የሰፊው ሕዝብ ድምፅ
ቁጥር 53፣ መጋቢት 15፣ 1969
የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ
በዚህ እትም መኢሶን በቅርቡ የሶሺያሊስት አገሮች ድጋፍ እየጨመረ መምጣቱን፣ በአንጻሩም በአለም አቀፍ ደረጃ በተለይም የአሜሪካን ኢምፔሪያዝም በአካባቢው ያሉ አድሃሪ አገሮችን ለማሰባሰብ የሚያደርገው ጥረት እንደበረታ ይጠቁማል። ለሰላምና ለእድገት የሚታገሉ አገሮች የሚያደርጉት አለም አቀፋዊ ትብብር መጠናከርን አስፈላጊነት ጠቅሶ፣ መኢሶንም በበኩሉ ተራማጅ አገሮች የኢትዮጵያን አብዮት እንዲደግፉ ያደረገውን መጠነኛ አስተዋጽኦ ያስታውሳል።ይህ ዓለም አቀፋዊ ትብብር አስፈላጊና ጠቃሚ ቢሆንም፣ አብዮታዊያን ከምንም በላይ በአንደኛ ደረጃ በኢትዮጵያ ሕዝብና በኢትዮጵያ ምድር ሃብት መተማመን እንዳለባቸው አጥብቆ ያስገነዝባል።
ከሦስት ወራት ወዲህ ሶሻሊስት አገሮች የኢትዮጵያን አብዮት በየዕለቱ ይበልጥ እየደገፉት መጥተዋል። በተለይ የሶቪየት ህብረት የወሬ ወኪል የሆነው ኤ.ፒ.ኤን. በጥር ወር መጀመሪያ ላይ ኢህአፖንና ሌሎችንም የኢትዮጵያን አብዮት የሚፃረሩትን ኃይሎች አውግዞ ከፃፈ በኋላ፣ የምስራቅ አውሮፓ አገሮችና የኪዩባ የኢኮኖሚ፣ የባህልና ወታደራዊ መልእክተኞች እየተፈራረቁ አገራችንን ጎብኝተዋል። ከጥር አጋማሽ ወዲህ ብቻ ሁለት ከፍተኛ የዩጎዝላቪያ መንግሥት መልእክተኞች፣ አንድ የቡልጋሪያ፣ ሦስት የምስራቅ ጀርመን፣ አንድ የቼኮዝሌቫኪያ፣ ፊደል ካስትሮን ሳንጨምር ሁለት የኪዩባ የመልክተኞች ቡድኖች ሀገራችንን ጎብኝተዋል። እንደዚሁ የሦስት አገሮች የባህል ተጫዋቾች መጥተዋል። አሁን በመጨረሻ የፊደል ካስትሮ መምጣት የሚያጸድቀው አንድ ትልቅ ነገር እነዚህ ሁሉ አገሮች የኢትዮጵያ አብዮት ለመደገፍ ከእንግዲህ ቆርጠው የተነሱ መሆናቸውን ነው። እንግዲህ ጥያቄው የኢትዮጵያ አብዮት ከተጀመረ ከሦስት አመታት በኋላና እንደሚታወቀው በወታደራዊው መንግሥት በኩል የሶሻሊስት አገሮችን ድጋፍ ለማግኘት ብዙ ጥረት ተደርጎ ሳይሳካ ከቆየ በኋላ፣ አሁን እነዚህ አገሮች ለኢትዮጵያ ይህን ያህል እንክብካቤ ለማሳየት የተነሱት በምን ምክንያት ነው የሚለው ነው። ለዚህ በርከት ያሉ ምክንያቶችን ለመስጠት ይቻላል።
አንደኛውና ዋናው ምክንያት በቅርብ ምስራቅ እና ኢትዮጵያ በምትገኝበት በዚህ የአፍሪካ ክፍል የሚታየው የኃይሎች አሰላለፍ መለወጥ ነው። የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም ቀደም ሲል ሶቪየቶችን ከግብፅ ካስወጣ በኋላ፣ አሁን በካርተር የሚመራው አዲሱ የአሜሪካ አድሚንስትሬሽን በዚህ አካባቢ የጥቃት እርምጃዎችን እየወሰደ ነው። ግብጽ፣ ሱዳንና ሳውዲ-አረቢያ የጋራ የመከላከያ ውል እንዲፈራረሙ አድርጓል። ኒሜሪ አሜሪካን ከጎበኘ በኋላ ፀረኮሚኒስት ድንፋታውን ለማባባስ የበቃው ያንኪዎች ስላበረታቱት ነው። /በተለይ ኢትዮጵያን በሚመለከተው በኩል፣ ፀረ አብዮት ፕሮፖጋንዳ ለኢ.ዲ.ዮ እና ለኢ.ህ.አ.ፓ የሚያካሂድ የሬዲዮ ፕሮግራም ሲ.አይ.ኤ በኦምዱርማን እንደከፈተ ይታወሳል።/ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ሶሪያን፣ ግብጽና ሱዳንን በማቀራረብ፣ በሶሪያም ሶቬቶችን ለማስወጣት ትልቅ ጥረት እያደረገ ነው። እንደዚሁም በሳውዲ-አረቢያ አማካይነት በዲሞክራቲክ የመንና በሶማሊያ ላይ ትልቅ ተጽእኖን ያደርጋል፣ ማለትም ለነዚህ አገሮች በብዙ መቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ፔትሮ-ዶላር በርዳታ በመስጠት ሶቪየቶችን እንዲያስወጡ ለማድረግ በመሞከር ላይ ይገኛል። እራቅ ብላ ወደ ምስራቅ የምትገኘው ኢራን በዚህ ክፍለዓለም የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም ፖሊስ መሆኗን ሲታወቅ የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም ቀይ ባህርንና የዘይት አገሮች ሙሉ በሙሉ ከቁጥጥር ስር እንዳያደረግ በአሁኑ ወቅት እንቅፋት ልትሆነው የምትችለው ኢትዮጵያ ብቻ መሆንዋ በግልጽ ይታያል። ስለሆነም፣ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ መፋለሚያ ቦታ ሆናለች ማለት ነው።
ሁለተኛ፣ ባንድ በኩል የኢህአፓ በፖለቲካ ትግል መክሰርና የነፍሰገዳዮች ቡድን ሆኖ መጋለጥ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የኢዲዩና የኤርትራ ተገንጣዮች፣ እንደዚሁም የአረብ አድሃሪ አገሮች እጅና ጓንት ሆኖ መስራት የብዙ የምስራቅ አገሮችን አስተሳሰብ ወደ ኢትዮጵያ ለመሳብ ትችሏል።
ሶስተኛ፣ በተራማጅ አገሮችና በኢትዮጵያ መካከል መቀራረብ እንዲኖር፣ ተራማጅ አገሮችና ድርጅቶች የኢትዮጵያን አብዮት ባህርይ እንዲረዱና ለአብዮታችን ሃቀኛ ድጋፍ እንዲያበረከቱ መኢሶን በበኩሉ ሰፋ ያለ ቅስቀሳ አካሂዷል። ይህ ቅስቀሳ ዛሬ የኢትዮጵያ አብዮት በማግኘት ላይ ላለው አለማቀፋዊ ድጋፍ መጠነኛ አስተዋጾ አድርጓል ለማለት ይቻላል።
እላይ እንደተባለው ሁሉ፣ ከነዚህም ምክንያቶች ዋነኛው የመጀመሪያው ነው። ወጣም ወረደም ግን የነዚህ ሶሻሊስት አገሮችና እንደዚሁም የሌሎቹ፣ ማለትም የነቻይና፣ የነኮርያ፣ የነቬየትናም፣ ከዚያም አልፎ ደግሞ የዓለም ተራማጅና ዲሞክራሲያዊ አገሮች ድርጅቶችና ግለሰቦች ሁሉ የፖለቲካና ማቴሪያላዊም ድጋፍ ለኢትዮጵያ አብዮት እንደሚያስፈልገው በፍጹም የማይጠረጠር ነገር ነው። የኢትዮጵያ አብዮት የዓለም ሕዝቦች ፀረኢምፔሪያሊስት ትግል አንድ አካል እንደመሆኑ መጠን፣ ይህንን አብዮት በተቻለ መንገድ ሁሉ ማገዝ የዓለም ፀረኢምፔሪያሊስት ኃይሎች ሁሉ አቀፋዊ ግዴታ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብም በበኩሉ ከኢምፔሪያሊዝም ጋር በሚያካሂደው ትግል ለአለም ሕዝቦች የነፃነት ትግል አስተዋጽዖን እንደሚያደርግ ግልጽ ነው።
ለሰላም፣ ለእድገትና ለሶሻሊዝም የሚታገሉ ልዩ ልዩ አገሮች፣ ድርጅቶችና ሕዝቦች የሚያደርጉትን የእርስ በርስ መደጋገፍ ከዓለምአቀፋዊነት አንፃር ልንገነዘበው ይገባል። ማንኛውም አገር በአለም አቀፋዊነት መርህ የተመራ ሌላውን ለነፃነት እና ለወደፊት እርምጃ የሚታገለውን አገር ሲረዳ ዞሮ ዞሮ ራሱን እንደረዳ ይቆጠራል። የቬትናም ሕዝብ ለሰላሳ ዓመታት ሙሉ ደሙን አፍስሶና አጥንቱን ከስክሶ ኢምፔሪያሊዝምን በማሸነፉ በዚህ ትግል ለረዱት ሀገሮቹ ሁሉና ላልረዱትም ጭምር ትልቅ እርዳታ አድርጓል፣ የነርሱም ነፃነት እንዳይደፈር ኢምፔራሊዝምን አዳክሞታልና። በሌላ አነጋገር፣ የቪየትናም ሕዝብ በተጋድሎ የሶቪዬት ሕብረትን የቻይናንና የሌሎችም ሶሻሊስት አገሮች በጠቅላላውም የአለምን ሕዝቦች ትግል ረድቷል ማለት ነው።
ኢትዮጵያ የምታደርገው ፀረ ኢምፔሪያሊስት ትግል፣ ምንም እንኳን ጀግናው የቬየትናም ሕዝብ ካደረገው ትግል ጋር ሊወዳደር የሚችል ባይሆንም፣ የኢትዮጵያን ሕዝቦች ጥቅም ብቻ የሚጠብቅ ትግል ሳይሆን የሶሻሊስት አገሮችን ለጠቅላላውም የሰው ዘርን ጥቅም ከሚጠብቁ ከሌሎች ተጋድሎዎች መሀከል ነው። ይህንን እውነት በሚገባ መረዳቱ እርዳታ ተቀባዮችን ከተመፅዋችነት ስሜት ጠብቆ የእርዳታንም ትርጉም ትክክለኛ ቦታ ያሳስባል የሚል እምነት አለን። በዓለምአቀፋዊነት መርሆ መሰረት የሚገኝ እርዳታ አስፈላጊ ይሁን እንጂ ለኢትዮጵያም ሆነ ለማንኛውም አገር ዋናው ቁም ነገር በራስ መተማመን ነው። እርዳታ ድጋፍ እንጂ መሰረት አይሆንም። ለእድገት፣ ለሶሻሊዝም፣… ዋናው መሰረትና ዋስትና በራስ ኃይል መተማመንና ማንኛውንም ጉዳይ ከዚሁ አንጻር መመልከቱ ነው። ይህንን መረዳቱ በአንድ በኩል የአገሪቷን ክብርና ነፃነት ለጥቂት ጊዜያዊ ጥቅሞች ከመሸጥ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የሌሎችም ሀገሮች እርዳታ የኢትዮጵያ አብዮት ወሳኝ ጥያቄ አድርጎ ከመውሰድ ይጠብቀናል።
ለማጠቃለል ያህል፣ የሶሻሊስት አገሮችና የሌሎችም የአለም ተራማጅ ኃይሎች ድጋፍ መገኘት ለኢትዮጵያ በጣም አስፈላጊና ሲገኝም ደግሞ በጣም አስደሳች ነገር ነው። ይሁንና፣ በማንኛውም ጊዜ ሁኔታ ቢሆን፣ ምንም ያህል ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና የማህበራዊ ኑሮ ችግሮች ቢኖሩም፣ የፈለገውን ያህል አብዮታዊ በአድሃርያን ጥይት ቢወድቅ፣ በአጭሩ፣ ማንኛውንም መስዋዕትነት ቢጠይቅምና ትግሉ የፈለገውን ጊዜ ቢፈጅም፣ አብዮታዊያን ከሁሉም በላይ መተማመን ያለባቸው በሃያ ስምንቱ ሚሊዮን የኢትዮጵያ ሕዝብና በኢትዮጵያ ምድር ሃብት ላይ ነው። ከዚህ አይነቱ እምነት መዛነፍ የመጣ እለትና ተስፋችንን በውጭ ኃይሎች ላይ መጣል ያመጣን እለት የተኮላሸ አብዮትና “በነፃነቷ ለዘላለም ትኑር!” የተባለችው ሀገራችን ተመልሳ ከባርነት ስር የምትወድቅበት ቀን እንዲመጣ ማገዛችን እንደሆነ መታወቅ አለበት።
አለምአቀፋዊነት ለዘላለም ይኑር!
በሰፊው ሕዝብ ላይ ሙሉ እምነት ይኑረን!
ሃቀኛ የተራማጆች ህብረትን እንገንባ!
ለወዛደሩ ፓርቲና ለሕዝባዊ ግንባር መፈጠር እንታገል!
ነጻነት ወይም ሞት!
ሰፊው ሕዝብ ያሸንፋል!!!
የሰሞኑ አንዳንድ ሁኔታዎች
- በአብዮትና በቢሮክራሲ መካከል ስለ መምረጥ
የሕዝብ ድርጅት ጉዳይ ጊዜያዊ ጽ/ቤት የማቋቋም ጉዳይ በደርጉ ውስጥ ኃይለኛ ትግልን አስከትሎ እንደነበረና በደርጉ ውስጥ ያሉት ተራማጆች ከዚህ ትግል አሸናፊ ሆነው በመውጣታቸው ጽ/ቤቱን ሊቋቋም እንደቻለ ይታወቃል። ጽ/ቤቱ ከተቋቋመም በኋላ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራም በይፋ ለማውጣት ትልቅ ትግል እንደነበረና ከዚህም ላይ የደርጉ አድሃሪዎች — እነ ሲሳይ ሃብቴ — ተሸንፈው ፕሮግራሙ ሊወጣ እንደቻለ ይታወቃል። ይሁንና በደርጉ ውስጥ በጽ/ቤቱ ጥያቄ ላይ የነበረው ትግል አላቆመም። እነ ዓለማየው ኃይሌ ከሰኔ 68 ጀምሮ በጽ/ቤቱ ላይ እና በተለይም ደግሞ በድርጅታችን ላይ ኃይለኛ ዘመቻን በይፋ ሲያካሄዱ እንደ ቆዩ፣ ጽ/ቤቱን የመኢሶን ጽ/ቤት ነው በማለት እንዲፈርስ መጠየቃቸውና በመጨረሻው ይህንኑ የማፍረስ አላማቸውን በጉልበት ከሥራ ላይ ለማዋል እንደ ሞከሩ ይታወቃል።
አሁን በጥር 26 በደርጉ ውስጥ የነበሩት የኢህአፓና የኢምፔሪያሊዝም ወኪሎች ከተደመሰሱ በኋላ፣ በጽ/ቤቱና በእርሱም ሳቢያ በመሲሶን ላይ የሚደረገው ዘመቻ በተፋፋመ ሁኔታ ቀጥሏል። የዚህ ዘመቻ ዋነኛ ኃላፊዎች ከየቦታው የተቀመጡት አድሃሪ ቢሮክራቶች ናቸው። በሲዳሞ፣ በከፋ፣ በጎጃምና በሌሎችም ክፍላተሃገር ቢሮክራሲው ጽ/ቤቱን በሚመለከተው በኩል “ከተከላካይነት ወደ አጥቂነት” ተሸጋግሮ ካድሬዎችን እስከማስገደልና እስከማሳሰር ደርሷል።
ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በአብዮታዊና በቢሮክራሲያዊ አሰራር መካከል በአብዮታዊያንና በቢሮክራቶች መካከል በተለያዩ ጊዜያትና በተለያዩ ጥያቄዎች ላይ ከሁለቱ አንዱን የመምረጥ ግዴታ እየቀረበለት እንደ ሁኔታውን መርጧል። አብዮታዊ አሰራርንና አብዮታዊያንን በመረጠ ቁጥር የኢትዮጵያውያን ሕዝብ ትግል ወደፊት አራምዷል። ቢሮክራሲያዊ አሰራርንና ቢሮክራቶችን በመረጠ ቁጥር ደግሞ ፀረሕዝብና ፀረአብዮት እርምጃዎችን ወስዷል። አሁን እንግዲህ ከጥር 26 በኋላ ይህ መንግሥት እንደ ገና ከዚህ ምርጫ ጋር ተፋጧል። በደርጉ ውስጥ የነበሩት አድሃሪዎች ከተደመሰሱ በኋላ ፖሊሲያቸው ግን ይቀጥል እንደሁ[እንደሆን]፣ በመደቦች ትግል ፈንታ የመደቦች ዕርቅ እንደገና በመፈክርነት ይቀርብ እንደሁ[እንደሆን] እንግዲህ በሚመጡት ጥቂት ቀናትና ሳምንታት ውስጥ ለሰፊው ሕዝብ ግልፅ እንደሚሆን እናምናለን።
የሕዝብ ድርጅት ጉዳይ ጽ/ቤትን ካድሬዎች በሚመለከተው በኩል፣ በእርግጥ እነዚህ ጓዶች በአንዳንድ ቦታዎች ስህተቶችን እንዳደረጉና እንደሚያደርጉም የማይታበል ሀቅ ነው። የጽ/ቤቱ ጓዶችም ሆኑ ሌሎች አብዮታዊያን በሚፈጽሟቸው ስህተቶች ላይ ሊኖር የሚችለው አስተያየት ከሁለት አንድ ነው፡— ወይ ከነኢ.ድ.ህ- ኢ.ህ.አ.ፓ- ኢምፔሪያሊዝም ጋር የገቢር ግንባር በመፍጠር በጽ/ቤቱና በካድሬዎቹ ላይ የጥላቻና የስም ማጥፋት ዘመቻን ማካሄድና እንደዚሁም የጭቆና እርምጃዎችን መውሰድ ነው፤ ወይም በአብዮታዊ አሰራር ዘዴ ስህተቶች እንዲታረሙ ማድረግ ነው። ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግና በየገጠሩ የተሰማሩት አባሎቹ ይህኛውን መንገድ እንደሚመርጡ ተስፋ እናደርጋለን። የጽ/ቤቱ ጓዶች በበኩላቸው የቀረቡባቸውን ክሶችና ያደረጓቸውንም ስህተቶች ለማጥናት፣ ለመተራረምና የአሰራር ዘዴያቸውን ለማስተካከል የአስር ቀናት ሴሚናር እንዳካሄዱ ይታወቃል። በዚህ ሴሚናር ላይ በትክክል የቀረቡባቸውን ሂሶች ተቀብለው ስህተቶቻቸውን እንዲያርሙ ዋና ምኞቻችን ነው።
- ቀይ ሽብር
ከረጅም ጊዜ ጀምሮ በሰፊው ሕዝብ ሲጠየቅ የነበረውን ነጭ ሽብር አብዮታዊያን ቀይ ሽብር የመተካት ጥያቄ ባሁኑ ወቅት ከሥራ ላይ እየዋለ ነው። በየክፍለ ሃገሩና በተለይም በአዲስ አበባ የኢትዮጵያ ወዛደሮች፣ አብዮታዊ ወጣቶችና አብዮታዊ መለዮ ለባሾች በእርግጥ አብዮቱን ከተከላካይነት ወደአጥቂነት በማሸጋገር ላይ ይገኛሉ። በፀረአብዮቱ ሰፈር ቀይ ሽብር ተፈጥሯል።
የተፈጠረው ቀይ ሽብር ሁለት ያስተሳሰብ መስመሮችን ለይቷል። አንደኛው መስመር የኢምፔሪያሊዝም እና የአድሃሪዎች ሁሉ ሲሆን፣ እርሱም ቀይሽብርን በጠቅላላ ግርግር፣ በከንቱ ግድያ፣ በሥርዓትና በሕይወት ዋስትና መጥፋት፣ በመንግሥት አለመኖር ይተረጉመዋል። ለስድስት ወራት ሙሉ በአብዮቱ ሰፈር ነጭ ሽብር ሲሰፍን አድሃሪዎች ሥርዓት ጠፋ፣ መንግሥት ጠፋ አላሉም ነበር። እያንዳንዱ ጓድ፣ እያንዳንዱ ሃቀኛ አገርወዳድ በአድሃርያን ጥይት በወደቀ ቁጥር በንጹሃን ደም አንጀታቸው እየራሰ “እሰይ፣ እሰይ” ይሉ ነበር። የሕግ፣ የስርዓት፣ የመንግሥት መጥፋት የሚታያቸው ዛሬ ነው! ሁለተኛው መስመር የሰፊው ሕዝብና የአብዮቱ ሰፈር መስመር ሲሆን፣ እርሱም በተፈጠረው ቀይ ሽብር የሚያየው የወደቁትን አብዮታዊያን ደም መበቀሉን አብዮቱን ከቅልበሳ ማዳኑንና የወደፊት እርምጃን ነው።
ይሁንናም በነዚህ በሁለት እንደሰማይና ምድር በተራራቁ አስተሳሰቦች መካከል የሚዋልሉ፣ ገና የንኡስ ከበርቴ ሸክማቸውን ሙሉ በሙሉ ያላራገፉ አብዮታዊያንም አሉ። የሰፊው ሕዝብ ነፃ ድርጊቶች፣ የሰፊው ሕዝብ የመፍጠር ችሎታ በግብር ቢታይ ንኡስ ከበርቴውን ያስበረግገዋል። ማርክስ እንዳለው ሁሉ፣ ሰፊው ሕዝብ ከንዑስ ከበርቴው በስተጀርባ በመሰለፍ ፈንታ ከፊቱ የቀደመ እለት የንኡስ ከበርቴው አብዮታዊነት ወዲያውኑ ፀሐይ እንደመታው በረዶ መቅለጥ ይጀመራል። ባንዳንድ አብዮታዊያን ዘንድ ይህ መታየት ጀምሯል። እነዚህ ጓዶች የሚጠብቁት ስህተት የማይደረግበትን፣ ያለመሰናክል በሃዲድ ላይ የሚሽከረከርን፣ ሙሉ በሙሉ በአብዮታዊያን ቁጥጥር ስር የሆነን “ንጹህ አብዮት” ነው። ነገር ግን የዚህ አይነት “ንጹህ አብዮት” የሚጠብቅ አብዮታዊ ሳያየው ይሞታል ብሏል ሌኒን። ስለሆነም፣ የኢትዮጵያ አብዮታዊያን የሰፊውን ሕዝብ ነፃ ድርጊቶችና የመፍጠር ችሎታውን ሙሉ በሙሉ በመደገፍ እነዚህ ድርጊቶችና ችሎታዎች በአብዮቱ ሰፈር ውስጥ እንዲጣመሩ እየታገሉ፣ በአብዮታዊ ሥራ ላይ የሚፈጸሙ አንዳንድ ስህተቶችን እያረሙና ከእነዚህም ስህተቶች ትምህርትን እየቀሰሙ፣ በዚያውም የፀረአብዮት ሰፈር ሰፊውን ሕዝብ በማንቋሸሽ የሚካሄደውን ዘመቻ ያጋልጡታል።
- የሹመት ጉዳይ
ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት በቅርቡ የሰጠው ሹመት ሰፊውን ሕዝብ ሳያደናግረው አልቀረም። ነገሩ ያልተጠበቀ አይነት “ኮክቴል” ነው። ተራማጆችም፣ አድሃሪዎችም፣ ከሁለቱ ወገኖች በየትኛው ውስጥ እንደሚገኙ የማይታወቁ ሰዎችም ተሾመዋል። በሌላ በኩል ደግሞ ይሻራሉ ተብሎ ይጠበቁ የነበሩት አሁንም በስልጣን ቦታ ላይ ይገኛሉ። ይህቺ የኢትዮጵያ አብዮት በጣም ፈጣን ስለሆነች፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ፣ ምናልባት በርከት ያሉ ተሽዋሚዎች ከአውቶቡሱ እንዲወርዱ ሳታስገድዳቸዉ አትቀርም የሚል እምነት አለን!!
ሹመትን በሚመለከተው በኩል፣ 1ኛ/ ወጣት ተራማጆችን፣ 2ኛ/ ከወዛደር ወገን የሆኑትን በኃላፊነት ቦታዎች ላይ ለማስቀመጥ /ለሞሾም/ መድፈር ያስፈልጋል። “አዋቂዎችን”፣ ተራማጅ እስካልሆኑ ድረስ፣ በእውቀታቸው እንዲያገለግሉ እንጂ፣ አመራር ውስጥ እንዲገቡ ማድረግ አያስፈልግም።
- የቤጌምድር ሁኔታ
እነአለማየሁ ኃይሌ ነግሰው በነበረበት ሰሞን በአዲስ አበባ ከተማ ይወራ የነበረው ወሬ ኢ.ዲ.ዩ በቀናት ውስጥ ጎንደርን እንደሚይዝና መንግሥትን እንደሚያውጅ፣ ስለሆነም ከኢ.ህ.አ.ፓ ጋር እርቅን ማድረግ እንደሚያስፈልግ ነበር። ኢህአፓም በበኩሏ በየትምህርት ቤቱ ኢዲዩን ለመቋቋምና ለማሸነፍ የሚችለው ጊዜያዊ የወታደራዊ መንግሥት ሳይሆን ኢህአፓ ራሷ መሆኗን በሰፊው አስወርታ ነበር። የአድሃሪያንን ጊዜያዊ መጠናከር ያስከተለውና ለኢዲዩም አንዳንድ ተጨባጭ ድሎችን [የማይነበብ]፣የካድሬዎችና የአገርወዳድ መለዮ ለባሾች መገደልና መማረክ፣ እነሰቲትን የመሳሰሉ ስፍራዎች መያዝ ወዘተ…- ያስገኘለት በተለይ በዚያ ክፍለሃገር በመ/ቤቶችና በመለዩ ለባሹም ውስጥ አድሃሪ ቢሮክራቶች መሰግሰግ መሆኑን የአይን ምስክሮች ያስረዳሉ።
ይህን የአድሃሪ ቢሮክራቶች አሻጥር የበጌምድር ሰፊ ሕዝብ እየተቋቋመ ጠላቱን መልሶ በማጥቃትና ድሎችን በመቀዳጀት ላይ ነው። የበጌምድር ሕዝብ በቅርቡ ባገኛቸው አብዮታዊ ውጤቶች ኢዲዩንም ኢሕአፓንም በገቢር አጋልጧል። ትክክለኛው ቀስቀሳና ትክክለኛው አመራር እንደዚሁም አስፈላጊው፣ ማቴርያላዊ ድጋፍ ከተሰጠው የበጌምድር ሕዝብ በራሱ ኃይል ኢዲዩን ለመቋቋም እንደሚችል በግብር አረጋግጧል። እዚያ የተመደቡት የደርግ አባሎችና ተራማጆች በሕዝቡ ላይ በመተማመን ያስገኟቸውን ድሎች ወደሌሎች ከፍተኛ ድሎች እንዲለውጧቸው እናበረታታለን።