የሰፊው ሕዝብ ድምፅ
ቁጥር 47፣ ጥቅምት 11፣ 1969
የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ
መኢሶን በዚህ የሰፊው ሕዝብ ድምፅ እትሙ፣ የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ድሎችን በተጎናጸፈ ቀጥር፤ በአንጻሩ ጠላቶቹ ድሎቹን ለመንጠቅና ትግሉን ለመገደብ ኃይላቸውን በእጥፍ እያሳባሰቡ መምጣታቸውን ያሰፍራል። ስለዚህም፣ ሕዝቡና ተራማጆች ሳይዘናጉ ትግላቸው አጠንክረው እንዲቀጥሉ ያበረታታል።በ1969 ዓ.ም. መጀመሪያ ላይ በኢሕአፓ የተጠሩት የሥራ ማቆም አድማዎች፣ ተቃውሞ ሰልፎች፤ እንደ ዶ/ር ፍቅሬ መርዕድ፣ ገብረ እግዚአብሔር ሃጎስና ሌሎች ግንባር ቀደም ታጋዮች ላይ የተካሄዱት ግድያዎች እንዲሁም ሻለቃ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ላይ የተደረገው የግድያ ሙከራ ሁሉ የሕዝባዊ ትግሉን ጉዞ ለመቀልበስ የተዘጋጁ ፀረ-አብዮታዊ ድርጊቶች መሆናቸው በማስረጃነት ያቀርባል።
የኢትዮጵያ ጭቁን ሕዝቦች ታሪካዊውን የየካቲት እንቅስቃሴ ከከፈቱ ከሁለት አመት ተኩል በላይ ሆኗል። በዚህ ጊዜ ውስጥ ያገባደድነው አብዮታዊ ጉዞ ውጣ ውረድ የበዛበት ነበር። ብዙ መሰናክሎችም ገጥመውናል። ወደፊትም፣ አብዮታችንን ከግቡ ለማድረስ በምናደርገው ትግል የሚቀረን ጉዞ እንዲሁም ውጣ ውረድ ይሆናል። ከፊታችን የሚጋረጡ አያሌ መሰናክሎች ይኖራሉ። ሆኖም፣ የሚጠይቀውን መስእዋትነት ከፍሎ አብዮቱን ከግቡ ለማድረስ ቆርጦ የተነሳ ሰፊ ሕዝብ የሚቀረው ጎዳና ውጣ ውረድ የበዛበት በመሆኑ ትጥቁን አይፈታም። በመሰናክሎች መብዛት አይሸበርም። አድሃሪውን ሥርዓት በመደምሰስ የመዘዘውን ሰይፍ የጠላቶቹን ምሽግ እስኪያፈርስበት ድረስ መልሶ አያጥፈውም።
ባለፉት የትግል ጊዜያት እንዳየነው የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ በትግሉ አንድ ታሪካዊ ድል በተቀዳጀ ቁጥር ጠላቶቹ ይህን ድል መልሶ ለመንጠቅ በእጥፍ ድርብ ኃይል ይነሳሳሉ። እስከ አሁን ተራማጅ ኃይሎችና ሰፊው ሕዝብ ያገኟቸውን ድሎች ላለማስነጠቅ ባካሄዱት ከባድ ትግል አድሃሪዎች የተገኙትን ድሎች መልሰው ለመንጠቅ አልቻሉም። ቢሆንም የሕዝብ ጠላቶች ተስፋ ቆርጠው እጃቸውን አጥፈው አልተቀመጡም። የሕዝብ ጠላቶች ከታሪክ መድረክ ላይ በማያዳግም ሁኔታ እስካልተወገዱ ድረስ ተሸናፊነታቸውን ተቀብለው ቁጭ አይሉም። በሰፊው ሕዝብ ክንድ በተጎሸሙ ቁጥር በይበልጥ ተጠናክረው በትግሉ ሜዳ ላይ ብቅ ይላሉ። ለዚህ ነው ደግመን ደጋግመን እስካሁን በተደረገው ትግል የኢትዮጵያ ጭቁኖችና የአብዮታችን ጠላቶች አልተሸነፉም፣ ሁለቱም ተጻራሪ ኃይሎች የተቃራኒ ግቦቻቸው ተመሳሳይ ዝግጅቶች በማድረግ ላይ ናቸው የምንለው።
በአገራችን፣ ከሐምሌ አጋማሽ ጀምሮ እስከዛሬ የምናየው ሁኔታ በአብዮትና በፀረ አብዮት ኃይሎች መካከል ከፍተኛ ትንንቅ እየተካሄደ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው። በሻለቃ ሲሳይ ሃብቴ/ጄኔራል ጌታቸው ናደው መሪነት ፋሺስታዊ የመንግሥት ግልበጣ ሙከራ ተደርጐ ከሸፈ። ከዚሁ የመንግሥት ግልበጣ ሙከራ ጋር ተያይዞ በአናርኪስቶች የተጠራ የሥራ ማቆም ሙከራ ተቀጨ። መስከረም ሁለትን ሰፊው ሕዝብ እንደ የድል በር ከፋች ቀን እንዳያከብረው የተደረገው የተቀነባበረ ቅስቀሳ ከሸፈ። በከሃዲ ወጣቶችና በተገዙ ቦዘኔዎች የተደረገው አውቶቡስ ሰበራና ሁከት ፈጠራ የሰፊውን ሕዝብ አብዮታዊ ቁጣ አጋጋለው እንጂ ሽብር ፈጣሪዎችና ቀልባሾች የተመኙትን አላስገኘም። ከመስከረም ሁለት አንስቶ ወዛደሩ ሥራ እንዲያቆም የተደረገው የአናርኪስቶች ፀረ አብዮታዊ ጥሪ ሰሚ ሳያገኝ ቀረ። እነዚህ ሁሉ ሙከራዎች ካለውጤት ቢቀሩም ሙከራውን ካካሄዱት ቀልባሾች በኩል ከፍተኛ ዝግጅት ተደርጐባቸው ነበር።
ሰፊውን ሕዝብ በተባባሪነት አሳልፎ ሁከት በመፍጠር በሚነሳው ግርግር ውስጥ እርኩስ ዓላማቸውን ከሥራ ላይ ለማዋል ያደረጓቸው ተከታታይ ሙከራዎች አልሆን ሲሉ፣ አድሃሪዎች፣ አናርኪስቶችና ቀልባሽ ኃይሎች ሁሉ ለየት ወዳለ የትግል ዘዴ ዞረዋል። መስከረም 12 ማታ የደርጉን ተቀዳሚ ም/ሊቀመንበር ሻለቃ መንግሥቱ ኃይለማርያምን ለመግደል ሙከራ ተደርጐ ከሸፈ። ይህ ሙከራ በአንድ ግለሰብ ላይ እንደተፈጸመ ድርጊት የሚታይ አይደለም። ከዚህ ሙከራ ቀደም ብሎ በአናርኪስቱ ቡድን ጋዜጦችና በአድሃሪ ኃይሎች በተካሄደው ሰፊ ቅስቀሳ ላይ እንደሚታየውም የግድያ ሙከራው ዓላማ ደርጉ ውስጥ ያሉትን ተራማጆች ለማለያየትና ለማዳከም፣ ጭቁኑን ወታደር ለመከፋፈል ነበር። በዚህ ትርምስ ውስጥ ደርጉ ሲዳከም በሲአይኤ ቅጥረኞች የሚመራ የአሻንጉሊት መንግሥት ለመፍጠር ነበር። ከዚያም ወዲህ ለትክክለኛ መስመርና ለጭቁኖች እውነተኛ ነፃነት በቆሙ ሃቀኛ አብዮታውያን ላይ ብዙ አደጋዎች ጥለዋል። የኢትዮጵያ ሃቀኛ ተራማጆችም እንደ ጓድ ፍቅሬ መርእድን፣ እንደ ጓድ ገብረእግዚአብሄር ሃጐስን የመሰሉ ግንባር ቀደም ታጋዩች አጥተዋል። ቀልባሾች የኢትዮጵያን አብዮት ለመቀልበስ በሚያደርጉት ትግል ግንባር ቀደም ታጋዩችን በማጥፋት የአብዮቱን ሰፈር ለማዳከም በጀመሩት በዚህ የትግል ዘዴ መግፋታቸው የማይቀር ነው።
የሆነ ሆኖ፣ ያለፉት ወራት አድሃሪዎች አብዮቱን ለመቀልበስ ያደረጉት መፍጨርጨር የታየበት ወቅት ብቻ አልነበረም። የአብዮት ኃይሎችም ያገኙዋቸውን ድሎች ለመጠበቅ፣ ለሚቀሩዋቸው ድሎች በይበልጥ ለመዘጋጀት ሲጣደፉ የታዩበት ወቅት ነው። መስከረም ሁለት በመላ ኢትዮጵያ በጋለ ድምቀትና አብዮታዊ ስሜት መከበሩ ሰፊው ሕዝብ በአብዮቱ ላይ ያለው እምነት እየፀና መሄዱን አሳይቷል። በዚሁ እለት በተደረጉት ሰልፎች የተያዙት መፈክሮች ሰፊው ሕዝብ በትክክለኛ የፓለቲካ መስመር ስር እየተሰለፈ መሄዱን አብስረዋል። በአናርኪስቶች ጥሪ፣ በቢሮ ከበርቴው ድጋፍ የተሞከሩ የሥራ ማቆም አድማዎች መክሸፍ ሰርቶአደሩ በራሱ አብዮት ላይ አምጾ የጠላቶቹ መጠቀሚያ ከመሆን እየራቀ መሄዱን አረጋግጧል። ቀልባሾች በሻለቃ መንግሥቱ ላይ የቃጡትን የመግደል ሙከራ፣ ያደረጉትን የሥራ ማቆም አድማ ጥሪ በመቃወም፣ ሲአይኤ፣ ኢዲዮና ኢህአፓን በማጋለጥና በመቃወም ሰፊው ሕዝብ ከዳር እስከዳር ባደረጋቸው አብዮታዊ ሰልፎች ወዳጅና ጠላትን እየለየ መሄዱን አስመስክሯል። በግንቦት/67 በአርናኪስቶች ውንብድና ምክንያት የተበተነው የፋብሪካ ወዛደሮች ስብሰባ በአራተኛ ወሩ እንደገና ተጠርቶ የተሳካ ውጤት ማስገኘቱ የወዛደሩ ሰፈር ከአናርኪስቶችና ሰርጎገብ አድሃሪዎች እየፀዳ መሄዱን አመልክቷል። ባንድ ቃል፣ ያለፉት ወራት አብዮቱን በሰፊው ሕዝብ ውስጥ በይበልጥ ሥር እየሰደደ መሆኑን ያስገነዝቡናል። አድሃሪዎች ጭቁኖችን አወናብደው ከጎናቸው ለማሰለፍ ያደረጉዋቸው ሙከራዎች እየከሸፉ መሆኑን አሳይተውናል።
በነዚህም ወራት የአናርኪስቱ ቡድን ተዋርዶ ከፖለቲካው መድረክ ወጥቷል። ይህ የሃቀኛ ተራማጆች የርዮተዓለምና የፖለቲካ ትግል ውጤት ነው። የኢትዮጵያ ሃቀኛ አብዮታውያን አንድነታቸውን ገንብተው ለጭቁኖች ትግል አብዮታዊ አመራር ለመስጠት በሚያደርጉት ትግል ከፍተኛ ቦታ የሚይዝ ድል ነው። ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የሀገራችን አናኪስቶች በውንብድናና የነፍስ ግድያ ሙከራ ላይ የተሠማሩትም በደረሰባቸው የፖለቲካ ክስረት ምክንያት ነው። ስለሆነም፣ በፖለቲካው መድረክ ተጋልጦ ሰፊው ሕዝብ አንቅሮ የተፋው የከሃዲ አናኪስቶች ቡድን ወደ ማጅራት መቺነትና ወደ ነፍሰ ገዳይነት መቀየሩ የሚገርም ነገር አይደለም። በየትኛውም የአብዮት ታሪክ የታየ ነው። አስመሳይ ተራማጆች በሕዝብ ፊት ተጋልጠው ከፖለቲካ መቃብራቸው ሲደርሱ ወደ ነፍሰ ገዳይነት ይቀየራሉ።
በዛሬው ተጨባጭ ሁኔታ ከፀረ አብዮት ሰፈር ከሁሉም የሚሯሯጡ የሚመስሉት ቀልባሽ አናርኪስቶች ቢመስሉም ሁለት ቁም ነገሮችን ማስተዋል ያስፈልጋል። አንደኛ ነገር የኢህአፓ ቀልባሾች የውንብድና ተግባሮቻቸውን የሚያካሂዱት በራሳቸውና ለብቻቸው አይደለም። የአብዮቱ ጠላቶች ሁሉ ድጋፍና ትብብር አላቸው። ሁለተኛ ነገር ላይ ላዩን ሲታይ ከፀረ አብዮት ኃይሎች ሁሉ ይበልጥ የሚፍጨረጨሩት የኢህአፓ ነፍሰ ገዳዮች ቢመስሉም፣ የፀረ አብዮት ዋና ኃይል እነርሱ አይደሉም። ኢትዮጵያን ሕዝቦች ትግል ከቅልበሳ ለማዳን የምናደርገው ትግል ከነዚህ መሠረታዊ ሀቆች መነሳት ይኖርበታል።
የኢትዮጵያ በዝባዥ መደቦች፣ እንኳን ዛሬ ብዙ ሚሊዮን ጭቁኖች ከዳር እስከ ዳር ተነስተውባቸው በሚርበደበዱበት ጊዜ ይቅርና ቀድሞውንም ካለኢምፔሪያሊዝም /በተለይም የአሜሪካ/ እርዳታ የጭቆናና የብዝበዛ ሥርዓታቸውን በራሳቸው ሊያስጠብቁ አልቻሉም ነበር። አሁን፣ ለ‘ዳግማዊ ትንሳዔያቸው’ በሚታገሉበት ወቅት የቀድሞ ረዳት-ጌታቸው በይበልጥ ከጎናቸው ቆሟል። የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ነፃነታቸውን ባላስጠበቁ አገሮች ሁሉ እጁን አስገብቷል። የበላይነትና ጣልቃ ገብነቱን ለማቆየት ቀጥተኛ ወረራ አንድ ዘዴው ሲሆን፣ በርከት ባሉ አገሮችና ሁኔታዎች የተጠቀመው ሲአይኤ በተባለው የስለላና የነፍሰ ገዳይ ድርጅቱ አማካይነት ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠላቶች ዛሬ በሚያካሄዱት ፀረ አብዮት ትግል የሚያስተባብራቸው፣ የሚያግዛቸውና የሚመራቸው የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ሲአይኤ በተባለው ድርጅት አማካኝነት ነው።
የኢትዮጵያ ቢሮክራሲ የፊውዳሊዝምን ጥቅም ለማስጠበቅ የቆመ የጭቆና መሳሪያ ነው። ባለፉት ጊዜያት በሰፊው ሕዝብ ትግል ተኮርኩመ እንጂ እንዳያንሰራራ ሆኖ አልተደቆሰም። በጋዜጣችን ደጋግመን እንዳነሳነው ሁሉ ኢምፔሪያዝምና ሌሎችም አድሃሪዎች የኢትዮጵያን አብዮት ቀልብሰው ሊያቋቁሙ ለሚያቅዱት አሻንጉሊት ፋሺስታዊ መንግሥት በመሪነት የታጨው የቢሮ ከበርቴው ነው። ባንድ በኩል ይህንን የፀረ አብዮት ሚናውን የተረዳ በመሆኑና በሌላ በኩል በእንቅስቃሴው ብዙ ባለመመታቱ ከፍተኛ የፖለቲካ ሥልጣን ዛሬም ስላለው የኢትዮጵያ ፀረ አብዮት ዋነኛ የመደብ መሰረት ይኸው የቢሮ ከበርቴው መደብ ነው። የፊውዳሉ መደብ ከየካቲት ጀምሮ ብዙ ጥቃቶች ደርሶበታል። ይህን መደብ በፖለቲካ ሥልጣን ያስወገዱና የብዝበዛ መሰረቱን የገረሰሱ ድሎች ተገኝተዋል። ሆኖም የዚህ መደብ አባሎችና ርዝራዦች ከሲአይኤና ከቢሮ ከበርቴው ጋር በመተባበር በፀረአብዮቱ ሰፈር ውስጥ ዛሬም ከፍተኛ ተሳታፊነትና አስተዋጽኦ አላቸው።
ዛሬ አብዮታችንን ለመቀልበስ ዋነኛው አደጋ የሚመጣው ከቀልባሽ አናርኪስቶች ውርውር አይደለም። አናርኪስቶች ከላይ በጠቀስናቸው የአብዮቱ ዋነኛ ጠላቶች የተለኮሰውን ፀረ አብዮት ይበልጥ እንዲቀጣጠል ከማራገብ ያለፈ ሚና የላቸውም። የኢትዮያን አብዮት ለመቀልበስ ዋነኛው አደጋ የሚመጣው በሲአይኤ ተቀናብሮ፣ ቢሮ ከበርቴው ላይ ተመስርቶ፣ ሌሎች አድሃሪ ኃይሎችን ሁሉ አጠቃሎ የሚካሄደው ፀረ አብዮት ትግል ነው። ይህ የፀረ አብዮት ኃይል ዛሬ በተለይ በከተሞች በንቃት በድፍረትና በተለይም በትጥቅ ከአብዮቱ ኃይሎች ልቆ ይገኛል። የገጠሩ አድሃሪ በብዛት በአርሶ አደሮች ቆራጥ ትግል ትጥቁን ሲፈታ፣ ከነትጥቁ ሸሽቶ ከተማ የመሸገው አያሌ ነው። የከተማን አድሃሪ ዛሬም እስከ አፍንጫው ታጥቋል። በከተሞች፣ በተለይም በአዲስ አበባ ከፍተኛ የፀረ አብዮትኃይሎች ክምችት አለ። ይህ የታሪኩ አንድ ገጽ ሲሆን፣ በሌላ በኩል በገጠር ፀረ አብዮት ኃይሎች አሁንም እንዳልተደመሰሱ ሌላኛው ሃቅ ነው። ከኢምፔሪያሊስቶችና ከጐረቤት አገር አድሃሪዎች ጋር በሙሉ ትብብር የሚሰሩት የነመንገሻ ሥዩም ኢትዮጵያ “ዲሞክራቲክ” ሕብረት/ኢዲህ/ና ኢኤልኤፍ በመሳሪያ ኃይል አብዮቱን ለመቀልበስ የሚያደርጉትን ዝግጅት ከመቼውም ይበልጥ አፋፍመዋል።
እንደዚህም በመሆኑ ከሁለት ዓመት ተኩል በላይ ሲካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ጭቁኖች አብዮታዊ ትግል ከከፍተኛ ፈተና ላይ መሆኑን ሃቀኛ ተራማጆችና ሰፊው ሕዝብ መረዳት ይኖርባቸዋል። የኢትዮጵያ ጭቁኖች ትግል ከዚህ ፈተና ባስቸኳይ ይወጣ ዘንድም የአብዮቱ ኃይሎች የንቃት፣ የድርጅትና በተለይም የትጥቅ ዝግጅት በኣስቸኳይ መሟላት አለበት። በንቃት፣ በድርጅትና በተለይም በትጥቅ ለቀልባሾች የሚያደላው የኃይል ሚዛን በፍጥነት ለሰፊው ሕዝብ ወደሚያደላበት ደረጃ መድረስ አለበት። አብዮቱን ከቅልበሳ ለማዳንና ከግብ ለማድረስ ያለው አማራጭ የለሽ መፍትሄ ይኸው ብቻ ነው። የነቃ፣ የተደራጀና የታጠቀ የሰፊው ሕዝብ ኃይል መገንባት ብቻ ነው።
ንቃትን በሚመለከተው በኩል፣ የኢትዮጵያ ሃቀኛ ተራማጆች በትክክለኛና አብዮታዊ መስመር ላይ ያካሄዱት ቅስቀሳና ኘሮፓጋንዳ ፍሬ እየሰጠ ነው። ተራማጅ መስሎ ሰፊውን ሕዝብ ሲያወናብድ የቆየው የከሃዲ አናርኪስቶች ቡድን ዛሬ አድሃሪ እርቃኑን ቀርቷል። የሰፊው ሠርቶ አደር ንቃተሕሊና የማይናቅ የወደፊት እርምጃ አድርጓል። ድርጅትን በሚመለከተውም በኩል፣ በሰፊው ሕዝብ ውስጥ መሠረት እየጣሉና እየተጠናከሩ የመጡ፣ በአብዮታዊ የፖለቲካ መስመር ላይ የቆሙ ተራማጅ ድርጅቶችና ቡድኖች አሉ።
የኢትዮጵያ ሃቀኛ ተራማጆች ከነዚህ የትግላቸው ውጤቶች ተነስተው በቆራጥነት ከታገሉ የሰፊዉን ሕዝብ የንቃትና የድርጅት ዝግጅት ባጭር ጊዜ ውስጥ ከከፍተኛ ደረጃ ሊያደርሱ ይችላሉ። ስለሆነም፣ የአድሃሪዎች መጠናከርና የፀረ አብዮት ትግላቸውም መፋፋም እጅግ አሳሳቢ በሆነበት ባሁኑ ወቅት ሃቀኛ ተራማጆች የማንቃትና የማደራጀት ተግባራቸውን በእጥፍ ድርብ መጨመር፣ ያለ የሌለ ኃይላቸውን የነቁ ወዛደሮችና ሃቀኛ ተራማጆች የሙያ ማህበራትን አጠናክሮ አብዮቱን ከቅልበሳ ለማዳን በሚደረገው ትግል ተገቢ ቦታ ለማሲያዝ፣ የአብዮቱን ወደፊት መቀጠል ዋስትና የሆነውን የወዛደር ፓርቲ የሚያደርጉትን ትግል ከመቼውም የበለጠ ማፋፋም ይኖርባቸዋል።
ደጋግመን እንደምናነሳው፣ የኢትዮጵያ ሃቀኛ ተራማጆች እነዚህን ሁሉ ታሪክ የጣለባቸውን ኃላፊነቶች ለመሸከም የሚችሉት አንድነታቸውን በፅኑ መሰረት ላይ ሲገነቡ ብቻ ነው። በተለይ ዛሬ፣ ምድረ አድሃሪ አንድነቱን አጠናክሮና ኃይሉን ሰብስቦ በኢትዮጵያ አብዮት ላይ በመጣበት ወቅት፣ የሃቀኛ ተራማጆች አንድነት መገኘት እጅግ አጣዳፊ ሆኗል። በእንደዚህ አይነቱ አጣዳፊ ጊዜ በቡድን ስሜት፣ በፀጉር ስንጠቃ፣ የቅንጦት ክርክር የዚህን አንድነት በአስቸኳይ መገንባት ማዘግየት በኢትዮጵያ ጭቁኖች ትግል ላይ ይቅርታ የሌለው በደል መፈፀም ነው። ስለዚህ፣ አብዮቱ የጣለብንን የግንባር ቀደምነት ኃላፊነት ለመወጣት፣ አንድነታችንን እንመስርት፣ ለዚህም ሌት ተቀን እንታገል። የአድሃሪዎችን ፀረ-ሕዝብ አንድነት በሃቀኛ ተራማጆችና የሠፊው ሕዝብ አብዮታዊ አንድነት ካልተቋቋምን አናሸንፍም። ወቅቱ ፋታ የማይሰጥ የተፋፋመ የመደብ ትግል የሚካሄድበት ወቅት ነው። ዛሬ ቸልተኝነት፣ ለነገ ማለት፣ ዳተኝነት፣. . . ለፀረ አብዮት ኃይሎች ድል በር መክፈት ነው።
የኢትዮጵያ ተራማጆችና ሰፊው ሕዝብ በአድሃሪ ኃይሎች በይበልጥ የተቀደሙት በትጥቅ ጉዳይ ነው። አብዮታዊ ኃይሎች ሺ ጊዜ ቢነቁና ቢደራጁ የትጥቅ ኃይል እስካልተጨመረበት ድረስ በምንም ተዓምር የታጠቁ ጠላቶቻቸውን ድል ሊመቱ አይችሉም። ዛሬ በምንገኝበት ተጨባጭ ሁኔታ የትጥቅ ጥያቄ ያለምንም ጥርጥር ለአብዮቱ የሕይወት እስትንፋስ ጥያቄ ሆኗል። በተለይ በከተሞች፣ የአድሃዎች ትጥቅ መፍታት ወይም አለመፍታት፣ የተራማጅ ኃይሎችና ንቁ ሰርቶ አደሮች መታጠቅ ወይም አለመታጠቅ የአብዮቱን የቅርብ ጊዜ እድል ይወስናል። የአብዮቱ ኃይሎች በአስቸኳይ ከታጠቁና ፀረ አብዮት ኃይሎች ትጥቅ ከፈቱ አብዮታችን ከመቀልበስ ድኖ በድል ጎዳና ላይ ወደ ፊት ይገሰግሳል። የአድሃሪዎች ከፍተኛ የትጥቅ ዝግጅት በተፋጠነበት ባሁኑ ወቅት የአብዮት ኃይሎች መታጠቅ በሰበብ ባስባቡ ከዘገየ ግን በአብዮታችን ላይ የተጠመደው አደጋ በይበልጥ ይጨምራለ። ስለሆነም፣ በአሁኑ ጊዜ የትጥቅ ጉዳይ በያዝ ለቀቅ የሚተው ጉዳይ ሳይሆን የአብዮት ወሳኝ ጥያቄ ነው።
ቀልባሽ አናርኪስቶችን በሚመለከተው በኩል፣ የአብዮቱ መቀልበስ ዋነኛ አደጋ የሚመጣው ከአናርኪስቶች ውር ውር አይደለም ስለተባለ፣ ሃቀኛ ተራማጆችና ሰፊው ሕዝብ እነዚህ ግልገል ፋሺስቶች በአብዮቱ ኃይሎች ላይ የሚያደርሱትን ጥቃት በዝምታና በቸልታ ያልፉታል ማለት እንዳልሆነ ጠላቶቻችን ሁሉ ሊረዱት ይገባል።
የኢህአፓ ግልገል ፋሽስቶች ግንባር ቀደም ታጋዮችን በመግደልና በጠቅላላው በአብዮቱ ሰፈር ሽብር ፈጥረው ለአብዮቱ ቅልበሳ ሁኔታውን ለማመቻቸት ከፍተኛ ፀረ አብዮት ሚና በመጫወት ላይ ናቸው።በዚህ ፀረ አብዮት ሚናቸውም ከለየላቸው የሕዝብ ጠላቶች የሚለዩበት ነገር የለም። እነርሱም እንደተቀሩት የሕዝብ ጠላቶች ሁሉ በተራማጅ ኃይሎችና የሰፊው ሕዝብ የተባበረ ክንድ መደምሰስ አለባቸው።
የኢትዮጵያ ሀቀኛ ተራማጆች በአብዮታዊው የፖለቲካ መስመራቸውና በርዕዮተአለም ጥራታቸው ላይ ሙሉ እምነት ስላላቸው እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ እነዚህ ሰርጎገብ አድሃሪዎች በፖለቲካው መድረክ ላይ በማጋለጥ ላይ ብቻ አተኩረው ነበር። የቀልባሽ አናኪስቶቹንም ቡድን ደጋግመው ለዲሞክራሲያዊ የፖለቲካ መስመር ትግል ጋብዘው ነበር። የኢህአፓ ነፍሰ ገዳዮች በፖለቲካው መድረክ ላይ ተሸነፈው ወደ ውንብድና ተግባር ሲዛወሩ ግን፣ ሀቀኛ ተራማጆች በቀድሞ የትግል ዘዴያቸው ብቻ አይጠቀሙም።
የሀቀኛ ተራማጆች መሰረታዊ አላማ፣ ሰፊው ሕዝብ ደመኛ ጠላቶቹን ለመደምስስ በሚያደርገው አብዮታዊ ዓመፅ በግንባር ቀደምነት እየተሳተፉ የጭቁኖችን እውነተኛ ነፃነት ለማስገኘት ነው። ለዚሁ እየታገሉ ሳሉ፣ ጓዶቻቸው በቅጥር ነፍሰ ገዳዮች እየተቀነጠቡ ሲወድቁ ግን ዝም ብለው አያዩም። የያዙት አብዮታዊ ትግል እንጂ ወንጌል ሰበካ ስላልሆነ ግራ ጉንጫቸው ሲመታ ቀኝ ጉንጫቸውን አይሰጡም። በፖለቲካው ትግል ከስረው ወደ ነፍሰ ገዳይነት የተሻገሩ ከሃዲዎችን የውንብድና ተግባር በአንድ ቃል እያወገዙ ህልውናቸውን ለመጠበቅ እና ለማሳየት አፀፋውን ለመመለስ ይገደዳሉ። የኢትዮጵያ ሀቀኛ ተራማጆችም ከቀልባሽ አናርኪስቶች የሚሰነዘርባቸውን ማንኛውንም ጥቃት እንደየመልኩ ለመቋቋምና አጸፋውን ለመመለስ ተዘጋጅተዋል።