የሰፊው ሕዝብ ድምፅ
ቁጥር 72፣ ሜይ ዴይ፣ 1972
የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ
መኢሶን በዚህ እትም፣ በ1972 ዓ.ም. ሜይ ዴይ ሲከበር፣ ወዛደሩ እና የኢትዮጵያ ሕዝቦች ባለፉት አመታት ያጋኟቸውን ድሎች፣ በስማቸውና በርዕዮተ ዓለማቸው ስም በሚመጻደቁ ቢሮክራቶችና አድሃሪዎች እንደተነጠቁ፣ በርካታ ኢትዮጵያውያን በእስር እንደሚማቅቁና በሚልዮን የሚቆጠሩ በረሃብ አለንጋ እየተገረፉ መሆናቸውን በማሳየት ይጀምራል። ሠራተኛው በስንት ትግልና መስዋዕትነት ያገኘው የሠራተኛ አዋጅ በየጊዜው በተለያዩ መመሪያዎች እንደተሸረሸረና በገጠርም አርሶ አደሩ ከአቅሙ በላይ የሆነ ግብር እንዲከፍል እየተጠየቀ መሆኑ፣ እንዲሁም “ለመንግስት እርሻ ያስፈልጋል” እየተባለ ከሚያርሰው መሬት መነቀሉንና ማለቂያ ለሌለው ጦርነት አሁንም ልጆቹን ለውትድርና አቅርብ እየተባለ መዋከቡን በሰፊው ይዘረዝራል። በማጠቃለለም አሁንም ከአምስት ሚሊዮን ሕዝብ በላይ በረሃብ እየተጠቃ መሆኑን አመልክቶ፣ ሕዝቡ አቅሙ በፈቀደው መጠን የተራቡ ወጎኖቹን እንዲረዳ፣ በውጪ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከሚያደርጉት እርዳታ ባሻገር የረሃቡን ሁኔታ ለአለም ሕዝቦች በማስተዋወቅ የእርዳታ እንቅስቃሴዎችን እንዲያስተባብሩና ከውጪ መንግስታትና ድርጅቶች የሚገኘው እርዳታ ለመሳሪያ መግዣ ሳይውል በቀጥታ ለተጎጂ ወገኖቻችችን እንዲደርስ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው ያሳስባል።
የዛሬዎቹ የወዛደሩ መደብ ጠላቶች፣ የ1972 ሜይ ዴይን ሲያከብሩ እነርሱ ለእነርሱ ባቋቋሙት ስመጥፉ “ኢሰፓአኮ መመስረት ማግስት ነው” እያሉ እየተኩራሩ ነው። እነሱ ምክንያት አላቸው። በወዛደሩና በሰፊው ሕዝብ ላይ ፈላጭ ቆራጭ አገዛዛቸውን በማደላደል በሚውረገረጉበት ወቅትና በመጨረሻው የጣረሞት አልጋቸው ላይ በመሆናቸው ነው። የኢትዮጵያ ወዛደር ግን ዘንድሮ ሜይ ዴይን ሲያከብር ከሰማይ በታች ከፍ የሚባሉ ነገሮች በመላ ኢትዮጵያ ላይ በወረዱበት ሰዓት በመሆኑ የእነርሱን መዝሙር የሚያደምቅበት አንዳችም ምክንያት የለውም።
የኢትዮጵያወዝአደር የዘንድሮውን ሜይ ዴይ ሲያከብር፣ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የእርሱ ወገኖች በአዲሶች ፈላጭ ቆራጮች ይታሰራሉ፣ ይገረፋሉ። አያሌ ወገኖቹ ይጨፈጨፋሉ ይረሸናሉ። በሚሊዩን የሚቆጠሩ ወገኖች በረሃብ ይገረፋሉ። በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠሩ ወገኖች ይሰደዳሉ፣ የኢትዮጵያ ወዛደር የ1972 ሜይ ዴይን የሚያከብረው ጥርሱን ነክሶ እንጂ አንዳችም የሚኩራራበት ጉዳይ ኖሮት አይደለም።
የኢትዮጵያ ወዛደር የዘንድሮውን ሜይ ዴይ የሚያሰበው፣ የኢትዮጲያ አብዮት በ1966 ከገነፈለበት ጊዜ አንስቶ አንዳችም ፋታ ሳያገኝ አብዮታዊ እንቅስቃሴውን ካካሄደ በኋላ፣ ያገኛቸው ከፍተኛ ድሎች እንዳልሆኑ ሆነው፣ በተከታታይ ባለፉት ሁለት አመታት ምድረ ቢሮክራትና አድርባዩች ፈንጭተውበት ዛሬ በእግራቸው የቆሙ መስሏቸው በሚንገዳገዱበት ወቅት ነው። የኢትዮጵያ ወዛአደር የዘንድሮውን ሜይዴይ የሚያከብረው፣ የመራራ ትግሉ ፍሬን የተነፈገበትና በርሱ ስም የሚነግዱ የፖለቲካ አመንዝሮች የሥራ ፍሬውን በሚያቆርጡበት፣ በሚበሉበትና በሚደልሉበት ወቅት ነው። እርሱ ወደ ችጋር አፋፍ፣ ሰፊው ሕዝብ በሚሊዮን ወደ ረሃብ መዓት የሚጓዝበት የከፋ ሀቅ ነው። ይህም ሆኖ ግን ዛሬ የዘንድሮን ሜይ ዴይ የኢትዮጵያ ወዛደሮችና ሕዝቦች ሲያከብሩት፣ የዛሬዎቹ ጠላቶች በሚያካሄዱት መረን የለቀቀ ጭቆናና ግፍ የተነሳ፣ “ቀን እስኪያልፍ ቅዝምዝምን አጎንብስ” እያሉ በችጋርና በረሃብ የጠወለገውን አንጀታቸውን አስረው አንገታቸውን ማቀርቀር ተገደው ነው። ይሁንና፣ የታመቀው ተቃውሟቸውም እንዳለ እስከሚገነፍልበት ጊዜ ድረስም ውስጥ ውስጡን እንደሚብላላ ጠላቶቻቸው ሊያውቁት ይገባል። ያውቁታልም።
ሜይ ዴይ በ1889 ዓ.ም ታላቅ የወዛደር በዓል ሆኖ በዓለም የወዛደሮች ቀን መከበር ከጀመረበት ቀን አንስቶ ከፊሉ የአለም ወዛደሮች ይህን ዕለት የሚያከብሩት ያለፈውን ቆራጥ ተጋድሏቸውን በኩራት እያሰቡ፣ በተጎናፀፏቸው ድሎች እየተመኩ ነቅተው እየጠበቁ ለሶሻሊዝምና ለበለጠ የወደፊት ብሩህ ጊዜያቸው ትግላቸውን እያራመዱ ነው። ከፊሉ ደግሞ፣ ወደኋላ አሻግረው የትግል ጉዟቸውን ሲያዩ አያሌ የሚያኮራቸው ተጋድሎዎች ማካሄዳቸውን ቢያውቁም፣ ገና ብዙ እንደሚቀራቸው ያስተውላሉ። በአለፈው ትግላቸው ጠላቶቻቸውን አርበድብደው ወደፊት እየተራመዱ ቢገፉበትም፣ ዛሬ የሚገኙበት የበዝባዥን ሥርዓት ከስሩ መንግለው የወዛደሮች የምትሆነውን ዓለም ገና እንዳልመሰረቱ እያሰቡና እያጤኑ ነው። የለየላቸው የመደብ ጠላቶቹ ባንድ ፊት፣ በዛው ፊት ደግሞ የለየላቸው የመደብ ጠላቶቹ ቢሆኑም፣ በርሱ ስም የሚነግዱ፣ በርሱ ስም የፖለቲካ ስልጣን ጨብጠው ሳይንሳዊ የትግል መመሪያውን በርዘውና ከልሰው በቀይ ካባ ያጌጡና የተመላለጡ አዲስ መጥ ጠላቶቹ ፀረ- አብዮትና ፀረ- ወዛደር አመፃቸውን እያወረዱበት መሆኑንም ወዛደሩ እያወቀ ነው። በተለይም ባለንበት ክፍለ ዘመን መጨረሻ፣ አለም አቀፍ የወዛደሮች የሶሻሊስት እንቅስቃሴ እየተጠናከረ የመምጣቱን ያህል፣ እነዚህ ቀይ ካባ ያጠለቁ ጠላቶችም ፈልተዋል። እነዚህ ከአፋቸው ቅቤ ከግብራቸው መርዝ የሚተፉት አወናባጅ የፖለቲካ ነጋዴዎችም እየረቀቁና እየረቡ መጥተዋል። የዓለም ወዛደሮች ደግሞ ባልተመረዘው በሳይንሳዊ የማርክሲዝም የቲዎሪ መሳሪያቸው ገመናቸውን እያጋለጡ ገና ለረዥም ጊዜ ማካሄድ ያለባቸው የረቀቀ የመደብ ትግል ውስጥ እንደሚገኙ ያውቁታል።
የኢትዮጵያ ወዛደርም የሚገኘው የኋለኞቹ የአለም ወዛደሮች በሚያካሄዱት ትግልና፣ በአንጻሩም ደግሞ የጭቆናና የብዝበዛ ሁኔታ ውስጥ ነው። እንደሌሎቹ የአለም ወዛደሮች የኢትዮጲያ ወዛደርም በ1972 ሜይ ዴይ ሲያከብር በርሱ አብዮታዊ ቲዎሪ የሚነግዱ፣ በርሱ ስም ስልጣን ላይ የተፈናጠጡ፣ በርሱ ስም ስልጣናቸውን ለማደላደል ለሚውገረገሩ፣ በርሱ ስም በሚበሉ፣ በሚደልቡ፣ አዎ በእርሱ ስም እርሱን መስለው የወዛደሩ የሆነውን የወዛደር ቀንንም አብረው በማክበር በሚያስመስሉ ከለየላቸው የመደብ ጠላቶችም ጋር ትግል ውስጥ እያለ ነው።
የኢትዮጵያ ወዛደር ዛሬ ሜይ ዴይን የሚያስበው፣ የርሱና የአጋሮቹ ሰብዓዊ መብቶች በተረገጡበት አስከፊ ሁኔታ ውስጥ እያለ ነው። የኢትዮጵያ ወዛደሮች ቀድመው ሲያካሂዱ በነበረው ትግል ውስጥ ተገርፈዋል፣ ታስረዋል፣ ተረሽነዋል፣ ተጨፍጭፈዋል፤ ዛሬም በዛሬዎቹ ጠላቶችም ምናልባትም ፋሽስታዊ አገዛዝ ሰፍነውባቸዋል ከሚባሉባት አገሮች ጋር ብቻ ተወዳዳሪ በሚገኝለት አኳኋን እየተረገጡ ናቸው። በተለይ ካለፉት ሦስት ዓመታት ጀምሮ የትግል ፍሬያቸውን ላለማስነካት ሲሉ የተጨፈጨፉትና ያለቁት በሺህ እና በብዙ መቶ የሚቆጠሩ መሆናቸው የታወቀ ነው። ዛሬ የታሪክ አተላ በሆኑ የቀኝ አደርባዮች ፊትአውራሪነት በአዲስ አበባ፣ በናዝሬት፣ በመተሀራ፣ በጐንደር፣ በድሬደዋ፣ በባህዳርና በአስመራ ወዝአደሮች ላይ የደረሰው ግፍ የዛሬዎቹን ፀረ-ወዝአደሮች የኢ-ሰብአዊነት ምልክት ያኖረ በመሆኑ ምንጊዜም የማይረሳ ነው። ፍጹም ኢ-ሰብአዊ በሆነ መንገድ የተገረፉ፣ መላ ገላቸውን በነዳጅ እሳት የተቃጠሉ፣ እንደከብት ሥጋቸው በላያቸው ላይ ነፍሳቸው ሳትወጣ የተዘለዘለ፣ አይናቸውን በጉጠት የተሸነቆረ፣ ብልታቸውን በጋለ ብረት የተጠበሱ፣ እንደ ከብት በየቦታው ታርደው የቀሩ በብዙ መቶ የሚቆጠሩ ሰማእታት ታጋይ ወዝአደሮች የሚታወሱ ናቸው። በዚያው መጠን ደግሞ በዛሬዎቹ አምባገነኖች ላይ፣ የመደብ ጥላቻችንን የሚቀሰቀስብን እነርሱ ያነገሱት ኢ- ሰብአዊነት።
የኢትዮጵያ ወዛደር ዛሬ ሜይ ዴይን የሚያስበው በሰፈነው ኢ-ሰብአዊነት የመኖር መብቱን ተገፎ ብቻ ሲሆን፣ ኢ-ሰብአዊነትን ያነገሰ ባርነትንም መጋበዙ ስለማይቀር፣ በከፊልም ቢሆን መብቱንና ጥቅሙን አስከብሮ የነበረው ወዝአደሩ በትግሉ ያገኘው የሠራተኛ አዋጅ በመሻር በመደለዝና በመሰረዝ ላይ ባለበት ወቅት ነው።
የሠራተኛው አዋጅ በከፍተኛ ተጋድሎ የተገኘ አብዮታዊ ድል መሆኑ የሚያጠራጥር አይደለም። ይህም ሆኖ ግን ወዝአደሩ የፖለቲካ ሥልጣን በእጁ እስካላስገባ ድረስ መብቱን ሙሉ ለሙሉ ለማስከበር ያስቸግረዋልና፣ የሠራተኛውም አዋጅ የወዛደሩን መብትና ጥቅም ሙሉ ለሙሉ ያሟላ አልነበረም። ይሁን እንጂ፣ የተነጠቀን መብት እየተጠቀሙ ላልተገኘ ድል ጠላቶችን ማፋጠጥ አብዮታዊ የወዛደር የትግል ታክቲክ በመሆኑ፣ ታጋይ ወዝአደሮች ከዛሬ አራት አመት በፊት ታውጆ የነበረውን የሠራተኛ አዋጅ ተቀብለው የትግላቸው ማሳሪያ አድርገውታል። መኢሶንም፣ ከኢትዮጵያ ወዛደሮች ጋር በመሆን በግንባር ቀደምትነት በሚያካሂደው ትግል ውስጥ፣ የአዋጁን ድክመት በአንድ በኩል እያጋለጠ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የተገኘውን መብት ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ በወቅቱ መሟገቱ የታወቀ ነው። የሠራተኛው አዋጅ ከነበሩት ጉድለቶች ውስጥ አንዱን ዋነኛውን ብንወስድ፣ የትግል መሳሪያ ሆነው የሥራ ማቆምን መብት የሚነፍግ ከመሆኑም በላይ፣ በአጠቃላይ ወዛደሩ መብቱን ለማስጠበቅ ሊያካሂድ የሚችላቸውን ትግሎች ይወስናል። ያም ሆነ ይህ ዛሬ ደግሞ እንኳን ያልተሟሉት ሊሟሉ ይቅርና፣ በአዋጁ ተገኝተው የነበሩት የመደራጀትና ጥቅምን የማስጠበቅ መብቶች በዛሬዎቹ ገዢዎች በውስጥ መመሪያ እየተሻሩ ናቸው። ዛሬ በውስጥ መምሪያ እየተሻረ ነገ ደግሞ በአዋጅ ሊሸረሸር ሽር ጉድ እየተባለ ነው።
ይህ የቅልበሳ እርምጃ በሚኒስቴሮቻቸው ምክር ቤት በነሐሴ 1971 ይፋ ውይይት ተካሂዶበት የፀደቀ ከመሆኑም በላይ፣ ዛሬ ወደ ማጠናከሪ አዋጅነት እያደገ ነው። “የሠራተኛው አዋጅ ማጠናከሪያ” የሚል ስም ተለጥፎበት፣ ወዛደሩን ወደባርነት የሚያሽቆለቁል አዋጅ መርቀቁ የአደባባይ ሚስጥር ነው። የሚጠበቀው አመቺ ሁኔታና ጊዜ ብቻ ነው።
የተባለውም ‘የውስጥ መመሪያ’፣ አዋጁ በይፋ እስኪሻር ድረስ በጊዚያዊነት እያገለገለ፣ ወዝአደሩ በታገለ እንዳልታገለ፣ ባመረተ እንዳላመረተ፣ ለአብዮቱ ሲል ሚስቱን ልጆቹንና ቤተሰቡን በሞላ እንዳላስራበ፣ እንዳላሳረዘ ሁሉ፣ የትግል ፍሬውን እንዳይቀምስ እየተደረገ ነው። ሌላ በላተኞች፣ የርሱን ፍሬ ሰብሳቢ ሌሎች አዲስ ወጥ ተባዩች አሉበትና፡ በዚህ መመሪያ መሠረት፣ ለኢትዮጵያ ወዛደር የደመወዝ ጭማሪ ላልተወሰነ ጊዜ እንዲታገድ ሆኗል። ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ መንገድ፣ እያንዳንዱ ድርጅት ወደ ኋላ ሁለት ዓመት ተመልሶ ማትረፉን ማረጋገጥ አለበት። ወደፊትም ካላተረፈ የደመወዝ ጭማሪ ማግኘት ይቅርና፣ “ኪሣራውን” ለማሟላት ትርፍ ሰዓት ያለ ክፍያ እንዲሰራ ሁሉ የሚያደርግ ድንጋጌ ነው። ባለፉት ሁለት ዓመታት ምርት አላሳደክም ማለት ደግሞ ለአብዮትህና ለእናት አገርህ ደምህን አላፈሰስክም ከማለት የተለየ አይደለም። ወዝአደሩ በአንድ በኩል ከውጭና ከውስጥ አድሃሪዎች ጋር እየተናነቀ፣ በሌላ በኩል ደግሞ በቀረው አቅሙና ጉልበቱ፣ ምርቱ ጨርሶ እንዳይንኰታኰት ያደረገውን ተጋድሎና የከፈለውን መስዋዕትነት ጨርሶ መካድ ነው። አዲሶቹ በላተኞች በየመግለጫዎቻቸው “ኢምፔሪያሊዝምና የሱማሌ ተስፋፊ ገዥ መደብ፣ የአረብ ደላሎች ወዘተ ባካሄዱብን መራራ ትግል የተንኰታኰተውን ኢኮኖሚያችንን ለመገንባት ተነስና ታጠቅ. . .” እያሉ ባንድ በኩል በይፋ ሲለፍፉ በሌላ በኩል ደግሞ በውስጥ፣ መመሪያቸው “…ባለፉት ሁለት ዓመታት ማትረፉን ካላረጋገጠ. . .” ማለታቸው ፍቺው አንድ ነው። “ሊበሉት የፈለጉትን ቁራ ጅግራ ይሉታል” እንዲሉ፣ በጠቅላላው የኢትዮጵያሰፊ ሕዝብ በተለይም ወዝአደሩ በዚሁ የትግል ወቅት ያካሄደውን መራራ ትግልና የከፈለውን ከፍተኛ መስዋእትነት ሸምጥጥ አድርጐ ክዶ፣ ከተባሉት ጠላቶች ላለመለየትና ጉልበቱን ለመጋጥ የሚያውጠነጥኑት ሴራ መሆኑ ለማንም የሚሰወር አይደለም። አዎ የኢትዮጵያወዝአደር ከፍተኛ የአብዮትና የፀረ-አብዮት ትንቅንቅ ላይ በነበረበት ወቅት ያመረተውም የፀረ-አብዮት ደምና አጥንት ነበር፣ በአኳያው ደግሞ ያተረፈው የርሱን መስዋእትነት ነበር። ያኔ ካላተረፍክ ብሎ ነገር ደግሞ፣ የዛሬዎቹ ፀረ-ወዝአደሮች ፀረ-አብዮተኛነት መግለጫ ነው።
የፀረ-አብዮትና የአብዮት ትንቅንቅ በሚጧጧፍበት ወቅት፣ ወዝአደሩ ትግሉን በሁለት አቅጣጫ ማካሄድ እንዳለበት የታወቀ ነው። በምርትና በአብዮት ላይ። አንደኛው በአንዱ ላይ፣ ሌላው በሌላው ላይ እየተፈራረቀ፣ ትግሉን ከምርቱ ጋር ሲያቀናጅ ደግሞ፣ እንደሁኔታው አንዱ የበለጠ ሊያመርት፣ ሌላው ሊከስር፣ ሌላው ይበልጥ ሊታገል ይበልጥ ሊሰዋና አንደኛው እንደገና ይበልጥ ሊያመርት ይቻላል። በተጨማሪ፣ “በዘመቻው” ሳቢያ ኢኰኖሚው 5.2 በመቶ አድጓል ተብሏል። የኢንዱስትሪውም ምርት ከ32.5 በመቶ በላይ እንደጨመረ ተነግሯል። ይህ ከሆነ ደግሞ አላተረፍክም የደሞዝ ጭማሪ አታገኝም ማለትን ምን አመጣው? ባለፉት ሁለት አመታት ላተረፈ ብቻ “የደመወዝ ጭማሪንስ” ምን ፈጠረው? ወዝአደሩ በአጠቃላይ እንዳለ ባለበት የዱር ሲቃ ውስጥ ተዘፍቆ እንዲቀር ለማድረግ የተጠነሰሰ የዛሬዎቹ “ጮሌ” ገዢዎች ዘዴ መሆኑ ነው። ሌላ ሊሆን አይችልም። ለነገሩማ እነርሱ ያላመረቱትም ያልታገሉትም ነበሩ፣ በየሰዓቱ በሹመትና በማዕረግ ስም የኢትዮጵያወዝአደሮችን የምርት ፍሬ የሚያግበሰብሱት።
ትርፍ አስገኙ ለሚባሉት ድርጅቶችም እንኳን ለወዛአደሩ የሚሰጠው “ጭማሪ” የፀጉር ስንጠቃ የይስሙላ ስሌት ተካሂዶ ከ5 በመቶ እንዳይበልጥ ተደንግጓል። እንግዲህ ይህም በተግባር የተተረጐመ ከሆነ ነው።
በዚህ ላይ ደግሞ፣ የዛሬዎቹ ገዢዎች ከአፋቸው የሚተፉት መርዝ ለከት አጥቷል። ባለፉት አመታት ለአብዮቱ ሲሉ በችጋር ተቆራምደው አብዩቱን ሲጠብቁ የቆዩት ወዝአደሮች፣ በችጋር ቤተሰቦቻቸውን እየቆሉ ሲታገሉ የኖሩት ወዝአደሮች፣ ዛሬ ያኔ አላመረታችሁም፣ ያኔ አላተረፋችሁም ይባሉ የገቡትና ‘የሚቀጡት’ የኢትዮጵያ ወዝአደሮች ይባስ ተብለው በከበርቴነት መወንጀል ከጀመሩ ሰንብተዋል። በፊቱንም እንዳይሆን ነውና፣ ‘ለኢኮኖሚው ዘመቻ’ የሚደረግ ስብከት ወደ ወዝአደሩ ላይ የሚደረግ የቢሮክራሲው ዘመቻ ተቀይሯል። የኢትዮጵያ ወዝአደርም እነርሱን ባደለበና ባጠገበ፣ በተቃራኒው ‘በዝባዥ ወዝአደር’ ‘የወዝአደር ከበርቴ’ ሆኗል በዚሁም ምክንያት፣ ዛሬ በእስር ፍዳቸውን የሚያዩ፣ በምርት ላይም ለመብታቸው አንገታቸውን ቀና ያደረጉ እንደሆነ እዚያው ሊቀበሩ የተበየነባቸው ከዳር እስከዳር የሚገኙት መላ የኢትዮጵያ ወዝአደሮች ናቸው።
በዚህ ላይ፣ ለሜይ ዴይ መከበር ምክንያት የሆነው የዓለምና የታሪካዊው የ1885ቱ የአሜሪካ ወዝአደሮች ንቅናቄ አይነተኛ የትግል ጥያቄ፣ የስምንት ሰዓት የሥራ ቀን ተሽሯል። የዓለም ወዝአደሮች በመጀመሪያው የኰሚዩኒስት ኢንተርናሽናል በበለጠ ተደራጅተው፣ በ1866 ዓ.ም. ከተላለፈው ውሳኔያቸው አንስቶ አንዱና ዋነኛ ተጋድሎአቸው፣ ስምንት ሰዓት የሥራ ቀንን ለማስከበር እንደነበር ግልጽ ነው። በተለይ ደግሞ ሜይ ዴይ በየአመቱ እንዲከበር በ1889 ከተወሰነበት ጊዜ ጀምሮ፣ የዓለም ወዝአደሮች ይህ የስምንት ሰዓት የሥራ ቀን እንዲጠበቅ ትግላቸውን ሲያፋፉሙና ሲዋደቁ ቆይተዋል። ይህንን መብታቸውንም መስዋአት በተመላበት ተጋድሎአቸው አማካይነት፣ ዛሬ በናጠጡ ካፒታሊስት አገሮች ሳይቀር አስከብረዋል። ሜይ ደይ በሚከበርባት በዛሬዋ ኢትዮጵያ ግን፣ ይህ የሜይ ዴይ አይነተኛ የትግል ጥያቄ የነበረው የስምንት ሰዓት የሥራ ቀን ተረግጧል። ራሳቸውን “ኮሚኒስትና ሶሻሊስት” እያሉ በሚያሞካሹት አስመሳዩችና ፀረ ወዝአደሮች፣ በሠራተኛው አዋጅ ውስጥ አንድ ወዝአደር በቀን ከስምንት ሰዓት በላይ እንዲሰራ እንደማይገደድ የተመለከተው ተደልዞ፣ የኢትዮጵያወዝአደሮች የዓለም ወዝአደሮች ያለፉትን የአንድ ክፍለ ዘመን የደም ጉዞ የኋሊት እንዲሄዱ ተገደዋል።
የሠራተኛው አዋጅ እንደሚያዘው፣ አንድ ወዝአደር ከስምንት ሰዓት በላይ ለመሥራት ፈቃደኛ ካልሆነ አይገደድም። ፈቃደኛ ከሆነም የትርፍ ሰዓት ክፍያ እንደሚደረግለት ይደነግጋል። የትርፍ ሰዓት ክፍያ ደግሞ እንደውነቱ ከሆነ፣ ባለፈው ስርዓት ውስጥ የነበሩ አንዳንድ የኢምፔርያሊስት ድርጅቶች እንኳን የሚያከብሩት ጉዳይ ነበር። ይሁንና፣ በዛሬዎቹ ፀረ ወዝአደሮች፣ ዛሬ አዋጁም በጫማ ተረግጦ፣ ይባስ ተብሎም ያለምንም እረፍት “በኢኰኖሚው ዘመቻ” ሰበብ፣ የኢትዮጵያወዝአደር በቀን አስራ ሁለት ሰዓት ቅዳሜንና እሁድን ጨምሮ በአፈሙዝ እንዲሠራ እየተገደደ ነው። የኢትዮጲያዮጵያን ኢኰኖሚ ለማሳደግ ደግሞ፣ “ዘመቻ” ቢሉት ሌላ፣ በወንድማማች ሕዝቦች መካከል የሚካሄደው እልቂት ቆሞ በወዳጅነት ስም የሚካበተው የጦር መሣሪያ ዕዳ ተሸካሚ መሆኑ እስካልተወገደ ድረስ፣ ወዝአደሩ ከርሱ ከንቱ መስዋዕትነትና ወዝ ማፍሰስ ሌላ የሚያተርፈው ነገር የለም። ደግሞም፣ በዛሬዎቹ መሪያዎች የፖለቲካ ባይተዋርነትና በሚያራምዱት ትምክህተኝነት የተነሳ፣ በወንድማማች ሕዝቦች መካከል የሚካሄደው እልቂት ትላንትም ዛሬም እልባት ሲያገኝ አይታይም። ስለሆነም፣ በዚህም በዚያ የኢትዮጵያወዝአደር ከአለበት የኑሮ ሲቃ ሊላቀቅ አልቻለም። የኢትዮጵያኢኰኖሚ እንደዚሁ።
የሠራተኛው አዋጅ፣ ምንም እንኳን እዚህም ላይ የወዝአደሩን መብትና ጥቅም በሚመለከት አንዳንድ የጉደሉት ነገሮች ቢኖሩም፣ በህብረት ስምምነት ወዝአደሩ መብቱን ለማስጠበቅ የሚያስችለው መድረክ ከፍቶለት ነበር። ይሁንና፣ ቀድሞ ከአድሃሪው ቢሮክራሲ ጋር እየታገለ በህብረት ስምምነት ወዝአደሩ ያገኝ የነበረው ጥቅም ታግዶበታል። ከዚህም አልፎ፣ አድሃሪው ቢሮክራሲ ለመፍለጥ ለመቁረጥ የሚያስችለው መብት ተሰጥቶት የህብረት ስምምነት ሥነ ሥርዓት ደብዛው እየጠፋ ነው። ወይንም ወደ ይስሙላ ደረጃ አዝቅጧል።
ዛሬ የህብረት ስምምነቱ የጊዜ ገደብ፣ በአብዛኛው የማምረቻ፣ ማከፋፈያ፣ የትራንስፖርትና የመገናኛ ድርጅቶች እንዲሁም የመንግሥት እርሻዎች ውስጥ፣ ከተላለፈ ዓመት ይበልጠዋል። ወይ ለህብረት ስምምነቱ የወጣውን መመሪያ ውስጥ ለውስጥ በግዴታ ሥራ ላይ ማዋል፤ የማይቻል በሚመስልበት አካባቢ ደግሞ፣ ወዝአደሩ ይህን ሲጠይቅ መመሪያ አልተሰጠንም ማለት፣ ወይ አዲስ የህብረት ስምምነት እንዲደራደር ‘አልተፈቀደለት’፤ ወይ ደግሞ በነበረው የህብረት ስምምነት ቀጥሎ ጥቅሙንና መብቱን አይጠይቅ ነገር፣ መመሪያ አልመጣም በሚል ሰበብ ብቻ፣ የዛሬዎቹ “ጓዶች” ያለፈው ሥርዓት “ክቡር እም ክቡራን”፣ ወዝአደሩን ቁም ስቅል እያሳዩት ነው። የመጨረሻ መጨረሻ ብቻ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የልብ ልብ ተሰምቷቸው በመመሪያቸው መሰረት፣ የቢሮክራሲውን አምባገነንነት የሚያሰፍኑ፣ ወዝአደሩን መብት አልባና የተረገጠ የሚያደርጉ የህብረት ስምምነቶች ከበላይ እየተደነገጉ ያለ ውዴታ ወደ ታች እየተወረወሩ ናቸው። በቅርቡም፣ አንድ ለህብረት ስምምነት የሚያገለግል ቋሚ መግለጫ ወጥቶ፣ የተረፉ ታጋይ የወዝአደር መሪዎችም ካሉ ተገደው እንደሚፈራረሙ ለመጠራጠር አይቻልም።
በዚህ ጉዳይ ላይ አንድ የመጨረሻ ነገር እናንሳ። ቀደም ሲል በአዋጁ መሠረት አንዳንዱ ህጋዊ ማህበር እንደ አካባቢው ሁኔታ መደራደር ይችል ነበር፣ ዛሬ ግን በአጠቃላይ እንጂ እያንዳንዱ ማህበር እንደማይችል እየተደረገ ነው። ወደፊት በአጠቃላይ ህብረት ስምምነቱን የሚደራደረው የሚፈራረመውና የሚያፈራርመው መኢሠማ ነው ቢባልም አይደንቀንም። ጭቆናና አምባገነንነት በሰፈነበት ሁኔታ ውስጥ፣ ለጥቅም ያደሩ፣ ለፍርፋሪ ሲሉ የወዝአደሩን መብትና ጥቅም አሳልፈው የሚሸጡ ይበልጡን የሚገኙት በወዝአደሩ ተጠሪዎች ዘንድ ወደላይ ከፍ ሲል መሆኑ የታወቀ ነው። ይህንንም፣ እንደ ኃይለ ሥላሴው በየነ ሰለሞኖች፣ የዛሬዎቹ የመኢሠማ መሪዎች በመንግሥት አፈቀላጤነት ተወዳዳሪ የማይገኝላቸዉ እየሆኑ መሄዳቸውን በሚያሳፍር ሁኔታ እያስመሰከሩ ናቸው።
ዘንድሮ የ1972 ሜይ ዴይን የምናከብረው፣ የወዝአደሩ የኑሮ ሁኔታ በማሽቆልቆል፣ አሽቆልቁሎ በመዳሸቅ፣ ዳሽቆ ከፍተኛ የኑሮ ሲቃ ውስጥ በወረደበት ደረጃ ላይ እያለን ነው።
የኢትዮጵያ ወዝአደር፣ የኢትዮጵያ አብዮትን ከቅልበሳ ለማዳን፣ በየጊዜውና በየፈርጁ፣ እየተፈራረቁና እያበሩም ጠላቶቹ ሲወጉት፣ ያልከፈለው መስዋእትነት ያላሳየው የትግል ወኔና ቆራጥነት እንዳልነበር ይታወቃል። በተለይ ከ1966 ዓ.ም እስከ 1971 ድረስ ያካሄደው ትግል በልዩ የታሪክ ምዕራፍ ተመዝግቦ የሚቆይ ነው። በዚህም ተጋድሎው ውስጥ፣በሌሎች አገሮች – ገና አብዮት በማካሄድ ላይ ለሚገኙ ወዝአደሮችና ሕዝቦች እንደምሳሌ በሚጠቀስ ደረጃ የማቴሪያል ጥቅሙን ሳይቀር ሰውቷል። ዛሬ እንዳልነበር ሆኖ፣ “ከበርቴ በዝባዥ ወዝአደር” እየተባለ በፀረ-ሕዝብ ቢሮክራቶችና በአዲሶቹ ፈላጭ ቆራጮች ቢዘለፍ ተገርፎ ቢታሰርና ቢረሸንም፣ ዛሬ እነርሱ በርሱ ፍሬ ደልበውና ጠርቅተው፣ እርሱ ከአለበት የኑሮ ሲቃ እንዳይወጣ አፍነው በችጋር ዓለሙ ውስጥ እንደተጠበሰ ቢተውቱም ታሪክ ሲመሰክረው የሚቆይ ሀቅ ነው። ታሪክም ወደፊት ይህንን ሲመሰክር ጠላቶቹ ትቢያ ሆነው እንደሚወርዱ ጥርጥር የለውም።
የኢትዮጵያ ወዝአደር፣ የሱማሌን አድሃሪ የመስፋፋት ጦርነት ለመቋቋም አባሎቹን አበርክቶ ለመስዋእትነት አቅርቦ፣ ንብረቱን ሰጥቶ፣ ከእጅ ወደ አፍ የሆነች ደመወዙን አስተዋጽኦ አድርጐ ለአብዮቱና ለብሄራዊ ነፃነቱ ሲል ተሟሙቷል። ከዚያም ወዲህ፣ የኢትዮጵያ ወዝ አደር ለብሄራዊ ነፃነቱ ቢሟገትም፣ ብሄራዊ ነፃነቱ በአዲስ አምባገነኖች፣ ለአዲስ ፀረ-ብሄራዊ ነፃነት ኃይሎች ተሸጧል። የወደቀለት አብዮት በስሙ ብቻ እየተነገደበት ተቦርቡሮ ባዶ ቀፎ ሆኗል። ያገኛቸው ድሎችም መላ ቅጣቸውን አጥተው ቀርተዋል። ወዲህም በልሲል፣ ዛሬ ለምርታማነት የገዛ ሰውነቱን እንኳን ብቁ ለማድረግ፣ ቤተሰቡን በወጉ ለማኖርና ለመመገብ ቀርቶ፣ ሕይወቱንም ለማሰንበት ወደሚያዳግትበት የኑሮ ሁኔታ አሽቆልቁሏል። ኑሮው ዳሽቋል። አዲስ በላተኞች።
የዛሬዎቹ ፈላጭ ቆራጮች፣ ምናልባት እንደ ኃይለሥላሴ ውሻ አይቀልቡ እንደሆነ ነው እንጂ፣ ከሰውም ውሻ አለውና ለእነርሱ የሚያድሩ አሽቃባጮችን፣ አድርባዮችን፣ አጐብዳጆችንና እበላ ባይ ቴክኖክራቶችን እየሾሙ እየሸለሙ እያደለቡና ራሳቸውም እየደለቡ ናቸው። የኢትዮጵያ ወዝአደር ደግሞ፣ እንደ ደቡብ የኢትዮጲያ ሕዝብ ጭፍጨፋ አስመርሮት ጠኔ አሸንፎት አይሰደድ እንጂ፣ እንደ ሰሜን ኢትዮጵያና ወሎ ተርቦ አይነቀል እንጂ፣ በችጋር ላይ እያጣጣረ ሳለ፣ እንደ ለ“ረሃብ ቋሚ መፍትሄ መዋጮ” “መልሶ ማቋቋሚያ መዋጮ” ለዚህም ለዚያም መዋጮ፣ በዚህም በዚያም “መዋጮ” “መዋጮ” እየተባለ ቁም ስቅሉን ያያል። “ቋሚ መፍትሄ” ሲያገኙ የሚታዩት፣ “ሲቋቋሙና መልሰው ሲቋቋሙ” የሚገኙት ደግሞ አዲሶቹ በላተኞች ብቻ ናቸው። የኢትዮጵያ ወዝአደር፣ ከርሱ አልፎ በነፍስ ወከፍ በቤተሰቡ፣ በሚስቱ፣ በልጁ በመዋጮ ስም የወዙን ፍሬ ሲነጠቅ፣ በመሥሪያ ቤቱ ሲያገባድድ በማሕበሩ፣ በማበሩ ሲያበቃ በቀበሌው፣ በያይነቱ ኮሚቴዎች ወዘተ እየተዘረፈ፣ ወር ሲደርስ ደመወዙን አሟጦ ለመግባት ምንም አይቀረውም። ሁኔታው ቀለብና ልብስ ከናንተ ሆኖ እንሥራላችሁ የሚያሰኝ የባርነት ደረጃ ላይ እየደረሰ ነው።
በዚህ ላይ፣ የደመወዝ ጭማሪው ጉዳይ ከፍ ብለን እንዳመለከትነው ነው። የትርፍ ሰዓት ክፍያውም እንደዚሁ። “እድገቱ” በወረቀት ላይ ተወስኖ ለአደንቋሪ ኘሮፖጋንዳቸው ብቻ ለሚያገለግለው ዘመቻ በቀን እስከ አስራ ሁለት ሰዓት ያለአንዳች ክፍያ ወዝን ማፍሰሰ በሚመለከተውም ከላይ እንደገለጽነው ነው።
በዚህ ላይ፣ በእነርሱ የትምክህተኛና የነፍጠኛ ፖለቲካ መሥመር የተነሳ፣ በነርሱ የበላይ አዛዦች የመስፋፋት ምኞት የተነሣ፣ የሱማሌን ወረራ ከተቋቋምን ወዲህም ማብቂያ ለሌላው ጦርነት እርዳታና መዋጮ።
በዚህ ላይ፣ በእነርሱ የትምክህተኛና የነፍጠኛ ፖለቲካ መሥመር የተነሳ፣ እልባት ማግኘት ስላልቻሉ፣ በኤርትራና በኢትዮጵያ ሕዝቦች መካከል በሚፈሰው የወንድማማቾች ደም ውስጥ አጉል መስዋአት እንዲሁኑ ለተገደዱ ቤተሰቦች እርዳታና የተጓደለውን ምርት ለማሟላት ጠብ የማይል ከንቱ የወዝ ማፍሰስ።
በዚህ ላይ፣ ለተዋረደና ለአዘቀጠ ኑሮ እንኳን፣ አስፈላጊ የሆኑት እቃዎች ዋጋ ቀን በቀን መናር፣ የኑሮ ውድነት፣ እዚህ ላይ በደረቅ እንጀራ ሕይወትን ለማሰንበት ለሚያስፈልጉ እህሎች የ1968 ዓ.ምንና የ1972 ዓ.ምን ዋጋ ብናወዳድር ፡-
| ሃምሳ ኪሎ የ1968 ዋጋ | ሃምሳ ኪሎ የ1972 ዋጋ /በኢት.ብር/ |
| ጥቁር ጤፍ 26 | 37.50 |
| ቦቆሎ …. | 20.00 |
| ገብስ 14 | 35.00 |
ሳሙናው እንጨቱ፣ ዘይት ወዘተ እንደዚሁ ይቀጥላል። የልብሱንና የጨርቃ ጨርቁን እንተወው “የምትበላው የላት የምታጌጠው አማራት” ይሆንብናል። ብቻ የአሻጥረኛ ነጋዴ ዋጋ እንዳንባል። ይኸውም ገበያ ላይ በተገኘ ያሰኛል። ለዚያውም ከመንግሥት ስታቲስቲክስ ጋር ሊመሳከር ይችላል። ሰው ሰራሽ እጥረት እንዳንባል፣ አጉል ክርክር እንገጥምና ብዙ ይዞን ይሄዳል። ለማናቸውም፣ ወዝአደሩ ለመኖርና ለማምረት እንዲችል፣ ምን ሆነ ምንም የሚፈልጋቸው እቃዎች ገበያ ላይ መታየት ነበረባቸው። የአውቶቡስ ኪራይ እንኳን በአቅሙ ጨምሮ እናገኘዋለን። የመንግሥት ንብረት የሆነው። ብቻ አልጨመረም እንዲባል በዘዴ ነው። ቀድሞ ከአዲስ አበባ ከተማ በ0.15 ሳንቲም የሚዘለቀው መንገድ ተቆራርጦ እጥፍ ይከፈልበት ከጀመረ አመት አልፎታል።በጠቅላላው በአ.አ ወስጥ የኑሮ ውድነት ከ1967 እስከ መስከረም 1972 ምን ያህል እንደመጠቀ ለመመልከት የሚከተሉትን አሃዞች ማስተዋሉ በቂ ነው።
ከ1967 እስከ 1972 መስከረም ድረስ የታየው የዋጋ እድገት፡-
…እህል – ከሁለት ጊዜ እጥፍ በላይ ማለትም 217 በመቶ
…ጥራጥሬ – ከአንድ ጊዜ እጥፍ በላይ ማለትም 106 በመቶ
…በአጠቃላይ ምግብ ነክ ነገሮች – ከአንድ ጊዜ ተኩል ከጥፍ በላይ ማለትም 158 በመቶ
…ልብስ ነክ እቃዎች – ከግማሽ በላይ ማለትም 50 በመቶ
…በአጠቃላይ የኑሮ ውድነት ደግሞ አንድ ከሩብ ጊዜ እጥፍ ማለትም በ125 ከመቶ ጨምሮ እናገኘዋለን።
ይህ የኑሮ ውድነት በቀላል አማርኛ ቢተረጐም፣ በ1967 አንድ ወዝአደር 80 ብር ደመወዝ ያገኘ እንደሆነ፣ እንደያኔው ለመኖር እስከአሁን አንድ መቶ ብር የሚሆን የደመወዝ ጭማሪ ማግኘት ይኖርበታል ማለት ነው። ባለፉት አምስት አመታት ደግሞ የትኛው ወዝአደር ይህን ያህል ጭማሪ አግኝቶ እንደሆን ሁላችንም እናውቀዋለን። “ወዝአደሩ ከበርቴ” ሆኗል ነው፣ የሚባልልን። ለባለ 80 ብር ደመወዝተኛ ያውም ባለፉት ሁለት ዓመታት “ማትረፍ ከተረጋገጠ” የዛሬዎቹ ፀረ-ወዝአደሮች ያሰቡለት የደመወዝ ጭማሪ ከአራት ብር እንደማይበልጥ የሚያደርግ ስሌት ተካሄዶ ነው። (5 በመቶ) የውስጥ መመሪያቸውን እንደሚያዘው።እዚህ ላይ እንግዲህ፣ የኑሮ ውድነትና የሸቀጥ እጥረት ነገር ቢነሣ፣ ሁሌ መሸሺያው አሻጥረኛ ነጋዴ ነውና፣ በሰሞኑ የሜይ ዴይ ዋዜማ ላይ ስለነበረው የስኳር እጥረት አንድ ነገር እናንሳ። የስኳር ዋጋ በዓለም ገበያ መናር፣ አንዱ ምክንያት የ“ወዳጃችን” የሩሲያ በዓለም ገበያ ውስጥ መግባት መሆኑ ይታወቃል። በዚህም ሳቢያ፣ የስኳር አንድ ነጥር ዋጋ ከ8.46 የአሜሪካ ሳንቲም ወደ 20 ሳንቲም (መቶ 134 እጅ መሆኑ ነው) ከፍ ይላል። በመሆኑም በሩሲያ “ዓለም አቀፋዊ ወዳጅነት” የተነሳ ብዙ የመሳሪያ እዳ ስላለብን፣ ያለ የሌለ ስኳራችን ወደ ሩሲያ ይጋዛል። ኢትዮጵያ ውስጥ ለደረሰው የስኳር እጥረት ደግሞ የሚሰጠው የተለመደው የቅጥፈት ምክንያት፣ ስኳር አከፋፋዩች የሚጠበቅባቸውን መጠን አልወሰዱም። “ሕዝባዊ ሱቆች” ሁሉ ማከፋፈል አልቻሉም። ወዘተ ወዘተ የአሻጥረኛ ነጋዴውም ነገር ይኸው ይሆናል።ስለቡና ደግሞ አንድ ነገር፡- የኢትዮጵያሰፊ ሕዝብ ሲቸገር የሚለው፣ እንዴት አንዲት ሲኒ ቡና ትረርብኝ ነው። አሮበታል። የቡና ምርት ግን አልቀነሰም። ቀድሞ አንድ ኪሎ ቡና ከቸርቻሪዎች በሶስት ብር ይገኝ ነበር፣ ዛሬ ነጋዴዎች “አሻጥረኛ” በመሆናቸው፣ መንግሥት ያለ የሌለን ቡና ያግበሰብሳል። ደህና ደህና ቡናውን ለ‘ወዳጆች’ ዕዳ መክፈያ የውጭ ምንዛሪ ማስገኛ፣ንፋሽ ንፋሹን ደግሞ ያሽግና በ13 ብር ኪሎውን ይቸረችራል። የአሻጥረኛ ነጋዴ ነገር ይኸው ይሆናል።ለሁሉም ችግር፣ አሻጥረኛ ነጋዴ ይባላልና፣ እዚህ ላይ እንደገና አንድ ምሳሌ ጠቅሰን የወታራዊው አምባነን መንግሥትን የንግድ አሻጥር እናመልክት። ጨርቃ ጨርቅ ዋጋ ተመን መውጣቱ ይታወቃል። በተተመኑት ጨርቃ ጨርቅ ዝርዝር ውስጥ ስማቸው የማይገኙ ልዩ ልዩ ስሞች ይፈለሰፋሉ። እነዚህ በቀለማ ቀለም ይነካራሉ። በተተመነው ዋጋ እንዳይሸጥ የተተመኑት ዝርዝር ውስጥ የሉምና ከዋጋ ዝርዝር ቁጥጥር ውጪ ይደረጋሉ።[የማይነበብ – አዘጋጆቹ] ያህል ትርፍ ተገኘ ተብሎ ይጠየቃል። የባህርዳር ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ አምስት ሚሊዮን ብር። ወደ ውጭ አይላክምና ከየት ቢባል ያው ከወዛደሩ እና ከጭቁኑ ነው። የአቡጀዲና በሀገር ውስጥ የሚመረት የጨርቃ ሸማች ቢሮክራት የለውምና። ምሳሌያችንን እናብቃና እንቀጥል።የኢትዮጵያ ወዛደር ኑሮ ሲያሽቆለቁል፣ በሌላ በኩል የሚያምርበትና ቤቱ የሚሞላ መገኘቱ አይቀርም። ይህን ሰፋ አድርገን እዚህ ላይ ጥናት የማቅረብ አላማ የለንም።ይሁንና፣ አንዳንድ ነጥቦች ብቻ ሳናስታወስ ደግሞ አናልፍም። የኢትዮጵያ ወዛደር ኑሮ ወርዶ ተዋርዶ፣ እራስን በሕይወት ለማቆየት የሚያዳግትበት ሁኔታ ላይ ሲደርስ፣ የዛሬዎቹ ገዢዎች ደግሞ ወደ ከፍተኛ መደብነት፣ ወደ ወታደራዊ ቢሮክራሲያዊ ወደ ከበርቴነት እየተመነደጉ፣ እያደጉ ናቸው። በዚያው መጠን እየደለቡ።የኢትዮጵያ ወዛደር ለእናት ሀገሩና ለአብዮቱ አልተዋደቀም!! የኢኮኖሚ ግንባታ ላይ ነንና ለወዛደሩ የደመወዝ ጭማሪ አይደረግም!! እንዲያውም ወዛደሩ በዝባዥ – ከበርቴ ያላመረተውን የሚበላ ሆኗል!! ባንድ በኩል፣ የአዲስ በላተኞች ወሬ ይኼ ነው። በሌላ በኩል ግን፣ ከነርሱ መካከል “ለአገራቸውም” ሲዋደቁ በጀብዱዋቸው ተመረጡ የሚባሉት መኮንኖችና ባለከፍተኛ ማዕረጎች፣የማዕረግ እድገት ካልተሰጣቸው አይሆንም። በዚህም ኑሯቸውን ያዳበሩትና ያደጉት በሺህ የሚቆጠሩ ናቸው። ከዚህ ሌላ፣ ያው ጊዜያቸውን ጠብቀው ስለሚያድጉም የሀገር ኢኮኖሚው ግንባታ ነገር እነርሱን አይመለከትም። የደሞዝ ጭማሪ እገዳውም አይጠቅሳቸውም ማለት ነው። የአንዱ ኑሮ ሲያሽቆለቁል፣ ሌላው ይጠረቃል የሚባለውም ያኸው ነው። እነርሱ እየተሿሿሙ፣እየተሸላለሙና እያደጉ፣ ወዛደሩን ደግሞ በምርት ጀግንነት በቆርቆሮና በብጣሽ ወረቀት ይሸኙታል። “ዓይኗን ቀቅላ በልታዋለች” ይባል የለ።ወደ ላይ፣ ወደ ዛሬዎቹ ገዢዎች ከፍ እያልን ስንሄድ ደግሞ ሌላ ነው፣ አንድ ምክትል አስር አለቃ፣ ከአሥር እልቅናው በአመት ውስጥ መቶ፣ ከሃምሳ እልቅና በመት ውስጥ ሻምበልና፣ ከአስር ዕልቅና መተዳደሪያው ወደ ዋና አስተዳዳሪነት፣ ወደ ሥራ አስኪያጅነት፣ ወደ ባለ ሺ አምስት መቶ ደሞዝ በይነት። እነዚህን ፀረ- ሕዝብ ዘራፊዎች የኢትዮጵያ ወዛደር ያውቃቸዋል። ለእነርሱና የአንድና የሁለት እጅ የኑሮ ውድነት እድገት ምናቸውም አይደለም። ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ በዚህ ዘዴ ያደጉትን የገዢው ረድፍ አባሎች አስተዳዳሪዎችና ሥራ አስኪያጆችም ገቢ ጠቅልለን ወስደን በመተማመን ወዛደሩ ኑሮው እያሽቆለቆለ እንዲሄድ ያደረገውና የደሞዝ ጭማሪውን እገዳ ያስከተለው ምን እንደሆነ ማሳየት ባላስቸገረን ነበር። ወደ ገዢ መደብነት ያደጉትና ከአብዮት ቅልበሳ ከፍተኛ የማቴሪያል ጥቅም ባገኙት የላይኞቹ ወታደራዊ ቢሮክራሲያዊ ከበርቴዎች የተነሳ፣ በኢትዮጵያ ወዛደሮች ላይ የመጣ መዘዝ መሆኑን ለማሳየት በቻልን ነበር። በዚህም “በዝባዥ” የት፣ “ከበርቴ” ወዴት፣ ያላመረተውን የሚበላ የትኛውን፣ “በዝባዥ” “ከበርቴ” ወዛደር ሲሉ ላንቃቸውን የሚሰነጥቃቸውን ደግሞ አዲሶቹ በላተኞች መሆናቸውን ባሳየን ነበር። ለሌላ ጊዜ እልናፈዋለን። በነገራችን ላይ ለነዚሁ አዲስ በላተኞች የነዳጅ፣ የመኪና፣ ለልዩ ወጪና ወዘተ እየተባለ የሚፈስሰውንና የሚባክነውን ገንዘብ ልብ ብሎ ብቻ ማለፍ በቂ ነው።
በዚህ ላይ፣ ይህ ሁሉ አልበቃ ብሏቸው፣ ለብሄራዊ ነፃነታቸውና ለአብዮታቸው ሲሉ የወደቁ ወዝአደሮች ቤተሰቦች እያራቆቱ ናቸው። በየጦር ሜዳው የወደቁ ወዝአደሮችን በሕይወት ያሉ በማስመሰል፣ መኮንኖችና የጦር አዛዦች ደመወዛቸውን ጠቅልለው እየተቀበሉ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የወዛደሮች ቤተሰቦችን በችጋርና በእርዛት እያሰቃዩ ናቸው።
በዚህ ሁሉ ላይ፣ “ሶሽያሊዝም” የእነርሱን፣ “ኰሚዩኒዝም” የእነርሱን፣ እየገነባንባት ነው፣ በሚሏት ኢትዮጵያችን ውስጥ፣ ባለው ሥራአጥ ላይ ወዛደር ሌላው ቀርቶ የሥራ መብቱንም እየተገፈፈ ነው። ከሥራ ላይ የሚፈናቀለው ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየመጠቀ ነው። ለመብቱ የሚቆም ማህበሩንና አዋጁን ተገፏልና፣ ይህም በግልጽና አንዳንዱም በዘዴ በየእለቱ የሚከናወን ጉዳይ ነው። በዘዴ ያልነው፣ የመንግሥት እርሻዎች ወይንም ሌሎች ድርጅቶች “ጥቅም” የማይሰጡ ሆነው ሲገኙ ወይንም ደግሞ “ወዳጅ” ሀገሮች ኢትዮጵያ ውስጥ ሊያራግፏቸው የሚችሉ ሸቀጦች የሚያመርቱ እንዲሆን፣እንዲዘጉ ስለሚደረጉ ነው። ከመዘጋታቸው በፊት ግን፣ በየቦታው ለመብታቸው ቆመው የሚሟገቱ ወዝአደሮች የተገኙ እንደሆን፣ ወደእነዚህ እንዲዛወሩ ይደረጋሉ። ከዚያ፣ ጥቂት ሳይቆይ ድርጅቶች ይዘጋሉ። ወዛደሮችም ከየአዲሱ የሥራ ገበታቸው ያለአንዳች ማካካሻ ተባረው ሥራአጥ ያጥለቀለቀው ሜዳ ላይ ይወረወራሉ። እዚህ ላይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ አየርመንገድ ወዛደሮች ላይ የሚደርሰውን እንደምሳሌ መጥቀስ ይቻላል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ መደበኛ የንግድ ሥራውን እንዲያስተጓጉል ተደርጎ፣ ለጦርነት፣ መሳሪያ እንዲያጓጉዝና ወታደር እንዲያመላልስ ሆኖ፣በዚህም ላይ የኃይለሥላሴን እግር ተክተው መምነሽነሻና መንሸራሸርያ አድርገውት ሰንብተው፣ ዛሬ ድርጅቱን ከስሯል ሲሉ ወዛደሩን ይወነጅላሉ። ያ በቀውጢ ጊዜ ለአብዩቱና ለእናት ሀገሩ ቀና ደፋ ሲል የነበረው ወዝአደርን ከሥራው በግፍ ያባርራሉ። ሊዘጉ የተበየነባቸው እርሻዎችና ድርጅቶች ውስጥ አንዳንዶቹ ይመደባሉ። ይህ የአዲሶቹ በላተኞች ተራ ማጭበርበሪያ ዘዴ መሆኑ የኢትዮጵያ ወዛደሮች እና ሰፊ ሕዝብ መገንዘብ አያቅተውም።ከቅርብ ጊዜ ወዲህ፣ እስካሁን መዘጋታቸው በግልጽ የታወቁ አንዳንድ ድርጅቶችን እንጥቀስ። የጫማ፣ ዘይት መጭመቂያ፣ በርከት ያሉ የድንጋይ ወፍጮዎች፣ አያሌ ትላልቅ ሆቴሎች ወዘተ የወለጋ ፋና ትራንስፖርት ድርጅት፣ሲዳሞ ትራንስፖርት። እንዲዘጉ ትእዛዝ የተሰጣቸው፡- የወሎ አ.ማ ትራንስፖርት፣ ለገሠ ፈለቀ ትራንስፖርት በቡናና ሻይ ሚኒስቴር ደግሞ አሥራ ሁለት የሚሆኑ የቡና ላኪ ድርጅቶች ፈቃዳቸውን ተነጥቀዋል፣ በዚህ የተነሳ ከነዚህ ድርጅቶች ብቻ አራት ሺህ ያህል ወዛደሮች ከሥራ ተባረው ይንከራተታሉ። ዘጠኝ ሺህ የሚሆኑ ቤተሰቦቻቸውም በችጋር ላይ ይገኛሉ። ከመንግሥት እርሻዎች በዘፈቀደ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ወዛደሮች በየወቅቱ ይባረራሉ፡ ወዘተ. ወዘተ። “አቤት” ይባልበት የነበረው የክርክር ኮሚቴስ? ካለቀለት ቆይቷል።የኢትዮጵያ ወዛደር ላይ የደረሰው ኢ-ሰብአዊነትና ጭቆና፣ ብዝበዛና የገባበት የዘቀጠ የኑሮ ሁኔታ አሰቃቂ ነው። ይሁንና፣ የኢትዮጵያ ወዛደር ዛሬ ዓለም አቀፍ የሜይ ዴይ እለቱን ሲያከብር፣ ባለፉት ዓመታት በርሱ ላይ የደረሰው ሁሉ፣የርሱ አጋሮች በሆኑ መደቦችና የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ የወረደ መሆኑንም አጥብቆ ያውቃል። ያለፈውን የኃይለሥላሴ መንግሥት አቅፎና ደግፎ ይዞት ከነበረው አድሃሪ የሲቪልና ወታደራዊ ቢሮክራሲ ጋር አዳዲሶቹ ገዢዎች ጋር ተጋብተው ያደጉበት ቢሮክራሲያቸው ውስጥ [ የማይነበብ – አዘጋጆቹ] እያልን ስንሄድ የላይኛውን ረድፍ ከያዙት በስተቀር፣ ዛሬ በኢትዮጵያ ላይ በወረደው ኢ-ሰብአዊ፣ በፀረ-ፍትህ፣ በፀረ-ቢሮክራሲና አምባገነን አየር ያልታፈነ የህብረተሰብ ኃይል አይገኝም።
የኢትዮጵያ አርሶአደር፡- የኢትዮጵያ አርሶአደር፣ ከፊት ለፊት በፀረ-ብሄራዊ ነፃነትና ፀረ-አብዮት ኃይሎች፣ ከጀርባው በወታደራዊው ቢሮክራሲና በውስጥ አድሃሪዎች እየተወጋም ቢሆን፣ ለእናት አገሩ ብሄራዊ ነፃነትና ለአብዮቱ የከፈለው መስዋእትነት በአርአያነት ሲታይ የሚቆይ ነው። ልጁን፣ ዘመዱን፣ ወገኑን ወደኋላ ሳይል ያበረከተው የሰው ኃይል፣ ያፈሰሰው ገንዘብ፣ የለገሰው ንብረትና የዘመቱ አርሶ አደሮችን ማሳ በማረስ ቤተሰቡን ለመንከባከብ ያፈሰሰው ወዝ በምሳሌነት ሲጠቀስ የሚኖር ነው። ይሁንና ደግሞ፣ ይህ መስዋእትነት ዛሬ መልኩን እየለወጠ ወደ እልቂት ደረጃ እየተሸጋገረ ነው። መኢሶንም “ለአብዮታዊ ጦርነት አብዮታዊ አመራር”፣ “ያለአብዮታዊ አመራር ጦርነት ሊኖር አይችልም”፣ “ቢሮክራሲ አያዘምት ይዘመትበት” ሲል በወቅቱ ያስተጋባ የነበረው ይህንን…. መልእክት ነበር። ዛሬ፣ እነዚህ በትምክህተኝነት እየተወጠሩ የመጡት አዲሶቹ ገዢዎች፣ ከወታደራዊ ኃይል በስተቀር ሌላ መፍትሄ ስለማይታያቸው በወንድማማች ሕዝቦች መካከል እልቂቱ እንዲቀጥልና የኢትዮጵያ ገጠር ወጣትና አምራች አልባ እስከማድረግ አድርሰውታል።የኢትዮጵያ አርሶአደር ለብሄራዊ ነፃነትና አብዮቱ ሲዋደቅ ቆይቷል። ዛሬ ግን የመኖር መብቱንም ቀስ በቀስ እሚነፈግበት ደረጃ ላይ እየደረሰ ነው ለማለት ይቻላል። የኢትዮጵያአርሶአደር እያለቀ እየተጨፈጨፈ ነው። ለዚህ አሰቃቂ ሁኔታ፣ በኢ-ሰብአዊነት የተካኑት ትምክህተኞች መልስ ደግሞ፣ “ሰው በሰው ይተካል” ሆኗል። የኢትዮጵያ አርሶአደር በዚህ ቀደም ለናት ሀገሩ ሲል ያበረከተው የሰው ኃይል የት እንደደረሰ ሳይታወቅ፣ ምናልባትም በነርሱ ትምክህተኛ አመራር ሳቢያ ለእልቂት ተዳርጎ፣ ዛሬም “ለታጠቅ” ጦር ሰፈር ልጁን፣ ዘመዱንና ወገኑን ጭዳ ለማቅረብ እየተገደደ ነው። የሚያፈሰውንም ወዝ ያንኑ ያህል ከልክ እያለፈ ነው።
በዚህ ላይ የኢትዮጵያ አርሶ አደር “መሬት ላራሹ” ሲል ተዋድቆ፣ በራሱና በኢትዮጵያ ሀቀኛ ልጆች ትግል መሰረቱን ከተነጠቀ ወዲህ የፖለቲካ ነፃነቱን እንደተገፈፈ ነው። ተገፎም፣ የተነጠቀው የመሬት መብቱን ለማስጠበቅ እንዳይችል፣ ዛሬ በፈላጭ ቆራጭ መንግሥትና በአድሃሪ ቢሮክራሲ ስር መማቀቅ ይዟል። በተጣለበት የመሬት ግብር ሳቢያ ቀስ በቀስ መሬቱን ነቅሎ እንዲሄድ የሚያስገድደው ሴራ እየተሸረበበት ነው። የመሬት ግብር አከፋፈል ላይ፣ ባለፈው ሥርዓት እንኳን፣ የመሬት አይነት ስም፣ ለም-ጠፍ፣ ጠፍ በሚል ተደልድሎ ለአንድ ሄክታር የሚከፈለው ከአንድና ሁለት ብር አይበልጥም ነበር። ዛሬ ግን በሄክታር በደፈናው 10 ብር እንዲከፍል በአፈ ሙዝ እየተገደደ ነው።
በዚህ ላይ፣ ከአለፈው የፊውዳል ሥርዓት በአዘቀጠ ሁኔታ፣ አርሶ አደሩ እህሉን ከአውድማ ሳያንቀሳቅስ፣ የወጣው ወጪ ምን ያህል እንደሆነ ሳይገምት፣ “ምርት ካድሬ” በሚባሉ አዲስ የተፈጠሩት የአምባገነንነት ወጠጤ ተጠሪዎች የገቢ ታክስ ይጫንበታል።በዚህ ላይ፣ ምክንያቱና መጠኑ ያልታወቀ፣ በዘፈቀደና ከልብ ባልሆነ ዘዴ የእህል መዋጮ ለማድረግ አርሶ አደሩ ይገደዳል።
በዚህ ላይ፣ ወላ የአካባቢ አርሶ አደር ሁኔታ፣ ወላ ፈቃደኝነትና ዝንባሌ ሳይጤን፣ ፀረ- ሕዝብ አስተዳዳሪዎች በሚያደርጉት “ቀደምኩሽ ቀደምከኝ” ፉክክር “የህብረት” እርሻ ማቋቋም አለብህ እየተባለ የአርሶ አደሩ ንብረት ይወድማል። አንዳንድ አስተዳዳሪዎችም የኢትዮጵያን ሕዝብ ይግረመው ብለው “ኮሚኒዝም ራሱን” ልንገነባ አንድ ሃሙስ ቀረን፣ “ድሮስ ቢሆን ኢትዮጵያ….” እስከ ማለት ደፍረዋል /የማይነበብ-አዘጋጆች/ ብሄራዊ ነጻነታችንን በሚያስደፍር ሁኔታ ላካበቱት የመሳሪያ እዳቸው መግዣ የውጭ ምንዛሪ ሲያሳድዱ፣ ልክ ባለፈ ብዛት የአርሶ አደሩን ከብት በርካሽ ዋጋ እየዘረፉ፣ እያረዱ፣ ቆዳውንና ሌጦውን ለገበያ ያቀርባሉ።በዚህ ላይ፣ “ለመንግሥት እርሻ ተስማሚ ነው- እዳሪው መሬት ላይ ሂድ” እያሉ አዲሶቹ አምባገነኖች በሚያዙት መሰረት፣ አርሶ አደሩ በፊውዳሉ ሥርዓት ካየው ግፍና እንዲያውም በባሰ ደረጃ ቤት ንብረቱና መሬቱ እየፈረሰ፣ እየታረሰ መንቀል እየተገደደ ነው። በዚህ ሳቢያ ከአርሲና ከባሌ ብቻ 200.000 በላይ የሚሆን ሕዝብ ተነቅሎ ይንከራተታል። የዚህም ዋና ኢላማ የሆኑት ጭቁን ብሄረሰቦች የሚገኙባቸው አካባቢዎች ናቸው።
በዚህ ላይ፣ ረሃብ መላ ኢትዮጵያን እንደገና እየቃኛት ነው። የኢትዮጵያን አርሶ አደር ወደ ረሃብ፣ ከዚያም ወደ ስደት ዓለም እየፈነቀለው ነው። የዛሬዎቹ ገዢዎች ደግሞ፣ የነርሱን “ሶሺያሊዝም”፣ የእነርሱን “ኮሚዩኒዝም” እየገነቡ፣ የተራበ አይሰደድ ይመስል፣ ጭፍጨፋ ያስመረረው ድንበር አይሻገር ይመስል፣ ኢትዮጵያ ጭቁን ብሄረሰቦች ያልፈጠረባት ይመስል፣ በሰው አገር የሚንከራተቱ ወገኖቻችንን በአለም አቀፍ ሸንጐዎች ሳይቀር ይከዱ ገብተዋል። ድሮስ “ከእንጀራ እናት” ምን ይጠበቃል።ዛሬ የኢትዮጵያ ወዝአደር ሜይ ዴይን ሲያከብር፣ የኃይለሥላሴ ዙፋን ላይ “ቀይ” ጃኖ ለብሰው በተፈናጠቱት አዲሶቹ አምባገነኖች የተከዱትን፣ እነዚህ በባዕድ ሀገር ባይተዋር ሆነው የሚንከራተቱ ወገኖቹን፣ እነዚህ በመላ ኢትዮጵያ በረሃብ የሚጠወልጉ ወገኖቹን ሊያስብ ይገባዋል።
ረሃብ፣ ጭፍጨፋና ስደት፡- በሙሉ ወይንም በከፊል ዛሬ ረሃብ የገባባቸው አካባቢዎች ትግራይ፣ ወሎ፣ ኤርትራ፣ ሸዋ፣ ሀረርጌ፣ ባሌ፣ ሲዳሞና ጋሞጎፋ ናቸው። በጠቅላላው ከአምስት ሚሊዩን በላይ የሚሆኑ ወገኖቻችን በረሃብ አለንጋ እየተቆሉ ናቸው። በሺህ እየተቆጠሩ በየቀኑ እንደሚረግፉም ለመጠራጠር አይቻልም። ከብትም እንደዚሁ። በቦረና አካባቢ ብቻ ከ100000 ሺህ በላይ ከብት አልቋል።ይህ ረሃብ ሥር እየሰደደና ወደፊት አስጊ ደረጃ ላይ ሊደርስ እንደሚችል የታወቀው ቢያንስ ከ1970 ዓ.ም አጋማሽ ላይ ነበር። ያኔ ግን አዲሶቹ ፀረ ሕዝቦች፣ እንኳን በረሃብ የሚያንገላታው ወገናችን እንዲረዳ ማድረግ ይቅርና የተረፈውንም ሕዝብ ለመጨረስ የሚንደፋደፉበት ፀረ አብዮት አመፃቸው ላይ ነበሩ። ከዚያም አንድ አመት በፊት፣ አንድ ሰሞን “በረሃብ እስከ ወዲያኛው ለማስወገድ” የኢትዮጵያ ሕዝብ እርዳታ እንዲያደርግ ተጠይቆ ነበር። የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚችለውን ካደረገ በኋላ “ለቋሚ መፍትሄ” ያስፈልጋል ተብሎ ሕዝቡ ያዋጣው 70 ሚሊዮን ብርም ምን እንደደረሰ አይታወቅም። “ቋሚ መፍትሄ” ያገኘ አይመስልም፣ ከዚያ ወዲህ ለአለም ሕዝብም ሆነ ለኢትዮጵያ የተነገረው ነገር የለም። የኢትዮጵያ አርሶ አደር ያመረተው በቆሎና ስንዴም ከኛ የተረፈ ይመስል፣ በተስፋፊ ፖለቲካቸው ምክንያት በአለም ላይ ስንዴ ሻጭ ላጡ “ወዳጅ” ሀገሮች ሲጋዝ ከርሟል። ኢትዮጵያ ሕዝብ ባዋጣው ገንዘብና ቁሳቁስ፣ የተራበው የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ “ቋሚ መፍትሄ” ሲያገኝ እና ሲቋቋም አልታየም። የተቋቋሙት አዲሶቹ አምባገነኖች ናቸው።አዲሶቹ አምባገነኖች፣ የተሰደደ ኢትዮጵያዊ በአለም የለም ሲሉ በአለም ሸንጎዎች እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ያስተጋቡ የነበሩት፣ በኢትዮጵያ የገባውን ረሃብ ለመካድ ነበር። ከዚህ የተለየ ሊሆን አይችልም። የመጨረሻ መጨረሻ ግን እነሆ ዛሬ ከስድስት ኢትዮጵውያን ውስጥ አንዱ መራቡን ለማመን ተገድደዋል። ይህም በረሃብ አፋፍ ላይ ያለውን ጭቁንና ወዛደሩን ሳይጨምር ነው። ይህ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከአፉ ነጥሎ ያዋጣውን ከተቋቋሙበት ወዲህ ነው። ይህ፣ የኢትዮጵያ አርሶ አደር ምርት ወደ ውጭ ለዕዳቸው መወጫ ከተጋዘ ወዲህ ነው። ይህም፣ የዓለም ሕዝቦች በኢትዮጵያ ላይ የወረደውን መዓት ከደረሱበት ወዲህ ነው። በቅድመ አብዮት፣ ኃይለሥላሴም የአለም ሕዝቦች ካጋለጡት በኋላ ኢትዮጵያ ገብቶ የነበረውን ረሃብ ማመን ተገዶ ነበር። ስለሆነም፣ የዛሬዎቹ አምባገነኖች ለጨፈጨፉት የሚጠይቁትን ያህል፣ በረሃብ ለሚገረፈው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከተጠያቂነት አያመልጡም። “ያመነ አይጠየቅም” ያለው ማነው??
በዚህ ላይ፣ በቆላማ አካባቢዎች በጥይት የሚቆሉ ወገኖቻንን ትተን በአፋር፣ በኢሳና፣ በሱማሌ ብሄረሰቦችና በከብቶቻቸው ላይ ከፍተኛ እልቂት እየተካሄደ ነው። እዚህ ላይ፣ የእኛዎቹ አምባገነኖች እንደለመዱት የትምክህተኛ አፋቸውን እንዳይከፍቱብን፣ ኢትዮጵያ የሱማሌና ሌሎች የአካባቢው ብሄረሰቦችም ምድር እንደሆነች ደግመን ደጋግመን ለመግለጽ እንወዳለን። ከአንድ ውሃ የተጠለቁት ትምክህተኞችና ተስፋፊው የሱማሌ ገዢ መደብ የሚያወሩት ሌላ፣ የእኛ አቋም ለቅል ነው።
በዚህ ላይ፣ ይህ ሁሉ እየሆነ “ለተከዱት” ወገኖቻችን በየትም ሆነ የት እርዳታ እንዳይደርሳቸው፣ ከዚህ ከዙፋቸው እያዘዙ፣ መልዕከተኞችም እየላኩ ኢ-ሰብአዊ ሴራቸውን እየተበተቡ ነበር። ናቸው።
በዚህ ላይ፣ ለተራቡ ወገኖቻችን ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣው ምግብ ገንዘብና ሌላም እርዳታ፣ ብሄራዊ ነፃነታችንን በጫማቸው ረገረጠው በሀገራችን ለሰፈሩ የውጭ ጦሮች ቀለብና አንሶላ መግዣ፣ ለእኛዎቹ አምባገነኖች ደግሞ ሜዳሊያ መሸለሚያ ያውም የሰላም፣ የግል ዝና ማፍሪያ፣ መሾሚያና መሸለሚያ እየተደረገ ነበር። ነውም።የኢትዮጵያ ወዛደር ዘንድሮ ሜይ ዴይን በሚያከብርበት ወቅት የሚታዘበውና የሚስተውለው በራሱ ላይ ብቻ የሚደርሱበትን ኢኮኖሚያዊና ኢ-ሰብአዊ ግፍ እንዳልሆነ ገልፀናል። ከላይኞቹ በስተቀር ያልተጨቆነ ያልተረገጠ የለም ብለናል። የመንግሥት ሰራተኞችን ሁኔታ ሳናነሳ አናልፈውም።
የመንግሥት ሠራተኞች፡- የመንግሥት ሠራተኞች ዛሬም የመደራጀት መብታቸውን እንደተገፈፉ፣ የወታደራዊው፣ የጥቅም ተካፋይ ቴክኖክራቶችና የሲቪል ቢሮክራሲ መፎለያና መፈንጫ እንደሆኑ ናቸው። ባለው የኑሮ ውድነት ሁኔታ፣ እንደነ አስር አለቃ፣ ሻምበል፣ እንደነ ጀግናው ጀነራሉ ሹመት አይሰጡምና፣ የደመወዝ ጭማሪ አይተው አያውቁም። መዋጮውና መቀጮው አስመርሯቸዋል። እነርሱንም ቢሆን፣ “ቀለብ ከናንተ ይሁን” ሊያሰኛቸው ደርሷል። ለቂም በቀል መወጣጫ፣ የዘመድ አዝማድ መጠቃቀሚያ በሆነው ሹመትም የተሰገሰጉት የወታደራዊ ቢሮክራሲያዊ ከበርቴ አፈቀላጤዎች ናቸው። አንገታቸውን ሰብረውታል። በዚህም በዚያም፣ በየጊዜው ከሀገር ሀገር ከቦታ ቦታ የሚደረገው የሥራ መዘዋወርም መቀጣጫ በመሆኑም፣ እንዳይቃወሙ እና እንዳይተነፍሱ አፋቸውን ተለጉመው ፍዳቸውን እያዩ ነው።ዛሬ የኢትዮጵያ ወዛደር ሜይ ዴይን በሚያከብሩበት ወቅት፣ በነገሰው ወታደራዊ ቢሮክሲያዊ አምባገነን መንግሥት የሚወርደው ኢ-ሰብአዊነት፣ ግፍና ችግር በእርሱ ላይ ብቻ ሳይሆን፣ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ላይም መሆኑን ያውቃል። መላው የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ መብቱ ተገፎ፣ በሰብአዊነቱ ተደፍሮ፣ ፍትህ ተነፍጎ፣ ብልጽግናው ታግዶ እየተረገጠ ነው። ኢትዮጵያ የልጆቿ እስር ቤት ተደርጋ ልጆቿና ወገኖቿ፣ ጭቁን ቤሄረሰቦቿና ሕዝቦቿ እየተገረፉ እየማቀቁና እየተጨፈጨፉ ናቸው።
በጭቁን ብሄረሰቦች ላይ ጦርነት፡- በአራቱም ማዕዘን፣ ለመብታቸው የሚታገሉ ጭቁን ብሄረሰቦች ላይ ከሚያደርገው ጭቆና አልፎና ዘልቆ ወታደራዊው ቢሮክራሲያዊ አምባገነን መንግሥት ጦርነት ከፍቶባቸዋል። ይህ በትምክህተኝነት የተወጠረው መንግሥት፣ በኢትዮጵያ ያለውን የብሄረሰቦች ችግር ሰላማዊ በሆነ መንገድና የፖለቲካ መፍትሄ ለመሻት ፍላጐት አልባ ሆኖ በሰሜን፣ በደቡብና በምሥራቅ ኢትዮጵያ በወንድማማች ሕዝቦች መካከል የሚደርሰው ደም መፍሰስ እየተባባሰ ሄዷል። በዚህ ሳቢያ፣ በሚወርድባቸው አጠቃላይ ጭቆናና በደረሰባቸው ረሃብ የተነሳ ቤት ንብረታቸውን ትተው ወደ ባእድ ሃገር ተሰደው በስቃይና በውርደት የሚኖሩት ወገኖቻችን ቁጥር ወደ 1.5 ሚሊዩን ደርሷል። ይህ በአፍሪቃ ተወዳዳሪ የማይገኝለት ነው። በዓለም ደግሞ አገራቸውን ከተነጠቁት ፍልስጤማውያን በስተቀር የሚስተካከለው የለም።
ብሄራዊ ውርደት፡- ኢትዮጵያ ብሄራዊ ነፃነቷ ተረጋግጦና ተዋርዶ፣ በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ስር የምትማቅቅበት ጊዜ አልፎ ነበር። ይሁንና ትንሽም ሳታገግም፣ ዛሬ በሌላ ኃያልና ተስፋፊ መንግሥት ስር ወድቃ ተቀጥላው ተደርጋለች። ቢያንስ 3 ቢሊዮን ብር የሚገመት የዚሁ ተስፋፊ መንግሥት የጦር መሳሪያ ባለ “ዕዳ” ተደርጋለች። ከፍተኛ መስዋዕትነት ተከፍሎበት ከሀገራችን እንዲነቀል የተደረገው የጦር ሰፈር እንደገና በሌላው መልክ ለአዲሱ ኃያል መንግሥት የጦር ሰፈር ተደርጓል። የባዕድ ጦር ኃይል በሀገራችን ምድር ላይ እንዲሰፍር ተደርጎ፣ ኢትዮጵያ የሁለት ኃያል መንግሥታት የጦር አውድማ ለመሆን ተቃርባለች። በአለምአቀፍ ሸንጎዎች፣ ኢትዮጵያ በአብዮታችን የመጀመርያዎቹ ሦሶት ዓመታት የነፃነት ደሴት ሆና ለመታየት የጀመረችውን ያህል፣ ዛሬ የአለም ሕዝቦች መሳቂያና መሳለቂያ ለመሆን በቅታለች። ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ወታደራዊና ማህበራዊ ተቋሟ በአዲሱ ተስፋፊ ኃያል መንግሥት ቁጥጥር ስር ወድቋል። በአጠቃላይ የዛሬዎቹ አምባገነኖች ኢትዮጵያን የተሟላ የብሄራዊ ውርደት አዘቅት ውስጥ ወርውረዋታል። ይሁንና፣ የኢትዮጵያ ወዛደሮችና ሰፊው ሕዝብ ደግሞ ለዚህ ውርደትና በጠቅላላው ለወረደባቸው ጭቆና ሁሉ የሚገዙ አይደሉም። አልተገዙም፣ ወደፊትም አይገዙም።የኢትዮጵያ ወዛደሮችና አጋሮቻቸው ትግል ይቀጥላል። ይኽም ሲሆን፣ ብሶታቸውን ብሶታቸው፣ ትግላቸውን ትግላቸው፣ አድርገው ሲዋጉ ዛሬ በነገሰው ወታደራዊው ቢሮክራሲያዊ አምባገነን መንግሥት የተቀነጠሱባቸውን የአዲሱ ትውልድ አኩሪ መስዋዕቶችን እያሰቡና እየኮሩባቸውም ነው። ዘንድሮ የሚከበረውን ሜይ ዴይ ሲያስቡ፣ ባለፈው ትግላቸው እየኮሩ፣ ለወደፊት ገና ብዙ የሚጠብቃቸውን የተወሳሰበ ትግልን እያስታወሱና ለዚህም እየተዘጋጁ ነው።
አብዮታዊ ትግል፡- አብዮት አንድ ወጥ ያልሆነ ረዥምና መራራ እንደመሆኑ ሁሉ፣ አብዩት ተሳክቶ በነበረባቸው እንደ ቻይና ቬየትናምና ሆነ የሶቭየት ህብረትም ሆነ፣ ገና በእንጭጫቸው እንደ ኢትዮጵያ በተቀነጠሱባቸው እንደ ኢንዶኒሽያ፣ ቺሊ ወዘተ. አገሮች ውሰጥ እንደታየው፤ ብዙ ውጣ ውረድና ወድቆ መነሳት ይኖረዋል። ከፍተኛ፣ ከቶም ተስፋ መቁረጥን የማያፀድቅ አብዮታዊ ትግልን ይጠይቃል። ይህ ውስብስብ አብዮታዊ ትግል፣ እንኳን ገና ባልተሳኩባቸው አገሮች ቀርቶ፣ ተሳክቶ በነበረባቸው አገሮችም የሚኖር በመሆኑ ሕዝባዊ ትግል የማያቋርጥ እንቅስቃሴ ነው። ይህም መሆን እንዳለበት፣ የአለም ሶሺያሊስት እንቅስቃሴ ታሪክና ተሳክቶ በነበረባቸው አገሮች ውስጥ ወደኋላ የተከሰቱት ሁኔታዎች በገቢር ያሳዩናል።ስለሆነም፣ የኢትዮጵያ ወዝአደሮችና ሰፊ ሕዝብ በከፍተኛ መስዋዕትነት ያካሄዱትን ትግል ወደፊት በመቀጠል፣ ምንም አይነት ችግርና ውስብስብ ሁኔታ ሳይበግራቸው፣ በተለያዩ ዘዴዎችና ስልቶች አብዮታዊ እንቅስቃሴያቸውን በአዲሶቹ ገዢዎች ላይ ማፋፋም አለባቸው። መኢሶን በግምባር ቀደምተኝነት የተሰለፈው ከኢትዮጵያ ወዛደሮችና ሰፊ ሕዝብ ጋር ነው።
አብዮታዊ ጥሪ አብዮታዊ ቃልኪዳን፡- ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ዛሬ ለነገሱት አምባገነኖች ያቀረቀረ ይምሰል እንጂ አላቀረቀረም። አምባገነኖቹ ሲመኙት ይቀራሉ። አልገዛም ማለትንም የኢትዮጵያ ገጠሮች የሚመሰክሩት ነው። የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝምንና የኃይለሥላሴ ፊውዳል ፋሽስታዊ አገዛዝን ከጫንቃው ላይ አሽቀንጥሮ እንደጣለው ሁሉ፣ ትግሉ ውስብስብና ረዥምም ቢሆን፣ በኃይለሥላሴና በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ምትክ ለነገሱት አምባገነኖችም ሳይበገር ትግሉ ይቀጥላል። ለኢትዮጵያ ተራማጅ ኃይሎች፣ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች፣ ለኢትዮጵያ ሀገር ወዳዶችና ለዲሞራሲያዊ የብሄረሰብ እንቅስቃሴዎች መኢሶን አሁንም በድጋሚ የሚያቀርበው ጥሪ፣ የብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ኘሮግራማቸውን የትግል መድረካቸው አድርገው የትግል አንድነታቸውን በማጠንከር፣ በጠላቶቻቸው ላይ የአንድነት ግንባር መስርተው አብዮታዊ እንቅስቃሴያቸው እንዲያፋፍሙ ነው።መ.ኢ.ሶ.ን፣ መላ የኢትዮጵያ ጭቁን ብሄረሰቦች የራሳቸውን እድል በራሳቸው የመወሰን መብት እስከመገንጠል ድረስ ያላቸው መብት እንዲከበር ያለማወላወል ከጎናቸው ቆሞ ይታገላል። በዚህ አጋጣሚ፣ ከጥር ወር ጀምሮ በኦሮሞ ብሄረሰብ ላይ የሚደርሰውን ጭቆና እሥራትና ግድያ፣ በአጠቃላይ በብሄረሰቡ ላይ የታወጀውን ጦርነት ይኰንናል። የኦሮሞ ብሄረሰብ ተራማጆች፣ የዲሞክራቶችና ወገን ወዳዶች ልዩነታቸውን አቻችለው፣ አንድነታቸውን አጠንክረው በበለጠ በመደራጀት፣ በትምክህተኞችና በነፍጠኞች የሚወርድባቸውን የፀረ አብዮትና የፀረ ጭቁን ብሄረሰብ አመፅ እንዲቋቋሙ አብዮታዊ ጥሪውን ያሰማል። ከዚህም ጋር አያይዞ መ.ኢ.ሶ.ን.፣ የኦሮሞ ብሄረሰብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ኦብዲን/ በልሳኑ በተርካንፊ ቁጥር 13 ይህን አስመልክቶ ያወጣውን ጥሪ እየደገፈ ከጐኑ እንደቆመ ያረጋግጥለታል።መ.ኢ.ሶ.ን፣ ማንኛቸውም በኢትዮጵያ የሚገኙ ብሄረሰቦች የራሳቸውን እድል በራሳቸው ለመወሰን እስከመገንጠል ድረስ ያላቸው መብትን እንዲከበር ለማድረግ፣ ምንግዜም የቆመለትና የሚታገልለት አቋም መሆኑ የታወቀ ነው። በዚህም አኳያ፣ መ.ኢ.ሶ.ን ቀድሞም ሆነ አሁን የኤርትራ ችግር በጦር ኃይል ብቻ ይፈታል ብሎ ያመነበት አንድም ጊዜ የለም።በተለይ ዛሬ በወንድማማች የኤርትራና የኢትዮጵያ ሕዝቦች መካካል የሚካሄደው ደም መፍሰስ አሳሳቢ ደረጃ ላይ በመድረሱ፣ የኤርትራ ችግር ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ መፍትሄ እንዲያገኝ ያልተቆጠበ ጥረቱንና ትግሉን በይበልጥ ይቀጥላል።መ.ኢ.ሶ.ን፣ ኢትዮጵያ ከዛሬዎቹ ትምክህተኞችና አምባገነኖች ፀረ አብዮት አመፅ ተላቃ የብሄረሰቦቿ መብት ሙሉ በሙሉ ተከብሮ፣ ብሄረሰቦቿ በእኩልት በወንድማማችነትና በመፈቃቀር ላይ የተመሠረተ አንድነታቸውን አጠንክረው የሚኖሩባት ሕዝባዊት ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እንደምትገነባም አይጠራጠርም።መ.ኢ.ሶ.ን፣ በዚህ በዛሬው የወዛደሮች ዕለት፣ ለኢትዮጵያ ወዛደሮች፣ አርሶአደሮች፣ ዲሞክራቶች፣ ሀገር ወዳዶች፣ ጭቁን ብሄረሰቦች፣ ታጋይ ምሁራንና፣ ወጣቶች ጭቁን ሴቶች እንዲሁም ታጋይ መለዮ ለባሾችና ለሀገር ወዳድ ብሄራዊ ከበርቴዎች፣ መልሶ መላልሶ የሚያስታውቀው ምንጊዜም የማይታጠፍ የአብዮታዊ ቃል ኪዳኑ ከሌሎች ተራማጅ ኃይሎች ጋር በመተባባር ለብሄራዊ ነፃነት፣ ለብሄረሰቦች እኩልነት፣ ለፍትህ፣ ለዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብት፣ ለሀገራችን ልማትና ለሕዝቦቿ ብልፅግና ያለምንም ማመንታት ትግሉን እንደሚቀጥል ነው። እስካሁንም መ.ኢ.ሶ.ን ለምንም ሁኔታና ችግር ሳይሸነፍ ለኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ መብትና ጥቅም ሲል እየተሰዋ፣ እየተነሳና እየወደቀ መዋጋቱ ለማንም የተሰወረ አይደለም። ለኢትዮጵያ ወዛደርና ሰፊ ሕዝብ የተቀደሰ ዓላማ ሲል፣ ገና ለረዥም ጊዜ ኢትዮጵያ ተተኪ ልታገኝላቸው የማትችላቸው አባሎቹን የሰዋው፣ በሺህ የሚቆጠሩ ወገኖቹን በየእስር ቤቱ ዛሬም የሚያማቅቀው ለዚህ ነው። ወደፊትም፣ የተሰዉ አንጋፋ አባሎቹም አርማ ከፍ አድርጎ፣ የኢትዮጵያ ወዛደርና ሰፊ ሕዝብ ለሚጠብቋት ብሩኋ ሕዝባዊት ኢትዮጵያ የተጠየቀውን መስዋእትነት እየከፈለ ረዥምና መራራ አሉታዊ ትግሉን እንደሚቀጥል ያረጋግጣል። ድል ለሰፊው ሕዝብ ነው።
በመጨረሻ፣ የወገን ጥሪ፡-
መ.ኢ.ሶ.ን በዚህ ቁጥር አንድ የተለየ ጥሪ አለው። ረሀብ ። ረሀብ በመላው ኢትዮጵያ አግጦ አፍጦ እንደገና ገብቷል። ከስድስት ኢትዮጵያውያን መካከል አንዱ ተርቧል።በዚህም በዚያም የኢትዮጵያን ሰፊ ሕዝብ በመዋጮ ሲያራቁቱ ከርመው፣ የራሱን ኑሮ እንኳን ለመግፋት የሚያዳግተው ችግር ውስጥ ሰፊውን ሕዝብ ከተው፣ በአለምአቀፍ ሸንጎዎች ረሀብ ኢትዮጵያ ውስጥ የሌለ በማስመሰል ሽርጉድ ሲሉ ቆይተውና፣ ረሀብና ጭፍጨፋ ከሃገር ያባረራቸው ወገኖቻችንን ሲክዱ ቆይተው ሰንብተዋል፤ ዛሬ ከአምስት ሚሊዩን የበለጠ ኢትዮጵያዊ መራቡን አምባገነኖቻችን “አብስረውናል”። ይህም ሆኖ ደግሞ፣ “ሞኝ የያዘው ፈሊጥ” ነውና፣ አሁንም የሚያሳስባቸው ‘በ ቡ’ የማይል አፍ እንጂ፣ ‘በ ቡ’ ለማለት መጉረስ የሚገባው አይደለም። እነርሱ ‘በ ቡ’ ሲሉ የኢትዮጵያ ሕዝብ እየረገፈ እያለቀ ነው።
- ያሁኑ ፈላጭ ቆራጭ መንግሥት በብዙ አስከፊ ነገሮች ተወዳዳሪ እንደሌለው ሁሉ፣ በመዋጮ የሚተዳደር መንግሥት በመምሰልም በአለም የሚስተካከለው የለም። እስኪያሰኝ መላ ኢትዮጵያን በመዋጮ አራቁቷል። “ለረሀብ ቋሚ መፍትሄ አግኝቻለሁ” ሲል ጭምር። ስለሆነም፣ ይህን አስመልክቶ መኢሶን ለኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ የሚያደርገው ጥሪ ምን እንደሚሆን ማወቅም ቸግሮታል። “እኛም ተርበን የለ” እንደሚል ይገባናል። በመሆኑም፣ መኢሶን ለኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ የሚያደርገው ጥሪ እንድያው በደፈናው፣ የተራቡ ወገኖችህን ለማዳን በቀረ አቅምህ የሚቻልህን አድርግ ብቻ ሆኖ ይቀራል።
- በውጭ ሀገር ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን፣ ለተራማጅ፣ ዲሞክራት፣ ሀገርና ወገን ወዳድ ኃይሎች ግን መኢሶን ልዩ መልእክት አለው። ዛሬ ከስድስት ኢትዮጵያዊ አንዱ ተርቧል። የቀሩት አምስትም እንዳይሆን እንዳይሆን መሆናቸውን ለማሳየት ከላይ ተሞክሯል። ፈላጭ ቆራጩ መንግሥት ‘በ ቡ’ እያለ አሁንም ከተኛበት አልተቀሰቀሰም። ስለሆነም፣ የአለም ሕዝቦች ለተራበው የኢትዮጵያ ሕዝብ ይደርሱ ዘንድ፣ እርዳታ የመሰብሰብ ከፍተኛ ዘመቻ እንዲያካሄድ መኢሶን ከሀገር ውጪ ለሚገኙ ተራማጅና ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ሰብአዊና የወገኑ ጥሪ ከፍ አድርጎ ያሰማል። ለሰብዕ አፍቃሪ ድርጅቶች፣ ለተራማጅና ለዲሞክራሲያዊ ኃይሎች እንዲሁም ለመንግሥታትና ግለሰቦች፣ መላ ኢትዮጵያን ስለ አጥለቀለቀው ረሀብ ገለፃ በማድረግ፣ ቅስቀሳ በማካሄድ ለተራቡት ወገኖቻችን የሚያስፈልገው እርዳታ ሁሉ እንዲደርሳቸው ባለ በሌለ ኃይላቸው እንዲያስተባብሩ፣ መኢሶን ጥሪውን ያስተጋባል። ይህ፣ ወገን አፍቃሪ የሆኑት ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያዊት ላይ የወደቀ ከፍተኛ አደራ ነው።
- የአለም ሰብአዊ ድርጅቶች፣ ተራማጅና ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች እንዲሁም መንግሥታትና ግለሰቦች ለተራበው የኢትዮጵያ ሕዝብ እርዳታቸውን በተሻለ ፍጥነት እንዲለግሱ አብዮታዊና ሰብአዊ ጥሪውን መኢሶን ያሰማል። የሚየደርጉትን እርዳታ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ለጦር መሳሪያ ዕዳ መወጫ ያውለው ለባአድ ወታደሮች ቀለብ፣ ለረሀቡ መቋቋሚያ ይጠቀምበት ለ“ወዳጆቹ” ይላከው አንድም ማረጋገጫ ስለሌለ፣ እርዳታቸው በቀጥታ ለተጠቃው ሕዝብ የሚደርስበትን መንገድ አብረው የመሻት ኃላፊነት እንዳለባቸውም አጥብቆ ያሳስባል።