የሰፊው ሕዝብ ድምፅ
ቁጥር 57፣ ሰኔ 7፣ 1969
የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ
መኢሶን ይህንን ጽሁፍ ያወጣው የኢትዮጵያ ማርክሲስት ሌኒኒስት ድርጅቶች ሕብረት (ኢማሌድሕ) ውስጥ፣ “መኢሶን የጠባብ ቡድን ስሜት” አለበት እየተባለ የሚወራውን ለማስተባበልና የቡድን ስሜት ምን ማለት እንደሆነ ለማስረዳት ነው። በዚህ ጽሁፍ በየጊዜው ብዙም ሳይታሰብ የሚወረወሩ አንዳንድ መፈክሮችና ቃላቶች ዴሞክራሲ በሌለበት ሁኔታ እንዴት ውዥንብር እንደሚነዙ ይገልጽና፣ ማንም ድርጀት ራሱን ለማስተዋወቅ፣ ለማስፋፋትና አላማውን ለማሳወቅ የሚያደርገው ጥረት የቡድን ስሜት ተብሎ መገለጽ እንደሌለበት ምክንያቶቹን ያቀርባል። እንዲያውም ድርጅቶች ከሃሜትና ከአሉባልታ ተላቀው ሃቀኛ ርዕዮተ ዓለማዊና ፖለቲካዊ ትግል ማድረግ እንደሚገባቸውና ለዚህም የዴሞክራሲ መብቶች መኖር ትልቅ ሚና እንዳለው አጥብቆ ያሳስባል።
የኢትዮጵያ አብዮት ፈጣን ነው ከሚባልባቸው ምክንያቶች አንዱ የድርጊቶቹ ወይንም የውሳኔዎች ካስተሳሰብ ቀድሞ መገኘት ነው። ለአስተሳሰብ ጥራት፣ ለቲዎሪ፣ ለጥናት፣ ለእቅድ ጊዜ ሳይገኝ ይቀርና አንዳንድ ድርጊቶች ከተከናወኑ በኋላ ብቻ ዘወር ብሎ ምርምር የማድረግ ግዴታ ይከተላል። ይህንን የአሰራር ዘዴ ከሚያሳዩን ነገሮች አንዱ የፅንሰ-ሃቦች፣ ወይንም የቃላት፣ ወይንም ያባባል ዘይቤዎች፣ ወይንም የመፈክሮች እንዳጋጣሚ መወርወር ነው። አንዳንድ ቃላት ወይ በአንድ ህቡዕ ወረቀት ላይ፣ ወይንም ሬዲዮ፣ በቴሌቪዥን፣ በጋዜጣ፣ ወይንም በአንድ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ድንገት ብቅ ይሉና ማንም ስለ ትርጉማቸው ራሱን ሳይጠይቅ፣ ሰው በእነርሱ መጠቀም ይጀምራል። አገሪቷን ያዳርሳሉ። ስለትርጉም ትክክለኝነት ወይንም ስለይዘት ጥያቄ የሚመጣው ከብዙ ወራት በኋላ ይሆናል። ከዚያም እንግዲህ ትክክለኛ ሆነው ካልተገኙ ተጠቃሚን ክፍል ከነርሱ ለማላቀቅ ብዙ ችግር ይኖራል፤ እንዳንዴም ፈጽሞ አይሳካም።
ለምሳሌ “አናርኪዝም”፣ “አናርኪስት” የሚሉት ቃላት በሳይንሱ ከሄድን ብቻቸውን ለኢህአፓ መጠሪያ ሊሆኑ እንደማይችሉ መግለጽ የተጀመረው ቃላቱን ብዙ ሕዝብ ከጨበጣቸው በኋላ ስለነበር አሁን ያንን ለመለወጥ አስቸጋሪ ሆኗል። ኢህአፓ የአድሃሪ ንዑስ ከበርቴዎች ቡድን እንጂ አናርኪስት ብቻ አይደለም ተብሎ ለመግለጽ ሙከራ ቢደረግ ይህን ያህልም ውጤት በአጭር ጊዜ ውስጥ አይገኝም። አሁን ደግሞ ኢህአፓ ትሮትስካይት ነው የሚለውን አባባል ለማስጨበጥ ሙከራ እየተደረገ ነው። በዚህ አዲስ ቃል የብዙ ሰው ምላስ እየተጠመዘዘ ነው። ይሁንናም፣ ኢህአፓ ትሮትስካይት እንዳይደለ አንድ ፀሐፊ በአዲስ ዘመን በሚገባ ያስረዳ ይመስለናል። ቢያስፈልግም እኛም እንመለስበታለን። ለማንኛውም ግን እነዚህን ምሳሌዎች የጠቀስናቸው በእነርሱ ላይ ለመከራከር ሳይሆን፣ አንዳንድ ቃላት በድንገት ሲወረወሩ ጥራትን ሳይሆን ውዥንብርን እንደሚያስከትሉ ለመጠቆም እና እንደዚሁም ዲሞክራሲያዊ መብቶችና ሰፊ ውይይት በሌለበት ሁኔታ የዚህ አይነቱ ችግር እንደሚቀጥል ለማስታወስ ያህል ነው።
በዚሁ መንገድ፣ በቅርቡ ውዥንብርን መምጣት ከጀመሩት ጽንሰ ሀሳቦች ውስጥ አንዱ “የጠባብ ቡድን ስሜት” የሚለው ነው። ይህኛው ግን እንደ አናርኪስት ወይም ትሮትስካይት በቸልታ ሊታለፍ የማይችልበት ምክንያት፣ ህብረትን ለመፍጠርና ለማጠንከር በሚታገሉ የኢትዮጵያ ማርክሲስት-ሌኒኒስት ድርጅቶች መካከል አለመግባባትን ሊፈጥር ስለሚችል ነው። በዚህ ጽንሰ ሀሳብ መኢሶንም ሲጠቀምበት የቆየ ቢሆንም፣ ዛሬ ግልጽ እየሆነልን የመጣው ሃቅ፣ ሌሎች ጓዶችና እኛ የምንናገረው ስለአንድ ነገር አለመሆኑን ነው። ለ“ጠባብ ቡድን ስሜት” የምንሰጠው ትርጉም ይለያያል።
አንዳንድ ጓዶችና ድርጅቶች ይህንን አባባል ሲተረጉሙ፣ “የጠባብ ቡድን ስሜት” የራስን ቡድን ከአብዮቱ ማስቀደም ነው ይላሉ። ለአብዮቱ መስራት ሲገባ ለራስ ቡድን መስራት፣ የራስን ቡድን “ማስፋፋት”፣ የራስን ቡድን “ማስተዋወቅ”፣ ወዘተ… የጠባብ ቡድን ስሜት ማሳየት ነው ይባላል። “ከኔ ወዲያ አብዮተኛ” ማለትም የጠባብ ቡድን ስሜት ነው ይላሉ። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን፣ ከእነዚህ መግለጫዎች ውስጥ ትንሽ ወደ ፅንሰ ሀሳቡ ትክክለኛ ይዘት የሚጠጋው የመጨረሻው ብቻ ነው። ሌላው ሁሉ፣ ከዚህ በታች እንደምንመለስበት ሁሉ፣ ከጠባብ ቡድን ስሜት የራቀ ብቻ ሳይሆን፣ እንዲያውም ተቀራኒው ነው።
የጠባብ ቡድን ስሜት ማለት ምን ማለት ነው?
አባባሉ፣ እኛ እንደገባን ከሆነ፣ እንግሊዘኛውን ቃል ሴክቴሪያኒዝምን፣ ለመተርጎም ተብሎ የቀረበ ነው። በእንግሊዘኛ ሴክት ማለት ብዙ ጊዜ በሃይማኖት ላይ የተመሠረተ፣ ሌሎች አምነቶችን የማያስጠጋ፣ በራሱ ላይ ብቻ የሚያተኩር የእምነት-አክራሪ ወይም ፋናቲክ ጠባብ ቡድን ማለት ነው። ለምሳሌ በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ውስጥ የነበሩትን “ሁለት ልደት”፣ “ሶስት ልደት”፣ “ከራ” ፣“ጸጋ”፣ ወዘተ… የሚባሉትን ያማኞች ክፍሎች ሴክቶች ለማለት ይቻላል። እንዲሁም በእስልምና ሃይማኖት ውስጥ ልዩ ልዩ ሴክቶች እንዳሉ ይታወቃል። የቃሉ ምንጭ እንደዚያ ሆኖ፣ በፖለቲካ ዓለም ሴክተርያን ማለት፣ በትንሽ ቡድን የተደራጀ፣ በድርጅት ውስጥ ሊሰበሰቡ የሚችሉትን ግለሰቦች ወይንም ኃይሎች የማያስጠጋ፣ መደራጀትን ራሱን እንደ መሳሪያ ሳይሆን እንደ ግብ በመውሰድ የሚረካ ድርጅት ወይንም የድርጅት አባል ማለት ነው። ስለዚህ ነው “ከኔ ወዲያ አብዮተኛ” የሚለው ምናልባት ወደ ትክክለኛ ትርጉሙ ይጠጋል የተባለው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ፣ ከላይ በተጠቀሱት ስህተተኛና እርስ በርስ በሚቃረኑ መግለጫዎች ላይ በመመርኮዝ፣ አንዳንድ ጓዶችና ድርጅቶች መኢሶንን በጠባብ ቡድን ስሜት ማሳጣት ይዘዋል። ቀደም ሲል በሰፊውና አሁንም ደግሞ አልፎ-አልፎ ከአድሃሪዎች ይሰነዘሩብን የነበሩት የስም ማጥፊያዎች መኢሶን የኦሮሞ ድርጅት ነው የሚለው የብሔር ትምክህተኞች ቅስቀሳና ተቃራኒው፣ መኢሶን የነፍጠኞች ድርጅት ነው የሚለው የጠባብ ብሄረተኞች ቅስቀሳ ነበሩ። አሁን ዛሬ የተያዘው መኢሶን የጠባብ ቡድን ስሜት ያሳያል ነው። ማለትም፣ በሂስ አቅራቢዎቹ አባባል፣ መኢሶን ከአብዮቱ በፊት እራሱን ያስቀድማል፣ ለአብዮቱ መስራት ሲገባው ለራሱ ይሰራል፣ እራሱን ያስፋፋል፣ እራሱን ያስተዋውቃል፣ “ከኔ ወዲያ አብዮተኛ” ይላል፣ ወዘተ…እና ስለዚህም የጠባብ ቡድን ስሜት አለበት ነው!!
ከአብዮት በፊት ቡድንን ማስቀደም፣ ወይንም ለአብዮቱ እንደመስራት ለገዛ ቡድን መስራት የሚለው ነገር፣ ለአብዮት መስራትንና መደራጀትን፣ ማለትም ለአንድ አብዮታዊ ድርጅት በተቃራኒነት ሊቀርቡ የማይችሉትን ነገሮች አቃርኖ የሚያቀርብ አባባል ነው። አንድ አብዮታዊ ድርጅት መጀመሪያውኑ የሚቋቋመው አብዮትን ለማካሄድ እንደሆነ ለማንም የፖለቲካ መሃይም ግልጽ እንደሆነ እናምናለን። የአንድ አብዮታዊ ድርጅት አላማና እለታዊ ድርጊቶች የሚቀየሱትና የሚከናወኑት አብዮትን ለማካሄድና ግቡን እንዲመታ ለማድረግ ነው። ለአንድ ማርክሲስት-ሌኒኒስት ድርጅት አብዮት የህልውና መሰረታዊ ምክንያት ነው። ስለሆነም፣ ድርጅትን ከአብዮት ማስቀደም የሚባለው ውዥንብርን የሚፈጥር ትርጉም-የለሽ አነጋገር ነው።
የራስን ድርጅት ማስፋፋት፣ የራስን ድርጅት ማስተዋወቅ የተባሉት ሂሶችም እንደዚሁ መክሰሻ እንዲሆኑ ከተፈለገ ትርጉም-የለሽ ናቸው። ማንኛውም ድርጅት፣ “እድሜያችን እንዲያጥር እንፈልጋለን” የሚሉትንም ጨምሮ፣ የፖለቲካ መስመሩ በሰፊው እንዲሰራጭለትና ብዙ አባላትና ደጋፊዎች እንዲኖሩት በተቻለው መንገድ ሁሉ ይታገላል። ጋዜጦቹ አገሪቷን በሙሉ እንዲያዳርሱ፣ አባሎቹ በብዙ ሺህ እንዲቆጠሩ ለማድረግ፣ ባጠቃላይም ያገሪቷንና የመንግሥቱን ፖለቲካ እርሱ በሚያምንበት መንገድ አቅጣጫ ለማስያዝ ይታገላል። ይህም እንግዲህ ደርጅትን ማስፋፋትና ራስን ማስታወቅ ነው። ደግሞም የዚህ አይነቱን ትግል የማያደርግ ድርጅት ከመጀመሪያውም ለምንስ ይቋቋማል?
በአሁኑ ወቅት አንድ የጋራ መግለጫን ያወጡና ለህብረት የሚታገሉ አምስት የኢትዮጵያ ማርክሲስት- ሌኒኒስት ድርጅቶች አሉ። አምስቱም በተቻላቸው መንገድ ሁሉ ድርጅታቸውን ለማስፋፋት፣ ድርጅታቸውን እንዲታወቅ ለማድረግ፣ በሰፊው ሕዝብ ውስጥ ተደማጭነትን ለማግኘት፣ ስር ለመስደድ በየዕለቱ ሙከራን ያደርጋሉ ይህም ትክክለኛና ተገቢ ነገር እንደሆነ ለማንም ግልጽ ሲሆን፣ እንዲያውም አንዱ ሌላውን ተስፋፋህ፣ ራስን አስተዋወቅህ ብሎ ለመውቀስ የሚሞክረውም ከዚሁ የተነሳ ነው። የዚህ አይነቱ ወቀሳ ግን አትስፋፋ፣ አትታወቅ የሚለውን ያዘለ ስለሆነ ፍጹም ፀረ ዲሞክራሲያዊና ፀረ አብዮታዊም ይሆናል።
በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንድ ድርጅቶችና ጓዶች የሰፊውን ሕዝብ ጥያቄዎችን በየወቅቱ ማንሳትን “ራስን እንደማስተዋወቅ” ስለሚቆጥሩት፣ ይህም አስተሳሰብ ዞሮ ዞሮ ፀረአብዮታዊ ሆኖ ይገኛል። በማርክሲዝም- ሌኒኒዝም አብዮትን የሚሰራው ጥቂት ግለሰቦች ሳይሆኑ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠረው ሰፊው ሕዝብ ነው። ስለሆነም፣ ትክክለኛ ጥያቄዎችና መፈክሮችን በየወቅታቸው ማንሳት ይህ ሰፊ ሕዝብ ንቃተ ህሊናውንና የመደራጀት ችሎታውን ከፍ እንዲያደርጋቸው ያግዛል። “የራስ ማስተዋወቅ” ሂስ ይቀርባል ተብሎ፣ እነዚህን ጥያቄዎችና መፈክሮች መተው ንፁህ አድርባይነት ይሆናል።
መኢሶን ድርጅቱን ለማስፋፋት፣ የፖለቲካ መስመሩ በሰፊው እንዲሰራጭና እንዲታወቅ ለማድረግ፣ በተቻለው መንገድ ሁሉ ይታገላል። በዚያውም ግን፣ መኢሶን የኢትዮጵያ ማርክሲስት-ሌኒኒስቶች ህብረት እንዲጠነከርና ይህ ህብረትም ወደ ውህደት አምርቶ የኢትዮጵያ የወዛደር ፓርቲ እንዲፈጠር ያልተቆጠበ ጥረት ያደርጋል። በራሱ መስመርና ዓላማ ትክክለኝነት ስለሚያምን፣ መኢሶን የራሱን መጠንከር እንደ አብዮቱ ሰፈር መጠንከር ለእውነተኛው የወዛደር ፓርቲ መመስረት እንደ አንድ ዋስትና ይቆጥረዋል። የራሱን መጠንከር ብቻ ሳይሆን የሌሎቹንም ድርጅቶች መጠንከር በዚሁ አይን ስለሚመለከተው፣ ድርጅታችን እስካሁን ድረስና ወደፊትም “ለምን ትስፋፋላችሁ”፣ “ለምን ራሳችሁን ታስተዋውቃላችሁ” ብሎ “ሂስ” አላቀረበም፣ አያቀርብምም። ነገር ግን የመኢሶንም ሆነ የሌሎቹ ድርጅቶች የፖለቲካ መስመር ፀረ አብዮታዊ ከሆነ፣ እንደኢህአፓ ሁሉ፣ የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ይነቃባቸዋል፣ ይተፋቸዋል። ስለዚህም ነው ሃቀኛ ተራማጆች አንድ ቡድን ተስፋፋ?፣ ታወቀ? ብለው በመጠየቅ ፈንታ የቡድኑ መስመር ትክክለኛ ነው ወይስ አይደለም ብለው መጠየቅ ያለባቸው። መስመሩ ትክክለኛ እና አብዮታዊ እስከሆነ ድረስ በጠባብ ቡድን ስሜት ተቀስፎ ያልተያዘ ሁሉ በአንድ ድርጅት መስፋፋት ይደሰታል።
ካለፉት ጥቂት አመታት የትግል ልምድ እንደምናየው ከሆነ፣ በመኢሶን የፖለቲካ መስመር ላይ አንድም መሰረታዊና በመርሆች ላይ የተመረኮዘ ክርክር ቀርቦበት አያውቅም። አሁንም በመኢሶን ላይ የሚቀርበው የጠባብ ቡድን ስሜት “ሂስ” በመስመር ላይ ክርክር እንዳይደርግ፣ መሰረታዊ የሆኑ ጥያቄዎች ለውይይት እንዳይቀርቡ የሚጋብዝ “ሂስ” ነው። ነገር ግን የዚህ አይነቱ “ሂስ” የቀራቢውን ግለሰብ ወይም ድርጅት የፖለቲካ መስመር ትክክለኛነት አያረጋግጥለትም። ደግሞም ለጊዜው ተድበስብሶ ሊታለፍ በሚሞክረው መሰረታዊ የክርክር ጥበብ ላይ ይዋል ይደር እንጂ ሰፊው ሕዝብ መንቃቱ ፈጽሞ የማይቀር እንደሆነ ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ የደረሰው የኢህአፓ መክሸፍ በሚገባ ያረጋግጣል።
ብዙውን ጊዜ በጠባብ ቡድን ስሜት ስም የሚቀርብብንን “ሂስ” ለፖለቲካ መስመራችን ከመከራከር እንድንቆጠብ ለማድረግ የሚቀርብ “ሂስ” ነው። ለግል ድርጅት የፖለቲካ መስመር መከራከር፣ የግል ድርጅትን ለማስፋፋት እና ለማስተዋወቅ መጣጣር ፓርቲዛንሺፕ ወይንም ማሊታንሲ /ታጋይነት/ እንጂ ሴክታሪያኒዝም አይደለም። ፓርቲዛንሺፕ ወይንም ማሊታንሲ /ታጋይነት/ ማለት ደግሞ ባጭሩ ለሚያምንበት ነገር ወገንን መርጦ፣ ሳይወላውሉ ሽንጥን ገትሮ መከራከር ማለት ነው። የመኢሶን አባሎችና ደጋፊዎች ሁሉ የዚህ አይነቱን መንፈስና አሰራር የማሳየትና የመጠቀም አብዮታዊ ግዴታ እንዳለባቸው ያውቃሉ። በእርግጥ አንዳንድ ጊዜ አንዳንድ ጓዶች የፓርቲዛንሺፕን ትርጉም በሚገባ ባለመረዳት ያንድን ጥያቄ የክርክር ገፆች ሁሉ በዲያሌክቲካዊ ዘዴ በማሳየት ፈንታ በደፈናው “ትክክለኛው መኢሶን ነው፤ ወይም እውነቱ ይህ ነው፣ ብትቀበል ተቀበል፣ ባትቀበል ተወው!!” ወደ ሚለው አነጋገር ሊያዘነበሉ ይችላሉ። ይህ ጎጂ ስህተት ነው። በተረፈ ግን ለድርጅቱ የፖለቲካ መስመር የማይከራከር፣ ትክክለኛነቱንም በትንተና አሳይቶ በጥራት አድማጩን ለመሳብ የማይሞክር የአንድ ድርጅት አባል ወይንም ደጋፊ ለድርጅቱም ሆነ ለአብዮቱ ምን ይጠቅማል? እንግዲህ በኛ ላይ ብቻ የጠባብ ቡድን ስሜትን “ሂስ” በሚያቀርቡት ጓዶች ወይንም ድርጀቶች ፓርቲዛንሺፕንና ሴክቴራያሊዝም ያማቱ ስለመሰለን ይታሰብበት እንላቸዋለን።
ነገር ግን ደግሞ መኢሶንን በእውነተኛ ትርጉሙ የጠባብ ቡድን ስሜት፣ ወይም ሴክቴሪያኒዝም አለበት የሚያሰኙ ያስራር ዘዴዎች አሉበት ወይ? ከላይ እንደተገለፀው፣ ሴክቴሪያኒዝም ማለት ለመሰብሰብ የሚችሉትን ግለሰቦች ወይንም ኃይሎች አለመሰብሰብ እና በራስ ድርጅት ላይ በማተኮር መደራጀትን እራሱን እንደ ግብ መውሰድ ማለት ነው። በእርግጥም ደግሞ በአሁኑ ጊዜ ለምን የድርጅቱ አባሎች አልተደረግንም? መኢሶን ለምን አላስጠጋንም? የሚሉ ግለሰቦችና ክፍሎች ሊኖሩ ይችላሉ። ባሁኑ ጊዜ እንኳን መኢሶን ብቻውን ይቅርና የተደራጁት ማርክሲስቶች በሙሉም ቢሆኑ የኢትዮጵያን ተራማጆች በሙሉ አላቀፉም። እጅግ በጣም ብዙ አብዮታዊያን ገና አልተደራጁም ስለዚህ መኢሶን እነዚህን ሁሉ በማደራጀትና በማስጠጋት ያምናል። ነገር ግን በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ተራማጅ ነኝ፣ አብዮታዊ ነኝ በማለት ሹመትና ሽልማት ያመጣ እንደሆነ እንጂ እንደ ኃይለሥላሴ ዘመን የሚያሳስር፣ የሚያስገርፍ ከአገር የሚያስወጣ ወንጀል አይደለም። ስለዚህም፣ ድርጅታችን ራሱን ከሰርጎ ገቦች ለመጠበቅ እየተጠነቀቀ ቆራጥ ታጋዮችና ግንባር ቀደም የሆኑትን የወዛደሩን፣ የድሃ አርሶ አደሩና የግራ ክንፍ ከበርቴ አባሎች ወደ ድርጅቱ ያስገባል። ሌሎችንም የአብዮቱን ደጋፊዎች በየፈርጁና በየደረጃው ለማደራጀት ይታገላል። ጊዜው ብዙ ጥንቃቄን የሚጠይቅ ነው። እንደዚያም ሆኖ ግን መቶ በመቶ ከሰርጎ ገቦችና ከፕሮቮካተሮች ነፃ ለመሆን እንደማይቻል ግልጽ ነው።
የስክቴሪያኒዝም ሌላ ገጽ፣ ማለትም በራስ ድርጅት ላይ ማተኮረንና ድርጅትን እንደግብ መውሰድን በሚመለከተው በኩል፣ ማንኛውም ሀቀኛና የድርጅታችንን ጽሁፎችና ድርጊቶችን የሚያውቅ ሰው የዚህ አይነቱን “ሂስ” ፈጽሞ ሊያቀርብብን አይችልም እንላለን። መኢሶንን በፕሮግራሙ ውስጥ ሳይቀር ከሌሎች ማርክሲስት-ሌኒኒስት ድርጅቶች ጋር ሃቀኛ ፖለቲካዊና ርእዮተዓለማዊ ትግሎችን አካሂዶ፣ ከነርሱ ጋር በመዋሃድ የወዛደሩን ፓርቲ የመፍጠር አላማ እንዳለው ቁልጭ አድርጎ ገልጿል። ድርጅታችን ከፕሮግራሙ መውጣት በፊትም ሆነ በኋላ፣ በርከት ባሉ ጽሁፎች፣ ምናልባት ከማንኛውም የኢትዮጵያ ማርክሲስት- ሌኒኒስት ድርጅት ይበልጥ ደጋግሞ፣ ስለ ወዛደሩ ፓርቲ አመሰራረት ጽፏል። ችግሩ በፊውዳላዊት ኢትዮጵያ የክርክር መብትም ሆነ ልምድ ስላልነበረና ዛሬም ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለሰፊው ሕዝብ ገና ስላልተለቀቁ፣ የሚደረግብን ዘመቻ በሃቅና ተጨባጭ ነገሮችን እያዩ በማመዛዘን፣ ለእውነት በመቆም ሳይሆን ቀድሞ በነበረው “የመደብ ትግል” ስልት፣ በወሬ፣ ባሉባልታ፣ ከንቱ ጥርጣሬን በመንዛት ላይ የተመረኮዘ ሆኖብን ነው! የኢትዮጵያን አብዮታዊያንና ሰፊውን ሕዝብ የምንለው፣ የእኛን ብቻ ሳይሆን የሁሉንም ድርጅት ጽሁፎች በሚገባ አንብቡ፣ የሁሉንም ድርጅት የቅስቀሳ ይዘት አጥኑ፣ በፅሁፍና በተግባር መካከል ያሉትንም ግንኙነቶች በሚገባ አስተውሉ ነው። ከፊውዳላዊ አስተሳሰብና ፊውዳላዊ ከሆኑት የሃሜት፣ የአሉባልታ፣ የማሳበቅ፣ የስም ማጥፋት፣ “የትግል ዘዴዎች” መላቀቅ አለብን። ሳይንሳዊ የትግል ዘዴን እንልመድ። እንደእርሱ ካላደረግን ለድርጅትም ሆነ ለአብዮት ምንም ጥቅም አናመጣም።
እንደተባለው፣ የኢትዮጵያ አብዮት አሁን በደረሰበት ደረጃ የኢትዮጵያ ማርክሲስት- ሌኒኒስት ድርጅቶች ህብረትን ለመፍጠር በመታገል ላይ ይገኛሉ። አምስቱም የህብረቱ ድርጅቶች ልዩ ልዩ ጠንካራና ደካማ ጎኖች አሏቸው። ጠንካራ ጎኖቹን ሁሉም ድርጅት አባል ያገኝ ደካማ ጎኖቹን ከሁሉም ድርጅት ለማስወገድ እንዲቻል ሃቀኛ ርእዮተዓለማዊና ፖለቲካዊ ትግል ማካሄድ አለበት። የዚህ ዓይነቱ ትግል ደግሞ ባንድ ጠረቤዛ ዙሪያ በሚሰበሰቡ ጓዶች መካከል ብቻ ከተካሄደ፣ ዞሮ ዞሮ ሃሜት፣ አሉባልታና ሌሎችም ፊውደላዊ የትግል ዘዴዎች መንገሳቸው ስለማይቀር፣ የዲሞክራሲያዊ መብቶችን ያለገደብ ባስቸኳይ መታወቅ ደጋግሞ፣ እንደሰፊው ሕዝብም ሁሉ ጠይቋል፤ አሁንም ይጠይቃል። በድርጅቶች መካከል መተማመንና ለአንድ አላማ እንዳንድ ሰው ሆኖ ለመሰለፍ የሚቻለው እነዚህ መብቶች ሲኖሩና እያንዳንዱ ድርጅት በሰፊው ሕዝብ ፊት ያለበትን ኃላፊነትና በትክክል ተገንዝቦ፣ በሃቅ የኢትዮጵያን ወዛደር ፓርቲና የኢትዮጵያን ሕዝባዊ አብዮታዊ ግንባር ለመመስረት የሚታገል መሆኑን ሲያረጋግጥ ብቻ ነው። ስለዚህም ነው መኢሶን ውይይት ይኑር፣ ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለጭቁኖች ያለገደብ ባስቸኳይ ይታወቁ የሚለው።
እንደ ሌሎቹ ድርጅቶች ሁሉ፣ መኢሶንም ደካማ ጎኖች አሉት። አባሎቻችንም ደጋፊዎቻችንም አልፎ-አልፎ የፖለቲካ ስህተቶችን እንደሚፈፅሙ የተወቀ ነው። እንደሚባለው ሁሉ፣ “የማይሳሳት የማይሰራ ብቻ ነው” መኢሶን ደግሞ በአብዮት አፍላ ውስጥ የሚታገል ድርጅት ነው። ይሁንናም፣ በማንኛውም ጊዜ እና ቦታ ድርጅታችን “ከኛ ወዲያም አብዮተኛ” የሚል መንፈስም ሆነ ድርጊት አሳይቶ አያውቅም። መኢሶን የአብዮታዊ ዕውቀትም ሆነ አሰራር ሞኖፖል እንደሌለው ያምናል። እኛ ከሌሎች እንማራለን፣ ሌሎችም ከኛ ይማራሉ የሚል እምነት አለን። እርስ በርሳችን እንተራረማለን፣ እንደጋገፋለን፣ ሁላችንም ለአብዮቱ ተሰልፈናልና የሚል እምነት አለን። በተረፈ ግን፣ በጠባብ ቡድን ስሜት ስም ወይንም በሌላ ቅፅል አማካይነት ሃቀኛ ፖለቲካዊና ርእዮተዓለማዊ ትግል እንዲታፈን፣ ውይይቶችና ክርክሮች እንዳይኖሩ ለማድረግ መሞከርና በዲሞክራሲያዊ አሰራር አለማመን የሰፊው ሕዝብ ትግል ወደፊት እንዳይገፋ መሰናክል መሆን ነው እንላለን።
ባሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ አብዮት በውስጥ እንደሚቦረቦርና በውጭም በየዕለቱ ይበልጥ እንደሚከበብ ተደጋግሞ ተገልጿል። አብዮቱና የአገሪቱ አንድነት ጭምር በትልቅ ፈተና ውስጥ ወድቀው ይታያሉ። የተራማጆችን ህብረት የማጠንከሪያውና ሰፊውን ሕዝብ ከዳር እስከዳር ማንቀሳቀሻው ወቅት አሁን ነው። ነገ ሊዘገይ ይችላል። ስለዚህም፣ የኢትዮጵያ ተራማጆች ሁሉና በተለይም ስልጣኑን የያዘው ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት፣ ባንድነት ሊሰበሰቡ የሚችሉትን ኃይሎች ሁሉ በአንድነት ለመሰብሰብ የመታገል ታሪካዊ ኃላፊነት አለባቸው። ይህንን ኃላፊነት አለመገንዘብና በሰበብ ባስባቡ የኢትዮጵያን ተራማጆች ለማራራቅ፣ በመካከላቸው ጥርጣሬንና አለመተማመንን ለመፍጠር መሞከር በነኢህአፓ -ኢዲዩ – ኢኤልኤፍ ወጥመድ ውስጥ መውደቅ ብቻ ሳይሆን በታሪክም ፊት የሚያስጠይቅ ድርጊት ይሆናል።
የኢትዮጵያ ማርክሲስት-ሌኒኒስት ድርጅቶች ህብረት ይጠንክር!
የነቃ የተደራጀ፣ የታጠቀ የሰፊው ሕዝብ አመጽ ያሸንፋል!
የሶማሊያ “ሶሻሊስትና” “አብዮታዊ” ነን ባዮች ሲጋለጡ!
ማርክሲዝም እንደሚያስተምረንና የዓለም ሕዝቦች አብዮታዊ ትግል ታሪክ በሚገባ እንደሚያሳየን አንድን መንግሥት ወይም ፓርቲ መፍረድ የሚቻለው ራሱ ለራሱ በሚሰጠው ስም ሳይሆን በትግሉ ውስጥ በድርጊት በሚወስዳቸው አቋሞች ነው። በተለይ በአሁኑ ዓላማችን አብዮትና ሶሻሊዝም በቢልዮን የሚቆጠሩ ጭቁን ሕዝቦች የኑሮ ተስፋ ሁኖ በሚታይበት ወቅት “አብዮታዊና” “ሶሻሊስት” የሚሉት ቅጽሎች አንድን ፓርቲ ወይንም መንግሥት አብዮታዊና ሶሻሊስት የግድ አያደርጉትም።
በአገራችን ከኢትዮጵያ “ሕዝባዊ” “አብዮታዊ” ፓርቲ ከተባለው ፀረሕዝብና ፀረአብዮት ቡድን የኢትዮጵያ ሕዝብ የቀሰመው ትምህርት ይኸው ነው። የሶማሊያ መንግሥት ንዑስ ከበርቴዎች ከምኑም ከምኑም ተጠራርተው አቋቋምን ያሉት “የሱማሊያ ሶሻሊስት አብዮታዊ ፓርቲ” ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተግባር የሚያሳያቸው ድርጊቶች ይህ የንዑስ ከበርቴዎች ጥርቃሞ በምንም አይነት አብዮታዊም ሆነ ሶሻሊስት እንዳይደል እያስመሰከረ ነው።
በተለይ በዓለምአቀፍ ሁኔታው ብንመለከተው “የወዛደር ዓለማቀፋዊነት” የሚለውን መርሆ ጨርሶ የማያውቅ፣ የኢትዮጵያን አብዮት አስቀልብሶ አካባቢውን ለኢምፔሪያሊዝም የተመቻቸ ለማድረግ፣ አገራችንን በበኩሉ እያስወረረና ይህንን አጉል መፍጨርጨሩን ደግሞ “የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ተዋጊዎች” ከሚላቸው ከነመንገሻ ስዩም ጋር በይፋ እያስተባበረ ነው። የአንድን ጭቁን ሕዝብ አብዮት ለመቀልበስ ያ ሕዝብ ከተፋቸው መሳፍንትና መኳንንት ጋር አንድ ሆኖ መስራት። እንዲህም አርጎ የለ “ሶሻሊስትና” “አብዮታዊ”።
***
ታጋይ ሲሞት ትግል እንዳይሞት
አድሃሪ ኃይሎች አሁንም የአብዮቱን ሰፈር ለማጥቃት በመፍጨርጨር ላይ ናቸው። በሲዳሞ፣ በአርሲ፣ በሐረርጌ፣ በባሌ፣ በጎንደር እና በኤርትራ ክፍለ ሃገሮች አድሃሪዎች ኃይላቸውን እያስተባበሩ አብዮታችንን እየወጉ ናቸው። በከተሞችም በብዙ ቦታዎች ከጥቂት ሳምንታት በፊት አንገታቸውን ደፍተው የነበሩትን ያህል አሁን ደግሞ ቀና ቀና ማለት ጀምረዋል። በቅጥር ነፍሰ ገዳዮች አማካኝነት የሚያካሄዱት የነጭ ሽብር ዘመቻ የብዙ ጓዶቻችንን ሕይወት እንድንሰዋ አድርጎናል። አሁንም የቀበሌ ተመራጭ ጓዶቻችን፣ ታጋይ ወዛደሮች፣ መለዮ ለባሾች፣ ወጣት አብዮታዊያን፣ የሕዝብ ድርጅት ጉዳይ ጊዜያዊ ጽ/ቤት ጓዶች፣ መምህራንና ሃገር ወዳድ ታጋዮች በያለበት በአድሃሪዎች ጥይት እየወደቁ ናቸው። ባለፉት ቀናት በደሴ፣ በአዲስ አበባ፣ በሀረር፣ በጎንደር፣ በብቸናና፣ ….በሌሎችም ብዙ ቦታዎች የፈሰሰው የነጓድ ስንታየሁ፣ ዓለማየሁ፣ ግርማ እንደዚሁም የነጓዲት የሸዋሉል፣ እምቅድመአለም፣ ሃና፣ እታለማሁ ደም ቅጥር ነፍሰ ገዳዮች ወደ አጥቂነት እየተሸጋገሩ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ነው።
በመሰረቱ አብዮት መስዋዕትነት የተሞላበት የረዥም ጊዜ ትግል በመሆኑ አብዮታዊያን ለሱ መዘጋጀትና ሰፊውን ሕዝብ ማዘጋጀት እንዳለባቸው ያውቃሉ። ነገር ግን አድሀሪያን ቅጥር ነፍሰ ገዳዮችን እያሰማሩ በብዙ ጊዜ ትግልና ልምድ የአብዮቱ አለኝታ የሆኑ ግንባር ቀደም ታጋይ ጓዶቻችንን ከጎናችን ሲቀነጥሱ እያየን “ታጋይ ይሞታል እንጂ ትግል አይሞትም” በሚል ፈሊጥ ብቻ እየተፅናናን መቀጠል አንችልም። ታጋይ ሲሞት ትግል አብሮ እንዳይሞት መታገል ያስፈልጋል። ከእያንዳንዱ ጓድና ከእያንዳንዷ ጓዲት ሞት ትምህርት እየቀሰምን የትግል ዘዴያችንን በዚሁ መሰረት እያሻሻልን መጓዝ አለብን። በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባለች አብዮቷን ያለግንባር ቀደም ድርጅት የምታካሂድ አገር የግለሰብ ታጋዮችን ሕይወት የሺህ ቅጥር ነፍሰ ገዳዮች ደም ሊተካው እንደማይችል መገንዘብ ያስፈልጋል።
ስለሆነም ተጋይ ሲሞት ትግል አብሮ እንዳይሞት የአድሃሪዎችና የቢሮክራሲው አሻጥር በተከላካይነት ሊወስነውና ሊያከሽፈው ከሚሞክረው አብዮታችን በተግባር በየእለቱ በቦታው ወደ አጥቂነት መሸጋገር አለበት። ለዚህም ሕዝባዊ ድርጅቶች ከአሁኑ ይበልጥ መጠንከር፣ አሁንም ሰፊውን ሕዝብ ይበልጥ ማደራጀትና ማስታጠቅ፣ አሁንም በይበልጥ ነፃ ሕዝባዊና አብዮታዊ እርምጃዎችን እየወሰደ አብዮቱን በተግባር ወደ አጥቂነት እንዲያሸጋግር፣ ለዚህም ሁሉ አሁንም በይበልጥ የቢሮክራሲውን አሻጥር ነቅቶ እንዲቋቋም መታገል ያስፈልጋል። ይህ ካልሆነ በአጭር ጊዜ ውስጥ አብዮታችን አስጊ የሆነ ደረጃ ላይ ሊደርስ እንደሚችል መገንዘብ ያስፈልጋል።
***
ማሳሰቢያ
ብዙ አባቢዎቻችንና ደጋፊዎቻችን ሀሳባቸውን ለመግለጽ አስተያየቶቻቸውን፣ አጫጭር የትግል ዜናዎችንና ደብዳቤዎችን ለሰፊው ሕዝብ ድምጽ ለመላክ እየፈለጉ መቸገራቸውን ገልጸውልናል። ከሰሕድ ቁ. 58 ጀምሮ ለእንደዚህ አይነቶቹ አስተያየቶች፣ ዜናዎችና ደብዳቤዎች ቦታ ስለሚኖረን ሰሕድን በሚያሰራጩ ጓዶች አማካይነት ቢላክልን የምናወጣ መሆናችንን እንገልጻለን።