ሰሕድ ቁ. 2

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ቁጥር 2፣    ነሐሴ 21፣ 1966

የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ

በዚህ የሰፊው ሕዝብ ድምጽ እትሙ ውስጥ መኢሶን፣ የሰው ልጆች ሥራ የሃብት ምንጭ እንደመሆኑ፤ ሠራተኞችም በጉልበታቸውና በአእምሮ ችሎታቸው የሃብት አመንጭዎችና የህብረተሰብ ምሰሶ እንደሆኑ ያረጋግጣል። ሠራተኞች፣ በፋብሪካ፣ ግብርና፣ ከብት እርባታና ንግድ ተሰማርተው የኢትዮጵያውያን ብሔራዊ ሀብት አምራቾች እንደሆኑ ያስገነዝባል። ስለዚህም፣ ያለሠራተኞች  እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች ሁሉ፤ ብሔራዊ ህልውና እንደማይኖራቸው ይገልጻል። ሆኖም ደግሞ፣ሠራተኞች፣ የንብረት አምራቾችና የሀብት አመንጭዎች ሆነው፤ የወዛቸውን ፍሬ ግን በቀጣሪ አሠሪዎችና በመሬት ባለሀብቶች እንደሚመዘበሩ ያመልከታል። ስለዚህም፣ ከዚህ ዓይነት ጀርባቸውን ካጎበጣቸው የምዝበራና የብዝበዛ ክብደት፤ ቀና ብለው ሙሉ ሰብዕናቸውን ለመጎናጸፍ እንዲችሉ ለነጻነታቸውና ለመብታቸው መታገል እንደሚኖርባቸው ያስገነዝባል።
በየካቲት 1966 ዓ.ም.፣ የኢትዮያጵያ ሠራተኞች በማኅበራቸው በኢሠአማ አማካኝነት የሚያደርጓቸውም ታሪካዊ ትግሎች፣ የሥራ ፍሬያቸው ባለቤት ለመሆንና መብታቸውን ለማስከበር ነው። ይህም ትግላቸው፣ ጥቅማቸውን በሚያስጠብቅላቸው እውነተኛ ማኅበር ሥርና ሐቀኛ በሆኑ የሠራተኞች መሪዎች አማካኝነት ብቻ መቀጠል እንዳለባቸው ያበክራል። ከዚህም አኳያ፣ ወታደራዊ ደርግም በአስቸኳይ መውሰድ የሚገባውን ስምንት እርምጃዎች፤ ማለትም፣ ጊዜያዊ መንግሥት ባስቸኳይ እንዲቋቋም፣ መሬት ለአራሽ ጢሰኞች እንዲደለደል፣ የሠራተኞች መብቶችን ማስክበርን፣ በድርቅና በረሃብ ለተጎዱ ወገኖች አፋጣኝ እርዳታ ማቅረብን፤ የፖለቲካ እስረኞች መፈታትንና የሕዝብ ሙሉ ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ያካተተ ለአገሪቱ አዲስ ሕገ መንግሥት መረቀቅን ወዘተ. ነጥብ በነጥብ ገልጾ ባጭሩ ይዘረዝራል።

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ለሰፊው ሕዝብ ሰራተኛ ገበሬ፣ ነጋዴ፣ ወታደር፣ ምሁር መብትና ጥቅም የሚታገል ጋዜጣ

የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ይቅደም

ቁጥር 2                                                                       ቀን 12/21/66

 

የየካቲቱ ሕዝባዊ እንቅስቃሴና የሰርቶ አደሩ ሚና

ሥራ የሃብት ምንጭ ነው። ሥራ ያለ ሠራተኛ ሊኖር አይችልም። ስለዚህ ሠራተኛ የሃብት የብልጽግና መሰረትና ፈጣሪ ነው። የህብረተሰብ ምሰሶና አውታር፣ ደግፎና ገትሮ ቀጥ አድርጎ የሚይዘው ሠራተኛ ነው። በጠቅላላው ሠርቶአደር ስንል በፋብሪካ በንግድ በግብርና በከብት እርባታና በሌሎችም ተግባሮች ላይ የተሰማራ በቀጥታም ሆነ በዘወርዋራ መንገድ ለሰው ልጅ ህይወት ተፈላጊ የሆኑትን ነገሮችና አገልግሎቶች የሚያበረክት ወይም በእንደዚህ አይነት ተግባር የሚሳተፍ ማለትን ያሰማል። ስለሆነም እዚህ ሠርቶአደር ወይም ሠራተኛ ስንል ጠበብ ባለ ትርጉም በፋብሪካ፣በንግድና በሌሎችም ተመሳሳይ የኢኮኖሚ ድርጅቶች ውስጥ በመቀጠር ጉልበታቸውን ወይም እውቀታቸውን እየሸጡ የሚኖሩ ማለታችን ነው።

ሠራተኛ በጉልበቱና በአእምሮው ኃይል ሃብት ይፈጥራል። ከሚፈጥረው ሀብት ግን የሚደርሰው በጣም አነስተኛ ነው። ከበርቴዎች አብዛኛውን እጅ ይወስዱበታል። በዚህ ምክንያት ከፍተኛ ብዝበዛና ምዝበራ፣ ጭቆናና ግፍ ይሠራበታል። በመደብ በተከፋፈለና የመንግሥቱን ስልጣን ባለአባቶችና ከበርቴዎች በያዙበት ህብረተሰብ ውስጥ ሠራተኛው የወዙን ፍሬ አየተበዘበ ከመኖር ሌላ ምንም አይነት ምርጫ እንደሌለው ታሪክ በጉልህ ይመሰክራል። ከዚህ አሰቃቂ ሁኔታ እራሱን ነፃ ለማውጣት የሚችለው በቆራጥነትና በአንድነት በመታገል ብቻ እንደሆነም ታሪክ ያስተምረናል።

በኢትዮጵያስ የሠርቶ አደሩ ሁኔታ እንዴት ነው? ይህ ነው የማይባል ብዝበዛ፣ ጭቆና፣ ግፍ አለበት፤ ህይወቱ ምድራዊ ሲኦል ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። የኢምፔሪያሊስቶች ቡችላ የሆነው አድሃሪው መንግሥት ሠራተኛውን ብሄራዊና በእዳን ከበርቴዎች እንደ እቃ እንዲጠቀሙበት አሳልፎ ሰጥቷቸዋል። አሰሪው ሠራተኛውን በፈለገው ደመወዝ ይቀጥረዋል፤ እንዳሰኘው ከሥራ ያባርረዋል። ሠራተኛው ምንም አይነት ዋስትና የለውም፤ የሥራው ሁኔታ እንዲሻሻልለት፣ የድካሙን ዋጋ እንዲያገኝ አሰሪውን ከመለማመጥ በስተቀር ሌላ ነገር ለማድረግ አይፈቀድለትም፤ ጭንቅ ሲሆንበት፣ ሲበዛበት፣ ሲያንገፈግፈው፣ የመጨረሻ መሣሪያው የሆነውን የሥራ ማቆም መብቱን ሊጠቀምበት በሚነሳበት ጊዜ የከበርተዎች ጥቅም ጠባቂ የሆነው ቡችላ መንግሥት በመጨቆኛና በመደምሻ ኃይሎች/ በፖሊስና በወታደር/ ያስጨፈጭፈዋል፤ ደሙን እንደ ክረምት ጎርፍ ለማፍሰስ አይመለስም። የከበርቴዎቹ ብዝበዛና ዘረፋ፣ የአድሃሪው መንግሥት ግፍ፣ በደልና ጭቆ እጅግ በጣም የበዛ ነው። ከዚህ ሁሉ አልፎ ይሄዳል። የኢትዮጵያ ሠራተኛ ከዓለም ሠራተኛ ውስጥ የባሰ የተጎሳቆለ፣ የተመዘበረ፣ የብዝበዛው ክብደት ያጎበጠው፣ የመጨረሻ ጭቁን መሆኑ የሚያጠራጥር አይደለም።

የኢትዮጵያ ሠራተኛ ከዚህ ከባርነት ራሱን ነፃ ለማውጣት ከባድ ትግል ሲያደርግ ቆይቷል። የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም አሻንጉሊቶች ፀረሠራተኛ ሕግ በማውጣት ሠራተኛውን እጅና እግሩን ጠፍረው ለከበርቴዎች ከመስጠታቸው በፊት የፈረንሳይና ኢትዮጵያ የምድር ባቡር ሠራተኞች፣ የሲሚንቶ ፋብሪካ ሠራተኞች፣ የጥጥ ፋብሪካ ሠራተኛ ማህበር አቋቁመው የጭቆናውንና የብዝበዛውን ቀንበር ለመስበር ከባድ ትግል ሲያካሂዱ እንደነበር የሚወስ ነው። በሕግ እግርብረት ቢታሰርም ሠራተኛው መፍጨርጨሩን፣ መታገሉን አላቆመም፤ ከሰፊው ሕዝብ በተለይ ከተማሪው በመደጋገፍ የመደብ ጠላቱን ለመቋቋም ትግሉን ሲያካሂድ ቆይቶ ታሪካዊው የየካቲት ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ፈነዳ።

የየካቲቱ እሳተጎሞራ ከመፈንዳቱና አገሪቷን ከማጥለቅለቁ በፊት በ1965 መጨረሻ ገደማ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሠራተኞች የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሠራተኞች፣ በዚህ አመት /በ1960/ የወንጂና መተሃራ ስኳር ፋብሪካ ሠራተኞች፣ የመልካ ሰዲ የእርሻ ተክል ሠራተኞችና ሌሎችም ከባድና ቆራጥ ንቅናቄ በማድረግ፣ ሕይወታቸውን ጭምር በመሰዋት፣ በአሰሪዎችና በቡችላው መንግሥት ላይ ድልን መቀዳጀታቸው የታወቀ ነው። በየፋብሪካውና በየድርጅቱ ደረጃ የሠራተኛው ትግል እየተጠናከረና እየተፋፋመ ሲሄድ ታሪካዊው የካቲት ዱብ አለ።

በሌላ በኩል፣ በከፍተኛ ደረጃ ላይ የኢትዮጵያን ሠራተኞች በማጠቃለል የመሪነቱን ቦታ የያዘው ኢሠአማ በሠራተኛው ትግል እንቅስቃሴ ውስጥ ምን ስፍራ ነበረው? በየካቲቱስ የሰፊው ሕዝብ ታሪካዊ መነሳሳት ምን ነበረ አቋሙ? ሰፊውን ሠርቶአደር በሚገባ አሰልፎታል ወይ?

የኢትዮጵያ ሠራተኞች አንድነት ማህበር የሠርቶአደሩን አንድነት ለማጠናከር፣ መብቱንና ጥቅሙን ለመጠበቅ ሳይሆን፣ ለብዝበዛ ለዘረፋ ለጭቆና እንዲመቻቸው ለማድረግ ኢምፔሪያሊስቶች በተለይ አሜሪካኖች የፈጠሩት የከበርቴዎች መሳሪያ ነው። ላይ ላዩን አንድነት ይላል፤ ውስጥ ውስጡን ይከፋፍላል። በአፉ የሠራተኛን መብት አስከብራለሁ፣ ጥቅሙን አስጠብቃለሁ በማለት ያውጃል፤ በእርግጥ ግን የሚያደርገው የዚህን ተቃራኒ ነው። የእድሃሪው ፊውዶቡርዧ ጥገኛ መንግሥትና የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም ጥገኛ ቡችላ በመሆን የኢትዮጵያን ሠርቶአደር ያስበዘብዛል፣ ያስጨቁናል፣ ያስደበድባል፣ ያስበድላል፣ የግፍ ግፍ ይሠራበታል።

የኢሠአማ መሪዎች የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝምና የቡችላው አድሃሪ መንግሥት ፍጡሮች ናቸው እንጅ ከሠራተኛው ውስጥ የወጡ የሠርቶአደሩ ወኪሎች አይደሉም። የሠራተኛውን አንድነትና ንቅናቄ ለማድከምና ለመስበር በልዩ ልዩ አይነት የተንኮል ዘዴ ይጠቀማሉ። በጥቅምና በመላሾ፣ በሹመት መደለልና ማባበል፣ በነገድ በጎሳ በሃይማኖት መከፋፈል፣ ማስፈራራት መወንጀል ማስከሰስ ማስገልበጥ ከሥራ ማስወጣት ማስደብደብ ማስገደል፣ በእነዚህና በመሳሰሉት ርካሽና እርኩስ ድርጊቶች በመጠቀም የሠራተኛውን የትግል ንቅናቄ ለመግታትና ለማዳከም በሙሉ ሃይላቸው እንደሚጥሩ የታወቀ ነው። የተሸጡት የኢሠአማ መሪዎች ይህንን ወንጀለኛ የአሠራር ዘዴ የወረሱት ከአሜሪካን ኢምፔሪያሊስቶች መሆኑን በቀላሉ ለመገንዘብ ይቻላል።

በየነ ሰሎሞን ለአሥራአንድ ዓመታት ቀንዳም የአሜሪካ ቡችላ በመሆን በኢሠአማ ላይ ነግሶአል። ከተላላኪነትና ከተራ ሠራተኛነት ተነስቶ በመለማመጥ፣ ጫማ በመላስ፣ ጭራ በመቁላት፣ ነገር በመሥራት፣ ለሲአይኤና ለፀጥታ መስሪያ ቤት ወሬ በማቀበል፣ በሠራተኛው ላይ በመሰለል፣ የኢትዮጵያ ሠራተኛ ንቅናቄ ወደፊት እንዳይራመድ አፍኖ ይዞታል። ለእግሩ እንኳን ጫማ ያልነበረው ምስኪን ዛሬ ትልቅ ዲታ ሆኗል። ቪላው በሁለት ሦስት ይቆጠራል፤ ዲታዎቹም እንደዚሁ፣ ንግዱ እርሻው፣ ስንቱ ተቆጥሮ እንደነ ጆርጅ ሚኒ እንደነ ጀምስ ሆፋ /ባለሚሊዮን ብር አሜሪካውያን ‘የሠራተኛ መሪዎች’/ ለመሆን ምንም ያህል አልቀረውም። ለምሳሌ ያህል ነው እንጅ በየነ ብቻውን አይደለም። እነ ፍሰሃጽዮንም ከሲአይኤ የሚያገኙት ገንዘብ ጉጉታቸውንና ስግብግብነታቸውን ስለአጋለባቸው ከሃብታሞች በመጋባት ከፍተኛ ስልጣንና ሃብት ለመጨበጥ ትግል በማድረግ ላይ ናቸው። ሌሎቹም እንደዚሁ ናቸው።ነገሩ ‘ከዝንጀሮ ቆንጆ ምን ይመራርጡ’ ነው።

ታጋዩንና ቆራጡን የኢትዮጵያ ሠርቶአደር ንቅናቄ ወደፊት እንዳይራመድ እንቅፋትና መሰናክል የሆኑት እነዚህ ይሁዳዎች፤ በየካቲቱም ታሪካዊ የሰፊው ሕዝብ እንቅስቃሴ ሠራተኛው ተገቢ ቦታውን እንዳይዝ ትልቅ ጥረት አድርገዋል። ከስር ሠራተኛው ፈንቅሏቸው ባይነሳ ኖሮ የአራቱም ቀናት ጠቅላላ ሥራ ማቆም አይደረግም ነበር። /እንዳልካቸውን በመደገፍ ፍሰሃጽዮን የሥራ ማቆሙን ውሳኔ ተቃውሞት ነበር። በተጨማሪም ሠራተኛው ሰላማዊ ሰልፍ እንዳያደርግ የኢሠአማ አድርባዮች አወናብደውታል።/ ከዚያም ወዲህ ሠራተኛው እነርሱን ወደዚያ ጥሎ ትግሉን በራሱ እንዳይቀጥል ነው። በተንኮላቸው እያጨናገፉትና እያወናበዱት ንቅናቄው መልክ እንዳይዝ፣ ቀጥታ ወደ ጠቅላላና ብሄራዊ ጉዳይ እንዳይተላለፍ፣ ከሰፊው ሕዝብ ጋር እንዳይሰለፍ፣ የትግሉን መሪነት እንዳይወስድ፣ ታሪካዊ ስፍራውን እንዳይዝ ከባድ እክል መሆናቸውን አስመስክረዋል። ሠራተኛው እነዚህን እስስቶች የሚያስወግድበት ጊዜው ሩቅ መሆን የለበትም። የሠራተኛው ንቅናቄ ደንበኛውን አቅጣጫ ሊይዝ የሚችለውና ትግሉ በከፍተኛ ደረጃ ላይ ሊካሄድ የሚችለው እነዚህን ተንኮለኞች አድርባዮች በቅድሚያ ሲያባርር ብቻ ነው። አሁን በቅድሚያ ሠርቶአደሩ ሁሉ እነዚህን የሲአይኤ መሳሪያዎች ድራሻቸውን ማጥፋት ይኖርበታል።

ኢሠአማ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠላት፣ የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም፣ የሲአይኤ ምሽግ መሆኑ መቅረት አለበት። ኢሠአማ የኢትዮጵያን ወዛደር መብት አስከባሪና ተቋም ጠባቂ፣ የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ አደራጅና መሪ መሆን አለበት። ወደፊት ተራማጅ እንጅ ወደ ኋላ ተመልካች የፊውዶቡርዧው አድሃሪ መንግሥትና የበላይ ጠባቂው የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም የስለላና የጸረሕዝብ ወንጀሎች መፈፀምያ፣ የሲአይኤ አፋኝ ጓድ ማፊያ መሆን የለበትም።

እዚህ ላይ ግልጽ መሆን ያስፈልጋል። ለኢምፔሪያሊዝምና ለአድሃሪው መንግሥት የተሸጡትን ደላሎችና ሰላዮች ማውገዛችንና ማጋለጣችን ነው አንጅ የኢትዮጵያን ሠራተኞች አንድነት፣ ኢሠአማን መቃወማችን አይደለም። ይህ ያለአንዳች ጥርጣሬ በግልጥ መታወቅ አለበት። ኢሠአማን የሚመሩ፣ ከሠራተኛው ወገን የሆኑ፣ ሌሎች ሃቀኞችና ትጉሆች ለሠራተኛውና ለሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያስቡ፣ የሚቆረቆሩ ችሎታ ያላቸው መሪዎች መሆን አለባቸው። ሠርቶ አደሩ እንደዚህ አይነት መሪዎች አሁን ቶሎ ብሎ ይምረጥና ታሪካዊ ሚናውን ይያዝ ነው የምንለው። ልዩነቱን ደህና አድርጎ መገንዘብ ያሻል።

ኢሠአማ ቶሎ ብሎ እነዚህን ወደ ኋላ ጎታች የሲአይኤ ቡችሎች ያባርር ስንል፤ በየካቲት ፈንድቶ በመገንፈል ላይ ባለው የሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ የትግል እንቅስቃሴ ውስጥ ተገቢና ታሪካዊ ስፍራውን እንዲይዝ በማለት ነው። ይህ ታሪካዊ ስፍራው ምንድነው? የትግሉን አላማ /አይዲዮሎጂ/ መግለጽ እና ማብራራት፣ የሰፊውን ሕዝብ ትግል በደንብ ማደራጀት፤ ደሀውና መሬት አልባ የሆነ ጢሰኛ ገበሬ /ከጠቅላላው ሕዝብ 80% ገደማ የሚሆነው ነው/ ለመሠረታዊ ለውጥ የሚደረገውን ትግል በደንብ እንዲደግፍና ከሠራተኛው ጋር አብሮ እንዲሰለፍ አስፈላጊውን ማድረግ፣ ዝቅተኛው ነጋዴ፣ ጠቢቡና ባለእጁ፣ ሥራአጡ፣ በድርብ ብዝበዛና ጭቆና ስር የሚማቅቁት ብሄረሰቦች ወታደሩና ምሁሩ ወዘተ. በሠራተኛው የትግል ባንዲራ ስር እንዲሰለፉ ማድረግ የኢሠአማ አብይ ተግባር ነው። ይህ ነው የኢሠአማ ታሪካዊ ሚና።

የኢሠአማ /ጠቅላላው የኢትዮጵያ ሠራተኞች/ ዋና ግዜያዊ ተግባር ምን መሆን አለበት?

  1. ኢሠአማን ፀረሠራተኛ ከሆኑት ከአሁኖቹ መሪዎችና ከአደገኛው የአሜሪካ የስለላ ድርጅት ማጽዳትና ነፃ ማውጣት፣ ለሠራተኛ መብትና ጥቅም በሀቅና በትጋት የሚሰሩ መሪዎች ከሠራተኛ መካከል በአስቸኳይ መምረጥ፣
  2. በአሁኑ መሪዎች ደንታ ቢስነትና ከሃዲነት ከሥራ የተባረሩት በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ሠራተኞች ቶሎ ብለው ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ፣ ማንኛውም ሠራተኛ ከሥራ እንዳይወገዱ፣ የኑሮ ዋጋ ማስተካከያ ደሞዝና ሌሎቹም መንግሥት በገባው ቃል መሠረት እንዲፈፀሙ አጥብቆ መታገል፣
  3. በመካሄድ ላይ ያለውን የሰፊውን ሕዝብ እንቅስቃሴ መልክ መስጠት፣ ማቀናበር፣ ማደራጀትና መምራት፣ በእንቅስቃሴው ውስጥ የበለጠ እንዲሳተፍ አስፈላጊውን ሁሉ ማድረግ፣
  4. በሠርቶአደሩ አይድዮሎጂ ስር ከተሰለፉት ግንባር ቀደም ምሁራን ጋር በአንድነት በመተባበር፣ የሰፊውን ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ትግል የሚያደራጅ፣ የሚያቀናብርና የሚመራ አንድ አጠቃላይ ዲሞክራሲያዊ የፖለቲካ ድርጅት ማቋቋም፣
  5. የሰፊ ዲሞክራሲያዊ መንግሥት በቅርብ እንዲመሰረት፣ እስከዚያው ድረስ አሁኑኑ ከሰፊው ሕዝብ የተወጣጣ ጊዜያዊ መንግሥት እንዲቋቋም ካሁኑ ጀምሮ መሰረታዊ ሰብአዊና ብሄራዊ መብቶችና ነፃነቶች አስፈላጊው ዋስትና ተሰጥቶ ሥራ ላይ እንዲወሉ እንዲደረግ አጥብቆ መታገል።
  

 

 

እውነተኛው ኢሠአማ ለዘላለም ይኑር፣
የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም፣ ሲአይኤና  ቡችሎቹ ይውደሙ፣
  ድሉ የሰፊው ሕዝብ ነው።

ታሪክን የሚገነባው ሰፊው ሕዝብ ነው።

በአሁኑ ያረጀ የኢትዮጵያ ፊውዳላዊ /ባላባታዊ/ ሥርዓተማህበር ውስጥ እንደሰፊው ሕዝብ ክፍሎች የሚቆጠሩት የሠራተኛው መደብ፣ ጢሰኛውና ደሀ ገበሬው፣ ትናንሽና መለስተኛ ነጋዴዎች፣ ዝቅተኛና መለስተኛ የመንግሥት ሠራተኞች፣ ተራ ወታደርና መለስተኛ መኮንኖች፣ ተማሪዎችንና አብዛኛው ምሁራን፣ ሾፌሮችና ታክሲ ነጅዎች፣ ጠቢቦች፣ ሥራአጦች…. ወዘተ. ናቸው።

የሕብረተሰቡን ጠቅላላ ሕይወትና እድገት የሚወስነው የሰፊው ሕዝብ የርባታ ትግብርት ነው። ሰፊው ሕዝብ ለህብረተሰቡ ኑሮ አስፈላጊ የሆኑትን ቁሳቁሶች ሠርቶ ከማውጣቱም ሌላ የሥራ መሣሪያዎችን ያሻሽላል፤ ከሥራ ልምድ የሚቀስመውን እውቀት እያከማቸ ከትውልድ ወደትውልድ በማስተላለፍ በርካታ ተግብርቱ አንድ ሥርዓተማህበርን ወደ ሌላ ከፍተኛ ሥርዓተማህበር ለማራመድ አስፈላጊ የሆነውን ማቴሪያላዊ /ቁሰአካላዊ/ መሠረት ይገነባል። በዚህ አድራጎቱ ነው እውነተኛውን የሰው ልጅ ታሪክ የሚገነባው።

ሰፊው ሕዝብ ራሱን ከብዝበዛና ጭቆና ነፃ የሚያወጣው ራሳቸውን ‘ዝቅ’ በማድረግ ‘ለተራው ሕዝብ’ ደግ ለመዋል በሚሞክሩ ታላላቅ ሰዎች ብርታት ሳይሆን በራሱ ትግል ነው። ይህንን እውነት በቲዮሪ ማወቅ ምናልባት በጣም አስቸጋሪ ላይሆን ይችላል። በተግባር ላይ ማዋሉ ግን ይህን ያህል ቀላል ሆኖ አልተገኘም። ከታሪክ እንደምንረዳው ከዚህ በፊት ብዙ የፖለቲካ ቡድኖች ሪቮሉሲዮናዊ አላማዎችን ይዘው ሥርዓተማህበሩን ለመለወጥ ታግለው፣ ግባቸውና ሚናቸው ትክክለኛ ሆኖ እያለ ሰፊው ሕዝብ የታሪክ አንቀሳቃሽ ሞተር መሆኑን በመዘንጋታቸው ራሳቸውን እንደ ነፃ አውጪዎች በመቁጠር የሰፊውን ሕዝብ ሪቮሉሲዮናዊ ችሎታ በመናቅ ሱታፌውን ስላላረጋገጡ ብቻ በበዝባዥ መደቦች ተደምስሰው ሊጠፉ በቅተዋል።

ዛሬ ባገራችን ካለፈው የካቲት ጀምሮ በሚደረገው የመሰረታዊ ለውጥ እንቅስቃሴ ‘ኢትዮጵያ ትቅደም’ የሚለውን ዓላማ ይዞ በግንባር ቀደምነት የሚገኘው የጦር ኃይሎች ደርግ ወደዚህ አይነት ከባድ የታሪክ ስህተት እንዳይወድቅ ያሰጋል።

ጠቅላላው ሠራዊት የሕዝቡን ፍቃድ እንዲፈጸም በዲሞክራሲያዊ መንገድ መርጦ ያቋቋመው አስተባባሪ ደርግ በሰፊውን ሕዝብ በመፈራት ወይም በመናቅ ይሁን አይታወቅም ከወታደሩ የተወከለበትን ተግባር በሚገባ ለመፈጸም ካለመብቃቱም ሌላ በሰፊው ሕዝብ ዘንድ ጥርጣሬንና ቅሬታን እስከ ማትረፍ ደርሷል።

‘ኢትዮጵያ ትቅደም’ በማለት በሠራዊቱ በተጀመረውና በሕዝቡ በተደገፈው ንቅናቄ ሰፊው ሕዝብ እንዲሳተፍ ደርጉ ምንም መንገድ አልከፈተም። እንዲያውም የሰፊውን ሕዝብ ሱታፌ ለመቀነስ የጽሁፍና የንግግር ነጻነት እስካሁን ድረስ እንደታገደ እንዲቆይ ከማድረጉም በላይ ሰፊው ሕዝብ እንዳይሰበሰብ በጥብቅ ከልክሏል። በአንዳንድ የመንግሥት መስሪያ ቤቶችም የሠራተኞች ኮሚቴዎች እንዲፈርሱ አድርጓል። ከዚህም አልፎ ተርፎ በሰፊው ሕዝብ ላይ ደጋግሞ ዝቷል። ራሱን እንደ ነፃ አውጭ ግንባር በመቁጠር ‘እኛ ከሌለን የሀገሪቱ ደህንነት የለም’ ሲል ፊውዳላዊ የሆነ አስተሳሰብ ሰንዝሯል።

ደርጉ እንደዚህ አይነቶቹን ድርጊቶች ሲፈጽም ምናልባት እንደገዢው መደብ ፈላስፎች ሰፊው ሕዝብ ደደብ ደንቆሮ መንጋ ነው ብሎ ይገምት ይሆን? ወይንስ ሰፊውን ሕዝብ ፈርቶ ነው? ይህ ከሆነ ሰፊው ሕዝብ ከመሳፍንት የበለጠ አስፈርቶት ይሆን በንቅናቄ ውስጥ መሳፍንት እየተቀያየሩ ሲሳተፉ ሕዝቡ ቁጭ ብሎ ብቻ እንዲመለከት የሚያስገድደው? እንግዲያውማ ደርጉ የማን ወገን ነው? የሰፊው ሕዝብ ወይስ የመሳፍንትና የመኳንንት?

ሰፊው ሕዝብ በንቅናቄው መሳተፍ አለበት፤ መብቱና ግዴታው ነው። በስሙ የሚሠራውና ሊሠራ የታቀደውን ሁሉ ማወቅ መብቱም ግዴታውም ነው። ስለዚህ ከደርጉ ጥርት ያለ ዝርዝር የሥራና የዓላማ ፕሮግራም ይጠየቃል። ‘ኢትዮጵያ ትቅደም’ የሚለው መርሆ ያለ ዝርዝር ፕሮግራም ግልጽ ፍች ሊኖረው አይችልም። ስለዚህ ሰፊ ሕዝብ ያለ ዝርዝር ፕሮግራም በንቅናቄው ሊሳተፍም ሆነ ያለ ጥርጣሬ ሙሉ ድጋፉን ሊሰጥ አይችልም። ለመሆኑ ደርጉ ዝርዝር የሥራና የዓላማ ፕሮግራም ለሕዝቡ እንዲያስታውቅ ደጋግሞ ሲጠየቅ ለሕዝቡ ጥያቄ የዝሆን ጆሮ የሚሰጠው ለምን ይሆን? የፕሮግራም ማውጣቱ ሥራ ይህን ያህል ከባድ ሆኖ ነው ወይስ ከሰፊው ሕዝብ ሊደበቅ የተፈለገ ነገር ቢኖር ነው?

የዝርዝር ፕሮግራም መጻፍና የሰፊውን ሕዝብ ተሳትፎ የሚደግፉ እንደነ ሻለቃ ተፈራ ተክለአብ ያሉ ተራማጆች በደርጉ ውስጥ መኖራቸው ታውቋል። ነገር ግን የሰፊውን ሕዝብ ወገን በመውሰዳቸው ብቻ ደርጉ አንዳንዴ ሲያሳስራቸው አንዳንዴም ፈትቶ በጥብቅ ሲከታተላቸው መታየቱ በደርጉ ላይ ትልቅ ጥርጣሬን አስከትሏል። እንዲሁም በአርሜ አቪየሽን፣ በጦር ኃይሎች የህክምና ክፍልና በጦር ኃይሎች የመሀንዲስ ክፍል ላይ ጭቆና የደረሰባቸዉ ዝርዝር ፕሮግራሙ ወጥቶ ሰፊው ሕዝብ በትግሉ እንዲሳተፍ በመጠየቃቸው ብቻ መሆኑ በጣም የሚያስገርም ነው። ሰፊው ወታደር ደርጉን የወከለው ለእንደዚህ አይነቱ ተግባር አልነበረም።

አሁንም ሰፊ ወታደር በደርጉ ውስጥ በሚታዩት ጉድለቶች ላይ ውይይት ካደረገ በኋላ በዲሞክራሲያዊ መንገድ በፍጥነት መፍትሄ ካላገኘለትና የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ትግል ወደፊት እንዲራመድ ለማድረግ ካልበቃ በሌሎች አገሮች ከዚህ በፊት እንደተደረገው ሕዝቡ በወታደሩ ተስፋ ቆርጦ የራሱን ጦር ኃይል ለመገንባት ከመገደድ ሌላ ምን ምርጫ ይኖረዋል? ይህስ አይቻልም ተብሎ ይጠረጠር ይሆን?

በሌላ በኩል ደግሞ ክቡር ደርጉን በትህትናና በሃቅ የምናሳስበው እንደዚህ አይነት ትችት ሲቀርብ የግል ጥቅምን ለማሻት ወይንም ሕዝቡን ሲጨቁኑና ሲበዘብዙ ኑረው አሁን የታሰሩትን የመንግሥት ባለስልጣኖች ለመርዳት አይደለም። ደርጉን በጥሞና ለማስገንዘብ የምንወደው ከጠላት በሚሰነዘረው አፍራሽ ሂስና ከሕዝብ ወገን በሚሰነዘረው ገንቢ ሂስ መካከል ትልቅ ልዩነት እንዳለ እንዲረዳልን ነው። ከዚህ በፊት በዚሁ ጋዜጣችን እንዳመለከትነው ሁሉ ደርጉ የሕዝቡን ፍላጎት የሚያረኩ አንዳንድ ድርጊቶችን በመፈፀሙ ድጋፍ ሊያገኝ ይገባዋል። ደግሞም በኃላፊነት ቦታ ሲገኙ ስህተት ከፈጸሙ ያለምንም ፍርሃት በገንቢ ሂስ መታረም፣ ወይንም ስህተት ሲደረግ ካዩ ማመልከት ግዴታ ነው። ከዚህ በላይ በደርጉ ላይ የቀረቡትም ሂሶች በዚህ አዉደ ሀሳብ ላይ የተመሠረቱ እንጅ ደርጉን በሃሰትና በተንኰል ለማጥላላትና ለማውደም በመፈለግ አይደለም። ደርጉ ጥፋት ሲያደርግ በገንቢ ሂስ ማረም፤ አድሃራዊ ኃይሎች በደርጉ ላይ ቢነሱ በጎኑ በመሰለፍ መታገል፣ ይህ ነው የማንኛውም እውነተኛ ተራማጅ የሕዝብ ወገን አቋም።

ወደ ዋናው ጉዳይ እንመለስና፤ ሰፊው ሕዝብ በትግሉ የግድ መሳተፍ አለበት። ‘ኢትዮጵያ ትቅደም’ የሚለው መርሆ ያለዝርዝር ፕሮግራም ፍች ሊኖረው አይችልም፤ ያለ ሰፊው ሕዝብ ሱታፌም ዘለቄታ ሊኖረው አይችልም። በከባድ አማርኛ የተፃፉ ብዙ ጽሑፎችን ደጋግሞ ከመስማት ይልቅ ጥቂት ገንቢና ተጨባጭ እርምጃዎች መውሰድ የበለጠ ዋጋ ይኖረዋል። ልጅ ወልደማርያምን በልጅ ገብረማርያም መለወጥ ለይስሙላ ያህል ከሕዝብ ወገን መጡ የሚባሉ አንዳንድ ሰዎችን መሾም ብቻ ትግሉ መመሪያ የሚያስፈልገውን ዝርዝር ፕሮግራምና ለዘለቄታው ዋስትና የሆነውን የሰፊው ሕዝብ ሱታፌ ሊተኩ አይችሉም።

ለምሳሌ ትላንት የተወሰደው እርምጃ – አጤ ኃይለሥላሴ ንብረቴ ነው በማለት የሚያናፉበት ቤተመንግሥት የሕዝብ መደረጉን፣ አጤ እንዴት አድርገው የሕዝብን ሃብት ለባለመዋሎቻቸው በመርጨት እንደሚያባክኑ ለሕዝብ መገለጡ – ደርጉን በሕዝብ ዘንድ የሚያስወድደውነና ሙሉ ድጋፍ የሚያሰጠው ነው። በሌላው በኩል ደግሞ ይህ አልፎ አልፎ ብቅ የሚለው ነጠላ ድርጊት ግልጥና ሀቀኛ የሆነን ጠቅላላና ዝርዝር ፕሮግራም ለሕዝብ መግለጥ አስፈላጊነትና አስቸኳይነት ከቶ አይቀንሰውም።

አሁን ሕዝቡ ከደርጉ ከሚጠባበቃቸውና ደርጉም በአስቸኳይ መውሰድ ከሚገባው እርምጃዎች መካከል የሚከተሉት ሊጠቀሱ ይገባል:-

  1. የልጆች መንግሥት ወደዚያ ተወግዶ ከወታደርና ከሲቪል የተወጣጣ የተራማጆች ጊዜያዊ መንግሥት ውሎ ሳያደር እንዲቋቋም፣
  2. የዚህን ጊዜያዊ መንግሥት መቋቋም ለማፋጠን ሰፊው ሕዝብ በትግሉ እንዲሳተፍ ካሁኑ ያለምንም የጊዜ ገደብ የንግግር፣ የጽሑፍ፣ የመሰብሰብና የፖለቲካ ማህበር የማቋቋም ነጻነት በሥራ ላይ እንዲውል እንዲደረግ፣
  3. የመሬት ይዞታ ጣራ ዝቅ ተደርጎ ተወስኖ መሬት ለጢሰኞች እንዲደለደል፣
  4. አሠሪዎች ሠራተኛውን ከሥራ ማባረራቸው እንዲከለከል፣ ከሥራ የተባረሩ እንደ ብላቴ እርሻ ሠራተኞች ያሉት በአስቸኳይ ወደሥራቸው እንዲመለሱ ትእዛዝ እንዲተላለፍ፣ ከአሁን ጀምሮ ምንም አይነት ሥራ እንዳይዘጋ፣ በቅርብ የተዘጉትንም የሥራ ቦታዎች /ፋብሪካዎች ወዘተ. / በሙሉ በሠራተኛውና በመንግሥቱ ትብብር እንዲካሄዱ እንደገና መክፈት፣ የኑሮ ዋጋ ማስተካከያ የደሞዝ ጭማሪ እስካሁን ላልተደረገላቸው ሠራተኞች እንዲደረግ፣
  5. የድርቅ ቀበሌዎችን ችግር ለማቃለል፣

ሀ/ ከሃገርና ከውጭ ሃገር እርዳታ በሰፊው እንዲጠየቅ፣ እንዲሁም ከመንግሥቱ ልዩ ባጀት እንዲመደብላቸው፣

ለ/ ታማኝና ችሎታ ያላቸው ሰዎች የዕርዳታውን ማከፋፈል ሥራ እንዲያከናውኑ፣ አሁን የሚደረገው የእርዳታውን ገንዘብ ማባከን ጉዳይ ቶሎ እንዲወገድና በአጥፊዎች ላይ ከባድ እርምጃ እንዲወሰድ፣

ሐ/ ተማሪዎች ከዚህ በፊት ቀደም ብለው ባቀረቡት ሀሳብ መሰረት የአስቸኳይ ጊዜ ፕሮግራም ታውጆ፣ ት/ ቤቶች ተዘግተው ተማሪዎች ለተወሰነ ጊዜ በድርቅ ቀበሌዎች የእርዳታ ማከፋፈልና የልማት ተግባሮችን እንዲያከናውኑ፣

  1. እስካሁን ያልተፈቱ የፖለቲካ እስረኞች በፍጥነት እንዲፈቱ፣
  2. አያሌ ያልታሰሩ የሕዝብ ጠላቶች አሁንም ተንደላቀው ግፍ በመፈጸም ላይ ስለሚገኙ በሙሉ እንዲታሰሩ፣ በተለይም የፊውዳሉ ሥርአት ቁንጮ በመሆናቸው ሕዝቡን የበደሉና ያስበደሉ፣ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ለተፈጸመው ግፍ ሁሉ ዋና ተጠያቂ የሆኑት አጤ ኃይለሥላሴና ንጉሳዊው ቤተሰብ ተይዘው ለፍርድ እንዲቀርቡ፤ ከሕዝብ ላይ በግፍ የተሰበሰበው የንጉሣዊው ቤተሰብ ሀብት በሙሉ በመንግሥት እንዲወረስ፣
  3. ሙሉ ዲሞክራሲያዊ መብቶችንና ነፃነቶችን የሚሰጥና የሰፊውን ሕዝብ ኑሮ ለማሻሻል የሚችል ሕገ መንግሥት በቶሎ ታውጆ ሥራ ላይ እንዲውል፣

እነዚህና መሰሎቻቸው እርምጃዎች አጣዳፊነታቸው ታውቆ በሥራ ላይ ባይውሉ ደርጉ ከትልቅ ኃላፊነት ላይ መውደቁን በጥብቅ እንዲያስብበት ያስፈልጋል።

 

ከሰፊው ሕዝብ ጋር ወደፊት እንራመድ
Scroll to Top