ተስፋዬ ገላን ባልኬር (ጀንጅስ)

ተስፋዬ ገላን ባልኬር ከእናቱ ወ/ሮ ጉደቱ ተመስገን እና ከአባቱ አቶ ገላን ባልኬር መስከረም 1 ቀን 1941 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ራጉዔል ሰፈር ተወለደ። የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በልዑል መኮንን (አዲስ ከተማ) ት/ቤት ተከታትሏል።  በዳግማዊ ቴዎድሮስ ት/ቤትም በ1963 እና 1964 ዓ.ም. የ5ኛና የ6ኛ ክፍል አስተማሪ በመሆን አገልግሏል።

በተማረባቸው ትምህርት ቤቶችና በመኖሪያ ሰፈሩ ታዋቂና ተወዳጅ ነበር። በቴዎድሮስ፣ በሰማያዊ ውቅያኖስ እና በጊዮርጊስ የእግር ኳስ ዋና ቡድኖች ተጫዋች ነበር።

ተስፋዬ ገላን እጅግ ጠባየ መልካም በመሆኑ፣ የሰፈሩ ታዳጊ ልጆች በትምህርት እና ስፖርት እንዲታነጹ ይጥር ነበር። በ1960ዎቹ መጀመሪያ ላይ በመርካቶ የተፈጠረውን የቻይና-ግሩፕ የተባለ አዋኪ ቡድን በመቃወም የራጉዔል ስፖርት ቡድንን መሪ ሆኖ አደራጀ። በቡድኑም አማካይነት የቻይና-ግሩፕን መስፋፋት በማገድ ወጣቶችን ከመጥፎ ተግባርና ልምድ ለማዳን ታግሏል። በኋላም የቻይና ግሩፕ አባላት ወደ ኢሕአፓ ሲሳቡ፣ እሱ ደግሞ ወደ መኢሶን አዘንብሎ ድርጅቱን ተቀላቀለ።

ተስፋዬ፣ በመኢሶን ውስጥ በሚያደርገው ጠንካራ የትግል አስተዋጽኦ የተነሳ የኢሕአፓ ነፍሰ ገዳዮች ኢላማ ሆኖ፣ ሰኔ 12 ቀን 1968 ዓ.ም. በጩቤ ወግተው ሊገሉት ሞከሩ። በመቀጠልም፣ ኅዳር 1 ቀን የወታደር የደንብ ልብስ የለበሱ የኢሕአፓ ገዳዮቸ ባካሄዱበት የግድያ ሙከራ የአገጭ አጥንቱና ጥርሶቹ በጥይት ተሰባበሩ፣ እሱም የሞተ መስሏቸው ጥለውት ሄዱ።

ነገር ግን የካቲት 12 ሆስፒታል በተደረገለት ህክምና ከሞት ተረፈ። ኅዳር 3፣ 1969 ዓ.ም.  እንደገና በተኛበት በየካቲት 12 ሆስፒታል ተጨማሪ የግድያ ሙከራ ተደረገበት።  ለአራተኛ ጊዜ፣ መጋቢት 30 ቀን 1969 አርብ ዕለት በአሜሪካ ግቢ ወደሚገኘው ወላጅ እናቱ ቤት ሊገባ ሲል በተደረገበት የግድያ ሙከራ ከተተኮሱበት አምስት ጥይቶች እየተገለባበጠ አምልጦ ራሱን አዳነ።

ለአምስተኛ ጊዜ፣ ሚያዚያ 11፣ 1969 ዓ.ም.  ማክሰኞ ዕለት በኢሕአፓ ነፍሰ ገዳዮች በሁለት ጥይት ተመቶ ዘውዲቱ ሆስፒታል ገብቶ አንድ ቀን ካደረ በኋላ በማግስቱ ረቡዕ ሚያዚያ 12፣ 1969 ዓ.ም. ከለሊቱ ስምንት ሰዓት ተኩል ላይ ሕይወቱ አለፈ።

ተስፋዬ ገላን ከአራት ዓመት የትዳር አጋሩ ከወ/ሮ ሙሉ ታደሰ ሁለት ሴት ልጆች አፍርቷል።

 

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top