የሰፊው ሕዝብ ድምፅ
ቁጥር 68፣ ጥር 11፣ 1970
የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ
በዚህ እትም መኢሶን፣ ደርግ የንዑስ ከበርቴው መደብ አባል በመሆኑ፣ ከአብዮቱ ኃይሎች ጋር የሚያደርገው ጉዞ አንድ ደረጃ ላይ እንደሚያከትምና ከአድሃሪያን ጋር እንደሚሰለፍ ቢሆንም ግን ከእንግዲህ ወዲህ ሰልፌን ቀይሬያለሁ ብሎ ከትግሉ መንሸራተቱን በይፋ እንደማያውጅ ያረጋግጣል። በደርጉ ውስጥ የነበሩ አድሃሪዎች ከተመቱ በኋላ፣ ተራማጅ የነበሩት አባላቱ ቀስ በቀስ እንዴት መወላወል እንደጀመሩና እምነታቸውንም ከሕዝብ ይልቅ ወደ ቢሮክራሲው ያዞሩበትን ሂደት ያሳያል። ይህም በመሆኑ ይታወጃል የተባለው የዴሞክራሲ መብቶች አዋጅ ተሰርዞ፣ በምትኩ በብዙ መስዋዕትነት የተሠረቱት ሕዝባዊ ድርጅቶች መፍረሳቸውን፣ ሃቀኛ ተራማጆች፣ አገር ወዳዶችና ዴሞክራቶች ፣መታሰራቸውን፣ መሰቃየታቸውና መገደላቸውን ይጠቁማ። በመጨረሻም ለብሄራዊ ዴሞክራሲያዊ አብዮት የቆሙ ኃይሎች ሁሉ አንድነታቸውን አጠንክረው ለዴሞክራሲ መብቶች መከበር እንዲታገሉ ጥሪውን ያድሳል።
“መላ የኢትዮጵያ ተራማጆች ከገዛ ሀገራቸው ትግል፣ ከሌሎች ጭቁኖች አብዮትና ከሳይንሳዊ ቲዎሪ ቀስመው ሲያስተጋቡት የቆዩት ሀቅ ምንድነው? ብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮትን ንኡስ ከበርቴው መደብ መርቶ ከግቡ ሊያደርሰው የሚችል ኃይል አይደለም የሚል ሀቅ ነው። በሌላና በተጨባጭ አነጋገር ምን ማለት ነው? ይህ ማለት አንደኛ ንዑስ ከበርቴው መደብ የአብዮቱ ግንባር ቀደም ኃይል በነበረበት ጊዜ ሰፊውን ሕዝብ ከጀርባው ለመሰብሰብ ሲል ያቀርባቸው የነበሩትን ፕሮግራሞች፣ ያስተጋባቸው የነበሩትን መፈክሮች ይክዳቸዋል፣ ይሽራቸዋል ማለት ነው። ሁለተኛ ንዑስ ከበርቴው መደብ በማንኛውም ትግል ውስጥ ራሱን ችሎ የሚሄድ ኃይል ባለመሆኑ የቀድሞ መፈክሮቹንና በነሱ ስር የተሰለፈውን ሰፊ ሕዝብ ለመዋጋት ከሱ በስተቀኝ ካሉ ኃይሎች ላይ መመርኮዝና በአብዮቱ ላይ ማሴር ይጀምራል ማለት ነው። ሦስተኛ በዚሁ ልክ ደግሞ የቀኝ ኃይሎች አብዮቱን ለመምታት፣ አብዮታዊያንን ለማሳደድ መሣሪያ አድርገው ይጠቀሙበታል ማለት ነው። ዛሬ በኢትዮጵያ የምናየው ይኽንኑ ነው።”
የአብዮት ፋና የመኢሶን ወጣት ክንፍ- የኢትዮጵያን አብዮታዊ ወጣቶች ንቅናቄ ልሳን ቁጥር 15- 25/3/70።
ከዛሬ ዓመት በፊት የኢትዮጵያ አብዮታዊያን እንደዚህ ግልጥልጥ ባለ ሁኔታ ያስተጋቡት ሀቅ ምንኛ እውነት እንደሆነ ዛሬ ያልተረዳ ማን አለ? የንኡስ ከበርቴው ደርግ ታሪካዊ ሚና የተወሰነ ነው ሲባል ሁኔታውን ከፍ ብለን በጠቀስነው መልክ ያልተመለከቱ ብዙ ተራማጆች ነበሩ። የደርግ ታሪካዊ ሚና አንድ የተወሰነ ደረጃ ሲደርስ ያከትማል ሲባል ደርግ ከዚህ “በተባለው ቦታ” ሲደርስ ጋግርት እንደያዘው ሰው ወደፊትም ወደኋላም አልልም ብሎ ባለበት የሚቆም የሚመስላቸው ብዙዎች ነበሩ። አብዮታዊያን ግን የደርግ ሚና ውስን ነው ሲሉ አንድ ደረጃ ከደረሰ በኋላ ከላይ በጠቆምነው መልክ መሽቆልቆል ይጀምራል ማለታቸው ነበር። ነውም። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ከላይ ተጠቁሟል። ንዑስ ከበርቴው መደብ ራሱን ችሎ የሚቆም መደብ አይደለም። ቀደም ሲል የታሪክ ማእበል ከሱ ቁጥጥር በሆነው ሁኔታ እያወከበ አምጥቶ እስከ ትግሉ ግንባር ቀደም ድረስ ያግደረደረውን ያህል የሕዝቡ አብዮታዊ ትግል እያየለ ሲሄድ ደግሞ ይህ መደብ ምንጊዜም ቢሆን ወደ ከበርቴው መደብ ለመንጠራራት ባለው ጉጉት ታግዞ አብዮቱን ለመቋቋም የእርቅ እጁን ወደ ጠላቶቹ ይዘረጋል። ይህ ህብረት ደግሞ ንዑስ ከበርቴውን ከጠጋኞች ሕልምና ቁጥጥር ውጪ በሆነው ሁኔታ እንደዚሁ እያዳፋ በጸረአብዮት ቁልቁለት ያወርደዋል። የቀኝ ኃይሎች ከላይ እንደተባለው “አብዮቱን ለመምታትና አብዮታዊያንን ለማሳደድ መሣሪያ አድርገው” ከተጠቀሙበት በኋላ ወደ ተሰናዳለት ቦታ ማለትም ወደ ታሪክ ትቢያ መጣያ ያወርዱታል።
ሂደቱ ይህ ነው። ነገር ግን ይህንን ሂደትና መንሸራተት ከድርጊቶችና ከተጨባጩ ሁኔታ መገንዘብ እንጂ ንኡስ ከበርቴው መደብ ከፕሮግራሙ መንሸራተቱን፣ ከቀኝ ኃይሎች ጋር ህብረት መፍጠሩን፣ አብዮታዊያንን ማሳደዱን በአጭሩ ሚናው ማክተሙን በአዋጅ ያበስራል ብሎ መጠበቅ አደገኛ የዋህነት ነው። እንኳን ለተወሰነ ጊዜ በአብዮቱ የትግል ማዕበል ውስጥ የግንባር ቀደምነት ሚና የደረሰው የህብረተሰብ ክፍል ቀርቶ ያረጀውና ያፈጀው የፊውዳል መደብ እንኳን ጣረሞቱን በሰፊ ሕዝብ ላይ በማመፅ ያራዝማል እንጂ “ጊዜ አልፎብኛል” ብሎ በገዛ ፈቃዱ መታለፉንና መበስበሱን አያበስርም።
ዛሬ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ከደርግ ጋዜጣና ሬድዮ ልፈፋዎች ባሻገር የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ የሚያሳየው የማይታበል ሀቅ ይኸው ነው። ዛሬ ተራማጆችና ሰፊ ሕዝብ ለአዲስ ሕይወታቸውና ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ክብር ያለ የሌለ ተስፋቸውን የጣሉበት አብዮታቸው የኋሊት መንሸራተት መጀመሩን፣ ለጊዜውም ቢሆን በተከላካይነት እያፈገፈጉ ለመታገል መገደዳቸውን፣ በሀገራችንም የፖለቲካ መድረክ ላይ ጠጋኞች፣ የለየላቸው አድሀሪዎችና የብሔራዊ ክብራችንና ነፃነታችን ጠንቅ የሆኑ ኃይሎች የበላይነትን ይዘው መፈንጨት መጀመራቸውን እጅ እጅ ማለት ከጀመረው የደርግ ልፈፋ አልፈው መመልከት ጀምረዋል።
ይህ መንሸራተት እንዴት መጣ? ያስከትለውስ ውጤት ምንድነው?
የመላው የኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ ይህንን አጠቃላይ መንሸራተትና በአብዮታችንና በብሔራዊ ነጻነታችን ላይ ሊያስከትል የሚችለው እጅግ አደገኛ ሁኔታ በግንበር ቀደምነት በመገንዘብ ለታሪክ፣ ለእናት አገርና ለአብዮት ደማቸውን ባፈሰሱት ኢትዮጵያዊያን ፈተና በሰፊው ሕዝብ ፊት የገባውን ቃል በማክበር ከአንድ አመት ተኩል በፊት የትግል ስልት ለውጥ ማድረጉ ይታወሳል። በዚያን ወቅት ይህ የተደረገው ውሳኔ በአካባቢውና በወቅቱ በነበሩ ምክንያቶች ብቻ የተወሰደ ውሳኔ አልነበረም። መኢሶንን ወደዚህ ውሳኔ ያደረሱት በጠቅላላው ከአብዮቱ ሂደት ጋርና በተለይ ከጥር 26 በኋላ ደርግ በሱ በስተቀኝ ካሉ ኃይሎች ጋር እንደገና አዲስ ህብረት ከመፍጠሩ ጋር የተያያዙ ምክንያቶች ናቸው።
ይህ አዲስ የቀኝ ኃይሎች ህብረት ከተጠነሰሰበት ከመጋቢት ሚያዚያ 1969 ዓ.ም እንስቶ መንሸራተት ሌላ መንሸራተትን እየወለደ ዛሬ አብዮታችንና ብሄራዊ ነፃነታችን የሚገኙበት አሳዛኝና አሳፋሪ ሁኔታ እሰክንደርስ ድረስ ያለው ታሪክ አንድ መልኩ የዚህ የቀኝ ኃይሎች ህብረት እየተጠናከረ መምጣት ታሪክ ነው። ይህንን በይበልጥ ለመረዳት የሀገራችንን ሁኔታ በቀልባሾች በነ ዓለማየው ኃይሌ መሪነት ደርግ ከቀኝ ኃይሎች ጋር መስርቶት የነበረው ህብረት ድል ከተመታበት አካባቢ ተነስቶ ማየት ያስፈልጋል።
አዲሱ የቀኝ ኃይሎች ሕብረት አመጣጥና ጠባዩ
የሕዝብ ድርጅት ጉዳይ ጊዜያዊ ጽ/ቤት ከተቋቋመ እና የብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራም ይፋ ከወጣ ወዲህ በሀገራችን አብዮትና ፀረአቢዮት የታገሉት ከዚህ ፕሮግራም አንጻር ወገን ለይተው ነበር። ከዚህ ፕሮግራም መታወጅ በኋላ በኢትዮጵያ ምድር ገሃድ እየሆነ የመጣው ሃቅ በአንድ በኩል በፕሮግራም አካባቢ የተሰለፈው ህዝብ አብዮታዊ ትግሉን ለማካሄድም ሆነ ራሱን በራሱ ለማስተዳደር በሚያስችሉት ሕዝባዊ ድርጅቶቹ አገሪቱን ማልበሱ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የሰፊውን ሕዝብ ትግል ግንባር ቀደምነት መስመር ለማስያዝ የሚታገሉት ነባርም ሆኑ አዳዲስ የፖለቲካ ቡድኖች እየተጠናከሩ መሄዳቸው ነበር። በዚህ የተነሳ በተለይ ከ1969 መጀመርያ አንስቶ በማደግ ላይ ባሉት የሰፊው ሕዝብ ድርጅቶች በአብዮታዊ የፖለቲካ ቡድኖች፣ በሕዝብ ድርጅት ጉዳይ ጊዜያዊ ጽ/ቤት በአንድ በኩል፤ የቀድሞ ስልጣን የበሰበሰ አውታር በሆነው ቢሮክራሲ፣ በኢዲዮ፣ በኢህአፓና በሌሎች ፀረሕዝቦች በሌላ በኩል የሞት የሽረት ትግል ተፋፋመ። በዚህ ትግል አድሃሪው ሰፈር የአብዮቱን የተለያዩ ኃይሎች ለመደምሰስ በነጭ ሽብር ተሰማራ። አሰራራቸውና እድገታቸውን ለማሰናከል ፀረዲሞክራሲን አነገሰ። ስለሆነም ከዚህ ወሳኝ ትግል በድል አድራጊነት ለመውጣት አብዮታዊያን ከዳር እስከዳር ሁለት መፈክሮችን አነሱ። ትጥቅ። ዲሞክራሲ።
በዚህ በሁለት ሰፈሮች በሚካሄደው ትግል ደርግ ራሱን ከሁለት ተከፍሎ ይታገል ነበር። በዚህ ወቅት ጸረ ሕዝብ የነበረውን ክፍል ይወክል ነበረው የነዓለማየሁ ኃይሌ ክንፍ “በአብዮታዊ ሰደድ” አካባቢ የተደራጁት ተራማጅ የደርግ አባላት ደግሞ ለትጥቅ፣ ለዲሞክራሲ፣ ለሕዝባዊ ድርጅቶች ማበብ፣ ለሕዝብ ድርጅት ጉዳይ ጊዜያዊ ጽ/ቤት ቤት ያለቢሮክራሲ ተፅዕኖ መስራት፣ ለአብዮታዊ ቡድኖች መስፋፋት፣ ለሃቀኛ የተራማጆች ሕብረት መጠናከር፣ ለብሄራዊ ነፃነታችን አለመደፈር … ወዘተ የሰፊው ሕዝብ ሰፈር ግንባር ቀደም በመሆን በቆራጥነት ይታገሉ ነበር። በዚህ ትግል ውስጥ አብዛኛው የደርግ አባል የት ነበር? በነዓለማየሁ በኩል ነበር። አብዛኛው የደርግ አባል በተለይ በህዳርና በታህሳስ 1969 ዓ.ም የደርግ ቋሚ ኮሚቴ ውስጥ ለቀልባሾቹ ቁልፍ ጽቦታዎችን ሲያስጨብጥ ለሕዝቡ ጥያቄዎች በግንባር ቀደምነት ወራት በተካሄደው የተጧጧፈ ትግል በነዓለማየሁ በኩል ወገን ለይቶ ከመታገሉ ሌላ በታሕሳስ ወር 1969 ዓ.ም. አዲስ በተቋቋመው የደርግ ቋሚ ኮሚቴ ውስጥ ለቀልባሾቹ ቁልፍ ቦታዎችን ሲያስጨብጥ ለሕዝቡ ጥያቄዎች በግንባር ቀደምነት ቆሞ የነበሩትን የደርግ አባላት በየአልባሌው ቦታ እያውተፈተፈ ከስልጣን አግልሏቸው ነበር። ስለሆነም በዚህ ወቅት የደርግ ተራማጆችና የሰፊ ሕዝብ ወገኖች ይተናነቁ የነበሩት ከጠቅላላው ፀረ ሕዝብ ሰፈር ጋር ሲሆን ለኢትዮጵያ አብዮት ወደፊት መግፋት ይደረግ የነበረው ትግል ከነዓለማየሁና በእነሱ ቁጥጥር ስር ከነበረው ከደርግ ከራሱ ጋርም ነበር። ጥር 26 ቀን በተደረገው ፍልሚያ በድል አድራጊነት የወጣው የደርግ ተራማጅ ክንፍ ድል የተጎናፀፈው በእለቱ በተደመሰሱት ሰባት ቀልባሾች ብቻ ላይ ብቻ ሳይሆን በጠቅላላው በደርግ በራሱም ላይ ነበር። ደርግ ይኽንን መሸነፍ ለጊዜው አምኖ ከሁለት ወራት ቀደም ሲል አውግዟቸውና ከስልጣን አግልግሏቸው የነበሩት ተላማጆች የደርግ አባላት ከዳር እስከዳር በሰፊው ሕዝብና በአብዮታውያን ዘንድ ያላቸውን ድጋፍ በማየቱ የበላይነታቸውን ሳይወድ ተቀበለ።
ስለሆነም ከጥር 26 በኋላ ደርግ አፍኖ የነበረው ትጥቅና የዲሞክራሲ ጥያቄ መጠነኛም ቢሆን መልስ ማግኘት ጀመረ። አብዮታችንም ወደ አጥቂነት ተሸጋገረ። በአጠቃላይ ይህ ነው የማይባል ሁኔታ እጅግ ወደፊት መገስገስ ጀመረ። ከዚህም ወቅት ማለትም ከየካቲት 1969 ጀምሮ በሃገራችን እየታየ የመጣውን የኃይሎች አሰላለፍ ለውጥ ለመገንዘብ ከዚህ የአብዮቱ አጥቂነት ሁኔታ መነሳት ያስፈልጋል። በዚህ የአጥቂነት ሁኔታ አብዛኛው የደርግ አባል፣ አድሃሪው ቢሮክራሲና በጠቅላላው ፀረሕዝብ ኃይሎች የሚያደርጉት መላቅጡ ጠፍቷቸው ሲርበተበቱ፣ አዲሱን ሁኔታ አምነው የተቀበሉ መስለው አጋጣሚ እየጠበቁ ሲያደቡ፣ ህብረታቸውን በማጠናከር ላይ ያሉትን ተራማጆች ለመከፋፈል መግቢያ ቀዳዳ እየፈለጉ ሲያነፈንፉ አጥቂነቱ ብዙ ሳይጓዝ የፈለጉት አጋጣሚ መጣላቸው። ትላንት በሰፊው ሕዝብ ሰፈር ጸንቶ ይታገል የነበረው የደርግ ተራማጅ ክንፍ ማወላወልድ ጀመረ። በዚህም ማወላዋል የተነሳ በሰፊው ሕዝብ ሰፈር የተፈጠሩት ልዩነቶች ከዕለት ዕለት እየሰፉ፣ ለደርግ አድሃሪዎችና ለጠቅላላው ፀረሕዝብ ኃይሎች ገብቶ የመፈትፈቻ መስክ ከፈቱላቸው። ተጠቀሙበት።
ከዚህን ወቅት አንስቶ በተራማጆች ሰፈር ለተፈጠረው ውዝግብ እና ውዥንብር መሰረታዊው ምክንያት የአብዮታዊ ሰደድ መሪዎች የአብዮቱን ሰፈር በጥርጣሬ አይን መመልከትና ከዚህ ጥርጣሬ በመነሳት የሰፊውን ሕዝብ ጥያቄዎች ለመመለስና የተዳከሙትን አድሃሪዎች ለመደምሰስ አስፈላጊ የሆኑትን እርምጃዎች በወቅቱ አለመውሰዳቸው ነው። ይህ የአብዮታዊ ሰደድ ጥርጣሬ ደግሞ ያለአንዳች መሰረት አልነበረም። በጊዜው ትጥቅ እየተሰጣቸው ወደ አጥቂነት የተሸጋገሩት ከመኢሰማ አንስቶ እስከ ፋብሪካ ማህበራት ድረስ ያሉ አያሌ አብዮታዊያን፣ የቀበሌ ማህበራት፣ የገበሬ ማህበራት፣ የወጣት ድርጅቶች በየአሉበት የተቋቋሙት የአብዮት ጥበቃ ኮሚቴዎች፣ የእነዚህ ሁሉ ግንባር ቀደም አስተባባሪ የነበሩት የሕዝብ ድርጅቶች ጉዳይ ጊዜያዊ ጽ/ቤትና በያለበት የተሰማሩት የማርክሲስት ሌኒኒስት ድርጅቶች አባላት… ሁሉ ትግላቸውን የሚያካሂዱት ከአብዮታዊ ሰደድ ቁጥጥር ውጭ ነበር። እርግጥ ከዚህ በግንባር ቀደምነት የሚንቀሳቀሰው ኃይል ውስጥ የማይናቅ ክፍል በመኢሶን ስር የተደራጀ ኃይል ነበር። ነገር ግን መኢሶን ይህንን ሁሉ ሕዝባዊና አብዮታዊ እንቅስቃሴ ከዳር እስከዳር አስተባብሮ ይመራ ነበር የሚል ከንቱነት የለብንም። እንዲያውም ከዚህ ግንባር ቅደም ኃይል ውስጥ አብዛኛውን የሚወክሉት በየትኛውም ድርጅት ስር ያልነበሩ ዲሞክራቶችና አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ነበሩ። በዚህ ወቅት በአጥቂነት ላይ ስለነበሩት ግንባር ቀደም ኃይሎች ማለት የሚቻል አጠቃላይ አገላለፅ አለ። እነዚህ ኃይሎች ከአብዮታዊ ሰደድ ቁጥጥር ውጪ ብሔራዊ ዲ. አብዮት ፕሮግራም መድረክ ላይ የተሰለፉ፣ በዚህ ፕሮግራምና በአምስቱ ማርክሲስት ሌኒኒስት ድርጅቶች መርሃግብር መሰረት ለሃቀኛ ድርጅቶች አንድነት፣ ለትጥቅ፣ ለዴሞክራሲ፣ ለብሔራዊ ነፃነት፣ ለብሔረሰቦች እኩልነት….. ወዘተ የሚታገሉና በዚህ ትግላቸው ከአድሃሪው ቢሮክራሲ፣ በጠቅላላው ከጸረ ሕዝብ ኃይሎች ጋር /ከደርግ አድሃሪያዎችም ጋር/ የሞትና የሽረት ትግል ውስጥ የገቡ ኃይሎች ነበሩ። ስለሆነም የደርግ ተራማጆች ሲወላወሉ፣ ተመለሰው ከነ ዓለማየሁ ጋር የተመታው የደርግና የአድሃሪው ቢሮክራሲ ህብረት እንዲያገግም ሁኔታዎችን ሲያመቻቹ፣ ቀደም ሲል የተሰለፉበትን መስመር አይን በአይን እየሻሩ ሲሄዱ፣ በዚህም የተነሳ አብዮታችን ከአጥቂነት እንደገና ወደ ተከላካይነት እየዘፈቀ ሲሄድ፣ ድሮም ቢሆን በአብዮቱ ሰፈር ስልጣኑ ብቻ ከደገፋቸው ሕዝባዊ አብዮታዊ ኃይል ጋር እየተባባሰ የሚሄድ ቅራኔ ውስጥ ወደቁ። አብዮታዊ ሰደድ ከዚህ ቅራኔ ውስጥ ለመውጣት የሰፊውን ሕዝብ ጥያቄዎች መመለስን አልመረጠም። የመረጠው አደገኛ ጎዳና ለጊዜው ለደርግ ታማኝ መስሎ በቀረበው አድሃሪ ቢሮክራሲ አማካኝነት የሰፊውን ህዝብ ትግል ከቁጥጥር ስር መዋልና፣ ራሱን አጠናክሮ “ወደ ወዛአደር ፓርቲ መለወጥ” የሚል ታክቲክ ነበር። እንደሚጠበቀው ይኽንን ዞሮ ዞሮ ቅልበሳን የሚጋብዝ ፖለቲካ ማንም በብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራም የተሰለፈ ሀቀኛ ተራማጅና ሀገር ወዳድ ሊቀበለው አልቻለም። እንደሚጠበቀው ደግሞ አድሃሪ የደርግ አባላትና አድሃሪ ቢሮክራሲ ይህንን ለጊዜው አብዮትን ገብ ያደርግልናል ብለው ያመኑበትን ፖለቲካ “እልል” ብለው ተቀበሉት። አዲሱ የቀኝ ኃይሎች ህብረት መሰረት ተጣለ።
ይህንን ህብረት የደርግ ተራማጆችና አድሃሪ ኃይሎች የፈለጉት በተለያዩ ዓላማዎች ነበር። የደርግ ተራማጆች ይህንን ህብረት ሲጠነስሱ አላማቸው አብዮት ለመቀልበስ ሳይሆን ግስገሳውን በመግታት ከነሱ ቁጥጥር ስር ለመዋልና ስልጣናቸውን ለማደላደል ነበር። አድሃሪ ኃይሎች ግን አላማቸው ለጊዜው ከተራማጅ የደርግ አባላት ተጋግዘው የአብዮትን ሂደት ለመግዛትና ለማረጋጋት ሲሆን የሩቅ ጊዜ አላማቸው ደግሞ በአብዮተ ስም አብዮታዊያንን ከመቱ በኋላ አብቱን ራሱን ጨርሶ መቀልበስ ነበር። የሆነ ሆኖ ይህ አዲስ የቀኝ ኃይሎች ሕብረት አብዮታችንን ከለት ዕለት ከማጥ ውስጥ እየከተተ፣ብሔራዊ ነጻናታችንን ከእለት እለት እያስደፈረ ከብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ የአብዮት ፕሮግራም መድረክ ከዕለት ዕለት እያንሸራተተ የሚሄድ ህብረት መሆኑ ከመጀመሪያው ግልጽ ነበር። በዚህም የተነሳ ይህ ህብረት እየተጠናከረ ሲሄድ ለጠቅላላው ከአብዮቱ ሰፈር ከቆሙት ተራማጆችና አገር ወዳዶች ጋር ግጭቱ እየተካረረ መሄዱ ምንም እንግዳ ነገር ሊሆን አይገባም።
ይህ በዚህ እንዳለ በተለይ ሰፊው ሕዝብ አብዮታዊያንና በአዲሱ የቅኝ ህብረት ማሃከል ባለው ትግል በግልጽ ወገን ለይቶ በመኢሶን በኩል መሰለፉን ካሳየበት ከሜይዴይ 1969 ሰልፍ በኋላ እየተጠናከረ የመጣው የውጭ ኃይሎች በኢትዮጵያ መግባት በዚህ የኃይል አሰላለፍ ውስጥ ምን ቦታ አለዉ? በተለያዩ ምክንያቶችም ቢሆን የአድሃሪው የሱማሌ መንግሥት ወረራም ሆነ የውጭ እርዳታ ያስከተለው ውጤት በአንድ በኩል “በብሄራዊ እርቅ” ስም ቀኙን ኃይሎች ህብረት ማጠናከር፣ በሌላ በኩል ደግሞ ጦርነቱን “በአዋቂዎች” በማካሄድ ስም አዲሱን የቅኝ ኃይሎቸ ሕብረት ከነቃ ከተደራጀና ከታጠቀ ሕዝብ ትግል መፈክራችን የባሰውን ማራቅ ነበር። የውጭ እርዳታ ይኽንን በአብዮት ስም አብዮቱን የሚመታ ህብረት አጠናክረው እንጂ የቅኝ ኃይሎችን ህብረት አድክሞ አብዮቱ ከገባበት ማጥ እንዲወጣ አላገዘውም። በዚህ ጉዳይ ላይ ወደፊት በጣም በሰፊው መመለስ ያስፈልጋል። አሁን ግን ማንም ሊክደው የማይችለው ሀቅ እንናገር። በአንድ በኩል የውጭ እርዳታ የተባለው በሀገራችን እያደገ ሲሄድ በሌላ በኩል ደግሞ በአብዮታውያን ላይ የሚካሄደው ጭቆና፣ ከብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ የአብዮት ፕሮግራም አንፃር የሚካሄደው መንሸራተት እየጨመረ ሄዷል። ዛሬ በአገራችን ብዙ ሺህ የበአድ ወታደሮች አሉ። እንደዚሁም ከእነሱ ቁጥር ጋር እየጨመረ የሄደ ብዙ ሺ ደሃ ገበሬዎች፣ ወዛደሮች፣ መለዮ ለባሾች፣ ታጋይ ሴቶችና ወጣቶች፣ አብዮታዊ ምሁራን ዲሞክራቶች፣ አገር ወዳድ የጦርና የፖሊስ መኮንኖች፣ በኢትዮጵያ እስር ቤቶች ውስጥ ይገኛሉ። አጋጣሚ? የውጭ ኃይሎች በኢትዮጵያ በገፍ መግባት የግድ ማስከተል የነበረበት ሁኔታ? ይህ እያንዳንዱ ሃቀኛ ኢትዮጵያዊ ሊወያይበት የሚገባው፣ አብዮታችንና ብሄራዊ ክብራችንን የሚመለከት ጥያቄ ነው። ከላይ እንዳልነው ወደፊት በሰፊው እንመለስበታለን። ለአሁኑ ግን ገና የዚህ ሁኔታ ሽታው በጀመረበት በመጋቢት 1969 ዓ.ም እርዳታን ጥቅምና አደጋ በማመልከት የሰፊው ሕዝብ ድምጽ ቁጥር 53 ያለውን ጥቅሰን እንለፈው፤-
“በማንኛውም ጊዜና ሁኔታ ቢሆን፣ ምንም ያህል ኢኮኖሚ፣ ፖለቲካዊና የማህበራዊ ኑሮ ችግሮች ቢኖሩም፣ የፈለገውን ያህል አብዮታዊ በአድሃርያን ጥይት ቢወድቅም፣ በአጭሩ ማንኛውንም መስዋዕትነት ቢጠይቅምና ትግሉ የፈለገውን ጊዜ ቢፈጅም፣ አብዮታዊያን ከሁሉ በላይ መተማመን ያለባቸው በ28 ሚልዮን የኢትዮጵያ ሕዝብና በኢትዮጵያ ምድር ሃብት ላይ ነው። ከዚህ አይነቱ እምነት መዛነፍ የመጣ እለትና ተስፋችንን በውጪ ኃይሎች ላይ መጣል ያመጣን እለት የተኮላሸ አብዮትና “በነፃ ለዘላለም ትኑር!” የተባለችው ሀገራችን ተመልሳ ከባርነት ስር የምትወድቅበት ቀን እንዲመጣ ማገዛችን እንደሆነ መታወቅ አለበት” /ሰህድ ቁ. 53 መጋቢት 15- 1969/
አንባቢ እነዚህን ቃላት ዛሬ በሀገራችን ካለው ሁኔታ ጋር እያገናዘበ እንዲመለከታቸው እየጋበዘን የዚህ የቀኝ ኃይሎች ህብረት ስላስከተለው ውጤቶች በአጭሩ ለመተንተን እንፈልጋለን።
የአዲሱ የቅኝ ኃይሎች ህብረት መጠናከር ያስከተለው ውጤት
ከላይ እንዳልነው ይሕ ህብረት የተጠነሰሰው የአብዮቱን ግንባር ቀደም ኃይሎች ለመቋቋም፣ ያደገውና የተጠናከረው እነዚህን ኃይሎች እየመታና እየዳከመ በመሆኑ የዚህ ህብረት መጠናከር ውጤት ምን እንደሆነ ለመገመት ፈጽሞ አያስቸግርም። ዛሬ ማንም በግልጽ እንደሚያየው ከብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራም አንጻር የሚደረገው መንሸራተት ከዕለት ዕለት ገሃድ እየሆነ መጥቷል። ገና ፕሮግራሙ ሀ ብሎ ይጀመር የአዲሲቱ ኢትዮጵያ መስራች ኃይሎች ብሎ የዘረዘራቸው ፀረፊውዳልና ጸረኢምፔሪያሊት ኃይሎች እንኳን ፕሮግራሙ እንደተጠቀሰው በመሰላቸው በፓርቲዎቻቸው ተደራጅተው ለትግሉ አስተዋጽኦ ሊያደርጉ ቀርቶ ለአዲሱ የቅን ኃይሎች ሕብረት አናጎበድድም በማለታቸው ብቻ እጣቸው እስራት፣ ግርፋት፣ እርሸና ሆኖ እናገኘዋለን። ሕዝቡ በየደረጃው እራሱን እንዲያስተዳድር ይደረጋል የተባለው ቀርቶ ለዚህ ህዝባዊ አስተዳደር ጥንስስና ለአዲሲቱ ኢትዮጵያችን ዲሞክራሲያዊ መሰረት ይሆናሉ ተብለው ተስፋ የተጣለባቸው ሕዝባዊ ድርጅቶች እንዳልነበረ ሆነው ፈራርሰዋል። ያለ አንዳች ገደብ ለሰፊው ሕዝብ በአስቸኳይ ይታወቃሉ የተባሉት ዴሞክራሲያዊ መብቶች ታፍነው ፀረዴሞክራሲ በኢትዮጵያችን አንሰራርቷል። የወዛደር ፓርቲ እንዲቋቋም፣ ሌሎች ፓርቲዎች እንዲቋቋሙ መብት ከመታወቅ አልፎ በመንግሥት በኩል እርዳታና ድጋፍ ይሰጣል በተባለው ፈንታ ሰፊው ሕዝብና የኢትዮጵያ ተራማጆች ድሮ “በኢትዮጵያ ሶሻሊዝም” ዘመን አሽቀጠረው የጣሉት “የአንድ ፓርቲ” ዘይቤ ተመልሶ መጥቷል። ብሄረሰቦች የራሳቸውን እድል በራሳቸው የመወሰን መብት ይታወቅላቸዋል፣ የሪጅናል ኦቶኖሚ መብት ይረጋገጥላቸዋል በተባለው ፈንታ ትምክተኛነት ነግሶ ጭቁን ብሔረሰቦች የመጀመሪያ ደረጃ ዴሞክራሲና ፍትህ ተነስተው በኢትዮጵያ ሕዝቦች እውነተኛ አንድነት እጅግ አደገኛ የሆነው ሁኔታ ተፈጥሯል። በፕሮግራሙ መሰረት ከማንም ኃይል መንግሥትና ከማንም ሰፈር ቃልኪዳን ውጭ የገለልተኛና የብሔራዊ ነጻነት ፖለቲካ ተከተላለች የተባለችው አገራችን በኃያላን መንግስታት ዓለም አቀፍ ገበጣ ጨዋታ ውስጥ ወደ ተራ ጠጠርነት እየተጓዘችና እየተዋረደች በመሄድ ላይ ነች።
እንደሚጠበቀው ትላንትናም ሆነ ዛሬ ለኢትዮጵያችን ብልጽግና፣ ደህንነትና ክብር የቆሙ ዲሞክራቶችና አገርወዳጆች ሁሉ፣ይህንን ሁኔታ በቆራጥነት ተቋቋሙት እንጂ ለአዲሱ የቀኝ ኃይሎች ህብረት አላጎበደዱም። በዚህም አሻፈረኝ ባይነት የተነሳ ከአንድ አመት ተኩል ወዲህ በሀገራችን በዲሞክራቶችና በአገር ሰዳዶች ላይ የተካሄደው ዘመቻ ሃገራችንን በፖለቲካ እስረኞች ብዛት ከነቺሊና አርጀንቲና የሚወዳደር ስፍራ እንድትይዝ አድርጓታል። አዲሱ የቀኝ ኃይሎች ህብረት፣ የእነሱ አጫፋሪዎችንና ምስኪን አድርባዮች የፈለጉትን ቢሉም ስለዚህ ዘመቻ አንዳንድ አይን የሚያወጡ ሃቆች አሉ። ከነዚህ ውስጥ በተለይ ሁለቱን መጥቀስ እንወዳለን። አንደኛ ይህ “ዘመቻ” የተሰጠው ሰበብ ቢሰጠው የተሰጠው ሽፋንና ካባ ቢደረብበት ጸረአብዮት ዘመቻ ነው። ሁለተኛ ዘመቻው ከመጀመሪያ አንዳልነው ዞሮ ዞሮ በብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ኘሮግራም መድረክ ላይ በቆሙ ኃይሎች ላይ በሙሉ እንጂ በአጀማመሩ ላይ እንደታየው “በጥቂት ፈርጣጮች” ላይ አይደለም።
ዘመቻው ፀረአብዮት ነው ስንል ዛሬ በኢትዮጵያ የሚታሰረው ማነው? የሚያስረው ማነው? የእስራቱስ ምክንያት ምንድነው? ከሚሉት በጣም ግልጽና ቀላል ከሆኑ ጥያቄዎች ተነስተን ነው።
በዛሬው ወቅት በኢትዮጵያ የሚታሰሩትና የሚረሸኑት ታጋዮች ቀደም ሲል በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን ከዚያም አብዮቱ ያስገኛቸውን ድሎች ለማንከባከብ በግንባር ቀደምት ይታገሉ የነበረው ኢትዮጵያዊያን ናቸው። ከነዚህ ኃይሎች በነዓለማየሁ ዘመን ከደርግ ተራማጆች ጎን ቆመው የቀኝ ኃይሎች ሕብረት የተዋጉ፣ በሰፊው ሕዝብ በራሱ ተመርጠው ሕይወታቸውን ለአብዮትና ለእናት ሀገር መድበው ትግል ባለበት ቦታ ሁሉ “አለን” እያሉ ግንባራቸውን የሰጡና የተጋፈጡ፣ በፀረሕዝብ አመፅ ውሽንፈር ሳይበገሩ “መራራው ትግል ይግፋ” እያሉ ይወደቁና የሰዉ የነበሩ ኃይሎች ናቸው።
የሚያስረውና የሚረሸነውስ ማን ነው? ከፍ ብለን ከጠቀስናቸው ታጋይ ኢትዮጵያውያን ይበልጥ ተራማጅ፣ ይበልጥ ዲሞክራት፣ ይበልጥ አገር ወደድ ኃይል ነው? በፍጹም! ጥቂት ምስኪን አድርባዮቹ ግንባር ቀደም መስለው መንጫጫታቸውና ያዙን ልቀቁን ማለታቸው ጥቂት የሰፊው ሕዝብና እና የተራማጆችን እምነት የተጣለባቸው የደርግ ተራማጆች ለዚህ ዘመቻ ሽፋን መስጠታቸው መሰረታዊውን ሃቅ ሊያዘናገን አይችልም። በአሁኑ ወቅት ከዚህ ሁሉ ዘመቻ በስተጀርባ ያለው ዋና ኃይል የፀረ ሕዝብ ኃይሎች ግንባር ቀደም የሆነው አድሃሪ የሲቪልና የሚሊታሪ ቢሮክራሲ ነው። እርግጥ ዛሬ ይሕ ፀረሕዝብ ኃይል በአብዮት ስም ይምላል ይገዘታል። ይህ ታዲያ ምን ያስደንቃል? እነዓለማየሁስ በአብቱ ስም አልነበረም እንዴ ቅልበሳ የሞከሩት? ከዚያም አልፈን “የተገላቢጦሽ” ምሳሌ እናስታውስ! አቢዮቱ ራሱ አፄ ኃይለሥላሴን ከማውረዱ በፊት ብቸኛ ያደረጋቸውና ያራቆታቸው በዙፋኑ ስም እየማለና እየተገዘተ ዙፋኑን በመገዝገዝ አይደለም እንዴ? ማርክስ አንተድ ቦታ “ታሪክ ሁለት ጊዜ እራሷን ትደግማለች አንዴ እንደ ኮሜዲ አንዴ ደግሞ እንደ ትራጀዲ ብሎ ነበር። ታድያ “የዙፋኑን ታማኝነት” ኮሜዲ የኖረ ታጋይ ዛሬ እንዴት የፀረአብዮቱን ቢሮክራሲ “ለአብዮቱ ታማኝነት” አደጋ መመልከት ይሳነዋል። ዛሬ ፀረአብዮት ኃይሎች ለአብዮታችን ሰፈርና በእናት ሀገራችን ክብር ላይ ይህ ነው የማይባል ጥቃት እያደረሱ በአብዮት ስም ለመማል ቢገደዱ እኮ ምክንያት አላቸው። ያለው የኃይል ሚዛን ከዕለት ዕለት ለእነሱ እያመዘነ ቢሄድም ቅሉ ገና ይፋ ፀረአብዮት ገጻቸውን ደፍረው የሚያሳዩበት ደረጃ ባለመድረሳቸው ብቻ እኮ ነው። ስለሆነም ከአንድ አመት ተኩል ወዲህ በሀገራችን የሚካሄደውን ፀረአብዮት ዘመቻ እነሱ የመሩ እየመሰላቸው “በግንባር ቀደምነት በማንቧረቅ ላይ ያሉ ኃይሎችንም ሆነ ለዚህ ዘመቻ “ተራማጅ ሽፋን” ለመስጠት የሚጥሩ የደርግ ተራማጆች ብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራምን ሙሉ በሙሉ ካልካዱ በስተቀር በዚህ መሳሪያነታቸው የራሳቸውንም መቃብር መቆፈራቸው እንደሆነ ግልጽ ነው።
የዚህ የዘመቻ ምክንያትስ? ይህን ዘመቻ “በመኢሶን ፍርጠጣ” የተነሳ አድርጎ ለማቅረብ የተደረገው ሙከራ መጀመርያ ላይ ጥቂት ሰዎች ሊያሳስት ቢችልም ዛሬ ከዘመቻው ስፋት የተነሳ “ፍርጠጣው” ሰበብ እንደነበረ፣ በዚህ ዘመቻ ለመምታት ትሞክረው በጠቅላላው በብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራም መድረክ ላይ ከመቆመው ኃይል ግንባር ቀደሙ ክፍል እንደሆነ ያልተገነዘበ የለም። ይህንን መካድ ሲያቀት ይኽ ሁሉ የሰፊው ሕዝብ ወገን የተዘመተበት ከአብዮቱ ስለተንሸራተ ነው በሚል ለመወናበድ ተሞክሯል። አንድ የተወሰነ የፖለቲካ መስመር ከዓለማየሁ ሃይሌ ሲያራምዱት ቀልባሽ “የነሱ ተቃዋሚዎ”ች እነሱን ከመቱ በኋላ መልሰው ያንኑ መስመር ሲይዙት ተራማጅ ካልተባሉ በስተቀር ዛሬ አዲሱ የቀኝ ኃይሎች ህብረት የሚከተለው ፖለቲካ ውሎ አድሮ ቅልበሳን የሚያመጣ ፖለቲካ ነው። ሀቀኛ ኢትዮጵያውያን በየእስር ቤቱ የሚንገላቱበት ዋና ምክንያት ይኽንን የፖለቲካ መስመር አሻፈረኝ በማለት በአብዮቱ ሰፈር በመጽናታቸው ነው።
ሌላው የዚህ ዘመቻ መልኩ በመኢሶን ላይ ብቻ ሳይሆን በጠቅላላው ግንባር ቀደም በሆኑ ተራማጅና አገር ወዳድ ኃይሎች ላይ በሙሉ መሆኑ ነው። ዘመቻው ሁለት እርከኖች አልፏል ለማለት ይቻላል። መጀመሪያ ላይ ደርግ ፀረሕዝብ ዘመቻውን የጀመረው “ፈረጠጡ” በተባሉ ጥቂት የመኢሶን “ቀኝ ክንፍ” ጓደኞች ላይ ነበር። ነገር ግን ሰፊው ሕዝብ በያለበት ይኽንን ፀረሕዝብ ዘመቻ መቃወሙንና የተመለከተውና በምንም ዓይነት መከፋፈል አለመቻሉን የተረዳው አዲሱ ህብረት ትንሽ ቆይቶ ታክቲኩን ለወጠ። “ፈረጠጠ” ይለው የነበረውን መኢሶንን በጦሩ ግንባር ሆኖ በመሃል ሀገር፣ በከተማ ሆነ በገጠር ኢትዮጵያዊያን ለአብዮትና ለእናት ሃገር በሚዋደቁበት ቦታ ሁሉ “የተሰከሰከ” ታጋይ ሃይል መሆኑን በማመን በያለበት “የተሰከሰኩትን” የመኢሶን አባላት “በመመንጠር” ላይ የተሰማራ። በዚህም ወቅት የዚህን ዘመቻ እውነተኛ ገጽታ በትክክል የተገነዘበው ንቅናቄዎችን ይህንን እየተስፋፋ የሚሄድ ፀረሕዝብ አመጽ ከማንኛውም የቡድን ስሜት በራቀ ሁኔታ በጋራ እንዲቋቋሙ የትግል አንድነት ጥሪውን በታህሳስ ወር 1970 ዓ.ም በይፋ አቀረበ። የአድርባይ ድርጅቶች መሪዎች ግን ገና ለረዥም ጊዜ ስለኢትዮጵያ ተራማጆች በተወሳ ቁጥር ሲያሳፍረን የሚኖረውን ከአፍንጫቸው አልፎ የማያይ አቋም በመያዝ እንኴን የቢሮክራሰውን ዓመጽ አብሮ ሊመለከቱ ቀርተው “በመኢሶን ላይ” የሚካሄደው ዘመቻ እንዲፋፋም ጠየቁ። አድሃሪው ቢሮክራሲ በዚህ በተራማጆች ሰፈር መከፋፈል ኃይልን ማግኘቱ አጥቂነቱን ወደ ሁለተኛ ደረጃ አሸጋገረው።
ይህ ሁለተኛው ደረጃ በተለይ ከጥር ወር 1970 ዓ.ም ወዲህ የተስፋፋ ሲሆን ዋናው ጠባዩ በጠቅላላው ከሕዝባዊ ድርጅቶች ከፋብሪካ፣ ከቀበሌ፣ ከትምህርት ቤት፣ ከገጠር ከሰራዊቱ ውስጥ “ቀኝ መንገደኞችን ማጥራት” በሚል ሰበብ ከመኢሶን አባላት አልፎ ለፍትህ፣ ዲሞክራሲ፣ ለብሄራዊ ክብራችን ወደ ቆሙ ኃይሎች በሙሉ መዛመት መጀመሩ ነው። የአድሃሪያን ዓላማ እስከዚህም ድረስ የተባሉትን አካባቢዎች “በቀኝ መንገደኞች” ማጥራት ሳይሆን ከዲሞክራቶችና ከአገር ወዳጆች “አፅድቶ” በዚህ መልክ የተኮላሹትን ሕዝባዊ ድርጅቶች እነሱ ተቀጢላ ለማድረግ ነበር። በያለበት ያሉ አብዮታዊ ሁሉ፣ ዲሞክራት ሁሉ፣ አገር ውዳድ ሁሉ ለደርግ አላጎበድድም በማለቱ ብቻ “የቀኝ መንገደኛው መኢሶን ሰርጎ ገብ” እየተባለ የሚታደንበት አዲስ ምዕራፍ ተከፈተ። የአድርባይ ድርጅቶች መሪዎች በአብዮቱ ጣረ ሞት ላይ ቆመው “በሕዝባዊ” ድርጅቶች ውስጥ በዲሞክራሲያዊ ምርጫ ማግኘት ያልቻሉትን ቦታ በተራ ሹም ሽር ለመያዝ በሚደረገው መራኮት “በይገባኛል አይገባህም” “በይኽ ለኔ በያ ላንተ” በሰፊው ሕዝብ ፊት ላይ ትዝብት ለወደቁበት አሰፋሪ ንትርክ ተጠምደው አሁንም ቢሆን አደጋው አልታያቸውም ነበር። በዚያው ልክ ደግሞ ታጋይ ህልውናቸውን ለፍርፋሪ ሸጠው ያጎበደዱለት ፀረአብዮት ከእንግዲህ እንደማያስፈልጉት እንደደረቀ ሎሚ ሊጥላቸው እንደተሰናዳ ልብ አለማለታቸውም ሊያስገርመን አይችልም። ነገር ግን ከአንድ አመት ተኩል ወዲህ ያለውን የቀኝ ኃይሎች ህብረት መጠናከር ለተመለከተ ሰው ዞሮ ዞሮ አድሃሪው ቢሮክራሲ በእነርሱም ላይ እንደሚዞር ግልጽ ነበር። ከነሀሴ 1970 ጀምሮ አዲሱ የቀኝ ኃይሎች ህብረት በትናንትና “ግንባር ቀደሞቹ” ላይ ዞሮባቸዋል። በአሁኑ ወቅት የወዛደር ሊግ መሪዎችና አባላት፣ እንደዚሁም ከአብዮታዊ ሰደድ ከራሱ ውስጥ ሳይቀር አንዳንድ መሪዎችና አባላት ራሳቸው ባጠናከሩት በአዲሱ የቀኝ ኃይሎች ሕብረት በመመታት ላይ ናቸው። ፀረሕዝቦች በነሐሴ ወር 1969 ዓ.ም የጀመሩትን አብዮቱን በአብዮቱ ስም የማጥቃት ዘመቻውን ቀጥለዋል።
የመላው ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን አቋም አለው? ከዚህ አጠቃላይ ሁኔታ የተራማጆች ተግባር ምንድነው ይላል?
በአንዳንድ ሀቀኛ ተራማጆች አካባቢ “አድርባዮቹ እኛን ከዚህ በፊት ያስጠቁ ስለሆኑ፣ አሁን ደግሞ ይኽ መራኮት የመጣው ሌባ ከሌባ ቢጣላ በሰው ገለባ እንዲሉ በቦታ ሽሚያ ስለሆነ ይበላቸው አበጀ” የሚል የተሳሳተ አነጋገር ይሰማል። እንዲህ አይነቱ አቋም የአብዮቱን ትግል ቁም ነገር አስረስቶ በማጥቃት ላይ ባሉት ኃይሎች እጅ ውስጥ ይጥላል። በኛ ግምት አሁንም ቢሆን የወሰዱትን ሽፋን ቢወስዱ፣ የሰጡትን ሰበብ ቢሰጡ በማጥቃት ላይ ያሉት፣ በዚህ ዘመቻ ሳቢያ በመጠናከር ላይ ያሉት ፀረአብዮትና ፀረ ኢትዮጵያ ኃይሎች ናቸው። ይኽ ከዛሬ አመት ዛሬ ይበልጥ ግልጽ ሆኗል። በመጪው ጊዜ ደግሞ ይበልጥ ግልጥ ይሆናል።
መኢሶን ከአድርባይ ድርጅቶች ጋር ያለውን የፖለቲካ ልዩነት የኢትዮጵያ ተራማጆዎችና አገርወዳዶች ሙሉ ያውቋቸዋል። ነገር ግን ከመጀመሪያውም ለማለት እንደፈለገው በብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ አቢዮት ፕሮግራም መድረክ ላይ ተሰልፈናል የሚሉ ኃይሎች በሙሉ ልዩነቶቻቸውን በዲሞክራሲያዊ ውይይት እንጂ በእስራትና በርሸና ሊፈቱ አይችሉም ብሎ ያምናል። ለዴሞክራሲያዊ መብቶች አለማቋረጥ የታገለውና የሚታገለውም አንዱ ምክንያት ለዚህ ነው። ስለሆነም መኢሶን ይህንን በአዲሱ የቀኝ ኃይሎች ህብረት በመካሄድ ላይ ያለውን እስራትና ርሸና ይቃወማል። በዚህ ጉዳይ ላይ ካለፈው የተለየ ጥሪ የለውም። በጠቅላላው በሀገሪቱ የሚገኙ ተላማጆችና አገር ወዳዶች በሙሉ ለአብዮታቸውና ለእናት አገራቸው ብሔራዊ ክብር ቡድን ሳይለያቸው፣ ብሄረሰብ ሳይለያቸው፣ ጾታ ሳይለያቸው፣ መለዮ ሳይለያቸው እንደ አንድ ሰው ተነስተው ፀረአብዮቱንና ፀረኢትዮጵያዊውን ፖለቲካ፣ ፀረሕዝቡን አመፅ በጋራ መቋቋም አለባቸው። በጥቂት መሪዎች በተሳሳተ የፖለቲካ መስመር ተሰልፈው የነበረው ጓዶች ሁሉ ባለፈው አንድ አመት በአብዮቱ ሰፈር በደረሱት ጥቃቶች አስፈላጊውን ትምህርት መቅሰም አብዮታዊና ብሔራዊ ግዴታቸው ነው። መኢሶንና ሌሎች አብዮታዊያን ከሁለት ዓመታት ጀምሮ ሀቀኛ ህብረት ሲሉ፣ ዲሞክራሲያዊ መብቶች ሲሉ፣ የብሄረሰቦች እኩልነት ሲሉ፣ ቢሮክራሲው ይውደም ሲሉ፣ አድሃሪ የደርግ አባላት ይውደሙ ሲሉ፣ ሕዝባዊ ድርጅቶች ያብቡ ሲሉ፣ የውጭ እርዳታ ጊዜያዊ ጥቅም አብዮታችንንና ብሔራዊ ክብራችንን አደጋ ላይ እንዳይጥል በራሳችን ኃይል እንተማመን ሲሉ፣…… በአሁኑ ወቅት አብዮታችንና ብሔራዊ ነጻነታችን ከሚገኙበት መቀመቅ እንዳንገባ የሚያስችሉንን አንገብጋቢ መፈክሮች መጠቆማቸው ነበር። አሁንም ቢሆን የኢትዮጵያ ተራማጆችና አገር ወዳዶች ለነዚሀ አላማዎች በአንድነት ካልታገሉ ካለንበት ሁኔታ የሚያወጣን ተአምር የለም። የባሰ ጸረአብዮት፣ የባሰ ብሔራዊ ውርደት እንጂ!
ንቅናቄችን በነዚህ አቋሞች ስር ተሰልፎ ሲታገል ያሳለፋቸው እጅግ አስቸጋሪ ወራት ቢሆንም ዛሬ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በአቋሙ ትከክለኛነት አምኖ በአብዮቱ ሰፈር ትግሉን ይቀጥላል። የፀረሕዝቦች ኃያልነት አብዮታዊያን ተከፋፍለው እስከተዳከሙላቸውና አንድነት መመከት አቅቷቸው ተራ በተራ እስከ ተመቱላቸው ድረስ ብቻ ነው። ይህንን ሀቅ ተገነዘበው፣ ተደጋጋሚ የትግል አንድነት ጥሪያችንን የኢትዮጵያ ተራማጆችና አገር ወዳዶች እንደሚቀበሉን ሙሉ ተስፋ አለን።