዛደር ፓርቲ ለመስረት የተያያዝነውን ትግል እጥፍ ድርብ ማድረግ እንዳለብን ያሳስባል።
ራሱን “የኢትዮጵያ ሠርቶ አደር ፓርቲ አደራጅ ኮሚሽን” ብሎ የሰየመ አንድ ጉድ በታህሣሥ 8 1972 ዓ.ም. ታውጇል። “እምርታ” እንበለው?
አብዮቱንና የኢትዮጵያን ብሄራዊ ነፃነት ከድቶ፣ ከአብዮቱ ጠላቶችና ለብሄራዊ ክብራችን ጠንቅ ከሆኑ የውጭ ኃይሎች ጋር የታመሰው “ጊዜያዊ” ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ፣ ዛሬ ስሙን ቀይሮ ከ“ሰርቶ አደር ፓርቲ” ተመሳስሎ ሲመጣ፣ የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብና ሃቀኛ ማርክሲስት ሌኒኒስቶች “መልከ ጥፉ በስመ ይደግፉ” ከማለት ሌላ ምን ይጨምሩለታል?? ደግሞስ፣ የባሰ አለ እንጂ። ከማርክሲስት ሌኒኒስቶችም አልፎ የኢትዮጵያ ዲሞክራቶችና አገር ወዳዶች በመቶ እየቆጠረ የረሸነ፣ በሺህ እያፈሰ በየእሥር ቤቱ እያጎረ፣ በጭቁን ብሄረሰቦች ላይ ታሪካችን አይቶት የማያውቀውን ጭፍጨፋ ያካሄደና የሚያካሂድ ደርግ፣ ዲሞክራሲያዊነቱንና አገር ወዳድነቱን አሟጦ ገበናው ከተጋለጠ በኋላ፣ ዛሬ “የሰርቶ አደሩን ፓርቲ” አደራጃለሁ፣ ለዚህ “ኮሚሽን” ፈጥሬአለሁ ቢል፣ የወዝአደሩ መደብና የኢትዮጵያ ሃቀኛ ተራማጆች “ፅድቁ ቀርቶብሽ በቅጡ በኮነኑሽ” ከሚለው የአባቶች ተረት ሌላ ምን ሊሉት ይችላሉ??
ባጭሩ እንናገረው። የኢትዮጵያ ጭቁን ሕዝቦች ዲሞክራሲ፣ ብልፅግና፣ ፍትህ፣ ብሄራዊ ክብርና ሰላም የሰፈነበትን ህልውናን እንዲያገኙ ይሆናል ብለው ያለ የሌለ ተስፋቸውን የጣሉበትና ይህ ነው የማይባል መስዋአትነት እየከፈሉ የተዋደቁለት የኢትዮጵያ ወዛደሮች ፓርቲ ይህኛው ሳይሆን፣ ያ ገና በትግላችን ገፍተን የኢትዮጵያ ግንባር ቀደም ወዛደሮች፣ አርሶአደሮች፣ አብዮታዊ ምሁራንና መለዮለባሾች ተባብረን የምንመሰርተው አብዮታዊ ድርጅት ብቻ እንደሚሆን እንኳን እኛና አዋጅ አስነጋሪዎቹም ያውቁታል።
ይህ “የሰርቶአደር ፓርቲ” አደራጅ የተባለ “ኮሚሽን” ግን፣ ከአጠቃላዩና ከሃቀኛው የወዝአደር ፓርቲ አፈጣጠር ዘዴ ውጭ የተቋቋመ፣ ተጨባጭ ሁኔታ ከሚጠይቀውና የኢትዮጵያ ማርክሲስት ሌኒኒስቶች ከተለሙት ሂደት ተቃርኖ የተፈጠረ፣ በሚከተለው ፖለቲካ፣ ታክቲክና ስትራቴጂ ፀረ ሕዝብና ፀረ አብዮት የሚነግሥና የሚያደላድል ነው። በኢትዮጵያ ጭቁን ሕዝቦች ዲሞክራሲያዊ አብዮትና በእናት አገራችን ክብር ጣረሞት ላይ ፀረ ሕዝቦች ተጠራርተው ያወጁት የጭቆና መሣሪያ ነው።
ግን ደግሞ፣ የኢትዮጵያ ማርክሲስት ሌኒኒስቶች ይህንን “ድርጅት” የሚቃወሙት “ለምን የወዛደር ፓርቲ አልሆንኩም” ብለው አይደለም። እዚህ ላይ ግልጽ መሆን ያስፈልጋል።
በዛሬይቱ ኢትዮጵያ አንድ ፓርቲ ወይንም አንድ ድርጅት ሲቋቋም፣ ገና ለገና “ለምን የወዝአደር ፓርቲ አልሆንኩም” ተብሎ አይንህን ላፈር አይባልም። መኢሶን እንኳን ዛሬ ፀረ አብዮት በነገሰበት ዘመን ቀርቶ፣ በአብዮቱ አጥቂነትና የዲሞክራሲ ዘመን ሳይቀር እየደጋገመ ይል እንደነበረው፣ የኢትዮጵያ አብዮት ግቡን የሚመታው በወዝአደሩ ፓርቲ መፈጠር ብቻ ሳይሆን፣ ሌሎች ዲሞክራሲያዊና አገር ወዳድ ኃይሎች ሁሉ በነፃና በዲሞክራሲያዊ መንገድ ተደራጅተውና የአብዮቱ ኃይሎችና ወዳጆች ሁሉ በጋራ የአላማና የትግል መድረክ ላይ በእኩልነት ተባብረው በሚመሰርቱት ሕዝባዊ አብዮታዊ ግንባር ነው። ይህ ትክክለኛ የትግል መስመር ከመኢሶን ፕሮግራም አልፎ፣ በሚያዚያ ወር 1968 ዓ.ም. በመጣው “የኢትዯጵያ ብሄራዊ ዲሞክራሲዊ አብዮት ፕሮግራም” ላይ በግልጽ ቋንቋ ሰፍሯል። መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ያውቀዋል። ስለሆነም ደግሞ፣ መኢሶን ይህንን “የሰርቶአደር ፓርቲ” አደራጅ ነኝ ባይ “ኮሚሽን” የሚቃወመው፣ ለምን የወዛደሩ መደብ ፓርቲ አልሆንክም በማለት ሳይሆን፣ በአመሰራረቱ ሆነ በሚከተለው ፖለቲካ፣ ታክቲክና ስርታቴጂ የብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራምን የሚፃረር፣ ፀረ ዲሞክራሲያዊ፣ ፀረ ሕዝብ፣ ፀረ አብዮትና ፀረ ብሄራዊ ክብር “ድርጅት” በመሆኑ ነው።
እዚህ ላይ እንቆይና፣ ከዚህ ትንተናችን የሚመነጨውን ተጨባጭ ተግባር ካሁኑ ግልጽ እናድርግ። እርግጥ የኢትዮጵያ ማርክሲስት ሌኒኒስቶች ይህን “የሠርቶ አደር ፓርቲ” አደራጅ ነኝ ባይ አካል፣ ልክ በኢህአፓው ዘመን እንዳደረጉት፣ የርዕዮተአለም አቋሙን፣ የፖለቲካ መስመሩን፣ የትግል ታክቲኩንና ስትራተጂውን፣ በጠቅላላው ምንነቱንና የእድገት አቅጣጫውን ከማርክሲዝም ሌኒኒዝም አንፃር እየተነተኑ ያጋልጡታል፣ ይዋጉታል። ነገር ግን መኢሶን ትግሉን “በማርክሲስቶች መካከል” ብቻ የሚደረግ ትግል እንዳልሆነ አጥብቆ ያውቃል። ሌሎች ሀቀኛ ተራማጆች፣ አገር ወዳዶችና ዲሞክራቶችም ደግሞ፣ ይህንን ትግል “በማርክሲስቶች መካከል” ብቻ እንደሚደረግ ትግል አድርገው መውሰድ የለባቸውም። ይህ የቀኝ ኃይሎች ህብረት በዘረጋው ወጥመድ ውስጥ መውደቅ ይሆናል።
ዛሬ ራሱን “በሠርቶ አደሩ ፓርቲ” አዋላጅነት ዱብ ያለው “ኮሚሽን”፣ ለዲሞክራሲና ለብሄራዊ ነፃነታችን፣ ለብሄረሰቦች እኩልነትና ለአብዮቱ ኃይሎችና ወዳጆች ሁሉ ፀር የሆነ ድርጅት ነው። ጥቂት የሥልጣንና የክብር ጥም ያናወዛቸው ግለሰቦች “በእከክልኝ ልከክልህ” የመሰረቱት ድርጅት ነው። በሌላው በኩል፣ ለብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራም የቆሙት ኃይሎች ግን ሚሊዮኖች ናቸው። እነዚህ በተያያዙት የትግል ምእራፍ ይገፉበታል። በሺህና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወዛደሮች፣ አርሶአደሮች፣ አብዮታዊ ምሁራን፣ መለዮ ለባሾች፣ የጭቁን ብሄረሰብ ታጋዮች፣ አገር ወዳዶች፣ ዲሞክራቶች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች…በኢትዮጵያ ብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራም መድረክ ላይ ተሰብስበውና ኃይላቸውን አስተባብረው ይነሳሉ። የሃቀኛ ማርክሲስቶች፣ አገር ወዳዶች፣ ዲሞክራቶችና የጭቁን ብሄረሰብ ታጋዮች የዛሬው መሰረታዊ ተግባርም፣ እነዚህን ሚሊዮኖች በገጠር ይሁን በከተማ፣ በአገር ውስጥ ይሁን ከአገር ውጭ በሰፊ የተግባር መድረኮች ላይ አስተባብሮ በዲሞክራሲያዊውና በአብዮታዊው የትግል ጎዳና መግፋት ነው። ስለሆነም፣…
መኢሶን በዚህ አንፃር ያለበትን የታሪክ ግዴታና ሃላፊነት በአንክሮ በመገንዘብ፣ በዚሁ አጋጣሚ አባሎቹ፣ ወዳጆቹና ደጋፊዎቹ ሁሉ የሚጠበቁባቸውን ተግባሮች ሁሉ ያለአንዳች ቸልተኝነት እንዲያሟላ ግልጽ መመሪያ አስተላልፎላቸዋል። እንደዚሁም፣ በብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራም መድረክ ላይ ቆመው ለሚዋደቁት ኃይሎች ሁሉ፣ ከመቸውም ጊዜ ይበልጥ ዛሬ እንዲሰባሰቡና ኃይላቸውን እንዲያስተባብሩ ደጋግሞ ያቀረበውን ጥሪ እንደገና ያድስላቸዋል።
**** * ****
አዎን፣ ይህ የሰዎቹ “የሠርቶ አደር ፓርቲ አደራጅ ኮሚሽን” እኛ ከምናውቀው ሠርቶ አደር ሕዝብ ጋር የሚያገኘው ቤሳ ነገር የለም። ይህ “ኮሚሽናቸው” ከመጀመሪያው የተቋቋመው፣ የወዝአደሩን መደብ ርዕዮተአለም በርዞና ከልሶ ነው። ይህች አገራችን በስንት መከራ ያፈራቻቸው ማርክሲስት ሌኒኒስቶች ከተጨፈጨፉና ያለዚያም በየእሥር ቤቱ እየተወረወሩ ከታጎሩ በኋላ ነው። ስንት በነፃ የተደራጁ ተራማጅ ድርጅቶች በተራ መግለጫና በጉልበት እንዲፈርሱ ከተደረገ በኋላ ነው። እንደዚሁም፣ የኢትዮጵያ አብዯት በአፍላነት ይገሰግስ በነረበት ወቅት፣ “ማርክሲስት ነን” ይሉ የነበሩት ድርጅቶች ሁሉ፣ የወዝአደሩን ፓርቲ ተባብረው ለማቋቋም የመሰረቱት የህብረትና የጋራ የትግል መድረክ (ኢማሌድህ) ምንሽርሽሩ ከወጣ በኋላ ነው። በመጨረሻም በዚህ ሂደት ውስጥ፣ በአብዮትና በሶሻሊዝም ስም እየተናገረ ፀረ አብዮትን የሠራው የቀኘ ኃይሎች ህብረት በተጠናከረበት ወቅት ነው።
ነገር ግን ደግሞ ባሰ አለ። ይህ “የሠርቶ አደር ፓርቲ አደራጅ ኮሚሽን” የተባለነገር የተቋቋመው ራሱ የወዛደሩ መደብ፣ ራሱ የሰርቶ አደሩ ሕዝብ በቀኝ ኃይሎች ህብረት እርግጫና ፈላጭ ቆራጭነት የቁም ስቃዩን በሚያይበት ወቅት ነው።
የቀኝ ኃይሎች ህብረት መተባበር የጀመሩትን ማርክሲስት ሌኒኒስቶች በማራራቅ፣ ውይይት የሚፈልጉትን በማፈን. . . .ወዘተ አልተወሰነም። ሃቀኛ ማርክሲስት ሌኒንስት የሆነ ማንኛውም ኃይል ሊዋሃዳቸው የሚፈልጋቸውን ሰፋፊ የወዛደርና ሌሎች ሕዝባዊ ድርጅቶች እንዳልነበሩ አድርጎ አውድሟቸዋል። “ለወዛደሩ የፖለቲካ ትግል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል” የተባለለት መኢሠማ ለአድሃሪዎች አላጎበድድ በማለቱ ከኢህአፓ ርሸና የተረፉት መሪዎቹ በየእሥር ቤቱ ታጎሩ። ከፋብሪካ አንስቶ እስከ ላይ ድረስ ያሉትን ታጋይ ወዛደሮች በየእሥር ቤቱ አጉሮ (ዛሬ በዚህ በስመ ጥፉ “ኮሚሽን” በሚመራው መንግሥት እሥር ቤቶች ውስጥ አራት ሺህ ታጋይ ወዝአደሮች እንደሚገኙ ማን ይረሳል?)፣ የወዝአደሩን እንቅስቃሴ በተራ ሹም ሽር አራቁቶ፣ በዲሞክራሲያዊ ዘዴ የተመረጡትን መሪዎች ሁሉ አስወግዶ፣ በቦታቸው የቢሮክራሲውን ሹማምን ተክሎባቸዋል። ሌሎችንም “ይደጉ፣ ያብቡ” ይባሉ የነበሩትን የአብዮታችን ፍሬና የአብዮታችን አራማጅ ኃይል የነበሩትን ሕዝባዊ ድርጅቶች በዚሁ መልክ አፈራርሷቸዋል። ባለፉት ሁለት ዓመቶች፣ የቀኝ ኃይሎች ህብረት የኢትዮጵያን ወዛደሮች ታጋይ መሪዎቻቸውን ከጉያቸው እየወሰደ በማሰርና በመረሸን አልተወሰነም። ከዚህ ጋር አብሮ፣ የኢትዮጵያ ወዛደሮች ከየካቲት ወዲህ በደማቸው እየከፈሉ የተቀዳጇቸውን ድሎች ሁሉ አንድ በአንድ ነጥቋቸዋል። እየነጠቃቸውም ነው። ኢህአፓ “የባርነት አዋጅ” ብሎ እያንቋቋሸ የተዋጋው የሠረተኛ ጉዳይ አዋጅ፣ አንቀጽ በአንቀጽ በድርጊትና በውስጥ መመሪያዎች እየሻረ በይፋ ሊበርዘው ዳር ዳር በማለት ላይ ነው። የኢትዮጵያ ወዛደሮች ጥረን ግረን ወግ ያለው ኑሮ እንኑር፣ የገዛ እድላችንን እጃችን እናስገባ እያሉ ከአድሃሪዎችና ከአሻጥረኞች ጋር በተዋደቁ፣ “በዲሲፕሊንና በምርት ዘመቻ” ስም ከፍ ያለ ፀረ ወዝአደር ቅስቀሳ እየተካሄደባቸው ነው። ለዚህ አብዮት እንዳልተዋደቁ፣ ለአብዮቱ መግፋት ሲሉ ያንን ያህል እንዳልተራቆቱ፣ ለዚህች ውድ አገራችን ክብርና ነፃነት በግንባር ቀደምነት ደማቸውን እንዳላፈሰሱና እንዳልተሰው፣ ከአንጀታቸውና ከልጆቻቸው ጉሮሮ እየነጠቁ ያቅማቸውን አንዳልሰጡ፣ በ120 ብር አብዮታችንን አንለወጥም እያሉ የወዛደር ድምፃቸውን ከፍ አድርገው እንዳላሰሙ ሁሉ፣ ዛሬ “ስግብግብ”፣ “ከበርቴ ወዝአደር”፣ “ያልነቃ ወዝአደር” “በዝባዥ ወዝአደር” “..ከበስተጀርባው የሚወጉ…” ወዘተ እየተባሉ ስድብና ማንጓጠጥ ይወርድባቸዋል።
ይህ የጦፈ ፀረ ወዝአደር ቅስቀሳ ከዚህ “ሰርቶ አደር ፓርቲ” ነኝ ባይ ድርጅት መፈጠር ሂደት ጋር አብሮ እየተጧጧፈ መምጣቱ ራሱ ለዚህ ፈጣሪ ነኝ ባይ “ኮሚሽንም” ሆነ ለሚፈጠረው “የሰርቶ አደር ፓርቲ” ማንነትና ምንነት በምንም አይነት የሚያወላዳ ማረጋገጫ ነው።
በመጨረሻም፣ ይህ “የሰርቶ አደር ፓርቲ አደራጅ ኮሚሽን” የታወጀው ባጠቃላይ ደግሞ ፀረ ዲሞክራሲና ትምክህተኝነት በነገሰበት ወቅት ነው። ደጋግመን እንዳመለከትነው ጭቆናው፣ እሥራቱና ጭፍጨፋው ለእውነተኛው የወዝአደሩ ፓርቲ መፈጠር ከሚቆረቆሩቱና ከሚታገሉት ግንባር ቀደም ክፍሎች አልፎ ዲሞክራቶችን፣ አገር ወዳዶችን፣ የጭቁን ብሄረሰብ ታጋዮችንና ባጠቃላይ ሰላማዊውን ሕዝብ በመላ በሸፈነበት ወቅት ነው። የውድ አገራችን ብሄራዊ ክብር በተረገጠበትና በተገሰሰበት ወቅት ነው። የሰፊው ሕዝብ ማህበራዊና ኢኮኖሚያው ህልውና በዳሸቀበት ወቅት ነው። . . .ወዘተ. ።
ሌላም አለ እንጂ። የዚህ “የሠርቶ አደር ፓርቲ” አደራጅ “ኮሚሽን” መሥራቾች በአብዮትና በሶሻሊዝም ስም ሺህ ቢለፍፉ ይህንን “ኮሚሽናቸውን” ያወጁት ምንነታቸውና ማንነታቸው እርቃኑን ተጋልጦ ካበቃ በኋላ ነው። ወዲህ ቢገላበጡ ወደዚያ፣ በዚህ ቢኳኳሉ በዚያ፣ ቢንጎላበሱ ቢያጋጊጡ የማንንም ልብ ለመማረክ ባልቻሉበትና መሣቂያና መሣለቂያ በሆኑበት ወቅት ነው።
አላስ፣ ይህ የታወጀው ጉድ የሠራተኛው መደብ አይደለም። በዚህ ጉድ ውስጥ ከየመደቦች የፈለሱ እበላባዮችና አደርባዮች (ምናልባትም ደግሞ ተገደው የተቀላቀሉት) ቢኖርም፣ የሚፈጠረው ፓርቲ የሚሆነው በመሰረቱ የከፍተኛ የጦርና የሲቪል ቢሮክራቶች ፓርቲ ነው። ስለሆነም ደግሞ፣ “ኮሚሽኑም” የርሱም ፍጡር የሚሆነው ፓርቲ የፀረ አብዮት ፓርቲ ነው። ለዚህ የፀረ አብዮት ፓርቲ በዛሬው ጊዜ ሺህ ይነገር፣ ሺህ ይለፈፍ እንጂ፣ እኛ ደግሞ ይህ “የሰርቶ አደር ፓርቲ” አደራ ነኝ ባይ “ኮሚሽን” የታወጀበት የዛሬው ዕለት፣ በኢትዮጵያ ሕዝቦች የትግል ታሪክ ውስጥ፣ ፀረአብዮት አክሊሉን እንደደፉበት እለት ሲታሰብ እንደሚኖር ከዛሬው ልንናገር እንችላለን።
እርግጥ በሚመጡት ሳምንታቶችና ወሮች ውስጥ ለዚህ ጉድ “የድጋፍ ጎርፍ” ሲወርድለት ይሰነብታል። እጅ እጅ እስከሚለን ድረስ ገና ብዙ እንሰማለን። አያስደንቀንም። ደግሞስ ምን ያስደንቃል። በዛሬው የፀረ ዲሞክራሲና የፀረ አብዮት አመፅ ዘመን፣ ለመጭው መራራ ትግል ራሱን በማዘጋጀት ላይ የሚገኘው ትዕግስተኛውና ቆራጡ ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ዛሬ እንኳን “የሰርቶ አደር ፓርቲ. . .” ቀርቶ፣ “ንጉሠ ነገሥት ዘ…” ቢታወጅም፣ አንጀቱ እያረረ “ሙያን በህቡዕ ነው” ቢል ከቶም አያስደንቀንም። ይህ እየወደቀ መነሳት ተደጋጋሚ የታሪክ ዕጣው የሆነው ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብና አርቆ አስተዋይ የሆነው ይህ ታጋይ ትውልድ፣ ዛሬ በግማሽ እያፌዘ በግማሽ እየበገነ “ኢማሌድህ ጥንስሱ ሳይፈላ ተደፋ” እንደሚለው ሁሉ፣ ነገ ደግሞ የዛሬው “ኮሚሽንና” “የሰርቶአደር ፓርቲ” ምንነትና ማንነት በቀላል ቋንቋ አበጣጥሮ ይገለጸዋል። ያሻው ጭቆና ቢወርድ፣ ያሻው ግፍ ቢፈጸም ኩራቱና ልበሙሉነቱ ምንጊዜም የማይዳሽቀው ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብና ይህ ታጋይ ትውልድ ወደፊት እያሉ በዲሞክራሲውና በአብዮታዊው የትግል ጎዳና ይገፋሉ።
እንግዲህ አንባቢ መቼስ ይህ ተጨባጭ ሁናቴ እያለ፣ ዛሬ በአገራችን ፀረ አብዮት ነግሶ፣ ፀረ የኢትዮጵያ ክብር ኃይሎች በሃገራችን ምድር ላይ እየፋለሉ ሳለ፣ ይህንን ፓርቲያቸውን ምን ቸገራቸው “የሠርቶአደሩ ፓርቲ” ባይሉት ኖሮ ይል ይሆናል። ነገሩ፣ ሰፊው ሕዝብ የወዛደር ፓርቲ እያለ ወትውቷልና በስሙ ለመነገድ እንዲያመችና፣ ከስሙ ስልጣን አደላድሎ ክብርና ሞገስ ለዘላቂው ለመጎናፀፍ ተጠንቶ የተደረገ ነው። ግን እኮ ሞኝነት ነው።
የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ እንደሆነ፣ ባለፉት ዓመታት በቀሰመው ትምህርት፣ እነ አስፋወሰን ኃይለሥላሴ ራሳቸውን “ዲሞክራት” ብለው መጥራት ከጀመሩ ወዲህ፣ ግለሰቦችና ቡድኖች ለራሳቸው በሚሰጡት መጠሪያና ሙገሳ ባሻገር፣ ከድርጊቶቻቸውና ከሚያንፀባርቁት አቋም ተነስቶ ማንነታቸውን እየፈለፈለ ማውጣቱን አውቆበታል። የኢትዮጵያ ግንባር ቀደም ወዛደሮችና ማርክሲስት ሌኒንስቶችም መጀመሪያ በኢህአፓ፣ ከዚያም የወዛደር ሊግ፣ ማሌሪድ አብዮታዊ ሰደድ እያሉ በተፈራረቁባቸው “ማርክሲስት ሌኒንስት” ድርጅቶች ወዲህ፣ በዚህ በመጣ ነገር “የዝንብ ጠንጋራ” መለየቱን ያውቁበታል። እንግዲህ ይህ ከእንግዲህ ምን ሊቀጥሉበት??
ነገር ግን አንድ የመጨረሻ ጉዳይ።
“እከክልኝ ልከክልህ” በሚለው ፖለቲካ መሰረት ከቀኝ ኃይሎች ህብረት ጋር ተሳስረው በሃገራችን ፀረ አብዮት እንዲሰፍን፣ የኢትዮጵያ ክብር እንዲጎድፍ የተባበሩት የውጭ ኃይሎች “ከባለቤቱ ያወቀ ቡዳ ነው” እንዲሉ፣ ከኛ ከኢትዮጵያ አብዮታውያን፣ ከኛ ከኢትዮጵያ ግንባር ቀደም ወዝአደሮች ባጠቃላይም ከሰፊው ዲሞክራትና አገር ወዳድ የኢትዮጵያ ዜጋ ይበልጥ “አውቀው” ለዚህ “ኮሚሽንም” ሆነ የሚፈጥረውን “የኢትዮጵያ ሰርቶ አደር ፓርቲ” ብለው ሙሉ ድጋፋቸውን አንደሚሰጡትና እንደሚያሚካሹት ሳይታለም የተፈታ ነገረ ነው። ይሁንና በዚህ አድራጎታቸው በበለጠ የኢትዮጵያን ሰፊ ሕዝብ ጥላቻ እንጂ፣ ወዳጅነትን እንደማያገኙ በግልጽ እናሳውቃለን። ከተጠያቂነትም እንደማያመልጡ፣ ይሄው ዛሬውኑ በኢትዮጵያ አብዮታውያን፣ በታጋይ ወዝአደሮች፣ በአብዮታዊ መለዩ ለባሾች፣ በጭቁን ብሄረሰብ ታጋዮች፣ ይህች ጥንታዊትና ኩሩ አገር ባፈራቻቸው አገር ወዳድና ዲሞክራቶች፣ እንደዚሁም በታጋይ ወጣቶችና ሴቶች ስም በገሃድ እናስታውቃለን።
**** * ****
ከዚህ በላይ እንደተገለጸው፣ መኢሶን ይህንን ድርጅት የሚቃወመውና የሚታገለው ከመላ ኢትዮጵያ ማርክሲስት ሌኒኒስቶች፣ ዲሞክራቶችና አገር ወዳዶች፣ በሺህና በሚሊዮን ከሚቆጠሩ ወዝአደሮች፣ ገበሬዎች፣ መለዮለባሾች፣ የጭቁን ብሄረሰብ ታጋዮች፣ ወጣቶችና ሴቶች . . ሆኖ ነው። ይህንን ድርጅት የሚቃወመውና የሚታገለው፣ በብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ . . . መድረክ ላይ የቆመ ዲሞክራሲያዊና አገር ወዳድ ድርጅት ባለመሆኑ ነው። ደግሞም፣ “ማርክሲስት ሌኒንስት” ነኝ ካለም “ማርክሲስት ሌኒንስትም” ስላልሆነ፣ “የሰርቶ አደር ፓርቲ”ም ሊያደራጅ ከቶም ሲለማይችል ነው።
የኛ የትግል መድረክ ሰፊ ነው። የትግላችን መድረክና ይህንን መታገያ መሣሪያችን የኢትዮጵያ ታጋይ ልጆች ንፁህ ደም እንደውሃ የፈሰሰበት፣ ያ ድፍን መደበኛና ሕዝባዊ ሠራዊት በደሙ እየተዋዠቀ ቃልኪዳን የገባበት፣ ያ ገና ለብዙ የትግልና የመስዋአትነት ዓመታት የትግል መመሪያችን ሆኖ የሚቆየው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራም ነው። ይህ ፀረ ማርክሲስት፣ ፀረ ወዝአደር ድርጅት፣ ትግሉ ከሃቀኛ ማርክሲስቶች ጋር መስሎት እንደሆነ ክፉኛ ተሳስቷል። ትግሉ፣ ለዲሞክራሲ፣ ለኢትዮጵያ ብሄረሰበቦች እኩልነት፣ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ክብር፣ ለፍትህ፣ ለዕድገት፣ ለብፅግናና ለሰላም በቆሙ እልፍ አእላፍ ኢትዮጵያውያን በአንድ በኩልና፣ ለፀረ ዲሞክራሲ፣ ለትምክህተኝነትና ለብሄራዊ ውርደት በቆመው ድርጅት በሌላ በኩል ነው።
አዎን የቀኝ ኃይሎች እንግዲህ “ፓርቲያችን መቋቋሙ ነው በሰላም እንገዛለን” ብለው ያልሙ ይሆናል። ሌሎችም፣ የዚህ ድርጅት መቋቋም በአንዳች አይነት ተዓምር በአብዮታችን ፊት የተደቀኑትን ችግሮች ይፈታ ይሆናል ብለው ሊያልሙ ይችላሉ። ሌሎች ደግሞ ችግሮቹም ባይፈቱ፣ የዚህ ድርጅት መፈጠር ትግሉን ያቀዘቅዘዋል ብለው ይገምቱ ይሆናል። ሃቁ ግን ሌላ ነው።
እርግጥ የዚህ ድርጅት መፈጠር፣ በጣም ለአጭር ጊዜም ቢሆን፣ በቀኝ ኃይሎች ህብረት ውስጥ አንዳች አይነት የሥልጣን ድልድል ላይ የተደረሰ መሆኑን ወይንም በሌላ አነጋገር ከተሻኳቾቹ አንደኛው የበላይነቱን እንዳረጋገጠና ለጥቂት ጊዜ ሊቆይ የሚችል “የተረጋገጠ” የኃይል ሚዛን፣ አለዚያም ቢያንስ ግን “የመቻቻል ሁኔታ” እንዳለ ይጠቁማል። ይህ ታዲያ በፀረ አብዮት ሰፈር ነው። ነገር ግን የዚህ ድርጅት መፈጠር በኢትዮጵያ ውስጥ በአብዯትና በፀረ አብዮት፣ በዲሞክራሲ ኃይሎችና በፀረዲሞክራሲ፣ ለብሄረሰቦች እኩልነት በሚዋደቁ ታጋዮችና በትምክህተኞች፣ በአገር ወዳዶችና በከሃዲዎች መካከል ያለውን የአቋም ልዩነትም ሆነ የኃይል ሚዛን እምብዛም አይለውጠውም። አንድ ፀረወዛደር ድርጅት ተቋቋመና፣ የኢትዮጵያ አብዮት አንገብጋቢ ጥያቄዎች ተገቢ መልሳቸውን በተአምር አያገኙም። የዚህ “ኮሚሽንና” የፓርቲው መሥራቾች ዛሬ “የሠርቶአደሩ ፓርቲ” አደራጅ ነን ቢሉ፣ ነገ “የሠርቶአደር ፓርቲ” ሆነናል ቢሉ፣ ትላንት ሌላ ስም የነበራቸው እነዚያው ሰዎች ናቸው። ስማቸውን ስለቀየሩ ብቻ ተዓምሮችን አይሰሩም። ደግሞ፣ ጥያቄዎች ተገቢ መልሳቸውን እስካላገኙ ድረስ፣ ወላ ድርጅት ተቋቋመ፣ ወላ “ድጋፍ” ጎረፈለት አልጎረፈለት፣ የኢትዯጵያ ጭቁን ሕዝቦች ትግል እያደር እየዳበረ፣ እየፋመና እየፈጋለ ይሄዳል እንጂ፣ እየቀዘቀዘ አይሄድም።
ትግሉ ይቀጥላል። የኢትዮጵያ ማርክሲስት ሌኒኒስቶች፣ ዲሞክራቶችና አገርወዳዶች ማንኛውም የውስጥና የውጭ ፀረሕዝብ ኃይል እየተቋቋመ ወዲፊት መራመዳቸውን ለአንዲት ደቂቃ እንኳን አያቆሙም። ይህንን ሃቅ አለማየት፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዘመናት የፊውዳሊዝም ጨለማ ተላቆ መጠነኛም ቢሆን ዲሞክራሲያዊ የሆነ ኑሮውን መገንባት ከጀመረ በኋላና በደሙና በመስዋዕትነቱ የሚገነባበትን አዲስ ኢትዮጵያ አሻግሮ መመልከት ከጀመረ በኋላ፣ አክ እንትፍ ብሎ ወደተፋው ፀረዲሞክራሲ አገዛዝ ራሱን ጭዳ ያቀርባል እንደማለት ይቆጥራል። ይህንን አለማየት፣ የኢትዮጵያ ጭቁን ብሄረሰቦች ከመቃብር በታች ቀብሮ ሲያዋርዳቸው ከነበረው ፊውዶ ፋሽስትና ትምክህተኛ ስርዓት በመራራ ትግላቸው መላቀቅና መጠነኛ የእኩልነት ጮራን መመልከት ከጀመረ በኋላ ተመልሰው ለጭፍን ትምክህተኛ እብሪት እጅና እግራቸውን አሥረው ያስረክባሉ እንደማለት ይቆጠራል። ይህንን አለማየት፣ በዓለም ሕዝቦች ሸንጎ የማይናቅ ማንነቱን በደመና በመስዋአትነቱ እያስከበረ አኩሪ የታሪክ ገጾችን ሲጽፍ ከኖረው ጀግናው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ አደራ የወረሰው ይህ የዛሬው ታጋይና አገር ወዳድ የኢትዮጵያ ትውልድ በሃገር ፍቅር እየፈላ ለኢትዮጵያ አብዮት እስካሁን ያፈሰሰውን ደም እነደውሃ ቆጥሮ ለአዲስ መጥ ጌቶች አጎባድዷል ማለት ነው። ይህንን ማለት፣ ራሱን ለቻለ ነፃና ብሄራዊ ኢኮኖሚ የተዋደቀው ሰፊው ሠርቶ አደር ሕዝብ፣ ኢኮኖሚያችንን ለአዲስ በዝባዦች፣ ብሄራዊ ሃብቱን ለአዲስ የቀኝ አገዛዝ ኢኮኖሚ ለመክፈትና ለማስመንዘር ፈቅዷል እንደማለት ይቆጠራል።
ይሁን እንጂ፣ እንደዚህ አይነቱ እምነት፣ በጠቅላላው ከአብዮቶች እየወደቁ መነሳት ባህሪይ ጋር በአንድ በኩልና፣ በሌለው በኩል ደግሞ ባለፉት አምስት ዓመታት የኢትዮጵያ ታጋይ ልጆች፣ ወዛደሮቿና አርሶ አደሮቿ፣ ወጣቶችና ታጋይ ሴቶቿ ካሳዩት አብዮታዊ ወኔ፣ እንደዚሁም በክፍለ ዘመናት በሚለካው ረዥም ታሪኳ፣ ታጋይ ልጆችዋ ካስመሰክሩት የተከበረ የሀገር ፍቅር ስሜት ጋር ተነጻጽሮ ሲመሳከር፣ የአድሃሪዎች የቁም ቅዠት እንጂ፣ ሌላ ምንም ትርጉምአይኖረውም።
ስለሆነም፣ እኛ ማርክሲስት ሌኒኒስቶች፣ የኢትዮጵያ ግንባር ቀደም ወዛደሮች የጊዜውን አስቸጋሪነትና የሚጠብቀንን መስዋእትነት ቅንጣት ዝቅ አድርገን ባናየውም፣ መጪውን ጊዜ የምንገጥመው በዘላቂ አሸናፊነታችን ያለንን የማይናወጥ እምነት እንደገና ሺህ በሽህ አድሰን ነው። ለዚህ ትግል ሰብሳቢና መሪ ብለን እምነታችንን የጣልንበት የኢትዮጲያ ወዛደሮች ፓርቲ በየፋብሪካውና በየማሳው፣ በየቀበሌውና በየመስሪያ ቤቶች፣ በየጦር ሰፈሩና በየትምህርት ቤቶች፣እንደዚሁም ከሀገር ውጭም ሆነው የሚዋደቁትን ግንባር ቀደም ወዛደሮችና ገበሬዎች፣ አብዮታዊ ምሁራንና መለዮ ለባሾች፣ ወጣቶችና ሴቶች አስተባብረን ለመመስረት የተያያዝነውን ትግል እጥፍ ድርብ አድርገን እንቀጥለዋለን።
የኢትዮጵያ ነፃ መውጣትና የብልፅግና መረጋገጠ ትግል የኛ ብቻ ሳይሆን፣ የዲሞክራትና የአገር ወዳድ ልጆችዋ ሁሉ ትግል ነው። ስለዚህ ከዚህ የኛም የእነሱም ካልሆነ ፀረ ሕዝብ ድርጅት ባሻገር፣ ከሱ ውጭና እርሱን ተቃርነው ለኢትዮጵያ ክብርና ነፃነት ለምናደርገው ትግል የመደራጀት ጥረታቸውን እንዲያፋፍሙ፣ ለኢትዮጵያ ሃገር ወዳድ ዲሞክራቶች ሁሉ ብሔራዊ ጥሪያችንን በድጋሚ እናስተላልፍላቸዋለን። ድሉ የሰፊው ሕዝብ ነው።