የሰፊው ሕዝብ ድምፅ
ልዩ መግለጫ፣ የካቲት 25፣ 1967
የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ
መኢሶን ይህንን ልዩ እትም ያወጣው ታሪካዊው “የመሬት ላራሹ” አዋጅ በታወጀበት ቀን ነው። በዚህ እትሙ የመሬት ላራሹ ጥያቄ የኢትዮጵያ ሕዝቦችና በርካታ አብዮታዊያን የተሰዉለት አቢይ ታሪካዊ ድል እንደሆነ ያስታውሳል። ቢሆንም ግን ፣ ይህ ታላቅ ድል የትግሉ መጀምሪያ እንጂ መጨረሻ ስላልሆነ፣ አሁንም ፊውዳሊዝምና ኢምፔሪያሊዝም ተደምስሰው የብሄራዊ ዴሞክራሲያዊ አብዮት ግቡን እንዲመታ ትግሉ መቀጠል እንዳለበት ያሳስባል። የድሉም ዋስትና የሰፊው ሕዝብ ድጋፍና ተሳትፎ ስለሆነ የዴሞክራሲ መብቶች መከበር አማራጭ የሌለው ትክክለኛ መንገድ መሆኑን አጥብቆ ያስገነዝባል፡፡
የየካቲቱ የኢትዮጵያ ሕዝቦችና ሪቮሉሽናዊ እንቅስቃሴ ፈንድቶ በገሃድ መንበልበል በጀመረ በዓመቱ፣ የፊውዳላዊውን ሥርዓት ኢኮኖሚያዊ መሰረት የሚደመስስ፡ ‘መሬት ላራሹን’ እውነት የሚያደርግና በሥራ ላይ የሚያውል አዋጅ ወቷል። ኢትዮጵያ ሕዝቦች በከባድ መስዋእትነት በሚያካሄዱት ሪቮሉሽናዊ ትግል አንድ ዓብይ ድል ተቀዳጅተዋል። ‘መሬት ላራሹ’ በሚለው የሰፊው ሕዝብ ከፍተኛ ጥሪ ስር በመሰለፍ የኃይለሥላሴን ፋሽስታዊ ጭቆናና ብዝበዛ የተቋቋሙትና ሕይወታቸውን ጭምር የሰውት የኢትዮጵያ ሰማእታት ምኞት ወደተግባር የሚተረጉምበት በር ዛሬ ተከፍቷል ለማለት ይቻላል። የሰማዕታቱ ደም በከንቱ አልፈሰሰም። ‘መሬት ላራሹን’ በስራ ላይ ለመዋል የወጣው የዛሬው ታሪካዊ አዋጅ በሰማዕታቱ ደም በቅሎ ያደገ ዛፍ አበባ ነው።
በእርግጥ በዛሬው ቀን በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ ተጀምሯል። ነገር ግን የዚህን አዋጅ በትክክል በሥራ ላይ መዋል የሚቃወሙ ኃይሎች አሁንም ያሉ መሆናቸው አያጠራጠርም። የመሳፍንትና መኳንንት ርዝራዦች፣ የገጠሩ ባላባታዊ መደብ፣ የቢሮና አቀባባይ ከበርቴዎች፣ እንደዚሁም የንዑስ ከበርቴው ቀኝ ክንፍ ከኢምፔሪያሊዝም ጋር ተደርበው በኢትዮጵያ መሰረታዊ ለውጥ እንዳይደረግ፣ መሬት በርግጥም በአዋጁ መሰረት የሕዝብ እንዳይሆን ባላቸው አቅም ሁሉ ለማጨናገፍ ይሞክራሉ፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች በእርግጥ የወደፊት እድላቸውን በገዛ- እጃቸው እንዳያገቡ የተቻላቸውን ያህል ይጥላሉ። አገሪቷ ራሱን የቻለ ነፃ ኢኮኖሚ እንዳትገነባና በጠቅላላውም መሳፍንታዊ ሥርዓትና ኢምፔሪያሊዝም ተመልሰው በሰፊው ሕዝብ ጫንቃ ላይ የጭቆና፣ የዘረፋ ቀንበራቸውን እንዲጭኑ በኃይል ይታገላሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ወዛደሩ፣ ደሃውና ጢሰኛው ገበሬ፣ ተራማጁ ወታደርና ምሁር፣ በአጠቃላይ የሰፊው ሕዝብ ወገኖች አዋጁ ከስራ ላይ እንዲውል፣ ፊውዳላዊ ሥርዓትና ኢምፔሪያሊዝም ተደምስሰው ብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ ሪቮሉሽን ግቡን እንዲመታና ወደፊት እንዲቀጥል አጥብቀው ይታገላሉ።
በቀዩ የደም ቀለም የተጻፈው የኢትዮጵያ ሕዝቦች ታሪክ ውስጥ ይህ ‘የመሬት ላራሹ’ አዋጅ የዋናው ትግል መጀመርያ እንጂ መደምደሚያው አይደለም። ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ገና ዲሞክራሲያዊ መብቶቹንና ነፃነቶቹን መቀዳጀት አለበት። ገና እንደአንድ ሰው ተነስቶ መሳፍንታዊውን ሥርዓትና ኢምፔሪያሊዝምን መደምሰስ አለበት። በእነርሱም መቃብር ላይ አዲስ በወዝአደሩ መደብ የሚመራ ሕዝባዊ ሥርዓትን መመስረት ይኖርበታል።
የኢትዮጵያ ተራማጆዎች ሁሉ ከሰፊው ሕዝብ ጎን በመሰለፍ የዛሬውን ታሪካዊ አዋጅ ይደገፉታል። ከሥራ ላይ እንዲውልም ከመቼውም ይበልጥ አንድነታቸውን አጠንክረው ይታገሉለታል። ይህንን አዋጅ ከሚደግፉና ለኢትዮጵያ ሕዝቦች እውነተኛ ነፃነት ከሚታገሉ ኃይሎች ጋር ያላቸውን የትግል አንድነት በማጠንከር የአድሃሪያንንና የኢምፒሪያሊዝምን ሴራ እስከመጨረሻው ይቋቋሙታል።
ይሁንናም፣ የተያዘው ሪቮሉሽናዊ ትግል ግቡን እንዲመታ ከተፈለገ፡ ሰፊው ሕዝብ እራሱ እንዲደራጅ የወደቀበት ገደብ ቶሎ ብሎ መነሳት ይኖርበታል። ወዛደሩ፣ ገበሬው፣ ተራማጁ የሰፊው ሕዝብ ወገንና የተጨቆኑ የሕዝብ ክፍሎች ሁሉ መደራጀትና ትግላቸውን በገዛ እራሳቸው ማካሄድ አለባቸው።የሰፊውን ሕዝብ በነጻ መደራጀትና የዲሞክራሲያዊ መብቶችን ለሰፊው ሕዝብ መመለስ የሚቃወሙና የተጀመረውን ሪቮሉሽናዊ እንቅስቃሴ ወደ ቢሮክራሲያዊ የለውጥ ጎዳና ለማዞር የሚፈልጉ ሁሉ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የሰፊውን ሕዝብ ድሎች የሚያደናቅፉና የትግሉንም እንቅስቃሴ የሚገቱ የለውጥ እንቅፋቶች ናቸው። ይህን ደህና አድርገው እንዲገነዘቡት ያስፈልጋል። ታጥቦ ጭቃ እንዳይሆን መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝቦች ከእንግዲህ ወደኋላ የማይመለሱበት ዓብይ የትግል ምዕራፍ ላይ ደርሰዋል። ሰማያት ቢናወጡ፣ መሬት ብትዋዥቅ እንግዲህ መሳፍንታዊው ሥርዓትና ኢምፔሪያሊዝም ከስርመሰረታቸው ሳይወድሙ፣ አዲስ ሕዝባዊ ሥርዓት ሳይቋቋምና የኢትዮጵያ ሕዝቦች የራሳቸውን እድል በራሳቸው ሳይጨብጡ የየካቲት የትግል እንቅስቃሴ ከቶ ገብ አይልም። ትግሉ መራራና ከፍተኛ መስዋዕትነት የሚጠይቅ፣ ብዙ ውጣ ውረድ የሚኖርበት መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ቢሆንም ከእንግዲህ ሰፊው ሕዝብ ወደነበረበት የብዝበዛና የጭቆና ቀንበር ስር አይመለስም፣ እስከመጨረሻው የደሙ ጠብታ ድረስ በቆራጥነት ይዋጋል እንጂ።
ይህ ታሪካዊ አዋጅ፣ ይህ የሰፊው ሕዝብ አብይ ድል ከንቱ እንዳይቀር ሰፊው ሕዝብ፣ ሰፊው አፈር ገፊ ሙሉ በሙሉ እንዲሳተፍበትና እንዲደግፈው አስፈላጊ ነው። ይህም ሊሆን የሚችለው የሰፊው ሕዝብ ዴሞክራሲ፣ የንግግር፣ የጽሁፍ፣ የድርጅት፣ የስብሰባ ወዘተ… መብቶችና ነፃነቶች በስራ ላይ ሲውሉ ነው። ሰፊው ሕዝብ በኢኮኖሚ በኩል የተቀዳጃቸውን ድሎች በቁጥጥሩ ስር ሊያደርጋቸው፣ እንደራሱ አድርጎ ሊሳተፍባቸው የሚችለው፣ የፖለቲካ ጥያቄዎቹ የተመለሱለት፣ ዲሞክራሲያዊ መብቶችና ነፃነቶቹ በተግባር የተረጋገጡለት እንደሆኑ ብቻ ነው። ትክክለኛው መንገድ ይሄ ነው። ሌላ አማራጭ ከቶ የለም።
ታሪካዊው አዋጅ ስራ ላይ እንዲውል የሰፊው ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ መብቶች በተግባር ይረጋገጡ፣
ፊውዳሊዝም፣ ኢምፔሪያሊዝም፣ ፋሺዝምና ታሪካዊውን አዋጅ የሚቃወሙ አድሃሪያን ሁሉ ይውደሙ!
ድሉ የሰፊው ሕዝብ ነው።
ከሰፊው ሕዝብ ድምፅ ዝግጅት
የወጣ ልዩ መግለጫ… 25/6/67