የሸዋሉል መንግሥቱ

የሸዋሉል መንግሥቱ፣ በ1937 ዓ.ም.  በዚያን ጊዜ መጠሪያው ሐረርጌ ክፍለ አገር ኤጄርሳ ጓሮ ተወለደች።  የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ሐረር ከተማ ከተከታተለች በኋላ የሐረርጌ ፖሊስ ማስታወቂያ ክፍል ውስጥ አገልግላለች።

የሸዋሉል ገና ትምህርት ቤት እያለች ድርሰትና ግጥም በመጻፍ ችሎታዋ የምትታወቅ ነበረች። የሐረርጌ ፖሊስ ማስታወቂያ ክፍል ባልደረባ በነበረች ጊዜ የዘፈን ግጥሞችን ከማበርከቷ በላይ “ሙዚቃ በሐረር” በመባል ይታወቅ የነበረውን መጽሄት ከሥራ ባልደረቦችዋ ጋር በመሆን በግንባር ቀደምትነት አዘጋጅታለች።

ከሐረር አዲስ አበባ ከመጣች በኋላም በማስታወቂያ ሚኒስቴር በጋዜጠኝነት ሙያ ተሰማራች። በኢትዮጵያ ሬድዮ በዜና አንባቢነት፣የባህል በየገጹ፣ የቀበሌ ማሕበራትና የሌሎችም ፕሮግራሞች አዘጋጅና አቅራቢ ሆና አገልግላለች። በሬድዮ የተነበቡ አጫጭር ታሪኮችና ግጥሞችም በየጊዜው አበርክታለች።

ከጋዜጠኝነት ሥራዋ በተጨማሪ፣ የሸዋሉል ለአንጋፋ አርቲስቶች እጅግ የተወደዱ ግጥሞችን በማበርከት ትታወቃለች። ከብዙ በጥቂቱ ለመጥቀስ፣ የጥላሁን ገሠሠን “አከም ነጉማ”፣ የመሐሙድ  አሕመድን “አስራኝ ግጥም አርጋ ሄዳለች ከአገር” እና፣ የመሉቀን መለሰን “ትዝታ” እንዲሁም ለሌሎች በርካታ አርቲስቶች ድንቅ የዘፈን ግጥሞችን አበርክታለች።

የሸዋሉል ግፍና አድሏዊነት የተንሰራፋበትን ፖለቲካዊ አገዛዝ በመቃወም ትታወቃለች። ለዚህም የየካቲት 1966 አብዮት ከመፈንዳቱ በፊት ገና በአንድ ግጥሟ ስንኞች እንዲህ ብላ ነበር።

ወሰንና ድንበር ገደብ የለውም ወይ

ጥቃት ከልኩ ሲያልፍ ያሳብድ የለም ወይ?

እኔ ለኑሮዬ ያሰብኩት ነገር

መገላበጥ ብቻ ዝም ብዬ ከማር

የሸዋሉል በትግሉ ውስጥም መኢሶንን ተቀላቅላ በመኢሶን ሴቶች ክንፍና በቀበሌ የህዝብ ማደራጀት ሥራዎች ላይ በንቃት ተካፍላለች። በተግባቢነቷ፣ ለሕዝብ ባላት ታላቅ ፍቅርና በስነ ጽሑፍ ችሎታዋ እጅግ ብዙ ኢትዮጵያውያንን ለመማረክ የቻለች ጽኑ ታጋይ ነበረች።

የሸዋሉል በሕዝብ የተመረጠችበትን ሥራዋን ለማከናወን አዲስ አበባ ከቤቷ ወደ ቀበሌ በመጓዝ ላይ እያለች፣ በኢሕአፓ ነፍሰ ገዳዮች ጥይት ግንቦት 18፣ 1969 ዓ.ም ተገደለች።

በ32 ዓመት ዕድሜዋ በሞት የተለየችን የሸዋሉል፣ የአምስት ልጆች እናት ነበረች።

 

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top