ልዩ እትም 4 1968

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ልዩ እትም፤    ግንቦት 10፣ 1968

የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ

ግንቦት 8፣ 1968 ዓ.ም. የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር “የኤርትራን ችህር ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለመፍታታ አዲስ ፖሊሲ አወጣ። ይህ የዘጠኝ ነጥብ ፖሊሲ ውሳኔ በዋናነት የኤርትራ ችግር በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ፣ በኤርትራ የታወጀው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲነሳ፣ የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ፣ በጦርነቱ የፈራረሱ የኢኮኖሚ መዋቅሮች እንደገና እንዲገነቡ የሚሉ ሃሳቦችን ያካተተ ነበር። በዚህ ልዩ እትም መኢሶን የፖሊሲ ውሳኔውን መደገፉን በይፋ ይገልጻል። ደርጉ ቀደም ሲል የኤርትራን ጥያቄ በጉልበት ለመፍታታ የነበረውን ውሳኔ፣ እንዲሁም “የኢትዮጵያ አንድነትና ፍጹምነት” ከሚለው ፖሊሲ ባሻገር በአብዮቱ መላስተኛ ፕሮግራም ላይ እንደተጠቀሰው፣ ወደ ብሄረሰቦች የራሳቸውን እድል በራሳቸው መወሰን መሸጋገሩ ትክክለኛ አቋም መሆኑን ይጠቁማል። መኢሶን ይህ ፖሊሲ በኤርትራ ለሚገኙ ተራማጅ ኃይሎች መልካም እድል እንደሚፈጥርና የኤርትራ ጭቁን ሕዞች ከኢትዮጵያ ጭቁኖች ጋር በአንድነት ጠላቶቻቸውን ለመታገል ያስችላቸዋል ብሎ ያምናል።

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ለሰፊው ሕዝብ ሰራተኛ ገበሬ፣ ነጋዴ፣ ወታደር፣ ምሁር መብትና ጥቅም የሚታገል ጋዜጣ

የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ይቅደም

 
ልዩ እትም                                                                     ቀን 10/9/68

 

ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት

የኤርትራን ችግር በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያስችላል ብሎ ያቀረበው የፖሊሲ ውሳኔና

የመኢሶን አቋም

ግንቦት 8/68 የጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት ‘በኤርትራ ክፍለ ሃገር ያለውን ችግር በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት’ ያስችላል ብሎ ያመነበትን አንድ ባለ ዘጠኝ ነጥብ የፖሊሲ ውሳኔ አቅርቧል።

ይህ የፖሊሲ ውሳኔ የኤርትራ ጥያቄ በዲሞክራሲያዊ መንገድ እንዲፈታና የሰላም ድርድር እንዲጀምር ለትግሉ ተራማጆች ሁሉ አንደ አንድ ታላቅ ድል የሚቆጠር ነው። ስለሆነም፣ መኢሶን ይህን ለሰላም ውይይት ዝግጁነትና ለዚህም ድርድር የውይይት ጥሪ መደረግ ሙሉ በሙሉ ይደግፋል። ከሥራም ላይ በትክክል እንዲውል ተመሳሳይ አቋም ካላቸው ተራማጅ ወገኖች ጋር ሁሉ አብሮ ይሰለፋል፣ ይታገላልም። ይህን ባለዘጠኝ ነጥብ የፖሊሲ ውሳኔ በቀጥታ መሪ መንገድ የሚቃወሙና በትክክል ሥራ ላይ ውሎ ለኤርትራ ጥያቄ ሰላማዊ መፍትሄ እንዳያስገኝ እንቅፋት የሚሆኑትን አድሃሪና አስመሳይ ተራማጆች አጥብቆ ይቃወማል። ሰልፋቸው ከኢትዮጵያ ሕዝቦች ጠላቶችና ከኤርትራ አድሃሪዎች ጋር መሆኑን ያጋልጣል።

ለዚህ ውሳኔ ከተራማጆች ድጋፍ የሚያሰጡ ብዙ ነጥቦች አሉ። የማያሻማ መንገድ ከጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት ከፊውዳሊስቶች፣ ከአካባቢው አድሃሪ ኃይሎችና ከኢምፔሪያሊስቶችም ጋር ካልተሳሰሩት የኤርትራ ተራማጅ ቡድኖችና ድርጅቶች ጋር ለመወያየት ዝግጁ መሆኑን ገልጿል። ከፍተኛ ግምት የሚሰጠውም ሌላ ነጥብ፣ ኤርትራ ተራማጆች የኤርትራን ሰፊ ሕዝብ ለፀረ ፊውዳል ለፀረ ኢምፔሪያሊስትና ለፀረ ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝም ትግል ለመቀስቀስ፣ ለማደራጀትና ለመምራት ስለመቻላቸው የተጠቀሰው ነው። ከነዚህም ሌላ፣ ስለ ስደተኞች መቋቋሚያ ማግኘት፣ ስለ ኤርትራ የፖለቲካ እስረኞች መፈታት፣ ሌሎች የተጎዱ ወገኖች ችግራቸው ስለሚቃለልበት ሁኔታ፣ ያስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስለሚነሳበት ሁኔታ የሚመለከቱት ነጥቦች ለሰላማዊ ድርድር እና የኤርትራን ጥያቄ በሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ መንገድ ለመፍታት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥሩ ናቸው።

ወታደራዊው ደርግ በአገራችን የፖለቲካ መድረክ ላይ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ፣ በሰፊው ሕዝብ አብዮታዊ ትግል እየተገፋ ለዚሁ ትግል የሚጠቅሙ ተራማጅ እርምጃዎች ወስዷል። የብሄርን ጥያቄና በተለይም የኤርትራን ጥያቄ በሚመለከተው በኩል ግን ብዙ የተራማጅ እርምጃዎቹ ተጻራሪ የሆኑ አቋሞችና እርምጃዎች ወስዷል። የኤርትራን ጥያቄ ለመፍታት ያሰበው በወታደራዊ ኃይል ነበር። መደብና ወገን ያልለየ በኤርትራ ሕዝቦች ላይ ጠቅላላ ዘመቻ ተወጥኖ ነበር። ይህ ዘመቻ የኤርትራን ችግር የሚያባብስ፣ ሁለቱን ሕዝቦች አብረው ለመኖር የማይችሉበት ሁኔታ የሚያደርስ፣ የኢትዮጵያንም አብዮት ከአደጋ ላይ የሚጥልና የቀኝ ኃይሎችን ብቻ ሊጠቀም የሚችል መሆኑን በመግለጽ በሰፊው ሕዝብ ደምጽ ልዩ እትማችን መቃወማችን ይታወሳል። ዛሬም በተለይ ከዚህ ዲሞክራሲያዊ የውይይት ጥሪ በኋላ፣ምንም ማለባበስ ሳይደረግበት የዚህ አይነቱ ዘመቻ መሰረዝ ይኖርበታል። የቀረበው ዲሞክራሲያዊ የፖሊሲ ውሳኔና የዚህ ዓይነቱ ዘመቻ አብረው የማይሄዱና ተጻራሪዎች ናቸው።

ከደርጉ የቅርብ ጊዜ ተራማጅ እርምጃዎች አንዱ፣ የኢትዮጵያ አብዮት መለስተኛ ፕሮግራም. በጊ.ወ.መ. መውጣት ነው። በዚህ ፕሮግራም ውስጥም ደርጉ ‘የኢትዮጵያ አንድነት ፍጹምነት’ የሚለውን ትምክህተኛ አቋሙን የብሔረሰቦች ራሳቸውን እድል በራሳቸው ለመወሰን ያላቸውን መብት ባወቀ ዲሞክራሲያዊ መርህ ተክቶታል። የአሁኑ ስለ ኤርትራ ጥያቄ የወጣ የፖሊሲ ውሳኔ፣ ከዚህ ፕሮግራም መውጣትና በአጠቃላይም ከኢትዮጵያ ሕዝቦች ትግል ትክክለኛ አቅጣጫ እየያዘ መሄድ ተነጥሎ ሊታይ አይችልም። የኢትዮጵያን ሕዝቦች ትግል ትክክለኛ አቅጣጫ ለማስያዝ የተደረገው ተጋድሎ ያስገኘው ድል ነው ልንል የምንችለውም ለዚህ ነው።

በሌላ በኩል፣ የኤርትራ ሕዝቦች ትግል ከኢትዮጵያ ቀርቶ ከአካባቢው ትግሎች ተፅዕኖ ነፃ ሊሆን አይችልም። የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ከታወቁ ጠላቶቹ ጋር በሚያካሂደው አብዮታዊ ትግል፣ የኤርትራ ጭቁኖች ከመቼውም የበለጠ ወደጅና ጠላት እንዲለዩና የራሳቸውን ትግል ከጭቁኖች ሁሉ የነፃነት ትግል አንፃር መመልከት እንዳለባቸው መረዳት መጀመራቸው አልቀረም። ይህም በመሆኑ ሀቀኛ የኤርትራ ተራመጆች ራሳቸውን ከአስመሳይ ተራማጆችና ከለየላቸው የፖለቲካ ነጋዴዎች እየለዩ በመሄድ ላይ ናቸው። ይህ በደርጉ የተገለጸው የፖሊሲ ውሳኔም እነዚህ የኤርትራ ተራማጆች ለራሳቸው ጭቁኖች ትክክለኛ አመራር ለመስጠት ያደረጉት መስዋእትነት የተሞላበት ተጋድሎ አንድ ውጤት ነው።

የኢትዮጵያ ሕዝቦች ትግል እየገፋ በሄደ ቁጥር በአለም አቀፍ ደረጃ ያሉ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጠላቶችና ወዳጆች ወገን እየወሰዱ መሄዳቸው የማይቀር ነው። ይህም በመሆኑ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አለም አቀፋዊ ጠላቶች ከመቼውም የበለጠ አብዮታችንን ለመቀልበስ በሚያሴሩትን ያህል፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ወዳጅ የሆነው ተራማጅ የዓለም ክፍል ለኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ትግል የሚያሳየውን ድጋፍ ጨምሯል። የኤርትራን ጥያቄ በሰላም ለመፍታት የደርጉን ዝግጁነት ያመጣው ሌላኛው ሀቅ ይኸው የኢትዮጵያ ሕዝቦች በአብዮታዊ ትግላቸው ከተራማጁ የዓለም ክፍል ያገኙት ድጋፍ ነው።

በመሠራቱ፣ ወታደራዊው ደርግ አሁን ያቀረበውን ለሰላማዊና ለዴሞክራሲያዊ መፍትሄ መንገድ የሚከፍት ውሳኔ ቀደም ብሎ ቢያቀርብ ኖሮ በኤርትራ ያለው ሁኔታ እስከዛሬ ተካሮ ያለመፍትሄ ባልቆየም ነበር። ሆኖም፣ ለሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ውሳኔ የሚበጀው ይህ ውሳኔ ዘግይቶ ቢደርስም ጊዜው አልፎበታል ወይም ከእንግዲህ አይሰራም ማለት አይደለም። የኤርትራ ሀቀኛ ተራማጅ ኃይሎችና ድርጅቶች በራሳቸው ትግል ጭምር የተገኘ ድል መሆኑን ተገንዝበው በቶሎ አብዮታዊ መልስ ከሰጡበት ዛሬም ቢሆን ለኤርትራ ጥያቄ ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ መፍትሄ ሊገኝ ይችላል።ሰፊው  የኤርትራ ሕዝብ ለረጅም ዘመን ያደረገው ተጋድሉና የደረሰበት ስቃይ ሰላምና ከጭቆና ነፃ ለሚያወጣው ድል ሊያበቃው ይገባል። የኤርትራ ሀቀኛ ተራማጆች፣ የኤርትራ ጭቆኖች ትግል ወደዚሁ እንዲያመራ በሚያስችል ሁኔታ በመጠቀም ለኤርትራ ጥያቄ ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ መፍትሄ ለማግኘት የራሳቸውን ከፍተኛና ታሪካዊ ድርሻ እንደሚያሟሉ እምነታችን ነው።

ይህ ሊሳካ ካልቻለ፣ ማለትም የኤርትራ ሀቀኛ ተራማጆች በበኩላቸው ለኤርትራ ጥያቄ ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ መፍትሄ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ካላበረከቱ፣ አድሃሪ ኃይሎች የተፈጠረውን አመች ሁኔታ ለማደፍረስ የበለጠ እድል ያገኛሉ። ይህም በኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ትግል ላይ ብቻ ሳይሆን በኤርትራ ሀቀኛ ተራማጆችም ላይ ትልቅ አደጋ እንደሚያመጣ ግልፅ ሊሆን ይገባል። የኤርትራ አሃድሪዎች የአሁኑን አመቺ ሁኔታ ለመቀልበስ እድል ካገኙ በቀድሚያ ሊያጠፉ የሚነሱት የኤርትራን ሀቀኛ ተራማጆች ነው። ለዚህም እስከዛሬ ለኤርትራ ጭቆናዎች እውነተኛ ነፃነት በተሰለፉ የኤርትራ ሀቀኛ ተራማጆች ላይ ያደረሱት ግድያና እስራት ጉልህ ማስረጃ ነው። አሁንም ቢሆን፣ በኤርትራ ግንባር አመራርና አካባቢ የሚገኙ አድሃሪዎች ጦርነት ቀጥሎ እነርሱም ከኢትዮጵያ መሳፍንት፣ ከነመንገሻ ስዩም ‘የኢትዮጵያ ዲሞክራቲክ ህብረት’ ጋር የጀመሩትን መመሳጠር ሊገፉበት እንጂ ለችግሩ ሰላማዊ መፍትሄ አይሹም።

የዚህን ለሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ መፍትሄ የሚበጅ ሁኔታ መቀልበስ የሚሹና ለዚሁም ግብ የሚታገሉት የታወቁት የኤርትራ አድሃሪዎች ብቻ አይደሉም። በስልጣን ላይ ያሉ ቢሮ ከበርቴዎችና ሌሎችም የኢትዮጵያ አድሃሪዎች ችግሩ እንዲባባስ፣ የወንድማማቾች እርስ በርስ መፋጨት እንዲቀጥልና እነርሱም ፋታ አግኝተው የራሳቸውን ፀረ አብዮት ሴራ ለማድራት እንዲያመቻቸው ይፈልጋሉ። በእኩልነት፣ በመፈቃቀድ እና የጋራ ጠላትን ለመደምሰስ ሊቆም የሚችለውን የኢትዮጵያና የኤርትራ ጭቆናዎች ትግል አንድነት እነርሱንም የሚያጠፋ ስልሆነ ይፃራሩታል። ስለዚህም ይህን የኤርትራን ጥያቄ ሰላማዊና በዲሞክራሲያዊ መንገድ ለመፍታት ምቹ ሁኔታ የሚፈጠር የጊ.ወ. መ የፖሊሲ ውሳኔ ለመቀልበስ ከመታገል በፍጹም አይቆጠቡም። በአጭሩ፣ የኤርትራ አድሃሪዎችና የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ጠላቶች ይህን ብቹ ሁኔታ ለመቀልበስ ይጥራሉ። የኢትዮጵያና ኤርትራ ሀቀኛ ተራማጆች ይህንኑ ተረድተው በዚህ ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ችግሩ ለኤርትራና ለኢትዮጵያ ጭቁኖች በሚጠቅም መንገድ እንዲያልቅ በአስቸኳይ መታገል ከፍተኛና ታሪካዊ ኃላፊነታቸው ነው። የአሁኑ ምቹ ሁኔታ መቀልበስ የሚጠቅመው የሁለቱንም ወገኖች ጠላቶች ነው።

የኤርትራ ጥያቄ ለኢትዮጵያና ለኤርትራ ጭቁኖች በሚጠቅም መንገድ መፈታት አለበት ማለት ከሁሉም በላይ የሁለቱም ወገን ሰፊ ሕዝቦች በጠላቶቻቸው ላይ ድልን መቀዳጀት አለባቸው ማለት ነው። የኢትዮጵያ ተራማጆ የኢትዮጵያን ሰፊ ሕዝብ የኤርትራንም ጭቁኖች ጠላቶች ለሚደመስሱበት ፀረ ፊውዳል ፀረ ኢምፔሪያሊስትና ፀረ ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝም አብዮታዊ ትግል ማንቃትና ማደራጀት አለባቸው። የኢትዮጵያን ሰፊ ሕዝብ ትግል በወዛደሩ ፓርቲ ወደሚመራ የነቃ፣ የተደራጀና የታጠቀ ትግል ማሳደግ አለባቸው። በኤርትራ፡ ሕዝቦችና በሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ መካከል መቃቃር እንዲሰፍን፣ ችግሩ ተባብሶ አብሮ ለመኖር ወደ ማያስችል ደረጃ እንዲደርስ የሚሹ ፀረ ሕዝብ ኃይሎችንና ባጠቃላይ የብሄር ትምከተኛነትን በማጋለጥ በኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብና በኤርትራ ጭቁኖች ተገቢው መግባባት እና ትብብር እንዲመሠረት መታገል አለባቸው።

የኤርትራ ተራማጆችም በበኩላቸው የኤርትራ ጭቁኖች ከታወቁ ጠላቶቻቸው፣ ከፊውዳሊዝም፣ ከቢሮክራሲዊ ካፒታሊዝምና ከኢምፔሪያሊዝም ጋር ለሚያደርጉት ትግል ትክክለኛ አመራር ለመስጠትና የኤርትራም ጭቁኖች ትግል ፀረፊውዳል ፀረኢምፔሪያሊስትና ፀረቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝም መስመር ይዞ እንዲራመድ የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው። የኤርትራ አድሃሪዎች የሰፊውን ሕዝብ ትግል ለፀረአብዮት አላማቸው ለማዋል የሚያደርጉት ሴራ ለማክሸፍና በጭቁኖች መሃል ሊኖር የሚገባውን የትግል አንድነት ለማምጣት በንጹህ ዓለምአቀፋዊነትና የጭቁኖች ወገንነት መንፈስ መታገል አለባቸው።

እነዚህ ሁኔታዎች እስካልተሟሉ ድረስ የዛሬው ለሰላማዊና ለዲሞክራሲያዊ መፍትሄ ሊበጅ የሚችል ሁኔታ በማንኛውም ጊዜ ሊቀለበስ ይችላል። ይህን ስንል የጉዳዩን አጣዳፊነትና አሳሳቢነት ለመግለጽ እንጂ ተስፋ የሚያስቆርጥ ሃሳብ ለመሰንዘር አይደለም። ይዋል ይደር እንጅ ኤርትራ ጥያቄ ትክክለኛና ዲሞክራሲያዊ መፍትሄ ማግኘቱ የማይቀር ነው። የኤርትራ ተራማጆች አድሃሪዎችን አሸንፈው ለኤርትራ ሕዝቦች ትክክለኛና አብዮታዊ አመራር ለመስጠት እንደሚችሉ እሙን ነው። የኢትዮጵያ ተራማጆችም የኢትዮጵያን ሕዝቦች ትግል በወዝአደሩ ፓርቲ የሚመራ የነቃ፣ የተደራጀና የታጠቀ ጎዳና እንደሚያሲይዙት እንደዚሁ እሙን ነው። የኤርትራና የኢትዮጵያ ሕዝቦች ትግል ትክክለኛና አብዮታዊ አመራር ካገኘ ደግሞ ተደጋግፎና ተቃቅፎ የጋራ ጠላትን የሚደመስስ አብዮታዊ ኃይል እንደሚሆንና ለወደፊቱም የጭቁኖች በኩልነት ላይ ለሚገነባ አንድነት መሠረት እንደሚሆን አያጠራጠርም።

መኢሶን የኤርትራ ጥያቄ አጣዳፊ መፍትሄ እንደሚያስፈልገው በማመንና ጭቁኖች በጋራ ጠላቶቻቸው ላይ በሕብረት የጋራ ድል ለማግኘት መነሳት እንዳለባቸው በማመን ለኤርትራ ተራማጆች የተለየ የትግል ጥሪ ያደርጋል። በዚሁ አጋጣሚ፣ ከኤርትራ ተራማጆችና ጭቁኖች ጋር በፀረ ፊውዳል፣ በፀረ ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝምና በፀረ ኢምፔሪያሊስት ትግል ላይ ያለውን የጋለ የትግል አንድነት ይገልፃል። ለኤርትራ ጭቁኖች እውነተኛ ነፃነት ሲታገሉ በትግሉ ሜዳ የወደቁትንም ሰማዕታት በከፍተኛ አብዮታዊ ስሜት ያስታውሳቸዋል።

የኤርትራና ኢትዮጵያን ሕዝቦች በጋራ ጠላቶቻችን ላይ ለምናገኘው የጋራ ድል እንዲያበቃን መታገል ከመኢሶን ዋና ዋና አላማዎቻች አንዱ ነው። ለዚሁ ግብ በሚታገሉ የኤርትራ ተራማጆች መኢሶን የትብብር እጁን ይዘረጋል።

ፀረ ሕዝብ ኃይሎች የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ እንዳያደፈርሱ ነቅተን እንታገል
የኤርትራና የኢትዮጵያ ተራማጆች የትግል ህብረት በፍጥነት ይመስረት የጭቁን ሕዝቦች አንድነት ይኑር
ድሉ የጭቁን ሕዝቦች ነው
Scroll to Top