ልዩ እትም 2 1970

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ልዩ እትም፣    ሚያዝያ 18፣ 1970 

የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ

በዚህ ልዩ እትም፣ መኢሶን ሜይ ዴይ መከበር ከጀመረበት ክ1967 ዓ.ም ጀምሮ እስከዛሬ የወዛደሩ መደብ ያሳለፈቻውን ትግሎች፣ ያገኛቸውን ድሎችና ያጋጠሙትን መሰናክሎች ያስታውሳል። የአድሃሪ እንቅስቃሴዎችን ለመመከት ሰፊው የገጠር ሕዝብ በብሄረሰቡ ዴሞክራሲ ጥያቄዎች ስር መደራጀት መጀመሩ ፣ የቢሮክራሲው ጡንቻ መፈርጥም፣ ከባድ የሆነ ረሃብ በሰሜን መታየት መጀመሩ፣እነዚህና ሌሎች ሁኔታዎችም ዛሬም ኢትዮጵያ ከባድ ችግር ውስጥ እንዳለች አመለካች መሆኑን ያስገነዝባል።አሁንም ሃቀኛ ተራማጆች አንድነታቸውን አጠናክረው ለዴሞክራሲ መብቶች እንዲታገሉ በድጋሚ ጥሪ ያቀርባል።

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ለሰፊው ሕዝብ ሰራተኛ ገበሬ፣ ነጋዴ፣ ወታደር፣ ምሁር መብትና ጥቅም የሚታገል ጋዜጣ

የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ይቅደም

 
ልዩ እትም                                                                    ቀን 18/08/70

 

ሜይ ዴይ -1970

ሜይ ዴይ (የወዛደሩ ቀን) በኢትዮጵያ አደባባዩች ላይ ለአራተኛ ጊዜ የሚከበርበት ቀን ተቃርቧል። በኢትዮጵያ አቆጣጠር ሜይ ዴይ 1970 ሚያዚያ 23 ቀን ይውላል። ወዛደሮች ያለፈውን ትግላቸውን የሚያስታውሱበት፣ ለመጪው ትግላቸው በህብረት የሚሰለፉበት፣ የአለም ወዝአደሮች ሁሉ የትግል አንድነታቸውን የሚገልፁበት ቀን ነው። በሜይ ዴይ ዕለት የአለም ወዝአደሮች በመላ በየአደባባዩች ላይ ወጥተው ከተሞችን ያጥለቀልቃሉ። ታሪካዊ ተልኳቸውን በከፍተኛ ድምፅ ያሰማሉ።

የኢትዮጵያ ታጋይ ወዛደሮችና ሃቀኛ አጋሮቻቸው ሁሉ ለዚህ የትግልና የአንድነት ቀን አየተዘጋጁ ናቸው። በያካባቢው፣ በየፋብሪካው ውይይቶች እየተካሄዱ፣ መፈክሮች እየተሰበሰቡ ሰልፎች ረድፋቸውን እየያዙ ናቸው የቀኝ አደርባዩችን አስመሳይ ተራማጆችም ዕለቱን በዓላቸው ለድረግ እየተሯሯጡ ናቸው።

ሜይ 1970፣ በውነትም “ታላቅ ትርዒት” ሳይሆን አይቀርም። ሁሉም ወገኖች ካምናውና ከካቻምናው የተለየ እንደሚሆን እየተናገሩ ናቸው። በዚህ ግምገማ በመካከላቸው ልዩነት ያለ አይመስልም።

የ1967 ዓ.ም ሜይ ዴይ ለራሱ ለወዛደሩ መደብ እንኳ አስከዚህም ድረስ ሳይሰማውና ሳይታወቀው ያለፈ ቀን ነበር። እንደ እውነቱም ከሆነ በዚያን ጊዜ፣ ከመንግሥት አንስቶ በልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ ስለ ሜይ ዴይ ያለውን ንቃተ ህሊና እስከዚህም የዳበረ አልነበረም። መለስ ብለን ብናስታውስ፣ “በኢትዮጵያ ሶሻሊዝም” ዘመን፣ ብሄራዊ በዓሎች ለመጀመሪያ ጊዜ ሲታወጁ፣ ሜይዴይ ከዝርዝሩ ውስጥ አልነበረም። በዚህ ለይ በወዝአደሩ መደብ ውስጥ ከፍተኛ ውዥንብር ነበር። ኢሠአማ ተከፋፍሎና በስልጣን ሽኩቻ ተተራምሶ ነበር። የንዑስ ከበርቴው መደብ ቀኝ ክንፍ፣ በኢሰአማ አመራር አካባቢ ተሰግስጐ ነበር። መንግሥትም ይከተለው በነበረው የተተራመሰ ፖሊሲ (የጉልበት ፖሊሲ ጭምር) የወዛደሩን መደብ አሸሽቶትና አስቆጥቶት ነበር።. . . ወዘተ። ስለሆነም፣ ከዚህ በላይ እንዳልነው፣ የ1967 ዓ.ም ሜይ ዴይ በኢትዮጵያ ወዛደሮች፣ የትግል ታሪክ ውስጥ ወደያውኑ ትዝ የሚሉ ሁኔታዎችን ሳይጥል አለፈ።እለቱ እንዴት እንዳለፈ የሚያስታውሱት ጥቂቶች ናቸው።

በ1968 ዓ.ም ግን ሁኔታው ፍፁም ተለወጠ።

የወዛደሩ ወደብ፣ በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ፣ ይህ ነው በማይባል ልፋት፣ በንዑስ ከበርቴው መደብ ቀኝ ክንፍ ርዕዩተ ዓለምና የፖለቲካ መስመር ተበከለ። የብዙ ሠራተኛ ማህበሮች አመራሮች በንዑስ ከበርቴው ቀኝ ክንፍ መዳፍ ውስጥ ወደቁ። የወዛደሩ ቤት፣ አሠአማ፣ የንዑስ ከበርቴው ቀኝ ክንፍ ጉሮኖና ፀረአብዮት ማስተናገጀ ጽ/ቤት ሁኖ ነበር። 1967/68 ባጭሩ፣ የወዝ አደሩ መደብ ለራሱና ለአጋር መደቦች ሳይሆን፣ ለንዑስ ከበርቴው መደብ ቀኝ ክንፍ የፖለቲካ ግቦች አምርሮ የታገለባቸው ዓመቶች ነበሩ። ይሁንና፤ በ1967/68 ዓ.ም ደግሞ፣ የአብዩቱ ሰፈር ኃይሎች በወዝአደሩ መደብ ውስጥ ቀስ በቀስ መሰረት አየጣለ የመጣባቸው ዓመታቶችም ነበሩ። በዚህ ጊዜ ውስጥ፣ በጠቅላላው በህብረተሰቡ ውስጥም፣ በተለይም በወዛደሩ መደብ ውስጥ፣ ከፍተኛ ርዕዩተዓለምና የፖለቲካ እንቅስቃሴዎችች ተካሂደው ነበር። የንዑስ ከበርቴው መደብ ቀይ ክንፍ ድርጅት ከሆኑ ከኢህአፖ ጋር ይፋ የሆነ ርዕዩተ-ዓለማዊ ክርክሮችን የፖለቲካ መስመር ትግሎች ተደርገው ነበር። እንደዚሁም፣ በየፋብሪካውና በየሥራ ቦታው፣ የወዛደሩን መደብ ከንዑስ ከበርቴው መደብ ቀኝ ክንፍ አሠራር ለማላቀቅ በርካታ ውስብስብና መራራ ተጋድሎዎች ተፈፅመው ነበር።

ስለሆነም፣ የ1968 ዓ.ም ሜይ ዴይ ሲከበር፣ ምንም እንኳ የኢህአፖ መፈክሮችን ጥያቄዎች (“ጊዚያዊ ሕዝባዊ መንግሥት፣ የሠራተኛው ደመወዝ 30፣ የእህል ዋጋ 60፣ 120፣ ብር. . . .) አደባባዩችን ቢያጥለቀልቁም፣ የአብዩቱ ሰፈር መፈክሮች ጐልተው ለመታየት በቅተው ነበር። እንደሚታወሰው በዕለቱ፣ “ጊዚያዊ ሕዝባዊ መንግሥት” በሚለው ፀረ-ሕዝብና ፀረ-አብዮት መፈክር ላይ በትልቁ ተስሎ የታየው X የስሌት ማስታወሻ ብቻ ሳይሆን፣ የወዛደሩን መደብ በ1968 ሜይ ዴይ፣ በወዛደሩ ታሪክ የትግል መደብ ውስጥ አንድ አዲስ ምዕራፍ የተገለጠበት ቀን ነው ብንል ስህተት አይሆንም ።

ከዚህ ጊዜ ወዲያ ኢህአፖ ከወዛደሩ መደብ ውስጥ መተፋት ጀመር። የወዛደሩ መደብ በራሱ ርዕዩተ- ዓለም ለመታነፅ እጅግ ጓጉቶ ተነሳ። የፈራረሱትንና የተተራመሱትን ማህበሮችን እንደገና አቋቋመ። ኢህአፖም ነግሶባቸው የነበረውን የሠራተኛ ማህበራት አመራር አንድ በአንድ እንድትለቅ ተገደደች። በ1968/69 ዓ.ም በተደረገው ተጋድሎ፣ ኢሠአማ ታህሳስ 29/1969 ሲመሠረት፣ ዕለቱ በእውነትም የአብዩትን ሰፈር አሸናፊነትን የሚያረጋግጥ ሆኖ ከታሪክ መዝገብ ውስጥ ለመስፈር በቅቷል። ከዚህ በኋላ፣ጥር 68/1969 ዓ.ም በራሱ በደርጉ ውስጥ መሽገው በነበሩት ኢህአፖዎች ላይ አብዮታዊ እርምጃ ሲወሰድ፣ የአብዩቱ ሰፈር በመንግስት ደረጃ ጭምር አሸናፊ ሆኖ ለመውጣት ቻለ። ከእንግዲህም፣ የንዑስ ከበርቴው መደብ ቀኝ ክንፍ ኮከብ እየጠለቀች ስትሄድ፣ የአብዮቱ ሰፈር ኮከብ እየደመቀች ሄደች።

የ1969 ዓ.ም. ሜይ ዴይ ከሦስት ወሮች በኋላ ሲከበር የአብዮት ሰፈር ኮከብ ከከተማ ከተማ አይላ ደምቃ ታይታ ነበር። አደባባዮች ሁሉ በአብዮቱ ሰፈር መፈክሮች ፈክተው ነበር። የወዛደሩም መደብ፣ ከእንግዲህ ለመደቦችና ላጋሮቹ ብቻ እንጂ፣ የጨቛኝ መደቦች ተቀጽላ ሆኖ መቆየት እንደማይፈልግ በገሃድ አሳይቶ ነበር። በእውነትም፣ በዚያች ዕለት፣ [የማይነበብ – አዘጋጆቹ] አብዮታዊው ጎዳና፣ በኢትዮጵያ አደባባዮች ላይ ሁሉ ፋሲካውን አክብሮ ነበር። በዕለቱ ታሪካዊነት ያልተመሰጠ አንድም ሃቀኛ አብዮታዊ፣ አንድም አገር ወዳድ፣ አንድም ዲሞክራት አልነበረም።

ይሁንና የዚየች ዕለት ውጤት በቀላሉ የተገኘ አልነበረም። በተጠቀሱት ሦስት ዓመቶች ውስጥ፣ ታጋይ ወዛደርና ሃቀኛ አብዮታውያን ያካሄዷቸው የጋራ ትግሎች እንደ አደርባዮች ጎዳናዎች ያማረና የለሰለሱ አልነበሩም። ለድሎች መገኘት ታጋይ ወዛደሮችና ሃቀኛ አብዮታውያን ከጓድ ፍቅሬ መርዕድ አንስቶ እስከ ጓድ ቴዎድሮስ በቀለ ድረስ ሕይወታቸውን ሰውተዋል። የነጓድ ገብረእግዚአብሄር፣ የነጓድ ብርሃኔ፣ የነጓድ ሰናይ ልኬ፣ የነጓድ ኮለኔል ዳንኤል ሁሉና ሰማቸውን  ዘርዝረን የማንጨርሰው ጓደኞቻችንና ወዳጆቻችን ህይወት ያለፈው በዚሁ የመራራ ትግል ወቅት ነው። በነዚያ ወሮች ውስጥ ስንቱ ታጋይ ወዛደር፣ ስንቱ አብዮታዊ ምሁር፣ ስንቱ፣ ስንቱ. . . ወደቀ?

እነዚያ፣ ለወዛደሩ መደብ እውነተኛ ኃያልነት ሲታገሉ የወደቁት ጓዶቻችንና ወዳጆቻችን፣ በአብዮታችን ታሪክ ውስጥ የክብር ቦታ ይዘው ለዘላለም ይኖራሉ። ሃቀኛና ቅን ተጋድሏቸው በታጋይ ወዛደሮች፣ በሃቀኛ አብዮታውያን፣ በአገር ወዳዶችና በዲሞክራቶች ልቦና ውስጥ ለዘላለም ሲያበራ ይኖራል። ምንግዜም አንረሳቸውም።

ወደ ርዕሳችን እንመለስና፣የዘንድሮውስ? ብለን እንጠይቅ።

የዘንድሮውስ ካለፉት ዓመቶች፣ በተለይም ካምናው ሜይ ዴይ በብዙ ረገዶች የተለየ ይሆናል የተለየ የሚያደርጉትም ምክንያቶች በርካታ ናቸው።

የ1969 ዓ.ም. ሜይ ዴይ እንደዚያ የደመቀና የፈካ ይሁን እንጂ፣ በክፉ አየር የታመቀ እንደነበርም ብዙዎች ያስታውሳሉ። እንደሚታወሰው፣ ገና የጥር 1969 ዓ.ም. ድልና ታሪካዊነት የተጻፈባቸው ቀለሞች ሳይደርቁ እንኳ፣ በአብዮት ሰፈር ውስጥ አደገኛ አለመተማምንና ጥርጣሬዎች ተስፋፍተው ነበር ከዚህም የተነሳ በርካታ አሳዛኝና አሳሳቢ ነገሮች ደርሰዋል።

እንደሚታወሰው፣ ገና ከጥር በፊት አብዮታውያን በአንድ የጋራ ድርጅት ጥላ ሥር ለመሰብሰብ ውይይቶችን ጀምረው ነበር። በየካቲት 1969 ዓ.ም. የጋራ መግለጫ አውጥተው ነበር። በመጋቢት 1969 ዓ.ም. “ኢማሌድህን” መሥርተው ነበር። ይሁንና ገና በጠረጴዛ ዙሪያ ከመቀመጣቸው ጠቅላላው አየር በአሉባልታና በሃሳባዊ ክሶች ተበከለ (ተመረዘ)። ከዚህም የተነሳ በርካታ አሳዛኝ ነገሮች ደረሱ። በተለይም በመኢሶን ላይ ይህ ነው የማይባል የአሉባልታና የክስ ዘመቻ ከየአቅጣጫው ወረደ። በነዚያ ወሮች ውስጥ፣ መኢሶን ለአንዳንዶች “ጠባብ ቡድን” ነበር።      

ለሌሎች “ጠባብ ብሄርተኛ” ለሌሎች ደግሞ “የነፍጠኞች ድርጅት”፣ለሌሎቹ “አዲሱ ኢህአፓ”፣ ሌሎችም “የቢሮክራት ማርክሲስቶች ጥርቅም”. . . ወዘተ እንደነበር ሁሉ የሚታወሰን ነው።

ከዚያም፣ የ1969 ዓ.ም. ሜይ ዴይ ሲቃርብ ፍትጊያው የባሰውን መናኛ እየሆነ ይመጣል። ሌላው ቀርቶ የ“ኢንተርናሽናል መዝሙርን” ትርጉም በሚመለከተው በኩል እንኳን፣ ዓይን ባወጣ አፀያፊ ቅጥፈት አስፈሪና አስቂኝ ቅስቀሳዎች ተካሄዱ። ሜይ ዴይ 1969፣ የመኢሶን አርማ በየአደባባዩ በብዛት መታየት ደግሞ፣ አንዳንዶችን ክፍሎች ያስቆጣቸዋል። መኢሶን እስከሚያውቀው ድረስ “በዕለቱ፣ እያንዳንዱ የኢማሌድህ አባል ድርጅት የራሱን አርማና የህብረቱን መፈክሮች ይዞ ይውጣ” በሚል በቅድሚያ ስምምነት በተደረሰበት ጉዳይ ላይ እንኳን መካካድ ይደርሳል።

ይልቁኑ፣ በተለይ ለሚያዚያ ወር 1969 በኋላ፣ በመኢሶን ላይ የተጀመረው ዘመቻ ይቀጥልና “መኢሶን ብቻውን ፓርቲ ለመሆን ይፈልጋል”፣ “መኢሶን ሥልጣንን ይፈልጋል”፣ “መኢሶን የታሪክ ሽሚያ ይዟል”፣ “መኢሶን ወዛደሩን አስታጠኩ ይላል”፣ “መኢሶን፣ መኢሶን፣ መኢሶን. . .” የሚሉ አሉባልታዎችና መሠረተ ቢስ ክሶች ይከምራሉ፣ ይነዛሉ፣ ይረጫሉ. . .ወዘተ መኢሶን፣ በተፈጠረው አደገኛና በአሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ፣ የክሶችንና የአሉባልታዎችን ሂሳዊነት እያስረዳ መግለጫዎችን ቢያወጣ፣ በግል ውይይቶች ለማስረዳት ቢሞክር፣ የኢማሌድህን ፕሮግራም ሺህ ጊዜ ቢፈርም፣ እንዳባባሉ “ቢምል፣ ቢገዘት ሰሚ ጆሮ ገለልተኛ ዳኛ ይጣል። ከነጭራሹ በሚያቀርባቸው ቅን ሃሳቦች ላይ እንኳን፣ የጥርጣሬ ዓይን ያንዣብብ ጀመር። በዚያን ጊዜ፣ በዚያው አካባቢ “መኢሶን በቅርብ ጊዜ የሚመታው ድርጅት መሆኑን” የሚያሳውቁም ጥቂቶች አልነበሩም በውነትም ደግሞ፣ ከለየላቸው አድሃሪዎች እስከ አስመሳይ ተራማጆች ድረስ መኢሶንን ለማስመታት ያልተደረገ ዘመቻ፣ ያልተቀነጠሰ ቅጠል፣ ያልተሸነቆረ ቀዳዳ አልነበረም። ብዙ ነገሮችም ይደርሳሉ።

በመጨረሻም፣ እንደሚታወቀው መኢሶን ብዙ ከጣረና ከደከመ በኋላ የትግል ስልት ለውጥ እንዲያደርግ ይገደዳል። መኢሶን የትግል ስልት ለውጥ እንዲያደርግ ከተገደደባቸው ምክንያቶች አንደኛው የ1969 ዓ.ምን ሜይ ዴይ ያመቀው ክፉ አየር የበከለው የፖለቲካ ሁኔታም እንደነበር የሚታወስ ነው። በተረፈ መኢሶን የትግል ስልት ለውጥ እንዲያደርግ የተገደደባቸውን ምክንያቶች በተለይ ሰህድ 61 ላይ ለሰፊው ሕዝብ በገሃድ ሰለተገለፀ፣ በእነርሱ ላይ መመለሱ አስፈላጊ አይሆንም። ይልቁኑ፣ ወደ 1970 ዓ.ም. ሜይ ዴይ እንመለስና የዛሬውን ሁኔታ እንመልከት።

የ1970 ዓ.ም. ሜይ ዴይ የሚከበረው እጅግ ውስብስብ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ነው። የሃገሪቱ ጠቅላላ ሁኔታ፣ ባለፉት አራት ዓመቶች ውስጥ፣ ምናልባት እንደዛሬም ውስብስብ፣ እንደዛሬም ዝብርቅርቅ እንደዛሬም የተተራመሰ ሆኖ አያውቅም። የዛሬውን ሁኔታ በሻምበል ፍቅረ ሥላሴ አነጋገር እንግለፅ ብንል፣ ጊዜው በውነትም “ፍፁም ፍፁም የሚያዝናና አይደለም” ወይንም ደግሞ በመቶ አለቃ ታምራት ፈረደ አነጋገር ለማብራራት “ሳናውቀው እንዳያመልጠን የሚያሰጋ . . ነው”።

ዛሬ በአንድ በኩል የምሥራቅ ድላችን አለ። በዚህ በኩል “እፎይታም” የገባ ይመስላል። ይሁንና እርሱ ራሱ ይዟቸው የመጣ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የሶሻል ጥያቄዎች ደግሞ በርካታ ናቸው። በዚህ ላይ ደግሞ ገና “ያልተነካ” የሰሜኑ ጉዳይ አለ። በሌላ በኩል በመሃል ኢትዮጵያ ቢሆን ጊዜው በሕዝብና በመንግሥት ናላ ላይ እጅግ ከብዷል። በጦርነቶች መካከል እያለ የኢኮኖሚ፣ የሶሻልና የፖለቲካ ችግሮች ተፈጥረዋል። በተለይ በወሎ ውስጥ እንደገና ከባድ ድርቅ ገብቷል። እኛ እስከምናውቀው ድረስ፣ ከየካቲት 1969 ወዲህ፣ ሃገሪቱ በዛሬው ዓይነት ጠቅላላ ክሪዝና የፖለቲካ ትርምስ ውስጥ ወድቃ አታውቅም።

የኢኮኖሚና የሶሻል ክሪዞች በሃገሪቱ ላይ ከዳር እስከዳር ተንሠራፍተዋል። በከተሞችና በገጠር ውስጥ በስፋት የሚታዩት የእህል እጥረት፣ የሸቀጣ ሸቀጦችና የማገዶ መጥፋትና መወደድ፣ የትራንስፖርትና የንግድ መዛባት፣ የፋብሪካዎች መቆም፣ ጠቅላላ የኑሮ ውድነት፣ የሥራ አጥነት የህክምና እጥረት. . . ወዘተ ሁሉ፣ በሰፊው ሕዝብ ጫንቃ ላይ እጅግ ከብዷል። ሁሉም በየቤቱ ሁሉም በየሥራ መስኩ አልገፋ ስላለው “ኑሮ” እያማረረ ነው። ከተማውም ከገጠሩም ባጠቃላይ ክሪዝና ትርምስ ተነክቷል።

ይሁንና፣ መንግሥትም ከብዙ ዕውነተኛና፣ ይልቁኑ ከብዙ ሰው ሰራሽ፣ ምክንያቶች የተነሳ የማስታገሻ እርምጃዎችን እንኳ ለመውሰድ አልቻለም። ክሪዞች በየእለቱ የባሰውን እየተስፋፉና እየተወሳሰበ በመዳበር ላይ ናቸው።[የማይነበብ – አዘጋጆቹ] በመንግሥትና በሰፊው ሕዝብ መካከል እየሆኑ በመሄድ ላይ ናቸው። አድሃሪ የሲቪልና የሚሊተሪ ቢሮክራሲ ደግሞ በመሃል ሰፋሪው የልባቸውን እያሻጠሩ ናቸው። ጠቅላላውን ሁኔታ ለፀረ-አብዮቱ ጥሪ እያመቻቹት ናቸው። ይህ አንደኛው አስጊና አሳሳቢ ሁኔታ ነው።

ሁለተኛ፣ የፖለቲካውን ሁኔታ በሚመለከተው በኩል፣ ጠቅላላው ሁኔታ እንደዚሁ ተተራምሷል። በመንግሥት በኩል፣ ከዚህ በላይ የጠቀስናቸው የኢኮኖሚና የሶሻል ችግሮች እያሉም ቢሆን እንኳ በትክክለኛው ፖለቲካ፣ ፕሮፖጋንዳና ቅስቀሳ አብዮቱንና ሰፊው ሕዝብ ለመገናኘት አልተቻለም። እንዲያውም “. . . ካያያዝ ይቀደዳል” እንዲሉ፣ በዛሬው ወቅት በባህሪያቸው የሁለተኛ ደረጃነትን ሥፍራ ሊይዙ የሚገባቸው ቅራኔዎች ባፋጣኝ ወደ አንደኛ ደረጃነት እየተቀየሩ ናቸው። ስለሆነም፣ በዛሬው ጊዜ ባንድ በኩል በመንግሥትና በሕዝባዊ ድርጅቶች፣ በመንግሥትና በብሄረሰቦች፣ በመንግሥትና በአርሶአደሩ፣ በመንግሥትና በንግድ ቡርዧው፣ በመንግሥትና በሃቀኛ ተራማጆች መካከል እየተባባሱ የመጡ በርካታ ቅራኔዎች በብዛት እየታዩ ናቸው። በሌላው በኩል ደግሞ፣ የቀኝ አደርባዮች ከሚከተሉት የአደርባይነት ፖለቲካ የተነሳ፣ ሌሎች ቅራኔዎች እንዳሸን ፈልተዋል። በተለይ እነዚህኞቹ ክፍሎች በጠቅላላው ትርምስ ላይ ቤንዚን እያርከፈከፉ መሆናቸው ደግሞ ገሃድ ነገር ሆኗል።

በዚህ አንፃር፣ በሃገሪቱ የፖለቲካ ዓለም ውስጥ፣ የቀኝ አደርባይነትና አስመሳይ ተራማጅነት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ተሰፋፍቷል። አድሃሪው የሲቪልና የሚሊተሪ ቢሮክራሲ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በራሱ በደርጉ ውስጥ ተደላድሎ መሽጓል። የትላንቶቹ የኢህአፓ ቅጥር ነፍሰ ገዳዮችና ጀሌዎች፣ ባንዳንድ ድርጅቶች ውስጥ እየገቡ የቀበሮ ጉድጓዳቸውን ምሰዋል። የእነዚህኞቹን ሁኔታ በማሌሪድ አነጋገር እንግለፀውና “የትላንቶቹ የኢህአፓ ቅጥር ነፍሰ ገዳዮችና ጀሌዎች ባንዳንድ ድርጅቶች እየተመለመሉ፣ እንዲያውም በሕዝባዊ ድርጅቶች ላይ ፈላጭ ቆራጭ ሆነው ተሰይመዋል . . . ወዘተ”። ባጭሩ፣ ፀረአብዮት እንደዛሬም አመቺ የማጥቂያ ሠፈሮችን ከመዳፉ ውስጥ አስገብቶ አያውቅም። በአብዮት ስም ደግሞ፣ እንደዛሬም ለፀረአብዮት የሥጋጃ ምንጣፍ ተነጥፎለት አይውቅም።

በዚህ ላይ ወደ ዝርዝር እንግባ ብንል ደግሞ፣ የኢማሌድህ አባል ድርጅቶች በሕዝባዊ ድርጅቶች አናት ላይ ለመቀመጥ በሚያደረጉት እሽቅድምድም ባንድ በኩል እርስ በርስ እየተተራመሱ ናቸው። በሌላ በኩል ደግሞ ሕዝባዊ ድርጅቶችን እየከፋፈሏቸውና እርስ በርስ እያጋጠሟቸው ናቸው። ሌሎቹም፣ መንግሥታዊ ሥልጣንን ተገን በማድረግ ሕዝባዊ ድርጅቶችን መንግሥታዊ አካል /መንግሥታዊ ድርጅት/ እያደረጓቸው ናቸው። አንዳዶቹንም አድርጓቸዋል። ስለሆነም፣ በዛሬው ወቅት ለምሳሌ በከተሞች ውስጥ፣ በቀበሌ አመራርና በ“ካድሬዎች”፣ በሰፊው ከተሜ ሕዝብና በ“ካድሬዎች”፣ በቀበሌ አመራርና በሰፊው ከተሜ ሕዝብ፣ በመንግሥት ሠራተኛነትና በ“ካድሬዎች”፣ በሕዝባዊ ድርጅቶች “ካድሬዎች”፣በሕዝባዊ ድርጅቶች ውስጥና በመካከላቸው፣ በሕዝባዊ ድርጅቶችና በመንግሥታዊ ሥልጣን፣ በኢማሌድህ አባል ድርጅቶ ውስጥና በመካካላቸው፣በኢማሌድህና በመንግሥታዊ ሥልጣን፣ በኢማሌድህ በሃቀኛ ተራማጆች፣ በመንግሥትና በሃቀኛ ተራማጆች. . . . ወዘተ መካከል ያሉት ቅራኔዎች ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ እየሰፋ መጥቷል። በገጠርም ውስጥ፣ ባንድ በኩል በአርሶ አደሩና በቢሮክራሲው (አስተዳደር፣ የደርግ አባሎች፣እዝ. .) በሌላ በኩል በአርሶ አደሩና በሕዝብ ድርጅት መካከል ያሉት ቅራኔዎች እንደዚሁ እየሰፉና አስከፊ እየሆኑ መጥተዋል።  በተጨማሪ፣ በተለይም ገጠሩን በሚመለከተው በኩል ደግሞ፣ በመንግሥትና በብሄረሰቦች መካከል ያለው ቅራኔ እንደዛሬም ተስፋፍቶ አያውቅም። አምናና አቻምና “ትጥቅ ትጥቅ” ይል የነበረው ሰፊ የገጠር ሕዝብ፣ በዛሬው ወቅት በብዛት በብሄረሰቡ ዲሞከራሲያዊ ጥያቄዎች አካባቢ እየተሰበሰበ ነው። በዚህ አንፃር ከታወቁት የኤርትራ፣ የትግራይ፣ የአፋር የባሌና ሲዳሞ ብሄረሰቦች እንቅስቃሴዎች በተጨማሪ፣ በሲዳማ፣ በደረሳ፣ በወላይታ፣ በከምባታና ሃድያ፣ በከፋ፣ በኢሊባቡር፣ በወለጋ፣ በሸዋ. . . ወዘተ አያሌ የብሄረሰብ እንቅስቃሴዎች እየተፈጠሩ ናቸው። ባጠቃላይ አሳሳቢ ጊዜ መጥቷል።   

እንግዲህ የ1970 ዓ.ም. ሜይ ዴይ የሚከበረው፣ ከሞላ ጎዳል ከዚህ በላይ ባመለከትነው ሁኔታ ውስጥ ነው። ያም ሆኖ፣ የትግሉ ቀን ከፍተኛ “በዓል”፣ ከፍተኛ “ትርዒት” ሆኖ መከበሩ አይቀርም። በእኛ፣ ቀኝ መንገደኞች ተብለን በምንጠራው ላይ ደግሞ፣ ውግዘትና እርግማን መሠፈራቸው አይቀርም። የትግሉ ቀን፣ በውነትም “በዓል” ሁኖ ይውላል። “የትርዕይት- በዓል” ደራሲዎች ካሁኑ ሊዘጋጁበት ይችላሉ።

ይሁንናም፣ ክሪዞች እንዳሉ ናቸው። በመፈከር ቦምቦች የሚፋቁ አይሆኑም። ትዕይንቶችም አይሸፍኗቸውም። ይልቁኑ፣ ሃቀኛ ተራማጆች፣ አገር ወዳጆችና ዲሞክራቶች በሆነው ባልሆነው መሰብሰብ፣ መወያየትና የጋራ ትግል ማካሄድ አቅቷቸው፣ ውስጥ ውስጡን ተብሰለሰሎ ባመጣው ፀረ-አብዮት እንዳይቀደሙ የሚያሰጋ ይሆናል። የአብዮቱ ሰፈር በመፈክሮች [የማይነበብ – አዘጋጆቹ] ተውቦ ካመለከትነው አደጋ ውስጥ እንዳይወድቅ የሚያሳስብ ነው።

መኢሶንን በሚመለከተው በኩል፣ ድርጅታችን የትግል ስልት ለውጥ ካደረገ እነሆ ስምንት ወሮች አልፈዋል። በዚህ ጊዜ ውስጥ፣ የቀኝ አድርባዮችና አስመሳይ ተራማጆች ካልጠፋ ሥራና ካልጠፋ ጠላት በድርጅታችን ላይ ተረባርበዋል። በርካታ ተተኪ የማይገኝላቸው የድርጅቱ ታጋይ ጓዶች፣ ወዳጆችና ደጋፊዎች በየሥፍራው ወድቀዋል። አያሌ የድርጅት አባሎች፣ ወዳጆችና ደጋፊዎች በየእስር ቤቱ እየማቀቁ ናቸው። በድርጅቱ አባሎች፣ ወዳጆችና ደጋፊዎች ላይ ከፍተኛ የክትትል የእስራት ዘመቻ እየተካሄደ ነው። እንደውም፣ ሌላው ሌላው ቀርቶ “መኢሶንን ለመምታት” አንዳች ዓይነት ያሰፈሰፈ ሁኔታ እንዳለም ከዕለት ዕለት ገሃድ እየሆነ መጥቷል።

ካንዳንድ ንግግሮች (መጋቢት 28) ለመገንዘብ እንደሚቻለው አስደናቂ የሆነ የታሪክ ማመሳሰል እየተሠራ ነው። አንዳንዶቹም፣ በከተማው ውስጥ ላለው የእህል መጥፋት እንኳ መኢሶንን፣ በነርሱ አነጋገር “ቀኝ መንገደኞችን”፣ ተጠያቂ ለማድረግ እየቀሰቀሱ ናቸው። ሌሎችም ራሳቸው ያሰማሯቸውን “ካድሬዎች” ዛሬ ደግሞ እነሱው መልሰው “ቀኝ መንገደኛ” በማለት ክርስትና እያነሱ በተዘዋዋሪ በድርጅታችን ላይ ለመዝመት እያሰፈሰፉ ናቸው። በቀበሌዎች በፋብሪካዎችና በሥራ ቦታዎች ሁሉ በሆነ ባልሆነው ጠብ እየጫሩ ናቸው። ባልገደዳቸው ሬዲዮና ጋዜጣ በድርጅታችን ላይ አሁንም በሃሰት እየዘመቱ ናቸው። የሆነ ያልሆነውን አሉባልታ እየሰፈሩ ናቸው። . . . . ወዘተ.

ስለሆነም፣ ከነዚህም ሁሉ ምክንያቶች የተነሳ፣ መኢሶን በ1970 ዓ.ም. ሜይ ዴይ ላይ የሚጋፈጥበ ምክንያት የለውም። አባሎች፣ ወዳጆቹና ደጋፊዎቹ ሁሉ ከጠብ አጫሪዎች በመጠንቀቅ በዝግጅት በሰልፉም ላይ በርጋታ እንዲሳተፉ መመሪያ አስተላልፏል። አባሎች፣ ወዳጆቹና ደጋፊዎች ሁሉ ይህንን መመሪያ በጥብቅ እንዲከተሉ በዚህም ጽሁፍ አማካይነት በድጋሚ ያሳሰባቸዋል። ድርጅታችን፣ በሰህድ ቁ.64 ለሃቀኛ ተራማጆች ህብረት ያደረገው ጥሪ፣ በሥራ ተተርጉሞ እስክናይ ገና ብዙ ውጣ ውረድ ይኖራል። ትግሉ ገና ረጅም፣ ውስብስብና መራራ ነው። ከዚህ በፊት ደጋግመን እንዳልነው፣ በከንቱ መጋፈጥ የሰማያታትን በር አይከፍትም።

እንደዚህም ሁኖ ግን፣ አቋማችን ግልጽ ነው። ለሃቀኛ ተራማጆች ህብረት በሰህድ ቁ.64 ያደረግነውን ጥሪ ዛሬም እንደገና እናቀርባለን። ሰፊው ሕዝብ አሁንም ከመኢሶን መስመር ጋር ነው። በችግሮች፣ በብሶቶች፣ በውዥንብሩና በጭፍኑ አመፅ መካከል አሁንም አብዮትን፣ አሁንም ሃቅን፣ አሁንም ሀቅን፣ አሁንም ዲሞክራሲያዊ መብቶችን፣ አሁንም ህብረትን ይፈልጋል። ድርጅታችን በብልህነትና በአርቆ አስተዋይነት ከታገለ፣ ደጋግሞ የሚጨቀጭቀው ሃቀኛ፣ ቅን፣ አብዮታዊና ዲሞክራሲያዊ የተራማጆች ህብረት ከተመሠረተ፣ ከሁሉም በላይ በሰፊው ሕዝብ ላይ ከተማመንን መጪው ጊዜ ብሩህ ነው።

ስለሆነም፣ ለ1970 ሜይ ዴይ የሚያስተጋባቸው ጥያቄዎችም አጭርና ግልፅ ናቸው። ታጋይ ወዛደሮች፣ ሃቀኛ ተራማጆች፣ አገር ወዳዶች፣ ዲሞክራቶችና የአብዮቱ ወገኖች ሁሉ፣ ለመኢሶን ጥያቄዎች እንዲታገሉ ጥሪያችንን እናቀርብላቸዋለን።

ከመፈክሮች ይልቅ ተጨባጭ አብዮታዊ እርምጃዎች!
የታሠሩት ታጋይ ወዛደሮች፣ አብዮታዊ ምሁራን፣ አገር ወዳዶች፣ ዲሞክራቶች ይፈቱ!
በመኢሶን ላይ የሚደረገው የክትትልና የእሥራት ዘመቻ ይቁም!
ሃቀኛ፣ ቅን አብዮታዊና ዲሞክራሲያዊ የተራማጆች ህብረት ይመስረት!
ሕዝባዊ ድርጅቶችን መከፋፈልና ማጋጨት ይቁም!
ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለጭቁኖች ያለገደብ አሁኑኑ!
 በሰህድ ቁ.64 መስመር ወደፊት!  
Scroll to Top