ብርሃኔ ተክለማርያም
ብርሃኔ ተክለ ማርያም፣ ከአባቱ ከአቶ ተክለ ማርያም ካሳየና ከእናቱ ከወ/ሮ ሂሩት ሠመረአብ፣ ነሐሴ 3 ቀን 1944 ዓ.ም. በኤርትራ ክፍለ አገር አስመራ ከተማ ገዛ ማንዳ ቀበሌ ተወለደ። በሕጻንነቱ ከወላጆቹ ጋር መኖሪያቸውን አዲስ አበባ አደረጉ። ብርሃኔ፣ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በዳግማዊ ምንሊክ ት/ቤት፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በአስፋ ወሰን አጠቃላይ ት/ቤት በ1964 ዓ.ም. አጠናቀቀ።
በአፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ዘመን፣ ብርሃኔ በተማሪዎች የፖለቲካ ተቃውሞ እንቅስቃሴ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ነበረው። በጉልህ የፖለቲካ ተሳትፎው ምክንያትም ከሌሎች የዩኒቨርስቲና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ መሪዎች ጋር በጊቤ በረሃ ለስድስት ወራት ታስሮ ተሰቃይቷል።
በግንበኝነት ሙያ ይተዳደሩ የነበሩትን ወላጅ አባቱን ለመርዳት ብርሃኔ ዩኒቨርስቲ ገብቶ ለመማር የነበረውን እቅዱን አቋርጦ፣ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሥር በሚተዳደረው በጋንዲ ሆስፒታል ተቀጥሮ ሥራ ጀመረ።
ከግንቦት ወር 1968 ዓ.ም. ጀምሮ፣ በሕዝብ ድርጅት ጉዳይ ጊዜያዊ ጽ/ቤት የአዲስ አበባና አካባቢዋ ቅርንጫፍ ባልደረባ ሆኖ ይሠራ ነበር።
በአዲስ አበባም በሚኖርበት ካዛንቺስ ሰፈር ውስጥ ወጣቶችን በኅቡዕ በማደራጀትና ፖለቲካዊ ጥናት በማካሄድ ንቁ ተሳትፎ ነበረው። የመኢሶን ወጣት ክንፍ የኢትዮጵያ አብዮታዊ ወጣቶች ንቅናቄ (ኢአወን) መሥራች አባል ነበር። ጥቅምት 11 ቀን፣ 1969 ዓ.ም. ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ላይ በኢሕአፓ ነፍሰ ገዳዮች ቡድን በደፈጣ ተገደለ።
ብርሃኔ ተክለ ማርያም፣ የኢሕአፓ ግድያ ሰለባ ከሆኑትና ሕይወታቸውን ካጡት ወጣት አብዮታውያን መሀል አንዱ ነበር።