በላይነህ ባንቁርሳ
በላይነህ ባንቁርሳ የተወለደውና ያደገው በሲዳሞ ክፍለ አገር፣ ሲዳማ አውራጃ፣ ይረጋ ዓለም ዙሪያ ባለው ገጠር አካባቢ ነበር። በላይነህ. ስድስተኛ ክፍል ሲደርስ ትምህርቱን አቋርጦ እንደ ቤተሰቦቹ ሁሉ በግብርና ሙያ ተሠማራ። የራሱ መሬት ስላልነበረው ይርጋዓለም ከተማ መግቢያ ላይ ካለው ሆስፒታል አጠገብ አዋዳ በሚባለው ቀበሌ የአንድ ፊውዳል ባለርስት ጭሰኛ ገበሬ ሆኖ ያርስ ነበር።
በላይነህ፣ አብዮቱን ተከትሎ በየካቲት ወር 1967 ዓ.ም. የታወጀው የገጠር መሬት አዋጅ ነጻ ካወጣቸው ብዙ ሚሊዮን የኢትዮጵያ ገበሬዎች መሃል አንዱ ነበር። በአዋጁ መሠረት የገበሬዎች ማኅበራት ሲደራጁ በላይነህ የመጀመሪያው የአዋዳ ቀበሌ ገበሬዎች ማኅበር ሊቀመንበር ሆኖ ተመረጠ። ከዚያም ለአዋጁ ተግባራዊነት በግንባር ቀደምነት በመንቀሳቀስ እውቅናን አተረፈ።
ነገር ግን፣ በላይነህ በመኢሶን አባልነቱ በሚያደርገው ገበሬዎችን የማንቃትና የማደራጀት ፖለቲካዊ አስተዋጽኦ የተከፋው የኢሕአፓ ነፍሰ ገዳይ ቡድን፣ በየካቲት ወር መጀመሪያ፣ 1969 ዓ.ም. በላይነህ ከሥራ ሲመለስ ጠብቆ መኖሪያ ቤቱ በራፍ ላይ በጥይት ገደለው።