ሰሕድ ቁ. 33

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ቁጥር 33፣    ታህሣሥ 6፣ 1968

የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ

መኢሶን በዚህ የሰፊው ሕዝብ ድምፅ እትሙ፣ ከየካቲቱ ሕዝባዊ አብዮት ወዲህ የተገለጠው ሁኔታ፣ ባንድ በኩል፣ የዓጼ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ከተገመተው በላይ የበሰበሰ እንደነበር እና በሌላ በኩል ደግሞ፣ የሕዝቡ ፖለቲካዊ ንቃተ-ህሊና እና ድርጅታዊ ብቃት ያልተሟላ እንደሆነ ነው። በዚህም ሁኔታ፣ በተወሰነው የንዑስ ከበርቴ ሃይሎች ተቃውሞ፣ በመንግሥት በራሱ ወታደሮችና ፖሊሶች ግፊት፣ የዓጼ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ፍርክስክሱ እንደወጣ ያትታል ። ሕዝቡ መንግሥታዊ ሥልጣንን ለመጨበጥ የሚያስችል ፖለቲካዊ ንቃት ስላልነበረው፣ ስልጣንን መያዝ አልቻለም ወደሚል ማጠቃለያ ይደርሳል።   

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ለሰፊው ሕዝብ ሰራተኛ ገበሬ፣ ነጋዴ፣ ወታደር፣ ምሁር መብትና ጥቅም የሚታገል ጋዜጣ

የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ይቅደም

ቁጥር 33                                                                        ቀን 6/4/68

​​​​

የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ዋና ቅራኔ

የየካቲት 1966 የኢትዮጵያ ሕዝቦች ሰፊ ሪቮሉሽናዊ እንቅስቃሴና ከዚህም ወዲህ የተፈጠረው ሁኔታ ሁሉ በማያሻማ አኳኋን ያረጋገጠው አንድ ነገር አለ። ይኸውም፣ የኃይለሥላሴ ፊውዶ-ፋሽስት መንግሥት ማንም ሊገምተው ከቻለው በላይ የበሰበሰ እንደ ነበርና፣ በዚያውም መጠን ደግሞ፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የፖለቲካ ንቃት፣ የድርጅት ስፋት፣ በጠቅላላ አነጋገርም ህሊናዊው ሁኔታ ገና ያልተሟላ እንደ ነበር ነው። ከብስብስነቱም የተነሳ፣ ያልተደራጀው የንኡስ ከበርቴው ልዩ ልዩ ክፍል፡ ሠራተኛውና ገበሬው በድንገት ሲነሳበት፣ የቀድሞ የጭቆናው መሳሪያ የነበረው ሰራዊቱና ፖሊሱ ሳይቀር በርሱው ላይ ዞሮበት ገፍተር ሲያደርገው ፍርክስክሱ ወጣ። የኢትዮጵያ ሕዝብ የፖለቲካ ንቃት በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ስለነበር ደግሞ፣ ይህ ሰፊ ሕዝብ ተደራጅቶና እንደአንድ ሰው ሆኖ ተነስቶ፣ የመንግሥትን ስልጣን ነጥቆ ሊወስድ አልቻለም።

ከሥርዓቱ ብስብስነት የተነሳ፣ የገዥ መደቦች የህብረተሰብ መመርኮዣ የነበሩት የገጠሩ ዝቅተኛ ጉልተኛ መደብ፣ አቀባባይና የቢሮ ከበርቴው፣ ኢምፔሪያሊዝምም እራሱ ቢሆን፣ ወዲያውኑ ተያይዘው ተነስተው የኃይለሥላሴን መንግሥት ከውድቀት ሊያድኑት አልቻሉም። እነዚህ ማንሰራራት የጀመሩት አሁን በቅርቡ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ያገሪትዋ ጠቅላላ ህሊናዊ ሁኔታ የቆረቆዘ ስለ ነበርም፣ ጭቁን መደቦችና የህብረተሰብ ክፍሎችም ወዲያውኑ ተደራጅተውና ተያይዘው፣ ፊውዳሊዝምንና ኢምፔሪያሊዝምን በተቀናበረ ትግል ለመደምሰስ ሊነሱ አልቻሉም። እነዚህም በመጠኑ መደራጀት የጀመሩት አሁን በቅርቡ ነው።

የኃይለሥላሴ መንግሥት በኢትዮጵያ ሕዝቦች ላይ የፈፀመው አንዱ ትልቅ ወንጀል አገሪትዋን በድንቁርና ጨለማ ውስጥ አፍኖ ማቆየቱ ነበር። ሕዝቡ በምንም አይነት ስለዓለም ሕዝቦች ትግልና ግስጋሴ እንዳያውቅ፣ እንዳይማር፣ እንዳይደራጅና በሪቮሉሽናዊ አስተሳሰብ ነቅቶ እንዳይነሳበት ያልፈፀመው በደል የለም።

በኢትዮጵያ ውስጥ የተደራጀና የነቃ መልክ የነበረው እንቅስቃሴ ቢኖር የኤርትራው ትግልና የተማሪው ያገር ውስጥና የውጭ አገር እንቅስቃሴ ነበር። የነዚህም ኃይሎች ሪሾሉሽናዊ ንቃት እራሱ ውሱን እንደ ነበር ዛሬ በግልጽ ይታያል። የኤርትራ ተዋጊዎች ከአሥራአራት ዓመታት በላይ የመሳሪያ ትግል ቢያደርጉም፣ የኤርትራን ሰፊ ሕዝብ ትግል አቀናብሮ የሚመራ፣ ኢንተርናሽናሊስት አቋም ያለው ሪሾሎሽናዊ የወዝአደር ፖርቲ ለመፍጠር ይኸው እስከዛሬ አልቻሉም። ከነዚያ ሁሉ የትልቅ መስዋእትነትና የተጋድሎ ዓመታት በኋላ፣ ዛሬ ገና በ1968 የኤርትራ ተዋጊዎች የግራ ክንፎች ‘አንድ ሪቮሉሽናዊ ፖርቲ’ አስፈላጊ መሆኑን ማሳየት ጀምረዋል። የተማሪውም የውስጥና የውጭ እንቅስቃሴ ብዙ መስዋእትነትን ካደረገ በኋላ፣ ዛሬ በጠቅላላው ሲታይ በትልቅ ውዥንብር ውስጥ ወድቋል። ደግሞም አሁን በኢትዮጵያ ብቅ ብቅ ያሉት የግራ ቡድኖች ከተማሪው እንቅስቃሴ የመነጩ ስለሆነ ውዥንብሩንም ብዙዎች የወረሱት ይመስላል።

በኢትዮጵያ መቼውንም ቢሆን ግልጽ የሆነ የፖለቲካ ትግል ልምድ አልነበረም። በቀድሞው ሥርዓት፣ ጠቅላላው የግራ ወይንም ሪቮሉሽናዊ እንቅስቃሴ ከዳር እስከ ዳር ይዘምት የነበረው በፊውዳሊዝምና በኢምፔሪያሊዝም ላይ ነበር። ያኔ ዋነኞቹን ጠላቶች መለየት ምንም ያህል አስቸጋሪ ነገር አልነበረም። በየካቲት እንቅስቃሴ ሳቢያ ፊውዳሊዝም ቢያንስ በመንግሥት ስልጣን ደረጃ ከተገረሰሰ ወዲያና ኢምፔሪያሊዝምም ቢያንስ በቃላት ደረጃ መደፈር ከጀመረ ወዲያ፣ ያገሪርዋ የኃይሎች አሰላለፍ በሌላ መልክ ቀርቧል። ስለዚህም ወዳጅንና ጠላትን እንደቀድሞው በቀላሉ ለመለየት የማይቻልበት ሁኔታ አለ።ይህንን ሁኔታ በደንብ ሊያጣራ ይችል የነበረው የሙሉ ዲሞክራሲያዊ መብት መኖር ነበር። ግን ከደርጉ ፀረዲሞክራሲያዊነት የተነሳ፣ በትግል፡ በግልጽ የፖለቲካ ክርክር ማን ከማን ጋር እንደተሰለፈ ለማሳየት አልተቻለም። ይህም ለውዥንብር ነዥዎችና ለአድሃሪዎች አመች ሆነ።

 ማንኛውም ሪቮሉሽናዊ እንቅስቃሴ ሊያድግና ግቡን ሊመታ የሚችለው ከታወቁትና ከለየላቸው አድሀሪዎች ጋር በሚደረገው ተጋድሎ ብቻ ሳይሆን፣ በሪቮሉሽኑ ደጋፊነት ቀርበው ነገር ግን የሬቮሉሽኑ አደናቃፊ የሆኑትን፣ በግራው ወገን ውስጥ ያሉትንና ሰርገው የሚገቡትን የቀኝና ‘የግራ’ አድርባዩችንም ጭምር በሰፊው ሕዝብ ፊት ለማጋለጥ ሲችል ነው።

አንዳንድ ተራማጆች የዚህ አይነቱን ዲሞክራሲያዊ ክርክር ይፈሩታል፤ የግራውን ኃይል፣ ተራማጁን የህብረተሰብ ክፍል ይከፋፍላል ይላሉ። እነዚህን ተራማጆች የምንመክራቸው የሪቮሉሽኖችን ታሪክ እንዲያስታውሱና በዚሁ በአዲስ አበባ ውስጥም በመካሄድ ላይ ያሉትን አንዳንድ የቀበሌ የወጣቶች ማህበራት ስብሰባዎችን ሄደው እንዲጐበኙ ነው። ሃቀኛ ክርክር ለትግላችን የግድ አስፈላጊ ነው። ሃቀኛ ክርክር ብዙ ትምህርት ይሰጣል፣ የተሳሳቱትን መስመሮች ያጋልጣል፣ መስመርን ያጠራል። ያለፖለቲካ ትግል የፖለቲካ መስመር ጥራት አይገኝም። እንደዚህ አይነቱን ትግል እዉነተኛ አብዩታውያን አይፈሩትም። ዴሞክራሳዊ ትግል ለአብዮታውያን ዋና መሳሪያቸው ነው። እውነተኛ አብዮታዊያን ዲሞክራሲያዊ ክርክርን በስም ማጥፋት፣ ባሉባልታና በሌላ ሌላ የፊውዳል ኢንትሪግ ሊተኩት አይሹም። ዴሞክራሳዊ ክርክር አድሃሪዎችን፣ ግራመሰል አወናባጆችና ውዥንብር ነዥዎችን ለብቻ ነጥሎ ያወጣቸዋል፤ ጠቅላላውን እንቅስቃሴም አጠናክሮ ያወጣዋል። ይህንን ዴሞክራሲያዊ አረማመድ የማይወዱ የጠቅላለውን እንቅስቃሴ መጠናከር የማይወዱ፣ የሰፊውን ሕዝብ የተጠናከረ ኃይል የሚፈሩ ፀረሕዝብ- ክፍሎች አለያም ሪሾሉሽናዊ ድልን ከሪሾሎሽናዊ ትግል ነጥለው የሚያዩ የዋህ ተራማጆች ናቸው።

ለዚህ አይነቱ የፖለቲካ መስመር ማጣሪያ ትግል ጊዜው አሁን ደርሷል። ስለዚህም በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ ግራ ውስጥ የልዩነት ነጥብ የሆኑ አንዳንድ ነገሮችን እዚህ ላይ ለማንሳት እንፈልጋለን። የኢትዮጵያ የጊዜው ሪቮልሽናዊ እንቅስቃሴ ወዳጆችና ጠላቶች የትኞቹ መደቦችና ኃይሎች ናቸው? በሀገራችን ሁኔታ ዛሬ የአንደኛ ደረጃ እና የሁለተኛ ደረጃ ቅራኔዎች የትኞቹ ናቸው? የደርጉ የመደብ ባህሪ ምንድነው? የመንግሥትን ሥልጣን በሰፊው ሕዝብ እንዴት አድርጎ ይይዛል?

እነዚህንና መሰል ጥያቄዎችን የሰፊው ሕዝብ ድምፅ ዴሞክራሲያም ደግመው አንስተዋል። ከፍ ብለው በተነሱት ጥያቄዎች ላይ ትንተና ስናቀርብ የምንጠቀመው በተለይ ባለፉት ሁለት የዴሞክራሲያ ቁጥሮች በ22 እና በ23 ነው። እዚህ ላይ ለማሳየት የምንፈልገው ይህ ጋዜጣ ያለውን ውዥንብር፣ ፀረሪቮልሺናዊ አስተያየትና የፖለቲካ መስመር ነው። በዚህ መስመር ብዙ ሀቀኛ ተራማጆች ተወናብደዋል። አሁን እንግዲ መንቃት አለባቸው እንላለን።

የጋዜጣው ቁጥር 23 “ፌውዳሎች፣ኢምፒሪያሊስቶች እና ፋሺስቶች አንድም ሦስትም ናቸው” በሚል፣ እራሱ አወናባጅና አደናቋሪ በሆነው “የሥላሴዎች ሚስጢር” በተመሰለ አርስት ስር ሰፋ ያለ “ትንተና” አቅርቧል። የዚህ መፃህፍ ጠቅላላ ይዘት ፊውዳሎች- እነመገሻ ስዩም፣ ነጋ ተገኝ፣ አሊ ሚራህ፣ ወ.ዘ.ተ የአሜሪካን ኢምፒሪያሊዝምና” ፋሺስቶች” ማለትም የደርጉ “ምርጥ መኮንኖች” የተያያዙ ስለሆኑ፣ ሦስቱንም ጠላቶች የኢትዮጵያ ሕዝብ ባንድነት መዋጋት አለበት የሚል ነው። ይህንን ቁጥር ያነበበ ማንም ሃቀኛ ሪሾሎሸናዊ ስለ ዴሞክራሲያ ሰዎች ሊስተው የማይችል አንድ እውነት ይኖረዋል። ሰዎቹ ወይ አውቀው ለማወናበድ ታጥቀው የተነሱ ናቸው፣ ወይንም የጊዜውን ሁኔታ፣ ያገሪትዋን የመደቦች አሰላለፍ፣ የህብረተሰቡን ቅራኔዎች አዝማሚያ፣ ከዚህም የተነሳ የኢትዮጵያ ግራ መከተል ያለበትን መስመር ፈጽሞ አልተረዱም ማለት ነው።

ይህ የጋዜጣቸው ቁጥር በሁለተኛ ገፁ ላይ የአብዮቱን ወዳጆችና ጠላቶች በመደብና በህብረተሰብ ክፍል በሞላ ጎደል ደህና አድርጎ ይደረድራል። በተለይ የአብዮቱ ጠላቶች “ጉልተኞች፣ የተለያዩ ከበርቴዎች…ዓለምአቀፍ ኢምፔሪያሊዝም”፣ የአብዮቱ ባለቤትና ወዳጆች ደግሞ ከዘጠና በመቶው በላይ የኢትዮጵያን ሕዝብ የሚያጠቃልል መሆኑን ከገለፀ በኃላ፣ የሚከተለውን ያሰፍራል፡-

 “ዋናው ቅራኔና ትግል የሚገኘው በነዚህ ሁለት ቡድኖች መካከል ሲሆን ​አብዩቱ ወደፊት በሚጓዝበት ወቅት ተፈጥሮ ባጭር ጊዜ ውስጥ የጐላው ​አዲስ ቅራኔ በሰፊው ሕዝብና በምርጥ መኰንኖች መንግሥት መካከል ያለው ነው።. . .”  (ስርዝ የተጨመረ)

ከዚያም፣ ዲሞክራሲያ ከቀድሞውም እንዴት “ሳይንሳዊ” ትንተናን ሲያቀርብ እንደ ነበር እራሱን ያወድስና ጽሁፍ፡- 

“ፋሽቶች ከፊውዳሊዝምና ከኢምፔሪያሊዝም ጋር በተለያዩ መንገዶች  የተሳሰሩ፣ በጠላትነትም ደረጃ ይበልጥ ጐልተው ወይም ኮስሰው ሳይሆን ባንድነት መታየት ያለባቸው መሆኑን አያሌ ጊዜ ጠቅሷል” ይላል።

“ባጭር ጊዜ ውስጥ የጐላው አዲስ ቅራኔ” ምን ማለት ነው? “በጠላትነትም ደረጃ ይበልጥ ጐልተው ወይም ኮስሰው ሳይሆን ባንድነት መታየት አለባቸው” ማለትስ? ይህ የመጨረሻው አረፍተ ነገር፣ ፊውዳሊስቶችም፡ ኢምፔሪያሊዝምም፡ “ፋሺስቶችም” እኩል ጠላቶች ናቸው ማለት ከሆነ በመጀመሪያው ጥቅስ “ዋናው ቅራኔና ትግል” በፊውዳሊዝም-ኢምፔሪያሊዝምና በሰፊው ሕዝብ መካከል ነው የሚለውን እንደሚቃረን ግልጽ ነው። ደግሞም፣ “የጎላው አዲስ ቅራኔ የሚለው፣ ምንም ያሀል ትርጉሙ ያልተጣራ የቃላት ውርወራ፣ በሰፊው ሕዝብና በደርጉ መካከል ያለው ቅራኔ ዋናው፣ የመጀመሪያው ደረጃ ቅራኔ ይሆናል ማለት አይደለም ወይ? ይህ ከሆነ ደግሞ ባንድ ህብረተሰብ ውስጥ ባንድ በተሰጠ ጊዜ ሁለት ዋና ቅራኔዎች ሊኖሩ ይችላሉ ለማለት ተስቦ ይሆን? 

ይህ ሁሉ የተምታታ አቀራረብ መቼስ የነዚህን ተራማጆች የትንተና ድህነት ከማጋለጡ በስተቀር፣ ባንድ በኩል በፊውዳሊዝም- ኢምፔሪያሊዝምና በሰፊው ሕዝብ መካከል፣ በሌላው በኩል ደግሞ በሰፊው ሕዝብና በደርጉ መካከል ያሉት ቅራኔዎች ምን አይነት ባህሪዮች እንዳሏቸው ቅንጣት ያህል ለአንባቢ አያስረዳም። እንዲያውም አንባቢው የሚይዝ የሚለቅቀውን እንዲያጣው የሚያደርግ የተምታታ አነጋገር ነው።

ከላይ እንደተጠቀሰውና መላ ጽሁፉ እንደሚያሳየው የዚህ የዲሞክራሲያ ቁጥር ዋና አላማ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ሦስቱንም ጠላቶች ባንድነት መዋጋት እንዳለባቸው ለማሳየት ነው። ግን እነርሱ እንደሚሉት ደርግ በርግጥ “ፋሺስት” ከሆነ ለምን ከነመንገሻ ስዩም ጋር ፀረፋሽስት ግንባር አናቋቁምም? ሌላው ቀርቶ ከኢምፔሪያሊዝም ከራሱ ጋር ወዳጅነትን ፈጥረን ለምን ደርጉን አንገለብጠውም? በስታሊን ስትመራ የነበረችው ታላቋ ሶቭየት ህብረት ለማይቀረው ጦርነት ፋታ ለማግኘትና ለመዘጋጀት መጀመሪያ ላይ ከፋሽስቱ ሂትለር ጋር የወዳጅነት ውል ፊርማ፣ ከዚያም ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲያ ከቀንደኞቹ ኢምፔሪያሊስት አገሮች ጋር በፋሽስቶች ላይ የአንድነት ግንባር አልፈጠረችምን? ጀግናው የቪየትናም ሕዝብ በፈረንሳይ ቅኝ ገዥዎች ላይ በከፊልም ቢሆን ከራሱ ፊውዳሊስቶች ጋር፣ በጃፖን ፋሽዝም ላይ ደግሞ ከፈረንሳይ ኢምፔሪያሊዝም ጋር ያንድነት ግንባሮች ፈጥሮ አልተዋጋምን? 

የዲሞክራሲያን የመሰለ አቋም ያላቸው “የኢትዮጵያ ተማሪዎች ፌዴሬሽን” /የኤዙና ፌዴሬሽን/ መሪዎች ይህንን “ደርግ ፋሽስት!” የሚለውን ቅዥታቸውን ማሳመን ሲያቅታቸውና ከነመንገሻ ስዩም ጋር በገሃድ መሰለፋቸው ሲታይባቸው፣ “የኢትዮጵያ ፋሽዝም የቀድሞው አይነት ፋሽዝም ስላልሆነ ፀረፋሽስት ግንባር መፍጠር አያስፈልግም” የሚል ስንኩል ፈሊጥ ለማጭበርበሪያ ፈጥረዋል። የዲሞክራሲያም ሰዎች እንደዚያው ማድረግ ሊኖርባቸው ነው።

ዲሞክራሲያ ቁጥር 23 በስደት ያሉት ጐልተኞችና ባገር ውስጥ ያሉት የመደብ ወንድሞቻቸው “እየተወያዩ እየተደራጁ በኋላም ሃይላቸውን የሚያስተባብሩ የአንድ የጋራ የትግል ግንባር አባላት ወደመሆኑ እያመሩ ነው። የተከታዮቻቸው ቁጥር፣ በተለይ ከሦስት ወራት ወዲህ፣ ባፋጣኝ እያደገ ነው” ይላል። ቀጥሎም እነመንገሻ ስዩም በሳውዲ አረቢያ ተሰብስበው እንደነበርና እነዚህ አድሃሪዎች “የጀመሩት ቀልድ አለመሆኑን” በደንብ ይጠቁማል። በጣም ጥሩ ትንተና ነው።(በነገራችን ላይ፣ እነዚሁ አድሃሪዎች እኤአ መስከረም 7 ቀን 1975 ላይ በጅዳ ከፒኤልኤፉ መሪ ከኦስማን ሳላህ ሳቢ ጋር “ግንባር” ለመፍጠር መዶለታቸውንና የኤርትራ ግንባር “በትግራይና በአውሳ ለሉት ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄዎች ሙሉ የሞራልና የማቴሪያል ድጋፍ” እንደሚሰጥ፣ እኤአ በጥቅምት 2 ቀን 1975 በመግለጫ ማስታወቁን ጽሁፉ አይጠቅስም። ጽሁፉ እንዴት ይህንን ትልቅ ቁም ነገር ሳተው?) እንደዚሁም ዓለም አቀፍ ኢምፔሪያሊዝም እነመንገሻ ስዩምንም ደርጉንም እንደሚረዳ ጽሁፉ ያመለክታል። ይህንን ለመጠቀም የተሰነዘረው የጽሁፍ ክፍልም እንደሌላው ሁሉ የተምታታ ነው። “ሰፊው ሕዝብ ከኢምፔሪያሊስት ብዝበዛ ለመላቀቀ የሚያካሂደውን ታላቅ አብዩት ለማውደም አሜሪካ፣ ምእራብ ጀርመንና የተቀሩት ኢምፔሪያሊስት ሃገሮች ባለሁለት ራስ ጦር ወርውረዋል. . . ወዘተ” ይላል። ሊሆን ይችላል። ግን የዲሞክራሲያን አመራር የትንተና ደካማነት ወይንም የአውቆ ማወናበድ ሥራ የሚያጋልጡ ሁለት እውነቶች አሉ።

አንደኛ፡- ያሜሪካ ኢምፔሪያሊዝምና ሌሎችም ኢምፔሪያሊስቶች በመሳሪያ ሽያጭና በ“እርዳታ” አማካይነት በወታደራዊው መንግሥት ላይ ተጽእኖ እንዳላቸው ምንም ጥርጥር የለውም። ይሁንናም፣ በተለይ ያሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም ባሁኑ ሰአት አዝማሚያው ወዴት እንደሆነ ገና ካልለየለት፣ አደገኛ ሊሆንበት ከሚችልና ቢያንስ በቃላት ደረጃ ፀረኢምፔሪያሊስት ከሆነው ደርግ እነመንገሻ ስዩምን እንደሚመርጥ ሳይታለም የተፈታ ነው። ለዚህ ትንሽ ማስረጃ ከተፈለገ የኢምፔሪያሊስት አገሮችን ጠቅላላ ኘሬስ ብቻ በደንብ መመልከት ይበቃል።

ከነዚህ አንዱን ቀንደኛ የሆነውን ለመጥቀስ ያህል ብቻ፣ የኦክቶበር 21፣ ያሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም ዋና አፈቀላጤ የሆነው “ዘ ኒውዩርክ ታይምስ” የተባለው ጋዜጣ “በኢትዮጵያ መንግሥቱ የሚገዛው በአመጽ ነው፤ ጠቅላላ ውዥንብር-ኬኦስ-ነግሷል” በሚል አርእስት ወታደራዊውን መንግሥት በማጥላላትና እነመንገሻ ስዩምን፣ የኃይለሥላሴንም የቀድሞ ሥርዓት ጭምር በማሞገስ ጽፏል። የጽሁፉ ይዘት “ፋሽዝም” በኢትዮጵያ ነግሷል ከሚለው የዲሞክራሲያ አቋምና ከነመንገሻ ስዩም ቋንቋ በምንም አይለይም። በዚህ ደረጃ፣ ሦሶቱም የደርግ ጠላቶች በተጨባጭ አኳኋን ባንድነት ተሰልፈዋል። ዲሞክራሲያ እነመንገሻ ስዩምን በማጋለጡ፣ ያውም በተድበሰበሰ ሁኔታ፣ከነርሱና ከኢምፔሪያሊዝም ደጋፊነት አመለጠ ለማለት አይቻልም።

በተረፈም ደርጉ በወሰዳቸው አንዳንድ ፀረኢምፔሪያሊስት እርምጃዎችና – “መሬት ላራሹም” እራሱ በባህርዩ ፀረኢምፔሪያሊስት ነው!- በደርጉ አመጣጥ፣ በመደብ ይዘቱ፣ እነመንገሻ ስዩም፣ ነጋ ተገኝ፣ አሊ ሚራህ ይበልጥ ለኢምፔሪያሊዝም የሚያመቹ መሆናቸውን ማንም ሪቮሉሽናዊ በቀላሉ ሊረዳ ይችላል። ደግሞም ወደፊት በግልጽ ኢምፔሪያሊዝም ከነዚያ ጋር ተሰልፎ እንደሚመጣ ማየታችን ፈጽሞ አይቀርም።

በደርጉ ውስጥና ውጭም የተጀመረው ትግል እየተፋፋመ ሄዶ ትክክለኛ መስመር የሚያዝበት፣ ፊውዳሊዝም፣ ኢምፔሪያሊዝምና ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝም ሙሉ በሙሉ የሚመቱበት፣ ሰፊው ሕዝብም ተደራጅቶና ታጥቆ ስልጣንን ለወጉ ሳይሆን በእርግጥ በእጁ የሚያስገባበትና የሚጠብቅበት ሁኔታ ላይ ካልተደረሰ በስተቀር የኢምፔሪያሊዝም አደጋ ያለ ነው። ኢምፔሪያሊዝም ባመቸው መሳሪያ ይጠቀማል፤ ብዙ አማራጭ መሳሪያዎች አሉት። የተራማጆች አንዱም ተግባር በመሃል የሚዋልሉ ክፍሎችን ገፍትሮ ወደኢምፔሪያሊዝም ጉያ መጨመር ሳይሆን ወደሕዝቡ ሰፈር ሊደባለቁ የሚችሉትን መሳብ፣ ሊሳቡ የማይችሉትንም በተቻለ መጠን መነጣጠልና ከነሙሉ ትጥቃቸው ወደጠላት ሰፈር እንዳይገቡ መከላከል ነው። አንድን ህብረተሰባዊ ቡድን (ስልጣን ኮርቻ ላይ ወጣም አልወጣ) እኛ ወደሕዝቡ ሰፈር፣ ወደአብዩቱ ልንስበው የምንሞክረውን ያህል ኢምፔሪያሊዝምም ወደራሱ ሰፈር፣ ወደ ፀረአብዩት ሊስበው ይፍጨረጨራል። ይህ እራሱ አንድ ትግል ነው። ግራና ቀኝ ዘላይና የቅራኔዎች ክምችት የሆነውን እንደደርግ ያለውን አካል ቢቻልም እያንዳንዱን የደርግ አባል ሚናውን እንዲለይ፣ ሰልፉን እንዲያሳምር፣ ወደአብዩቱ እንዲደባለቅ የሚያስችሉ ሁኔታዎችን መፍጠር አለብን። ይህም በመሰረቱ የአብዩቱን ደጋፊዎች ማብዛት ነው። ይህ መቼም ለዲሞክራሲያ ምስጢረ-ሥላሴን ለማፋለስ መሞከር ነው፤ የከፋ ሃጢአት ነው።

ሁለተኛ፡- ከላይ እንደተጠቀሰው ሁሉ፣ ዲሞክራሲያ ከፍ ብሎ “ዋናው ቅራኔና ትግል” በፊውዳሊዝም- ኢምፔሪያሊዝምና በሰፊው ሕዝብ መካከል ያለው መሆኑን፣ ነገሩ በተምታታ አኳኋን ቢቀርብም፣ ተናግሯል። እዚህም ላይ፣ እነመንገሻ ስዩም- ነጋ ተገኝ “ለቀልድ” ያልተነሱ መሆናቸውንና “ከደንከል በረሃ እስከመተማ፣ ከተከዜ እስከአባይ ያለው የአድሃሪያን ትግል መቀነባበሩ እንደማይቀር” ገልጿል። (በነገራችን ላይ፣ ለምን “ከተከዜ” ብቻ? ለምንስ እስከ “አባይ” ብቻ?) ይህ ቢምታታና ከኋላው አንድ ግልጽ ያልሆነ ነገር ቢኖርበትም በመሰረቱ ትክክለኛ ትንተና ነው። ግን ከዚህ ትንተና መከተል የነበረበት መደምደሚያ ፊውዳሊዝም- ኢምፔሪያሊዝም፣ ወይንም እነመንገሻ ስዩምና ያሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም፣ አሁንም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ዋና ጠላቶች ናቸውና በቅድሚያ በነርሱ ላይ መተባበር አለብን የሚል መሆን ነበረበት። ባንድ በኩል እነመንገሻ ስዩም- ነጋ ተገኝ እየተጠናከሩ መጥተዋል እያለና፣ አመጣጣቸውም ደርጉን አስወግደው ስልጣንን ለመያዝ መሆኑን እየጠቆመ፣ በሌላ በኩል ደግሞ “ፋሽስቱ” ደርግና ደመኛ ጠላቶቹ እነመንገሻ አንድ ናቸውና በሰፊው ሕዝብ ላይ ህብረት ሊመሰርቱ የሚችሉ ማስመሰል በሬ ወለደን ለማሳመን መሞከር ብቻ ሳይሆን ሰፊው ሕዝብ የጊዜውን ወዳጆችና ጠላቶች በትክክል እንዳይለይ በማወናበድ በቀጥታ ጠላቶቹን ማገዝ ነው።

ዲሞክራሲያ ቁጥር 23፣ እኛ እስከምናውቀው ድረስ ለመጀመሪያ ጊዜ፣ ከኢትዮጵያ ድንበር ውጭ ያለውን የኃይሎች አሰላለፍ ለማጤን ሞክሯል። በተለይ አድሃሪ የአረብ መንግሥታት እነአሊ ሚራህን፣ መንገሻ ስዩምን፣ ወዘተ… እንደሚረዳ ጠቅሷል። በጣም ጥሩና የሚያስመሰግን አቀራረብ ነው። ግን እነዚሁ አድሃሪ ኃይሎች የኤርትራንም ግንባሮች ከኃይለሥላሴ ጊዜም ይበልጥ ዛሬ በግፍ እንደሚረዱ አይጠቅስም። ለምን? ከዚህም አልፎ፣ “እነዚህ ሁሉ /አድሃሪ ያካባቢው አገሮች መንግሥታት/ የምርጦቹን መንግሥት ጠልተው አይደለም፣ በዚህ ረገድ አቋማቸው ከኢምፔሪያሊዝም አይለይም . . .ወዘተ.” የሚል ፈጽሞ የተወናበደ አስተሳሰብ ያቀርባል። አደሃሪ የአረብና ያካባቢው አገሮች የደርጉን አዝማሚያ የማይጠሉ ከሆነና አብዩቱን እንደሚያጨናግፍላቸው ካወቁ ለምን ካሁኑ ለነአሊ ሚራህ የሚሰጡትን ሚልዩን ለርሱ አይሰጡትም? ገና ለመንግሥት ስልጣን ከሚታገሉት ከነመንገሻ ስዩም ነጋ ተገኝ- አሊ ሚራህ፣ ቀድሞ ስልጣኑን የያዘው ኃይል አይሻላቸውም ነበርን? ይህም የዲሞክራሲያ ሌላ የትንተና ጉድለትና አወናባጅ አቋም ነው።

ዲሞክራሲያ ቁጥር 23 እጅግ የሚያሳዝን፣ የወንድሞቻችንን የትንተና ደካማነት ወይንም አንዳንዶቹ አውቀው ለማወናበድ መነሳታቸውን የሚያሳይ ጽሁፍ ነው። አልፎ አልፎ ደህና አድርገው ሁኔታውን ያዩትና በንኡስ ከበርቴው ድንፋታ ብቻ ተመልሶ አይናቸው የሚታወር ይመስልባቸዋል።

ያገሪቷን የመደቦችና የኃይሎች አሰላለፍ በሚመለከተው በኩል የኛ አቋም ግልጽ ነው። በፊውዳሊዝም-ኢምፔሪያሊዝምና በሰፊው ሕዝብ መካከል ያለው ቅራኔ አሁንም ዋነኛው ነው። በሀገሪቷ ላይ ያንዣበበው ትልቅ አደጋ የነመንገሻ ስዩም፣ አሊ ሚራህና ሌሎችም ፊውዳሊስቶች በኢምፔሪያሊዝም ተደግፎ ፀረሬቮሉሽኑን ከሁሉም አቅጣጫ ማምጣት ነው። የፊውዳሊዝም- ኢምፔሪያሊዝም የቀድሞ መመርኮዣዎች፣ ቢሮክራሲያዊውና አቀባባይ ከበርቴው፣ በደርጉ ውስጥ ያሉትም አድሃሪዎች ጭምር፣ በዚህ አይነቱ ፀረሪቮሉሽናዊ ቅልበሳ ሊተባበሩ የሚችሉ፣ አሁንም ቢሆን በብዙ ገመዶች ከነዚያ ጋር የተሳሰሩ ኃይሎች ናቸው። የኤርትራ ግንባሮች አድሃሪዎችም ወደዱም ጠሉም ከነዚህ አድሃሪ ኃይሎች ጋር ተሰልፈዋል። የአረብና የሌሎችም አድሃሪ ያካባቢ አገሮች ሁኔታም እንደዚያው ነው። ሁሉም በኢትዮጵያ የተያዘውን ሪቮሉሽናዊ እንቅስቃሴ ርቆ ሳይሄድ ሊያቆሙት እንደሚፈልጉ ለማንም ሃቀኛ ተመልካች ግልጽ ነው። ይህንን እንቅስቃሴ ለመስበርም የሚመቸው የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ ያመራሩን ቦታ የያዘውን ደርግ በመገልበጥም እንደሆነ እንደዚሁ ግልጽ ነው።

ይሁንናም፣ በዚህ ደርግና በሰፊው ሕዝብ መካከል ቅራኔ የለም ማለት አይደለም። ደርጉ እስከዛሬ ፀረዲሞክራቲክ ኃይል ሆኖ ሰፊው ሕዝብ በቶሎ እንዳይነቃ፣ እንዳይደራጅና ለማይቀረው ፀረፊውዳል- ፀረኢምፔሪያሊስት- ፀረቢሮከበርቴ የመጨረሻ ጦርነት እንዳይዘጋጅ አድርጓል። ፍፁም አሰቃቂ የሆኑ ፋሽስታዊ እርምጃዎችንም በየጊዜው ወስዷል። በየከተማው በወዛደሮች ላይና በየገጠሩም በለፍቶአዳሪው ገበሬ ላይ የተወሰዱት ፍፁም ፋሽታዊ የሆኑት የጭፍጨፋ እርምጃዎች ከታጋዩ ሰፊ ሕዝብ አእምሮ በቀላሉ የማይፋቁ ቋሚ ምስክሮች ናቸው።(በነገራችን ላይ ግን ፋሽስታዊ “እርምጃዎችን” መውሰድና ፋሽስታዊ ሥርዓትን ማቋቋም ሁለት ልዩ ነገሮች መሆናቸውን እናስታውስ)

በሌላ በኩል ግን መሰረታዊ ነገሮችን የሚነኩ ተራማጅ አዋጆች አሉ። አድሃርያንን ባንድነት ያሳለፏቸው እነዚህ አዋጆች ናቸው። የእነዚህም እውነተኛ አድሃርያን፣ ግንባር ቀደም የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠላቶች መነሳት በደርጉና በሰፊው ሕዝብ መካከል ሊኖር ይችል የነበረውን የመጀመሪያ ደረጃ ቅራኔ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ቅራኔ አዛውሮታል። ስለዚህ ወደድንም ጠላንም፣ በንኡስ ከበርቴ አለሁ-አለሁ- ባይነት ካልተመራንና ተጨባጩን ሁኔታ ለማየት አንፈልግም ካላልን በስተቀር፣ እንደዲሞክራሲያዎች፣ እነመንገሻም፣ ኢምፔሪያሊዝምም፣ ደርጉም አንድ ናቸውና ሦስቱንም እኩል እንዋጋቸው አንልም። የተራማጆች ተግባር ጊዚያዊ ወዳጆችን ሁሉ ባንድነት ማስተባበርና በዋናው ጠላት ላይ መረባረብ፣ በርሱ ላይ ብቻ ማተኮርና በርሱ ላይ ሊሰለፍ የሚችለውን ሁሉ ኃይል ማሰለፍ መሆኑን የሪቮሉሽኖች ቴዎሪና ታሪክ ያስተምረናል። ወዳጅንና ጠላትን፣ ጊዜያዊም ሆነ ዘላቂ፣ አማታቶ ሁሉም ያው ነውና ዉጋው፣ ወይንም ልትወጋው ትችላለህ ማለት ሰፊውን ሕዝብ በተጨባጭ መንገድ ለጠላቶቹ አሳልፎ መስጠት ነው። ተራማጆች ስለደርጉ ሊኖራቸው የሚገባቸው አቋም አብዩታዊ ሂስ የሚለው የኛ አቋም ብቻ ነው የምንለውም ለዚህ ነው።

“አብዩታዊ ሂስ” ስንል ምን ማለታችን ነው? ዋናው መነሻችን የመንግሥት ስልጣን በሚያስተማምን አኳኋን ወደሰፊው ሕዝብ እጅ የሚገባበትን መንገድ መሻት ነው። ለዚህም እስከመጨረሻው እንታገላለን። ስለዚህም ይህን ደርግ በፀረሕዝብነቱ፣ በፀረዲሞክራሲያዊነቱና በፀረአብዩትነቱ እንቃወመዋለን፣ እንታገለዋለን። ሰፊው ሕዝብ ተደራጅቶና ታጥቆ ከደርጉም ሆነ እርሱን ከሚተካው ሌላ ተመሳሳይ መንግሥት እጅ ስልጣንን ፈልቅቆ እንዲወስድ የሚያስችለውን ትምህርት እንዲያገኝ፣ እንዲደራጅ አስፈላጊውን ትግል እናደርጋለን። ዋናው አብዩታዊ ቁም ነገር የአብዩቱ ወደፊት መግፋት፣ ስልጣን ዝውውር ላይ ብቻ በማተኮር በጓዳ ሾልከው ለሚገቡ ቀልባሾች፣ ለፀረአብዩት ኃይሎች መሳሪያ አንሆንም፤ ከሰፊው ሕዝብ ዋና ጠላቶች ጋር አንተባበርም። በአብዩቱ አንፃር እያየን ፀረአብዮት ኃይሎችን በየደረጃቸው እየለየን እንታገላቸዋለን። የተለያዩ ጠላቶችን እንደየጠላትነት ደረጃቸው በተለያዩ ዘዴ እንመታቸዋለን እንጂ ሁለት እግር ስላለን ሁለት ዛፍ ላይ እወጣለሁ የሚለውን የታክቲክ ስህተት በማድረግ ሁለት ጦርነት በአንድ ጊዜ አናውጅም። ለአብዮቱ መግፋት ስንል የሁለተኛ ደረጃ ጠላቶችን በልዩ ልዩ ዘዴ እናዳክማቸዋለን እንጂ ከዋናው ጠላት ጋር እንዲሰለፉ አናደርግም፣ ወይም ከዋነኛው ጠላት ጋር ተሰልፈን በሁለተኛ ደረጃ ጠላቶች ላይ አንዘምትም። የሂሳችን አብዮታዊነት ከሞላጐደል ይህ ነው።

ወደልዩነት ነጥቦች እንመለስና፣ በዚህ ጽሁፍ መጀመሪያ ላይ ባነሳናቸው የልዩነት ነጥቦች ላይ ሰፋ ያለ አስተያየት ማቅረብ ባስፈለገ ነበር። በብዙዎቹ ላይ ወደፊት “የሰፊው ሕዝብ ጽምጽ” ይመለስባቸዋል። አሁን ግን አንዲት የመጨረሻ ነጥብ፡- ዲሞክራሲያ ስለደርጉ የመደብ ባህርይ ደጋግሞ የተምታቱ አስተያየቶችን አቅርቧል። በጋዜጣው ቁጥር 22 የሚከተለው ሰፍሯል፡-

“በደርጉ ውስጥ በደርግ ስም የመንግሥት ስልጣን የያዙት ጥቂት መኮንኖች ለስልጣናቸው ሲሉ የቻሉትን ያህል ሰፊውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ከማፈንና ከመጨፍጨፍ የማይመለሱ፣ ለቢሮ ከበርቴዎችና ለኢምፔሪያሊስቶች አገልግሎት ያደረ፣ የስልጣናቸውን ጊዜ የሚያራዝም መስሎ ከታያቸው ከፊውዳሊስቶችም ጋር ከመታረቅና አብሮ ከመስራት የማይመለሱና የወጣላቸው መሆናቸውን አሳይተዋል።. . .” (ስርዝ የተጨመረ)

በቁጥር 23 ደግሞ፣ ይኸው ደርግ 

“መንግሥትነቱ ግን ለቢሮ ከበርቴ፣ አቀባባይ ከበርቴና ንኡስ ከበርቴው መደብ ነው።. . .”ይላል።

በአሁኑ ጊዜ የመንግሥትን ስልጣን የያዘው የትኛው የህብረተሰብ መደብ ነው የሚለውን ጥያቄ በማያሻማ አኳኋን ለመመለስ ዲሞክራሲያን የጨነቀው ይመስላል። ወንድሞች፣ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት የንኡስ ከበርቴው መንግሥት ነው። “መንግሥትነቱ ለዚህ ነው፣ ለዚያ ነው” አይደለም። የንኡስ ከበርቴው መንግሥት ነው።

ይህ የንኡስ ከበርቴ መንግሥት ገና አልተደላደለም። ይሁንናም፣ በተለይ በቢሮ ከበርቴውና ባቀባባዩም ላይ አንድ አይነት ጊዚያዊ አምባገነንነትን አስፍሮ እነዚህን መደቦች፣ በዲሞክራሲያ ቋንቋ፣ “በአርጩሜ” የሚያሰራ መንግሥት ነው። ስለዚህም፣ በነርሱና በደርጉ መካከልም ቅራኔ አለ። ስለዚህም፣ እንደ ኢምፔሪያሊዝም ሁሉ፣ እንደነ መንገሻ ስዩም ሁሉ፣ እንደዲሞክራሲያም የቢሮከበርቴውና አቀባባይ ከበርቴው “ጊዚያዊ ሕዝባዊ መንግሥት” ይፈልጋሉ። በተቻለ ፍጥነት የሲቪል መንግሥት እንዲፈጠርላቸው ይፈልጋሉ። ከዲሞክራሲያ ጋር የተሰለፉት ንኡስ ከበርቴዎችና ሌሎችም የቀኝ ክንፍ ኃይሎች ይህንን የሚፈልጉት ደግሞ ደርጉ የያዘባቸውን የመንግሥት ስልጣን ለመውሰድ አቋራጭና ጥሩ “አጋጣሚ” መሆኑን ስለሚያውቁት ነው። ስለዚህም፣ በተጨባጭ መንገድ ሲታይ፣ በዲሞክራሲያና በደርጉ መንግሥት መካከል ያለው ጥል በንኡስ ከበርቴው መደብ ውስጥ የሚደረግ የስልጣን ትንንቅ ነው ለማለት እንችላለን። የዲሞክራሲያም ሆነ የደርጉ ሺህ ጊዜ የሰፊው ሕዝብ ስም ማንሳት ማንንም ሊያሳስት አይገባም።

በነገራችን ላይ፣ ይህንን የደርጉን የመደብ ባህርይ በሚመለከተው በኩል፣ እነዚሁ የዲሞክራሲያ ወንድሞች በ30/6/67፣ የመሬት አዋጁን ምክንያት በማድረግ ባወጡት ልዩ እትም የሚቀጥለውን አስፍረው ነበር።-

    “ከወዝአደሩና ከገበሬው አብራክ የተገኙት ተራ ወታደሮችና የበታች ሹማምንት፣ እንዲሁም ጥቂት ተራማጅ    መኮንኖች ይህንን ከፍተኛ ቆራጥነት የሚጠይቅ ታሪካዊ እርምጃ በመውሰድ ለመደብ ጓደኛቸው ለሰፊው ሕዝብ ያላቸውን ጽኑ ታማኝነት በተጨባጭ ማስረጃ በማሳየታቸው … ወዘተ.” (ስርዝ የተጨመረ)

ከመሬት አዋጁ እስከዛሬ ባሉት ጥቂት ወራት ውስጥ ደርጉም፣ የዲሞክራሲያም ወንድሞች የመደብ ባህርያቸውን ለውጠው ይሆን? አይደለም። ሁለቱም የንኡስ ከበርቴው መደብ አባሎች እንደመሆናቸው መጠን፣ በሬቮሉሽንና በፀረሬቮሉሽን መካከል እንደወላወሉ ናቸው። ይህ እንግዲህ ባጠቃላይ ስንመለከት ነው። ቀረብ ብለን ስናይ ደግሞ፣ በደርግ ውስጥ ባንድ በኩል ጥቂት ሃቀኛ ተራማጆች፣ ለሰፊው ሕዝብ ጥቅም በርግጥ እስከመጨረሻው ለመሰዋት የተነሱ አሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ትምክህተኞች፣ በርግጥም የንኡስ ከበርቴውን ፈላጭ ቆራጭነት ብቻ በሰፊው ሕዝብ ላይ አስፍረው ለመኖር የሚፈልጉ፣ እስከመጨረሻው ድረስ የማይለወጡ አድሃሪዎች አሉ። አንዴ ያንዱን አንዴ የሌላውን ክንፍ አቋም የሚደግፉ፣ ባጠቃላይ ግን ለሰፊው ሕዝብ የሚጠቅሙ እርምጃዎችን የማይቃወሙ፣ በመደብ ምንጫቸውም ቢሆን ከሰርቶ አደሩና ከአርሶ አደሩ ጋር በይበልጥ የሚቀራረቡ ሕዝባውያንም /ፖፑሊስቶች/ በብዛት ይገኛሉ። በመጀመሪያዎቹ በሁለቱ ክንፎች መካከል ያለው ትግል ገና አልለየለትም።

በዲሞክራሲያም ውስጥ ብዙ ሃቀኛ፣ የሬቮሉሽን ፍላጐት ያላቸው፣ በርግጥ በወዝአደሩ ርእዩተዓለም ተመርተው እስከመጨረሻው ለመታገል የቆረጡ ባንድ በኩል እና እራሳቸው ተወናብደው ሌላውን የሚያወናብዱ፣ ሬቮሉሽኑን ባቋራጭ ለማምጣት የሚቻል የሚመስላቸው፣ የመንግሥትን ስልጣን ሕዝቡ እራሱ ተደራጅቶና ታግሎ እንዲይዝ ሳይሆን እነርሱ እንዲይዙለት የሚመኙ አድሃሪዎች በሌላ በኩል አሉ። ከነዚህ ለመጀመሪያዎቹ የምንለው፣ የሌኒንን ምክር በመከተል፣ የተጨባጭን ሁኔታ ተጨባጭ ትንተና እናድርግ ነው። የዛሬይቱን ኢትዮጵያ ሁኔታ በመፈክሮችና በግል ፍላጐት በማሰብ ፈንታ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ካጤንነው፣ የውስጥና የውጭ ኃይሎችን አሰላለፍ በሃቅ ከተመለከትነው፣ ከኢትዮጵያ ፊውዳላዊ ሥርዓት በተወረሰው የሃሜትና የስም ማጥፋት ዘዴ በመጠቀም ፈንታ ዲሞክራሲያዊና አብዩታዊ ክርክር ካደረግን የማንገባባበት ምንም ምክንያት የለም። ስለዚህም፣ ክርክሩ ይቀጥል፤ አወናባጅ አስተሳሰቦችና ግምቶች ይወገዱ፣ የጠራና ተጨባጭ የፖለቲካ መስመር ይኑር።

ሃቀኛ ውይይት ሊጀመርና ትክክለኛ መስመር ሊሰምር የሚችለውም ተራማጆች በሙሉ ኃይል፡-
ለዲሞክራሲ መብቶች መከበር፣
በየወህኒ ቤቱ ለተወረወሩት ተራማጆች፣ የሠራተኛ
ማህበር መሪዎች፣ የገበሬ ማህበራት መሪዎች
መፈታት ሲታገሉ ነው።አቅማችን የተወሰነ በመሆኑ ብዙ ቅጂዎችን
አላሰራጨንምና በይዘቱ የምትስማሙ አንባብያን
በሙሉ አንብባችሁ ላላነበቡ ብታስተላልፉ፣
ከተቻለም ጋዜጣው የሚበራከትበትን ዘዴ በየፊናችሁ
ብትፈልጉ ለትግላችን ይበጃል።
Scroll to Top