ዮናስ ለማ
ዮናስ ለማ፣ መስከረም 12 ቀን 1942 ዓ.ም. ከእናቱ ከወ/ሮ ተዋበች እንቁሥላሴ እና ከአባቱ ከደጃዝማች ለማ ወልደ ጻድቅ አዲስ አበባ ተወለደ። የመጀመሪያ ደርጃ ትምህርቱን በተስፋ ኮከብ፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በሽመልስ ሀብቴ ት/ቤቶች አጠናቀቀ።
ዮናስ፣ በተማሪነት ዘምኑ አንደበተ ርቱዕና ከሰዎች ጋር እጅግ ተግባቢ ነበር። በት/ቤት ውስጥ በተለያዩ የተማሪዎች ክበቦች ውስጥ ቀልጣፋ ተሳትፎ ነበረው። በክርክር ክበብ ውስጥ ተሳትፎው፣ በድንቅ የንግግር ችሎታው ይታወቅ ነበር። ዮናስ፣ በ1963 ዓ.ም. በማስታወቂያና መርሐ ብሔር ሚኒስቴር ውስጥ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን መምሪያ አባል ሆነ። በጋዜጠኝነት ሙያውም፣ ተደናቂና ብርቱ ሠራተኛ ነበር። በፕሮግራም አቅራቢነትና በዜና አንባቢነት በኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ ይታወቃል።
ዮናስ፣ ከሐምሌ 10 ቀን፣ እስከ ጳጉሜ 3 ቀን 1968 ዓ.ም. በየካቲት 1966 የፖለቲካ ት/ቤት ይሰጥ የነበረውን ትምህርት ተከታትሏል።ከዚያም፣ ወደ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ሥራው እንደተመለሰ፣ “የወዝአደር ዓለም” እና “የወጣቶች” ፕሮግራሞች ዋና አዘጋጅና አቅራቢም ነበር።
በመኢሶን አባልነቱና በጋዜጠኝነት ለሕዝብ በሚያቀርባቸው ፕሮግራሞች ምክንያት የኢሕአፓ የግድያ ዒላማ ሆነ። ዮናስ፣ መጋቢት 29 ቀን፣ 1969 ዓ.ም. ከሥራው ለምሳ ወደ ቤቱ ሲገባ፣ መኖሪያ ቤቱ ደጃፍ ላይ በኢሕአፓ ነፍሰ ገዳይ በተተኮሰ ጥይት ክፉኛ ቆሰለ። ሆስፒታል ከገባ አንድ ቀን በኋላ መጋቢት 30 ቀን ሕይወቱ አለፈ።
ዮናስ ለማ ሕይወቱ ሲያልፍ የ27 አመት ወጣት ነበር።