ልዩ እትም 3 1968

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ልዩ እትም፣    ሚያዝያ 23፣ 1968

የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ

በዚህ ልዩ እትም፣ የሰፊው ሕዝብ ድምፅ የአለም ወዛደሮች  የስራ ሰዓት በቀን 8 ሰዓት እንዲሆን ከመታገል ጀምሮ እስከዛሬ ከፍተኛ ድሎችን መጎናጽፉንና ይህ ትግል ወደፊትም ገና የሚቀጥል መሆኑን በማብራራት ይጀምራል። ወዛደሩ የአለምን ጭቁን ሕዝቦች ሁሉ መርቶ ነጻ የማውጣት ሃላፊነት እንዳለበት ለዚህም ትግል በራሱ ፓርቲ መደራጀት እንዳለበት ያስታውሳል።

የኢትዮጵያ ወዛደር ምን ቢታገልና መስዋዕትነት ቢከፍልም በራሱ የነቁ ጓዶቹ በሚመሠረተው የወዛደር ፓርቲ እስካልተመራ ድረስ በጠላቶቹ ላይ ድልን መቀናጀት እንደማይችል ያረጋግጣል። ይህ ልዩ እትም፣ በኢትዮጵያ ውስጥም ወዛደሩ ነቅተሃል፣ ተደራጅተሃል ከሚሉት አዋናባጆች እራሱን አጥርቶ፣ ራሱን በሳይንሳዊ ሶሺያሊዝም አንፆና አንድነቱን አጠናክሮ በእውነተኛ የወዛደር ፓርቲ እየተመራ ለሥልጣን መታገል እንዳለበት አጥብቆ ይሟገታል።

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ለሰፊው ሕዝብ ሰራተኛ ገበሬ፣ ነጋዴ፣ ወታደር፣ ምሁር መብትና ጥቅም የሚታገል ጋዜጣ

የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ይቅደም

 
ልዩ እትም                                                                  ቀን 23/08/68

 

ሜይ አንድ- የዓለም ወዛደሮች የትግል ቀን

የአለም ወዛደሮች በካፒታሊስት ሥርዓት ላይ ያላቸውን ተቃውሞ በህብረት በመግለጽ መታገል ከጀመሩ ብዙ ዓመታት አልፈዋል። ይህም የዓለም ወዛደሮች ህብረትና ተጋድሎ ከፍተኛ ደረጃ መድረሱ የተመሰከረው፣ በወቀቱ የዓለም ወዛደሮች አንገብጋቢ ጥያቄ የነበረውን የስምንት ሰአት የሥራ ቀን ለማስወሰን የዛሬ 86 ዓመት በዛሬው ቀን በተከበረው ዓለም አቀፋዊ የወዛደሮች የትግል ቀን ነበር። ከዚያን ጊዜ ወዲህ የወዛደሩ መደብ ባካሄዳቸው ትግሎች ብዙ ድሎችን ተጎናጽፏል። ዛሬም፣ ወዛደሩ የዓለምን ሕዝብ ሲሶ ነጻ በማውጣት ወደ መደብ የለሹ ህብረተሰብ በመገስገስ ላይ የሚገኝባቸው በርከት ያሉ አገሮች አሉ። የተቀሩትም ወዛደሮች ካፒታሊዝምንና ለጭቆና ሥርዓቶችን ሁሉ በመቃወም በታላቅ ትግል ላይ ይገኛሉ።

ሜይ አንድ በአገራችን ሲከበር ሁለተኛው ጊዜ ይሁን እንጂ በተቀሩት ብዙ አገሮች 86 ዓመት ሙሉ በጋለ ስሜት የሚከበር የወዛደር የትግል በዓል ሆኖ ሲከበር ቆይቷል። የወዛደሩ መደብ በዚህ ቀን ባለበት ሥርዓት ውስጥ የሚገኘውን ብዝበዛና ጭቆና በመቃወም ለጊዜያዊ ጥቅሙና ለአጣዳፊ ችግሮቹ መፍትሄ እንደ አንድ ሰው ተነስቶ ይታገላል። ራሱንና ጭቁኖችን ሁሉ ነፃ ለማውጣት ያለበትን የታሪክ ተልዕኮ ለማሟላት ምን ያህል እንደተጓዘ እና ምን ያህል እንደሚቀረው ያመዛዝናል። ዓለምአቀፋዊ አንድነቱንም በገቢር ይገልፃል።

የኢትዮጵያ የወዛደር መደብ በዘመናችን የሰውን ዘር ከጭቆና ቀንበር ለማውጣት የታሪክ ተልዕኮ ያለበት የአለም አቀፉ ወዛደር አካል ነው። ይህም በመሆኑ፣ የዛሬውን ሜይ አንድ ለረዥም ጊዜ ሲከበርክበት በኖረው የትግል መንፈስና አብዮታዊ ይዘት ማክበር ግዴታው ነው። የኢትዮጵያ ወዛደር በዛሬው ቀን ለአንገብጋቢና ለአጣዳፊ ጥያቄዎቹ መሰለፍ አለበት። ካለፉት ትግሎቹ ተገቢውን ትምህርት ቀስሞ ለሚቀረው ትግሉ አስፈላጊ የሆኑትን ሁኔታዎች ለማሟላት ለሚያስችሉት ጥያቄዎች መሰለፍ አለበት። እስከዛሬ ላደረገው ተጋድሎ ተገቢ ቦታ ሰጥቶ ለሚቀረው ትግሉ አስፈላጊውን  ዝግጅት ለማድረግ መነሳት አለበት። ከአለም ወዛደሮችና ጭቁን ሕዝቦች ጋር ያለውን የትግል አንድነት በመግለጽ በኢምሪያሊዝም ላይ የተቃውሞ ድምፁን ማሰማት አለበት።

በዚህ አብዮታዊ በዓል ላይ፣ የወዛደሩ መደብ ከማይናቁ ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎቹ አልፎ፣ ሊያነሳቸው ከሚገባቸው አስቸኳይ የትግል መፈክሮች ዋነኛው የዲሞክራሲያዊ መብቶቹን ለሰፊው ሕዝብ መከበር መጠየቅ መሆን አለበት። በዛሬው የአገራችን ሁኔታ፣ የወዛደሩ መደብ ሆነ የሰፊው ሕዝብ ትግል በከፍተኛ ደረጃ ወደፊት መቀጠል የሚችለው ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለሰፊው ሕዝብ በአስቸኳይ ሲከበሩ ብቻ ነው። ይህ ሲሆን፣ ወዛደርና የተቀረውም ሰፊ ሕዝብ በፍጥነት ንቃታቸውን ሊያዳብሩ፣ ሊደራጁና ሊታጠቁ የሚችሉበት ሁኔታ ይፈጠራል። የሰፊው ሕዝብ ትግል የነቃ የተደራጀና የታጠቀ የትግል ጎዳና መያዝ ደግሞ፣ ጠላቶቻችንን መደምሰስና የአብዮታችንን ድል መምታት የሚያረጋግጥ ይሆናል።

በኢትዮጵያ የወዛደር መደብ ትግል አንፃር በዛሬው ቀን እንደ አጠዳፊ የትግል ጥያቄ መቅረብ ያለበት የወዛደሩ ፓርቲ መፈጠር ጉዳይ ነው። የወዛደሩ መደብ በራሱ ርእዮተ አለም ታንጾ፣ የወዛደሩን መደብ ስልጣን ለማስጨበጥ እና ጭቆናን እንዳይመለስ አድርጎ ለማጥፋት በሚፈጥረው ፓርቲው ስር ሳይደራጅ የሚጠበቅበትን ታሪካዊ ኃላፊነት ሊያሟላ፣ የዲሞክራሲያዊ የአብዮቱ መሪ ሊሆን አይችልም። የወዛደሩ ፓርቲ በአስቸኳይ አለመፈጠር፣የወዛደሩ መደብ ለዚህ ኃላፊነቱ ብቁ አለመሆን የወዛደሩን መደብ ትግል ብቻ ወደ ኋላ የሚያስቀር ነገር አይደለም። በጠቅላላው የኢትዮጵያን የዛሬ አብዮታዊ ትግል ከግብ መድረስ ወይንም መክሸፍ የሚወስን ከፍተኛ ጉዳይ ነው።

የተያዘውን አብዮታዊ ትግል መርቶ ከፍጻሜ ሊያደርስ የሚችለው የወዛደሩ መደብ ብቻ ነው። ወዛደሩ ለዚህ ብቁ እንዲሆን ግን አስቀድሞ በራሱ ፓርቲ ስር መደራጀት አለበት። ለዚህ መደብ ታሪካዊ ጥቅምና ፖለቲካዊ አላማ የሚቆመው የወዛደሩ መደብ ፓርቲ ብቻ ነው። ይህ ፓርቲ እስካልተፈጠረ ድረስ የኢትዮጵያ አብዮት አለኝታ የሆነው ወዛደር አርሶ አደር ትብብር ሊፈጠር አይችልም። ይህ ፓርቲ እስካልተፈጠረ ድረስ በወዛደር አርሶ አደር ህብረት ላይ የተመሠረተ ሌሎችም ተራማጅ ኃይሎች የሚጠቀልል በወዛደሩ ፖርቲ የሚመራ አብዮታዊ የአንድነት ግንባር ሊቋቋም አይችልም። እነዚህ ሁኔታዎች ሳይሞሉ ደግሞ በምንም ዓይነት ተአምር መደብ መሪነት ሊጨበጥ፣ ዲሞክራሲያዊቱ አብዮቱ ከግቡ ሊደርስ አይችልም።

ይህ የወዛደሩ ከፍተኛ ድርጅት እንዲፈጠር፣ የወዛደሩ መደብ አባሎች ተሳትፎና ከፍተኛ ተጋድሎ ያስፈልጋል። የወዝአደሩ ፓርቲ ጥቂት “ማርክሲስት ነን” ባዮች የሚያውጁት ድርጅት አይደለም። በወዝአደሩ ርዕዮተዓለም ላይ ተመርኩዞ በሚደረግ ሰፊ ቅስቀሳና ፕሮፓጋንዳ ወዛደሩ በራሱ ርእዮተአለም ሲታነፅ በንቁ ወዝአደሮችና ጊዜ ጉልበትና ሕይወታቸውን ለዚህ መደብ ባዋሉ ሀቀኛ አብዮታዊያን ትብብር የሚፈጠር ፓርቲ ነው። የወዛደር ፓርቲ የዚህ መደብ የነቁ አባሎች ያቀፈ እና በወዛደር ውስጥ መሰረት የጣለ ድርጅት ነው። ከዚህ በተለየ መንገድ ተፈጠርኩ የሚል “የወዛደር ፓርቲ” ነኝ ባይ ሁሉ በወዛደሩ ስም የሚነግዱ አወናባጆች ፓርቲ ነው።

የኢትዮጵያን ወዛደር ፓርቲ ለመፍጠር የሚደረገው ትግል በወዛደሩ ንቅናቄ ውስጥ ሰርገው የገቡና የንቅናቄውን አመራር ለመያዝ ከሚፍጨርጨሩ አዋናባጆች ጋር ከሚደረግ ትግል ተነጥሎ ሊታይ አይችልም። እነዚህ አዋናባጆች የወዝአደሩ ንቅናቄ ጠላቶች ለመሆናቸው ከድርጊቶቻቸው የበለጠ ምስክር የለም።

እውነተኛውን የወዛደር ፓርቲ ለመፍጠር የሚደረገውን ትግል ለማደናቀፍ ‘የወዛደር ፓርቲ’ ፈጥረናል በሚል በሬ ወለደ ውዥንብር ይነዛሉ። የእውነተኛ አብዮታውያንና የንቁ ወዘደሮችን ትብብር ለማፋለስ በስም ማጥፋትና በአሉባልታ ለመከፋፈል ይጥራሉ።

እንኳን በአድሃሪና በሰርጎገብ መሪነን ባዮች ተከቦ፣ የሙያ ማህበር ምንጊዜም ቢሆን የመንግሥት ስልጣን መጨበጥንና አመራር መስጠትን በሚመለከት የወዛደሩን ፓርቲ ተክቶ አያውቅም። ወዛደሩን የአብዮት መሪ ለማድረግና የመንግሥት ስልጣን ለማስጨበጥ የወዛደሩ ፓርቲ ተኪ የለሽ ነው። የወዛደሩ ፓርቲ አለመኖሩ ለሞያ ማህበሩ ይህን ሚና አያሰጠውም። እንዲያውም፣ ለወዛደሩ ፓርቲ መፈጠር አጣዳፊነት ትልቅ ምክንያት የሚሆነው ሞያ ማህበር በምንም ተአምር የፓርቲውን ሚና ሊወስድ ስለማይችል ነው። እነዚህ አዋናባጆች የወዝአደሩ መደብ ይህን ሳይንሳዊ ሃቅ ተረድቶ በአስቸኳይ የራሱን ፓርቲ ለመፍጠር እንዳይሰለፍ፣ በጊዜው የኢሰአማ አመራር ላይ በማወናበድና በሴራ የተገኘ ተፅዕኖ ስላላቸው ብቻ የወዛደሩን ፓርቲ ሚና ለዚህ ከአድሃሪዎች ላልጸዳ የሙያ ማህበር ሊያሰጡ ይጥራሉ። ወዛደሩ በዛሬው ትግሉና በዛሬው ንቃቱ እንዲወስን፣ ለታሪካዊ ግቡ ለሚያስፈልገው ከፍተኛ ትግል እና ንቃት እንዳይዘጋጅ ‘ነቅተሀል፣ በቅተሃል’ በሚል የእወደድ ባይነት ድለላ ትግሉን ሊያደናቅፉ የሞክራሉ። ዛሬ ከዘመናት መታፈንና አደንቋሪ ስብከት በኋላ ሳይንሳዊ ሶሻሊዝምን ለማስፋፋት ያልተጠበቀ አጋጣሚ ተፈጥሯል። ሀቀኛ አብዮታዊያን በዚህ ሁኔታ በመጠቀም በወዛደሩ ንቅናቄ ውስጥ ሳይንሳዊ ሶሻሊዝም ካስፋፉ ወዛደሩ መደብ በርዕዮተዓለሙ ይታጠቃል። ይህ ከሆነ ደግሞ አወናባጆቹ የሚነዙት ውዥንብር ይጠራል፣ በወዛደሩ ትግል ውስጥ ያላቸውም እድሜ ያጥራል። በዚሁ ስጋት ይህን ሁኔታ እንዲቀለበስ ከሚጥሩት መሳፍንትና ጳጳሳት ጋር ‘በሶሻሊዝም ስም ፋሺዝም አንፈልግም’ ብለው ተሰልፈዋል።  ‘አድርባይ ምሁራን፣ ፋሺስት መንግሥት’ የሚል የፈጠራ ጠላት ሰርተው የሰፊው ሕዝብ የትግል እሳት በዋነኛ ጠላቶቹ ላይ እንዳያተኩር ለመጋረድ ይሞክራሉ።

በሌኒን ቋንቋ ለመናገር፣ የወዛደሩ መደብ የማይበገር የፖለቲካ ኃይል የሚሆነው በራሱ ርእዮተዓለም ታንፆ በዚሁ ርእዮተዓለሙ ላይ በቆመ ድርጅቱ ስር ሲዋሃድ ብቻ ነው። ካለዚህ ድርጅቱም የመንግሥት ስልጣን መጨበጫ መሳሪያ የለውም። እነዚህ አወናባጆች ይህንን ሳይንሳዊ ህግ ሽረው፣ ወዛደሩ እነዚህ ርዕዮተአለማዊና ድርጅታዊ ዝግጅቶች ሳይደረጉ ስልጣን ለመያዝ እንደማይችል ተረድተው ‘ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት’ ይመረጥ በሚል አድሃሪ መፈክር ትግሉን ሊከፋፍሉና አጣዳፊ ተግባሮቹን ሊያዘናጉት ይጥራሉ። የኢትዮጵያ ወዛደር በሙያ ማህበር አማካኝነት ሊያካሂድ የሚችለውን ትግል ከከፍተኛ ደረጃ አድርሷል። ለወዛደሩ፣ ተከታዩ ትግል፣ በአስቸኳይ የወዛደሩ ፓርቲ ተፈጥሮ፣ በዚህ ፓርቲ መሪነት ዓላማውን ስልጣን መጨበጥና ራሱንና ጭቁኖችን ሁሉ ነፃ ማውጣት ወደ መታገል መሻገር ነው። እነዚህ አወናባጆች ሳይደረግ ‘ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት’ ይመረጥ የሚሉት የወዛደሩ ትግል እዚህ ደረጃ ሳይደርሱና እንዳይደርስ ቀድመውት ስልጣን ለመጨበጥ ነው።

እናጠቃል። የወዛደሩ  የዛሬ ትግል አጣዳፊ ጥያቄ  የወዛደሩን ፓርቲ የመፍጠር ጉዳይ ነው። ንቁ  ወዛደሮችና ሃቀኛ አብዮታውያን  ወዛደሩን በሳይንሳዊ ሶሻሊዝም ለማነፅ ከመቼውም ይበልጥ መታገል አለባቸው።  የወዛደሩ ፓርቲ መፈጠር የኢትዮጵያ አብዮት ወሳኝ ጥያቄ መሆኑን ማስረዳት አለባቸው። ለዚሁ ፓርቲ መፈጠር ለመታገል አንድነታቸውን ማጠናከር አለባቸው። ለዚሁ ግብም በኢሰአማ አመራር ዙሪያና አካባቢ የተገጠገጡትን አወናባጆች ማጋለጥና በወዛደሩ ንቅናቄ ውስጥ ቦታ ማሳጣት አለባቸው።

በዚህ ታሪካዊ ትግል ድልን ለመቀዳጀት ዋስትናው የወዛደሩ በሳይንሳዊ ሶሻሊዝም መታነፅ ከወዛደሩ ንቅናቄ፣ ከሀቀኛ አብዮታዊያንና ንቁ ወዛደሮች ትግል የሚወጣው የእውነተኛ የወዛደር ፓርቲ መፈጠር ነው።

እውነተኛውን የወዛደር ፓርቲ ለመፍጠር እንታገል
የሃቀኛ አብዮታዊያንና የንቁ ወዛደሮች አንድነት ይኑር
የወደዛሩ ዓለምአቀፋዊ ትግል ይኑር
የነቃ የተደራጀና የታጠቀ ሰፊው ሕዝብ ያሸንፋል
Scroll to Top