የሰፊው ሕዝብ ድምፅ
ቁጥር 58፣ ሰኔ 21፣ 1969
የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ
በዚህ እትም መኢሶን፣ ወደ ምስራቅና ሰሜን ሊዘምት የተዘጋጀው መደበኛ መለዮ ለባሽና የሕዝባዊ ሰራዊቱ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ አብዮትን፣ የሀገር ክብርና ነፃነትን እንዲሁም የሕዝቦቿን መብት ለማስጠበቅ ቆርጦ መነሳቱን እንደሚያሳይ ይገልጻል። ነገር ግን ይህ ሠራዊት በሠለጠነበት አጭር ጊዜ ሁሉን ስልጠና አግኝቷል ማለት ስለማይቻል ፣ በተለይም የንቃተ ህሊናው ማደግና አብዮታዊ አመራር ወሳኝ ስለሆኑ የሰለጠኑ ካድሬዎች አብረውት ተሰልፈው እንዲያነቁት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ያሳስባል። ዘመቻው ድል እንዲጎናጸፍና አብዮቱ እንዳይቀለበስ፣ ፋታ ሳይሰጡ አብዮቱን ማፋፋም ግዴታ እንደሆነም ያብራራል።
ባለፈው ቅዳሜ፣ ሰኔ 18 ቀን 1969፣ በአዲስ አበባ ከተማ የተከናወነው የመደበኛ መለዩ ለባሹና የሕዝባዊ ሠራዊቱ ሰልፍ፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ፈፅሞ ታይቶ የማይታወቅ ዓይነት ወደር የሌለው ሰልፍ እንደነበር ተመልካች ሁሉ ተገንዝቦታል። የኢትዮጵያ አብዮት በጣም አጭር በሆነ ጊዜ ውስጥ ይህንን ሕዝባዊ ጦር ለመሰብሰብ፣ ለማሰልጠንና ለማስታጠቅ በመቻሉ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ተመልካቾችን ሁሉ ሳያስደንቅ እንዳልቀረ ለመገመት ይቻላል። ይህ ሠራዊት በመደብ ምንጩ፣ በወታደራዊ ትምህርቱ፣ በትጥቁ፣በብዛቱና እንደዚሁም ከሰፊው ሕዝብ በተደረገለትና በሚደረግለትም ድጋፍ በእርግጥ በአብታዊት ኢትዮጵያ አንድ ትልቅ ኃይል ለመሆን የሚችል ሠራዊት ነው ለማለት ይቻላል።
መደበኛ መለዮ ለባሹና ሕዝባዊ ሠራዊቱ በዚሁ ቀን የተቀበሉት ቃለ መሃላ እጅግ በጣም ከባድ መሆኑን በዚሁ አጋጣሚ ማስታወስ ያስፈልጋል። ከቃለ መሃላው ሰባት ነጥቦች የመጀመሪያው ይህ ሠራዊት የኢትዮጵያን ብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ የአብዮት ፕሮግራም በተግባር ለመተርጎም መታገል እንዳለበት ይገልጻል። ሁለተኛው፣ የሀገርን ክብርና ነፃነት፣ የጭቁን ሕዝቦችዋን መብት፣ የአብዮቱን ድሎች ለመጠበቅ እና አዲስ ህብረተሰብን ለመገንባት በሚደረገው ትግል ሰራዊቱ እንደሚሳተፍ ይናገራል። አምስተኛው ነጥብ አብዮታዊ መለዮለባሹና ሕዝባዊ ሠራዊቱ የታጠቀ የወዛደሩና የአርሶአደሩ ከንድ እንደሆኑ ይገልጸና፣ የመጨረሻው ነጥብ መለዮ ለባሹና ሕዝባዊ ሠራዊቱ የሀገሪቷን ነጻነት፣ የግዛት አንድነቷንና የጭቁን ሕዝቦችዋን ሰላምና ፀጥታ ለመጠበቅ ቃል እንደገቡ ያስታውቃል።
እነዚህ የቃለ መሃላው ነጥቦች እጅግ በጣም ከባድ ናቸው ያልንበት ምክንያት፣ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ የአብዮት ፕሮግራም በተግባር ለመተርጎም ቃልየ ገባ ሠራዊት ከሁሉ አስቀድሞ የፕሮግራሙን ይዘት በሚገባ የማዋሃድ ሃላፊነት እንዳለበት ግልፅ ስለሆነ ነው። የአገርን ክብርና ነፃነት፣ የኢትዮጵያን ጭቁን ሕዝቦች መብትና የአብዮቱን ድሎች ለመጠበቅ ቃል የሚገባ ሠራዊት፣ የአብዮታዊት እናት ሃገርን፣ የብሄራዊ ነፃነትን፣ የጭቁን ሕዝቦችን መብት፣ የአዲስ ህብረተሰብን ትርጓሜዎች በሚገባ የመረዳትና ለሌላም የማስረዳት ሃላፊነት አለበት። እንዲሁም የወዛደሩና የአርሶ አደሩ ክንድ መሆን ማለት በማንኛውም ጊዜና ቦታ፣ በጦርነትም ሆነ በሰላም ወቅት፣ እነዚህ መደቦች ጥቅምና ደህንነት መቆምንና መሰዋትን እንደሚጠይቅ እያንዳንዱ የሰራዊቱ አባል ማወቅ ይኖርበታል ማለት ነው። ስለሆነም፣ መደበኛ መለዮ ለባሹና ሕዝባዊ ሠራዊቱ የተቀበሉትን ቃልኪዳን ከሥራ ላይ በሚገባ ለማዋል እንዲችሉ በአብዮታዊ አስተሳሰብ በመታነፅ የከፍተኛ ንቃተህሊና ባለቤት መሆን እንዳለባቸው ከቃለ መሃላው ለመረዳት ይቻላል።
ማንም በቀላሉ ሊገምተው እንደሚችል ሁሉ፣ በታጠቅ ሜዳ የሰለጠነውና ቅዳሜ ያንን ታላቅ ሰልፍ ያሳየው ሕዝባዊ ሰራዊት እነዚህን የግድ የሚያስፈልጉትን እውቀቶችና እምነቶች በዚህ በአጭር ጊዜ ውስጥ አግኝቷቸዋል ለማለት አይቻልም። ይሁንናም፣ ይህ ሰራዊት አሁን ባለው ወታደራዊ ትምህርቱ፣ ባለው ትጥቁ፣ የውጊያ ፍላጎቱና የቀሰማትን አነስተኛ የፖለቲካ ትምህርት ይዞ እንደሚዘምት ይገመታል። አብዮታውያን እንደሚያምኑበት ሁሉ፣ የኢምፔሪያሊዝምን ኃይሎች ተዋግቶ ለማሸነፍ የመሳሪያ ብዛትና ጥራት፣ ወይንም በባህላዊ ጀግንነት መዋጋት፣ ወይንም የሰራዊቱን ቁጥር ማብዛት ብቻውን የድል ዋስትና አይሆኑም። ከሁሉ አስቀድሞ ለመተማመን የሚቻለው በተዋጊው አብዮታዊ ንቃተ ህሊናና በአብዮታዊ አመራር ላይ መሆኑን የብዙ አብዮታዊ ጦርነቶች ታሪኮች ያስረዳሉ።
መኢሶን “አብዮታዊ አመራርን” ለዘማቹ ሰራዊት በሚጠይቅበት ጊዜ ይህንን ጥያቄ ጥቂት ግለሰቦችን በሰራዊቱ አመራር ውስጥ እንደማስቀመጥ አድርጎ አይመለከተውም። አብዮታዊ አመራር ማለት በአጠቃላይ የዘመቻን ጉዳዮች፣ ወታደራዊ ጉዳዮችን፣ ከኢትዮጵያ አብዮት መሰረታዊ ጥያቄዎች ጋር የሚያያዝ፣ ስለሆነም ለማንኛውም ድርጊት መነሻውንና መድረሻውን የሚያደርግ አመራር ማለት። ይህም፣ ሰራዊቱን በሚመለከተው በኩል፣ በተግባር ሲተረጎም፣ ከላይ እስከታች በርዕዮተዓለም፣ በአስተሳሰብና በአሰራር ዘዴ፣ በአብዮታዊ ዲስፕሊን የተሳሰሩ አያሌ ሺህ የፖለቲካ አንቂዎችን ከሰራዊቱ ጋር ማዋሃድና ከተራ ተዋጊ ጋር በጥብቅ እንዲተሳሰሩ ማድረግን ይጠይቃል። ምናልባት የዚህ አይነቶቹን አንቂዎች ለማግኘትም ለማሰልጠንም ጊዜ አይገኝም ሊባል ይችላል።ነገር ግን ዘመቻው ክፍተኛ ውጤቶችን እንዲያስገኝ ከተፈለገ፣ ይህ ሰራዊት ቃለ መሃለውን በትክክል ከሥራ ላይ እንዲያውልና ተዋግቶ የማሸነፍ ዕድሉ በጣም ከፍ ያለ እንዲሆን ለማድረግ ከተፈለገ፣ በዚህ ሥራ ላይ ለመረባረብ ይቻላል የሚል ግምት አለን።
ለዚህ አይነቶቹ አንቂዎች በሕዝባዊ ሠራዊቱ ውስጥ ያሉትን ብሄረሰቦች ቋንቋዎች የሚያውቁና በነዚህም ቋንቋዎች የፖለቲካ ትምህርትን ለመስጠት የሚችሉ ከመሆናቸውን በላይ፣ እነርሱም እራሳቸው የኢትዮጵያንና የዓለም ሁኔታዎች በማያቋርጥ መንገድ በመከታተል እውቀታቸውን የሚያዳብሩበት ዘዴ መፈጠር ይኖርበታል። ሊፈጠርም ይችላል። በተረፈም፣ ሕዝባዊ ሠራዊቱ በውጊያዎች መካከል የጥቂት ጊዜያትን እረፍቶች ማግኘቱ ስለማይቀር፣ ይህንንም ለከፍተኛ ወታደራዊና የንቃተ ህሊና ትምህርት የሚያውልበት ዘዴ ቢፈጠር ይጠቅማል እንላለን።
አብዮታዊ አመራር ሲባል ይህ ብቻም አይደለም። አብዮታዊ አመራር፣ በተለይ በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ሁኔታ፣ የማርክሲዝም-ሌኒኒዝምን ሚሊተሪ ሳይንስና፣ ዳይሌክቲካዊ የውጊያ ስልትን፣ በአዝማችና በዘማች፣ በመኮንንና በተራ ወታደር፣ በአዛዥና በታዛዥ መከከል የሚኖሩትን ግንኙነቶች፣ በጠቅላላውም ያቀራረብና የአሰራር ዘዴን ሁሉ ይመለክታል። በርግጥ እነዚህ ነገሮች ሁለ ለማቅናትና ለመሟላት ጊዜን ይጠይቃል። ቢሆንም፣ በአንድ በኩል የነዚህ ነገሮች መሟላት የድሉን ወቅት የሚያዘገይ ሳይሆን እንዲያውም የማያፋጥነው መሆኑንና፣ በሌላ በኩል ደግሞ የነገሮችን አስፈላጊነት በሙሉ ልብ ተቀብሎ ይህ ሠራዊት በተቻለ መጠን፣ በማያቋርጥ አኳኃን፣ እይተዋጋ እንዲማርም ለማድረግ መጣር የግድ ያስፈልጋል ብለን እናምናለን።
የኤርትራን ችግር በተለይ በሚመለከተው በኩል፣ የተባለው አብዮታዊ አመራር አስፈላጊነት ሊታለፍ የማይችል ግዴታ ነው። በዚያ መስክ የሚሰማራው ሠራዊት በድርጊቶቹ፣ በሚፈጥራቸው ግንኙነቶች፣ ባቀራረቡ፣ የኤርትራን ሰፊ ሕዝብ እምነት ለማትረፍ የሚችል፣ ለሰፊው ሕዝብ ደህንነት የሚንከባከብ እንጂ ወዳጅና ጠላትን ሳይለይ የማይመታ፣ ቢቻልም ሰፊውን ሕዝብ የሚያነቃና የሚያደራጅ፣ በዚህ ሕዝብ ሊታቀፍ የሚችል ሠራዊት መሆን ይኖርበታል። የዚህን አይነት ሁኔታ ለመፍጠር የሚችል ሠራዊት ተገንጣይ ቡድኖቹን ብቻውን ሳይሆን ሕዝቡንም አሰልፎ ስለሚወጣ በእርግጥ ድልን ይቀዳጃል። ደግሞም፣ እንኳንስ ተገንጣይ ቡድኖቹ ቀርተው የውጭ ወራሪዎችን በብዙ ሺህ ተሰለፈው ቢመጡም፣ የዚህ አይነቱ ሠራዊትና ሕዝብ ምንጊዜም ቢሆን አሸናፊ ይሆናል። እንደዚህ ካልሆነ ግን፣ የአረብ አድሃሪ ኃይሎችን በፖለቲካ ካልበለጥናቸው፣ ኤርትራ ያሉ አድሃሪ ቢሮክራቶችና ሌሎችም አድሃሪዎች እንደሚመኙት፣ ሰራዊቱ ከሰፊው ሕዝብ ጋር ከተጋጨ፣ አብዮታችን እንደሚቀለበስና እንድነታችንም እንደሚናጋ ምንም ጥርጥር የለውም።
በመጨረሻም፣ አብዮታዊ አመራር ማለት በጠላት ሰፈር ያሉትን ቅራኔዎች በሚገባ ተረቶ የሚጠቀምባቸው፣ ወደ አብዮቱ ለመምጣት የሚችሉትን ኃይሎች የሚሰበስብ፣ እስከመጨረሻው ሊተናነቁን የሚፈልጉትን አድሃሪ ኃይሎች የሚበታትንና ነጥሎ የሚመታ፣ የሀገር ዉስጥንና የዓለምአቀፍን ሁኔታዎች እየተከታተለ ለወቅቱ የሚያገለግሉ የትግል ታክቲኮችን የሚያመጣ አመራር ማለት ነው።
መኢሶን የአብዮታዊ አመራርን ጥያቄ የሚያነሳው እነዚህ ሁሉ የትግሉ መስኮች በማመዛዘንና ዘመቻው እስከተቻለ ድረስ ለኢትዮጵያ አብዮት ከሁሉ ከፍተኛ የሆኑ ውጤቶችን እንዲያስገኝ ለማድረግ ባለው ጉጉት እንጂ ድርጅታችን ተቃዋሚ አሉባልተኞች ለሚያስወሩት ለማንኛውም ሌላ ምክንያት እንዳይደለ አንባቢዎቻችን ሁሉ እንዲያውቁት በዚህ አጋጣሚ ልንጠይቅ እንወዳለን። የመኢሶን ምኞት ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ተዋርደው፣ ተረግጠውና በኢሰብአዊ ፊውዶ-ፋሽስት ሥርዓት እጅ እግራቸውን ተጠፍረው የሚኖሩት የኢትዮጵያ ጭቁን ሕዝቦች በአብዮታቸውና በአንድነታቸው ጠላቶች ላይ በተቻለ ፍጥነተ ድል እንዲያገኙና አዲስ ህብረተሰብን ለመገንባት እንደችሉ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረግ ብቻ ነው።
ድርጅታችን በየጊዜው ባወጣቸው ጽሁፎች የኢትዮጵያ ሕዝቦችና ትግል ረጅምና መራራ እንደሚሆን ደጋግሞ ገልጿል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራም፣ ፊውዳሊዝምን፣ ኢምፔሪያሊዝምንና እና ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝምን ጨርሶ ለመደምሰስና ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክን ለመገንባት የሚያስችሉን ሦስት መሳሪያዎች የወዛደር ፓርቲና በዚህ ፓርቲ የሚመሩ ሕዝባዊ አብዮታዊ ግንባርና ሕዝባዊ አብዮታዊ ጦር መሆናቸውን በግልጽ አስፍሯል። እነዚህን ሶስት ፍቱን የአብዮት መሣሪያዎች ለመፍጠርና በእነርሱ አማካይነት ሰፊውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ከዳር እስከዳር አንቀሳቅሶ፣ እንደአንድ ሰው እንዲነሳ ለማድረግ፣ ይህም ሕዝብ ሶስቱን ጠላቶች በማያዳግም አኳኋን እንዲደመስሳቸው ለማድረግ፣ ገና ብዙ የትግል ጎዳና ይቀረናል። ስለሆነም፣ ሰፊ ሕዝብ ለአብዮትና ላገሩ አንድነት ለመሰዋት በተዘጋጀበት በአሁኑ ወቅት፣ ደጋግመን ለማሳሰብ የምንፈልገው፣ እየተዋጋና እየተከላከለም፣ ካሁኑ ለረጅም ጊዜ ትግሉም እንዲዘጋጅ ነው።
በሚዘጋጀው ዘመቻ ለኢትዮጵያ አብዮት ከፍተኛ ድሎችና ለማስገኘትና አብዮትን ከቅልበሳ ለማዳን የሚያስችለው አማራጭ የሌለው ብቸኛ ጎዳና አብዮቱን ማፋፋም ብቻ እንደመሆኑ መጠን፣ አብዮቱን ማፋፋምም ለረጅም ጊዜ ትግል እንደመዘጋጀት ይቆጠራል። የኢትዮጵያ አብዮት በደረሰበት ደረጃና ባሉት የአገሪቷ ችግሮች፣ ይህ አብዮት ዛሬ እንኳንስ ወደ ኋላ ሊያሸገሽግ ቀርቶ ባለበትም እንኳን ለመቆም ቢሞክር እንደሚደመሰስ እርግጠኞች መሆን አለብን። ስለዚህም ነው አብዮቱን ማፋፋም አማራጭ የሌለው ጎዳና ነው የምንለው።
ግን ደግሞ አብዮቱን ማፋፋም ማለት ምን ማለት ነው?
አብዮቱን ማፋፋም ማለት፣ የተዘጋጀውና የሚዘጋጀው ዘመቻ፣ “ንጹህ” ወታደራዊ ድርጊት ሳይሆን፣ ካገሪቷ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና የማህበራዊ ኑሮ ጉዳዮች ሁሉ ጋር የተያያዘ መሆኑን ተገንዝቦ፣ በነዚህ መስኮች ሁሉ የሚካሄዱትን ትግሎች ከዘመቻው ጋር ማቀነባበር ማለት ነው። እንደዚሁም አሁን ባሉት የአገሪቷ ችግሮች ላይ ሌሎች ሌሎች ሊጨመሩ እንደሚችሉ አስቀድሞ ለማየትና ለእነዚህም ችግሮች መዘጋጀት ማለት ነው። ለምሳሌ በጅቡቲ ነፃነት ሳቢያና በነሳውዲ አረቢያ ድጋፍ አማካኝነት፣ የአሊሚራህ ሰዎች በአፋር በኩል አዲስ ግንባርን ሊፈጥሩብን ይችላሉ። ኢምፔሪያሊዝምም በኬንያ በኩል እንደዚሁ ሊሞክር ይችላል። የቅዳሜ ዕለቱን ሰልፍ ያየው አድሃሪው ቢሮክራሲ ሴራዎቹንና ተንኮሎቹን የበለጠ ረቂቅ በማድረግ ለፀረ አብዮት ኃይሎች መሥራቱን ይቀጥላል፣ ወዘተ። ስለዚህም፣ ለአገሪቷ አብዮትና ለአንድነቷ የሚደረገው ተጋድሎ ዛሬ ካለው ሁኔታ አስር እጅ ወይንም መቶ እጅ የበለጠ የሰፊውን ሕዝብ ተሳትፎ የሚጠይቅበት ጊዜ ይመጣል ማለት ነው።
በዚህ ሁኔታ፣ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፣ በማህበራዊ ኑሮ፣ በዲፕሎማሲና በወታደራዊ መስኮች አገሪቷን አቀነባብራ ልታካሂዳቸው የሚገቧት ትግሎች እጅግ የተወሳሰቡና አስቸጋሪ ስለሚሆኑ፣ ካሁኑ አንዳንድ እርምጃዎችን በመውሰድ ለተባለው ረጅም እና መራራ ትግል ዝግጅት ለማድረግ ይቻላል። ከነዚህም እርምጃዎች ውስጥ አንዳንዶቹን ባጭሩ ለመጠቆም ያህል፣ በኢኮኖሚ በኩል የሥራ አጠን ቁጥር አሁንም ይበልጥ ለመቀነስና አዳዲስ የሥራ መስኮችን በተቻለ ፍጥነት ለመክፈት ጥረት ማድረግ፣ ዋጋን መቆጣጠር፣ ወዛደሩና አርሶአደሩ ምርትን ከፍ አንዲያደርጉ መቀስቀስ ያስፈልጋል። በፖለቲካ በኩል፣ የተራማጆችን ህብረት ማጠንከር፣ ዲሞክራሲያዊ መብቶችን ለሰፊው ሕዝብ ማወቅ፣ የብሄረሰቦችን መብቶች ካሁኑ ደረጃ በደረጃ ከሥራ ላይ በማዋል የሰፊውን ሕዝብ ተሳትፎ እጅግ በጣም መጨመር ያስፈልጋል። እንደዚሁም፣ አብዮቱ የፈጠራቸውን አዳዲስ ሕዝባዊ ድርጅቶች፣ ማለትም የገበሬ ማህበራትን፣ የቀበሌ ማህበራትንና ሌሎችንም የሕዝብ ድርጅቶች ማጠናከር፣ የነዚህን ሕዝባዊ ኃይሎች የንቃትና የትጥቅ ሁኔታ በፍጥነት ከፍ ማድረግና ሰፊው ሕዝብ የራሱን ነፃ እርምጃዎች የሚወስድበትን ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል። ይህንንም ለማድረግ፣ ውስጥ ውስጡን ተደራጅቶ በተቀናበረ መንገድ በአብዮቱ ላይ የሚያሻጥረውን ቢሮክራሲ የላንዳች ማወላወል መታገል ያስፈልጋል። በመጨረሻም፣ በማህበራዊ ኑሮና በወታደራዊ መስኮች፣ በዲፕሎማሲ፣ በአሁኑ ሰአት መንግሥት ሊወስዳቸው የሚችለውን እርምጃ ሁሉ ካለው ትግል አንፃር፣ የሰፊውን ሕዝብ ሙሉ ድጋፍና ተሳትፎ በሚያስገኝ መንገድ ሁሉ ከሥራ ላይ ለመዋል መጣጠር፣ ለሚካሄደው ዘመቻ የማይበገር ደጀንን ለመፍጠር ይችላል ብለን እናምናለን። ለዚህም በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ካድሬዎችን በሕዝቡ ውስጥ ማሰማራት ያስፈልጋል።
ዞሮ ዞሮ ጥያቄዎችና ዝግጅቶች ሁሉ ቁልፍ የሰፊው ሕዝብ ይበልጥ መንቃት፣ መደራጀትና መታጠቅ፣ ማለትም በመሰረቱ የፖለቲካ ጥያቄ መሆኑን በመገንዘብ፣ ቅድሚያውን ለፖለቲካ መስጠት ያስፈልጋል። የኢትዮጵያ አብዮታውያንና ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ከሁሉም በላይ እምነታቸውን መጣል ያለባቸው በሰፊው ሕዝብ ላይ ነው። በሰፊው ሕዝብ በሙሉ ልብ ለመተማመን እንደሚቻል ደግሞ ባለፈው ቅዳሜ የተሰለፉት በብዙ ሺ የሚቆጠሩ አርሶ አደሮች በተጨባጭ መንገድ አሳይተዋል።
የቅዳሜ፣ ሰኔ 18 ቀን፣ ወታደራዊ ሰልፍ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ቦታን የሚይዝ ሰልፍ ነው። የዚያ ከፍተኛ አርሶአደር ቁጥር በወታደራዊ ስልት መሰልጠንና መታጠቅ እራሱ [የማይነበብ – አዘጋጆቹ] በወደፊቱ የኢትዮጵያ አብዮት ሂደት ላይ ተዕእኖውን እንደሚያኖር ሳይታለም የተፈታ ነው። ይህንን ሰራዊት በትክክለኛው ጎዳናና በርግጥም በሳይንሳዊ ሶሻሊዝም ለመመራት ከተቻለ፣ የኢትዮጵያ አብዮት ትላልቅና አስደናቂ ድሎችንም ሊያገኝ ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ ልዩ ልዩ የፖለቲካ ስህተቶች ከተፈጸሙ እና ይህንን ሠራዊት በሚገባ ለማሰለፍ ካልተቻለ የኢትዮጵያ አብዮት በጣም አስቸጋሪ ቀናት ሊያጋጥሙትና ሂደቱን ሊያዘገዩት ይችላሉ። የፊተኛው ከደረሰ እጅግ በጣም ጥሩ ነው። የኋለኛው ከደረሰም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ከተጋድሏቸውና ከለምዳቸው ተምረው ትግሉን ይቀጥሉና ለመጨረሻም ያሸንፋሉ።
አብዮቱን ለማዳን፣ አብዮቱን ማፋፋም!
ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለጭቁኖች ያለ ገደብ!
የማርክሲስት-ሌኒኒስት ድርጅቶች ህብረት ይጠንክር!
የነቃ፣ የተደራጀና የታጠቀ የሰፊው ሕዝብ ትግል ያሸንፋል!
አብዮቱ አጥቂነቱን እንዲቀጥል፣ ያድሃሪው ቢሮክራሲ አሻጥር እንቋቋም!
አድሃሪ ኃይሎች በኢትዮጵያ ከተሞች የሽብር ፈጠራ ዘመቻቸውን ከጀመሩበት ከመስከረም ወር 1969 ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ከቀበሌ ማህበራት ሊቃነመናብርት፣ ምክትል ሊቃነመናብርትና ከፀሐፊዎች፣ ከፍርድ ሻንጎ፣ የአብዮት ጥበቃና የሕዝብ ደህንነት አባሎች ውስጥ 62 ጓዶች በአድሃሪዎች ጥይት ወድቀዋል፤ 93 ጓዶች ቆስለዋል።
ደጋግመን እንደገለጽነው አብዮት መራራና ብዙ መስዋዕትነት የሚጠይቅ ተጋድሎ ነው። ታጋዮች ከጎናችን እየተቀነጠሱ ሲወሰዱብን የነሱን የትግል አርማ አንስተን እኛም መቀጠል እንዳለብን እናውቃለን። በነዚህ በተሰዉት ጓዶች ምክንያት በየጊዜው የትግልቃል ኪዳናችንን እያደሰን በንጹህ ደማቸው የተነከረውን የትግል አርማ እያነሳን፣ “ታጋይ ይሞታል እንጂ ትግል አይሞትም” እያልን እስካሁን ወደፊት በመጓዝ ላይ ነን። እስካሁን አድሀሪዎች እንደተመኙት መሪዎቻቸው በነጭ ሽብር ስለተመቱ የቀበሌ ማህበራት አልፈረሰም። ሰፊው ሕዝብ ተሸብሮ ወደዚያ የባርነት ስርዓት ተመልሶ መግባትን አልመረጠም።
ነገር ግን ደጋግመን እንደገለጽነው በጓዶች መስዋእትነት ትግሉ ወደፊት ሊቀጣጠል የሚችለው ከእነዚህ ጓዶች ሞት አስፈላጊው ትምህርት ስንቀስም ብቻ ነው። ሰኔ 14 ቀን 1969 የአብዮቱን የመጨረሻ መስዋዕትነት ተቀብሎ ሕይወቱን ለውድ እናት አገር አሳልፎ በሰጠው በጓድ አምበርብር በላይ የቀብር ሥነ ስርዓት ላይ የተሰበሰበው ሕዝብ ደጋግሞ ያስተጋባው መፈክር “አብዮታችን ከጥቂት ወደ ተከላካይነት ማፈግፈጉ አንገብግቦናል” የሚል እንደነበር ይታወሳል። በኛ ግምት ታጋይ ጓዶችንና አብዮታቻንን በማስጠቃት ላይ ያለው አንዱና ዋነኛው ምክንያት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አድሃሪው ቢሮክራሲ በቀበሌን ማህበራት ተመራጮች ላይ እና በጠቅላላው በተራማጆች ላይ የሚያደረገው ተጽዕኖ ነው። የቀበሌ ተመራጮችን በማሰር፣ በማንገላታት፣ ነፃ እርምጃ እንዳይወስዱ ያፍናል። የታወቁ አድሃሪዎችን ጠቁመው አሲዘው ዘወር ከማለታቸው ቢሮክራሲው የተረከባቸውን አድሃሪዎች እንኳን ተገቢ ቅጣት ሊሰጣቸው ይቅርና መልሶ ይለቅባቸዋል። እነዚህ አድሃሪዎች በቀበሌያቸው ተመልሰው በመደንፋት የቀበሌ ተመራጮችንም ሆነ ሕዝቡን ተስፋ ሊያስቆርጡ ይሞክራሉ። አንዳንዶቹ እንዲያውም (በተለይ ቀበሌው ያልታጠቀ ከሆነ) ይፋ የሆነ የማጥቃት እርምጃ ይወስዳሉ። በአጭሩ የአብዮቱ ደጋፊዎች እንኳን ራሳቸው ነፃ እርምጃ እየወሰዱ የአብዮቱን አጥቂነት ሊያፋፍሙ ይቅርና በዛሬው ወቅት ሕጋዊ በሆነ መንገድ እንኳን በአድሃሪዎች ላይ እርምጃ ለማስወሰድ ተስኗቸው እናያለን። ይህ እንግዲህ አድሃሪ ኃይሎችን አርበድብደን ይዘን ከነበረበት ከየካቲትና ከመጋቢት ወር ምን ያህል እንዳሸገሸግን የሚያሳይ ነው። አብዮታዊያንና ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት በአድሃሪው ቢሮክራሲ ረቂቅ ሤራ ባስቸኳይ ነቅተው የማያደግም አርምጃ ካልወሰዱ ይህ አደገኛ ማሸግሸግ አብዮቱን ሊያጠፋ ይችላል።
አብዮታችን በገቢር ወደ አጥቂነት ካልተሸጋገረ፣ በዚህ መልክ የቀበሌ ጓዶች ብቻ ሳይሆኑ ተራማጆች ከያሉበት እየተለቀሙ መመታታቸው ይቀጥላል። እንደ ኢትዮጵያ ባለች ግንባር ቀደም ድርጅት በሌለባት አገር የታጋይ ግለሰቦች ሞት ወሳኝ የሆነ ሚና እንደሚኖረው ግልጽ ነው። በተለይ ደግሞ ጓዶች ሲገደሉ፣ ከነሱ ሞት አስፈላጊውን ትምህርት ቀስመን አብዮቱን ለማራመድ ተጨባጭ እርምጃዎች ካልወሰድን “ታጋይ ቢሞት ትግል አይሞትም” የሚለው አነጋገር ትርጉም- የለሽ ይሆናል። የጓዶችን የትግል አርማ ይዞ ትግሉን መቀጠል ማለት ከነሱ ሞት ትምህርት ቀስሞ ወደፊት መግፋት ማለት ነው። በአሁኑ ወቅት፣ ለብዙ ጊዜ ተተኪ የማናገኝላቸው ታጋይ ጓዶችን እያጣን ነው። እነዚህን ጓደኞች ለማጣት የቻልንበት ዋነኛው ምክንያት አብዮታችን ወደ ተከላካይነት እያፈገፈገ በመምጣቱ ነው። የአድሃሪውን ቢሮክራሲ ሴራ አክሽፈን አብዮታችንን ወደ አጥቂነት ካላሸጋገርነው በየዕለቱ ከሚቀነጠሱት ጓዶቻችን ጋር አብዮታችንን አብሮ መገዝገዙን ይቀጥላል። ይህ ደግሞ ቀልበሳን መጋበዝ ነው።
***
ጓዶች፡- ጋዜጣችንና የሌሎች ድርጅቶችንም ጋዜጦች አንብቡ፣ አስነብቡ፣ ተወያዩባቸው፣ ይዘታቸውን በሚገባ መርምሩ። አብዮታዊ ሂሳችሁን ሰንዝሩ።