ሰሕድ ቁ. 74

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ቁጥር 74፣    ታህሣሥ 29፣ 1973 

የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ

መኢሶን በዚህ ሰፋ ባለ እትም፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ለብሄራዊ ነፃነት ያደረጉትን የትግል ታሪክ  ከአብራራ በኋላ ፣ ዛሬ ደግሞ የሩሲያ ተስፋፊ መንግሥት የጦር እርዳታ መስጠት በሚል ተልዕኮ እንዴት ኢትዮጵያ ገብቶ  በአገራችን ላይ ወታደርዊ ተፅዕኖ እንዳሰፈረና እንዲሁም የፖለቲካውንና የኢኮኖሚውን ዘርፍ እንቅስቃሴዎች ሊቆጣጠር እንደቻለ ያብራራል።  ከዚህም አልፎ አብዮቱ እንዲከሽፍ፣ መንግስቱ ኃይለማርያም አንድ ወጥ ፓርቲ እንዲያቋቁምና ሠራዊቱም በዚህ ፓርቲ የሚመራ እንዲሆን ምክሩና ትዕዛዙ የመጣው ከሩሲያ መሪዎች መሆኑን ያረጋግጣል።  

በዚህ እትም፣ መኢሶን  አሁንም የሩሲያ ተስፋፊዎች ከአገራችን ተዋርደው እንዲወጡ እንዲሁም የማንም ተቀጢላ ያልሆነች፣ነፃ፣ዴሞክራሲያዊት፣ ኩሩ፣ የበለፀገችና በራሷ የምትተማመን ሕዝባዊት ኢትዮጵያን ለመመሥረት ከሌሎች አገር ወዳዶች ጋር አብሮ ለመስራት ያለውን ፍላጎት ይገልጻል።

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ለሰፊው ሕዝብ ሰራተኛ ገበሬ፣ ነጋዴ፣ ወታደር፣ ምሁር መብትና ጥቅም የሚታገል ጋዜጣ

የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ይቅደም

                ቁጥር 74[1]                                                      ቀን 29/4/73

 

ብሄራዊ ነፃነት ሲደፈር 

 

ክፍል አንድ

1.መግቢያ

መኢሶን ገና በመጋቢት 1969 ዓ.ም. 

“ተስፋችንን በውጭ ኃይሎች ላይ መጣል ያመጣን ዕለት፣ የተኰላ አብዮትና ‘በነፃነት ለዘላለም ትኑር’ የተባለችው አገራችን ተመልሳ ከባርነት ስር የምትወድቅበት ቀን እንዲመጣ ማገዛችን አንደሆነ መታወቅ አለበት” /ሰህዱ ቁ.53/

ሲል አስጠንቅቆ ነበር ። ይህ የፀና አቋሙን ግልፅ ያደረገበት ቢሆንም፣ ትህትና የተመላበት ለዘብተኛ አነጋገርም ይመስል ነበር። ጉዳዩ ግን የትህትናም የለዘብተኝነትም አንዳይደል ደግሞ የታወ ነው። አስተዋይና ብልህ የሆነ ማንም አብዮዊ የፖለካ ድርጅት የሚያደርገው ነበር። በተለይ ደግሞ እንደ መኢሶን ያለ፣ ሳይንዊ የትግል ዘዴን የራሱ ያደረገ ወዝአደራዊ የፖለካ ድርት ከዚህ የተለየ ሊያደርግ አይችልም። አይገባውምም ነበር። የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ  በወቅ ከግንባር ቀደም ጠላቱ ከአሜሪካ ኤምፒሪያሊዝምና ቡችሎቹ ጋር አብታዊ ትንንቅ ላይ ስለነበር፣ መኢሶን አብዮታዊ ታክቲክን ተንተርሶ ሁሉንም እንደየአመጣጣቸው መታገል ነበረበት። የኢትዮጵያ ለጋ አብዮት ጠላቶቹን እየነጠለና እየከፋፈለ መምታት ነበረበት። ነገር ግን ሰላም አንዲት ጉዳይ ነበረች። እንደዛሬው ብሄራዊ ወኔያቸው ላሽቆ ወደ ዘመናዊ ባንዳነት ከማሽቆልቆላቸው በፊት የጊዜው የፖለቲካ ተዋንያኖችን፣ መቼም ኢትዮጵያዊ ነበሩና ከማንም ኢትዮጵያዊ ዜጋ የሚጠበቅ ብሄራዊ ወኔ ይኖራቸው ይሆናል ሎ መገት፣ መኢሶን በጥሞና መግራትም ጭምር ነበር። የሩስያ ተስፋፊዎችን በሚመለከት ግን፣ የታላቁን የጥቅት ሶሊስት አብዮት ድሎች ቀልብሰው ታላቅና ሶሊስት የነበረችውን ሶቭየት ህብረት አዝቅው ወደ ኢምፔሪያሊስትነት ደረጃ  ያወረዱ ፀረ ጭቁን ሕዝቦች መሆናቸውን መኢሶን ያኔም ቢሆን አላጣውም። ያም ሆነ ይህ፣ መኢሶን መቼም ቢሆን ደግሞ፣ ኢትዮጵያ ሕዝዊና ዲሞክራሲያዊ ሆና የምታብበው፣ በራሷ  ታጋይ ሕዝቦችና ሃብት እንጂ በውጭ ይል ላይ ተስፋዋን ጥላ አንዳልሆነ፣ ኢትዮጵያ የምትገነው ብሄራዊ  ወኔያቸው ባልላሸቀ ለማንም ማጎብደድን ባላወቁ በልበ ሙሉዎቹ ሃቀኛ ተራማጅ ልጆቿ፣  በዲሞክራቶቿና በአገር-ወገን አፍቃሪዎቿ ጅ እንጂ ለማንም ዕድ አጐንብሳ እንዳልሆነ የፀና አቋሙን ሳይገልጽበት የቀረበት ጊዜ አልነበረም። 

“ብሄራዊ ነፃነታችንና መኢሶን” በሚል ርዕስ፣ በሰህድ ቁጥር 73 እትማችን ውስጥ፣ በዚያን ወቅት መኢሶን ያካሄደውን የተወሳሰበ ትግል አውስተናል። ዛሬ አፍጦና  አግጦ በኢትዮጵያ ሕዝቦች ላይ የመጣባቸው የሩስያ ተስፋፊዎች የዕድ ይል  ከገፋና ተጨባጭ ሁኔታው የመጀመሪያ ደረጃ ጠላት ደረገው ደግሞ፣ ይቅርታ የለሽ አብዮታዊ  ትግል ማካሄዱንም መኢሶን ያውቅበታል። በዚህ ዕትማችንም በጉዳዩ እንደገና ተመስንበት  ብሄራዊ  ነፃነታችን እንዴት እንደተደፈረ በተጨባጭ ለማሳየትና መኢሶን ደጋግሞ ያሰማውን ብሄራዊ ጥሪ ለማደስ ነው። 

የአሜሪካ ምፔሪያሊዝም ድ ተመቶ ከኢትዮጵያ ከተባረረ ወዲህ በርሱ እግር ለመተካት ያኔ ያነፈንፉ የነበረው የሩስያ ተስፋፊዎች መንግሥት ዛሬ ብሔራዊ ነፃነታችንን በጫማው ረግጦ በአገራችን ላይ ተንሰራፍቷል። ሃገራችንን ሽጠውና ብሔራዊ ነፃነታችንን አስደፍረው ዕድሜያቸውን ለማራዘም የቋመጡ ዘመናዊ ባንዳዎች ተከስተውበናል። እኛም ሃቀኛ ተራማጆች፣ ዲሞክራቶች፣ ሃገር ወዳዶችና የጭቁን ብሄረብ ታጋዮች ጅ ለጅ ተያይዘን ሰፊውን ሕዝብ በማስተባበር፣ ይህን አዲስ ፀረ ብሔራዊ ነፃነትና ፀረ አብዮት ተስፋፊ ኃይል ከነቡችሎቹ ድባቅ ለመታት በቆራጥነት መታገል የሚኖርብን ሁኔታ ውስጥ ገብተናል። ከእንግዲህም በውድ አገራችንና በዝባችን ላይ አዲስ የመጣበት ተስፋ ኃይል ሊጋለጥ ይገበዋል። የጋራ ክንዳችንን ልናነሳበት ይገባል። 

አገርና ወገን ወዳድ ሁሉ ብሄራዊ ነፃነቱ እንደምን እንደተደፈረ ተረድቶ፣ ለነፃነቱ ለክብርና ለኮራ ህልውናው በማለት ጅ ለጅ ተያይዞ ካልተነሳ ግን፣ ይህች ውድ ሃገራችን እንደዛሬው ዘመን የተስፋፊዎችና የጣልቃ ገቦች መናኽሪያ፣ የጥቂት ዘመናዊ የሃገርና የወገን ደላሎች ማጎሪያና መፈንጪያ፣ የብዙሃን ሲኦልና የያላን መንግሥታት መፋለሚያ ሆና  ትቀራለች። እኛ ከትውልድ ትውልድ በብሄራዊ ነፃነታችን ኮርተን የኖርነው አገር- ወገን ወዳዶች፣ ዲሞክራቶችና ሃቀኛ ተራማጆች፣ ውስጥ ለውስጥ ከመብሸቅሸቅ ባሻገር ወደ ጋራ-እምቢተኝነት እንድንሻገር ሁኔታዎች ሁሉ አጥብቀው  እጠይቁናል። ተደራጅተን የምንገኘውም ነፃ፣ ሃቀኛ፣ ተራማጅና ዲሞክራቲክ የፖለቲካ ድርጅቶችና የብሄረሰብ እንቅስቃሴዎች ይህን የተቀደሰ ትግል አስተባብረን ልንመራው እንችል ዘንድ መተባበራችን የግዴታ መሆኑ ግልጽና የማይታለፍ ጉዳ ሆኖ ቀርቧል። መኢሶን ዛሬም እንደገናና ለወደፊቱም ደግሞ ደጋግሞ ብሔራዊ ሪውን የሚያስተጋባው ከዚሁ መሠረታዊ ግብ ላይ ለመድረስ ነው። 

ሀ/ ለብሄራዊ ነፃነትና ለሕዝባዊ አርነት የተደረገ ትግል

የሃገራችን የጂኦግራፊ አቀማመጥ፣ የምድራችን ሃብትና ለምለምነት፣ የሕዝባችን ታታሪነትና ብሩህነት በየጊዜው የተነሱትን ኃያልና ተስፋፊ መንግሥቶች ሁሉ በኢትዮጵያችን ምድር ላይ እንዲያተኩሩ ሲያደርጋጭቸው ኑሯል። ይህች ውድ ሃገራችንን፣ ቢሆንለት በቀጥታ ወረራ የቅኝ ግዛቱ ለማድረግ፣ ካልሆነለትም በእጅ አዙር ሊገዛት ያልቋመጠ አንድም ኃያል መንግሥት አልነበረም። ባለፈው ክፍለ ዘመን እንግሊዝ፣ ፈረንሳይና ኢጣልያን ኢትዮጵያን ለመቃረጥ የቋመጡት ዋና ዋናዎቹ ነበሩ። ጣልያን ካንድም ሁለትና ሦስቴ የወረራ ጦርነት ከፍታብናለች። የዛሬዎቹ ዘመናዊ ዛሮች ቅም አያቶች— የቀድሞዎቹ ዛሮች ሳይቀሩ ሁሉ ይህችን ውድ ሃገራችን ከሌሎች ጋር ለመቃረጥ የቋመጡበት ጊዜ ነበር። ያም ሆነ ይህ ግን፣ ኢትዮጵያ ጀግና ሕዝቦች እንኳን ለነርሱ ቀርቶ ለማንም አልበጁም። ደጋግማ ጦርነት የከፈተችብንን ጣልያንን በድል እየመቱ አባረዋል። ከአድዋ ጦርነትና ከአርባ ዓመታት በኋላም፣ የጣልያኑ ፋሽስት መንግሥት አገራችንን እንደገና ለመድፈር ቢቃጣውም፣ የኢትዮጵያ ጀግናና አገር ወዳድ አርበኞች በተለመደው ልበ ሙሉነት በየዱር ገደሉ ተሰማርተው ተናንቀውታል። ከአምስት ዓመት የአርበኝነት ጦርነት በኋላ፣ ወራሪው የፋሽስት ጦርን ከነባንዳዎቹ ደምስሰው፣ በኢትዮጵያ ሸለቆዎችና ተራሮች ላይ ሁሉ ‘ጉሮ ወሸባዬ’ እያሉ የብሄራዊ ነፃነትን ችቦ ለማብራት ችለው ነበር።

ነገር ግን ደግሞ ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ አገሪቱ ያበቀለቻቸው ዲሞክራቶች፣ አገር—ወገን ወዳዶችና አጋሮች ለነፃነትና ለብሄራዊ ክብር ምንጊዜም የተሟሟቱትን ያህል፣ ለሥልጣን፣ ለግል ጥቅም፣ ለከንቱ ክብር ሙገሳና ውዳሴ ህሊናቸውን የሚሸጡ ከሃዲና የሃገር- ወገን ደላሎችም ከውስጡ በቅለውበት ታሪካችንን ያጎደፉ አልጠፉም። ከፋሽስቱ ጣልያን ጋር ተሰልፎ ኢትዮጵያን የወጋት ባንዳ ጥቂት አይደለም። ኢትዮጵያዊ ወኔያቸው ላሽቆ፣ ብሄራዊ ነፃነታችንን ለአዲሱ ተስፋፊ የሩስያ መንግሥት ሽጠው በቅምጥ መንግሥትነት የሚያገለግሉት የዘመኑ ባንዳዎችም የሚደግሙት ይህንኑ ታሪክ እንጂ አዲስ ነገር አይደለም።

ሆኖም ግን ደግሞ፣ በብሄራዊ ነፃነት የትግል ጎዳና ላይ ሺህ ባንዳ፣ ሺህ ደላላ ሺህ ፍርፋሪ ለቃሚ ቢፈላ የማታ ማታ የድሉ ባለቤት የሚሆነው የታጋዩ አርበኛ ወገን መሆኑ ከቶም አያጠራጥርም። ታሪክ ደጋግሞ ያሳየው ነው።

ከፋሽስቱ ጣልያን ወረራ በኋላ፣ በመጀመሪያ በእንግሊዝ፣ ከዚያም በአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም የሚመራው የምዕራብ ኢምፔሪያሊዝም አገራችንን በእጅ አዙር ቅኝ ግዛትነት ይዞ ፈንጭቶ ነበር። ይሁንና፣ የየካቲቱ 1966 ዓ.ም. ሕዝባዊ አብዮታዊ ማዕበል ሲነሣ ደግሞ፣ የምዕራብ ኢምፔሪያሊስቶች ለዓርባ ዓመታት አቅፈውና ደግፈው ያቆሙትን ሥርዓት እንደክርታስ ቤት ደርምሶታል።

የየካቲትን አብዮት በተከተሉት ሦስት ዓመታት የኢትዮጵያ ወዝአደሮች፣ አርሶአደሮች፣ አገር ወዳድ መለዮለባሾች፣ አብዮታዊ የብሄረሰብ እንቅስቃሴዎች፣ ታጋይ ወጣቶችና ሴቶች፣ ዲሞክራቶችና አገር ወዳዶች በተለያዩ መልኮች የተከሰቱባቸውን የጋራ ቀዳሚ ጠላቶቻቸውን ተናንቀው ታላላቅ ሕዝባዊና ዲሞክራሲያዊ ድሎችን ተጎናጽፈዋል። ኢትዮጵያችንም በብሄራዊ ነፃነት ጣዕም የደመቁ ብሩህ የታሪክ ገፆችን ለመፃፍ የተዘጋጀች መስላ ነበር። እውነተኛ ብሄራዊ ነፃነትና ሕዝባዊ አርነት ፈንጥቆባት ነበር። ይሁንና ድሎቹ የተፃፉበት ቀለም ሳይደርቅ፣ ከመጋቢት 1969 ጀምሮ የብሄራዊ ነፃነታችንን ጥያቄ እንደገና ባዲስ ቀርቦ ነበር። ያሁኑ ፀረ ብሄራዊ ነፃነት ኃይል ግን ከቀድሞዎቹ ሁሉ ፈጽሞ የተለየ ነበር።

ለ/ አዲሱ ፀረ ብሄራዊ ነፃነትና ፀረ ሕዝብ ኃይል

አንደኛው ‘አብዮት’ አንደኛው ‘ሶሻሊዝም’ የሚል፣ በ ‘ወዛደራዊ አለም አቀፋዊነት’ና ‘በሶሺያሊስት ወንድማማችነት’ ስም እየነገደና እየተመፃደቀ ብሄራዊ ነፃነትን የሚደፍር፣ ለጋ አብዮታችን የሚቦረቡርና በመጨረሻም የሚያኮላሽ ነው። በመሆኑም፣ ያሁኑ የብሄራዊ ነፃነታችን ተቀናቃኝ ልዩና አደገኛ ነው። ይህም፣ የታላቁ የጥቅምት ሶሻሊስት አብዮት ድሎችን ቀልብሶ፣ ታላላቆቹ የወዛደር መሪዎች የገነቡትን ሶሻሊዝም ከሥር መሰርቱ ቦርቡሮ፣ ዓለም ዓቀፋዊ የኮምኒስት እንቅስቃሴ መመሪያ የሆነው ማርክሲዝም—ሌኒኒዝምን በርዞና ከልሶ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የሶሻሊዝምን ስምና ዝና ያጎደፈ፣ በመሰረታዊ ይዘቱ ከኢምፔሪያሊዝም ያልተለየው የዘመኑ ዛሮች— የሩስያ ተስፋፊና ጣልቃ ገብ መንግሥት ነው።

ስለሆነም፣ ሶቭየት ህበረት በስም እንጂ በገቢር ሶሻሊስት መሆን ካቆመች ዓመታት አልፈዋታል። ሶቭየት ህብረት በመሰረቱና በገቢር ኢምፔሪያሊስት የሆነች ኃያል መንግሥት ሁናለች። ሶሻሊስት ያልሆነና ኃያል መንግሥት ደግሞ በውጭ ፖሊሲው በምንም አይነት ሁኔታ ወዝአደራዊና ዓለም አቀፋዊ ሊሆን አይችልም። በመሆኑም፣ የሩስያ ተስፋፊዎች መንግሥት በዓለም አቀፍ ደረጃ ወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ አካባቢዎችን ለመቆጣጠር ከሌሎች ኃያል መንግሥቶች- በተለይም ከአሜሪካን ጋር በከፍተኛ ውድድርና ፉክክር ውስጥ የሚገኝ መንግሥት ነው። የውጭ ፖሊሲው ዋና መመሪያ፣ በየጊዜው እየሰፉ የሚሄዱ አካባቢዎችን በርሱ ተፅዕኖና ቁጥጥር ሥር ማዋል እንጂ፤ የሕዝቦች አብዮት፣ ነፃነትና ክብር አይደለም። የሩስያ ተስፋፊዎች መንግሥት በአንድ አገር ውስጥ ለርሱ ያደሩ ንዑስ ከበርቴዎችን በቢሮክራሲያዊ ከበርቴዎችን፣ ወይንም እንደርሱ በነማርክስና በነሌሊን ስም የሚነግዱ ጥቂት ከሃድያንን እጁ ካስገባና የሚፈናጠጣቸው እስካገኘ ድረስ፣ እነዚህም የርሱ ጫማ ላሽ ሁነው በአሻንጉሊትነት— በቅምጥ መንግሥትነት ካገለገሉት፣ ሕዝቦች በእርስ በርስ ጦርነት ቢተላለቁና ዕጣቸው በሚሊዮን መሰደድ ቢሆን፣ ሃገሮች በወታደራዊ አምባገነን አገዛዝ ታፍነውና ተረግጠው ቢገዙ፣ በኑሮአቸው ቢማቅቁና በረሃብ ቢረግፉ ደንታ የለውም። ፍላጎቱ፣ ከምዕራብ አገሮች ጋር ለዕውነተኛ ነፃነታቸው የሚታገሉ ሕዝቦች መካከል “በዓለም አቀፋዊነት ድጋፍ” ስም ሰርጎ መግባትና፣ አገሮችንና ሕዝቦችን በርሱ ተፅዕኖ ሥር ለማጠቃለልና ለመመዝበር ነው። ለዚህም፣ በደቡብ አሜሪካ ኩባ፣ በአፍሪቃ አንጎላና አገራችን፣ በእሲያ ቪየትናም፣ ኮምፑችያ፣ ላኦስና አፍጋኒስታን፤ በቅርብ ምስራቅ ደቡብ የመን ተጨባጭ የሆኑ ምሳሌዎች ናቸው። ከዚህም ሌላ በሶቭየት ህብረት ሥር የሚማቅቁት ራሳቸው የምስራቅ አውሮፓ ሕዝቦች አሉ። ከዚሁ በተያያዘ፣ ፍላጎቱ አገሮችን በተፅዕኖው ሥር ለማጠቃለልና ኃያልነቱን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማንገሥ የሆነ መንግሥት፣ የግዴታ ተስፋፊ፣ የግዴታ ጣልቃ ገብ መንግሥት ይሆናል። አልፎም በዕብሪት በተሞላው “የእኔ አውቅላችኋለሁ” ፖሊሲው ወደ ዘረኝነት ጭምር ይጠጋል። ሕዝቦችን ረግጦ ለመግዛት፣ ለስቃይና ለግፍ ዳርጎ የበላይነቱን ለማፅደቅ ይገደዳል።

“ይገደዳል”፣ ምክንያቱም አንድ ተስፋፊ መንግሥት ዓላማው አንድን አገር በቁጥጥር ሥር አውሎ በኢኮኖሚ በመመዝበር፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሚደረገው ትንንቅ መሣሪያ ለማድረግ ከሆነ፤ ይህ ፍላጎቱ የግዴታ ከሃገሪቱ ሕዝብ ፍላጎት ጋር ይጋጫል። አንድ ሕዝብ ደግሞ አብዮታዊ ትግል የሚያካሂደው፣ ደርሶ መታገል አምሮት ሳይሆን፣ የውስጥም ሆነ የውጭን የብዝበዛና የጭቆና ቀንበር ለመጣል ነው። ይህንን ዓላማ ከሥራ ላይ የሚያውል ሕዝባዊ፣ ዲሞክራሲያዊና ብሄራዊ የሆነ መንግሥት ለማቋቋም ነው። የአብዮቱ ግብ መምታትና የእንደዚህ አይነቱ መንግሥት መቋቋም፣ ከሩስያም ሆነ ከሌላ ተስፋፊ ዓላማ ካለው መንግሥት ጋር ሙሉ ለሙሉ ይፃረራል። የሩስያ ተስፋፊዎች፣ ጥቅማቸውን ሆነ ዓለም አቀፋዊ እስትራተጂያቸውን ከሥራ ላይ ለማዋል ሕዝባዊ ሳይሆን፣ አገሩንና ወገኑን ከድቶ ለእነርሱ ጥቅም ያደረ፤ ዲሞክራሲያዊ ሳይሆን እነሱው ዕዳ በዕዳ እየነከሩ በሚሰጡት መሣሪያ ታግዞ በፈላጭ ቆራጭነት የሚገዛ አምባገነናዊና ቅምጥ መንግሥት ይፈልጋሉ። በሌላ በኩል ግን፣ የሕዝብ ድጋፍ ያለው፣ የሃገሩን ብሄራዊ ጥቅም የሚያስቀድም መንግሥት የተስፋፊዎች ፀር እንጂ፣ ተባባሪ አይሆንም። ለዚህ ነው፣ የሩስያ ተስፋፊዎች ጥቅም መከበር የአብዮቱን መቀልበስ ይጠይቃል የሚባለውም። ለዚህ ነው፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ከመጋቢት 1969 በኋላ እያንዳንዱ ፀረ አብዮቱን የሚያጠናክር እርምጃ ሁሉ፣ በዚያው ልክ ብሄራዊ ነፃነታችንን ገደል እየጨመረው የመጣው። ለዚህ ነው፣ እያንዳንዱ ብሄራዊ ነፃነታችንን በይበልጥ የደፈረ እርምጃ ሁሉ፣ ከኢትዮጵያ አብዮት መቀልበስና ከብሄራዊ ነፃነቷ መገሰስ ጋር ተያይዞው የተከናወኑት። የሩስያ ተስፋፊ መንግሥትና ተቀጥላዎቹ በሃገራችን ላይ የፈጸሙትን የጣልቃ ገብነት ታሪክ ስንመለከት የምንረዳውም መሰረታዊ ሃቅ ይኸው ነው።

2. የሩስያ ተስፋፊ መንግሥት ወደ ሃገራችን መግባት

ሀ/ ከየካቲት በፊት

የህንድ ውቅያኖስ፣ ቀይ ባህርና የአፍሪቃ ቀንድ በዓለም አቀፍ ወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ ስትራተጂ ውስጥ ከፍተኛ ስፍራ አሏቸው። አብዛኛዎቹ የዓለም ገብያ ሸቀጦች በህንድ ውቅያኖስ ላይ ይመላለሳሉ። ቀይ ባህር ወደ አውሮፓና ሩቅ ምስራቅ እስያ ለሚተላለፈው ሸቀጥ አቋራጭ የባህር መንገድ ነው። የዘይት አምራች አገሮች በህንድ ውቅያኖስ፣ በቀይ ባህር ዙሪያ ተራ በተራ ተደርድረው ይገኛሉ። ወዲህም ደግሞ፣ በሰው ኃይልና በሌሎች የእርሻና የማዕድን ኃብታቸው የታወቁ ሃገሮች /እንደ ኢትዮጵያ/ የሚገኙት በዚሁ አካባቢ ነው። በወታደራዊ ሰፈርነታቸውም አንፃር፣ እነዚህ አካባቢዎች ለማጥቃት ሆነ ለመከላከል፣ ወይንም ለወታደራዊ ስለላና ሎጀስቲክ. . . እጅግ አመቺ የሆነ አቀማመጥ አሏቸው። የጂኦግራፊ ተፈጥሮአቸውና የአየር ባህሪያቸው ሁሉ እጅግ አመቺ ነው።

ስለሆነም፤ የዓለም ኃያላን መንግሥታት፣ ዙሪያችንና ሃገራችንን በተፅዕኖዋቸው ሥር ለማዋል ከፍተኛ ውድድርና ግብ ግብ ሲያካሂዱ ኑረዋል። ቀደም ሲል የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም የበላይነቱን ይዞ ሃገራችንን ጭምር በተፅዕኖው ሥር አድርጎ ይገኝ ነበር። ይሁንና፣ ሶቭየት ህብረት በዚያን ጊዜም ቢሆን አልተኛችም ነበር። አካባቢያችን አገሮች ኢ ዲ አሚን ሳይቀር በግብፅ፣ በሱዳን፣ በሱማሊያና በደቡብ የመን ሃገሮች ላይ ከባድ ተፅዕኖዎችን አሳርፋ ኑራለች። ከዚህም ባሻገር፣ የአፍቃሪን ቀንድ በሚመለከተው፣ ገና ከ60ኛው ዓመት ጀምሮ፣ “የአፍሪቃ ቀንድ ሃገሮች በዘርና በባህል ተመሳሳይነት አሏቸው” በሚል ሱዳን፣ ኢትዮጵያ፣ ጅቡቲ፣ ሱማሌና የሁለቱ የመን ግዛቶች በአንዳች ዓይነት የፌደራል መንግሥት ሥር ተጠቃልለው በርሷ የበላይነት ሥር እንዲተዳደሩ ታቅዶ እነደነበር የታወቀ ጉዳይ ነው። ይህ፣ ሶቭየት ለአፍቃሪ ቀንድና ከዚያም ባሻገር የተለመችው “የፌደራል መንግሥት” እቅድ፣ በሩቅ ምሥራቅ እስያ ለቪየትናም—ካምፑችያ—ላኦስ ከተለመችው እቅድ በምንም አይለይም። እንዳውም፣ በስፋቱ ሆነ በአጠቃላይነቱ እጅግ የላቀ ነው። አልፎም ወደ ዘረኝነት ተጠግቶ “ለፌደሬሽኑ” መሠረት የሚያደርገው “ዘርና ባህልን” እንጂ፣ የዲሞክራሲያዊና የለውጥ መመሪያዎችን እንኳን አይደለም።

ኢትዮጵያን በሚመለከተው በኩል፣ ሶቭየት ህብረት ገና በኃይለሥላሴ ዘመን በብዙ ዘዴ ስር ለመስደድ ትሞክር ነበር። ከዚህም አልፎ፣ ለመጭው ጊዜ “ዝግጅቶችን” ታደርግ ነበር። በነጋሲው አገዛዝ ሥር ከፊውዳል ኃይለሥላሴ ጋር ሶቭየት የነበራትን “የወዳጅነት” ፖለቲካ ማንም ያስታውሳል። “ታላቁ መሪ” “የአፍሪቃ አባት”፣ “ዘመናዊው ንጉሥ” ከማለትም አልፋ፣ የነመንግስቱ ነዋይን የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ፣ “የሃገሪቱን እርምጃ ለማደናቀፍ የቀኝ ኃይሎች የጠነሰሱት ሴራ” በሚል “ኒው ታይምስ”  በተባለው ጋዜጣዋ ላይ አትታ እንደነበርም ይታወሳል። በጊዜው በነበረው የተማሪ እንቅስቃሴም ላይ ልክ ዛሬ እንደምታደርገው ልዩ ልዩ መሰናከሎችን ታደርግ እንደነበር በጊዜው በሶቭየት ህብረትና በምሥራቅ አውሮፓ የነበሩት ተማሪዎች ያስታውሱታል። በኢኮኖሚ ይዞታም በኩል ሥር ለመስደድ /ባልቻ ሆስፒታል፣ ባህር ዳር ፖሊ ቴክኒክ፣ በአሰብ ዘይት ማጣሪያ፣ በልዩ ልዩ የንግድ ድርጅቶች. . . ወዘተ አማካኝነት/ ስትሰረስር ቆይታለች። የፖለቲካውን በሚመለከት ደግሞ፣ በዚህ ጊዜ ውስጥ በይበልጥ ያተኮረችው፣ “ከንጉሥ ኃይለሥላሴ በኋላ” ለሚደረገው ትግል ተጠሪዎቿን በማዘጋጀት ላይ እንደነበር የሚሰራጭ በርካታ መረጃዎች አሉ። ይህንን ጉዳይ በሚመለከተወው ወደ መኢሶን ታሪክ ተመልሰን ብናስታውስ እንኳን፣ ገና በኃይለስላሴ ዘመን “ምነ አለ    አንድ አሥራ አንድ ሁናችሁ ፓርቲ ብትመሰርቱ?በተረፈው እኛ እንረዳችኋለን፡” እየተባሉ ከሶቭየት በኩል የተነገራቸው የመኢሶን አመራር አባሎች ጥቂት አልነበሩም። እነርሱ፣ ምንም እንኳን መኢሶንን መሥርተው በህቡዕ በመታገል ላይ ቢገኙም፣ “እኛ ተማሪዎችና ምሁራን ነን. . . እንዲህ አይሆንም” ሲሉ አሳፍረው መልሰዋቸዋል። የሩስያ ተስፋፊዎች ግን፣ የኢህአፓ ምሥራቾች ዘንድ ተልከስክሰው የኋላ ኋላ ሁሉ የኢትዮጵያን አብዮት በአፍላው ላይ አንዴት እንዳሳወቁ የታወቀ ጉዳይ ነው። በዝርዝር ወደፊት የቀንን ብርሃን ማየቱ ደግሞ አይቀርም። ከዚህ ላይ ግን የሩስያ ተስፋፊዎች ኢትዮጵያን በቁጥጥራቸው ሥር ለማድረግ ያበቃቸው ዋና ዋና ሥራ ላይ ማተኮሩ በቂ ነው።

ለ/ ከየካቲት ወዲህ

ከ1966 ዓ.ም. ወዲህ፣ አብዮቴና ነፃነቴ በሚሉ ሃቀኛ ተራማጆች ሥር እየሰደደ የገፋው የየካቲት አብዮት ሩስያ ተስፋፊና ተጋፊ መንግሥት መግቢያ ቀዳዳ አልተከፈተለትም ነበር። በተቃራኒው፣ አገራችን እውነተኛ ገለልተኛና ነፃ ሃገር እንድትሆን ሃቀኛ ተራማጅ፣ ዲሞክራትና ሃገር ወዳድ የተያያዘውን ትግል አፋፍሞ ቀጠለ። ለዚህ ራሱ የብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራም ሊጠቀስ የሚችል ትልቁ ማስረጃ ነው። በወቅቱ ስለራስ መተማመንና በብሄራዊ ነፃነት ጥያቄዎች ላይ የተሰጡትን የትምህርትና የፕሮፖጋንዳ ቅስቀሳዎችን ማስታወስም ይቻላል. . . .ወዘተ።

ይሁንና፣ በዚሁ ጊዜ ውስጥ ደግሞ፣ ለብሄራዊ ነፃነታችን የሚያሰጉ አንዳንድ እርምጃዎች በያኔው የንዑስ ከበርቴ የደርግ መንግሥት አልተወሰዱም ማለት አይደለም። በዚህ አንፃር ከሁሉም በላይ መነሳት ያለበት ጉዳይ፣ ደርግ አንዳንድ አባሎቹንና ሌሎችን “ለፖለቲካ ትምህርት” በሚል ወደ መስኮብ መላኩ ነው። የሩስያ ተስፋፊ መንግሥት በቁጥጥር ሥር ሊውሉ የሚችሉ ከሃዲዎችን ሊመለምል የቻለውም ይህንኑ አጋጣሚ በመጠቀም ነበር። እንደሚታወቀው የኋላ ኋላ “አብዮታዊ ሰደድ” ተብሎ በወጣው ድርጅት ውስጥ፣ በ፶ አለቃ ለገሰ አስፋው የሚመራውን ከሃዲና አረመኒያዊ ቡድን በማቋቋም እንደልቡ ሊጠቀምበትም ችሏል።

የሩስያ ተስፋፊና ጣልቃ ገብ መንግሥት የሃገራችንን የብሄራዊ ነፃነት በር ለመበርገድ የበቃው ግን ይልቁኑ እራሱ አስታጥቆና ገፋፍቶ የለቀቁብን የሶማሌ ጦር ድንበራችንን በደፈረበት ወቅት ነው።

  • የሱማሌ ወረራና ሶቭየት ህብረት

ሶቭየት ህብረት በአፍሪቃ ቀንድ ያሉ አገሮችን ባለ በሌለ ኃይሏ በቁጥጥር ሥር ማድረግን አላማዋ ከአደረገች ብዙ ጊዜዋ ነው። ሱማሌ በርሷ ቁጥጥር ሥር በነበረችበት ወቅት ኢትዮጵያም ከተደመረች አላማዋ ግቡን ለመምታት ተቃረበ ማለት ነው። በየሃገሩ የርሷ ቅምጥ መንግሥቶች ከተቋቋሙ፣ በርሷ የበላይነት በቅድሚያ ሱማሌ፣ ጅቡቲና ኢትዮጵያን በኋላም ሌሎችን የሚጠቀልል “ፌደሬሽን” ማቋቋሙ አይገድም። ይህ እንዲሆን ግን ኢትዮጵያን በራሷ ቁጥጥር ሥር ማድረጉ የማይታለፈው ተግባሯ ነበር። እንዴት ይሆናል? እርሷ አስታጥቃ ያሰለጠነችው የሱማሌ ጦር፣ ኢትዮጵያ ገና በአብዮት አፍላ ላይና ከምዕራብ ኢምፔሪያሊዝም ጋር ቅራኔ ውስጥ ባለችበት ወቅት፣ ወረራ እንዲካሄድ፣ ወረራው ሲገፋ የኢትዮጵያ አብዮትና አንድነት እንዲወጠር፤ የኢትዮጵያ አብዮትና አንድነት አደጋ ላይ ሲወድቅ በኢትዮጵያ ውስጥ ባሏት ምልምሎቿ አማካይነት ኢትዮጵያ ዝቅ ብላ የሩስያ ተስፋፊዎች መንግሥትን እጅ እንድትነሳ፣ ብሄራዊ ነፃነቷን አስረግጣ እንድትማጠን፤ በሶቭየት ህብረት የበላይ ዳኝነት የሱማሌና የኢትዮጵያ “ችግር” መፍትሄ እንዲያገኝ፤ በኢትዮጵያና በሱማሌ ቅምጥ መንግሥቶች አማካይነት የአካባቢውን በዓለም አቀፍ የጦርነትና የምዝበራ ስትራቴጂዋ ውስጥ አስገብታ ሕዝቦቻቸውንና ሃብቶቻቸውን መመዝበር። የሩስያ ተስፋፊዎች መንግሥት ዕቅድ ይህ ነበር። ሆኖም ዕቅድ ሁሌም እንደተተለመው አይገጥምምና፣ የኋላ ኋላ ሶቭየት ህብረት በሱማሌና በኢትዮጵያ መካከል ምርጫ ማድረግ ተገዳለች። ኢትዮጵያ ለወረራ በማጋለጥና በማመቻቸት ሶቭየት ህብረት የተጫወተችውን ሚናና ያኔ የነበረውን  ሁኔታ ከዚህ የበለጠ ገባ ብሎ መመልከቱ ነገሩን ይበልጥ ግልጽ ያደርገዋል። የሁኔታው ሂደት ዝቅ ብለን እንደምናየው ፈጣንና ሤራ የተሞላበት ነበር።

እንደሚታወቀው፣ ከመጋቢት 1969 ዓ.ም. አንስቶ፣ የሩስያ ተስፋፊዎች የ“ሶሻሊዝም” ስምንና “የዓለም አቀፋዊ ወዛደራዊነት” ባንዲራቸውን አንግበው ኢትዮጵያን መቅረብ ይጀምራሉ። የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ከአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝምና ከቡችሎቻቸው ጋር የሞት የሽረት ትንንቅ ሲያደርግ ይልቁንም ከጠላቶቹ ጋር ውስጥ ውስጡን ያልተሰለፉትን ያህል፣ ምንግዜም “ከጎናችሁ ነበርን”፣ “አብዮቱን ካልደገፍን ሞተን እንገኛለን ይሉ ጀመር። “በውነቱም” ይሉ ገቡ፣ “በውነቱም ስለአብዮታችሁ እስካሁን ያላወቅነው በዜና እጥረት ምክንያት ነው” እያሉ፣ ይቅርታ ማለት ሲቀራቸው አድናቆታቸውን አጎረፉት. . . . ወዘተ። የባህል መልእክተኞቻቸውነና ልዩ ልዩ አማካሪዎቻቸው በብሄራዊ ቲያትርና በየአብዮት አደባባይ ተዋናዩ . . . . ወዘተ. . . ። የሶቭየት ህብረትና የተቀጥላዎቿ ቀንደኛ መሪዎችም፣ ገና እግራቸው አገራችንን እንደረገጠ፣ የቆየ “የፌደሬሽን” ህልማቸውን ከሥራ ላይ ለማዋል ያሽቃብጡ ጀመር። በመጋቢት 1969፣ በኤደን ከተማ ውስጥ በካስትሮ ሊቀመንበርነት የተካሄደው የሻለቃ መንግሥቱ /ዚያድ ባሬ ድርድር ዓላማም ይኸው ነበር። በድርድር ወቅት ካስትሮ ከዚህ በላይ ያነሳነውን “የፌደሬሽን” ሃሳብ ለሁለቱም መሪዎች አቅርቦ “ለማግባባት” ሞከረ። ዚያድ ባሬ ተቀበለው።

ዚያድ ባሬ ሃሳቡን በወቅቱ የተቀበለው፣ “ፌደሬሽን” የሚባለው ነገር “ኢትዮጵያን፣ ኡጋዴንን፣ ሱማሌን..” እንዳያጠቃልል በሚል ነበር። የሩስያ ተስፋፊዎች፣ ይህንን ሃሳብ ያመነጩትና የሚደግፉትም ቢሆኑ የኢትዮጵያን እምቢታ ለመወጣት ዘዴ መፈለግ ነበረባቸው። በመሆኑም፤ ባንድ በኩል፣ ሱማሌ በጦር ኃይል ኦጋዴንን እንድትወርና እንድትይዝ፣ በዚህ መልክ ኢትዮጵያ በተከላካይነት ደረጃ ከተቀመጠች በኋላ የፌዴሬሽኑ ሃሳብ እንደገና እንዲነሳ ያሴራሉ። ለዚህም እንዲያመች፣ 14 ዓመት ሙሉ ያስታጠቁትን የሶማሌ ጦር ከመጋቢት 1969 በኋላ በጥድፊያ ስንቅና መሣሪያ እያጋዙ ያጠናክሩት ጀመር። በሌላ ወገን ደግሞ፣ ኢትዮጵያን ትጥቅ ወደ ማስፈታት ተሻግረው “በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተቀነባበረው መረጃችን እንደደረስንበት” ይሉ ጀመር። “በሚመጡት ወራት ኢድዩና ኤርትራውያን ከግብፅና ከሱዳን ጋር በመተባበር ከፍተኛ የጥቃት ዘመቻ ያደርጋሉ በሱማሌ በኩል /በኛ ይሁንባችሁ!/ ምንም አደጋ የለም። ስለዚህ ኦጋዴን ያለው ሜካናይዝድ ጦር ወደ ሰሜን ይሂድ” የሚል ሃሳብ ለደርግ ያቀርባሉ። እንደውነቱም ከሆነ፣ ባልቀረው የሱማሌ ወረራ ጥያቄ ላይ በዚያን ጊዜ የታየው ታሪክም እጅግ አስደናቂ ነበር።

ከሃረርጌ የሕዝብ ድርጅት ፅ/ቤት የሚደርሱ መረጃዎች ሱማሌ ለወረራ በመዘጋጀት ላይ መሆኗን ይገልፃሉ። በጊዜው የፅ/ቤት ኃላፊ የነበረው ጓድ አብዱላሂ የሱፍን/ በነርሱ እጅ በቅድሚያ መስዋዕት የሆነውም ለዚህ ነው/ አንደኛ፣ ያካባቢው ጦር እንዲጠናከር፣ ሁለተኛ፣ ሕዝብ እንዲታጠቅ በማለት በተደጋጋሚ ይጠይቃል። በኋላ ይፋ ወጥቶ የታየው የሩስያ ተስፋፊዎች አሻንጉሊት፣ በደርግና በ“አብዮታዊ ሰደድ” ውስጥ የተቀመጠው የነ፶ አለቃ ለገሰ አስፋው ቡድንና አድሃሪው ቢሮክራሲ ግን ምን ይሉ ነበር??

“አደጋ የለም መኢሶን ሕዝብ ይታጠቅ እያለ የሚጨቀጭቀው ትጥቅ ለመሰብሰብ ነው” ወዘተ.   

ምን ይሄ ብቻ! በሰኔ ወር 1969 ዓ.ም. ከሃረርጌ፣ ከሲዳሞና ከባሌ ሕዝብ የተላኩ የገበሬ ማህበራት መሪዎች አዲስ አበባ ድረስ መጥተው፣ የአደጋውን አሳሳቢነት በመግለጽ ትጥቅ እንዲሰጣቸውና መንግሥትም መግዛት ካቃተው አዋጥተው ወጭውን ለመቻል ዝግጁ መሆናቸውን ሁሉ አስታውቀው ነበር። ይህም “የመኢሶን ሤራ” ተብሎ፣ የገበሬዎቹ መልዕክተኞች አዲስ አበባ ውስጥ ለብዙ ጊዜ ሲንከራተቱ ከቆዩ በኋላ ባዶ እጃቸውን ተመልሰዋል። የደርግ ልቡና በተቃራኒ ባንድ ወገን ተስፋፊዎች በሚሰጡት መረጃና ማረጋገጫ ተስልቦ ነበር። በሌላው ወገን፣ ለሃገር ጉዳይ ከመጨነቅ ይልቅ መኢሶንን በመፍራትና በመጠራጠር የፀረ አብዮተኞችን ብብት ማሽተት ጀምሮ ነበር።

ነገር ግን፣ ለጥቃት በተጋለጠው የምሥራቅና የደቡብ ምሥራቅ ድንበር ዙሪያ በጥቂት ቀናት ውስጥ የጦርነት ደመና አንዣበበ። የሱማሌ ጦር በየዕለቱ ሺህ በሺህ እየሆነ ጎረፈ። የሩስያ ተስፋፊዎች “ሱማሌን እንገታለን” እያሉ ደርግን የሰበኩት ቃል ነጭ ውሸት ሆኖ የተጋለጠውን ያህል፣ ቢሮክራሲው “ስለ ሰርጎ ገብ አንድም ተጨባጭ መረጃ የለም” እያለ የዘራው መረጃ፣ ከባድ የፀረ አብዮት ተንኮል እንደነበር ገሃድ ሆነ። ይሁንና፣ ኢትዮጵያ በምኗ ትከላከል??

የውጋዴኑ የጦር ኃይል በሩስያ ተስፋፊዎች ሤራ ወደ ሰሜን ተልኳል። አብዛኛው ሠራዊት በኤርትራው ጦርነት ተጠምዷል። ባጭሩ፣ ከራሱ ከሕዝቡ በስተቀር ሌላ ኃይል የለም። ሕዝቡ “ትጥቅ! ትጥቅ! እያለ ይጮሃል። አድሃሪው ቢሮክራሲ “የመኢሶን ተንኮል” እያለ ያላዝናል። ደርግ ሕዝቡን ቀስቅሶና አስታጥቆ ማዝመቱን ይፈራል። የሩስያ ተስፋፊዎችና ተቀጢላዎቹ “ታገሱን፣ አቋማችንን እናስታውቃለን” እያሉ ጊዜ ለመግዛት አድብተዋል። ጊዜ የሚገዙት ሃገሪቱ የበለጠ ተጨናንቃ እግራቸው ሥር የምትወድቅበት ጊዜ እስኪመጣ ነበር። የጠበቁትም አልቀረም። የሱማሌ ወረሪ ጦር መድፍና መትረየስ ጅጅጋን ተሻግሮ በሃረርና በድሬደዋ ከተሞች ላይ ያጓራ ጀመር። በዚህ አስከፊ ወቅት፣ ሽንጣቸውን ገትረው ሲዋደቁ የነበሩት፣ በአካባቢያቸው የሕዝብ ድርጅት ፅ/ቤት ካድሬዎች እየተመሩ ሕይወታቸውን የሰውት የድሬደዋ ሲሚንቶና የጥጥ ፋብሪካ ወዛደሮች፣ የገበሬ ማህበራት ጥበቃ አባላት፣ የአካባቢው ገበሬዎችና ወጣቶች ነበሩ። ይህን ወደፊት ታሪክ በሚገባ ይገልፀዋል።

የሆነው ሆኖ፣ ኡጋዴን እንደተያዘ አንድ በብርሃኑ ባየህ የሚመራ የመልዕክተኞች ቡድን፣ “ሱማሌዎችን ግቱልን እንጂ” ለማለት ወደ ሶቭየት ህብረት ሄዶ ነበር። የሱማሌ መልዕክተኞችም እዚያው ሞስኮ ከተማ ይገኛሉ። ይሁንና፣ የብርሃኑ ባየህ ቡድን ሞስኮ ከተማ ሆቴል ውስጥ ለአንድ ሳምንት ያህል ሲቀመጥ፣ እንኳን ብሬዥኔቨና ኮሲጊን ቀርቶ በወጉ የሚቀበለው ሌላ ባለሥልጣን ሳያገኝ ይከርማል። በመጨረሻ ላይ፣ አንድ የውጭ ጉዳይ ባለሥልጣን ቢቀበለውም፣ “ሱማሌዎችም እዚሁ አሉላችሁ። በውጋዴን ጉዳይ ላይ ተወያዩ” ብሎ ከመሸኘት ሌላ የጨመረበት ነገር አልነበረም። ይህ ቡድን እንደተመለሰም፣ በጠቅላላው በደርግ አካባቢ “ሶቭየት ሸረሞጠች !” / የተጠቀሰው ቃል በቃል ነው/፣ “በመረጃ ስም ጉድ ሠሩን”፣ “ተከላካይነት ደረጃ አውርደውን ተደራደሩ ይሉናል” የሚለው ትችት በሰፊው ይሰማ ነበር።

ነገር ግን በዚያው ሰሞን ደግሞ፣ ሱማሊያ በሶቭየት ህብረት የተሰጣትን የኡጋዴን ገደብ አልፋ መሻገሯና እስከ አዋሽ ድረስ ለመዝለቅ የዘረጋችው እቅድና እንቅስቃሴ ይፋ ወጣ። የሩስያ ተስፋፊዎች ይህንን የሱማሌ እርምጃ/ ማለትም ከኡጋዴን ክልል ማለፍ/ በሱማሌ በኩል “ቃል እንደተጣሰባቸው” አድርገው አቀረቡት። በአፍቃሪ አገሮችና በዓለም ሕዝቦች ፊት ሱማሌን ደግፈው ለመቆም እንደማይችሉ ግልጽ ሆነላቸው። በመጀመሪያ፣ ሱማሌን በዲፕሎማሲ ግንኙነቶችና በምክር ለመጫን ሞከሩ። ከኡጋዴን እንድታልፍ አጥብቀው አሳሰቧት። ሱማሌ ግን አሻፈረኝ አለች። የሩስያ ተስፋፊዎችን የማግባባት ሙከራ በተቃራኒ ክህደት እንደተፈፀመባት አድርጋ ቆጠረችው። በጀመረችው ጦርነት ገፋችበት። “ያልታሰበ” እንበለውና፣ አዲስ ሁኔታ ተፈጠረ።

የሩስያ ተስፋፊዎች በአፍሪቃና በዓለም አቀፍ ፖለቲካ አንፃር ወገን እንዲመርጡ ተገደዱ። በተፈጠረው ሁኔታ የኢትዮጵያ አቋም በአፍሪቃና በዓለም አቀፍ ፖለቲካ ውስጥ፣ ተደጋፊነት እንዳለው የታወቀ ነበር። ስለሆነም፣ ፊታቸውን ወደ ደርግ አዞሩ። “ከተወረረችው ኢትዮጵያ ጎን ተሰልፈን እንገኛለን” በማለት፣ የተጠቁ ሕዝቦች ወዳጅነታቸውንም ለፈፉ። ነገር ግን ውስጣዊ ምክንያታቸው ሌላ ነበር። ዞሮ ዞሮ፣ ከሱማሌና ከኡጋዴን ይልቅ፣ የ30 ሚሊዮን ታታሪ ሕዝብ ባለቤት የሆነችው ሃብታሟና ለምለሚቷ ኢትዮጵያ ሺህ ጊዜ የበለጠ እንደምታዋጣ በማሰባቸው ነበር። ደግሞም በወረራው ተደናግጦ የሚይዝ የሚጨብጠውን ያጣው ደርግ፣ ከነርሱ ጫማ ስር ለመውደቅ የተዘጋጀ መሆኑንም አውቀውታል። ቀድሞውንም ቢሆን ያሴሩ የነበሩት ለዚህ ሁኔታ መፈጠር ነበር። ሰመረላቸው። እንዲያውም፣ ከዚህ ሌላ በሤራቸው ውስጥ፣ ዚያድ ባሬን ሊያስኮርፍ ለሚችል ሁኔታ ሁሉ የተዘጋጁ ነበሩ። የዚያድ ባሬ መንግሥት ያካሄደው ወረራ ከከሸፈ ወዲህ የተሞከረበት መፈንቅለ መንግሥት የሚያረጋግጠው ይህንኑ ነው። የሩስያ ተስፋፊዎች ዕቅድ በዚያም ሆነ በዚህ፣ በሱማሌና በኢትዮጵያ ሁለት ቅምጥ መንግሥቶችን ማቋቋምና የአፍሪቃ ቀንድ በቁጥጥር ሥር ማዋል ነበር። ከዚያም “የፌደሬሽኑ” ነገር።

ይሁንና፣ ከዚያ ጊዜ በኋላ፣ ሱማሌ “ክህደት ተፈጸመብኝ” በማለት በሃገሯ ውስጥ የሚገኘውን የሶቭየት ህብረት ተወላጅ በ48 ሰዓት ውስጥ አባረረች። ከፊደል ካስትሮ መንግሥት ጋር የዲፕሎማሲ ግንኙነቷን አቋረጠች። የምዕራብ አገሮች የፖለቲካ፣ የመሣሪያና የማቴሪያል እርዳት እንዲሰጧት አካባቢዎችን ማሰስ ጀመረች። ኢትዮጵያችንም፣ የሩስያ ተስፋፊና ጣልቃ ገብ መንግሥት በእጅ አዙር የሚገዛት የቅኝ ግዛት ወደ መሆን አመራች። በዚህም የሱማሌ ወረራና የሩስያ ተስፋፊዎች ሤራ የመጀመሪያው ዙር መጋረጃ ይዘጋል። ከዚህ በኋላ የሆነው የታወቀ ነው።

ጠቅላላው የአፍሪቃ ቀንድ አካባቢ በከፍተኛ ደረጃ የሁለቱ ኃያል መንግሥታት የፍልሚያ አውድማ ሆነ። የአካባቢው ሕዝቦች፣ ሁለቱ ኃያላን መንግሥታት ለሚያደርጉት ጦርነት ጭዳ ለመሆን ተጋለጡ። ኢትዮጵያም ሆነች ሱማሌ በሕዝባቸውና በሃገራቸው የሚያዙ ነፃ ምድሮች መሆናቸው ቀርቶ፣ የሁለቱ ኃያላን መንግሥታት ዓለም አቀፋዊ ስትራቴጂ ውስጥ ወደ ተራ ጠጠርነት ተዋረዱ። ሱማሌ ለአሜሪካ የጦር ሰፈሮች ሰጠች። ቅምጡ ወታደራዊ አምባገነን መንግሥትም ኢትዮጵያን የሩስያ ተስፋፊዎች የጦር ሰፈር አደረጋት። ተጨማሪ የጦር ሰፈሮችን /የዳህላክ ደሴቶች፣ ምፅዋ፣ አሰብ/ ለመስጠት ተዋዋለ። ባሁኑም ሰዓት፣ ተጨማሪ የባዕድ ወታደሮችን ለማስፈር እያሰፈሰፈ ነው። በአካባቢው ያለው አደገኛ ሁኔታ የሚያመለክተው ሁለቱ ኃያላን መንግሥታት በአፍሪቃ ቀንድ ላይ የሚያደርጉትን ከባድ ጦርነት ነው። የነርሱ ባልሆነው ጦርነት የሚረግፉት ደግሞ የአካባቢው ሕዝቦች መሆናቸው የታወቀ ነው። በዚህም፣ ብሄራዊ ነፃነታችንን አስረግጦ ኢትዮጵያን የሩስያ ተስፋፊዎች የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት ያስደረጋት ቅምጡ መንግሥት ከተጠያቂነት አያመልጥም። ዛሬ “በርበራ ኪሰማዩ ጦርነት ወረራ” እያለ የዓለም ሕዝቦችን ማደንቆሩ ይህንን ሃቅ አይቀይረውም። “ቀድሞውንስ ኢትዮጵያን የሩስያ ጦር ሰፈር ባታደርጓት በኢትዮጵያ የሰፈሩትስ ሩስያዊያን ለየትኛው የሰላም ተልዕኮ ይሆን?” ሲሉ ነፃ ሕዝቦችና ሃገሮች መሣለቂያ ሲያደርጉ ማየቱም አያስደንቅም።

  • የሩስያ ተስፋፊ መንግሥት ሥር መስደድ

እንደሚታወሰው፣ ከሰኔ/ ሐምሌ 1969 ጀምሮ፣ ሃገራችን አይታው የማታውቀው እልቁ መሳፍርት የጦር መሣሪያ በአንቶኖቭ እየተጫነ ምድራችንን አጥለቅልቀው። ይህች ያሻው ወረራ ቢፈፅምባት፣ የባዕድ ወታደሮችን “ድረሱልኝ” ብላ የማታውቅ የኩሩ ጀግኖች አገር በጥቂት ሳምንታት ውስጥ በሺህ በሚቆጠሩ በኩባና በደቡብ የመን ወታደሮች ጫማ ተረገጠች። 30 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ጀግና ሕዝብ ያንዲት ሱማሌን ጦር መቋቋም ያቅተው ይመስል፣ “የወዳጅ አገሮች” ጦር በምድሯ ላይ ፎለለ። ሕዝቧ እንኳን ከፍሎ ጥሮም ከማይጨረሰው እዳ ውስጥ ተዘፈቀ። ደርግ በሩስያ ተስፋፊዎች ኪሱ ውስጥ የወደቀ ጠጠር ሆነ። ከንግዲህ ያለው ታሪካችን፣ ሰህድ ገና በመጋቢት 1969 ዓ.ም. እንዳለው፣ ባንድ በኩል በአብዮት መኮላሸትና መቀልበስ፣ በሌላው በኩል ደግሞ በብሄራዊ ነፃነታችን መገሰስ፣ እየተጠናከረ በመጣው የሩስያ ተስፋፊና ጣልቃ ገብ መንግሥት ተፅዕኖና ቁጥጥር፣ ብዝበዛና ምዝበራ አይነተኛ ሆነ። ሕዝባዊ ኃይሎች ተራ በተራ ተጠቁ። ለሦስት ዓመታት ሙሉ ለህዝባዊነትና ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ የተዋደቀው ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሩስያ ተስፋፊዎች ቅምጥ-አሻንጉሊት በሆነ የወታደራዊ አምባገነን አገዛዝ ሥር ወደቀ።

ያ ያላንዳች የውጭ እጅ በሃቀኛ ሃገርና ወገን ወዳድ የኢትዮጵያ ተራማጆች የተዘጋጀው፣ የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ በማጤን የሰፊውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍላጎት መነሻ በማድረግ የወጣው፤ ያ ያብዮቱን ኃይሎች ሁሉ ለመሰብሰብና በዲሞክራሲያዊ የሕብረት መድረክ ላይ ለመሰለፍ ሆኖ የተዘጋጀው ሳይንሳዊው የአብዮታችን መመሪያ— የብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራማችን ዕውነተኛ የሃገሪቱ የፖለቲካ መመሪያ መሆኑ ቀርቶ፣ የዘመናዊ ባንዳዎችና ተስፋፊዎች መመፃደቂያና ጭንብላቸው እንዲሆን ተበየነበት። ያ ብሄራዊ ነፃነታችንን የማያስደፍርና የማንም ኃያል ሆነ የባዕድ መንግሥት የበላይነትን ነፃነትን የማይቀበለው፣ እንኳንስ እንደምዕራብ ኢምፔሪያሊዝም በግልፅ የሚጋፋንን ቀርቶ፣ እንደ ሩስያ ተስፋፊ መንግሥት “በሶሻሊዝም”ና “በወዛደራዊ ዓለም አቀፋዊነት” ተኳኩሎ ለሚመጣ ኃይልም መግብያ ቀዳዳ የማይሰጠው፣ የኢትዮጵያን ሕዝቦች ጥቅምና የራስ ዕድል በራስ የመወሰን መብት ማስቀደም እንጂ፣ አገራችን የማንም ኃያል መንግሥት ተቀጥላ መሆኗን አምርሮ የማይቀበለው የአብዮታችን ፕሮግራም ከተስፋፊዎች መግባት ጋር ተይይዞ አለቀለት።

የወዝአደራዊነትና የሶሻሊዝም ሽታውም በማይነፍስበት “በሶሻሊስት ወንድማማችንት” ና “በወዛደራዊ ዓለማቀፋዊነት” ስም አጊጦ የብሄራዊ ነፃነታችንን በር የበረገደው የሩስያ ተስፋፊና ጣልቃ ገብ መንግሥት ምድራችንን ከረገጠ ወዲህ፣ የቅልበሳው ሴራ በየፈርጁ ተጠምጥሞ አብዮታችን ተቀለበሰ። “እኔ አውቅላችኋለሁ” በሚል የገዢዎች ፈሊጥ የኢትዮጵያ ሃቀኛ ተራማጆችን፣ አገር ወዳዶችን፣ ዲሞክራቶችንና አርበኞችን ሁሉ ከጥቃቅን የዕለት ጉዳዮች አንስቶ እስከ ጦሩ ግንባር ድረስ በየመስኩ በየሥፋራው ተፈታትኖ ቁጥጥሩንና ተፅዕኖውን አንሰራፋ። የመላ ሃገሪቱን ወታደራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ የፖለቲካና የማህበራዊ ተቋሞችን በእጁ እያስገባ ሄደ።

በቅድሚያ፣ በ“ጦር ዕርዳታ” ስም በመላው የኢትዮጵያ ሠራዊት ላይ የበላይነቱን ተቀዳጀ። የኢትዮጵያ ሠራዊት ቢሻው በመሳሪያ ቢሻው በሎጀስቲክ፣ ቢሻው በጦር ትዕዛዝ፣ ቢሻው በእሥራት በዝውውርና በሞት ቅጣት ጭምር እንደልቡ ያወጣውና ያወርደው ጀመር። የእዝ ሰንሰለቱን ያዘ። እንደውነቱም ከሆነ፣ የኢትዮጵያ ሠራዊት በታሪኩ ውስጥ እንደዚህ ጊዜ የባዕድ ጦር “አማካሪዎች” ና አዛዦች ተገዢና ተላላኪ ሆኖ አያውቅም።  የኢትዮጵያ ጦር  አዛዦች እንደዚህም ዘመን ለስሙ የተቀመጡ አሻንጉሊቶች ሆነው አያውቁም። በዚህ ላይ፣ ወደ 20 ሺህ የሚጠጋ “የወዳጅ” ጦር ከነጦር ሰፈሩ ተንሰራፍቷል። እስከዚህ ድረስ የኢትዮጵያን ምድር የደፈረ የባዕድ ጦር ቢኖር የፋሽስቱ ሙሶሎኒ ጦር ብቻ ነበር።

3. የሩስያ ተስፋፊ መንግሥት ወታደራዊ ተፅዕኖና ቁጥጥር

በታሪክ ውስጥ መቼም ቢሆን እንደታየው፣ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ነፃነት ለመድፈር የሞከሩ የባዕድ ኃይሎች “ኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት ልናደርግ ነው” ሲሉ ከማስጠንቀቂያ ጋር የመጡ የዋሆች አልነበሩም። ባለፈው ክፍለ ዘመን ጣልያንም ሆነች ፈረንሳይና እንግሊዝ፣ በዚህ ክፍለ ዘመን ደግሞ እንግሊዝም ሆነች የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም፣ ማናቸውም ቢሆኑ ኢትዮጵያን የቀረቧት እጅ መንሻ ሳይዙ አልነበረም። እንደው ታሪክን እናስታውስና፣ ባለፈው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያን ለመቃረጥ ከቋመጡ መንግሥታት ጋር፣ የቀድሞዋም ሩስያ ድርሻዋን ለማግኘት ስትሯሯጥ፣ “ለኢትዮጵያ የክርስትና ሃይማኖት ጳጳስ የማቅረብ መብት ይገባኛል” ስትል ነበር ብቅ ያለችው። ታዲያ፣ ያኔ የተላከው የጳጳሱ የሃይማኖትና የሳይንስ ምርምር ቡድን “ወታደራዊ እንጂ ሳይንሳዊና ሃይማኖታዊነቱ ምኑ ላይ ይሆን?” በመባል በጊዜው የታሪክ ፀሐፊዎች ማፌዣ ሆኖ ነበር። የዘመኑ ዛሮችም፣ ብሄራዊ ነፃነታችንን የደፈሩት “ኢትዮጵያን ልንገዛ መጣን!” የሚል መፈክር አንግበውልን እንዳልሆነ ግልፅ ነው። ለኢትዮጵያ አገር-ወገን ወዳዶች እጅ እጅ ያለውን ያንኑ “የድጋፍ” መዝሙር ይዘው ነው።

በቅድሚያ የሚቀርበው የዘመኑ የሩስያ ተስፋፊዎች የ“ድጋፍ” መፈክር የጦር መሣሪያ “ዕርዳታ” የሚለው ነው። ኢትዮጵያንም በመጀመሪያ የቀረቧት፣ አሻንጉሊታቸው ለሆነው ለደርግ መንግሥት የመሣሪያና የወታደራዊ “ድጋፍ” በመስጠት ስም ነበር። በዚሁ ሳቢያ፣ ሃገራችን ዛሬ በከፍተኛ ዕዳ ውስጥ ሰጥማለች። ሃገራችን ዛሬ፣ በግምት የ3.5 ቢሊዮን ዶላር የሩስያ ተስፋፊዎች ባለ ዕዳ ሆናለች። ይህ ለጦር መሣሪያ ብቻ የሚከፈለው ዕዳ ነው። በተጨማሪ መሣሪያውን ለማለማመድና ለጦር ምክር በሚል፣ ቁጥራቸው ያልታወቀ የሶቭየት ህብረትና የተቀጢላዎቿ አገሮች የጦር “አማካሪዎች” በምድሪቷ ላይ ፈስሰዋል። የኢትዮጵያን ሰራዊት እዝ መላ በመላ እየተቆጣጠሩት ናቸው። በመጨረሻም፣ ከ20ሺህ የማያንስ የባዕድ ጦር በምድራችን ላይ ሰፍሯል። እንደዚሁም ሁለት ወታደራዊ የጦር ሠፈሮችን በሁርሶና በጦሌ አካባቢ በመቋቋም ላይ ይገኛሉ። የአሰብ ወደብንና የዳህላክ ደሴቶችን እንደ ባህር የጦር ሰፈር ጣብያ አድርገው መቆጣጣር ከጀመሩ ሰንብተዋል። የተረፈ ሃገር ካለንም ያሰኛል፣ ተጨማሪ የጦር ሰፈሮችን ለመስጠት፣ ሻላቃ መንግሥቱ ኃይለማርያም ከጥቅምት 18 ቀን እስከ ህዳር 3 1973 ድረስ ክሬምሊን ውስጥ ሲዋዋል ከርሞ መጥቷል። ዳህላክ ደሴቶችና ምፅዋ ውስጥ ከባድ የሩስያ ጦር ሰፈሮች እንዲመሰረቱ ከመስማማቱም በላይ ብዙ ሺህ ተጨማሪ የባዕድ ወታደሮች በሃገራችን እንዲሰፍሩ ጠይቋል። ይህ ሁሉ ደግሞ እንዲታወቀው፣ የዘመኑ ባንዳዎች ከዘመኑ ዛሮች ጋር ባደረጉት የዘመኑ ውጫሌ ውል ከሁለት ዓመት በፊት የተረጋገጠ ነው። በዚህ በህዳር 1 ቀን 1971 ዓ.ም. ቅምጡ መንግሥት በተፈራረመው በዝነኛው የ20 ዓመት የባርነት ውል ብሄራዊ ነፃነታችን ሙሉ በሙሉ ለሩስያ ተስፋፊዎች ተሽጧል።

እነዚህ ሁሉ ጉዳዮች የታወቁ ናቸው። በዝርዝር አንመለስባቸውም። የሩስያ ተስፋፊ መንግሥት በሃገራችን ላይ የተቀዳጀውን ወተደራዊ ተፅዕኖና ቁጥጥር ለማፅናት የሚፈጽማቸውንና የፈጸማቸውን ሌሎች በርካታ ጉዳዮች ይልቁኑ እንመልከት።

የሶማሌ ወረራ እንደተከፈተብን፣ የኢትዮጵያ ሠራዊት ምርጫና ግዴታ ለሃገር ነፃነትና ክብር መዋደቅ ነበር። ስለሆነም፣ ፊቱን ወደ ምሥራቅና ደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያ አዙሮ ዘምቶ ነበር። አድሃሪው ቢሮክራሲ ስንት አሻጥር ቢፈጸምበትም፣ ወራሪውን የሱማሌ ጦር ግንባሩን ሳያጥፍ ፊት ለፊት ተጋጥሞ ተዋድቋል። ነገር ግን ጥቃት የወረደበት በሱማሌ ጦር ብቻ አልነበረም። በአድሃሪው የሲቪል/ሚሊተሪ ቢሮክራሲ ብቻም አልነበረም፣ በተጨማሪ፣ የከሃዲው የ፶ አለቃ ለገሰ አስፋው ቡድን፣ ይህ ነው የማይባል የጥፋትና የፍጅት ጦርነት ከበስተጀርባው ከፍቶበታል። በዚህ ወቅት ውስጥ፣ አያሌ አብዮታዊያንና አገር ወዳድ መኮንኖች፣ ወታደሮችና የዘማቹ ሠራዊት አባሎች “ቀኝ መንገደኛ፣ ጠባብ ብሄረተኛ፣ ሠርጎ ገብ . . .” እየተባሉ እንደተጨፈጨፉ፣ ለእስር ስቃይ እንደተዳረጉና አነሰም ቢባል በጡረታና በዝውውር ስም እንደተገለሉ አገር ያውቀዋል። ይህ በኢትዮጵያ ሰራዊት ላይ ከበስተጀርባው የተፈጸመው ጥቃት፣ የሩስያ ተስፋፊዎች ሠራዊቱን እንደልባቸው ለመቆጣጠር እንዲችሉ በማለት የወሰዱት /ያልወሰዱት/ እርምጃ ነበር። ዛሬም እንደቀጠለ ነው። የተስፋፊዎች ወታደራዊ ተፅዕኖ ቁጥጥር አንደኛው ዘዴ፣ ሠራዊቱን የነቁ ወታደሮች አልባ አድርጎ ማስቀረት እንደሆነም በዚሁ እንረዳለን። የሚፈልጉት በእነርሱና በእኛ መካከል የቅኝ ገዢዎችና የተገዢዎች ግንኙነት እንዲኖር ነው። እነርሱ ጌቶች እኛ ሎሌዎች

ሁለተኛ፣ በወታደራዊ ቴክኒክም ቢሆን፣ የሩስያ ተስፋፊዎች የኢትዮጵያ ሠራዊት የሠለጠኑ የወታደር ቴክኒሽያኖች እንዲኖረው አይፈልጉም። በዚህ አንፃር በየጦር ክፍሉ የሚፈጸመው ደባና ተንኮልም እጅግ ብዙ ነው። ለምሳሌም ያህል፣ የሩስያ ቴክኒሺያኖች መሣሪያዎችን በሚገጣጥሙት ወይንም በሚያድሱበት ወቅት፣ የኢትዮጵያ ወታደራዊ ቴክኒሺያኖች እንዳይጠጓቸው በጥብቅ የተከለከለ ነው። ሌላው ቀርቶ በገዛ ሃገራችን የገዛ ቴክኒሺያኖችንን እንኳን ለማሰልጠን የተከለከልን ይመሰላል። አንድ ምሳሌ እንመልከት።

በአንድ ወቅት በ1972 ዓ.ም. ውስጥ የመገናኛ መሣሪያ ለመግዛት ይፈለግና፣ በርካሽ የሚገኝበት አካባቢ ይታሰሳል። በዚህም መሰረት፣ የሩስያ ተስፋፊዎች ከሚያቀርቡት መሣሪያ ጋር ሲመጣጠን ከጥራቱ ሌላ፣ በዋጋውም አነስተኛ የሆነ የመገናኛ መሣሪያ ከአሜሪካው አይቲ ቲ ኩባንያ ይገኛል። ይህ መሣሪያ እንዳይገዛ ተስፋፊዎቹ በተለመደው አይን ያወጣ መንገድ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያደርጋሉ። ይሁንናም፣ ጉዳዩ የሚመለከተው ባለሥልጣን፣ መቼም ኢትዮጵያዊ ነውና ድንገት ብሄራዊ ወኔው ተነስቶበት ይመስላል፣ በርካሽ ከተገኘበት ይገዛ ብሎ በድፍረት ያዛል። ከአይቲ ቲ ይገዛል። ይህ መሆኑን የሰሙት የራሺያ ነጋዴዎች ያዙን ልቀቁን ይላሉ። በዚህ ፍራቻ፣ የአይቲ ቲው የመገናኛ መሣሪያ “አልተገዛም” ተብለው ይሸኛሉ። ይህ መሣሪያም መገዛቱን እንዳያውቁ ታስቦ የመሣሪያውን አሠራር ለማስተማር የመጡ አሜሪካኖች ከራሺያኖቹ ጋር እንዳይገናኙ ጥንቃቄ ያደርጋል። ለዚህ ታስቦ የኢትዮጵያ ቴክኒሽያኖች በድብቅ እንዲሰለጥኑ ያደርጋሉ። በሽሽግም ቢሆን፣ እዚህ ላይ የኢትዮጵያ ቴክኒሽያኖችን የሚያሰለጥኑ መገኘታቸውን ማስታወስ ያስፈልጋል። የተስፋፊዎቹ “አዋቂዎች” ግን እንኳን ሊያሰለጥኑ ቀርቶ፣ የአንድ መሣሪያ ተራ ማንዋሎችን /በኢትዮጵያን እጅ እንዳይወድቁ/ ተንተርሰው ማደር ነው የሚቀራቸው። ይህን የመሰሉ በኢትዮጵያ አየር መንገድ የደረሱ ብዙ ተመሳሳይ ‘አስደናቂ’ ነገሮች አሉ። እንተወው። እንደእውነቱ ከሆነ ግን፣ ዓለም ዛሬ ከደረሰችበት የባህል እድገት አንፃር ስንመለከተው፣ ይህ በ18ኛው ክፍለ ዘመን የቀረ፣ እንኳን ለጠላቶቻቸው ለወዳጆቻቸውም እጅግ አሳፋሪ የሆነ ባህላዊ ኋላ ቀርነትና ዘረኝነት ነው ማለት እንገደዳለን። አዎ የሚፈለገው በኛና በነርሱ መሃከል የቅኝ ገዢዎችና ተገዢዎች ግንኙነት እንዲኖር ነው። ምናልባትም ፊውዳል ፊውዳል የሚሸት። እነርሱ ጌቶች እኛ ሎሌዎች

ሌላም ደግሞ፣ “ለትምህርት” እየተባለ ወደ ሶቭየት ህብረት የተወሰዱት ቴክኒሺያኖችና ፓይለቶች ትምህርታቸውን ጨርሰው ወደ ሃገራችው ሲመለሱ፣ እነርሱ እጅግም ያላወቁበትን ሚግ የኢትዮጵያ ፓይለቶች እንደማይሆን አድርገው ሲያበሩላቸውና ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እንደሚበጅ አድርገው የኛ ቴክኒሽያኖች፣ እነርሱ ዕዳ የሰጡንን መሣሪያዎችና አይሮፕላኖችን ሲያሻሽሉ፣ ማስታወሻ የወሰዱበትን ደብተርና መዝገብ ሁሉ እንዲያስረክቡ ሲደረጉ ምን ይባላል?? ነገሩ ያው የጌታና የሉሌ ጉዳይ ነው። ይህ ሁሉ ሲያንሳቸው፣ በስንት ውድ ዋጋ የመጡት አውሮፕላን ሞተሮች ሲበላሹ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲታደሱ እንኳን አይፈቀድም። ሞተሮቹ እንዳሉ ወልቀው እንደገና በስንት ወጪ ወደ ሞስኮ ተልከውና እዚያው ታድሰው ይመለሳሉ። ምን አለፋን፣ የሩስያ ተስፋፊዎች ወታደራዊ ተፅዕኖና ቁጥጥር ሁለተኛው ዘዴ፣ ሠራዊታችንን የወታደራዊ ቴክኒሺያኖች አልባ አድርጎ ማስቀረት እንደሆነም በዚሁ እንረዳልን። የሚፈለገው የቅኝ ገዢና ተገዢ ግንኙነት ነው። ያው ፊውዳል ፊውዳል የሚሸተው። እነርሱ ጌቶች እኛ ሎሌዎች

ሦስተኛው ዘዴ፣ ሃገራችንና ሕዝቦቿን ከማያልቅ ጦርነት ውስጥ በመክተት በሚፈጸመው ሤራ የሚከናወን ነው። የሩስያ ተስፋፊ መንግሥት በሃገራችን የውስጥ ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ፣ በምድሪቷ ላይ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ በየጊዜው እየሰፋና እየተወሳሰቡ የሚካሄዱትን ጦርነቶች ለዚሁ ምስክር ናቸው። የሩስያ ተስፋፊ መንግሥት፣ “የኢትዮጵያ ብሄረሰቦች አንድነት በመፈቃቀድና በእኩልነት፣ እርስ በርስ በመረዳዳትና በወንድማማችነት ላይ ተመሥርቶ” አገሪቱ ሰላምና ጥንካሬን ከምታገኝ ይልቅ፣ በወንድማማች ጦርነት ተወጥራ ብትዳከም ይመርጣል። በዚህ ሤራው የሚፈስለትም ጥቅም ለብቻው ነው። በአንድ የጦር ክፍል ብቻ የሚደርሰውን ወስደን፣ ይህን ጉድ በአሃዝ እየደገፍን ማሳየት አለብን።

ከፍ ብለን እንዳልነው፣ ኢትዮጵያ እንኳን ከፍላ ቆጥራም የማትጨርሰው የተስፋፊዎች ዕዳ ውስጥ ተዘፍቃለች። ይህ ዕዳ የጦር መሣሪያ እንጂ የልማት እንዳልሆነ ደግሞ የታወቀ ነው። ታዲያ የገዛ ሕዝቦቻችንም አልቀው፣ ኢትዮጵያም በገፍ እየተበዘበዘች እንዴት እንዴት ተደርጋ ባለዕዳ እንደሆነች ማየቱ አስፈላጊ ነው። ባንድ በኩል፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች እንደቅጠል እየረገፉ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ደረቅ ሽሮ አሮበት በችጋር፣ በረሃብና በቸነፈር እያለቀ አንዲት ሳንቲም እንኳን በከንቱ “ስትባክን” ማየቱ አገር-ወገን አፍቃሪን ሁሉ ያንገበግባል። “የሚባክኑት” ግን ሳንቲሞች አይደሉም። ሚሊዮኖች ናቸው። ምሳሌዎቹ በአየር ኃይል ብቻ የደረሱና የሚደረሱ ናቸው።

በሚግ አውሮፕላን ዋጋ እንጀምርና፣ ተስፋፊዎች “በሶሻሊስት ወንድማማችነት” መሣሪያ ለመሸጥ ውለታ ሲገቡ፣ ግማሽ ዋጋ ብቻ እናስከፍላለን ባዮች ናቸው። ይሁንና፣ የኋላ ኋላ ተተምኖ ሲመጣ ለእያንዳንዱ ዕቃ የሚከፈለው እጥፍ ሆኖ ይገኛል። ያለ ብዙ ሂሳብ፣ ለምሳሌ 4 ሚሊዮን የሚያወጣው ሚግ አይሮፕላን 8 ሚሊዮን ይከፈልበታል። ለ8 ሚጎቻችን 4×8= 32 ሚሊዮኖች ተጨማሪ ተከፍሎባቸዋል ማለት ነው።

ይህ 8 ሚሊዮን የሚያወጣው አይሮፕላንና በዚህ የሚካሄደው ጦርነት የሚጠይቀውን ወጪ እንመልከት።-

  1. አንድን ሚግ አንድ ጊዜ ብቻ ለማብረር 15000 የአሜሪካን ብር ይጠይቃል።
  2. ውድ የሆነው የአውሮፕላኑ ትጥቅ፤ ለአንድ ሮኬት 200 የአሜሪካን ብር፣ ለአንድ ጥይት 20 የአሜሪካን ብር፣ ለአንድ ቦምብ 3000 የአሜሪካን ብር ይፈጃል። በጠቅላላው አንድ ሚግ አጥቅቶ እንዲመለስ ለማድረግ 45000 የአሜሪካን ብር ወጪ ይደረጋል። የሚሰማሩት ሄሊኮፕተሮች የሆኑ እንደሆን ደግሞ 35000 የአሜሪካን ብር ይጠይቃል።
  3. በጦርነት ላይ በአማካኝ የወጣ ወጭን እንመልከት፡-

ሀ/ ኤርትራ፡-

በቀን የሚደረግ አማካይ የሚግ በረራ – 85

ለአንድ ጊዜ በረራ ወጪ – 45000 የአሜሪካን ብር

የቀኑ ወጪ – 3825000 የአሜሪካን ብር

ቅምጡ መንግሥት በኤርትራ ውስጥ የትምክህተኛ ጦርነቱን ሲያፋፋም፣ በቀን 85 የሚግ በረራዎች ለ60 ቀናት በተከታታይ ያካሂዳል።

ለ60 ቀናት፣ 60x 3825000= 229.500.000/229 ተኩል ሊየኖች/ የአሜሪካን ብር ወጪ ያደርጋሉ።

ለ/ ትግራይ

በቀን የሚደረግ አማካኝ የሄሊኮፕተሮች በረራ – 15  /15 ሄሊኮፕተሮች ይሰማራሉ ማለት ነው/

ለአንድ ጊዜ በረራ ወጪ – 35000 የአሜሪካን ብር

የቀኑ ወጪ – 525000 የአሜሪካን ብር

ቅምጡ ወታደራዊ መንግሥት የትምክህተኛ ጦርነቱን በትግራይ ሲያፋፍም በአማካኝ ለ60 ቀናት በተከታታይ ቢያንስ በየቀኑ 15 ሄሎኮፕተሮችን ያሰማራሉ። ይህም፣ 60x 525000= 31.500.000 /31 ተኩል ሚሊዮኖች/ የአሜሪካን ብር ወጪ ያስከትላል።

ወጪዎቹን በሙሉ ስንተምን በአሜሪካን ብር እንዳሉ የተውናቸው ለሩስያ ተስፋፊዎችም የምንከፍላቸውን በአሜሪካን ብር /በውጭ ምንዛሪ/ ስለሆነ ነው። ይህ ሁሉ ወጪ እንግዲህ፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች በሚወርድባቸው ቦምብና ጥይት እያለቁ በችግርና በረሃብ እየተጠበሱ፣ በቅምጡ መንግሥትና በሩስያ ተስፋፊዎች ጦርነት ሳብያ፣ ኢትዮጵያ በውጭ ምንዛሪዋ ለተስፋፊዎች በከፊል አሁኑኑ የምትከፍለው ሲሆን፣ በከፊል ደግሞ የተስፈፊዎቹ የሃብት መዝገብ ውስጥ፣ የኢትዮጵያ የዕዳ መዝገብ ውስጥ የሚሰፍር ነው።

በአራቱም ማዕዘን የሚካሄደው ጦርነት ቢጠቀልል፣ በሌሎች የጦር ክፍሎች የሚደረገውን ወጪ ሲጨምር፣ ጠቅላላ የጦርነቱ ወጪ ምን ያህል እንደሚሆን አንባቢ መገመት አያቅተውም። እኛ ግን እዚሁ አየር ኃይል እንቆይና እንቀጥል።

ከፍ ብለን እንዳልነው፣ እነርሱ ጌቶች እኛ ሎሌዎች እንደሆን ነውና የሩስያ ተስፋፊዎች የእኛ ቴክኒሽያኖችን የእነርሱ ሚጎች አጠገብ ዝር እንዲሉ አይፈቅዱላቸውም። በመሆኑም የአንድ ሚግ ሞተር ብልሽት ሲደርስበት ሞስኮ ሂዶ ካልተጠገነ አይሆንም። የ35 ዓመት ልምድ ያለው አየር ኃይል የሜይንትናንስ ክፍል ይህን ለመጠገን ምናልባት “ቢፈቅድለት” ከ5000 ብር የበለጠ አይፈጅበትም ነበር። “ወዳጆቻችን የሚጠይቁን ግን የ5000 መቶ ጊዜ እጥፍ የሆነውን ግማሽ ሚሊዮን የአሜሪካን ብር ነው።

ይህንኑ ጥገና በሚመለከት ደግሞ፣ ምናልባት ጥገናውን በሃገራችን ለማድረግ ይፈቀድልን ዘንድ፣ ለከባድ ጥገና ምን ያህል የሰው ኃይል እንደሚያስፈልግ በኢትዮጵያውያንና በሩስያውያን አዋቂዎች ጥናት ተደርጎ ነበር። ኢትዮጵያውያኑ ባደረጉት ጥናት የቴክኒክ አዋቂዎች ብቻ እንደሚያስፈልግ ሲደርሱበት፣ የተስፋፊዎች የጥናት ውጤት ደግሞ 25000 ሰዎች እንደሚያስፈልጉ ያመለክታል። ምክንያቱ ግልጽ ነው። ጥገናው በሃገራችን እንዳይካሄድ፣ እነርሱም ከተራበው ከኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ መንጋጋ ግማሽ ግማሽ ሚሊዮን የአሜሪካን ብራቸውን እየነጠቁ ለመቆት፣ እኛም የብሄራዊ ውርደት ሸማችንን ተከናንበን እነርሱን እጅ እየነሳን እንድንኖር ነው። ያው ፊውዳል ፊውዳል የሚሸት የቅኝ ገዢና ተገዢ ግንኙነት። አዎ! እነርሱ ጌቶች እኛ ሎሌዎች

በመጨረሻ፣ የሩስያ ተስፋፊዎች አይን ያወጣ ዝርፊያ ያካሄዱበትን አንድ ምሳሌ አውስተን እናብቃ። የማጓጓዣ አይሮፕላንን የሚመለከት ነው። ተስፋፊዎቹ በገቡ የመጀመሪያዎቹ ሁለት ዓመታቶች፣ በአየር ኃይል ውስጥ የነርሱን የማጓጓዣ አይሮፕላኖች መከራየት ግዴታ ነበር። ለአንድ ጊዜ በረራ 10000 የአሜሪካን ብር ይከፈላል። በወቅቱ እስከ አራት ጊዜ ደርሶ መልስ በረራ ይከናወን ነበር። ይህም ሁለት ዓመት ማለትም፣ 730 ቀናት ሙሉ ነበር። በትንሹ በቀን በአማካይ ሁለት በረራዎች እንኳን ተደርገዋል ብንል፣ የነዳጅና የሰው ሃይል ወጪን ሳይጨምር በጠቅላላው 15 ሚሊዮን የአሜሪካን ብር ተዘርፈን ነበር ማለት ይቻላል። ይህም እንደተለመደው ያው በአሜሪካን ብር /በውጭ ምንዛሪ/ በቀጥታ ወደ ተስፋፊዎች ባንክ ይተላለፍ ነበር። በመጨረሻ የኪራዩ ገንዘብ እንዳይበዛብን አስበውልን ይመስል፣ የማጓጓዣ አይሮፕላን ከነርሱ እንድንገዛ እንሆናለን። አሥር ይገዛሉ። ዋጋቸው እያንዳንዱ 10 ሚሊዮን፣ መቶ ሚሊዮን የአሜሪካን ብር ነው። የአገልግሎት ዘመናቸው አምስት አመት ብቻ ነው። እነዚህም ከጎማ አቅም እንኳን ሲያልቅባቸው በሰዓቱ ተተኪ ስለማይላክላቸው፣ አሥመራ ቆመው ከሚውሉት የነርሱን እንድንከራይ እንገደዳለን። ታዲያ፣ እነዚህ አይሮፕላኖች ከመገዛታቸው በፊት፣ በማንኛውም የአፈር ሜዳ ላይ ሊያርፍ የሚችሉ፣ ለመነሳትና ለማረፍ አጭር ሜዳ የሚበቃቸው፣ የአገልግሎታቸው ዘመን ቢያንስ አስር ዓመት የሆኑ፣ ከሁሉም በላይ ዋጋቸው ደግሞ እያንዳንዳቸው ሦስት ሚሊዮን የአሜሪካን ብር የሆኑ የማጓጓዣ አይሮፕላኖችን ከካናዳ ለመግዛት እንደሚቻል የጉዳዩ አዋቂዎች ሃሣብ አቅርበው ነበር። አልተገዙም። “በደም የተሳሰረው” የዘመኑ ባንዳዎችና የዘመኑ ዛሮች ወዳጅነት መቅደሙ ነው። “ቢገዙ ኖሮ” እንበልና፣ እነዚህ ቢገዙ ኖሮ፣ ያ ለ“ቋሚ መፍትሄና” 70 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ብር ያስፈልገው ነበር ለተባለው ለተራበው የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ 70 ሚሊዮን የአሜሪካን ብር በተረፈው ነበር። ደግሞስ 70 ሚሊዮን ማን ይሰጣል? በእርግጠኝነት ለመናገር፣ የሩስያ ተስፋፊዎች እንደማይሰጡ እናውቃለን። እነርሱ “በወዳጅነት” ኮሚቴዎቻቸው አማካይነት ለ፶ አለቃ ለገሰ የተከለሱ መፃሕፍቶቻቸውን ከሰጡ፣ ለኮሚሽነር ይድነቃቸው የስፖርት ጫማዎች ካበረከቱና ሰብዓዊነት ሲያምራቸው ደግሞ ጥቂት ቶን የመድኃኒት ካርቶኖች ለኮሚሽነር ሽመልስ ከለገሱ መች አነሳቸው። ሆኖም ግን፣ የሻለቃ መንግሥቱን ተረት ለማስታወስ እዚህ ላይ እኛም “እፍኝ ቆሎ ይዘህ ከአሻሮ ተጠጋ” ይሉሃል ይሄ ነው እንላለን። እኛ “ፎከቲያሞቹን” / ‘የተከበሩት’ ሻለቃ ሰሞኑን ለተቃዋሚ ኃይሎች ያወጡት ስም! “የድሃ ልጅ” አይሻልም?/ እኛ ‘ፎከቲያሞቹን’ የሚያንገበግበን እንግዲህ ይኸው የኢትዮጵያ ሕዝብ ችግር፣ የተስፋፊዎች ዘረፋና የቅምጦች ቅምጥነት ነው። የሩስያ ተስፋፊዎች የዘረፋ ታሪክ ተሳስበን አንዘልቀውም።

እንግዲህ ተስፋፊዎችና ቅምጡን መንግሥታቸው ሰላማዊ መፍትሄ እንዲያገኝ በማይፈልጉት፣ በአራቱም ማዕዘን በኢትዮጵያ ጭቁን ሕዝቦች ላይ በሚደረገው ጦርነት ሳቢያ ኢትዮጵያ ተወጥራ ብትዳከም፣ ተስፋፊዎች የማይመርጡበት ምንም ምክንያት እንደሌለ በትንሹ ከላይ ለማሳየት የሞከርነው ግልጽ ያደርገዋል ብለን እናምናለን።

የሩስያ ተስፋፊዎች መንግሥት ባንድ በኩል፣ የመሣሪያዎቹ አቀባይ ሆኖ ለተራዘመ ጊዜ ይቆያል። ይህም በሌላ አነጋገር፣ የዛሬዎቹን የሃገሪቱን መሪዎች እንደዚሁ ለተራዘመ ጊዜ ጥገኛዎቹና ታዛዦቹ አድርጎ ይቆያል ማለት ነው። በሌላው በኩል፣ የመሣሪያ ሸቀጡን ያለማቋረጥ በሃገራችን ላይ በማራገፍ ከፍተኛ የገቢ ምንጮችን ይገኛል። ሃገሪቱ ከዕለት ዕለት እየጨመረ በሚሄደው ወታደራዊ ዕዳ ውስጥ የበለጠውን ትዘፈቃለች። ጠቅላላው ኢኮኖሚዋም፣ በዚያው መጠን የሩስያ ኢኮኖሚ አገልጋይና ደጓሚ ሆኖ የበለጠውን ይታሠራል። ጥገኝነታችን የተሟላ ይሆናል ማለት ነው። በዚሁ አንፃር፣ ሌላው ቀርቶ ለወታደራዊ ኦፕሬሽን ለሚያደርጉት “ጥናቶች” የምንገፈግፈው ገንዘብ እንኳን በቀላሉ የሚገመት አይደለም። ባንድ በሆነ አካባቢ ወታደራዊ ኦፕሬሽን ሲታቀድ፣ ስለአካባቢው የአየርና የጆኦግራፊ ባህሪይ፣ ስለሕዝቡ ሁኔታና የሎጀስቲክ ጥያቄዎች. . . ወዘተ. በቅድሚያ ጥናት ይደረግ ይባልና ተያይዞ ዋጋው ይቀርባል። ውጤት ይስጥ አይስጥ ጠያቂ የለም። ዋጋው ግን በዕዳ ይመዘገባል። ከዚህ በተያያዘ፣ ከመለዩ ለባሹ አካባቢ እንደሚነገረው፣ የጦር እንቅስቃሴና እርምጃ ጥናቶችን /ወታደራዊ ምስጢሮችን/ የሩስያ ተስፋፊ መንግሥት ለተቃራኒ ወገን እያሳለፈ እንደሚሸጥ . . .ወዘተ. ሁሉ ይታወቃል።

በመጨረሻ፣ ይህ ሁሉ የማይሰራ ሆኖ ቢገኝ፣ የሩስያ ተስፋፊ መንግሥት ሃገራችንን በወታደራዊ ወረራ ለመያዝ የተጠናና በተግባር የተፈተሸ ዕቅድ አለው። የኢትዮጵያ ሕዝብ አምጾ ቢነሳ፣ ልክ በአፍጋኒስታኑ ላይ እንደፈጸመው ሃገራችንን በጦር ለመውረር የሚያስችለውን ወታደራዊ እርምጃ በምድራችን ላይ ፈትሾ አብቅቷል። ከአንድ አመት በፊት /ጥቅምት 1972/ ሁለት ብርጌድ የሩስያ ጦሮች /10 ሺህ የተሟላ መሣሪያና ስንቅ የታጠቀ ሠራዊት/ አንቶኖቭ 22 በሚባሉ የጦር ማመላለሻ አውሮኘላኖች ተጭነው ከደቡብ ሩስያ በመነሳት፣ በቱርክና በኢራን ጠረፍ አድርገው፣ ሶሪያና ኢራክ ላይ ነዳጅ ከሞሉ በኋላ፣ ደቡብ የመንና ኢትዮጵያ ምድር ላይ አርፈው ወታደራዊ ልምምድ አድርገዋል። ይህ ሁሉ ሲሆን፣ ቅምጡ መንግሥት የሚያውቀው አንድም ነገር አልነበረም። ያም ሆነ ይህ፣ የሩስያ ተስፋፊዎች ግን ወታደራዊ አስፈላጊ ቢሆን፣ በ36 ሰዓት ውስጥ ሊፈጽሙት እንደሚችሉ ፈትሸዋል። የሻለቃ መንግሥቱ የዘንድሮ ጉዞ ውጤት ሲታይ ደግሞ እስከነአካቴው በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ተጨማሪ የሩስያ ወታደሮች በኢትዮጵያ ምድር ላይ ይሰፍራሉ። ያኔ ሃገራችን ከዛሬው የአፍሪቃ አፍጋኒስታን ሆነች ማለት ነው። የኢትዮጵያ ሠራዊት ለሃገሩ ለወገኑና ለአብዩቱ ያልተዋደቀ ይመስል፣ በገዛ አገሩ በገዛ ምድሩ በራሽያ አዛዦችና በኩባ ወታደሮች እንደከብት እየተነዳና እየተረሸነ የገዛ ወገኑን እስከአሁን እንዲፈጅ መደረጉ ራሱ ኢትዮጵያን ሲያሳፍር የሚኖር ነው። ከእንግዲህ ደግሞ፣ ይባስ ተብሎ በገዛ ሃገሩና በገዛ ምድሩ ሳይታመን ቀርቶ፣ በወገኑ ላይ ሺህ በሺህ የሚቆጠር ተጨማሪ የባዕድ ጦር ከፈነጨበትና ካዘዘበት፣ ኢትዮጵያዊውን ወታደር ብሄራዊ ስሜቱ ምን ያዘው ይሆን ብለን ከመጠየቅ በቀር የምንጨምርበት የለንም።

እንግዲህ ባጭሩ፣ የሩስያ ተስፋፊ መንግሥት ወታደራዊ ተፅዕኖና ቁጥጥር አስፈላጊ ቢሆን እስከወረራ ድረስ የታቀደ እንደሆነ መረዳቱ ቀላል ነው። ኢትዮጵያን ሁለተኛዋ አፍጋኒስታን ለማድረግ አይናቸውን እንደማያሹ መረዳቱ ቀላል ነው። የኢትዮጵያ ሃቀኛ ተራማጆች ዲሞክራቶች፣ አገር—ወገን ወዳዶችና አርበኞች ተግባር፣ ይልቁኑ ይህንን ውስብስብ ሁኔታ ተረድቶ ይህች ብሄራዊ ክብሯንና ነፃነቷን ጠብቃ የኖረች አገር የታሪክ ቦታዋን መልሳ እንድታገኝ ለማይቀረው ትንንቅ ከዛሬው መተባበር፣ መዘጋጀትና መነሳት ነው።

ክፍል ሁለት

4. የሶቭየት ህብረትና የአጋሮቿ የኢኮኖሚ ቁጥጥርና ዘረፋ

የሩስያ ተስፋፊ መንግሥት፣ በሌሎችም አገሮች ተለማምዶ የተካነበት፣ አንድን ነፃ አገር ሙሉ በሙሉ በቁጥጥሩ ሥር የሚያደርግበት የተፈተነ ዘዴ አለው። ይህም፣ በኢትዮጵያ ውስጥ እንዳየነው፣ ባለ በሌለ ደባና ሴራ “በዓለም አቀፋዊነት… ሶሻሊዝም… በወንድማማችነት … በወዘተ” ስም በመጀመሪያ በተቻለ መጠን የነፃይቷን ወይንም የከጀላትን ሃገር ብቸኛ የጦር መሣሪያ አቀባይ መሆንና የመከላከያ ኃይሏን ሙሉ ለሙሉ በቁጥጥር ሥር ማድረግ ነው። የነፃይቷን ወይንም የከጀላትን አገር ብሄራዊ ነፃነት ደፍሮ የመከላከያ ኃይሏን ቁጥጥር ሥር ከአደረገ በመሣሪያ እዳ እጅ እግሯን አውተብትቦ ኢኰኖሚዋን በቁጥጥሩ ሥር እንድታደርግ ማስገደድ ነው። አስቸጋሪም አይደለም። ኢትዮጵያም ጥሩ ምሳሌ ሁናለች። ከዚያ፣ ‘የዕርዳታ’ ስምምነቶች፣ የኢኰኖሚ ውሎች፣ የንግድ ልውውጥ ስምምነቶች፣ “የስጦታ” አገልግሎት ድርጅቶች… ወዘተ. የሚባሉ በርካታ የዘረፉና የጥገኛ ማድረጊያ ዘዴዎች ተያይዘው ይመጣሉ። በዚህ ደረጃ የሚከናወኑት ጉዳዩች ሁሉ ባሻው ስም ቢፈጸሙ የመጨረሻ ግባቸው አንድን አገር ሙሉ በሙሉ የኢኰኖሚ ጥገኛ፣ ብሎም የፖለቲካ ተገዢ ለማድረግ እንጂ ሌላ በጐ ዓላማ የላቸውም።

     በኢኰኖሚው መስክ የሚከናወነው ቁጥጥርና ዘርፉ የሚጀምረው በገፍ ለገባውና ለሚገባው የጦር መሣሪያ ከምንከሰክሰው የጦር ዕዳ ክፍያ ስለሆነ ይህን በቅድሚያ እንመልከት።

ሀ/ የጦሩ “ዕርዳታ”

ሶቭየት ህብረት ከሌሎች “ዕርዳታዎች ሁሉ የሚቀላትና የምትፈልገውም በመጀመሪያ የጦር “ዕርዳታ” የሚባለውን ማድረጉ ነው። ምክንያቶቹም አጭርና ግልጽ ናቸው። አንደኛ፣ የሶቭየት ህብረት የጦር ክምችት መጠንና ገደብ አጥቶ ተትረፍርፏል። ሁለተኛ፣ እንደጦር “ዕርዳታ” አገሮችን በኢኰኖሚ ጥገኝነት ለመያዝ የሚያመቻች ዕርዳታ የለም። ሦስተኛ፣ የሩስያ ተስፋፊዎች እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገሮች ከጦር መሣሪያ በስተቀር፣ ከምዕራብ አገሮች በተሻለ ሁኔታ “የሚለግሱት” ይህ ነው የሚባል የተሻለ የገንዘብም ሆነ የቴክኖሎጂ ወይንም “የችሎታ” ‘ዕርዳታ’ የላቸውም። እንዳውም ብዙውን ጊዜ የምዕራቦቹ ተሽሎ የሚገኝበት ሁኔታ አለ። የጦር “ዕርዳታውንም” በሚመለከተው፣ ሶቭየት ህብረት “ዕርዳታውን” የምትጠቀምበት አገሮችን ልክ እንደካፒታሊስት አገሮች ጥገኛና ቅኝ ተገዥ ለማድረግ እንጂ ለሌላ አይደለም። በዚህም አንፃር፣ ከዚህ በላይ እንዳመለከትነው፣ የጦር እርዳታዋን በአንድ በኩል፣ በሃገሮችና ባካባቢዎች ላይ የወታደራዊ ተፅዕኖዋን ለማንገሥ ስትጠቀምበት፣ በሌላው በኩል ደግሞ፣ እያንዳንዱን ጥይት ሳይቀር በውጭ ምንዛሪ እየተቀበለች ከፍተኛ ጥቅም ታገኝበታለች። በዚህ ክንውን ውስጥ የሚጐዳውንና የሚጠቀመውን ብሎም ተከታዩን መዘዝ ለመለየትና ለመረዳት ብዙም አስቸጋሪ አይደለም።

ከመጀመሪያው፣ የሶቭየት ህብረት የውጭ ምንዛሪ እየደለበ ሲሄድ፣ የኛው እየመነመነ ይሄዳል። ይህም፣ ቢያንስ የሚከተሉትን ሦስት የኢኮኖሚ ሁኔታ ውጤቶችን ያስከትላል። አንደኛ፣ እኛ ሸቀጦችን ከዓለም ገበያ ለመሸመት የሚኖረን አቅም ይሟሽሻል። ሁለተኛ፣ “ከድጡ ወደ ማጡ” እንዲሉ፣ የሚጐድለንንና አስፈላጊ የሆነውን የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ከሌሎች ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅቶችና መንግሥታት ዘንድ የውጭ ምንዛሪ ብድር እንድንጠይቅና የባሰውን ከሌላ ዕዳ ውስጥ እንድንገባ እንገደዳለን። ይህ የመጀመሪያው ዙሪያ ጥምጥም ነው።

ይህም ሆኖ፣ የውጭ ምንዛሪን የሚያበድር ወይንም ሸቀጦችን በዱቤ የሚሸጥ ማግኘቱም ቀላል አይደለም። ምክንያቱም፣ አገሪቱ በሶቭየት ህብረትና በተቀጢላዎቿ አገሮች በተተበተበችበት ሁኔታ፣ ለማንም ዓለም አቀፋዊ የገንዘብና የንግድ ድርጅት አስተማማኝ ይዞታ የላትም። ዛሬ አንዳንድ የምዕራብ ካፒታሊስት መንግሥታት “ዕርዳታ” ቢለግሱ፣ ነገ ከሶቭየት መንጋጋ ብትላቀቁ በሚል ምክንያት ብቻ እንጂ፣ በተስፋፊዎቹ ቅምጥ መንግሥት ላይ ተማምነው አይደለም።

ይሁንና፣ ሶቭየት ህብረትና ተቀጢላዎቿ አገራችንን በቅኝ ግዛትነት ይዘው ለመቆየት ባላቸው የረጅም ጊዜ ዕቅድ ደግሞ፣ ሌላም ሸር ተብትበውልናን “የዓይነት ንግድ ልውውጥ” የሚባለው ለምሳሌ ቡናን ለጭነት መኪና ወይንም ለሌላ ሸቀጥ በመለወጥ የሚከናወን ንግድ ማለት ነው። በቅድሚያ፣ በጦሩ ዕዳ በኩል ያለውን ትርጉም እንመልከተው።

የጦር ዕዳው ከዚህ በላይ እንዳልነው፣ በውጭ ምንዛሪ የሚከፈል ነው። ታዲያ ይህንን ለመወጣት የሃገሪቱ የዓለም አቀፍ ገበያ ንግድ መጨመርና ብሎም የውጭ ምንዛሪ ይዞታችን ማደግ ነበረበት። ይህ ቢሆን፣ ዕዳውን በተመጣጣኝ ባጭር ጊዜ ውስጥ ከፍሎ ለመጨረስ የሚያስችል ሁኔታ በተገኘ ነበር። ሆኖም፣ የረጅም ጊዜ የዘረፉና የቁጥጥር ዕቅድ ያላቸው የሩስያ ተስፋፊዎችና አጋሮች እንደዚህ ዓይነቱ “የተሻለና” ከፋም ለማም ብሄራዊ ነፃነታችንን የሚያግዝ ሁኔታ እንዲኖር እንኳን አይፈልጉም። በተቃራኒ፣ዕቅዳቸውን ከግቡ ለማድረስ እንዲችሉ በማለት፣ ለሃገራችን የውጭ ምንዛሪ ማስገኝያ ይሆኑ የነበሩትን ሸቀጦችን “በዓይነት ንግድ ልውውጥ” ስምምነት ስም አስቀድመው አሥረው፣ ወደነሱ አገሮች እንዲጫኑ አድርገዋል። በዚህም ባንድ ወገን፣ በውጭ ምንዛሪ የሚፈጸመው የጦር ዕዳ ክፍያ ተራዝሞ እንዲቆይ የተደረገ ሲሆን፣ በሌላው ወገን ደግሞ፣ የውጭ ምንዛሪ ገቢያችን የባሰውን እየመነመነ እንዲሄድ ተደርጓል ማለት ነው። የሩስያ ተስፋፊዎችም በዚያው መጠን ቁጥጥራቸውን የማፅናትና የማንሰራፋት እምነትና ዕቅድ አላቸው ማለት ነው።

ሦስተኛ፣ የሩስያ ተስፋፊዎች አገራችንን የከተቱበት የተራዘመና መውጫ የሌለው የርስ በርስ ጦርነት ባንድ በኩል ተተኪ የጦር መሣሪያዎችን ያለማቋረጥ ከነሱ እንድንገዛ ያስገድደናል። ይህ በራሱ፣ ከማንወጣው ዕዳ ውስጥ በየዕለቱ በበለጠ እየጠነከረና የሃገሪቱም የጦር ጥገኝነት እየተጠናከረ እንዲሄድ ሲያደርግ፤ በሌላ በኩል ደግሞ፣ ለመሣሪያ መለዋወጫና እድሳት እየተባለ የምንነከርበት ዕዳም በቀላሉ የማይገመት እንደልሆነ ከፍ ብለን በሰፊው አይተናል። አንመለስበትም። ነገሩ ባጭሩ፣ ደጋግመን እንበለውና እንኳን ተከፍሎ ተቀጥሮም የማያልቅ እየሆነ፣ ሃገራችንም “በዓለም አቀፋዊነት” ስም በወለድ አገድ የተያዘች አገር ሆናለች ማለት ነው።

ለ/ የኢኮኖሚው ግንኙነትና “ዕርዳታ”

የዜና ማሰራጫዎችና የመንግሥቱ ቀንደኛ ተጠሪዎች፣ የምሥራቅ አገሮች ስለሚያደርጉልን የኢኮኖሚ “ዕርዳታ” የማይለፈልፉት ነገር እንደሌላቸው ሕዝብ ያውቀዋል። በርግጥም ደግሞ፣ “ዕርዳታ፣ ድጋፍ፣ ስጦታ፣ ብድር … ወዘተ” እያሉ ከቅምጡ መንግሥታቸው ጋር ብዙ ውሎችን ፈርመዋል። ከሚያዚያ 1969 እስከ ታህሳስ 1972 ድረስ ብቻ እንኳን 89 የሚሆኑ የንግድ፣ የቴክኖሎጂ፣ የአየር ትራፊክና ሌሎች ልዩ ልዩ “የትብብር” ውሎች ተፈርመዋል። እንዲያም ሲል፣ በየሳምንቱ የሚጐርፈው የምሥራቅ ሃገሮች ሹማምንት አንድ በስምምነት ውል የሚታሰር ነገር በኪሱ ቋጥሮ ሳይዝ እንደማይወጣ የታወቀ ነገር ነው። የሚያስገርመው እንበልና ደግሞ፣ የሩስያ ተስፋፊዎች መንግሥትና ተቀጢላዎቹ ሃገሮች ቅምጡን መንግሥታቸው አብዛኛውን የኢኮኖሚ ውል ያስፈረሙት፣ ስለኢኮኖሚ ምንም የማይገባቸውን የደርግ አባሎች በጥቃቅኑ እየደለሉና በነጭ ውሸት እያታለሉ ነው። እነርሱ ግን፣ በመሣሪያ ዕዳ ያውተበተቡትን አገር በኢኮኖሚ ቁጥጥር ሥር የሚያደርጉት በቅድሚያ አቀነባብረው በሚፈጽሙት የአጭርና የረጅም ጊዜ ኘላን እንጂ አንዳው በመላ ምት እንዳልሆነ ግልጽ ነው። መመሪያ የሚያደርጓቸው የሚከተሉትን ዋና ዋና ጉዳዩች ለመጥቀስ ይቻላል።

አንደኛ፣ በየትኛውም ክፍለ ኢኮኖሚ ቢሆን በተቻለ መጠን፣ አዲስ ኢንቨስትመንት የሚጠይቅ ኘሮጀክት ውስጥ ምንም አይነት ተሳትፎ አለማድረግ፣ ከተደረገም ከፍተኛ የወሳኝነት ሚና በሚያጫውት ደረጃና ግዴታ በሚያስገባ ሁኔታ /የመሣሪያ ዕዳ ክፍያ…/

ሁለተኛ፣ በሃገሪቱ ውስጥ የበላይነት ያለውን ዋና ዋና ተንቀሳቃሽ ካፒታል ማዳከም፡ ማጥቃትና መተካት /ኢንዱስትሪ፣ ንግድ፣ እርሻ…/፣ ይህን ካፒታል የሚያንቀሳቅሱ ድርጅቶችንም ሲያስፈልግ ማፈራረስ፣ ወይንም በራሳቸው ቁጥጥር ሥር ማድረግ፣ በዚህም ጠቅላላ ኢኮኖሚው መቆጣጠር /ከሃገሪቱ የኢኰኖሚ ኘላን አንስቶ እስከ ውጭ ንግድ ድረስ/

ሦስተኛ፣ ቀድመው በተደራጁ የማምረቻ ድርጅቶች፣ በተለይም የተፈጥሮና ጥሬ ዕቃ በሚያወጡ ድርጅቶች /ከባድ ኢንዱስትሪዎች/ ላይ ማተኰር፣

አራተኛ፣ በሃገሪቱ ውስጥ ሊመረቱ የሚችሉ ጥቂት ውጤቶች ላይ [የማይነበብ – አዘጋጆች]   መሆን፣ ሃገሪቱ የሚያስፈልጋትን በማቅረብም ብቸኛ ሞኖፖል መያዝ /ኢምፖርት ሞኖፖል/ ማለትም የውጭ ንግድን በቁጥጥር ሥር ማድረግ … ናቸው።

በዚህ ዘዴ የሩስያ ተስፋፊዎች የኢኮኖሚ ተጽዕኖዎቸውን ከአንሰራፉ በኋላ፣ በአጠቃላይ የሃገሪቱ ኢኮኖሚ፣ በተለይ ደግሞ በቁጥጥራቸው ሥር የገቡት የማምረቻ ድርጅቶች… የመጀመሪያ ግዴታ ሃገሪቱ ለእነርሱ የገባችበትን ዕዳ እነርሱ ራሳቸው በሚወስኗቸው ሁኔታዎች መከፈል ብቻ ይሆናል። የኢትዮጵያ የምርት ውጤቶች በዚህ ዘዴ ከእርሻ ምርት ከስንዴ አንስቶ እስከ የማዕድን ውጤት ወርቃችን ድረስ ያሉት በ“ዓይነት የንግድ ልውውጥ” ወደ ሶቭየት ህብረትና ተቀጢላዎቿ አገሮች ተግዘዋል። ይጋዛሉ።

እንግዲህ በዚህ ዘዴ የሩስያ ተስፋፊዎችና ተቀጢላዎች ከመጀመሪያው የኢትዮጵያን የማዕድንና የኢንዱስትሪ ሃብት በቁጥጥራቸው ሥር ለማድረግ በቀላሉ የማይገመቱ አያሌ እርምጃዎችን ወስደዋል። ለምሳሌም ያህል፣ የአዶላውን የወርቅ ማዕድን፣ የቤንዚንና የዘይት ፍለጋን፣ የመተሃራውን የስኳር ፋብሪካ፣ የድሬዳዋውን የሲሚንቶ ፋብሪካና የባህር ዳሩን ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ለመጥቀስ ይቻላል። እነዚህ የኢኮኖሚ መስኰች በእነርሱ ቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ከተደረገ ረዘም ያለ ጊዜ አልፏል። በውጭ ንግድም በኩል፣ ሃገሪቱን የሸቀጣቸው ማራገፊያ በማድረግ ከፍተኛ ዘረፋ ማካሄድ ከጀመሩ ቆይተዋል። በዚህ አንፃር፣ አንዳንዴ እጅ ይዘው ማስፈረም እስኪቀራቸው ድረስ እየተጫኑ፣ ያንኑ የቅምጥ መንግሥታቸውን በርካታ ሃገራችንን የሚጐዱ ውሎችን እንዳስፈረሙት በየመስኩ ያሉት ባለሙያዎች ሁሉ ያውቁታል። ለምሳሌም ያህል፣ ለምሥራቅ ጀርመን የተሰጠውን የአሰብ ወደብ ማስፋፋት ሥራና ለቺኰዝላቫኪያ መንግሥት የተሰጠውን የ180.000.000 ብር የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ማቋቋሚያ /ኮንቦልቻ- ደሴ አጠገብ/ ውሎች ለመጥቀስ ይቻላል። ሌሎች ብዙዎችም አሉ። እነዚህ ውሎች የተፈረሙት፣ በተመናቸውና በውል ግዴታቸው ምንም እንኳን አንዳንድ የናጠጡ የካፒታሊስት ሃገሮች ከሚያቀርቡት አራት አምስት ጊዜ የበለጡም ቢሆኑ ነው።

የባሰም አለ እንጂ፣

“ሸቀጥ አምጥተናል፤ አሰብ ደርሷል፤ ያስፈልጋችኋል፣ ውሰዱ” እየተባለ ያለአንዳች ቅድሚያ ውልና ግዴታ በየጊዜው የሚራገፈውም ሸቀጥ ጥቂት አይደለም። ባለሙያዎችና ህሊና ያላቸው ባለሥልጣኖች “መቼ ጠየቅንና መቼ ተስማማንና?” ብለው ለመጠየቅ መብቱም የላቸውም። የጠየቁም ቢኖሩ “ዓለም አቀፋዊነት ነው” እየተባሉ በቅምጡ መንግሥት ትዕዛዝ እንዲረከቡ ተደርገዋል። በዚህ አንፃር፣ ለምሳሌም ያህል፣ ምሥራቅ ጀርመኖች አምጥተው ያራገፏቸውን ትራክተሮች ለመጥቀስ ይቻላል። ከዚህ በተያያዘ፣ የሚያራገፉብን የማምረቻ መሳሪያዎችም ሆኑ አላቂ ሸቀጦች በመጀመሪያ ላይ ረከስ ብለው ከገቡ በኋላ፣ የኋላ ኋላ መዘዛቸው ብዙ እንደሆነም ከልምድ የታወቀ ነገር ሆኗል። አንደኛ፣ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ለብልሽት ይበቃሉ። ሁለተኛ፣ የመለዋወጫ ዕቃቸው ዋጋ እጥፍ ድርብ ሆኖ ይገኛል። ሶስተኛ፣ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ የመሣሪያዎችም ሆነ የመለዋወጫ ዕቃዎቹ፡ ዋጋ ሕዝቡ እንደሚለው “እንደ ስፑትኒክ” ተተኩሶ ይቀርባል። በዚህ ዘዴ ብቻ የሚፈጸመው ዘረፋና ብዝበዛ እጅግ ከፍተኛ ነው።

እንዲያም ሲል፣ የውጭ ንግዱም አጠቃላይ ሁኔታ አለ። የዚህን መስክ ሁኔታና የፖለቲካ ትርጉም ቀጥሎ በቀረበው ሠንጠረዥ አማካኝነት ልንረዳ እንችላለን። ሠንጠረዡ የሚያሳየው በ1968/70 መካከል የተከናወነውን የንግድ ልውውጥ ቢሆንም፣ የጦር መሣሪያን አይጨምርም።

ከ1968/70 ከምሥራቅ አጋሮች ጋር የተደረገው የንግድ ልውውጥ /በሚልዩን ብር  

ወደ ኢትዮጵያ ያስገቡት                  ኢትዮጵያ የላከችው
1969   1970   1971              1969   1970   1971
24.471 36.802 48.486           10.531 104.835  53.580

1969 ዓ.ም.ን እንደመቶ ብንወስደው፣ ይህ ሰንጠረዥ /የጦር መሣሪያን ሳይጨምር/ ሶቭየት ህብረትና ተቀጢላዎቿ አገሮች ወደ ሃገራችን የሚያፈሱት ሸቀጥ ከ1969 ዓ.ም እስከ 1970 በ50 ከመቶ፣ እስከ 71 ዓ.ም. ደግሞ በ98.1 ከመቶ እንደጨመረ ያመለክተናል። በአንፃሩ ደግሞ እኛ የላክነው ከ69 ወደ 70 ዓ.ም. በ89.4 እጅ፣ ወደ 71 ደግሞ፣ በ411.3 እጅ ተመንድጓል። ባጭሩ እንግዲህ፣ አንደኛ፣ የውጭ ንግዳችን በጥቂት ጊዜ ውስጥ ከሶቭየትና ከተቀጢላዎቿ አገሮች ገበያ ጋር በከፍተኛ ደረጃ ተሳስሯል። ሁለተኛ፣ ይህ በራሱ ለኢኮኖሚ ቁጥጥርና ለፖለቲካ ተፅዕኖ የሚያመቻቸውን የበላይነት ሁኔታ ፈጥሮላቸዋል። ሦስተኛ፣ ከዚሁ በተያያዘ፣ የሃገሪቱ ዓለም አቀፋዊ የንግድ ግንኙነት እየጠበበና አገሪቱ ወደ ኢኮኖሚ ብቸኝነት እያመራን በመሄድ ላይ እንደምትገኝም እንረዳለን። በቀላሉ ለማየት እንደሚቻለው የሃገራችን የውጭ ንግድ ወደ ምሥራቅ አገሮች የዞረው፣ ከሌሎች /በተለይም ከሦስተኛው ዓለምና ከገለልተኛ አገሮች/ ጋር ይከናወኑ የነበሩትን የንግድ ልውውጦች በማቀዝቀዝ ወይንም ጨርሶ በማዳፈን ነው። ብሎም፣ በዚህም ደረጃ ጭምር፣ የሃገሪቱ ገለልተኝነት ሽታው እንኳን እየጠፋ እንደሄደ እንገነዘባለን።

በዚሁ የንግድ ልውውጥ ሥር፣ ቀደም ስንል ያነሳነው “የዓይነት ንግድ ልውውጥ” ጉዳይ ደግሞ፣ ራሱን የቻለ ስፍራ ይዞ ይመጣል። ይህኛው የንግድ ልውውጥ ዘይቤ፣ የሃገሪቱን ዓለም አቀፋዊ የንግድ ግንኙነት ከመሰበሩና የሃገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ገቢ ከመቀነሱም በላይ፣ ባንድ በኩል በልዋጭ ስም በሚመጡት ሸቀጦች ምክንያት የሚደርሱብንን መጐዳትና፣ በሌላው በኩል ደግሞ፣ እነርሱ ከእኛ በዓይነት ለውጥ ስም የሚወስዱትን ሸቀጥ አዙረው በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ በመሸጥ የሚያገኙትን ጥቅም ስናስተያየው፣ ራስን አስይዞ የሚያስጮህ ጉዳይ ሆኖ እናገኘዋለን። እንደዚህ ዓይነቱ ንግድ፣ በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ “የሦስት ማዕዘን ንግድ” ተብሎ ይታወቃል። ኢትዮጵያን ለሚመለከተው፣ ከምሥራቅ ጀርመን ጋር የተደረገውን አንድ “የዓይነት ንግድ ልውውጥና” ውጤቱን ብቻ አሳይተን እንለፍ።

በ1970 መጀመሪያ ገደማ ላይ ነው። በቅምጡ የኢትዮጵያ መንግሥትና በምሥራቅ ጀርመን መካከል፣ ኢትዮጵያ ወደ ምሥራቅ ጀርመን በየዓመቱ 10000 ቶን ቡና ልትልክ፤ ምሥራቅ ጀርመን ደግሞ በምትኩ ልዩ ልዩ የኢንዱስትሪ ምርቶችን እንድትልክ አንዳች ዓይነት ስምምነት ይደረጋል። ነገር ግን ኘሮቶኰሉ ከመፈረሙ በፊት፣ ኢትዮጵያ 5182 ቶን ወደ ምሥራቅ ጀርመን ልካ ነበር። ኘሮቶኮሉ በተፈረመበት ጊዜም፣ ወደ ምሥራቅ ጀርመን የተላከው ቡና 14766 ቶን ደርሶ ይገኛል። ለዚያውም፣ በፖለቲካ ምክንያቶች የተነሳ፣ ዋጋው በዓለም አቀፍ ገበያ ተመን ሳይሆን፣ “የወዳጅ ዋጋ” በሚል በዝቅተኛ ተተምኖ እንዲለወጥ ነበር ስምምነቱ የተደረገው። በምትኩም፣ “በየፈፋው ተደፋ” ተብሎ የተሰየመው ሃይፋ /አይ ኢፍ ኤ ደብሊው ኤስ ኦ / የተሰኘው ካሚዩንና ዚቲ የሚባለው ትራክተር ይገባሉ። ውጤቱ ምንድን ሆነ??

ምሥራቅ ጀርመን ከኢትዮጵያ “በወዳጅ ዋጋ” ያስጫነችውን ቡና በጥቂት ጊዜ ውስጥ አሳልፋ ለምዕራብ ጀርመን በዓለም ገቢያ ዋጋ ተመን ሸጠች። በዚህም፣ ባንዱ ወገን በዋጋው ልዩነት እንኳን ብቻ ከፍተኛ ጥቅም ስታገኝ፤ በሌላው ወገን፣ በውጭ ምንዛሪ ገቢዋ ከበረች። ኢትዮጵያ ግን፣ በውነትም በየፈፋው እየተደፋ ባለቁት ተሽከርካሪዎች ከኪሳራ ውስጥ ገባች። የውጭ ምንዛሪ ገቢዋን አጣች። አልፎም፣ ከጥንት ጀምሮ የቡና ደንበኛ በመሆን ሲያገለግላት የነበረውን የምዕራብ ጀርመን ገበያ፣ አሳልፋ ለምሥራቅ ጀርመን አቀባዩች አስረከበች።… መቼ በዚህ አልቆ…

ከጥቂት ጊዜ በኋላ ቅምጡ መንግሥት፣ “በትርፍ የላክነውን ቡና እንተሳሰብ፣ ሲሆን ችግርም አለብንና ለቤንዚን መግዣ እንዲሆነን ለውጭ ምንዛሬ ስጡን፣ ያለዚያም ለሶቪየት ዕዳችን ማቻቻያ እንዲሆን እዳችን ወደዚያው ይከፈልልን” በማለት የልመና ጥያቄ ለምስራቅ ጀርመን አስገብቶ ነበር። እነርሱ ግን ምን ገዷቸው! “ቢሻችሁ ሌላ ሸቀጥ በምትኩ ውሰዱ” ብለው መለሱ። የተላከው ቡድን በምትኩ ሊወስድ የሚችለውን ሸቀጥ አፈላለግ ተባለ። ምንም የሚያረካውን ሸቀጥ ሳያገኝ ይቀራል። በመጨረሻም፣ በበሰበሰ የፓስታ ክምር ተስማምቶ የምስራቅ ጀርመን ማካሮኒ ሲራገፍብን ከረመ…።

እንደዚህ አይነቱ ያልተመጣጠነና ሃገራችንን የባዕድ ሀገሮች ጥቅም ተንከባካቢ አድርጎ የሚያስቀር የኢኮኖሚ ግንኑኝነት፤ በዕኩልነት፣ በጋራ ጥቅምና በመረዳዳት ላይ ከሚመሰረተው ሶሻሊስታዊ የኢኮኖሚ ግንኑኝነት ጋር አንዳችም መቀራረብ የለውም። በተቃራኒ፣ በዘራፊና በተዘራፊ፣ በገዢና በተገዢ፤ አዎን፡ ሃገራችንን ወደ ቅኝ ግዛትነት የሚያዘቅጥ የኢኮኖሚ ግንኑኝነት ነው። ከዚህ በገሃድ ከሚታየው አልፈን፣ “ብድር፣ ዕርዳታ፣ ስጦታ” ወደሚባሉት የተሻገርን እንደሆነ ደግሞ፣ ነጋ ጠባ በቅምጡ መንግሥትና እና በአጋሮቹ መንግሥታት የሚለፈፈው ሁሉ በቅምጡ መንግሥትና በሶቭየት ህብረት መካከል በ“ዕርዳታ” ስም የተደረገውን የ170- ሚሊዩን ብር ብድር ይመለከታል። ታሪኩንም ለመጀመር 20 ዓመታት ወደ ኋላ መመለስ ያስፈልጋል።

እንደሚታወሰው፣ በሃምሌ ወር 1951 ዓ.ም.፣ ኃይለሥላሴ ሶቭየት ህብረትን ለመጐብኘት ሄደው ነበር። በዚያ በተደረገው ስምምነት መሰረትም፣ ሶቭየት ህብረት ለኢትዮጵያ የ250- ሚልዩን ብር ብድር ልትሰጥ ቃል ትገባለች። ብድሩ፣ ለአንድ ዓመት ከክፍያ ነፃ ሁኖና በ2.5 ከመቶ ወለድ በ12 ዓመት ውስጥ ተመልሶ እንዲከፈል በተደረገ ስምምነት መሰረት የተሰጠ ነበር። ይሁን እንጂ፣ የ12 ዓመቱ የውል ዘመን ሲያልቅ /ማለትም እስከ 1963 ድረስ/ የኃይለሥላሴ መንግሥት ከብድር ውስጥ የተጠቀመው 25 በመቶ /56-ሚልዩን ብር/ የሚሆነውን ብቻ ነበር። ከዚህም ውስጥ፣ 26 ሚልዮኑ የአሰብን የቤንዚን ማጣሪያ ለማቋቋም ሲውል፤ 30- ሚሊዩን የሚሆነው ደግሞ “ኢትዮ- ሶቭየት የንግድ ኩባንያ” የተሰኘውን የሶቭየት ህብረት የውጭ ንግድ ማስፋፊያ ድርጅት ለማቋቋሚያ ውሎ ነበር።

የውሉ 12 ዓመት እንዳለቀ፣ የኃይለሥላሴ መንግሥት ቀሪውን ብድር በመጠየቅ ሁለተኛ ስምምነት ይፈራረማል። የሁለተኛው ስምምነት የውል ግዴታዎችም ልክ እንደ መጀመሪያው ውል /በ2.5 ከመቶ ወለድ በ12 ዓመት እንዲከፈል/ ነበር። ይሁን እንጂ፣ ከ1963 – 1968 ዓ.ም ድረስ፣ ከ1951ዱ ጠቅላላ ብድር ውስጥ የተላለፈው ገንዘብ ከ30 በመቶ /75- ሚልዮን/ ሳይበልጥ ይቀራል። 175 ሚልዮን የሚሆነው በሶቭየት ህብረት እጅ ውስጥ ያለ ነበር ማለት ነው። በመሆኑም፣ ቀሪውን ብድር ለመጠየቅ በሃምሌ 1968 አንድ የደርግ ቡድን ወደ ሞስኮ ይሄዳል። ሆኖም፣ ከዚህ በላይ እንዳመለከትነው፣ ሶቭየት ህብረት በዚያን ወቅት የኢትዮጵያን አብዮት ከሚወጉ ኃይሎች ጋር ከመልከስከሷም በላይ፣ ገና በመሣሪያ ዕዳ ኢትዮጵያን ስላላውተበተበች ቀሪ የተባለውን ብድር ለመስጠት ፈቃደኛ ሳትሆን ቀረች። ቡድኑም ባዶ እጁን ተመለሰ። ሶቭየት ህብረት፣ ገና ከ20 ዓመታት በፊት ለኃይለሥላሴ የገባችውን ውል “አሟልታ” ለመፈጸም ፈቃደኛ የሆነችው፣ ይልቁኑ ደርግን እጇ ውስጥ ማስገባቷን ካረጋገጠች በኋላ ሆነና፣ ከዚህ በላይ ያወሳነውን የ170-ሚልዮን ብር ቀሪ ብድር ለመልቀቅ ወሰነች። ስንት መዓት ሙገሳ የወረደለት “ዝነኛው” የሚያዝያ 1971 ዓ.ም ውልም ተፈረመ።

ነገር ግን ሶቭየት ህብረት ለ“ሶሻሊስቷ” ኢትዮጵያና ለ “ኰሚኒስት” መሪዎቿ /ምን አለፋን ለቅምጥ መንግስቷ/ የሰጠችው “ሶሽያሊስታዊ ዕርዳታ”፣ ከ20 ዓመታት በፊት ለአፄይቱ ኢትዮጵያ ከሰጠችው “ዕርዳታ” ትራፊ ሲሆን፣ ከሱም በምንም የሚለይ አልነበረም። ምክንያቱም፣ የሚያዚያ 1971 ውል ኃይለሥላሴ ከ20 ዓመት በፊት ከተዋዋሉት ስምምነት በምንም ሳይለይ፣ ያው ከአንድ ዓመት ከክፍያ ነፃ ሆኖ፣ በ2.5 ከመቶ ወለድ በ12 ዓመት ውስጥ ተከፍሎ አንዲጠናቀቅ የሚያስገድድ ውል ነበር። እንዲያውም ጉዳት አለው እንጂ። ምክኒያቱም፣ በገንዘብ አቅምነቱ ሲተረጐም፣ ለአፄ ኃይለሥላሴ ተሰጥቷቸው የነበረው ብልጫ አለው። የዚያን ጊዜውና የዛሬው ገንዘብ በፍጹምም ሆነ በተመጣጣኝ የመግዣ አቅማቸው ትይዩ አይደሉም። የዛሬው ገንዘብ የመግዣ አቅም ዝቅተኛ ነው። በ12 ዓመት ውስጥ ከነወለዱ ሲከፈል ደግሞ፣ ወደ ሶቭየት ህብረት ካዝና የሚፈሰው ገንዘብ የትርፍ ትርፍ ይሆናል።

ባጭሩ እንግዲህ፣ ሶቭየት ህብረትና ተቀጢላዎቿ አገሮች፣ በ“ሶሻሊስታዊ” የኢኮኖሚ ግንኙነትና “ዕርዳታ” ስም ከዛሬው የቅምጥ መንግሥታቸው ጋር የሚሸቅሉት፣ አገራችንን በበለጠ በነርሱ ተፅዕኖና ቁጥጥር ሥር ለማዋል እንጂ፣ በውነትስ ሕዝባችን ከድኀነቱና ከችጋሩ ተላቅቆ ብልጽግና እንዲኖር ተመኝተውለት አይደለም። ባጭር ባጭሩ ከፍ ብለን ያየናቸው ጉዳዩች ይህን በሚገባ የሚያረጋግጡ ናቸው።

በገሃድ እንደሚታወቀው፣ ሃገራችን ዛሬ ከ5 ሚልዮን በላይ ረሃብተኞችን ይዛ በመማቀቅ ላይ ትገኛለች። በዚህ ወቅት እንኳን፣ የነርሱ “ዕርዳታ” ያው ብዝበዛ ነው፣ ሰብዓዊ ዕርዳታቸው ከቁጥር የሚሰፍር ሆኖ አልተገኘም። በተቃራኒ፣ የሃገሪቱ የእርሻ ምርቶች ወደነርሱ ይፈሳሉ። ስንዴያችን… ከድንች አቅምም ከችርቻሮ ገበያ እየተለቀመ ይጋዛል። ጤፋችንንም ሳይቀር “ለፈረንጅ ይሆን እንዲሁ፣ ኸረ ይሄ ነገር ይጠና” ተብሎ እየተመኙት ነው። ይልቁንስ፣ የነርሱ ‘ሰብዓዊ’ ዕርዳታ ቀርቶብን፣ ለነርሱ “ኤክስፐርቶችና ለአማካሪዎች” ለአንሶላና [የማይነበብ – አዘጋጆች]። ደግሞስ፡ ስንት መዓት የማምረቻ ድርጅቶች ሲዘጉ [የማይነበብ -አዘጋጆች]   ቴክኒክና ‘ኤክስፐርትነት’ በየትኛቸው ላይ ነፍስ ሲዘራ ታየ?? በተቃራኒ፣ ሥራ አጡ እንደ አሸን እየፈላ፣ ረሃብተኛውና ለማኙ እየጨመረ፣ ስደተኛው እየበረከተ፣ መጪው ጊዜ እየጨለመና ውል እየጠፋበት ሄዷል። የሃገሪቱ ኢኮኖሚ ለሕዝቦቿ ጥቅም ከመዋል ይልቅ፣ ከዕለት ዕለት በበለጠ የሩስያ ተስፋፊዎችና የተቀጢላ አገሮች ኢኮኖሚ ለማዳበርና እነርሱ በሃገራችን ላይ ያላቸውን ቁጥጥር ለማጠናከር የሚያግዝ ብቻ ሆኗል። “ዕርዳታው” ብድሩ . .  ወዘተ. ዓይን ያወጣ የዝርፍያ መሣሪያ፤ “የንግድ ልውውጡ”፣ የንግድ ግንኙነቱ ሃገራችንን በከፍተኛ ደረጃ የሚጐዳ፣ ጥገኝነትን የሚያጠናክርና ብሎም ነፃ ህልውናችንን የሚገስ መሆኑ ታይቷል።

የሩስያ ተስፋፊ መንግሥት በኢኰኖሚ ቁጥጥር ሥር ያዋለውን ሃገር በፖለቲካም ካልተቆጣጠረው ግን፣ የተሟላ እንዳልሆነ ያውቀዋል። ጣልቃ ገብነቱና ዘረፋው በሙሉ በፖለቲካ መረጋገጥ ይኖርበታል።

5. በሃገሪቱ የውስጥና የውጭ ፖለቲካ ላይ የሶቭየት ህብረት ቁጥጥር

የሩስያ ተስፋፊ መንግሥት የረጅም ጊዜ እቅድና ፍላጐት አንድን ሃገር ለሱ ታማኝ በሆነ ድርጅት ቁጥጥር ሥር አስገብቶ፣ ለረጅም ጊዜ የእጅ አዙር ቅኝ ግዛቱ አድርጐ ማቆየት ነው። ኢትዮጵያውያንም በሚመለከት፣ ይህ ዓላማው ግቡን እንዲመታ፣ መጀመሪያ የኢትዮጵያን አብዮት በሚወጉ ድርጅቶችና ሃይሎች አካባቢ ተልከስክሶ ከዚያም ፈረስ በመለወጥ ከደርግ ጋር ሲረግጥ ቆይቶ፣ በመጨረሻ ደርግን ጫማው ሥር ጥሎ አሻንጉሊቱ ሊያደርገው በቅቷል። በኋላም ወደ “ኢሠፓኮ” ገስግሷል።

ሀ/ የሩስያ ተስፋፊዎች መግባትና የአብዮታችን መቀልበስ

ሃገርና ወገን አፍቃሪ የሆኑት ሃቀኛ ተራማጆች፣ ዲሞክራቶችና አርበኞች ምን ጊዜም ቢሆን የማንም የውጭ መንግሥት የበላይነት አይቀበሉም። የማንም ኃያል መንግሥት ቡችላና ቅምጥ ሆነው ለማደር አይፈቅዱም። ይልቁኑ፣ ማንኛውንም መስዋዕትነት ተቀብለው ለብሄራዊ ነፃነታቸውና ክብራቸው ይዋደቃሉ። እነሱ፣ ለስልጣን፣ ለከንቱ ክብርና ሙገሳ የሃገራቸውን ነፃነትና ክብር አሳልፈው አይሰጡም። በተቃራኒው፣ በአቋማቸው ፀንተውና በሕዝቡ ላይ ብቻ ተማምነው እስከመጨረሻው ድረስ ለመሟሟት የተዘጋጁ ናቸው። በመሆኑም፣ ከመጋቢት 1969 አንስቶ እስከ አሁንም ድረስ ታይቶ የማይታወቅ ጭፍጨፋና ግፍ ወርዶባቸዋል።

በዚህ ጭፍጨፋና ግፍ፣ የሩስያ ተስፋፊና ጣልቃ ገብ መንግሥት ጉዳይ አስፈፃሚ በመሆን ያገለገለው የ፶ አለቃ ለገሰ አስፋው ከሃዲ ቡድን እንደነበር ዛሬ ለማንም የተሰወረ አይደለም። ይህ ቡድን ባንድ ወገን፣ ለሶቭየት ተስፋፊ መንግሥት እየተሟገተ፣ በሌላው ወገን የአብዩቱን ሃቀኛ ኃይሎችና ወዳዶች እያጠፋና እየበታተነ፤ ባንድ ወገን ብሄራዊ ነፃነታችንን እያስገሰሰ፣ በሌላው ወገን አብዮታችንን አኰላሽቶ እስከ መቀልበስ አድርሶታል።

ከሱማሌ ወረራና ከሩስያ ተስፋፊ መንግሥት መግባት አንስቶ እስከ ቀኞች ህብረትና እስከ “ኢሠፖአኮ” ድረስ የነበረው ሁኔታ፣ የተነሱት የአብዮታችንና የነፃነታችን ጥያቄዎች የታወቁ ናቸው። አቋማችንንም በየጊዜው ስላሳወቅን እዚህ ላይ አንመለስባቸውም። የአብዮታችን መቀልበስና የተስፋፊዎች መግባት ግንኙነትን ለመረዳት ግን አጠንክሮ ማስታወስ የሚያስፈልግ ቁም ነገር አለ። ይህም፣ የሩስያ መንግሥት ተፅዕኖ መጠናከርና የፀረ አብዮት መግነን ተደጋግፈው ያደጉ ክስተቶች መሆናቸው ነው። ምክንያቶቻቸው የተለያዩ ቢሆኑም፣ የሩስያ ተስፋፊ መንግሥትና የኢትዮጵያ ፀረ-አብዮት ኃይሎች በእከክልኝ ልከክልህ ፓለቲካ በኢትዮጵያ ምድር ላይ በአንድ ወቅት ለመገናኘት በቅተዋል።

በመሆኑም፣ የሩስያ ተስፋፊና ጣልቃ ገብ መንግሥት በአፍሪቃ ቀንድ ተፅዕኖውን አጠንክሮ ለማሳረፍ አመቺ ሁኔታ አጋጥሞት ነበር። ከዚህ ግቡ ለመድረስ ግን፤ እንደዚያ ራስን በራስ ለመቻል፣ ለብሄራዊ ነፃነትና ለገለልተኝነት የሚሟገተውን የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮት መጋፋጥ ነበረበት። ተጋፍጧል ለነዚ የተቀደሱ ዓላማዎች ፀንተው የሚታገሉት ሃቀኛ ተራማጆች፣ ሃገር ወዳዶችና ብሄርተኛ ኃይሎችም ተናንቀውታል። በሌላ በኩል ግን ለኢትዮጵያ ፀረ አብዩት ሃይሎች እንደዚህ [የማይነበብ -አዘጋጆች] ተንሸራቶ ቢሮክራሲው ጉያ ውስጥ ለመከተት እየተሽመደመደ ነበር። በሕዝቡ ላይ ከመተማመን ይልቅ በቢሮክራሲውና በውጭ ኃይሎች ላይ እምነቱን እየጣለ ነበር። በዚህ ሂደት ውስጥ፣ የአብዩቱ ወገኖች ደግሞ በራሱ በ“አብዮቱ”ና በ“በሶሻሊዝም” ስም እየተመቱና እየተጨፈጨፉ ነበር። የኢትዮጵያ ፀረ ሕዝቦች፣ ከተስፋፊዎች አቅጣጫም ሆነ ከቀኝ ኃይሎች፣ ከዚህ የበለጠ የሚፈልጉት ነገር አልነበረም። ተሳክቶላቸዋል።

ቀድሞውንስ ቢሆን፡ አገርና ወገን አፍቃሪ የሆኑትን ሃቀኛ ተራማጆች፣ ዲሞክራቶችና ብሄርተኛ ኃይሎችን ሳይጨፈጭፍ፣ ሳያዳክምና ሳይበትን በኢትዮጵያ ላይ የበላይነቱን ሊያነግሥ የሚችለዉ የውጭ መንግሥት የትኛው ነው??. ፀረ አብዮትንስ ሊሰራ የሚችለው ፀረ አብዮት የትኛው ነው?….. የሩስያ ተስፋፊና ጣልቃ ገብ መንግሥትም በዚህ ልዩ አልሆነም። ውጤቱ ተናግሯል።

“ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሬፑብሊክ ለማቋቋም” የሚታገለው የኢትዮጵያ ሕዝብ በወታደራዊ አምባገነን አገዛዝ ሥር ወደቀ። “ነፃና ጠንካራ የሆነ ብሄራዊ ኢኮኖሚ ለመገንባት” የሚታገለው የኢትዮጵያ ሕዝብ በሩስያ ተስፋፊ መንግሥትና በተቀጢላዎቹ አገሮች የሚበዘበዝና የሚመዘበር ሆነ። “የኢትዮጵያ ብሄረሰቦች አንድነት በእኩልነት፣ እርስ በርስ በመረዳዳት፣ በወንድማማችነትና በመፈቃቀድ ላይ የተመሠረተ እንዲሆን” የሚታገለው ሕዝብ ትምክህተኞች ናጥጠውበት ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ማለቂያ ከሌለው የርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ተከተተ። “የኢትዮጵያ ሠራዊት የሀገሪቱን ነፃነት፣ አንድነትና ሰላም ለመጠበቅ በሚያስችለው ሁኔታ ለማደራጀት” የሚታገለው ሕዝብ፣ ሠራዊቱ በሩስያ ተስፋፊ መንግሥት ተፅዕኖና ቁጥጥር ሥር መውደቁን ማየት በቃ። “የሃገሪቱ የውጭ ፖለቲካ በታወቁት የገለልተኛ አገሮች መርሆች ላይ ተመሥርቶ እንዲመራና ሃገሩ ዕውነተኛ ገለልተኛ አገር እንድትሆን” የሚታገለው ሕዝብ ፣ ገዢዎቹ በውስጥ ቅምጥ መንግሥት የሆኑትን ያህል፣ በውጭ ደግሞ በየደረሱበት የሩስያ ተስፋፊ መንግሥት አፈቀላጤና ግንባር ቀደም አጨብጫቢዎች መሆናቸውን ለመስማትና ለማየት በቃ። በመጨረሻም፣ “ኢሠፓአኮ” የተሰኘው የአድርባዩች፣ የትምክህተኞችና የቢሮክራቶች ድርጅት ተጫነበት።

ነገሩ ግልጽ ነው። ባለፉት ሦስት ዓመቶች ውስጥ፣ የሩስያ ተስፋፊዎች ባንድ በኩል፣ የኢትዮጵያ አድርባዩችና ፀረ አብዮተኞች በሌላ በኩል እየተላላሱ የየልባቸውን አድርሰዋል። የትግል ፍልሚያውም፣ በዛሬው አገዛዝና በሩስያ ተስፋፊ መንግሥት ባንድ ወገንና በሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ በሌላው ወገን እንደሆነ የዚያኑ ያህል ግልጽ ሆኗል። ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ፡ ለዲሞክራሲና ለብሄራዊ ነፃነት የሚያደርገውን ትግል የቀጠለው በዚሁ አቅጣጫ ነው።

ለ/ የተሟላ የፖለቲካ ቁጥጥር

የሩስያ ተስፋፊዎች የደርግን መሪዎች ከኪሳቸው ለመክተት ሲስገበገቡ /በ፶ አለቃ ለገሰ ጀምረው በሻለቃ መንግሥቱ እስከጨረሱ ድረስ/፣ ዋና እቅዳቸው የነሱ ቅምጥና ተገዢ የሆነ መንግሥትና የፖለቲካ ድርጅት ለመፍጠር ነበር። በሚያዚያ ወር 1969 ዓ.ም በሻለቃ መንግሥቱ ኃ/ማርያም የሚመራው ቡድን ሞስኮን ሲጐበኝ በብብሬዥኔቭ የተሰጠው ምክርና ትእዛዝ “በተቻለ መጠን አንድ ወጥ የሆነ ፖርቲ አቋቁሙ፣ በዚህ ፓርቲ አመራር ሥር ለምታቋቁሙት ሠራዊት ማንኛውንም መሣሪያ እንሰጣችኋለን” የሚል ትዕዛዝ ነበር።

ከዚህ ጊዜ በኋላ የሰደድ ክሊክ የብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ኘሮግራሙን ተቃውሞ መጀመሪያ ኢማሌድህን እንዴት እንዳኰላሸውና እንደበተነው፣ ከዚያም በኋላ እንዴት ወደ “ኢሠፖአኮ” እንዳመራ አገር ምድር ያውቀዋል። እንደተጠበቀው “ኢሠፓአኮ የተሰኘውን ጉድ ደግሞ፣ ከመጀመሪያ እስከመጨረሻው በበላይነት በመቆጣጠር ያደራጁት የሩስያ ተስፋፊዎችና ተቀጢላዎች ነበሩ። የመዋቅሩን ቅርፅ የሰጡት፣ “የታወቀው” ሩስያዊው ቫራዩቨ /በነገራችን ላይ ኢህአፖም ሲመሠረት ያግዝ የነበረ የኬጂቢ ሰላይ/ እና እንደ ኩብያዊው ራኦል ቫልዲሶ ቪቮ የመሳሰሉት ሰዎች ናቸው። ኢትዮጵያውያንን በሚመለከተው፣ ሞስኮና ሌሎች ምሥራቅ አገሮች ውስጥ “እየነቁ” መጡ የተባሉት “ጓዶች” በተላላኪነትና ቢበዛ በአማርኛ ሥነ ፅሁፍ አገልግለው እንደሆን እንጂ፣ አንዳችም ስፍራ አልነበራቸውም። “ኢሠፖአኮ” ከተመሰረተም በኋላ፣ የተስፋፊዎች ቤተሰብ ውስጥ፣ “የትልቁ” ሰውዬ- የአባወራው የብሬዠነቭ ፊት በተቋጠረ ቁጥር፣ የሻለቃ መንግሥቱን ድንፋታ ከማዳመጥ በስተቀር ሌላ የሚሠሩት ነገር የላቸውም። አይችሉምም። ባጭሩ፣ የ“ኢሠፖአኮ” አመሠራረትም ሆነ አሠራር የማንኛውንም አሻንጉሊት ለመሆን የታጨ ድርጅት አመሠራረትና የአሠራር ህግን የተከተለ ነው። የሩስያ ተስፋፊዎች የተሟላ የፖለቲካ ቁጥጥር የሚያደርጉበትን የሃገር ደላሎች የተሰበሰቡበትን የድርጅት መሣሪያ አግኝተዋል።

ሆኖም፣ የውስጡን የፖለቲካ ሁኔታ ለመቆጣጠር የሚያደርጉት ጥረት የተሟላ ፍሬውን ሊሰጣቸው አልቻለም። በጠቅላላ የፓለቲካ ተቃውሞ ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ፣ ፖርቲያቸውን ለማደራጀት መንፈራፈር ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ መሣቂያና መሣለቂያ በማድረግ አክ እንትፍ ብሎ ተፍቷቸዋል። ኢሠፓአኮአቸውም፣ በውነትም ሰፊው ሕዝብ ባወጣለት – የኢትዮጵያ ሠላጣና ፖፖዬ አምራች ኮርፖሬሽን /ኢሠፖአኮ/ ስሙ ሊጠራ ይችላል። መሰብሰብ የቻሉት፣ በትክክል ‘ሠላጣና ፖፖዬ’ የሚመሳሰሉ የሚሊተሪ – የሲቪል ቢሮክራቶችን ወይንም ዓይን ያወጡ አደርባዮችን፣ ያለዚያም በትእዛዝ የሚያስገድዱትንና የሞሾሙትን ብቻ እንደሆነ “ታሪካዊው” የመጀመሪያ ጉባኤያቸውን መስክሯል።

የሃገሪቱ የውጭ ፖለቲካ በሚመለከተው ግን የሩስያ ተስፋፊዎች የሚመኙትን አግኝተዋል። ኢትዮጵያም “ስንተኛዋ የሶቭየት ሕብረት ጠቅላይ ግዛት ትሆን??” ተብሎ የሚጠየቅበት የሃፍረት ደረጃ ላይ ደርሳለች። በተለይ፣ ልክ እንደውጫሌው ውል ተስፋፊዎችን ሳናማክር በዓለም አቀፍ ሸንጎዎች ላይ አቋም ላንወስድ ከተፈረመበት “የሰላምና የወዳጅነት ስምምነት” ጊዜ አንስቶ፣ ኢትዮጵያ በዓለም ሕዝቦች ሸንጎ ላይ ከቁጥር መግባቷ ቀርቷል ለማለት ይቻላል። “ኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርስ ምን አስፈለገ?” መባሉም ትክክል ነው። የኢትዮጵያ “ተወካዮች” ውንጥ ውንጥ የሚሉት ከሞስኮ በሚቃኝላቸው የውጭ ፖሊሲ ሙዚቃ እንጂ፣ የኢትዮጵያ ክብርንና ጥቅም ለማስከበር እንዳልሆነ ዓለም አውቆታል። ከሁሉ አሳፋሪም ነገር አለ እንጂ!!

ዛሬ ሃገሪቱ ላይ የሚፈነጩት ባለሥልጣኖች አገራችንን ለፍርፋሪና ለከንቱ ሙገሳ መሸጣቸው አንሶ፣ አፍሪካንም ለማስማማት ሽር ጉድ ይላሉ። “ሞኝ ያገኘው ፈሊጥ” እንዲሉ፣ የቻይናን መንግሥት እንዴት ሲያወግዙ እንደነበር እናውቃለን። በሄዱበት አገሮች ሁሉ በዚህ ጥያቄ ላይ “አቋም ለማስወሰድ” በጥራዝ ነጠቅ አንደበታቸው ሲያጓሩ ያተረፉት ነገር ቢኖር፣ ራሳቸው መሳለቂያና መሳቂያ ሆነው፣ ሃገሪቱንም ከውርደት ላይ መጣል ነው። አንዴ፣ ሻለቃ መንግሥቱ ኃይለማርያም ለጉብኝት ታንዛንያ በሄዱበት ወቅት፣ ኒሬሬን በዚህ ጉዳይ ላይ አቋም እንዲወስድ ጠይቋቸው ነበር። ነገሩ አልዋጥ ያላቸው የተማሩት ኒሬሬ ሲመልሱ ግን፣ “የለም ጎበዝ፣ ባይሆን ሁላችንም ንግግር ማድረጉ ይቅርብን” ብለው በራት ግብዣና በትዝብት ግብዣ እንደሸኙት ይነገራል። ሃቫና ተደርጎ በነበረው የገለልተኛ ሃገሮች ጉባኤም ላይ፣ ሌላው ቀርቶ ፊደል ካስትሮ ራሱ እስኪታዘባቸው ድረስ፣ “ገለልተኛ አገሮች የሶሻሊስት አገሮችን ወገን መመምረጥ አለባቸው” እያሉ ሲያጓሩ ሃገሪቱን የተለመደው ትዝብት ላይ ጥለውታል።

የአፍጋኒስታን ሁኔታም፣ ካለፈው ሁሉ ይበልጥ ማፈር ከተቻለ፣ ይበልጥ የሚታፈርበት ነው። ከዓለም አገሮች ሁሉ፣ ሶቭየት በአፍጋኒስታን የፈፀመችውን ወረራ የደገፉት 18 የሶቭየት ተቀጢላ አገሮች ብቻ ነበሩ። ከነዚህ ውስጥ እንደ ዩክሬን ዓይነቶቹ በሃገርነት ስም የተመዘገቡ7/ የሶቭየት ህብረት ክፍለ ሃገራትና እንደ ኢትዮጵያ ዓይነቶቹ አዲስ ቅኞች ናቸው። መቼም ነገሩ የሚያስገርምና እንደው ባጭሩ “አልሰሜ የእናቱን ተዝካር ይበላል” የሚባለውን ያባቶች ተረት የሚያስታውስ ነው። የሩስያ ተስፋፊዎች አፍጋኒስታንን ሲወሩ የተመረኮዙበት ሰነድ፣ ከወረራው ጥቂት ወራት ቀደም ብለው ከዚያች አገር መሪዎች ጋር የተፈራረሙትን የ20 ዓመት “የሰላምና የወዳጅነት ስምምነት” የተባለው ሰነድ ነው። እንደዚህ ዓይነቱን “ስምምነት” ደግሞ፣ የዘመናችን ባንዳዎች ከአፍጋኒስታኑ ወራሪ ከሶቭየት ህብረት ጋር ተፈራርመውታል።

ደግሞ የዙምባብዌን ጉዳይ እንመልከት፦

የአርበኞቹ መሪዎች በለንደን አድርገውት የነበረው ስምምነት ሶቭየት ህብረት “ጦርነት ሊቆምብኝ ነው፣ ምርጫ ከተባለ ደግሞ እኔን የማይደግፈኝ የሙጋቤ ወገን ሊመረጥ ይችላል” በሚል ርኩስ አስተሳሰብ ታቃውማ ነበር። ይህችን ሲሰሙ፣ የኛዎቹ ቅምጦች ባሱ! [የማይነበብ -አዘጋጆች] “ሕዝባዊ” ድርጅቶችን እየሰበሰቡ “ውይይቱንም፣ ስምምነቱንም፣ የምርጫውንም ውጤት አንቀበልም” የሚሉ ውሳኔዎችን ያዥጎደጉዱት ጀመር። “የፈሩት ይደርሳል” ነውና ምርጫው ተካሄዶ የሙጋቤ ወገን አሸነፍኩኝ ብሎ ብቻውን ሥልጣን ከመያዝ ይልቅ፣ እጅግ አስተዋይነቱን ያስመሰከረበትን፡ ከቀድሞ ጠላቶች ሳይቀሩ በሃገሪቱ አስተዳደር ውስጥ የሚሳተፉበትን መንግሥት ሙጋቤ አቋቋመ። ሃገሪቱም ፍጹም ገለልተኛ እንደምትሆን አስታወቀ። የኛዎቹም፣ የሩስያ ተስፋፊዎችን ጠብቀው ሲፈሩ ሲቸሩ የሙጋቤን መንግሥት አወቀ። ጦርነቱ ቢቀጥልላቸውማ ኖሮ ለሩስያ ተስፋፊዎች ጥቅም የኢትዮጵያ ወጣቶች ወደ ዚምባብዌ ዘምተው እንዲያልቁ ተደግሶላቸው ነበር። ከባዕድ ቅምጥ መንግሥት ከዚህ የተለየ አይጠበቅም።

6.ማህበራዊና ባህላዊ ተፅዕኖ

የሩስያ ተስፋፊና ጣልቃ ገብ መንግሥት አገሪቱን በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በወታደራዊ መስኮች እንዴት ከቁጥጥር ሥር እንደቀጠለ ባጭሩ ያሳየን ይመስለናል። ነገር ግን ማንም ሃቀኛ ኢትዮጵያዊ ዜጋ እንደሚያስተውለው፣ ተስፋፊዎቹ በሃገሪቱ ጉዳይ ውስጥ የማይገቡበት ቀዳዳ እንደሌለም ግልጽ ነው። በዚህ በኩል፣ የሶቭየት ህብረትን “ኃያልነትና” የሶቭየት ህብረትን “የበላይነት” ለመጋትና፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሃገር ፍቅር ስሜት እንዲላሽቅ ለማድረግ የሚወርደው የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ ራሱን የቻለ ክፍል ሆኖ ይመጣል።

ለሕዝብ ማስተማሪያ፣ ለሃገር ፍቅር ስሜት ማጠናከሪያ፣ ለዲሞክራሲያዊና ሕዝባዊ ትግል መቀስቀሻ መዋል የሚገባቸው የዜና ማሰራጫዎች፣ የትምህርት ተቋሞች፣ ሕዝባዊና መንግሥታዊ ድርጅቶች፣ በሃገር ቋንቋዎች የሚሠሩ የሩስያ ተስፋፊዎችና የተቀጢላዎቻቸው አፈቀላጤ ሆነዋል። በማርክሲዝም አስታከው የሚለፍፉትም፣ የሩስያ ተስፋፊዎችን “ፍጹማዊ የበላይነት” በኢትዮጵያ ሕዝብ ህሊና ውስጥ በጉልበት ለመስረፅ እንጅ ሌላ ዓላማ ያለው ጉዳይ አይደለም። የሶቭየት ህብረት ‘ታላቅነት’፣ የሶቭየትና የተቀጢላዎቿ ‘የበላይነት’፣ የመሪዎቻቸው ‘አስተዋይነትና ብልህነት’ ካልተወደሰ የማይሆነው ለዚህ ነው። ይህን ከንቱ ውዳሴ ያላዘለ ፅንሰ ሃሳብና ንግግርም የማይሰማው ለዚህ ነው። እንደውም ግዴታ ነው። ይህ በ‘ግራ’ አድርጎ ወደ ዘረኝነት ይጠጋ እንደሁ እንጂ ከወዝአደሩ ርዕዮተዓለም ጋር የሚያዛምደው ነገር የለም።

የአዲሱን ትውልድ አእምሮ ለመሰለብ፣ ማናቸውም ማህበራዊ አውታሮችና የትምህርት ተቋሞችን በቁጥጥር ሥር ለማዋል ከፍተኛ ዘመቻ ይካሂዳል። ሃገሪቱን ምሁር አባል አደርጎ፣ የአሜን ባይ ምሁራንን ትውልድ ለመተካት ዓይን ያወጣ ፀረ ምሁር ዘመቻና ፕሮፖጋንዳ ይካሄዳል። በዩኒቨርሲቲ አካባቢ የሚገኙ ሃገር ወዳድ ምሁራን “የኢምፔሪያሊስቶች ግርፍ” እየተባሉ የቁም ስቅላቸውን ያያሉ። በነሱ ፈንታ አፍ ያልፈቱ የሶቭየት ህብረትና የሌሎች ምሥራቅ አገሮች መምህራን እየተተኩ መደነቋቆሩ አንሶ፣ ብሄራዊ ይዘት ያለው ትምህርት እንዲጠፉ እየተደረገ ነው። በዚህ ላይ ደግሞ፣ ከጣልያን ዘመን ወዲህ ባልታየ ትምክህተኝነትና ዘረኝነት የኩሩውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ቆሽት እያሳረሩት ናቸው። ሕዝቡ ሚስቱንና ልጁን “ለዓለም አቀፍ” ፍትወት ማስተናገጃ እንዲያቀርብ እየተገደደ፣ አሳፈሪ የሆነ የውርደትና የፀፀት ታሪክ በመፃፍ ላይ ይገኛል።

እንግዲህ እናጠቃል፣

መኢሶን ገና በመጋቢት 1969 ዓ.ም. የዚህ ሁሉ ውርደትና ፀረ አብዮት ሽታ ሲጀምር፣ “በዓለም አቀፋዊነት” ስም ከሚደገስልን ባርነት እንድንጠነቀቅና ይህንን ሤራ እንድንዋጋ ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል። በፕሮግራሙም ላይ ሆነ፣ በርሱ ግንባር ቀደምነት በተዘጋጀው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራም ላይ አብዮታችንንም የሚያራምድ፣ ብሄራዊ ነፃነታችንንም የሚያስከብር የገለልተኛነት ፖለቲካ ቀይሶ ተዋድቋል። እየተዋደቀም ነው። ከዚህ ዓላማው ቅንጣትም ፈቀቅ ሳይል ባለፉት ሦስት ዓመታት በፖለቲካ፣ በፕሮፖጋንዳና በዲፕሎማቲክ መስኮች ከፍተኛ ትግል አካሂዷል። ሌላው ቀርቶ፣ በመኢሶን የውጭ አካል አማካኝነት፣ በተለይ ከኩባና የደቡብ የመን መንግሥታት ጋር በመገናኘት “በኢትዮጵያ በሚካሄደው የአብዮት ቅልበሳ፣ እንደጎርፍ በሚፈሰው የኢትዮጵያ ልጆች ደም በታሪክ ፊትና በዓለም ተራማጆች ፊት ተጠያቂ እንደሚሆኑ ለማስረዳት ከፍተኛ ጥረት ተደርጎ ነበር። ነገር ግን መኢሶን የተጠየቀው፣ ገለልተኝነትን ትቶ የነርሱን “ዓለም አቀፋዊነት” እንዲቀበል። በኢትዮጵያ ሕዝብ እተማመናለሁ የሚለውን ትቶ፣ እምነቱን ሁሉ “በታላቋ ሶቭየት ህብረት ላይ እንዲጥል”። የሃቀኛ ተራማጆች ህብረትን ትቶ የሻለቃ መንግሥቱን “ብቸኛ መሪነት” እንዲቀበል፣[የማይነበብ -አዘጋጆች] ክብሩን ሽጦ ለተስፋፊዎች እንዲያድር ተፅዕኖዎች በተደጋጋሚ ተሞክረውበት ነበር።

የተደረጉት ውይይቶችና ውጤታቸው መኢሶንን በሃገር ፍቅር ስሜቱ እንዲበረታ አደረጉት እንጂ፣ ለተስፋፊዎችና ለቡችሎቻቸው እንዲያጎበድድ አላደረጉትም። ወደፊትም ቢሆን፣ ንቅናቄያችን አብዮታችን ግቡን ሳይመታ፣ ብሄራዊ ክብራችንን መልሰን ሳንጎናፀፍ፣ የውጭ ጦር ከነ ጓዙና ከነ ከተቱ ከኢትዮጵያ ምድር ሳይወጣ በፊት የትግላችንን ትጥቅ አንፈታም። ይህ ለተስፋፊዎቹም፣ ለከሃዲዎቹም፣ ግልጽ መሆን ያለበት ገዳይ ነው። ከዚህ በላይ እንዳልነው፣ በዛሬው ወቅት ዋናው ቅራኔ በዛሬው አገዛዝና በሩስያ ተስፋፊ መንግሥት ባንድ ወገን፣ በኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ በሌላው ወገን ነው። መኢሶን ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን ተሰልፎ በትግሉ ይቀጥላል።

7. አቋማችን እንደገና

የኢትዮጵያ ሕዝቦች ለብሄራዊ ነፃነትና ለሕዝባዊ አርነት እስከዛሬ ያካሄዱት ተጋድሎ በኩራት የሚታወሰውን ያህል፣ ዛሬ ደግሞ በሃፍረት የምንመዘግበው ሃቅ አለ። “በብሄራዊ ነፃነቷ ለዘላለም ትኑር” የምንላት ኢትዮጵያችን በሩስያ ተስፋፊዎች የእጅ አዙር ቅኝ ግዛትነት ለባርነት ተዳርጋ፣ የነርሱ ቅምጥ በሆነ ወታደራዊ አምባገነን አገዛዝ ሥር እየማቀቀች ነው። ከሁሉም በላይ፣ እኛ ሃቀኛ ተራማጆችን የሚያንገበግበው ደግሞ ይህ ሁሉ በ“ሶሻሊዝም” ስም፣ ይህ ሁሉ በ“ኮሚዩኒዝም” ስም መሆኑ ነው። ይሁንና፣ ይህ ብሄራዊ ነፃነትን በብሄራዊ ባርነት፣ ፍትህን በአምባገነንት፣ ዲሞክራሲን በፈላጭ ቆራጭነት፣ ሰብዓዊ መብትን በሰብዓዊ ስቃይ፣ የብሄረሰቦች ዕኩልነትን በትምህክተኝነት፣ ሰላምን በጦርነት፣ ሕዝባዊ ብልፅግናን በረሃብ በስደትና በጭቆና የሚለውጠው ‘ሶሻሊዝም’ የተስፋፊዎችና የቅምጦቻቸው እንጂ፣ እኛ ከምናውቀው፣ እኛ ከሞትንለት፣ እኛ ከምንሰዋለትና የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ በአድናቆት ያልመው ከነበረው ሶሻሊዝም ጋር የሚያዛምደው አንዳችም ነገር እንደሌለ መታወቅ አለበት።

የሩስያ ተስፋፊዎች “ሶሻሊዝምና ኮሚዩኒዝም”፣ በአደናቋሪ ፕሮፖጋንዳና በአፍ ሳይሆን ዛሬ ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ በገሃድ በሚያየው በብሄራዊ ባርነት፣ በፈላጭ ቆራጭነት፣ በስቃይና ግፍ፣ በጦርነትና ዕልቂት፣ በረሃብና በጭቆና የሚመስለው ነው። እውነተኛ ሶሻሊዝም ግን፣ በማይገሰስ ብሄራዊ ነፃነት በብሄረሰቦች እኩልነት፣ በዲሞክራሲና በሰብአዊ መብት፣ በሕዝባዊ ብልፅግናና በሃገር ዕድገት መሠረት ላይ የሚገነባው፣ የሰውን ተሰው መበዝበዝ ከሥረ መሠረቱ የሚያስወግድና እውነተኛ እኩልነትን የሚያሰፍነው ነው። ይህ የታወቀ ጉዳይ ነው። ይሁንና፣ ተስፋፊዎችና ቅምጦቻቸው በሳሉት የ“ሶሻሊዝም” የጣረ ሞት ምስል የተነሳ ኢትዮጵያ ለዚህ መብቃቷ ራሱ፣ በኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ንቃተ ህሊና ውስጥ ስለ ሶሻሊዝምና ኮሚዩኒዝም የተዛባ ስዕል /በጭንቅላቱ የቆመ/ እንዲሰርጽ ማድረጉ አይቀርም።  ስለሆነም፣ የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ለተቀደሰው ሃቀኛ ሶሻሊዝም ያለው አድናቆትና አክብሮት ተመልሶ እንዲታደስ ለማድረግ እንኳን፣ ራሱን የቻለና ካለፈው ያላነሰ መስዋዕትነት የሚጠይቅ እጅግ የተወሳሰበ ትግል፣ ሃቀኛ ተራማጆችን ወደፊት እንደሚጠብቃቸው ከአሁኑ መናገር ይቻላል። ዛሬ ግን ለሁሉም መነሻ የሚሆነው የተገሰሰው የብሄራዊ ነፃነታችን ጉዳይ አለ። ከሁሉም አስቀድሞ ኢትዮጵያ ዛሬ ካለችበት ከሩስያ ተስፋፊዎች የባርነት ቀንበርና ከቅምጥ መንግሥታቸው ፈላጭ ቆራጭነት ተላቃ “በብሄራዊ ነፃነቷ ለዘላለም ትኑር” የምንላት መሆን አለባት። ለዚህ ሃገሩንና ወገኑን አፍቃሪ የሆነ ሁሉ ለብሄራዊ ነፃነቱና ለሕዝባዊ አርነቱ የሚደረገውን የጋራ ተጋድሎ በቆራጥነት መቀጠል ይኖርበታል። የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሰጠው የብሄራዊ ነፃነታችን ጉዳይ ነው። የሩስያ ተስፋፊዎች ሃገራችንን ለቀው ይውጡ

 

1. ብሄራዊ ነፃነት፦

የኢትዮጵያ ሕዝብ ነፃነቱንና ክብሩን ለማስጠበቅ ሲጋደል የኖረና የሚኖር ሕዝብ መሆኑ ተብሎ ያላቀ ነው። ይህ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሲዋደቅለት የኖረው ብሄራዊ ነፃነት ግን ከአብዮታችን ቅልበሳ ጋር ተያይዞ በዘመናዊ ባንዳዎችና ከሃዲዎች አማካኝነት የባዕድ ኃይሎች እጅ መንሻ ተደርጎ ተገሷል። በኢትዮጵያ ሕዝብ ጫንቃ ላይ የተፈናጠጠው ወታደራዊ አምባገነን መንግሥት፣ የሩስያ ተስፋፊና ጣልቃ ገብ መንግሥት ጫማ ላሽ ሆኖ በቅምጥ መንግሥትነት እያገለገለው፣ ሃገራችን ኢትዮጵያን የብሄራዊ ውርደት ማቅ አከናንቧታል። ይሁንና፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ደግሞ ይህን የዓለም መሣለቂያ ያደረጋቸውን [የማይነበብ -አዘጋጆች]

መኢሶን ለብሄራዊ ነፃነት ተጋዳይነቱን ምንጊዜም እንዳስመሰከረው ሁሉ ዛሬም፣ የሃገራችንን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የወታደራዊ ተቋም በቁጥጥራቸው ሥር አድርገው ኢትዮጵያን በባርነት የሚገዙት የሩስያ ተስፋፊዎች እንደ አሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም በቅሌት ከኢትዮጵያ እንዲባረሩ ለማድረግ ትግሉን ይቀጥላል። መኢሶን ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ሆኖ የሚዋደቀው፣ የዛሬዎቹ የቅምጥ መንግሥት ባለሟሎች እንዲህ ላዋረዷት ኢትዮጵያ ሳይሆን፤ የማንም ተቀጢላ ያልሆኑች፣ ነፃ፣ ዲሞክራሲያዊት፣ ኩሩ፣ የበለፀገችና በራሷ የምትተማመን ሕዝባዊት ኢትዮጵያን ለመመሥረት ነው። በማንም የባዕድ ኃይል እንዲገሰስበት ለማይፈቀደው ብሄራዊ ነፃነት፣ መኢሶን ለሃገር ክብርና ለወገን ነፃነት ከቆሙ ሃቀኛ ዜጎች፣ ሃገር ወዳድና ዲሞክራቶች ጋር ጎን ለጎን ሆኖ ተጋድሎውን ይቀጥላል

2. የብሄረሰብ ጥያቄና የርስ በርሱ ጦርነት፦

የብሄረሰቦች እኩልነት ያለአንዳች ገደብ ታውቆ በሥራ ካልተተረጎመና ካልተረጋገጠ፣ ይህች የአያሌ ብሄረሰቦች ምድር የሆነችው ውድ ኢትዮጵያችን ከቶም አንድነቷን ልታገኝ አትችልም። በእኩልነት፣ በመፈቃቀድና በወንድማማችነት ላይ የተመሠረተች፣ አንድነቷ ከብረት የጠነከረ፣ ሕዝባዊትና ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያም ልትመሰረት የምትችለው፣ ይህ የብሄረሰቦች የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የመወሰን እስከመገንጠል ድረስ ያላቸው የማይናወጠው ዲሞክራሲያዊ መብታቸው ተከብሮ ሲረጋገጥ ብቻ ነው። በተስፋፊው የሩስያ መንግሥት እየተደገፈ፣ ቅምጡ ወታደራዊ አምባገነን መንግሥት በጭቁኑ ብሄረሰቦች ላይ ዛሬ በሚያወርደው ትምክህተኝነት የተነሳ ግን፣ ኢትዮጵያ እውነተኛ አንድነቷን ከቶም ልታገኝ አልቻለችም። እንዲያውም፣ ወንድማማች ሕዝቦች የሚተላለቁበት፣ የተስፋፊዎች የጦር መሳሪያ መፈተሻ፣ የነርሱ ጦር መሳሪያ ማራገፊያና የነርሱ ጥቅም ማካበቻ የሆነ የርስ በርስ ጦርነት በየአቅጣጫው የተስፋፋባት የተበታተነች ሃገር ሆናለች። በሰሜን፣ በደቡብ፣ በምሥራቅና በምዕራብ፣ በኢትዮጵያ አራቱም ማዕዘን በኢትዮጵያ ጭቁን ብሄረሰቦች ላይ የሚወርደው የትምክህተኛ ቅምጥ መንግሥትና የሩሲያ ተስፋፊዎች ፀረ ጭቁኖች አመፅ መረን ለቋል። ኢትዮጵያ ብሄረሰቦቿ በነፃና በዲሞክራሲያዊ መንገድ የሚያብቡባት ነፃና ጠንካራ ኩሩ ምድር ሳትሆን፣ የገዛ ብሄረሰቦቿ እንደቅጠል የሚረግፉባት፣ በእርስ በርስ ጦርነት የተወጠረች . . .  ብሎም የሁለቱ ኃያላን መንግሥታት መፋለሚያ ለመሆን የቀረበች ሃገር ሆናለች።

  የኢትዮጵያ መለዮ ለባሽም፣ በአብዮት ስም ለተቀለበሰ አብዮትና ለፀረ አብዮት፣ በአንድነት ስም ለመበታተን፣ በብሄራዊ ነፃነት ስም ብሄራዊ ነፃነታችንን ለባዕድ ተስፋፊ ኃይል ለሸጠ ቅምጥ መንግሥት በከንቱ ደሙን የሚያፈስ ወገን እንዲሆን ተደርጓል። ቃልኪዳን ለገባላት፣ ሰላም ብልፅግናና ዕድገት ለሚታይባት ሕዝባዊት ኢትዮጵያ በመዋደቅ ፋንታ፣ በተስፋፊዎች እየታዘዘና እየተረሸነ የትምክህተኞች ጦርነት እንዲያካሂድ እየተገደደ ነው። ይሁንና፣ የኢትዮጵያ መለዮ ለባሽ ቃልኪዳኑ ለብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራም እንጂ ለትምክህተኝነት አይደለም። ፍላጎቱ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምን አባሮ ብሄራዊ ተፃነቱን ለማስከበር እንጂ የሩስያ ተስፋፊዎችን በርሱ እግር ተክቶ ለሌላ ብሄራዊ ውርደት ለመቆም አይደለም። ፍላጎቱ ሰላም እንጂ፣ የኢትዮጵያ ጭቁን ብሄረሰቦች ላይ ጦርነት ማካሄድ ከቶም አይደለም። በመሆኑም፣ ቃልኪዳኑ ለብሄራዊ ነፃነቱና ለአብዮቱ፣ አቋሙ ከጭቁን ብሄረሰቦችና ከኢትዮጵያ ሕዝቦች ዲሞክራሲያዊ መብት መከበር ጋር እንጂ ሌላ ሊሆን አይገባም።

ዛሬ በኢትዮጵያ አራቱም ማዕዘን የሚታየው የርስ በርስ ጦርነት “የሰርጎ ገቦች ጦርነት፣ የሱማሌ ወረራ፣ የተገኝጣዮች ሴራ. . . ወዘተ” ተብሎ በሚያደነቁር መዝሙር የሚታለፍ ጉዳይ አይደለም። በኢትዮጵያ የሚታየው የርስ በርስ ጦርነትን ምንጭ፣ እንደ ሱማሌ ያሉ ፀረ ኢትዮጵያ የሆኑ ተስፋፊ ኃይሎች የፈለጉትን ያህል ቢኖሩም፣ የችግሩ ምንጭ በኢትዮጵያ የብሄረሰቦች ጥያቄ ተገቢ መልሱን አለማግኘቱ ነው። የቅምጡ መንግሥት ትምክህተኝነት ያስከተለው ጠንቅ ነው። የሩስያ ተስፋፊዎች ለሚያካብቱት ጥቅም ሲሉ ኢትዮጵያን ማለቂያ የሌለው ጦርነት ውስጥ ለመክተት በፈለጋቸው ነው። የሩስያ ተስፋፊዎች ኢትዮጵያን በቁጥጥራቸው ሥር አድርገው በብሄራዊ ባርነት መግዛታቸው ነው። ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ መለዮ ለባሽም ሰላም የሚያገኙት ትምክህተኛው ቅምጡ መንግሥት በጭቁን ብሄረሰቦች ላይ ያወጀው ጦርነት ሲቆምና የኢትዮጵያ ብሄረሰቦች የራሳቸውን [የማይነበብ -አዘጋጆች]

መኢሶን፣ ተስፋፊዎችና ቅምጡ መንግሥታቸው በጭቁን ብሄረሰቦች ላይ የሚያወርዱትን ጭፍጨፋ እያወገዘ፣ ይህ መብታቸው እንዲከበር ያላሰለሰና የማያወላውል ተጋድሎውን ይቀጥላል። መኢሶን፣ ይህ ለሩስያ መንግሥት ጥቅም ማካበቻ በቅምጥ መንግሥታቸው የሚካሄደው የርስበርስ ጦርነት እንዲቆም፣ መብታቸው ከተረገጠና ከሚጨፈጨፉት ጭቁን ብሄረሰቦች ጎን በመሆን እየታገለ፣ ሰላም ለኢትዮጵያ መለዮ ለባሽ እንዲወርድ፣ ሰላም በኢትዮጵያ እንዲሰፍን፣ ብሎም ብሄራዊ ነፃነቷ የተከበረና ብሄረሰቦቿ በእኩልነት የሚኖሩባት አንድነቷ ከብረት የሚጠነክር፣ ሰላማዊት፣ ኩሩና የበለፀገች ኢትዮጵያ እንድታብብ ይታገላል

3. ፍትህ፣ ዲሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብት፦

በራሱ ሃገርና በራሱ ሕዝብ ላይ ዲሞክራሲን አፍኖ በአምባገነንነት የሚገዛ፣ የገዛ ሕዝቡን ሰብአዊ መብት ረግጦ በጭካኔ የሚመራ የባዕድ ኃይል- /ሶቭየት ሕብረት ከአርጀንቲና ጋር ሰብአዊ መብትን በመድፈር ከመጀመሪያዎቹ ሦስት የዓለም ሃገሮች አንዷ ናት/ – ቅምጥ ከሆነ መንግሥት ጌታው ከሆነው የተለየ ይሆናል ተብሎ አይጠበቅም። የሩስያ ተስፋፊዎች በሃገራችን ጉዳይ ጣልቃ መግባት እንደጀመሩ አብዮታችን እየተቀለበሰ የመምጣቱን ያህል፣ ዲሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶችም በቅምጡ መንግሥታቸው ያንኑ ያህል እየተረገጡ፣ ዛሬ በፀረ ዲሞክራሲ፣ በፀረ ርትዕና በኢ-ሰብአዊ አየር ውስጥ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ታፍኗል። ታጋይ የኢትዮጵያ አብዮታዊ ልጆች በመቶ ሺህ ያለቁትን ያህል በብዙ ሺህ በአስር ቤቱ ታጉረው ፍጹም ኢ-ርትዕና ኢ-ሰብአዊ ስቃይ እየደረሰባቸው ነው። በነዚሁ በሩስያ ተስፋፊዎችና ተቀጢላዎቻቸው፣ በኢ-ሰብአዊነት የሠለጠኑትና ዘመናዊ በሆነ የጭካኔ ዘዴ በተካኑት፤ በእነርሱ አማካሪዎች አማካኝነት መሠረታዊ የሰው ልጅ መብት በኢትዮጵያ ተረግጦ ይገኛል። ፍትህ ተጥሷል፣ ዲሞክራሲና ሰብአዊ መብት ተረግጧል።

መኢሶን፣ የሩስያ ተስፋፊዎችና ቅምጡ መንግሥታቸው በኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ላይ የሚያወርዱትን ኢ- ርዕትና ኢ-ሰብአዊነት እያጋለጠ፣ የፖለቲካ እስረኞች ያለአንዳች ግዴታ እንዲለቀቁ ይሟገታሉ። በአጠቃላይ ለፍትህ፣ ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ሙሉ በሙሉ ያለአንዳች ገደብ መከበር ያሰለሰ ትግሉን መኢሶን ይቀጥላል።

4.  የደቀቀና የዘቀጠ የኑሮ ሁኔታ፣ ረሃብና ችግር፦

የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ አብዮቱን ያካሄደው ከ5 ሚሊዮን የሚበልጡ ወገኖቹ በረሃብ እንዲያልቁ፣ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ወገኖቹ ከውድ እናት ሃገራቸው ተሰደው በሰው ሃገር ባይተዋር ሆነው እንዲኖሩና መላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች በችጋርና በስቃይ ወስጥ እንደዛሬው እንዲማቅቁ አልነበረም። ይሁንና፣ አብዮቱ የተቀለበሰበት፣ ብሄራዊ ነፃነቱ ከተራበ ሕዝብ መንጋጋ ዳቦ /ስንዴ/ በሚነጥቅ ተስፋፊ መንግሥት የተገሰሰበት፣ በሕዝባዊና በዲሞክራሲያዊ አስተዳደር ፈንታ ፀረ ዲሞክራሲያዊ ወታደራዊና የባዕድ ኃይል ቅምጥ የሆነ መንግሥትን ያተረፈ ሕዝብ ዕጣው ይኸው ነው። ወዛደሩ፣ ገበሬው፣ ከተሜው በጠቅላላው መላው የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ በርሃብና በችጋር እየተጠበሰ ነው።

በጀግናው ሰፊ የኢትዮጵያ ሕዝብና በግንባር ቀደም ልጆቹ  ትግል የተገኘው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራም አንደኛው አላማ፣ የሰፊውን ሕዝብ ኑሮ ማሻሻል ነበር። ብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት በሚካሄድበት አገር ውስጥ ደግሞ የሰፊውን ሕዝብ ኑሮ ለማሻሻል የተተለሙ ዓላማዎች ለዝንተ ዓለም የተነደፉ፣ ወይንም ለቅምጦች መመፃደቂያና ለግድግዳ ጌጣቸው የታሰቡ ሳይሆኑ የቅርብ ጊዜ ዓላማዎች ናቸው። መለስተኛ ፕሮግራም የሚባለውም ለዚሁ ነበር። ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራም ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ አላማዎች ውስጥ ዋና ዋናዎቹ ደግሞ፤ አርሶአደሩ የመሬቱ ባለቤት ሆኖ የሥራ ፍሬውን ይጠቅመኛል በሚለው መልክ እንዲገለገልበት፣ ወዛደሩ የሥራ መብቱ ተጠብቆ እንደሥራው የጉልበቱ ዋጋው እንዲከፈው፣ ነጋዴው ሥርዓት ባለው መንገድ በተመጠነለት መስክ ተሳትፎውን እንዲያሳድግ፣ ብሄራዊ ከበርቴው የውጭ ኢምፔሪያሊስት ተፅዕኖ ታግዶለት ለሃገር ብልፅግና እንዲሠራ፣ ንዑሱና የቀረው የሕብረተሰብ ክፍልም እንደሥራው የአገልግሎቱ ፍሬ እንዲያገኝ፣. . . ወታደሩ ሰላም አግኝቶ ብሄራዊ ነፃነትን ከመንከባከብ ባሻገር በምርት ሥራ ውስጥ እየተሳተፈ የሃገር ኢኮኖሚን እንዲያዳብር፣ የእርሱም ኑሮ እንዲሻሻል. . . ወዘተ ነበር። ይሁንና፣ ብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮቱ የተቀለበሰበት ሕዝብ፣ የባዕድ ቅምጥ መንግሥት የተንሰራፋበት ሕዝብ ምሱ ሌላ መሆኑ የታወቀ ነው።

አርሶአደሩ ያተረፈው እርሻ መሬቱን በተስፋፊዎች መነጠቅና መራብ፣ በጦርነት እየተገፉ መሬቱን መልቀቅና መሰደድ፤ ወዛደሩ ያተረፈው በባርንት ደሞዝ የሥራ ጉልበቱን መሸጥና በብዙ ሺህ ወደ ቦዘኔነት ማሽቆልቆል፤ ነጋዴውና ብሄራዊው ከበርቴ ያተረፉት የተስፋፊ መንግሥት ከበርቴ አዲስ ተፅዕኖና የርሱ አልባሌ ሸቀጣ ሸቀጦች መራገፊያ መሆን፤ ንዑሱ . . . ሌላው የህብረተሰብ ክፍል ያተረፈው በ“ኤክስፐርትነት በአማካሪነት” በወዘተ ስም የሚጎርፉት ተስፋፊዎችና የቅምጡ መንግስት ሎሌነት. . . መለዮ ለባሹ ያተረፈው የፀረ ብሄራዊ ነፃነት ኃይሎች ቅጥረኛና ታዛዥ መሆን፣ በባዕድ ወታደሮች እየተነዳና ከጀርባው እየተረሸነ በገዛ ወገኖቹና በኢትዮጵያ ጭቁን ብሄረሰቦች ላይ ጦርነት ማካሄድ ሆኖ እናገኘዋለን።

አብዮት ከተቀለበሰና አዲስ በዝባዥና ጨቋኝ መደብ በአንድ ሕዝብ ላይ ከተንሰራፉ፣ የአንድ ሃገር ብሄራዊ ኢኮኖሚ በባዕድ ኃይል ከተመዘበረ— ያውም የዚህ ባዕድ ኃይል ቅምጥ መንግሥት የፖለቲካ ሥልጣን ጨብጦ ከተደላደለ— ረሃብና ችግር ተወግዶ ሕዝባዊ ብልፅግናና እድገት ከቶም ሊተካ አይችልም። ማለትም፣ የዓለም ሕዝቦችን ለመመዝበር ገና አዲስ የሆነው የሩስያ ተስፋፊ መንግሥት ኢትዮጵያን በቁጥጥር ሥር አውሎ እንዳሻው እየረገጠ፣ ገና በልቶ ያልጠረቃ የሚመስለው አዲስ የተደላደለው የተስፋፊዎቿ ቅምጥ ወታደራዊ አምባገነን መንግሥት በኢትዮጵያ ሕዝብ ጫንቃ ላይ እየጨፈረ፣ ረሃብና ችግር ከኢትዮጵያ ተወግደው ሕዝቡ ካዘቀጠና ከደቀቀ ኑሮ ተላቆ ብልፅግናና እርምጃ ሊሰፍን ይችላል ማለት ዘበት ነው። መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዛሬ ከገባበት ረሃብና ችግር ለመላቀቅና ከሰጠመበት የኑሮ ረመጥ ለመውጣት እንደየካቲቱ ከዳር እስከ ዳር ተነስቶ እነዚህ ሁለት ቀንደኛ ጠላቶቹን ማስወገድ ይኖርበታል።

መኢሶን ለእያንዳንዱ ብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራም ዓላማዎች የተዋደቀውን ያህል፣ ዛሬም ሆነ ወደፊት ሁለቱ ቀንደኛ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠላቶችን— የሩስያ ተስፋፊዎችና ቅምጡ መንግሥታቸውን በግንባር ቀደምትነት እየተናነቀ ለሰፊው ሕዝብ ኑሮ ሻሻል ይታገላል

ባጭሩ፣ አንደኛ፣ መኢሶን ንም ይል ለማይናወጸው ብሄራዊ ነፃነት፣

       ሁለተኛ፣ መኢሶን ለሰላምና ከራሳቸው ከጭቁን ብሄረሰቦች ሌላ

                ማንም ለማያዝበት የተሟላ የብሄረሰቦች ዕኩልነት፣

       ሦስተኛ፣ መኢሶን ለፍትህ፣ ለዲሞክራሲና ለሰብዓዊ መብቶች

               ያለአንዳች ገደብ መከበር

      አራተኛ፣ መኢሶን ለሰፊው ሕዝብ ኑሮ መሻሻል፣ ለኢትዮጵያ

               ብልፅግናና እርምጃ አብዮታዊ ተጋድሎውን ይቀጥላል

5. የትግል አንድነት ጥሪ፦

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ነፃነትና ክብር ጉዳይ፣ የኢትዮጵያ ሰላምና የብሄረሰቦች እኩልነት ጉዳይ፣ የዲሞክራሲ የሰብአዊ መብትና የፍትህ ጉዳይ፣ የኢትዮጵያ ብልፅግናና እርምጃ ጉዳይ መቼም ሆነ ዛሬ የመኢሶን ብቻ አልነበሩም። አይደሉም። ሥልጣን ካሰከራቸው ጥቂት ከሃዲያን በስተቀር፣ ክብራቸውንና ክብራችንን ሸጠው የባዕድ ቅምጥ ሆነው ከሚያገለግሉ ያሃገር ደላሎች በስተቀር፣ የተስፋፊዎቹና የወታደራዊው ቢሮክራሲያዊ መንግሥት ጥቅም ተካፋይ ከሆኑ ታላላቅ የሚሊተሪ/ ሲቪል ቢሮክራቶችና ቴክኖክራቶች በስተቀር፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ በሙሉ የሚመለከቱ ናቸው። እንደውም፣ በተለይ ዛሬ፣ ሃገራቸውን የሚወዱና በተስፋፊዎችና በቅምጦቻቸው የሚብሸቀሸቁት ኢትዮጵያውያን ሁሉ የሚመለከቱ ጉዳዮቹ ሆነው ቀርበዋል።

አሰላለፉም ግልጽና አጭር ነው። ለብሄራዊ ባርነትና ውርደት የቆሙ ቅምጦችና ተስፋፊዎች ባንድ በኩል፣ ለብሄራዊ ነፃነት፣ ክብርና ሞገስ፣ ለኢትዮጵያ ሰላምና ብልፅግና የቆመ ሕዝብ በሌላ በኩል ነው።

የመኢሶን የትግል ጥሪም አጭር ነው።

በሩስያ ተስፋፊዎችና በቅምጦቻቸው የተቆጣ ኃይል ሁሉ እነዚህ ጥያቄዎቹን አንግቦ በአንድነት ጠጋራ ክንዱን ማንሳት አለበት። መኢሶን ለነዚህ [የማይነበብ- አዘጋጆች] ሃገር ወዳዶችና አርበኞች ጋር— አልፎም ከማንም አገራቸውን ከሚወዱ ኢትዮጵያዊያን ጋር ለመተባበር፣ ድርጅታዊ የትግል አንድነት ለመፍጠርና ለመታገል ዝግጁ ነው።

የመኢሶን ጥሪ የያሻማ ነው።

በዘረኛ የባዕድ መኮንኖች እየተመራ፣ እነሱ ባስታጠቁት መሣሪያ ኢትዮጵያን ወገኖቹን መጨረስ ያስቆጣው መለዮ ለባሹ፤ ነጋ ጠባ የሃገሪቱን ከብርና ጥቅም ገደል የሚከቱ የባህል፣ የኢኮኖሚና የንግድ ውሎችን እየታዘዘ መፈራረም ያንገበገበው ባለሥልጣን፤ በባዕዳን ትጥቅ የናጠጡ ከሃዲያን የጫኑበት ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ያንገፈገፈው ሰፊው ሕዝብ፤ የሃገሩ ብሄራዊ ነፃነት መደፈር ያስቆጣው አገር ወዳድ፤ ለመብቱና ለእኩልነቱ በተከራከረ የተስፋፊዎች ጥይት ማብረጃ የሆነው የጭቁን ብሄረሰብ ታጋይ፤ ተስፋፊዎች አቅፈው ደግፈው ባጠናከሩት ፀረ-አብዮት ድሎቹን ሁሉ የተቀማው ወዝአደር፤ ዘረፋቸው ሃገሪቱን አራቁቷት በሃገራችን ታሪክ ተሰምቶ ታይቶ ለማይታወቅ ረሃብና ቸነፈር የተጋለጠው ገበሬ፤ የተስፋፊዎች ጥይትና ቦምብ ስንዝር መሬት እየነሳው በሚሊዮን እየተቆጠረ ለስደት ለመከራና ለውርደት የተጋለጠው ኢትዮጵያዊ፣ ክብሯንና ሰውነቷን ለአዲስ መጤዎቹ ዘረኞች ማስተናገጃ እንድታቀርብ የተገደደችው ኢትዮጵያዊት፤ የከሃዲዎች ዝቅተኛ ስነ-ልቦና “ለተለየ” ዘመቻ ያጋለጠው ምሁር. . . .ወዘተ. ተባብረው እጃቸውን ማንሳት አለባቸው። አገራቸውን ከጥፋትና ከባሰ ውድቀት ማዳን አለባቸው። የሃገር ፍቅር ስሜታቸውን አስተጋግዘው በአንድነት መታገል አለባቸው። አለያም የባሰ ውድቀት፣ የባሰ ድቀት፣ የባሰ ውርደት ነው።

ጎበዝ!! ደግሞም አንድ መገንዘብ ያለብን ሃቅ አለ!

ዛሬ የሃገራችን ብሄራዊ ነፃነት ብቻ ሳይሆን፣ ህልውናዋ ራሱ ከጥያቄ ውስጥ የገባበት ወቅት ነው። የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝምና የሩስያ ተስፋፊዎች እንደ ካምቦዲያና እንደ አፍጋኒስታን የአዳዲስ ጦር መሣሪያዎች መፈተሻና መፋለሚያ እያደረጉን ነው። የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም “ኢትዮጵያን ለማስመለስ”፣ በአካባቢው የነበረውን የበላይነት መልሶ ለማግኘት ከፍተኛ ዝግጅት እያደረገ ነው። ለዚህም በሱማሊያ፣ በኬኒያ፣ በኦማንና በግብፅ የሚያደርገው የጦር ክምችት በቂ ማስረጃ ነው። ተስፋፊው የሩስያ መንግሥት ደግሞ፣ “የመከላከያ” ዝግጅቱን በየመንና በኢትዮጵያ እያጠናከረ ነው። በቀይ ባህር የኢትዮጵያ ደሴቶችና ወደቦች ላይ የባህር ጦር ሰፈሩን መሥርቷል። በመሃል ሃገርም፣ በሁርሶና በቦተርጦሌ /ጊቤ ወንዝ አካባቢ/ የጦር ማከማቻ ሠፈር እንዲሠራ ከሃዲዎች እንደፈቀዱለትና አገር ከልለው እንደሰጡት የታወቀ ነው። በዚህ ሳቢያ፣ ሃገራችን የሁለት ሃያላን መንግሥታት የጦር አውድማ የምትሆንበት ጊዜ ሩቅ አይደለም። ያኔ፣ ስለ ብሄራዊ ነፃነት ቀርቶ ስለህልውናችንም መናገር አንችልም።

እንግዲህ ሁኔታው እንደዚህ አሳሳቢና አሳፋሪም ነው። በሌላው በኩል፣ እኛ የሃገር ፍቅር ስሜት የሚያንገበግበን ኃይሎች፣ ጊዜው በሚጠይቀው መልክ ተባብረንና ተያይዘን ገና አልተነሳንም። ይህን እስካላደረግን ድረስ ደግሞ፣ ወደ ውስጥ ዲሞክራሲያዊ ህልውናችን ወደ ውጭ ብሄራዊ ነፃነታችን ተከብሮ ልንኖርባት የምታስችለንን ኢትዮጵያ ለመፍጠር አንችልም።

መኢሶን ያለመሰልቸት ለኢትዮጵያ ዲሞክራቶች፣ ሃገር ወዳዶችና የብሄረሰብ እንቅስቃሴዎች ሁሉ የአንድነት ግንባር ጥሪ አድርጓል። በዚህ ዕትሙም የሚያድሰው የትግል አንድነት ጥሪ የዚሁ አካል ነው። የዚህ ግንባር ጥያቄ በየዕለቱ ይበልጥ አንገብጋቢ እየሆነ እንደመጣ ያለፉት ወራት ሁኔታ በግልጽ ያሳየናል። መኢሶን አሁንም ደግሞ ደጋግሞ የሚለው፤ ለብሄራዊ ነፃነት፣ ለዲሞክራሲና ለብሄረሰቦች ራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ኃይላችንን እናስተባብር ነው። ለዛሬው ሁኔታ መፍትሄው ሃቀኛ ተራማጆች፣ ሃገር ወዳዶች፣ ዲሞክራቶችና የጭቁን ብሄረሰብ ታጋዮች በአንድነት የሚመሰርቱት ሰፊ ሕዝባዊ ግንባር ብቻ ነው።

ለብሄራዊ ነፃነት!
ለዲሞክራሲ ለፍትህና ለሰብዓዊ መብት!
ለብሄረሰቦች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት!
ሰፊ ሕዝባዊ ግንባር እንመሥርት!
Scroll to Top