ገብረ እግዚአብሔር ተስፋይ
ገብረ እግዚአብሔር ተስፋይ፣ በአዲግራት ከተማ ትግራይ ክፍለ አገር ተወለደ። የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በትግራይ እና በሐረር ክፍለ አገር ተከታተለ። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን የተከታተለው ሐረር ከተማ በሚገኘው በሐረር መድኀኔ ዓለም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው። ለጋ የወጣትነት ዘመኑን ያሳለፈው በሐረር ስለነበር ብዙዎቸ የሚያውቁት እና የሚያስታውሱት በሐረር ልጅነቱ ነው።
በ1961 ዓ.ም. የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በአመርቂ ውጤት በማለፍ በቀዳሚዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ በሕግ ፋከልቲ ትምህርቱን ቀጠለ። በትምህርቱ ጎበዝ ከሚባሉት ተማሪዎችም መሀል አንዱ ነበር። በወቅቱ በነበረውም የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ንቁ ተሳታፊ ነበር። ገብረ እግዚአብሔር (ብዙዎች ጓደኞቹ “ገብሬ” በማለት የሚጠሩት) በአድማጭነቱ፣ በትህትናውና አንድን የሕግ ሆነ የፖለቲካ ወይም ማኅበራዊ ጉዳይ በመተንተን ችሎታው ያስታውሱታል።
ገብሬ፣ በዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን ለአራት ዓመታት ከተከታተለ በኋላ የዩኒቨርሲቲ አገልግሎት (ሰርቪስ)የተባለውን ግዴታውን በፍርድ ሚኒስቴር አጠናቅቆ ወደ ሕግ ፋከልቲ በመመለስ፣ በዲግሪ ለመመረቅ የቀረውን አንድ ዓመት ለመጀመር ጥቂት ቀናት ሲቀሩት አዲስ አበባ ውስጥ መርካቶ በተባለው ሠፈር በአንዲት ክፍል ውስጥ ከጥቂትየቅርብ ጓዶቹ ጋር ተሰብስበው የፖለቲካ ጥናት በመምራት ላይ እንዳለ ከሌሎች ሁለት ጓዶቹ፣ ከአቡበከር አብዱልመጂድ እና ክንፈ አስፋው ጋር መስከረም 17 ቀን፣ 1969 ዓ.ም.፣ በኢሕአፓ ነፍሰ ገዳዮች ቡድን የመጀመሪያው ሰለባ ከሆኑትና ሕይወታቸውን ካጡት ወጣት አብዮታውያን መሃል አንዱ ነበር።