የሰፊው ሕዝብ ድምፅ
ቁጥር 66፣ ግንቦት 5፣ 1970
የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ
በዚህ እትም መኢሶን ጌዜውን አይነተኛ የሚያደርጉትን ክንውኖች ከተነተነ በኋላ መኢሶን ባለፉት ጥቂት አመታት የወሰዳቸውን አቋሞች ያብራራል። በመቀጠልም መኢሶን፣በዚህ ሂደት የቀሰማቸውን ትምህርቶች በመጥቀስ፣ በተራማጆች መካከል ያሉትን ልዩነቶች አስወግዶ ጠንካራ ሕብረት ለመመስረት መፍትሄ ይሆናሉ የሚላቸውን ሃሳቦች ያቀርባል። በመጨረሻም አቢይ በሚባሉ የፖለቲካ ጉዳዮችና እንዲሁም በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ላይ ያሉ ችግሮችን በጥልቀት መርምሮ ለመፍታት መወሰድ ያለባቸውን እርምጃዎች ይሰነዝራል።
1. መግቢያ
3.1 ስለ መኢሶን “ፈርጣጭነት”
4.1 የተራማጆች ህብረት ጥያቄ
4.2 የምስራቅ ኢትዮጵያ ጥያቄ
4.4 የኤርትራ ጥያቄ
4.5 የብሄረሰቦች ጥያቄ
4.6 የቢሮክራሲው ጥያቄ
4.7 የኢድህ-ኢህአፓ ጥያቄ
4.8 የዲሞክራሲ መብቶች ጥያቄ
4.11 የብሔራዊ ነፃነታችን ጥያቄ
4.12 የኢኮኖሚና የሶሻል ጉዳዮች ጥያቄ
4.13 የወዛደሩ ፓርቲ ጥያቄ
6. መደምደሚያ
1.መግቢያ
ከዚህ ቀደም ደጋግመን እንዳልነው፣ የኢትዮጵያ አብዮት ሂደት እጅግ ፈጣን ነው። ከፍጥነቱም የተነሳ ይመስላል፣ በአንድ በኩል በአብዮቱ ላይ አናት በአናት እየተደራረቡ አያሌ ሴራዎች ይመጣሉ። በሌላ በኩል መደቦች፣ የፖለቲካ ድርጅቶችና ግለሰቦች ከአንደኛው አቋማቸው ወደሌላው፣ ደግሞ ከዚያም ወደሌላኛው ከምን ጊዜው እንደሚሸጋግሩ እንኳን አይታወቅም። ስለዚህም ሳይሆን አይቀርም አብዮታችን ገና አንዱን የቅልበሳ ሴራ ሳይወጣው ተመልሶ በሌላ በተጠናከርና በተራቀቀ ፀረ አብዮት የሚወጠረው። ተዋናዮች ደግሞ፣ አስደናቂ የሆኑ የሎጂክ አክሮባቶችን ሲሰሩ የሚታዩት።
ይሁን እንጂ፣ የኢትዮጵያ ጭቁን ሕዝቦች ደግሞ፣ በየጊዜው ያሰፈሰፉትን ፀረ አብዮት በዚህም በዚያም
ሊቋቋማቸው ችለው እንደነበረም የማይታበለው ሀቅ ነው። ነገር ግን ይህ በዚህም በዚያም ደግሞ፣ በየደረጃው ከባድና ውስብስብ ጥያቄዎችን እያስከተለ ሲመጣ ቆይቷል። በዛሬው ወቅትም እንደዚሁ ከባድና ውስብስብ ከሆኑት ጥያቄዎች ፊት ሳንቆም አልቀረንም።
ለማስታወስ ያህል፣ ስለ እነዚህ ሁኔታዎች በተናገርን ቁጥር፣ ደጋግመን ያነሳነውም አንድ ሌላ ጥያቄ ነበር። በየጊዜውም “ምናልባት” በማለት ጠይቀን ነበር። “ምናልባት” በኢትዮጵያ አብዮት ላይ የቅልበሳ ሴራዎች እንደዚህ ተደራርበው የሚመጡት፣ አንድም የኢትዮጵያ ተራማጆች ከአብዮቱ ፈጣን ሂደት ጋር እኩል ባለመራመዳቸው ይሆን? እነርሱ በቅድሚያ ተዘጋጅተው የአብዮቱን ወገኖች እንደዚሁ በቅድሚያ ሳያዘጋጇቸው በመቅረታቸው ይሆን? ወይንስ እነርሱንም የመደብ ሉጋም የሚባለው ነገር አጠንክሮ እየሳባቸው ይሆን?
ዛሬ የጊዜውን የኢትዮጵያ ሁኔታ በጥሞና ልንመለከተው ስንነሳም፣ ከዚሁ አዋሳኝ ጥያቄ ፊት ተመልሰን የቆምን ይመስላል። በተለይም፣ ከየካቲት /ከመጋቢት 1969 ዓ.ም. ወዲህ፣ በአጠቃላይ በአብዮቱ ሰፈርና በተለይም በተራማጆች መካከል የደረሱትን ነገሮች ስናጤን ደግሞ፣ ጥያቄዎችን አጠንክረን እንድናነሳ የሚያስገድዱን ሁኔታዎች እናያለን። መልሱ ግን ዞሮ ዞሮ ከሁለት አንድ እንደሆነም አንጠራጠርም። ማለትም፡-
– ወይ ታሪክ፣ በኢትዮጵያ ተራማጆች ላይ ከአቅማቸው በላይ የሆኑ ተግባሮችን ጭኖባቸዋል።
– ወይ ደግሞ፣ የመደብ ሉጋም የሚባለው ነገር ተዋናዮቹን በእውነት አጠንክሮ ስቧቸዋል ።
ያም ሆነ ይህ፣ መልሱ የመጀመሪያው ከሆነ፣ የኢትዮጵያ ሀቀኛ ተራማጆች፣ እውነተኛ አገር ወዳጆችንና ዲሞክራቶችን /በደርጉ ውስጥ ያሉትም ጭምር/ ዛሬም ቢሆን ተጋግዘው ለአብዮቱ ጥያቄዎች ሁሉ አብዮታዊ መልሶችን ለመስጠት የሚችሉበት አመቺ አብዮታዊ ሁኔታ እንዳለ ነው። እነዚህኞቹ፣ በመካከላቸው ያሉትን ችግሮችና ቅራኔዎች አርቆ አስተዋይነት በተመላበት ፓለቲካ አስወግደው ለመተባበር የሚችሉበትም አመቺ ሁኔታ አለ።
በዚህ አንጻር፣ መኢሶንን በሚመለከተው በኩል፣ መኢሶን ባሻው ዓይነት አሉባልታ፣ ባሻው ዓይነት የፈጠራ ክስ፣ ባሻው ዓይነት ተንኮል፣ ባሻው ዓይነት ዘመቻ….ወዘተ. የማይፈታ ጽኑ አቋም አለው። ይህንን የመኢሶንን አቋም ወዳጆችም ጠላቶችም ያውቁታል። መኢሶን፣ የኢትዮጵያ ሀቀኛ ተራማጆች ታሪክ የጣለባቸውን ተግባሮች በጋራ ትግላቸው እንዲወጡት፣ የበኩሉንና የአቅሙን አስተዋጽኦ ከማድረግ አይቆጠብም። ለዚህ የተቀደሰ ተግባር ያለ ማቋረጥ ታግሏል ይታገላለም።
መልሱ የኋለኛው ከሆነ ግን፣ ጉዳዩ የአብዮትና የፀረ አብዮት ፍልሚያ እንደሆነ የሚያከራክር አይሆንም። ይህኛው አዲስም ባይሆን ሌላ ታሪክ እንደሆነ የዚያኑ ያህል ግልጽ ነው።
ለማንኛውም፣ በኛ ግምት ታሪክ የመጨረሻ ፍርዷን የሰጠች አይመስለንም። የዛሬው ወቅት አንደኛው፣ ምናልባትም ወሳኙ፣ የታሪክ ምዕራፍ ሳይሆን አልቀረም። የሚመጡት ወራቶች ከሁለት አንዱን በገሃድ እንደሚያሳዩንም አንጠራጠርም።
እንግዲህ ይህንኑ እያመለከትን ወደ ርዕሳችን እንመለስ። በዚህ ጽሁፍ ውስጥ አንደኛ በጊዜው የኢትዮጵያ ሁኔታ ላይ፣ ሁለተኛም በጊዜው የአብዮቱ ዋና ዋና ጥያቄዎች ላይ ያሉ አስተያየቶችና አቋሞች እንገልፃለን። አያይዘንም፣ ሦስተኛ፣ በተራማጆች መካከል ላሉት ችግሮች መፍትሄ የምንላቸው ሀሳቦች እናቀርባለን። ይሁንናም፣ ከመቀጠላችን በፊት ደግሞ አንድ ሁለት ማስታወሻዎችን ማስቀደሙ ጠቃሚ ሳይሆን አይቀርም።
አንደኛ፣ የዛሬው ወቅት ተቀዳሚ ተግባራችን ባለን አቅም ሁሉ ሀቀኛ አብዮታዊ፣ ዲሞክራሲያዊ ታጋይ የሆነ የተራማጆች ህብረት እንዲመሰረት መታገል ነው። ስለዚህም በዚህ ጽሁፍ ውስጥ፣ በአንድ በኩል በተራማጆች መካከል ያሉትን የልዩነት ነጥቦች፣ በሌላ በኩል ደግሞ የጋራ የሆኑትን የፖለቲካ አቋሞች በየመልካቸው እየለዩ ማስፈሩ ጠቃሚ በሆነ ነበር።
ይሁንና፣ በሌሎች ክፍሎች ውስጥ በቃልና በድርጊት መካከል የምናያቸው ከባድ ቅራኔዎች ደግሞ ጽሑፉን ባመለከትነው መንገድ እንዳንደርሰው አገዱን። በዚህ ላይ በጽሁፎች በሚሰፍሩትና በቃል በሚነገሩት ነገሮች
መካከል እንኳ አያሌ ቅራኔዎች ይታያሉ። ደግሞም፣ በፈጠራና በግምት የሚወሩት ወሬዎች መዓት ናቸው። የትኛውን ይዞ የትኛውን ለመተው እንደሚቻል አስቸጋሪ ነው። በቅርብ ለመወያየት ገና አልተቻለም።
ስለዚህም፣ እንደምንፈልገው ብንጽፈው፣ ጽሁፉ አለቀጥ ከመርዘሙም በላይ፣ “ሆኗል አልሆነም፣ ተብሏል አልተባለም” ከሚሉት “የእምነት ክህደት” ክርክር ውስጥ እንዳይከተን አሰብን። የሚሻለው፣ ነገሮች የማያሻሙ ካልሆነ በስተቀር፣ እንዳልነው “ያሉንን አስተያየቶችና አቋሞች ማሳወቅ ነው” ብለናል።
ሁለተኛ፣ ይህንን ጽሁፍ እንደምንፈልገውና እንደምንመኘው ያክልም አሟልተን ልንድርሰው አልቻልንም። ምክንያቱም፣ አንዳንድ በዝርዝር ልንተችባቸው የማንችልባቸው አርዕስት አሉ። በዛሬ ወቅት፣ በነርሱ ላይ በዝርዝር መመለሱ ጠቃሚ ሊሆን አይችልም። አንባቢዎች፣ ይህ ጽሁፍ ከዚህ በላይ ባቀረብናቸው ሁለት ምክንያቶች የተወሰነ እና የተገደበ መሆኑን እንዲረዱት እናሳስባለን።
**************************************************
ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ የመኢሶን ጽኑ ወገኖች፣ የመኢሶን ወዳጆች፣ የተወናበዱ የመኢሶን ጠላቶች እንዲሁም አስመሳይ ተራማጆች ጭምር፣ ከሌሎች ቀደም ጥረቶች በኋላ ይህችን ባጭሩ ያወጣችን ጽሑፍ በጥሞና እንዲያነቧት አብዮታዊ ጥሪያችንን እንገልጻለን። ተግባራዊ መፍትሄም ለመውሰድ የሚችሉ ወገኖች የሚያስፈልገውን ከማድረግ ወደኋላ እንዳይሉ እናሳስባለን። የጊዜው የፖለቲካ ተዋናዮች ከፍ ብለን ያመለከትነው የመደብ ልጓም አጥብቆ ከሳባቸውም፣ ይህች ታሪካዊ ወቅትና ሰነድ በታሪክ መዝገብ ውስጥ ልዩ ቦታዋን ትይዛለች። ይዋል ይደር እንጂ ሰፊው ሕዝብ የድሉ ባለቤት እንደሚሆን አንዳችም ጥርጣሬ አይገባንም።
የመኢሶን ጽ /ቤት
2. አጠቃላዩ የጊዜው ሁኔታ
ከዚህ በላይ “የኢትዮጵያ አብዮት ሂደት እጅግ ፈጣን ነው። ፀረ አብዮት ባናት ባናቱ ይመጣበታል። መደቦች፣ ለታሪክ እጅግ አጭር በሆኑ ጊዜ ውስጥ አስደነቂ ሽግሽጎችን ያደርጋሉ። የፖለቲካ ድርጅቶችና ግለሰቦች፣ የፖለቲካ አቋማቸውን በሚያስደንቅ ፍጥነት ይለዋውጣሉ…” ወዘተ. ብለን ነበር። ነገር ግን የኢትዮጵያ አብዮት ባህርይ በዚህች መግለጫ ብቻ የሚብራራም አይደለም።
ተደጋግሞ እንደተነገረው፣ የኢትዮጵያችን አብዮት “ዕድል” ሆኖ፣ የአብዮታችን መሪ ተዋናይ የንዑስ ከበርቴው መደብ ነው። ይህ መደብ፣ ካርል ማርክስ እንዳለው እዚያው በዚያው “ከበርቴም የሕዝብ ሰውም” በመሆኑ፣ በአብዮታችን ባህሪይ ላይም ይህ የመደብ ማህተሙ ተረግጦ ይገኛል። አብዮታችን የሚራመደውና እዚያው በዚያው አብዮትና ፀረ አብዮት በሆነ መንገድ ነው።
ስለዚህም፣ ባለፉት አራት ዓመቶች ውስጥ አብዮትና ፀረ አብዮት ያላሻሙበት አንድም ወቅት አንድም ድርጊት፣ አንድም እርምጃ አልነበረም ብንል ስህተት አይሆንም። አሁን የምንገኝበት ወቅት፣ ካለፉት ወቅቶች ይልቅ በተሸከማቸው አያሌ የአብዮትና የፀረ አብዮት ጥያቄዎች እንጅ፣ በሌላ የተለየ አይደለም። የአሁኑ ወቅት በእውነትም፣ ከምንጊዜውም ይልቅ በአብዮትና በፀረ አብዮት በመካከል የሚያሻማ ነው።
ባለፉት አራት ዓመቶች ውስጥ፣ እንደዛሬው ጊዜ አብዮትና ፀረ አብዮት ተደበላልቀውና በአንድ ፉርጎ ውስጥ ተሳፍረው አልተጓዙም። እንደ ዛሬው ጊዜ የአብዮቱና ሰፈር በአብዮትና በሶሻሊዝም ስም አልተቦረቦረም። ፀረ አብዮት እንደ ዛሬው ጊዜ በራሱ በአብዮቱ ሰፈር ውስጥ ተንሰራፍቶ አልሰፈረም። የአብዮቱ ወዳጆችና ጠላቶች፣ እንደዛሬው ጊዜ ከአንድ ሙቀጫ ውስጥ ተከተው አልተወቀጡም። ነገሮች ሁሉ፣ እንደዛሬው ጊዜ እዚያው በዚያው አብዮትና ፀረ አብዮት ሆነው ለማመን የሚያስቸግሩ ድራማዎች አልሆኑም። በዛሬው ወቅት፣ በኢትዮጵያ “ሰማያት” በታች አያሌ ውስብስብና የተተራመሱ ሁኔታዎች ሰፍነዋል ለማለት እንችላለን።
ለመሆኑ የዛሬው ሁኔታ እንዴት ሊፈጠር ቻለ? በመካከል የደረሱት ነገሮች ምንድን ናቸው? የመደቦችና የፖለቲካ ድርጅቶች አሰላለፍ እንዴት ተለወጠ? ዛሬስ ከምን ዓይነት ሁኔታ ላይ ደርሰናል?
መለስ ብለን እስከ ጥር/የካቲት 1969 ዓ.ም ደረስ የነበረውን ሁኔታ ስንገመግመው፣ እስከዚህ ጊዜ ድረስ የአብዮትና የፀረ አብዮት ሰፈር ይብዛም ይነሰም ተከልለው ይታወቁ እንደነበር ይታወሳል። እስከዚህ ጊዜ ድረስ፣ አብዮትና ፀረ አብዮት በርዕዮተ ዓለም ወይንም በፖለቲካ መስመር፣ በመፈክሮች ሆነ ወይንም በድርጅቶች ወይም ደግሞ በትግል ዘዴያቸው የብርሃንና የጨለማን ያክል ተለያይተው ይታዩ ነበር። ያሻው ዓይነት ውዥንብር ቢኖርም፣ ድንበሩ ግልጽ ነበር። ደግሞም፣ ሁሉም በየሰፈራቸው ውስጥ፣ ሁኔታው የፈቀደውን ያህል ውህደት፣ ትብብርና የአንድነት ስሜት ነበራቸው። ለየሰፈራቸው ከፍተኛ ወገናዊነት ያሳዩ ነበር።
ከዚህም ምክንያት የተነሳ ነው፣ እስከተባለው ጊዜ ድረስ አብዮትና ፀረ አብዮት ፊት ለፊት ተፋጥጠው በቀጥታ ይፋለሙ ነበር። ወዳጅና ጠላት፣ አብዮታዊና ፀረ አብዮታዊ፣ ይብዛም ይነስም ተለይተው ይታወቁ ነበር። ስለዚህም፣ የአብዮቱ ወገኖች ለአብዮታቸው ለመሟሟት ምንንም ያላስቀሩትን ያህል፣ ፀረ አብዮት ደግሞ ያልፈፀመው ድርጊትና ያልሸነቆረው ቀዳዳ አልነበረም። ፍልምያው ግልጽ እና አስደሳች ነበር።
ያ ወቅት ጥር 26.1969 ዓ.ም. በተወሰደው ፈጣንና አብዮታዊ ዕርምጃ ሲያከትም፣ የአብዮቱ ሰፈር ያለ ጥርጥር በአሸናፊነት ወጣ። አሸነፈ። ባጠቃላይ፣ ኢትዮጵያ ሀቀኛ ተራማጆች እንደ አንድ ሰው ቆመው በካሄዱት የጋራ ትግል፣ በእውነትም ሰፊውን ሕዝብና አብዮቱን ለማገናኘት ችለው እንደነበር የማይታበለው ሀቅ ነው። ይህንኑም፣ በጥርና በየካቲት 1969 ዓ.ም በሀገሪቱ በመላ የተደረጉት የድጋፍ ሰልፎች ሁሉ ይመሰክራሉ።
እንደዚሁም፣ በየካቲት/መጋቢት ወሮች የአብዮቱ ማጥቃት ይቀጥላል። በነዚህ ወሮች ውስጥ ተፈፅመው የነበሩት የወዛደሮችና የቀበሌ ማህበራት ነፃ እርምጃዎች፣ የመጋቢት “መንጠር ዘመቻ”፣ አብዮታችን ከውጭ ያገኛቸው ድጋፎች፣ የኢማሌድህ መመሥረት ….ወዘተ. ሁሉ የሚታወሱን ናቸው። ይሁንና፣ ከሚያዝያ/ግንቦት ወር ጀምሮ ደግሞ፣ አብዮታችን እንደገና ወደ ተከላካይነት ይመለሳል። እጅግ የተወሳሰበ ሁኔታ ይፈጠራል። ብዙ ነገሮች ይደርሳሉ። አያሌ ጥያቄዎች እየተነሱ ይወድቃሉ። እንደ እውነቱም ከሆነ፣ ነገሮች ሁሉ ከምንጊዜውም ይልቅ ያው ከዚያው በዚያው አብዮትና ፀረ አብዮት የሆኑት ፀረ አብዮት በአብዮት እና በሶሻሊዝም ስም በራሱ ሰፈር ውስጥ ማንሰራራት የጀመረው በተለይም ከተባለው ጊዜ ወዲህ ነው። አጠቃለን ለመግለጽ ብንሞክር፣ ከየካቲት/መጋቢት ወዲህ ያለውን ሁኔታ ዓይነተኛ የሚያደርጉት ጉዳዮችም በአንድ በኩል በአብዮት ሰፈር ውስጥ በአብዮት ስም በስፋት የሰረገው ፀረ አብዮትና፣ በሌላው በኩል ደግሞ፣ በውጭ እየተጠናከረና እየተራቀቀ የመጣው ፀረ አብዮት ናቸው።
በዚህ ጽሁፍ ውስጥ፣ ከመጀመሪያዎቹ ቀኖች ጀምሮ የደረሱትን ነገሮች በዝርዝር ማንሳቱ ጽሁፉን ያለ ቅጥ ያረዝመዋል። በተጨማሪ፣ በየጉዳዮች ላይ በየጊዜው መግለጫዎችን ማብራሪያዎችን ስለተሰጡ፣ በነርሱ ላይ እንደገና መመለሱ አስፈላጊ አይሆንም። ይሁንና ዋና ዋናዎቹን ጉዳዮች ለማስታወስ ያህል፣ የሚከተሉትን ልንዘረዝር እንችላለን።
– በጥር/የካቲት ኢማሌድህን ለመመሥረት ተጀመረው የነበሩት ውይይቶች።- በየካቲት ወር መጨረሻ ላይ የወጣው “የጋራ መግለጫ”። – በመጋቢት ወር የኢማሌድህ መመስረት። – የነጻ እርምጃዎች መፋፋም። – ሆኖም፣ በዚሁ ጊዜ ውስጥ በድርጅቶች መካከል ቅራኔዎች መፈጠር። -በተለይም በመኢሶን ላይ አያሌ የአሉባልታና የፈጠራ ክሶች መነዛት መጀመራቸው።- የ1969 ዓ.ም ሜይ ዴይ አከባበር። – ከዚያ በኋላ የደረሰው መካካድና በመኢሶን ላይ የተጀመረው ዘመቻ መባባስ። – እንደገና “ለመማማል በተጨማሪ ወኪሎችም ለረጅም ጊዜ የተደረጉት ስብሰባዎች። -“የመርሃ ግብር” ከዚያም “የድርጊት ፕሮግራም” መውጣት። -ሆኖም በመኢሶን ላይ የሚደረገው ዘመቻ አሁንም ተባብሶ መቀጠሉና….. ወዘተ. ሁሉ የነገሩን አንድ መልክ ያሟሉታል። ሁኔታውን ባንድ ቃል ለመግለጽ፣ በነዚያ ወራቶች ውስጥ “ህብረትና” ፀረህብረት በአንድ ቦታ /እዚያውም በዚያው/ ይሰሩ ነበር ልንል እንችላለን። በዚያም ሁኔታዎች ሁሉ ለሀቀኛ አብዮታዊያን ውስብስብና አስቸጋሪ እየሆኑ ሲመጡ፣ ለቀኝ አድርባዮችና ለአስመሳይ ተራማጆች ደግሞ አመቺ እየሆኑ ሄዱ። ፀረ አብዮት በአብዮትና በሶሻሊዝም ስም በራሱ በአብዮቱ ሰፈር ውስጥ መዳበር ይጀምራል።
በተጨማሪ፣ ፀረ አብዮት በሌሎች መስኮችም፣ በሌሎች ስፍራዎችም እየተጠናከርና እየተራቀቀ ይመጣል። የውስጡ ቡርቦራ፣ የውጭ ከበባ ከከፍተኛ ደረጃ ላይ ይደርሳል። በሰሜን በኤርትራና በጎንደር፣ በምስራቅና በደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያ፣ በሀረርጌ፣ በባሌና በሲዳሞ፣ ኢትዮጵያችንና አብዮታችን በፀረ አብዮት የጦር ኃይል ተወጥረው ይያዛሉ። በመሐል አገር የቢሮክራሲው አሻጥርና የኢሀአፓ ርሸና ይፋፋማሉ። አድርባይነት ይስፋፋል። በአጭሩ፣ የአብዮቱ ሰፈር በራሱ ውስጥ ባሉት ቅራኔዎች ጭምር አንገቱን ሲደፋ፣ ፀረ አብዮት እየተሰበሰበና እያዝገመገመ ይመጣል። ኢትዮጵያችንና አብዮታችን እጅግ አስጊ ከሆነ ሁኔታ ላይ ይወድቃሉ።
በዚህ ሁኔታ ውስጥ ተራማጆችና የአብዮቱ ኃይሎች ሁሉ እንዲሰበሰቡ መታገል ዋናውና ተቀዳሚው ተግባር በሆነ ነበር። ይሁን እንጅ፣ በሚያስደንቁ መንገዶች ይካሄዱ በነበሩት ዘመቻዎች ምክንያት በተቃራኒ በተራማጆች መካከል የተፈጠሩት ቅራኔዎች ይባባሳሉ። መኢሶን በዚህ ጊዜ፣ ያሰፈሰፈውን ፀረ አብዮት ለመከላከል እንዲቻል አያሌ ሀሳቦችን ቢያቀርብ /ስለትጥቅ፣ ስለ ሕዝባዊ ሠራዊት፣ ስለ ቢሮክራሲው፣ ስለብሄረሰቦች መብት፣ ስለዲሞክራሲ መብቶች፣ ስለነፃ እርምጃዎች…/፣ ሰሚ ጆሮ ያጣል። በጋራ ውይይት ስምምነት የተገኘባቸውም ጉዳዮች በሥራ ሳይተረጎሙ ይቀራሉ። መኢሶን ከነጭራሹ በጥርጣሬ ዓይን ይታያል። “በስልጣን ጥመኝነት” ይጠረጠራል፣ ይከሰሳል። መኢሶን የሚነዛበትን አሉባልታዎች ሃሰተኝነት በመግለፅ፣ በዚያን ጊዜ እንደሚባለው ‘እየማለ እየተገዘተ’፣ አያሌ መግለጫዎችን ቢያወጣ፣ ቢያስረዳ፣ ቢያስተባብል …ወዘተ እንደዚሁ ሰሚ ጆሮና ደጋግሞ የጠየቀውን “ገለልተኛ” ዳኛ ያጣል። በተቃራኒ አንዳንድ እርምጃዎች ተወሰዱበት። ከዚያም፣ አንድ እጅግ አሳሳቢ የሆነ ዜና ይደርሰዋል። እንደሚታወቀው፣ መኢሶንም የመጨረሻ መጨረሻ የትግል ስልት ለውጥ እንዲያደርግ ተገደደ።
መኢሶን በነሀሴ ወር 1969 ዓ.ም የትግል ስልት ለውጥ ሲያደርግ፣ ምክንያቶችን በሰሕድ ቁ.61 እና ከዚያ በኋላ ባወጣቸው ጽሁፎች አማካይነት ስላሳወቀ፣ በጉዳዩ ላይ እንደገና መመለስ አስፈላጊ አይሆንም። ደግሞ፣ ዛሬ ካንዳንድ አካባቢዎች እንደሚሰማው፣ ያ ዜና ምናልባት በአድሃሪዎች ሆነ ተብሎ የተተከለ ይሁን አይሁን የሚያረጋግጡ ሌሎች መረጃዎች የሉንም። የሆነው ሆኖ፣ በዚህ ጊዜ ውስጥ አድሃሪ የሲቪልና የሚሊታሪ ቢሮክራቶች፣ የቀኝ አደርባዮችና አስመሳይ ተራማጆች ቅራኔዎችን ለማፋፋምና የተሸነቆረውን አመቺ ቀዳዳ ለማስፋት ያልነከሱት አጥንት ያልለኮሱት እሳት እንዳልነበረ የማይካድ ጉዳይ ነው። ሆኖም ደግሞ፣ ኃላፊነት ያለባቸው ሰዎች ጭምር በአንፃሩ፣ ተራቅቆ በመጣው ፀረ አብዮት ላይ ነቅተው በህብረት ለመቆም አለመቻላቸው ደግሞ የዚያኑ ያህል ሀቅ ነው። እንደውም በተቃራኒ፣ ብዙዎች /አውቀውትም ይሁን ሳያውቁት/ በግለሰብና በድርጅት ደረጃዎች ጭምር የፀረ አብዮቱ ሴራና ተንኮል መስዋዕት ሳይሆኑ አልቀሩም። አንዳንዶች በዚያን ጊዜ በመኢሶን ላይ ያሳዩት የነበረው ጭፍን ጥላቻ እጅግ የሚያስገርም ነበር።
ይህ ሁሉ እንግዲህ እስከ ነሐሴ ወር 1969 ዓ.ም ድረስ ነበር።
ከዚህ ጊዜም በኋላ ቢሆን፣ አጠቃላዩን የሀገሪቱን የፖለቲካ ዓለም ዓይነተኛ አድርገውት የቆዩት ጉዳይ ከዚህ በላይ ያመለከትናቸው ናቸው። በተፋፋመ መልክ ይሁን እንጂ፣ ጠቅላላውን ሁኔታ ዓይነተኛ አድርገውት የቆዩት ጉዳዮች፣ በአንድ በኩል በአብዮቱ ሰፈር ውስጥ የተፈጠሩት ቅራኔዎች መካረርና መስፋት፣ በሌላ በኩል ደግሞ፣ የተጠናከረው ፀረ አብዮት መግፋትና ማየል ናቸው።
ከተራማጆች መካከል የተፈጠሩትን ቅራኔዎች በሚመለከተው በኩል፣ በመኢሶን ላይ የሚደረጉት የሀሰት ቅስቀሳዎች ተስፋፍተው ይቀጥላሉ። ለመኢሶን “ፈርጣጭ”፣ “ቀኝ መንገደኛ” ወዘተ… የሚሉ አዳዲስ ቅጽሎች ይወጣሉ። አያሌ የመኢሶን አባሎች፣ ወዳጆችና ደጋፊዎች በግልጽና በስውር ይረሸናሉ። አያሌ የድርጅቱ አባሎች፣ ወዳጆችና ደጋፊዎች በአዲስ አበባና በክፍላተአገር እስር ቤቶች ውስጥ ይወረወራሉ። በመኢሶን ላይ እጅግ ከባድ የሆነ የክትትል፥ የእስራትና የአፈና ዘመቻ ይካሄዳል።
ይሁንና፣ መኢሶን ይህ ሁሉ እየደረሰበትም ቢሆን፣ ከአቋሙ ዝንፍ አላለም። መኢሶን ዛሬም ቢሆን ለሀቀኛ ተራማጆች ህብረት በሚያደርገው ትግል እንደቀጠለ ነው። ዛሬም ቢሆን ደጋግሞ የሚያቀርበው ይህንኑ ጥሪ ነው። ጊ.ወ.አ ደርግን በሚመለከተው በኩል፣ የመኢሶን አቋም ዛሬም ቢሆን፣ “ሂስዊ ድጋፍ” የሚለው ነው። ስለ መኢሶን “የስልጣን ጥመኝነት” የሚነገሩት ነገሮች ሁሉ አነሰ ቢባል ዲማጎዢ ናቸው።
የሆነው ሆኖ፣ በተራማጆች መካከል የተፈጠሩት ቅራኔዎች እንደዚህ እየሰፉ ሲሄዱ፣ በአንጻሩ ደግሞ ፀረ አብዮት ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ከበባውን ያጠናክራል። በከፍተኛ ደረጃ ያጠቃል። በሰሜን፣ በምስራቅ እና በደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያ ብዙ ስፍራዎችን ይይዛል። በተለይም፣ በምስራቅ ኢትዮጵያ እስከ ሐረር ከተማ ተራሮችና አስከ ድሬዳዋ ሜዳዎች ድረስ ያለውን ሀገር በቁጥጥሩ ስር ያደርጋል። በመሐል ሃገርና በጦር ሜዳዎች ላይ ደግሞ፣የሲቪል ሚሊተሪ ቢሮክራሲ አሻጥሩን ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ያፋፍማል፣ ያስፋፋል። የኢህአፓ ርሸና እስከዚያ ጊዜና ድረስ ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ ደረጃ ሀገሪቱን ያጥለቅልቀዋል። [የማይነበብ-አዘጋጆች] ፀረ አብዮት ይንራል።
በነዚያ ወራቶች ውስጥ፣ በጦርነቱ ስፍራዎች የደረሱብን ጉዳቶች ከፍተኛ የነበሩትን ያህል፣ በመሃል ሀገርም አያሌ ጥቃቶች ይደርሳሉ። አያሌ ታጋዮች ይቀነጠሳሉ። የአብዮቱ ኃይሎችና ወገኖች፣ በጦርነቶቹ ቦታዎች ላይ እስከ የካቲት/ መጋቢት፣ በመሀል አገር ደግሞ እስከ ቀይ ሽብር መፋፋም ድረስ፣ በተከላካይነት ከመቆም በስተቀር አንዳችም ነገር ማድረግ ሳይችሉ ይቀራሉ። እጣቸው መርገፍ ብቻ ሆኖ ነበር።
ከየካቲት/መጋቢት 1970 ዓ.ም በኋላ፣ የአብዮት ሰፈር ወደ ማጥቃት ይሻገራል። በጥቂት ጊዜ ውስጥ አያሌ ድሎችን ይቀዳጃል። ከነዚህም ውስጥ በኢድህ “ነጭ ሰራዊት”፣ በሶማሌ ጦርና በኢህአፓ ላይ የተቀዳጃቸው ዋና ዋናዎቹ ናቸው። እንደዚሁም፣ አብዮታችን ከብቸኝነት መውጣቱና የአያሌ የሶሻሊስት አገሮችን ድጋፍ ለማግኘት መቻሉ ተጨማሪውና ወሳኝ ድል ነው።
በነዚህ ድሎች የማይደሰትና የማይኮራ አንድም ሃቀኛ ተራማጅ፣ አንድም እውነተኛ አገር ወዳድና ዲሞክራት የለም። በዚህም፣ በአብዮታችንና በሀገራችን ታሪክ ውስጥ አስጊና [የማይነበብ-አዘጋጆች] የነበረ አንድ ወቅት ያለፈ፣ ያከተመ ይመስላል።
ይሁንና፣ በመካከል የተፈጠሩ አያሌ ሁኔታዎች ደግሞ፣ እንድንጠነቀቅ ያሳስቡናል በድሎች ሜዳሊያ የገልባጭ ገጽታ ላይ የሚታዩትን አሳሳቢ ሁኔታዎች ባንክሮ መመልከት ያስፈልጋል። ድል አድርጊው ሰፊ ሕዝብ ተመልሶ የድሎቹ መስዋእት እንዳይሆን የሚያሰጋው መሆኑን የሚያመለክቱ አያሌ ሁኔታዎች አሉ። ከዚህ በታች ዋና ዋናዎቹን ብቻ እናመለክታለን፦
አንደኛ፣ በአጠቃላይ በአብዮቱ ሰፈር ውስጥ፣ በተለይም ተራማጆች መካከል ያሉት ቅራኔዎች እየከረሩ እንጅ እየለዘቡ እየሰፉ እንጂ እየጠበቡ አልመጡም። በዚህ አንጻር በመኢሶን ላይ ዛሬም ቢሆን በቀላሉ የማይገመቱ ዘመቻዎች እየተካሄዱ ናቸው። በመኢሶን ላይ ከባድ የሆነ ክትትል እስራት እየተፈጸመበት ነው። በአሁኑ ወቅት፣ መኢሶንን ለመምታትና ለማጥፋት አንዳች ዓይነት ያሰፈሰፈ ሁኔታ ያለ ይመስላል።
በተጨማሪ /የአምልኮ አነጋገር አይሆንብንና/ “ዓመቱን ጠብቆ” ደግሞ፣ በመኢሶን ላይ ይደረግ የነበረው ዓይነት ዘመቻ ዘንድሮ በኢጭአት ላይ ተጀምሯል። በኢጭአት ላይ የውግዘትና የውሳኔ ናዳዎች እየወረዱ ናቸው። ኢጭአት ባለፈው ወር መጨረሻ ላይ፤ ከህብረቱ መድረክ እንደ ታገደ የአደባባይ ሚስጥር ነው። ሌሎች፣ እኛ ዛሬ ልንተች የማንፈልግባቸው ቅራኔዎች፣ በኢማሌድህ አባል ድርጅቶች መካከልም እየታዩ ናቸው።
ለማንኛውም፣ በተራማጆች መካከል ያሉት ቅራኔዎች በሆነው ባልሆነው መክረራቸውና መስፋፋታቸው ለፀረ አብዮት እንጂ፣ ለአብዮቱ ሰፈር እንደሁ አንዳች ጥቅም አይኖራቸውም። እንደ እውነቱም ከሆነ፣ ነገሮች በዚህ ዓይነት ከቀጠሉ ደግሞ፣ በአብዮታችን ታሪክ ውስጥ “ጠላቶች” የሚባሉትን አብዝቶ የቆጠረውና ያመረተው “አብዮተኛ”፣ የአብዮቱ ኃይሎች ቅራኔዎቻቸውን በዲሞክራሲኣዊ መንገዶች አቻችለው በህብረት እንዲታገሉ የሚጥሩት ደግሞ “ፀረ አብዮተኛ” ተብለው ስፍራቸውን በጅምላ እንዳይቀያየሩ የሚያሰጋ ነው። ይህ እንግዲህ፣ አስደናቂው የስፍራ መቀያየር እስካሁን ድረስ ካልተከናወነ እንደሁ በማለትም ነው።
ሁለተኛ፣ በውነትም፣ “አስደናቂው” ሽግሽግ በመከናወኑ ሳይሆን አይቀርም፣ በዛሬው ወቅት ፀረ አብዮት የልቡን የሚሰራው በራሱ በአብዮቱ ሰፈር ውስጥ መሽጎና ተንሰራፍቶ ነው። በአብዮትና በሶሻሊዝም ስም እየፎከረ ነው።
በዚህም አንጻር፣ በአንድ ወገን የቀኝ አድርባይነትና አስመሳይ ተራማጅነቱ መረን ለቅቀው ተስፋፍተዋል። የማይናቁ የማጥቂያ ጣቢያዎችን ይዘዋል። በሌላ ወገን ደግሞ የአብዮት ሰፈር በሮች ለፀረ አብዮት ተበርግደው ተከፍተዋል። በዚህም፣ አድሃሪው የሲቪል ሚሊተሪ ቢሮክራሲ የንዑስ ከበርቴ መደብ ቀኝ ክንፍ አባሎች በመንግሥትና በኢማሌድህ ውስጥ ጭምር እንደልባቸው ገብተው ለመስፈር ችለዋል። በተጨማሪ ሚያዚያ፣1970 ዓ.ም በታተመው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ አንድ ገጣሚ “እንዴት ነው ነገሩ?” በማለት ጠይቆ እንዳለው፣ ፀረ አብዮት “ቀይ ባንዲራ በቅሎ/ የአብዮቱን ሰፈር/ በነጭ ጥይት እየተመታ”፣ እያጠቃ ነው። ስለዚህም፣
ሦስተኛ፣ ዛሬ በአብዮቱ ሰፈር ውስጥ ባንድ በኩል ከፍተኛ የሆነ ውዥንብር ሰፍኗል። አብዮትና ፀረ አብዮት የሚካለሉበት ድንበር ደብዛው ጠፍቷል። በሌላ በኩል ደግሞ፣ ሰፊው ሕዝብ በከፍተኛ ፍርሃት ተውጧል። “የነገሰው ሁሉ ንጉሳችን፣ የአበራ ሁሉ ፀሃያችን” እንደሚባለው እያለ ከነገሮች ሁሉ በመሸሽ ላይ ነው። የባሰ እንዳይመጣበት “ሁሉንም እሺ” ማለቱን መርጧል።
ነገር ግን፣ የዚያኑ ያህል ደግሞ አያሌ ቅራኔዎች በከተማም በገጠርም እየፈሉ ናቸው። ዛሬ በቀበሌ አመራርና በ‘ካድሬዎች’፣ በቀበሌ[1] ነዋሪዎችና በ‘ካድሬዎች’፣በሕዝባዊ ድርጅቶች ውስጥና በመካከላቸው፣ በኢማድህ አባል ድርጅቶችና በመካከላቸው፣ በሕዝባዊ ድርጅቶች አድሃሪ ቢሮክራሲ፣ በመለዮ ለባሹና በሚሊታሪው ቢሮክራሲ . . ወዘተ መካከል የፈነዱት ቅራኔዎች አንዳንዶቹ ናቸው። ደግሞም፣
አራተኛ፣ እነዚህ ሁሉ ቅራኔዎች ዞሮ ዞሮ ወደ መንግሥት ተንፀባርቀዋል። በመንግሥትና በሰፊው ሕዝብ መካካል ባሉት ቅራኔዎች ላይ ማህተማቸውን እየረገጡ ናቸው። አንዳንዶቹን ለማውሳት ያህል፣ በደርግና በሲቪል ሚሊታሪ ቢሮክራሲ ባንድ በኩልና በሰፊው ሕዝብ በሌላ በኩል፣ በመንግሥት የመጨቆኛ መሳሪያዎችና በሰፊው ሕዝብ፣ በመንግሥትና በብሄረሰቦች፣ በመንግሥትና በሕዝባዊ ድርጅቶች፣ በመንግሥትና በንግድ ቡርዥዋዚው… መካከል እየሰፉ የመጡትን ቅራኔዎች ለመጥቀስ ይቻላል። የነገሮቹ ሂደት በዛሬው መልኩ ከቀጠለ፣ የቅራኔዎቹ የሁለተኛ ደረጃነት ባህሪ እንዳይለወጥ የሚያሰጋ ነው። ለዛሬው ወቅት እነዚህን ቅራኔዎች ባንድ ወገን እየተሸፋፈኑ በሌላ ወገን እየሰፉ እንጅ፣ አብዮታዊ መልሶችን እያገኙ ሲፈቱ አይታይም። በተለይ፣ የሲቪል ሚሊታሪ ቢሮክራሲውን በሚመለከተው በኩል ደግሞ፣ የምናየው ከፊውዶ ቡርዧው ሥርዓት የተወረሰው ቢሮክራሲ እየተጠናከረና እየደለበ ሲሄድ እንጅ እየፈረሰ ሲሄድ አይደለም። ይህኛው ከሁሉም በላይ የሚያሳስበው ጉዳይ ሳይሆን አይቀርም።
በመጨረሻም፣ እነዚህ ሁሉ ውስብስብ ሁኔታዎች ላይ፣ አስቸኳይ መልሶችን የሚሹ አያሌ ጥያቄዎች ተደራርበው መጥተዋል። በዚህ አንጻር፣ በኢኮኖሚው በኩል ከዳር እስከ ዳር የተንሰራፋው የክሪዝና የትርምስ ሁኔታ አንደኛው አሳሳቢ ጉዳይ ነው። ሁለተኛ፣ በፖለቲካውም መስክ ቢያንስ የምስራቅ ኢትዮጵያና የኤርትራ ጥያቄ፣ የፊውዶ ቡርዧው ሥርዓት ቢሮክራሲ መደምሰስ ጥያቄ፣ የብሔረሰቦች መብት ጥያቄ፣ የብሄራዊ ነፃነታችን ጥያቄ፣ የዲሞክራሲ መብቶች ጥያቄ፣ የሀቀኛ ተራማጆች ህብረት ጥያቄ፣ የወዛደሩ ፓርቲ ጥያቄ ዋና ዋናዎቹ ናቸው። እነዚህ ሁሉ አስቸኳይ መልሶችን የሚጠይቁ ናቸው።
አጠቃላዩ የጊዜው ሁኔታ ከሞላ ጎደል አይነተኛ የሚሆነው፣ ከዚህ በላይ ባመለከትናቸው ፍሬ ነገሮች ነው። የአብዮታችን “ዕድል” የሚወሰነውም፣ ያነሳናቸው ጥያቄዎች ሁሉ እንደሚያገኙት መልስ ነው።
በእርግጥ ሁኔታው እጅግ ውስብስብ ነው። ተደራርበው የመጡት ጥያቄዎች አያሌ ናቸው። ከሁሉም በላይ ደግሞ፣በተራማጆች መካከል በዚህም በዚያም በሆነው ባልሆነው ተካርረው የመጡትን ቅራኔዎች በውይይትና በዲሞክራሲያዊ ዘዴዎች ለመፍታት እንዲቻል ገና አመቺ ሁኔታ የተፈጠረ አይመስልም። በመኢሶን በኩል ስህተቶች አሉ ቢባል እንኳ /ደግሞ ደፍሮ መኢሶንን አይሳሳትም የሚል የለም ይህ አይንቀሳቀስም ማለት ነው።/ ለሂስና ግለ ሂስ አመቺ ሁኔታ አልተፈጠረም። ስለ አጠቃላዩ አዝማሚያ የሚከተለውን ለመናገር ይቻላል።
ከዚህ በላይ እንዳልነው፣ የአብዮታችን ባህሪይ መቼው እዚያው በዚያው አብዮትና ፀረ አብዮት በሆነው መልኩ የሚገለጽ ነው። አዝማሚያውም እነዚህ ሁለት አግጣጫዎች ውጭ ያለ ነገር አይደለም። በዛሬው ወቅት እጅግ የሚያስደንቅ አኳኋን ለአብዮትም ለፀረ አብዮትም አመቺ የሆኑ ሁኔታዎች አሉ። ይሁንና፣ ወሳኝ ከሆነ የሽግግር ወቅት ውስጥ የገባን ይመስላል። ታሪክ ገና የመጨረሻ ፍርድዋን አልሰጠችም።
ያም ሆነ ይህ፣ ዛሬ ባለው አስጊና አሳሳቢ ሁኔታ፣ ወይ የአብዮቱ ሰፈር በአርቆ አስተዋይነትና ያለ ቂም በቀል ተሰብስቦ አንድ ወሳኝ እርምጃ ወደፊት ይራመዳል። አብዮታዊ መፈክሮቹን ወደ ተጨባጭ ድርጊቶች በመተርጎም አብዮቱን እና ሰፊውን ሕዝብ ያገናኛል። ወይ ደግሞ፣ በቦረቦረው ፀረ አብዮት ሴራ ጭምር አሁን በሚገኝበት ትርምስ ውስጥ ይቆይና፣ ፀረ አብዮት በበለጠ ጥንካሬና ስፋት ብዙ እርምጃዎችን የኋሊት ያስኬደዋል፣ ይወረውረዋል። በዚህ መካከል በአንዳንድ “የመስከን” ምልክቶች ልንዘናጋ አንችልም። አብዮት የማስከኛና የመደላደያ ወቅት እንዳለው ሁሉ፣ ፀረ አብዮትም በአብዮት አስመስሎ የተደላደለባቸውን ወይንም አያሌ የታሪክ ምሳሌዎች ልናስታውስ እንችላለን። ከንግዲህም፣ ወደ ርእሳችን እንመለስና፣ ዛሬ ባሉት ዋና ዋና የአብዮቱ ጥያቄዎች ላይ ያሉንን አስተያየቶች በዝርዝር እናስፍር። በቅድሚያ በመኢሶን ላይ በሚሰነዘሩት ሁለት ጥያቄዎች ላይ አንዳንድ ማስታወሻዎችን ብናመለክት የተሻለ ሳይሆን አይቀርም።
[1] “በቀበሌ ነዋሪ ሕዝብና በቀበሌ አመራሮች፥ በሠራተኛ ድርጅቶችና በ“ካድሬዎች”
3. በመኢሶን ላይ ስለሚቀርቡት “ሂሶች” ወይንም “ወቀሳዎች”
በዚህ ጽሑፍ ውስት በመኢሶን ላይ የሚደረጉ ዘመቻዎች ከወቅት ወደ ወቅት እንደምን እየተባባሱና እየከፉ እንደመጡ በአጭር ባጭሩ ጠቁመናል። በዛሬው ወቅትም ቢሆን፣ በመኢሶን ላይ የተጠናከረ ዘመቻ እየተካሄደ ነው። በክትትልና በእስራት… ወዘተ. የሚካሄዱትን ዘመቻዎች ወደ ጎን ብንተዋቸው እንኳ፣ ቅስቀሳዎቹ በቀላሉ የሚገመቱ አይደሉም። በተጨማሪ የሚያሳዝነው ነገር ደግሞ፣ ይህ ሁሉ የሚካሄደው መኢሶን ደጋግሞ “ውይይት” እያለ በሚጨቀጭቅበት ወቅት ነው። ለመወያየት እንዲቻል አያሌ ሙከራዎችን በሚያደርግበት ወቅት ነው።
አሁን፣ ባንዳንዶቹ ጥያቄዎች ላይ ያሉንን አስተያየቶች ስንገልጽም፣ ሌሎች አስተሳሰቦች እንዳይፈጠሩ እናስባለን።ይሁንና “ዝም” ማለቱ ደግሞ ጉዳት እንጂ ጥቅም አይኖረውም። መቼም “ሆድ ይቻለው” ከማለት መገላለጡ
3.1 ስለ መኢሶን “ፈርጣጭነት”
መኢሶን በነሀሴ ወር 1969 ዓ.ም የወሰደውን “የትግል ስልት ለውጥ” እርምጃ፣ ዛሬ የሚገለጸው “መፈርጠጥ” ከሚለው ግሥ በሚወርዱ እርባታዎች ነው። ነገር ግን ገለጻዎቹ ሁሉ የሚያተኩሩት፣ እስከዚህም መኢሶን “የትግል ስልት ለውጥ” በማድረጉ ላይ ሳይሆን፣ ይህንኑ እርምጃ በዚያ ሰዓት ከመውሰዱ ላይ ነው። በእርግጥ ደግሞ፣ መኢሶን በዚያ ሰዓት የወሰደውን እርምጃ፣ በዚያ ሰዓት ከነበሩት ሁኔታዎች ውጭ ካስቀመጥነው፣ እርምጃው “ፍርጠጣ” ይመስላል። ይሁንና፣ ነገሮችን በተከናወኑበት ሁኔታ ውስጥ አድርጎ መመርመርና መመዘን ደግሞ ማንም ማሌ የሚመራበት የትንተና ዘዴ ነው። ስለዚህ በዚያን ሰዓት የነበሩትን ሁኔታዎች እንደገና እንድናስታውስ የግዴታ መገፋፋታችን አይቀርም። እርግጥ መኢሶን ዛሬም ነገሮቹን ሊመለከታቸው የሚችለው፣ መኢሶን በዚያን ሰዓት የነበሩትን ሁኔታዎች በዚያ ሰዓት እንደተረዳቸው ነው። እንግዲህ በጥያቄ መልክ እንመለስባቸው።-
ሀ. የተራማጆችን ህብረት በሚመለከተው በኩል
- – መኢሶን ከጥር/የካቲት 1969 በፊት ጀምሮ የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማበረከት ከልቡ አልሰራም ወይ?
- – ከየካቲት/መጋቢት በኋላ በመኢሶን ላይ አያሌ አሉባልታና የፈጠራ ክሶች አልተነሱም ወይ?
- – መኢሶን: አሉባልታዎቹንና የፈጠራ ርዕሶቹን ለማስተባበል አያሌ ሙከራዎችን አላደረገም ወይ?
- – በጋራ ኮሚቴዎች አማካይነት መፍትሄዎችን ለማግኘት ብዙ ውይይቶችና ብዙ ውሳኔዎችን ተላልፈው አልነበረም ወይ?
- – ሆኖም ውሳኔዎቹ በሥራ ሳይተረጎሙ አልቀሩም ወይ?
- – ይልቁኑ በመኢሶን ላይ የሚደረጉት ዘመቻዎች ተባብሰው አልቀጠሉም ወይ?
- – “በጋራ መግለጫ” ላይ ስምምነት የተደረሰባቸው ጉዳዮች /ለምሳሌ፣ ዲሞክራሲያዊ መብቶች/፣ በኋላ “ድርጊት ፕሮግራም” ላይ ሲደርስ ውኃ አልተከለሰባቸውም ወይ? የዲሞክራሲያዊ መብቶች ጥያቄ “ከድርጊት ፕሮግራምና ከጋራ መግለጫ” በፊት፣ በታህሳስ ወር 1968 ዓ.ም ለህ.ድ ጽ/ቤት አባልነት ቃለ መጠይቆች ሲደረጉ ስምምነት የተደረሰበት ጉዳይ አይደለም ወይ?
- – በመጨረሻም፣ በሐረርጌ፣ በጅማና በአዲስ አበባ አያሌ የመኢሶን አባሎች ወዳጆችና ደጋፊዎች በሆነው ባልሆነው አልታሰሩም ወይ?
ለ. የ1969 ሜይ ዴይን በሚመለከተው በኩል
- – እያንዳንዱ የህብረቱ አባል ድርጅት የራሱን አርማና የህብረቱን መፈክሮች ይዞ እንዲመጣ በቅድሚያ የተደረገ ስምምነት አልነበረም ወይ?
- – የበአሉ ዕለት “መኢሶን ፓርቲያችን ነው”፣ “መኢሶን አስታጠቀን” የሚሉ አንዳንድ “ኩነቶች” ባልነቁ ደጋፊዎችም ይሁን በጠብ አጫሪዎች ቢለፈፍ፣ መኢሶን በገሃድ አቋም አልወሰደም ወይ?
ሐ. አድሃሪውን ቢሮክራሲና የኢህአፓን ነጭ ሽብር በሚመለከተው በኩል
- – የሲቪል/የሚሊቴሪ ቢሮክራሲ እንደዚያ በተስፋፋበት በዚያ ወቅት በቢሮክራሲ ላይ የሚደረገው ቅስቀሳ እንዲቀዘቅዝ በልዩ ልዩ ግልጽ እና ስውር መንገዶች አልተገደበም ወይ?
- – እንደውም የለየላቸውና የታወቁ አድሃሪ ቢሮክራቶች በሹመት ጥሪ ቁልፍ ቦታዎችን አልያዙም ወይ?
- – የኢህአፓ ርሸና በተለይ በሰኔ /ሐምሌ/ ነሐሴ ወሮች ውስጥ እጅግ ተፋፍሞ አልመጣም ወይ?
- – መኢሶን በዚህ ሰዓት ደጋግሞ ያሰማው “የነፃ እርምጃ” ጥያቄ ጩኸት ሆኖ አልቀረም ወይ?
- – በየካቲት/መጋቢት 1969 በነበረው የሰፊው ሕዝብ ነጻ እርምጃ ላይ ገደብ አልተጣለም ወይ? በሰኔ /ሐምሌ/ ነሐሴ ወሮች ውስጥ፣ የህ.ድ.ጽ/ቤት ወደ “ቀብር አደራጅ ጽ/ቤት” ለመቀየር ምን ያህል ቀርቶት ነበር።
መ. የሶማሌን ወረራ በሚመለከተው በኩል
- – የሶማሌ ሰርጎ ገቦችን መምጣት አድሃሪው ቢሮክራሲ ሲሸፋፍን፣ የሐረር – ሲዳማ አርሶ አደሮች አዲስ አበባ ድረስ በመምጣት አላመለከቱም ወይ? “ትጥቅ ትጥቅ” እያሉ ድምፃቸውን አላሰሙም ወይ?
- – መኢሶን ገና በጥር/የካቲት 1969 በሶማሌ ሰርጎ ገቦች ላይ አስቸኳይ እርምጃ እንዲወሰድ አልወተወተም ወይ?
- – የደቡብ ገበሬዎች ባስቸኳይ ታጥቀው ሰርጎ ገቦችን ለመቋቋም እንዲዘጋጁ አልወተወተም ወይ?
- – በዚህ አንጻር፣ ባጋጣሚ ካጠገባችን ያገኘነውን አንድ ገሃድ ፅሑፍ ለመጥቀስ ያህል፡-
“…ከሱማሊያ የሚመጡት ሰርጎ ገቦች በዘመናዊ የጦር መሳሪያ የታጠቁ ናቸው። እንዲያውም፣ በጠረፍ ያሉትን ብሔረሰቦች የሚያወናብዱበትና ከፀረ አብዮት ሰፈር የሚያስገቡበት ‘እኛ ዘመናዊ መሳሪያ እናስታጥቃችኋለን። አዲስ አበባ ያለው የአማራ መንግሥት ግን ስለማያምናችሁ አያስታጥቃችሁም’ የሚል ፕሮፓጋንዳ ይነዛሉ። በተለይም ጠባብ ብሄረተኝነትን በማባባስ አንዳንድ ቡድኖች ‘በነፃ አውጪነት’ ስም እየሰረጉ ናቸው።”
“…ከሚነዙት አድሃሪ ፕሮፖጋንዳ አልፈው የሚቃወማቸውን ይገድላሉ። ለደጋፊዎቻቸው ደግሞ መሳሪያ በገፍ ከማስገባት አይመለሱም። ከዚህም የተነሳ የጭቁን ብሄረሰቦች ሰፊ ሕዝብ፣ የታጠቀውን ሰርጎ ገብ በመፍራት በዝምታ የሚመለከትበት ወይም በገቢር የሚተባበርበት ደረጃ ላይ ደርሷል። ሰርጎ ገቦችን ለመቋቋም ጭቁን አርሶ አደሮችን ማስታጠቅ እጅግ አጠዳፊ ነው። መንግሥት የማስታጠቁን ጉዳይ ጨርሶ በቸልታ ሊያልፈው የማይችልበት ሁኔታ ላይ ደርሷል። ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ባጣዳፊ እርምጃ ከወሰደ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሰርጎ ገቦችን ሴራ ለማክሸፍ ይቻላል።
/አዲስ ፋና መጽሄት፣ የካቲት 1969 ዓ.ም ገጽ 29-30/
-ይሁንና፣ በተቃራኒ ጉልተኞች ታጥቀው በተለይ በሐረርጌ ገበሬዎች ላይ ብዙ ጉዳቶችን አላደረሱም ወይ?
-ዘመቻው ሲዘጋጅ፣ መኢሶን “ቢሮክራሲ አያዝምት – ይዘመትበት” እያለ ድምጹን አላሰማም ወይ?
የህብረቱ አባል ድርጅቶች በጋራ የሚያዋጧቸው ካድሬዎች ወደ ጦርነቱ ስፍራዎች እንዲላኩ ደጋግሞ ሀሳብ አላቀረበም ወይ? መኢሶን በበኩሉ ከ200 የማያነሱ ጓዶችን ለማቅረብ ዝግጁ መሆኑን ደጋግሞ አላሳወቀም ወይ?
ሠ. አለም አቀፋዊ ድጋፍን በሚመለከተው በኩል
-መኢሶን በራሱ አነሳሽነት፣ ሆኖም በጊ.ወታ.አ.ደ ድጋፍና እርዳታ፣ “የወዳጅነትና የሰላም ኮሚቴን” አቋቁሞ የኮሚቴው/አባሎች የድርጅቱ አባሎች ብቻ አልነበሩም/። አለም አቀፋዊ የፖለቲካ ድጋፎችንና ማቴሪያላዊ ዕርዳታዎችን ለመሰብሰብ አልተሯሯጠም ወይ?
-ይህንኑ ለማስፋፋት ሌሎች የወዳጅነት ኮሚቴዎች /ለምሳሌ፡-“የኢትዮ-ጀርመን ዲሞክራቲክ ሪፑብሊክ፣”፣ “የኢትዮ-ሕዝባዊት ዲሞክራሲያዊት የመን ሪፑብሊክ”…./እንዲቋቋሙ አልሠራም ወይ?
-ሆኖም፣ በዚያ ሰዓት በመኢሶን ላይ በነበሩት የጥርጣሬ አስተያየቶች ምክንያት አያሌ መሰናክሎች ተፈጥረው አልነበረም ወይ?
ወዘተ።
ከዚህ በላይ ያቀረብናቸውን ጉዳዮች እንደገና የተመለስንባቸው፣ መኢሶን በዚያ ሰዓት ያቀረባቸውን አንዳንድ ጥያቄዎችና የወሰዳቸውን አቋሞች እንደገና ለማውሳት እንጂ፣ እንደዚህም በዚያ ሰዓት የነበረውን የፖለቲካ አካባቢ እንደገና ለማስታወስ እንጅ፣ ክሬዲቱ ሁሉ የመኢሶን ነው…. ወዘተ ለማለት አይደለም። መኢሶን የዚህ ዓይነቱን አስተሳሰብ ፈጽሞ ቦታ አይሰጠውም። አይቀበለውም።
ይሁንና፣ ይህን ክፍል ከመጨረሻችን በፊት ደግሞ፣ በዚያ ሰዓት በነበረ አንድ ሁኔታ ላይ እንደገና መመለሱ አስፈላጊ ሳይሆን አይቀርም። ይህም፣ በዚያ ሰዓት ከአንዳንድ አቅጣጫዎች ለመኢሶን የደረሰውን አሳሳቢ ዜና የሚመለከተው ጉዳይ ነው። ዜናው ባጭሩ፣ “በህጋዊ መስክ ላይ የሚገኙትን የመኢሶን አባሎችን አንድ በአንድ ረሽኖ ለመጨረስ በለየላቸው አድሃሪዎች የተወጠነና የበሰለ ሴራ እንዳለ” የሚገልጽ ነበር። በእውነትም ደግሞ፣ በዚያ ሰሞን የተካሄዱት ርሸናዎች እጅግ ግራ የሚያጋቡ ሁነው ነበር። ዜናውም ያለማቋረጥ ይመጣ ነበር።….ያም ሆነ ይህ፣ መኢሶን በዚያ ሰዓት የመጨረሻ መጨረሻ “የትግል ስልት ለውጥ” /ማለትም “አንዳንድ አባሎቹን ወደ ህቡዕ የትግል መስክ ማዛወር”/ እንዲያደርግ የተገደደው በተለይም በዚህ ምክንያት ሆነ። ከነጻ እርምጃ በስተቀር ሌላ መከላከያ አልነበረውም። ደግሞ በዚያ ሰዓት “አልተፈቀደም” ነበር።
እንግዲህ ከእነዚህ ሁሉ ሁኔታዎች በኋላ፣ በመጨረሻ፣ ለማለት የሚቻለው ነገር “ቢሆንም በዚያ ሰዓት” ነው።መኢሶንን ይህንን ጥያቄ በዚያን ሰዓት “ስለዚህም አንዳንድ ለጥቃት የተጋለጡትን አባሎቹን ወደ ህቡዕ የትግል መስክ ማዛወር በሚል መልሶታል። ይሁንና ከዚህ ጊዜም በኋላ ቢሆን፣ መኢሶን አብዮታችንን፣ የሀገራችንን ህልውና፣የተራማጆችን ህብረትና ጊ.ወ.አ ደርግን በሚመለከቱት ጥያቄዎች ላይ ከነበር አቋሞቹ ዝንፍ አላለም። ይህ እንግዲህ፣ምንም እንኳ ከዚያ ጊዜ በኋላ አያሌ ጥቃቶች ቢደርሱበትም ማለት ነው። ይህ እንግዲህ፣ ምናልባትም ላይ የጠቆምነውን የሚያረጋግጡ ጭፍንና ግፍ የተሞላበት የጭቆናና የርሸና እርምጃዎች “ህቡዕ በተዛወሩ” ግንባር ቀደም የመኢሶን ጓዶችና አያሌ ደጋፊዎች ላይ ተወስዶም ማለት ነው!!
3.2 ስለ መኢሶን “ቀኝ መንገደኝነት”
ይህ ጥያቄ መቼም በመጀመሪያ ደረጃ የቲኦሪ ጥያቄ ነው። እንደሚገባን ከሆነ፣ መኢሶን “ቀኝ መንገደኛ” የሚባለው በመሰረቱ “የዲሞክራሲ መብቶችን ጥያቄ አለጊዜው አነሳ” በሚል ነው። ይህ ከሆነና “ግራ መንገደኛ” የሚባል ነገር ካለ፣ መኢሶን “ግራ መንገደኛ” እንጅ፣ “ቀኝ መንገደኛ” በሚል “አርእስትና መነሳት” አልነበረበትም። ይህም እንግዲህ፣ ጥያቄው “ጊዜያዊ ነው፣ ጊዜያዊ አይደለም” “አብዮታዊ ነው፣ አብዮታዊ አይደለም”…. ወዘተ የሚሉትን ጥያቄዎች ሁሉ ወደ ጎን ትተንም ማለት ነው።
እንደዚሁም፣ “የዲሞክራሲ መብቶች ጥያቄ የመንግሥት ስልጣን ጥያቄ ነው” በሚል አሳሳች ታውቶሎጊ፣ መኢሶንን “በዲሞክራሲ ሰም ለስልጣን እንደሚቋምጥ” ድርጅት አድርጐ ለማቅረብ ከተፈለገ፣ መኢሶንን አሁንም “ግራ መንገደኛ” አንጅ “ቀኝ መንገደኛ” በማለት ለመሰየም አይቻልም። ምክንያቱም፣ ተቺዎቹ መኢሶንን በሚመለከተው በኩል ሁለቱን ጥያቄዎች አያይዘው ሲተቹ እንደሚሰማው ከሆነ፣ መኢሶንን ከበስተግራው እንጅ ከበስተቀኝ ሊያስቀምጡት አልቻሉም።*[1]
በተጨማሪ፣ ለማለት የሚቻል ነገር ቢኖር፣ “ቀኝ እና ግራ መንገደኝነት ዞሮ ዞሮ አንድ ናቸው” ብቻ ነው። ይህ ሃቅ ግን፣ “ልጁን በስሙ ከመጥራት” የሚያግድ ነገር አይደለም። እንዲያውም ነገሮች ግልፅ የሚሆኑት እንደርሱ ሲሆን ነው። ብቻ የትኛው?
በተረፈ የመኢሶንን “ቀኝ መንገደኝነት” ለማሳመን፣ ከዲሞክራሲያዊ መብቶች አንስተው ባሉት ጥያቄዎች ላይ ሁሉና በመኢሶን አቋሞች ላይ መመለስ ያስፈልጋል። አንድ በአንድ ግራና ቀኙን መለየት ያስፈልጋል። አንደዚሁም፣ በየደረጃው የመኢሶን አቋም እንደሚነገረው ነው ወይንስ “ላስቲኩ ከአቅሙ በላይ ተስቧል” የሚለውን ጥያቄ ማቅረብ ተገቢና የመጀመሪያው ተግባር ነው ብለን እናምናለን።
በመጨረሻ በዚያ ሰዓት “የትግል ስምምነት ለውጥ” በማድረጉ “ቀኝ መንገደኛ” የሚባልም ከሆነ፣ ተመልሶ በዚያ ሰዓት የነበረውን የፖለቲካ አካባቢና መኢሶን በዚያ ሰዓት ይገኝ የነበረበትን ሁኔታ መገምገም ሊያስፈልግ ነው። ይህ ደግሞ በ3.1 ሥር ወዳቀረብናቸው ጥያቄዎችና መልሶች ይመልሱናል። “በዲሞክራሲ መብቶች ጥያቄ” ላይ ያሉት አቋሞች በ4.7 ሥር ተመልክተዋል።
ከእንግዲህም ወደ ዝርዝር የጊዜው ጥያቄዎች እንመለስ እና በእነርሱ ላይ ያሉንን አቋሞች አንድ በአንድ እንግለፅ።
[1] *ደግሞ አይችሉምም
4. ጊዜያዊ ጥያቄዎችና አቋማችን።
ከዚህ በላይ እንዳመለከትነው፣ በዛሬው ወቅት ያሉት ጥያቄዎች አያሌ ናቸው። ውስብስብ ናቸው። አብዮታችን እንደ ዛሬውም ጊዜ በተደራረቡ ጥያቄዎች ተጭኖ አያውቅም። ይሁንና፣ በጥያቄዎቹ ላይ አንድ በአንድ ከሄድንባቸው ደግሞ፣ለአብዛኞቹ ጥያቄዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ መልሶችን ለመስጠት እንደሚቻል እምነታችን ነው። ከሁሉም በፊት የችግራችን ሁሉ ቁልፍ የተራማጆች ህብረት ነው ብለን እናምናለን።
4.1 የተራማጆች ህብረት ጥያቄ
በኢትዮጵያ አብዮት ታሪክ ውስጥ የኢማሌድህ መመስረት አንደኛው ታላቅ ድል ነው። የአብዮታችን “ዕድል” የሚወሰነው፣ በዚህ ድርጅት ጥራት፣ ጥንካሬ እና ድርጅቱ ለአብዮቱ ካለው ታማኝነት ነው ብንልም ማጋነን አይሆንም።ጊዚያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ይህንን ድርጅት ለመንከባከብ ያለበትም ኃላፊነት በቀላሉ የሚገመት አይደለም።
ኢማሌድህ ሲመሠረት፣ ከዚህ በላይ የተነገረውን ያልተገነዘበ አንድም ሀቀኛ ተራማጅ አልነበረም። ሁላችንም ፈንጭተን ነበር። አድሃሪን ደግሞ የዚያኑ ያህል “የቀዘነች ፍየል” መስለው ነበር።
ይሁንና፣ ድርጅቱ “ከጋራ መግለጫ” እስከ “ድርጊት ፕሮግራም” ድረስ ባደረገው ጉዞ በአያሌ እንቅፋቶች ተወጥሮ ተያዘ።አያሌ ነገሮችም ደረሱ። ኢማሌድህ፣ በሌኒኒን ቋንቋ “በጨቅላነት በሽታዎች” ተለከፈ፣ ተጎሳቆለ፣ ተሰቃየ።
ነገር ግን ለአብዮታችን መግፋት የተራማጆች ህብረት መኖር፣ የህብረታቸው ጥራትና ጥንካሬ በምንም ዓይነት ሊፋቅ የማይችለው ጉዳይ ነው። ስለዚህም፣ ካለፉት ጥንካሬያቸው እና ደካማቸው ተገቢ ትምህርቶችን ቀስመው በህብረት ለመራመድ ምንጊዜም መታከት የለባቸውም እንላለን።
ከዚህ አንጻር፣ መኢሶን ካለፉት ጊዜዎች የቀሰማቸውን ትምህርቶች ለመጠቆም ብንሞክር የሚከተሉትን ለመዘርዘር እንችላለን።-
- በቅድሚያ የአድሃሪዎችን ሴራ መጠርጠር
- የአድሃሪዎችን ጥቃት በህብረት መከላከል
- አሉባልታዎችንና የፈጠራ ወሬዎችን በእንጭጩ መቅጨት
- ነገሮችን ከአቅማቸው በላይ አተልቆ ወይም አሳንሶ ከመመልከት መቆጠብ
- ግልጽ፣ ቅን፣ ዲሞክራሲያዊ ውይይቶች እንዲካሄዱ ማበረታታት
- ሂስና ግለ ሂስ በየጊዜው እንዲካሄዱ ማድረግ
- በጥፋቶች ላይ ጓዳዊ መወቃቀስ እንዲኖር ማድረግ
- በሆነው ባልሆነው መወነጃጀልንና ስሜተኝነትን መታገል
- ወንድማማችነት፣ ጓዳዊነትና መተማመን እንዲሰፍኑ መታገል
- የራስን ቤት በውስጥ የርዕዮተ- ዓለማዊና የፖለቲካ መስመር ትግል ማፅዳት
- ስህተቶችን መቀበልና ማረም
- ሁሉንም ነገር ለአብዮቱ መስጠት
እነዚህ መኢሶን የቀሰማቸው ትምህርቶች ጥቂቶቹ ናቸው። መኢሶን እነዚህንና ለወደፊት የሚቀስማቸውን አያሌ ትምህርቶች ይዞ፣ ምንጊዜም ቢሆን ሀቀኛ፣ ታጋይ፣ አብዮታዊና ዲሞክራሲያዊ ለሆነ የተራማጆች ህብረት ይታገላል።ዛሬ በመኢሶንና በሌሎች ተራማጅ የፖለቲካ ድርጅቶች መካከል ያሉትን ቅራኔዎች በውይይትና በዲሞክራሲያዊ ዘዴዎች ሊፈቱ የሚችሉ ናቸው ብሎ ያምናል። ለዚህ አብዮታዊ ተግባር ግን፣ የመጀመሪያው እርምጃ ለመወያየት እንዲቻል አመቺ የሆኑ ሁኔታዎች መፍጠር ነው። መኢሶን በዚህ በኩል ያሉትን አስተሳሰቦች ቀደም ሲል አብዮታዊ ሰደድ፣በዚያውም ለጊ.ወ.አ.ደ ሊቀመንበር እንዲደርስ አድርጓል። ይሄኛውም ጽሁፍ ደግሞ ከሚመለከታቸው ኃይሎች ጋር በሞላ ለውይይቱ ይረዳል ብሎ ያምናል።
4.2 የምስራቅ ኢትዮጵያ ጥያቄ
በምስራቅ ኢትዮጵያ የሱማሌ መንግሥት የከፈተብን ጦርነት፣ በኢትዮጵያ ሕዝቦች ድል አድራጊነት አክትሟል። አስደሳቹ ድል፣ በኢትዮጵያ ሕዝቦች የትግል ታሪክ ውስጥ ከፍተኛና ወሳኝ ስፍራ እንደሚኖረው የሚያጠራጥር አይደለም።
ይሁን እንጂ፣ በዚያ አካባቢ ዛሬም ቢሆን አያሌ ችግሮችና ጥያቄዎች አሉ። ችግሮችና ጥያቄዎቹ በጦርነቱ ምክንያት የደረሱትን አያሌ ጉዳቶች ከመጠገን ከሱማሊያ መንግሥት ጋር እስከሚኖሩ የወደፊት ግንኙነቶች ድረስ የሚዘልቁ ናቸው። የመኢሶን አቋም እንደሚከተለው ነው።
– ከሶማሊያ ጋር የሚኖረን ግንኙነት በሚመለከተው በኩል፣ ጊ.ወ.አ.ደ ይህንኑ በማስመልከት የሚወሰደውን አቋም እና መግለጫ መኢሶን ሙሉ በሙሉ ይደግፋል፣ ለዚሁም ይታገላል።
– በጦርነቱ ምክንያት የደረሱትን ጉዳቶች ለመጠገን በሚደረገው ጥረት መኢሶን ሙሉ በሙሉ ይሳተፋል። ባሁኑም ወቅት ቢሆን፣ በቅስቀሳና በተጨባጭ ድርጊቶች ባሉት መንገዶች ሁሉ የአቅሙን እያበረከተ ነው ።
– እንደዚሁም የሱማሌ ሰርጎ ገቦች ዛሬም የሚፈፅሙትን የሽምቅ ጦርነት ለመከላከል በሚደረገው ትግል ባሉት መንገዶች ሁሉ ተሰልፎ ከመታገል ወደኋላ አይልም። ካድሬዎችንም አዋጥቶ ለማሰለፍ ዝግጁ ነው።
– በመጨረሻም፣ በዚያ አካባቢ ያሉ የአስተዳደርና የብሔረሰቦች ጥያቄዎች ሁሉ ፖለቲካዊና ዲሞክራሲያዊ መልሶችን እንዲያገኙ ይታገላል።
4.3 የደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያ ጥያቄ
በደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያ /ባሌ- አርሲ- ሲዳሞ/ ያሉት ችግሮች በመሰረቱ ከብሄረሰቦች ጥያቄ የሚመነጩ ናቸው። በነዚህ ክፍሎች ውስጥ በእርግጥ የሱማሌ መንግሥት መሣሪያዎች የሆኑ የሀገሮቹ ተወላጆች አሉ። የለየላቸው የፊውዳል ጦር ጌቶችም በአካባቢው ይፈነጫሉ። የተቀሩት በግርግር በመከበር ላይ ያሉ ተራ ባንዲቶች ናቸው። ነገር ግን ሕዝቡ፣ በምንም ዓይነት ቢሆን የሱማሌን ወይንም የሱማሌን ቡችሎች የበላይነት የሚቀበል አይደለም። ሆኖም፣ በብሔረሰቡ ጥያቄዎች ላይ ደግሞ በቀላሉ ተስቦ የለየላቸው አድሃሪዎች መሳሪያ ሊሆን ይችላል።
መኢሶን ባደረገው ጥናት፣ እነዚህ አካባቢዎች በተጠናከሩ ካድሬዎች[1] አማካይነት ስፋት ያላቸው የፖለቲካ ሥራዎች ከተሰሩ ብዙ እርምጃዎችን ወደፊት ለመራመድ ይቻላል። በተለይም ደግሞ፣ እዚያው በስፍራው ተገኝቶ ለብዙዎቹ “ጥቃቅን” ለሚመስሉት ጥያቄዎች መልሶችን መስጠት ያስፈልጋል። አድሃሪ አስተዳዳሪዎችን ማንሳትና እነዚህን ከተቻለ በሀገሬው ተወላጆች፣ ያለዚያም የብሄር ትምከተኝነት ባልተቆራኛቸው መተካት ያስፈልጋል። ትምህርት ቤቶችን የህክምና ድርጅቶች ወደዚያ አካባቢ እንዲያተኩሩ አንዳንድ እርምጃዎችን መውሰድ ያስፈልጋል። በተጨማሪ፣ በብሔረሰቦቹ መካከል ያሉትን የድንበር ክርክርና ግጭቶች ለማስተካከልና የተጠናከረ የፖለቲካ እርምጃ መወሰድ ይኖርበታል።
እነዚህ የጠቆምናቸው እርምጃዎች ባጭር ጊዜ ውስጥ ሲታይ በአካባቢው የፖለቲካ መረጋጋትን ሊያስገኙ የሚችሉ ናቸው። በተጨማሪ፣ በአካባቢው የነገሱትን የፊውዳል- ጦር – ጌቶችና ተራ ባንዲቶች ለመቋቋም የሚያግዙ ናቸው።ይሁንና፣ በረጅሙ ጊዜ ግን፣ የብሄረሰቦች ጥያቄ መልስ እስካላገኘ ድረስ፣ ሁኔታው አሳሳቢ ሆኖ እንደሚቆይ ጥርጥር የለውም።
4.4 የኤርትራ ጥያቄ
የኤርትራ ጥያቄ በመሠረቱ ግንቦት 6/1968 ዓ.ም በወጣው ባለዘጠኝ ነጥብ የፖሊሲ ውሳኔ የፖለቲካ መልስ ተሰጥቶበታል። መኢሶንም በመሠረቱ የሚደግፈው እሱኑ ነው። ይሁንና “የፖሊሲው ውሳኔ” የቱን ያህል በሥራ ላይ እንደዋለ ለማወቅ አስቸጋሪ ነው። ችግሮቹም ለሕዝብ በይፋ አልተገለፁም። ያም ሆነ ይህ፣ ዛሬም ቢሆን ለኤርትራ ጥያቄ ያለው መልስ ወታደራዊ የሆነውን ያህል ፖለቲካዊ፣ ፖለቲካዊ የሆነውን ያህል ወታደራዊ እንደሆነ መኢሶን ያምናል። ዋናው ነገር፣ በሁለቱ እርምጃዎች መካከል ያሉትን ዳይሌክቲካዊ ግንኙነቶችና እድገት መጠበቅ ነው እንላለን። በኛ እምነት ዛሬ ባለው የውስጥና የውጭ ሁኔታ ከመገንጠል መስተቀር በኢትዮጵያ የግዛት አንድነት ውስጥ ማንኛውም የፖለቲካ መፍትሄ ጠቃሚና አብዮታችንን የሚያግዝ ነው። ወታደራዊ መፍትሄ ብቻ ግን፣ አብዮታችንን ዛሬ ለመገንባት ከማንችለው አደጋ ላይ ሊጥለው ይችላል።
4.5 የብሄረሰቦች ጥያቄ
በዚህ ጥያቄ ላይ በመኢሶንና በሌሎች ድርጅቶች መካከል ያሉት ልዩነቶች የታወቁ ናቸው። ልዩነቶች የቲኦሪና የፕራክቲስም ጭምር ናቸው። በዚህም ጽሁፍ ውስጥ እንደገና አንመለስባቸውም።
የሆነው ሆኖ፣ በዛሬው ወቅት ደግሞ የብሄረሰቦች ጥያቄ እየገፋ እንደመጣ የማይካደው ሀቅ ነው። በኤርትራ፣ በትግራይና በአፋር ከሚታወቁት የብሄረሰብ እንቅስቃሴዎች በተጨማሪ በተለይም በደቡብ ክፍላተ ሀገር ያሉት ብሄረሰቦች /አርሲ፣ ጉጂ፣ ሲዳማ፣ ወላይታ፣ ከምባታና ሃዲያ የወለጋ፣ የኢሊባቡርና የከፋ ሕዝቦች…./ በብሄረሰቦቻቸው ጥያቄዎች አካባቢ እየተሰበሰቡና እየተደራጁ ናቸው። ይህ ጉዳይ አስቸኳይ ተግባራዊ መልሶችን የሚጠይቀውን ያህል፣ “ጠባብ ብሄርተኝነት” በሚል ብቻ ወደ ጎን ተገፍቶ ለመቆየት የሚችል አይደለም።
መኢሶን በዚህ ጥያቄ በኩል፣ ተግባራዊ መልሶች ይሰጡ ይላል እንጅ፣ “አማራጭ የሌለው ተግባራዊ መፍትሄ ይህኛው ብቻ” ነው የሚለው ነገር የለውም። በመኢሶን እምነት፣ መፍትሔው እንደየሁኔታው ቢሻው የላላ ወይንም የጠበቀ ኮንፌዴሬሽን[2] ቢሻው አውቶኖመስ ሬጅን፣ ቢሻው ውህደታዊ…ወዘተ. ሊሆን ይችላል። ይሁንና መኢሶን ደግሞ በአሁኑ ወቅት መገንጠል የሚለውን መብት ያውቃል እንጅ፣ መገንጠልን አይደግፍም፣ ለዚህ መብት ቅስቀሳ አያደርግም። በሌላው በኩል ግን፣ የብሔር ትምክህተኝነትና ጠባብ ብሄርተኝነትን ለመቋቋም የሚደረገው ጥረት በተግባር ጭምር እንዲገለጽ ይታገላል። በተጨማሪ፣ ወዝ-ሊግ እንደሚለው “የብሄረሰቦች ኢንስቱትት” ቢቋቋም መኢሶን ደግፋል። እንደዚሁም መኢሶን እንደሚለው “የብሔረሰቦች ሸንጎ” እንዲቋቋም ይጠይቃል፣ ይታገላል።
4.6 የቢሮክራሲው ጥያቄ
በዚህ ጥያቄ ላይ በተራማጆች መካከል የሚያወዛግብ ብዙ የቲኦሪ ነገር የለም። ሁሉም የትላንቱ የኃይለሥላሴ መንግሥት የስልጣን አውታር የሆነው ፊውዶ-ቡርዣ ይውደም ይላሉ። የሁሉም- የሁሉም አንጀት በሲቪል/ሚሊቴሪ ቢሮክራሲው ያልተቋረጠ አሻጥር አሯል። ልዩነቱ የሚፈጠረው ወደ ድርጊት ጥያቄዎች ስንሻገር ብቻ ነው።
ምክንያቱም ዛሬ በተያያዘው መንገድ፣ ባንድ በኩል አድሃሪው ቢሮክራሲ እየተጠናከርና እየደለበ ነው። በሌላው በኩል የሲቪል ሚሊተሪ ቢሮክራቶችን በመንግሥትና በኢማሌድህ አባል ድርጅቶች ውስጥ ጭምር ቁልፍ ቦታዎችን እየያዙ ናቸው፣ ወይንም ይዘዋል። እንደዚህ ጠቅላላው የሥራና የአሰራር ትርምስ ለቢሮክራሲ አሻጥር አመቺ ሆኗል።በቢሮክራሲ ላይ የሚዘመተውም በመፈክር ብቻ ነው። እርሱም “ኑሮ በዘዴ በሚል አስመስሎ አገብድዷል። የሆነው ሆኖ፣ መኢሶን በጊዜው ሁኔታ ውስጥ የሚያቀርባቸው የጋራ ትግል ጥሪዎች ደግሞ የዚያኑ ያህል ግልጽ ናቸው። መስመሩ የሚከተለው ነው።
እርግጥ የአሮጌውን ሥርዓት ቢሮክራሲ በአንድ ቀን ጀንበር ለማፈራረስ አይቻልም። አዲሱንም የስልጣን አውታር በአንድ ቀን ውስጥ ለመገንባት አይቻልም። ይሁንና፣ አብዮታዊያን ባላቸው አቅም ሁሉ ተጋግዘው ደግሞ፣ ጊዜውን ሊያፋጥኑት ይችላሉ። ለዚህም በዛሬው ሁኔታ ውስጥ ቢያንስ የሚከተሉትን ተግባሮች ወደ ሥራ ለመተርጎም በህብረት መሰለፍ ይቻላል ብለን እናምናለን።
- – ቢሮክራሲው ጭቁኖች መርጠው የገነቧቸውን የአስተዳደርና የትግል አውታሮች እንዳያፍን ለመከላከል።
- – ሕዝባዊ ድርጅቶች በተጠናከሩበት ቦታ ሁሉ፣ እነርሱ በአሮጌው ሥርዓት ቢሮክራሲ ላይ ያላቸውን የበላይነት ማወቅና እነርሱን መደገፍና ባልተጠናከሩባቸው ስፍራዎች እንዲጠናከሩ ማገዝ።
- – የሕዝባዊ ድርጅቶች ዲሞክራሲያዊና ነፃ ህለውና እንዲከበሩ መታገል።
- ሕዝባዊ ድርጅቶች ውስጥ በየጊዜው የሚያንስራራውን መሥፍንነትና አምባገነንነት በጋራ ለመቆጣጠርና ለመቅጨት
- – የሲቪል ሚሊተሪ ቢሮክራሲ የሚፈፅሟቸውን አሻጥሮችና ጥቃቶች ነጥብ በነጥብ በይፋ ለማጋለጥና ለሕዝቡ ለማሳወቅ።
- – የለየላቸው አድሃሪ ቢሮክራቶች እንዲመነጠሩና በሃቀኛ ተራማጆች፣ አገር ወዳዶችና ዲሞክራቶች እንዲተኩ ለማድረግ
- – ተለይተው የታጠቁት አድሃሪዎች ያላቸውን እውቀት በሕዝባዊ ድርጅቶች ቁጥጥር ስር ሆነው ለሰፊው ሕዝብ ጥቅም እንዲተረጉሙት ማድረግ።
- – ከቀድሞ ሥርዓት የተወረሱትን አድሃሪ አሰራሮችንና ቢሮክራሲ ለማቃለልና የውሳኔ ስልጣኖችን ወደ ታች ለማውረድ
- – የሰፊውን ሕዝብ አርምጃዎች ለማገዝ፣ ለማበረታታትና ለመንከባከብ
4.7 የኢድህ-ኢህአፓ ጥያቄ
እነዚህ ሁለት ድርጅቶች የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮት ደመኛ የሆኑት ጠላቶች መደቦች የተደራጁባቸው ድርጅቶች ናቸው።የፊውዳሉ መደብ የነቁ ክፍሎች፣ የሲቪል/ሚሊተሪ ቢሮክራሲ አድሃሪ ክፍሎች፣ አሻጥረኛ ከበርቴዎች፣ የንዑስ ከበርቴው መደብ ቀኝ ክንፍ አባሎችና የሲ.አይ.ኤ ወኪሎች ሁሉ ተደራጅተው የሚገኙት በኢድህ-ኢህአፓ ውስጥ ነው። ስለዚህ ከነዚህ ክፍሎች ጋር የሚደረገው ትግል በምንም ዓይነት ቢሆን ማመንታት፣ መለዘብ፣ ወይንም በቀጠሮ ማደር የለበትም። ሳያቋርጥ መቀጠል አለበት።
አሁን የኢድህ “ነጭ ሠራዊት” በጎንደር፣ ኢህአፓ ደግሞ በቀይ ሽብር ከተመቱ ወዲህ፣ እነዚህ ክፍሎች እንዳሉ ታክቲካቸውን ለውጠዋል። “ፀረ አብዮትን በመንግሥትና በኢማሌድህ አባል ድርጅቶች ውስጥ ሆኖ ማካሄድ” በሚለው መመሪያቸው ስር እየፈተሉትና እየጎነጎኑት ናቸው። በዚህም በራሱ በአብዮት ሰፈር ውስጥ “ነጭ ድሎችን” ሳይቀዳጁ አልቀሩም። “ቀይ ባንዲራ ሰቅለው ነጭ ጥይት እየተኮሱ” ናቸው
መኢሶን በዚህ በኩል “ሪቮሉሽን” ቁ. 27 እና ቁ. 28 ፣ “አብዮታዊ ሰደድ” ቁ.20 ያወጡትን መግለጫዎች ሙሉ በሙሉ ይቀበላል። ይደግፋል። እርግጥ ከመጀመሪያውስ እንዴት ሊሆን ቻለ? የሚለውን ጥያቄ የመመለስና ለሕዝብ የማስረዳት ኃላፊነትና ግዴታ አለባቸው እንላለን።
4.8 የዲሞክራሲ መብቶች ጥያቄ
ምናልባት ካሉት ጊዜያዊ ጥያቄዎች ሁሉ ብዙ መጎሳቆል የደረሰበት ጥያቄ ይሄኛው ነው ብንል አንሳሳትም። በተነገሩት ነገሮች ላይ ሁሉ ብንመለስባቸው ደግሞ፣ አንድ ወፍራም መፅሐፍ መድረስ አስፈላጊ ሳይሆን አይቀርም። ይሁንና ይህ ደግሞ ራሱን የቻለ ጥያቄ ይሆናል። በዚህች ጽሁፍ አቅም እንወሰንና አቋማችንን እንደገና ግልጽ እናድርግ። እንደሚከተለው ነው።
በመጀመሪያ ስለመፈክሩ፣
የዲሞክራሲ መብቶች “አሁኑኑ” ተባለ ወይንም “ባስቸኳይ” ወይንም “በትግል” ወይንም “ያላንዳች ተጨማሪ”….ወዘተ.፣ በመሰረቱ ይህን ያህል ከፍተኛ ልዩነት ባልኖረው ነበር፣ የመብቱን መለቀቅ ካልተቃወሙ በስተቀር። “አሁኑኑ” ወይም “ባስቸኳይ” ስለተባለ ዛሬ በዚህች ደቂቃ ወይንም አንዳችም “ትግል” ሳይደረግ ማለት አይደለም። ደግሞ “በትግል” ወይንም “ያለአንዳች ተጨማሪ” ስለተባለው ጥያቄው ጨርሶ አልተነሳም ማለት አይደለም። በመጨረሻም “አሁኑኑ” ወይንም “ባስቸኳይ” ስለተባለ ኢ-ሳይንሳዊ፣ “በትግል” ስለተባለ እና “ያላንዳች ተጨማሪ” ስለተባለ “ሳይንሳዊ” የሆነ ማለት አይደለም። ይልቁኑ፣ ልዩነቶች የሚነሱት ያልተባለውን ተባለ ማለት ሲጀመር፣ ነገሮችን ከምንነታቸው በላይ አሰተልቆ ለመሳል ሲሞከር የነበሩና ያሉ ሁኔታዎችን በዚያም በዚህ ለማጣመም አስደናቂ የሆኑን የሎጂክ አክሮባቶች መስራት ሲጀመር ነው።
የሆነው ይሁን። መኢሶን “ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለጭቁኖች ያለ ገደብ አሁኑኑ” ሲል ምን ማለቱ ነው? ወይንም ደግሞ ወደ ኋላ ተመልሰን ማስታወስ ግዴታ ነውና፣ ምን ማለቱ ነበር?
ይህ የመኢሶን መፈክር፣ ሌላ ምንም ትርጉም የለውም። ወደ ዝርዝር እና ተግባራዊ ነጥቦች ሲተረጎም፡-
– የፊውዶ ቡርዣውን ቢሮክራሲ ሥርዓት ለመደምሰስ የሚደረገው ትግል አሁኑኑ ይፋፋም ማለት ነው። ነበር።
– በአንጻሩ ሕዝባዊ ድርጅቶችን አሁኑኑ እናጠናከር ማለት ነው። ነበር።
– የሰፊውን ሕዝብ በበለጠ መንቃት፣በበለጠ መደራጀትና በበለጠ መታጠቅ አሁኑኑ በበለጠ እንጣድፍ ማለት ነው። ነበር።
– የሰፊው ሕዝብ ነጻ እርምጃ እንዲፋፋም አሁኑኑ እንጠይቅ፣ እንታገል ማለት ነው። ነበር።
– በእስራት ላይ የሚገኙ ሀቀኛ ታጋዮች አሁኑኑ በነፃ ይለቀቁ ማለት ነው። ነበር።
– ለአብዮታዊያን መረሸን እና ማለቅ ተጠያቂ የሆኑት ቢሮክራቶች አሁኑኑ ለፍርድ ይቀረቡ፣ እርምጃ ይወሰድባቸዉ ማለት ነው። ነበር።
– በመንግሥት ቁጥጥር ስር በዋሉት ቅጥር ነፍሰ ገዳዮች ላይ አሁኑኑ እርምጃ ይወሰድ ማለት ነው። ነበር ።
– ረቅቆ ለተቀመጠው የዲሞክራሲ መብቶች አዋጅ ሰፊው ሕዝብና አብዮታዊያን እንዲታገሉለት አሁኑኑ በይፋ እንቀስቅስ ማለት ነው። ነበር።
– …ወዘተ።
እንግዲህ መኢሶን በዚያን ጊዜም ሆነ አሁን፣ “አሁኑኑ” ሲል የጠየቀውና የሚጠይቀዉ ከዘረዘርናቸው የተለዩ ተግባራዊ እርምጃዎችን አይደለም። እነዚህ ተግባራዊ እርምጃዎች ደግሞ፣ ወደ ተግባር ተተርጉመው ሲገለጹ “ከዲሞክራሲያዊ መብቶች” ሌላ ምን ሊሆኑ ይችላሉ? ደግሞስ፣ ወደ ተግባር የሚተረጉሙት በ“ትግል” እንጂ በሌላ በምን አይነቱ ተአምር ነው?
ይሁን እንጂ፣ ሰፊው ሕዝብ ደግሞ የዘረዘርናቸውን ዓይነት እና ሌሎችንም ተጨማሪ ዲሞክራሲያዊ ትግሎች ለማካሄድ፣ እንደሚባለው የወዛደሩን መንግሥት መጠበቅ አይኖርበትም። በጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት ስር፣ በእርሱ ድጋፍና ትብብር ሊያካሂዳቸው ይችላል። ችሏልም። ቀይ ሽብርና ሌሎችም እርምጃዎች በየካቲት/መጋቢት 1969 ዓ.ም እንደጀመሩት ቢቀጥሉ ኑሮ ይህችንም ጽሑፍ አስፈላጊ ባላደረጓት ነበር። ዛሬ ሌሎች ታሪኮችን በመፃፍ ላይ እንገኝ ነበር።
እንግዲህ መኢሶን ዛሬም ቢሆን “አሁኑኑ” ሲል፣ በጠላቶቻችን ላይ የምናደርገው ትግል አሁኑኑ ይፋፋም፣ አይዘግይ፣ ፋታ አይሰጥ፣ አያመንታ፣ አይታፈን….ወዘተ. ማለቱ ነው።
በሌላው በኩል ደግሞ፣ የአብዮቱን ሰፈር ለማጠናከርና ለማደራጀት “አሁኑኑ” በበለጠ እንጣደፍ፣ እንግፋበት ማለቱ ነው። ለመኢሶን ይህ መፈክር አንዳችም ሌላ ትርጉም የለውም። ያመለከትናቸው ጣምራ ተግባሮች አሁኑኑ በሥራ ከተተረጎሙ ቢሻው “ቅ…..” ይባል።
በተረፈ፣ የመንግሥትን ስልጣን በሚመለከተው በኩል ከሆነም፣ መኢሶን በፊትም ሆነ አሁን በዛሬው ወቅትና ገና ረዘም ባለ ጊዜ /በይዘት ያው በቅርፅ ግን “እንዳች” ዓይነት “ወዛደራዊ” ወይንም ሌላ አምባገነንነት በአቋራጭ አቋቁመንልሃል ካልተባሉ በቀር/ አገሪቱን ሊመራና ሊያስተዳደር የሚችለው ጊ.ወ.አ.ደ ብቻ መሆኑን ያምናል። በዚህ በኩል አንዳችም ጥርጣሬ የለውም። ስለዚህም መኢሶን በፊትም ሆነ አሁን ጊ.ወ.አ.ደርግን በሚመለክተው በኩል ከ“ሂሳዊ ድጋፍ” መስመር ዝንፍ አላለም። “አንዳንድ አባሎችን ወደ ህቡዕ ትግል መስክ ማዛወር” ምናልባትም ከዚህም አልፎ ሂሶችን ጠንከር አድርጎ መሰንዘር መኢሶንን በዛሬው ወቅት የስልጣን ተቀናቃኝ አያደርገውም። በተቃራኒ መኢሶን “የትግል ስልት ለውጥ አድርጎና” ሂሱንም አጠናክሮ ቢሆንም፣ ጊ.ወ.አ.ደርግን ለመገልበጥ የሚደረጉ ሤራዎችን ባለው አቅም ሁሉ ተጋግዞ ለማክሸፍ ከመተባበር ወደ ኋላ አላለም። አይልም። ይህ ጽሑፍ በራሱ የታሪክ ምስክር ሆኖ ይኖራል።
ሌሎች በትርጉም ትርጉም የሚነገሩት ነገሮች አሁንም የፀረ አብዮት ሤራ እንጅ፣ መኢሶንን የሚመለከቱ አይደሉም። /ከዚህ ባሻገር ጥያቄው በሰህድ ቁ. 65 ተመልሷል/
4.9 አብዮታዊት እናት ሀገር ወይም ሞት
ሰህድ ቁ. 64 /7.3.70/ እንዳለው፣ ከፀሐይ በታች በዕውነትም እንደዚህ መፈክር ግልፅ የሆነ ጉዳይ የለም። ይህ መፈክርና የውጭ ጠላቶቻችን ተቀነባብረው የሚታገሉን ስለሆነ፣ ወረራውን ለመቋቋም በምንም ዓይነት ከውስጥ አድሪዎች ጋር እርቅ መፈለግ የለብንም። የጦፈውን የመደቦች ትግል በማቀዝቀዝ ቅልበሳን መጋበዝ የለብንም ማለት ነው። የውጭ ጠላቶችን ለመቋቋምና ለመደምሰስ በውስጥ የመደቦችን ትግል ማፋፋምና የውስጥ አድሃሪዎችን መደምሰስ ያስፈልጋል ማለት ነው። “በታላቁ የጀርመን ወዝአደሮች መሪ ሊብ ክኒክት ተነግሮ እንደነበረው ጠላት ያለው ከውስጥ ነው” የሚለውን ሀቅ አንዘንጋው፣ አንለፈው ማለት ነው።
ይህ መፈክር ዛሬም ቢሆን ለመኢሶን ሌላ ትርጉም የለውም። ዛሬ ይህ መፈክር በተጨማሪ፣ በጦርነቶችና በቀይ ሽብር መካከል የተከናወነውን “አስደናቂ” የመደቦች ሽግሽግ ማረም ማለት ነው። የጦሩን ግንባር ለማጠናከርና መሃል አገርን የጦሩ አስተማማኝ ደጀን ለማድረግ በመካከላቸው ያሉትንም ግንኙነቶች ምንጊዜም አለመንዘንጋት ማለት ነው።
መኢሶን በጦርነቱ ወቅትም ሆነ አሁን የበኩሉን አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ይገኛል። ለወደፊትም ቢሆን ካድሬዎችን በየጦሩ ግንባሮች በማሰማራት ሆነ የደጀኑን ክፍል ለማጠናከር በሚደረጉ ጥረቶች ባሉት መንገዶችና ባለው አቅም ሁሉ ከመታገል ወደ ኋላ አይልም።
የሰፊውን ሕዝብ ታሪክ ሰሪነት በጥቂት ግለሰቦች እየለወጡ የሚደሰቱ ንዑሳን ናቸው። መኢሶን የትግል ስልት ለውጥ ስላደረገ ለጦርነቱ ያበረከተውን መጠየቅ የሚቃጣቸው የሰፊው ሕዝብ ታሪክ እንደራሳቸው አርገው ለመጻፍ የሚቋምጡ ብቻ ናቸው። የመኢሶን አባሎች፣ ደጋፊዎች ወገኖች በውስጥ በአስመሳይ ተረማጆችና በፀረ አብዮተኞች እየተሰበሩ፣ እየተመቱም ቢሆን፣ በጥሩነቱ ወቅትም ሆነ አሁን፣ ግንባርም ሆነ በደጀን የበኩላቸውን አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ መሆናቸው ገሃድ ነው።
4.10 የኢምፔሪያሊዝም ከበባና የጎረቤት አገሮች ጥያቄ
ኢምፔሪያሊስቶች፣ በተለይም የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም፣ ከረጅም ጊዜ ጀምሮ ወደ ሥራ እየተረጎሙ የመጡት ጆን ኤች ስፔንሰር የተባለው ሰው እ.አ.አ በነሐሴ 1976 ዓ.ም ለአሜሪካ ምክር ቤት ባቀረበው ራፖር ላይ የሚገኙትን ዕቅዶች ነው። እንደሚታወሰው የስፔንሰር ራፓር ከአዲስ አበባ አንስቶ እስከ ሶማሌ ወረራ ድረስ ለፀረ አብዮት እንቅስቃሴ ዝርዝር መመሪያዎችን የሚሰጥ ነበር። እቅዶችም ሁሉ ባለፈው አንድ አመት ተኩል ውስጥ በሥራ ላይ ውለው ታይተዋል።ይሁንና፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች መራራ ትግል ደግሞ፣ ኢምፔሪያሊዝም የሰነዘረውን ጥቃት ለመቋቋም ተችሏል። በዚህ በኩል ወዳጅ የሶሻሊስት ሀገሮች መንግሥታትና ፓርቲዎች የሰጡት ድጋፍ እጅግ ወሳኝ ነበር። ነውም።
ነገር ግን፣ ኢምፔሪያሊዝም የሚተኛልን ኃይል አይደለም። አሁንም ቢሆን እንዳለፈው አመት በውስጥ አመቺ ሁኔታዎችን ካገኘ “አፍጥጦና አግጦ መውጣቱ አይቀርም። በመንግስትና በኢማሌድህ አባል ድርጅቶች ውስጥ ጭራቸውን ቆልፈው የሰረጉት አድሃሪዎች መሳሪያዎች ሊሆኑ ይችላሉ። ምናልባትም በኤርትራ በኩል ወታደራዊ እርምጃዎችን ጭምር ሊያስብ ይችላል። እንደሚታወቀው በዛሬው ወቅት ሁኔታዎችን ለማመቻቸት በተለይ በኤርትራ ጉዳይ ላይ ኃይለኛ የሆነ ፀረ ኢትዮጵያ ፕሮፖጋንዳ በመካሄድ ላይ ነው። ለሶማሌ የሚሰጠውንም የፖለቲካ፣ የቅስቀሳና የማቴሪያል ድጋፍ እጅግ አባብሶታል። እንደዚሁም፣ በኢህአፓ ላይ የተወሰዱት እርምጃዎች እያጋነነ በመለፈፍ ላይ ነው። በመጨረሻም፣ አብዮታችንና አገራችን የኢምፔሪያሊዝም ቡችሎች በሆኑ አገሮች የተከበቡ ናቸው።ኢምፔሪያሊዝም፣ እነዚህን ሁሉ ያለማቋረጥ በአብዮታችን ላይ ለማሰለፍ እንደሚጥር ፈጽሞ አይጠረጠርም። በአካባቢያችን፣ የኢምፔሪያሊዝም የጊዜው ዋና ጥረት፣ የኢትዮጵያን የየመን ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ እና የፓላስቲን ሕዝብ የነፃነት ትግሎች ብቸኛ አድርጎ መደቆስና የቀይ ባህርን ስትራቴጂያዊ ሰፈር በቁጥጥር ስር ማዋል ነው። ለዚህ ግቡ ገና ብዙ ይሟሟታል።
በግብጽም በአድሃሪ የአረብ አገሮችና በእስራኤል መካከል የሚደረገውን “ርኩስ መቀራረብ” አንደኛ መሳሪያው ነው። በዚህ አንጻር፣ በአንድ በኩል የአረብ አገሮችን ለመከፋፈል ችሏል። በሌላ በኩል የፓላስቲን ሕዝቦችን እንቅስቃሴና የአረብ ኮሚኒስቶችን ትግል ለመደምሰስ ኃይለኛ ዘመቻ እያካሄደ ነው። ይህ አንደኛው ጉዳይ ነው። ሁለተኛው፣ጎረቤቶቻችን ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ ኬንያ፣ ጅቡቲ፣ የአረብ ፔኒሱላ ሁሉ ሙሉ በሙሉ በኢምፔሪያሊስቶች ቁጥጥር ስር የሆኑ አገሮች ናቸው። ምንም እንኳን እንደ ኬንያ አካሉት አገሮች ጋር አንዳንድ ጊዜያዊ ሁኔታዎች ቢያገናኙንም፣ ጎረቤቶቻችን በሙሉ በአሁኑ ወቅት በመሰረቱ ከአብዮታችን ጋር በጠላትነት የቆሙ ናቸው። ገና ለረዥም ጊዜ የኢትዮጵያ አብዮት የሚፃረሩትን ኃይሎች መፈልፈያና ማደራጃ ሰፍራዎች ሆነው ይቆያሉ።
በሌላው በኩል በእነዚህ ሃገሮች ውስጥ አብዮታዊ እንቅስቃሴዎች ሊነሱ የሚችሉበት አብዮታዊ ሁኔታዎች አሉ።ጎረቤቶቻችን በሙሉ በውስጣዊና በውጫዊ ችግሮች የተወጠሩ ናቸው። የሀገሮቹ /ሕዝቦችና የኢትዮጵያችን “ዕድል” ሆኖ፣ ካሉት መንግሥታት በስተቀኝ የሰፈሩ ኃይሎች ወደ ስልጣን ካልመጡ በስተቀር፣ ቢያንስ ገለልተኛ የሆኑና በውስጥ ችግሮቻቸው ላይ የሚያተኩሩ መንግሥታት ሊመጡ እንደሚችሉ ልንጠብቅ እንችላለን። በግብጽ፣ በሱዳን እና በኬንያ ያሉት ሁኔታዎች ይህንን የሚያመለክቱ ሳይሆኑ አይቀሩም። ይሁን እንጂ፣ በሁሉም ቦታ በአንድ ወቅት ውስጥ የሚፈጸም ነገር ደግሞ አይኖርም።
ዞሮ ዞሮ ይህ ሁሉ የሚያመለክተን፣ በአካባቢያችን ገና ለረጅም ጊዜ ገና ብዙ ውስብስብ ሁኔታ እንደሚኖር ነው።ጉዳዩ አህጉራዊና ክፍለ አህጉራዊ ብቻ አይደለም። እጅግ፣ እጅግ በጣም አለም አቀፋዊ ነው። ያም ሆነ ይህ አማራጭ የሌለው መፍትሄ የውስጥ ጥንካሬያችን እና ጥረታችን ነው። በተጨማሪ፣ ይህንኑ ለማገዝ በጎረቤት አገሮች፣ በአፍሪካ አህጉር፣ በአረቦች ዓለም ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ/ በኢምፔሪያሊስት አገሮች መዲናዎች ጭምር/ የምንጫወተው ዲፕሎማሲ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል። በዚህ ጽሁፍ ውስጥ ወደ ዝርዝር መግባቱ አስፈላጊ አይመስለንም።
4.11 የብሔራዊ ነፃነታችን ጥያቄ
ይህንን ጥያቄ በጥቂት ቃላቶች ለመመለስ አስቸጋሪ ነው። ከብዙ ሀገሮች ታሪክ አያሌ ትምህርቶችን መቅሰም ይኖርብናል። ይሁን እንጅ፣ ከጂኦግራፊ አቀማመጣችንና ከማቴሪያላዊ አቅማችን ደካማነት የተነሳ በብሄራዊ፣ በአህጉራዊና በዓለም አቀፍ ደረጃዎች ከአያሌ ጥያቄዎች ፊት እንደምንቆም አያጠራጥርም። ዞሮ ዞሮ፣ ይህም ጥያቄ የሚመለሰው እንደ አብዮታችን ውስጣዊ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የባህል ጥረት፣ ጥንካሬና ውህደት ነው።
4.12 የኢኮኖሚና የሶሻል ጉዳዮች ጥያቄ
ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የኤኮኖሚና የሶሻል ችግሮች በመሰረቱ የሚመነጩት በገጠርና በከተማ፣ በዕቅድ እና በማቴሪያላዊ አቅም፣ በመንግሥታዊ የኢኮኖሚ ዘርፎችና በግላዊ ኢኮኖሚ ዘርፎች፣ በወጭ እርዳታ እና በራሳችን ችሎታ፣ በኢምፔሪያሊዝምና በአብዮታችን፣ በጦርነት እና በምርት፣ በቢሮክራሲ አሻጥርና በመንግሥታዊ ቁጥጥር…. መካከል ካሉት ቅራኔዎች ውስጥ ነው። እንደዚሁም በአሁኑ ወቅት የብሔራዊ ከበርቴውን /በሀገራችን ሁኔታ የንግድ ከበርቴ/ ለመያዝ ከምንከተለው ወይንም ከማንከተለው ፖሊሲ የሚመነጩ ናቸው።
በእነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች ላይ በዝርዝር ለመመለስ አያሌ የስታትስቲክስ ሰነዶችን ማገላበጥ ያስፈልጋል። ያሉትን ፖሊሲዎች እንደገና መመርመር ያስፈልጋል።…. በፖሊሲዎችና በድርጊት መካከል ባሉት ቅራኔዎች ላይ ሁሉ አንድ በአንድ መመለስ ያስፈልጋል። የቢሮክራሲውንና የንግድ ከበርቴዎችን አሻጥር ማጥፋት ያስፈልጋል።… ይሁንና ይህ ሁሉ ከዚህች ፅሑፍ አቅም ውጭ ነው። ችግሮቹ የትላንትና አይደሉም። ከአብዮታችን በፊትና ከአብዮታችን የመጀመሪያ ቀኖች አንስቶ ሲጠራቀሙ የመጡ ናቸው። በአበዮትና በፀረ አብዮት መካከል በተካሄዱት ትንቅንቆች ሁሉ የተፈጠሩ ናቸው።
የሆነው ሆኖ፣ በአሁኑ ወቅት የሚነሱት አያሌ የኢኮኖሚና የሶሻል ጥያቄዎች ደግሞ የእህል መጥፋት፣ የሸቀጣ ሸቀጦች መጥፋትና መወደድ፣ የትራንስፖርትና የንግድ መዛባት፣ የፋብሪካዎች መቆም፣ የኑሮ ውድነት፣ የቤት እጥረት፣ ህክምና፣ የዘማቾችና የወደቁት ታጋዮች ቤተሰቦች… የተወሰኑ አካባቢዎች ጥያቄዎች ብቻ አይደሉም። ሀገር አቀፍ መልክ እየያዙ የመጡ ናቸው። የሀገሪቱ አጠቃላይ ክሪዞች ናቸው።
በኛ እምነት፣ ችግሮቹም እያሉ ቢሆን እነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች በትክክለኛ ፖለቲካ፣ ከአቅም ጋር በተመጣጠነ መለስተኛ ፖሊሲ፣ አላማ ባለው ፕሮፖጋንዳና ቅስቀሳ ሊመለሱ ይችላሉ። በዚህ አንጻር፣ በተለይም በአድሃሪው የሲቪል/ሚሊተሪ ቢሮክራሲ ላይ የሚደረጉ የቁጥጥርና የማጋለጥ ዘመቻዎች ከፍተኛ ሚና ይኖራቸዋል። በአንፃሩ፣ የኢኮኖሚ ካድሬዎች፣ የምርትና የስራ ኤክስፐርቶችን በብዛት አፍርቶ ማሰማራት እጅግ ጊዜያዊ ነው። ራሱን የቻለ የምርትና የመገንባት ፕሮፖጋንዳና ቅስቀሳ መጀመር አለበት። የሰፊውን ሕዝብ የመፍጠርና የሥራ ችሎታ ለመቀስቀስ፣ለማደራጀትና ለመምራት አያሌ ጥረቶች መደረግ ይኖርባቸዋል። እንደዚሁም፣ ቢያንስ በተወሰኑ የኢኮኖሚ ዘርፎች በኩል ወደ ፕላን-ኢኮኖሚ ለመሻገር መጀመር እጅግ ጊዜያዊ ነው እንላለን።
በዚህ አንጻር የውጭ እርዳታዎች ሁለተኛ ራስን መቻል የመጀመሪያው የሚለው ፖሊሲ በጥብቅ መቀጠል እንዳለበት እምነታችን ነው። በአንድ በኩል በተጨባጭና ከእኛም ጋር በተመጣጠኑ ድርጊቶች፣ በሌላ በኩል ሕይወት ባለው ፕሮፓጋንዳ፣ ቅስቀሳና የማያቋርጥ የመደብ ትግል ከሰራን፣ በዚች ሀብታም በሆነችው አገራችን ላይ ተአምሮች ሊሰሩ ይችላሉ።
4.13 የወዛደሩ ፓርቲ ጥያቄ
እኛ እስከምናውቀው ድረስ፣ በዚህ ጥያቄ ላይ በተራማጆች መካከል ልዩነቶች ያሉ አይመስልም። “ህብረት፣ ውህደት/ፓርቲ/፣ አብዮታዊ ግንባር” በሚሉት ደረጃዎች ላይ አጠቃላይ ስምምነት አለ። ወደ ወዛደሩ ፓርቲ “በአቋራጭ” እንሻገር አንሻገር እንደሁ የሚመጡት ጊዜዎች ያሳያሉ።
የሆነው ሆኖ፣ የወዛደሩ ፓርቲ መሠረት በትግል የተፈተነ፣ ጥራት፣ ጥንካሬና ውህደት ያለው የተራማጆች ህብረት ነው። ዛሬም የምንገኘው በዚሁ ደረጃ ላይ ነው። ከተራማጅ ድርጅቶች ሃቀኛ፣ አብዮታዊና ዲሞክራሲያዊ ህብረት እስከ ወዛደሩ ፓርቲ ድረስ ገና ረጅም የሆነው ውስብስብ መንገድ አለ። በሌላው በኩል “በአቋራጭና” ከአስመሳዮች ሁሉ ጋር ገና ከመጀመሪያው “የወዛደሩ ፓርቲ ኮንግሬስ” ላይ እንዳንደርስ መታገል የሃቀኛ ተራማጆች ሁሉ ማሌያዊ ተግባር ነው ብለን እናምናለን።
[1] በተለይም ከሕዝቦቹ ውስጥ ተወጣጥተው በሰለጠኑ ካድሬዎች
[2] ቢሻው የላላ ወይንም የጠበቀ ፌዴሬሽን፣ ቢሻው ሪጅናል አውቶኖሚ
5. እንደገና ስለ ተራማጆች ህብረት
ሀቀኛ፣ አብዮታዊ፣ ዲሞክራሲያዊ የሆነ ህብረት እጅግ አስፈላጊ ነው። የጊዜው ሁኔታ ይህንን ጥያቄ ደጋግሞ እያስገነዘበ ሊያበቃ አይችልም። አሁንም፣ አሁንም ወደ እርሱ እንድንመላለስ እንገደዳለን።
መኢሶን እንደዚሁ ላለው የተራማጆች ህብረት ከመታገል አቋርጦ የማያውቅበት ወቅት የለም። ገና በ1966 ዓ.ም ጀምሮ “የተራማጆች ህብረት” በተሰኘው ጋዜጣ አማካይነት ይህንን ጥሪ ደጋግሞ እንዳሰማ ነው። ዛሬም ይህ የትግል አንድነት ተመስርቶ፣ ተራማጆች ሁሉ በአንድነት እንዲሰበሰቡ ጥሪ ከማድረግና ከመታገል ወደኋላ አይልም። ያሻው ችግር ቢኖር፣ ትክክለኛው መስመር ይህችው ብቻ እንደሆነ መኢሶን በጥብቅ ያምንበታል።
ሀቀኛ የተራማጆች ህብረት ሊያብብ የሚችለው አንደኛ፣ መሰረታዊ በሆኑት ጥያቄዎች ላይ በዲሞክራሲያዊ ዘዴ በመወያየትና በመስማማት ነው። ሁለተኛ፣ በየአለቱ በሚፈልቁት የአብዮት ጥያቄዎች ላይ ግልጽ የሆኑ የታክቲክ ውይይቶችን በማካሄድ እና የረዥምና የአጭር ጊዜ እቅዶችን ለይቶ በመውጣት ነው። ሦስተኛ እያንዳንዱ ድርጅት ስምምነት የተደረገባቸውን ጉዳዮች ሲያከብር ነው። አራተኛ እያንዳንዱ ድርጅት የህብረት መርሆችን ሲያከብር ነው።አምስተኛ እያንዳንዱ ድርጅት ስምምነት የተደረሰባቸውን ጉዳዮች በሥራ ለመግለጽ የበኩሉን አስተዋጽኦ ያላንዳች መቆጠብ ሲያበረከት ነው። ስድስተኛ ጓዳዊ ሂስና ግለ ሂስ ሲኖር ነው።…. እነዚህ መሰረታዊ የሆኑትን ያህል፣ በተጨማሪ ደግሞ ከጋራ ጠላት ፊት በህብረት መቆምና የውስጥ ቅራኔዎች በዲሞክራሲያዊ ዘዴዎች ለመፍታት መታገል እጅግ አስፈላጊ ናቸው እንላለን።
እነዚህ የትግልና የአሰራር ዘዴዎች ያለማቋረጥ ከሥራ ላይ ከዋሉ፣ የተራማጆች ህብረት ይጠራል፣ ይጠናከራል አያሌ የትግል ልምዳችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ይሰበሰባል፣ ከህብረት ወደ ውህደት የሚደረገው ሽግግር በተመጣጣኝ የቀለለና የአማረ ይሆናል። በተቃራኒ አሉባልታዎች፣ የፈጠራ ክሶች፣ ነገሮችን ከአቅማቸው በላይ መጫንና እና ማጋነን፣ በሆነው ባልሆነው መወነጃጀል፣ ስሜተኝነት ወዘተ እጅግ የሚጎዱና ትግሉንም የሚያወሳስቡ ናቸው። አደፍራሾች፣ ከፋፋዮች አትራማሾች ናቸው።
የመጀመሪያው አብዮታዊ የሆነውን ያህል፣ የኋለኛው ፀረ አብዮት ይሆናል፣ ስለዚህ፣ መኢሶን ዛሬም ቢሆን በተራማጆች መካከል ላሉት ቅራኔዎች መፍትሄው ግልጽ ውይይት ነው ብሎ ያምናል። ለዚህም እንዲያመች፣ ዋና ዋና በሆኑ የጊዜው ጥያቄዎች ላይ ያሉትን አቋሞች በአጭር ባጭሩ አቅርበናል። በተረፈ መኢሶን ሁኔታዎች እንደፈቀዱ ይፋ የሆነ ሂስና ግለሂስ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አሁንም በድጋሚ ያሳውቃል።
6. መደምደሚያ
በኢትዮጵያ አብዮት አያሌ የውስጥና የውጭ ችግሮች አሉበት። የጊዜ ሁኔታ ለአብዮታችን መግፋት አመቺ የሆነውን ያህል፣ ለፀረ አብዮት ማንሰራራትም አመቺ ነው። ከሁሉም በላይ፣ በተራማጆች መካከል የተፈጠሩት ቅራኔዎች መክረር እና መስፋት ለፀረ አብዮት እንጅ፣ ለአብዮቱ ጠቃሚ አይሆንም። ዛሬ በአንድ በኩል በመኢሶንና በጊ.ወ.አ.ደ፣ በሌላው በኩል በመኢሶንና በኢማሌድህ አባል ድርጅቶች መካከል የተፈጠሩት ቅራኔዎች በመስፋታቸው የሚፈነድቁት አድሃሪዎች ናቸው። “እነሱ አይደሉም ወይ ያኔ!” በሚል በመኢሶን ላይ በቀላቸውን እየተወጡ ናቸው። ጊዜው ከምንጊዜውም ይልቅ አርቆ አስተዋይነትን የሚጠይቅ ነው።
የተራማጆች ህብረት ከምንጊዜውም ይበልጥ ያስፈልገናል። ተራማጆች ችግሮቻቸውንና ቅራኔዎቻቸውን ሁሉ በውይይትና በዲሞክራሲያዊ ዘዴዎች ሊወጡት ይችላሉ። ይህ በራሱ በአድሃርያን ላይ የምንቀዳጀው አንድ ወሳኝ ድል ይሆናል። “ጥርሳቸውን ያገጠጠውን” የለየላቸው አድሃሪዎች ሁሉ እናሳፍርበታለን። እናሸንፋለን።
የኢትዮጵያ ሀቀኛ ተራማጆች ተጋግዘው ጊዜያዊ ችግሮቻቸውን ከተወጡ፣ መጪው ጊዜ አስቸጋሪ የሆነውን ያህል ብሩህ ነው።