ልዩ እትም 1 1971

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ልዩ እትም፣    ነሐሴ፣ 1971 

የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ

በዚህ ልዩ እትም፣ መኢሶን የተመሠረተበትን 11ኛ ዓመት ያስታውሳል። የኢትዮጵያ ተማሪዎች ፣ ለለዴሞክራሲ መብቶች፣ ለብሄረሰቦች እኩልነትና ለብሄራዊ ነጻነት ያደርጉ የበረውን ትግል በአጭሩ ይዳስሳል። የኢትዮጵያን ጭቁኖች አስተባብሮ ለመምራት  ግንባር ቀደም ድርጀት አስፈላጊ መሆኑን በመርዳት፣ በተለያየ የአለም ክፍል የሚገኙ ግንባር ቀደም ታጋዮች በማርክሲዝም ሌኒኒዝም የሚመራ ድርጀት በጀርመን አገር በሃንቡርግ ከተማ በ1960 ዓ.ም እንደመሠረቱ ይናገራል። ጽሁፉ መኢሶን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከኃይለ ስላሴና ከደርግ መንግስት ጋር ያደርጋቸውን  ትግሎች ያወሳል። በዚህ አጋጣሚ፣ ዛሬም ወዛደሮች፣ ገበሬዎች፣ ተማሪዎች፣ ዴሞክራቶች፣ አገር ወዳዶች፣ የጭቁን ብሄርሰብ ታጋዮች በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝቦች ቀደም ሲል የወደቁ ጓዶች የወደቁለትን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ዴሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራምን ይዘው በሕብረት እንዲጓዙ ጥሪ ያቀርባል።

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ለሰፊው ሕዝብ ሰራተኛ ገበሬ፣ ነጋዴ፣ ወታደር፣ ምሁር መብትና ጥቅም የሚታገል ጋዜጣ

የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ይቅደም

 
 ልዩ እትም                                                                        ነሐሴ 1971

 

የመላ ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ የተመሠረተበትን

11ኛ ዓመት ምክንያት በማደረግ ከመኢሶን መአከላዊ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ

ይህ ትግል ዘመን አልፎ መጭው ትውልድ መለስ ብሎ የዘመኑን ትግል ታሪክ በሚመረምርበት ጊዜ የኢትዮጵያ ተማሪዎች በመራራ ትግላቸው የፃፉት ገፅ በኢትዮጵያ ጭቁኖች የትግል ታሪክ ውስጥ አሸብርቀው ከሚታዩት ገፆች አንዱ እንደሚሆን አንጠራጠርም። ባለፉት አመታት የኃይለሥላሴን አገዛዝ ከተለያዩ አቅጣጫዎች፣ በተለያዩ ቦታዎችና በተሰበጣጠሩ ዓለማዎች እየተነሡ ያዋከቡትና ያዳከሙት ብዙ እንቅስቃሴዎችና ሕዝባዊ ትግሎች ነበሩ። ነገር ግን በተለይ ከሃያ ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ላይ ብቅ ያለው አብዮታዊው የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ከነዚህ እንቅስቃሴዎች ሁሉ ዓይነተኛ የሚያደርጉት ጠባዮች ነበሩት። በመጀመሪያ  የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ከየአቅጣጫው፣ በየቦታውና በተሰበጣጠሩ ዓላማዎች ከተነሱት ተቃውሞዎች ዘልቆ እነዚህን ሁሉ በሚያስተባብሩ አጠቃላይ መፈክሮች ሥር የሚንቀሳቀስ አገር አቀፍ ንቅናቄ ነበር። ሁለተኛ ደግሞ የኢት. ተማሪዎች ንቅናቄ ሃገራችን የደረሰችበትን የህብረተሰብ እድገት ደረጃ ጠንቅቆ ያወቀ፣ የፊውዳሊዝምንና የኢምፔሪያሊዝምን ቀንደኛ ጠላትነት የተረዳ፣ እነዚህ ጥንድ ጠላቶች ከኢትዮጵያ ምድር ካልተደመሰሱ፣ ለሃገራችን ዕድገት ለኢትዮጵያ ጭቁኖች እርምጃና ነፃነት፣ እንደማይገኝ ጠንቅቆ የተገነዘበ አብዮታዊ ንቅናቄ ነበር። እንደዚህም በመሆኑ በዚህች ምንም ዓይነት የተደራጀና ሃገር አቅፍ የሆነ የፖለቲካ ታቃውሞ ትግል በማታውቅ አገራችን የተማሪው ንቅናቄ አገር አቀፍነትና አብዮታዊነት፣ ላለፈው የተማሪ ትውልድ ከሌሎች አገሮች የተማሪዎች ንቅናቄዎች የበለጠ ኃላፊነት ጥሎበት ቆይቷል። ታጋይ ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ዘላለማቸውን ሲኮሩ የሚኖሩት ይህ የተማሪ ትውልድ ይህንን ከፍተኛ ሃላፊነት በለጋ ትከሻው ላይ ተሸክሞ ታሪክ ለጣለበት አደራ ብቁ መሆኑን በማስመስከሩ ነው።

በነዚህ የትግልና የመስዋዕትነት ዓመታት ይህ የተማሪ ንቅናቄ ኃይለሥላሴ ፋሽስታዊ አገዛዝ ባሳለፉት ፀረ ሕዝብ ኃይል በምንም ሳይፈታ “መሬት ላራሹ” “ዲሞክራሲያዊ መብቶች” “የብሄረሰቦች እኩልነት”፣ “ብሄራዊ ነፃነት” እያለ ብዙ የከፈለበትን ትግል አካሄደ። ነገር ግን ይህ ትግል ወደፊት እየገፋ ሲሄድና በአጠቃላይ የሥርዓቱ እየበሰበሰ መሄድ በያለበት የሕዝቡን ትግል ሲያስፈጽመው በተማሪው ንቅናቄ ውስጥ በግንባር ቀደምነት ለተሰለፈውና ማርክሲዝም ሌኒኒዝምን እያዋሀደ የትግል መመሪያው ማድረግ ለጀመረው የመጀመሪያው የኢት. ማርክሲስት ሌኒኒስት ትውልድ አንዳንድ ነገሮች ግልጽ ሆነው መታየት ጀመሩ። በመጀመሪያ እነዚህ ግንባር ቀደም ኃይሎች በመቀጣጠል ላይ ያለውን የኢትዮጵያ ጭቁኖች የነፃነት ተጋድሎ ከዳር እስከዳር አስተባብሮ ለመምራት ይቻል ዘንድ ይህ ታጋይ ትውልድ ከተማሪው ንቅናቄ ባሻገር የማደራጀትን ጉዳይ ካሁኑ መያያዝ እንዳለበት ተገነዘበ። ሁለተኛ ከላይ የተጠቀሱትን ዓላማዎች ከሥራ ላይ ለማዋል ለሚደራጁትና ለመሰለፉት ኃይሎች ሁሉ የተጣራና አብዮታዊ አመራር ሊሰጥ የሚችለው ኃይል በማርክሲዝም ሌኒኒዝም ርዕዮተ ዓለም የሚመራ ድርጅት መሆን እንዳለበት አመኑበት።

ከዚህ እምነት በመነሳት በአገር ውስጥ፣ በአውሮፓ፣ በሰሜን አሜሪካና በቅርብ ምሥራቅ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ውስጥ በግንባር ቀደምነት ከተሰለፉትና የድርጅትንም አስፈላጊነት ሆነ የማርክሲዝም ሌኒኒዝም መርህ ተቀብለው ትግሉን ከተማሪው ንቅናቄ ባሻገር ለመቀጠል በታሪክና በኢትዮጵያ ሕዝብ ፊት ሃላፊነትን በተቀበሉ አብዮታውያን ተሳትፎ በነሐሴ ወር 1960 ዓ.ም. በሃምቡርግ ከተማ በምዕራብ ጀርመን በተደረገው የመመስረቻ ጉባዔ ላይ የመላ ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ ተቋቋመ።

ይህ በስመ ጥሩ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ውስጥ ተፀንሶ በጊዜው በሃገሪቱ የሚገኙትን ማርክሲስት ሌኒኒስቶች አስተባብሮ የያዘው የመላ ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ ሲመሠረት ጀምሮ ዓላማዬ ብሎ የያዘው፣ ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ በረዥም ጊዜ የትግል ታሪኩ ያገኘውን ቆርጥነትና ልበሙሉነት፣ ታታሪነቱንና በራስ የመተማመን ኩራትን፣ ተመፅዋችነትንና በማንም ይሁን በማን ፊት የበታችነትን አሻፈረኝ ሲል የቆየ አመፀኛነቱን፣ በአጭሩ በዓለም ሕዝቦች ሸንጎ የማይናቅ ማንነቱን በሚያድስበት የብሄራዊ ነፃነትና ትግልና ይህችን ሃገር የሰላምና የእኩልነት የነጻነትና የብልፅግና ምድር በሚያደርጓት ሕዝባዊ አብዮታዊ ትግል ውስጥ የግንባር ቀድሞ ድርሻውን ለማበርከት ነበር።

የመላ ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ ታጋዮች ገና በዚያ በኃይለሥላሴ ዘመን ይህንን ግልፅ ዓላማ ይዘው ሲነሱ ለዚህ ታላቅና ክቡር ግብ ተመጣጣኝ የሆነ መስዋዕትነትና ፈተና እንደሚጠብቃቸው እያወቁ ነበር። ትግሉ መራራና ረዥም እንደሚሆን፣ ብዙ ውጣ ውረድ እንደሚበዛበት፣ መውደቅ መነሳት እንደሚፈራረቅበት ይገነዘቡ ነበር። ስለሆነም አንዳንዴ እየበረደና ጨርሶ የተዳፈነ እየመሰለ፣ አንዳንዴ ደግሞ እየተጧጧፈ ምንግዜም መክሰምን ሳያውቅ ለኢትዮጵያ ነፃነትና ክብር በሚደረገው በዚህ የማያቋርጥ ተጋድሎ ውስጥ አንዴ ይህንን  የትግል ስልት፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ያኛውን ታክቲክ እየተጠቀሙ ጊዜና ሁኔታን እያየ በሚለዋወጥ ስልት ምንም ጊዜና ምንም ሁኔታ ሊለውጠው በማይገባው ቆራጥነትና ታታሪነት መታገል አስፈላጊ መሆኑን አንድም ቀን ስተውት አያውቁም። እንደዚህም በመሆኑ መኢሶን አብዮታዊ ጥራቱንና ወኔውን ምንግዜም ከማይላሽቀው የታጋይ አባላቱ የሃገር ፍቅር ስሜት ጋር እያስተጋገዘ መዝኖና ፈቅዶ በጀመረው የትግልና የመዋዕትነት ጎዳና ረዥም ጉዞውን ተያያዘው።

ነገር ግን ይህ የመጀመሪያ የኢትዮጵያ ማርክሲስት ትውልድ ለዚህ ዓላማ በዚህ ቆራጥነት ተደራጅቶ ትንሽ መራመድ እንደጀመረ መደባቸውን ሙሉ በሙሉ ከድተው ከወዝአደሩና ከአርሶአደሩ በተደባለቁትና የነፃነቱን ትግል ረዥም ጉዞ ለመያያዝ በተነሳሱት አብዮታዊ ምሁራንና ከሕዝቡና ከአብዮቱ ቀድመው በአቋራጭ ለሥልጣን በቋመጡ፣ የነፃነት ተጋድሎ የሰፊው ሕዝብ የረዥም ጊዜ ተጋድሎ ሳይሆን የጥቂት ግንባር ቀደም ነን ባዮች የአንድ ሰሞን ውርውር መስሏቸው በተቅበጠበጡ፣ ለዚህ ለመራራው ትግል መደባዊ ትዕግሥቱም ሆነ ወኔው፣ ኢትዮጵያዊ ሃገር ፍቅሩም ሆነ አብዮታዊ ጥራት ቶሎ ብሎ በከዳቸው “አጭር ጉዞኞች” መሃከል ከፍተኛ የመሥመር ትግል ተጀመረ። በዚህ ትግል “የአጭር ጉዞኞቹ” ክንፍ በመኢሶን ውስጥ ሥር መስደድ የጀመረውን ሃቀኛ መሥመር ማሸነፍ ስለተሳነው የዚህ የቀኝ ክንፍ ንዑስ ከበርቴ አዝማሚያ መሪዎች በነሐሴ ወር 1963 ዓ.ም. ከመኢሶን መገንጠላቸውን አስታወቁ። ጥቂትም ቆይተው በሚያዚያ ወር 1964 ዓ.ም. በበርሊን ከተማ በኢትዮጵያ ጭቁኖች ትግል ውስጥ ታሪክ የማይረሳቸው ወንጀሎች ከፈፀመ በኋላ እንደገለባ እሳት ቦግ ብሎ የጠፋውን “የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ” የተባለውን ስም ጥፉ ድርጅት መሠረቱ።

በቅድመ አብዮት ኢትዮጵያ በተለይ በውጭ ሃገር ተማሪ ማህበራት አማካኝነት ከየካቲት በኋላም በይፋ በመኢሶንና በኢህአፓ መሃከል የተደረጉትን ትግሎች መላው  ኢትዮጵያ ሕዝብ ያውቃቸዋል። በዚህ ትግል በመጀመሪያ ላይ ባላቸው “ዓይን ሳቢ” መፈክሮችና በተሰበጣጠሩ ምክንያቶች ከተለያዩ የውጭ ኃይሎች ከሚጎርፍላቸው የማቴሪያል ድጋፍ የተነሣ ኢህአፓ ገናና መስሎ ይታይ እንደነበር ማንም አይረሳውም። ነገር ግን ይህ የአድሃሪያን ጊዜያዊ ማየል በሃቀኛ መሥመሩና በኢትዮጵያ ሕዝቦች እያደረ መንቃትና መደራጀት ተማምኖ ትግሉን ለቀጠለው መኢሶን አስደንጋጭ ነገር አልነበረም። የኢትዮጵያ አብዮት ፍጥነት፣ የጭቁን ሕዝቦቿ ከትግላቸው እየተማሩና እየነቁ መሄድ፣ ለመኢሶን የዚያኑ ያህል የዕድገትና የመለምለም ጎዳና ሲከፈትለት በዚያው ልክ ደግሞ በውጭ ኃይሎች የማቴሪያል ድጋፍ ከኢትዮጵያ ጭቁኖች የትግል ዕድገት ደረጃ ባልተመጣጠነ ሁኔታ “አብጦ” የቆመው ኢህአፓ እየተዋረደና እየከሠረ ሄደ። በአጭር ጊዜ ውስጥም ከለየላቸው ፀረሕዝቦች ጋር በመዳበል በአብዮቱ ላይ የኪሣራ ምልክቱ በሆነው ፀረሕዝብ አመጽ ተሰማርቶ የብዙ ሰማዕታት ደም የከፈልንብትን ግን ደግሞ ከአብዮታዊ አቋማችን አንዲት ስንዝር ፈቅ ያላደረገንን የሽብር ፈጠራ ዘመቻ ተያያዘው። ይህ አዲስ ምዕራፍ ግን የኢትዮጵያ አብዮት ወደፊት ከመራመድ፣ መኢሶንንም ከመለምለም የኢህአፓንም ቅጥረኞች ወደ ታሪክ ትቢያ መጣያ እየተደፉ ከመውረድ አላገዳቸውም።

በኢትዮጵያ አብዮት ሂደት ውስጥ ያለውንና በየጊዜው የሚቀያየረውን የኃይሎች አሰላለፍ እያዘመነ ታክቲኩን የሚቀይሰው መኢሶን በአንድ በተወሰነ የታሪክ ወቅት ንኡስ ከበርቴ ደርግ ያለውን የተወሰነ ተራማጅ ሚና በመገንዘብ በተለይ ከ1968-1969 ከጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት ጋር ጊዜያዊ የትግል ህብረት በመፍጠር ሰፊው ሕዝብ በንቃት በድርጅትና በትጥቅ ጎዳና ላይ እንዲገፋ ከፍተኛ ተጋድሎ አድረጓል። ነገር ግን ይህ ንዑስ ከበርቴ ደርግ በኢትዮጵያ ጭቁኖች አብዮታዊ ትግል መግፋት ተደናግጦ የሕዝቡን ሠፈር መክዳት ሲጀምርና ከርሱ በስተቀኝ ከነበሩ ኃይሎች ጋር ህብረት ፈጥሮ፣ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት እየከዳ፣ ብሄራዊ ነፃነታችንን ከከፍተኛ አደጋ ውስጥ እየከተተው ሲመጣ፣ መኢሶን ከጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት ጋር በቅልበሳ፣ በክህደትና በብሄራዊ ውርደት ጎዳና አልነጎደም። በነሐሴ ወር 1969 ዓ.ም. የትግል ስልት ለውጥ በማድረግ ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ሌሎች ጓዶችና ጓዲቶችን የሰዋበትን በኢትዮጵያ ጭቁኖችና በታሪክ ፊት ቃል የገባበትን ዓላማ አንግቦ የግንባር ቀደምነት ጉዞውን ቀጠለ።

በዚህ ወቅት ደግሞ የመኢሶንን ሀቀኛ አብዮታዊ መሥመር ለመዋጋት ሌሎች የታሪክ አተላዎች ተነሱ። እየተጠናከረ በመጣው ፀረአብዮት ፊት በመንበርከክ፣ አብዮትንና የእናት አገርን ክብር ለፍርፋሪ በመሸጥ በጠላት ፊት ካጎበደዱበት የቀኝ አደርባይ ድርጅቶች ጋር ሌላ ዙር የመሥመር ትግል ተካሄደ። ነገር ግን የሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ንቃት ከፍተኛ ደረጃ ላይ በሚገኝበት በዚህ ወቅት የቀኝ አደርባዮችን ጨርሶ ለማጋለጥ የጥቂት ወራት ትግል እንኳን አልፈጀም። በዚህም ትግል የቀኝ አደርባዮች ልክ እንደ ኢህአፓ ሙሉ በሙሉ ርቃናቸውን ከቀሩ በኋላ ልክ እንደ ኢህአፓው “ዘመን” ደግሞ የኪሣራቸው ምልክትና የግብዐተ መሬታቸው ወግ በሆነው ፀረሕዝብ አመፅ በአብዮቱ ሰፈር ላይ ተሠማሩ። በመኢሶን አባላት ላይ ብቻ ሳይሆን በጠቅላላው በዲሞክራቶችና በአገር ወዳጆች ላይ ይህ ነው የማይባል ግፍና በደል ፈፀሙ። ነገር ግን የመጀመሪያው ዙር ፀረሕዝብ አመፅ መኢሶንን ከሃቀኛ መሥመሩ ፈቅ እንዳላደረገው ሁሉ ይኸኛውም በንዑስ ከበርቴው ደርግ፣ በአድሃሪው ቢሮክራሲና በቀኝ አደርባይ ድርጅቶች አማካኝነት በአብዮት ሠፈር ላይ የወረደው የእሥራት፣ የግርፋትና የርሸና ዘመቻ ለአብዮትና ለኢትዮጵያ ክብር ብሎ ከተያያዘው ትግል እንዲያፈገፍግ አላደረገውም። ፀረ ሕዝቦችንም ከኪሣራና ከታሪክ ትቢያነት እንዳላዳናቸውና እነርሱም ልክ እንደ ኢህአፓ በሰፊው ሕዝብ ተተፍተውና የውርደት ማቅ ተከናንበው እንደከሰሙ በዚህ በያዝነው ዓመት የቀኝ አደርባይ ድርጅቶች ያጋጠማቸው ዕጣ አበጥሮ አሳይቶናል።

ዛሬ መኢሶን ሦስት ዓመት ሙሉ ከተለያዩ ፀረ ሕዝብ ኃይሎች በተለያዩ ጊዜያት እየተፈራረቀ የወረደበትን አመፅ አልፎ፣ ድርጅታዊ ህልውናውን ሳያስደፍር በመዝለቁ ለኢትዮጵያ ክብርና ለአብዮታችን የቆመ ሃቀኛ ኢትዮጵያውያን ሁሉ የሚኮሩበትና የሚመኩበት ድርጅት ነው። ዛሬ ይህ ድርጅታችን እየወደቀና እየተነሣ ሳያቋርጥ ወደፊት የተራመደበትን የአሥራ አንድ ዓመት የትግል ጉዞ ዘወር ብሎ ሲቃኝ ብዙ የታሪክ ገፆችን በታጋይ አባላቱ ደም የፃፈ መሆኑን እየተመለከተ በነዚህ ጓዶችና ጓዲቶች ፊት ተገቢ የሆነ ኩራት ይሰማዋል። ዛሬም በብዙ ሺ የሚቆጠሩ የመኢሶን አባላት፣ ደጋፊዎችና ወገኖች ሁሉ በደርግ አሥር ቤት ቢማቅቁም፣ አያሌ የመኢሶን ግንባር ቀደም ታጋይ ጓዶችና ጓዲቶች ቢወድቁም፣ ደርግና ፀረ ሕዝቦች ሲያልሙት ይኖራሉ እንጂ የነርሱ አርማ ከቶም አይወድቅም፤ አልወደቀምም። በሚሊዮን የሚቆጠረው የኢት ሰፊ ሕዝብ ያነሳው አርማ ነውና። በነዚህ ታጋይ አባላቱም ፊት ሆነ በጠቅላላው ለኢትዮጵያ ክብርና ነፃነት ሲከራከሩ በወደቁ ገበሬዎችና ወዛደሮች፣ መለዮ ለባሾችና ምሁራን፣ ወጣቶችና ሴቶች፣ ዲሞክራቶች አገር ወዳዶችና የጭቁን ብሄረሰቦች ታጋዮች ሁሉ ፊት “የነፃነቱ ትግል ይቀጥላል” እያለ መኢሶን የትግል ቃልኪዳኑን ያድሳል። ይህን ቃልኪዳን በማክበር መኢሶን የወደፊት ትግሉን የሚቀይሰው ከዛሬይቱ ኢትዮጵያ ሁኔታ ከሚፈልቁ አንዳንድ መሠረታዊ ሃቆች ተነስቶ ነው። እነርሱም የሚከተሉት ናቸው።

አንደኛ፣ ዛሬ መኢሶንም ሆነ በጠቅላላው ኢትዮጵያ ሕዝብ የቆመላቸውና ያ ሁሉ ደም የተገበረላቸው የዲሞክራሲ፣ የእኩልነትና የብሄራዊ ነፃነት ዓላማዎች ገና ግባቸውን አልመቱም። እርግጥ ከየካቲት 1966 ዓ.ም. ጀምሮ ተፋፍሞ በተካሄደው ትግል ብዙ ድሎች ተገኝተዋል። ነገር ግን ከሁለት ዓመት ወዲህ በኢትዮጵያ ምድር የሚታየው ሃቅ በአብዮታችን መመሪያ የተዘረዘሩት ዓላማዎች አንቀፅ በአንቀፅ እየተሻሩ የኋሊት ጉዞ መጀመሩ ነው። በዚህ ሂደት ከተቀጠለ ዛሬ በተግባር የተሻረው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራም በፀረ አብዮት ኃይሎች በይፋ እንደሚሻር መጠራጠር አይቻልም። ስለሆነም ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ በከፍተኛ ምስዋዕትነት ከተጎናፀፏቸው በኋላ የተነጠቁትን ድሎቹን መልሶ ለመጎናፀፍ እንደዚሁም አዲስ ድሎችን ተጎናፅፎ ወደ ሕዝባዊት ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እንዲያመራ ትግሉን ማፋፋም አለበት። በዚህ ትግል ውስጥ መኢሶን ገና በፕሮግራሙ ውስጥ “የኢትዮጵያ ጭቁኖች የሚያደርጉት የተበታተነ ትግል ከዳር እስከዳር አስተባብሮ የተጣራ አብዮታዊ አመራር ለመስጠት በታሪክ ፊት የተቀበለውን አደራ እስከ መጨረሻው ይጠብቃል” ባለው መሠረትና ከዚያም ወዲህ እያደጋገመ ባደሰው ቃልኪዳን መሠረት በኢትዮጵያ ብሄራዊና ዲሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራም ባንዲራ ሥር ትግሉን ይቀጥላል።

ሁለተኛ፣ ምንም እንኳን ዛሬ በኢትዮጵያ ፀረአብዮት አይሎ የብሄራዊ ክብራችን ፀር የሆኑ ኃይሎች በሃገራችን አንሠራፍተው፣ በሰፊው ሕዝብና በወገኖቹ ላይ ከፍተኛ የሆነ ፀረ ሕዝብ አመፅ ቢወርድም መኢሶን፣ በአጠቃላይ ወቅቱ ለኢትዮጵያ ክብርና ነፃነት ለሚታገሉ ኃይሎች ያመቸ ነው ብሎ ያምናል። ዛሬ የኢትዮጵያ ሕዝብ እስኪያንገፈግፈው ድረስ ከመረረው ሥርዓት በትግሉ ተላቆ አዲሲቱን ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ መመልከት የጀመረበት ወቅት ነው። መልኩን የቀየረ ሌላ ፀረ ሕዝብ ፈላጭ ቆራጭነት፣ መልኩን የቀየረ ሌላ ብሄራዊ ውርደትና የአፍሪካ ሃፍረትነት በምንም ዓይነት አይሻም። ከዚህ በተጨማሪ በመጀመሪያ ጊዜ በታሪኩ ከዳር እስከዳር የሚያውቀው፣ የተቀበለውና የተሰዋለት ሳይንሣዊ የሆነ መመሪያ አለው። ስለሆነም በዚህ ሳይንሣዊ ፕሮግራም እየተመራ ለመጓዝ እስከፈለገ ድረስ በሱ የአብዮት ፍላጎት አንፃር የፀረአብዮት ኃይሎች ማየል ዘላቂነት የለውም፣ በሱ የሃገር ፍቅር ስሜትና ወኔ አንፃር የጥቂት የታሪክ ጉድፎች ማየልም ዘላቂነት አይኖረውም። ስለሆነም መኢሶን የኢትዮጵያን ማርክሲስት ሌኒኒስቶች ዲሞክራቶችና አገር ወዳዶች ሁሉ ይህንን መሠረታዊ ሃቅ ተገንዝበው ተስፋ መቁረጥንና ውዥንብርን እየተዋጉ የነፃነቱን በአንድነት በግንባር ቀደምነት እንዲያፋፍሙ አብዮታዊና ብሄራዊ ጥሪ ያቀርብላቸዋል።

ሦስተኛ በዚህ ትግል ዘመን መጭው ጊዜ ለአብዮትና ለኢትዮጵያ ክብር ለሚታገሉ ማርክሲስቶች፣ ዲሞክራቶችና አገር ወዳዶች ሁሉ ይበልጥ እያመቸ እንደሚሄድም መኢሶን አይጠራጠርም። ይህንን ሃቅ አለመቀበል የኢትዮጵያን አብዮት አንገብጋቢ ጥያቄዎች የሕዝቡን የዲሞክራሲ መብቶች ጥያቄም ሆነ የብሄረሰቦችን የእኩልነት ጥያቄ፣ የብሄራዊ ነፃነታችንንም ሆነ ሌሎችን የሰፊው ሕዝብ ጥያቄዎች ታሪክ ያለፈው የቀኝ ኃይሎች ህብረት በሚገባ ይመስላቸዋል እንደማለት ይቆጠራል። ወይም ደግሞ የኢትዮጵያ ጭቁኖች ዲሞክራሲን ከቀመሱ በኋላ ወደ አዲስ ፀረሕዝብ ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ፣ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምን እያደከሙ ብሄራዊ ነፃነታቸውን መልሰው መጎናፀፍ ከጀመሩ በኋላ ወደ ሌላ አይነት ብሄራዊ ውርደት ሲነጉዱ አይናቸው እያየ ዝም ይላሉ እንደማለት ይቆጠራል። ሁለቱም የአድሃሪያን የቁም ቅዥቶች ናቸው። ከሃገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታም ከሕዝቦቿም የሃገር ፍቅር ተጋድሎ ታሪክ ጋር የሚጣጣሙ አይደሉም። እንደዚህም በመሆኑ የቀኝ ኃይሎች ሕብረት ከዕለት ዕለት በክህደት ቁልቁለት እየተሽቆለቆለ፣ ከዕለት ዕለት ይበልጡን ከሰፊ የኢትዮጵያ ሕዝብ ህልምና ፍላጎት እየራቀ፣ በዚህም የተነሳ ከዕለት ዕለት በሕዝቡ እየተፋፋመ ተቃውሞም እየቀሰቀሰ እንደሚሄድ ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው። በዚህ ልክ ደግሞ ክህደትን አሻፈረን ብለው በሰፊው ሕዝብ ወገን የፀኑ ማርክሲስት ሌኒኒስቶች፣ ዲሞክራቶችና አገር ወዳጆች ሁሉ ምንም ያህል መስዋዕትነት ቢጠይቃቸውም መጭውን የመራራ ትግልና የመስዋዕትነት ብሎም የመጨረሻ ድል ዘመን የሚያያዙት በማይቀረው አሸናፊነታቸውና በዘላቂው ኃያልነታቸው ያላችውን ፅኑ ዕምነት አድሰው ነው ማለት ነው።

አራተኛ ከነዚህ ሃቆች በመነሣት ዛሬ የተመሠረተበት 11ኛ ዓመት በሚያከብርበት ወቅት መኢሶን ለኢትዮጵያ ማርክሲስቶች፣ ዲሞክራቶችና አገር ወዳጆች፣ ያ ሁሉ ደም የተለገሠለት አብዮታችን መቀልበስ፣ የተደነቀው የብሄራዊ ነፃነታችን ታሪክ መጉደፍ ላንገበገባቸው ኢትዮጵያውያን/ት/ ሁሉ በሰፊው ሕዝብ ድምፅ ቁ.69 ያቀረበውን ጥሪ ያድስላቸዋል። የኢትዮጵያ አብዮት ከግቡ መድረስም ሆነ የብሄራዊ ነፃነቷን መክበር የመሰለ ቁም ነገር የኔ ብቻ ታሪካዊ አደራ ነው ብሎ የተመፃደቀበት ወቅት በመኢሶን የትግል ታሪክ ውስጥ አይገኝም። የመኢሶን ዓላማ እርሱ ለቆመለት የአብዮትና የብሄራዊ ነፃነት ዓላማ የቆመ ሁሉ ተባብረው በሁላችንም ትግል የሁላችንም የሆነች ሕዝባዊት ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ለመመሠረት በሚደረገው ትግል የበኩሉን አስተዋፅኦ ለማድረግ ነው። ስለሆነም ይህ የጉዞ አንድነት ካምናው ይልቅ ዘንድሮ በይበልጥ በሥራ እንዲተረጎም፣ የኢትዮጵያ ገበሬዎች ወዛደሮች፣ መለዮ ለበሾችና ምሁራን፣ ወጣቶችና ሴቶች፣ አገር ወዳድ የጦርና የፖሊስ መኮንኖች/ በደርጉ ውስጥ የቀሩት ጭምር/ ዲሞክራቶችና የጭቁን ብሄረሰብ ታጋዮች ሁሉ ጥቃቅን ልዩነታቸውን አቻችለው በዋናው ቁም ነገር ማለትም የኢትዮጵያ አብዮትና ብሄራዊ ነፃነት ጉዳይ ላይ እንዲሰበሰቡ፣ ሌሎች ታጋዮች ቀደም ሲል ያወቁለትን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራም አርማ ይዘው በህብረት ወደፊት እዲጓዙ አብዮታዊና ብሄራዊ ጥሪውን ያስተላልፍላቸዋል።

የመኢሶን ሰማዕታት አርማ አልወደቀም!  
  ከፕሮግራማችን ጋር ወደፊት!
አብዮታዊት እናት አገር ወይም ሞት!
የነቃ የተደራጀ የታጠቀ ሕዝብ ትግል ያሸንፋል!

የመላ ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ  ማዕከላዊ ኮሚቴ

“መስከረም 2” አምስተኛ ዓመት

የኢትዮጵያ ተማሪዎች ምሁራን አብዮታዊ ንቅናቄ፣ የኢትዮጵያ ጭቁን ብሄረሰቦች ለእኩልነትና ለመብታቸው ያካሄዱት ትግል፣ የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች ለመሬትና ለነፃነት በየቦታዉ ያደረጉት ግብታዊ ትግል፣ የኢትዮጵያ ወዛደር መደብ በየጊዜው ያደረገው ተጋድሎ፣ ዲሞክራትና ሃገር ወዳድ መለዮ ለባሾች ያደረጉት አብዮታዊ የትግል ተሳትፎ፣ በጠቅላላው የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ፊውዳሊዝምንና ኢምፔሪያሊዝምን ለመደምሰስ ያደረገው አብዮታዊ ትንንቅ፣ በየካቲት 1966 ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ ምድሪቷን ያንቀጠቀጠ አብዮታዊና ሕዝባዊ እንቅስቃሴን አስነስቶ ነበር። ይህ ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ እንቅስቃሴ፣ ለዘመናት የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብን በፋሽስታዊ አመፅ ረግጦ የገዛውን፣ የበሰበሰው የፊውዶ ፋሽስቱ የኃይልሥላሴ መንግሥትን ከውድቀት አፋፍ ላይ ጥሎት ነበር።

በንፁህ የሃገር ወዳድነት ስሜት ከኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ጋር በወቅቱ አብሮ “መሬት ላራሹ”፣ “ዲሞክራሲያዊ መብቶች”፣ “የብሄረሰቦች እኩልነት”፣ “እውነተኛ ብሄራዊ ነፃነት” በማለት አብዮታዊ ትግል ያደረግ የነበረው የኢትዮጵያ የምድር ጦር የአየር ኃይልና የፖሊስ ሠራዊት አስተባባሪ ደርግ፣ በመስከረም 2 1967፣ የጭቆናና የምዝበራ፣ የብሄራዊ ውርደትና ቅሌት ምልክት የነበረውን የፊውዶ-ፋሺስቱ መንግሥትን ቁንጮ፣ ኃይለሥላሴን ከዙፋኑ አወረደ። ይህ በየካቲት 1966 የተቀጣጠለው ሕዝባዊ አብዮታዊ እንቅስቃሴ፣ አንድ ከፍተኛና የመጀመሪያው ድል ነበር። የኢትዮጵያ ጭቁኖች በሙሉ ይህን ቀን በትግል ታሪካቸው ውስጥ፣ የወደፊቱ የዲሞክራሲ፣ የፍትህና የእውነተኛ ብሄራዊ ነፃነት ጮራ ጭላንጭል የተመለከቱበት በመሆኑ፣ እንደ አንድ የትግል ምዕራፍ መክፈቻ ይመለከቱታል።

በመስከረም 2 1967 ፋሽስቱ ኃይለሥላሴ ሲወድቅ፣ የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ በየካቲት ወር የዲሞክራሲና የፍትህ፣ የብሄረሰብ እኩልነት፣ የመሬትና የነፃነት፣ የብሄራዊ ክብርና ነፃነት መፈክሮችን አንግቦ ለተነሣበት ትግል አዲስ ምዕራፍ  መክፈቻ እንጂ ማብቂያ አድረጎ እንዳልተመለከተው ግልፅ ነው። ስለሆነም ከዚህ ቀን አንስቶ ያለፉት አምስት ዓመታት ብዙ መስዋዕትነት የተከፈለበት፣ ብዙ ውጣ ውረድ የበዛበትና ከፍተኛ ድሎች የተቀዳጀባቸው፣ ብሎም አብዮታዊው ትግል እየገፉ ሲሄድ ቋሚ ወዳጁንና ጠላቱን ሰፊው ሕዝብ ለመለየት የቻለበት ከፍተኛ የመደብ ፍልሚያ የነበረበት ዓመታት ናቸው።

ባለፉት አምስት ዓመታት የተገኘ አንድ ትልቅ ትምህርት ሰፊው ሕዝብ በአደረጋቸው ትግሎች የተቀዳጃቸውን ድሎች ላለመስነጠቅ ዋናው አስተማማኝ ኃይል በእርሱ ስም የማመፃደቅ ማንም ሌላ ኃይል ሳይሆን፣ እራሱ ሰፊው ሕዝብ የፖለቲካ ሥልጣን ባለቤት ሲሆን ብቻ መሆኑን ነው። ሰፊው ሕዝብ የፖለቲካ ሥልጣን ባለቤት የሚሆነውም በሰላምና በስምምነት ወይንም በአንዳች ሌላ ዘዴ ሳይሆን፣ በረዥሙና መራራ ትግል ብዙ መስዋዕትነት ሊከፈልበት በሚችል ከፍተኛ ተጋድሎ፣ በመደብ ፍልሚያው ውስጥ፣ በሕዝባዊ አመፅ አማካይነት የፖለቲካ ሥልጣን ሲነጥቅ በቻ ነው። ይህን ያለፈው አጭሩ የአምስት ዓመት የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ የትግል ልምድ ያሳየው ሃቅ ነው።

ኃይለሥላሴ ከዙፋኑ ከወደቀበት ጊዜ አንስቶ ያለፈውን የትግልና የመስዋዕትነት ጊዜ ዞር ብለን ብንመለከት፣ በአንድ ፊት አያሌ ድሎች የተጎናፀፍንባቸው፣ የዲሞክራሲና የእውነተኛ ብሄራዊ ነፃነት ጭላንጭል ማየት የጀመርንበት ሁኔታን እናስታውሳለን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ዛሬ የደረስንብት፣ ዲሞክራሲ የታፈነበት፣ ፍትህ የተረገጠበት፣ ኢትዮጵያ ወደ ብሄራዊ ውርደትና አዘቅት እየተሽቆለቆለችበት፣ በአጠቃላይ የተገኙት ድሎች እየተቀለበሱ የወታደራዊው መንግሥት ፈላጭ ቆራጭነት የተንሠራፋበት ሁኔታ ውስጥ መገኘታችን እንረዳለን።

1967 ዓመት በአገር ወዳድነት ስሜት በመግፋት ብቻ ኃይለሥላሴን ከሥልጣን ያወረደው ንዑስ ከበርቴው ወታደራዊ አስተደዳር ደርግ በአብዮትና በፀረአብዮት መካከል የሚዋልበት፣ ይሁንና በውስጡ የነበሩ የወቅቱ ተራማጅ ኃይሎች የሰፊውን ሕዝብ ወገን መርጠው አቢዮታዊ ትግል ያካሄዱበት ወቅት ነበር።

1968 በደርጉ ውስጥ የነበሩት የወቅቱ ተራማጅ ኃይሎች የበላይንት የነበራቸው ወቅት፣ በመሆኑም በመኢሶን ግንባር ቀደም ትግልና በሰፊው ሕዝብ አብዮታዊ እንቅስቃሴ መግፋት ከፍተኛ ሕዝባዊ ድሎች የተገኙበት ዓመት ነበር። የኢትዮጵያ የፊውዳል ሥርዓተ ማህበር ከሥር መሠረቱ ያናጋው ከመሬት ላራሹ አዋጅ አንስቶ፣ እስከ ሳይንሳዊው የአብዮታችን መመሪያ፣ የብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራም ድረስ የታወጀበት ዓመት ነበር።

1969 መኢሶን፣ ሌሎች ማሌና ተራማጅ፣ ዲሞክራሲያዊና አብዮታዊ ኃይሎች አብዮታችንን ከሚፈታተኑት፣ ደርግ ውስጥ ከነበሩት ፀረ ሕዝቦች ጭምር ከኢህአፓ ከኢዲዮና ከሌሎች ፀረ አብዮተኞች ጋር በተለይ በትግሉ ውስጥ በግንባር ቀደምነት የተሳተፈው መኢሶን ብዙ መስዋዕትነት የከፈለበት የአብዮትና የፀረአብዮት ትንንቅ የተካሄደበት ወቅት ነበር። ሰፊው ሕዝብ በድል አድራጊነት በመውጣት የመኢሶንን የነቃ የተደራጀና የታጠቀ ሕዝብ ትግል የፖለቲካ መሥመር አንግቦ የተጋደለበት ከፍተኛ የመደብ ፍልሚያ ወቅት ነበር።

በሌሎች አብዮቶችም እንደታየው፣ የሰፊው ሕዝብ አብዮታዊ እንቅስቃሴ ሲገፋ ከርሱ በስተኋላ መዳከርና ከቀኝ  ኃይሎች ጋር ማበር ጠባዩ የሆነው የፖለቲካ ሥልጣን የጨበጠ የንዑስ ከበርቴው መደብ በኢትዮጵያም ከ1969 ዓ.ም. አጋማሽ አንስቶ ይህ በሽታ ተፀናውቶት ነበር። ስለሆነም መኢሶን በ1968 የሰፊው ሕዝብ ዋና ጠላት የሆኑትን ፊውዳሊዝምንና አምፔሪያሊዝም ለመዋጋት ከ.ወ.አ. ደርግ ጋር የመሠረተውን ጊዜያዊ የትግል ህብረት በ1969 መጨረሻ ላይ ሠርዞ የትግል ስልት ለውጥ አደረገ።

መኢሶን ወገናዊነቱና አንድነቱ ምንጊዜም ከሰፊው ሕዝብ ጋር በመሆኑ፣ የዲሞክራሲ፣ የብሄራዊ ነፃነትና የአብዮታዊ አመራር መፈክሩን አንግቦ ነፃ ሕዝባዊና አብዮታዊ እንቅስቃሴን ማካሄድ ቀጠለ። 1970 በአብዮታችን ውስጥ አይነተኛ ውስጥ የሚያደርገው በአንድ በኩል የታሪክ አተላ የሆኑ ቀኝ አደርባዮች፣ የፖለቲካ ሥልጣኑን ለማደላደል የመረጠው ጊ.ወ. መንግሥትና ፀረአብዮት ኃይሎች በአዲሱ ህብረታቸው አማካይነት በኢትዮጵያ አብዮትና ሰፊ ሕዝብ ላይ መነሣታቸው ነው። በሌላ በኩል ደግሞ መኢሶን፣ ሌሎች አብዮታውያን፣ ዲሞክራቶችና አገር ወዳዶች ከለየላቸው ፀረ ሕዝብና ፀረአብዮት ኃይሎች ጋር በዲሞክራሲ፣ በብሄራዊ ነፃነትና በአብዮታዊ አመራር አርማ ሥር ያደረጉት ትግል፣ ጊ.ወ. መንግሥት የተያያዘውን የክህደት ጎዳና ለመቋቋም ያካሄዱት አብዮታዊ እንቅስቃሴ ነው። በአጭሩ 1970 አዲሱ የቀኝ ኃይሎች ህብረት የተቋቋመበት በመሆኑ፣ የዛሬውን ፀረዲሞክራሲያዊ አገዛዝ፣ የዛሬውን የኢት. ብሄራዊ ነፃነት መደፈር፣ የዛሬውን ብሄራዊ ውርደትና ቅሌት፣ የዛሬውን ቢሮክራሲያዊ የወታደራዊ መንግሥት ፈላጭ ቆራጭነት እንዳያስከትል፣ በአጠቃላይ የብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራሞችን እንዳይቀለበስ በመኢሶን ግንባር ቀደምነት መስዋዕትነት የተሞላበት ሕዝባዊ አብዮታዊ ትግል የተካሄደበት ዓመት ነበር። ይሁንና የሰፊው ሕዝብ ወገን ከማጥቃት ወደ አቻነት፣ ከአቻነት ወደ መጠቃት ተሸጋግሮ፣ በተለይም የአዲሱ የቀኝ ኃይሎች ህብረት ፊታውራሪ በነበሩበት፣ ዛሬ የታሪክ ቆሻሻ መጣያ ውስጥ በወደቁ የቀኝ አደርባይ ድርጅቶች የክህደት ምርጫ የተነሣ፣ ብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራማችንን ከመቀልበስ ለማዳን፣ ጊ.ወ. መንግሥት የተያያዘውን የፀረዲሞክራሲና የብሄራዊ ውርደት ሂደት ለመግታት አልተቻለም። የ1970 አብዮታዊ ትንንቅ  ለመኢሶን ብዙ ምስዋዕትነት የጠየቀ ተጋድሎ ነበር። ትግሉ ግን ይበልጥ መራራና ረዥም ሆነ እንጂ አልቆመም አይቆምም።

1971 አዲሱ የቀኝ ኃይሎች ህብረት የተደላደለ የመሰለበት፣ ቢሮክራሲያዊው ወታደራዊ መንግሥት ፀረ ዲሞክራሲን ያነገሠበት፣ ኢትዮጵያን ጠቅልሎ በብሄራዊ ውርደት ጎዳና ይዞ የነጎደበት፣ የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ብዙ መስዋዕትነት ከፍሎ ባስወጣው የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም እግር የሌላ ኃያል መንግሥት ኢትዮጵያን ተቀጥያ ያደረገበት፣ የራስ በራስ መተማመን መርሆች በጫማ የተረገጠበት፣ በአጠቃላይ ደግሞ ወታደራዊ ፈላጭ ቆራጭነት የነገሠበት ዓመት መሆኑ፣ እንኳን መኢሶን፣ እንኳን ዲሞክራቶችና ሃገር ወዳዶች ቀርቶ በየስብሰባው ላይ የመፈክር አውራጅ የሆነ ቢሮክራት ሁሉ የማይክደው ሃቅ ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ ግን 1971 ያሳየን ኮሜዲ ቢኖር በ1970 የቀኝ ኃይሎች ህብረት ፊታውራሪ የነበሩት ምስኪን የቀኝ አደርባይ ድርጅቶች ከነ “ኢማሌድሃቸው” የታሪክ ትብያ ሆነው እንደተመጠጠ ሎሚ መወርወራቸው ነው። ይህ ሁሉ ሲሆን መኢሶንና ሰፊው ሕዝብ ከአለፈው ትግላቸው ብዙ እንደውሃ የጠራ ልምድና ትምህርት ቀስመው አልፈዋል።

ዛሬ ኃይለሥላሴ የወደቀበትን አምስተኛ ዓመት እንደ አንዱ የየካቲት አብዮታዊ እንቅስቃሴ ድል ስናስበው፣ ያለፉት ዓመታት ብዙ የአብዮትና የፀረአብዮት ድርጊቶች የተከናወኑበት መሆኑን እንረዳለን። ባለፉት አምስት ዓመታት መኢሶን ጊዜውና ሁኔታው በሚጠይቀው ልዩ ልዩ አብዮታዊ የትግል ዘዴ በመጠቀም ከሰፊው ሕዝብ ጎን ሆኖ በቆራጥነት መታገሉን አሳይቷል። ሆኖም ሰፊው ሕዝብ ገና በድል አድራጊነት አልወጣም። በድል አድራጊነት የሚመጣውም ገና መራራና ረዥም አብዮታዊ ትግል ከአካሄደ በኋላ ብቻ መሆኑን እንረዳለን። ለዚህ ትግልም መጪው ጊዜ ብሩህና ለትግል ቆርጦ ለተነሣ አብዮታዊ ኃይል ሁሉ ያመቸ መሆኑን አንጠራጠርም።

በየካቲት የተነሳሳበት የዲሞክራሲ ጥያቄ ቀርቶ፣ የብሄረሰብ እኩልነት መብት ጥያቄ በትምክህተኝነት ተተክቶ፣ የሃገር ፍቅርና የሃገር ወዳድነት ስሜት በብሄራዊ ውርደትና አጎብዳጅነት ተሽሮ፣ በ1967 ኃይለሥላሴን ከዙፋኑ ያወረደው የያኔው ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ በኢትዮጵያ ቢሮክራሲያዊ ፈላጭ ቆራጭ ወታደራዊ አገዛዝን አንሰራፍቶታል ሃገሪቱን የተራማጆች የዲሞክራቶችና ሃገር ወዳዶች እሥር ቤት አድርጓታል። የአብዮታዊ ምሁራን፣ የማሌዎችና የተራማጆች መረሸኚያ መድረክ አድርጓታል። ሰፊው ሕዝብ ተቀዳጅቶ የነበራቸው ሕዝባዊ ድሎች እየተነጠቁ ናቸው። በአጠቃላይ የብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራማችን በተግባር ተቀልብሷል።

ስለሆነም የወደፊት ትግላችን በአጠቃላይ የተነጠቁት አብዮታዊ ድሎችን የፈለገውን ምስዋዕትነት ቢጠይቅም ለማስመለስና ለከፍተኛ ድሎችም ረዥሙንና መራራውን ተጋድሎ መያያዝ ነው። ብሎም የኋላ ኋላ ሕዝባዊትና ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን መመሥረት ነው። ለዚህ የረዥም ጊዜ ዓላማችን የወቅቱ ዋናው የመኢሶን ጥሪ ለዲሞክራሲ ለእውነተኛ ብሄራዊ ነፃነትና ክብር የቆሙ አብዮታዊ ኃይሎች በሙሉ የትግል አንድነት እንዲመሠርቱ ነው። የመኢሶን ጥሪ አሁንም በቁጥር 69 ያስተላለፈውን የትግል አንድነት ጥሪ እንደገና ደጋግሞ ማደስ ነው።

 
 የሃቀኛ ተራማጆች፣ የዲሞክራቶችና የሃገር ወዳዶች የትግል አንድነት ይኑር!
ከብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራም ጋር ወደፊት!
የመኢሶን ሰማዕታት አርማ አይወድቅም!
የነቃ የተደራጀ የታጠቀ የሕዝብ ትግል ያሽንፋል!
Scroll to Top