ሰሕድ ቁ. 62

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ቁጥር 62፣    መስከረም 25፣ 1970

የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ

መኢሶን በዚህ እትሙ፣ “የዴሞክራሲ መብቶች” መለቀቅ በብሄራዊ ዴሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራም ላይ የሰፈረ መሆኑን አስታውሶ፣ ነገር ግን ይህ መብት በስራ ላይ ባለማዋሉ አብዮቱን እንዴት ወደ ተከላካይነት እንደመለሰው ያስረዳል። በተጨማሪም ይህ መብት የአብዮቱን ድሎች ለማጠናከርና ሕዝቡም የአብዮቱ ባለቤትነት እንዲሰማው ለማድረግ የሚያደርገውን እገዛ ከዘረዘረ በኋላ የዴሞክራሲ መብቶች ጉዳት ያመጣሉ የሚሉ አድርባዮች የሚያቀርቧቸውን ምክንያቶች አንድ በአንድ እያነሳ ስህተተኛ መሆናቸውን ያጋልጣል።

የሰፊው ሕዝብ ድምፅ

ለሰፊው ሕዝብ ሰራተኛ ገበሬ፣ ነጋዴ፣ ወታደር፣ ምሁር መብትና ጥቅም የሚታገል ጋዜጣ

የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ይቅደም

ቁጥር 62                                                                      ቀን 25/1/70

 

የዲሞክራሲ መብቶች ለጭቁኖች ያለገደብ በአስቸኳይ

በሚያዚያ ወር 1968 ዓ.ም በጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ የጸደቀ የብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራም በክፍል 3 በጊዜው አጣዳፊ ተግባሮች ስር ከዚህ የሚከተለውን አስፍሮ ይገኛል።

“ሕዝቡ በአብዮቱ መግፋት የሚችለው ነቅቶ፣ ተደራጅቶ፣ ታጥቆ ለትግሉ የተሟላ ዝግጅት ሲኖረው ብቻ በመሆኑና ይህ ዝግጅት የሰመረ ውጤት ሊሰጥ የሚችለው የሰፊው ሕዝብ ወገኖች በሙሉ ለመማር፣ ለማስተማር፣ ለመደራጀትና ለማደራጀት አስፈላጊ የሆኑት ዲሞክራሲያዊ መብቶች ያለአንዳች ገደብ ከሥራ ላይ ሲወሉ ብቻ ስለሆነ ለፀረ-ፊውዳል፣ ፀረ-ቢሮክራሲያዊ ቡርዧ፣ ፀረ-ኢምፔሪያሊስት ኃይሎች በሙሉ የመናገር፣ የመፃፍ፣ የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ፣ የመደራጀትና የመሳሰሉት ሰብአዊ ዲሞክራሲያዊ መብቶችን በአስቸኳይ ከሥራ ላይ ማዋል ነው።”

በዚህ ፕሮግራም ውስጥ የዲሞክራሲያዊ መብቶች ለጭቁኖች ያለገደብ ባስቸኳ የመለቀቅ ጉዳይ በማያሻማ ቋንቋ የተገለጸ ቢሆንም በየምክንያቱ ነገሩ እየተድበሰበሰ በመዘግየቱ ዛሬ የአብዮቱና የኢትዮጵያ ሕዝቦች አንድነት የሕይወት እስትንፋስ ጥያቄ ለመሆን በቅቷል። የአብዮቱና የሕዝቡ ጥያቄዎች ባለመሟላታቸውና በአድሃሪው ቢሮክራሲ ማነቆ የተነሳ አብዮቱ ወደ ተከላካይነት አፈግፍጓል።

ከአብዮቱ ወደኋላ ማፈግፈግ ጋር የተያያዘው የሰፊው ሕዝብ ጠላቶች ማንሰራራት ብቻ ሳይሆን የአብዮታዊት ኢትዮጵያ ህልውና በውጪ ወራሪ መደፈር ነው። በውስጥ የሚቦረቦረውን አብዮትና በውጪ ወረራዎች የተደፈረውን አንድነት ለማዳን የሕዝባችንን ሃይል አስተባብሮ በጠላቶቹ ላይ በድል አድራጊነት ለማዝመት በተቻለ ነበር። የዲሞክራሲ መብቶች ለጭቁኖች ያለገደብ ባስቸኳይ መለቀቁ በአብዮቱ ሰፈር ለሚገኙት ብዙ ችግሮች መፍትሄ ይሰጣል።

  1. ሰፊው ሕዝብ እንደ አሁኑ “ከላይ” የሚተላለፉትን ውሳኔዎች በመፈፀም ብቻ ሳይወሰን በአብዮቱ ጥያቄዎች ላይ በሚደረገው ውሳኔ አወሳሰድም ስለሚያሳትፈው አብዮቱን እንደራሱ አድርጎ ይመለከተዋል። በአብዮቱ ሰፈር የተሰለፉት ልዩ ልዩ ኃይሎች በመካከላቸው ያለውን ግንኙነት በየወቅቱ ለማስተካከልና ያሉትንና ሊነሱ የሚችሉትን ልዩነቶች ለማቻቻል ያበቃቸዋል። በትግሉም ውስጥ የሚያጋጥማቸውን የጋራ ችግሮች ለመፍታትና ለማስወገድ ለመወያየት የሚያስችላቸው ዲሞክራሲያዊ መድረክ ይከፍትላቸዋል። ቁጥራቸው በርከት ያለ አብዮቱን መደገፍ የሚገባቸው ጭቁኖች ከመወናበድ ወይንም ከንቃተ ህሊና ዝቅተኝነት የተነሳ በአብዮቱ ላይ በጽኑ ያማረራሉ። ወይም ይቃወሙታል። በእነዚህ በተወናበዱት ጭቆኖች መካከል ከፍተኛ ቅስቀሳ አድርጎ ወደ አብዮቱ ሰፈር ለመመለስ በር ይከፍታል።
  1. የተራማጆችን ህብረት እውነት ያደርገዋል። በተግባር የሚተረጉምበትን ሁኔታ በጣም ያፋጥነዋል። የዲሞክራሲ መብቶች ለጭቁኖች ያለገደብ አለመለቀቅን ተገን አድርገው አሉባልታና ሃሜትን የሚነዙትን ለማጋለጥ ያስችላል። ሰፊው ሕዝብ አብዮታዊ መሪዎችን መከተል፣ አስደናቂ ንግግሮቻቸውን ማድመጥ ብቻ ሳይሆን “መመሪያ” ለመስጠት፣ ለመከታተልና ለመቆጣጠር ይችላል። አሁን በሰፈነው የታፈነና በፍራቻ የተወጠረ የፖለቲካ አካባቢ ሰፊው ሕዝብ መሪዎቹን ለመረምና ለመቆጣጠር በሌላ አነጋገር ከእነርሱ ጋር የጠበቀ ዳይሌክቲሪካዊ ግንኙነት ሊመሰረት አይችልም።
  2. ሰፊው ሕዝብ ስልጣንን ለመጨበጥ እንዲችል፣ ለዚህም የሚያደርገውን ትግል እንዲያፋፍም ሰፊ በር ይከፍትለታል። እንቅስቃሴውን ከቢሮክራሲው በማላቀቅ በሕዝባዊ ድርጅቶች አማካኝነት የአስተዳደርን ተግባር ደረጃ በደረጃ ለመረከብ ይበቃል።

ከዚህ በላይ እንደተጠቀሰው የብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራም የዲሞክራሲያዊ መብቶች ለጭቁኖች ያለ ገደብ የመለቀቁን ጉዳይ ከጊዜው አጣዳፊ ተግባሮች ውስጥ አስገብቶታል። እንደዚሁም በደርግ ውስጥ የነበረው የእነዓለማየሁ ኃይሌ የቀኝ ክንፍ ሴራ በኋላ በጥር 27/1969 የጊዜያዊ ወታደራዊ ደርግ ሊቀመንበር የዲሞክራሲያዊ መብቶች ለጭቁኖች ያለ ገደብ በአስቸኳይ እንደሚለቀቅ በአደባባይ ለተሰበሰበ ሕዝብ አስታውቀው ነበር። የኢትዮጵያ ተራማጅ ድርጅቶች በየካቲት ወር 1969 ባወጡት የጋራ መግለጫ ላይ የዲሞክራሲ መብቶች ለጭቁኖች ያለ ገደብ እንዲለቀቁ እንደሚታገሉ አረጋግጠው ነበር። ይሁንና የጋራ መግለጫውን ከፈረሙት ውስጥ አንዳንዶች በኋላ እንደታየው በዚህ ጥያቄ ላይ ማፈግፈግ ጀመሩ። ተጨማሪ ምላስ አብቅለው መናገር ጀምረዋል። አብዮታዊ ሰደድ፣ የወዛደር ሊግና ማሌሪድ አቋማቸውን ቀይረዋል፣ ትናንት የተናገሩትን ቃል አጥፈዋል።

እንደሚታወቀው አብዮታዊው የመሬት አዋጅ የፊውዳሊዝምን የኢኮኖሚ መሠረት ቢደመስሰውም የፊውዶ-ቡርዧ ላዕላይ መዋቅር አሁንም ቢሆን አልተነካም። ከታሪክ እንደምንማረው የእኛም የአብዮት ታሪክ እንዳረጋገጠው የፊውዳሊዝም ኢኮኖሚ መሠረት መደምሰስ የሥርዓቱን ላዕላይ መዋቅር መፈራረስ ወዲያውኑ አያስከትልም ማለትም አብሮት አይወድምም። የሰፊው ሕዝብ ከፖለቲካ መድረክ መገለልና በጌታ እና በሎሌ መመስረት በአእምሮ ውስጥ የተቀረፀውን አስተሳሰብ፣ ልምድ ወዘተ ለመቀየር ረዥምና ውስብስብ ትግል ማካሄድ ያስፈልጋል። ሰፊው ሕዝብ አሁንም ቢሆን ሕልውናውን መልሶ አልተጎናፀፈም፣ ማንነቱን በሚገባ አልተረዳም። የኢምፔሪያሊዝም በጠቅላላው መስመር አድሃሪነትና ቢሮክራሲው ደግሞ ኢትዮጵያን በመሳሰሉ አገሮች ውስጥ በጭቆና፣ ዘረፋና ብዝበዛ ላይ የተመሰረተ መዋቅር መሆኑን ስንረዳ ለኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ እነዚህን ጠላቶቹን ለማውደም ዴሞክራሲያዊ መብቶች ያለ ገደብ ምንኛ እንደሚያስፈልጉት ለመረዳት ባላስቸገረ ነበር።

የዲሞክራሲ መብቶች ለጭቆኖች ያለገደብ በአስቸኳይ እንዳይለቀቁ የሚቃወሙት ድርጅቶች የሚሰጧቸው ብዙ ምክንያቶች አሉ። ይህንን በዝርዝር በሌላ ጊዜ እንመለስበታለን። ግን ከሚያቀርቧቸው ምክንያቶች ውስጥ ባጭሩ የሚከተሉት ይገኙባቸዋል።

ሀ/ አሁን ባሉን ዲሞክራሲያዊ መብቶች መቼ መጠቀም ቻልንና ነው ተጨማሪ መብቶችን የምንጠይቀው?

ዛሬ ሰፊው ሕዝብ በቀበሌ፣ በገበሬ፣ በሰራተኛ ማህበራት በመደራጀት አንዳንድ የጋራ ጉዳዮች ላይ ለመወያየትና ውሳኔም ለመድረስ ይችላል። እነዚህ ድርጅቶች ለእያንዳንዱ የሕዝብ ክፍል በተወሰኑና በመለስተኛ ጥያቄዎች ላይ መብት ቢሰጡትም፣ ጠቅላላውን ሕዝብ በሚመለከትና መሰረታዊ በሆኑ የአብዮቱ ጥያቄዎች ውሳኔ አሰጣጥ ውስጥ በግልፅና በዲሞክራሲያዊ መንገድ አያሳተፉትም። በሌላ አነጋገር መብቶች ጠባብ ናቸው። አሁን ለተያዘው ትግል አይበቁም። ሰፊው ሕዝብ አብዮቱንና የኢትዮጵያን ሕዝቦች አንድነት በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ሀሳቡን ለመግለጽ ለመወያየትና ለመፃፍ መድረክ አላገኘም።

በእነዚህ ውስን መብቶችም ቢሆን ሙሉ በሙሉ ለመጠቀም አልተቻለም። ይህንን ለመረዳት መቻል ያስፈልጋል። ብዙ ምክንያቶች አሉ። አንዱ ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለጭቁኖች ያለገደብ ታፍኖ በመያዙ ተራማጅ የስውር ድርጅቶች በነዚህ ሕዝባዊ ድርጅቶች አካባቢ እንደ ልብ እንዳይንቀሳቀሱ አለመቻላቸው ነው።

ከዚህ ጋር ተያይዞ መታለፍ የሌለበት ነገር የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ በፍጹም አድርባይነት በመዋጡ እምነቱ በተራማጆች እና በሰፊው ሕዝብ ከመሆን ይበልጥ ወደ ቢሮክራሲ በማዘንበሉ እነዚህን ውስን መብቶች ሰፊው ሕዝብ ለመጠቀም እንቅፋት እያጋጠመው ነው። በየቦታው ብዙ ሀገር ወዳጆችና ተራማጆች ይታሰራሉ፣ ይጉላላሉ፣ አልፎ አልፎም ይረሸናሉ። በአሁኑ ሰዓት የዲሞክራሲ መብቶችን ለጭቁኖች ያለገደብ በአስቸኳይ መለቀቅን ይበልጥ አንገብጋቢ ከሚያደርጉት ምክንያቶች ውስጥ አንዱ ይህ ሁኔታ እየተባባሰ መምጣቱ ነው።

ለ/ የዲሞክራሲ መብቶችን ለጭቁኖች ያለ ገደብ ማለት ለስልጣን መቋመጥ ነው የሚለው አቋም፦

ይህ ደግሞ ምክንያቶቹ ሁሉ አስቂኝና ከጨነቀው ሰው አእምሮ የሚፈልቅ ነው። ማረሻውን ከበሬው ፊት ያስቀምጠዋል። በመጀመሪያ ነገር አንድ ለስልጣን የቋመጠ ቡድን ወይም ድርጅት በሰፊው ሕዝብ ጀርባ እየተሽሎከለከ በስልጣን ኮርቻ ላይ ፊጥ ለማለት ይሞክራል እንጂ እንዴት የሰፊውን ሕዝብ መናገርን፣ መሰብሰብን፣ መደራጀትን፣ በጠቅላላው ሕዝባዊ ንቅናቄን ይመርጣል። የዲሞክራሲ መብቶች ለጭቁኖች ያለ ገደብ አሁን ይለቀቁ ማለት ሰፊው ሕዝብ ስልጣን ለመጨበጥ እንዲችል አስፈላጊ የሆኑትን መሳሪያዎች ያግኝ ማለት አይደለም ወይ?

ሐ/ አገራችን በጦርነት ውስጥ ስለምትገኝ የዲሞክራሲ መብቶች ለጭቆች ያለ ገደብ አሁኑኑ መታወቅ የለባቸውም የሚለው ምክንያት፦

ይህ ነገሩን የተገላቢጦሽ የሚመለከት አቋም ነው። እንዲያውም ከዚህ ጦርነት ውስጥ አሸናፊ ሆኖ ለመውጣትና የብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮትን ፕሮግራም በሥራ ለመተርጎም ዴሞክራሲያዊ መብቶች ለጭቁኖች ያለ ገደብ መለቀቅ አለባቸው። ይህ ጦርነት ሕዝባዊና አብዮታዊ እስከሆነ ድረስ የሰፊውን ሕዝብ ሙሉ ተሳትፎ ይጠይቃል። ሰፊው ሕዝብ ለማንና ለምን እንደሚዋጋ አውቆ ትግል ውስጥ እንዲገባ ማድረግ ያሻል። ይኸም አብዮታዊ ውሳኔውን፣ ለመስዋዕትነት ዝግጅቱን ጀግንነቱን እጅግ በጣም ይጨምርለታል።

መ/ ዲሞክራሲያዊ መብቶች አሁኑኑ ቢለቀቁ ይበልጡን የሚጠቀሙት የሕዝብ ጠላቶች ነው የሚለው ምክንያት፡-

እንደዚህ ያለው ምክንያት የሚቀርበው ተጨባጭ ሁኔታን በደንብ ካለመረዳትና ከዚያም የኃይሎችን ሚዛን በደንብ ለማጤን ካለመቻል ነው። እንደሚባለውም የዲሞክራሲ መብት ለጭቁኖች ያለገደብ ቢለቀቁ አድሃሪዎች በዚህ ሳቢያ ተሽሎኩልከው አንዳንድ የማወናበድ ተግባሮች ሊፈጽሙ ይችላሉ። ይህንን ሀቅ መቀበሉና ከአሁኑም ለዚሁ ዝግጅት ማድረጉ ጥሩ ነው። ግን ደግሞ የጠላትን ኃይል ከልክ በላይ አጋኖ ማቅረብ ከፍተኛ ስህተት ውስጥ ያስገባል። አሁን ያለው ሁኔታ እንዲያውም ያመቸው ለፀረ-ሕዝብ ኃይሎች ነው። የፀረሕዝብ ኃይሎች ምሽግ የሆነውን አድሃሪ ቢሮክራሲ የቅልበሳ ሴራውን ለመቋቋም የሚቻለው ሰፊውን ሕዝብ በማነቃነቅ ብቻ ነው። ዲሞክራሲ መብቶች ለጭቁኖች ያለ ገደብ አሁኑኑ ቢለቀቁ በጣም ይበልጡን የሚጠቅምበት የሰፊው ሕዝብ ወገን ነው።

የጠላትን ኃይል እያጋነነ የሚያቀርበው ይህ አቋም በሌላ በኩል ደግሞ የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ባለፉት ሦስት ዓመታት ከጠላቶቹ ጋር ባደረገው ትንቅንቅ ምንም አይነት የትግል ልምድ እንዳላገኘ፣ አሁንም ቢሆን ጠላቶቹ እንደፈለጋቸው ሊደልሉት እንደሚችሉ አድርጎ ማቅረቡ ነው።

እነዚህ ላይ የዘረዘርናቸው ነጥቦች በአሁኑ ወቅት የዲሞክራሲ መብቶች እንዳይለቀቁ ከየአቅጣጫው በተደጋጋሚ የሚቀርቡት ዋና ዋና ምክንያቶች ሲሆኑ፣ አንዳንድ ተራማጅ ድርጅቶች በተናጠል የሚያቀርቧቸው የራሳቸው የሆኑ ልዩ አቋሞችና ሰበቦች አሉ። በዲሞክራሲ ጥያቄ ላይ የወዝ አደር ሊግና ማሌሪድ አቋማቸውን በግልጽ አስታውቀዋል። እነዚህ ሁለት ድርጅቶች የዲሞክራቲክ መብቶች ለጭቁኖች አለገደብ ሊለቀቁ አይችሉም ወይንም መለቀቅ የለባቸዉም በማለት የሚያቀርቧቸውን ምክንያቶች የክርክር ነጠቦች በአጭሩ ከዚህ በታች እንመለከታለን።

የማሌሪድ ልሳን ሬቮሉሽን ቁጥር 21 ስለ ዲሞክራሲ ምንነት ሰፋ ያለ ትንተና /ትንተናው ያልተብራሩ ነጥቦች ቢይዝም/ ከሰጠ በኋላ ከአሁኑ ደርግ የዲሞክራቲክ መብቶች ለጭቁኖች ያለ ገደብ ሊገኙ እንደማይችሉ ለማሳመን ከዚህ የሚቀጥለውን አስቀምጧል።

“በኢትዮጵያ ውስጥ በስልጣን ላይ ያለው አስተዳደር የግራ ዝንባሌ ስላለው ለሕዝብ ጥያቄዎች ይበልጥ መልስ ለመስጠት ፈቃደኛ ስለሚሆን የዲሞክራሲ መብቶችን ያለ ገደብ ሊያውጅ ይችላል የሚል አከራከር በአንድ አካባቢ ይሰጣል። (ጋራ መግለጫው ተረስቷል ሰ.ህ.ድ!!) እርግጥ ነው በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አስተዳደር ለሕዝብ ጥያቄዎች የዝሆን ጆሮ አልሰጠም። እስካሁን ከሕዝቡ ጎን ቆሟል፣ የሪቮሉሽኑንም ሂደት አግዟል። ግን በመጨረሻ ትንተና ላይ የሕዝብ አስተዳደር ስላልሆነ፣ አሮጌውም የመንግሥት አውታር ገና ስላልተደመሰሰ፤ በዚህ ሁኔታ የዲሞክራሲ መብቶች ለጭቆኖች ያለገደብ ከቶ ሊገኝ አይችሉም። ከዚህ ሁኔታ የዲሞክራሲ መብቶች ለጭቁኖች ያለገደብ ሊገኙ ቢችሉ ኖሮ ዲሞክራሲ የመንግሥት ገጽታ ነው የሚለው የሌኒን አባባል ትክክል ባልሆነም ነበር፣ ሕዝባዊ መንግሥትንም ማቋቋም አስፈላጊነቱ አይኖርም ነበር”።

በዚህ ረገድ ሬቮሉሽን ቁ.21 የብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራም የዲሞክራሲ መብቶች ለጭቆኖች ያለ ገደብ ባስቸኳይ የሚለው አንቀፅ እንዲታረም ለጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ሀሳብ ቢያቀርብ ኖሮ አስተያየቱን ሙሉ ያደርገው ነበር።

እንደዚሁም በየካቲት ወር 1969 ዓ.ም ከሌሎች የኢትዮጵያ ማርክሲስት-ሌኒኒስት ድርጅቶች ጋር በወጣው የጋራ መግለጫ ላይ ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለጭቁኖች ያለገደብ ባስቸኳይ እንዲለቀቁ ማሌሪድ ከሌሎች ተራማጅ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ለመታገል የገባው ቃል ኪዳን በስህተት (!) ነው ብሎ ቢያምን አስተያየቱን ያሟላው ነበር።

ሬቮሉሽን ቁጥር 21 የሚያምታታቸው ብዙ ነገሮች አሉ። የማይረዳው ወይንም አውቆ የሚዘነጋቸው ነጥቦች አሉ። ዲሞክራሲ የመንግሥት ገፅታ መሆኑን ሌኒን በመጥቀስ ለማሳየት ይሞክራል። ግን ደግሞ ሌኒን በሌላ ቦታ አጠቃላይ ሕጎችን ከተጨባጭ ሁኔታ ጋር ማገናዘብ ወይንም ተጨባጭ ሁኔታን በተጨባጭ መንገድ መተንተን የማርክሲዝም እምብርት መሆኑን አልተናገረም ወይ?

የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ምንድነው?

እርግጥ ያለው መንግሥት የሕዝብ መንግሥት አይደለም። እንዲያውም ብዙ ፀረ-ሕዝብ እርምጃዎችን የፈፀመና የሚፈጽም መንግሥት ነው። ይህ ደርግ በሕዝብ ግፊትና ትግል የተነሳ አንድ አብዮታዊ መንግሥት ሊወስድ የሚችለው እርምጃዎችን (እንደመሬት አዋጅ) እንደወሰደ እናያለን። ይህ ደግሞ ከደርግ የመደብ ይዘት፣ ካለው ህብረተሰባዊ ሚናና ታሪካዊ ቦታ ጋር በቅርብ የተያያዘ ነው።

ኢህአፓ የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታና የደርግን ምንነት በሚገባ ከማጥናት ይልቅ “በአጠቃላይ ሕጎች” በመመስረት ደርግ የጭቁኖች መንግሥት ስላልሆነ ጭቁኖችን የሚጠቅም እርምጃ ሊወስድ አይችልም የሚለውን አቋም ስለወሰደ የደርግን አብዮታዊ እርምጃዎች ሁሉ እስከመቋቋም ደረሰች። ይህንን አቋም እንዴት በቶሎ ረሳው።

የሬቮሉሽን ቀ. 21 መሰረተ ሃሳብ የድሮውን ሥርዓት ተደምስሶ ሕዝባዊ ሥርዓት ካልተመሰረተ የዲሞክራሲ መብቶች ለጭቁኖች ያለ ገደብ ሊኖሩ አይችሉም ነው። እርግጥ ዲሞክራሲያዊ መብቶችና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት በቅርብ የተያያዙ ቢሆኑም በመካካላቸው ልዩነት እንዳለንና እስከ ተወሰነ ደረጃም ቢሆን ሊነጣጠሉ እንደሚችሉ መዘንጋት የለበትም። ከየካቲት 1917- ጥቅምት 1917 በሩሲያ ውስጥ ሰፍኖ የነበረውን ሁኔታ የተመለከተ የተግማማው አድሃሪ ቢሮክራሲ እያለ ጎኑ ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለጭቁኖች የለገደብ ተለቀቀው የሕዝባዊ ሥርዓት እንጭጭ መፍለቅ ጀምረው እንደነበረ ለማየት ይቻላል። በአንድ በኩል የፊውዳል ቢሮክራሲው፣ በሌላ በኩል አብዮታዊ ዲሞክራሲ የሆነው ሌላውን ለማጥፋት ከፍተኛ ትንቅንቅ ውስጥ ይገኙ ነበር። የህብረተሰብን ታሪካዊ ሂደት በደረቁ ሳይሆን በተጨባጭ መንገድ የተመለከተና የመረመረ በወሳኝ ወቅቶች እንዲህ አይነት ሁኔታዎች ሊፈጠሩ እንደሚችሉ ይረዳል። ማሌሪድ “አጠቃላይ ሕግን” በጥንቃቄ ከልያዙት መደናበርን እንደሚያስከትል የተገነዘበው አይመስልም።

ማሌሪድ በደርግ እና በአድሃሪው ቢሮክራሲ መካከል ልዩነት ለማድረግ ፈጽሞ አልቻለም። የዲሞክራሲ መብቶች ለጭቁኖች አለመኖሩን ዋና ምክንያት አድርጎ የሚመለከተው ደርግን ሳይሆን ቢሮክራሲውን ነው። አህያውን ቢፈሩ ዳውላውን! ለዴሞክራሲ መብቶች ለጭቁኖች አለገደብ አለመለቀቅ ዋና ምክንያት ደርግ እንጂ ቢሮክራሲው አይደለም። በእውነትም ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለጭቁኖች አለገደብ ቢለቀቅ ቢሮክራሲ ይህንን ለማጨናገፍ ከፍ ያለ መፍጨርጨር ማድረጉ አይቀርም። ዳሩ ግን የመንግሥትን ስልጣን የያዘው አካል ዲሞክራሲያዊ መብቶችን ለጭቁኖች ያለ ገደብ እንዲለቅ ቢገደድ፣ ሰፊው ሕዝብ የቢሮክራሲን ተጽዕኖ እየታገለ እነዚህን መብቶች ለማስከበር ይችላል። ሰፊው ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ መብቶችን ለማስከበር የሚችለው ቢሮክራሲውን እየታገለ ብቻ ሳይሆን ቢሮክራሰውን ለመደምስስ የዲሞክራሲያዊ መብቶች ያለ ገደብ ያስፈልጉታል።

ሬቮሉሽን ቁ. 21 በሌላ ቦታ ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለጭቁኖች ያለገደብ እንዲለቀቁ መታገልን “ኢትዮጵያን በሚመለከት በኩል ይህ አቋም በስልጣን ላይ ያለውን አስተዳደር መመፃደቅ” አድርጎ ይወስደዋል። ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለጭቁኖች ያለገደብ ባስቸኳይ እንዲለቀቁ አደርጋለሁ ብሎ የገባውን ቃል እንዲያከብር ሰፊው ሕዝብ በመጠየቁ ተመፃዳቂ የሚያደርገው ምክንያት ፈጽሞ ግልጽ አይደለም። እንደሚታወቀው ሰፊው ሕዝብ ለደርግ የሚያቀርባቸው በርካታ ጥያቄዎች አሉ። ምክንያቱም ስልጣንን የጨበጠው አካል ነውና። ሰፊው ሕዝብ ይህንን ስላደረገ ተመፃዳቂ፣ “ለማኝ” የሚያሰኘው ምንድነው? ዋናው ነገር ደርግን ለመተካት እስከ ተሳነው ድረስ በአንድ በኩል ደርግን እየታገለ በሌላ በኩል ጥያቄዎች እንዲሟሉ እየተጋደለ ለወደፊት ትግሉ ኣመቺ ሁኔታዎችን ለመፍጠር መቻሉ ነው። የማሌሪድ ደርግን “አትመፃደቅ” ማለት ቃሉን እንዲጠብቅ አትወትውቱት በተለይ ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለጨቁኖች በሚመለከተው በኩል አሁኑኑ ብላችሁ አታስበርግጉት ነው!

የወዛደር ሊግ አቋም እንደማሌሪድ የዲሞክራሲ መብቶች ለጭቁኖች ያለ ገደብ ሊለቀቁ አይችሉም የሚል ሳይሆን እነዚህ መብቶች መገደብ አለባቸው ነው። በወዝ ቁጥር 32 ከዚህ የሚከተለው አስፍሯል።

“ሃቀኛ ተራማጆች” “ዲሞክራሲ መብቶች ለጭቆኖች ያለገደብ” በሚልና በሌሎች ተመሳሳይ መፈክሮች ተክተውታል። ይሁን እንጂ “ያለገደብ” የሚለው ሀረግ አሁንም ቢሆን አሻሚና የዲሞክራሲን ትርጉም የሚፃረር ፅንሰ ሀሳብን ያዝላል። ርግጥ ገደብ በሕዝቡ ላይ መጣል የለበትም ማለቱ ትክክል ነው። ነገር ግን ሕዝቡ መረን የሌለው፣ ሥነ ሥርዓትና ዲሲፕሊን የማይቀበል ሁሉ በፈለገው የሚሄድበትን ዲሞክራሲ አይፈልግም። ሕዝቡ በድርጅቱ ማለትም በወዛደሩ ፓርቲ እማኝነት ሥርዓቱን ያወጣል፣ መንገድን ይቀይሳል፣ በሌላ አነጋገር ገደቡን ይተልማል። ስለሆነም የዲሞክራሲ መብቶች ለጭቁኖች የሚለው መፈክር ይመረጣል።”

ይህ አባባል ግራ ከመጋባቱም በላይ አደገኛ አዝማሚያዎችን ያዘለ ነው። ግራ ያጋባል የምንለው መጀመሪያ ከፍ ብሎ “በሕዝቡ ላይ ገደብ መጣል የለበትም” ብሎ ከተቀበለ በኋላ ትንሽ ወረደ ብሎ ደግሞ መብቶች መገደብ እንዳለባቸው አስታወቃል።

  1. ሊግ እንደሚለው ሳይሆን የሰፊው ሕዝብ መብቶች፣ መብቶች ባጠቃላይ ሊገደቡ አይችሉም፣ ለምሳሌ የንግግርን መብት ብንወስድ፣ እንዴት አድርገን ነው የምንገድበው፣ ለሰፊው ሕዝብ እስከዚህ ድረስ ልትናገር ትችላለህ፣ ከዚያ ወዲያ ለመናገር አትችልም ልንለው እንችላለን ወይ?

ሊግ የዲሞክራሲያዊ መብቶች ለጭቁኖች መገደብ አለባቸው የሚለው ዲሲፕሊንና ስነ-ሥርዓት ይጠፋል ከሚል ስጋት ነው። ግን ዲሞክራሲ የራሱ ውስጣዊ ሥርአትና ዲስፕሊን እንዳለው ለማሰላሰል አልቻለም ወይም ሌላ ፍራቻ አለው። በምርጫ ጊዜ ጥቂቱ የብዙሀኑን ውሳኔ መቀበል እንዳለበት፣ የዲሞክራሲ መብት አለኝ ብሎ የሌሎችን ዜጎች መብት አለመፃረር የሚያሳዩት ዲሞክራሲ መብትን ብቻ ሳይሆን ግዴታም እንደሚያጠቃልል ነው። ይህ ግዴታ ግን ገደብ ሳይሆን መብቱ ሊረጋገጠ የሚችልበትንና ለዚህም መሟላት ያለበት አይነተኛ ሁኔታ ነው። ማለትም መብትና ግዴታ፣ ነጻነትና ሥነ- ሥርዓት የዲሞክራሲ ጣምራ ገጽታ ናቸው።

በተረፈ የወዛደር ሊግ ይህንን ነጥብ በሚመለከተው በኩል በሬሳ ላይ ነፍስ ለመዝራት እንደሚሞከር ግልጽ ነው። ባለፈው ዓመት በገደብ ያለ ገደብ በሚለው ጥያቄ ላይ ሰፊ ክርክር ተደርጎበት ካለቀለትና ከደቀቀ በኋላ እንደገና መልሶ መምጣቱ አንድ አይነት ድንገተኛ “በሽታ” ገብቶ ካልሆነ በስተቀር ለማወቅ አስቸጋሪ ነው።

  1. ወዝ ቁጥር 32 እንደሚለው መብቶቹን የሚገድበው የወዛደር ፓርቲ ከሆነ የወዛደሩ ፓርቲ ከመፈጠሩ በፊት የዲሞክራሲ መብቶች ለጭቁኖች ቢለቀቁ ማን ሊገድበው ነው? ያለው አድሃሪ ቢሮክራሲ ነው? አድሃሪው ቢሮክራሲ እያለ በሌላ በኩል ደግሞ ሰፊው ሕዝብ ከቢሮክራሲው ማነቆ እንዲላቀቅና ትግሉን ወደፊት ለማራመድ እንችል ከመቼውም ይበልጥ ዲሞክራሲያዊ መብቶች በሚያስፈልጉበት ወቅት የዲሞክራሲ መብቶች ለጭቁኖች መገደብ አለባቸው /ገና ሳይኖሩ!/ እያሉ መናገር ሕዝቡ ለዴሞክራሲያዊ መብቶች የሚያደርገውን ትግል ማደናቀፍ ነው። ሌላ ትርጉም የለውም።

የወዛደር ሊግ “ዲሞክራሲ መብቶች ለጭቁኖች” የሚለው መፈክሩ ከአስተሳሰቡ ጋር አብሮ አይሄድም። ከአስተሳሰቡ ጋር የሚስማማው መፈክር “የዲሞክራሲ መብቶች ለጭቁኖች በገደብ” የሚለው ነው።

የወዛደር ሊግ የወዛደሩን ፓርቲ አመሰራረት ከዴሞክራሲያዊ መብቶች ለጭቁኖች ያለ ገደብ በአስቸኳይ ከመለቀቅ ጋር አያይዞ እንደማይመለከተው በሌላ ቦታ ተገልጿል። ሊግ ለተራማጆች ህብረት፣ ውህደትና የወዛደሩ ፓርቲ መመስረት ዴሞክራሲያዊ መብቶች ለጭቁኖች ያለ ገደብ አስፈላጊ መሆናቸውን አያምንም። እንደ ሊግ አባባል “ይህ የግራ ክንፍ የሚገኘው የተራማጆች ህብረት በውይይትና በትግል ተፈትኖ በመጠናከር ወደ ውህደት ሲያመራ ብቻ ነው” ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለጭቁኖች ያለገደብ መለቀቅ ያለበት። በመሠረታዊ ጥያቄዎች ላይ ለሰፊው ሕዝብ ሳይገለፅ፣ በሰፊው ሕዝብ ጀርባ የሚደረጉት ውይይቶችና ስምምነቶች አብዮታዊ ሥራዎች ያለመሆናቸውን እንዴት ሊግ ሊረዳው አይችልም። ያለዲሞክራሲ ውይይት ማካሄድ በጣም ያስቸግራል፣ በትግልም የተፈተነ ጥንካሬን ለማፍለቅ ያዳግታል።


የጊዜያዊ ወታደራዊ ደርግ ታሪካዊ ኃላፊነት

የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ የሰፊውን ሕዝብ እንቅስቃሴ በመፍራት ወይም በመናቅ አሁን እንደተያዘው በሲቪልና በወታደራዊ ይበልጡን መቆጣጠርን ከመረጠ ከሰፊው ሕዝብ ይራራቃል። በኋላም መንግሥትና ሕዝቡ ሁለት የተለያዩ ቋንቋዎች መናገር መጀመራቸው አይቀርም።

የዲሞክራሲ መብቶች ለጭቁኖች ያለ ገደብ ባስቸኳይ የመለቀቅ ጉዳይ ዛሬ የሰፊው ሕዝብ ጥያቄ ሆኗል። አሁን በኢትዮጵያ ያሉ ተራማጅ ድርጅቶች በዚህ ጥያቄ ላይ የተለያየ አቋም አላቸው። ይሁንናም በተራማጅ ድርጅቶች መካከል እኩልነት ስለሌለ ማለትም አንዳንዶቹ በጊዜያዊ ወታደራዊ የአስተዳደር ደርግ ይበልጥ ተደማጭነት ስላላቸው የዚህን ጥያቄ አንገብጋቢነት ከአብዮቱ ሂደት አንጻር ለመመልከት አስቸጋሪ ሁኔታን እንደሚፈጥር ጥርጥር የለውም።

የሀቀኛ ተራማጆች ህብረት ይመስረት!
የፊውዶ ቡርዧው ቢሮክራሲ ይውደም!
የነቃ፣ የተደራጀ፣ የታጠቀ የሕዝብ አመጽ ያሸንፋል!
ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለጭቁኖች ያለ ገደብ አሁኑኑ!!
Scroll to Top