የሰፊው ሕዝብ ድምፅ
ቁጥር 25፣ ሚያዝያ 17፣ 1967
የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ
መኢሶን በዚህ የሰፊው ሕዝብ ድምፅ እትሙ፣ በምሥራቅ እስያ የካምቦዲያ ነጻ አውጭ ታጋዮች ከአሜሪካን ኢምፔሪያሊዚምና ከአሻንጉሊት መንግሥታቸው ከሎንሎል እጅ ዋና ከተማቸውን ኖምፔንን ሙሉ በሙሉ ነጻ መውጣታቸውን ለሦስተኛው ዓለም ሕዝቦች የምሥራች ድል እንደሆነ አብስሯል። ከዚህም በተጨማሪ፣ የቪየትናም ነጻነት ታጋዮችም የሀገራቸውን ድቡብ ክፍል ከአሜሪካን ቅኝ ግዛትነት እያስለቀቁና ቀስ በቀስም አገራቸውን ሙሉ በሙሉ ነጻ ለማውጣት እንደተቃረቡ በእርግጠኝነት ይናገራል። መኢሶን በዚህ እትሙ፣ኢምፔሪያሊዝምን ለማሸነፍ፣ የተደራጀ ሕዝብ ፍቱን መድሃኒት መሆኑን ከካምቦዲያና ቬትናም ሕዝቦች መማር እንደሚያስፈልግ ያስገነዝባል።
በካምቦዲያ ነፃ አውጭ ግንባር የሚመራው ሰፊው ተራማጅ የካምቦዲያ ሕዝብ በሚያዝያ 9 ቀን ዋናውን ከተማ ኖምፔንን አስለቀቀ፣ ካምቦዲያ አሁን ሙሉ በሙሉ ነፃ ወጥታለች። የመጨረሻዎቹ የአሜሪካ ኤምፔሪያሊዝም አሻንጉሊቶች የእጅ መስጠት ድርድራቸውን አርበኞቹ ውድቅ ስለአደረጉት [እንደአደረጉት – የአዘጋጆች እርማት] ህይወታቸውን ለማዳን ብቻ ሹልክ ሹልክ እያሉ ከአገር ወጥተዋል። በቪየትናም ደቡባዊ ክፍል /ደቡብ ቪየትናም/ የነፃ አውጭ ሃይሎች ከምን ጊዜውም ይበልጥ ሃይላቸውን በማጠንከር ከሰላሳ ዓመታት በላይ የተዋጉለትና ደማቸውን ያፈሰሱለትን ነፃነት በሙሉ ወደማግኘቱ የተቃረቡ መሆናቸውን የአሜሪካ ኤምፔሪያሊዝም እንኳን ለማመን ተገድዷል። ነፃ አውጭ አርበኞቹ በቅርቡ ሳይጐንን በመያዝ መላውን የቪየትናም አገር ነፃ እንደሚያወጡ ዛሬ ምንም ጥርጥር የለውም። በካምቦዲያ መሪ አሻንጉሊት የነበረው ሎንኖል በነፃ አውጭዎቹ አርበኞች ተወጥሮ በመያዙና ቀኖቹ መቃረባቸውን በማያጠራጥር አኳኋን ስለተረዳ አሞኛል፡ ኢንዶኒዥያ ‘እረፍት’ እወስዳለሁ፡ ‘ለህክምና’ ወደ አሜሪካ እሄዳለሁ፡ወዘተ. ብሎ በመቀባጠር ከካምቦዲያ ከፈረጠጠ ሳምንታት ሆነዋል። በደቡብ ቪየትናማውያን ላይ ተጭኖ የነበረውም ቲዩ የሎንኖል ጽዋ እንደማይቀርለት በመገንዘብ ከስልጣን ወርዷል።
የእነዚህ አሻንጉሊቶች ፈጣሪና ጌታ የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም፡ የደረሰበትን ታላቅ ውርደትና መሸነፍ ለመሸፈን ልኡል ሲሃኑክን ይምጡና የመንግሥቱን ስልጣን ይረከቡ፣ ካምቦዲያኖች ጉዳያችሁን ‘ራሳችሁ’ ፈጽሙ፣ በመግባባትና በሰላም ‘አንድነታችሁንና ነፃነታችሁን’ ጠብቁ ወዘተ. በማለትና በቪየትናምም የእርቅ ድርድር እናድርግ እያለ ለማወናበድ ከሞከረ በኋላ፡ ነገሩ ‘ጅብ ከማያውቁት አገር ሄዶ ቁርበት አንጥፉልኝ አለ’ እንደሚባለው ሆነና ጓዙን ጠቅልሎ መውጣት ጀመረ። የካምቦዲያና የቪየትናም ተራማጅ አርበኞችና ሰፊው ሕዝብ አፈር አስግጠውና በጦር ሜዳ ላይ አንበርክከው፡ለዘለአለም የማይፋቅ ውርደትና ሃፍረት አትመውበት ድል በመምታት ቅስሙን ሰብረው ከአገራቸው አስወጡት።
ባሁኑ ጊዜ የኢምፔሪያሊስት አገሮች ቀንደኛ የሆነው አሜሪካ በኢንዶቻይና ሰፊ ሕዝቦች “የማርያም ጠላት” ተብሎ ራሱን እንደእባብ በመወገርና በመቀጥቀጥ ላይ ነው። ገና ታዳጊና ደካማ ሕዝቦች በአለም ተወዳዳሪ የሌለውን የኢምፔሪያሊስት ኃይል በጦር ሜዳ በማንበርከክና ድል በመምታት ላይ ናቸው። ለመሆኑ የአለም ሕዝቦችን ነፃነት ለመግፈፍና ለመበዝበዝ ቆርጦ የተነሳውንና በዘመናዊ መሳሪያ ከራስ ጠጉሩ እስከእግር ጥፍር የታጠቀውን የኢምፔሪያሊስት ኃይል ማሸነፍ የቻሉት እንዴት ነው?
ይህ ድል የተገኘው ቆራጥነት በተመላበት የሕዝብ ትግል እንጂ በመሳሪያ አይነትና ብዛት አይደለም። በዚህም የቪየትናምና የካምቦዲያ ሕዝቦች ለመላው አለም ትልቅ ትምህርት ሰጥተዋል። በጦርነት ለማሸነፍ ከዘመናዊ መሳሪያ ጋጋታ ይልቅ ትክክለኛ አላማን ይዞ የሚዋጋ ሕዝብ ይበልጥ ቀዋሚነት እንዳለው አሳይተዋል። ሕዝባዊ ጦርነት በማድረግ አንድ ትንሽ አገር ትልቁን የኢምፔሪያሊስት ኃይል ማሸነፍ እንደምትችል በተግባር አስመስክረዋል። የቪየትናምና የካምቦዲያ ሕዝቦች የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝምንና ቡችሎቹን በጦር ሜዳ ድል መምታት የቻሉት አላማቸው ትክክለኛ አላማ ስለሆነ፡ የሃገር ፍቅርንና ሶሻሊዝምን በሚገባ ስላዋሃዱ፡የሕዝባዊ ጦርነትን ህጐች በሚገባ በሥራ ላይ ስላዋሉና ከብረት የጠነከረ ዲሲኘሊን ስላላቸው ነው።
ከመቶ ዓመታት በፊት ካርል ማርክስና ፍሬድክ ኤንገልስ ሳይንሳዊ ሶሻሊዝምን በሚያስፋፉበትና ከወዝአደሩ ጋር በመሰለፍ ከሥራ ላይ ለማዋል ትግል ያደርጉ በነበረበት ጊዜ፡በአውሮፓና በአሜሪካ ሰፍኖ የነበረው ካፒታላዊ ሥርዓት በአቀፋቸው የመደብ ቅራኔዎች ተጠፍሮ ተይዞ ነበር። ገበያውን ለማስፋፋትና ቅራኔዎቹን ለማስታገስ ወደኋላ የቀሩትን አገሮች በመያዝ የብዝበዛና የጭቆና ቀንበሩን በአለም ሕዝቦች ላይ ጫነ።ይህም በመጠኑና ለጊዜውም ቢሆን በምርት ሃይሎችና በምርት ግንኙነቶች መካከል በጣም ከርሮና ከመፈንዳት ደረጃ ተዳርሶ የነበረውን ቅራኔ አስታገሰው። በዚህ ጊዜ ነው ካፒታሊዝም ወደኢምፔሪያሊዝም መለወጥ የጀመረው። የእንግሊዝና የፈረንሳይ ኢምፔሪያሊስቶች ይዘውት የነበረውን የመሪነት ስፍራ ከመጀመሪያው የኢምፔሪያሊስቶች የርስበርስ ጦርነት /የመጀመሪያው የአለም ጦርነት/ በኋላ የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም ወሰደው። እነዚህ በዝባዦች ለገበያ ሽሚያና ወደ ኋላ የቀሩትን አገሮች ለመከፋፈል ካደረጉት ከሁለተኛው “የአለም ጦርነት” በኋላ የበላይነቱን ይዞ የነበረው የያንኪ ኢምፔሪያሊዝም የበለጠ ተጠናክሮ ወጣ። እንግሊዝና ፈረንሳይ እንደዚሁም ሌሎቹም ይዘውት የነበረውን ገበያ ወሰደባቸው። አምባገነን ፈላጭ ቆራጭ ስልጣኑን በአለም ላይ በመዘርጋት፡ የተቀጣጠለውን የነፃነት ትግል ቋያ ለማጥፋት በያለበት ጥልቅ ጥልቅ በማለት የካፒታላዊው ሥርዓት ዘበኛና ፀጥታ ጠባቂነቱን አስመሰከረ።
የኢንዶቻይና ሕዝቦች ቀደም ብለው እአአ ከ1944 ጀምሮ መሳሪያዊ ትግል በማካሄድ የጃፓንን ኢምፔሪያሊዝም አንበርክከው ብሄራዊ ነፃነታቸውን እአአ በ1945 አወጁ። ያኔም ቢሆን የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም ከሻንጋይሼክና ከፈረንሳይ ኢምፔሪያሊዝም ጀርባ ሆኖ አሁን ገብቶ ከሚወገርበት የጦርነት ማጥ ውስጥ እጁ ከትቶ ነበር። ለፈረንሳይ መሳሪያ በማቀበልና ገንዘብ በመስጠት በቪየትናም ውስጥ ጦርነቱን እስከ 1954 ድረስ አካሄደ። በዲየንቡየንፉ ላይ የፈረንሳይ ኃይል በቪየትናማውያይን የነፃነት ተዋጊዎች ከባድ ተጋድሎ ከደቀቀና ታሪክ ሲያስታውሰው የሚኖር ታላቅ መሸነፍ ከደረሰበት በኋላ አገሩን ለቅቆ ሲወጣ፡ በደቡቡ ክፍል እንደነዲየም ያሉትን አሻንጉሊቶቱን በመፍጠርና በስልጣን ላይ በማስቀመጥ ትግሉን በሌሎች ሰዎችና በሌላ መልክ ቀጠለ። ይኸውም ብዙ ሳይቆይ እአአ ከ1959 ጀምሮ የገዛ ወታሩን በመላክ ይበልጡኑ በቀላሉ ያለውርደትና ያለውድቀት ሊወጣ ከማይችልበት ማጥ ውስጥ እየሰጠመ ሄደ። በ1968 ብሄራዊው ነፃ አውጭ ግንባር አብዛኞቹን ከተሞች በጦር ኃይል በመያዝ፡ኢምፔሪያሊዝምና አሻንጉሊቶቹ፡ኮሙኒስቶችን ድል አድርገናቸዋል፡አሸንፈናል በማለት የሚነፉትን መሰረተቢስ ኘሮፖጋንዳ ባከሸፈበት ጊዜ ኢምፔሪያሊዝምና ግብረአበሮቹ ወደአንድ ሚልዩን ተኩል የሚሆን ወታደር በድቡብ ቪየትናም አሰልፈው ነበር። ታዲያ ምን ይሆናል! ቴት ኦፌንሲቭ በተባለ የነፃ አውጭው የማጥቃት እርምጃ እንደእንቧይ ካብ ተንኮታኮተ።
የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም ኢንዶቻይናን የአዲስ መሳሪያ መሞከሪያ፡የሃይሉ መፈተኛና የሞኖፖሊስቶች ካዝና ማዳበሪያ አደረጋት። በዚህ አንፃር ደግሞ የቪየትናምን፡የላኦስንና የካምቦዲያን ሕዝቦች በተከለከሉ የኬሚካል መሳሪያዎች ያለምንም ርህራሄ ፈጃቸው። በናፖልምና በተመሳሳይ መርዞች ይህንን ቀበሌ የሰው ልጅ ሊኖርበት የማይችል ፍፁም ምድረ በዳ ለማድረግ ከባድ የአረመኔ ተግባር ፈጽሟል። የቪየትናምና የላኦስ ጦርነት ተፋፍሞ፡እዚህ ከገባው ማጥ ውስጥ ለመውጣት ሳይችል፡በ197ዐ በልኡል ሲሃኑክ የሚመራውን መንግሥት፡ፈቃዴን ለጥ ሰጥ ብለህ አልፈፀምክም በማለት አስገልብጦ በሎንኖል የሚመራውን የፍፁም ታዛዥ አሻንጉሊት መንግሥት አቋቋመ። ከብዙ ዓመታት በፊት ጀምረው ለሙሉ ነፃነትና ለሶሻሊዝም ይታገሉ የነበሩት ቀይ ካሜሮች ትግሉን በማፋፋም አስጨንቀው ስለያዙት ልክ ቪየትናም ውስጥ እንደሚያደርገው እዚያም ወታደር ልኮ ጦርነቱን ያካሂድ ጀመር። በቪየትናም ዲሞክራሲያዊ ሬፐብሊክ /ሰሜን ቪየትናም/ ላይም ቀደም ብሎ በ1965 የጀመረውን የቦምብ ውርጅብኝ እያፋፋመ ወደቦችን በፈንጂዎች እስከማጠርና እንደ ሃኖይ ያሉትን ትላልቅ ከተሞች እስከመደብደብ ደረሰ። ከዚህም አልፎ ደቡባዊውን የሕዝባዊት ቻይና ግዛትም መደብደብ ጀመረ። ጦርነቱን በጣም አባባሰው፣ ባለ በሌለ ሃይሉ ተጠቀመ። ይህንንም ሁሉ አድርጐ እነሆቺሚን ደጋግመው እንደአሉት የመጨረሻውን ውድቀትና ውርደት ከማባባስ ሌላ ምንም ውጤት አላገኙም። ብሎ ብሎ ከመሸነፍ በስተቀር ምንም የማይሆንለት መሆኑን ስለተረዳና የአሜሪካና የአለምም ሰፊ ሕዝቦች በዚህ በግፈኛና አሰቃቂ ጦርነት ላይ ከፍ ያለ ተቃውሞ በማድረጋቸው፣ እንደዚሁም ለጥቂት የመሳሪያ ፋብሪካ ባለቤቶች የማትነጥፍ ላም የሆነው ጦርነት የኤኮኖሚውን አቋም በኃይል ስለአናጋበት በ1972 ‘ስምምነት እናድርግ’ ወታደሮቼን አወጣለሁ ብሎ መሸነፉን ስለተቀበለ በ1973 ለስሙ ስምምነቱ ተፈረመና ወታደሮቹን አወጣ። ግን ውስጥ ውስጡን በጦር መሳሪያ፡በምክርና በመሰልጠን ወዘተ. ጦርነቱን ከመቀጠል አልተቆጠበም ነበር። መሸነፉን የተቀበለበትን ስምምነት ባለማክበሩና ከጀርባ ሆኖ የአገሬውን ሕዝብ እርስበርሱ ለማፋጀት ባለፉት ሶስት ዓመታት ከሞከረ በኋላ ትልቅ ሃፍረት ወደተመላበት ወደ አሁኑ ታሪካዊ ውድቀትና መዋረድ ደረሰ።
የቪየትናም ጦርነት የኤምፔሪያሊዝምን ቀስም ሰበረው። ሕዝባዊ የነፃነት ጦርነቶችን አቋቋማለሁ፣ በየስፍራው የሚነሳውን ፀረኢምፔሪያሊስትና ፀረፊውዳል ትግል፡ ለሕዝባዊ ዲሞክራሲና ለሶሻሊዝም የሚደረገውን ትግል አፍኜ አጠፋለሁ፣ የካፒታላዊውን ሥርዓት ዘላቂነት አረጋግጣለሁ፣ ወዘተ. እያለ በትምክህት ይደነፋ የነበረውን ሁሉ በድቡሽት ላይ እንደተሰራ ግንብ ጠራርጐ እርቃነ ስጋውን አስቀረው። እንደሎንኖልና ቲዩ ያሉትን አንዳንድ ፀረሕዝብ አሻንጉሊቶች ጐልቶ በሰፊው ሕዝብ መጫወትና የሌሎችን ሃብት መበዝበዝ የማክተሚያው ደወል ጮዃል። የኢንዶቻይና ጦርነት በርግጥ የኢምፔሪያሊዝም ቁንጮ የሆነው ትእቢተኛውና እብሪተኛው የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም እንኳን፡የሚበገር፡የሚደፈር፡ የሚሸነፍ የወረቀት ነብር መሆኑን በገሃድና ተጨባጭ በሆነ መንገድ ለአለም አሳየ። ከማንኛቸውም አይነት መሳሪያ ሰው የሚበልጥ ለመሆኑ ታላቅ ምስክርነቱን አረጋገጠ።
ገና በቴክኖሎጂና በሳይንስ ያልተራቀቁ፡ወደኋላ የቀሩ ተበዝባዥ ሕዝቦች በእውቀትና በኃይል የተራቀቀውን ሃያል መንግሥት በቆራጥነት ከታገሉ ሊያንበረክኩትና ሊያሸንፉት የሚችሉ መሆናቸውን የኢንዶቻይና ሕዝቦች፡ በተለይም የቪየትናም ሕዝብ በማያጠራጥር አኳኋን ለአለም ሕዝብ በማሳየት ቋሚ ታሪክ አድርጐ አስመዘገበ። እርግጥ ይህ ሁሉ ድል በቀላሉ የተገኘ አይደለም። በሚሊዩን የሚቆጠር ሕዝብ ሳያልቅ አልቀረም። ለግምት የሚያዳግት ጉዳት በሃብትና ንብረት ላይ መድረሱን ለመካድ አይቻልም። ይሁንና የቪየትናም ሕዝብ ተጋድሎ በዘመናችን አቻ የሌለው፡የዚያን ቀበሌ ብቻ ሳይሆን የሶስተኛውን አለም ተበዝባዠና ጭቁን ሕዝቦች የሚወክል፡ ለእነዚህ ሁሉ ታላቅ አርአያ የሚሆን ታሪካዊ ትግል ነው። የዚህ ቀበሌ ሕዝቦች በቆራጥነታቸው፡ አቻ በሌለው መስዋእትነታቸው፡በዘዴያቸው፡በብልህነታቸውና በጦር ስልታቸው አለም ሰፊ ዩኒቨርሲቲ እንደሚሆኑ አይጠረጠርም።ወዳጅ ቀርቶ ጠላት እንኳን እንዴት ያደንቃቸው?
ይህን ስናይ ለራሳችን የምናቀርበው ጥያቄ ታዲያ እኛስ ዘንድ መደረግ ያለበት ምንድነው? የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝምን እንዴት ነው የምንመለከተው የሚል ነው። አሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የደቡብ ምሥራቅ እስያን ሕዝቦች የሚፈጀው፡ይህን ያህል ረጅም ለሆነ ጊዜ ጦርነት የሚያደርገው፡መአት ገንዘብና የሰው ህይወት የሚያባክነው በቪየትናም ወይም በካምቦዲያ ሕዝቦች ላይ የተለየ ጥላቻ አድሮበት አይደለም። የተለመደ የኢምፔሪያሊስት ብዝበዛውን ለመቀጠል እንዲችል አካባቢዉን በሙሉ በቁጥጥሩ ስር ለማድረግ ሲል ነው፣ በተጨማሪም ለአንዳንድ የአሜሪካ ሞኖፖሊስቶች /ከበርቴዎች/ ጦርነት የገበያ ማስፋፊያ፡የሃብት ምንጭ ስለሆነ ነው።
ታዲያ የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም ለኢትዮጵያ ሕዝብ የተለየ ፍቅር አለው ይሆን? ብዝበዛውን ስንቃወም “እሺ እንዳላችሁ” ይለን ይሆን? አይለንም። ትንሽም ብትሆን ጥቅሙ ከተነካች የኢትዮጵያን ሕዝብ ትግል ከመደምሰስ አይመለስም። ሙሉ ለሙሉ የራሱን አሻንጉሊት የሆነ መንግሥት በላያችን ላይ እስካልጫነ ድረስ አይተኛም። ታዲያ ወታደራዊው መንግሥት የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝምን እንዴት ይመለከተዋል? ፊውዳሊዝምና ኢምፔሪያሊዝም ጣምራ ጠላቶቻችን ናቸው ብለናል። አንዱን ደምስሼ ሌላውን እተዋለሁ፣አባብለዋለሁ ማለት ዘበት ነው። ፊውዳሊዝምን ጨርሶ ለማጥፋትም ቢሆን የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝምን ከነግሳንግሱ ካገር ማስወጣት ያስፈልጋል፣ ከእርሱ ተጽእኖ ሙሉ ለሙሉ መላቀቀ ያስፈልጋል። ታዲያ ወታደራዊው መንግሥት እስከመቼ ድረስ ነው ከመንታ መንገድ ላይ ቆሞ ግራና ቀኝ የሚመለከተው? የወሰዳቸው አንዳንድ ተራማጅ እርምጃዎች እንኳን በእርግጥ በሥራ ላይ እንዲውሉ ከተፈለገ በአሜሪካን ኤምፒሪያሊዝም ላይ ምንም ማመንታት አያስፈልግም። ጨርሶ ለማስወገድና እንዳይመለስ ለማድረግም ሰፊውን ሕዝብ ማደራጀት ያስፈልጋል። ኢምፔሪያሊዝምን የሚያጠፋ መድሃኒት የተደራጀ ሰፊ ሕዝብ ብቻ ነው። ይህን ከቪየትናምና ከካምቦዲያ ሕዝቦች ለመማር ዛሬ ከመቼውም ያመቻል።
የቪየትናም ከካምቦዲያ ሕዝቦች እንማር።
ተደራጅተን ትግላችንን እንቀጥል።
ትግሉን ለመምራት ወይስ ሕዝቡን ለመግራት?
መጋቢት 28 ቀን የኢትዮጵያ አርበኞች ከጣሊያን ኢምፔሪያሊዝም ጋር አምስት አመት ሙሉ በዱር በገደል ከተናነቁ በኋላ አዲስ አበባን አስለቅቀው የያዙበት ቀን ነው። ይህ እለት ከ34 አመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በመላ ኢትዮጵያ ተከብሮ መዋሉ ከልብ የሚደገፍ ነው። በዚህ እለት በኢትዮጵያ ጊዚያዊ ወታደራዊ መንግሥት ሊቀመንበር በበአሉ ስነሥርዓት ላይ ረዘም ያለ ንግግር መደረጉ የሚታወስ ነው። በዚህ ንግግር ላይ “ሶሶት ታላላቅ ተግባሮች” ተብለው የወታደራዊውን መንግሥት የወደፊት አላማዎች የሚያብራሩ ነጥቦች ቀርበዋል። ይህ ጽሁፋችን ለማተኮር የሚፈልገው በነዚህ የትግሉን አቅጣጫ በሚወስኑት ነጥቦች ላይ ነው። በቅድሚያ ግን በጣሊያን ኢምፔሪያሊዝም ላይ የኢትዮጵያ አርበኞች የተጎናፀፉት ድል ለተራማጆች ምን ትርጉም እንዳለው ለማብራራት እንፈልጋለን።
የሊቀመንበሩ ንግግር ከላይ እስከ ታች ሲታይ የጣሊያን ኢምፔሪያሊዝም ድል ተመትቶ ከወጣ በኋላ ሌላ ምንም አይነት ኢምፔሪያሊዝም አልደፈረንም የሚል ይመስላል። ከዚያን ወዲህ ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከእንግሊዝ ኢምፔሪያሊስቶች ጋር ለአሥር ዓመታት ያህል እንደታገለ አያወሳም። በዚህም ትግል በከሃዲው አጤ ኃይለሥላሴና በእንግሊዝ ኢምፔሪያሊስቶች ፀረሕዝብ ትብብር ብዙ ፀረ ፋሺስትና አገር ወዳድ አርበኞች እየታደኑ እንደጠፉ አያመለክትም። ከዚያም በኋላ ደግሞ ላለፉት ሃያ ዓመታት የመላው አለም ዋና ጠላት የሆነው የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም አገራችንን ይዞ እንደቆየና ዛሬም ቢሆን ለብሄራዊ ነፃነታችን የሚደረገው ተጋድሎ ገና በመፋፋም ላይ መሆኑን አያበስርም።
ያለፈውን ፀረኢምፔሪያሊስት ትግል ብቻ እያሞጋገሱ አይናችን ስር የሚካሄደውን ተጋድሎ እንደሌለ አድርጐ ማለፍ የሕዝቡን ትግል የሚያዘናጋና ትጥቁን የሚያስፈታ አደገኛ አዝማሚያ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ የመሳፍንቱን አገዛዝና የኢምፔሪያሊስቶችን ጭቆናና ተጽእኖ፡በተለይም የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝምን ተጽእኖ ከአገሪቱ ጨርሶ በመደምሰስ ነፃና ዲሞክራቲክ አገር ለመገንባት በመታገል ላይ ያለ ሕዝብ ነው። “የአባት ዘራፍ ለልጅ አያልፍ” የሚለውን የአዛውንት አነጋገር አልረሳም። እንደዚህም ስለሆነ አባቶቻችን ከኢምፔሪያሊስቶች ጋር ያደረጉትን መራራና አኩሪ ትግል እንዳለፈ ታሪክ ብቻ እየዘከረ የሚዝናናበት ደቂቃ ጊዜ የለውም። ስለዚህ ‘የኢምፔሪያሊስቶች ወረራ አልፏል፣ ዛሬ አገራችን ነፃ አገር ነች’ እያሉ ከሚያዘናጉት ክፍሎች ጋር ትልቅ ልዩነት አለን።
ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ገና በማያወላውል አኳኋን የነፃነቱን ፋና እጁ አላስገባምና፣እንደዚህም እንዳይሆን አሁንም ገና ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶቹ ታፍነውበታልና፣ አሁንም የመሳፍንቱን ሥርዓት ለማፈራረስ የሚደረገው ትግል ገና ብዙ እንቅፋቶች አሉበትና፣አሁንም የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም በአገራችን ስር እየሰደደ የኢትዮጵያን ሕዝብ ትግል አደጋ ላይ የሚጥልበት ሁኔታ አለና፣ ለተሟላ ነፃነታችን የምናደርገው ተጋድሎ ገና ብዙ ፈተና ይቀረዋል እንላለን። ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ እስከአጥንቱ ሰርስሮ ከገባው መራብ፣ መራቆት፣ መዋረድ ገና ያልተላቀቀ በመሆኑ ‘ሲያልፍ ዋዛ’ እያለ አይዝናናም። ‘ያልፋል፡እስኪያልፍ ግን ያለፋል’ እያለ ታሪክ ካደነቀው ደግነቱ ሳይቆጥብ ቀሪውን የጨለማ ዘመን ለመወጣት ትግሉን ይቀጥላል እንጂ!
በዚህ በኩል እንግዲህ አቋማችንን ግልጽ ካደረግን ዘንድ ትግሉ ስለሚቀጥልበት አቅጣጫ ያለንን አስተያየት ለመስጠት እንፈልጋለን። ሚያዝያ 12 ቀን ወታደራዊው መንግሥት ባወጣው አንድ መግለጫ ላይ የኢትዮጵያን ሬቮሉሽን አቅጣጫ በሚመለከተው ጉዳይ እያንዳንዱ መደብ የራሱ አስተያየት ሊኖረው እንደሚችል በሰፊው አብራርቷል። ይህ እውነት ነው። በመጋቢት 28 ቀን የተደረገውንም የሊቀመንበሩን ንግግር የምንመለከተው ከዚሁ አንፃር ነው። በዚህ በመጋቢት 28ቱ የሊቀመንበሩ ንግግር ወታደራዊው መንግሥት ስለወደፊቱ አቅጣጫ ሲያትት ሶስት ዋና ዋና ተግባሮች እንዳሉትና ሊፈፀሙ እንደሚታሰቡ ይናገራል። ግን የነዚህን ተግባሮች ይዘት ከማየታችን በፊት የኢትዮጵን ሕዝብ ትግል የቱ መደብ ምን አቅጣጫ ሊሰጠው እንደሚሞከር በአጠቃላይ እናመለክታለን።
እልም ያሉት አድሃሪ ሃይሎች የሚፍጨረጨሩት የትግሉን አቅጣጫ ጨርሶ ለመቀልበስና የኢትዮጵያን ሰፊ ሕዝብ መልሰው ከጨለማ ስርአታቸው ለመጨመር ነው። የትግሉ ወደፊት መራመድ የግድ የሚጠይቃቸው አንዳንድ እርምጃዎች ባስቸኳይ ካልተወሰዱ ለጊዜውም ቢሆን የሰፊው ሕዝብ ትግል በመሳፍንቱና በኢምፔሪያሊስቶች ሴራ ሊገታ ይችላል።
በሌላ በኩል ደግሞ የተለያየ ርቀት ለመሄድ የሚፈልጉ የተሰባጣጠሩ ተራማጅ ሃይሎች አሉ። ከነዚህ ውስጥ በመጀመሪያ የምንጠቅሰው የወዝአደሩንና የድሃውን አርሶአደር መደቦች ነው። እነዚህ በመደባዊ አቀማመጣቸው የተነሳ ትግሉ እስከመጨረሻ ገፍቶ አብዛኛው ሕዝብ ነፃ ካልወጣ ነፃ ሊሆኑ አይችሉም። ስለዚህ ያለአንዳች ማወላወል ጭቆናን ጨርሶ ለማጥፋት ትግሉን ወደፊት ይገፋሉ። በተለይ የወዝአደሩ መደብ ትግሉ ድል ሲመታ አውተብትቦ ከያዘው ከባርነቱ ሰንሰለት በስተቀር ምንም የሚቀርበት ነገር ስለሌለ ከሁሉ ቆራጥ የሆነ የሬቮሉሽኑ ደጋፊ ነው።
ከነዚህ ሌላ ደግሞ እንደዚሁ በህብረተሰቡ ውስጥ በያዙት ቦታና በመደባዊ አቀማመጣቸው ወላዋይነት የማይለያቸው ሃይሎች አሉ። እነዚህ ደግሞ የንኡስ ከበርቴው መደብ አባሎች ናቸው።የሳይንቲፊክ ሶሻሊዝም መሥራች የዚህን መደብ አባል በአጠቃላይ ሲጠቁሙት “እዚያው በዚያው ከበርቴም የሕዝብም ወገን” ይሉታል። “ንኡስ” ወይም አነስተኛ ነውና ከበላዩ ያሉትን መደቦች ይጠላቸዋል።ይቃወማቸዋል፡ይታገላቸዋል። ከሁሉም በላይ ደግሞ የማይለየው የመንፈስ ቁራኛ አለ። ይኸውም ምንጊዜም ቢሆን ተንጠራርቶ የነርሱን ቦታ ለመያዝ ያለው ጉጉት ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ‘ከበርቴም’ ነውና በመደባዊ አቀማመጣቸው ከበታቹ ያሉትን ወዝአደሩንና ድሃውን አርሶአደር ይንቃል፣ይፈራል፣ ይጠራጠራል።
በህብረተሰቡ ውስጥ ዋና ዋናዎቹ የሃብት ባለቤቶች ከበላዩ ያሉት መደቦች ናቸው። ዋናዎቹ የሃብት አምራቶች ደግሞ ከበታቹ ያሉት ናቸው። የንኡስ ከበርቴው መደብ ከሁለቱም እየጠቃቀሰ፣ሁለቱን እያገናኘ ቃርሞ የሚኖር መደብ እንጂ የራሱ የሆነ የጠነከረ የኢኮኖሚ መሰረት የለውም። እንግዲህ ከበዝባዥም ከተበዝባዥም መደቦች ስለሚጠቃቅስ በነፃነቱ ትግል ቁጥር ያለ ሚና መጫወት ይሳነዋል። ተቃውሞው፡ትግሉ፡ለተወሰነ ጊዜ በግንባር ቀደምነት ጉድጉድ ማለቱ ሁሉ ለጠቅላላው ለህብረተሰቡ ነፃነት ሳይሆን ራሱ ከንኡስነት ክልል ወጥቶ ሙሉ ከበርቴ ለመሆን የሚያደርገው ሙከራ ነው። ትግሉ ጭቆናን ጨርሶ ለማውደም ሳይሆን በርሱ ላይ ያለውን ጭቆና በሕዝብ አጋዥነት ጥሎ ለራሱ ጥቅም አመቺ የሆነ ሥርዓት ለማንገስ ነው።
እንግዲህ በመሰረቱ የተወሰነ የትግል አንድነት ቢኖራቸውም ንኡስ ከበርቴውና ቆራጥ ሬቮሉሽናውያን የሚጋጩበት የአላማ ልዩነት አላቸው ማለት ነው። ምክንያቱም የሰፊው ሕዝብ ተጋድሎ አንዱን አይነት ጭቆና በሌላ አይነቱ ጭቆና ለመተካት ሳይሆን ብዝበዛን ጨርሶ ለማጥፋት ነውና።
አንቺው ታመጭው አንቺው ታሮጭው ይባላል። የንኡስ ከበርቴው ጥረት ለትግሉ ደጋፊ ለመሰብሰብ ሲሆን እርሱ ራሱ በግንባር ቀደምነት አንስቶ ይዋጋላቸው የነበሩትን መፈክሮች በሚሊዩን በሚቆጠረው ሕዝብ አእምሮ ታንፀው የትግሉን ማእበል የሚያንቀሳቅሱ ሞተሮች ሲሆኑ ከጦር ይፈራቸውና ቁጭ ይላል። እነርሱንም ሽሮ ሊቋቋማቸው መውደቅ መነሳት ይጀምራል። ይህን ጊዜ የግንባር ቀደምነቱ ሚና ከሞላ ጐደል ያልቅበትና በወጉ መምራት ያቃተውን ትግል ለመግራት ፀረሕዝብ መፍጨርጨሩ ይጀምራል። ራሱንና ጠቅላላውን ህብረተሰብ ከጭቆና ለማላቀቅ የተነሳው ቆራጡ ወዝአደርና ወገኖቹ ግን እነዚህን መፈክሮች ከመቸውም ይበልጥ አቅፈው ይዘው ትግላቸውን እስከመጨረሻው ድል ያካሄዳሉ።
ይህ እንግዲህ በአጠቃላይ በታሪክ ተደጋግሞ በብዙ ህብረተሰቦች ሬቮሉሽን የታየ ትንተናና ሃቅ ነው። እንግዲህ ይህንን ትንተና እያስታወስን ደርጉ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ትግል መስጠት የሚያስፈልገውን አቅጣጫ እንመልከት።
ከሊቀመንበሩ ንግግር እንደሚታየው ደርጉ ‘ሶስት ታላላቅ ተግባሮች አሉብኝ፣ እነርሱን እንዳከናወንኩ ተመልሼ ጦር ሰፊሬ እገባለሁ’ ይላል። እነዚህም ሶስት ዋና ዋና ተግባሮች ተብለው የቀረቡት
1ኛ/ አርሶአደሩን፣ወዝአደሩንና ወታደሩን ማስተማርና ማደራጀት፣
2ኛ/ የሰፊውን ሕዝብ የፖለቲካ ድርጅት ማቋቋም፣
3ኛ/ ከዚህ ምእራፍ እንደደረሰና በሚገባ ‘መዘጋጀቱ እንደተረጋገጠ’ በሕዝቡ ከሕዝቡ መሃል መንግሥት መምረጥ።
ሶስቱ ተግባሮች እነዚህ ናቸው። ከየካቲት ወር ጀምሮ ሰራዊቱ ከሰፊው ሕዝብ ጐን ሆኖ ሲዋጋለት የነበረው የዲሞክራሲ ጥያቄ ፈጽሞ ተሽሮ እስከነሽታውም ጠፍቷል። እነዚህን አላማዎች በሥራ ላይ ለማዋል እንኳን የሰፊው ሕዝብ መሰረታዊ ዲሞክራሲያዊ መብቶች፡በተለይ በግልጽና በይፋ የመፃፍ፡የመናገርና የመወያየት መብቶች በቅድሚያ እንዲከበሩ ያስፈልጋል። እነዚህን ሰብአዊ መብቶች ዘግቶ ይዞ ይህን አደርጋለሁ፡ ያንን እፈጥራለሁ ማለት ሰፊውን ሕዝብ ከመግራት የተለየ አላማ አለው ለማለት ያስቸግራል። ወደዚህ ወደዲሞክራሲ ጥያቄ በሰፊው ከመመለሳችን በፊት ስለተግባሮቹ አንዳንድ አስተያየቶች እንስጥ።
የመጀመሪያውን አላማ እንውሰድ። እዚህ ላይ የኢትዮጵያ ንኡስ ከበርቴ መደብ ወዝአደሩን፡አርሶአደሩንና ወታደሩን አደራጃለሁ ሲል የራሱን መደራጀትና መጠናከር ትቶ ለሌሎች መደቦች ጥቅሙን የሰዋ ሊመስል ይችላል። ግን አይደለም። ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ ይባላል። ንኡስ ከበርቴው እነዚህን ሃይሎች አደራጃለሁ፡አስተምራለሁ የሚለው ራሱ በቅድሚያ ተደራጅቶ ለትግሉ የራሱን አቅጣጫ ለመስጠት ስለፈለገ ነው። ይህ አላማ ስላለው ያለመደቡ ገብቶ ለማስተማርና ለማደራጅት በሚሞክርበት ጊዜ ወዝአደሩን ለማስተማርና ለማደራጀት ታሪካዊ ኃላፊነት ያለባቸውን አብዩታዊ ምሁራን በዲሞክራሲ ተጠቅመው እንዳይሰሩ እየከለከለ ነው። ዲሞክራሲ ታውጆ የህብረተሰቡ ተራማጅ ክፍሎች መደራጀትና ማደራጀት እስከቻሉ ድረስ ደርጉ እኔ ራሴ ሁሉንም አደራጃለሁ ቢል የሕዝቡን ትግል ከቁጥጥሩ ስር ለማስገባት የሚያደርገው ጥረት መሆኑ መታወቅ አለበት።
የሕዝቡን ትግል ለርሱ በሚያመቸው አቅጣጫና ለራሱ ጠቃሚ እስከሆነበት ድረስ ብቻ ለማስኬድ እንዲያመቸው የሌሎችን መደቦች የመደራጀት መብት አፍኖ ይያዝ እንጂ የንኡስ ከበርቴው መደብ ራሱን የማደራጀቱን ነገር ችላ አላለም። ከሶስቱ ታላላቅ ተግባሮች በሁለተኛው ነጥብ የተጠቀሰው አላማ ‘የሰፊውን ሕዝብ የፖለቲካ ድርጅት’ ማቋቋም ነው ይላል። በዚህ ጉዳይ ላይ ወደፊት ለብቻው በሰፊው እንመለስበታለን። እዚህ ላይ ባጭሩ ለማመልከት የምንፈልገው በመሰረቱ ሕዝቡን ለማስተማርና ለማደራጀት ዲሞክራሲ እስካልታወጀ ድረስ ከሕዝቡ በትግል ተፈትነው በወጡ ሳይሆን ደርጉ በመለመላቸው ቢሮክራቶች አስተማሪነትና አደራጅነት የተቋቋመ ድርጅት ያው የንኡስ ከበርቴው ድርጅት ብቻ ነው። ይህ መደብ በዚህም በኩል የማይለየው ጠባይ አለው። ይኸውም ለትግሉ አጋዥ ሲሰበስብ ራሱ ያቅሙን ያህል በዝባዥ መሆኑን ለማረሳሳትና በርሱና በተቀሩት የሰፊው ሕዝብ ወገኖች /ክፍሎች/ በተለይም በርሱና በወዝአደሩ መሃከል ያለውን ቅራኔ ለማድበስበስ ‘አንድ ነን፡አንድ ድርጅት ብቻ!’ እያለ ይሰብካል። ገና የዛሬ 13ዐ አመት የሳይንቲፊክ ሶሾሊዝም ሊቃውንት እነማርክስና ኤንግልስ ‘ንኡስ ከበርቴው በአንድነት ስም በአንድ ፖርቲ እንሰማራ ይላችኋል፣ ግን የተለያየ ርቀት ስለምትሄዱ ለየብቻችሁ ተደራጅታችሁ ተጋገዙ እንጂ እጅ እግራችሁን አሥራችሁ አትደባለቁ’ ብለው ለአለም ወዝአደሮች አስታውቀው ነበር። ከዚያም ወዲህ በየትም አገር የተደረጉ ሬቮሉሽኖች፡ ዛሬ እንኳን በአይናችን ስር ድል በድል ላይ የሚጐናፉት የኢንዶቻይና ሕዝቦች ለዚህ የበቁት ይህን ምክር በሥራ ላይ በማዋላቸው ነው። እርግጥ እነዚህ ህዝቦች የሚታገሉት በሰፊ ግንባር ውስጥ ተሰማርተው ነው። ግን በዚህ ግንባር ውስጥ በየመደባቸው የተደራጁ የሰፊው ሕዝብ ወገኖች የሆኑ ፖርቲዎች አሉ።
እርግጥ ነው በፀረፊውዳልና በፀረኢምፔሪያሊስት ትግሉ ውስጥ እስከተሳተፈ ድረስ ከንኡስ ከበርቴው መደብ ጋር የግድ የትግል አንድነት ያስፈልጋል። ተራማጆች ሁሉ ይህ አንድነት እንዲመሰረት መጣር አለባቸው። ግን ይህ አንድነት የመግበስበስ አንድነት አይደለም። አባቶቻችን ሲተርቱ የወዳጅ ስልቻ ለየብቻ ይላሉ። ሁላችንም በዲሞክራሲ ላይ ተመርኩዘን በየመደባችን እንደራጅ። ከዚያ በኋላ በዲሞክራሲያዊ አሰራር ተሳስረን የጊዜውን ጠላቶቻችንን በጠነከረ አንድነት አንምታቸው፣ እንደምስሳቸው።
የሕዝቡ ዲሞክራሲያዊ መብቶች እስካልተረጋገጡ ድረስ በሶስተኛው አላማ ላይ ‘ሕዝቡ ከህዝቡ መንግሥት ይመርጣል’ የሚለው ለኔ እንደሚመች አስተምሬው፣ ለኔ እንደሚመች አደራጅቼው፣ ‘በሚገባ መዘጋጀቱ እንደተረጋገጠ’ /ይህ የኛ አይደለም፡የሊቀመንበሩ አነጋገር ነው/ ንኡስ ከበርቴው የሕዝቡን ቡራኬ ያገኘ ‘የሕዝብ’ መንግሥት ያቋቁማል ማለት ነው። እዚህ ላይ ከሃገራችን ወጣ ብለን የፖርቱጋል ሕዝብ የተከተለውን ዲሞክራሲዊ ጎዳና መመልከት ትክክለኛውን ጎዳና ያሳየናል ብለን ስለምናምን ባጭሩ ዛሬ ሕዝባዊ መንግሥቱን ለመመረጥ ድምጽ በመስጠት ላይ እንዴት እንደደረሰ እንመልከት።
የፖርቱጋል ሰራዊት በፖለቲካ ንቃታቸው ከፍ ካሉት ተራማጅ ወታደሮች ንቅናቄ ተመርቶ አምና በሚያዝያ ወር ለአርባ ዓመታት በከፋ የፋሺስት አገዛዝ ስር ወድቆ የነበረውን ሕዝብ ነፃ ለማውጣት እርምጃ ወሰደ። የፋሽስቱ የካይታኖ መንግሥት ተገለበጠ። ይህ ከመሆኑ በፊት የፖርቱጋል ሕዝብ እጅግ አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ትግሉን ያካሂድ ነበር።ቢሆንም ማንም ሊክደው የማይችለው አንድ ሃቅ ነበር። ከጭቆናው አገዛዝ የተነሳ ሕዝቡን ለማስተማርና ለማደራጀት እጅግ አስቸጋሪ ስለ ነበረ የሕዝቡ የፖለቲካ ንቃት ደረጃ ከፍተኛ አልነበረም። ግን ቢሆንም ሰራዊቱ የካይታኖን መንግሥት በሕዝብ ተረድቶ እንደገለበጠ ለሰፊው ሕዝብ ወገኖች ዲሞክራሲያዊ መብቶችን አወጀ እንጂ ‘ሕዝቡ አልተማረም፣ዲሞክራሲ ቢሰጠው አድሃሪዎች ይጠቀሙበታል’ አላለም። በጨለማው ዘመን እጅግ በመረረ ጭቆና ስር ተይዘው እየታሰሩና እየተፈቱ፡እየወደቁና እየተነሱ ለሰፊው ሕዝብ ነፃነት በምስጢር ይታገሉ የነበሩት ሃይሎች ሁሉ በይፋ ወጥተው በመሰላቸው መንገድ ሕዝቡን እንዲያስተምሩና እንዲያደራጁ ታገዙ።
በዚህም የተነሳ የፖርቱጋል ሕዝብ ተብትበው ከያዙት አድሃሪ እምነቶች ሁሉ እየተላቀቀ ትግሉን አፋፋመ። የንቃቱም ደረጃ በየእለቱ እየዳበረ ሄደ። ዲሞክራሲ ለሰፊው ሕዝብ ወገኖች በእርግጥ ከሥራ ላይ በመዋሉ አሁን እኛ አገር እንደሚፈራው ሕዝቡ በአድሃሪዎች አልተወናበደም፣ትጥቁን አልፈታም። ይህ ደግሞ በፍፁም ሊያስደንቀን አይገባም። በመላው አለም ታሪክ፡በየትም ቢሆን የዲሞክራሲ ሙሉ በሙሉ ከሥራ ላይ መዋል አድሃሪዎችን አድሃሪዎችን አመችቶአቸው አያውቅም። እንዲህማ ቢሆን ኖሮ፣ ዲሞክራሲ የሕዝብ ማስተማሪያ ሳይሆን ማወናበጃ መሳሪያ ቢሆን ኖሮ፣ የሰፊውን ሕዝብ ትግል ወደፊት ማራመድ ትቶ የሚገታ ቢሆን ኖሮ፣ ባጭሩ ትግሉን የሚያደናቅፈው ቢሆን ኖሮ ገደል ይግባ እንል ነበር። ግን የፖርቱጋል ብቻ ሳይሆን የማንም አገር ታሪክ ቢሆን እንደሚያሳየው ዲሞክራሲ የአድሃሪዎችን መቃብር ቆፈረላቸው እንጂ ከወደቁ በኋላ የመመለሻ መሰላል አልሆነላቸውም።
የፖርቱጋል አድሃሪዎች ይህንን አላጡትም። በዲሞክራሲ ተጠቅመው ሺህ ጊዜ ለማወናበድ ቢሞክሩ እንደማያዋጣ ተረዱ። ስለዚህ በግልጽ በኃይል በመጠቀም በመስከረም ወርና ከዚያም በኋላ እንደገና በመጋቢት ወር ዲሞክራሲን ለመደምሰስ ሙከራ አድርገው ነበር። ነገር ግን ይህ ሙከራቸው በተራማጁ ሰራዊትና ነቅቶ በሚጠብቀው ሰፊ ሕዝብ ትብብር ውድቅ ሆነ። እንደዚህም ስለሆነ በአሁኑ ወቅት የፖርቱጋል ሕዝብ በእውነት የእርሱ የሆኑትን ወኪሎች መርጦ ሕዝባዊ መንግሥቱን ለማቋቋም በመዘጋጀት ላይ ነው።
በኛ አገር ግን ለደርጉና ለአንዳንድ የሕዝብ ፍራቻ ለተቆራኛቸው ንኡስ ከበርቴዎች ብቻ በተገለጠ ተአምር ዲሞክራሲ ቢታወጅ የአድሃሪዎች መሳሪያ ይሆናል እየተባለ ይለፈፋል። እዚህ ላይ የንኡስ ከበርቴው መደብ ቁልጭ አድርጐ የሚያሳየው ነገር ቢኖር ከላይ የተጠቀሰውን ወላዋይ መደባዊ ጠባዩን እንጂ የሰፊውን ሕዝብ ለዲሞክራሲ ብቁ ለመሆን አይደለም። እንዴት?
ይህንን ለመረዳት ሩቅ ሳንሄድ የየካቲቱ ንቅናቄ ተተጀመረ ወዲህ የዚህን የዴሞክራሲ ጥያቄ እድል መመልከት ይበቃል። እስካሁን ድረስ በትግሉ መድረክ ላይ የታዩት ሃይሎች (ከራሱ ከእንዳልካቸው ጀምሮ እስከዛሬው ደርግ ድረስ) በዚህ ጉዳይ ላይ አንድ ተመሳሳይ አዝማሚያ አሳይተዋል። ለትግላቸው አመቺ መስሎ በታያቸው ጊዜ ሁሉም ቢሆኑ ዲሞክራሲን ጠይቀዋል። የሕዝቡን ተባባሪነት ለማግኘት ሲሉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዲሞክራሲ ብቁ መሆኑን ተናግረዋል። እስከዛሬም ድረስ ሰፊው ሕዝብ እነዚህንን መብቶቹን መነፈጉ ፈጽሞ ተገቢ አይደለም በማለት ጠላቶቻቸውን ወንጅለውበታል።
እንዳልካቸው አክሊሉን በገለበጠ ማግስት ጋዜጠኞችን ሰብስቦ ከእንግዲህ ዲሞክራሲን አወጅሁ አለ። ሳንሱር አነሳሁ አለ።ለማንኛውም የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዳልካቸው ፈቀደ አልፈቀደ፣የመናገር፡የመፃፍ፡የመሰብሰብ፡ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግና ሥራ የማቆም መብቱን ከእጁ አስገብቶ ነበር። እነዚህንም መብቶቹን በእለታዊ ትግሉ በሥራ ላይ ስላዋለ ይበልጥ ነቃ፣ ትግሉ ይበልጥ ወደፊት ገፋ እንጂ፣ አድሃሪዎቹን ይበልጥ አደቀቃቸው እንጂ ተወናብዶ ትጥቁን ሲፈታ የት አየነው? እንዲያውስ እነእንዳልካቸው የሕዝቡ ትግል ቢያይልባቸው አይደለም ዲሞክራሲያዊ መብቶቹን ሊያፍኑ የተነሱት?መልሰውስ ሳንሱርን፡ብሄራዊ ፀጥታ ኮሚሽንን፡ የሥራ ማቆም አድማና የሰላማዊ ሰልፍ መከልከልን…የመሰሉ እርምጃዎች የወሰዱት ሕዝቡ እጁ ባስገባቸው ዲሞክራሲያዊ መብቶች በሚገባ መጠቀም ስለጀመረ አይደለም? ተራማጁ ሰራዊትስ ከሕዝቡ ጐን ሆኖ በነእንዳልካቸው ላይ የተነሳውና የጣላቸው በነዚህ ዲሞክራሲያዊ መብቶች መታፈን አማርሮና ይህንኑ ድርጊት ተቃውሞ አይደለም?
እርግጥ ነው ዛሬ ደርጉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዴሞክራሲ ብቁ አይደለም፣ ገና መማር አለበት እያለ የሕዝቡን መብት ለመግታት ይሞክራል። ግን የትግሉን አስተዳደግ ከየካቲት ጀምሮ እንየው። ሰራዊቱ ሀሁ ብሎ በፖለቲካው መድረክ ላይ ብቅ ሲል ለቀድሞው ንጉስ ካቀረባቸው ጥያቄዎች ውስጥ የመናገር፡የመፃፍ፡የመሰብሰብ፡የመደራጀት…መብቶች ነበሩበት። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ወታደሩ በተነቃነቀ ቁጥር ራሱ ስልጣን ይዞ እስኪሽራቸው ድረስ በዲሞክራሲ መብቶች ጉዳይ ደጋግሞ ከሰፊው ሕዝብ ጐን፡አንዳንዴ እንዲያውም በግንባር ቀደምነት ተሰልፏል። በተለይ አቶ ሃዲስ አለማየሁ ስለዲሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶች ያቀረቡትን የህግ ረቂቅ ደግፎ እንደነበረና እነዚህን አቅፎ የያዘው ህገመንግሥት ‘ባስቸኳይ ታውጆ ከሥራ ላይ እንዲው’ እየደጋገመ ሲወተውተው ነበር። ከዚያም ደርጉ ከተቋቋመ በኋላ እንኳን አላማውን እንዲያሳውቅ [እንዲ(የማይነበብ) – የአዘጋጆች እርማት] ከሕዝቡ ወገን ሲጠየቅ ሃምሌ ሁለት ቀን 13 ነጥቦች የያዘ ‘የደርግ ኘሮግራም’ ተብሎ ለሕዝብ መገለጡን እናስታውሳለን። ይህ ኘሮግራም በአራተኛው ነጥቡ ላይ ‘ደርጉ በመዘጋጀት ላይ ያለው ህገመንግሥት ባስቸኳይ በሥራ ላይ እንዲውል ያደርጋል’ ይል ነበር። ይህም ‘በአስቸኳይ ከሥራ ላይ ይውላል’ የተባለው ህገመንግሥት ነሃሴ 4 ቀን ለሕዝብ በጋዜጣ ተገለጸ። እርግጥ ይህ ህገመንግሥት መአት ጉድለቶች ነበሩበት። እነርሱን ለጊዜው ወደጐን ብንተዋቸው ዲሞክራሲያዊ መብቶችን በሚመለከተው በኩል ስለመደራጀት፡ስለመፃፍ፡መናገር፡መሰብሰብ..ወዘተ. ዛሬ በአዋጅ የተሰረዙትን መሰረታዊ መብቶች ይዞ ነበር።
ይህ ሁሉ ቀረና ደርጉ አጼ ኃይለሥላሴን አውርዶ ስልጣን ሲይዝ ሕዝቡ የሚጠበቅበትን አላማ ወደጐን ትቶ የሕዝቡን መብት የሚያፍን ፀረዲሞክራሲያዊ አዋጅ አወጣ። ከየካቲት ጀምሮ መብቶቹን በትግል እጁ እያስገባ ብሶቱን እየተናገረና እየፃፈ፣ በመፍትሄው ላይ በግልጽ እየተወያየ፣ ሰላማዊ ሰልፍ እያደረገ፣ የሥራ ማቆም አድማውን በሥርዓት እየመራ፣ በስንት መስዋአትነትና ጀግንነት ትግሉን እዚህ ደረጃ ያደረሰው ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ እስከነአካቴው በአዋጅ ‘ከዚህ ቀን ጀምሮ ለዲሞክራሲ ብቁ አይደለህም’ ተብሎ ተሰደበ።
በኛ ግምት ግን የዛሬ አመት ብቁነቱ ታምኖበት እነዚህ መብቶች ‘በአስቸኳይ’ ከሥራ ላይ እንዲውሉ ከተጠየቀ ዛሬ ደግሞ ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድ አመት ትግሉ ለዘመናት የማይገኙ ትምህርቶች ቀስሞ ከብቁም ብቁ ሆኗል። ስለዚህም እነዚህ መብቶች ‘በጣም በአስቸኳይ’ ከሥራ ላይ መዋል አለባቸው እንላለን።
ይህ በገሃድ የሚታይ ሃቅ ተክዶ ከዛሬ አመት ዛሬ የኢትዮጵያ ሕዝብ ወደኋላ አሸግሽጓል ተብሎ ቢሰደብ እንኳን ዲሞክራሲያዊ መብቶቹ ታፍነው እስከተያዙ ድረስ በአድሃሪዎችም ሆነ በአጉል ተራማጆች፡ በንኡስ ከበርቴ ወላዋዩችም ሆነ ‘በአዋጅ ሶሻሊስቶች’ ሊወናበድ ስለሚችል የእነዚህ መብቶች መታወጅ እንደህይወት እስትንፋስ ያስፈልጉታል እንላለን። የዲሞክራሲ ከሥራ ላይ መዋል የማንንም ሕዝብ ትግል ወደኋላ እንዳልጐተተ ሁሉ የኢትዮጵያንም ሬቮሉሽን ያራምደዋል እንጂ አያደናቅፈውም።
ዛሬ ደርጉ ለቆራጥ የሕዝብ ወገኖች አስፈላጊ የሆነውን መብት አፍኖ ይዞ እኔው አስተምራለሁ፡አደራጃለሁ እያለ የሕዝቡን ንቃት ከቁጥጥሩ ስር ለማስገባት ቢሞክር የኢትዮጵያን ሕዝብ ትግል ለራሱ አገዛዝ በሚያመች አቅጣጫ ለመግራት የሚያደርገው ትንንቅ መሆኑ መታወቅ አለበት። በዚህም ድርጊቱ ታሪክ ደጋግሞ ካሳየው የንኡስ ከበርቴ ወላዋይ ሚና የወጣ ምንም የፈፀመው ነገር የለም።
እንግዲህ ይህ በግልጽ ከታወቀ ዘንድ ዛሬ በአገራችን ለዲሞክራሲያዊ መብቶች የሚደረገው ትግል በመደቦች ትግል አንፃር መታየትና ይህ ትግል በሚጠይቀው ቆራጥነት መመራት አለበት ማለት ነው።በዚህ ትግል እስከመጨረሻ ለመግፋት የሚችሉትና የሚፈልጉት የወዝአደሩና የአርሶአደሩ ወገኖችና ሌሎችም ቆራጥ ተራማጆች (ከደርጉም ውስጥ ያሉት ተጨምረው) ይህን በሚገባ መረዳት አለባቸው።እንደዚህ ከተመለከትነው የንኡስ ከበርቴው እጅግ ወላዋይ ክንፍ የሕዝቡን ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች አፍኖ ለመያዝ ሲል ያመጣውን ሰበብና ‘መከራከሪያ’ ቢያመጣ አንወናበድም ማለት ነው።ሙከራው ሁሉ ከላይ እንዳልነው ከእንግዲህ በግንባር ቀደምነት ለመምራት ያቃተውን ሕዝብ ለመግራትና ለትግሉ የሚስማማውን አቅጣጫ ሰጥቶ የራሱን ሥርዓት ለማንገስ መሆኑ በሰፊው ሕዝብ ፊት መገለጥ አለበት።
ጊዜው ለዚህ እርምጃና ለነፃነት ለሚደረገው ትግል እጅግ ያመቸ ጊዜ ነው። የኢትዮጵያ ተራማጆች እንኳን ዛሬ በሚሊዩን የሚቆጠረው ሰፊው ሕዝብ አላማቸውን ተረድቶ አቅፎ ይዞአቸው ይቅርና ጥቅጥቅ ባለው የኃይለሥላሴ የጭለማ ዘመን እንኳን ሰፊውን ሕዝብ ለማንቃትና ለማደራጀት ብዙ መስዋአትነት የጠየቋቸውን ተግባሮች ፈጽመዋል። ዛሬም የነፃነቱ ተጋድሎ አላለቀምና ትጥቃቸው የሚፈታበት ምንም ምክንያት የለም። በሰበብ በአስባቡ የሕዝቡን ትግል ወደፊት ለመግፋት ብቻ ሳይሆን ጨርሶ እንዳይቀለበስ የሚያስፈልጉትን ዲሞክራሲያዊ መብቶች ማስገኘት የተራማጆች አንዱ ዋና ግዴታ ነው።እነዚህን መብቶች ለማፈን የሚፈልጉ ሃይሎች ሕዝቡ ለዲሞክራሲ ገና ብቁ አይደለም የሚለው ዘይቤአቸው ማንንም አያታልልም። ስለዚህ አንድን አይነት ጭቆና ደምስሰው በሌላ ጭቆና ለመተካት ሳይሆን የመሳፍንቱን ሥርዓትና ኢምፔሪያሊዝምን ደምስሰው አዲሲቱን ኢትዮጵያ ለመመስረት የሚታገሉት ቆራጥ ተራማጆች በሙሉ የዚህን የንኡስ ከበርቴዎች እቅድ መደባዊ ይዘት ተረድተው ከመዋጋት አይቦዝኑም።