የሰፊው ሕዝብ ድምፅ
ቁጥር 59፣ ሐምሌ 4፣ 1969
የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ
ኢማሌድሕ ውስጥ የነበረው ልዩነት እየከረረ ሲመጣ የህብረቱ አባል ከነበሩት ውስጥ በተለይም አብዮታዊ ሰደድና የወዛደር ሊግ የተባሉት ድርጅቶች መኢሶን ላይ አሉባልታዎችና ሃሜቶችን ማሰራጨት ጀመሩ። በዚህ ጽሁፍ መኢሶን ዋና ዋናዎቹን አሉባልታዎች አንድ በአንድ እያነሳ ትክክለኛ፣ ተገቢና ገንቢ እንዳልነበሩ ያሳያል።
የአንድ ንቅናቄ አብዮታዊነት ሊለካ ከሚችልበት ነገሮች አንዱ ፀረ አብዮት ኃይሎች በዚያ ንቅናቄ ላይ ሊያደርሱ የሚሞክሩት ጥቃት ነው። የተለያዩ የአድሃሪዎችን መስመሮች እያጋለጠ፣ አወናባጅ መፈክሮችን ሁሉ ተራ በተራ እየተዋጋ፣ “ለነቃ፣ ለተደራጀና ለታጠቀ ሕዝባዊ ዓመፅ” ብሎ ለረጅሙና መራራው የነፃነት ተጋድሎ የተሰለፈው ድርጅታችን በዚህ በኩል ብዙ ጥቃቶች እንደደረሱበት ግልጽ ነው።
በተለይ ከአንድ አመት ወዲህ በየጊዜውና በየቦታው የመኢሶን አባላትና ደጋፊዎች ከሌሎች የአብዮትና የትግል ጓዶቻቸውን ጎን ለኢትዮጵያ ጭቁን ሕዝቦች ነፃነት የሚጠበቅባቸን የደምና የመስዋዕትነት አስተዋኦ እየከፈሉ አልፈዋል። ሌላው ቀርቶ በዚች በያዝናት ሳምንት እንኳን ብዙ የመኢሶን አባላትና ደጋፊዎች “የነቃ፣ የተደራጀና የታጠቀ የሕዝብ አመፅ ሸንፋል” የሚለውን አብዮታዊ ዓርማ አንግበው ከጠላት ኃይሎች በተተኮሱ ጥይቶች ሕይወታቸውን ለውድ እናት አገራቸው ሰውተዋል። ነገር ግን መኢሶን የሚደርስበት፣ መኢሶን የሕዝብ ወገንነቱን የሚያስመሰክርበት ጥቃት ይህ ብቻ አይደለም።
የግልገል ፋሽስቶቹ ቡድን እንደ ዛሬ ከሲአይኤና ከኢዲዩ ጋር ሆኖ ተራ ነፍሰ ገዳይ ቡድን ከመሆኑ በፊት መኢሶን የሚከተለውን የፖለቲካ መስመር የተሳሳተና ፀረ ሕዝብ መስመር ለማስመሰል ብዙ ትግል አካሂዶ እንደነበረ ይታወሳል። ነገር ግን በአብዮታዊውና በፀረ አብዮቱ መስመር መካከል በተካሄደው የርዕዮዓለም ትግል መኢሶንና ሌሎች አብዮታዊያን በአሸናፊነት ወጡ። ኢህአፓም ወደ ተራ ነፍሰ ገዳይነት፣ ወደ ነጭ ሽብር ተሰማራ። ነገር ግን ዛሬም ቢሆን ምንም እንኳን አብዮታዊያን ከቅጥር ነፍሰ ገዳዮች ጋር አስከፊ የሆነ ትግል በማካሄድ ላይ ቢሆኑም ፀረአብዮት ኃይሎች በፕሮፖጋንዳው መሰክ በመኢሶን ላይ የሚያካሄዱትን ዘመቻ አላቆሙም። እንዲያውም መኢሶን ከእለት ዕለት እየተጠናከረና በወዛደሮች፣ በአርሶአደሮች፣ በመለዮ ለባሾች፣ በወጣቶች፣ በጭቁን ብሔረሰቦች፣ በአገር ወዳዶች፣ በምሁራንና በጭቁን ሴቶች አካባቢ ተቀባይነትን እያገኘ በመሄዱ አድሃሪዎችን አስደንግጧቸዋል። በዚያው ልክ ደግሞ ውስጥ ውስጡንና በይፋ፣ በቀጥታና በተዘዋዋሪ በመኢሶን ላይ የሚሰነዘሩት አሉባልታ መጠን እየሳተ ሲሄድ እናየዋለን።
እነዚህን አሉባልታዎች በተለይ ዛሬ አገራችን በስንት ችግሮች ተውጣ እያየናት እዚህ ላይ ማንሳታችን ለነሱ ዋጋ ለመስጠት አይደለም። አሉባልታ፣ ሃሜት፣ በተገለፀ አቋም ላይ ሳይሆን ባልተባለ እና ባልተጻፈ ባልተነገረ ጉዳይ ላይ አንድን ንቅናቄ መተቸት የሚያሳየው ምንድነው? ቢያንስ ሁለት ነገሮችን ያሳያል። አንደኛ፣ አድሃሪዎችና አድርባዮች በአንድ ንቅናቄ ላይ አሉባልታ ሲያበዙ ያ ንቅናቄ በያዘው አብዮታዊ አቋም የተነሳ ለጠላቶቹ ከአሉባልታና ከፊውዳል ሀሜት ሌላ መፈናፈኛ ነስቷቸዋል ማለት ነው። ይህ ደግሞ ለዚያ ንቅናቄ በጣም ጥሩ ነገር ነው። ሁለተኛ ደግሞ፣ ሌኒን እንዳለው በአሉባልታ መጠቀም የፖለቲካ ክስረት አስተማማኝ ምልክት ነው። ይህም ለአብዮቱ በጣም ጥሩ ነው። ምክንያቱም በተለይ አድርባዮች በመኢሶን ላይ የሚሰነዝሯቸው አሉባልታዎች የሚያጋልጡት መኢሶንን ሳይሆን ራሳቸውን የከሠሩትን “አጋላጮች” እንደሆነ ግልጽ ነውና።
ነገር ግን ይህንን ስላልን አሉባልታዎች አደጋ የላቸውም ማለት አይደለም። ዝም ብለው ከተጠራቀሙ አድሃሪዎችና አድርባዮች የአብዮቱን ሰፈር ለመከፋፈል ለማጋጨትና ለማዳከም ሊጠቀሙባቸው ይችላሉ። እንዲያውም ዛሬ ሀገራችን በብዙ ችግሮች ተዋጥራ በእነዚህ ጉዳዮች ለመፃፍ መነሳታችን ዛሬ በመኢሶን ላይ የተጠራቀሙት አሉባልታዎች ከመግነናቸው የተነሳ ተራማጆችን ሊያጋጩና የአብየቱን ሰፈር ሊከፋፈሉ የሚችሉበት አደገኛ ደረጃ ላይ ደርሰዋል ብለን በማመናችን ነው። ስለሆነም የዚህ ጽሁፋችን አላማ በአድሃሪዎች የመከፋፈል ሴራ በተራማጆችና በሰፊው ሕዝብ ሰፈር የተነዛው አደገኛ ውዥንብር እንዲጠራና የአብዮቱ ሰፈር በዚያው ልክ ጥራትና ጥንካሬ አገኝቶ ቆራጥ ትግል ለማድረግ ነው። ለምሳሌ ያህል አድሃሪዎች ተራማጆችን ለመከፋፈል በመኢሶን ላይ ከነዟቸው አደገኛ አሉባልታዎቸ አንዳንዶቹን እንጥቀስ።
መኢሶን በጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት ላይ ከአድርባይነት የራቀ የአብዮታዊ ሂስ አቋም እንዳለው የታወቀ ነው። መኢሶን ከጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት ጋር ያሉት ልዩነቶች አሁንም በአብዮቱ ሰፈር ያሉ ልዩነቶች ናቸው ብሎ ያምናል። አድሃሪው ቢሮክራሲ ግን እነዚህን ልዩነቶች በማጉላት ተራማጆችን ይበልጥ ለመከፋፈልና ለማጋጨት ይሞክራል። አድሃሪው ቢሮክራሲ በየመጠጥ ቤቱና በየስርቻው ላይ የሚያስመራውን ትተን መኢሶንን ለማስመታት ባለፉት 15 ቀናት እንኳን የጠነሰሳቸውን ሁለት ሴራዎች እንመልከት።
ሰኔ 20 ቀን መኢሶን በት/ቤቶች ትምህርት እንዲቆም፣ በፋብሪካዎች ሥራ እንዲቆም አድማ እያስደረገ ነው በማለት ለመንግሥት “መረጃ” በማስተላለፍ በደርግና በመኢሶን መካከል ያለውን ልዩነት ለማባባስ ሞክሮ ነበር። ይህ ሲከሽፍ ደግሞ ሊቀመንበሩ ከሊቨርቪል ሲመለሱ መኢሶን በደርግ ላይ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ አስቧል ብሎ አሁንም መሰረተ ቢስ ወሬ በማቅረብ እንደዚሁ በደርግና በመኢሶን መካከል ያለውን ልዩነት በአሉባልታ ተጠቅሞ ለማስፋት ሞክሮ እንደነበር የታወቀ ነው።
ነገር ግን በእንደዚህ አይነቱ ዘዴ የሚጠቀመው የለየለት አድሃሪ ብቻ አይደለም። መሰረታዊ የኢትዮጵያ አብዮት ጥያቄዎች ላይ ትክክለኛ አቋም በይፋ መቃወም ተስኖት፣ በሌላ በኩል ደግሞ በእነዚህ አቋሞች የተነሳ መኢሶን ከእለት እለት ተቀባይነትን እያገኘ ሲሄድ እያየ ዝም ማለት ጨንቆት ውጭ ነፍስ ግቢ ነፍስ ላይ የሚገኝ አስመሳይ ተራማጅና አድርባይ ክፍልም አለ። ይህም ወገን ከፊውዳል አሉባልታ ሌላ መኢሶንን የሚዋጋበት ምንም ሌላ የረባ መሳሪያ የለውም። ስለዚህ እሱም እኩል ያሉባልታ ዘመቻ ያካሂዳል።
መኢሶን በኢትዮጵያ አብዮት መሰረታዊ ጥያቄዎች ላይ ግልጽ የሆኑ አቋሞች አሉት። እነዚህ አቋሞቹ የተጠናከሩትና ጥራት ያገኙት መኢሶን እንዲሁ በወረቀት ላይ አቋሜ ይህ ነው ብሎ ስላሰፈራቸው አይደለም። ተቀባይነትን ያገኙት ከተጨባጩ የኢትዮጵያ ሁኔታ አብዮቱን ወደፊት የሚያራምደው አቋሞች በመሆናቸውና መኢሶን እነዚህን ያመነባቸውን አቋሞች ከሥራ ላይ ለማዋል በጓዶቹ ደም እየከፈለ በሰፊው ሕዝብ ዘንድ ታጋይነቱን በማስመስከሩ ነው።
እነዚህ ግልጽ አቋሞች ምንድናቸው? ሌሎች “አገራችን ጦርነት ውስጥ ነችና በአሁኑ ጊዜ የዲሞክራሲ መብቶች አያስፈልግም” እያሉ የሰፊውን ሕዝባዊ ተሳትፎ “ከተያዘው ትግልና ጦርነት በድል አድራጊነት እንድንወጣ የዲሞክራሲ መብቶች ለጭቁኖች ያለ ገደብ መታወቅ አለባቸው” በማለት እምነቱ በሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብና በሰዉ ላይ ብቻ እንደሆነ እየደጋገመ ያስታውቃል። ሌሎች “ዲሞክራሲ ሊፈቀድ የሚችለው ዛሬ ሳይሆን በአንድ ባልታወቀ ታምረ-እግዚአብሄር የተራማጆች ህብረት ተጠናክሮ ወደ ውህደት ከተለወጠ በኋላ ነው” እያሉ የሃቀኛውን የትግል አንድነት ዘመን ሲያራዝሙ መኢሶን “የተራማጆች ህብረት እንዲጠናከር ዲሞክራሲ ለጭቁኖች ያለገደብ መታወጅ አለበት” በማለት ይታገላል። ሌሎች ኢምፔሪያሊዝምን በቅድሚያ እንዋጋ በማለት ከውስጥ ጠላቶቻችን በተለይ ደግሞ ከአድሃሪው ቢሮክራሲ በኩል የሚመጣውን አደጋ ችላ ሲሉት መኢሶን በአሁኑ ወቅት የውስጥና የውጭ ጠላቶች በምንም አይነት ሊነጣጠሉ የማይችሉ በአንድነት መመታት ያለባቸው ናቸው ብሎ ያምናል። ሌሎች የበሰበሰውንና አሁንም በረቀቀ ዘዴ ተደራጅቶ አብዮታችንን ለመቀልበስ ሌት ተቀን የሚያሴረውን ቢሮክራሲ “ለጊዜውም ቢሆን ልንጠቀምበት እንችላለን” ብለው አብዮቱ አንገት ላይ የተጠመጠመውን እባብ እሹሩሩ ሲሉ መኢሶን ሳይንሳዊ በሆነው የማርክስ ትምህርት በመመርኮዝ አድሃሪው ቢሮክራሲ መደምሰስ አለበት ብሎ ከሰፊው ሕዝብ ጎን ይታገላል። ሌሎች አብዮታውያን በየዕለቱ ከጎናችን እየተቀነጠሱ ሲረግፉ “ታጋይ ይሞታል እንጂ ትግል አይሞትም” በሚለው መፈክር እራሳቸውን አጉል ለማጽናናት ሲሞክሩ መኢሶን በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ “ታጋይ ሲሞት ትግል እንዳይሞት” የቢሮክራሲውን አሻጥር እንቋቋም፣ ያስጠቃን ወደ ተከላካይነት ማሸጋሸግ ነው፤ አብዮታችን በሰፊው ሕዝብ ነፃ እርምጃዎች አማካኝነት እንደገና ወደ አጥቂነት ይሸጋገር ይላል።
በዚህ መልክ ብዙ የመኢሶንን አቋሞች እየዘረዘሩ ማሳየት ይቻላል። በጠቅላላው በአሁኑ ጊዜ ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ በራሱ በመተማመን በነቃ፣ በተደራጀና በታጠቀ ሕዝብ አመጽ ጠላቶቹን ሁሉ ደምስሶ የታሪካዊት እናት ሀገሩን ብሄራዊ ክብርና ነጻነት ሳያስነካ አብዮቱን ከግቡ ለማድረስ በሚያደርገው ትግል ከጎኑ የቆመ ድርጅት ነው። ለዚህም የሚከተለውን ታክቲክ በየጊዜው በአንገብጋቢ ጥያቄዎች ላይ ሁሉ በይፋ አቋም እየወሰደ የሚታገል ድርጅት በመሆኑ ተራማጆችና ሰፊው ሕዝብ አቋሞቹን ያውቃሉ። አድሃሪዎችና አድርባዮች መኢሶንን በነዚህ መሰረታዊ አቋሞች ላይ ሊታመኑ አይችሉም። ስለሆነም እንደሁኔታውና እንደአካባቢው እያዩ የተለያዩ አሉባልታዎችን በመሰንዘር ድርጅታችንን ለማዳከምና ከሰፊው ሕዝብ ለመነጠል አጉል መፍጨርጨር ያደርጋሉ። ከነዚህ አሉባልታዎች አንዳንዶቹን ብንጠቅስ የሚከተሉትን እናገኛለን።
አሉባልታ ቁጥር 1፦ “መኢሶን የነፍጠኞችና የትምክህተኞች ድርጅት ነው።”
ሃሰት። መኢሶን ስሙ ራሱ እንደሚያመለክተው ከመላው ኢትዮጵያ አብዮታዊያን ብሄረሰብ፣ ጾታ፣ ሃይማኖት፣ ቋንቋ ሳይል አስተባብሮ ለመላ ኢትዮጵያ ጭቁኖች እኩልነት የሚታገል ማርክሳዊ ሌኒናዊ ድርጅት ነው። ዛሬ ሳይሆን ገና በጨለማው በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ጭቆን ብሄረሰቦች ይህ ነው የማይባል ግፍ እና በደል ይደርስባቸው በነበረበት ጊዜ “ብሄረሰቦች የገዛ እድላቸውን ለመወሰን ያላቸውን መብት እስከ መገንጠል” ያወቀ ድርጅት ነው። ይህንን በፕሮግራሙ ቁልጭ አድርጎ ጽፎ የሚያስቀመጥ ድርጅት “የትምክህተኞች” ድርጅት ነው ብሎ መለፈፍ ከአድሃሪያን ደደብነት የፈለቀ አላዋቂ አነጋገር ይመስላል። ግን አይደለም። እንደዚህ አይነቱ ክስ የሚነሳበትን አካባቢ ብንመለከት ይህ ክስ የሚነሳው በጠባብ ብሄረተኝነት የተመረዙ አድሃሪ ኃይሎች ባሉበት አካባቢ ነው። አላማውም “በትምክህተኛው” መኢሶን ሳቢያ ጭቁን ብሔረሰቦችን ጓዶችና በአብዮቱ ላይ ለማስነሳት እንደሆነ ግልጽ ነው።
አሉባልታ ቁጥር 2፡- “መኢሶን የጠባብ ብሄረተኞች ድርጅት ነው”
ሃሰት። አንባቢ ራሱ አንድ ድርጅት እንዴት “የትምክህተኞች” ድርጅት እየተባለ እዚያው በዚያው ደግሞ በጠባብ ብሄርተኝነት ይከሰሳል ይል ይሆናል። እዚህም ላይ የሚሞክረው እንዳአካባቢው እየታየ የአድሃሪ ኃይሎች ዘንድ ተቀባይነት የሚያገኝ ክስ ለመሰንዘር ነው። መኢሶን እንኳን ዛሬ የኢትዮጵያ ጭቁን ሕዝቦች ከዳር እስከ ዳር በአንድነት ከመደብ አንጻር እየተሰለፉ ይቅርና በመሳፍንቱ አገዛዝ ስር በብሄረሰቦች መካከል ከፍተኛ ጥርጣሬ፣ አለመግባባት እና ጥላቻ በነበረበት ወቅት ጠባብ ብሄርተኝነትን ተዋግቷል። ይህ ጥርጣሬና አለመግባባትም ተወግዶ በብሄረሰቦች መካከል እኩልነት፣ አንድነት፣ ፍቅርና ሰላም እንዲሰፍን እየታገለና አሁንም የሚታገል ድርጅት ነው። የብሄረሰቦችን መብት ሙሉ በሙሉ ካወቀላቸው በኋላ በዚያው ልክ ደግሞ በእኩልነት፥ በመፈቃቀር በመረዳዳት ላይ ለተመሠረተ አንድነት እንደሚታገል ይህንንም በፕሮግራሙ ቁልጭ አድርጎ አሳይቷል። ታድያ ይህም አሉባልታ እንደላኛው ሆን ተብሎ አካባቢንና ሁኔታን እየገመተ የሚወረወር አሉባልታ ነው። አድሃሪዎችና አድርባዮች “መኢሶን የጠባብ ብሄርተኞች ድርጅት ነው” እያሉ የሚያቶሰቱሱት አካባቢያቸውን ገምተው የትምክህተኞች አካባቢ ውስጥ እንዳሉ ሲረዱና እነዚህን አድሃሪዎች በንቅናቄዎች እና በአብዮቱ ላይ ለመቀስቀስ ሲያሴሩ ነው።
አሉባልታ ቁጥር 3፡- “መኢሶን በአሁኑ ሰዓት የኤርትራን መገንጠል ደግፋል።”
ሃሰት። በዛሬው የኢትዮጵያና የአካባቢ ሁኔታ ኤርትራን መገንጠል አይደገፍም። በኢትዮጵያ ያሉት ማርክሲስት-ሌኒኒስት ድርጅቶች በሙሉ እንደሚቀበሉት መኢሶንም በብሔረሰቦች ጥያቄ ላይ ሳይንሳዊ የሆነ አቋም አለው። በዚህ ጥያቄ ላይ የማርክሲዝም ሌኒኒዝም አቋም በመውሰድ እንደ ሌሎቹ ማርክሲስት- ሌኒኒስት ድርጅቶች ሁሉ የብሄረሰቦች ራስን እድል በራስ የሚወሰን መብት እስከመገንጠል ድረስ የሚጨምር መሆኑን ያምናል። ይህንንም በፕሮግራሙ አስፍሮታል። የማርክሲዝም ሌኒኒዝም ቲዎሪ እንደሚያስገነዝበን ማርክሲስቶች የመገንጠል መብትን ብቻ ሳይሆን ለብሄረሰቦችም አንድነት መታገል አለባቸው። እንዲያውም “የመገንጠልን መብት” እንዲታወቅ የሚታገሉት ብሄረሰቦች በሙሉ እኩል መሆናቸውን ለማረጋገጥ እና በእኩልነት ላይ የተመሰረተ አንድነት ለመገንባት እንደሆነ የማርክሲዝምን ሀሁ የቆጠረ፣ የብሔረሰቦችን ጥያቄ በሩቅ ያሸተተ ሁሉ የሚረዳው ጉዳይ ነው። እዚህ ላይ ለአሉባልተኞች በዚህ ጉዳይ ላይ ሌኒን “የመገንጠልን መብት ካወቅህ አገር መገንጠልህ ነው” ብለው ይከሱት ለነበሩ ሁሉ ይሰጥ የነበረውን ምሳሌ እንጥቀስ። ባልና ሚስት ሲጋቡም ማንኛውም ዲሞክራት ቢሆን፣ ማንኛውም በወንድና በሴት እኩልነት የሚያምን ግለሰብ ቢሆን “የመፋታት መብት” እንዲታወቅ ይታገላል። ይህ ማለት ግን ይህ ዲሞክራት ወይም ይህ ታጋይ በየደረሰበት ባልና ሚስት እንዲፋቱ የሚከራከር የትዳር ጠር ነው ማለት አይደለም። እንዲያውም ይህ መብት እንዲታወቅ የሚከራከረው ጋብቻ በፍቅር፣ በመግባባት፣ በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ጽኑ መሠረት እንዲኖረው በማሰብ ነው።
በኤርትራም ጉዳይ መኢሶን በዛሬይቱ የኢትዮጵያ እና የአካባቢው ሁኔታ መፍትሄው መገንጠል ሳይሆን የኢትዮጵያ ብሄረሰቦች ከብረት የተጠነረ አንድነት ብቻ ነው ብሎ ያምናል። ይህ አንድነት የሚገኘው በእኩልነት
ብቻ ነው። ለእኩልነት መታገል ማለት ደግሞ የብሄረሰቦችን መብት ሙሉ በሙሉ እንዲታወቅ መታገል ማለት ነው።
አሉባልታ ቁጥር 4:- “መኢሶን የሕዝብ ድርጅት ጉዳይ ጽ/ቤትን በሞኖፓል ይዟል”
ሃሰት። መኢሶን የሕዝብ ድርጅት ጉዳይ ጊዜያዊ ጽ/ቤት እንዲቋቋም፣ ከአባላቱም ውስጥ አንዳንዶቹ በዚህ ጊዜያዊ የትግል መስክ እንዲሰማሩ ከደርግ ተራማጆችና ከሌሎች አብዮታዊያን ጋር ተሰልፎ ታግሏል። በዚህ ፅ/ቤት አማካኝነትም ሰፊውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ለማንቃትና ለማደራጀት በተደረገው ትግል ብዙ የመኢሶን ጓዶች ተሳትፈዋል፣እየተሳተፉም ናቸው። ብዙ ጓዶቻችንም ተሰውተዋል፣ እየተሰዉም ናቸው። ነገር ግን በዚህ ጽ/ቤት ውስጥ መጀመሪያ ላይ ሌላው ቀርቶ የኢህአፓ አባላት እንኳን ነበሩበት። ሌሎች ጓዶችና ሌሎች ቡድኖችም አሉበት። እነሱም እንደዚሁ ታግለዋል፣ ተሰውተዋልም። ይህ ሀቅ እያለ የሕዝብ ድርጅት ጉዳይ ጽ/ቤት የመኢሶን ጊዜያዊ ጽ/ቤት ነው ማለት ለድርጅታችን ከሚገባው ድርሻ በላይ ስለሆነ አንቀበለውም። ሌሎችም ታጋዮች አሉ።
እርግጥ የመኢሶን አባላት በጽ/ቤቱ ተግባር በሰፊው ይሳተፋሉ። ይህ ደግሞ ጽ/ቤቱ የተቋቋሙበትን ሁኔታና አካባቢ ብንመለከት በምንም አይነት የሚደንቅ ነገር አይደለም። ፅ/ቤቱ በተቋቋመበት ወቅት ተደራጅተው ይሰሩና “ተራማጅ” ተብለው ይታወቁ የነበሩ ህቡዕ ድርጅቶች መኢሶንና ኢህአፓ ነበሩ። በዚያን ወቅት በነበረው ሁኔታ “ፋሽስቱ ደርግ” እያለ ኢህአፓ በሚነዛዉ ፕሮፓጋንዳ የተነሳ ብዙ ሀቀኛ አብዮታዊያን ተወናብደው እንደነበር ይታወሳል። ስለሆነም “የባንዳዎች ጉሮኖ የሆነው ጽ/ቤት” ውስጥ ገብቶ በይፋና በርዕዮተአለሙ መስክ “ገናናውን” አህአፓን ለመቋቋም ብዙም ታጋይ አልነበረም። በዚህ ሁኔታ በመስመሩ፣ በሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብና በደርግ ተራማጆች እምነት ኖሮት አባላቱን አጋልጦ ለህጋዊ ሥራ ለመስጠትና ለመሰዋት ፈቃደኛ ሆኖ የተገኘ ድርጅት መኢሶን ነበር። ለዚያውም የመኢሶን አባላት በጽ/ቤቱ ውስጥ የገቡት በግለሰብ ደረጃ እንጂ መኢሶን ከጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ጋር ተደራድሮ እንዳልሆነ ግልፅ ነው።
አሉባልታ ቁጥር 5፡- “መኢሶን ለደርግ ያደረ አድርባይ ድርጅት ነው”
ሃሰት። መኢሶን ለኢትዮጵያ ጭቁን ሕዝቦች አብዮት፣ ለውድ እናት ሃገራችን ብሔራዊ ክብርና ነፃነት የቆመ ድርጅት እንጂ ለማንም ያደረ ድርጅት አይደለም። መኢሶን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ የአብዮት ፕሮግራም ይዘቱ በትግል እየጠራና በነቃ፣ በተራጀና በታጠቀ ሕዝባዊ አመጽ ከስራ ላይ እንዲውል ከሌሎች አብዮታዊያንና ከሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን ተሰልፎ የሚታገል ድርጅት ነው። በዚህ ትግል በደርግ ውስጥ ሆነው በብዙ መስዋዕትነትና ፈተና አስቸጋሪ የሆነ ትግል እያካሄዱ የወዛደሩን ፓርቲ ለመመስረት ከሚታገሉ አብዮታዊ መለዮ ለባሾች ጋር እና “አብዮታዊት እናት አገር ወይም ሞት” ብለው ለዚች እናት ሀገራችን ክብርና ነፃነት ከተነሱ ዲሞክራቶችና አገር ወዳድ መኮንኖችና ባለ ሌላ ማዕረጎች ጋር እጅ ለእጅ ተያይዞ ወደፊት ይጓዛል። በደርግ ውስጥ አድሃሪዎችም አሉ። ከመላው ኢትዮጵያ አብዮታውያን ጋር አብሮ መሰለፍ ማለት በደርግ ውስጥ ካሉ አብዮታዊያን፣ዲሞክራቶችና አገር ወዳዶች ጋር መሰለፍ የሆነውን ያህል በመላ ኢትዮጵያ አድሃሪዎች ላይ መነሳት ማለት ደግሞ በደርግ ውስጥ ባሉት አድሃሪዎችም ላይ መነሳት ማለት ነው። በዚህ የተነሳ የመኢሶን አቋም የአድርባይነት ሳይሆን የአብዮታዊ ሂስ አቋም እንደሆነ ተደጋግሞ የተነገረ ነው።
አሉባልታ ቁጥር 6:- “መኢሶን ሥልጣን የጠማው ድርጅት ነው”
ሃሰት። መኢሶን ሰፊወ ሕዝብ በነቃ፣ በተደራጀና በታጠቀ ሕዝባዊ ትግሉ ፊውዳሊዝምን፣ ኢምፔሪያሊዝምንና ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝምን ደምስሶ ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ እንዲመሠረት የሚታገል አብዮታዊ ድርጅት ነው። ለዚህ ስልጣን ሰፊ ሕዝብ ብቁ የሚሆነው በወዛደሩ አማካኝነት ብቻ ነው ብሎ ያምናል። መኢሶን ደግሞ እንኳን አሁን ራሱን እንደወዛደር ፓርቲ ቆጥሮ ስልጣን ሊጠይቅ ይቅርና ከሌሎቹ ማርክሲስት-ሌኒኒስት ቡድኖች ጋር ሳይዋሃድ ፓርቲ ሊፈጠር እንደማይችል ደጋግሞ ገልጽዋል። መኢሶን ለስልጣን ቢስገበገብ ኖሮ ከሰፊው ሕዝብ ቀድሞ ስልጣን ለመያዝ የሚገፋፋው ርኩስ ህልም ቢኖረው “ጊዜያዊ ‘ሕዝባዊ’ መንግሥት” የሚለውን የስልጣንን ጥመኛ ንኡስ ከበርቴ መፈክር ለምን ተቃወመ? ይህንንስ መፈክር ሲታገሉና “ለነቃ፣ ለተደራጀና ለታጠቀ ሕዝብ ትግል” በሚለው መፈክር ስር ቆመው ብዙ ጓዶቻችን ለምን ተሰዉ? ለመሆኑ መኢሶንን ከነኢህአፓ ጋር ያጋጨውና የምድረ-አድሃሪ የጥላቻ ምሳር ማረፊያ እንዲሆን ያደረገው አቋም ምንድን ነውና?
አንድ ድርጅት እዚያው በዚያው “ለነቃ፣ ለተደራጀና ለታጠቀ የሕዝብ አመጽ” እየታገለና እየተሰዋ ስልጣን በአቋራጭ ይፈልጋል ብሎ ማውራት አንድም የዚህን መፈክር ይዘት ጨርሶ አለመረዳት፣ አልያም መፈክሮች የትግል መመሪያውና መሳሪያ ሳይሆኑ እንዲያው ለላንቲካ የሚወረወሩ የሚመስለው አስመሳይ መሆን አለበት እንላለን።
አሉባልታ ቁጥር 7:- “መኢሶን ዘመቻውን አይደግፍም”
ሃሰት። መኢሶን የንዑስ ከበርቴ “ፓስፊስት” ወይንም ሰላም አምላኪ ድርጅት አይደለም። በሕዝባዊ አብዮታዊ አመጽ ያምናል። ከዚህ አንጻር በሰሜን ኢትዮጵያም ሆነ በሌላው በማንኛውም የኢትዮጵያ ክፍለ ሃገር አድሃሪ ኃይሎችን ለመደምሰስ የኢትዮጵያን አብዮትና አንድነት ለመጠበቅ የሚደረገውን ተጋድሎ ይደግፋል። እንዲህ ካልሆነ “ለነቃ፣ ለተደራጀና ለታጠቀ የሕዝብ አመጽ” ብሎ ለምን ይታገላል? “ሰፊው ሕዝብ ይታጠቅስ” ብሎ ለምን ከሌሎች አብዮታዊያን ጎን አብሮ ይሰለፋል? እርግጥ ይህ ዘመቻ በአድሃሪው ቢሮክራሲ እንዳይመራ ይታገላል፣ አብዮታዊ አመራር ይኑረው ይላል። ቢሮክራሲው ይዘመትበት እንጂ አያዝምት ይላል። ይህ ደግሞ ዘመቻውን መቃወም ሳይሆን ይህ ዘመቻ ለኢትዮጵያ አብዮት ተገቢ የሆነውን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ የሚያስችሉትን ሁኔታዎች ያሟላ ብሎ መከራከር ነው። ዘመቻውን በእርግጥ መደገፍ ማለት እንዲያውም አንዱ መልኩ ይኸው ነው።
አሉባልታ ቁጥር 8:- “መኢሶን የጠባብ ቡድን ስሜት ያጠቃዋል።”
ሃሰት። ባለፈው ቁጥራችን እንዳልነው ጠባብ ቡድን ስሜት ማለት ድርጅቱን እንደ ዋና ግብ አድርጎ መውሰድ፣ ሌሎች ሊታገሉ የሚችሉ ኃይሎችን ማግለል፣…ወዘተ የመሳሰሉትን ያጠቃልላል። መኢሶን አብዮቱን እንጂ የራሱን መደራጀት እንደግብ አድርጎ አይወስደውም። እንዲያውም በራሱ ፕሮግራም ውስጥ ከሌሎች ጋር ተዋህዶ የወዛደሩን ፓርቲ የመመስረት አላማ እንዳለው ገልጿል። በቅርቡ ከሌሎች ማርክሲስት-ሌኒኒስት ድርጅቶች ጋር ህብረት ፈጥሮ ወደ ውህደት ለመሸጋገር እየታገለ ነው። አብዮቱን እንጂ የራሱን ማደግ እንደ ዋና ግብ አድርጎ ስለማይወስድ ለአብዮቱ ለመታገልና ለመሞት ቆርጠው ከተነሱት በስተቀር አድርባዮችና አወናባጆች ድርጅቱ ውስጥ ሠርገው እንዳይገቡበት ከፍተኛ ጥንቃቄን ያደርጋል። ይህም ደግሞ “ከብዛት ጥራት ይሻላል” የሚለውን የማርክሲዝም መርህ በመከተል እንጂ “ቡድኑን በራሱ ለመጠበቅ” ብሎ የሚከተለው ፖለቲካ አይደለም።
መኢሶን የቡድን ስሜትን አጥብቆ ይቃወማል። ነገር ግን ደግሞ አባላትና ደጋፊዎቹ ሊታገሉለትና ሊሞቱለት የተሰናዱትን፣ ብዙ ጓዶቹን የሰዋለትን የፖለቲካ መስመር ለማስፋፋት ወገን ለይቶ ይታገላል። ይህንን ወገናዊነት /ፓርቲዛንሺፕ/ “የጠባብ ቡድን ስሜት ብሎ መክሰስ አንድም የራሱ የሆነ ወገን ለይቶ በይፋ የሚከራከርለት መስመር የሌለው አድርባይ፣ አሊያም በያዛት መስመሩ እምነት የማይሰማውን ሰው አስተሳሰብ ያመለክታል። ሁለቱም ቢሆኑ ትክክለኛ የፖለቲካ መስመር እንዳይስፋፋ፣ በዚህ ፈንታ የሚያዝ የሚለቀቅ ጫፍ የሌለው ውዥንብር እንዲሰፍን የሚያግዝ ፀረ ድርጅትና ፀረ አብዮት አቋም ነው። እንዲህ አይነቱ አቋም ፀረ ድርጅት አስተሳሰብ በተለይ ለአቋም መታገልን፣ ወረቀት መበተንን፣ በህቡእ መደራጀትን፣ ወዘተ. “ኢህአፓ እንደመሆን” እያስመሰለ ስለሚያስወራ በአሁኑ ጊዜ ሰፊው ሕዝብ መደራጀትን ጥቅም አስፈላጊነት እንዳይረዳ የሚያወናብድ ፀረ ድርጅት አነጋገር ነው። እንዲህ አይነቱ አቋም ላይ “አሉባልታ” በማስፋፋት አንድን ቡድን አሳጥቶ ራስን ለማራመድ መሞከር ሲታከልበት ደንበኛ የቡድን ስሜት የሚመጣው ያኔ ነው።
አሉባልታ ቁጥር 9፡- “መኢሶን ሌላው ኢህአፓ ነው።”
ሃሰት። የመኢሶን ፕሮግራም አብዮታዊ ነው። የኢሕአፓ ፕሮግራም ቀልባሽ ነው። የመኢሶን መፈክሮች አብዮታዊ ናቸው። የኢህአፓ መፈክሮች ቀልባሾች ናቸው። መኢሶን ሰፊው ሕዝብ ያቀፈው፣ አድሃሪዎች አይንህን ላፈር ያሉት ድርጅት ነው። ኢህአፓ ሰፊው ሕዝብ አንቅሮ የተፋው፣ አድሃሪዎች ያቀፉት ድርጅት ነው። ይህንን በመረዳት ኢህአፓ፣ ኢዲዩ፣ ኢኤልኤፍና ሌሎች አድሃሪ ኃይሎች በሙሉ በአሁኑ ጊዜ አብዮታዊ ድርጅታችንን በማጉላት ፀረ አብዮት አመጻቸውን እያወረዱበት ነው።
ኢሕአፓና መኢሶን ገና በአጼ ኃይለሥላሴ ዘመን መስመር ለይተው የተቋቋሙ ድርጅቶች ናቸው። ልዩነቶቻቸውም እየጎሉ ሄደው ዛሬ አንዱ በአብዮት ሰፈር፣ ሌላው በፀረ አብዮት ሰፈር እንዲቆሙ አድርጓቸዋል። መኢሶን ኢህአፓን ገና ሰፊው ሕዝብ ጉያ ውስጥ ሆኖ ሲያወናብድ አጋልጦ ርቃኑን ያስቀረው ድርጅት ነው። በዚህም ትግሉ በብዙ ጓዶች ደም የጻፈው ድልን ተቀዳጅቷል። ዛሬ መኢሶን ሌላው ኢህአፓ ነው ብሎ መክሰስ በሰማዓታት ጓዶቻችን ፊት አድሀሪ ኃይሎችን ሁሉ ለመደምሰስ የገባውን ቃል ኪዳን እንዳልነበረ አድርጎ መቁጠር ነው እንላለን። በዚህ ትግል ውስጥ የወደቁብንን ጓድ ወዛደሮች፣ የአርሶአደሮች፣ የመለዮለባሾች፣ የወጣቶች፣ የቀበሌ ተመራጮች፣ የታጋይ ሴቶችና የሌሎች አብዮታዊያንን ደም እንደ ውሃ ቆጥረን ከደመኞቻችን ጋር ተዋህደናል ማለት ነው። መኢሶን እንዲህ ዐይነቱን ክህደት በምንም ዓይነት አይፈፅመውም። በሰፊው ሕዝብ የገባነውን ቃል ለመፈፀም ለነቃ፣ ለተደራጀና ለታጠቀ የሕዝብ አመጽ ብሎ ወደፊት ይጓዛል እንጂ ሰፊውን ሕዝብ ከድቶ ምንጊዜም ሌላው ኢህአፓ እንደማይሆን ማንም አሉባለልተኛ አድርባይ ሊገነዘው የሚገባው ሀቅ ነው።
አሉባልታ ቁጥር 10፡- “መኢሶን ራሱን ለማስተዋወቅ ይሞክራል።”
ደግ አረገ። እንኳን ድርጅት ነኝ ብሎ ይቅርና በግለሰብ ደረጃ ያለ ታጋይ ቢሆን የትግል ስልቱን ለማሳመን፣ አላማውን እና ግቡን ለማብራራት፣ ሌሎች ደጋፊዎችን ለዚህ አላማ ለማሰለፍ ሌት ተቀን መታገል አለበት። ይህን ማድረግን እንደወንጀል የሚቆጥር ሁሉ ከሁለት ፀረ አብዮት ጠንቆች አንዱ ተጠናውቶታል ማለት ይቻላል። ወይ የሚተማመንበት ከሰፊው ሕዝብ ፊት አብራርቶና አንጠርጥሮ ተናግሮ የያሳምንበት ዓላማና ፕሮግራም የሌለው፣ ግን በሌላው አቋም ተራማጅ ተብሎ ለማለፍ የሚፈልግ አድርባይ መሆን አለበት። ወይ ደግሞ እንከን የለሽ ፕሮግራምና ዓላማ ኖሮት ያንን ያለ ሰፊው ሕዝብ ተሳትፎ ጥቂት “የሚስጥሩ ተካፋዮች” ጋር ሆኜ አላማዬን እመታለሁ የሚል በሐሳብ ብቻ የሚዋዥቅ ሀሳባዊ /አይዲያሊስት/ መሆን አለበት። የፊተኛው በራሱ እምነት የለውም። የኋለኛው በሰፊው ሕዝብ እምነት የለውም። ሁለቱም ለአብዮቱ አይረቡም። መኢሶን ግን በራሱም ሆነ በሰፊው ሕዝብ ይተማመናል። ትክክለኛ ዓላማ አለኝ ብሎ ያምናል። ግን ደግሞ ይህ አላማ ሺህ ጊዜ ትክክለኛ ቢሆን በሚሊዮን የሚቆጠረው ሰፊ ሕዝብ አምኖበት ካልተከተለውና ካልተዋጋለት ከሥራ ላይ እንደማይል ያውቃል። በማርክስ አነጋገር ትክክለኛ ሀሳቦች ወደ ተጨባጭ እና የማይበገር ኃይል የሚለወጡት በሚሊዮን በሚቆጠረው ሕዝቦች አዕምሮ ሲታነጹ ብቻ ነውና።
ስለሆነም ግቡን፣ ፕሮግራሙን፣ የትግል ስልቱን፣ ወዘተ…. በአጭሩ ራሱን ለማስተዋወቅ ይታገላል። ይህ ደግሞ በሰፊው ሕዝብና በራሱ እምነት እንዳለው የሚያሳይበት አብዮታዊ ድርጊቱ ነው።