የሰፊው ሕዝብ ድምፅ
ቁጥር 21፣ ጥር 21፣ 1967
የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ
መኢሶን በዚህ የሰፊው ሕዝብ ድምፅ እትሙ፣ “የኢትዮጵያ ሶሻሊዝም” በወታደራዊ ደርግ ከታወጀ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ፤ በአንድ በኩል፤ ጥቂት ባንኮችንና የኢንሹራንስ ኩባንያዎችን የመንግሥት ንብረት አድርጎ መውረሱን ይጠቅሳል። በተጨማሪም፣ ወታደራዊ መንግሥት ሕዝብን ለማገልገል መቆሙንና፤ የሕዝብን በደልና ጭቆናም እየጠቀሰ በመንግሥት ዜና ማሰራጫዎች ያስታውቃል። በአንጻሩ ደግሞ፣ በሚናገረውና በተግባር ከሚገለጸው የመንግሥት ባህሪ ላይ ጉልህ ልዩነቶች እንደሚታዩ ይገልጻል። ለምሳሌም፣ የአርሶ አደሩ ዋና ጥያቄ የሆነው፣ ‘የመሬት ላራሹ’ በሕግ ይታወጃል ከተባለ ወራት እንዳለፉ ይጠቅሳል። እንዲያውም፣ በአንዳንድ የገጠር አካባቢ በመጠኑ የተደራጁ አራሾችና ጭሰኞች እየተገናኙ ስለመሬት ይዞታ ጉዳይ መወያየታቸውን፣ ወታደራዊ መንግሥት ሲከለክል ይታያል።
ደርጉ የኢትዮጵያ ሶሻሊዝም ብሎ የጠራውን መመሪያ ካስታወቀ ይኸው ወር ሆነው። አንዳንድ የዚህን መመሪያ መንፈስ የተከተሉ እርምጃዎች በመውሰድ የሶስት ባንኮችና የጥቂት ኢንሹራንስ ኩባንያዎችን ባለቤትነት ወደ መንግሥት ካዛወረም ሰነበተ። የሰፊውንም ሕዝብ ብዝበዛ በደልና ጭቆና፣ የሰፊውን ሕዝብ በመሳፍንትና በኢምፒሪያሊዝም መረገጥና መቦጨቅ በፕሮፓጋንዳ መሣሪያዎቹ ሲገልፅ ቆይቷል። ወታደራዊው መንግሥት ለሰፊው ሕዝብ የቆመ፣ ሰፊውን ሕዝብ ለማገልገል የተነሳ፣ ለሕዝቡ መብቱን ሊመልስ የቆረጠ መሆኑ በመደጋገም ተገልጿል። የእስልምና ሐይማኖት ተከታዮች መብት በከፊል መመለሱ፣ ከተጨቆኑት ብሔሮች አንዱ የሆነው የኦሮሞ ብሔር ቋንቋ በመጠኑ ማእረግ ማግኘቱ ይህንን የመብት መመለስ መንገድ የጀመርን መሆኑን ያሳምን ይሆናል።
በሌላ በኩል ደግሞ በሚነገረውና በሚደረገው መካከል ከፍ ያለ ልዩነት ይታያል። በመጀመሪያ መታየት ያለበትን የመሬቱን ጉዳይ የወሰድን እንደሁ በቅርቡ ህግ ይወጣል ከተባለ ወራት በወራት ተተክተው ሲሄዱ ህጉ አለመውጣቱን እናያለን። ህጉ እንኳን ቢዘገይ ለህጉ መሰናዶ ሊሆን የሚገባው የጭሰኛውና የአነስተኛ ገበሬ የመደራጀት መብት እስካሁን ተነፍጎ ይታያል። በመጠኑም ቢሆን ከዚህ በፊት ተደራጅተው የነበሩ የአንዳንድ አውራጃ ጭሰኛና አነስተኛ ገበሬዎች እየተገናኙ በችግራቸው ላይ እንዳይወያዩና ለችግራቸውም መፍትሄ እንዳይፈልጉ በደርግ ተወካዮች ታግደዋል።መሬት ላራሹ ብላችሁ ተናግራችሁ፡ ባለርስቱን አስቀየማችሁ በመባል ከየካቲት ጀምሮ በጸረሕዝቡ በእንዳልካቸው መንግሥትና ከመስከረምም ወዲህ በተቋቋመው ወታደራዊ መንግሥት የታሰሩት ጭሰኞችና ተማሪዎች አሁንም በየእስር ቤቱ ይማቅቃሉ።
ከፍተኛ ባለርስቶች፣ ባላባቶች፣ ሕዝቡን የሚያወናብዱ ገፈፊ ቃልቻዎችና ባለዛሮች አንዳንድ የቤተክርስቲያንና የመስጊድ መሪዎች እንደልባቸው ቅሚያቸውን ሲቀጥሉ ይታያሉ። ጭሰኛውና ድሀው ገበሬ መሬት መሬት እያለ ሲጮህ እነኝህ አወናባጆች መሳሪያ እያከማቹ፤ አሽከር እየቀጠሩ ለጦርነትና ለሽፍትነት ሲዘጋጁ ይታያሉ። ባላባትነታቸውንና የሃይማኖት መሪነታቸውን እያስታከኩ ሕዝቡን ለመከፋፈል በየአደባባዩ በየገበያው ሲሰብኩና ሲያሰብኩ ውስጥ ውስጡን ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጠላቶች ከአልጋወራሽ አስፋወሰን፣ ከዘውዴ ገብረላሴ፣ አገራቸውን ከከዱት የአፄ አምባሳደሮች ጋር፣ ከተራማጆች ጠላት ከአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና ከቡችሎቹ ከነሳውዲው ፋይሳል ጋር ሲላላኩ ይታያሉ። በቸልተኝነት ያመለጡት እነመንገሻ ስዩም፣ እነነጋ ተገኝ በቤጌምድርና ሰሜን፣ በትግራይ በወሎ፣ በጎጃም በሸዋ ከሚገኙት መሰል ወገኖቻቸው የሕዝብ ተባዮች ጋር አሁንም በመዶለት ላይ ይገኛሉ። ሕዝባዊውን ንቅናቄ ለማክሸፍ የማይሞክሩት ሴራ የለም። ቢትወደድ አሌሚራህም ረሃብ የጨረሰውን ያደቀቀውን የአፋርን ሕዝብ አሁንም ለመበዝበዝ እንዲያመቸው ከመንገሻ ስዩምና ከሳውዲ አረቢያ ጋር በመላላክ ለመሸፈት ይዘጋጃል። በላቸው ጀማነህም ከነዚህ አድሃሪ ወገኖችና ከኢምፔሪያሊስቶች ጋር በመመሳጠር የአሁኑን መንግሥት ገልብጦ የኢምፔሪያሊስት ጥገኛ መንግሥት ለማቋቋም ልዩ ልዩ የዝግጅት ሴራዎችን ከመጠንሰስ አልተቆጠበም። እነኝህና ሌሎችም የሕዝብ ጠላቶች ቀደም ብለው እንዲያዙ ከመወትወት ባንቆጠብም እስካሁን ድረስ ምንም አይነት እርምጃ አልተወሰደባቸውም። እንዲያውም አንዳንዶቹ ክብርና ሞገስ አልተነፈጋቸውም። እንደ ጅማው ባለባት ይህንን ያህል ጋሻ ለድርቅ ሰጠን እያሉ የሚያፌዙም አሉ። በጠቅላላው መሬትን ላራሹ ልሰጥ ነው ከሚል መንግሥት የማይጠበቅ ተባዮችን የማባበል፡ እንደልባቸው የመልቀቅ፡ እንዲረቡ እንዲሰቡና ሕዝቡን ለመውጋት እንዲዘጋጁ ፋታ የመስጠት ሁኔታ በሰፊው ይታያል።
ስለገበሬው ካነሳን ዘንዳ ሌላ የሚያስገርም ድርጊት በንግድ ሚኒስቴርና በአንዳንድ የደርጉ ተወካዮች ተዘጋጅቶ የታወጀው የዋጋ ቁጥጥር ጉዳይ ነው። የዋጋ ቁጥጥር የሰፊው ሕዝብ ወገን ነኝ በሚል መንግሥት ሲታወጅ ሰፊውን ሕዝብ /ጭሰኛውንና ትናንሽ ገበሬውን፣ ላብአደሩን፣ ዝቅተኛ የቢሮ ሰራተኛውን፣ አስተማሪውን፣ ተማሪውን፣ አነስተኛ ነጋዴውንና ወታደሩን/ የሚጠቅም መሆን ነበረበት። ነገር ግን የዋጋ ቁጥጥር ተብሎ የተገለጸው ዋጋ ከብት አርቢውን፣ ከብት ቀላቢውን፣ አራሹን ገበሬ፣ አነስኛውን ነጋዴ ወዘተ. የሚጎዳ ሆኗል። ለምሳሌ የስንዴ ዋጋ ከመወሰኑ በሸዋ በአሩሲ ነጋዴው ከገበሬው ኩንታሉን ስንዴ በአስራ ስድስትና በአስራ ሰባት ብር ገዝቶ በአዲስ አበባ ገበያ ላይ በሃያ ሶስትና በሃያ አራት ብር ይሸጥ ነበር። አዲሱ የዋጋ ውሳኔ ከወጣ ወዲህ ግን ያንኑ እህል ነጋዴው ከገበሬው ላይ በአስራ ሁለትና በአስራ ሶስት ብር ይገዛል። ብዙ ጋሻ መሬት በዘመናዊ ዘዴ አርሶ ብዙ ሺህ ኩንታል አምርቶ የሚሸጠው ሃብታም ገበሬ /የገጠር ዲታ/ እህሉን በጅምላ ለትልልቅ ወፍጮ ቤቶች ስለሚሸጥና ከመሰለውም እህሉን በመጋዘኑ አስቀምጦ ደህና ዋጋ ስለሚጠብቅ ምንም ያህል አይጎዳም። አነስተኛው ገበሬ ግን ዋጋ ተጨመረም ተቀነሰ ከላይ እስከታች ከተረበረቡበት ነጋዴዎች ገፈፋ ስለማይድንና የአሁኑም ዋጋ ቅናሽ ሙሉ በሙሉ በቀጥታ በእርሱ ትከሻ ላይ ስላረፈ ክፉኛ ተጎድቷል፣ ቀን ወጣልህ እየተባለ ከስሯል።
ሌሎቹም የግብርና ምርት ዋጋቸው ይኸው ናቸው። የሚጠቅሙት የከተማውን ደመወዝተኛና ከበርቴ ክፍል ብቻ ነው። እንዲያውም ይህ ውሳኔ ሰፊውን ሕዝብ በገጠሬና በከተሜ ይከፋፍለዋል። የዋጋው መወሰን የሰፊውን ሕዝብ ጥቅም መጠበቅ ነበረበት። የከተሜው ቀለብ እንዳይጓደል መንግሥት አስቀድሞ ንግዱን በቁጥጥሩ ስር ማግባት ነበረበት። የድሮው አገዛዝ ሕዝብን ለመጨቆን ያዘጋጃቸው እንደእህል ቦርድና እህል ማህበር የመሳሰሉ ድርጅቶች ለሕዝቡ እንዲሰሩ መደረግ ነበረባቸው። ይህ ሳይሆን ቀርቷል። ለሰፊው ሕዝብ ህልውና በጣም አስፈላጊ በሆኑት በምግብ በልብስ ወዘተ. ላይ የዋጋ ውሳኔና ቁጥጥር መደረጉ በመሰረቱ ትክክል ነው። ዋጋ በሚወሰንበት ግዜ ግን አዲሱ ዋጋ የገበሬውንም ሆነ የላብአደሩን ጉልበት እንዳያራክስበት፣ ሰፊውን ሕዝብ ወደባሰ ችግር እንዳይከትተው ሰፊ ጥናትና ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። ለምሳሌ አሁን እንደተደረገው የእህል ዋጋ ተቀንሶ የስንዴ ዱቄትና የዳቦ ዋጋ ሳይነካ መቅረቱ የጠቀመው ባለትልልቅ ወፍጮ ቤቶችንና ዳቦ ጋጋሪዎችን ነው።
የዋጋ ቁጥጥር ዋና አላማው አፈር ገፊው አነስተኛ ገበሬ እንዳይጎዳ፣ እንዲሁም ዝቅተኛ ገቢ ያለው ከተሜ እንዳይጎዳ፣ ነጋዴዎች ከገበሬው የሚገዙበት ዋጋ ዝቅ በማድረግና ለተጠቃሚው የሚሸጡበትን ዋጋ በጣም ከፍ በማድረግ ከልክ በላይ የሆነ ትርፍ እየዛቁ ሰፊውን ሕዝብ እንዳይበዘብዙ ለማድረግ ነው። በመሠረቱ ነጋዴዎችም ትርፋቸው ከልክ በላይ እንዳይሆን ማድረግ ነው እንጂ ኢትዮጵያውያን ነጋዴዎች እስከሆኑና መጠነኛ ንግድ ውስጥ እስከተሰማሩ ድረስ የንግድ ስራ ለመቀጠል የሚያበቃቸው መጠነኛ ትርፍ ማግኘት እንደሚገባቸው ማወቅ ያስፈልጋል።
በተጨማሪም የዋጋ ቁጥጥር ያለበቂ ጥናት በአንድ ጊዜ በሁሉም እቃ ላይ ሊደረግ አይችልም። ምክንያቱም የዋጋ ጉዳይ ከረቂቅ የኢኮኖሚ አሰራር ህግጋት ጋር የተያያዘ በመሆኑ ነው። እያንዳንዱን እቃ ዋጋ ለመቆጣጠርና በተለይም ዝቅ ለማድረግ የሚቻለው በጠቅላላው የእቃውን እጥረት ለማስወገድ ሲቻል ነው። በአንድ ጊዜም በችኮላ ሊከናወን አይችልም።
እነዚህን ጉዳዮች በሙሉ ባለመገንዘብ አሁን እንደተደረገው የኢኮኖሚን አሰራር ህግጋት የማይከተል የእቃዎች ዋጋ መታወጅ በከተማው የእቃ እጥረትን በመፍጠር ለሕዝቡ ችግርን ለመንግሥቱም ጥላቻን ያተርፋል። ይህንን በመመልከት ነው የሰሞኑን የዋጋ ቁጥጥር መሰረት ምን እንደሆነ የምንጠይቀው። ያም ሆነ ይህ ቁጥጥሩ በኢኮኖሚው ጥናት ላይ ያልተመሰረተ፣ ከእርሻም ሆነ ከገበያ ጋር ግንኙነት ያላቸው ድርጅቶች ያልመከሩበት፣ ምስኪኑ አፈርገፊ ገበሬ ይጠቅመው እንደሁ፣ ይጎዳው እንደሁ፣ ያልተጠየቀበት ምናልባትም ያው መንግሥቱ ወዳጅና ጠላትን ባለመለየት በሚመርጣቸው አድሃራዊ አማካሪዎችን እርሱኑ መልሰው ለማጥላላት ያቀዱት የአድማው ድርጊት ይመስላል።
ሌላው የገጠሩ አጣዳፊ ችግር የድርቁ መስፋፋት መሆኑ ገልፅ ነው። ይህን መቋቋም ለሀገሪቱ ዋና ጥያቄ ነው፣ የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ ነው። ታዲያ በዚህም አቅጣጫ ቢሆን የሚታየው ብዙ ፕሮፖጋንዳና ትንሽ ስራ፡ ትንሽ ውጤት ነው። የመቋቋሚያው ስራ ችላ ተብሏል፣ ተዘንግቷል። እርዳታ ሰጪዎቹም ሆኑ የእርዳታ ሰብሳቢው ድርጅት አድሃሪ እንደመሆናቸው መጠን እርዳታውን እንደ ምጽዋት ስለሚቆጥሩት ሕዝቡ ራሱን በራሱ እንዲያድን ምንም ሙከራ አላደረጉም። ይህን ቀደም ብለን በዚሁ ጋዜጣ በሰፊው አብራርተናልና አንመለስበትም።
በሌላውስ በኩል ቢሆን የሕዝቡን ጥቅም ለመጠበቅ ምን ጥረት ተደርጓል ብንል ያንኑ በሚነግረውና በሚሰራው መካከል ያለውን ከፍ ያለ ልዩነት እናያለን። ተራማጆች በእስር ቤት ይማቅቃሉ። እነሻለቃ ተፈራ ተክለአብ፡እነዶክተር እሸቱ ጮሌ፣ እነኮሎኔል እምሩ ወንዴ፡ እነአቶ ዘውዴ በዳዳና ሌሎችም የሰፊው ሕዝብ ወገኖች ለሰፊው ሕዝብ ተቆርቋሪነታቸው በግልጽ እየታወቀ በእስር ቤት ውስጥ ሲማቅቁ የኃይለሥላሴ መንግሥት ከፍተኛ ባለስልጣኖችና የመሳፍንት ወገኖች ‘በርእሰብሄሩ ምህረት ተደርጎላቸው’ ተለቅቀዋል። የኢ.ዩ.ተ.ማ መሪዎች ተይዘው መያዛቸው እንኳን አልተገለጠም። አባሎቻቸውን ወክለው የተነሱት የኢሰማ መሪዎች ክሳቸው እንኳን አልተነገራቸውም። አስራሦስት የገንዘብ ሚኒስቴር ሰራተኞች ክሳቸው አሁንም በቀጠሮ ተራዝሟል።
ስለ ሕዝብ በተነሱ ወገኖቻችን ላይ ይህን በደል ማድረሱ ምን ይባላል? በሌላ በኩል ደግሞ ሰራተኛው እንዲደራጅ፡ እንዲሰበሰብ፡ እንዲመካከር መብቱ አልተጠበቀለትም። በአንድ በኩል ሶሻሊዝም እየተባለ እየተለፈፈ በሌላ በኩል የአሜሪካ የስለላ ድርጅት /ሲ.አይ.ኤ/ የኢሠአማን መሪዎች ለመግዛት ገንዘቡን ያፈሳል። አማካሪ አሰልጣኝ እያለ የሚልካቸው ሰላዮቹ ሴሚናር ያዘጋጃሉ። ስለሶሻሊዝም፣ ስለሠራተኛ መብት ጥቅም፣ ስለትግሉ አመራር ተራማጆች እንዳያስተምሩ፣ እንዳያደራጁ ተከልክለው ተይዘዋል። የቀንደኛው ሰላይ የበላቸው ጀማነህ ቱልቱላዎች እረፉ፣ እጅ እግራችሁን አጣምራችሁ የምንለፍፍላቸሁን ብቻ አዳምጡ ይሉናል።
ቀደም ብሎ በተያዘው መስመር በመቀጠል ደርግ ተዋናይ፣ ሕዝብ ተመልካች ስለሆነ ትእይንቱን ሲከታተል ሕዝብ እንዲያጨበጭብ ይጠየቃል። ለውጥ ከላይ ወደታች ከአስተዳደሪ ወደ ሕዝብ ይመጣል። አርፋችሁ ተቀመጡ፡ የመሬት ህግ ይታወጃል እያሉ የደርግ ተወካዮች በየገጠሩ ያስረዳሉ። የእድገት በህብረት ዘማቾች ለሕዝቡ የፖለቲካ ትምህርት እንዳይሰጡ ለራሳቸውም ቢሆን ምንም አይነት ገለፃ ሳይደረግላቸው ቀርቷል። መንግስቱ የሚጨነቀው ከአድሃዎች ማለት ሬዲዮ ጣቢያዎች/ ጀርመን ሬዲዮ፣ ቢቢሲ፣ የአሜሪካ ድምጽ፣ወዘተ./ ከፊውዳል ጨቋኞች ለሚወረወረው ሂስ ነው።
ይህ ሁሉ እንዴት ሊሆን ቻለ? ከዚህ በፊት እንደገለጽነው በደርጉ ውስጥና በደርጉ አካባቢ አድሃሪ ኃይሎች የሕዝቡን እንቅስቃሴ ለማክሸፍና ወደ ኋላ ለመመለስ የማያደርጉት ሙከራ የማያጠምዱት ሴራ የለም። በቀንደኛው ሰላይ በበላቸው ጀማነህ መሪነት፣ በመሃረነ ምንዳ፣ በደምሴ ተፈራ፣ በሽመልስ አዱኛና በተካልኝ ገዳሙ፣ በአንዳንድ የፖሊስ ንኡስ ደርግ አባሎች ውስጥ በተለይ በሻለቃ እንየው አዝማችነት የማወናበድ ስራቸውን ቀጥለዋል። በአድራጎታቸው የሲአይኤ የገንዘብና የምክር ድጋፍ እንዳለና ከደርጉም ውስጥ የነዚህ ሰዎች የሴራ ባልንጀሮች እንዳሉበት ግልጽ ነው። የሚከተሉት እስትራቴጅም እንደሚከተለው ነው። ለአዲሱ አስተዳደር ቁልፍ የሆኑት ቦታዎች፡ የክፍለሃገሩን አስተዳደር፣ የአውራጃውንና የወረዳውን አስተዳደር፣ በሰዎቻቸው ይሞላሉ። በአፋቸው የለውጡ ደጋፊዎች በመምሰል በመንግሥት የተያዙትን ፋብሪካዎች፣ እርሻና የንግድ ድርጅቶች፣ ‘በተማሩ ወጣቶች’ አስያዝን እያሉ አድሃሪነታቸው የታወቀውን ሰዎች በእነዚህ ስፍራዎች ይተክላሉ። ለምሳሌ አዲሱን የብሔራዊ ኃብት ልማት ሚኒስቴር በሚኒስትርነት፣ በቋሚ ተጠሪነት፣ በመምሪያ ኃላፊነት ያስያዙት ከጥቂቶች በስተቀር /ለአይን ያህል/ በአድሃሪዎች ነው። እንዲያውም በድሮ መንግሥት እንኳን በሌብነት የተገለሉትን እንደነ ዶክተር ጥላሁን ኣይነቶቹን ከፍ ያለ ስልጣን ሰጥተዋቸዋል።
ወጣትነትና መማር ለተራማጅነት የምስክር ወረቀት ያለመሆኑን ሲታወቅ የዲግሪ ጋጋታ በመቁጠር የዋህ የሆነውን አንዳንድ ሀገርወዳድ ሊያታልሉ ይሞክራሉ። ሁለተኛው ዘዴያቸው በሚኒስቴሮች ምክር ቤትና በደርጉም ውስጥ ጭምር ባሏቸው ቡችሎች አማካኝነት የተዘጋጀው የመሬት ይዞታ ህግ እንዳይፀድቅ፣ ከፀደቀም ስራ ላይ መዋሉ እንዲዘገይ ይጥራሉ። ጥቃቅን ነጥቦችን አጣመው በመተርጎም እንዳልካቸው በሾማቸው ስራ በማይችሉ ሚኒስትሮች እየተረዱ መኣት ሊወርድ ነው፣ የለውጥ አላማችን ሊጨናገፍ ነው፣ የኤርትራ ችግር ሳይፈታ አይሆንም፣ ጎሳ ለጎሳ ወገን ለወገን ሊዋጋ ነው እያሉ ከዋናው ጉዳይ ጋር ራቅ ያለ ግንኙነት ያላቸው ጉዳዮችን በመቀስቀስ ይህንን ህግ ለማቆየት ይጥራሉ። በተለይ የሚያተኩሩት ስለድርጅት በሚነሳው ጉዳይ ላይ ነው። ገበሬው ከተደራጀ፡ ተደራጅቶም ከላብአደሩ ጋር ከተባበረ፤ ከተራማጅ ኃይሎችም ጋር ከገጠመ የአድሃሪዎች መጥፊያ ቀን መቃረቡን ስለሚያውቁ የድርጅትን መፈቀድ በተጭበረበረ የፀጥታ ሪፖርት ላይ እያስመረኮዙ አደገኛ ነው፣ ሕዝቡ ቀድሞ ይማር፣ ጠላቶቻችን ተጠናክረዋል እያሉ በደርጉ ውስጥና በአካባቢው ያሉትን የተራማጅ ወገኖች ያወናብዳሉ።
ሦስተኛው ዘዴያቸው የሳቦታጅ ዘዴ ነው። ከላይ እንደጠቀስነው ‘የኢትዮጵያ ትቅደም ዓላማ’ ተቃውሟል እያሉ የገጠርና የከተማውን ተራማጅ ያሳስራሉ። ይህም የሚደረገው በደርጉና በሕዝቡ መካከል መቃቃር እንዲፈጠር ነው። በብዙ ክፍለ ሀገሮች እንደተደረገው መሬት ላራሹ የሚሉትን ተራማጆች ማስፈራራት በደርጉ አባሎችና በንኡስ ደርጎች እንዲስፋፋ ያደርጋሉ።
አራተኛው ዘዴያቸው ከተራማጆች ቀድመው ይበልጥ ለውጥ የሚፈልጉ በመምሰል ያልተጠና የችኮላ እርምጃ እንዲወሰድ ያደርጋሉ። ከላይ እንዳስረዳነው የዋጋው ቁጥጥር ጨዋታ ይህን የሚመስል ነው። እንዲሁም በቅድሚያ መወሰድ ያለባቸው እርምጃዎች ሳይወሰዱ ለመንግሥት ለጊዜው ብዙ ጥቅም የማይሰጡ የማያዋጡ የንብረት መውረስ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ይገፋፋሉ። በንግድ ዓለም የጊዜው ዋና ጠላቶች የኢምፔሪያለዝም ቅጥያ የሆኑ አቀባባይ ነጋዴዎች ሲሆኑ መንግስቱ በአነስተኛ ከበርቴዎች ላይ እንዲያተኩር ይገፋፋሉ ትልቁን ትቶ ትንሹን፣ አደገኛውን ትቶ ደካማውን፣ ጠላቱን ትቶ ወዳጁን እንዲያጠቃኝ ይመክራሉ፣ ያዛሉ ይወስናሉ። ሰሜን ከደቡብ፡ እስላም ከክርስቲያን፣ ብሄር ከብሄር እንዲጋጭ ይጥራሉ። በፖሊስ፣ በብሄራዊ ጦርና በአንዳንድ የጦር ኃይሎች ክፍሎች ውስጥ ወሬ በማሰራጨት የሚያስቆጣ ድርጊት በመፈፀም ደርጉን ወደፋሺዝም ይገፋፋሉ።
እንግዲህ ከዚህ ሁሉ የምንረዳው አድሃሪ ኃይሎች በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም መሪነት፣ በበላቸው ጀማነህና በግብረአበሮቹ ግንባርቀደምነት፣ በደርጉ ውስጥና በአካባቢው ባሉ ባለስልጣኖች ደጀንነት በሕዝብ ንቅናቄ ላይ መዝመታቸውን ነው። በደርጉ ውስጥ ያሉ ተራማጆችና በጠቅላላውም የሕዝብ ወገን የሆኑ አገርወዳዶች መገንዘብ ያለባቸው ከዚህ በፊት ደጋግመን እንደተናገርነው ትግሉ ከግፈኛው ንጉስ መያዝ ወይንም በጥቂት አምባገነን መኳንንት መገደልና በንብረታቸው መወረስ የሚቆም ያለመሆኑን ነው። መዘንጋት የሌለባቸው ትግሉ የሚቀጥልና የሚፋፋም መሆኑን፣ በሰባት ወይንም መቶ የጦር ኃይል አባሎች ብቻ ሊካሄድ የሚችል ያለመሆኑን፣ ንቅናቄውን ሰፊው ሕዝብ ራሱ መምራት እንዳለበትና ንቅናቄውም ከዳር የሚደርሰው ትክክለኛ ያልተዘበራረቀ መሪነት ሲያገኝ መሆኑን ነው። በአድሃሪ ኃይሎች በኢምፔሪያሊስቶች እርዳታ በውጭና በውስጥ ይደራጃሉ። የብሄሮችም ጥያቄ በተለይ የኤርትራ ጉዳይ የኤርትራን መብት በሚገባ ታውቆ ከፍጹም እኩልነትና ከወንድማማችነት አንጻር ሕዝቡ ራሱ በሚፈቅደው መንገድ ሊፈታ ሲገባ ልዩ ልዩ ሰንካላና አድሃሪ ሃሳብ በማቅረብ ሰላማዊ መፍትሄ እንዳያገኝ ይጥራሉ። መንግስቱ ውስጥ ገብተው ተንሰራፍተው በመቀመጥ የመንግስቱን የቢሮከራሲ መኪና ለተንኮላቸው ያውላሉ።
በዚህን ጊዜ በደርጉም ውስጥ ሆነ በውጭ የሚገኙ ተራማጆች ምን ማድረግ አለባቸው? በመጀመሪያ የንቅናቄውን ወዳጆችና ጠላቶች መለየት አለባቸው። የንቅናቄውን ወዳጆች- ለረጂም ጊዜ ኢምፔሪያሊዝምንና ባላባታዊ አገዛዝን ሲቋቋሙ የቆዩትን ተራማጆች- ማስጠጋት መሰብሰብና እንዲደራጁ መፍቀድ አለባቸው፣ ለሰፊው ሕዝብ የመደራጀት መብቱን መፍቀድና የፖለቲካ ህሊናውን ከፍ እንዲያደርግ ማበረታታት አለባቸው። አድሃሪዎች ከስልጣንም ሆነ ከምክር ቦታ አካባቢ ያለማመንታት መነቀል አለባቸው። እነዚህንም በአገርወዳድነት፡ በተራማጅነት፡ በስራ ችሎታ ብቻ በተመረጡ ሰራተኞች መተካት አለባቸው። የታሰሩ ተራማጆች እንዲፈቱ መወትወት አንዱ የነኚህ በደርግ ውስጥና ውጭ ያሉ ተራማጆች ተቀዳሚ ተግባር ነው። የነርሱ መፈታትም በተራማጆች መካከል ሊፈጠር የሚችለውን የመደጋገፍ ሁኔታ ሊያበስር እንደሚችል ማስረዳት የሁላችንም ተግባር ነው። የመሬቱ ህግ ያለማገጃ፡ ያለማድበስበሻና መንፈሱን የሚሽር ለውጥ ሳይደረግበት በስራ ላይ የሚውል አይነት ሆኖ እንዲታወጅ መግፋት ሌላው የተራማጆች ግዴታ ነው። በተለይ በደርጉ ውስጥ የሚገኙ ተራማጆች ወዳጅና ጠላታቸው ማወቅና ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል። ከአድሃሪ ኃይሎች ጋር ትከሻ ለትከሻ እየተሻሹ መቀጠል እንደማያዋጣቸው ተረድተው ከእነርሱ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ማቋረጥና ከተራማጆች ጋር ለመተባበር መጣር ያስፈልጋል። ተራማጆችም ደጋግመው በጠየቁት መሰረት የታሰሩትን ተራማጆች መፍታት፣ የሰፊውን ሕዝብ መደራጀት መፍቀድና ማበረታታት፣ ከሌሎች አገሮች ታሪክም መማር ያኖርባቸዋል። የነብርን ጅራት አይዙም ከያዙም አይለቁም እንደሚባለው አድሃሪዎችን ነካክቶ ሳያጠፉ መቀመጥ እንደማይቻል ይረዱ። ከወዳጆቻቸው ከተባበሩ ድል ያደርጋሉ፣ ከጠላቶቻችው ጋር ከሰነበቱ ይጠፋሉ።