ሰሕድ ቁ. 56

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ቁጥር 56፣    ግንቦት 21፣ 1969 

የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ

በዚህ እትም፣ መኢሶን አብዮቱ ድል እንዲመታ ሰፊው ሕዝብ ለምን መንቃት፣ መደራጀትና መታጠቅ እንዳለበት ያብራራል። አሸናፊነቱንም ለማረጋገጥ፣ ሰፊው ሕዝብ በወዛደሩ መሪነት ሕዝባዊ ግንባር መገንባትና አብዮታዊ ሠራዊት ማቋቋም እንዳለበት ከተነተነ በኋላ ለአሸናፊነቱ ዋስትና ከዚህ ሌላ ምንም አማራጭ እንደሌለው ያስገነዝባል። በሰሜን ኢትዮጵያ የሚደረገው ዘመቻም ድል ሊያገኝ የሚችለው የኤርትራን ሕዝብ በመቀስቀስና በማደራጀት ከሕዝባዊው ጦር ጋር ተሰልፎ አድሃሪዎችንና ጣልጋ ገቦችን እንዲዋጋ ማድረግ ሲቻል ብቻ እንደሆነ ያሳስባል። ይህንንም ድል ለማረጋገጥ ቢሮክራሲው አዝማች መሆን እንደሌለበትና  ቢሮክራሲው ራሱ ላይ ሊዘመትበት ይገባል ይላል። 

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ለሰፊው ሕዝብ ሰራተኛ ገበሬ፣ ነጋዴ፣ ወታደር፣ ምሁር መብትና ጥቅም የሚታገል ጋዜጣ

የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ይቅደም

ቁጥር 56                                                                    ቀን 21/09/69

 

ቢሮክራሲው አያዝምት!  ይዘመትበት!

ከየካቲት በፊትም ሆነ ከየካቲት 1966 ወዲህ የኢትዮጵያ ተራማጆች ከፋፍሎ ብዙ ሲያከራክር የቆየ አንድ ዋና ነጥብ አለ። ይኸውም የኢትዮጵያን አብዮት መሰረታዊ ጠባይ የሚመለከት ነጥብ ነው። በአንድ በኩል መኢሶን ሲመሠረት ጀምሮ የቆመለትና የታገለለት መስመር አለ።  ይህ መስመር አብዮት የሰፊው ሕዝብ ተግባር ነው ይላል። አብዮት ሊሳካ የሚችለውም ሰፊው ሕዝብ በረጅም ጊዜ ቅስቀሳና ትግል ነቅቶ፣ ተደራጅቶና ታጥቆ ሕዝባዊ ዓመጽን ሲያካሂድ ብቻ እንደሆነ ያምናል። በሌላ በኩል ደግሞ ኢህአፓ ከመጀመሪያውም ከመኢሶን የተለየበትና ዛሬ በሰፊው ሕዝብ ተተፍቶ የተወረወረበት ሌላ መስመር አለ። ይኸ ደግሞ አብዮት የሰፊው ሕዝብ ተግባር መሆኑን አይቀበልም። አብዮትን ያለ ሰፊው ሕዝብ ተሳትፎ ከግቡ ለማድረስ፣ ድልን ያለ ሰፊው ሕዝብ ለመቀዳጀት ለረጅሙና ለመራራው ትግል የሌለ አቋራጭ ይፈልጋል። ካለሰፊው ሕዝብ ተሳትፎ ከሰፊው ሕዝብ ቀድሞ በስልጣን ላይ ለመውጣት የሚሻ የከሰረ የፖለቲካ መስመር በመሆኑ በአብዮቱ ሂደት ታልፎና ተተፍቶ ቀርቷል።

መኢሶን ከመጀመሪያው የቆመለት ይህ የአብዮታዊ መስመር ሃቀኛ መስመር መሆኑን ዛሬ ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዳር እስከዳር ተረድቶታል። ስለሆነም ከዳር እስከዳር “ለነቃ፣ ለተደራጀና ለታጠቀ ሕዝባዊ አመጽ” ብሎ ተነስቷል። ሰፊው ሕዝብ በአፋጣኝ እንዲነቃና እንዲደራጅ “ዴሞክራሲያዊ መብቶች ያለገደብ ለጭቁኖች” ብሎ ሳይንሳዊ መፈክሩን አንስቷል። ሰፊው ሕዝብ በአመፅ ጠላቶቹን እንዲደመስስ “ትጥቅ ለሰፊው ሕዝብ ወገኖች” ብሎ ዳር እስከዳር ተነሳስቷል። ዛሬ ተራማጆች በሙሉ ይህንን መስመር ተቀብለው፣ ሰፊውም ሕዝብ አምኖበት የአብዮታዊ ትግላችን መሪ መፈክር ቢሆን የኢትዮጵያ ጭቁን ሕዝቦች አብዮት ግቡን ሊመታ የሚችለው በነቃ በተደራጀና በታጠቀ ሕዝብ አመጽ ብቻ መሆኑን ቲዎሪ ብቻ ሳይሆን የትግል ልምዳችንም አበጥሮ ያሳየን ሀቅ በመሆኑ ነው።

ለብዙ አመታት በደሙና በመስዋዕትነቱ ያጠራቀመው የትግል ማእበል በየካቲት ወር 1966 ከፈነዳበት ወቅት አንስቶ ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዙና እጅግ ታላላቅ ድሎችን ተጎናጽፏል። እነዚህን ድሎች ለማግኘትም ሆነ ለመጠበቅ ሲታገል በንቃቱ፣ በድርጅቱና በትጥቁ ከእለት ወደ እለት እየዳበረ መቷል። ዛሬ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ወደ መጨረሻው ድል ተቃርቧል። ግን ደግሞ ዛሬ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ወደሕዝባዊት ኢትዮጵያ የሚያደርገው ጉዞ ረጅምና የተወሳሰበ እንደሚሆን መገንዘብም አለበት። አብዮታችንና እናት አገራችንን በውስጥም ሆነ በውጭ ወጥረውና አዋክበው የያዟትን ችግሮች ስንመለከት በእርግጥም ገና ብዙ ትግል፣ ብዙ መስዋዕትነት፣ ብዙ መውደቅ መነሳት እንደሚያስፈልገን መረዳት ይኖርብናል።

ወደሕዝባዊት ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ የምናደርገው ጉዞ ረጅም ጉዞ ነው ስንል ምን ማለታችን ነው? ትግሉ የረጅም ጊዜ ትግል ነው ስንል የአንድ አመት ትግል፣ የአስር ዓመት ትግል የሰላሳ ዓመት ትግል ብለን የጊዜ ገደብ ለመጠቆም አይደለም። ከውስጥ የሚቦረቡሩንና ከውጭ የከበቡን፣ የተሰበጣጠሩ ጠላቶች ዞሮ ዞሮ ከፊውዳሊዝም፣ ከኢምፔሪያሊዝምና፣ ከቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝም ጋር የተያያዙ ናቸው። እነዚህን ጠላቶች ደምስሰን በነርሱ መቃብር ላይ ኩሩና ነፃ የሆነች ሕዝባዊት ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመመስረት እንታገላለን። ይህን ግባችንን እንድንመታ ደግሞ የወዛደሩን ፓርቲ መመስረት፣ ሕዝባዊ አብዮታዊ ግንባር መገንባትና ሕዝባዊ አብዮታዊ ሰራዊት ማቋቋም አማራጭ የሌለው መከተል ያለብን ጎዳና ነው። በነዚህ ጠላቶቻችን ላይ የማያዳግም ድል ለመቀዳጀት ሰፊውን ሕዝብ ከዳር እስከዳር ማንቃትና ማንቀሳቀስ፣ በጠቅላላው ፀረፊውዳል፣ ፀረኢምፔሪያሊስትና ፀረቢሮክራሲያዊ ካፒታሊስት የሆኑ ኃይሎችን በፈርጅ በፈርጃቸው ማደራጀት፣ የተራማጆችን ህብረት አጠንክሮና ወደውህደት አሸጋግሮ የወዝአደሩን ፓርቲ መመስረት፣ በዚህ ፓርቲ አመራር ስር ሕዝባዊ አብዮታዊ ግንባር እንዲቋቋምና ሕዝባዊ ጦር ተገንብቶ የጠላትን ድርጅትና ጦር እንዲደመስስ ማድረግ ያስፈልጋል። ከዚህ ሌላ ምንም አይነት የትግል ዘዴ፣ ምንም አይነት አቋራጭ እንደሌለ አብዮታዊያን ሁሉ የሚገነዘቡት ነው። ይህ ደግሞ እንዲሳካ ከአብዮታዊያን ብዙ ትግልና ብዙ መስዋዕትነት፣ ብዙ ትዕግስትና ብዙ ታታሪነት የሚጠብቅ ትግል ነው። በዚህ ጎዳና ላይ ትንሽ ይሁን ትልቅ ማንኛውንም እርምጃ ከጠላቶቻችን ሳንታገልና ሳንዋደቅ ማግኘት አይቻልም። ትግሉ ረጅምና የተወሳሰበ የሚሆነውም ለዚህ ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ ይህንን ትግል ከግቡ ለማድረስ ትግሉ አብዮታዊ አመራር ያስፈልገዋል። ይህ ደግሞ ምን ማለት ነው? አብዮታዊ አመራር ያስፈልገዋል ማለት አብዮት ከግቡ እንዲደርስ የሚፈልግና ለዚህም በየወቅቱና በየሁኔታው ለስትራቴጂው የሚስማማ ታክቲክ እያወጣ መጓዝ የሚችል አመራር ማለት ነው። አብዮታዊው አመራር መሰረታዊ አላማው አብዮቱን ከግቡ ማድረስ ነው። አብዮታዊው አመራር አብዮት የሰፊው ሕዝብ ተግባር መሆኑን ያምናል። አብዮታዊው አመራር ያለ ሰፊው ሕዝብ የነቃ የተደራጀና የታጠቀ ተሳትፎ አብዮቱ በምንም አይነት ግቡን እንደማይመታ ያምናል። አብዮታዊ አመራር የሰፊው ሕዝብ ትግል እንደማይበገር ያውቃል። አብዮታዊ አመራር ዛሬ አገራችንን ወጥሮ የያዘው ማንኛውም ችግር ሊፈታ የሚችለው በጠቅላላው በአብዮቱ መግፋትና መሳካት እንጂ ብቻውን ተነጥሎ መፍትሄ የሚያገኝ ምንም ነገር የለም ብሎ ያምናል። አብዮታዊ አመራር ሰፊ ሕዝብ ከእለት ዕለት ይበልጥ እንዲነቃ፣ ይበልጥ እንዲደራጅ፣ ይበልጥ እንዲታጠቅ፣ በጠላቶቹም ላይ ይበልጥ እንዲያምፅ፣ ለመጨረሻውም ድል ይበልጥ ብቁ እንዲሆን ሌት ተቀን ይታገላል።

በአሁኑ ወቅት አብዮታዊት እናት አገራችንን ከየአቅጣጫው ቀስፈው የያዙትን ችግሮች ሁሉ መኢሶን የሚመለከታቸው ከላይ ከተተነተኑት ሃቆች አንፃር ነው። በዛሬው ወቅት የውስጥ አድሃሪ ኃይሎች በተለይ በቢሮክራሲ ውስጥ መሽገው አብዮታችንን በመቦርቦር ላይ ናቸው። በደቡብ ሶማሊያ ሰርጎገቦች ከጭቆን ገበሬዎችና ከመለዮ ለባሹ ጋር ከፍተኛ ትግል በማካሄድ ላይ ናቸው። ለጂቡቲ ነጻ ህልውና ማረጋገጫ ለመስጠት ያልፈለገችው የሶማሊያ ሪፑብሊክ ይቺን አገር በኃይል ለመያዝ እምብዛም ያልተሸፈነ ዛቻ እያካሄደች ትገኛለች። በሰሜን ኢትዮጵያ በአድሃሪ የአረብ መንግሥታትና በዓለም አቀፍ ኢምፔሪያሊዝም የሚረዳው የመሳፍንቱ ቡድን ኢ.ዲ.ዩ. ለማንሰራራት ከፍተኛ ሙከራ በማድረግ ላይ ከመሆኑም በላይ በኤርትራ ክፍለ ሃገር በውጭ እርዳታ የተጠናከሩ አንድነታችንን በመፈታተን ላይ ይገኛሉ። ነገር ግን ጠላቶቻችንን የተሰበጣጠሩ ይምሰሉ እንጂ ዞሮ ዞሮ ጠላቶቻችን ፊዳሊዝም፣ ኢምፔሪያሊዝም እና ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝም ናቸው። ለአብዮታችንና ለአንድነታችን ብለን የምናደርገው ዛሬ በምንም ዓይነት ሊነጣጠል የማይችለው ትግላችን እነዚህን ቀንደኛ ጠላቶቻችንን ለመደምሰስ የምናደርገው ትግል የማይነጠል አካል ነው።

ስለሆነም ዛሬ ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ የሚደረገው፣ ከጠቅላላው አብዮታዊ ትግላችን የማይለየው ትግል የረጅም ጊዜ ትግል እንደሚሆን ሳይታለም የተፈታ ነገር ነው። አብዮታዊያን ይህንን ሀቅ ተቀብለው በምንም አይነት ሊሸሹት የማይችሉት ኃላፊነታቸው ነው። በኤርትራ ክፍለሀገርም ሆነ በጠቅላላው በሰሜን ኢትዮጵያ ፀረአብዮትና ፀረአንድነት ኃይሎችን መደምሰስ የሚችለው የነቃ፣ የተደራጀና የታጠቀ ሕዝባዊ አመጽ ብቻ ነው። ስለሆነም የዘማቹ ሠራዊት ዋና ተግባር የአድሃሪዎችንና የጣልቃ ገቦችን አመጽ ተቋቁሞ እስከዛሬ እንዳይነቃና እንዳይደራጅ ታፍኖ ለቆየው ለኤርትራ ሰፊ ሕዝብ የመንቂያ፣ የመደራጃና ራሱም ታጥቆ ጠላቶቹን የመደምሰሻ ፋታ ለመስጠት ነው። በኤርትራ ክፍለ ሃገር የሚገኙ ሀቀኛ አብዮታዊያን ከአድሃሪዎች ጭፍጨፋ ተከላክሎ ሰፊውን የኤርትራ ክፍለሀገር ሕዝብ የማንቃትና የማደራጀት ተልዕኮውን እንዲፈጽሙ ለማስቻል ነው። ዘማቹን ሠራዊት ለዚህ አላማና ለዚህ የረጅም ጊዜ ተጋድሎ ብቁ ለማድረግ ከመጀመሪያ እስከመጨረሻው የትግሉን አብዮታዊ ይዘት፣ ማንን እንደሚዋጋ፣ ለምን እንደሚዋጋ የሚያስተምሩት፣ ከመከራውና ከመስዋዕቱ ባሻገር ድል የሰፊው ሕዝብ እንደሚሆን የሚያበስሩለት ካድሬዎች አብረውት ሊዘምቱ ይገባል። በመጨረሻም ትግል የጠቅላላው የአብዮታችን አካል እንደመሆኑ መጠን የጠቅላላው የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ያልተቋረጠ ተሳትፎ ያስፈልገዋል። ሰፊው ሕዝብ በትግሉ ውስጥ በሚገባ እንዲሳተፍ ዲሞክራሲያዊ መብቶቹ ያለ ገደብ እንዲለቀቁለት ያስፈልጋል። በያለበት ምርቱን ለማዳበር እንዲቻል መቀስቀስ አለበት። በያለበት የመደብ ትግሉን ማፋፋም አለበት። በያለበት ለዘማቹ ሰራዊት አስተማማኝ ደጀን መሆን አለበት። ትግሉ የረዥም ጊዜ ትግል የሚሆነው እነዚህን ሁሉ ተግባሮች አቀነባብሮ ከሥራ ላይ ማዋል አስፈላጊ በመሆኑ ነው።

እንደማንኛውም አብዮታዊ ትግል ይህም ዘመቻ አብዮታዊ አመራር ያስፈልገዋል የምንለው ለዚህ ነው። በመጀመሪያ ከቀንደኛ ጠላቶቻችን አንዱ የሆነውና ራሱ የሚዘመትበት አድሃሪው ቢሮክራሲ የዚህ ዘመቻ አመራር ሊይዝ አይችልም። አድሃሪው በቢሮክራሲ ቢበዛ የሚፈልገው የአጭር ጊዜ እና “ቴክኒካዊ” የሆነ መፍትሄ ነው። የረጅም ጊዜና ሰፊውን ሕዝብ አንቅቶ፣ አደራጅቶና አስታጥቆ የሚገኛውን ድል አድሃሪው ቢሮክራሲ ፈጽሞ አይሻውም። ይህ ማለት የአብዮቱ መሳካት ነውና። ስለሆነም አብዮታዊ አመራር የሕዝቡን የነቃ ተሳትፎ እንደ ዋና ነገር አድርጎ  የሚቆጥር አመራር ነው። ቢሮክራሲያዊ አመራር ግን የሕዝቡን ንቃትና መደራጀት እንደተቀጥላ አድርጎ ይቆጥረዋል። አብዮታዊው አመራር በጠቅላላው በሰፊው ሕዝብ ላይ እና በሰፊው ሕዝብ የነቃ ተሳትፎ ይተማመናል። ቢሮክራሲያዊ አመራር ግን በግንባር የተሰለፈው ዘማች ላይ እንጂ ሰፊውን ሕዝብ በመቀስቀስና በትግሉ በማሳተፍ አያምንም። አብዮታዊው አመራር የሰሜኑን ሕዝብ፣ በተለይም የኤርትራን ሰፊ ሕዝብ፣ በመቀስቀስና በማደራጀት ያምናል። ቢሮክራሲ ግን በዘማቹ ሰራዊት ብቻ የኤርትራን አድሃሪዎችንና የጣልቃገቦቹን ጦር ለመመልከትና ለመደምሰስ ይሞክራል። ባጭሩ አብዮታዊ አመራር ዘመቻውን ከረጅሙ ጊዜ የአብዮት ትግል ሳይገነጥል ይመለከተዋል። ለዚህም ራሱንም ሆነ ሰፊውን ሕዝብ አዘጋጅቶ በነቃ፣ በተደራጀና በታጠቀ ሕዝባዊ አመጽ ወደ ድል ለመሄድ በግንባር ቀደምነት የሚሰለፍ አመራር ነው። ቢሮክራሲያዊ አመራር የረጅም ጊዜ ተጋድሎ ለሚካሄደው፣ በሰፊው ንቃትና ድርጅት ለመተማመን ፍላጎቱም ችሎታውም የለውም።ራሱ የሚዘመትበት ጠላት በመሆኑ ዘመቻውን ለሱ አመራር መተው የማያምንበትንና የሚዋጋውን አብዮት ከሰፊው ሕዝብ ወገኖች አውጥቶ ለራሱ እንደማስረከብ ነው። ስለሆነም ውድቀትን እንጂ ድልን እንደማያስገኝ፣ የአብዮታችንና የእናት ሀገራችንን ህልውና ሊያስጠብቅ እንደሚችል የታወቀ ነገር ነው።

እንግዲህ ጥያቄው ይህንን አመራር ማን ሊሰጠው ይችላል? እንዴትስ ሊሰጠው ይችላል የሚለው ጥያቄ ነው። በአሁኑ ጊዜ ተራማጆች ራሳቸውን አጠናክረው ወደ ህብረት የተሸጋገሩበት ወቅት ነው። የወዛደሩ ፓርቲ እና የሕዝባዊ አብዮታዊ ግንባር በሌሉበት ሁኔታ፣ ይህንን አብዮታዊ አመራር ሊሰጡ የሚችሉ ህብረት ከፈጠሩ ማርክሲስት ሌኒኒስት ድርጅቶች የተውጣጡ ካድሬዎች ናቸው። እነዚህ ካድሬዎች ደግሞ ዝም ብለው በተበታተነ መልክ ተሳትፎ ሊበረከቱ አይችሉም። አብዮታዊያን የተወያዩበትና ጥራት ያለው መመሪያ ይዘው እሱን ተከትለው መስራት አለባቸው። ለዚሀም ደግሞ የመጨረሻውን ድል መጎናጸፍ የሚቻለው የሰፊው ሕዝብ ትግል ጠንካራና የማያወላውል አመራር ሲያገኙ

ስለሆነ ህብረታቸውን አጠንክረውና አመራር ፈጥረው ወደፊት ለመጓዝ ዝግጁ መሆን አለባቸው። የኢትዮጵያ ጭቁን ሕዝቦች አብዮታዊ ትግል ድል ዋስትናው ይሀው ብቻ ነው።

ለማጠቃለል ያህል፣

ሀ/ ትግሉ የረዥም ጊዜ ትግል እንደሚሆን ካሁኑ ተገንዝበን በዚሁ አንጻር ሰፊውን ሕዝብ በፖለቲካ፣ በርዕዮተዓለምና በድርጅት ማዘጋጀት፣

ለ/ ለዚህ ረጅም ትግል የሰፊው ሕዝብ ተሳትፎ ፍፁም አስፈላጊ መሆኑን በመገንዘብ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይበልጥ እንዲነቃ፣ እንዲደራጅ እና እንዲታጠቅ፣ ዲሞክራሲያዊ መብቶችን እንዲጠቀምባቸው ማድረግ እና በዚህም መንገድ የአብዮቱን መሰረት ማጠናከር፣

ሐ/ የውስጥ አድሃሪዎችን፣ በተለይም ደግሞ ቢሮክራሲውን፣ በሙሉ ቁጥጥር ስር ማድረግና

መ/ ለዘመቻው፣ ባለው የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ፣ አብዮታዊ አመራርን ማስገኘት ያስፈልጋል።

እነዚህን አስፈላጊ ነገሮች ለማሟላት ከታገልን የከበቡንም ፀረአብዮታዊ ኃይሎች የመቋቋም እና የመደምሰስ እድላችን ከፍተኛ እንደሚሆን መኢሶን ያምናል።

 
የነቃ፣ የተደራጀና የታጠቀ ሰፊ ሕዝብ ያሸንፋል!
አጫጭር ዜናዎች

ብዙሃን የኢትዮጵያ ሴቶች በአብዮት ውስጥ ያላቸውን ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍ እያደረጉ መጥተዋል። በተለይም በዚህ በያዝነው ዓመት በአብዮት ውስጥ ገለልተኛ ሚናቸውን ይዘው እንደማይቆዩ እያስመሰከሩ ነው። በየካቲት 23 ዓለምአቀፍ የሴቶች ቀንም ይህንኑ አስመስክረዋል።

ሚያዝያ ወር 1969 የኢትዮጵያ ሴቶች አብዮታዊ ንቅናቄ በሚል መጠሪያ ስም ተራማጅ ሴቶች መርሃ-ግብራቸውን በይፋ አውጥተዋል። ሴቶች በተደራጀ፣ በተቀነባበረና አላማ ባለው ትግል ውስጥ ለመሳተፍ የሚያደርጉት ቆራጥ ተጋድሎ የሚደገፍ ነው። ሕዝባዊ ድርጅቶች እንዲያብቡ መኢሶን እስካሁን የማያቋርጥ ትግል አድርጓል፤ ወደፊትም ያደርጋል። በኢ.ሴ.አ.ን አካባቢ የተደራጁትን ጓዲቶች መኢሶን በርቱ እያለ በፀረፊውዳል፣ ፀረ ኢምፔሪያሊስትና ፀረ ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊስት ጎዳና ሴቶችን ለማሰለፍ የሚያደርጉትን ትግል እንደራሱ ትግል አድርጎ የሚወስደው መሆኑን ያረጋግጥላቸዋል።

***

በድርጅታችን ላይ ፀረ ሕዝብ ኃይሎች ዘመቻ ማድረግ ከጀመሩ ቆይተዋል። በዚሁ ዘመቻቸውም በፕሮፖጋንዳ ሳይወሰኑ ብዙ የመኢሶን አባላትንና ደጋፊዎችንም ገድለዋል፤ አሁንም በመግደል ላይ ናቸው። ሰሞኑን የኦምዱርማን ራድዮ ጣቢያ በአማርኛ በሚያስተላልፈው ፕሮግራም ውስጥ ማእከላዊው አርዕስት መኢሶን ሆኗል። የኢዲዩ አድሃሪዎችን ለመጀመሪያ እንዲያውም ግልጽ የሆነ ሶሻሊስት ፕሮፖጋንዳ ለማካሄድ ሞክረው ነበር። ቅስቀሳቸው እዚህ ይህን ያህልም ተቀባይነት እንዳላገኘ ስለደረሱበት አሁን ይዘቱን ለውጠዋል። የኢ.ዲ.ዩ. ሬዲዮ ጣቢያ መኢሶንን ከሚከስባቸው ነጥቦች ዋና ዋናዎቹን ብንመለከት የወዛደሩን ርእዮተዓለም ይበርዛል፣ የወዛደሩን ድርጅት ያዳክማል ወዘተ የሚሉ ናቸው። በአጠቃላይም የመላው ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ የሚያካሄደቸው ተግባሮች ፀረ ሶሻሊስት ናቸው ነው። አንዳንድ የመኢሶን ደጋፊዎች ናቸው ተብለው የሚጠረጠሩትን ሰዎች ስም እየጠቀሰም የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደሚፋረዳቸው ይናገራል ።

አድሃሪያን በሕዝብ ድርጅት ጉዳይ ጊዜያዊ ጽ/ቤት ላይ እና በመኢሶን ላይ የሚያደርጉት ዘመቻን ፀረ አብዮት ኃይሎች በአብዮታዊያን ላይ የሚያደርጉት ዘመቻ መሆኑ ግልጽ ነው። ስለሆነም ኢ.ድ.ህ መኢሶንን ቢጠላው አይገርመንም፣ ቢወደው ነበር እንጂ! ዘመቻው ወደፊትም መቀጠሉ የማይቀር ነው። ግን መኢሶን በጠላት መጠቃትን እንደመጥፎ ነገር አይቆጥረውም። ጠላትን ካስቆጣ በሰፊው ሕዝብ ሰፈር መቆሙ ተረጋገጠ ማለት ነውና። 

***

በአውሮፓ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማህበር የኢትዮጵያ ማርክሲስት ሌኒኒስትቶች ባወጡት የጋራ መግለጫና የጋራ መርሃ-ግብር ላይ አንድ መግለጫ በ11/4/77 እ.አ.አ. አውጥቷል። በመግለጫውም ውስጥ፡-

“በአውሮፓ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማህበር ከረጅም ጊዜ አንስቶ የኢትዮጵያ ተራማጆዎች የትግል ህብረት እንዲፈጥሩ፣ የጋራ ጋዜጣ በማውጣትም ዲሞክራሲያዊ ውይይትና ክርክር በማድረግ በጠራና ትክክለኛ የፖለቲካ መስመር ላይ ውህደትን ፈጥረው የወዛደር ፓርቲ እንዲፈጥሩ ታግሏል። የማያቋረጥ ቅስቀሳና ጥሪ አድርጓል አሁንም በዚህ መንገድ ይታገላል”

ይልና መኢሶንና ህብረቱን በሚመለከት ደግሞ መኢሶን ለዚህ ህብረት መፈጠርና መጠንከር ያደረገውንና የሚያደርገውን ተጋድሎ እያደነቀ አድሃሪዎቹ ተራማጅ ኃይሎችን መከፋፈልና መኢሶንን ብቸኛ ለማድረግ የሚሸርቡትን ሲራና አንዳንድ ቡድኖች እና ግለሰቦችም “መኢሶን ተስፋፋ፣ መኢሶን ከሌሎች ተራማጅ ድርጅቶች ጋር አንድነት ለመፍጠርም አይፈልግም፣ መኢሶን አራሹን የወዛደር ፓርቲ ለማድረግ ይጥራል ወዘተ… በማለት የሚያቀርቧቸው ክሶች መሰረተ ቢስ መሆናቸውን ይገልፃል። ቀጥል አድርጎ፣ መኢሶን ከረጅም ጊዜ አንስቶ የታገለለት የተራማጆች ህብረት መፈጠር ለመኢሶን ሆነ ለሌሎች የህብረት ድርጅቶች ትልቅ ድል መሆኑን፣ ከቀኝም ሆነ ከ“ግራ” በመኢሶን ላይ የተሰነዘሩበተን መሰረተ ቢስ ክሶች ለማክሸፍና የመኢሶን ለእውነተኛ የተራማጆች አንድነትና አብዮት የሚታገል ማርክሲስት-ሌኒኒስት ድርጅት መሆን እንዳስመሰከረ ይገልፃል።

ቀደም ሲል በአውሮፓ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማህበር በ16ኛ ዓመታዊ ጉባኤ፣ የተባበሩ የተራማጅ ኢትዮጵያውያን ማሕበር በሰሜን አሜሪካ የመጀመሪያው ጉባኤ ላይ እና በአውሮፓ የኢትዮጵያ ሴቶች ዲሞክራሲያዊ ማህበር አምስተኛ ዓመታዊ ጉባኤ ላይ በተላለፉት ውሳኔዎች ውስጥ እነዚህ ማህበራት ለመኢሶን ድጋፋቸውን በመስጠት የመኢሶንን አቋም ለአለም ተራማጆች እንደሚያስተጋቡ ማረጋገጣቸው የሚታወስ ነው።

Scroll to Top