የሰፊው ሕዝብ ድምፅ
ቁጥር 48፣ ታህሣሥ 8፣ 1969
የፅሁፉ ፍሬ ሀሳብ
መኢሶን በዚህ የሰፊው ሕዝብ ድምፅ እትሙ፣ “ከማይታመኑ ሰዎች ጋርም ቢሆን ጊዜያዊ ህብረትን መፍጠር የሚፈሩ፤ በራሳቸው የማይተማመኑ ሰዎች ናቸው” የሚለውን የሌኒንን አባባል ጠቅሶ፤ የመላ ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ ከሃቀኛ ተራማጆች ጋር ህብረት ለመመስረት ያለውን በጎ ፈቃድ ይገልጻል። አያይዞም፣ በተለይ ኢሕአፓ፣ አድሃሪ ሃይሎችና ኢምፔሪያሊስቶች መኢሶን ላይ የሚወረውሯቸው አሉባልታዎችና ተራ ስድቦች ከአብይ የፖለቲካ ክርክሮች ለመሸሽ የሚደረጉ ማዘናጊያዎች ናቸው ይላል። መኢሶንን አንዴ “የብሔር ትምክህተኛ ነው” ሌላ ጊዜ ደግሞ “ጠባብ ብሔርተኛ ነው” ፣ “መኢሶን ተስፋፋ” እያሉ የማይጠቅም ወሬ ከማሰራጭት ይልቅ፣ የአገሪቱ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ እንዲከራከሩና እንዲወያዩ፣ ከዚያም ወደ ትብብር እንዲያመሩ ያሳስባል።
“ከማይታመኑ ሰዎች ጋርም እንኳን ቢሆን ጊዜያዊ ህብረትን መፍጠር የሚፈሩ በራሳቸው የማይተማመኑ ብቻ ናቸው፤ የዚህ አይነቶቹን ህብረቶች ሳይፈጥር ሊኖር የሚችል አንድም የፖለቲካ ፖርቲ የለም።”
ሌኒን፡ ምን መደረግ አለበት
ከ1967 መጨረሻ ጀምሮና በተለይም ከመጋቢት 1968 ወዲህ፣ የኢህአፓን ደንፊ ቡድን ፀረ አብዮታዊነት ለሰፊው ሕዝብ ካጋለጡት የግራ ድርጅቶች ውስጥ አንዱ መኢሶን ነው። እንዲያውም ባለፈው አመት በመንግሥት ሬዲዩና ጋዜጦች አማካይነት ሰፋ ያለ የፖለቲካ ትግል በተካሄደበት ጊዜ ስለ “ሁለቱ የፖለቲካ መስመሮች” ሲነገር ስለመኢሶንና ስለኢህአፓ መወራቱ እንደነበረ ለማንም አንባቢና አድማጭ ግልጽ ነበር። ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ ሃቀኛ ተራማጆች ሁሉ በዚህ ፀረአብዮታዊ ቡድን ላይ በጊዜው ቆራጥና የማያወላውል ትግል በማድረግ ለኢህአፓ የማይቀርለት የፖለቲካ ክስረት ውስጥ መግባት ተገቢውን አስተዋፅዎ አድርገዋል። አሁን ባለንበት ሰዓት ኢህአፓ በፖለቲካ በኩል ፈፅሞ እንደከሰረ ለማንም ተመልካች ግልፅ ነው። በርከት ያሉ ጓዶቻችንን መግደሉም የክስረቱ እንጂ የጥንካሬው ምስክር አይደለም። ስለሆነም፣ በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ላይ አሁን ተጠናክረው የሚታዩት መኢሶንና ሌሎች ሃቀኛ ተራማጆች ድርጅቶች ናቸው።
በመጠናከራችን ምክንያት ሳይሆን አይቀርም፣ ከጥቂት ወራት ወዲህ፣ በተለይ ድርጅታችን የኢምፔሪያሊዝምና የሌሎችም አድሃሪዎች የጥቃት ኢላማ ሆኗል። ኢምፔሪያሊስት ፕሬስ ደጋግሞ ኢህአፓን እያሞጋገሱ መኢሶንን እያጥላላና “በሕዝቡ ውስጥ ተደማጭነት የለውም” እያለ ለፍፏል፤ እየለፈፈም ነው። አንዳንድ የብሄር እንቅስቃሴዎች መኢሶንን “የነፍጠኛ ድርጅት ነው” ሲሉ፣ አንዳንድ የብሄር ትምክህተኛ ሰፈሮች ደግሞ ድርጅታችንን “የጠባብ ብሄርተኞች ድርጅት ነው” ይላሉ። በዚህ አይነት ሁሉም በፈጠራና በአሉባልታ መኢሶንን ለመቃወም ሲፍጨረጨሩ ይታያሉ። ከኢምፔሪያሊዝምና ከሌሎችም አድሃሪዎች የሚደርሱብንን ጥቃቶችና ዘመቻዎች በደስታ እንቀበላቸዋለን። የመስመራችንን ትክክለኝነት ያረጋግጡልናልና። ይልቁንስ አሳሳቢ የሚሆነው ማርክሲስት-ሌኒኒስት ድርጅቶች ናቸው ብለን ከምንገምታቸው ቡድኖች የሚሰነዘሩብን መሰረት የሌለው ክስ፣ ወቀሳና ዘመቻ ነው። “መኢሶን ለዘላለም ይኑር!” ፣ “ኢህአፓ ይውደም፣ መኢሶን ይለምልም!” ስለ ተባለ፣ አንዳንድ ጓዶችና ቡድኖች ይህንን እንደትልቅ የመከራከሪያ ነጥብ ወስደው፣ በድርጅታችን ላይ ዘመቻ ያካሂዳሉ። “መኢሶን ተስፋፋ!” ተብሎም እንደክስ ቀርቧል። አሁን ያለው አዝማሚያ በእውነተኛ የልዩነት ነጥቦች ላይ ለመከራከር የመፈለግ ሳይሆን፣ ጥቃቅን ነጥቦችን በማንሳት፣ ወይንም ምንም መሰረት በሌለው ጥርጣሬ ብቻ በመገፋፋት፣ በመኢሶን ላይ መዝመትና ከሌሎች አድሃሪ ተቃዋሚዎቻችን ጋ በግብር የመሰለፍ አዝማሚያ ነው። ያህም ኢምፔሪያስቶችና ሌሎችም አድሃሪዎች ተራማጆችን ለመከፋፈል ለሚያደርጉት ጥረት መግቢያ ቀዳዳ ከመስጠት አልፎ ለአብዮት ወገኖች ምንም የሚሰጠው ጥቅም እንደሌለ እናምናለን።
የየካቲት 66 የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ እንቅስቃሴ ከመጀመሩ በፊት በመኢሶንና በኢህአፓ መካከል ስለነበረው ግኑኝነት ወደፊት በታሪክ ይፃፋል። እዚህ ላይ ግን ለማመልከት የምንፈልገው፣ የንዑስ ከበርቴው ደንፊ ቡድን ከእኛ ጋር ሀ ብሎ ግጭቶችን ሲጀምር፣ እርሱም እንደዚሁ በትርኪ ምርኪ፣ በአሉባልታ፣ በጥርጣሬ ላይ ያተኩር እንደነበር ነው። የኢህአፓን ሰዎች ከዚህ አይነቱ የተወናበደ አሳባዊ አቀራረብ አውጥቶና ጎትቶ በግድ ወደ ፖለቲካ ክርክር፣ ወደ መስመር ክርክር ለማስገባት ብዙ ድካምና ጊዜን ጠይቆ ነበር። ማርከሲስት – ሌኒኒስት ቡድኖች ናቸው የምንላቸው አንዳንድ ድርጅቶች በጥርጣሬ ላይ ከተመሰረተ ክስና ከአሉባልታ ወጥተው፣ ከአሁኑ በእውነተኛ የመስመር ልዩነት ጥያቄዎች ላይ እንዲያተኩሩ ያስፈልጋል።
በቅርቡ በመኢሶን ላይ እየተጠናከረ የመጣው ክስ፣ መኢሶን የተራማጆችን ህብረት አይፈልግም፤ ማርክሲስት – ሌኒኒስት ድርጅቶች ተቀራርበውና ተዋህደው የወዛደሩን ፓርቲ እንዲፈጥሩም አይፈልግም፤ ራሱን ወደ ወዛደሩ ፓርቲ ለመለወጥ ይታገላል፣ ወዘተ. የሚል ነው። ይህ ሁሉ የሚመሰረተው በአሉባልታ፣ በጥርጣሬ፣ በአሳባዊ “ትንተና” ላይ እንጂ የመኢሶንን ኘሮግራም፣ ጽሁፎቹንና ድርጊቶቹን በማጥናት ላይ አይደለም። ስለሆነም፣ የተራማጆችን ህብረትና የወዛደሩን ፓርቲ ስለመፍጠር ጉዳይ ድርጅታችን የነበረውንና ያለውን አቋም ደጋግሞ ግልጽ ማድረግ ስለሚያስፈልግ፣ ከዚህ በታች ባጭር ባጭሩ አንዳንድ ነጥቦችን እናነሳለን፡-
I
“ለመደራጀት ወይንም በትንሽም ቢሆን የተደራጁትን የግራ ኃይሎች በአንድነት ባንዳች አይነት መንገድ ለመሰብሰብ፣ የተራማጆችን ህብረት በተቻለ ፍጥነት በተግባር ዙሪያ ለመፍጠር፣ ከሁሉ አስቀድሞ በኢትዮጵያ ሁኔታ ትንተና ላይ ለመቀራረብና ወደ ተመሳሳይ አቋም ለመድረስ መሞከር አለብን። . . . እንግዲህ የመጀመሪያው ለህብረት መመስረቻ የሚያገለግለው መንገድ ከተግባር ጋር የተጣመረ የትንተና አንድነት ሲሆን፣ በተራማጆች መካከል ያሉት ልዩነቶች የትኞቹ እንደሆኑ ለይቶ ማወቅና እነዚህም በውስጣችን ተድበስብሰው እንዳይታለፉ፣ የሃቀኛና የጋለ ዴሞክራሲያዊ ትግል ርዕስ እንዲሆኑ ማድረግ ያስፈልጋል።. . . . የትግሉ አላማ በተቻለ ፍጥነት ወደ ድርጅታዊ መቀራረብና አብሮ መስራት ከዚያም ወደ አንድነት ለመተላለፍ መሆን አለበት። አላማችን በፍጥነት ወደ መቀራረብና የሥራ ትብብር ለማድረስና የሰፊውን ሕዝብ ትግል ወደ ፊት ለማራመድ ተራማጆች የድርሻቸውን እንዲያረክቱ ለማድረግ ከሆነ፣ የነፃ ክርክር መስፋፋትና የእያንዳንዱ ተራማጅ ቡድን በተቀናበረ አኳኋን ሙሉ አስተያየቱን ለመስጠት መቻል ያጠነክረናል እንጂ ፈፅሞ አይጎዳንም. . ..”
እነዚህ ቃላት ዛሬ የተፃፉ አይደሉም። የዛሬ 2 ዓመት፣ በየካቲት 3 ቀን 1967 ተፅፈው፣ በዚያ ወር በ23፣ “የተራማጆች ህብረት” ተብሎ በሚጠራው የመኢሶን መፅሄት፣ በቁጥር 2 ላይ የወጡ ነበሩ።
በየካቲት 1967 መኢሶን የተራማጆች ህብረት እንዲፈጠር ጥሪ አድርጎ ነበር። በተጠቀሰው መፅሄት ውስጥ ስለዚህ ህብረት ጥሪ ብቻ ሳይሆን የተጨበጡ እርምጃዎችም ተሠንዝረው እንደነበር ይታወሳል። ከቀረቡት ነጥቦች ውስጥ የሚከተሉት ይገኙበት ነበር፡-
– በአዲስ አበባና በሌሎችም ክፍላተአገር የነበሩት ቡድኖች እንዲቀራረቡ
– ፅሁፎቻቸውን ማውጣት እንዲቀጥሉ፣ ግን የፅሑፎቹን ይዘቶች ለማቀራረብ እንዲሞክሩ
– አንድ የጋራ መፅሄት ቦርድ እንዲፈጥሩ። “የተራማጆች ህብረት” ራሱ የጋራ መፅሄት ሊሆን እንደሚችል።
በጠቅላላው የእያንዳንዱ ቡድን ትግል በሚመለከተው በኩል፣ ለሁሉም የተግባር አንድነትን የሚያስከትል ፕሮግራም ማውጣት እንደሚያስፈልግ መፅሄቱን ከጠቀሰ በኋላ፣ የሚከተሉትን የፕሮግራም ነጥቦች ይሰነዝራል፡-
1ኛ/ ሥራ ተከፋፍሎ ሶሻሊስት ስነ ፅሑፎችን መድረስና መተርጎም
2ኛ/ በእድገት በህብረት ዘመቻና ሊወጣ የታቀደውን የመሬት አዋጅ ከሥራ ላይ ለማዋል በሚደረገው ትግል መሳተፍ።በገጠር እንደርሱ ሲሆን፣ በከተማም በወዛደሩ ውስጥ የፖለቲካ ሥራን ማስፋፋት።
3ኛ/ ብዙዎች አብዮታውያን በገጠር እንዲሠማሩ ማድረግ
4ኛ/ ለዴሞክራሲያዊ መብቶች መታገል። በተለይም የብሄረሰቦች እኩልነት እንዲታወቅና የኤርትራ ችግር
በፍጥነት ሠላማዊ መፍትሄን እንዲያኝ። በብሄረሰብ የተደራጁትን አብዮታዊያን በሚመለከት በኩል “በኛ አስተያየት በብሄረሰብ ደረጃ የተደራጁ ተራማጆችን ሁሉ ከትምክህተኛ ሆነ ከጠባብ ብሄርተኝነት በሽታ እንዲፈወሱና አብረውን እንዲሰለፉ ለማድረግ መጣጣር ያስፈልጋል። የተራማጆች ህብረት እነርሱንም ለማጠቃለል መቻል አለበት። . . . ” የሚል ነበር።
5ኛ/ የታሰሩ ተራማጆች እንዲፈቱ፣ በመንግሥት ዙሪያና በቢሮክራሲው ውስጥ የተሰገሰጉት የኢምፔሪያሊዝም ቡችሎች እንዲጋለጡ መታገል
6ኛ/ የደርጉን የአንድ ፓርቲ አሳብ መታገልና ማክሸፍ።
“በተራማጆች ህብረት” ቁጥር 2 ውስጥ የዛሬ ሁለት አመት ቀርበው የነበሩት የተጨበጡ እርምጃዎች እነዚህ ሲሆኑ፣ ያኔ ይህ ህብረት እንዲፈጠር በተለይ ተፈልጐ የነበረው በዲሞክራሲያና በአብዮት ጋዜጦች ዙሪያ ተሰብስበው ከነበሩት ተራማጆች ጋር ነበር። ያን ጊዜ በርግጥም ከነዚህ ሁለት ጋዜጦችና ከሰፊው ሕዝብ ድምጽ በስተቀር ድምፁን ያሰማ የተራማጆች ቡድን አልነበረም።
ምንም እንኳን በመኢሶን ውስጥ ያኔም ቢሆን ከዲሞዎች [ኢህአፓ ሰዎች – የአዘጋጆች ጭማሪ] ጋር ውይይትና መቀራረብ ሊኖር እንደማይችል በርከት ያሉ ጓዶች ቢያምኑበትም፣ ድርጅቱ ውይይት እንዲደረግ ስለወሰነ፣ ረዘም ያለ ጊዜን የፈጀ ግንኙነት ተደርጐ ነበር። ከዚህ በላይ የተጠቀሰው አንቀጽ ደጋግሞ እንደሚያመለክተው፣ ለመቀራረብ፣ ህብረትን ለመፍጠርና፣ ከዚያም ለመዋሃድ መሰረታዊውና የመጀመሪያው እርምጃ በኢትዮጵያ ሁኔታ ትንተና ላይ መስማማት ስለነበር፣ ከዲሞዎች ጋር በዚህ ነጥብ ላይ ምንም ስምምነት ሊገኝ አልቻለም። ስለሆነም፣ ኢህአፖና መኢሶን በሁለት ተቃራኒ ወገኖች ተሰልፈው ይኸው እስከዛሬ፣ ኢህአፓ በግልጽ ፀረአብዮታዊነቱን እስከሚያረጋግጥበት ደረጃ ድረስ መጥተናል።
ይህንን የየካቲት 67ን አቋማችንን በሰፊው የጠቀስንበት ምክንያት አለን፡-
1ኛ) ይህ አቋማችን ከላይ የጠቀስነውን የሌኒንን መመሪያ የተከተለ መሆኑና አሁንም በዚያው መመሪያ ስር እንደተሰለፍን ለማረጋገጥ ነው።
“ከማይታመኑ ሰዎች ጋርም እንኳን ቢሆን ጊዚያዊ ህብረትን መፍጠር የሚፈሩ በራሳቸው የማይተማመኑ ብቻ ናቸው፤ የዚህ አይነቶቹን ህብረቶች ሳይፈጥር ሊኖር የሚችል አንድም የፓለቲካ ፓርቲ የለም።” ይላል ሌኒን።
ቀድሞም ሆነ ዛሬ መኢሶን ህብረት መፍጠርን ያልፈለገበትና ይህንኑም ለሌሎች ያላመላከተበት ወቅት የለም።
2ኛ) ከላይ የተጠቀሱት የህብረት መመስረቻ ሂደቶችና የኘሮግራም ነጥቦች፣ እነዚህኞቹ ከዛሬው ሁኔታ ጋር እንዲገናዘቡ ተደርገው ከሥራ ላይ ሊውሉ ይችላሉ።
በነዚህ ምክንያቶች፣ የዛሬ ሁለት ዓመት የነበረንን አቋም እንደገና ማስታወሱ ጠቃሚ መሰለን።
II
ከየካቲት 1967 ወዲህና በተለይም ደግሞ 1968፣ በኢትዮጵያ በርከት ያሉ አዳዲስ የተራማጆች ቡድኖች ተፈጥረዋል።ወደፊትም ሌሎች ሊፈጠሩ ይችላሉ። መኢሶንን በሚመለከተው በኩል፣ በርግጥ በነዚህ ባለፉት ሁለት አመታት ውስጥ፣ ድርጅታችን በአስተሳሰብም ሆነ በሰው ጠንክሯል። ይህንን ጥንካሬ ያገኘው እንዲሁ በባዶ ቦታ ትክክለኛ መስመር አለኝ ብሎ እጆቹን አጣጥፎ በመቀመጥ ወይንም በአንድ አይነት ተአምር ሳይሆን፣ በውስጡም ሆነ በውጭ የቀኝና “የግራ” አስተሳሰቦችን በቆራጥነት በመታገል ነው። በሌላ በኩል ደግሞ፣ የዛሬ ሁለት አመት ከነበርንበት ሁኔታ ይበልጥ በሰፊው ሕዝብ ውስጥ ለመግባት መቻሉ፣ ድርጅታችን ትክክለኛ መስመርን ተከትሎ እንደነበር ያሳያል።
ይሁንናም፣ መኢሶንም ሆነ ሌሎች የሃቀኛ ተራማጆች ቡድኖች በርግጥ በሰፊው ሕዝብ ውስጥ ገብተው ከዳር እስከ ዳር ሊያንቀሳቅሱት ከሚችሉበት ደረጃ ፈጽሞ አልደረሱም። ድርጅታችን ገና ለጋ ድርጅት እንደመሆኑ መጠን፣ የኢትዮጵያን የወዛደር ፓርቲና የሰፊውን ሕዝብ አብዮታዊ ግንባር፣ ከዚያም የኢትዮጵያን ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሬፑብሊክ ለመፍጠር በሚደረገው ትግል ውስጥ፣ አባሎቹ ዛሬ በመኢሶናዊነት ነገም በወዛደሩ ፓርቲ ውስጥ ብዙ መማርና መታገል ይኖርባቸዋል።
የወዛደሩን ፓርቲ አፈጣጠር በሚመለከተው በኩል፣ ከላይ የተጠቀሰው የዛሬ ሁለት አመት አቋማችን ካሬም እንዳለ ነው። ይህንኑ አቋማችንን በተለይ ኘሮግራማችን በደንብ አጽድቆታል።
ኘሮግራሙ እዲህ ይላል፡-
“መኢሶን በተቋቋመበት ወቅት በብዛት በአባልነት የያዛቸው አብዮታዊ ምሁራንን እንጂ በላብአደሩም ውስጥ ሆነ በጠቅላላው ለሰፊው ሕዝብ መሃል ገብቶ፣ ሰፊ ቅስቀሳና የማደራጀት ጥረት አድርጎ፣ ለመላ ኢትዮጵያ ጭቁኖች ትግል ተገቢውን አመራር የሚሰጥ ድርጅት አልነበረም። ይህንንም በመገንዘብ ከፓርቲ ይልቅ ራሱን ንቅናቄ ብሎ ሰየመ። አሁንም ቢሆን፣ ምንም እንኳን ተጠናክሮና ከላብ አደሩና ከሰፊው ሕዝብ ተዋህዶ፣ ለትግሉ የተጣራ አመራር ለመስጠት ያደረገው ተጋድሎ ብዙ ከፍተኛ ፍሬዎችን ቢያስገኝም፣ አንደኛ በላአደሩ ውስጥ የመዋሃዱ ዘመቻ ገና ብዙ ተጋድሎ እንደሚቀረው ለማመልከት፣ ሁለተኛ የማርክሲዝም – ሌኒኒዝም ተከታይ ቡድኖች ጋር ሃቀኛ የርእዩተአለም ትግል አድርጐ፣ ከነርሱ ጋር ተዋህዶ፣ በተጣራ የፖለቲካ መስመር የሚመራና ባላብአደሩ መደብ ላይ የተመሰረተ ፓርቲ ለመገንባት ያለውን ፍላጐት ለማመልከት “ንቅናቄ” የሚለውን መመሪያ ይዞ እንዲቆይ ተደርጓል።”
መኢሶን ዛሬ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ቆራጥ ታጋዮችንና ብዙ፣ ድርጅቱ እራሱ እንኳን የማያውቃቸውንና የማይደርስባቸውን ደጋፊዎች አፍርቷል። ይሁንናም፣ ድርጅታችን አሁንም ገና ለጋ ከመሆኑም በላይ፣ በብዙ ልዩ ልዩ ነጥቦች ከርሱ የተሻሉ ማርክሲስት-ሌኒኒስት ቡድኖች እንዳሉ ያምናል። መኢሶን እራሱን ሊያጠራና ለወዛደሩ ፓርቲም የሚጠበቅበትን አስተዋጽኦ ለማቅረብ የሚችለው በውስጥና በውጭ ከቀኝና “ግራ” አስተሳሰቦች ጋር ሲታገል፣ በተለይም ደግሞ ከወዛደሩና ከድሃው ገበሬ ጋር በሚገባ ሲዋሃድ ብቻ ነው።
በኘሮግራማችን ውስጥ ቁልጭ ብሎ የተቀመጠውን መስመር በመከተል፣ ከሌሎች ማርክሲስት-ሌኒኒስት ቡድኖች ጋር ሃቀኛ ርእዩተአለማዊ ትግልን አካሂደን፣ ተቀራርበን፣ በመጨረሻም ተዋህደን የኢትዮጵያን የወዛደር ፓርቲ እንፈጥራለን። ይህ አቋማችን በቃል ብቻ የሚገለጽ አለመሆኑንና በገቢርም ወደዚያው እንደምንጓዝ የሚያሳየው፣ በቅርቡ ከሬቮሉሽን ጓዶች ጋር የፈጠርነው የትግል ህብረት ነው። ከሬቮሉሽን ጓዶች ጋር ህብረትን ለመፍጠር የቻልነው በኢትዮጵያ ሁኔታ ትንተና ላይና በሌሎችም የአብዮቱ ጥያቄዎች ላይ ሰፋ ያለ ዲሞክራሲያዊ ውይይትን ካካሄድን በኋላ ነው። ውይይቱ ያተኮረው በመስመር ጥያቄዎች ላይ ነበር። ወደፊትም ከሌሎች ቡድኖች ጋር ለመተባበር የምናደርገው ክርክር በኘሪንሲኘል ጥያቄዎች ላይ እንዲያተኩር በጣም እንመኛለን።
III
የኢትዮጵያ አዮብት ባሁኑ ሰአት በጣም አስጊ በሆነ ሁኔታ ላይ ይገኛል። የኢምፔሪያሊዝም፣ የነኢዲዩ-ኢ.ኤል.ኤፍ.፣ የባሌ ሰርጐገቦች፣ የቢሮክራሲው፣ የትላልቅ ነጋዴዎች አሻጥርና ጠቅላላ የኢኮኖሚ ችግር፣ እነዚህ ሁሉ አብዮቱን ወጥረው ይዘውታል። ፀረአብዮታዊ ቅልበሳን ለመከላከልና በመጨረሻም አድሃሪዎችን ለመደምሰሰ የሚችለው ኃይል የነቃ፣ የተደራጀና የታጠቀ የሕዝብ ኃይል ብቻ መሆኑን ደጋግመን ገልፀናል። መኢሶን የሚታገለው የዚህ አይነቱ የሕዝብ ኃይል እንዲፈጠር እንጂ የመንግሥትን ስልጣን በአቋራጭ ለመያዝ አይደለም። የዚህ አይነት ቅዠትማ ቢኖረው እራሱ መጀመሪያ አንስቶ ለዲሞዎች ያስታቀፈውን የጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት መፈክር እኝኝ ብሎ እስከመጨረሻው በታገለለት ነበር!!
ከኢሀአፓ ግልገል ፋሺስቶችና ከኢምፔሪያሊስት ደጋፊዎቻቸው ጋር ባደረግነው ትግል በርከት ያሉ ጓዶቻችን የመጨረሻውን መስዋአትነት ተቀብለዋል። ወደፊትም ሌሎች ጓዶች ለቆምንለት አላማ እንደሚወድቁ ምንም ጥርጥር የለውም። ይሁንናም፣ ዋናው ቁም ነገር የፀረአብዮት ኃይሎች በግለሰቦች ግድያ ጊዚያዊ ውጤቶችን ማግኘት ሳይሆን፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮት ከግቡ መድረስ ነው። ለዚህም የተራማጆች የጠነከረ ህብረት ስለሚያስፈልግ ዋናው ትግላችን በጥቂት ቀናት ውስጥ ያልተብላላ ህብረትን ለመፍጠር ሳይሆን በትክክለኛ መስመር ላይ የተገነባ ህብረትን በመፍጠርና በዚያውም ለሰፊው ሕዝብ የረጅም ጊዜ ተጋድሎ አስተማማኝ መሰረትን ለመጣል መታገልና መሰዋትም ነው። ስለዚህም ነው የሚደረግብንን ዘመቻ በመቋቋም ዲሞክራሲያዊ ክርክር እንዲኖር የምንጠይቀው።
የሀቀኛ ተራማጆች ቡድኖች የሚባሉት ሁሉ፣ የእኛንም ድርጅት ጨምሮ፣ ከደርጉ ጋር የገቢር ህብረትን የፈጠሩ ድርጅቶች ናቸው። እነዚህ ድርጅቶች አባሎች ለመሆን የሚሯሯጡት ግለሰቦች ሁሉ እውነተኛ አብዮታዊያን ናቸው ለማለት አይቻልም። እንዲያውም፣ በእንደዚህ አይነቱ ሁኔታ፣ የኢምፔሪያሊዝም ቡችሎች፣ የሌሎችም አድሃሪዎች ሰርጎ ገቦችና መስለው ለመኖር የሚፈልጉ አድርባዮች ሁሉ ወደ እነዚህ ድርጅቶች በብዛት ለመግባት እንደሚታገሉ ሳይታለም የተፈታ ነው። በዚህ ላይ በተጨማሪ፣ በግራ ክንፍ ውስጥ በተፈጠረውና አሁን በመፋፋም ላይ ባለው ውድድር ምክንያት፣ አንዳንድ የህብረት ጓዶቻችን አባሎቻቸውን ለማብዛት ሲሉ፣ ያገኙትን ሁሉ ሳያግበሰብሱ በይበልጥ ለወዛደሩና በደሃው ገበሬ ላይ እንዲያተኩሩ አደራ እንላለን። ዛሬ የምንፈጥረው ህብረት ለወዛደሩ ፓርቲ መመስረት መንገድ መክፈቻ ነው። ስለሆነም፣ በማርክሲስት- ሌኒኒስት መርሆች ካልተመራንና የጊዜውን ጥቅም ብቻ ካየን ነገ የሚፈጠረው ፓርቲ የወዛደሩ ሳይሆን የንዑስ ከበርቴው፣ የሚታገልለትም አላማ የሰፊውን ሕዝብና ከዛም የወዛደሩን አምባገነንነት ለማስፈን ሳይሆን የንዑስ ከበርቴውን አምባገነንነት ለማስፈን ይሆናል። ለብዙ የአፍሪካ ሃገሮች በተለይና ለዓለምም ጭቁን ሕዝቦች በአጠቃላይ የተስፋ ምክንያት የሆነውና በመሆን ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ አብዮት ዞሮ ዞሮ የተኮላሸ አብዮት ሆኖ ይቀራል ማለት ነው።
በኢትዮጵያ የተራማጆች ድርጅቶች መካከል በልዩ ልዩ ነጥቦች ላይ ልዩነቶች እንዳሉ የታወቀ ነገር ነው። በነዚህ ነጥቦች ላይ ሰፋ ያለና ግልጽ ውይይት መካሄድ ይኖርበታል። መኢሶን በበኩሉ ለዚህ አይነት ውይይት መቼውንም ቢሆን ዝግጁ ነው። አንዳንድ ጓዶችና ቡድኖች ይህ ውይይት ተራማጆችን ይከፋፍልና በተለይ አሁን የኢትዮጵያ አብዮት አደጋ ላይ ባለበት ሁኔታ የሰፊውን ሕዝብ ትግል ያዳክማል የሚል እምነት አላቸው። መከፋፈልና መዳከም የሚያመጣው ይልቁንስ ጥብቅ ውይይት በሌለበት ሁኔታ በፕሪንሲፕል ላይ ያልቆመ ህብረትን ወይንም አንድነትን ለመፍጠር መቻኮሉ ነው።
በተረፈ ግን አሁንም መኢሶን መቶ ጊዜ ይበልጥ በወዛደሩና በደሃው ገበሬ ውስጥ መተከል አለበት እንላለን። መቼስ ነገ የኢትዮጵያ ወዛደር ፓርቲ ይፈጠራል ስለተባለ እያንዳንዱ ተራማጅ ቡድን ለራሱ ድርጅት መስራቱን ትቶ ወይ ለሌላ ቡድን ወይንም እንዲያው በደፈናው “ለወዛደሩ ፓርቲ” ብቻ ቅስቀሳን ሊያካሂድ አይችልም። በማርክሲዝም-ሌኒኒዝም በመመራት ከታገለ፣ የረጅሙን ጊዜ አላማዎች ለእለታዊ ጥቅሞች ካልሰዋና በጠባብ ቡድን መንፈስ ካልተመረዘ፣ የያንዳንዱ ተራማጅ ድርጅት መስፋፋት ለአብዩቱ መቀጠል ዋስትና እንጂ በምንም መንገድ እንቅፋት አይሆንም። ይህ ስለተባለ ግን ባሁኑ ሰአት መቀራረብ፣ ህብረትን መፍጠርና አንድ ጠንካራ የወዛደር ፖርቲን ለመመስረት መታገል የለብንም ማለታችን እንዳይደለ ግልጽ ነው። ሁለቱም ትግሎች፣ ማለትም የያንዳንዱ ቡድን መጠናከርና የቡድኖቹም መቀራረብ፣ ባንድ ላይ የሚካሄዱ ነገሮች ናቸው።